Telegram Web Link
#ጥቅምት_22

#ቅዱስ_ሉቃስ_ወንጌላዊ
አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ጥቅምት ሃያ ሁለት በዚህች ቀን ብልህ ጥበበኛ የሆነ ቅዱስ ወንጌላዊ ሉቃስ በሰማዕትነት አረፈ።

በሀገረ አንጾኪያ ከአሕዛብ ወገን የተለወደው አይሁዳዊው ሉቃስ ከሰባ ሁለቱ አርድእት የተቆጠረ ባለ መድኃኒትና ወንጌልን የጻፈ ቅዱስ ሐዋርያ ነው፡፡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በወንጌል ትርጓሜያቸው ስሙ ‹ዓቃቤ ሥራይ› ወይም ‹ባለ መድኃኒት› የሚል ትርጉም በውስጡ የያዘ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ በላቲን ቋንቋ ‹ሉካስ› ማለት ‹ብርሃናማ፣ ብርሃን የያዘ› ማለት ነው፡፡ መጽሐፈ ስንክሳር ደግሞ ብልህና ጥበበኛ በማለት ይገልጸዋል፡፡

ቅዱስ ሉቃስ የሚመሰለው በገጸ ላህም ነው፡፡ ‹‹ፍሪዳ አምጡና እረዱ፤ ከእርሱ ጋር እየበላን ደስ ይበለን›› እያለ ምሳሌውን ይጽፋልና፡፡ (ሉቃ.፲፭፥፳፫) በጤግሮስም ወንዝ ይመሰላል፤ ጤግሮስ ፈለገ መዓር ወይም የመዓር ወንዝ ነው፤ ርስትነቱም ጸዊረ ነገር (ምሥጢር መሸከም) የሚቻላቸው ሰዎች ርስት ነው፡፡

ቅዱስ ሉቃስ በአቴና ሀገር በእስክንድሪያ ሕክምናን አጥንቷል፤ የሥነ ሥዕልም ችሎታ ነበረው፤ ይህን የሥዕል ችሎታውንም በወንጌሉና በሐዋርያት ሥራ መጻሕፍቱ ላይ በሥዕላዊ መልክ ገልጾታል፡፡ የቤተ ክርስቲያን ትውፊት እንደሚናገረው እመቤታችን #ቅድስት_ድንግል_ማርያም ልጇን አቅፋ (ምስለ ፍቁር ወልዳ) ለመጀመርያ ጊዜ የሣለው እርሱ ነው፡፡ ሥዕሎቹም በኢትዮጵያ በተድባባ ማርያም፣ በደብረ ዘመዶ፣ በዋሸራና በጀብላ ይገኛሉ፡፡ ተመሳሳዩም በስፔን ቅድስት #ማርያም ካቴድራል እንደሚገኝ ይነገራል፡፡ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በሰዓታት ምስጋናው ‹‹ከወንጌላውያን አንዱ የሆነው ጠቢቡ ሉቃስ ለሣላት ሥዕልሽ ሰላምታ ይገባል›› በማለት አመስግኗል፡፡

ቅዱስ ሉቃስ #ጌታችን_መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ከመረጠው በኋላ የቅዱስ ጳውሎስ ደቀ መዝሙር በመሆን አገልግሏል፡፡ ቀድሞ ዓቃቤ ሥራይ ዘሥጋ (ሥጋዊ ሐኪም) ቢሆንም በኋላ ግን ዓቃቤ ሥራይ ዘነፍስ (መንፈሳዊ ሐኪም) እንደሆነ ሊቃውንቱ ይናገራሉ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ስለ እርሱ ሲመሰክር ‹‹የተወደደው ባለ መድኃኒቱ ሉቃስ ዴማስም ሰላምታ ያቀርቡላችኋል›› በማለት ገልጦታል፡፡ (ቆላ.፬፥፲፬) ቅዱስ ሉቃስ ተንሣኢ (ፈጣን) እየተባለም የሚጠራው ለስብከተ ወንጌል ስለሚፋጠን ነበር፤ በወንጌሉም አጻጻፍ ላይ ስለ ሕመማቸውና ድኅነት ስለሚያገኙበት ሁኔታ ገልጦ ጽፏል፤ ለዚህም ምሳሌ የሚሆኑት ታሪኮች የደጉ ሳሚራዊና ደም ይፈሳት ስለነበረችው ሴት ናቸው፡፡ (ሉቃ.፲፥፴‐፴፭፤፰፥፵፫) ሐዋርያው መበሥር ወይም ብሥራት ነጋሪ እየተባለም ይጠራል፤ ይህም ብሥራተ መልአክን ጽፏልና ነው፡፡ (ሉቃ.፩፥፩)

የቅዱስ ሉቃስ ወንጌል የተጻፈው በሀገር አኪይያ (ሮም) በጽርዕ (ግሪክ) ቋንቋ ነው፤ የሉቃስ ወንጌል ‹የአሕዛብ ወንጌል›፣ ‹ሰባኬ መንፈስ ቅዱስ›፣ ‹ሰባኬ ጸሎት›፣ ወንጌለ አንስት ተብሎም ይጠራል፡፡

፩. ‹የአሕዛብ ወንጌል› እየተባለ የሚጠራው ወንጌሉ የተጻፈው ለአሕዛብ በመሆኑ ነው፡፡

፪. ሰባኬ #መንፈስ_ቅዱስ የሚባለው ስለ #መንፈስ_ቅዱስ ደጋግሞ ስለሚናገር ነው፡፡

፫. ሰባኬ ጸሎት የተባለው ከሌሎች ወንጌላት የበለጠ ደጋግሞ የ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስን እና እመቤታችን ቅድስት ድንግል #ማርያምን ጸሎት ጽፏልና ነው፡፡

፬. ወንጌለ አንስት የሚባለው ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል #ማርያም፣ ስለ ቅድስት ኤልሳቤጥ፣ ስለ ማርያም እንተ እፍረት፣ ስለ ናይን እና ወዘተ በስፋት ስለሚናገር ነው፡፡

ወንጌሉን ከመጻፉ አስቀድሞም ቅዱስ ሉቃስ የቅዱስ ጳውሎስ ደቀ መዝሙር ከመሆኑ በፊት የቅዱስ ዮሐንስ ደቀ መዝሙር እንደነበረ ትርጓሜ ወንጌል ላይ ተጽፎ ይገኛል፡፡ በአንጾኪያ ሀገር ቅዱስ ጳውሎስን ካገኘው በኋላም ሊቀ ሐዋርያው ሰማዕት እስከሆነበት ድረስ አገልግሎታል፡፡ ከሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ጋርም በነበረበት ጊዜም መቄዶንያ የምትባል ሀገር ከፍሎ እንዲስተምር እንደሰጠው በወንጌል ትርጓሜ ተገልዿል፡፡ ቅዱስ ሉቃስም በዚያ ሀገር ከ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ መፀነስ ጀምሮ፣ መዋዕለ ስብከቱን፣ የሠራውን ትሩፋትና ገቢረ ተአምሩን በሙሉ ለአሕዛቡ በነገራቸው ጊዜ ከኃጢያት ወደ ጽድቅ፣ ከአምልኮ ጣዖት ወደ አምልኮ #እግዚአብሔር ተመለሰው በማመን የክርስትና ጥምቀት ተጠምቀዋል፡፡ ለስብከት በሚጓዝበትም ወቅት ትምህርት ባልተዳረሰባቸው ስፍራ ሲያስተምር አንድ ታዖፊላ የተባለ የእስክንድርያ መኮንን ስብከቱን አድምጦ በማመን ‹ዜና ሐዋርያትን› (ገድለ ሐዋርያትን) እንዲጽፍለት በጠየቀው መሠረት ጽፎለታል፡፡ በዚህም ቅዱስ ሉቃስ የጻፋቸው መጻሕፍት ከወንጌሉና ከሐዋርያት ሥራ ጋር ሦስት ናቸው፡፡

ቅዱስ ሉቃስ የሕይወት ታሪኩ እንደሚገለጸው በድንግልና የኖረ ሐዋርያ ነው፤ ሐዋርያዊ አገልግሎቱንም የፈጸመው በአብዛኛው በግሪክ ነበር፡፡ ሐዋርያቱ ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ጳውሎስ ካረፉ በኋላም በሮም ሀገር ማስተምር ቀጠለ፤ በቀናች ሃይማኖትም ይጸኑ ዘንድ ለምእመናን መልእክትን ይጽፍ ነበር፤ ስለዚህም ጣዖት አምላኪዎች ከአይሁድ ጋር በመስማማት በአንድ ምክር ሆነው በንጉሥ ኔሮን ፊት በመቆም ስለ ሐዋርያው ሉቃስ እንዲህ ብለው ተናገሩ፤ ‹‹ይህ ሉቃስ በሥራይ ብዙ ሰዎችን ወደ ትምህርቱ አስገባቸው፡፡›› ንጉሥ ኔሮንም ወደ ፍርድ ዐደባባይ ሉቃስን እንዲያቀርቡት ባዘዘ ጊዜ ሐዋርያው ሉቃስ ዕረፍቱ እንደ ደረሰ በ #መንፈስ_ቅዱስ ዐውቆ ወደ ባሕር ዳርቻ ሄደ፡፡ በዚያም ዓሣ የሚያጠምድ አንድ ሽማግሌ ሰው አግኝቶ መጻሕፍቱንና ደብዳቤዎችን እንደሰጠውና ‹‹ወደ #እግዚአብሔር መንገድ መርተው ያደርሱሀልና እነዚህን መጻሕፍት ጠብቃቸው›› በማለት እንደገነገረው መጽሐፈ ስንክሳር ይጠቅሳል፡፡

ከዚህም በኋላ በንጉሥ ኔሮን ፊትም ቀርቦ በቆመ ጊዜ ንጉሡ ‹‹በሥራይህ ሕዝቡን የምታስት እስከ መቼ ነው?›› ብሎ ጠየቀው፤ ቅዱስ ሉቃስም ‹‹እኔ ለሕያው #እግዚአብሔር ልጅ ለ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ሐዋርያ ነኝ እንጂ ሥራየኛ አይደለሁም›› ብሎ መለሰለት፡፡ ንጉሥ ኔሮንም ሁለተኛ እንዲህ አለው፤ ‹‹እየጻፈች ሰዎችን የምታስት ይህች እጅህን እኔ እቆርጣታለሁ፤›› ይህንንም ብሎ የቀኝ እጁን እንዲቆርጡት አዘዘ፡፡ በቆረጡትም ጊዜ ‹‹ንጉሥ ሆይ እኛ የዚህን ዓለም ሞት እንደማንፈራ ዕወቅ፤ ነገር ግን የ #ጌታዬና የፈጣሪዬን ኃይሉን ታውቅ ዘንድ አሳይሃለሁ፤›› ይህንንም ብሎ የተቆረጠች የቀኝ እጁን በግራ እጁ አንሥቶ ከተቆረጠችበት ቦታዋ ላይ አገናኝቶ እንደ ቀድሞዋ ደኅነኛ አደረጋት፤ ከዚህም በኋላ ለያት፤ በዚያም የነበሩ አደነቁ፤ የሠራዊቱም አለቃና ሚስቱ ብዙዎችም ሰዎች ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ አመኑ፤ ቁጥራቸውም ዐራት መቶ ሰባ ሰባት ነፍስ ሆነ፡፡ ንጉሡም ከቅዱስ ሉቃስ ጋር ራሶቻቸውን እንዲቆርጡ በማዘዙ ቆረጡአቸው፤ የምስክርነት አክሊልም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበሉ፡፡ ቅዱስ ሉቃስ ያረፈው በ፹፬ ዓመቱ ነው፡፡

ከዚህም በኋላ ሥጋውን በማቅ አይበት ውስጥ አድርገው ወደ ባሕር ጣሉት፡፡ በ #እግዚአብሔር ፈቃድ ወደ አንድ ደሴት ደረሰ ምእመናንም አግኝተው ወስደው ገነዙት፤ በአማረ ቦታም አኖሩት፡፡

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን የወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ አማላጅነት፣ ተረዳኢነትና በረከት አይለየን፤ አሜን!

(ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምት_22)
#ውራ_ኢየሱስ ገዳምን የመሠረቱትና #ጌታችን ከገነት ዕንጨቶች የተሠሩ ታቦታት አምጥቶ የሰጣቸው ታላቁ ጻድቅ #አቡነ_ዮሐንስ ዘውራ #ኢየሱስ ጥቅምት 22 ቀን ዕረፍታቸው ነው።
+ + + + +
#አቡነ_ዮሐንስ_ዘውራ_ኢየሱስ፦ የአባታቸው ስም የማነ ብርሃን የእናታቸው ስም ሐመረ ወርቅ ይባላል።በመጀመሪያ እናታቸው ሐመረ ወርቅን ወላጆቿ ያለ ፈቃዷ ሊድሯት ሲሉ እርሷ ግን “ደብረ ሊባኖስ ሔጄ ከአባታችን ተክለ ሃይማኖትና ከሌሎቹም ቅዱሳን መቃብር ሳልባረክ አላገባም በማለት ነሐሴ 16 ቀን ወደ ደብረ ሊባኖስ ሔደች። በዚያም ሳለች አቡነ ተክለ ሃይማኖት በራእይ ተገለጡላትና የብርሃን ምሰሶ አሳይተዋት ይኸ ለአንቺና ለባልሽ ለየማነ ብርሃን ነው› አሏት። ይኽንንም ራእይ ለሰባት ቀን የገዳሙ አባቶችና አበ ምኔቱ አባ ዳንኤል አዩት። ከዚኸም በኋላ ባለጸጋውና ሃይማኖትን ከምግባር አስተባብሮ የያዘው የማነ ብርሃን ከዘርዐ ያዕቆብ ሀገር በ #እመቤታችን ትእዛዝ ወደ ደብረ ሊባኖስ ሲመጣ አበ ምኔቱ አባ ዳንኤል የማነ ብርሃንን እና ሐመረ ወርቅን ኹለቱ ተጋብተው የተባረከ ልጅ እንደሚወልዱ በራእይ ያዩትን ነገሯቸው፤ ከዚኽም በኋላ በአባታችን በተክለ ሃይማኖት የዕረፍታቸው በዓል ዕለት ነሐሴ 24 ቀን ተጋቡ። እነርሱም በሃይማኖት በምግባር #እግዚአብሔርን ደስ አሰኝተው ሲኖሩ #እግዚአብሔር ልጅ ሰጣቸውና አቡነ ዮሓንስ ነሐሴ 24 ቀን ተፀንሰው ግንቦት 24 ቀን ተወለዱ።

የፈለገ ብርሃን ናዳ #ማርያም እና የክብረ ደናግል ናዳ ቅዱስ ላሊበላ አንድነት ገዳም አበምኔት፣ የቅኔ፣ የትርጓሜ መጻሕፍት፤ የፍትሐ ነገሥት እና የባሕረ ሐሳብ መምህር የሆኑት ሊቀ ብርሃናት ቆሞስ ይባቤ በላይ ከግእዝ ወደ አማርኛ የተረገሙት የአቡነ ዮሐንስ ዘውራ ኢየሱስ ገድል እንደሚናገረው ጻድቁ በሰባት ዓመታቸው ይኸችን ዓለም ንቀው የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ኹለተኛ ልጅ ወደሆነው አባ ጸጋ ኢየሱስ ዘንድ ሔደው 5 ዓመት እየተማሩ ተቀምጠው በ12 ዓመታቸው መነኰሱ። ከዚኽም በኋላ አቡነ ዮሐንስ ወደ ዋልድባ በመሔድ አባቶችን ማገልገል ጀመሩ። መነኰሳቱም ሌሊትና ቀን እንዲገለግሏቸው በሥጋ ቍስል ሁለንተናው
ለተላና ለሸተተ ግብሩ ለከፋ ለአንድ መነኵሴ ሰጧቸው። በሽተኛውም መነኵሴ አቡነ ዮሐንስን ይረግማቸው አንዳንድ ጊዜም ይደበድባቸው ነበር፣ ነገር ግን አቡነ ዮሐንስ በዚህ ከማዘን ይልቅ ደስ እያላቸው ያንን ሊቀርቡት የሚያሰቅቅ በሽተኛ በማገልገል ለዓመታት አስታመመ።

እንዲሁም የዋልድባ መነኰሳትን መኮሪታ በማብሰል፣ ቋርፍ በመጫር እና ዕንጨት በመልቀም፣ ውኃ በመቅዳት ገዳማውያንን ያገለግሉ ነበር። ከዕለታትም በአንደኛው ቀን በዋልድባ የሚኖር በክፉ በሽታ ተይዞ የሞተ አንድ መነኩሴ ሞቶ ሣለ ሽታውን ፈርተው መነኰሳቱ ለመገነዝ ፈሩ፡ ነገር ግን አበ ምኔቱ ለመገነዝ ወደ ውስጥ ሲገባ አቡነ ዮሐንስ አብረው ገቡ። አቡነ ዮሐንስም ወደሞተው መነኵሲ ቀርበው አቀፉት፣ በዚኸም ጊዜ ጥላቸው ቢያርፍበት ያ የሞተው መነኵሴ አፈፍ ብሎ ከሞት ተነሣና ከሞትሁ 3ኛ ቀኔ ነው አይቶ የጎበኘኝ የለም፣ ዛሬ ግን የ #እግዚአብሔር ሰው የገዳማት ኮከብ የቅድስት ውራ ገዳም መነኰሳት አባት፣ የማይጠልቅ ፀሓይ፣ የማይጠፋ ፋና ወደ ሰባቱ ሰማያት ወጥቶ ከ24ቱ ካህናተ ሰማይ ጋር የ #ሥላሴን ዙፋን የሚያጥን አባታችን ዮሐንስ ባቀፈኝ ጊዜ ነፍሴ ከሥጋዬ ጋር ፈጽማ ተዋሐደች፤ አምላክን የወለደች #እመቤታችን_ማርያምም ንዑድ ክቡር ቅዱስ በሆነ በዮሐንስ ጸሎት ከሞት አስነሥቶ ሕያው አደረገህ አለችኝ› ብሎ ተናገረ። ዳግመኛም #እመቤታችን አባ ዮሐንስን ወደ ኢየሩሳሌም ሔደው እርሳቸውን ሲጠብቁ የኖሩትን ሦስት ታቦታት ያመጡ ዘንድ አቡነ ዮሐንስን እንዳዘዘቻቸው ተናገረ። በዚኽም ጊዜ የዋልድባ መነኰሳትና የገዳሙ አለቃ ለፍላጎታችን አገልጋይና ታዛዥ አደረግንህ ይቅር በለን ብለው ከእግራቸው ሥር ወድቀው ለመኗቸው። አባታችንም ‹‹አባቶቼ ሆይ! እናንተ ይቅር በሉኝ፡ ይህ የሆነው ስለ እኔ አይደለም፡ ስለ ክብራችሁ ነው እንጂ አሏቸው። መነኰሳቱም በትሕትናቸው ተገርመው እያለቀሱ ወደ ኢየሩሳሌም ሸኟቸው። በዚኸም ጊዜ አባታችን ዕድያቸው ገና 19 ነበር።

አባታችን ዮሐንስም ጎልጎታ ደርሰው ከቅዱሳት ቦታዎች ተባርከው ወደ አስቄጥስ ገዳም ሔዱ። በዚያም 500 ዓመት የኖረ ኹለተኛ እንጦንስ የተባለ አንድ ባሕታዊ ኣገኙ። #እመቤታችንም አባ እንጦንስን ታቦተ ኢየሱስን፣ ታቦተ ኪዳነ ምሕረትን እና ታቦተ ጽዮንን እያስጠበቀችው ይኖር ነበር። አባ እንጦንስም ኣቡነ ዮሐንስን ባገኛቸው ጊዜ በልቡ ተደስቶ በመንፈሱ ረክቶ በዐይኖቼ አንተን ያሳየኝ በጆሮዎቹም ቃልህን ያሰማኝ የአባቶቻችን አምላክ #እግዚአብሔር ይክበር ይመስገን፤ እመቤታችን #ማርያም ከልጇ ከወዳጇ ከ #ኢየሱስ_ክርስቶስ ጋር በእጇ የሰጠችኝን ያስጠበቀችኝን እነዚኽን ታቦታት ተቀበለኝ›› ብለው ሦስቱን ጽላት ‹‹ወደ ሀገርህ ይዘህ ሒድ›› ብለው ሰጧቸው። አባታችን ዮሐንስም ‹‹…እኔ እርሱ አይደለሁም እንዴት አወከኝ?› ሲሏቸው አባ እንጦንስም ፈገግ ብለው ከሞተ ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት የሆነውን ሰው በጸሎትህ ከሞት ካስነሣኸው በኋላ ከሀገርሀ ከኢትዮጵያ ከዋልድባ ገዳም ከተነሣኽ ዘጠኝ ወር ነው፤ ይኸንንም የ #እግዚአብሔር መላእክት ነገሩኝ መምጣቱን ተስፋ የምታደርገው ኢትዮጵያዊው ጻድቅ ከሀገሩ ዛሬ ተነሣ አሉኝ አሏቸው። አባታችን ዮሐንስም እመቤታችን #ማርያምን እንዴት አገኘሃት? አሏቸው። አባ እንጦንስም ከልጇ ከወዳጇ ጋር በብርሃን መርከብ ላይ ተቀምጣ መላእክት፣ ነቢያት፣ ሐዋርያት ጻድቃን፣ ሰማዕታት ሲከቧትና በክብር በምስጋና ሲሰግዱላት ግንቦት 21 ቀን በደብረ ምጥማቅ አገኘኋት አሏቸው። #እመቤታችንም ልጇን #ኢየሱስ_ክርስቶስን ፈቃድህን ለሚያደርጉ ለኢትዮጵያ ሕዝብና ለዓለሙ ሁሉ የመዳን ተስፋ ስጠኝ አለችው። #ጌታችንም ያንጊዜ መላእክትን ከገነት ዕንጨትና ዕብነ በረድ፡ ከጎልጎታ መቃብሩና ከጌቴሴማኒ አፈር እንዲያመጡ አዘዛቸው። መላእክትም የታዘዙትን አምጥተው በሰጡት ጊዜ #ጌታችን ከገነት የመጡትን ዕንጨትና ዕብነ በረድ ሦስቱን ታቦታት አድረጋቸው በማለት አባ እንጦንስ ለአባ ዮሐንስ ነገሯቸው።

አቡነ ዮሐንስም ሦስቱን ጽላት ይዘው አንዲት እንደፀሓይ የምታበራ ድንጋይ እየመራቻቸው ሰኔ 12 ቀን ጎጃም ደረሱ። ድንጋዩዋንም መንገድ እንድትመራቸው የሰጣቸው #ጌታችን ነው። ከዚያም ውሮ ተብሎ የሚጠራ አንድ ባላባት ቤት ገብተው አድረው በሚገባ ተስተናግደው በቀጣዩ ቀን ድንጋዩዋ እየመራቻቸው ቅዱሳን ከነበሩበት ጫካ ወስዳ አገናኘቻቸው። ቅዱሳኑም ለአቡነ ዮሐንስ የጠበቅንልህን ይኸችን ቦታ ተረከበን የዘለዓለም ማረፊያህ ናትና› ብለው እነርሱ ወደ ኢየሩሳሌም ሔዱ። አባታችንም ታቦተ #ኢየሱስን በዚኽች ገዳም ተክለው ቦታዋን መጀመሪያ በተቀበላቸው ሰው በውሮ ስም "ውራ #ኢየሱስ ብለው ሰየሟት።

ከዘጠኝ ዓመትም በኋላ መልአኩ ቅዱስ ዑራኤል እየመራቸው ወደ ጣና ወስዶ ዘጌ አደረሳቸውና ታላቋን ዑራ #ኪዳነ_ምሕረትን ተከለ።
ከዚያ ቀጥለው ታቦተ ጽዮንን አዴት አካባቢ ተከሉ። እነዚህን ሦስት ገዳማት አቅንተው ከኖሩ በኋላ መልካም የሆነውን ተጋድሏቸውን ፈጽመው ጥቅምት 22 ቀን ዐርብ በ9 ሰዓት ዐረፉ። ከማረፋቸውም በፊት #ጌታችን #እመቤታችንን#መላእክትን#ቅዱሳንን #ሰማዕታትን አስከትሎ መጥቶ “…ጸሎት አድርጎ መልክህን የደገመ እባብ አይነድፈውም፤ መብረቅ አይገድለውም የሚል ድንቅ የምሕረት ቃልኪዳን ገባላቸው። ዳግመኛም ስምህን የጠራውን መታሰቢያህን ያደረገውን፤ በበዓልህ ቀን ማኅሌት የቆመውን የገድልህን መጽሐፍ የጻፈውን ያጻፈውን ያነበበውን የሰማውን፣ እጅ መንሻ ለቤተ ክርስቲያን የሰጠውን እምርልሃለሁ፤ ልጆቹንም እስከ 15 ትውልድ እባርክልሃለሁ፤ በገዳምህ በውራ መብረቅ ነጎድጓድ፣ እባብ ሰውን አይገድልም የማይጸድቅ ሰው ወደ ገዳምህ አይመጣም" አላቸው።

አባታችንም ካረፉ በኋላ መነኰሳት ልጆቻቸው ሥጋቸውን ተሸክመው ከደብረ ጽዮን ኮቲ ተነሥተው ወደ ውራ #ኢየሱስ ለመውሰድ ሲጓዙ በበረሓ ሣሉ መሸባቸውና ፀሓይ ገባች፣ ወዲያውም ሰባት አንበሶች መጥተው እንዳይፈሯቸው መነኰሳቱን በሰው አንደበት ካናገሯቸው በኋላ የአቡነ ዮሓንስን ዐፅም ተሸክመው ሰባት ምዕራፍ ያህል ወሰዱት። ወቅቱ ቢመሽባቸውም በ #እግዚአብሔር ፈቃድ ፀሓይ ግን በተኣምራት ወጣችላቸውና ውራ #ኢየሱስ ገዳም በሰላም ደረሱ። ያንጊዜም ፀሓይ ገባች፤ አንበሶቹም እጅ ነሥተው ወደ ቦታቸው ተመለሱ።

አቡነ ዮሐንስ መላ ዘመናቸውን የማያዩ ዐይነ ሥውራንን እንዲያዩ፣ የማይሰሙ እንዲሰሙ፣ የማይራመዱ እንዲራመዱ በማድረግ፤ ሕሙማንን በመፈወስ፣ ሙታንን በማስነሣት በርካታ ተኣምራትን በማደረግ ወንጌልን በመስበክ ያገለገሉ ሲሆን ከዕረፍታቸውም በኋላ በርካታ ድንቅ ድንቅ ተኣምራትን አድርገዋል። ከተኣምራታቸውም አንዱ ይኸ ነው፡- ንዑድ ክቡር ልዩ በሚሆን በአባታችን ዮሐንስ የዕረፍታቸው ቀን ጥቅምት 22 ቀን አንድ ዐረማዊ እስላም ሰው ለተሳልቆና ለመዘባበት ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ገብቶ ቈረበ። በአባታችን በዓል ዕለትም #ቅዱስ_ሥጋውንና #ክቡር_ደሙን ተቀብሎ ወጥቶ እየተቻኮለ ሔዶ ከእስላሞች መስጊድ ገብቶ በአባታችን በዮሐንስ በዓል ምክንያት የቆረበውን ቍርባን ተቀብሎ በወገኖቹ በከሃዲያኑ እስላሞች ፊት ተፋው። ወዲያውም የዚያ እስላም ሰው መላ ሰውነቱ አበጠ በንፋስ ገመድነትም ታንቆ ሰዎች እስኪያዩት ድረስ በሰማይና በምድር መካከል ተሰቀለ።

በተሰቀለበትም ቦታ ወፎችና አሞራዎች ይበሉት ጀመር፤ ሥጋውንም በሉት። በዚኽም ጊዜ ያ እስላም ድምፁን ከፍ አድርጎ ‹‹እኔ ንዑድ ክቡር ልዩ በሆነ በአባታችን በዮሐንስ አምላክ አምኛለሁ ብሎ መሰከረ። #እግዚኣብሔርም የገዳማት ኮከብ በሆነው በብፁዕ ዮሓንስ ልመናና ጸሎት ፈጽሞ ይቅር አለው። ከዚኽም በኋላ ለብቻው ቀኖና ገባ የቀኖና ሥርዓቱንም ጨርሶ ንስሓ ገብቶ ከባለቤቱ ከልጆቹ ከቤተሰቦቹና ከዘመዶቹ ከጎረቤቱቹ ሁሉ ጋር የክርስትና ጥምቀትን ተጠመቀ ስሙንም ገብረ ዮሐንስ አሉት ትርጓሜውም የዮሐንስ ባለሟል ማለት ነው።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በአቡነ ዮሐንስ ጸሎት ይማረን የአቡነ ዮሐንስ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን፣ ለዘላለሙ አሜን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ጥቅምት_22_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ቆላስይስ 4
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹² ከእናንተ የሆነ የክርስቶስ ባሪያ ኤጳፍራ ሰላምታ ያቀርብላችኋል፤ በእግዚአብሔር ፈቃድ ሁሉ ተረድታችሁና ፍጹማን ሆናችሁ እንድትቆሙ፥ ሁልጊዜ ስለ እናንተ በጸሎቱ ይጋደላል።
¹³ ስለ እናንተ በሎዶቅያም በኢያራ ከተማም ስላሉቱ እጅግ እንዲቀና እመሰክርለታለሁና።
¹⁴ የተወደደው ባለ መድኃኒቱ ሉቃስ ዴማስም ሰላምታ ያቀርቡላችኋል።
¹⁵ በሎዶቅያ ላሉቱ ወንድሞችና ለንምፉን በቤቱም ላለች ቤተ ክርስቲያን ሰላምታ አቅርቡልን።
¹⁶ ይህችም መልእክት በእናንተ ዘንድ ከተነበበች በኋላ፥ በሎዶቅያ ሰዎች ማኅበር ደግሞ እንድትነበብ አድርጉ፤ ከሎዶቅያም የምትገኘውን መልእክት እናንተ ደግሞ አንብቡ።
¹⁷ ለአክሪጳም፦ በጌታ የተቀበልኸውን አገልግሎት እንድትፈጽሙው ተጠንቀቅ በሉልኝ።
¹⁸ በገዛ እጄ የተጻፈ የእኔ የጳውሎስ ሰላምታ ይህ ነው። እስራቴን አስቡ። ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ዮሐንስ 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁴ ደስታችሁም እንዲፈጸም ይህን እንጽፍላችኋለን።
⁵ ከእርሱም የሰማናት ለእናንተም የምናወራላችሁ መልእክት፦ እግዚአብሔር ብርሃን ነው ጨለማም በእርሱ ዘንድ ከቶ የለም የምትል ይህች ናት።
⁶ ከእርሱ ጋር ኅብረት አለን ብንል በጨለማም ብንመላለስ እንዋሻለን እውነትንም አናደርግም፤
⁷ ነገር ግን እርሱ በብርሃን እንዳለ በብርሃን ብንመላለስ ለእያንዳንዳችን ኅብረት አለን፥ የልጁም የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል።
⁸ ኃጢአት የለብንም ብንል ራሳችንን እናስታለን፥ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም።
⁹ በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው።
¹⁰ ኃጢአትን አላደረግንም ብንል ሐሰተኛ እናደርገዋለን ቃሉም በእኛ ውስጥ የለም።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹-² ቴዎፍሎስ ሆይ፥ ኢየሱስ የመረጣቸውን ሐዋርያትን በመንፈስ ቅዱስ ካዘዛቸው በኋላ እስከ ዐረገበት ቀን ድረስ፥ ያደርገውና ያስተምረው ዘንድ ስለ ጀመረው ሁሉ መጀመሪያውን ነገር ጻፍሁ፤
³ ደግሞ አርባ ቀን እየታያቸው ስለ እግዚአብሔርም መንግሥት ነገር እየነገራቸው፥ በብዙ ማስረጃ ከሕማማቱ በኋላ ሕያው ሆኖ ለእነርሱ ራሱን አሳያቸው።
⁴ ከእነርሱም ጋር አብሮ ሳለ ከኢየሩሳሌም እንዳይወጡ አዘዛቸው፥ ነገር ግን፦ ከእኔ የሰማችሁትን አብ የሰጠውን የተስፋ ቃል ጠብቁ፤
⁵ ዮሐንስ በውኃ አጥምቆ ነበርና፥ እናንተ ግን ከጥቂት ቀን በኃላ በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ አለ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ጥቅምት_22_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇🌹

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
   "አልቦ ነገር ወአልቦ ነቢብ ዘኢተሰምዐ ቃሎሙ። ውስተ ኵሉ ምድር ወፅአ ነገሮሙ። ወእስከ አፅናፈ ዓለም በጽሐ ነቢቦሙ"። መዝ 18፥3-4።
"ነገር የለም መናገርም የለም፥ ድምፃቸውም አይሰማም። ድምፃቸው ወደ ምድር ሁሉ፥ ቃላቸውም እስከ ዓለም ዳርቻ ወጣ"። መዝ 18፥3-4።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ጥቅምት_22_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
“የከበርህ ቴዎፍሎስ ሆይ፥ ከመጀመሪያው በዓይን ያዩትና የቃሉ አገልጋዮች የሆኑት እንዳስተላለፉልን፥ በኛ ዘንድ ስለ ተፈጸመው ነገር ብዙዎች ታሪክን በየተራው ለማዘጋጀት ስለ ሞከሩ፥ እኔ ደግሞ ስለ ተማርኸው ቃል እርግጡን እንድታውቅ በጥንቃቄ ሁሉን ከመጀመሪያው ተከትዬ በየተራው ልጽፍልህ መልካም ሆኖ ታየኝ።”— ሉቃስ 1፥1-4
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️  🌹
 የሚቀደሰው ቅዳሴ  የ #ቅዱሳን_ሐዋርያት_ቅዳሴ ነው። መልካም የወንጌላዊው የቅዱስ ሉቃስ የዕረፍት በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።
🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ጥቅምት_23

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ጥቅምት ሃያ ሦስት በዚህች ቀን የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት #አባ_ዮሴፍ አረፈ፣ የከሀዲ ዱድያኖስ ንጉሥ ሚስት #ቅድስት_እለእስክንድርያ መታሰቢያዋ ነው፣ የቆሮንቶስ አገር ኤጲስቆጶስ #ቅዱስ_ዲዮናስዮስ በሰማዕትነት አረፈ፣ በአቡነ ተክለ ሃይማኖት ተተክለው በደብረ ሊባኖስ የተሾሙት #አቡነ_ኤልሳ ዕረፍታቸው ነው፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አባ_ዮሴፍ_ሊቀ_ጳጳሳት

ጥቅምት ሃያ ሦስት በዚህች ቀን ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ኀምሳ ሁለተኛ የሆነ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት አባ ዮሴፍ አረፈ ። ይህም አባት ከመኑፍ አገር ከታላላቆች ተወላጆች ወገን ነው ወላጆቹም ብዙ ገንዘብ ያላቸው ነበሩ ታናሽም ሁኖ ሳለ አባትና እናቱ ትተውት ሲሞቱ ድኃ አደግ ሆነ አንድ #እግዚአብሔርንም የሚወድ ሰው አሳደገው።

አድጎ በጎለመሰም ጊዜ የወላጆቹን ገንዘብ ሁሉንም ወስዶ ለድኆችና ለምስኪኖች መጸወተ ከዚህም በኋላ ወደ አስቄጥስ ገዳም ወጥቶ ከአንድ ፃድቅ ሽማግሌ ሰው አባት ዘንድ መነኰሰ በበጎ ገድል ሁሉ እየተጋደለ ኖረ ።

ዳግማዊ አባ ማርቆስም ሊቀ ጵጵስና በተሾመ ጊዜ የዚህን አባ ዮሴፍን በጎ ጠባዩንና የትሩፋቱን ዜና ሰምቶ መልእክተኞችን ልኮ ወደርሱ አስመጣው በቤቱም አኖረው ።

ከብዙ ወራትም በኋላ አባ ዮሴፍ ሊቀ ጳጳሳቱን አባ ማርቆስን ወደ አስቄጥስ ገዳም እሔድ ዘንድ ተወኝ ብሎ ለመነው ያን ጊዜም ቅስና ሹሞ አሰናበተው ሊቀ ጳጳሳት አባ ስምዖንም እስከ አረፈ ድረስ በዚያ በእስቄጥስ ገዳም ኖረ ከዚህም በኋላ የግብጽ አገር ያለ ሊቀ ጳጳሳት ብዙ ወራት ኖረች ።

ከዚህም በኋላ ኤጲስቆጶሳቱ መማለጃ ስለተቀበሉ ከአንድ ሚስቱ ከሞተችበትና መዓስብ ከሆነ ጸሐፊ ጋር ሊቀ ጵጵስና ይሾሙት ዘንድ ተስማሙ እኩሌቶቹ ግን ተቃወሟቸው እንዲህም አሏቸው የአባቶቻችን ቀኖና መማለጃ የሚቀበለውን ሁሉ ወይም ስለ ክህነት ሹመት መማለጃ የሚሰጠውን ያወግዛል ። ይልቁንም ይህ ሰው ሚስት አግብቷል እንዴት ሊሾም ይችላል በወንጌላዊ ማርቆስ ወንበር ላይ የሚሾም ንጹሕ ድንግልም ነውና።

ይህንንም በአሏቸው ጊዜ ፈሩ ተመልሰውም ተስማሙ ለዚች ለከበረች ሹመት የሚሻለውን ይገልጽላቸው ዘንድ ክብር ይግባውና ወደ #ጌታችን በአንድ ምክር ሁነው ጸለዩ #እግዚአብሔርም ሰምቷቸው ለዚች የከበረች ሹመት የሚሻል አባ ዮሴፍ እንደሆነ አሳሰባቸው።

ከዚህም በኋላ አባ ዮሴፍን ያመጡት ዘንድ ወደ አስቄጥስ ገዳም መልእክተኞችን ላኩ መልክተኞችም ይህን አባት ዮሴፍን የመረጥከው ከሆነ ምልክትን ትገልጥልን ዘንድ አቤቱ እንለምንሃለን የቤቱም ደጃፍ ክፍት ሁኖ ካገኘን ምልክት ይሁንልን ብለው ወደ #እግዚአብሔር ለመኑ።

በደረሱም ጊዜ አንዱን መነኰስ እየሸኘ የበዓቱም ደጃፍ ክፍት ሁኖ አባ ዮሴፍን አገኙት በአያቸውም ጊዜ መንፈሳዊ ሰላምታ በመስጠት እጅ ነሣቸውና በደስታ ተቀብሎ ወደ በዓቱ አስገባቸው በዚያንም ጊዜ ለአባ ዮሴፍ ሊቀ ጵጵስና ይገባዋል ይገባዋል ይገባዋል እያሉ ይዘው አሠሩት ። እርሱ ግን እኔ ብዙ ኃጢአትን ሠርቻለሁና ይህ የከበረ ሹመት አይገባኝም እያለ ይጮህ ነበር እነርሱም ወደ እስክንድርያ ከተማ ወስደው ሊቀ ጵጵስና ሾሙት እንጂ ምንም ምክንያት አልተቀበሉትም።

በወንጌላዊ ማርቆስ ወንበርም በተቀመጠ ጊዜ ለአብያተ ክርስቲያን እጅግ የሚያስብ ሆነ ለርሱ የሆነውን የግብሩን ገቢ ወስዶ ምድሮችን በመግዛት ለአብያተ ክርስተያን መተዳደሪያ ሊሆኑ ጉልቶች ያደርጋቸው ነበርና።

አዘውትሮም ሕዝቡን የሚያስተምራቸው ሆነ በምንም በምን ለየአንዳንዱ ቸለል አይልም ነገር ግን ሰይጣን ስለቀናበት ያለ ኀዘን አልተወውም ። ይህም እንዲህ ነው በምስር አገር የተሾሙ ሁለት ኤጲስቆጶሳት በሕዝቡ ላይ ክፉ ነገር በማድረግ በማይገባ ሥራ አስጨነቋቸው እርሱም በርኅራኄና በፍቅር መንጎቻቸውን እንዲጠብቁ አዘዛቸው ለመናቸውም እነርሱ ግን ሰምተው ከክፋታቸው አልተመለሱም።

በሕዝቡም ላይ ችግርን በአበዙ ጊዜ ሕዝቡ ሁሉም በጠቅላላ ወደ ሊቀ ጳጳሳት አባ ዮሴፍ መጡ በፊቱም እንዲህ ብለው ጮኹ እሊህን ኤጲስቆጶሳት ከላያችን ካላነሣሃቸው እኛ ወደሌላ ሃይማኖት እንገባለን አባ ዮሴፍም በመካከላቸው ሰላምን ለማድረግ ብዙ ትግልን ታገለ ግን አልተቻለውም።

ከዚህም በኋላ በግብጽ አገር ያሉትን ኤጲስቆጶሳት ለጉባኤ ሰበሰባቸውና ስለ እሊህ ሁለት ኤጲስቆጶሳት ነገራቸው አሁንም ከመንጋዎቻቸው ጋር ሊአስታርቅ ሽቶ እሊህን ኤጲስቆጶሳት ወደ ጉባኤው አስቀረባቸው እነርሱ ግን የጉባኤውንም የእርሱንም ቃል አልተቀበሉም ስለዚህም ያ ጉባኤ ከሹመታቸው ሻራቸው።

እነርሱም ወደ ግብጽ ንጉሥ ሒደው በሊቀ ጳጳሳት አባ ዮሴፍ ላይ በሐሰት ነገር ሠሩበት ሊቀ ጳጳሳት አባ ዮሴፍንም ያመጡት ዘንድ ንጉሡ ወንድሙን ከጭፍራ ጋር ላከው። የንጉሡም ወንድም ወደ ሊቀ ጳጳሳቱ በደረሰ ጊዜ ተበሳጨ ሊገለውም ወዶ ሰይፉን መዞ ሊቀ ጳጳሳቱን ሊመታው ሰነዘረበት ግን እጁ ወደ ሌላ አዘንብሎ ምሰሶ መትቶ ሰይፉ ተሰበረ እጅግም ተቆጥቶ ሌላ ሰይፍን መዝዞ በመላ ኃይሉ መታው ያን ጊዜም ሰይፉ ከአንገቱ ወደ ወገቡ ተመልሶ ልብሱንና ቅናቱን ብቻ ቆረጠ የንጉሡም ወንድም ከክፋት ንጹሕ እንደሆነ ስለዚህም አምላካዊት ኃይል እንደምትጠብቀው አሰበ አስተዋለም።

ወደ ንጉሡም በክብር አደረሰው ወንድሙ ለሆነ ንጉሥም በእርሱ በሊቀ ጳጳሳቱ ላይ የሆነውን ሁሉ ነገረው ንጉሡም ፈራው አከበረውም ከዚህም በኋላ ስለከሰሱት ስለ ሁለቱ ኤጲስቆጶሳት ጠየቀው እርሱም ስለ ክፉ ሥራቸው በጉባኤ እንደተሻሩ እውነቱን ለንጉሡ አስረዳው ያን ጊዜም ሐሰተኞች እንደሆኑ ንጉሥ አወቀ ይገድሏቸውም ዘንድ አዘዘ።

ሊቀ ጳጳሳት አባ ዮሴፍም ንጉሡን እንዲህ ብሎ ማለደው #ጌታችን በክፉ ፈንታ በጎ እንድናደርግ እኛን አዞናልና ስለ #እግዚአብሔር ብለህ እሊህን ማራቸው እንጂ አትግደላቸው ንጉሡም ስለ የዋህነቱ አደነቀ ልመናውንም ተቀብሎ ማረለት።

ከዚህም በኋላ በሹማምንቱና በኤጲስቆጶሳቱ ሁሉ ላይ የፈለገውን ያደረግ ዘንድ ቢፈልግ እንዲሾም ወይም እንዲሽር የሚቃወመው እንዳይኖር ደብዳቤ በመጻፍ ሥልጣንን ሰጠው።

በዚህም አባት ዘመን የኢትዮጵያ ንጉሥ ወደዚህ አባት ወደ ሊቀ ጳጳሳት አባ ዮሴፍ እንዲህ ብሎ መልእክትን ላከ ለወንጌላዊ ማርቆስ መንበርና በላዩ ለመቀመጥ ለተገባው ቅድስናህ እጅ እነሣለሁ በእኔና በመንግሥቴ ላይ በመላው ወገኖቼ በኢትዮጵያ ሰዎች ላይ ይቅርታ እንድታደርግና አባታችንን አባ ዮሐንስን እንድትልክልን እለምንሃለሁ ከሀገራችን ሰዎች ከእውነት መንገድ የወጡና የሳቱ ጳጳሳችንን አባ ዮሐንስን እኔ ሳልኖርና ሳላውቅ አባረውታልና ስለዚህም በሀገራችን ቸነፈርና ድርቅ ሁኖ ከሰዎችም ከእንስሶችም ብዙዎች አለቁ።

አሁንም አባቴ ሆይ ስንፍናችንን ይቅር በል መሐሪና ይቅር ባይ ወደ ሆነ #እግዚአብሔር ፈጽሞ ይማልድልን ዘንድ በከበረች ጸሎቱም ከዚህ መከራ እንድን ዘንድ አባታችንን አባ ዮሐንስን ላክልን።

አባቴ ሆይ የተባረረበትን ምክንያት እኔ አስረዳሃለሁ እኔ ልጅህ ከአባቴ ከጳጳስ አባ ዮሐንስ ቡራኬ ተቀብዬ እርሱ ከሠራዊቴ ጋር በፍቅር አሰናብቶኝ ወደ ጦር ሜዳ ሔድሁ ከጦር ሜዳም በተመለስኩ ጊዜ አባቴን አባ ዮሐንስ ጳጳሱን አጣሁት ስለርሱም በጠየቅሁ ጊዜ በቀድሞ ዘመን ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅን ንግሥት አውዶክስያ እንዳሳደደችው በክፉዎች ሰዎች ምክር ንግሥቲቱ ሚስቴ ማሳደዷን የቀኖናውንም ትእዛዝ በመተላለፍ በፈቃዳቸው ሌላ ጳጳስ እንደሾሙ ነገሩኝ።
እርሱ አባ ዮሐንስም ከኢትዮጵያ በአሳደዱት ጊዜ ወደ አስቄጥስ በመሔድ አስቀድሞ በመነኰሰባት በአባ ሙሴ ጸሊም ገዳም በዚያ ተቀመጠ። የኢትዮጵያ ንጉሥ መልእክትም ወደ ሊቀ ጳጳሳት አባ ዮሴፍ በደረሰች ጊዜ አነበባት ስለ ኢትዮጵያ ንጉሥ የሃይማኖት ጽናት እጅግ ደስ አለው ፈጥኖም ወደ አስቄጥስ ገዳም መልእክተኞችን ልኮ አባ ዮሐንስን ወደርሱ አስመጥቶ አረጋጋው አጽናናው ከዚያም በኋላ ከደጋጎች ሰዎች ጋር ወደ ኢትዮጵያ አገር ላከው።

አባ ዮሐንስም ወደ ኢትዮጵያ አገር በደረሰ ጊዜ ቸነፈር ተወገደ ዝናብም ዘነበ ንጉሡና መላው የኢትዮጵያ ሰዎች ደስ ብሏቸው #እግዚአብሔርን አመሰገኑት። ይህም ሊቀ ጳጳሳት አባ ዮሴፍ መናፍቃንን የሚገሥጻቸው ሆነ ሕዝቡንም ከአባቶቻቸው በተቀበሏት በቀናች ሃይማኖት እንዲጸኑ አስተማራቸው ከቅዱሳት መጻሕፍትም ለእነርሱም ሥውር የሆነውን ተርጉሞ ያስረዳቸዋል ያስገነዝባቸዋልም በትምህርቱና በጸሎቱም እንዲህ ጠበቃቸው #ጌታችንም በእጆቹ ብዙዎች ተአምራትን አደረገ ያማረች ገድሉንም ፈጽሞ #እግዚአብሔርንም አገልግሎ በሰላም በፍቅር አረፈ ። መላ የሕይወቱም ዘመን ሰባ ስምንት ነው ከምንኲስና በፊት ሃያ አመት በምንኲስና ተጋድሎ ሠላሳ ዘጠኝ ዓመት በሊቀ ጵጵስና ሹመት ዓሥራ ዘጠኝ ዓመት ኖረ ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን አበው ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_እለእስክንድርያ_ሰማዕት

ዳግመኛም በዚህች ቀን የከሀዲ ዱድያኖስ ንጉሥ ሚስት የከበረች እለእስክንድርያ መታሰቢያዋ ነው። ይኸውም ለጣዖቶቹ እንደሚሠዋ መስሎ ቅዱስ ጊዮርጊስ በዘበተበት ጊዜ ዝንጉዕ ዱድያኖስም ዕውነት መስሎት ራሱን ሊስም ተነሣ። ቅዱሱ ግን ለአማልክት ከመሠዋት አስቀድሞ አይሆንም ብሎ እንዳይስመው ከለከለው።

ከዚህ በኋላም ዱድያኖስ ወደ ቤተ መንግሥቱ አዳራሽ ቅዱስ ጊዮርጊስን አስገባው በዚያም በንግሥት እለእስክንድርያ ፊት የዳዊትን መዝሙር በማንበብ ጸለየ። በሰማችም ጊዜ ይተረጒምላት ዘንድ ለመነችው ያን ጊዜም ተረጐመላት የክብር ባለቤት #የጌታችን_የኢየሱስ_ክርስቶስን ጌትነቱን ገለጠላት ትምህርቱም በልቡዋ አድሮ በክብር ባለቤት በ #ጌታችን_በኢየሱስ_ክርስቶስ አመነች።

ከዚህም በኋላ ሲነጋ ለአማልክት ወደሚሠዋበት ቅዱስ ጊዮርጊስን ወሰዱት እርሱም የረከሱ አማልክትን ትውጣቸው ዘንድ ምድርን አዘዛት ምድርም ዋጠቻቸው። ንጉሥ ዱድያኖስም አፈረ እየአዘነና እየተከዘ ወደ ሚስቱ ወደ እለእስክንድርያ ዘንድ ገባ። እርሷም ክርስቲያኖችን አትጣላቸው አምላካቸው ጽኑዕና ኃያል ነው አላልኩህምን አለችው። ይህንንም ሰምቶ በእርሷ ላይ ተቆጣ ያሠቃዩዋት ዘንድ ጡቶቿንም ሠንጥቀው ይሰቅሏት ዘንድ አዘዘ። የሰማዕትነትንም አክሊል በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለች።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅድስቷ ሰማዕት ጸሎት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ዲዮናስዮስ_ኤጲስቆጶስ

በዚችም ቀን የቆሮንቶስ አገር ኤጲስቆጶስ ዲዮናስዮስ በዐላውያን ነገሥታት በዲዮቅልጥያኖስና በመክስምያኖስ ዘመን በሰማዕትነት አረፈ ይህንንም ቅዱስ በያዙት ጊዜ ብዙ ሥቃይን አሠቃዩት ማሠቃየቱንም በሰልቹ ጊዜ ራሱን በሰይፍ አስቆረጡት የሰማዕትነት አክሊልንም ተቀበለ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎቱ ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ጻድቁ_አቡነ_ኤልሳ

ዳግመኛም በዚህች ቀን በአቡነ ተክለ ሃይማኖት ተተክተው በደብረ ሊባኖስ የተሾሙት አቡነ ኤልሳ ዕረፍታቸው ነው፡፡ ጻድቁ ሀገራቸው ሸዋ ነው፡፡ በዐፄ ይኩኖ አምላክ ዘመን የነበሩ ሲሆን ከአቡነ ተክለ ሃይማኖት ቀጥለው በደብረ ሊባኖስ ገዳም በእጨጌነት የተሾሙ የመጀመሪያ ዕጨጌ ናቸው፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከማረፋቸው በፊት ‹‹በእኔ ወንበር ኤልሳዕ ይሾም ነገር ግን ዘመኑ ትንሽ ስለሆነ ከእርሱ ቀጥሎ ፊሊጶስን ትሾማላችሁ›› ብለው ለቅዱሳን ተከታይ ሐዋርያቶቻቸው ተናግረው ነበር፡፡

በዚህም መሠረት አቡነ ኤልሳዕ ተሹመው ብዙም ሳይቆዩ አንድ ዲያቆን ሞተና ሊቀብሩት ሲወስዱት በመንገድ ላይ ሳለ ድንገት ከሞት ተነሥቶ ‹‹አባቴ ተክለ ሃይማኖት ኤልሳዕ አሁን ወደኔ ስለሚመጣ ፊሊጶስን ሹሙት ብለህ ተናገር ብለውኝ ነው›› ብሎ ከተናገረ በኋላ ተመልሶ ዐርፎ ተቀበረ፡፡ አቡነ ኤልሳዕም ወዲያው ዐርፈው አቡነ ፊሊጶስ 3ኛ ሆነው ተሾሙ፡፡ አቡነ ኤልሳዕ ከተጋድሎአቸው ብዛት የተነሣ በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ ጎናቸውን አሳርፈው ተኝተው አያውቁም ነበር፡፡ ነገር ግን ማረፍ ሲኖርባቸው በወንበር ላይ ተደግፈው ትንሽ ብቻ ያርፉ ነበር፡፡ አቡነ ኤልሳዕ በሞት ያረፉትም እንደልማዳቸው ጎናቸውን ሳያሳርፉ በወንበር ላይ እንደተደገፉ ነበር፡፡ አባታችን ስለዚህም ጉዳይ ሲናገሩ እንዲህ ይሉ ነበር፡- ‹‹ነፍስ ትጋትን ትወዳለች፣ ሥጋ ግን ይደክማል፡፡ ለመነኮሳትና ለ #እግዚአብሔር አገልጋዮች ሁሉ መኝታ ማብዛት አይገባቸውም፡፡ መኝታ ማብዛት ሕልምን ያመጣል፣ ነፍስን ይጎዳል፣ ሰውነትንም ያደክማል፡፡››

አቡነ ኤልሳዕ በዘመናቸው ወንጌልን በማስተማርና ድንቅ ድንቅ ተአምራትን በማድረግ ይታወቁ ነበር፡፡ እንደ ነቢዩ ኤልሳዕ እሳቸውም ሙት አስነሥተዋል፡፡ ባሕር እየከፈሉ ቀደ መዛሙርቶቻቸውን ያሻግሩ ነበር፡፡ በጸሎታቸው የዠማን ወንዝም ለሁለት የከፈሉ ታላቅ አባት ናቸው፡፡

ለእግዚአብርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምት_23 እና #ከገድላት_አንደበት)
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ጥቅምት_23_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ጢሞቴዎስ 6
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁷ በአሁኑ ዘመን ባለ ጠጎች የሆኑት የትዕቢትን ነገር እንዳያስቡ፥ ደስም እንዲለን ሁሉን አትርፎ በሚሰጠን በሕያው እግዚአብሔር እንጂ በሚያልፍ ባለ ጠግነት ተስፋ እንዳያደርጉ እዘዛቸው።
¹⁸-¹⁹ እውነተኛውን ሕይወት ይይዙ ዘንድ፥ ለሚመጣው ዘመን ለራሳቸው መልካም መሠረት የሚሆንላቸውን መዝገብ እየሰበሰቡ፥ መልካምን እንዲያደርጉ በበጎም ሥራ ባለ ጠጎች እንዲሆኑ፥ ሊረዱና ሊያካፍሉም የተዘጋጁ እንዲሆኑ ምከራቸው።
²⁰ ጢሞቴዎስ ሆይ፥ በውሸት እውቀት ከተባለ ለዓለም ከሚመች ከከንቱ መለፍለፍና መከራከር እየራቅህ፥ የተሰጠህን አደራ ጠብቅ፤
²¹ ይህ እውቀት አለን ብለው፥ አንዳንዶች ስለ እምነት ስተዋልና። ጸጋ ከአንተ ጋር ይሁን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ያዕቆብ 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹² በፈተና የሚጸና ሰው የተባረከ ነው፤ ከተፈተነ በኋላ ለሚወዱት ተስፋ ስለ እርሱ የሰጣቸውን የሕይወትን አክሊል ይቀበላልና።
¹³ ማንም ሲፈተን፦ በእግዚአብሔር እፈተናለሁ አይበል፤ እግዚአብሔር በክፉ አይፈተንምና፤ እርሱ ራሱስ ማንንም አይፈትንም።
¹⁴ ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ይፈተናል።
¹⁵ ከዚህ በኋላ ምኞት ፀንሳ ኃጢአትን ትወልዳለች፤ ኃጢአትም ካደገች በኋላ ሞትን ትወልዳለች።
¹⁶ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፥ አትሳቱ።
¹⁷ በጎ ስጦታ ሁሉ ፍጹምም በረከት ሁሉ ከላይ ናቸው፥ መለወጥም በእርሱ ዘንድ ከሌለ በመዞርም የተደረገ ጥላ በእርሱ ዘንድ ከሌለ ከብርሃናት አባት ይወርዳሉ።
¹⁸ ለፍጥረቱ የበኵራት ዓይነት እንድንሆን በእውነት ቃል አስቦ ወለደን።
¹⁹ ስለዚህ፥ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፥ ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ ለመናገርም የዘገየ ለቍጣም የዘገየ ይሁን፤
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 15
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ አንዳንዶችም ከይሁዳ ወረዱና፦ እንደ ሙሴ ሥርዓት ካልተገረዛችሁ ትድኑ ዘንድ አትችሉም ብለው ወንድሞችን ያስተምሩ ነበር።
² በእነርሱና በጳውሎስ በበርናባስም መካከል ብዙ ጥልና ክርክር በሆነ ጊዜ፥ ስለዚህ ክርክር ጳውሎስና በርናባስ ከእነርሱም አንዳንዶች ሌሎች ሰዎች ወደ ሐዋርያት ወደ ሽማግሌዎችም ወደ ኢየሩሳሌም ይወጡ ዘንድ ተቈረጠ።
³ ቤተ ክርስቲያኑም በመንገድ እየረዳቸው እነርሱ የአሕዛብን መመለስ እየተረኩ በፊንቄና በሰማርያ አለፉ፥ ወንድሞችንም ሁሉ እጅግ ደስ አሰኙአቸው።
⁴ ወደ ኢየሩሳሌምም በደረሱ ጊዜ ቤተ ክርስቲያንና ሐዋርያት ሽማግሌዎችም ተቀበሉአቸው፥ እግዚአብሔርም ከእነርሱ ጋር ያደረገውን ሁሉ አወሩ።
⁵ ከፈሪሳውያን ወገን ግን ያመኑት አንዳንዶቹ ተነሥተው፦ ትገርዙአቸው ዘንድና የሙሴን ሕግ እንዲጠብቁ ታዙአቸው ዘንድ ይገባል አሉ።
⁶ ሐዋርያትና ሽማግሌዎችም ስለዚህ ነገር ለመማከር ተሰበሰቡ።
⁷ ከብዙ ክርክርም በኋላ ጴጥሮስ ተነሥቶ እንዲህ አላቸው ወንድሞች ሆይ፥ አሕዛብ ከአፌ የወንጌልን ቃል ሰምተው ያምኑ ዘንድ እግዚአብሔር በመጀመሪያው ዘመን ከእናንተ እኔን እንደ መረጠኝ እናንተ ታውቃላችሁ።
⁸ ልብንም የሚያውቅ አምላክ ለእኛ ደግሞ እንደ ሰጠን መንፈስ ቅዱስን በመስጠት መሰከረላቸው፤
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ጥቅምት_23_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇🌹

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"እስመ መምህረ ሕግ ይሁብ በረከተ። ወየሐውር እምኀይል ውስተ ኃይል። ወያስተርኢ አምላከ አማልክት በጽዮን"። መዝ 83፥6-7።
"በልቅሶ ሸለቆ ውስጥ በወሰነው ስፍራ የሕግ መምህር በረከትን ይሰጣልና። ከኃይል ወደ ኃይል ይሄዳሉ፤ የአማልክት አምላክ በጽዮን ይታያል"። መዝ 83፥6-7።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ጥቅምት_23_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሉቃስ 6
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
³⁶ አባታችሁ ርኅሩኅ እንደ ሆነ ርኅሩኆች ሁኑ።
³⁷ አትፍረዱ አይፈረድባችሁምም፤ አትኰንኑ አትኰነኑምም። ይቅር በሉ ይቅርም ትባላላችሁ።
³⁸ ስጡ ይሰጣችሁማል፤ በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ተመልሶ ይሰፈርላችኋልና፥ የተጨቈነና የተነቀነቀ የተትረፈረፈም መልካም መስፈሪያ በእቅፋችሁ ይሰጣችኋል።
³⁹ ምሳሌም አላቸው፦ ዕውር ዕውርን ሊመራ ይችላልን? ሁለቱ በጕድጓድ አይወድቁምን?
⁴⁰ ደቀ መዝሙር ከመምህሩ አይበልጥም፤ ፈጽሞ የተማረ ሁሉ ግን እንደ መምህሩ ይሆናል።
⁴¹ በወንድምህም ዓይን ያለውን ጉድፍ ስለ ምን ታያለህ፥ በራስህ ዓይን ግን ያለውን ምሰሶ ስለ ምን አትመለከትም?
⁴² በዓይንህ ያለውን ምሰሶ ራስህ ሳታይ፥ እንዴት ወንድምህን፦ ወንድሜ ሆይ፥ በዓይንህ ያለውን ጉድፍ ላውጣ ፍቀድልኝ ልትል ትችላለህ? አንተ ግብዝ፥ አስቀድመህ ከዓይንህ ምሰሶውን አውጣ ከዚያም በኋላ በወንድምህ ዓይን ያለውን ጉድፍ ታወጣ ዘንድ አጥርተህ ታያለህ።
⁴³ ክፉ ፍሬ የሚያደርግ መልካም ዛፍ የለምና፥ እንዲሁም መልካም ፍሬ የሚያደርግ ክፉ ዛፍ የለም።
⁴⁴ ዛፍ ሁሉ ከፍሬው ይታወቃልና፤ ከእሾህ በለስ አይለቅሙም፥ ከአጣጥ ቍጥቋጦም ወይን አይቈርጡም።
⁴⁵ በልብ ሞልቶ ከተረፈው አፉ ይናገራልና መልካም ሰው ከልብ መልካም መዝገብ መልካሙን ያወጣል፥ ክፉ ሰውም ከልብ ክፉ መዝገብ ክፉውን ያወጣል።
⁴⁶ ስለ ምን፦ ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ ትሉኛላችሁ፥ የምለውንም አታደርጉም?
⁴⁷ ወደ እኔ የሚመጣ ሁሉ ቃሌንም ሰምቶ የሚያደርገው፥ ማንን እንዲመስል አሳያችኋለሁ።
⁴⁸ ቤት ሲሠራ አጥልቆ የቆፈረ በዓለት ላይም የመሠረተ ሰውን ይመስላል፤ ጐርፍም በመጣ ጊዜ ወንዙ ያን ቤት ገፋው፥ በዓለት ላይም ስለ ተመሠረተ ሊያናውጠው አልቻለም።
⁴⁹ ሰምቶ የማያደርገው ግን ያለ መሠረት በምድር ላይ ቤቱን የሠራ ሰውን ይመስላል፤ ወንዙም ገፋው ወዲያውም ወደቀ የዚያ ቤት አወዳደቅም ታላቅ ሆነ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️ 🌹
የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #ሠለስቱ_ምዕት_ቅዳሴ ነው። መልካም የአቡነ እጨጌ ኤልሳዕ የዕረፍት በዓል፣ የሊቀ ጳጳስ የአባ ዮሴፍ፣ የቅድስት እለስክንድርያና የቅዱስ ዲዮናስዮስ የዕረፍት በዓልና ቀዳሚት ሰንበት ለሁላችንም ይሁንልን።
🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
2024/12/28 05:07:16
Back to Top
HTML Embed Code: