Telegram Web Link
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#መስከረም_7_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ዕብራውያን 13
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹³ እንግዲህ ነቀፌታውን እየተሸከምን ወደ እርሱ ወደ ሰፈሩ ውጭ እንውጣ፤
¹⁴ በዚህ የምትኖር ከተማ የለችንምና፥ ነገር ግን ትመጣ ዘንድ ያላትን እንፈልጋለን።
¹⁵ እንግዲህ ዘወትር ለእግዚአብሔር የምስጋናን መሥዋዕት፥ ማለት ለስሙ የሚመሰክሩ የከንፈሮችን ፍሬ፥ በእርሱ እናቅርብለት።
¹⁶ ነገር ግን መልካም ማድረግን ለሌሎችም ማካፈልን አትርሱ፤ እንዲህ ያለው መሥዋዕት እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘዋልና።
¹⁷ ለዋኖቻችሁ ታዘዙና ተገዙ፤ እነርሱ ስሌትን እንደሚሰጡ አድርገው፥ ይህንኑ በደስታ እንጂ በኃዘን እንዳያደርጉት፥ ይህ የማይጠቅማችሁ ነበርና፥ ስለ ነፍሳችሁ ይተጋሉ።
¹⁸ ጸልዩልን፤ በነገር ሁሉ በመልካም እንድንኖር ወደን፥ መልካም ሕሊና እንዳለን ተረድተናልና።
¹⁹ ይልቁንም ፈጥኜ እንድመለስላችሁ ይህን ታደርጉ ዘንድ አጥብቄ እለምናችኋለሁ።
²⁰ በዘላለም ኪዳን ደም ለበጎች ትልቅ እረኛ የሆነውን ጌታችንን ኢየሱስን ከሙታን ያወጣው የሰላም አምላክ፥
²¹ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በፊቱ ደስ የሚያሰኘውን በእናንተ እያደረገ፥ ፈቃዱን ታደርጉ ዘንድ በመልካም ሥራ ሁሉ ፍጹማን ያድርጋችሁ፤ ለእርሱ እስከ ዘላለም ድረስ ክብር ይሁን፤ አሜን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ጴጥሮስ 3
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁴ ነገር ግን ስለ ጽድቅ እንኳ መከራን ብትቀበሉ ብፁዓን ናችሁ። ማስፈራራታቸውንም አትፍሩ አትናወጡም፥
¹⁵ ዳሩ ግን ጌታን እርሱም ክርስቶስ በልባችሁ ቀድሱት። በእናንተ ስላለ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቁአችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ሁኑ፥ ነገር ግን በየዋህነትና በፍርሃት ይሁን።
¹⁶ በክርስቶስ ያለውን መልካሙን ኑሮአችሁን የሚሳደቡ ሰዎች ክፉን እንደምታደርጉ በሚያሙበት ነገር እንዲያፍሩ በጎ ሕሊና ይኑራችሁ።
¹⁷ የእግዚአብሔር ፈቃድ እንዲህ ቢሆን፥ ክፉ ስለ ማድረግ ሳይሆን በጎ ስለ ማድረግ መከራን ብትቀበሉ ይሻላችኋልና።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 16
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁶ ወደ ጸሎት ስፍራም ስንሄድ፥ የምዋርተኝነት መንፈስ የነበረባት ለጌቶችዋም እየጠነቈለች ብዙ ትርፍ ታመጣ የነበረች አንዲት ገረድ አገኘችን።
¹⁷ እርስዋ ጳውሎስንና እኛን እየተከተለች፦ የመዳንን መንገድ የሚነግሩአችሁ እነዚህ ሰዎች የልዑል አምላክ ባሪያዎች ናቸው ብላ ትጮኽ ነበር።
¹⁸ ይህንም እጅግ ቀን አደረገች። ጳውሎስ ግን ተቸገረና ዘወር ብሎ መንፈሱን፦ ከእርስዋ እንድትወጣ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አዝሃለሁ አለው፤ በዚያም ሰዓት ወጣ።
¹⁹ ጌቶችዋም የትርፋቸው ተስፋ እንደ ወጣ ባዩ ጊዜ ጳውሎስንና ሲላስን ይዘው ወደ ገበያ በሹማምት ፊት ጐተቱአቸው፤
²⁰ ወደ ገዢዎችም አቅርበው፦ እነዚህ ሰዎች አይሁድ ሆነው ከተማችንን እጅግ ያናውጣሉ።
²¹ እኛም የሮሜ ሰዎች ሆነን እንቀበላቸውና እናደርጋቸው ዘንድ ያልተፈቀደልንን ልማዶች ይናገራሉ አሉ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#መስከረም_7_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"እስመ መምህረ ሕግ ይሁብ በረከተ። ወየሐውር እምኀይል ውስተ ኃይል። ወያስተርኢ አምላከ አማልክት በጽዮን"። መዝ.83፥6-7።
"በልቅሶ ሸለቆ ውስጥ በወሰነው ስፍራ የሕግ መምህር በረከትን ይሰጣልና። ከኃይል ወደ ኃይል ይሄዳሉ፤ የአማልክት አምላክ በጽዮን ይታያል"። መዝ.83፥6-7።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#መስከረም_7_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ማርቆስ 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²³ በዚያን ጊዜም በምኩራባቸው ርኵስ መንፈስ ያለው ሰው ነበረ፤
²⁴ እርሱም፦ የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለን? ልታጠፋን መጣህን? ማን እንደ ሆንህ አውቄአለሁ፥ የእግዚአብሔር ቅዱሱ ብሎ ጮኸ።
²⁵ ኢየሱስም፦ ዝም በል ከእርሱም ውጣ ብሎ ገሠጸው።
²⁶ ርኵሱም መንፈስ አንፈራገጠውና በታላቅ ድምፅ ጮኾ ከእርሱ ወጣ።
²⁷ ሁሉም፦ ይህ ምንድር ነው? በሥልጣን ርኵሳን መናፍስትን ያዝዛል፤ እነርሱም ይታዘዙለታልና ይህ አዲስ ትምህርት ምንድር ነው? ብለው እስኪጠያየቁ ድረስ አደነቁ።
²⁸ ዝናውም ወዲያው በየስፍራው ወደ ገሊላ ዙሪያ ሁሉ ወጣ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #እመቤታች_ማርያም_ቅዳሴ ነው። መልካም የቅድስት ሐና የልደት በዓል፣ የአባ ዲዮስቆሮስ የዕረፍት በዓል፣ የቅድስት ኤልሳቤጥ የዕረፍት በዓል፣ የቅዱስ ሳዊርያኖስ የዕረፍት በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#መስከረም_8

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
መስከረም ስምንት በዚህች ቀን የነቢያት አለቃ #ነቢዩ_ቅዱስ_ሙሴ ዕረፍቱ ነው፣ የበራክዩ ልጅ ካህንና ነቢይ የሆነ #ቅዱስ_ዘካርያስ በሰማዕትነት አረፈ፣ የከበረ #ቅዱስ_ዲማድዮስ በሰማእትነት አረፈ፣ የካህኑ #ቅዱስ_አሮን በትሩ ለምልማ የተገኘችበት ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ሙሴ_ሊቀ_ነቢያት

መስከረም ስምንት በዚህች ቀን የ #እግዚአብሔር ሰው የሆነ የዋህ ቅን ጻድቅ የነቢያት አለቃ የሙሴ ዕረፍቱ ነው። ይህ ነቢይ ነፍሱን ስለእሳቸው አሳልፎ እስከ መስጠት ከ #እግዚአብሔር ወገኖች ጋር የደከመ ነው እርሱም በግብጽ አገር በኤርትራ ባሕርም ድንቆች ተአምራትን ያደረገ ነው።

ይህም ስለ ፈርዖን ትእዛዝ ወላጆቹ በግብጽ ወንዝ ውስጥ በጣሉት ጊዜ አውጥታ ላሳደገችው ለፈርዖን ልጅ ለተርሙት ልጅዋ መባልን አልወደደም። እርሱ ፈርዖን የዕብራውያንን ወንዶች ልጆች ይገድሏቸው ዘንድ አዝዞ ነበርና። በአገኘችውም ጊዜ ለርሷ ልጅ ሊሆናት ወስዳ በመልካም አስተዳደግ አሳደገችው።

አርባ ዓመትም በሆነው ጊዜ አንዱን ዕብራዊ የግብጽ ሰው የሆነ ሲያጠቃው አየ ለዕብራዊውም ተበቅሎ ግብጻዊውን ገደለው። በማግሥቱ ደግሞ ሁለት ዕብራውያን እርስ በርሳቸው ሲጣሉ አያቸው ሊአስታርቃቸውና በመካከላቸው ሰላምን ሊአደርግ ወደደ። አንዱ ዐመፀኛም ትላንት ግብጻዊውን እንደገደልከው ልትገድለኝ ትሻለህን አለው።

ስለዚህም ነገር ሙሴ ፈርቶ ወደ ምድያም አገር ሸሸ በዚያም ሚስት አግብቶ ሁለት ልጆችን ወለደ በዚያም አርባ ዓመት ኖረ በጳጦስ ቍጥቋጦ ውስጥም እሳት እየነደደ ራእይን አየ። አይቶ ሊረዳ በቀረብ ጊዜ ጳጦስ በተባለ ቊጥቋጦ ውስጥ #እግዚአብሔር ተናገረው። ወደ ግብጽ አገርም ሒዶ የእስራኤልን ልጆች ከዚያ እንዲአወጣቸው አዘዘው።

ከዚህን በኋላ #እግዚአብሔር በሙሴ እጅ በግብጻውያን ላይ ዐሥር መቅሠፍቶችን አመጣ። መጀመሪያው የወንዙን ውኃ ደም ማድረግ የመጨረሻው የግብጻውያንን የበኵር ልጅ መግደል ነው።

ከዚህም በኋላ ሕዝቡን ከግብጽ አገር አወጣቸው የኤርትራንም ባሕር ከፍሎ በውስጡ አሳለፋቸው የባሕሩንም ውኃ በጠላቶቻቸው በፈርዖንና በሠራዊት ላይ ገልብጦ አሠጠማቸው።

ከዚህም በኋላ በምድረ በዳ ውስጥ አርባ ዓመት ሙሉ መና አወረደላቸው ውኃንም ከአለት አፈለቀላቸው ይህን ሁሉ በጎ ሥራ በዚህ በደግ ነቢይ ሙሴ እጅ #እግዚአብሔር አደረገላቸው እነርሱ ግን ይዘልፉት ነበር ብዙ ጊዜም በድንጊያ ሊወግሩት ሽተው ነበር።

እርሱ ግን በእነርሱ ላይ ልቡን አስፍቶ በመታገሥ ስለርሳቸው ወደ #እግዚአብሔር ይማልዳል። እነርሱንም አብዝቶ ከመውደዱ የተነሣ #እግዚአብሔርን አቤቱ የዚህን ሕዝብ በደሉን ይቅር ካላልክ ከሕይወት መጽሐፍህ ሰርዘኝ አለው።

ሰው ከወዳጁ ጋር እንደሚነጋገር አምስት መቶ ሰብዓ ቃላትን ከ #እግዚአብሔር ጋር እንደተነጋገረ መጽሐፍ ምስክር ሆነ። የእስራኤል ልጆችም በሚያዩት ጊዜ እንዳይሞቱ ፊቱን እስከ ሸፈነ ድረስ በ #እግዚአብሔር በጌትነቱ ብርሀን ፊቱ በራ።

መቶ ሃያ ዓመት የሆነ ዕድሜውም በተፈጸመለት ጊዜ ለአገልጋዩ ለነዌ ልጅ ለኢያሱ ሕዝቡን እርሱ እንደጠበቃቸው እንዲጠብቃቸው በእጁ ውስጥ እንዲአስረክበው #እግዚአብሔር ሙሴን ለኢያሱ አስረክብ ብሎ አዘዘው።

ሙሴም ኢያሱን ጠርቶ የ #እግዚአብሔርን ትእዛዝ አዘዘው ሕጉንም እንዲጠብቅ ሕዝቡንም ለኢያሱ በእጁ አስረከባቸው ወደ ምድረ ርስትም እርሱ እንደ ሚአስገባቸው አረጋገጠለት። ሙሴም #እግዚአብሔር እንዳዘዘው በምስክሩ ድንኳን ውስጥ የሚሠራውን ሁሉ ሠርቶ ከአዘጋጀ በኋላ በተራራ ውስጥ አረፈ በዚያም በመላእክት እጅ በሥውር ተቀበረ። የእስራኤል ልጆች ወስደው እንዳያመልኩት #እግዚአብሔር የሙሴን ሥጋ ሠወረ።

በእስራኤል ልጆች ውስጥ እንደ ሙሴ ያለ ደግ የዋህ ቅን የሆነ ነቢይ እንደማይነሣ መጽሐፍ ምስክር ሆነ። ሰይጣንም የሙሴን ሥጋ ለእስራኤል ሊገልጥላችው በወደደ ጊዜ ሐዋርያው ይሁዳ በጻፈው መጽሐፉ እንደመሰከረ የመላእክት አለቃ ሚካኤል ገሠጸው ከዚህም ሥራ ከለከለው የእስራኤል ልጆችም አርባ ቀን አለቀሱለት።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ ሙሴ ጸሎት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ዘካርያስ_ካህን_ወነቢይ

በዚህችም ቀን የበራክዩ ልጅ ካህንና ነቢይ የሆነ የከበረ ዘካርያስ በንጉሥ ሄሮድስ እጅ በሰማዕትነት አረፈ። ይህም ካህን ስለ ልጁ ዮሐንስ መወለድ የመላእክት አለቃ ገብርኤል በነገረው ጊዜ ነገሩን አምኖ አልተቀበለም ። ስለዚህም ሕፃኑ እስቲወለድ ዲዳ ትሆናለህ አለው። በተወለደም ጊዜ አንደበቱ ተፈትቶ #እግዚአብሔርን አመሰገነው የልጁንም ስም ዮሐንስ ነው ብሎ ጻፈ። እርሱና ሚስቱ በ #እግዚአብሔር ሕግ ያለ ነቀፋ የጸኑ ደጎች እንደሆኑ የከበረ ወንጌል ስለዚህ ምስክር ሆኗል።

ክብር ይግባውና #ጌታችን_ክርስቶስም በተወለደ ጊዜ ሊሰግዱለት የጥበብ ሰዎች መጡ። ሄሮድስም ስለ መንግሥቱ ፈራ ደነገጠም። ስለዚህም ጭፍሮቹን ልኮ በይሁዳ አገር የቤተ ልሔምንና የገሊላን ሁሉንም ሕፃናት ዕድሜያቸው ሁለት ዓመት የሚሆናቸውን ከዚያም የሚያንሱትን ገደላቸው ሰነፍ የሆነ ሄሮድስ #ክርስቶስን ከሕፃናት ጋር እንደ ሚገድለው አስቦ ነበርና።

ከዚህም በኋላ የ #እግዚአብሔር መልአክ ለዮሴፍ በሕልም ተገልጾለት ስለአዘዘው #ጌታችን ሕፃኑንና እናቱን እመቤታችንን ድንግል #ማርያምን ይዞ ወደ ግብጽ አገር መጡ። ኤልሳቤጥ ግን ሕፃኗን ዮሐንስን ይዛ ወደ ዱር ወጣች ወደ ሲና በረሃም ሸሸች በዚያም ሕፃኗን እያሳደገች ሰባት ዓመት ኖረች ከዚህም እርሷ አረፈች ሕፃኑም በመምህርነት ለእሥራኤል እስከሚገለጥበት ጊዜ ድረስ በበረሀ ውስጥ ብቻውን ኖረ።

ሕፃናትንም ከገደላቸው በኋላ ዮሐንስ #ክርስቶስ እንደሆነ ሄሮድስ አሰበ ተጠራጠረ ከአባቱ ከዘካርያስ ዘንድ ሕፃኑን ይሹ ዘንድ ወታደሮቹን ላከ ዘካርያስም ሕፃኑ ያለበትን ወይም እናቱ ያለችበትን እኔ አላውቅም አለ። ሄሮድስም ልጅህን ካላመጣህልኝ እኔ እገድልሃለሁ አለው። ዘካርያስም ከእርሱ ዛቻ የተነሣ አልፈራም ወታደሮቹንም አዝዞ በቤተ መቅደሱና በመሠዊያው መካከል ገደሉት ክብር ይግባውና #እግዚአብሔርም ሥጋውን ሠወረ ደሙ ግን እንደ ደንጊያ ሆነች።

ካህናቱና ሕዝቡ እንደ ልማዳቸው ለጸሎት በመጡ ጊዜ ከካህናት አንዱ ወደ ቤተ መቅደስ ውስጥ ገባ። የረጋ ደምን አገኘ ከመጠዊያውም እንዲህ የሚል ቃልን ሰማ እነሆ የበራክዩ ልጅ ዘካርያስ ተገደለ የሚበቀልም እስሚመጣ ደሙ ስትጮኽ ትኖራለች።

እንዲህ የሚልም አለ ከዐሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት የሆነ የበራክዩ ልጅ ዘካርያስ ይህ አይደለም ያ አልተገደለም በዕድሜው ኡረት በሚባል አገር ሞተ እንጂ ሥጋውም በዚያ ያለ ጥፋት ተገኝቶ ቤተ ክርስቲያን ሠርተውለታል። የዚህ ዘካርያስ ግን ሥጋው አልተገኘም ስለ መገደሉ የደሙ ድምፅ ምስክር ሆነ እንጁ።

ደግሞ እንዲህ ተባለ ሄሮድስ ሕፃናትን በገደላቸው ጊዜ ከአይሁድ አንድ ሰው መጥቶ የ #እግዚአብሔር መልአክ ትወልዳለህ ብሎ ነግሮት ለዘካርያስ ልጅ ተወልዶለታል ምናልባት እርሱ #ክርስቶስን ይሆን አለው። ስለዚህ ሄሮድስ ሕፃኑን ዮሐንስን ይገድሉት ዘንድ ወታደሮችን ላከ።
ዘካርያስም ወታደሮችን እንዲህ አላቸው ሕፃኑን እኔ ወደሌላ ቦታ ወስጄዋለሁ ከእኔ ጋራ መጥታችሁ ራሳችሁ ከዚያ ቦታ ውሰዱት ወደ ቤተ መቅደስም እስከ አስገባቸው ድረስ ወታደሮቹ አብረውት መጡ። እርሱም ሕፃኑን ልጁን በመሠዊያው ጠርዝ ላይ አኑሮ ጸለየበት ይህም የልጁን መወለድ የ #እግዚአብሔር መልአክ ለእርሱ የነገረበት ነው።

ያን ጊዜም የ #እግዚአብሔር መልአክ ሕፃኑን ዚፈታ ወደሚባል በረሀ ነጥቆ ወሰደው ሕፃኑንም ባላገኙት ጊዜ አባቱን ዘካርያስን ገደሉት። ስለዚህም #ጌታችን አይሁድን በቤተ መቅደሰ መካከል የገደላችሁት የዘካርያስ ደም በላያችሁ ይደርሳል አላቸው ለመገደሉ ምክንያት አይሁድ ናቸውና እንዲህ አለ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎቱ ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ዲማድዮስ

በዚህች ቀን የከበረ ዲማድዮስ ከግብጽ ደቡብ ደንጡ ከሚባል አውራጃ ደርሰባ ከሚሏት ከተማ በሰማእትነት አረፈ። እርሱ ሁል ጊዜ ወደ ቤተ ክርስቲያን ይገሠግሣል ድኆችንና በሽተኞችን መጐብኘትንም ይወዳል።

ብርሃናዊ ሰውም ተገልጦለት ሒዶ የሰማእትነት አክሊልን እንዲቀበል አዘዘው ሰማያዊ የሆነ ቃል ኪዳንንም ገባለት በዚህም እጅግ ደስ አለው።

አባቱንና እናቱንም ትቶ ከሀረጉ ወጣ ስለ ከበረ ስሙ በሚቀበለው መከራ ውስጥ ርዳታ እንዲሰጠው እንዲአጸናው ወደ #እግዚአብሔር ጸለየ ወደ ሀገር አትሪብም ሔዶ በመኰንኑ ፊት ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ታመነ።

መኰንኑም ታላቅ ስቃይን አሰቃይቶ የእስክንድርያ አገረ ገዥ ወደ ሆነ ወደ ሉክያኖስ ሰደደው። በመርከብም ውስጥ ሳለ ክብር ይግባውና #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ተገለጠለት በብዙ ደስታም አረጋግቶትና አጽናንቶ ቃል ኪዳንን ሰጠው ልቡናውም ፈጽሞ እጅግ ደስ አላት።

መኰንኑ ሉክያኖስም በጽኑዕ ስቃይ አሰቃይቶ ራሱን በሰይፍ ቆረጠ የሰማዕትነት አክሊልንም በመንግስተ ሰማያት ተቀበለ። የሀገሩ ሰዎችም መጥተው ስጋውን ወሰዱ ታላቅ ክብርንም አከበሩት ከስጋውም ታላላቅ የሆኑ ድንቆችና ተአምራት ተገለጡ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎቱ ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አሮን_ካህን

በዚህች ቀን የካህኑ አሮን በትሩ ለምልማ የተገኘችበት ነው። በቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት የቅዱሱ ካህን የአሮን በትር ሳይተክሏትና ውሃ ሳያጠጧት ለምልማ፣ አብባ፣ አፍርታ የተገኘችው በዚህ ቀን ነው። ዳታን፣ አቤሮንና ቆሬ ከተከታዮቻቸው ጋር በፈጠሩት ሁከት ምድር ተከፍታ ከዋጠቻቸው በሁዋላ #እግዚአብሔር የ12ቱን ነገደ እሥራኤል በትር ሰብስቦ ሲጸልይበት እንዲያድር ሙሴን አዞት እንዲሁ ሆነ።

በነጋም ጊዜ ይህቺ ደረቅ የነበረች በትረ አሮን 12 ፍሬ (ለውዝ፣ ገውዝ፣ በኩረ ሎሚ) አፍርታ ተገኘች። (ዘኁ. 17፥1-11) ለጊዜው ክህነት ከቤተ አሮን እንዳይወጣ ምልክት ሆናለች። ለፍጻሜው ግን ምሳሌነቷ ለ #ድንግል_"ማርያም ነው። እመ ብርሃን የወንድ ዘር ምክንያት ሳይሆናት አምላክን ወልዳ ተገኝታለችና።

"ጸናጽል ዘውስተ ልብሱ ለአሮን ካህን ወዓዲ በትር እንተ ሠረጸት ወጸገየት ወፈረየት" እንዳለ #አባ_ሕርያቆስ። (#ቅዳሴ_ማርያም)

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም ቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_መስከረም_8)
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#መስከረም_8_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ዕብራውያን 11
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²³ ሙሴ ከተወለደ በኋላ ወላጆቹ ያማረ ሕፃን መሆኑን አይተው በእምነት ሦስት ወር ሸሸጉት የንጉሥንም አዋጅ አልፈሩም።
²⁴ ሙሴ ካደገ በኋላ የፈርዖን የልጅ ልጅ እንዳይባል በእምነት እምቢ አለ፤
²⁵-²⁶ ከግብፅም ብዙ ገንዘብ ይልቅ ስለ ክርስቶስ መነቀፍ እጅግ የሚበልጥ ባለ ጠግነት እንዲሆን አስቦአልና ለጊዜው በኃጢአት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራ መቀበልን መረጠ፤ ብድራቱን ትኵር ብሎ ተመልክቶአልና።
²⁷ የንጉሡን ቍጣ ሳይፈራ የግብፅን አገር የተወ በእምነት ነበር፤ የማይታየውን እንደሚያየው አድርጎ ጸንቶአልና።
²⁸ አጥፊው የበኵሮችን ልጆች እንዳይነካ ፋሲካንና ደምን መርጨትን በእምነት አደረገ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ይሁዳ 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁹ የመላእክት አለቃ ሚካኤል ግን ከዲያብሎስ ጋር በተከራከረ ጊዜ ስለ ሙሴ ሥጋ ሲነጋገር፦ ጌታ ይገሥጽህ አለው እንጂ የስድብን ፍርድ ሊናገረው አልደፈረም።
¹⁰ እነዚህ ግን የማያውቁትን ሁሉ ይሳደባሉ፥ አእምሮም እንደሌላቸው እንስሶች በፍጥረታቸው በሚያውቁት ሁሉ በእርሱ ይጠፋሉ።
¹¹ ወዮላቸው፥ በቃየል መንገድ ሄደዋልና ስለ ደመወዝም ለበለዓም ስሕተት ራሳቸውን አሳልፈው ሰጥተዋል በቆሬም መቃወም ጠፍተዋል።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 7
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
³⁰ አርባ ዓመትም ሲሞላ የጌታ መልአክ በሲና ተራራ ምድረ በዳ በቍጥቋጦ መካከል በእሳት ነበልባል ታየው።
³¹-³² ሙሴም አይቶ ባየው ተደነቀ፤ ሊመለከትም ሲቀርብ የጌታ ቃል፦ እኔ የአባቶችህ አምላክ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ ነኝ ብሎ ወደ እርሱ መጣ። ሙሴም ተንቀጥቅጦ ሊመለከት አልደፈረም።
³³ ጌታም፦ የቆምህባት ስፍራ የተቀደሰች ምድር ናትና የእግርህን ጫማ አውልቅ።
³⁴ በግብፅ ያሉትን የሕዝቤን መከራ ፈጽሜ አይቼ መቃተታቸውንም ሰምቼ ላድናቸው ወረድሁ፤ አሁንም ና፥ ወደ ግብፅ እልክሃለሁ አለው።
³⁵ ሹምና ፈራጅ እንድትሆን የሾመህ ማን ነው? ብለው የካዱትን፥ ይህን ሙሴን በቍጥቋጦው በታየው በመልአኩ እጅ እግዚአብሔር ሹምና ቤዛ አድርጎ ላከው።
³⁶ ይህ ሰው በግብፅ ምድርና በኤርትራ ባሕር በምድረ በዳም አርባ ዓመት ድንቅና ምልክት እያደረገ አወጣቸው።
³⁷ ይህ ሰው ለእስራኤል ልጆች፦ እግዚአብሔር ከወንድሞቻችሁ እንደ እኔ ያለ ነቢይ ያስነሣላችኋል፤ እርሱን ስሙት ያላቸው ሙሴ ነው።
³⁸ ይህ ሰው በሲና ተራራ ከተናገረው መልአክና ከአባቶቻችን ጋር በምድረ በዳ በማኅበሩ ውስጥ የነበረው ነው፤ ይሰጠንም ዘንድ ሕይወት ያላቸውን ቃላት ተቀበለ፤
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#መስከረም_8_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"ካህናቲከ ይለብሱ ጽድቀ። ወጻድቃኒከ ትፍሥሕተ ይትፌሥሑ። በእንተ ዳዊት ገብርከ"። መዝ 131፥9-10
"ካህናቶችህ ጽድቅን ይልበሱ፥ ቅዱሳንህም ደስ ይበላቸው። ስለ ዳዊት ስለ ባሪያህ የቀባኸውን ሰው ፊት አትመልስ"። መዝ 131፥9-10
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#መስከረም_8_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ማቴዎስ 23
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²⁹ እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ የነቢያትን መቃብር ስለምትሠሩ የጻድቃንንም መቃብር ስለምታስጌጡና፦
³⁰ በአባቶቻችን ዘመን ኖረን በሆነስ በነቢያት ደም ባልተባበርናቸውም ነበር ስለምትሉ፥ ወዮላችሁ።
³¹ እንግዲያስ የነቢያት ገዳዮች ልጆች እንደሆናችሁ በራሳችሁ ላይ ትመሰክራላችሁ።
³² እናንተ ደግሞ የአባቶቻችሁን መስፈሪያ ሙሉ።
³³ እናንተ እባቦች፥ የእፉኝት ልጆች፥ ከገሃነም ፍርድ እንዴት ታመልጣላችሁ?
³⁴ ስለዚህ፥ እነሆ፥ ነቢያትንና ጥበበኞችን ጻፎችንም ወደ እናንተ እልካለሁ፤ ከእነርሱም ትገድላላችሁ ትሰቅሉማላችሁ፥ ከእነርሱም በምኵራባችሁ ትገርፋላችሁ ከከተማም ወደ ከተማ ታሳድዳላችሁ፤
³⁵ ከጻድቁ ከአቤል ደም ጀምሮ በቤተ መቅደስና በመሠዊያው መካከል እስከ ገደላችሁት እስከ በራክዩ ልጅ እስከ ዘካርያስ ደም ድረስ በምድር ላይ የፈሰሰው የጻድቅ ደም ሁሉ ይደርስባችሁ ዘንድ።
³⁶ እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ በዚህ ትውልድ ላይ ይደርሳል።
³⁷ ኢየሩሳሌም ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ነቢያትን የምትገድል ወደ እርስዋ የተላኩትንም የምትወግር፥ ዶሮ ጫጩቶችዋን ከክንፎችዋ በታች እንደምትሰበስብ ልጆችሽን እሰበስብ ዘንድ ስንት ጊዜ ወደድሁ! አልወደዳችሁምም።
³⁸ እነሆ፥ ቤታችሁ የተፈታ ሆኖ ይቀርላችኋል።
³⁹ እላችኋለሁና፥ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው እስክትሉ ድረስ ከእንግዲህ ወዲህ አታዩኝም።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱስ ኤጲፋንዮስ ቅዳሴ ነው። መልካም የነቢዩ ቅዱስ ሙሴ የዕረፍት በዓል፣ የካህኑ ቅዱስ ዘካርያስ የዕረፍት በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#መስከረም_9

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
መስከረም ዘጠኝ በዚህች የመላእክት አለቃ #ቅዱስ_ሚካኤል በሮም አገር ፍሩምያ በምትባል ከተማ ላደረገው ተአምር መታሰቢያ ነው፣ #ቅዱስ_አባት_አባ_ቢሶራ በሰማዕትነት አረፈ፣ #ቅዱስ_ያሳይ_ንጉሥ እረፍቱ ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ሊቀ_መላእክት_ቅዱስ_ሚካኤል

መስከረም ዘጠኝ በዚህች ቀን በሮም አገር ፍሩምያ በምትባል ከተማ ለሆነው ተአምር መታሰቢያ ሆነ። ይህም እንዲህ ነው የሰማይ ሠራዊት አለቃ በሆነ በከበረ መልአክ በሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሚታዩ ድንቆችና ተአምራቶች ምክንያት ዮናናውያን ሰዎች ሰይጣናዊ ቅናትን እንደ ቀኑ ከመቅናታቸውም ብዛት የተነሣ በዚያ አካባቢ የሚወርደውን የወንዝ ውኃ በዚያች ቤተ ክርስቲያን ላይ ሊመልሱትና ከሚጠብቃት መጋቢዋ ጋር በውኃ ስጥመት ሊአጠፉአት ፈልገው መለሱት።

የሰማያውያን ሠራዊት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልም ለቤተ ክርስቲያኑ መጋቢ ለናርጢኖስ ተገለጠለት ወደርሱም ቀርቦ ጽና አትፍራ አለው ይህንን ብሎ በእጁ ውስጥ ባለ በትር አለቱን መታው አለቱም ተሰንጥቆ እንደ በር ሆነ የዚያ ወንዝ ውኃም በውስጡ አልፎ ሔደ።

ይህንንም ያዩ ምስጉን #እግዚአብሔርን አመሰገኑት የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልንም አከበሩት። ከዚያች ቀን እስከ ዛሬ የወንዙን ውኃ በዚያች በተሠነጠቀች አለት ውስጥ አልፎ ሲሔድ ያዩታል ወደ መላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ከቶ አይቀርብም።

#ለእግዚአብሔርም ምሽጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ ሚካኤል አማላጅነት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አባት_አባ_ቢሶራ

በዚህችም ቀን መጺል የምትባል አገር ኤጲስቆጶስ ቅዱስ አባት አባ ቢሶራ በሰማዕትነት አረፈ።

ይህም ቅዱስ በግብጽ አገር #እግዚአብሔርን በምትወድ መጺል በምትባል ከተማ ኤጲስቆጶስ ሆነ። ዲዮቅልጥያኖስም ነግሦ ክርስቲያኖችን በሚያሠቃያቸው ጊዜ ክብር ይግባውና በ #ክርስቶስ ስም ደሙን ያፈስ ዘንድ ይህ አባት ወደደ።

ሕዝቡንም ሀሉ ሰብስቦ በቤተ መቅደሱ ፊት በዐውደ ምሕረቱ አቆማቸው ሊጠብቁት የሚገባውን ለጽድቅ የሚያበቃቸውን ትእዛዝ ሁሉ አዘዛቸው። ከዚህም በኋላ ክብር ይግባውና በ #ክርስቶስ ስም ደሙን ማፍሰስ እንደሚሻ ነገራቸው ይህንንም በሰሙ ጊዜ ታላቆችም ታናሾችም በላዩ አለቀሱ።

የሙት ልጆች እንሆን ዘንድ የምትተወን ምን ያደርግልሃል እኛስ እንድትሔድ አንለቅህም አሉት ሊይዙትም ቃጡ ግን አልተቻላቸውም ተውትም እርሱም ወደ ክብር ባለቤት #ክርስቶስ አደራ አስጠበቃቸውና ሰላምታ ሰጥቷቸው ከእነርሱ ዘንድ ወጥቶ ተጓዘ። እነርሱም መሪር ልቅሶን እያለቀሱ ሸኙት።

ስማቸው ቢስኮስ ፊናቢክስ ቴዎድሮስ የሚባሉ ኤጲስቆጶሳት አብረውት ሔድ መኰንኑ ወደ አለበት አገርም ደርሰው የክብር ባለቤት በሆነ በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ታመኑ። እርሱም መኰንኑ አሠቃያቸው ኤጲስቆጶሳትም እንደሆኑ አውቆ ሥቃያቸውን አበዛ እሊህ አባቶች ግን በታላቅ ትዕግሥት የጸኑ ናቸው። ክብር ይግባውና ጌታችን ክርስቶስ ያጸናቸዋልና።

ከዚህም በኋላ መኰንኑ ራሶቻቸውን በሰይፍ ይቆርጧቸው ዘንድ አዘዘ የሕይወት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበሉ። የቅዱስ ቢሶራ ሥጋው ግን ንሲል በሚባል አገር እስከ ዛሬ ይኖራል።

#ለእግዚአብሔርም ምሽጋና ይሁን እኛንም በቅዱሱ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ያሳይ_ንጉሥ

በዚችም ቀን ተጋድሎውን በዛፍ ላይ ሆኖ የፈጸመ እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘ ንጉሥ ያሳይ አረፈ።

በቀደመው ዘመን መንግስታቸውን ትተው ከመነኑ ነገሥታት አንዱ ቅዱስ ያሳይ ነው። ምናኔ በቁሙ ከባድ ነው። መንግስትን፣ ዙፋንን፣ ክብርን ትቶ መመነንን ደግሞ ከማድነቅ በቀር እንዲህ ብለው ሊገልጹት ይከብዳል።

ቅዱስ ያሳይም መንግስቱን ትቶ ልምላሜ ወደሌለበት ደረቅ በርሃ ሔደ። በዚያም ከአንዲት ዛፍ በቀር ምንም ነገር አላገኘም። በዚያች ደረቅ ዛፍ ላይ ወጥቶ ለዓመታት በጾምና በጸሎት ተጋደለ።

በዘመነ ተጋድሎው ከዛፏ አልወረደም ሰውም አይቶ አያውቅም። በመጨረሻም ስለ ቅድስናው ዛፏ ለምልማለች። እርሱም በዚህች ቀን ዐርፏል።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም
በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_መስከረም_9_ዲያቆን_ዮርዳኖስ_አበበ)
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#መስከረም_9_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሮሜ 8
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
³⁵ ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ፥ ወይስ ጭንቀት፥ ወይስ ስደት፥ ወይስ ራብ፥ ወይስ ራቁትነት፥ ወይስ ፍርሃት፥ ወይስ ሰይፍ ነውን?
³⁶ ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን፥ እንደሚታረዱ በጎች ተቆጠርን ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው።
³⁷ በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን።
³⁸ ሞት ቢሆን፥ ሕይወትም ቢሆን፥ መላእክትም ቢሆኑ፥ ግዛትም ቢሆን፥ ያለውም ቢሆን፥ የሚመጣውም ቢሆን፥ ኃይላትም ቢሆኑ፥
³⁹ ከፍታም ቢሆን፥ ዝቅታም ቢሆን፥ ልዩ ፍጥረትም ቢሆን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል ተረድቼአለሁ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ያዕቆብ 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²-³ ወንድሞቼ ሆይ፥ የእምነታችሁ መፈተን ትዕግሥትን እንዲያደርግላችሁ አውቃችሁ፥ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቍጠሩት
⁴ ትዕግሥትም ምንም የሚጎድላችሁ ሳይኖር ፍጹማንና ምሉዓን ትሆኑ ዘንድ ሥራውን ይፈጽም።
⁵ ከእናንተ ግን ማንም ጥበብ ቢጎድለው፥ ሳይነቅፍ በልግስና ለሁሉ የሚሰጠውን እግዚአብሔርን ይለምን፥ ለእርሱም ይሰጠዋል።
⁶ ነገር ግን በምንም ሳይጠራጠር በእምነት ይለምን፤ የሚጠራጠር ሰው በነፋስ የተገፋና የተነቃነቀ የባሕርን ማዕበል ይመስላልና።
⁷-⁸ ሁለት አሳብ ላለው በመንገዱም ሁሉ ለሚወላውል ለዚያ ሰው ከጌታ ዘንድ አንዳች እንዲያገኝ አይምሰለው።
⁹-¹⁰ የተዋረደው ወንድም ግን በከፍታው፥ ባለ ጠጋም በውርደቱ ይመካ፤ እንደ ሣር አበባ ያልፋልና።
¹¹ ፀሐይ ከትኵሳት ጋር ይወጣልና፥ ሣርንም ያጠወልጋልና፥ አበባውም ይረግፋልና፥ የመልኩም ውበት ይጠፋልና፤ እንዲሁ ደግሞ ባለ ጠጋው በመንገዱ ይዝላል።
¹² በፈተና የሚጸና ሰው የተባረከ ነው፤ ከተፈተነ በኋላ ለሚወዱት ተስፋ ስለ እርሱ የሰጣቸውን የሕይወትን አክሊል ይቀበላልና።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 20
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁶ ጳውሎስ በእስያ እጅግ እንዳይቀመጥ ኤፌሶንን ይተው ዘንድ ቆርጦ ነበርና ቢቻለውም በዓለ ኀምሳን በኢየሩሳሌም ይውል ዘንድ ይቸኩል ነበርና።
¹⁷ ከሚሊጢንም ወደ ኤፌሶን ልኮ የቤተክርስቲያንን ሽማግሌዎች አስጠራቸው፤
¹⁸-¹⁹ ወደ እርሱም በመጡ ጊዜ እንዲህ አላቸው፦ ወደ እስያ ከገባሁበት ከመጀመሪያ ቀን ጀምሮ፥ በትሕትና ሁሉና በእንባ ከአይሁድም ሴራ በደረሰብኝ ፈተና ለጌታ እየተገዛሁ ዘመኑን ሁሉ ከእናንተ ጋር እንዴት እንደ ኖርሁ እናንተው ታውቃላችሁ፤
²⁰-²¹ ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ንስሐንና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ማመንን ለአይሁድና ለግሪክ ሰዎች እየመሰከርሁ በጉባኤም በየቤታችሁም አወራሁላችሁና አስተማርኋችሁ እንጂ፥ ከሚጠቅማችሁ ነገር አንዳች ስንኳ አላስቀረሁባችሁም።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#መስከረም_9_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"ደምፁ ወተሐምገ ማያቲሆሙ። ወአድለቅለቁ አድባር እምኃይሉ። ፈለገ ዘይውኅዝ ያስተፌሥሕ ሀገረ እግዚአብሔር"። መዝ 45፥3-4።
"ውኆቻቸው ጮኹ ተናወጡም፥ ተራሮችም ከኃይሉ የተነሣ ተናወጡ። የወንዝ ፈሳሾች የእግዚአብሔርን ከተማ ደስ ያሰኛሉ፤ ልዑል ማደሪያውን ቀደሰ"። መዝ 45፥3-4።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#መስከረም_9_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ማቴዎስ 7
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²⁴ ስለዚህ ይህን ቃሌን ሰምቶ የሚያደርገው ሁሉ ቤቱን በዓለት ላይ የሠራ ልባም ሰውን ይመስላል።
²⁵ ዝናብም ወረደ ጎርፍም መጣ ነፋስም ነፈሰ ያንም ቤት ገፋው፥ በዓለት ላይም ስለ ተመሠረተ አልወደቀም።
²⁶ ይህንም ቃሌን ሰምቶ የማያደርገው ሰው ሁሉ ቤቱን በአሸዋ ላይ የሠራ ሰነፍ ሰውን ይመስላል።
²⁷ ዝናብም ወረደ ጎርፍም መጣ ነፋስም ነፈሰ ያንም ቤት መታው፥ ወደቀም፥ አወዳደቁም ታላቅ ሆነ።
²⁸ ኢየሱስም ይህን ነገር በጨረሰ ጊዜ ሕዝቡ በትምህርቱ ተገረሙ፤ እንደ ጻፎቻቸው ሳይሆን
²⁹ እንደ ባለ ሥልጣን ያስተምራቸው ነበርና።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #ቅዱስ_ያዕቆብ_ዘሥሩግ ቅዳሴ ነው። መልካም የቅዱስ ሚካኤል የተአምራት በዓል፣ የንጉሥ ቅዱስ ያሳይ የዕረፍት በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#መስከረም_10

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
መስከረም ዐሥር በዚች ቀን #ጼዴንያ በምትባል አገር ሥጋ የለበሰች ከምትመስል ሥዕል ከሠሌዳዋ ቅባት እየተንጠፈጠፈ አምላክን የወለደች የእመቤታችን የድንግል ማርያም ተአምር ተገለጠ፣ የሜራሪ ልጅ #ቅድስት_ዮዲት እረፍቷ ነው፣ የከበረች #ቅድስት_መጥሮንያ በሰማዕትነት አረፈች፣ #ንግስት_ሳባ እረፍቷ፣ #ተቀጸል_ጽጌ #አጼ_መስቀል ይከበራል።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ጼዴንያ

መስከረም ዐሥር በዚህች ቀን ጼዴንያ በምትባል አገር ሥጋ የለበሰች ከምትመስል ሥዕል ከሠሌዳዋ ቅባት እየተንጠፈጠፈ አምላክን የወለደች የእመቤታችን የ ድንግል_ማርያም ተአምር ተገለጠ።

ይቺንም ሥዕል የሣላት ወንጌላዊ ሉቃስ ነው ይባላል። ወደ ጼዴንያ አገርም የመጣችበት ምክንያት አንዲት ስሟ ማርታ የሚባል መበለት ሴት ነበረችና ቤቷንም ለእንግዳ ማደሪያ ያደረገች ናት። አምላክን የወለደች እምቤታችን #ድንግል_ማርያምንም እጅግ ትወዳት ነበር። በሚቻላትም ሁሉ ታገለግላታለች።

በአንዲት ቀንም ስሙ ቴዎድሮስ የሚባል መነኩሴ ከእርሷ ዘንድ እንግድነት አደረ በመልካም አቀባበልም ተቀበለችው በማግሥቱም ስተሸኘው አባት ሆይ የምትሔደው ወዴት ነው አለችው። እርሱም በከበሩ ቦታዎች ውስጥ ልሰግድ ወደ ኢየሩሳሌም እሔዳለሁ አላት እርሷም ከእኔ ገንዘብ ወስደህ የእመቤታችን #ማርያምን ሥዕል ግዛልኝና በመመለሻህ ጊዜ አምጣልኝ አለችው። እርሱም በራሴ ገንዘብ ገዝቼ አመጣልሻለሁ አላት።

ከዚህም በኋላ ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ ከቅዱሳት መካናት ተባረከና ሥዕሏን ሳይገዛ ወደ ጎዳናው ተመለሰ። ያን ጊዜም ሥዕል መግዛትን ለምን ረሳህ የሚል የሚያስደነግጥ ቃልን ሰማ ወደ ገቢያም ተመልሶ ላሕይዋና መልኳ ያማረና የተወደደ የሆነ የእመቤታችን #ማርያምን ሥዕል አግኝቶ ገዛት በሐርና በንጹሕ ልብስም ጠቀለላት።

በጎዳናውም እየተጓዘ ሳለ ከሚያስፈራ ዱር ውስጥ ወንበዴዎች ተነሡበት ሊሸሽም ወደደ ከዚያቺም ሥዕል መንገድህን ሒድ የሚል ቃል ወጣ የተከተለውም ሳይኖር መንገዱን ተጓዘ። ሁለተኛም ነጥቆ ሊበላው አንበሳ ተነሣበት ያን ጊዜም ከዚያች ሥዕል የሚያሥፈራ ድምፅ ወጥቶ አንበሳውን አባረረው።

አባ ቴዎድሮስም ይህን ሁሉ ድንቅ ተአምር ባየ ጊዜ ያቺን ሥዕል ወደ አገሩ ሊወስዳት ወደደ ግዛልኝ ላለችው መበለት ይሰጣት ዘንድ አልፈለገም።

ከዚህም በኃላ በመርከብ ተሳፍሮ በሌላ አቅጣጫ ሲጓዝ ታላቅ ነፋስ ተነሣበት ወደ ማርታ አገር ወደ ጼዴንያም ወሰደው ከመርከቡም ወርዶ ከብዙ እንግዶች ጋር ወደዚያች መበለት ቤት ሔደ ማንነቱንም አልገለጠላትም እርሷም አላወቀችውም።

በማግሥቱም ተሠውሮ ወጥቶ ወደ አገሩ ሊሔድ በፈለገ ጊዜ የቅጽሩን ደጃፍ አጥቶ ሲያጥመሰምስ ዋለ በመሸ ጊዜም ወደ ማደሪያው ተመለሰ። ያቺም መበለት በአየችው ጊዜ ታደንቃለች እንዲህም ሁኖ እስከ ሦስት ቀን ኖረ በመሸ ጊዜ በሩን ያየዋል ነግቶ መሔድን ሲሻ የበሩ መንገድ ይሠወረዋል። ያቺም መበለት ያዝ አድርጋ አባቴ ሆይ አእምሮህ ተነክቷልን ስትቅበዘበዝ አይሀለሁና ምን ሆነህ ነው አለችው።

ከዚህም በኋላ ከዚያች ሥዕል የሆነውን ሁሉ ነገራት ራሱንም ገለጠላት። ያቺንም ሥዕል ሰጣት ተቀብላም የተጠቀለለችበትን ልብስ ፈታች ወዝ ከሥዕሊቱ ሲንጠፈጠፍ አገኘች። ከደስታዋም ብዛት የተነሣ የዚያን መነኩሴ እጆቹንና እግሮቹን ሳመች።

ከዚህም በኋላ ያቺን ሥዕል ወደ ጸሎት ቤቷ ወስዳ በታላቅ ክብር የምትቀመጥበትን አዘጋጅታ አኖረቻት ማንም እንዳይዳስሳትም የነሐስ መስኮትን ሠራችላት በቀንና በሌሊትም የሚበሩ መቅረዞችን በፊቷ ሰቀለች ከመቅረዞችም ውጭ የሐር መጋረጃን ጋረደች። ከሥዕሊቱ በታችም ከሥዕሊቱ እየተንጠፈጠፈ የሚወርደው የወዝ ቅባት የሚጠራቀምበት ከዕብነ በረድ የተሠራ ወጭት አኖረች ያም መነኩስ እስከሚሞትበት ቀን ድረስ የእመቤታችንን #ድንግል_ማርያምን ሥዕል እያገለገለ ኖረ።

የሀገሩም ሊቀ ጳጳሳት የዚያችን ሥዕል ዜና በሰማ ጊዜ ከኤጲስቆጶሳትና ከካህናት ከሕዝቡም ሁሉ ጋር መጣ በሠሌዳውም ውስጥ በአዩዋት ጊዜ ሥጋ የለበሰች ሁና አገኙዋት ከዚህ ከአምላካዊ ግብር የተነሣ አደነቁ ከዚህም ቅባት ቀድተው ለበረከት በተካፈሉ ጊዜ ወዲያውኑ በወጭቱ ውስጥ ይመላል።

ወደ ሌላ ቦታም ሊወስዷት በፈለጉ ጊዜ ንውጽውጽታ ሆኖ ብዙዎች በድንጋጤ ወደቁ ሥዕሊቱም እስከ ዛሬ በዚያች አገር ትኖራለች።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በእናቱ በእመቤታችን በ #ድንግል_ማርያም ጸሎት ይማረን በረከቷም ከእኛ ጋር ይኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_ዮዲት

ዳግመኛም በዚህች ቀን ባሏ ምናሴ ሞቶባት፣ ከወንድ ርቃ ንጽሕናዋን ጠብቃ በጾም፣ በቀኖና፣ በትኅርምት፣ በኀዘን፣ በጸሎት ተወስና የምትኖር የሜራሪ ልጅ ቅድስት ዮዲት አረፈች።

ቅድስት ዮዲት ከከሀዲው ሆሎፎርኒስ እጅ በጥበቧ እስራኤልን ያዳነቻቸው ጥበበኛ የከበረች፣ በ #እግዚአብሔር ኃይል ራሱን እስከ ቆረጠች ድረስ በልቧ ተራቀቀች ወገኖቿንም ያዳነች ናት።

ነገሩም እንዲህ ነው፦ ለፋርስ ንጉሥ ለናቡከደነፆር የጦር አበጋዝ የነበረው ሆሎፎርኒስ ፈቃድ ተሰጥቶት እስራኤልን ለመውረር ሲመጣ በሠራዊቱ (ዮዲ2፣2-7) የእሥራኤል ልጆችም ሆሎፎርኒስ የአሕዛብን አገር እንዳጠፋና ንብረታቸውን እንደዘረፈ ሰምተው ስለ ቤተ መቅደሱ መፍረስና ሰለ ንዋያተ ቅድሳት መርከሰ ማቅ ለብሰው አመድ ነስንሰው ከቤተ መቅደሱ በር ወድቀው አለቀሱ።(ዮዲ4፡2-15) ሆሎፎርኒስ ግን የሚጠጡትን ምንጫቸውን በመያዙ ፣ የእሥራኤል ልጆች በውኃ ጥም ከመቸገርና ከመሞት ይልቅ እጃቸውን ለጠላት ለመስጠት ወሰኑ፡፡ ነገር ግን ዖዝያን የአባቶቻቸው አምላክ መልስ እስኪሰጣቸውና ቸርነቱን እስኪመልስላቸው መከራውን በትዕግሥት እንዲቀበሉ ስለመከራቸው ጸኑ፡፡ ዮዲ 7፥10-32)

በዚህ ጊዜ ዮዲት ማቅ ለብሳ በራስዋ ላይ ትቢያ ነስንሳ፣ ሱባዔ ገባች! አምላክም ሕዝቡን የሚያድንበትን ዕውቀትና ጥበብ ግብር በገባች በሦስተኛ ቀን ገለጸላት፡፡(ዮዲ8፡2) ከዚያም “ወዴት ትሔጃለሽ አትበሉኝ አምላክ እሥራኤል ይከተልሽ ብሉኝ” ብላ የኀዘን ልብሷን ጣለች፡፡ ሰውነቷን ታጠበችና ሽቱ ተቀባች ባሏ በሕይወት ሳለ የምትለብሰውን የክት ልብሷን ለበሰች፣ የጠላት ሰዎች ሁሉ እስኪወዷት ድረስ ፈጽማ አጊጣ ሄደች፡፡ (ዮዲ.10፥2-3) እነርሱም ለእኔ ትገባለች ለእኔ ትገባለች እያሉ ተሻሙባት፡፡ የንጉሥ ጃንደረባ ጋይ የሚባል ይህችስ ለጌታዬ ትገባለች አለ፣ ለምን እንደመጣች ጠይቀዋት ለመልካም ነገር እንደመጣች ሲረዱ ከጦር አበጋዙ አደረሷት፡፡ (ዮዲ10፥12-22)

በአንዲትም ዕለት ሆሎፎርኒስ የአሽከሮች የምሣ ግብዣ አድርጎ ሲያበላ ሲያጠጣ ያችን ዕብራዊት ጥሩ ብሎ አስጠርቶ ከፊቱ አስቀምጦ ሲበላ አብዝቶ ሲጠጣ ውሎ ሰከረ፡፡(ዮዲ12፥1-20) ከዚያም አሽከሮችን ከሁሉ አስወጥቶ ድንኳኑን ቆልፎ እንደተኛ ከባድ እንቅልፍ ያዘው ዮዲትም ከፀለየች በኋላ ከራስጌው ያለውን ሰይፍ አንስታ የራስ ጠጉሩን ይዛ አንገቱን ቆርጣ በድኑን ከመሬት ጥላ ቸብቸቦውን በአቁማዳ ቋጥራ ለብላቴናዋ አሸክማ ግንዱን በታች ገልብጣ ዙፋኑን በላይ አድርጋ ወደ ሃገሯ ተመለሰች፡፡ (ዮዲ13፥1-10) ሕዝበ እሥራኤል በዚህ ድርጊቷ እጅግ ተደነቁ፣ ጠላታቸውን በእጃቸው የጣለላቸውን #እግዚአብሔር አምላካቸውንም አመሰገኑ፡፡ በኋላም የሆሎፎርኒስን ራስ በተራራው ላይ ሰቅለው መዋጋት ጀመሩ፡፡ እስከ ዮርዳኖስም እየተከተሉ አጥፍተዋቸዋል፡፡
ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም የዚህችን ቅድስት እናት በዓለ እረፍቷን በዚህች ዕለት አክብራ ትውላለች ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅድስቷ ጸሎት ይማረን በረከቷም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_መጥሮንያ

በዚችም ቀን የከበረች መጥሮንያ በሰማዕትነት አረፈች። ይቺም የከበረች መጥሮንያ ለአንዲት አይሁዳዊት ሴት አገልጋይዋ ናት ። ይችም አይሁዳዊት እመቤቷ ከክርስትናዋ አፍልሳ ትክክል ወደ አልሆነ ሃይማኖቷ ልታስገባት ትሻ ነበር ስለዚህም ታጉሳቁላታለች በላይዋም የአገልግሎት ሥራን ታከብድባታለች ።

ከዚህም በኃላ በአንዲት ቀን አይሁዳዊት እመቤቷን ተከትላ ወደ አይሁድ ምኩራብ ሔደች ተመልሳም ወደ ከበረች ቤተ ክርስቲያን ገብታ ጸለየች። ወደ ቤት በገቡም ጊዜ ወዴት ሒደሽ ነበር ወደእኛ ምኩራብ ለምን አልገባሽም ብላ ጠየቀቻት ቅድስት መጥሮንያም ከእናንተ ምኩራብ #እግዚአብሔር ርቋል እኮን እንዴት ወደርሱ እገባለሁ። በውስጧ ልገባባት የሚገባኝ ቦታዬ ግን ክብር ይግባውና #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ በከበረ ደሙ የዋጃት ይህች ቤተ ክርስቲያን ናት ብላ መለሰችላት።

እመቤቷም ይህ ነገር በሰማች ጊዜ ተቆጣቻት እጅግም ደብደባ በጨለማ ቤት ውስጥ አሠረቻት ያለ መብልና መጠጥም አራት ቀን ኖረች። ከዚህም በኃላ ከእሥር ቤት አውጥታ በጅራፍ ታላቅ ግርፋትን ገርፋ ሁለተኛ ወደ እሥር ቤት መልሳ አሠረቻት በዚያም አረፈች።

እመቤቷም በድኗን አንሥታ ከቤቷ ደርብ ላይ አውጥታ በውጭ ወደታች ጣለቻት። ወድቃ የሚያዩዋት ሰዎች በገዛ ፈቃድዋ እንደወደቀች አድርገው እንዲናገሩ ብላ ነው ስለ መገደሏ ዳኞች እንዳይመራመርዋት ፈርታለች።

በዚያንም ጊዜ በዚያች አይሁዳዊት ሴት ላይ የ #እግዚአብሔር ቁጣ ወረደ ከደርቧ ላይ ስትወርድም በድንገት ወድቃ ሞተች ወደ ዘላለማዊም እሳት ሔደች ይህች የከበረች መጥሮንያ ግን የሰማዕታትን አክሊል ተቀብላ ወደ ዘላለም ሕይወት ሔደች።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅድስት መጥሮንያ ጸሎት ይማረን በረከቷም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ንግሥተ_ሳባ

ንግሥት ሳባ ደግ ኢትዮዽያዊት ከ3 ሺ ዘመናት በፊት የነበረች ደግ እናት ናት። በሥጋዊ ደረጃ ከታንዛንያ እስከ የመን ያስተዳደረች ስመ ጥር ንግሥት ስትሆን በመንፈሳዊው ደረጃ ደግሞ #እግዚአብሔር የቀባውን ሰው ፍለጋ ወደ ኢየሩሳሌም ተጉዛለች።

ከዚያውም አምልኮተ #እግዚአብሔርን ከሥርዓተ ኦሪት ጋር አምጥታለች። ድንግልናዋን ለታላቁ ንጉሥ ሰሎሞን ሰጥታ ምኒልክን ወልዳለች። ይህቺ ንግሥት በ #ጌታችን (በፈጣሪ) አንደበትም ተመስግናለች። (ማቴ. 12:42) በስምም "ሳባ: አዜብና ማክዳ ተብላ ትታወቃለች። ዛሬ ዕለተ ዕረፍቷ ነው።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎቷ ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ተቀጸል_ጽጌ /#አጼ_መስቀል/

'ተቀጸል ጽጌ' ማለት 'መስቀል ሆይ! በአበባ አጊጥ' እንደ ማለት ሲሆን 'አጼ መስቀል' ደግሞ አጼ ገብረ መስቀልን አንድም አፄ ዳዊት ቀዳማዊን ይመለከታል። ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ፦

በሃገራችን ኢትዮዽያ የነገረ መስቀሉ ትምሕርት ከመጣ ጀምሮ መስቀል ይከበራል። በአደበባባይ ግን እንዲከበር ያደረጉት የቅዱስ ካሌብ ልጅ አፄ ገብረ መስቀል ናቸው። በወቅቱ ንጉሡ፣ ሠራዊቱ፣ ዻዻሱና ሕዝቡ በተገኙበት ቅዱስ ያሬድ "መስቀል መልዕልተ ኩሉ ነገር ያድኅነነ እምጸር።" "መስቀል ከሁሉ ነገር በላይ ነው: ከጠላትም ያድነናል።" እያለ ይዘምር ነበር።

የአበባ ጉንጉንም ለመስቀሉና ለንጉሡ ይቀርብ ነበር። ከ800 ዓመታት በሁዋላም አፄ ዳዊት ግማደ መስቀሉን ባስመጡ ጊዜ መስከረም ቀን ተተክሎ ታላቅ በዓልም ሆኖ ተከብሯል።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ይኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_መስከረም_10 ና_ዲያቆን_ዮርዳኖስ_አበበ)
2024/09/21 03:19:54
Back to Top
HTML Embed Code: