Telegram Web Link
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ነሐሴ_27_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ዕብራውያን 5
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ ሊቀ ካህናት ሁሉ ስለ ኃጢአት መባንና መስዋዕትን ሊያቀርብ ከሰው ተመርጦ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ ስለ ሰው ይሾማልና፤
² እርሱ ራሱም ደግሞ ድካምን ስለሚለብስ፥ ላልተማሩትና ለሚስቱት ሊራራላቸው ይችላል፤
³ በዚህም ምክንያት ስለ ሕዝብ እንደሚያቀርብ እንዲሁ ስለ ራሱ ደግሞ መስዋዕትን ስለ ኃጢአት ሊያቀርብ ይገባዋል።
⁴ እንደ አሮንም በእግዚአብሔር ከተጠራ በቀር ማንም ክብሩን ለራሱ የሚወስድ የለም።
⁵ እንዲሁ ክርስቶስ ደግሞ ሊቀ ካህናት ሊሆን ራሱን አላከበረም ነገር ግን፦ አንተ ልጄ ነህ እኔ ዛሬ ወልጄሃለሁ ያለው እርሱ ነው፤
⁶ እንደዚህም በሌላ ስፍራ ደግሞ፦ አንተ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ካህን ነህ ይላል።
⁷ እርሱም በስጋው ወራት ከሞት ሊያድነው ወደሚችል ከብርቱ ጩኸትና ከእንባ ጋር ጸሎትንና ምልጃን አቀረበ፥ እግዚአብሔርንም ስለ መፍራቱ ተሰማለት፤
⁸ ምንም ልጅ ቢሆን፥ ከተቀበለው መከራ መታዘዝን ተማረ፤
⁹-¹⁰ ከተፈጸመም በኋላ በእግዚአብሔር እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ሊቀ ካህናት ተብሎ ስለ ተጠራ፥ ለሚታዘዙለት ሁሉ የዘላለም መዳን ምክንያት ሆነላቸው።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ጴጥሮስ 3
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁴ ነገር ግን ስለ ጽድቅ እንኳ መከራን ብትቀበሉ ብፁዓን ናችሁ። ማስፈራራታቸውንም አትፍሩ አትናወጡም፥
¹⁵ ዳሩ ግን ጌታን እርሱም ክርስቶስ በልባችሁ ቀድሱት። በእናንተ ስላለ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቁአችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ሁኑ፥ ነገር ግን በየዋህነትና በፍርሃት ይሁን።
¹⁶ በክርስቶስ ያለውን መልካሙን ኑሮአችሁን የሚሳደቡ ሰዎች ክፉን እንደምታደርጉ በሚያሙበት ነገር እንዲያፍሩ በጎ ሕሊና ይኑራችሁ።
¹⁷ የእግዚአብሔር ፈቃድ እንዲህ ቢሆን፥ ክፉ ስለ ማድረግ ሳይሆን በጎ ስለ ማድረግ መከራን ብትቀበሉ ይሻላችኋልና።
¹⁸ ክርስቶስ ደግሞ ወደ እግዚአብሔር እንዲያቀርበን እርሱ ጻድቅ ሆኖ ስለ ዓመፀኞች አንድ ጊዜ በኃጢአት ምክንያት ሞቶአልና፤ በሥጋ ሞተ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ፥
¹⁹ በእርሱም ደግሞ ሄዶ በወኅኒ ለነበሩ ነፍሳት ሰበከላቸው፤
²⁰ ጥቂቶች ማለት ስምንት ነፍስ በውኃ የዳኑበት መርከብ ሲዘጋጅ፥ የእግዚአብሔር ትዕግሥት በኖኅ ዘመን በቈየ ጊዜ ቀድሞ አልታዘዙም።
²¹ ይህም ውኃ ደግሞ ማለት ጥምቀት ምሳሌው ሆኖ አሁን ያድነናል፥ የሰውነትን እድፍ ማስወገድ አይደለም፥ ለእግዚአብሔር የበጎ ሕሊና ልመና ነው እንጂ፥ ይህም በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ነው፤
²² እርሱም መላእክትና ሥልጣናት ኃይላትም ከተገዙለት በኋላ ወደ ሰማይ ሄዶ በእግዚአብሔር ቀኝ አለ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 3
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁷ አሁንም፥ ወንድሞቼ ሆይ፥ እናንተ እንደ አለቆቻችሁ ደግሞ ባለማወቅ እንዳደረጋችሁት አውቄአለሁ፤
¹⁸ እግዚአብሔር ግን ክርስቶስ መከራ እንዲቀበል አስቀድሞ በነቢያት ሁሉ አፍ የተናገረውን እንዲሁ ፈጸመው።
¹⁹-²⁰ እንግዲህ ከጌታ ፊት የመጽናናት ዘመን እንድትመጣላችሁ አስቀድሞም ለእናንተ የመረጠውን ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲልክላችሁ፥ ኃጢአታችሁ ይደመሰስ ዘንድ ንስሐ ግቡ ተመለሱም።
²¹ እግዚአብሔር ከጥንት ጀምሮ በቅዱሳን ነቢያቱ አፍ የተናገረው፥ ነገር ሁሉ እስከሚታደስበት ዘመን ድረስ ሰማይ ይቀበለው ዘንድ ይገባልና።
²² ሙሴም ለአባቶች፦ ጌታ አምላክ እኔን እንዳስነሣኝ ነቢይን ከወንድሞቻችሁ ያስነሣላችኋል፤ በሚነግራችሁ ሁሉ እርሱን ስሙት።
²³ ያንም ነቢይ የማትሰማው ነፍስ ሁሉ ከሕዝብ ተለይታ ትጠፋለች አለ።
²⁴ ሁለተኛም ከሳሙኤል ጀምሮ ከእርሱም በኋላ የተናገሩት ነቢያት ሁሉ ደግሞ ስለዚህ ወራት ተናገሩ።
²⁵ እናንተ የነቢያት ልጆችና እግዚአብሔር ለአብርሃም፦ በዘርህ የምድር ወገኖች ሁሉ ይባረካሉ ብሎ፥ ከአባቶቻችን ጋር ያደረገው የኪዳን ልጆች ናችሁ።
²⁶ ለእናንተ አስቀድሞ እግዚአብሔር ብላቴናውን አስነሥቶ፥ እያንዳንዳችሁን ከክፋታችሁ እየመለሰ ይባርካችሁ ዘንድ፥ ሰደደው።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ነሐሴ_27_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"ወሳሙኤልኒ ምስለ እለ ይጼውዑ ስሙ። ይጼውዕዎ ለእግዚአብሔር ውእቱኒ ይሰጠዎሙ። ወይትናገሮሙ በዐምደ ደመና"። መዝ 98፥6-7።
"ሙሴና አሮን በካህናቱ ዘንድ፥ ሳሙኤልም ስሙን በሚጠሩት ዘንድ ናቸው፤ እግዚአብሔርን ጠሩት፥ እርሱም መለሰላቸው። በደመና ዓምድም ተናገራቸው፤ ምስክሩንና የሰጣቸውን ትእዛዝ ጠበቁ"። መዝ 98፥6-7።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ነሐሴ_27_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ዮሐንስ 12
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²⁶ የሚያገለግለኝ ቢኖር ይከተለኝ፥ እኔም ባለሁበት አገልጋዬ ደግሞ በዚያ ይሆናል፤ የሚያገለግለኝም ቢኖር አብ ያከብረዋል።
²⁷ አሁን ነፍሴ ታውካለች ምንስ እላለሁ? አባት ሆይ፥ ከዚህ ሰዓት አድነኝ። ነገር ግን ስለዚህ ወደዚህ ሰዓት መጣሁ።
²⁸ አባት ሆይ፥ ስምህን አክብረው። ስለዚህም፦ አከበርሁት ደግሞም አከብረዋለሁ የሚል ድምፅ ከሰማይ መጣ።
²⁹ በዚያ ቆመው የነበሩትም ሕዝብ በሰሙ ጊዜ፦ ነጐድጓድ ነው አሉ፤ ሌሎች፦ መልአክ ተናገረው አሉ።
³⁰ ኢየሱስም መለሰ፥ እንዲህ ሲል፦ ይህ ድምፅ ስለ እናንተ መጥቶአል እጂ ስለ እኔ አይደለም።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈ_ወርቅ ቅዳሴ ነው። መልካም የመልአኩ የቅዱስ ሱርያል በዓልና የአቡነ ዘርዐ ቡሩክ የልደት በዓል። ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ነሐሴ_28

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ነሐሴ ሃያ ስምንት በዚች ቀን የአባቶቻችን #የአብርሃም #የይስሐቅና #የያዕቆብን መታሰቢያቸው ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አበ_ብዙሃን_አብርሃም

ነሐሴ ሃያ ስምንት በዚች ቀን የአባቶቻችን የአብርሃም የይስሐቅና የያዕቆብን መታሰቢያቸውን እናደርግ ዘንድ የቤተ ክርስቲያን መምህራን አባቶቻችን አዘዙን ከእርሳቸው ለዘላለም የሚኖር ርስትን ተቀብለናልና።

የእሊህንም አባቶች ትሩፋታቸውንና ጽድቃቸውን ከሰው መናገር የሚችል ማነው?

ከሁሉ ነገር አስቀድሞ #እግዚአብሔር አብርሃምን ጠርቶ እንዲህ አለው ከአገርህ ወጥተህ ከዘመድህ ከአባትህ ወገን ተለይተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ሒድ። ታላቅ ሕዝብ አደርግሃለሁ ስምህንም ከፍ ከፍ አደርገዋለሁ የተባረክህም ትሆናለህ።

የሚአከብሩህንም አከብራቸዋለሁ የሚረግሙህንም እረግማቸዋለሁ የዚህ ዓለም አሕዛብም ሁሉ በአንተ ይከብራሉ። አብርሃምም #እግዙአብሔር እንዳዘዘው ሔደ የወንድሙን ልጅ ሎጥንና ሚስቱ ሣራንም ከርሱ ጋር ወሰደ።

አብርሃምም ከካራን በወጣ ጊዜ ዕድሜው ሰባ አምስት ዘመናት ሁኖት ነበር በካራንም ያጠራቀሙትን ገንዘባቸውን ሁሉ ይዘው ወደ ከንዓን ምድር ደረሱ። አብርሃምም ያቺን አገር ረጅም ዕንጨት እስከ አለበት እስከ ሴኬም ድረስ ዞራት የከነዓን ሰዎች ግን የዚያን ጊዜ በዚያች አገር ነበሩ።

#እግዚአብሔርም ለአብርሃም ተገልጦለት ይችን አገር ለልጆችህ እሰጣታለሁ አለው አብርሃምም በዚያ ለተገለጠለት ለ #እግዚአብሔር መሥዋዕትን አዘጋጀ። ከዚያም ወደ ምሥራቅ ወደ ቤቴል ሔደ በቤተልም በጋይ በኩል በስተምዕራብ ድንኳኑን ተከለና በዚያ ተቀመጠ በዚያም ለ #እግዚአብሔር መሠዊያ ሠራ የ #እግዚአብሔርንም ስም ጠራ።

አብርሃምም ከዚያ ተነሥቶ ሔደ በዚያም ሊኖር ወደ አዜብ ተጓዘ። ባገርም ራብ በጸና ጊዜ አብርሃም በዚያ ሊኖር ወደ ግብጽ ወረደ በአገሩ ራብ ጸንቷልና ። አብርሃምም ወደ ግብጽ ይገባ ዘንድ በቀረበ ጊዜ እንዲህ ሆነ አብርሃም ሚስቱን ሣራን እንዲህ አላት አንቺ መልከ መልካም ሴት እንደሆንሽ አውቃለሁ የግብጽም ሰዎች ካዩሽ ሚስቱ ናት ብለው ይገድሉኛል አንቺንም በሕይወት ያኖሩሻል።

እንግዲህ ስለ አንቺ ይራሩልኝ ዘንድ በአንቺ ዘመንም ነፍሴ ትድን ዘንድ እኔ እኅቱ ነኝ በዮአቸው። አብርሃም ወደ ግብጽ በደረሰ ጊዜ እንዲህ ሆነ የግብጽ ሰዎች ሚስቱን እጅግ መልከ መልካም እንደሆነች አዮዋት ለፈርዖን ወሰዷት ወደ ቤቱም አገቧት።

ስለርሷም ለአብርሃም በጎ ነገርን አደረጉለት ሴቶች አገልጋዮችንና ወንዶች አገልጋዮችን ላሞችንና በጎችን በቅሎዎችንና ግመሎችን አህዮችንም አገኘ። #እግዚአብሔርም በአብርሃም ሚስት በሣራ ምክንያት ፈርዖንንና ቤተሰቡንም ጽኑ ሥቃይን አሠቃያቸው።

ፈርዖንም አብርሃምን ጠርቶ በእኔ ያደረግከው ይህ ነገር ምንድን ነው ሚስትህ መሆኗን ያልነገርከኝ ለምንስ እኅቴ ናት አልከኝ ሚስት ልትሆነኝ ወስጃት ነበር አሁንም ሚስትህ ያቻት ይዘሃት ሒድ አለው። ፈርዖንም አብርሃምንና ሚስቱን ሣራን ከጓዛቸው ሁሉ ጋር እንዲሸኙአቸው ብላቴኖቹን አዘዘ።

ከዚህም በኃላ ለአብርሃም ዘጠና ዘጠኝ ዓመት በሆነው ጊዜ #እግዚአብሔር ለአብርሃም ተገለጠለት እንዲህም አለው በፊትህ የሔድኩ ፈጣሪህ #እግዚአብሔር እኔ ነኝ በፊቴ በጎ ነገርን አድርግ ንጹሕም ሁን።

በእኔና በአንተ መካከል ኪዳኔን አጸናለሁ ፈጽሜም አበዛሃለሁ ለብዙ አሕዛብም አባት ትሆናለህ። እንግዲህም ስምህ አብራም አይባልም አብርሃም እንጂ እጅግም አበዛሃለሁ አሕዛብ ነገሥታትም ከአንተ እንዲወለዱ አደርጋለሁ። አብርሃም በቀትር ጊዜ በድንኳን ደጃፍ ተቀምጦ ሳለ #እግዚአብሔር በወይራ ዛፍ አጠገብ ተገለጠለት።

ዐይኖቹንም አቅንቶ በተመለከተ ጊዜ እነሆ ሦስት ሰዎች በፊቱ ቁመው ነበር አይቶም ከድንኳኑ በር ሊቀበላቸው ሮጠ በምድር ላይም ሰገደ እንዲህም አለው አቤቱ በፊትህ ባልሟልነትን አግኝቼ ከሆነ ባሪያህን አትለፈኝ ውኃ አምጥተን እግራችሁን እንጠባችሁ ከጥላው ዕረፉ።

እንጀራም እናምጣላችሁና ብሎ ከዚህም በኃላ ወደ አሰባችሁት ትሔዳላችሁ እንዳልክ እንዲሁ አድርግ አሉት። አብርሃምም ወደ ሚስቱ ወደ ሣራ ሩጦ ወደ ድንኳን ገብቶ እንዲህ አላት ቶሎ በዬ ሦስቱን መሥፈሪያ ዱቄት አቡክተሽ አንድ ዳቦ ጋግሪ።

አብርሃምም ሁለተኛ ላሞች ወዳሉበት ሮጠ አንድ የሰባ ወይፈን ወሰደና ለብላቴናው ሰጠው እርሱም ፈጥኖ አዘጋጀው። ማርና እርጎ ያዘጋጀውንም ሥጋ አምጥቶ አቀረበላቸውና በሉ እርሱ ግን ቁሞ ያሳልፍላቸው ነበር።

እርሱም ሚስትህ ሣራ ወዴት ናት አለው። እነሆ በድንኳን ውስጥ አለች አለው በተመለስኩ ጊዜ የዛሬ ዓመት እንደዛሬው ወዳንተ እመጣለሁ ሣራም ወንድ ልጅን ታገኛለች አለው ሣራም በድንኳኑ ደጃፍ በስተኃላው ቁማ ሳለች ይህን ሰማች። አብርሃምና ሣራ ግን ፈጽመው አርጅተው ዘመናቸው አልፎ ነበር ሣራንም የሴቶች ልማድ ትቷት ነበር።

ሣራም ለብቻዋ ሳቀች በልቧ እንዲህ ብላለችና እስከ ዛሬ ገና ነኝን ጌታዬም አርጅቷል። #እግዚአብሔርም አብርሃምን እንዲህ አለው ሣራን ለብቻዋ ምን አሳቃት እስከ ዛሬ ገና ነኝን በውነትስ እወልዳለሁን ጌታዬም አርጅቷል እኔም እነሆ አርጅቻለሁ ብላ በውኑ ለ #እግዚአብሔር የሚሳነው ነገር አለን በቀጠርኩህ ዓመት ወደ አንተ በተመለስኩ ጊዜ ሣራ በሰባተኛ ወርዋ ልጅን ታገኛለች።

የዚህም አባት ተጋድሎው ትሩፋቱ ርኅራኄው ጽድቁም ብዙ ነው ሁል ጊዜ እንግዳ ካላገኘ በቀር በማዕዱ አብሮት ካልተቀመጠ አይበላም ነበር ስለዚህም ልዩ ሦስቱ አካላት በማዕዱ እንዲቀመጡ የተገባው ሆነ። አብርሃምም ከዚያ ተነሥቶ ወደ አዜብ ምድር ሔደ በሱሬና በቃዴስ መካከልም ኖረ በጌራራም ተቀመጠ።

አብርሃምም ሚስቱ ሣራን እኃቴ ናት አላቸው አቤሜሌክም ልኮ ሣራን ወሰዳት። በዚያችም ሌሊት አቤሜሌክ ተኝቶ ሳለ #እግዚአብሔር ወደ አቤሜሌክ ገባ በሕልም እንዲህ አለው እሷ የጎልማሳ ሚስት ናትና ስለዚች ስለወሰድካት ሴት እነሆ አንተ ትሞታለህ።

አቤሜሌክ ግን አልነካትም ነበር አቤሜሌክም እንዲህ አለ በውኑ ያላወቀ ሰውን ታጠፋለህን እሱ እኅቴ ናት አለኝ እሷም ወንድሜ ነው አለችኝ ይህንንም ሥራ በንጹህ ልቤ በንጹሕ እጄ አደረግሁት።

#እግዚአብሔርም በሕልም እንዲህ አለው እኔም በየዋህነትህ እንዳደረግከው አውቄአለሁና ራራሁልህ ኃጢአትም እንዳትሠራ ጠበቅሁህ ስለዚህም እንድትቀርባት አልተውኩህም ።

አሁንም ለዚያ ሰው ሚስቱን መልስለት ነቢይ ነውና ስለ አንተ ይፀልይልህ አንተም ትድናለህ ባትመልስለት ግን አንተ ሞትን እንድትሞት ያንተ የሆነው ሁሉ እንዲጠፋ ዕወቅ። አቤሜሌክም አብርሃምን ጠርቶ ይህ በእኔና በመንግሥቴ ላይ ያደረግከው ምንድር ነው ማንም የማይሠራው ታላቅ ኃጢአት ነው ይህንንስ ያደረግህ ምን አይተህ ነው አለው።

አብርሃምም እንዲህ አለ ምናልባት በዚህ ቦታ #እግዚአብሔርን መፍራት የለምና ስለሚስቴ ይገድሉኛል ብዬ ነው። ዳግመኛም በእውነት ከእናቴ ያይደለች ከአባቴ ወገን የሆነች እኅቴ ናት ሚስትም ሆነችኝ #እግዚአብሔርም ከአባቴ ቤት ባወጣኝ ጊዜ ይህንን በጎ ሥራ አድርጊልኝ በገባንበትም ቦታ ሁሉ ወንድሜ ነው በዬ አልኋት።

አቤሜሌክም ሺህ ምዝምዝ ብርን ሴቶች አገልጋዮችን ወንዶች አገልጋዮችን ላሞችና በጎችንም አምጥቶ ለአብርሃም ሰጠው ሚስቱ ሣራንም መለሰለት።
አብርሃምም ወደ #እግዚአብሔር ለመነ #እግዚአብሔርም አቤሜሌክን ፈወሰው ሚስቱንም ባሮቹንና ቤተሰቦቹንም ልጆቹንም ሁሉም ወለዱ ስለ አብርሃም ሚስት ስለሣራ #እግዚአብሔር ማሕፀንን ሁሉ በአፍአ በውስጥ ዘግቶ ነበርና።

ከዚህም በኃላ በጎ ተጋድሎውን ፈጽሞ #እግዚአብሔርንም አገልገሎ በመቶ ሰባ አምስት ዕድሜው ወደ ወደደው #እግዚአብሔር ሔደ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በአባታችን በቅዱስ አብርሃም ጸሎት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ይስሐቅ

በዚህችም ቀን ዳግመኛ የአባቶች አለቃ ለሆነ ለአብርሃም ልጅ ለይስሐቅ የዕረፍቱን መታሰቢያ እንድናደርግ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን መምህራን አባቶቻችን አዘዙን። ይህ ጻድቅ ይስሐቅም በልዑል አምላክ ብሥራት ተወለደ።

ይህንንም ንጹሕ ይስሐቅን #እግዚአብሔር ለልጁ ክርስቶስ ምሳሌው አደረገው። አብርሃምን እንዲህ ብሎታልና የምትወደው ልጅህ ይስሐቅን ከአንተ ጋራ ውሰደውና ወደላይኛው ተራራ ሒደረ እኔ ወደ እምነግርህ ወደ አንዱ ተራራ ላይ አውጥተህ በዚያ ሠዋው።

አብርሃምም በጥዋት ተነሥቶ አህያውን ጫነ ልጁ ይስሐቅንና ሁለቱ ብላቴኖቹንም ወሰደ ለመሥዋዕትም ዕንጨትን ፈልጦ አሸክሞ ሔደ። በሦስተኛም ቀን #እግዚአብሔር ወዳለው ወደዚያ ቦታ ደረሰ አብርሃምም በዐይኑ ቃኘ ቦታውንም ከሩቅ አየ።

አብርሃምም ብላቴኖቹን እናንተ አህያውን ይዛችሁ ከዚህ ቆዮ እኔና ልጄ ግን ወደ ተራራ እንሔዳለን ሰግደንም ወደ እናንተ እንመለሳለን አላቸው። አብርሃምም መሥዋዕት የሚቃጠልበትን ዕንጨት አምጥቶ ለልጁ ለይስሐቅ አሸከመው እሱም ወቅለምቱንና እሳቱን በጁ ያዘ ሁለቱም በአንድነት ሔዱ።

ይስሐቅም አባቱ አብርሃምን አባ አለው እርሱም ልጄ ምነው አለው እነሆ እሳትና እንጨት አለ መሥዋዕት የሚሆነው በጉ ወዴት ነው አለው አብርሃምም መሥዋዕት የሚሆነውን በግ #እግዚአብሔር ያዘጋጃል አለው።

አብረውም ሔደው #እግዚአብሔር ወዳለው ወደዚያ ቦታ ደረሱ አብርሃምም በዚያ መሠዊያን ሠራ ዕንጨቱን ደረደረ ልጁ ይስሐቅንም አሥሮ ጠልፎ በመሠዊያው በዕንጨቱ ላይ በልቡ አስተኛው። አብርሃምም ልጁን ያርደው ዘንድ እጁን ዘርግቶ ወቅለምቱን አነሣ።

#እግዚአብሔርም አብርሃምን አብርሃም አብርሃም ብሎ ጠራው እርሱም አቤት አለ በልጅህ ላይ እጅህን አትዘርጋ ምንም ምን አታድርግበት አንተ #እግዚአብሔርን እንደምትፈራው አሁን አወቅሁ ለምትወደው ለልጅህ አልራራህለትምና አለው።

አብርሃምም በተመለከተ ጊዜ ቀንድና ቀንዱ በዕፀ ሳቤቅ የተያዘ አንድ በግ አየ አብርሃምም ሔደና ወስዶ በልጁ በይስሐቅ ፈንታ ሠዋው። ይህም ንጹህ ይስሐቅ ጎልማሳ ሲሆን አባቱ ሊሠዋው በአቀረበው ጊዜ #እግዚአብሔር በበግ እስከ አዳነው ድረስ ለአባቱ በመገዛት ለመታረድ አንገቱን ዘርግቶ ሰጠ።

እርሱም በአባቱ በአብርሃም ሕሊና ፍጽም መሥዋዕተ ሆነ። ከዚህም በኃላ ይስሐቅን መቸገርና ስደት አግኝቶታል በአባቱ በአብርሃም ዘመን ከሆነው ሌላ በሀገር ረኃብ ሁኖ ነበርና የፍልስጥዔም ንጉሥ አቤሜሌክ ወዳለበት። ወደ ጌራራ ይስሐቅ ሔዶ በዚያ ተቀመጠ።

የአገር ሰዎችም ይስሐቅን የሚስቱን የርብቃን ነገር ጠየቁት እርሱም እኅቴ ናት አላቸው ስለ ሚስቱ ስለ ርብቃ የዚያች አገር ሰዎች እንዳይገድሉት ሚስቴ ናት ብሎ መናገርን ፈርቷልና መልከ መልካም ነበረችና። በዚያም ብዙ ዘመን ኖሩ አቤሜሌክም በመስኮት በተመለከተ ጊዜ ይስሐቅን ከርብቃ ጋር ሲጫወት አየው።

አቤሜሌክም ይስሐቅን ጠርቶ እኅቴ ናት አልከኝ እንጂ እነሆ ሚስትህ ናት አለው ይስሐቅም በርሷ ምክንያት ይገድሉኛል ብዬ ነው አለው። አቤሜሌክም ይህ ያደረግኽብኝ ነገር ምንድን ነው ከዘመዶቼ የሚሆን አንድ ሰው ከሚስትህ ጋር ሊተኛ ጥቂት ቀርቶት ነበር ባለማወቅም ኃጢአትን ልታመጣብኝ ነበር።

ንጉሡም የዚህን ሰው ሚስቱን የነካ ሁሉ ፍርዱ ይሙት በቃ ነው ብሎ ሕዝቡን አዘዛቸው። ይስሐቅም በዚያች ምድር ዘርን ዘራ መቶ ዕጽፍም ሆነለት #እግዚአብሔርም ባረከው ከፍ ከፍም አለ እጅግም ገነነ ወንድ ባርያን ሴት ባርያን ላምን በግን አብዝቶ ገዛ የፍልስጥኤም ሰዎችም ቀኑበት።

በአባቱም ዘመን የአብርሃም ብላቴኖች የቆፈሩአቸውን ጉድጓዶች የፍልስጥኤም ሰዎች ደፈኑዋቸው አፈርንም መሏቸው። አቤሜሌክም ይስሐቅን ፈጽመህ በርትተህብናልና ከእኛ ተለይተህ ሒድ አለው።

ይስሐቅም ከዚያ ተነሥቶ በጌራራ ሸለቆ ሰፍሮ በዚያ ተቀመጠ። ይስሐቅም ያባቱ አገልጋዮች የቆፈሩዋቸውን አባቱ አብርሃምም ከሞተ በኃላ የፍልስጥኤም ሰዎች የደፈኗቸውን የውኃ ጉድጓዶች እንደገና ቆፈራቸው አብርሃም እንደጠራቸው ጠራቸው።

የይስሐቅም አገልጋዮች በጌራራ ቆላ ጉድጓድ ቆፍረው የሚጣፍጥ የውኃ ምንጭ አገኙ የይስሐቅ እረኞችና የጌራራ እረኞች ይህ ውኃ የኛ ነው የኛ ነው በማለት ተጣሉ ያችንም የውኃ ጉድጓድ የዓመፅ ጉድጓድ ብሎ ጠራት ዐምፀውበታልና።

ይስሐቅም ከዚያ ተጎዞ ሒዶ በዚያ ሌላ ጉድጓድ ቁፈረ በርሷም ምክንያት ተጣሉት ስሟንም ጠብ ብሎ ምክንያት ተጣሉት ስሟንም ጠብ ብሎ ጠራት። ከዚያም ተጎዞ ሒዶ ሌላ ጉድጓድን ቁፈረ በርሱም ምክንያት ግን አልተጣሉትም ስሙንም ሰፊ አለው ዛሬ #እግዚአብሔር አሰፋልን በምድርም አበዛን ሲል።

ከዚህም በኃላ ሁለት ልጆችን ኤሳውንና ያዕቆብን ወለደ። ይስሐቅም ኤሳውን ጽኑዕ ኃይለኛ ስለሆነ ይወደዋል። ይስሐቅም አርጅቶ ዐይኖቹ ፈዘው የማያይ ከሆነ በኃላ እንዲህ ሆነ ታላቁ ልጁ ኤሳውን ጠርቶ እነሆ አረጀሁ የምሞትበትንም ቀን አላውቅም ማዳኛ መሣሪያህን የፍላፃ መንደፊያህን ይዘህ ወደ በረሃ ውጣ። ሳልሞት ነፍሴ እንድትመርቅህ እበላ ዘንድ እንደምወደው አድርገህ አምጣልኝ አለው።

ርብቃም ልጁ ኤሳውን እንዲህ ሲለው ይስሐቅን ሰማችው ኤሳውም ወደ አደን ሔደ። ርብቃም ታናሹ ልጇ ያዕቆብን እንዲህ አለችው እነሆ አባትህ ወንድምህን ኤሳውን ሳልሞት በ #እግዚአብሔር ፊት እንድመርቅህ ከአደንከው አዘጋጅተህ የምበላውን አምጣልኝ ሲለው ሰምቼዋለሁ።

አሁንም ልጄ ሆይ በማዝህ ነገር እሽ በለኝ ወደ በጎቻችንም ሒደህ ያማሩ ሁለት ጠቦቶችን አምጣልኝና አባትህ እንደሚወደው አዘጋጃቸው ዘንድ ሳይሞት በልቶ እንዲመርቅህ ወስደህ ለአባትህ እንድትሰጠው አለችው።

ያዕቆብም እናቱ ርብቃን እንዲህ አላት እነሆ ወንድሜ ኤሳው ጠጉራም ነው እኔ ግን ጠጉራም አይደለሁም ምናልባት አባቴ ቢዳስሰኝ በፊቱ እንደምዘብትበት እሆናለሁና ምርቃን ያይደለ በላዬ መርገምን አመጣለሁ።

እናቱም ልጄ ሆይ መርገምህ በእኔ ይሁን ቃሌን ብቻ ስማኝ ሒድና የምልህን አምጣልኝ አለችው ሒዶም ለእናቱ አመጣላትና አባቱ እንደሚወደው አድርጋ መብሉን አዘጋጀች።

ርብቃም ከርሷ ዘንድ የነበረ ያማረውን የታላቅ ልጅዋ የኤሳውን ልብስ አምጥታ ለታናሽ ልጅዋ ለያዕቆብ አለበሰችው ያንንም የሁለቱን ጠቦቶች ለምድ በትከሻውና በአንገቱ ላይ አደረገች ያንን ያዘጋጀችውን እንጀራና ጣፋጭ መብልን ለያዕቆብ በእጁ ሰጠችው።

ወደ አባቱ ገብቶ አባቴ ሆይ አለው አባቱም እነሆኝ ልጄ ሆይ አንተ ማነህ አለው ያዕቆብም እኔ የበኩር ልጅህ ኤሳው ነኝ ያልከኝን አዘጋጅቻለሁ ተነሥና ተቀመጥ ከአደንኩልህም ብላና ነፍስህ ትመርቀኝ ዘንድ አለው።
ይስሐቅም ልጁን ልጄ ሆይ ፈጥነህ ያገኘህ ይህ ምንድነው አለው እርሱም ፈጣሪህ #እግዚአብሔር በፊቴ የሰጠኝ ነው አለው። ይስሐቅም ልጄ ቅረበኝ ልዳሥሥህ አንተ ኤሳው እንደሆንክ ወይም እንዳልሆንክ አለው በቀረበም ጊዜ ዳሠሰውም ቃልህ የያዕቆብ እጆችህ አድነህ ያመጣህልኝን በልቼ ነፍሴ ትመርቅህ ዘንድ አምጣልኝ አለው አቅርቦለት በላ ወይንም አመጣለት ጠጣ።

ይስሐቅም ልጄ ቅረበኝና ሳመኝ አለው ቀርቦም ሳመው የልብሱን ሽታ አሸተተው እነሆ የልጄ ልብስ ሽታው #እግዚአብሔር እንደባረከው እንደዱር አበባ ሽታ ነው አለ። እንዲህም ብሎ መረቀው ከሰማይ ጠል ከምድር ስብ ይስጥህ ሥንዴህን ወይንህንና ዘይትህን ያብዛልህ አሕዛብም ይገዙልህ አለቆችም ይስገዱልህ ለወንድሞችህም ጌታ ሁን የአባትህም ልጆች ይስገዱልህ። የሚረግምህም የተረገመ ይሁን ይህም በ #እግዚአብሔር ፈቃድ ሆነ።

ይህም አባት ይስሐቅ ወደ መቶ ሰማንያ ዘመን ደረሰ አባታችን ይስሐቅም እንዲህ ብሎ ተናገረ ከዚህም በኃላ መልአክ ወደ ሰማይ ወሰደኝ አባቴ አብርሃምን አየሁትና ሰገድሁለት እርሱም ሳመኝ ንጹሕን ሁሉ ስለ አባቴ ተሰበሰቡና ወደ ውስጠኛው የአብ መጋረጃ ከበውኝ ከእኔ ጋራ ሔዱ እኔም ወድቄ ከአባቴ ጋራ ሰገድኩ።

የሚያመሰግኑ መላእክት ሁሉ ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ ተብሎ የሚመሰገን አሸናፊ #እግዘአአብሔር ምስጋናው በሰማይና በምድር የመላ ነው እያሉ ጮኹ።

አባቴ አብርሃምን እኔ በቦታዬ ልዩ ነኝ ሰው ሁሉ ልጁን በወዳጄ ይስሐቅ ስም ቢሰይም በቤቱ ውስጥ በረከቴ ለዘላለም ይኖራል የቡሩክ ወገን የሆንክ አንተ ቡሩክ አብርሃም ሆይ መምጣትህ መልካም ነው። አሁንም በወዳጄ በልጅህ ይስሐቅ ስም የሚለምን ሁሉ በረከቴ በቤቱ ውስጥ ለዘላለም እንዲኖር ቃል ኪዳኔን አጸናለታለሁ አለው።

ትሩፋቱን ቅንነቱን ገድሉን የሚጽፍ ካለ ወይም በስሙ የተራበ የሚያጠግብ በመታሰቢያው ቀን የተራቆተ የሚያለብስ እኔ የማያልፈውን መንግሥት እሰጠዋለሁ።

አብርሃምም እንዲህ አለ አቤቱ ዓለሙን ሁሉ የያዝክ #አብ ሆይ ቃል ኪዳኑን ገድሉን ይጽፍ ዘንድ ካልተቻለው ቸርነትህ ትገናኘው አንተ ቸር መሐሪ ነህና አንጀራ የሌለው ችግረኛ ቢሆንም። #ጌታም እንዲህ ብሎ መለሰለት በወዳጄ በይስሐቅ በመታሰቢያው ዕለት ከሌሊት ጀምሮ በጸሎት ይትጋ አይተኛ እኔም መንግሥቴን ከሚወርሱ ጋራ ከበረከቴ እሰጠዋለሁ።

አባቴ አብርሃምም ሁለተኛ እንዲህ አለ በሽተኛ ድውይ ከሆነ ቸርነትህ ታግኘው #ጌታም እንዲህ አለ ጥቂት ዕጣን ያግባ ዕጣንን ካላገኘ የቃል ኪዳኑን መጽሐፍ ፈልጎ በልጅህ በወዳጄ በይስሐቅ መታሰቢያ ቀን ያንብበው። ማንበብም የማያውቅ ከሆነ ወደሚያነቡለት ሒዶ እሷን አስነብቦ ይስማ። ከእነዚህም ይህን ማድረግ ካልቻለ ወደ ቤቱ ገብቶ ደጁን ይዝጋ እየጸለየ መቶ ስግደቶችን ይስገድ እኔም የሰማይ የመንግሥት ልጅ አደረገዋለሁ።

ለቁርባን የሚሆነውንና መብራትን ያገባ እኔ ያልኩትን ሁሉ የሚያደርግ እርሱ የመንግሥተ ሰማያትን ርስት ይቀበላል። ቃል ኪዳኑንና ገድሉን ትሩፋቱን ለመጻፍ ልቡን ያበረታውን እኔ ስሙን በሕይወት መጽሐፍ እጽፋለሁ በሺው ዓመት ምሳ ላይም ይገኛል።

#እግዚአብሔርም ይህን ብዙ ነገርን በተናገረ ጊዜ ያዕቆብ አይቶ በመደንገጥ ነፍሱ ተመሠጠች ይስሐቅም ያዕቆብን አንሥቶ ልጄ ሆይ ዝም በል አትደንግጥ ብሎ ጠቀሰው ከዚህም በኃላ ሳመውና በሰላም አረፈ። ከኤሞር ልጆች በገዛው እናቱ ሣራ በተቀበረችበት በአብርሃም መቃብር ተቀበረ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ ይስሐቅ አማላጅነት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ያዕቆብ

በዚችም ቀን ደግሞ #እግዚአብሔር እስራኤል ብሎ ስም ያወጣለትን የአባቶች አለቃ የሆነ የያዕቆብን የዕረፍቱን መታሰቢያ እናደርግ ዘንድ የቤተ ክርስቲያን መምህራን አባቶቻችን አዘዙን። ይህም ቅዱስ በበጎ ሥራ ሁሉ በመራራት በቅንነት በትሕትና በለጋስነት የአባቶቹን የአብርሃምንና የይስሐቅን መንገድ የተከተለ ሆነ።

ወንዱሙ ኤሳውም ብኩርናውን በምስር ንፍሮ ደግሞ በረከቱን ስለወሰደበት አብዝቶ ስለጠላው ሊገድለው ይፈልግ ነበር ስለዚህም አባቱ ይስሐቅና እናቱ ርብቃ ያዕቆብን ወደ ርብቃ ወንድም ወደ ላባ ሰደዱት።

እየተጓዘም ሳለ በአደረበት በረሀ ከምድር እስከ ሰማይ የሚደርስ መሰላል የ #እግዚአብሔርም መላእክት በውስጡ ሲወርዱ ሲወጡ በሕልሙ አየ እንዲህም አለ ይህ የሰማይ ደጅ ነው ከዚህም የ #እግዚአብሔር ቤት ይሠራል።

በሶርያ ምድር ወደሚኖር ወደእናቱ ወንድም ወደ ላባ በደረሰ ጊዜ ሁለቱን ልጆቹን ልያንና ራሔልን አጋባው በዚያም የላባን በጎች እየጠበቀ ሃያ አንድ ዓመት ያህል ኖረ። ላባም የምሰጥህ ምንድን ነው አለው ያዕቆብም ምንም የምትሰጠኝ የለም አሁን ወደፊት የምነግርህን ነገር ካደረግህልኝ ዳግመኛ በጎችህን ፈጽሜ እጠብቃለሁ።

አሁን በጎችህ በፊት ይለፉና ከበጎችህ ሁሉ ጠጉራቸው ነጫጭ የሆኑትንና መልካቸው ዝንጉርጉር የሆነውንም ስለዋጋዬ ለይልኝ አለው። ዓይነቱ ዝንጉርጉር ያልሆነውና መልኩ ነጭ ያልሆነው ሁሉ ግን ላንተ ይሁን አለው። ላባም እንዳልክ ይሁን አለ።

በዚያችም ቀን ነጩንም ቀዩንም ዝንጉርጉሩንም መልኩ ዳንግሌ የሆነውንም የፍየሉንም አውራ ለይቶ ለልጆቹ ሰጠ። በእነርሱና በያዕቆብ መካከል ሦስት ቀን የሚያስኬድ ጎዳና ርቀው ሔዱ ያዕቆብ ግን የቀሩትን የላባን በጎች ይጠብቅ ነበር።

ያዕቆብም የልምጭ በትርንና ታላቅ የሎሚ በትርን ወስዶ ቅረፍቱን ልጦ ጣለው ያዕቆብ የላጣቸው በትሮች ነጫጭ ሁነው ታዩ። እነዚያንም በትሮች በጎች ከሚጠጡበት ገንዳ ላይ ጣላቸው በጎች ውኃ ሊጠጡ በመጡ ጊዜ እነዚያ በትሮች በፊታቸው ሁነው ይታዩ ዘንድ። መጥተውም በጠጡ ጊዜ እነዚያን በትሮች አስመስለው ፀንሰው ነጩንና ሐመደ ክቦውን ዝንጉርጉሩን ወለዱ።

ያዕቅብም አውራ አውራዎቹን በጎች ለየ አውራ አውራውን ከለየ በኃላ እንስት እንስቶቹን በጎች ለይቶ ዝንጉርጉር ሐመደ ክቦና ነጭ በሆኑ አውራዎች ፊት አቆማቸው የራሱንም በጎች ለያቸው እንጂ ከላባ በጎች ጋራ አልቀላቀላቸውም።

ያዕቆብም እጅግ ፈጽሞ ባለጸጋ ሆነ ሴቶችንም ወንዶችንም አገልጋዩችን ገዛ ብዙ ከብት ላሞችን በጎችን ግመሎችንና አህዮችን ገዛ። ያዕቆብም ወደአገሩ በተመለሰ ጊዜ እስከ ንጋት ድረስ አንድ ሰው ሲታገለው አደረ ከእርሱም ጋራ ሲታገል እንዳልቻለው ባየ ጊዜ እርም የሚሆንበት ሹልዳውን ያዘው ጎህ ቀድዷልና ልቀቀኝ አለው ካልመረቅከኝ አልለቅህም አለው።

ስምህ ማን ይባላል ቢለው ስሜ ያዕቆብ ነው አለው እንግዲህ ስምህ ያዕቆብ አይባል እስራኤል ይባል እንጂ አለው ከ #እግዚአብሔርና ከሰው ጋራ መታገልን ችለሃልና።

ከዚህም በኃላ ስለ ልጁ ዮሴፍ ብዙ ኀዘን አገኘው ወንድሞቹ ወደ ግብጽ ሸጠውታልና በጠየቃቸውም ጊዜ ክፉ አውሬ በልቶታል አሉት ከልቅሶውም ብዛት የተነሣ ዐይኖቹ ታወሩ።

ከዚህም በኃላ ታላቅ ረሀብ ሆነ በግብጽ አገር እህል የሚሸጥ መሆኑን ያዕቆብ ሰማ ሥንዴ ይሸምቱ ዘንድ ልጆቹን ላካቸውና ወደ ዮሴፍ ደረሱ ንጉሥ ሆኖም አግኘተውት ሰገዱለት ወንድማቸው እንደሆነም አላወቁትም እርሱ ግን አውቋቸዋል ሥንዴውንም ሰጥቶ አስናበታቸው ሁለተኛም በተመለሱ ጊዜ ራሱን ገለጠላቸውና ወደዚህ ስለ ሸጣችሁኝ አትፍሩ እመግባችሁ ዘንድ በፊታችሁ #እግዚአብሔር ለሕይወት ልኮኛልና አላቸው።

አሁንም ፈጥናችሁ ሒዱና ለአባቴ ንገሩት ልጅህ ዮሴፍ እንዲህ ይላል በሉት ለግብጽ አገር ሁሉ #እግዚአብሔር ጌታ አድርጎኛል ፈጥነህ ና በዚያ ልኑር አትበል።
ስለዚህም እስራኤል ወደግብጽ አገር ከቤተሰቡ ሁሉና ከጓዙ ከገንዘቡ ጋር ወርዶ በዚያ የሚኖር ሆነ። ዕረፍቱም በቀረበ ጊዜ ልጆቹን ጠርቶ እየአንዳንዳቸውን መረቃቸው ትንቢትንም ተናገረላቸው የዮሴፍንም ልጆች ኤፍሬምንና ምናሴን እጆቹን አመሳቅሎ ባረካቸው መረቃቸውም። ከዚህም በኃላ በመቶ ሠላሳ ሰባት ዕድሜው በሰላም በፍቅር አረፈ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በአባቶቻችን በአብርሃም፣ በይስሐቅ እና በያዕቆብ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን ።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ነሐሴ_28)
#ነሐሴ_28_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ማቴዎስ 22
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²³ በዚያን ቀን፦ ትንሣኤ ሙታን የለም የሚሉ ሰዱቃውያን ወደ እርሱ ቀረቡ፥
²⁴ እንዲህም ብለው ጠየቁት፦ መምህር ሆይ፥ ሙሴ አንድ ሰው ልጅ ሳይወልድ ሲሞት ወንድሙ ሚስቱን አግብቶ ለወንድሙ ዘር ይተካ አለ።
²⁵ ሰባት ወንድማማች በእኛ ዘንድ ነበሩ፤ ፊተኛውም ሚስት አግብቶ ሞተ፥ ዘርም ስለሌለው ሚስቱን ለወንድሙ ተወለት፤
²⁶ እንዲሁ ደግሞ ሁለተኛው ሦስተኛውም፥ እስከ ሰባተኛው ድረስ።
²⁷ ከሁሉም በኋላ ሴቲቱ ሞተች።
²⁸ ሁሉ አግብተዋታልና በትንሣኤ ቀንስ፥ ከሰባቱ ለማናቸው ሚስት ትሆናለች?
²⁹ ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኃይል አታውቁምና ትስታላችሁ።
³⁰ በትንሣኤስ እንደ እግዚአብሔር መላእክት በሰማይ ይሆናሉ እንጂ አያገቡም አይጋቡምም።
³¹-³² ስለ ትንሣኤ ሙታን ግን፦ እኔ የአብርሃም አምላክ፥ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ ነኝ የሚል ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ እናንተ የተባለውን አላነበባችሁምን? የሕያዋን አምላክ ነው እንጂ የሙታን አይደለም።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
መልካም የአርእስተ አበው የቅዱሳን የ #አብርሃም#ይስሐቅ#ያዕቆብ የዕረፍት በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"#ሰላም_ለአብርሃም_ዘበዘርዑ_ተባረከ ኵሉ ዓለም ርእሰ አበው ግሩም ዘይቤሎ እግዚአብሔር ክቡር አንተ ዘከመ ስብሐትየ። ትርጉም፦ እግዚአብሔር እንደ ጌትነቴ ያከበርኹኽ አንተ የከበርኽ ነኽ ያለው፤ የተወደደ የአባቶች አለቃ ዓለም ኹሉ በዘሩ የተባረከለት ለኾነ #ለቅዱስ_አብርሃም_ሰላምታ_ይገባል#ሊቁ_አባ_ጊዮርጊስ_ዘጋስጫ_በተአምኆ_ቅዱሳን_ላይ
"#ሰላም_ለይሥሐቅ_ንጹሕ_ወጻድቅ ዘኮነ መሥዋዕተ ኅየንቴሁ ኢየሱስ ሊቅ በአምሳለ በግዕ ዘስቁል በዕፀ ሳቤቅ"። ትርጉም፦ በዕፀ ሳቤቅ ላይ በተሰቀለው በግ አምሳል መምህር ኢየሱስ በርሱ ፈንታ መሥዋዕት የኾነለት ለኾነ #ለንጹሕና_ለጻድቅ_ለቅዱስ_ይሥሐቅ_ሰላምታ_ይገባል#ሊቁ_አባ_ጊዮርጊስ_ዘጋስጫ_በተአምኆ_ቅዱሳን_ላይ
"#ሰላም_ለያዕቆብ_ምንዙህ_ዘኮነ_በረከቱ_ብዙኀ እምጠሉ ለሰማይ ወእምስፍሓ ለምድር፤ ዘአስተርአዮ እግዚአብሔር ገጸ በገጽ ወተናገሮ በምድረ ሎዛ፤ ወሰመየ ስሞ እስራኤል"። ትርጉም፦ ከሰማይ ጠልና ከምድርም ስፋት ይልቅ በረከቱ የበዛ የኾነ እግዚአብሔር ፊት ለፊት የተገለጸለት (የታየው) በሎዛ ምድርም የተናገረው፤ ስሙንም እስራኤል ብሎ ለሰየመለት ቅምጥል ድልድል ለኾነ #ለቅዱስ_ያዕቆብ ሰላምታ ይገባል። #ሊቁ_አባ_ጊዮርጊስ_ዘጋስጫ_በተአምኆ_ቅዱሳን_ላይ
#ነሐሴ_29

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ነሐሴ ሃያ ዘጠኝ በዚህች ቀን ከእመቤታችን ከቅድስት #ድንግል_ማርያም መድኃኒታችን #ኢየሱስ_ክርስቶስ በሥጋ ለመወለዱ መታሰቢያ በዓል ሆነ ለእርሱም ምስጋና ክብር ይሁን ለዘላለሙ አሜን፣ #የአባ_ዮሐንስ_ሐጺር ወደ አስቄጥስ ገዳም የሥጋው ፍልሰት ሆነ፣ #ቅዱስ_አትናቴዎስ #ገርሲሞስና_ቴዎዶጦስ ከሚባሉ ሁለት አገልጋዮቹ ጋር በሰማዕትነት አረፈ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አባ_ዮሐንስ_ሐጺር

ነሐሴ ሃያ ዘጠኝ በዚህች ቀን የአባ ዮሐንስ ሐጺር ወደ አስቄጥስ ገዳም የሥጋው ፍልሰት ሆነ። ይህም የአባ እንጦንዮስ በሆነ በቊልዝም ገዳም ከአረፈ በኋላ ነው። ለእስክንድርያ አባ ዮሐንስ ሊቀ ጵጵስና በተሾመ ጊዜ እርሱም ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት አርባ ስምንተኛ የሆነ ነው። እርሱም ወደ አስቄጥስ ገዳም ሔደ የከበሩ መነኰሳትም እንዲህ አሉት የቅዱስ ዮሐንስ ሐጺር ሥጋ በዚህ በቤተ ክርስቲያኑ ቢሆን እኛም ሥጋው በአለበት ለፈጣሪያችን #እግዚአብሔር እንሰግድ ዘንድ እንሻ ነበር።

ያን ጊዜ የ #እግዚአብሔር ቸርነት አነሣሣችውና ስሙ ቆዝሞስ ለሚባል ለአንድ አበ ምኔት መልእክትን ጻፈ ከእርሱም ጋር የቊልዝም አገር የሆነ አረጋዊ አለ በደረሱም ጊዜ በዚያን ሰዓት ሥጋውን መውሰድ አልተቻላቸውም። የቅዱስ ዮሐንስ ሐጺር ሥጋ የኬልቄዶንን ጉባኤ በተቀበሉ መለካውያን ዘንድ ይጠበቅ ስለነበረ ነገር ግን ቦታውን አወቁ ተረዱ ወደ ቦታቸውም ተመልሰው ሃይማኖታቸው የቀና ምእመናን ሰዎችን አገኙ እነርሱም በዚያች አገር የሚኖሩ ናቸው ስለርሱ የመጡበትን ነገሩአቸው።

ከጥቂት ቀኖች በኋላም ከታላላቅ ዐረቦች ወገን ለቊልዝም አገር መኰንን ተሾመ እርሱም ለኤጲስቆጶስ አባ ሚካኤል ወዳጁ ነው ሊቀ ጳጳሳት አባ ዮሐንስም ስለ ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺር ሥጋ ወደ ኤጲስቆጶሱ መልእክትን ጻፈ። በመልእክቱም የቅዱስ ዮሐንስ ሐጺርን ሥጋ ከከሐድያን መለካውያን እጅ እስከ አፈለሱት ድረስ መልእክተኞች አእሩግ መነኰሳትን ምክንያት ፈልጎ እንዲረዳቸው በማሳሰብ አዘዘው።

ኤጲስቆጶሱም በሰማ ጊዜ ፈጽሞ ደስ አለው ሒዶም ወዳጁ ለሆነ ለመኰንኑ ጸሐፊ ነገረው። ጸሐፊውም ለመኰንኑ ነገረው። እነሆ መኰንኑም ከመነኰሳቱ ጋራ ሔደ ጸሐፊውም መነኰሳቱ ወደዚያ ቦታ እንዲገቡ ምክንያት እንዴት እናገኛለን አለ። መኰንኑም በልብሶቻቸው ላይ የዓረቦችን ልብሶች ያልብሱአቸውና ከእኔ ጋራ ወደዚያ ቦታ ይምጡ አለ እንዲሁም እንዳላቸው አደረጉ።

ከዚህም በኋላ መኰንኑ ሔደ ከእርሱም ጋራ ብዙ ፈረሰኞች ሰዎች ብዙ ሕዝብም የአስቄጥስ ገዳም የከበሩ አረጋውያን አሉ ወደቊልዝም ገዳምም ደረሱ። መኰንኑም በዚያ የሚኖራውን የመለካውያን ኤጲስቆጶስ እንዲህ ብሎ አዘዘው ያንተን ሰዎች ከቤተ ክርስቲያን ውስጥ አስወጣቸው በዚች ሌሊት እኔ በውስጧ አድራለሁና ያ መለካዊም መኰንኑ እንዳዘዘው አደረገ።

መነኰሳቱም እንስሶቻቸውን ከከተማ ውጭ አዘጋጅተው በሌሊት ወደዚያ ገብተው የቅዱስ ዮሐንስ ሐጺርን ሥጋ ይዘው ወደ ምስር ደረሱ ከዚያም ወደ አስቄጥስ ገዳም ደረሱ የአባ መቃርስ ገዳም መነኰሳትም መስቀሎችን፣ ወንጌሎችን፣ ማዕጠንቶችንና መብራቶችን በመያዝ እየዘመሩና እያመሰገኑ ተቀበሏቸው ወደ አባት መቃርስ ሥጋም አቀረቡትና ከእርሱ ተባረኩ በላዩም ብዙ ሽቱዎችን ነሰነሱ የቊርባን ቅዳሴንም ቀደሱ የከበረ ወንጌልም በሚነበብ ጊዜ ታላቅ ድንቅ ተአምር ተገለጠ ቤተ ክርስቲያኒቱ ሁለመናዋ በሰማያዊ ብርሃን በራች። ከቶ እንደርሱ ሆኖ የማያውቅ በጎ መዓዛ ሸተተ ታላቅ ደስታም ሆነ በዚያም ቦታ ሰባት ቀን ኖረ።

ከዚህም በኋላ ወደ ራሱ ቤተ ክርስቲያን ተሸክመው ወሰዱት ዕብራውያንም በ #እግዚአብሔር ስም የሚመጣ የተባረከ ነው እያሉ #መድኃኒታችንን እንደተቀበሉት ልጆቹ መነኰሳት ተቀበሉትና ወደ ቦታው አኖሩት ከእርሱም ድንቆች ተአምራቶች ተገለጡ።

ከዚህም በኋላ ወደ አስቄጥስ ገዳም ሊቀ ጳጳሳት አባ ማርቆስ በወጣ ጊዜ ወደ አባ ዮሐንስ ሐጺር ቤተ ክርስቲያን ገባ። ከእርሱም ጋር ብዙዎች ኤጲስቆጶሳትና የእስክንድርያ አገር ታላላቆች ከግብጽ አገር ሁሉ አሉ። የአባ ዮሐንስ ሐጺር ሥጋ የተጠቀለለበትን ሰሌን ገልጦ ከእርሱ ተባረከ መሪር ልቅሶንም አለቀሰ ያን ጊዜ ሥጋው ሲገለጥ መብረቅና ነጐድጓድ ሆነ። በቤተ ክርስቲያኑም ውስጥ ያሉት ሁሉም ደንግጠው ወደቁ ሊቀ ጳጳሳቱም ሰሌኑን መልሶ በፍጥነት ሥጋውን ጠቀለለ በሽብሸባ እየዘመሩና እያመሰገኑ እንደቀድሞው ሸፈነው።

ከዚህም በኋላ ዳግመኛ እንዲህ እያሉ ሊያመሰግኑ ጀመሩ ፈጣን ደመና ሁነህ የ #መንፈስ_ቅዱስን ዝናም የተሸከምክ ሠለስቱ ደቂቅ ወዳሉበት ወደ ባቢሎን የሔድክ በላይህ በአደረ በ #መንፈስ_ቅዱስ ኃይል ወደ እስከንድርያ አገር የተመለስክ ሁለተኛም ወደ ቊልዝም የሔድክ የጣዖታትን ቤቶች አፍርሰህ ሃይማኖትን የሰበክ በሽተኞችን የፈወስክ አጋንንትን ያስወጣህ ወደርስትህም የተመለስክ አንተ የበረከት ማደሪያ ነህና። የአባ ዮሐንስ ሐጺር የሥጋው ፍልሰት ከንጹሐን ሰማዕታት ዘመን በአምስት መቶ ሃያ ዓመት ሆነ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ ጻድቅ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አትናቴዎስ_ሰማዕት

በዚህችም ቀን ኤጲስቆጶስ አትናቴዎስ በሰማዕትነት ሞተ ከእርሱም ጋር ስማቸው ገርሲሞስና ቴዎዶጦስ የሚባል ሁለት አገልጋዮች በሰማዕትነት አረፉ።

ይህንንም ቅዱስ አትናቴዎስን የእንጦኒቆስን የጭፍራ አለቃውን ልጅ እርሱ እንዳጠመቃት በንጉሥ ዘንድ ወነጀሉትና ንጉሥ አርስያኖስ ያዘው እርሱም ክርስቲያን እንደሆነ ታመነ ብዙ ሥቃይንም አሠቃየው።

በሃይማኖቱም ጸና እንጂ ሃይማኖቱን ባልካደ ጊዜ ራሱን በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ እንዲሁም እሊህን ሁለቱን አገልጋዮች ገርሲሞስንና ቴዎዶጦስን በግርፋትና በስቅላት ከቀጣቸው በኋላ ራሶቻቸውን በሰይፍ አስቆረጠ ሦስቱም የሰማዕትነት አክሊልን ተቀበሉ።

አማንያን ሰዎችም መጡ ለወታደሮችም ገንዘብ ሰጥተው የቅዱሳኑን ሥጋቸውን ወሰዱ በአማሩ ልብሶችም ገንዘው በሣጥን ውስጥ አኖሩአቸው ከሥጋቸውም ታላላቅ ድንቆች ተአምራቶች ተገለጡ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ነሐሴ_29)
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ነሐሴ_29_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ገላትያ 3
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁵ ወንድሞች ሆይ፥ እንደ ሰው ልማድ እላለሁ። የሰው ስንኳ ቢሆን እርግጠኛውን ኪዳን ማንም አይንቅም ወይም አይጨምርበትም።
¹⁶ ለአብርሃምና ለዘሩም የተስፋው ቃል ተነገረ። ስለ ብዙዎች እንደሚነገር፦ ለዘሮቹም አይልም፤ ስለ አንድ እንደሚነገር ግን፦ ለዘርህም ይላል፥ እርሱም ክርስቶስ።
¹⁷ ይህንም እላለሁ፤ ከአራት መቶ ሠላሳ ዓመት በኋላ የተሰጠው ሕግ አስቀድሞ በእግዚአብሔር የተረጋገጠውን ኪዳን የተስፋውን ቃል እስኪሽር ድረስ አያፈርስም።
¹⁸ ርስቱ በሕግ ቢሆንስ እንግዲያስ በተስፋ ቃል አይሆንም፤ በተስፋ ቃል ግን እግዚአብሔር ለአብርሃም ሰጥቶአል።
¹⁹ እንግዲህ ሕግ ምንድር ነው? ተስፋው የተሰጠው ዘር እስኪመጣ ድረስ በመካከለኛ እጅ በመላእክት በኩል ስለ ሕግ መተላለፍ ተጨመረ።
²⁰ መካከለኛውም ለአንድ ብቻ አይደለም እግዚአብሔር ግን አንድ ነው።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ዮሐንስ 4
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁹ በዚህ የእግዚአብሔር ፍቅር በእኛ ዘንድ ተገለጠ፥ በእርሱ በኩል በሕይወት እንኖር ዘንድ እግዚአብሔር አንድ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታልና።
¹⁰ ፍቅርም እንደዚህ ነው፤ እግዚአብሔር እርሱ ራሱ እንደ ወደደን ስለ ኃጢአታችንም ማስተስሪያ ይሆን ዘንድ ልጁን እንደ ላከ እንጂ እኛ እግዚአብሔርን እንደ ወደድነው አይደለም።
¹¹ ወዳጆች ሆይ፥ እግዚአብሔር እንዲህ አድርጎ ከወደደን እኛ ደግሞ እርስ በርሳችን ልንዋደድ ይገባናል።
¹² እግዚአብሔርን ማንም ከቶ አላየውም፤ እርስ በርሳችን ብንዋደድ እግዚአብሔር በእኛ ይኖራል ፍቅሩም በእኛ ፍጹም ሆኖአል።
¹³ ከመንፈሱ ስለ ሰጠን፥ በእርሱ እንድንኖር እርሱም በእኛ እንዲኖር በዚህ እናውቃለን።
¹⁴ እኛም አይተናል አባትም ልጁን የዓለም መድኃኒት ሊሆን እንደ ላከው እንመሰክራለን።
¹⁵ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ በሚታመን ሁሉ እግዚአብሔር በእርሱ ይኖራል እርሱም በእግዚአብሔር ይኖራል።
¹⁶ እኛም እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር አውቀናል አምነንማል። እግዚአብሔር ፍቅር ነው፥ በፍቅርም የሚኖር በእግዚአብሔር ይኖራል እግዚአብሔርም በእርሱ ይኖራል።
¹⁷ በፍርድ ቀን ድፍረት ይሆንልን ዘንድ ፍቅር በዚህ ከእኛ ጋር ተፈጽሞአል፤ እርሱ እንዳለ እኛ ደግሞ እንዲሁ በዚህ ዓለም ነንና።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 20
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²⁸ በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።
²⁹-³⁰ ከሄድሁ በኋላ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኩላዎች እንዲገቡባችሁ፥ ደቀ መዛሙርትንም ወደ ኋላቸው ይስቡ ዘንድ ጠማማ ነገርን የሚናገሩ ሰዎች በመካከላችሁ እንዲነሡ እኔ አውቃለሁ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ነሐሴ_29_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"እዜም ወእሌቡ ፍኖተ ንጹሐ። ማእዜ ትመጽእ ኀቤየ። ወአሐውር በየዋሃተ ልብየ ማእከለ ቤትየ"። መዝ 100፥1-2።
"አቤቱ፥ ምሕረትንና ፍርድን እቀኝልሃለሁ።
²እዘምራለሁ፥ ንጹሕ መንገዱንም አስተውላለሁ፤ ወደ እኔ መቼ ትመጣለህ? በቤቴ መካከል በልቤ ቅንነት እሄዳለሁ"። መዝ 100፥1-2።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ነሐሴ_29_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ማቴዎስ 5
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ ሕዝቡንም አይቶ ወደ ተራራ ወጣ፤ በተቀመጠም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀረቡ፤
² አፉንም ከፍቶ አስተማራቸው እንዲህም አለ፦
³ በመንፈስ ድሆች የሆኑ ብፁዓን ናቸው፥ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና።
⁴ የሚያዝኑ ብፁዓን ናቸው፥ መፅናናትን ያገኛሉና።
⁵ የዋሆች ብፁዓን ናቸው፥ ምድርን ይወርሳሉና።
⁶ ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ብፁዓን ናቸው፥ ይጠግባሉና።
⁷ የሚምሩ ብፁዓን ናቸው፥ ይማራሉና።
⁸ ልበ ንጹሖች ብፁዓን ናቸው፥ እግዚአብሔርን ያዩታልና።
⁹ የሚያስተራርቁ ብፁዓን ናቸው፥ የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና።
¹⁰ ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው፥ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና።
¹¹ ሲነቅፉአችሁና ሲያሳድዱአችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብፁዓን ናችሁ።
¹² ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ፥ ሐሴትም አድርጉ፤ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያትን እንዲሁ አሳድደዋቸዋልና።
¹³ እናንተ የምድር ጨው ናችሁ፤ ጨው አልጫ ቢሆን ግን በምን ይጣፍጣል? ወደ ውጭ ተጥሎ በሰው ከመረገጥ በቀር ወደ ፊት ለምንም አይጠቅምም።
¹⁴ እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ። በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሰወር አይቻላትም።
¹⁵ መብራትንም አብርተው ከዕንቅብ በታች አይደለም እንጂ በመቅረዙ ላይ ያኖሩታል በቤት ላሉት ሁሉም ያበራል።
¹⁶ መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
የሚቀደሰው ቅዳሴ #ቅዳሴ_እግዚእነ ነው። መልካም የአባ ዮሐንስ ሐጺር የፍልሰት ሥጋ በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ጌታዬ_ኢየሱስ_ሆይ ከሁሉ ይልቅ በሦስትነትህ መታመን ይበልጣል። አንተ በወለደችህ በ #ማርያም መማጸን መልካም ዕድል። #ፈጣሪዬ_ክርስቶስ_ሆይ ከቤተ መንግሥትና ከቤተ ክህነት ወገን የአንተን ሰው መሆን የሚጠራጠር ወይም አምላክ ሰው፤ ሰው አምላክ መሆኑን የሚክድ ቢኖር ዕመቀ እመቃት መንጸፈ ደይን ወርዶ ይንኮታኮት።

#መልክአ_ኢየሱስ
#ነሐሴ_30

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ነሐሴ ሠላሳ በዚች ቀን ከዐሥራ ስድስቱ ነቢያት አንዱ #ታላቅ_ነቢይ_ሚልክያስ ያረፈበት እና ጌታ ባሕር ውስጥ #ለሐዋርያ_እንድርያስ በሊቀ ሐመር አምሳል ተገልጦ ድንቅ ተአምር ያደረገለት ቀን ነው፣ የእናታችን #ቅድስት_ዜና_ማርያም የእረፍቷ መታሰቢያ ነው፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ነቢዩ_ሚልክያስ

ነሐሴ ሠላሳ በዚች ቀን ከዐሥራ ስድስቱ ነቢያት አንዱ ታላቅ ነቢይ ሚልክያስ አረፈ። ይህም ነቢይ የእስራኤል ልጆች ከተሰደዱበት ከባቢሎን ሀገር በተመለሱ ጊዜ የ #እግዚአብሔርን ትእዛዝ በመተላለፋቸው ገሥጿቸዋል።

ሁለተኛም ነቋር ስለሆነ መሥዋዕት ስለ አሥራትና በኵራት ገሥጿቸዋል። በዚህ ነቢይ አንደበት #እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ተናግሯልና ርኅራኄ አድርጋችሁ ምጽዋትን መጽውቱ፣ ዐሥራቴንና በኵራቴንም አስገቡና እስቲ ፈትኑኝ እኔ ከሰማይ ዝናሙን ባላወርድላችሁ በረከትንም አስቲበቃችሁ ባልጨምርላችሁ የምድራችሁንም ፍሬ ነቀዝና መሰክ እንዳይበሉት እከለክላለሁ።

ዳግመኛም ከክብር ባለቤት #መድኃኒታችን_ክርስቶስ አስቀድሞ መጥምቁ ዮሐንስ ስለ መምጣቱ ስለ ነቢዩ ኤልያስም ተናገረ። ደግሞ ስለ አይሁድ የሥርዓተ ክህነት ፍጻሜ ተናገረ በአሕዛብም አገር ውስጥ ለ #እግዚአብሔር የሚቀበላቸውን መሥዋዕት የሚያሳርጉ ዕውነተኞች ንጹሐን ካህናት እንዳሉ ገለጠላቸው።

በበጎ ተጋድሎውም #እግዚአብሔርን ከአገለገለ በኋላ ከዚህ ዓለም በመፍለስ በሰላም አረፈ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ ነብይ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።


✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ሐዋርያው_ቅዱስ_እንድርያስ

በዚችም ቀን #ጌታችን በባሕር ውስጥ ለሐዋርያ እንድርያስ በሊቀ ሐመር አምሳል ተገልጦ ድንቅ ተአምር አደረገለት።

እንድርያስም #ጌታችንን በመርከብህ አሳፍረን ነገር ግን የምንከፍልህ የመርከብ ዋጋ የለንም አለው። በሊቀ ሐመር የተመሰለ #ጌታችንም ስለምን የላችሁም አለው እንድርያስም በከረጢታችን ወርቅን፣ ብርን እንዳንይዝ ስለአዘዘን ነው አለው። #ጌታችንም እንዲህ ከሆነ ወደ መርከቤ ወጥታችሁ ተሳፈሩ አላቸው ያንጊዜም ወደ መርከብ ወጥተው ተሳፈሩ።

ከዚህም በኋላ #ጌታችን እንድርያስንና ደቀ መዛሙርቱን ከባሕሩ ማዕበል የተነሣ መታገሥ እንድትችሉ ተነሥታችሁ እንጀራ ብሉ አለ። እንድርያስም አድንቆ እንዲህ አለው በመንግሥተ ሰማያት የሕይወት እንጀራ #እግዚአብሔር ይስጥህ። ደቀ መዛሙርቱ ግን በባሕር ላይ ጉዞ ስለአልለመዱ ከባሕሩ ማዕበል ፍርሀት የተነሣ መብላት መነጋገርም ተሳናቸው ።

#ጌታችንም እንድርያስን ደቀ መዛሙርትህን ወደ ምድር እንዲወርዱ እዘዛቸው ሲፈሩ አያቸዋለሁና ይህ ካልሆነ እንዳይፈሩ አንተ የ #ኢየሱስ ደቀ መዝሙሩ ከሆንክ ጣዕም ባለው ቃል አስተምራቸው እነሆ ከየብስ ርቀናልና አለው። #ጌታችንም መርከቡን መቅዘፍ ጀመረ እንድርያስም ማስተማርና ማጽናናት ያዘ በልቡም ጸለየ ያን ጊዜም ከባድ እንቅልፍን አንቀላፉ ስለተኙለትም እንድርያስ ደስ አለው።

እንድርያስም ወደ #ጌታችን ተመልሶ እንዲህ አለው ዐሥራ አራት ጊዜ በባሕር ላይ ጒዞ አድርጌአለሁ እንዳንተ የሚቀዝፍ አላገኘሁም። #ጌታም መልሶ እንዲህ አለው እኛስ በባሕር ላይ ስንጓዝ ሁል ጊዜ እንቸገራለን። ነገር ግን አንተ የክብር ባለቤት የ #ኢየሱስ_ክርስቶስ ደቀ መዝሙር እንደሆንክ ባሕር ስለአወቀችህ ማዕበሏን በአንተ ላይ አላነሣችም እንድርያስም በታላቅ ቃል እንዲህ ብሎ ጮኸ። የክብር ባለቤት #ጌታዬ_ኢየሱስ_ክርስቶስ አመሰግንሃለሁ ከሚያከብርህ ሰው ጋር ተገናኝቼ ተነጋግሬአለሁና።

ከዚህም በኋላ #ጌታችን እንድርያስን እንዲህ አለው አንተ የ #ክርስቶስ ደቀ መዝሙሩ ነህና ንገረኝ። አይሁድ የ #እግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ስለምን አላመኑም የሠራውን ብዙ ድንቅ ተአምርን ሰምተናልና አለው። እንድርያስም እንዲህ አለው አዎን ወንድሜ እርሱ የ #እግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ገልጦልናል አንካሶችንም በትክክል እንዲሔዱ አድርጓልና፣ ደንቆሮዎችንም አሰምቷልና፣ ዲዳዎችንም አናግሮአልና፣ ለምጻሞችንም አንጽቷልና፣ ውኃውንም ወይን አድርጓልና፣ አምስት እንጀራና ሁለት ዓሣን አንሥቶ ያዘ ሕዝቡንም በመስክ ሣር ላይ እንዲቀመጡ አዘዘ ሣሩም እንጀራ እስቲለብስ ድረስ በልተው ጠገቡ የተረፈውንም በብዙ ቅርጫቶች አነሣን ይህም ሁሉ ሲሆን አላመኑም።

#ጌታ_ኢየሱስም እንዲህ አለው ይህን ያደረገ በግልጥ ነው ወይስ በሥውር። እንድርያስም እንዲህ አለው ይህንስ በግልጥ ነው ያደረገ በሥውር ያደረገውም አለ ግን የምትፈትነኝ መሰለኝ #ጌታችንም እንዲህ አለው ወንድሜ ሆይ ልቤን ደስ ስለሚላት ነውና ንገረኝ።

እንድርያስም እንዲህ አለው ልጄ ሆይ በጎ ሥራህን ሀሉ #እግዚአብሔር ይፈጽምልህ አሁንም ስማ #ጌታችን ያደረገውን ተአምር እኛ ዐሥራ ሁለታችን ሐዋርያቶቹ ከእርሱ ጋራ ስንጓዝ ከሊቃነ ካህናትና ከሕዝቡ ብዙዎች አሉ። ወደ ምኵራብም ደረስን #ጌታችንም እንዲህ አለ በሰማይ ባሉ በኪሩቤልና በሱራፌል አምሳል በምድር ላይ ሰው የሠራትን ይቺን የተቀረጸች ሥዕል ታያላችሁን።

ከዚህም በኋላ ወደሥዕሊቱ ተመልሶ ብልህ ሰው የተጠበበብሽ የሰማያውያን መልክን ያደረግሽ አንቺን እላለሁ ከቦታሽ ተነቅለሽ ውረጂ የካህናት አለቆችንም ወቀሻቸው እኔም ዕሩቅ ብእሲ ወይም #እግዚአብሔር እንደሆንኩ መስክሪ አላት። ወዲያውኑ ከቦታዋ ተነቅላ ወረደች እንደሰውም በመናገር እንዲህ አለች እናንተ የደነቆራችሁ አይሁድ የራሳችሁ መደንቆር ያልበቃችሁ ሌሎችንም ለማደንቆር የምትሹ ለድኅነታችሁ ሰው የሆነ #እግዚአብሔርን እንዴት ዕሩቅ ብእሲ ትሉታላችሁ አስቀድሞ ሰውን የፈጠረው በንፍሐት ልጅነትንም የሰጠው ይህ ነው።

አብርሃምን የተናገረው፣ ይስሐቅንም ከመታረድ ያዳነው፣ ያዕቆብንም ወደ አገሩ ያስገባው ይህ ነው ለሚፈሩት በረከትን የሚሰጥ ለማይታዘዙለት ቅጣትን የሚያዘጋጅ ይህ ነው ።

እውነት እነግራችኋላሁ እናንተ ስለምትክዱት ሕጉንና ሥርዓቱንም ትለውጣላችሁና ስለዚህ እነሆ መስዋዕታችሁ ይሻራል ምኵራቦቻችሁም በዋሕድ ወልደ #እግዚአብሔር ስም አብያተ ክርስቲያናት ይሆናሉ። ይህንንና የሚመስለውን ተናግራ ዝም አለች።

እኛም የካህናት አለቆችን መልሰን እንዲህ አልናቸው እነሆ ቅርጺቱ ሥዕል ተናግራ ወቀሰቻችሁ ታምኑ ዘንድ ይገባችኋል። የካህናት አለቆችና አይሁድም እንዲህ አሉን ይህ የሚያናግረው በሥራይ ነው አብርሃምን በወዴት አገኘው ከሞተ ዘመኑ ብዙ ነውና።

#ጌታ_ኢየሱስም ወደ ቅርጺቱ መለስ ብሎ እንዲህ አላት አብርሃምን እንዳነጋገርኩት አላመኑምና ሔደሽ እንዲህ በይው። አስቀድሞ አዳምን የፈጠረው፣ አንተንም ወዳጁ ያደረገህ፣ አንተ ልጆችህ ይስሐቅና ያዕቆብን ይዘህ ተነሥ ከመቃብርም ወጥተህ ወደዚህ ኑ የካህናት አለቆችን ትወቅሱአቸው ዘንድ እኔ የማውቃችሁና የተነጋገርኳችሁ መሆኔን አስረዷቸው። ቅርጺቱም ሥዕል ይህን ሰምታ እያየናት ሔደች ወደ አብርሃምም መቃብር ደርሳ በውጭ ቁማ ጠራቻቸው። ወዲያውኑ ከሦስቱ አርእስተ አበው ጋር ዐሥራ ሁለቱ ወጡ ከእኛ ውስጥ ወደ ማን ነው የተላክሽ አሏት። ቅርጺቱም እንዲህ ብላ መለሰች ወደ ሦስቱ የአባቶች አለቆች ነው እናንተ ግን እስከ ትንሣኤ ሙታን ድረስ ተኙ ያን ጊዜም ወደ መቃብራቸው ተመለሱ።
እሊህ ሦስቱ አባቶችም የካህናት አለቆችና እኛ ወደ አለንበት ከቅርጺቱ ሥዕል ጋር መጥተው ወቀሷቸው የ #እግዚአብሔር ልጅ እንደሆነም ነገሩአቸው።

ከዚህም በኋላ #ጌታችን አባቶችን ወደቦታችሁ ሒዱ አላቸው ወዲያው ተመለሱ ቅርጺቱንም ወደቦታሽ ተመለሽ አላት እርሷም ወደ ቀደመው አኗኗርዋ ተመለሰች ይህንንም አይተው የካህናት አለቆች አላመኑም ሌላም ብዙ አለ ብነግርህ መወሰን አትችልም ነገር ግን ለብልህ ጥቂት ቃል ትበቃዋለች ለሰነፍ ግን ቢነግሩት በቁም ነገር ላይ አይታመንም።

ከዚህም በኋላ #ጌታችን ማነጋገሩን ገታ ራሱንም እንደሚያንቀላፋ አደረገ እንድርያስም አንቀላፋ እንድርያስንና ደቀ መዛሙርቱን እንዲሸከሙአቸውና ሊገቡበት ወደሚሹት አገር በውጭ እንዲአኖሩዋቸው መላእክትን አዘዛቸው።

ከዚህም በኋላ እንድርያስ በነቃ ጊዜ ዐይኖቹን ገለጠ የከተማውንም በር ተመለከተ በየብስም ላይ እንዳለ አውቆ ደነገጠ አደነቀም። ደቀ መዛሙርቱንም አነቃቸውና እንዲህ አላቸው #ጌታችንን በባሕር ላይ ሳለን ያላወቅነው ምን አደረገብን ሲፈትነን መልኩን ለውጦ እንደ ሰው ሁኖ ታይቶናልና።

ደቀ መዛሙርቱም እንዲህ አሉት እኛም በጌትነቱ ዙፋን ላይ ሁኖ የመላእክት ሠራዊት ሁሉ በዙሪያው ሁነው #ጌታችንን አየነው አብርሃምን፣ ይስሐቅን፣ ያዕቆብንም ቅዱሳንን ሁሉ አየናቸው ንጉሥ ዳዊትም በመሰንቆ ይዘምር ነበር። እናንተንም ዐሥራ ሁለት ሐዋርያት በፊቱ ቁማችሁ ዐሥራ ሁለቱንም የመላእክት አለቆች በፊታችሁ ሌሎች መላእክት በኋላችሁ ሁነው አየናችሁ። #እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስንም መላእክትን እንዲህ ብሎ ሲያዛቸው ሰማነው የሚሉአችሁን ሁሉ ሐዋርያትን ስሟቸው።

እንድርያስም በሰማ ጊዜ እጅግ ደስ አለው ይህን ድንቅ ምሥጢር ያዩ ዘንድ ደቀ መዛሙርቱ የሚገባቸው ሆነዋልና። ከዚህም በኋላ እንድርያስ ዐይኖቹን ወደ ሰማይ አቅንቶ እንዲህ ብሎ በታላቅ ድምጽ ጮኸ #ጌታዬ_ኢየሱስ_ክርስቶስ ሆይ ከእኛ ከባሮችህ ሩቅ እንዳልሆንክ አወቅሁ። ነገር ግን በመርከብ ላይ እኔ እንደማስተምረው ሰው መስለኸኝ በድፍረት ተናግሬሃለሁና #ጌታዬ ይቅር በለኝ ።

በዚያንም ጊዜ የክብር ባለቤት #መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ለእንድርያስ ዳግመኛ ተገለጠለት እንዲህም አለው። አዎን እኔ ነኝ በሊቀ ሐመር አምሳል በባሕር ውስጥ የተገለጥኩልህና መርከቡን የቀዘፍኩልህ። አትፍራ አትደንግጥ እኔ ከአንተ ጋራ እኖራለሁ ይህንንም ብሎ ወደ ሰማያት በክብር ዐረገ እንድርያስም መንገዱን ሄደ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጌቶቻችን ሐዋርያት በጸሎታቸው ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ጻድቋ_ቅድስት_ዜና_ማርያም

በዚህች ዕለት የእናታችን ቅድስት ዜና ማርያም የእረፍቷ መታሰቢያ ነው፡፡ ከአባቷ ከገብረ ክርስቶስ ከእናቷ አመተ ማርያም በ11መቶ ክፍለ ዘመን በቅዱስ ላሊበላ ዘመነ መንግሥት በምድ ነጋሲ በጎጃም ምድር ግንቦት 30 ቀን የተወለደች ሲሆን ለአቅመ ሔዋን በደረሰች ጊዜ በንፅህ ድንግልና በምድረ ሂንፍራንስ ጣራ ገዳም አካባቢ በሚገኘው በአቡነ እንድርያስ ዋሻ ለ25ዓመት በጾም በፀሎት ምንም አይነት የላመ የጣፈጠ እህል ሳትቀምስ በቅል ውስጥ የሚገኘውን መራራ ፍሬ ከኮሶ ጋር በአንድነት ደርጣ (አዋህዳ) በመዘፍዘፍ ከ3 ቀን በኃላ በመመገብ እስከ ሕይወቷ ፍጻሜ ድረስ #ጌታችን_አምላካችን_መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ በቀራንዮ አደባባይ ላይ የቀመሰውን መራራ ሐሞትን በማሰብ ሙሉ ሕይወቶን እየተመገበች ታላቅ ተጋድሎዋን ፈፅማለች፡፡ ከዚህ የተነሳ ሸክላ ማርያም ተብላ ትጠራ የነበረችው ቦታ ስያሜ ተቀይሮ ደሪጣ ዜና ማርያም ዋሻ ተብሎ እስከ አሁን ድረስ በስሞ እየተጠራ ይገኛል፡፡

ከአቡነ እድርያስ ዋሻ በመቀጠል ከአዲስ አበባ ተነስተን ስንጓዝ አዲስ ዘመን ከተማ በስተቀኝ በኩል ተገንጥለን 15ኪሜ ያክል የጥርጊያ መንገድ እንደተጓዝን በስሞ የተሰየመውን ደሪጣ ጻድቋ ቅድስት ዜና ማርያም ገዳም ላይ ቀሪ ሕይወቷን ምንም አይነት ዋሻ ባልነበረበት በከፍተኛ ተራራ ላይ እጅግ አስቸጋሪ ቀዝቃዛ አየር ባለበት ብርዱን፣ ፀሐዩን፣ ቁሩን፣ ረኃቡንና ጥሙን በመቋቋም ራቁቶን በመሆን መራራ ምግቦችን አዋህዳ በመመገብ በጾም በፀሎት በመትጋት አስቸጋሪ የሆነውን ተጋድሎዋን በመፈፀም በዚሁ በተቀደሰ ስፍራ በዚህች ቀን በታላቅ ክብር አርፋለች፡፡

በዚህም ወቅት #ጌታችን_አምላካችን_መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ከእናቱ ከቅድስት #ድንግል_ማርያምና ከእልፍ አላፋት ቅዱሳ መላዕክት ጋር እንዲሁም ከሐዋርያት ፣ ከሰማዕታት ፣ ከጻድቃን ፣ ከደናግል ጋር በመሆን ከሰማይ በመውረድ በታላቅ ክብር ዕረፍቷን አክብሮላታል ታላቅ ኪዳንም ገብቶላታል፡፡

በዚሁ በተቀደሰ ስፍራ ላይ ወይንም በአሁኑ ሰዓት መቃብሯ በሚገኝበት ዋሻ ቤተመቅደስ አካባቢ በተጋድሎዋ ጊዜ ራቁቷን በሆነች ሰዓት መላ ገላዋን የሸፈነላት ፀጉር በእየ ዛፎቹ ላይ እስከ አሁን ድረስ አለ ፡፡ ይህም የጸጉር አምሳያ ከገዳሙ በመውሰድ ብዙ ሰዎች በቤታቸው በመታጠን ከአስም እንዲሁም ከተለያዩ በሽታዎች እየተፈወሱና እየዳኑ ሲሆን ታላላቅ ታምራትን እያደረገ ይገኛል፡፡

በዚህ ገዳም ከሌሎች ገዳማት ለየት የሚያደርገው ታሪክ #ጌታችን_አምላካችን_መድኃኒታችንን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ከሰማይ በመውረድ ራሱ የባረከው ልዩ ታሪክ ያለው ጠበል የሚገኝ ሲሆን ይህም ጠበል በቦታው ላይ ሆኖ የተጠመቀ ፣ የጠጣ ፣ አልያም በአለበት ቦታ ሆኖ የተጠቀመ እስከ አሁን ድረስ መካን የሆኑ ሰዎች በፍጥነት ልጅ የሚያገኙ ከመሆናቸው ባሻገር ከማንኛውም ከተለያዩ በሽታዎች በመፈወስ ታላላቅ ታምራትን እየሰራ ይገኛል፡፡

በ11ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ቅዱስ ላሊበላ በ #ጌታችን_በአምላካችን_በመድኃኒታችን_በኢየሱስ_ክርስቶስ ትዕዛዝ መሰረት ወደዚሁ ታላቅ ስፍራ በመምጣት የጻድቋ ማረፈያ/መታሰቢያ ዋሻ ቤተ መቅደስ በመፈልፈል የሰራላት ሲሆን በመቀጠል አፄ ይስሐቅ በ14ተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ይህን ገዳም በስሟ በመገደም በዚሁ ዋሻ ውስጥም የጻድቋ የቅድስት ዜና ማርያም መቃብሯ እንዲሁም የመታሰቢያዋ ፅላት የሚገኝ ከመሆኑ አንጻር በአካባቢው ያሉት ሕዝበ ክርስትያን ከካህናት ጋር በመሆን ሥርዓተ አምልኮ በመፈፀም እየተገለገሉበት ይገኛሉ፡፡

ይህ ዋሻም አስቀድሞ ሦስቱ ቅዱሳን ማለትም አቡነ እንድርያስ ዘጣራ ገዳም ፣አቡነ ተክለኃይማኖት ዘደብረ ሊባኖስ፣ ጻድቋ ቅድስት ዜናማርያም ዘደሪጣ ውስጥ ለውስጥ በ #መንፈስ_ቅዱስ ገላጭነት በፀጋ #እግዚአብሔር ይገናኙበት የነበረ ሲሆን በአሁን ሰዓትም #እግዚአብሔር የመረጣቸው ቅዱሳን ይመላለሱበታል፡፡

ለጻድቋ ቅድስት ዜና ማርያም የተሰጠ ቃል ኪዳን #እግዚአብሔር አምላክ መርጦና ፈቅዶ በጻድቋ አማላጅነት ካለበት ስፍራ ተነስቶ የጻድቋ ደጃን የረገጠ ለ3 ግመል ጭነት ጤፍ ወይም የሦስት አህያ ጤፍ ያህል ነፍሳትን እምርልሻለሁ፤ ከሲዖልም እሳት ነፍሳትን አወጣልሻለሁ የሚል ቃል ኪዳን ለጻድቋ ቅድስት ዜና ማርያም ተሰቶታል።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጌቶቻችን ሐዋርያት በጸሎታቸው ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ነሐሴ_30#ከገድላት_አንደበት_ግንቦት_30)
2024/09/21 13:50:08
Back to Top
HTML Embed Code: