Telegram Web Link
ከዚህ በኋላም ዜናቸው በመስከረም ወር በዐሥራ ሰባት የተጻፈ በከበሩ ቦታዎች ውስጥ አብያተ ክርስቲያናትን ትሠራ ዘንድ ጀመረች። ለአባ መቃርስም በከበሩ ቦታዎች ሁሉ አብያተ ክርስቲያናትን እንዲሠራ ብዙ ገንዘብ ሰጠችው።

ከዚህ በኋላ ወደ ልጇ ተመልሳ የሆነውን ሁሉ ነገረችው የከበረ #መስቀል በመገኘቱ እጅግ ደስ አለው።

ይቺም ቅድስት በጎ ገድሏን ከፈጸመችና #እግዚአብሔርንም ከአገለገለች በኋላ ስለ ካህናትም ልብስና ቀለብ ለአብያተ ክርስቲያናትና ለገዳማት ብዙ ጉልቶችና ርስቶችን ለድኆችና ለምስኪኖችም እንዲሁ ከሠራችና ከተከለች በኋላ በሰላም ግንቦት ዘጠኝ ቀን አርፋለች መላ ዕድሜዋም ሰማንያ ሆነ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎታቸው ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ይኑር ለዘላለሙ አሜን ።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ነሐሴ_21_እና_ግንቦት_9)
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ነሐሴ_21_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ቆሮንቶስ 7
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²⁵ ስለ ደናግልም የጌታ ትእዛዝ የለኝም፥ ነገር ግን የታመንሁ እሆን ዘንድ ከጌታ ምሕረትን የተቀበልሁ እንደ መሆኔ ምክር እመክራለሁ።
²⁶ እንግዲህ ስለ አሁኑ ችግር ይህ መልካም ይመስለኛል፤ ሰው እንዲህ ሆኖ ቢኖር መልካም ነው።
²⁷ በሚስት ታስረህ እንደ ሆንህ መፋታትን አትሻ፤ በሚስት አልታሰርህ እንደ ሆንህ ሚስትን አትሻ።
²⁸ ብታገባ ግን ኃጢአት አትሠራም ድንግሊቱም ብታገባ ኃጢአት አትሠራም፤ ነገር ግን እንዲህ በሚያደርጉ በሥጋቸው ላይ መከራ ይሆንባቸዋል፥ እኔም እራራላችሁ ነበር።
²⁹ ዳሩ ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ይህን እናገራለሁ፤ ዘመኑ አጭር ሆኖአል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሚስቶች ያሉአቸው እንደሌላቸው ይሁኑ፥
³⁰ የሚያለቅሱም እንደማያለቅሱ፥ ደስ የሚላቸውም ደስ እንደማይላቸው፥
³¹ የሚገዙም ምንም እንደሌላቸው፥ በዚችም ዓለም የሚጠቀሙ በሙሉ እንደማይጠቀሙባት ይሁኑ፤ የዚች ዓለም መልክ አላፊ ነውና።
³² ነገር ግን ያለ አሳብ ልትኖሩ እወዳለሁ። ያላገባው ጌታን እንዴት ደስ እንዲያሰኘው የጌታን ነገር ያስባል፤
³³ ያገባው ግን ሚስቱን እንዴት ደስ እንዲያሰኛት የዓለምን ነገር ያስባል፥ ልቡም ተከፍሎአል።
³⁴ ያልተጋባች ሴትና ድንግል በሥጋም በነፍስም እንዲቀደሱ የጌታን ነገር ያስባሉ፤ የተጋባች ግን ባልዋን እንዴት ደስ እንድታሰኘው የዓለምን ነገር ታስባለች።
³⁵ ይህንም ለራሳችሁ ጥቅም እላለሁ፤ በአገባብ እንድትኖሩ ሳትባክኑም በጌታ እንድትጸኑ ነው እንጂ ላጠምዳችሁ ብዬ አይደለም።
³⁶ ዳሩ ግን ማግባት ወደሚገባው ዕድሜ በደረሰ ጊዜ ስለ ድንግልናው ያፈረ ሰው ቢኖር፥ የወደደውን ያድርግ፤ ኃጢአት የለበትም፤ ይጋቡ።
³⁷ ሳይናወጥ በልቡ የጸና ግን ግድ የለበትም፥ የወደደውን እንዲያደርግ ተፈቅዶለታል፤ ድንግልናውንም በልቡ ይጠብቅ ዘንድ ቢጸና፥ መልካም አደረገ።
³⁸ እንዲሁም ድንግልን ያገባ መልካም አደረገ ያላገባም የተሻለ አደረገ።
³⁹ ሴት ባልዋ በሕይወት ሳለ የታሰረች ናት፤ ባልዋ ቢሞት ግን በጌታ ይሁን እንጂ የወደደችውን ልታገባ ነጻነት አላት።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
2ኛ ዮሐንስ 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹-² በእኛ ስለሚኖርና ከእኛ ጋር ለዘላለም ስለሚሆን እውነት፥ እኔ ሽማግሌው በእውነት ለምወዳቸውና እኔ ብቻ ሳልሆን እውነትን የሚያውቁ ሁሉ ደግሞ ለሚወዱአቸው ለተመረጠች እመቤትና ለልጆችዋ፤
³ ከእግዚአብሔር አብና ከአብ ልጅ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ምሕረት ሰላምም በእውነትና በፍቅር ከእኛ ጋር ይሆናሉ።
⁴ ትእዛዝን ከአብ እንደ ተቀበልን ከልጆችሽ በእውነት የሚሄዱ አንዳንዶችን ስለ አገኘኋቸው እጅግ ደስ ብሎኛል።
⁵ አሁንም፥ እመቤት ሆይ፥ እርስ በርሳችን እንድንዋደድ እለምንሻለሁ፤ ይህች ከመጀመሪያ በእኛ ዘንድ የነበረች ትእዛዝ ናት እንጂ አዲስ ትእዛዝን እንደምጽፍልሽ አይደለም።
⁶ እንደ ትእዛዛቱም እንሄድ ዘንድ ይህ ፍቅር ነው፤ ከመጀመሪያ እንደ ሰማችሁ፥ በእርስዋ ትሄዱ ዘንድ ትእዛዙ ይህች ናት።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 16
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹³ በሰንበት ቀንም ከከተማው በር ውጭ የጸሎት ስፍራ በዚያ መሆኑን ስላሰብን ወደ ወንዝ አጠገብ ወጣን፤ ተቀምጠንም ለተሰበሰቡት ሴቶች ተናገርን።
¹⁴ ከትያጥሮን ከተማም የመጣች ቀይ ሐር ሻጭ እግዚአብሔርን የምታመልክ ልድያ የሚሉአት አንዲት ሴት ትሰማ ነበረች፤ ጳውሎስም የሚናገረውን ታዳምጥ ዘንድ ጌታ ልብዋን ከፈተላት።
¹⁵ እርስዋም ከቤተ ሰዎችዋ ጋር ከተጠመቀች በኋላ፦ በጌታ የማምን እንድሆን ከፈረዳችሁልኝ፥ ወደ ቤቴ ገብታችሁ ኑሩ ብላ ለመነችን፤ በግድም አለችን።
¹⁶ ወደ ጸሎት ስፍራም ስንሄድ፥ የምዋርተኝነት መንፈስ የነበረባት ለጌቶችዋም እየጠነቈለች ብዙ ትርፍ ታመጣ የነበረች አንዲት ገረድ አገኘችን።
¹⁷ እርስዋ ጳውሎስንና እኛን እየተከተለች፦ የመዳንን መንገድ የሚነግሩአችሁ እነዚህ ሰዎች የልዑል አምላክ ባሪያዎች ናቸው ብላ ትጮኽ ነበር።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ነሐሴ_21_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"አዋልደ ንግሥት ለክብርከ። ወትቀውም ንግሥት በየማንከ። በአልባሰ ወርቅ ዑጽፍት ወኊብርት"። መዝ 44፥9።
“የንጉሦች ሴት ልጆች ለክብርህ ናቸው፤ በወርቅ ልብስ ተጐናጽፋና ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች።” መዝ 44፥9።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ነሐሴ_21_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ማቴዎስ 25
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ በዚያን ጊዜ መንግሥተ ሰማያት መብራታቸውን ይዘው ሙሽራውን ሊቀበሉ የወጡ አሥር ቆነጃጅትን ትመስላለች።
² ከእነርሱም አምስቱ ሰነፎች አምስቱም ልባሞች ነበሩ።
³ ሰነፎቹ መብራታቸውን ይዘው ከእነርሱ ጋር ዘይት አልያዙምና፤
⁴ ልባሞቹ ግን ከመብራታቸው ጋር በማሰሮአቸው ዘይት ያዙ።
⁵ ሙሽራውም በዘገየ ጊዜ ሁሉ እንቅልፍ እንቅልፍ አላቸውና ተኙ።
⁶ እኩል ሌሊትም ሲሆን፦ እነሆ፥ ሙሽራው ይመጣል፥ ትቀበሉት ዘንድ ውጡ የሚል ውካታ ሆነ።
⁷ በዚያን ጊዜ እነዚያ ቆነጃጅት ሁሉ ተነሡና መብራታቸውን አዘጋጁ።
⁸ ሰነፎቹም ልባሞቹን፦ መብራታችን ሊጠፋብን ነው፤ ከዘይታችሁ ስጡን አሉአቸው።
⁹ ልባሞቹ ግን መልሰው፦ ምናልባት ለእኛና ለእናንተ ባይበቃስ፤ ይልቅስ ወደሚሸጡት ሄዳችሁ ለራሳችሁ ግዙ አሉአቸው።
¹⁰ ሊገዙም በሄዱ ጊዜ ሙሽራው መጣ፥ ተዘጋጅተው የነበሩትም ከእርሱ ጋር ወደ ሰርግ ገቡ፥ ደጁም ተዘጋ።
¹¹ በኋላም ደግሞ የቀሩቱ ቈነጃጅት መጡና፦ ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ፥ ክፈትልን አሉ።
¹² እርሱ ግን መልሶ፦ እውነት እላችኋለሁ፥ አላውቃችሁም አለ።
¹³ ቀኒቱንና ሰዓቲቱን አታውቁምና እንግዲህ ንቁ።
¹⁴ ወደ ሌላ አገር የሚሄድ ሰው ባሮቹን ጠርቶ ያለውን ገንዘብ እንደ ሰጣቸው እንዲሁ ይሆናልና፤
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #እመቤታች_የማርያም ቅዳሴ ነው፡፡ መልካም በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ልመናዋ ክብሯዋ የልጇም ቸርነት በሁላችን ላይ ለዘለዓለም በእውነት ይደርብንና አምላክን የወለደች በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ የጸናች ክብርት #እመቤታችን ያደረገችው ተአምር ይሕ ነው።

ብዙ ንብ ያለው አንድ ሰው ነበረና ከሰው ሁሉ ይልቅ ፈጽሞ ንቡ ይበዛለት ዘንድ ይወድ ነበር። ወደ አንዲት ስራየኛ ሴት ሒዶ ንቤ ይበዛልኝ ዘንድ ማርም ሰምም ከሰው ሁሉ ይልቅ ይበዛልኝ ዘንድ የምሠራውን ሥራ እንድትመክሪኝ እለምንሻለሁ አላት። ያችም ሰራየኛ ሴት እኔስ #ሥጋውን _ደሙን በተቀበልህ ጊዜ ካፍህ አውጥተህ በዚያ ቀፎ ወስጥ ጨምረው። ብዙ ንብ ሰምና ማርም ይሆንልሃል ብዬ እመክርሃለሁ አለችው። በሁለተኛውም ቀን ወደ ቤተ ክርስትያን ሒዶ #ሥጋውን_ደሙን ተቀብሎ እንደ ነገረችው አደረገና ካፉ አውጥቶ በንቡ ውስጥ ጨምሮ አንዲት ሰዓት እልፍ አለ።

ሁለተኛም ንብ ወዳለበት በተመለሰ ጊዜ ሥጋውን ካስቀመጠበት ከዚያ ቀፎ ውስጥ እጅግ ፍጹም ብርሃንና የ #እመቤታችን ሥዕል በዚያ ቀፎ ውስጥ በንቦች መካከል ተቀምጣ አየ። በደረቷም ከፀሐይና ከጨረቃ የሚያበራ ልጅ ታቅፋ ነበር። ይሕን ምልክት ባየ ጊዜ ጽኑዕ ፍርሃት ፈራና ወደ ቄስ ሒዶ ያደረገውን ሁሉ በቀፎ ውስጥም ያየውን ነገረው፤ ቄሱ ግን ነገሩን አልተቀበለውም ነበር። ነገር ግን ያሳየህን ተመልከት እይ ብሎ አንድ ዲያቆን ከእርሱ ጋራ ላከ። ዲያቆኑም ሒዶ ያ ሰው እንደተናገረው አይቶ በፍጹም ፍርሃት ተመልሶ ያየውን ለቄሱ ነገረው።

ቄሱም ይሕን ነገር ሰምቶ ሕዝቡ ሁሉ በፍጹም ተድላ ደስታ ይሰበሰብ ዘንድ አዘዛቸውና ወደዚያ ቦታ ደረሱ። ያም ቄስ ወደዚያ ቀፎ ቀረበና ያን ፍጹም ብርሃን አይቶ #ድንግል ንጽሕት እመቤታችንም ሕፃኑን አቅፋ በብዙ ንቦች መካከል አይቶ ፈጽሞ ፈራ። ቀፎውንም ተሸክመው ወስደው በታቦቱ ላይ ያኖሩት ዘንድ አዘዘ ያችንም ሥዕል አውጥቶ በመንበሩ ላይ አስቀመጣት። እስከ ፍታቴ ድረስ ይቀደስ ዘንድ አዘዘ ሥዕሊቱም ተመልሳ በታቦቱ ላይ ባለ ሥጋው አደረች። ቅዳሴው እንደ ታዘዘ ተፈጸመ።

ይችም ምልክት ባራቱ ማዕዘን ሁሉ ተረዳች። የሰሙም ሁሉ አደነቁ። #እግዚአብሔርን አምሰገኑት አምላክን የወለደች በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ የጸናች ክብርት #እመቤታችንንም አመሰገኗት።

ልመናዋ ክብሯም በእኛ ለዘለዓለም በእውነት ይደርብን።
#ደብረ_ጥሉል_አቡነ_አብራኒዮስ ገዳም!

በዐፄ ሱስንዮስ ዘመን የነበረውን የቤተ ክርስቲያንን ጥፋት ላለማየት ሳይወለዱ በእናታቸው ማኅፀን 7 ዓመት ከ6 ወር የቆዩት አቡነ አብራኒዮስ ነሐሴ 21 ቀን በዓመታዊ የዕረፍት በዓላቸው ታስበው ይውላሉ፡፡ አባታቸው ወልደ ክርስቶስ እናታቸው ወለተ ትንሣኤ የሚባሉ ደጋግ ክርስቲያኖች ናቸው፡፡ የተወለዱት በ1624 ዓ.ም ምሥራቅ ጎጃም አካባቢ ልዩ ስሙ እነብሴ ይሁን እንጂ ተጋድሏቸውን ያደረጉትና ገዳማቸውን የገደሙት በዛሬዋ ኤርትራ ውስጥ ነው፡፡ ገዳሙ ኤርትራ ውስጥ ዞባ ድባርዋ ደቂ ድግና በተባለ አካባቢ ይገኛል፡፡ የገደሙት ጻድቁ በ1705 ዓ.ም ነው፡፡

አቡነ አብራኒዮስ የተፀነሱት በመልአኩ በቅዱስ ገብርኤል አብሳሪነት ነው፡፡ ነገር ግን ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት ጻድቁ በዐፄ ሱስንዮስ ዘመን የነበረውን የቤተ ክርስቲያንን ጥፋት ላለማየት ሳይወለዱ በእግዚአብሔር ፈቃድ በእናታቸው ማኅፀን 7 ዓመት ከ6 ወር ተቀምጠዋል፡፡ በዚህም ወቅት እሳት ልትጭር ከጎረቤቷ የመጣች አንዲት ሴት የአቡነ አብራኒዮስ እናት ‹‹የማትወልጂው ምን ሆነሽ ነው?›› ብላ ስትናገር ጻድቁ በእናታቸው ማኅፀን ሆነው ‹‹…ለምን ክፉ ትናገሪያለሽ?› ብለው መልስ ሰጥተዋታል፡፡ ይህም ቅዱሳን ልክ እንደ ነቢዩ ኤርምያስ ገና በእናታቸው ማኅፀን ሳሉ እንደሚመረጡ አንድ ማሳያ ነው፡፡

በርካታ ምእመናንን በሰማዕትነት ከገደሉ በኋላ በመጨረሻም ዐፄ ሱስንዮስ በመቅሰፍት ተመተው ሊሞቱ ሲሉ ‹‹ሃይማኖት ይመለስ፣ ፋሲል ይንገሥ›› ብለው የቤ/ክ ሰላም መልሰው ንስሓ ገብተው ሞቱ፡፡ አቡነ አብራኒዮስም ይህ የቤ/ክ የመከራ ዘመን ሲያልፍና ሃይማኖት ሲመለስ ተወለዱ፡፡ ገና በ5 ዓመታቸው ከጥንቆላ መጻሕፍት በቀር ሁሉንም የቤ/ክ መጻሕፍትንና ምሥጢራትን ሁሉ ተምረው ዐወቁ፡፡ በ12 ዓመታቸው መነኮሱ፡፡ ዲቁና ሲሾሙም ጳጳሱ ‹‹ገና ሕፃን ነው፣ አሁን አልሾመውም›› ሲሉ የሰማይ መላእክት ‹‹ይባዋል›› ብለው መስክረውላቸዋል፡፡

በልጅነታቸውም መነኮሳቱ ወደ ጫካ ሔደው ዕንጨት እንዲሰብሩ ሲያዟቸው ጌታችን ግን ለአቡነ አብራኒዮስ ኃይል ሰጥቷቸው በነፋስ ሠረገላ እየሔዱ የ6 ሰዓቱን የእግር መንገድ እሳቸው ግን ዕንጨቱን ሰብረው በቶሎ ይመለሱ ነበር፡፡ ይህም ሲታወቅባቸው ውዳሴ ከንቱን ንቀው ከዚያ ገዳም ወጥተው ወደ አቡነ ተጠምቀ መድኅን ዘንድ ሔዱ፡፡ በዚያም በታላቅ ተጋድሎ ከኖሩ በኋላ አቡነ ተጠምቀ መድኅን ‹‹በአንተ ምክንያት ብዙ ነፍሳት ይድናሉ፣ ክፍልህ በዚያ ነው›› ብለው አሁን ገዳማቸውን ወደገደሙበት ቦታ (ኤርትራ) ላኳቸው፤ ሲመጡም ቅዱስ ሚካኤልና ቅዱስ ገብርኤል እየመሯቸው እንደመጡ ገድላቸው ይናገራል፡፡ ጻድቁ ወደዚህ ገዳም ሲመጡ በፊት ይቀመጡባት የነበረችው ትልቅ ድንጋይ በተኣምር ከመሬት 7 ክንድ ከፍ ብላ አብራቸው መጥታለች፡፡ ድንጋይዋ ዛሬም ድረስ በገዳማቸው በክብር ስለተቀመጠች ምእመናን እየዳሰሷት ይባረኩባታል፣ መካኖች ይወልዱባታል፣ ሕሙማን ይፈወሱባታል፡፡

አቡነ አብራኒዮስ በቅዳሴ ጊዜ ጌታችንን በዕለተ ዐርብ እንደተሰቀለ ሆኖ ይመለከቱት ስለነበር በኀዘን በተመስጦ ሆነው ይቆዩም ስለነበር ሕዝቡም ‹‹በቅዳሴ ሰዓት ይተኛል›› እያሉ ያሟቸው ነበር፡፡ ከዚህም በኋላ ጻድቁ ወደ አካለ ጉዛይ በመሔድ በዘንዶ ላይ አድሮ ይመለክ የነበረውን ሰይጣን በጸሎታቸው አጥፍተው ዘንዶውን ገድለው ሕዝቡንም አስተምረው በንስሓ መልሰው አጥምቀዋቸዋል፡፡ ወደ ታላቁ ገዳም ደብረ ቢዘንም ሲሔዱ 6400 አጋንንትን አግኝተው በጸሎታቸው አጥፍተዋቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት አቡነ አብራኒዮስ ‹‹ሰዳዴ አጋንንት-አጋንንት አባራሪ›› ተብለዋል፡፡

አቡነ አብራኒዮስ ወደ ሌላ ቦታ ሔደው ሰለዳዋ የምትባል ቦታ ላይ ሆነው ሳለ አንድ ሰው ወደ ገዳማቸው ገብቶ አንዲትን ዛፍ ሲቆርጥ በመንፈስ ቅዱስ መነጽርነት አዩት፡፡ ቆራጩም ሰው ‹‹ተው አትቁረጥ›› የሚል የአባታችንን ድምፅ ሰማ፣ በአካል የሉም ብሎ እምቢ አለ፣ ነገር ግን በመቅሠፍት ተመቶ ወዲያው ሞተ፡፡ በአንድ ዕለትም ልጃገረዶች እየዘፈኑ ሲሔዱ ብዙ አጋንንት በዘፈናቸው ተደስተው አብረዋቸው ሲጨፍሩ አባታችን በመንፈስ ተመልክተው ለልጃገረዶቹ ዘፈን የአጋንንት መሆኑን እንዳስተማሯቸው ገድላቸው ይናገራል፡፡

ለአቡነ አብራኒዮስ ክብርት እመቤታችን ተገልጻ ‹‹ቤተ ክርስቲያን በስሜ አንጽልኝ›› አለቻቸው፡፡ እርሳቸውም ውብ አድርገው በእመቤታችን ስም አነጹ ነገር ግን ፍጻሜውን ሳያዩ በዕለተ ቀኗ ነሐሴ 21 ቀን ዐረፉ፡፡ በዕረፍታቸውም ወቅት ጌታችን ተገልጦ ታላቅ ቃልኪዳን ሲሰጣቸው ‹‹...ዋስ እፈልጋለሁ፣ ዋስ ስጠኝ›› አሉት፡፡ ጌታችንም ‹‹ሐዋርያት፣ ሰማዕታት፣ ከአንተ በፊት የነበሩ ጻድቃን ያልጠየቁኝን አንተ እንዴት ጠየከኝ?›› አላቸው፡፡ እርሳቸውም ‹‹አምላኬ ሆይ! አንተ መሐሪና በጽድቅ ፈራጅ ቃልህም የማይለወጥ እንደሆንክ አውቃለሁ›› አሉት፡፡ ጌታችም ፍግግ ብሎ ‹‹ይሁን የምትሻውን አላሳጣህም›› በማለት ከፈጣሪ በታች ከፍጡራን በላይ የሆነች ክብርት እመቤታችንንና ሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስን ዋስ አድርጎ ቃልኪዳን ከገባላቸው በኋላ ነሐሴ 21 ቀን 1713 ዓ.ም በሰላም ዐረፉ።

የታላቁ ጻድቅ አቡነ አብራኒዮስ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን፣ በጸሎታቸው ይማረን!!!
✞ ✞ ✞
#ነሐሴ_22

#ነቢዩ_ሚክያስ

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ነሐሴ ሃያ ሁለት በዚህች ቀን ታላቅ ነቢይ የሞራት ልጅ ሚክያስ አረፈ። ይህም ነቢይ በይሁዳ ነገሥታት በኢዮአታም፣ በአካዝና በሕዝቅያስ ዘመን ትንቢት በመናገር አስተማረ።

ስለ #ጌታችን መውረድም እንዲህ አለ። እነሆ #እግዚአብሔር ከልዑል መንበሩ ወደዚህ ዓለም ይወርዳል ።

ሁለተኛም ስለ ልደቱ እንዲህ ብሎ ትንቢት ተናገረ የኤፍራታ ዕጣ የምትሆኚ አንቺም ቤተ ልሔም የእስራኤል ነገሥታት ከነገሡባቸው አገሮች አታንሺም ወገኖቼ እስራኤልን የሚጠብቃቸው ንጉሥ ከአንቺ ይወጣልና ።

ስለ ምኵራብ መቅረት፣ ስለ ቤተክርስቲያን በዓለም ሁሉ መታነፅ ትንቢት ተናግሯል። ዳግመኛም ስለ ሕገ ወንጌል መሠራት ሕግ ከጽዮን የ #እግዚአብሔርም ቃል ከኢየሩሳሌም ይወጣል አለ። የትንቢቱም ወራት ሲፈጸም ወደ በጎ ሽምግልና ደርሶ ወደ ወደደው #እግዚአብሔር ሔደ።

የትንቢቱም ዘመን ከ #ጌታችን መምጣት በፊት በስምንት መቶ ዓመት ነው። ማርታ በምትባልም ቦታ ተቀበረ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኅ_ነሐሴ)
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ነሐሴ_22_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሮሜ 11
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²⁵ ወንድሞች ሆይ፥ ልባሞች የሆናችሁ እንዳይመስላችሁ ይህን ምሥጢር ታውቁ ዘንድ እወዳለሁ፤ የአሕዛብ ሙላት እስኪገባ ድረስ ድንዛዜ በእስራኤል በአንዳንድ በኩል ሆነባቸው፤
²⁶ እንደዚሁም እስራኤል ሁሉ ይድናል፤ እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፦ መድኃኒት ከጽዮን ይወጣል ከያዕቆብም ኃጢአተኛነትን ያስወግዳል።
²⁷ ኃጢአታቸውንም ስወስድላቸው ከእነርሱ ጋር የምገባው ኪዳን ይህ ነው።
²⁸ በወንጌልስ በኩል ስለ እናንተ ጠላቶች ናቸው፥ በምርጫ በኩል ግን ስለ አባቶች ተወዳጆች ናቸው፤
²⁹ እግዚአብሔር በጸጋው ስጦታና በመጥራቱ አይጸጸትምና።
³⁰ እናንተም ቀድሞ ለእግዚአብሔር እንዳልታዘዛችሁ፥ አሁን ግን ከአለመታዘዛቸው የተነሣ ምሕረት እንዳገኛችሁ፥
³¹ እንዲሁ በተማራችሁበት ምሕረት እነርሱ ደግሞ ምሕረትን ያገኙ ዘንድ እነዚህ ደግሞ አሁን አልታዘዙም።
³² እግዚአብሔር ሁሉን ይምር ዘንድ ሁሉን በአለመታዘዝ ዘግቶታልና።
³³ የእግዚአብሔር ባለ ጠግነትና ጥበብ እውቀቱም እንዴት ጥልቅ ነው፤ ፍርዱ እንዴት የማይመረመር ነው፥ ለመንገዱም ፍለጋ የለውም።
³⁴ የጌታን ልብ ያወቀው ማን ነው?
³⁵ ወይስ አማካሪው ማን ነበር? ወይስ ብድራቱን ይመልስ ዘንድ ለእርሱ አስቀድሞ የሰጠው ማን ነው?
³⁶ ሁሉ ከእርሱና በእርሱ ለእርሱም ነውና፤ ለእርሱ ለዘላለም ክብር ይሁን፤ አሜን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
2ኛ ጴጥሮስ 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁹ ከእርሱም ይልቅ እጅግ የጸና የትንቢት ቃል አለን፤ ምድርም እስኪጠባ ድረስ የንጋትም ኮከብ በልባችሁ እስኪወጣ ድረስ፥ ሰው በጨለማ ስፍራ የሚበራን መብራት እንደሚጠነቀቅ ይህን ቃል እየጠነቀቃችሁ መልካም ታደርጋላችሁ።
²⁰ ይህን በመጀመሪያ እወቁ፤ በመጽሐፍ ያለውን ትንቢት ሁሉ ማንም ለገዛ ራሱ ሊተረጉም አልተፈቀደም፤
²¹ ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና፥ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 7
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁵¹ እናንተ አንገተ ደንዳኖች ልባችሁና ጆሮአችሁም ያልተገረዘ፥ እናንተ ሁልጊዜ መንፈስ ቅዱስን ትቃወማላችሁ፤ አባቶቻችሁ እንደ ተቃወሙት እናንተ ደግሞ።
⁵²-⁵³ ከነቢያትስ አባቶቻችሁ ያላሳደዱት ማን ነው? የጻድቁንም መምጣት አስቀድሞ የተናገሩትን ገደሉአቸው፤ በመላእክት ሥርዓት ሕግን ተቀብላችሁ ያልጠበቃችሁት እናንተም አሁን እርሱን አሳልፋችሁ ሰጣችሁት ገደላችሁትም።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ነሐሴ_22_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"ወገሠፀ ነገሥተ በእንቲአሆሙ። ወኢትግሥሡ መሲሐንየ። ወኢታሕስሙ ዲበ ነቢያትየ"። መዝ 104፥14-15።
“የቀባኋቸውን አትዳስሱ፥ በነቢያቴም ክፉ አታድርጉ ብሎ፥ ሰው ግፍ ያደርግባቸው ዘንድ አልፈቀደም፥ ስለ እነርሱም ነገሥታትን ገሠጸ።” መዝ 104፥14-15።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ነሐሴ_22_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ማቴዎስ 2
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹-² ኢየሱስም በይሁዳ ቤተ ልሔም በንጉሡ በሄሮድስ ዘመን በተወለደ ጊዜ፥ እነሆ፥ ሰብአ ሰገል፦ የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው? ኮከቡን በምሥራቅ አይተን ልንሰግድለት መጥተናልና እያሉ ከምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ።
³ ንጉሡ ሄሮድስም ሰምቶ ደነገጠ፥ ኢየሩሳሌምም ሁሉ ከእርሱ ጋር፤
⁴ የካህናትንም አለቆች የሕዝቡንም ጻፎች ሁሉ ሰብስቦ ክርስቶስ ወዴት እንዲወለድ ጠየቃቸው።
⁵-⁶ እነርሱም፦ አንቺ ቤተ ልሔም፥ የይሁዳ ምድር፥ ከይሁዳ ገዢዎች ከቶ አታንሽም፤ ሕዝቤን እስራኤልን የሚጠብቅ መስፍን ከአንቺ ይወጣልና ተብሎ በነቢይ እንዲህ ተጽፎአልና በይሁዳ ቤተ ልሔም ነው አሉት።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #እመቤታችን_ማርያም ወይም የ #ቅዱ_ዮሐንስ_ወልደ_ነጎድጓድ ቅዳሴ ነው። መልካም የነቢዩ የቅዱስ ሚክያስ የዕረፍት በዓል። ለሁላችን ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ነሐሴ_23

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ነሐሴ ሃያ ሦስት በዚች ቀን በእስክንድርያ አገር ከክርስቲያን ወንድሞቻችን ሠላሳ ሺህ ሰዎች በሰማዕትነት ሞቱ፣ ሰማዕቱ #ቅዱስ_ድምያኖስ ዕረፍቱ ነው፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#የግብፅ_ሰማዕታት

ነሐሴ ሃያ ሦስት በዚች ቀን በእስክንድርያ አገር ከክርስቲያን ወንድሞቻችን ሠላሳ ሺህ ሰዎች በሰማዕትነት ሞቱ።

ይህም እንዲህ ነው ንጉሥ መርትያኖስ አባታችን ዲዮስቆሮስን ወደ ደሴተ ጋግራ በአጋዘው ጊዜ ብዙ ዘመናት በእስክንድርያ አገር ሁከትና ብጥብጥ ሆነ።

መርትያኖስም በሞተ ጊዜ በርሱ ፈንታ ልዮን ነገሠ እርሱም አብሩታርዮስ የተባለውን መለካዊ ከሮማውያን ወገን ለእስክንድርያ አገር ሊቀ ጳጳሳት ሾመ ይህም መለካዊ በኬልቄዶን ጉባዔ የሚያምን ነው ስለዚህም ከጥቂት ግብዞች ሰዎች በቀር የእስክንድርያ ሰዎች አልተቀበሉትም።

ያልተቀበሉትም ሰዎች አስቀድሞ አባታችን ዲዮስቆሮስ ከሾማቸው ቀሳውስት ሥጋውንና ደሙን የሚቀበሉ ሆኑ። ከዚህም በኋላ በቃሉ ለሚያምኑ ባልንጀሮቹ ጉባኤ አደረገላቸውና የክርስቶስ መለኮቱ ከትስብእቱ ተቀላቀለ የሚል አውጣኪን አወገዘው ።

አብሩታርዮስም ይህን ማድረጉ የእስክንድርያን ሰዎች ሸንግሎ ወደ ከፋች እምነቱ ሊስባቸው ወዶ ነው እንጂ ስለዚህ ነገር አባ ዲዮስቆሮስ አውጣኪን አስቀድሞ አውግዞታል። የአባታችን የዲዮስቆሮስ ሃይማኖት እንደ ባስልዮስና ጎርጎርዮስ እንደ ቅዱስ ቄርሎስ ቃል ከሥጋ ጋር ከተዋሐደ በኋላ አንድ አካል፣ አንድ ባሕርይ ብለው እንደሚያምኑ የሚያምን ነውና።

ከጉባኤውም በኋላ የሰበሰባቸው የአብሩታርዮስ ተባባሪዎቹ ወደየቦታቸው ተመለሱ። እርሱም ራሱ አብሩታርዮስ በቤቱ ውስጥ ተገድሎ ተገኘ ለባልንጀሮቹም የአባታችን ዲዮስቆሮስ ደቀ መዛሙርት ወይም የአውጣኪ ባልንጀሮች ወይም ሌቦች ገንዘቡን ለመውሰድ የገደሉት መሰላቸው ይህም እውነት ይመስላል።

የአብሩታርዮስም ባልንጀሮች ወደ ንጉሥ እንዲህ ብለው መልእክትን ላኩ እነሆ የዲዮስቆሮስ ወገኖች የንጉሥን ትእዛዝ በማቃለል ደፍረው የሾምከውን ሊቀ ጳጳሳት ገደሉት። በዚያንም ጊዜ ወንድሞቻችን የእስክንድርያ ሰዎች በላያቸው ጢሞቴዎስን ሊቀ ጵጵስና ሾሙት።

እሊህ መናፍቃንም ከዚህ በኋላ ሁለተኛ እንዲህ ብለው ወደ ንጉሥ መልእክትን ላኩ። እነሆ አብሩታርዮስን የገደሉት ሰዎች አሁንም ያለ ንጉሥ ፈቃድ ደፍረው ሊቀ ጳጳሳት ሾሙ።

ንጉሡም በሰማ ጊዜ ከሁለቱ መልእክቶች የተነሣ እጅግ ተቆጣ። ሰይጣንም በልቡ አድሮ ጭፍሮቹን ልኮ ሃይማኖታቸው ከቀና ወንድሞቻችን ክርስቲያኖች ታላላቆችና ታናናሾች ሠላሳ ሺህ ሰዎች ተገደሉ ጢሞቴዎስንም ወደ ደሴተ ጋግራ አጋዘው በዚያም ሰባት ዓመት ኖረ።

ከአባታችን ዲዮስቆሮስ ደቀ መዛሙርት አንዱ የገደለውስ ቢሆን ስለ አንድ ሰው ፈንታ ሠላሳ ሺህ ሰው መግደል ይገባልን ስለዚህ ከሰይጣን ሥራ እንደሆነ ይታወቃል።

ከዚህ ከከፋ ዕልቂት በኋላም ወንድሞቻችን የሆኑ የዲዮስቆሮስ ደቀ መዛሙርት አብሩታርዮስን እንዳልገደሉት ንጉሡ ተረዳ እጅግም አዘነ ጢሞቴዎስንም ከተሰደደበት መልሶ በመንበረ ሢመቱ አኖረው ታላቅ ክብርንም አከበረው። መንጋውንም እያበረታ ዐሥራ ሁለት ዓመት ኖረ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ድምያኖስ

ዳግመኛም በዚህች ዕለት ሰማዕቱ ቅዱስ ድምያኖስ ዕረፍቱ ነው፡፡ ይህንንም ቅዱስ የአንጾኪያ አገር መኮንን ይዞ ብዙ አሠቃየው፡፡

በኋላ ቅዱስ ድምያኖስ በእምነቱ መጽናቱን ሲያውቅና ማሠቃየትም በሰለቸው ጊዜ አንገቱን በሰይፍ ቆረጠውና ሰማዕትነት ፍጻሜው ሆነ፡፡ የክብር አክሊንም ተቀዳጀ፡፡

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በእሊህ ሰማዕታት ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ትድረሰን ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኅ_ነሐሴ_23)
#ነሐሴ_24

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ነሐሴ ሃያ አራት በዚህችም ቀን ታላቅ የከበረ ሐዲስ ሐዋርያ #አባታችን_ተክለሃይማኖት አረፈ፣ የከበረች #ቅድስት_ክርስቶስ_ሠምራ የዕረፍቷ መታሰቢያ ነው፣ የክርስቶስ የመርዓስ ኤጲስቆጶስ #ቅዱስ_አባት_ቶማስ_አረፈ

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ጻድቁ_አቡነ_ተክለሃይማኖት

ነሐሴ ሃያ አራት በዚህችም ቀን ታላቅ የከበረ ሐዲስ ሐዋርያ የትሩፋትም መምህር የሆነ አባታችን ተክለሃይማኖት አረፈ። የዚህም ቅዱስ የአባቱ ስም ጸጋ ዘአብ የእናቱ ስም እግዚእ ኀረያ ነው እሊህም ቅዱሳን ለኢትዮጵያ የሃይማኖት ብርሃንን ላበሩ ካህናት ከወገኖቻቸው የሆኑ ናቸው። እግዚእ ኀረያም መካን ስለሆነች ልጅን ይሰጣቸው ዘንድ ወደ #እግዚአብሔር እያዘኑ ሲጸልዩ ኖሩ።

በዚህም ነገር እያሉ የዳሞት ገዥ ሞተለሚን ሰይጣን አነሣሣው የሸዋን አውራጃዎች እስከ ጅማ እስከ ገዛ ድረስ። የሀገር መኳንንቶችም በየተራቸው ሚስቶቻቸውን ይሰጡታል። ከማረከውም ደምግባት ያላቸውን ሴቶች ያገኘ እንደሆነ ቁባቶች ያደርጋቸዋል።

በዚያም ወራት ወደ ጽላልሽ ደርሶ ብዙ ክርስቲያኖችን ገደለ ከእርሳቸውም የሚበዙትን ማረከ ጸጋ ዘአብም ከግድያ ፍርሃት የተነሳ ሸሸ አንድ ወታደርም ተከተለው እርሱም ወደ ባሕር ተወርውሮ ገባ በ #እግዚአብሔርም ፈቃድ በባሕሩ ውስጥ ተሸሸገ።

ሚስቱን እግዚእ ኀረያንም ወታደሮቹ ማረኳት ወደ ሞተለሚም አደረሷት ባያትም ጊዜ ውበቷንና ላህይዋን አደነቀ በልቡም እጅግ ደስ ብሎት ብዙ ሽልማትን ጌጥን ሰጥቷት በሽልማትና በጌጥ ሁሉ ሸለማት አስጌጣትም የጋብቻ ሥርዓትንም ማዘጋጀት ጀመረ ለሠርጉም እንዲሰበሰቡ ወደመኳንንቶቹ ሁሉ ላከ።

እግዚእ ኀረያም ይህን በሰማች ጊዜ ከአረማዊ ጋር አንድ ከመሆን ያድናት ዘንድ በብዙ ልቅሶ ወደ #እግዚአብሔር ጸሎትን አደረገች። ያን ጊዜም የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል በብርሃናዊ ክንፉ ተሸክሞ ከዳሞት አገር ወደ ምድረ ዞራሬ አድርሶ ወዲያውኑ ወደ ቤተ መቅደስ አስገብቶ በሴቶች መቆሚያ አቆማት። ባሏ ጸጋ ዘአብም ከማዕጠንት ጋራ በወጣ ጊዜ እንደተሸለመች ቁማ አያት አድንቆ በልቡ ይቺ ሴት ምንድን ናት ወደዚህስ ማን አመጣት አለ።

የማዕጠንቱንም ሥራ ጨርሶ ወጣ በጠየቃትና በመረመራት ጊዜ እርሷ ሚስቱ እግዙእ ኀረያ እንደሆነች አገኛት እርሷም ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው #እግዚአብሔር ያደረገላትን ነገረችው።

ከዚህም በኋላ የ #እግዚአብሔር መልአክ በአንዲት ሌሊት ተገለጠላቸው የዜናው መሰማት በዓለሙ ሁሉ የሚደርስ የተባረከ ልጅ ይወልዱ ዘንድ እንዳላቸው ነገራቸው አበሠራቸው።

ከጥቂት ቀኖችም በኋላ ይህ ቅዱሱ ተፀንሶ በታኀሣሦ ወር በሃያ አራት ተወለደ በጸጋ ዘአብና በእግዚእ ኀረያ ቤታቸው ታላቅ ደስታ ሆነ ከዘመዶቻቸውና ከጐረቤቶቻቸው ጋራ ደስ አላቸው።

ለክርስትና ጥምቀትም በአስገቡት ጊዜ ፍሥሓ ጽዮን ብለው ሰየሙት። ሕፃኑም አደገ ድንቅ ተአምራትንም እያደረገ ዕውቀትንና ኃይልንም ተመልቶ በመነፈስ ቅዱስ ጸና።

ከዚህም በሗላ ዲቁና ይሾመው ዘንድ አባ ጌርሎስ ወደ ተባለ ጳጳስ ወሰዱት በዚያንም ዘመን በዛጔ መንግሥት የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት አባ ብንያሚን ነበር። ወደ ጳጳሱም በአደረሱት ጊዜ ይህ ልጅ የተመረጠ ዕቃ ይሆናል ብሎ ትንቢት ተናገረለት። የዲቁና ሹመትንም ተቀብሎ ወደ ሀገሩ ተመለሰ።

ጐልማሳ በሆነ ጊዜ አራዊትን ሊያድን ወደ ዱር ሔደ። ቀትር ሲሆንም የክብር ባለቤት #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ መልኩ የሚያምር ጐልማሳ አምሳል በቅዱስ ሚካኤል ክነፍ ላይ ተገለጠለትና እንዲህ አለው ወዳጄ አትፍራ እንግዲህ የኃጢአተኞችን ነፍስ ወደ ሕይወት የምታጠምድ ትሆናለህ እንጂ አራዊትን የምታድን አትሆንም ስምህም ተክለ ሃይማኖት ይሁን እንደ ኤርምያስና እንደ አጥማቂው ዮሐንስ እኔ ከእናትህ ማኀፀን መርጬ አከብሬሃለሁና እነሆ በሽተኞችን ትፈውስ ዘንድ ሙታንንም ታሥነሣ ዘንድ ሥልጣንን ሰጠሁህ ርኩሳን አጋንንትንም ከሁሉ ቦታ ታሳድዳቸዋለህ።

ወደ ቤቱም በተመለሰ ጊዜ ገንዘብን ሁሉ ለድኆችና ለምስኪኖች በተነ ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጠፋ ለሰው ምን ይጠቅመዋል እያለ ቤቱን እንደ ተከፈተ ትቶ ምርኩዙን ይዞ በሌሊት ወጣ።

ከዚህም በኋላ ወደ ጳጳስ ሔዶ የቅስና ሹመት ተቀብሎ ለሸዋ አገር ሁሉ ወንጌልን መስበክ ጀመረ። ዐሥራ ሁለት ሽህ ሦስት መቶ ነፍስ ያህል አጠመቀ ለጣፆት የሚሠውበትን ሁሉ ሻረ በውስጡ የሚኖሩ አጋንንት እስከሸሹ ድረስ ዐፀዶቻቸውን ሁሉ ቆረጠ።

ሁለተኛም ወደ ዳሞት ምድር ሔዶ ብዙ ሟርተኞችንና አስማተኞችን ጠንቋዮችን አሳመነ ከሀዲ ሞተለሚም ብዙ ወራት ተቃወመው በጉማሬ ማጥመጃ ውስጥ በመጨመር ብዙ ጊዜ ወደ ገደል ወረወረው እርሱ ግን በደኀና ይመለሳል ደግሞ ሊወጋው ጦር ወረወረ ጦሩም ተመልሶ እጁን ወግቶ ተጠመጠመበት በተሠቃየም ጊዜ አባታችንን ለመነው እርሱም የክብር ባለቤት በሆነ በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ አሳምኖ አዳነው የተጠመጠመበትንም ጦር ፈታለት ቀናውን መንገድ የሚያጣምሙ ሟርተኞችንም አጠፋቸው።

ከዚህም በኋላ በክብር ባለቤት #ጌታችን ስም ያደረገውን ድንቅ ተአምራቱን አይተው የአገር ሰዎች ሁሉም ከንጉሣቸው ጋራ አመኑ የክርስትና ጥምቀትንም አጠመቃቸው ቤተ ክርስቲያንም ሠርቶላቸው የቤተ ክርስቲያንን ሥርዓት አስተማራቸው በቀናች ሃይማኖትም አጸናቸው ከዚህም ሁሉ ጋራ በጾም በጸሎት በስግደት ሁልጊዜ ያለ ማቋረጥ ተጠምዶ ይጋደል ነበር።

ዜናውንም ሰምተው ወደርሱ የሚመጡትን የነፍሳቸውን ድኀነት ያስተምራቸዋል የክብር ባለቤት የሆነ #ጌታችን_ኢየሱስን በማመን ያጸናቸዋል።

ከዚህ በኋላ በኤልያስ ሠረገላ ተቀምጦ ወደ አምሐራ ሀገር ሔደ በገድል ተጸምዶ ወደሚኖር መነኰስ ወደ አባ በጸሎተ ሚካኤል በአንዲት ቀን ደርሶ በዚያ እንደባሪያ ሲያገለግል ኖረ በአንድነት የሚኖሩ መነኰሳትንም ያገለግላቸው ነበር የሞተውንም እስከማንሳት ድረስ ከደዌያቸው ይፈውሳቸው ነበር።

በዚያም ዐሥራ ሁለት ዓመት ከሆነው በሗላ ሐይቅ በሚባል ቦታ ወደሚኖር ወደ ኢየሱስ ሞዓ የ #እግዚአብሔር መልአክ እንዳዘዘው ሔዶ ከእርሱም የምንኲስና ልብስ ቀሚስና ቅናትን ተቀበለ። ከዚያም ወደ ደብረ ዳሞ ሔዶ ለአቡነ አረጋዊ አራተኛ ከሆነ ከአባ ዮሐኒ ዘንድ ቆብንና አስኬማን ተቀበለ። ሁለተኛም ወደ ኢየሩሳሌም ሒዶ ከከበሩ ቦታዎችና ከሊቀ ጳጳሳቱ ቡራኬን ተቀበለ።

በዚያም ወደ ሸዋ ምድር ተመልሶ የአባቱ ወንድም ልጅ የሆነ አባ ዜና ማርቆስን አገኘው በወግዳ በረሀም በአንድነት ኖሩ ከዚያም ግራርያ ወደ ሚባል አገር ሒዶ በኮረብታ መካከል ዋሻ አዘጋጅቶ ተቀመጠ በቀንም በሌሊትም ከዚያ አይወጣም ነበረ ከጥቂት ቅጠልም በቀር እህልን አይቀምስም መጠጡም ጥቂት ውኃ ነው።

ብዙ ወንዶችና ሴቶች ወደርሱ መጥተው መነኲሳቶች ሆኑ በአንድ ቤት ውስጥ በአንድ መኝታ ላይ ተኝተው ያድራሉ እርስበርሳቸውም አይተዋወቁም እነርሱም እንደ ሕፃናት ናቸው በጸሎትና በቅዳሴ ጊዜም በአንድነት ይቆማሉ በዘመኑ ሰይጣን ሰለ ታሠረ ወንዱ ሴቷን ሴት እነደሆነች አያውቅም እንዲሁም ሴቷ ወንዱን ወንድ እንደሆነ አታውቅም።

በዚህም በኋላ መጠጊያ ሠርቶ በፊቱ በሗላው በቀኙ በግራው የተሳሉ ፍላጻዎችን ተከለ ይህንም ማድረጉ በመደገፍና በመተኛት እንዳያርፍ ነው በዚያም እግሩ ከቅልጥሙ እስቲሰበር ሰባት ዓመት ቆመ። በዚያም ወራት ምንም የዕንጨት ፍሬ ወይም ቅጠል ሳይቀምስ ውኃም ሳይጠጣ ኖረ።
2024/09/21 20:34:08
Back to Top
HTML Embed Code: