Telegram Web Link
#ነሐሴ_4

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ነሐሴ አራት በዚህች ቀን ከዳዊት ዘር የሆነ የአካዝ ልጅ #ቅዱስ_ሕዝቅያስ ንጉሥ አረፈ፣ እንደ በግ የጸጒር ልብስ ለብሶ በበረሃ የሚኖር #አባ_ማቴዎስ አረፈ፣ በተጨማሪ በዚች ቀን የከበሩ #ዳዊትና_ወንድሞቹና ከግብጽ ደቡብ ስንካር ከሚባል አገር #ፊልጶስም በሰማዕትነት ሞቱ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ሕዝቅያስ_ጻድቅ (ንጉሠ ይሁዳ)

ነሐሴ አራት በዚህች ቀን ከዳዊት ዘር የሆነ የአካዝ ልጅ ሕዝቅያስ ንጉሥ አረፈ። ከጻድቁ ንጉሥ ከዳዊት በኋላ እንደ ሕዝቅያስ ያለ በእስራኤል ውስጥ አልተሾመም ከዚህ ጻድቅ ንጉሥ በቀር ሁሉም ጣዖትን አምልከዋልና መሠዊያም ሠርተዋልና።

እርሱም በነገሠ ጊዜ ጣዖታትን ሰበረ መሠዊያቸውንም አፈረሰ ከነሐስ የተሠራውንም እባብ ቆራረጠ የእስራኤል ልጆች አምልከውት ነበርና #እግዚአብሔርም ዘመነ መንግሥቱን እጅግ አሳመረለት በጎ ነገርንም ሁሉ ሰጠው ።

ሕዝቅያስም በነገሠ በዐሥራ አራተኛው ዘመን የፋርስ ንጉሥ ሰናክሬም መጥቶ ኢየሩሳሌምን ከበባት ይህም ሰናክሬም በዘመኑ እንደርሱ ያለ የሌለ ኃይለኛ ብርቱ የምድር ነገሥታት ሁሉ የፈሩትና የታዘዙለት ነው ። ሕዝቅያስም ከእርሱ ግርማ የተነሣ ፈርቶ አገሩን እንዳያጠፋ ብዙ ወርቅና ብር እጅ መንሻ ላከለት ሰናክሬምም ደስ ብሎት ምንም ምን አልተቀበለም በእርሱ ላይና በልዑል #እግዚአብሔር ላይ ተቆጥቶ #እግዚአብሔር ከእኔ እጅ ሊያድናችሁ አይችልም በማለት የስድብን ቃል ላከ እንጂ ።

ሁለተኛም በልዑል ስም ላይ ስድብና ቍጣ የተጻፈበትን ደብዳቤ ላከ ሕዝቅያስም በሰማ ጊዜ ወደ #እግዚአብሔር ቤት ገብቶ አለቀሰ ልብሱንም ቀዶ ማቅ ለበሰ እንዲህም ብሎ ጸለየ ። አቤቱ የእስራኤል አምላክ በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ አንተም ብቻህን በዓለም መንግሥታት ላይ ንጉሥ የሆንክ አንተም ሰማይና ምድርን የፈጠርህ ልመናዬን አድምጥ ። ዐይኖችህን ገልጠህ ተመልከት ሕያው #እግዚአብሔር አንተን እያቃለለ ሰናክሬም የላከውን ቃሉን ስማ ።

ከዚህም በኋላ ንጉሥ ሕዝቅያስ የፋርስ ንጉሥ ሰናክሬም የተናገውን እንዲነግሩትና ስለርሱና ስለ ሕዝቡ ይጸልይ ዘንድ ወደ ኢሳይያስ መልእክተኞችን ላከ ። ኢሳይያስም ከ #እግዚአብሔር ቃልን ተቀብሎ እንዲህ ብሎ መለሰለት ልብህን አጽና አትፍራ በዓለሙ ሁሉ እንደርሱ ያለ ያልተሰማ ዕፁብ ድንቅ የሆነ ሥራ በሰናክሬም ላይ ሊሠራ #እግዚአብሔር አለውና ።

ከዚህም በኋላ #እግዚአብሔር የላከው መልአክ መጥቶ ከፋርስ ሠራዊት መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ ሰዎችን ገደለ የለኪሶም ሰዎች ሲነጋ በተነሡ ጊዜ የሞቱትን ሰዎች ሬሳ ሁሉ አገኙ የተረፉትም ከንጉሣቸው ጋራ ሸሽተው ነነዌ አገር ገቡ ። ሰናክሬምም ሊጸልይ ወደጣዖቱ ቤት በገባ ጊዜ ልጆቹ አድራማሌክና ሶርሶር በሰይፍ መትተው ገደሉት ። ሕዝቅያስም ከሰናክሬም እጅ ድኖ የተመሰገነ #እግዚአብሔርን አመሰገነ ።

በዚያም ወራት ሕዝቅያስ ታመመ ለሞትም ደረሰ የአሞፅ ልጅ ኢሳይያስም ወደረሱ መጥቶ #እግዚአብሔር እንዲህ አለ ትሞታለህ እንጂ አትድንምና ቤትህን ሥራ አለው። ሕዝቅያስም ፊቱን ወደግድግዳው መልሶ ወደ #እግዚአብሔር ለመነ እያመሰገነውም እንዲህ አለ አቤቱ በቀና ልቡና በዕውነት ሥራ በፊትህ ጸንቼ እንደኖርኩ ፈቃድህንም እንደፈጸምሁ አስብ ብሎ ሕዝቅያስ ፈጽሞ ጽኑዕ ልቅሶን አለቀሰ ።

ኢሳይያስም ወደ መካከለኛው ዐፀድ ደረሰ #እግዚአብሔርም እንዲህ ብሎ ተናገረው ሒደህ ለወገኖቼ ንጉሥ ለሕዝቅያስ ያባትህ የዳዊት ፈጣሪ #እግዚአብሔር እንዲህ አለ በለው ። ጸሎትህን ሰማሁ ዕንባህንም አየሁ እነሆ እኔ አድንሃለሁ እስከ ሦስት ቀንም ወደ #እግዚአብሔር ቤት ትወጣለህ ።

በዘመኖችህም ላይ ዐሥራ አምስት ዓመት ጨምሬልሃለሁ ከፋርስ ንጉሥ እጅም አድንሃለሁ ይቺንም አገር ስለ እኔና ስለ ባለሟሌ ዳዊት አጽንቼ እጠብቃታለሁ ። ሕዝቅያስም ኢሳይያስን እንዲህ አለው #እግዚአብሔር እንደሚያድነኝና እስከ ሦስት ቀን ወደ #እግዚአብሔር ቤት ለመውጣቴ ምልክቱ ምንድ ነው ።

ኢሳይያስም እንዲህ አለው የተናገረውን ቃል ያደርግ ዘንድ ከ #እግዚአብሔር የተገኘ ምልክቱ ይህ ነው እነሆ ጥላው ወደ ዐሥረኛው እርከን ቢመለስ ምልክቱ ይህ ነው ። ሕዝቅያስም እንዲህ አይደለም የጥላው ወደ ዐሥረኛ እርከን መመለስ ቀላል ነው ። መመለስስ ከሆነ ፀሐይ ወደ ዐሥረኛው እርከን ይመለስ አለ ። ኢሳይያስም ወደ #እግዚአብሔር ጮኸ ፀሐይም ዐሥሩን እርከን ተመለሰ ።

ሕዝቅያስንም የምድር ነገሥታት ሁሉ ፈሩት እጅ መንሻም አገቡለት የ #እግዚአብሔር ኃይል ከእርሱ ጋራ እንዳለ አውቀዋልና ። በመንበረ መንግሥቱም ሃያ ዘጠኝ ዓመት ነግሦ ኖረ ። #እግዚአብሔርን አገልግሎ በሰላም አረፈ ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎቱ ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አባ_ማቴዎስ_ገዳማዊ

በዚችም ቀን እንደ በግ የጸጒር ልብስ ለብሶ በበረሃ የሚኖር አባ ማቴዎስ አረፈ። ይኸውም አባ ማቴዎስ የአቶሩን ንጉሥ በተአምሩ ከነቤተሰቡ ያሳመነው ነው፡፡ በእርሱም ትምህርት በሀገሪቱ ብዙ ሰማዕታት ተገኝተዋል፡፡ ቅድስት ሣራና ወንድሟ መርምህናም አባታቸው የአቶር ንጉሥ ሲሆን እርሱም የተቀረጹ ጣዖታን ያመልክ ነበር፡፡ እናታቸው ግን አማኝ ክርስቲያን ነበረች፡፡ አባቱን ለምኖና አስፈቅዶ ወደ ዱር ሄዶ አራዊትን ለማደን በወጣ ጊዜ እናቱ የሰማይና የምድር አምላክ #እግዚአብሔር በላዩ በረከትን ያሳድርበት ዘንድ ከጸለየችለት በኋላ ሸኘችው፡፡

መርምህናም ከአርባ ፈረሰኛ አገልጋዮቹ ጋር ወጥቶ ሄደ፡፡ ወደ አንድ ተራራም ወጥቶ በዚያ አደረ፡፡ በሌሊትም የታዘዘ መልአክ ጠራውና ‹‹መርምህናም ሆይ ተነሥተህ ወደዚህ ተራራ ጫፍ ላይ ውጣ፣ ስሙ ማቴዎስ የሚባል ቅዱስ ሰው ታገኛለህ፡፡ እርሱም የሕይወትን ነገር ይነግርሃል›› አለው፡፡

ሲነጋም ወደ ተራራው ጫፍ ላይ ወጣና የበግ ጠጉር ለብሶ አባ ማቴዎስን ባገኘው ጊዜ እጅግ ፈራ፡፡ አባ ማቴዎስም ‹‹አይዞህ አትራ እኔም የእግዚአብሔር ፍጥረት ነኝና አትፍራ›› ብለው አበረቱት፡፡ መርምህናም የ #እግዚአብሔርን ስም ሲጠሩ ሲሰማ ‹‹አባቴ ከአማልክቶች በቀር አምላክ አለን?›› ብሎ ጠየቃቸው፡፡ አባታችንም የሃይማኖትን ነገር ሁሉንም አስተማሩት፡፡ መርምህናም ‹‹ከራስ ጠጉሯ እስከ እግር ጥፍሯ ድረስ በለምጽ የተመታች እኅት አለችኝና እርሷን የአምላክህን ስም ጠርተህ ካዳንክልኝ በእውነት በአምላክህ አምናለሁ›› አላቸው፡፡ ተያይዘውም ከተራራው ወርደው ወደ ንጉሡ ቤት ሄደው መርምህናም ለእናቱ ያጋጠመውን ነገር ነገራትና በለምጽ የተመታችውን እኅቱን ሣራን በሥውር ወደ አቡነ ማቴዎስ ዘንድ ወሰዳት፡፡ አቡነ ማቴዎስም መሬቱን ባርከው ውኃ አፍልቀው አጠመቋትና ከለምጹዋ ፈወሷት፡፡ አርባው ጭፍራዎችም አምነው በአባታችን እጅ ተጠመቁ፡፡

አባታችንም ሰማዕትነትን እንደሚቀበሉ ትንቢት ነግረዋቸው ባርከው መርቀው አሰናበቷቸው፡፡ የአቶሩም ንጉሥ ልጆቹንና ያመኑትን አርባውን ጭፍራዎቹን በሰይፍ ገደላቸው፡፡ ሰይጣንም በአቶሩ ንጉሥ አድሮ አሳበደው፡፡ እንደ እሪያም መጮህ ጀመረ፡፡

ክርስቲያን የሆነችው የቅዱስ መርምህናምና የቅደስት ሣራ እናታቸው ወደ አባ ማቴዎስ ሄዳ ንጉሡ በልጆቹ ላይ ያደረገውንና በእርሱም ላይ የተፈጸመበትን ነገር ነገረቻቸው፡፡ አባ ማቴዎስም ንጉሡን ዘይት ቀብተው ጸልየው ፈወሱት፡፡ በውስጡ አድሮበት የነበረውንም ሰይጣን በእሪያ መልክ ከንጉሡ ውስጥ አስወጡት፡፡
ንጉሡም ወደ ልቡ ሲመለስ በአቡነ ማቴዎስ ትምህርት በ #ጌታችን አመነ፡፡ በሚገዛቸው አገሮች ሁሉ ያሉትን ሰዎች ይዞ ከነቤተሰቡ ተጠመቀ፡፡ አቡነ ማቴዎስም #እግዚአብሔርን ሲያገለግሉ ኖረው በዚህች ዕለት በሰላም ዐረፉ፡፡

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ነሐሴ_4)
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ነሐሴ_4_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሮሜ 12
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁶ እርስ በርሳችሁ በአንድ አሳብ ተስማሙ፤ የትዕቢትን ነገር አታስቡ፥ ነገር ግን የትሕትናን ነገር ለመሥራት ትጉ። ልባሞች የሆናችሁ አይምሰላችሁ።
¹⁷ ለማንም ስለ ክፉ ፈንታ ክፉን አትመልሱ፤ በሰው ሁሉ ፊት መልካም የሆነውን አስቡ።
¹⁸ ቢቻላችሁስ በእናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ።
¹⁹ ተወዳጆች ሆይ፥ ራሳችሁ አትበቀሉ፥ ለቍጣው ፈንታ ስጡ እንጂ፤ በቀል የእኔ ነው፥ እኔ ብድራቱን እመልሳለሁ ይላል ጌታ ተብሎ ተጽፎአልና።
²⁰ ጠላትህ ግን ቢራብ አብላው፤ ቢጠማ አጠጣው፤ ይህን በማድረግህ በራሱ ላይ የእሳት ፍም ትከምራለህና።
²¹ ክፉውን በመልካም አሸንፍ እንጂ በክፉ አትሸነፍ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ጴጥሮስ 5
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁶ እንግዲህ በጊዜው ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከኃይለኛው ከእግዚአብሔር እጅ በታች ራሳችሁን አዋርዱ፤
⁷ እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት።
⁸ በመጠን ኑሩ ንቁም፥ ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና፤
⁹ በዓለም ያሉት ወንድሞቻችሁ ያን መከራ በሙሉ እንዲቀበሉ እያወቃችሁ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት።
¹⁰ በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዘላለም ክብሩ የጠራችሁ የጸጋ ሁሉ አምላክ ለጥቂት ጊዜ መከራን ከተቀበላችሁ በኋላ ራሱ ፍጹማን ያደርጋችኋል ያጸናችሁማል ያበረታችሁማል።
¹¹ ለእርሱ ክብርና ኃይል እስከዘላለም ድረስ ይሁን፤ አሜን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 17
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²³ የምታመልኩትን እየተመለከትሁ ሳልፍ፦ ለማይታወቅ አምላክ የሚል ጽሕፈት ያለበትን መሠዊያ ደግሞ አግኝቼአለሁና፦ እንግዲህ ይህን ሳታውቁ የምታመልኩትን እኔ እነግራችኋለሁ።
²⁴ ዓለሙንና በእርሱ ያለውን ሁሉ የፈጠረ አምላክ እርሱ የሰማይና የምድር ጌታ ነውና እጅ በሠራው መቅደስ አይኖርም፤
²⁵ እርሱም ሕይወትንና እስትንፋስን ሁሉንም ለሁሉ ይሰጣልና አንዳች እንደሚጎድለው በሰው እጅ አይገለገልም።
²⁶-²⁷ ምናልባትም እየመረመሩ ያገኙት እንደ ሆነ፥ እግዚአብሔርን ይፈልጉ ዘንድ በምድር ሁሉ ላይ እንዲኖሩ የሰውን ወገኖች ሁሉ ከአንድ ፈጠረ፥ የተወሰኑትንም ዘመኖችና ለሚኖሩበት ስፍራ ዳርቻ መደበላቸው። ቢሆንም ከእያንዳንዳችን የራቀ አይደለም።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ነሐሴ_4_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"እግዚኦ በኃይልከ ይትፌሣሕ ንጉሥ። ወብዙኀ ይትኀሠይ በአድኅኖትከ። ፍትወተ ነፍሱ ወሀብኮ"። መዝ 20፥1-2።
"አቤቱ፥ በኃይልህ ንጉሥ ደስ ይለዋል፤ በማዳንህ እጅግ ሐሤትን ያደርጋል። የልቡን ፈቃድ ሰጠኽው፥ የከንፈሩንም ልመና አልከለከልኸውም"። መዝ 20፥1-2።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ነሐሴ_4_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሉቃስ 14
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
³¹ ወይም ሌላውን ንጉሥ በጦርነት ሊጋጠም የሚሄድ፥ ከሁለት እልፍ ጋር የሚመጣበትን በአንድ እልፍ ሊገናኝ የሚችል እንደ ሆነ አስቀድሞ ተቀምጦ የማያስብ ንጉሥ ማን ነው?
³² ባይሆንስ ሌላው ገና ሩቅ ሳለ መልክተኞች ልኮ ዕርቅ ይለምናል።
³³ እንግዲህ እንደዚሁ ማንም ከእናንተ ያለውን ሁሉ የማይተው ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም።
³⁴ ጨው መልካም ነው፤ ጨው አልጫ ቢሆን ግን በምን ይጣፈጣል?
³⁵ ለምድር ቢሆን ለፍግ መቈለያም ቢሆን አይረባም፤ ወደ ውጭ ይጥሉታል። የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️ 
የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #እመቤታች_የማርያም_ቅዳሴ ነው። መልካም የጾም ጊዜና በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
➩** ለምን ጽንዕት በድንግልና ሥርጉት በቅድስና አላት ቢሉ ?
ትርጓሜው :*
ጽንዕት በድንግልና ሥርጉት በቅድስና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን አእምሮውን ጥበቡን በልቦናችን ሳዪልን አሳድሪልን፡፡

#ቅድስት አለ ንጽሕት ጽንዕት ክብርት ልዩ ሲል ነው፡፡

#ንጽሕት አለ :- ሌሎች ሴቶች ቢነጹ ከነቢብ(ከቃል ከመናገር)፣ ከገቢር(ከሥራ ከድርጊት) ነው ከሐልዮ (ከሐሳብ)አይነጹም፡፡ እርሷ ግን ከነቢብ(ከቃል ከመናገር) ከገቢር(ከሥራ ከድርጊት) ከሐልዮ (ከሐሳብ) ንጽሕት ናትና፡፡

#ጽንዕትም አለ :- ሌሎች ሴቶች ቢጸኑ ለጊዜው ነው፡፡ ኋላ ግን ተፈትሖ አለባቸው፡፡ እሷ ግን ቅድመ ፀኒስ(ከመፀነሷ በፊት) ጊዜ ፀኒስ(በፀነሰች ጊዜ) ድኅረ ፀኒስ(ከፀነሰች በኋላ) ቅድመ ወሊድ(ከመውለዷ በፊት) ጊዜ ወሊድ(በወለደች ጊዜ) ድኅረ ወሊድ(ከወለደች በኋላ) ፅንዕት በድንግልና ናትና፡፡

#ክብርትም አለ:- ሌሎች ሴቶችን ብናከብራቸው ጸድቃን ሰማዕታትን፤ ጳጳሳት ኤጲስ ቆጶሳትን፤ ቀሳውስት ዲያቆናትን፤ ነገሥታት መኳንንትን ወልዱ ብለን ነው፡፡ እሷን ግን ወላዲተ አምላክ፣ እመ አምላክ፣ እመ ብርሃን ብለን ነውና፡፡

#ልዩም አለ:- እናትነት ከድንግልና አስተባብራ የተገኘች ከእመቤታችን በቀር ሌላ ሴት የለችም ወደፊትም አትኖርምና ፡፡

#ሰአሊ/ሰዓሊ ለነ አለ፡፡

ዐይኑ ‹ዓ› ነው ያሉ እንደሆነ (ሰዓሊ ለነ) አእመሮውን ለብዎውን ሳይብን አሳድሪብን ማለት ነው፡፡ አልፋው ‹አ› ያሉ እንደሆነ (ሰአሊ ለነ) ለምኚልን ማለት ነው፡፡
#ነሐሴ_5

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ነሐሴ አምስት በዚህች ቀን የደብረ ቢዘን #አባ_ፊልጶስ አረፈ፣ #ቅዱስ_አባ_አብርሃም ገዳማዊ አረፈ፣ የከበረ ተጋዳይ ወታደር #ቅዱስ_ዮሐንስ_ጻድቅ አረፈ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አቡነ_ፊልጶስ_ዘደብረ_ቢዘን

ነሐሴ አምስት በዚህች ቀን የደብረ ቢዘን አባ ፊልጶስ አረፈ። አቡነ ፊልጶስ ዘደብረ ቢዘን እንደ ነቢዩ ኤርምያስ በእናታቸው ማኅፀን ሳሉ የተመረጡና እንደተወለዱ ነው ሰማንያ አንዱን የብሉይ መጻሕፍትን አጠናቀው ያወቁት ናቸው፡፡ በ12 ዓመታቸውም ለመመንኮስና ገዳም ለመግባት ወስነው ወላጅ እናታቸውን አሰናብቺኝ በማለት ጠይቀዋል፡፡ ቅድስት እናታቸውም መርቀው ሸኟቸውና ትግራይ ውስጥ ወደሚገኘውና ደብረ ጸራቢ ወደሚባለው ገዳም ገቡ፡፡ የገዳሙ አስተዳዳሪ አቡነ በኪሞስም የምንኩስና ቀንበሩና ሸክሙ እጅግ ከባድ መሆኑን በመንገር ወደ እናታቸው እንዲመለሱ ቢመክሯቸውም አቡነ ፊልጶስ ግን ለምንኩስና የታጩ ሙሽራ መሆናቸውን ነገሯቸው፡፡ ከብዙ ፈተናም በኋላ አመነኮሷቸው፡፡

በገዳሙም እንጨት እየለቀሙና እየፈለጡ፣ ውኃ እየቀዱ፣ የክርስቶስን ሕማሙን ሞቱን እያሰቡ በጾምና ጸሎት ሲጋደሉ ከኖሩ በኋላ ጌታችን ተገልጦላቸው ወደ ሽሬ እንዲሄዱ ነገራቸውና ሽሬ አደያቦ ወደሚባለው ስፍራ ሄዱ፡፡ ብዙ አስደናቂ ተአምራት እያደረጉ ወንጌልን በሀገሩ ዞረው ሰበኩ፡፡ እንደ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በጥላቸው ድውያንን ይፈውሱ ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ ወደ ደብረ ቢዘን እንዲሄዱ ተነግሯቸው የእርሳቸውን በረከት ለመቀበል ከመጡ 16 ደጋግ መነኮሳት ጋር ወደ ደብረ ቢዘን ሄዱ፡፡ ይኸውም በኤርትራ ክፍለ ሀገር በሐማሴን አውራጃ ከአሥመራ ከተማ በስተምሥራቅ 25 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኘው አስደናቂው ገዳም ነው፡፡

ጻድቁ የሐይቅ እስጢፋኖስን ባሕር በተአምራት ያቃጠሉት አባት ናቸው፡፡ በንጉሡ በዐፄ ዳዊት ዘመን ሰንበትን አንድ ብቻ ናት እያሉ በአንደኛዋ ሰንበት ሥራ ሲሠሩ ጻድቁ አቡነ ፊልጶስ ይህን ሰምተው አንዲት ሰንበት የሚሉትን ሁሉ ተቃወሟቸው፡፡ ከግብፅ የመጡት ጳጳስም ቀደም ብሎ ከአቡነ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ አሁንም ከአቡነ ፊልጶስ ጋር ንጉሡ ዐፄ ዳዊት አከራክረዋቸው ጳጳሱም በክርክሩ ተረቱ፡፡ ክፉዎችም በአቡነ ፊሊጶስ ላይ በክፋት ተነሱባቸው፡፡ በአቁማዳ ጠቅልለው ሐይቅ ባሕር ውስጥ ጣሏቸው፡፡ በዚህም ጊዜ እሳቸው የተጣሉበት ባሕር በእሳት ተቃጥሎ ጽድቃቸውን መስክሮላቸዋል፡፡ ዛሬም ድረስ በሐይቅ እስጢፋኖስ ባሕር ዳርቻ ላይ የተቃጠለው ድንጋይ ምልክቱ በግልጽ ይታያል፡፡ በወቅቱ የንጉሡ ሚስት በዋናተኛ አስፈልጋ ከሐይቁ ውስጥ አስወጣቻቸው፡፡ እግራቸውንም አጥባቸው ስትጨርስ የእግራቸውን እጣቢ ጠጣችው፡፡ ወዲያውም ‹‹ከማኅፀንሽ ፍሬ ታላቅ ጻድቅ ልጅ ይወጣል›› ብለው ትንቢት ነገሯት፡፡ በትንቢታቸውም መሠረት ታላቁ ጻድቅ ንጉሥ ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ተወልዱ፡፡ በወቅቱ በተፈጠረው አለመግባባትና ክፉዎችም በባሕር ውስጥ ስለጣሏቸው ንጉሡ ዐፄ ዳዊትም አቡነ ፊልጶስን ከልብ ይቅርታ ጠይቀው ወዲያው ታርቀዋል፡፡ በዘመናቸውም ርኃብ ስለነተሳ ጻድቁን ከገዳማቸው አስጠርተው ‹‹ምን ባደርግ ይሻለኛል?›› ብለው አማክረዋቸዋል፡፡ አቡነ ፊልጶስም ‹‹የ #ጌታችንን መስቀል ያስመጡ›› ብለው መከሯቸው፡፡

ንጉሡ ዐፄ ዳዊትም በአቡን ፊልጶስ ምክር መሰረት ከኢየሩሳሌም፣ ከቍስጥንጥንያና ከእስክንድርያ መንግሥታት ጋር ተጻጽፈው ዓሥሩን ታላላቅ ቅዱሳን ይዘው ሄደው መስቀሉን መስከረም 10 ቀን አምጥተውታል፡፡ ቅዱስ መስቀሉን ያመጡት ዓሥሩ ቅዱሳንም የደብረ ቢዘኑ አቡነ ፊልጶስ ፣ የጣና ደሴቱ አቡነ ኂሩተ አምላክ፣ የጣና ደሴቱ አቡነ እንድርያስ፣ አቡነ በትረ ማርያም፣ አቡነ ዮሐንስ፣ አቡነ ታዴዎስ፣ አቡነ ያፍቅረነ እግዚእ፣ አቡነ ዘካርያስ፣ አቡነ ያሳይና አቡነ ቶማስ ናቸው፡፡ አቡነ ፊሊጶስ ዘደብረ ቢዘን በታላቅ ተጋድሎ ኖረው ከ #ጌታችን ዘንድ ታላቅ ቃልኪዳን ከተቀበሉ በኋላ ነሐሴ 5 ቀን በታላቅ ክብር ዐርፈዋል፡፡

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አባ_አብርሃም_ገዳማዊ

በዚህች ቀን ሌላው አብርሃም አረፈ። የዚህም ቅዱስ ወላጆቹ ባለጸጎች ናቸው በተግሣጽና ፈሪሃ እግዚአብሔርን በማስተማር አሳደጉት ። በአደገ ጊዜም ያለ ፈቃዱ አጋቡት #እግዚአብሔርም ወደሚፈቅደው ይመራው ዘንድ ሲለምን ኖረ።

በሰባተኛውም ቀን በዐልጋው ላይ ሳለ የ #እግዚአብሔር ቸርነት አነሳሥቶት ከጫጉላ ቤቱ ወጣ ብርሃን እየመራው ሒዶ ባዶ ቤት አግኝቶ በውስጡ ገብቶ ኖረ ምግቡን ከሚቀበልባት ከጥቂት መስኮት በቀር መዝጊያ ሠርቶ ደጁን ዘጋ።

ዓለምን ከተወ በዓሥረኛው ዓመት አባትና እናቱ ብዙ ጥሪት ትተውለት ሞቱ እርሱ ግን ለድኆችና ለችግረኞች በትኖ በጾምና በጸሎት ተወስኖ እየተጋደለ ኖረ ከአንድ ዐጽፍና ሰሌን በቀር ምንም ምን ጥሪት አላኖረም እንዲህም ሆኖ ዐሥር ዓመት ተጋደለ።

#እግዚአብሔርም ትዕግሥቱን አየ በአንዲት አገርም አረማውያን ነበሩ ከታናሾቻቸው እስከ ታላላቆቻቸው ወደ ሃይማኖት ሊመልሳቸው የሚችል የሌለ። በአንዲት ቀንም አባ አብርሃምን ጳጳሱ አሰበው ብርታቱንና ብልህነቱንም አይቶ ቄስ እንዲሆንና እነዚያን አረማውያን እንዲመልሳቸው አስገደደው በግድ አስጨንቆም ቅስና ሾመው ። ወደዚያም ቦታ ደርሶ ቤተ ክርስቲያን ሠራ እነዚያን አረማውያን እርሱን ፈጣሪያቸውን ወደ ማወቅ ይመልሳቸው ዘንድ በውስጧ ወደ #እግዚአብሔር ጸለየ።

በአንዲት ቀንም ወደ ጣዖቶቻቸው ቤት ገባ ያን ጊዜ ጣዖታቱን ከመቀመጫቸው ጣላቸው የአገር ሰዎችም በአዩ ጊዜ ቁጣን ተመልተው አብዝተው ደበደቡትና ከአገር አበረሩት በጥዋትም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሲጸልይ አገኙት።

ሁለተኛም በገመድ አሥረው ወደ ከተማው ውጭ ጐትተው በላዩም አፈር ቆልለው እንዳይሞት ጥቂት መተንፈሻ ትተው አልፈው ከዚያ ሔዱ። በ #እግዚአብሔርም ኃያል ተነሥቶ ሔደ ስለ መመለሳቸውም ሲጸልይ አገኙት በእንዲህ ያለ ሥራም እየተጋደለ ዐሥር ዓመት ኖረ።

የክብር ባለቤት #እግዚአብሔርም ትዕግሥቱን አይቶ ወደ ቀናች ሃይማኖት ልባቸውን መለሰ በ #አብ#ወልድ#መንፈስ_ቅዱስ ስም ከታናናሾች እስከ ታላላቆች ድረስ ሁሉንም አጠመቃቸው
የክብር ባለቤት በሆነ በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ሃይማኖትም ጸኑ።

ከዚህም በኋላ በሃይማኖታቸው መጽናታቸውን ባየ ጊዜ ከንቱ ውዳሴ እንዳያመጣበት ፈርቶ ወደ #እግዚአብሔር ጸለየ አገሪቱንም በ #መስቀል ምልክት አማተበባትና ማንም ሳያውቅ ወጥቶ ወደ ሌላ አገር ሔደ ።

ሰይጣንም በሚያስፈራው በብዙ ሥራ ይፈታተነው ነበር ቅዱሱም የክብር ባለቤት በሆነ በ #ጌታችን ኃይል አሸነፈው ። ጽኑ በሆነ ተጋድሎም ኖረ ያለ ዕንባም ሰዓት አላለፈችውም በጥርሶቹም አልሳቀም በከንፈሮቹም ፈገግ አላለም ስጋውን ቅባት አልነካውም ስጋውንና ደሙን ከሚቀበልበት ጊዜ በቀር ፊቱንና እግሩን አልታጠበም ።

እናትና አባቱ በስድስት ዓመቷ ትተዋት የሞቱ እኅት ነበረችው ስሟም ማርያ ይባላል ዘመዶቿም ወደ አብርሃም አምጥተዋት ፈሪሀ #እግዚአብሔር ሃያ ዓመት ሆናት ድረስ ትሕትናንም እያስተማራት በእርሱ ዘንድ አደገች።

ከዚህም በኋላ ሰይጣን ቀንቶባት ከአንድ መነኩሴ ጋር አፋቀራት ድንግልናዋንም አጠፉች ልብሷንና አስኬማዋን ለውጣ ወደ ሌላ አገር ሔደች።
አባ አብርሃምም በዚያች ሌሊት ታላቅ ከይሲ ርግቢቱን ሲውጣትና ጥቂት ቆይቶ ከእግሩ በታች ሲተፋት ራእይን አየ። በማግሥቱም ማርያ ከቦታዋ ታጣች አባ አብረሃምም ደነገጠ ወደ #እግዚአብሔርም ከብዙ ዕንባ ጋር ጸለየ እርሷን ያገናኘው ዘንድ።

ከጥቂት ወራትም በኋላ እኅቱ ያለችበትን አባ አብርሃም ሰማ ሰዎችም እንዳያውቁት የምንኩስናውን ልብስ ለውጦ ፊቱንም ተከናንቦ የወታደር ልብስ ለብሶ በፈረስ ተቀምጦ ወዳአለችበት አገር ሔደ ከዚያም ደርሶ ማርያ ወዳለችበት ገባ የመሸተኛንም ልብስ ለብሳ በአያት ጊዜ እጅግ አዘነ ነገር ግን እንዳትሸሸው እንድታውቀው አልሆነም።

ከዚህም በኋላ ለሚያገለግላት አሽከር ከማርያ ጋር የሚደሰትበት መብልና መጠጥ እንዲያዘጋጅ የወርቅ ዲናር ሰጠው ለርካሽ ሥራ እንደሚፈልጓት ሰዎች ይመስላት ዘንድ።

ከራት በኋላም ወደ ውስጠኛው ቤት አስገባት በሩንም ዘጋ እጇንም ይዞ ራሱን ገለጠላት በአወቀችውም ጊዜ ደንግጣ እንደ በድን ሆነች ልጄ ሆይ አይዞሽ ከ #እግዚአብሔር በቀር ከኃጢአት ንጹሕ የሆነ የለም ነገር ግን ወደ ንስሐ ተመለሺ ወደቦታሽም ገብተሽ የቀድሞ ሥርዓትሽን ያዢ አላት እርሷም እሺ አለች።

በነጋም ጊዜም ወስዶ በፈረሱ አስቀመጣትና ደስ እያለው ተመለሰ እኅቱን ከሰይጣን እጅ ማርኳልና ወደቦታውም በደረሰ ጊዜ የቤቷን ደጅ ዘግቶላት ማቅ በመልበስ እየተጸጸተች የተጋድሎንም ሥራ እየተማረች በብርታቷና በተጋድሎዋ ያዩ ሁሉ እስቲአደንቁ ጸንታ ኖረች ።

#እግዚአብሔርም በዚህ ቅዱስ ሰው እጆች ድንቆች ተአምራቶችን አደረገ አጋንንትን በማስወጣት በሽተኞችን በማዳን ከአንዲት ዓመትም በኋላ የማርያን ንስሓዋን አይቶ በሰባ ዘመኑ የተመሰገነ #እግዚአብሔርን እያመሰገነ አረፈ።

ማርያ እኅቱም ከለቅሶ ጋር ትርኅምትን በማብዛት ቀንና ሌሊት እየተጋደለች ሌሎች አምስት ዓመታትን ኖረች ከዚያም በኋላ አረፈች ያዩዋትም በፊቷ ውስጥ ስለአለው ብርሃን #እግዚአብሔርን አመሰገኑ።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ዮሐንስ_ጻድቅ

በዚህችም ቀን የከበረ ተጋዳይ ወታደር ዮሐንስ አረፈ። የዚህም ቅዱስ ወላጆቹ ክርስቲያኖች ናቸው እርሱም በከሀዲ በዑልያኖስ ሠራዊት ውስጥ ወታደር ሆነ። ንጉሡም ከባልንጀሮቹ ወታደሮች ጋራ ላከው የክርስቲያን ወገኖችንም በሚኖሩበት ቦታ ሁሉ እንዲአሠቃዩአቸው አዘዛቸው።

እርሱም ለባልንጀሮች ጭፍሮች ክርስቲያኖችን እጅግ እንደሚጠላቸውና እንደሚጣላቸው ይገልጽላቸዋል በጭልታም ገብቶ በጎ ነገርን የሚሹትን ሁሉ ይሰጣቸዋል ያጽናናቸዋልም። ሁል ጊዜም ይጸልያል ይጾማል ይመጸውታልም የቅዱሳንንም አኗኗር ኖረ ምስጉን #እግዚአብሔርንም አገልግሎ በሰላም አረፈ።

#ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ነሐሴ_5 እና #ከገድላት_አንደበት)
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ነሐሴ_5_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሮሜ 6
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹² እንግዲህ ለምኞቱ እንድትታዘዙ በሚሞት ሥጋችሁ ኃጢአት አይንገሥ፤
¹³ ብልቶቻችሁንም የዓመፃ የጦር ዕቃ አድርጋችሁ ለኃጢአት አታቅርቡ፥ ነገር ግን ከሙታን ተለይታችሁ በሕይወት እንደምትኖሩ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር አቅርቡ፥ ብልቶቻችሁንም የጽድቅ የጦር ዕቃ አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር አቅርቡ።
¹⁴ ኃጢአት አይገዛችሁምና፤ ከጸጋ በታች እንጂ ከሕግ በታች አይደላችሁምና።
¹⁵ እንግዲህ ምን ይሁን? ከጸጋ በታች እንጂ ከሕግ በታች ስላይደለን ኃጢአትን እንሥራን? አይደለም።
¹⁶ ለመታዘዝ ባሪያዎች እንድትሆኑ ራሳችሁን ለምታቀርቡለት፥ ለእርሱ ለምትታዘዙለት ባሪያዎች እንደ ሆናችሁ አታውቁምን? ወይም ለሞት የኃጢአት ባሪያዎች ወይም ለጽድቅ የመታዘዝ ባሪያዎች ናችሁ።
¹⁷-¹⁸ ነገር ግን አስቀድማችሁ የኃጢአት ባሪያዎች ከሆናችሁ፥ ለተሰጣችሁለት ለትምህርት ዓይነት ከልባችሁ ስለ ታዘዛችሁ፥ ከኃጢአትም አርነት ወጥታችሁ ለጽድቅ ስለ ተገዛችሁ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን።
¹⁹ ስለ ሥጋችሁ ድካም እንደ ሰው ልማድ እላለሁ። ብልቶቻችሁ ዓመፃ ሊያደርጉ ለርኵስነትና ለዓመፃ ባሪያዎች አድርጋችሁ እንዳቀረባችሁ፥ እንደዚሁ ብልቶቻችሁ ሊቀደሱ ለጽድቅ ባሪያዎች አድርጋችሁ አሁን አቅርቡ።
²⁰ የኃጢአት ባሪያዎች ሳላችሁ ከጽድቅ ነፃ ነበራችሁና።
²¹ እንግዲህ ዛሬ ከምታፍሩበት ነገር ያን ጊዜ ምን ፍሬ ነበራችሁ? የዚህ ነገር መጨረሻው ሞት ነውና።
²² አሁን ግን ከኃጢአት አርነት ወጥታችሁ ለእግዚአብሔርም ተገዝታችሁ፥ ልትቀደሱ ፍሬ አላችሁ፤ መጨረሻውም የዘላለም ሕይወት ነው።
²³ የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነውና፤ የእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን የዘላለም ሕይወት ነው።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ያዕቆብ 4
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ በእናንተ ዘንድ ጦርና ጠብ ከወዴት ይመጣሉ? በብልቶቻችሁ ውስጥ ከሚዋጉ ከእነዚህ ከምቾቶቻችሁ አይደሉምን?
² ትመኛላችሁ ለእናንተም አይሆንም፤ ትገድላላችሁ በብርቱም ትፈልጋላችሁ፥ ልታገኙም አትችሉም፤ ትጣላላችሁ ትዋጉማላችሁ ነገር ግን አትለምኑምና ለእናንተ አይሆንም፤
³ ትለምናላችሁ፥ በምቾቶቻችሁም ትከፍሉ ዘንድ በክፉ ትለምናላችሁና አትቀበሉም።
⁴ አመንዝሮች ሆይ፥ ዓለምን መውደድ ለእግዚአብሔር ጥል እንዲሆን አታውቁምን? እንግዲህ የዓለም ወዳጅ ሊሆን የሚፈቅድ ሁሉ የእግዚአብሔር ጠላት ሆኖአል።
⁵ ወይስ መጽሐፍ፦ በእኛ ዘንድ ያሳደረው መንፈስ በቅንዓት ይመኛል ያለው በከንቱ እንደ ተናገረ ይመስላችኋልን?
⁶ ነገር ግን ጸጋን አብልጦ ይሰጣል፤ ስለዚህ፦ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፥ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል ይላል።
⁷ እንግዲህ ለእግዚአብሔር ተገዙ፤ ዲያብሎስን ግን ተቃወሙ ከእናንተም ይሸሻል፤
⁸ ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ወደ እናንተም ይቀርባል። እናንተ ኃጢአተኞች፥ እጆቻችሁን አንጹ፤ ሁለት አሳብም ያላችሁ እናንተ፥ ልባችሁን አጥሩ።
⁹ ተጨነቁና እዘኑ አልቅሱም፤ ሳቃችሁ ወደ ኀዘን ደስታችሁም ወደ ትካዜ ይለወጥ።
¹⁰ በጌታ ፊት ራሳችሁን አዋርዱ ከፍ ከፍም ያደርጋችኋል።
¹¹ ወንድሞች ሆይ፥ እርስ በርሳችሁ አትተማሙ። ወንድሙን የሚያማ በወንድሙም የሚፈርድ ሕግን ያማል በሕግም ይፈርዳል፤ በሕግም ብትፈርድ ፈራጅ ነህ እንጂ ሕግን አድራጊ አይደለህም።
¹² ሕግን የሚሰጥና የሚፈርድ አንድ ነው፤ እርሱም ሊያድን ሊያጠፋም የሚችል ነው፤ በሌላው ግን የምትፈርድ አንተ ማን ነህ?
¹³ አሁንም፦ ዛሬ ወይም ነገ ወደዚህ ከተማ እንሄዳለን በዚያም ዓመት እንኖራለን እንነግድማለን እናተርፍማለን የምትሉ እናንተ፥ ተመልከቱ፥ ነገ የሚሆነውን አታውቁምና።
¹⁴ ሕይወታችሁ ምንድር ነው? ጥቂት ጊዜ ታይቶ ኋላ እንደሚጠፋ እንፍዋለት ናችሁና።
¹⁵ በዚህ ፈንታ። ጌታ ቢፈቅድ ብንኖርም ይህን ወይም ያን እናደርጋለን ማለት ይገባችኋል።
¹⁶ አሁን ግን በትዕቢታችሁ ትመካላችሁ፤ እንደዚህ ያለ ትምክህት ሁሉ ክፉ ነው።
¹⁷ እንግዲህ በጎ ለማድረግ አውቆ ለማይሠራው ኃጢአት ነው።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 7
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁴⁴ እንዳየው ምስል አድርጎ ይሠራት ዘንድ ሙሴን ተናግሮ እንዳዘዘው፥ የምስክር ድንኳን ከአባቶቻችን ዘንድ በምድረ በዳ ነበረች፤
⁴⁵ አባቶቻችንም ደግሞ በተራ ተቀብለው እግዚአብሔር በፊታቸው ያወጣቸውን የአሕዛብን አገር በያዙት ጊዜ ከኢያሱ ጋር አገቡአት፥ እስከ ዳዊት ዘመንም ድረስ ኖረች።
⁴⁶ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ አግኝቶ ለያዕቆብ አምላክ ማደሪያን ያገኝ ዘንድ ለመነ።
⁴⁷ ነገር ግን ሰሎሞን ቤት ሠራለት።
⁴⁸-⁵⁰ ነገር ግን ነቢዩ፦ ሰማይ ዙፋኔ ነው ምድርም የእግሬ መረገጫ ናት፤ ለእኔ ምን ዓይነት ቤት ትሠራላችሁ? ይላል ጌታ፥ ወይስ የማርፍበት ስፍራ ምንድር ነው? ይህንስ ሁሉ እጄ የሠራችው አይደለምን? እንዳለ፥ ልዑል የሰው እጅ በሠራችው አይኖርም።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ነሐሴ_5_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"ዘይሁብ ሲሳየ ለኲሉ ዘሥጋ። እስመ ለዓለም ምሕቱ። ግነዩ ለአምላክ ሰማይ"። መዝ 135፥26
“የሰማይን አምላክ አመስግኑ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና።”መዝ 135፥26
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ነሐሴ_5_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ዮሐንስ 7
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
³² ፈሪሳውያንም ሕዝቡ ስለ እርሱ እንደዚህ ሲያንጐራጕሩ ሰሙ፤ የካህናት አለቆችም ፈሪሳውያም ሊይዙት ሎሌዎችን ላኩ።
³³ ኢየሱስም፦ ገና ጥቂት ጊዜ ከእናንተ ጋር እቆያለሁ ወደ ላከኝም እሄዳለሁ።
³⁴ ትፈልጉኛላችሁ አታገኙኝምም፤ እኔም ወዳለሁበት እናንተ ልትመጡ አትችሉም አለ።
³⁵ እንግዲህ አይሁድ፦ እኛ እንዳናገኘው ይህ ወዴት ይሄድ ዘንድ አለው? በግሪክ ሰዎች መካከል ተበትነው ወደሚኖሩት ሊሄድና የግሪክን ሰዎች ሊያስተምር አለውን?
³⁶ እርሱ፦ ትፈልጉኛላችሁ አታገኙኝምም እኔም ወዳለሁበት እናንተ ልትመጡ አትችሉም የሚለው ይህ ቃል ምንድር ነው? ብለው እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ።
³⁷ ከበዓሉም በታላቁ በኋለኛው ቀን ኢየሱስ ቆሞ፦ ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ ይምጣና ይጠጣ።
³⁸ በእኔ የሚያምን መጽሐፍ እንዳለ፥ የሕይወት ውኃ ወንዝ ከሆዱ ይፈልቃል ብሎ ጮኸ።
³⁹ ይህን ግን በእርሱ የሚያምኑ ሊቀበሉት ስላላቸው ስለ መንፈስ ተናገረ፤ ኢየሱስ ገና ስላልከበረ መንፈስ ገና አልወረደም ነበርና።
⁴⁰ ስለዚህ ከሕዝቡ አያሌ ሰዎች ይህን ቃል ሲሰሙ፦ ይህ በእውነት ነቢዩ ነው አሉ፤
⁴¹ ሌሎች፦ ይህ ክርስቶስ ነው አሉ፤ ሌሎች ግን፦ ክርስቶስ በእውኑ ከገሊላ ይመጣልን?
⁴² ክርስቶስ ከዳዊት ዘር ዳዊትም ከነበረባት መንደር ከቤተ ልሔም እንዲመጣ መጽሐፍ አላለምን? አሉ።
⁴³ እንግዲህ ከእርሱ የተነሣ በሕዝቡ መካከል መለያየት ሆነ፤
⁴⁴ ከእነርሱም አንዳንዶቹ ሊይዙት ወደዱ ነገር ግን እጁን ማንም አልጫነበትም።
⁴⁵ ሎሌዎቹም ወደ ካህናት አለቆችና ወደ ፈሪሳውያን መጡ፤ እነዚያም፦ ያላመጣችሁት ስለ ምን ነው? አሉአቸው።
⁴⁶ ሎሌዎቹ፦ እንደዚህ ሰው ማንም እንዲሁ ከቶ አልተናገረም ብለው መለሱ።
⁴⁷ እንግዲህ ፈሪሳውያን፦ እናንተ ደግሞ ሳታችሁን?
⁴⁸ ከአለቆች ወይስ ከፈሪሳውያን በእርሱ ያመነ አለን?
⁴⁹ ነገር ግን ሕግን የማያውቀው ይህ ሕዝብ ርጉም ነው ብለው መለሱላቸው።
⁵⁰ ከእነርሱ አንዱ በሌሊት ቀድሞ ወደ እርሱ መጥቶ የነበረ ኒቆዲሞስ፦
⁵¹ ሕጋችን አስቀድሞ ከእርሱ ሳይሰማ ምንስ እንዳደረገ ሳያውቅ በሰው ይፈርዳልን? አላቸው።
⁵² እነርሱም መለሱና፦ አንተም ደግሞ ከገሊላ ነህን? ነቢይ ከገሊላ እንዳይነሣ መርምርና እይ አሉት።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #እመቤታች_የማርያም_ቅዳሴ ነው። መልካም ዕለተ ሰንበትና የሱባኤ የጾም ጊዜ በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ነሐሴ_6

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ነሐሴ ስድስት በዚህች ቀን ጌታችን ሰባት አጋንንትን ከእርሷ ያወጣላት የከበረች #ቅድስት_መግደላዊት_ማርያም አረፈች፣ ከቂሳርያና ከቀጰዶቅያ አገር የከበረች #ቅድስት_ኢየሉጣ ምስክር ሁና አረፈተች ፣ታላቁ አባት #አቡነ_ኢዮስያስ መታሰቢያ በዓላቸው ነው

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_መግደላዊት_ማርያም

ነሐሴ ስድስት በዚህች ቀን ጌታችን ሰባት አጋንንትን ከእርሷ ያወጣላት የከበረች መግደላዊት ማርያም አረፈች። የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስን ተከትላ ያገለገለችው በመከራውም ጊዜ ከባልንጀሮቿ ጋራ የነበረች እስከ ቀበሩትም ድረስ ያልተለየች እናት ነች።

በእሑድ ሰንበትም ገና ጨለማ ሳለ በማለዳ ማርያም ወደ መቃብር ገሥግሣ ሔደች ደንጊያውንም ከመቃብሩ አፍ ተገለባብጦ መልአክም በላዩ ተቀምጦ አየችው ከእርሷም ጋራ ጓደኛዋ ማርያም አለች። መልአኩም እናንተስ አትፍሩ ጌታ ኢየሱስን እንድትሹት አውቃለሁና ግን ከዚህ የለም እነሣለሁ እንዳለ ተነሥቷል አላቸው ።

ለእርሷም ዳግመኛ ተገልጾላት ሒደሽ ለወንድሞቼ እኔ ወደ አባቴ ወደ አባቴታችሁ ወደ አምላኬ ወደ አምላካችሁ እንደማርግ ንገሪያቸው አላት። ወደ ሐዋርያትም መጥታ የመድኃኒታችንን መነሣቱን እንዳየችውና ንገሪ እንዳላትም አበሠረቻቸው።

ከዕርገቱም በኋላ ሐዋርያትን እያገለገለቻቸው ኖረች። በኃምሳኛው ቀንም መንፈስ ቅዱስ በወረደ ጊዜ በወንዶችና በሴቶች አገልጋዮቼ ላይ ቅዱስ መንፈሴን አሳድራለሁ አለ ብሎ ኢዩኤል ትንቢት እንደ ተናገረ ያንን አጽናኝ መንፈስ ቅዱስን ከሐዋርያት ጋር ተቀብላለች።

ከዚህም በኋላ ከሐዋርያት ጋራ ወንጌልን ሰበከች ብዙዎች ሴቶችንም የክብር ባለቤት ወደሆነ ወደጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሃይማኖት መልሳ አስገባቻቸው። ሴቶችን ስለ ማስተማርም ሐዋርያት ዲያቆናዊት አድርገው ሾሟት ከአይሁድም በመገረፍ በመጐሳቈል ብዙ መከራ ደረሰባት። ተጋድሎዋንም ፈጽማ በሰላም በፍቅር አረፈች።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_ኢየሉጣ_ዘቂሳርያ

በዚህች ቀን ከቂሳርያና ከቀጰዶቅያ አገር የከበረች ኢየሉጣ ምስክር ሁና ሞተች። ይቺም ቅድስት ከወላጆቿ ብዙ ገንዘብን ወረሰች ከታጋዮችም አንዱ በግፍ በላይዋ ተነሥቶ ጥሪቷን ሁሉ ወንዶች ሴቶች ባሮቿንም ለዳኛ መማለጃ በመስጠት ነጠቃት።

ይህም ዐመፀኛ እንደምትከሰውና ሐሰቱንም እንደምትገልጥበት በአወቀ ጊዜ ወደ ቂሳርያው ገዢ ሒዶ ክርስቲያን እንደ ሆነች ወነጀላት። በልቧም እንዲህ አለች የዚህ ዓለም ገንዘብ ኃላፊ ጠፊ አይደለምን እነሆ እርሱን ነጠቁኝ የሰማይ ድልብን ገንዘብ ካደረግሁ ማንም ከእኔ ነጥቆ ሊወስድብኝ አይችልም።

ያን ጊዜም ወደ መኰንኑ ቀረበች በፊቱም ቁማ እንዲህ አለች እኔ ክርስቲያዊት ነኝ ሰማይና ምድርን በውስጣቸውም ያለውን ሁሉ በፈጠረ በሕያው እግዚአብሔር ልጅ በጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ አምናለሁ። መኰንኑም ሰምቶ ተቆጣ ወደ እሳትም ውስጥ እንዲወረውሩዋት አዘዘ ነፍሷንም በእግዚአብሔር እጅ ሰጠች።

ነገር ግን እሳቱ አልነካትም ምንም ምን አላቃጠላትም ከውኃ ውስጥ እንደሚወጣም ከእሳት ውስጥ አወጧት። ስለ ገንዘቧና ስለ ጥሪቷም የማያልፍ የሰማይ መንግሥትን ወረሰች። ቅዱስ ባስልዮስም ብዙ ወድሷታል።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አቡነ_ኢዮስያስ

ዳግመኛም በዚህች ቀን ታላቁ አባት አቡነ ኢዮስያስ መታሰቢያ በዓላቸው ነው። ትውልዳቸው ሸዋ ሲሆን የንጉሥ ዓምደ ጽዮን ልጅ ናቸው፡፡ ጥር 6 ቀን ሲወለዱ ቅዱሳን መላእክት ከበዋቸው ታይተዋል፡፡ የንጉሥ ልጅ ቢሆኑም በዓለም ነግሠው መኖርን ንቀው በመመነን በመጀመሪያ ወደ ሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም ገቡ፡፡ አቡነ ኢዮስያስ በሐይቅ ገዳም ለ14 ዓመታት በታላቅ ተጋድሎ ኖረዋል፡፡ በዚያም ብሉይንና ሐዲስን፣ መጽሐፈ መነኮሳትንና መጽሐፈ ሊቃውንትን አጠናቀው ተምረዋል፡፡ በኋላም በእግዚአብሔር ትእዛዝ ወደ ትግራይ ደብረ በንኮል ገዳም ሄዱ፡፡ በደብረ በንኮልም በታላቅ ተጋድሎ ኖረው በታላቁ አባት በአቡነ መድኃኒነ እግዚእ እጅ መነኮሱ፡፡ ቆብ የተቀበሉት ግን ከአቡነ ተክለሃይማኖት ነው፡፡

አቡነ መድኃኒነ እግዚእም ሰባት ዓመት ከእሳቸው ጋር ካቆዩአቸው በኋላ አቡነ ኢዮስያስን ወንጌልን ዞረው እንዲሰብኩና ገዳም እንዲገድሙ በማዘዝ መርቀው ሸኝተዋቸዋል፡፡ አቡነ ኢዮስያስም ወደ አዱዋ አውራጃ ዛሬ በስማቸው ወደተጠራው ገዳም ሄደው በቦታው ላይ በተጋድሎ ኖሩ፡፡ ገዳሙንም ከገደሙት በኋላ በርካታ መነኮሳትን አፍርተዋል፡፡ ጻድቁ ያፈለቁት ጠበል በፈዋሽነቱ የታወቀ ነው፡፡ በየዓመቱ በዕረፍታቸው ዕለት ነሐሴ 6 ቀን ሶሀባ በሚባለው ቦታ ቆመው በጸለዩበት ወንዝ ላይ ዓሣ ከሰማይ ይዘንባል፡፡ ይህ አሁንም ድረስ በየዓመቱ ነሐሴ 6 ቀን በግልጽ እየታየ ይገኛል፡፡

አቡነ ኢዮስያስን ከሃዲያን የሆኑ አረማውያን ቢያስቸግሯቸው ጻድቁም በጸሎት ቢያመለክቱ ከየት እንደመጣ የማይታወቅ ነጭ የንብ መንጋ መጥቶ አረማውያኑን አንጥፍቶላቸዋል፡፡ ጻድቁ በጸሎታቸው አራት ሙታንን በአንድ ጊዜ ከሞት ያስነሡ ታላቅ አባት ናቸው፡፡ በገዳማቸው ውስጥ በበዓላቸው ቀን ገድላቸው ሲነበብ አጋንንት ከሰው ልቡና እንደ ትቢያ በነው ይጠፋሉ፡፡ ጻድቁን እንደ ረድእ ሆኖ የሚያገለግላቸው አንበሳ ነበራቸው፡፡ ወደ ገዳማቸው መጥቶ መካነ ዐፅማቸውን የተሳለመውን እስከ 14 ትውልድ ድረስ እንደሚምርላቸው ጌታችን ቃልኪዳን ገብቶላቸዋል፡፡ ልጁን በስማቸው የተሰመ ቢኖር የሰይጣንን ፊት ፈጽሞ እንደማያይ ገድላቸው ይናገራል፡፡

#ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ነሐሴ_6 እና #ከገድላት_አንደበት)
2024/09/22 11:46:09
Back to Top
HTML Embed Code: