Telegram Web Link
በዚህችም ቀን ደግሞ ይስሐቅ በሰማዕትነት ሞተ። ይህም ቅዱስ ሳምሳ ከምባል አገር ነበር እሱም የአታክልት ቦታዎች ጠባቅ ነበረ ደግ የዋህና ፁሙድ አገልጋይ ነበረ ሰጋም አይበላም ነበር ወይንም አይጠጣም ነበር በየሁለት ቀን ይፆም ነበረ ቅጠልም ይበላ ነበረ ድሆችንና ችግረኞችንም ይጎበኛቸው ነበረ ከደመዙም የምተርፈውም ይሰጣቸዋል።

ክብር ይግባውና ጌታችንም በራእይ ተገለጠለትና ወደ መኩንኑም ሒዶ በቅዱስ ስሙ እንዲታመን አዘዘው ከዝህም ቡኃላ ብዙ ቃል ክዳን ሰጠው ያዘጋጀለትንም የደስታ አክልሎችን ተስፍ አስደረገው።

በነቃ ግዜም እጅግ ደስ አለው ተነሥቶም ከእርሱ ያለውን ገንዘብ ለድሆች ሰጠ ከዝያም ቡኃላ ይረዳው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ ወደ መኩንኑም ደርሶ ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ታመነ መኩንኑም ጽኑ ሥቃይን አሠቃየው በእሳትም አቃጠለው ሕዋሳቱንም ቆራርጦ ሰቀለው በመንኩራኲርም አበራየው ጌታችንም ያጸናውና ይፈውሰው ነበር ከመሠቃየቱም የተነሣ በሰለቸ ጊዜ ራሱን በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ የሰማዕትነትንም አክልሊ በመንግስተ ሰማያት ተቀበለ።

ከዚህም በኃላ ምእመናን ሰዎች ከሀገሩ ሳምሳ መጥተው ሥጋውን ወሰዱ በአማሩ ልብሶችንም ገንዘው የመከራው ዘመን እስክፈጸም ድረስ በመልካም ቦታ አኖሩትከዝያም ቡኃላ ውብ የሆነች ቤተክርስትያን ሠሩለት ሥጋውን በዝያ አኖሩት ከእርሱም ድንቆችና ተአምራቶች ተገለጡ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_ኢላርያ

ዳግመኛም በዚች ቀን በድሜራ አቅራብያ ድምድል ከሚባል አገር ቅድስት ኢላርያ በሰማዕትነት ሞተች። የዚችም ቅድስት ወላጆቿ ደጎች ምእመናን ነበሩ እርሷዋም በስጋዋና በነፍሷ የነጻች ነበረች ሁሉ ጊዜም ተጻምና ትጸልይ ነበረች።

አሥራ አንድ አመትም በሆናት ጊዜ እርሷ ቆማ ስትጸልይ ጌታችን ታላቅ። ብርሃንን ገለጠላት የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሩፍኤልም ተገልጦ እንድህ አላት ተጋድሎ ተዘርግቶ ሳለ ክብር ይግባውና በክርስቶስ ስም ለምጋደሉም አክልሎች ተዘጋጅተው ሳሉ አንቺ ለምን ከዝህ ተቀምጣሻል አላት።

ይህንንም በሰማች ግዜ ደስ አላት ገንዘቧዋንም ሁሉ ለድኖችና ለችግረኞች ሰጥታ ጣው ወደ ምባል አገር ሔደች ከዝያም ስርስና ወደ ምባል አገር ሒዳ በመኩንኑ ፊት ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰም ታመነች ጌታችንም ሳኑሲ ለሚባል ሰው ለዝች ቅድስት ከእርሷ የሚሆነውን ነገረው።

ባያትም ጊዜ በእርሷ ደስ አለው አረጋጋት ልቧንም አጸናናት መኩንኑም ታላቅ ሥቃይን አሰቃያት ሥጋዋን ሁሉ ሠነጣጠቀ በእሳት ያጋሏቸውንም የብረት ችንካሮች በሥጋዋ ውስጥ ቸነከሩ።

ከዝህም ቡኃላ ከአምስት መቶ ባልንጀራሞች ሰማዕታት ጋራ አሠራት በመርከቦችም ከእርሱ ጋራ ወስዳቸው እነርሱም በመርከብ ስጓዙ አንበሪ መጥቶ ከእናቱ እቅፍ አንዱን ሕፃን ልጅ ነጥቆ ወሰደ እናቱም ከእርሱ በቀር ሌላ ስለሌላት እጅግ አዝና አለቀሰች ይች ቅድስትም አይታ ራራችላት ስለእርስዋም ጌታችንን ለመነችው ጌታችንም አንበርውን አዘዘውና ሕፃኑን ደኅና እንደሆነ ወደ እናቱ መለሰው ምንም ጥፋት አላገኘውም።

ከዚህም በኃላ ሕዋሳቷን ቆራረጡ የእጆቿንና የእግሮቿን ጥፍሮች ነቀሉ ምላሷንም ቆረጡ እግሮቿንም በብረት ችንካሮች ቸነከሩ። በብረት ዐልጋ ላይም አስተኝተው ከበታችዋ እሳትን አነደዱ። ነገር ግን ምንም ምን ጥፋት አልደረሰባትም ክብር ይግባውና ጌታችን አድኗታልና።

መኮንኑም እርሷን ከማሠቃየት የተነሣ በሰለቸ ጊዜ ራሷን በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘ የሰማዕትነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለች።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱሳት_ቴክላና_ሙጊ

በዚችም ቀን ከእስክንድርያና ከባሕያራ አውራጃ ቀራቁስ ከሚባል መንደር የከበሩ ቴክላና ሙጊ ሰማዕታት ሆኑ። እሊህም ቅዱሳት ቀራቁስ በሚባል መንደር በአንዲት እግዚአብሔርን በምትፈራ አማኒት ሴት ዘንድ አደጉ።

ወደ ባሕር ዳርቻ በአለፉ ጊዜም የክርስቲያን ወገኖችን ሲአሠቃያቸው መኰንኑን አዩት። እነዚያም ደናግል ስለ ልቡ ደንዳናነት አደነቁ ያን ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ተገለጠላቸው ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም መከራን ለሚታገሡ ለቅዱሳን ሰማዕታት የተዘጋጀውን ክብራቸውን አሳያቸውና አጽናናቸው።

ከዚህም በኃላ በመርከብ ተጭነው ወደ እስክንድርያ ተጓዙ። እመቤታችን ማርያምም አልቃሾች በሆኑ በሁለት ሴቶች አምሳል ከኤልሳቤጥ ጋራ ተገለጸችላቸው ከእርሳቸውም ጋራ ወደ ከተማው በደረሱ ጊዜ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም በመኮንኑ ፊት ታመኑ መኰንኑም ጽኑ ሥቃይን አሠቃያቸው።

ከዚህም በኃላ የቅድስት ሙጊን ራስ በሰይፍ ቆረጠ ተጋድሎዋንም ፈጸመች። ቅድስት ቴክላን ግን ድሙጢ ወደሚባል አገር ላካት በዚያ ሰማዕት ሆነች።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አበከረዙን

በዚችም ቀን ዳግመኛ ባንዋን ከሚባል አገር ቅዱስ አበከረዙን ሰማዕት ሆነ። ይህም ቅዱስ አስቀድሞ ወንበዴ ነበር ሌሎችም ሁለት ወንበዴዎች ነበሩ ገንዘቡን ሊሰርቁ ወደ አስቄጥስ ገዳም ወደ አንድ መነኩስ በአንድነት ሔዱ በጸሎትም እየተጋ አገኙት ጸሎቱን ጨርሶ እስቲተኛ ድረስ ጠበቁት እርሱ ግን ከቶ አልተኛም በልቡናቸውም ፍርሀት አደረባቸውና ደነገጡ።

በነጋ ጊዜም ያ ሽማግሌ መነኰስ ወደ ሽፍቶቹ ወጣ ባዩትም ጊዜ ከእግሩ በታች ሰገዱ ሰይፎቻቸውንም በፊቱ ጥለው ደቀ መዝሙሮቹ ያደርጋቸው ዘንድ ለመኑት በርሱም ዘንድ መነኰሱ። ቅዱስ አባ አበከረዙንም በሥጋውም በመንፈሱም ታላቅ ተጋድሎን ተጋደለ። አንድ አረጋዊም ክብር ይግባውና ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ሰማዕት ይሆን ዘንድ እንዳለው ነገረው።

ከሰባት ዓመት በኃላም ሰይጣን በክርስቲያን ወገኖች ላይ መከራን አመጣ አባ አበከረዙንም ተነሥቶ መንፈሳዊ አባቱን እጅ ነሥቶ ከእርሱም ቡራኬ ተቀብሎ ኒቅዮስ ወደሚባል አገር ሔደ ንጉሥ መክስምያኖስንም አገኘው ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሰም በፊቱ ታመነ መኰንኑም በጽኑ ስቃይ አሰቃየው በብረት መጋዝም ስጋውን መገዘው ቁስሉንም በመጣጣና በጨው አሸው።

ከዚህም በኋላ ወደ እስክንድርያ ከተማ ሲወስዱት አምስት ጊዜ በመርከብ ምሰሶ ላይ ሰቀሉት ገመዶችም ተበጠሱ ከማስ በተሠራ ጋን ውስጥም አድርገው በባሕር ጣሉት ከእግዚአብሔርም የተላከ መላክ ከባሕር አውጥቶ ወደ ገምኑዲ ከተመሰ እንዲሔድ አዘዘው ብንውም ወደሚባል አገር ደረሰ ስለ አባ አበከረዙንም ጠየቀ እነርሱም አላወቁትም ነበርና ከብዙ ጊዚያትም ጀምሮ ከዚህ ሔዷል ወዴት እንዳለም አናውቅም ወሬውንም አልሰማንም አሉት።

አንዲት ብላቴና ግን አስተውላ አወቀችው ፈራችም ከፍርሀቷም ብዛት የተነሣ ወደቀችና እንስራዋ ተሰበረ እርሷም ሰዎች ይህ አባ አበከረዙን ነው አለቻቸው የአገሩ ሰዋችም ሁሉም ፈጥነው መጥተው ከእርሱ ተባረኩ ደዌ ያለባቸውም ወደርሱ ይመጡ ነበር እርሱም በዘይት ላይ ጸልዮ ሲቀባቸው ወዲያውኑ ይድኑ ነበር።

ከዚህም በኋላ ወደ ገመኑዲ ከተማ ሔደ ከወታደሮቹም አንዱን እኔ ክርስቲያን ነኝና በዚች ከተማ ውስጥ አሥረህ ጎትተኝ አለው እርሱም ወደ መኰንኑ እስከሚአደርሰው እንደ አዘዘው አደረገ መኰንኑም በእንጨት ላይ ዘቅዝቆ ሰቀለው በአፍንጫውና በአፋም ብዙ ደምእየፈሰሰ ዐሥር ቀኖች ኖረ አባ አበከረዙንም የጭፍራ አለቃውን ልጅ ረገማትና ወዲያውኑ ሞተች በመቃብርም ዐሥራ ሁለት ቀኖች ኖረች። ስለ እርሷም አባ አበከረዙንን ለመኑት ክብር ይግባውና ወደጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጸለየ ያንጊዜም ከሙታን ተለይታ ተነሥታ
በሲኦል ያየችውን ሁሉ ነገረቻቸው ከጭፍሮቹ ጋር ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አምነው በሰማዕትነት ሞቱ ቁጥራቸውም ዘጠኝ መቶ አርባ አምስት ነፍስ ነበር።

ከዚህ በኋላ አባ አበከረዙንን ወደ እስክንድርያ ሰደደው በዚያም ጽኑ ሥቃይን አሠቃዩት ዳግመኛ ወደ ገምኑዲ ላኩት በዚያም በብረት በትሮች ደብድበው የጀርባውን አጥንት ሰበሩት እርሱ ግን በፈጣሪው ኃይል ዳነ።

መኰንኑም ማሰቃየት በደከመ ጊዜ ዳግመኛ ወደ እስክንድርያ ከተማ ላከው ወደ እስክንድርያም በሚያዚያ ወር በደረሰ ጊዜ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገለጠለትና አጽናናው ገድሉንም በዚያ እንደሚፈጽም ነገረው።

ስሙን ለሚጠራ ሁሉ መታሰቢያውንም ለሚያደርግ ኃጥያቱን እንደሚያስተሠርይለት ቃል ኪዳን ሰጠው ከዚህም በኃላ ራሱን ቆረጡት ተጋድሎውንም ፈጽሞ የሰማዕትነትን አክሊል ተቀበለ።

የእግዚአብሔር መልአክም መኑፍ ከሚባል አገር ለአንድ ቄስ ተገልጦ የቅዱስ አበከረዙን ሥጋ ያለበትን ቦታ ነገረውና እንዲወስደው አዘዘ። እርሱም ወስዶ ባማሩ ልብሶች ገነዘው የመከራውም ወራት እስከሚፈጸም በመልካም ቤት አኖረው ከዚህም በኋላ ቦታ ክርስቲያን ሰርተውለት ሥጋውን በውስጧ አኖሩ ከእርሱም ድንቆችና ተአምራቶች ተገለጡ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ሰማዕት_ዱማድዮስ

ዳግመኛም በዚች ቀን የሶርያ ሰው ቅዱስ ሰማዕት ዱማድዮስ አረፈ። ይህም ቅዱስ በፋርስ አገር አደገ የከዋክትን ምግብን ጥበብ ተማረ ከዚህም በኋላ ክርስርስቲያን ሊሆን ወደደ ከፋርስ ሰዎችም ስሙ አጋሊዮስ የሚባል ቄስ በገበያ ውስጥ አገኘ እርሱም ወደ እግዚአብሔር የሚያደርስ ሃይማኖትን አስተማረው እጅግ ደስ ብሎት ቤተሰቦቹን ወደ እግዚአብሔር ይመለሱ ዘንድ ያስተምራቸው ጀመረ አሳመናቸውም።

ከዚህም በኋላ በሶሪያና በሮም መካከል ወዳለች አገር ሔደ በዚያም የክርስትና ጥምቀትን ተጠመቆ መነኮሰ ታላቅ ተጋድሎንም መጋደል ጀመረ መነኰሳቱም ታላቅ የሆነ ተጋድሎውን በአዩ ጊዜ በእርሱ ላይ ቀንተው ከገዳም ሊያሳድዱት ወደዱ።

በአወቀም ጊዜም ወጥቶ ወደ ቅዱስ ሰርጊዮስ ገዳም ሔደ በዚያም በአንድ ባህታዊ ቄስ ዘንድ ተቀመጠ ከዚህም በኋላ ዲቁና እንዲሾመውና ከእርሱ ጋር በቤተ መቅደስ ውስጥ እንዲያገለግል ቅዱስ ዲማድዮስን አስገደደው ትዛዙንም መተላለፍ ባልተቻለው ጊዜ ዲቁና ተሾመ።

አረጋዊው ቄስ በመሰዊያው ላይ በሚሰየም ጊዜ በቅዳሴው እኩሌታ በምሥዋቱ ላይ ርግብ ስትወርድ ቀዱስ ዱማድዮስ ያያት ነበር እርሱም ሥጋዊት ርግብ እንደሆነች ያስብ ነበር ሽማግሌው ግን አያያትም ነበር የቅዳሴው ሥርዓት ከተፈጸመ በኋላ ባሕታዊው ቄስ እንዲህ ብሎ ጠየቀው በቅዳሴ ጊዜ የምትደነግጥ እጅህንም ወደ መሥዋቱ የምትዘረጋው ምን ሆነህ ነው እርሱም ርግቧን እንዳያት ነገረው ከእንግዲህ ስታያት ንገረኝ አለው።

ከዚያም በኋላ በአያት ጊዜ አባቴ ሆይ ያቺ ርግብ መጣች ብሎ ነገረው ሽማግሌው ግን አላያትምእጅግም አዝኖበእግዚአብሔር ፊት ሰገደ ያቺንም ርግብ እስከሚያያት ድረስ ፈጽሞ ይጸልይና ይማልድ ነበር ያቺ ርግብ መንፈስ ቅዱስ እንደ ሆነ ያውቅ ነበርና ለዲያቆን አባ ዱማድዮስም ልቡ እንዳይታበይ አልነገረውም።

ከዚህ በኃላም ሽማግሌው ቄስ ወደ ኤጲስቆጶስ ሒዶ ዱማድዮስን የቅስና መዐረግ ይሾምለት ዘንድ ለመነው ልመናውንም ተቀብሎ ያለ ውዴታው ቅስናን ሾመው።

ሊቀ ጳጳሳቱም ዜናውንና ገድሉን በሰማ ጊዜ ከእርሱ ጋራ ወገኖቹን ወሰደ ከወገኖቹ ጋራም ወደርሱ ሔዶ በረከቱን ሊቀበል ወደደ። ቅዱስ ዱማድዮስ ግን በመንፈስ ቅዱስ አውቆ ከዚያ ተሠውሮ ሔደ ወደ ሰማዕቱ ቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያንም ደረሰ ከዚያም ወደ በረሀ ሔዶ በዚያ ሣር እየበላ ኖረ እርሱ ከከንቱ ውዳሴ ይሸሽ ነበረና።

እግዚአብሔርም በእጆቹ ድንቆችንና ተአምራቶችን ያደርግ ነበር። በአንዲት ቀንም ውኃ ሊቀዳ ወደ ወንዝ ሔደ ውኃ የሚቀዱ ሴቶችም አይተውት በመጠቃቀስ በእርሱ ላይ ተዘባበቱ በልቡም እያዘነ ውኃ ሳይቀዳ ተመለሰ ያን ጊዜም ወንዙ ደረቀ።

ሰዎችም ቅዱስ ዱማድዮስ እንዳደረቀው በአወቁ ጊዜ ሴቶችና ወንዶች ሁሉ ወጥተው በብዙ ለቅሶ ለመኑት ልቅሶአቸውንም አይቶ ክብር ይግባውና ጌታችንን ለመነው የወንዙንም ውኃ እንደ ቀድሞው መለሰላቸው።

ሰዎችም ሲያከብሩት በአየ ጊዜ ከዚያ መጠለያ ከሰማይ በታች ያለውን የበጋውን ቃጠሎና የክረምቱን ቅዝቃዜ ታግሦ እየተጋደለ ዓመት ሙሉ ኖረ በብዙ ድካምም አስገድደው ትንሽ ጎጆ ሠርተው በውስጧ አስገብት።

ከእርሱም ብዙዎች ድንቆችና ተአምራቶች ተገለጡ ከእነርሱም አንድ ዐይኑ የታወረች አንድ ሰው ነበረ ከእርሱም በተባረከ ጊዜ ዐይኑ ድና አየች እንደ ሁለተኛዋም ሆነች ሁለተኛም ጉባጣ ሰው ወደርሱ አመጡ በውኃና በዘይትም ላይ ጸልዮ የመጻጉዑን ሥጋ አጥቦ አዳነው ዲዳውንም እንዲሁ አዳነው።

ከዚህም በኃላ ባልና መካን ሚስቱ መጡ ስለ እነርሱም ይጸልይ ዘንድ ለመኑት እርሱም ክብር ይግባውና እግዚአብሔርን ለምኖላቸው ልጆችን ሰጣቸው ወደርሱም ልጆቻቸውን አምጥተው ባረካቸው። ከዚህም የሚበዛ ብዙ ተአምራትን አደረገ።

በከሀዲው በዋሊጦስ ዘመንም የአምላክ ወዳጅ ንጉሥ ቁስጠንጢኖስ ያሠራቸውን አብያተ ክርስቲያናት ጭፍሮቹ ወደ አንጾኪያ መጥተው አፈረሱ። ከዚህም በኃላ የፋርስ ሰዎች ጦርነት ሊገጥሙት መጡ ሲጓዙም ወደ ቅዱስ ዱማድዮስ ማደሪያ ደረሱ ስለ ርሱም ለመኵንኑ ነገሩት እርሱም ይወግሩት ዘንድ አዘዘ ከረድኡም ጋራ በድንጊያ ወገሩት። የጣሉባቸው ድንጋይም በበዐታቸው ላይ ታላቅ ኮረብታ ሆነ። እርሱና ረድኡም እንዲህ በሆነ ድርጊት አረፉ።

ከአንድ ዓመትም በኃላ ለአንድ መንገደኛ ነጋዴ ሰው ገለጠለት።ገመልም ጭኖ ነበር። እርሱም ሲያልፍ ገመሉ ከምድር በታች በጉድጓድ ውስጥ ወደቀ። ሰዎችም ገመሉን ሊያወጡት በመጡ ጊዜ የቅዱስ ዱማድዮስ በዐት ተገለጠ። ቆፍረውም የቅዱስ ዱማድዮስንና የረድኡን ሥጋ በክብር አወጡ ይኸውም በአረፈበት በሐምሌ ሃያ አምስት ቀን ነበር። ቤተ ክርስቲያንም ሠርተው የእርሱን ሥጋና የረድኡን ሥጋ በውስጥዋ አኖሩ ጌታችንም ከእርሱ ብዙዎች ተአምራትን ገለጠ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

ቅዱስ_ኄኖክ_ነቢይ

በዚችም ቀን አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር ስላደረገ በሞት ፋንታ የተሰውረው ነቢዩ ቅዱስ ሄኖክ የዕርገቱ መታሰቢያ በዚህች ዕለት ሆነ፡፡ ዘፍ 5፡21፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም "ሄኖክ ሞትን እንዳያይ በእምነት ተወሰደ፥ እግዚአብሔርም ስለ ወሰደው አልተገኘም። ሳይወሰድ እግዚአብሔርን ደስ እንዳሰኘ መስክሮለታልና" በማለት ገልጾታል፡፡ ዕብ 11፡5፡፡

ነቢዩ ሄኖክ ብዙ ሰማያዊ ምሥጢራትን ያየ ነው፡፡ ስለጌታችንም እንዲህ ብሎ ትንቢትን ተናገረ፡- ‹‹የዘመናት አለቃ ወደሆነው የሰው ልጅ ተጠራ፣ ዓለም ከመፍጠሩ አስቀድሞ የነበረ ሆነ፣ ሁለተኛም ለጻድቃን የጽድቅ በትር ለአሕዛብም ብርሃን ተስፋ ለሌላቸውም አለኝታ ይሆናል›› አለ፡፡ ዳግመኛም ስለምኩራብ ሲናገር ‹‹ያንን አሮጌ ቤት እስኪያሳንሰው ድረስ አየሁ፣ ምሰሶዎቹንም ከውስጡ አውጣ፡፡ ስለ ቤተ ክርስቲያንም ጌታ አዲስ የበጎች ቤት አምጥቶ ሲሠራ አየሁ፣ ከቀድሞውም የበለጠ ነው፣ በጎችም ሁሉ በውስጧ ይሰማራሉ›› አለ፡፡ ስለ ምእመናንም ‹‹የእነዚህ በጎች ፀጉራቸው ንጹሕ ነጭ ነው፣ የተበተኑትም ከአራዊት ጋራ ይሰማራሉ፤ ሁሉም በአንድነት ተሰብስበው ገራሞች ሆነዋል›› አለ፡፡

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
#ሐምሌ_26

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ሐምሌ ሃያ ስድስት በዚች ቀን የእመቤታችን ድንግል ማርያም እጮኛዋ ለጌታችንም አሳዳጊው ለመሆን የተገባው #ጻድቁ_ዮሴፍ አረፈ፣ ለኢትዮጵያ ሀገር ብርሃንን የገለጠ ቅዱስ አባት #አባ_ሰላማ አረፈ፣ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት #ቅዱስ_ጢሞቴዎስ አረፈ፣ #አቡነ_ሳሙኤል_ዘደብረ_ሃሌሉያ ዕረፍታቸው ነው፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ጻድቁ_ዮሴፍ

ሐምሌ ሃያ ስድስት በዚች ቀን መልካም ሽምግልና የነበረው የእመቤታችን ድንግል ማርያም እጮኛዋ ድካሟን ለመሳተፍ ክብር ይግባውና ለ #ጌታችንም አሳዳጊው ለመሆኑ የተገባው ጻድቁ ዮሴፍ አረፈ።

እርሱም #እምቤታችንን በርሱ ዘንድ ካስጠበቋት ጀምሮ በሁሉ ነገር ያገለግላት ነበር። በመከራዋም ሁሉ አልተለያትም። በወለደችም ጊዜ በቤተ ልሔም ከርሷ ጋራ ነበረ። ወደ ግብጽም በተሰደደች ጊዜ ከእርሷ ጋራ ብዙ መከራ ደረሰበት። ከዚህም ዓለም የሚለይበት ጊዜው በደረሰ ጊዜ ወንዶችና ሴቶች ልጆቹን ጠርቶ ተሰናበታቸው እጆቹንም ዘርግቶ ነፍሱን በ #እግዚአብሔር እጅ ሰጠ። የዘላለምንም ሕይወት ወረሰ።

በአረፈበትም ጊዜ #ጌታችን ወደርሱ መጥቶ እጆቹን በላዩ ጫነ ለሥጋውም መፍረስና መበስበስ እንዳያገኘው ኃይልን ሰጠው በአባቱ በያዕቆብም መቃበር አኖሩት። ዕረፍቱም ክብር ይግባውና ከ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ሥጋዊ በዐሥራ ስድስት ዓመት ነው።

#ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አባ_ሰላማ_ከሳቴ_ብርሃን

በዚችም ቀን ለኢትዮጵያ ሀገር ብርሃንን የገለጠ ቅዱስ አባት አባ ሰላማ አረፈ። ዜናውም እንዲህ ነው ስሙ ሜሮጵዮስ የሚባል የጥበበኞች አለቃ አንድ ሰው ወደ ሕንድ አገር ሊአልፍ ወዶ ከጢሮስ አገር መጣ ከእርሱም ጋራ ከዘመዶቹ ወገን የሆኑ ሁለት ብላቴኖች ነበሩ። የአንደኛው ስሙ ፍሬምናጦስ የሁለተኛውም ኤዴስዮስ ይባላል። ሲድራኮስ የሚሉትም አሉ። በኢትዮጵያ በኩል ወዳለው ወደ አፍሪቃ ባሕር ወደብ ደረሱ ልቡ የተመኘችውን የኢትዮጵያን አገር መልካምነቷን ሁሉ ተመለከተ።

ከዚህም በኃላ በድንገት ወንበዴዎች ተነሥተው በመርከብ ከአሉት ሁሉ ጋር ገደሉት እኒህ ሁለት ልጆች ግን ተረፉ። የአገሩ ሰዎችም አገኙዋቸው ወደ ንጉሥም ወስደው አንደ እጅ መነሻ አድርገው እነርሱን ሰጡት ንጉሡም ተቀበላቸው።

ከጥቂት ቀኖች በኃላም ንጉሡ ኤዴስዮስን በፊቱ የሚቆም ጋሻ ዣግሬ አድርጎ ሾመው ፍሬምናጦስን ግን በገንዘቡ ሁሉ ላይ በጅሮንድ አድርጎ ሾመው ይህም ንጉሥ የአብርሀና የአጽብሐ አባታቸው ስሙ አይዛና የተባለው ነበር። እነርሱ ሕፃናት ሳሉም አረፈ። እኒህም አካለ መጠን እስከሚያደርሱ ድረስ የንጉሡን ልጆች እያሳደጉ ኖሩ ክብር ይግባውና በ #ክርስቶስ ማመንንም አስተማሩዋቸው።

የንጉሡም ልጆች አድገው በነገሡ ጊዜ ኤዴስዮስ ወደ አገሩ ተመለሰ ፍሬምናጦስ ግን ወደ ግብጽ ሔደ ወደ እስክንድርያው ሊቀ ጳጳሳት ወደ አባ አትናቴዎስም ደረሰ። የደረሰብትንም ሁሉ ነገረው። ስለ ኢትዮጵያውያንም ሃይማኖት ጳጳስ ሳይኖራቸው ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_በኢየሱስ_ክርስቶስ እንዴት እንዳመኑ ነገረው። አባ አትናቴዎስም በሰማ ጊዜ እጅግ አደነቀ ፍሬምናጦስንም የነጻ ሕዝብ አገር ለሆነችው ለኢትዮጵያ አገር ጳጳስ ይሆን ዘንድ ግድ አለው። ጵጵስነትንም ሾመ ከታላቅ አክብሮት ጋራ ላከው በአብርሀና በአጽብሐ ዘመነ መንግሥትም ወደ ኢትዮጵያ በደረሰ ጊዜ በክብር ተቀበሉት።

በኢትዮጵያም አገሮች ሁሉ የቀናች ሃይማኖትን ሰበከ አስተማረም ክብር ይግባውና #ክርስቶስን የጌትነቱን ብርሀን በሁሉ አገሮች ገለጠ ስለዚህም ብርሃንን ገላጭ ሰላማ ተባለ ሁሉንም አስተካክሎ በሰላም አረፈ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ አባት ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ጢሞቴዎስ

በዚችም ቀን ከአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ቁጥር ውስጥ የሆነው የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ ጢሞቴዎስ አረፈ። በተሾመ ጊዜም የክርስቶስን መንጋዎች ከአርዮስ ከመቅዶንዮስና ከሰባልዮስ ተኩላዎች ጠበቀ።

ይህም አባት በተሾመ በስድስተኛው ዓመት ለክርስቲያን ወገኖች ደግ የሆነ ቴዎዶስዮስ ነገሠ በዚያችም ዓመት ክብር ይግባውና #መንፈስ_ቅዱስን ስለ ካደው ስለ መቅዶንዮስ በቁስጥንጥንያ የተሰበሰቡ የመቶ ሃምሳ ቅዱሳን ኤጲስቆጶሳት ጉባኤ ተደረገ ይህም አባት ጢሞቴዎስ ሊቀ ጉባኤ ሆኖ መቅዶንዮስንና ሰባልዮስን አቡሊናርዮስንም ተከራከራቸው። ረትቶም አሳፈራቸው። እነሆ የክህደታቸውንና የክርክራቸውንም ነገር የካቲት አንድ ቀን ላይ ጽፈናል።

ከዚህም በኃላ ይህ አባት በሹመቱ ዘመን አብያተ ክርስቲያናትን በማነፅና በሚገባውም ሥራ ሁሉ በእድሳታቸውም አሰበ። ለመጻተኞችም ቤቶችን ሠራላቸው።

መንጋዎቹንም ሁልጊዜ ያስተምራቸው ነበር በመልካም እውቀቱና በትምህርቱ ጣዕም ሁልጊዜም በማስረዳቱ በቀናች ሃይማኖት አጸናቸው። ከአርዮስና ከመቅዶንዮስ ወገኖችም ብዙዎቹን መልሶ ክብር ይግባውና የ #ጌታችን_የኢየሱስ_ክርስቶስ ወደ ሆነች የቀናች ሃይማኖት አስገባቸው።

በወንጌላዊው ማርቆስ መንበርም ላይ ዘጠኝ ዓመት ተኩል ኖረ ከዚያም በኃላ በሰላም አረፈ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አቡነ_ሳሙኤል_ዘደብረ_ሃሌሉያ

በዚህችም ቀን አቡነ ሳሙኤል ዘደብረ ሃሌሉያ ዕረፍታቸው ነው፡፡ የትውልድ ሀገራቸው ተንቤን ነው፡፡ አባታቸው ይስሐለነ እግዚእ እናታቸው ትቀድሰነ ማርያም ይባላሉ፡፡ አቡነ አቢየ እግዚእ አጎታቸው ናቸው፡፡ እናታቸው እሳቸውን ፀንሳ ሳለ ቡራኬ ለመቀበል ወደ ወንድሟ ስትሄድ አቡነ አቢየ እግዚእ መሬት ላይ ወድቀው ሰግደውላታል፡፡ ደቀ መዛሙርቶቻቸውም ‹‹ለዚህች ሴት እንዴት ሰገዱላት?›› ብለው ቢጠይቋቸው አቡነ አቢየ እግዚእ ስለ አቡነ ሳሙኤል ክብርና ጽድቅ ትንቢት ነግረዋቸዋል፡፡

አቡነ ሳሙኤል ሲወለዱ እናታቸው ለአቡነ አቢየ እግዚእ ሰጠቻቸው፣ እርሳቸውም በሃይማኖት በመግባር ኮትኩተው ሁሉን አስተምረው አሳደጓቸው፡፡ አባታችን የጻድቃንና የሰማዕታትን ታሪክ እያነበቡ ያዝኑና ያለቅሱ ነበር፡፡ እንደ እነርሱ በሆንኩም እያሉ ይመኙ ነበር፡፡ አቡነ አቢየ እግዚእ ሀሳባቸውን በመንፈስ ተረድተውላቸው ነበርና መርቀው ባርከው አሰናበቷቸው፡፡ አቡነ ሳሙኤልም በሕፃንነታቸው መንነው ወደ አቡነ እንጦንዮስ ገዳም ገብተው በ14 ዓመታቸው መነኮሱ፡፡

ከየት እንደመጣ የማይታወቅና መላ አካሉ እንደበረዶ ነጭ የሆነ አንበሳ መጥቶ እየመራቸው አሁን ደብረ ሃሌሉያ እየተባለ ወደሚጠራው ገዳማቸው ሄደው በዓታቸውን አጽንተው ገዳሙን መሠረቱት፡፡ አቡነ ሳሙኤል ዘሀለሎም እየተባሉ ይጠራሉ፡፡

ጻድቁ የጌታችን መከራ በማሰብ ከተወለዱ ጀምሮ ተላጭተውት የማያውቁትን ፀጉራቸውን ከትልቅ ዛፍ ላይ እያሠሩ ይጸልዩ ነበር፡፡ እንዲሁ አድርገው ዛፍ ላይ ራሳቸውን ሰቅለው 40 ቀንና 40 ሌሊት ሲጸልዩ በመጨረሻ የታሠሩበት ፀጉራቸው ተነቅሎ ከመሬት ላይ ወደቁ፡፡ ደማቸውም እንደ ውኃ ፈሰሰ፡፡ ክብር ይግባውና #ጌታችንም ቅዱስ ሚካኤልንና ቅዱስ ገብርኤልን አስከትሎ ተገልጦላቸው እጃቸውን ይዞ አንሥቷቸዋል፡፡ ‹‹ምን እንዳደርግልህ ትወዳለህ?›› ቢላቸው ስለ ሀገራችን ሰላም ይልቁንም በዚህ በቆረቆሩት ገዳማቸው የሚኖሩትን ልጆቻቸውን እንዲጠብቅላቸው ለመኑት፡፡ #ጌታችንም
በገዳማቸው ውስጥ በፍጹም ሕማም፣ ደዌና ተስቦ በሽታ እንደማይገባ ቃልኪዳን ገብቶላቸዋል፡፡

ለመንግሥተ ሰማያትም ያልታጨ ሰው በዚህ ገዳም ገብቶ አይቀበርም፡፡ ጻድቁ ከዛፉ ላይ ወድቀው ሳለ #ጌታችንን እጨብጣለሁ ብለው የዘረጓት እጃቸው እያበራች ኖራለች፡፡ እንደ መብረቅም እየጮኸች ለገዳሙ እንደ ደወል ታገለግል ነበር፡፡ በመጨረሻም ሊያርፉ ሲሉ ልጆቻቸውን ሰብስበው ባርከዋቸዋል፡፡ ያ አቡነ ሳሙኤል የባረኩበት ቡራኬም በመጽሐፈ ግንዘት ላይ ተደንግጎ ይገኛል፡፡ ዛሬም ድረስ ሰው ሲሞት ‹‹ቡራኬ ዘአቡነ ሳሙኤል›› ብሎ ካህኑ ይደግማል፡፡ እንደ አለመታደል ሆኖ በከተማ አካባቢ ግን እየተደረገ አይደለም፡፡ አቡነ ሳሙኤል ብዙዎችን ያመነኮሱ ሲሆን እንደነ አቡነ ተጠምቀ መድኅን፣ አቡነ ዘኢየሱስ፣ አቡነ ገብረ ክርስቶስ ያሉ ሌሎችንም በርካታ መነኮሳትን አፍርተዋል፡፡

አባታችንን ያመነኮሷቸው አባት አቡነ እንጦንዮስ ሊጠይቋቸው ወደ ደብረ ሃሌሉያ ሄደው ሲመለሱ እንዲላላካቸው አንድ ትንሽ ልጅ ትተውላቸው ተመለሱ፡፡ አቡነ ሳሙኤልም በጥበብ መንፈሳዊ ኮትኩተው አሳደጉት፡፡

አንድ ቀን ምግባቸው የሚሆን የእንጨት ፍሬዎችን ለመልቀም ከበዓታቸው ሲወጡ ልጃቸው እንዳይደክምባቸው በማሰብ በገዳማቸው ትተውት ለመሄድ አሰቡ፡፡ ብቻውን ስለሆነ አስፈሪ አራዊት እንዳያስደነግጡት በማሰብ ጉድጓድ ቆፍረው በዚያ አኑረውት ሄዱ፡፡ ርቀው ሄደው የእንጨቶችን ፍሬ ሲለቅሙ በጫካው እሳት ተስቶ ገዳማቸውንም ሙሉ በሙሉ አቃጠለው፡፡ ጻድቁ ስለ ልጃቸው ወደ ፈጣሪያቸው ጸልየው ካበቁ በኋላ ወደ ገዳማቸው ቢሄዱ የልጃቸው የራስ ፀጉር እንኳን ሳትቃጠል በሰላም አገኝተውታል፡፡ ያ ልጅም በኋላ አቡነ ገብረ መስቀል የተባለው ገድለኛ አባት ነው፡፡

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ሐምሌ_26 እና #ከገድላት_አንደበት)
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ሐምሌ_26_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ጢሞቴዎስ 6
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
³ እነዚህን አስተምርና ምከር። ማንም ልዩ ትምህርት የሚያስተምር ከጌታችንም ከኢየሱስ ክርስቶስ በሆነው ጤናማ ቃልና እግዚአብሔርን ለመምሰል በሚስማማ ትምህርት የማይጠጋ ቢሆን፥
⁴-⁵ በትዕቢት ተነፍቶአል አንዳችም አያውቅም፥ ነገር ግን ምርመራን በቃልም መዋጋትን እንደ በሽተኛ ይናፍቃል፤ ከእነዚህም ቅንዓትና ክርክር ስድብም ክፉ አሳብም እርስ በርስ መናደድም ይወጣሉ፥ አእምሮአቸውም በጠፋባቸው እውነትንም በተቀሙ፥ እግዚአብሔርን መምሰል ማትረፊያ የሚሆን በመሰላቸው ሰዎች ይገኛሉ። እንደነዚህ ካሉት ራቅ።
⁶ ኑሮዬ ይበቃኛል ለሚለው ግን እግዚአብሔርን መምሰል እጅግ ማትረፊያ ነው፤
⁷ ወደ ዓለም ምንም እንኳ አላመጣንምና፥
⁸ አንዳችንም ልንወስድ አይቻለንም፤ ምግብና ልብስ ከኖረን ግን፥ እርሱ ይበቃናል።
⁹ ዳሩ ግን ባለ ጠጎች ሊሆኑ የሚፈልጉ በጥፋትና በመፍረስ ሰዎችን በሚያሰጥምና በሚያሰንፍ በሚጎዳም በብዙ ምኞትና በፈተና በወጥመድም ይወድቃሉ።
¹⁰ ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነውና፥ አንዳንዶች ይህን ሲመኙ፥ ከሃይማኖት ተሳስተው በብዙ ሥቃይ ራሳቸውን ወጉ።
¹¹ አንተ ግን፥ የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፥ ከዚህ ሽሽ፤ ጽድቅንና እግዚአብሔርን መምሰል እምነትንም ፍቅርንም መጽናትንም የዋህነትንም ተከታተል።
¹² መልካሙን የእምነት ገድል ተጋደል፥ የተጠራህለትንም በብዙም ምስክሮች ፊት በመልካም መታመን የታመንህለትን የዘላለምን ሕይወት ያዝ።
¹³ ሁሉን በሕይወት በሚጠብቅ በእግዚአብሔር ፊት፥ በጴንጤናዊውም በጲላጦስ ዘንድ መልካሙን መታመን በመሰከረ በክርስቶስ ኢየሱስ ፊት አዝሃለሁ፤
¹⁴ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እስኪገለጥ ድረስ ያለ እድፍና ያለ ነቀፋ ሆነህ ትእዛዙን ጠብቅ፤
¹⁵ ያንም መገለጡን በራሱ ጊዜ ብፁዕና ብቻውን የሆነ ገዥ፥ የነገሥታት ንጉሥና የጌቶች ጌታ፥ ያሳያል።
¹⁶ እርሱ ብቻ የማይሞት ነው፤ ማንም ሊቀርበው በማይችል ብርሃን ይኖራል፤ አንድ ሰው እንኳ አላየውም ሊያይም አይቻለውም፤ ለእርሱ ክብርና የዘላለም ኃይል ይሁን፤ አሜን።
¹⁷ በአሁኑ ዘመን ባለ ጠጎች የሆኑት የትዕቢትን ነገር እንዳያስቡ፥ ደስም እንዲለን ሁሉን አትርፎ በሚሰጠን በሕያው እግዚአብሔር እንጂ በሚያልፍ ባለ ጠግነት ተስፋ እንዳያደርጉ እዘዛቸው።
¹⁸-¹⁹ እውነተኛውን ሕይወት ይይዙ ዘንድ፥ ለሚመጣው ዘመን ለራሳቸው መልካም መሠረት የሚሆንላቸውን መዝገብ እየሰበሰቡ፥ መልካምን እንዲያደርጉ በበጎም ሥራ ባለ ጠጎች እንዲሆኑ፥ ሊረዱና ሊያካፍሉም የተዘጋጁ እንዲሆኑ ምከራቸው።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ዮሐንስ 2
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ ልጆቼ ሆይ፥ ኃጢአትን እንዳታደርጉ ይህን እጽፍላችኋለሁ። ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።
² እርሱም የኃጢአታችን ማስተስሪያ ነው፥ ለኃጢአታችንም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን ለዓለሙ ሁሉ ኃጢአት እንጂ።
³ ትእዛዛቱንም ብንጠብቅ በዚህ እንዳወቅነው እናውቃለን።
⁴ አውቄዋለሁ የሚል ትእዛዛቱንም የማይጠብቅ ውሸተኛ ነው እውነትም በእርሱ ውስጥ የለም።
⁵ ቃሉን ግን የሚጠብቅ ሁሉ በእርሱ የእግዚአብሔር ፍቅር በእውነት ተፈጽሞአል። በእርሱ እንዳለን በዚህ እናውቃለን፤
⁶ በእርሱ እኖራለሁ የሚል እርሱ እንደ ተመላለሰ ራሱ ደግሞ ሊመላለስ ይገባዋል።
⁷ ወንድሞች ሆይ፥ ከመጀመሪያ የነበረቻችሁ አሮጌ ትእዛዝ እንጂ የምጽፍላችሁ አዲስ ትእዛዝ አይደለችም፤ አሮጌይቱ ትእዛዝ የሰማችኋት ቃል ናት።
⁸ ዳግመኛ አዲስ ትእዛዝን እጽፍላችኋለሁ፥ ይህም ነገር በእርሱ በእናንተም እውነተኛ ነው፤ ጨለማው ያልፋልና እውነተኛውም ብርሃን አሁን ይበራል።
⁹ በብርሃን አለሁ የሚል ወንድሙንም የሚጠላ እስከ አሁን በጨለማ አለ።
¹⁰ ወንድሙንም የሚወድ በብርሃን ይኖራል ማሰናከያም የለበትም፤
¹¹ ወንድሙን የሚጠላ ግን በጨለማ አለ፥ በጨለማም ይመላለሳል፥ የሚሄድበትንም አያውቅም፥ ጨለማው ዓይኖቹን አሳውሮታልና።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 5
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²⁰ ሂዱና ቆማችሁ የዚህን ሕይወት ቃል ሁሉ ለሕዝብ በመቅደስ ንገሩ አላቸው።
²¹ በሰሙም ጊዜ ማልደው ወደ መቅደስ ገብተው አስተማሩ። ግን ሊቀ ካህናቱና ከእርሱ ጋር የነበሩት መጥተው ሸንጎውንና የእስራኤልን ልጆች ሽማግሌዎች ሁሉ በአንድነት ጠሩ፥ ያመጡአቸውም ዘንድ ወደ ወኅኒ ላኩ።
²²-²³ ሎሌዎችም መጥተው በወኅኒው አላገኙአቸውም፤ ተመልሰውም፦ ወኅኒው በጣም በጥንቃቄ ተዘግቶ ጠባቂዎችም በደጁ ፊት ቆመው አገኘን፥ በከፈትን ጊዜ ግን በውስጡ አንድ ስንኳ አላገኘንም አሉአቸው።
²⁴ የመቅደስ አዛዥና የካህናት አለቆችም ይህን ነገር በሰሙ ጊዜ፦ እንጃ ይህ ምን ይሆን? እያሉ ስለ እነርሱ አመነቱ።
²⁵ አንድ ሰውም መጥቶ፦ እነሆ፥ በወኅኒ ያኖራችኋቸው ሰዎች እየቆሙ ሕዝቡንም እያስተማሩ በመቅደስ ናቸው ብሎ አወራላቸው።
²⁶ በዚያን ጊዜ አዛዡ ከሎሌዎች ጋር ሄዶ አመጣቸው፥ በኃይል ግን አይደለም፤ ሕዝቡ እንዳይወግሩአቸው ይፈሩ ነበርና።
²⁷ አምጥተውም በሸንጎ አቆሙአቸው።
²⁸ ሊቀ ካህናቱም፦ በዚህ ስም እንዳታስተምሩ አጥብቀን አላዘዝናችሁምን? እነሆም፥ ኢየሩሳሌምን በትምህርታችሁ ሞልታችኋል፤ የዚያንም ሰው ደም በእኛ ታመጡብን ዘንድ ታስባላችሁ ብሎ ጠየቃቸው።
²⁹ ጴጥሮስና ሐዋርያትም መልሰው አሉ፦ ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል።
³⁰ እናንተ በእንጨት ላይ ሰቅላችሁ የገደላችሁትን ኢየሱስን የአባቶቻችን አምላክ አስነሣው፤
³¹ ይህን እግዚአብሔር፥ ለእስራኤል ንስሐን የኃጢአትንም ስርየት ይሰጥ ዘንድ፥ ራስም መድኃኒትም አድርጎ በቀኙ ከፍ ከፍ አደረገው።
³² እኛም ለዚህ ነገር ምስክሮች ነን፥ ደግሞም እግዚአብሔር ለሚታዘዙት የሰጠው መንፈስ ቅዱስ ምስክር ነው።
³³ እነርሱም ሲሰሙ በጣም ተቈጡ ሊገድሉአቸውም አሰቡ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ሐምሌ_26_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"ይምጹኡ ተናብልት እምግብፅ። ኢትዮጵያ ታበጽሕ እደዊሃ ኀበ እግዚአብሔር። ነገስተ ምድር ሰብሕዎ ለእግዚአብሔር"። መዝ 67፥31-32።
"መኳንንት ከግብጽ ይመጣሉ፤ ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች።
የምድር ነገሥታት፥ ለእግዚአብሔር ተቀኙ፥ ለጌታም ዘምሩ"። መዝ 67፥31-32።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ሐምሌ_26_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ማቴዎስ 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁸ የኢየሱስ ክርስቶስም ልደት እንዲህ ነበረ። እናቱ ማርያም ለዮሴፍ በታጨች ጊዜ ሳይገናኙ ከመንፈስ ቅዱስ ፀንሳ ተገኘች።
¹⁹ እጮኛዋ ዮሴፍም ጻድቅ ሆኖ ሊገልጣት ስላልወደደ በስውር ሊተዋት አሰበ።
²⁰ እርሱ ግን ይህን ሲያስብ፥ እነሆ የጌታ መልአክ በሕልም ታየው፥ እንዲህም አለ፦ የዳዊት ልጅ ዮሴፍ ሆይ፥ ከእርስዋ የተፀነሰው ከመንፈስ ቅዱስ ነውና እጮኛህን ማርያምን ለመውሰድ አትፍራ።
²¹ ልጅም ትወልዳለች፤ እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ።
²² በነቢይ ከጌታ ዘንድ፦
²³ እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ይሉታል የተባለው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሁሉ ሆኖአል፥ ትርጓሜውም፦ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር የሚል ነው።
²⁴ ዮሴፍም ከእንቅልፉ ነቅቶ የጌታ መልአክ እንዳዘዘው አደረገ፤ እጮኛውንም ወሰደ፤
²⁵ የበኩር ልጅዋንም እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም፤ ስሙንም ኢየሱስ አለው።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #እመቤታችን_ማርያም ወይም የ #ሠለስቱ_ምዕት_ቅዳሴ ነው። መልካም የአረጋዊው የ #ቅዱስ_ዮሴፍ፣ የአባ #ሰላም_ከሳቴ_ብርሃን የዕረፍት በዓልና የአቡነ ሳሙኤል ዘደብረ ሃሌሉያ የዕረፍት በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
የአቡነ ሳሙኤል ዘደብረ ሃሌሉያ አጎት የሆኑትና በምግባር በሐይማኖት ኮትኩተው ያሳደጓቸው አባት ማን ይባላሉ?
Anonymous Quiz
41%
አቡነ አቢየ እግዚእ
19%
አቡነ መድኃኒነ እግዚእ
28%
አቡነ ዜና ማርቆስ
13%
አቡነ ተክለ ሐይማኖት
አረጋዊ ቅዱስ ዮሴፍ ከወለዳቸው ልጆች መካከል አይደለም(ችም)?
Anonymous Quiz
23%
ስምዖን
25%
ሰሎሜ
20%
ቢንያም
33%
ዮሳ
ጻድቁ የጌታችን መከራ በማሰብ ከተወለዱ ጀምሮ ተላጭተውት የማያውቁትን ፀጉራቸውን ከትልቅ ዛፍ ላይ እያሠሩ ይጸልዩ ነበር፡፡ እንዲሁ አድርገው ዛፍ ላይ ራሳቸውን ሰቅለው 40 ቀንና 40 ሌሊት ሲጸልዩ በመጨረሻ የታሠሩበት ፀጉራቸው ተነቅሎ ከመሬት ላይ የወደቁት አባት ማን ይባላሉ?
Anonymous Quiz
18%
አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ
32%
አቡነ ሳሙኤል ዘደብረ ወገግ
36%
አቡነ ሳሙኤል ዘቆይጻ
14%
አቡነ ሳሙኤል ዘደብረ ሃሌሉያ
2024/09/23 23:14:14
Back to Top
HTML Embed Code: