Telegram Web Link
††† እንኳን ለቅዱሳኑ ገብርኤል ሊቀ መላእክት: ቂርቆስ ወኢየሉጣ: በጥላን ጠቢብ እና ሰማዕታተ እስና ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱሳን ቂርቆስ ወኢየሉጣ: ወቅዱስ ገብርኤል ሊቀ መላእክት †††

††† ቅድስት ኢየሉጣ እናታችን በዘመነ ሰማዕታት ከነበሩና በዚህ ስም ከሚጠሩ ቅዱሳት አንዷ ናት:: በወቅቱ ቅዱስ ቂርቆስ የሚባል ደግ ልጅ ወልዳ ባሏ ባለመኖሩ በመበለትነት ትኖር ነበር:: የዚያ ዘመን ክርስቲያኖች ለክርስቶስ የነበራቸው ፍቅር ከመነገር በላይ ነው:: በዛው ልክ ደግሞ መከራው በጸጉራቸው ቁጥር ልክ ነበር::

ከሮም ግዛት በአንዱ ከቅዱስ ልጇ ጋር የምትኖረው ቅድስት ኢየሉጣ የስደቱ ዘመን ሲመጣ እርሷም እንደ ሌሎቹ ክርስቲያኖች ተሰደደች:: እስክንድሮስ የተባለው ከሃዲ ንጉሥ ግን ያለችበት ድረስ ተከትሎ እንድትያዝና እንድትቀርብ አደረገ::

ወዲያውም "ስምሽ ማን ይባላል?" ቢላት "ክርስቲያን እባላለሁ" አለችው:: ንጉሡ ተቆጣ:: "መዋቲ ስሜን ከፈለክ ኢየሉጣ ይባላል" አለችው:: ንጉሡ መልሶ "አሁን ለጣዖት ካልሠዋሽ ሲጀመር ስቃይ: ቀጥሎም ሞት ይጠብቅሻል" ቢላት ቅድስቲቱ መልሳ "በከተማ ውስጥ የሦስት ዓመት ሕፃን አለና እርሱን አምጣው:: ማንን ማምለክ እንዳለብን ይነግረናል" አለችው::

አስፈልጐ ቅዱስ ቂርቆስን አስመጣው:: "ስምህ ማን ይባላል?" አለ ንጉሡ:: "ከማይደፈርስ ከንጹሕ ምንጭ የተቀዳ ጥሩ ምንጭ ስሜ ክርስቲያን ይባላል:: መዋቲ ስሜን ከፈለግህ ግን ቂርቆስ ይባላል" አለው::

ንጉሡ ሊያታልለው "ደስ የተሰኘህ ሕፃን" ቢለው ቅዱሱ ሕፃን "ትክክል ተናገርክ: ለእኔ በሰማያት ደስታ ይጠብቀኛል:: አንተ ግን እውነተኛው አምላክ ይፈርድብሃል" አለው:: በሦስት ዓመት ሕፃን አንደበት ዘለፋ የገጠመው ከሃዲ ተቆጣ::
እናትና ልጅን በብዙ መክፈልተ ኩነኔ አሰቃያቸው::

ሰውነታቸውን ቸነከረ: አካላቸውን ቆራረጠ: ዓይናቸውን አወጣ:: ሌላም ሊናገሩት የሚጨንቅ ስቃይን አሰቃያቸው:: በዚህች ቀን ግን ትልቅ ድስት አሰርቶ ባሩድ: አረር: ስብና የመሳሰሉትን ጨምረውበት በእሳት አፈሉት::

የእሳቱ ወላፈን አካባቢውን በላው:: በድስቱ ውስጥ ያለው ነገር እየፈላ ሲገላበጥ እንደ ክረምት ነጐድጓድ ይጮህ ነበር:: የስድስት ሰዓት የእግር መንገድ ድረስም ተሰምቷል:: ቅድስት ኢየሉጣ ይሔኔ ነበር ልቧ ድንግጥ ያለው:: ሕፃኑ ቂርቆስ የእናቱን ፍርሃት ሲመለከት ጸለየ::

"ፈጣሪዬ! ፍሬው ያለ ግንዱ አይቆምምና እኔን እንዳጸናሕ እናቴንም አጽናት" ሲል ለመነ::
"እግዚኦ ትፈቅድኑ ለፍሬሁ ተአልዶ:
እንዘ በእሳት ታውኢ ጉንዶ" እንዲል::
በዚያች ሰዓት ቅድስት ኢየሉጣ ዓይኖቿ ተከፍተው ሰማያዊ ክብርን ተመለከቱና ልቧ ወደ ድፍረቱ ተመለሰ::

ልጇንም "አንተ አባቴ ነህ: አንተን የተሸከመች ማኅጸኔ የተባረከች ናት" አለችው:: ከዚያም ሁለቱንም ወደ ፈላው ድስት ውስጥ ቢጨምሯቸው ፍጡነ ረድኤት ቅዱስ ገብርኤል ከሰማይ ወረደላቸው:: በበትረ መስቀሉ ባርኮ የፈላውን አቀዘቀዘው:: የነደደውን ውኃ አደረገው:: ቅዱሳኑ ቂርቆስና ኢየሉጣ ከብዙ መከራ በኋላ በሰማዕትነት አልፈዋል::

††† ቅዱስ በጥላን ጠቢብ †††

††† ቅዱሱ ከአሕዛብ ወላጆቹ ተወልዶ: ያደገውም በጣዖት አምልኮ ነው:: በሙያው እጅግ የተመሠከረለት ሐኪም ነበር:: የሃገሩ ሰዎች "ጠቢብ" እያሉም ይጠሩታል:: በጥላን ምንም ጣዖት አምላኪ ቢሆን በተፈጥሮው ተመራማሪና ቅን ነበር::

አንድ ካህንም በጐረቤቱ ነበርና ዘወትር ስለ ሃይማኖት ይከራከሩ ነበር:: ካህኑ ሌሊት ሌሊት ስለ በጥላን ተግቶ ይጸልይ ነበርና ተሳክቶለት አሳመነው::

አንድ ቀን በጥላን መንገድ ሲሔድ እባብ ሰው ነድፎ ለሞት ደርሶ አየውና ጸሎት አድርሶ ስመ ክርስቶስን ቢጠራ የተነደፈው ድኖ እባቡ ሞተ::

በዚህ ተዓምር ደስ ብሎት ወደ ካህኑ ሒዶ ተጠመቀ:: ከዚያም ጾም ጸሎትን ጀመረ:: በየቦታው እየዞረ ሕሙማንን እንደ ቀድሞው በመድኃኒት ሳይሆን በጸሎት ያድናቸው ነበር:: ስላዳናቸውም በርካቶቹ ወደ ክርስትና መጡ::

የአካባቢው ሰው: ወላጆቹን ጨምሮ ክርስቲያኖች ሆኑ:: በመጨረሻም ቅዱስ በጥላን: ቤተሰቦቹ: ካህኑና ከደዌ የዳኑት ወገኖቹ በአካባቢው ጣዖት አምላኪ ንጉሥ ፊት ቀርበው ክርስቶስን ሰብከው በሰማዕትነት ዐርፈዋል::

††† ቅዱሳን ሰማዕታተ እስና †††

††† እስና ማለት ግብጽ ውስጥ የምትገኝ የቀድሞ አውራጃ ናት:: በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን በከተማዋ በርካታ ክርስቲያኖች ይኖሩ ነበር:: የእንዴናው መኮንን መጥቶ "ክርስቶስን ካዱ: ለጣዖት ስገዱ" አላቸው:: ሕዝቡ በአንድ ድምጽ መለሱ:- "ይሕማ ፈጽሞ ሊደረግ አይችልም::" መኮንኑ ተቆጥቶ "ሁሉንም ግደሉ" አለ::

ወታደሮቹ ሰው አልመረጡም:: ከታዘለ ሕፃን አልጋ ላይ እስካለ ሽማግሌ: ከጤነኛ እስከ ሕመምተኛ: ሁሉንም ጨፈጨፏቸው:: ከተማዋ በደም ተነከረች:: ከከተማዋ ክርስቲያኖች ወሬ ለመንገር አንድ ሰው እንኳ አልተረፈም:: ሁሉም ስለ ክርስትና ደማቸውን አፈሰሱ::

††† ጌታችን ስለ ሰማዕታቱ ብሎ: ደማቸውንም አስቦ በሃይማኖታችን ያጽናን:: ከመከራም ይሰውረን:: በረከታቸውንም ያድለን::

††† ሐምሌ 19 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ገብርኤል ሊቀ መላእክት
2.ቅዱስ ቂርቆስ ወእሙ ኢየሉጣ
3.ቅዱስ በጥላን ጠቢብ ሰማዕት እና ማኅበሩ
4.ቅዱሳን ሰማዕታተ እስና

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ኤስድሮስ ሰማዕት
2.አቡነ ዓቢየ እግዚእ ጻድቅ
3.አቡነ ስነ ኢየሱስ
4.አቡነ ዮሴፍ ብርሃነ ዓለም

††† "ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ: ወይስ ጭንቀት: ወይስ ስደት: ወይስ ራብ: ወይስ መራቆት: ወይስ ፍርሃት: ወይስ ሰይፍ ነውን?
'ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን:: እንደሚታረዱ በጐች ተቆጠርን::' ተብሎ እንደተጻፈው ነው::
በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን::" †††
(ሮሜ. ፰፥፴፭-፴፯)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
እንኳን ለቅዱስ ቂርቆስ ወኢየሉጣና ለሊቀ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ)

#ሐምሌ_፲፱#በዓለ_ቅዱስ_ገብርኤል_ወቅዱስ_ቂርቆስ_ወቅድስት_ኢየሉጣ_ወሥርዐተ_ማኅሌት፡፡
  በቀጨኔ ደ/.ሰ/መድኀኔ ዓለም ወደ.ት.ቅ.ገብርኤል.ቤ.ክ የፍኖተ ሕይወት ሰ.ት.ቤት የተዘጋጀ

    ቅዱስ ገብርኤል ሊቀ መላእክት

✼ ነቢዩ ዳንኤል “ዐይኖቼንም አነሣሁ” አለና አስከትሎ “እነሆም በፍታ የለበሰውን ጥሩም የአፌዝን ወርቅ በወገቡ ላይ የታጠቀውን ሰው አየሁ፡፡
አካሉም እንደ ቢረሌ ይመስል ነበር፤ ፊቱም እንደ መብረቅ አምሳያ ነበረ፤ ዐይኖቹም #እንደሚንበለበል ፋና፣ ክንዶቹና እግሮቹም እንደ ጋለ ናስ፣ የቃሉም #ድምፅ እንደ ብዙ #ሕዝብ ድምፅ ነበረ፡፡… ይህንንም ታላቅ ራእይ አየሁ፤ ኃይልም አልቀረልኝም፤ ክብሬም ወደ ውርደት ተለወጠብኝ #ኃይልም አጣሁ፡፡ የቃሉንም ድምፅ ሰማሁ፤ የቃሉን ድምፅ በሰማሁ ጊዜ ደንግጬ በምደር ላይ #በግምባሬ_ተደፋሁ” አለ፡፡(ዳን.10፥5-9) ነቢዩ ዳንኤል እንዲህ ብሎ የተናገረው የመላእክትአለቃ የቅዱስ #ገብርኤልን አስፈሪ ግርማ በተመለከተ ጊዜ ነበር፡፡
✤ ገብርኤል የሚለው ቃል የሁለት ቃለት ጥምር ነው እነዚህም #ገብር እና #ኤል ሲሆኑ ትርጕማቸውም ገብር #አገልጋይ ማለት ሲሆን ኤል ማለት ደግሞ አምላክ ማለት ነው፤ በተገኛኘ ገብርኤል ማለት #የአምላክ_አገልጋይ /የእግዚአብሔርን ልጅ የሚመስል የአምላክ አገልጋይ ማለት ነው።

“እነሆ ከዋነኞቹ አለቆች” አንዱ ሚካኤል ሊረዳኝ መጣ”(ዳን.10፥13) ብሎ በተናገረው ንግግሩ በመላእክት ላይ የተሾሙ ሌሎች አለቆች እንዳሉ ማስተዋል እንችላለን፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም በቅዱሳን መላእክት ዘንድ ስላሉት ነገዶች ሲገልጽ “… በሰማይ ያለውን በምደር ያለውን የሚታየውንና የማይታየውን መናብርትም ቢሆኑ አጋእዝትም ቢሆኑ መኳንንትም ቢሆኑ ቀደምትም ቢሆኑ ሁሉም በእጁ ሆነ፤ ሁሉም በእርሱ ለእርሱ ተፈጠረ” (ቈላ.1፥16) በማለት ይዘረዝራቸዋል፡፡ ከዚህ ተነሥተን መላእክት በተለያዩ ዐበይት ነገዶች የተከፈሉና ለእያንዳንዱም ነገድ የራሱ የሆነ አለቃ እንዳለው ማስተዋል እንችላለን፡፡
ቅዱስ ገብርኤልም ከእነዚህ ዐበይት የመላእክት ነገዶች መካከል አንዱ በሆነው #እርባብ በሚባለው ዐቢይ ነገድ ላይ የተሾመ ሲሆን ከ100ው ነገደ መላእክት መካከል ከበታቹ የሚመራቸው ዐሥር ነገደ መላእክት አሉት፤ ከተማቸውም በሰማየ #ራማ ነው፡፡

✼ ቅዱሳን መላእክት በቅዱስ ሚካኤል ፊት አውራሪነት የሰው ልጆች ጠላት የሆነውን ዲያብሎስን ተዋግተው ድል ከመንሳታቸው አስቀድሞ ቅዱስ ገብርኤል፣ እንደ አምላክ ሊመለክ የወደደውን ሳጥናኤልን በመቃወም ‹‹#ንቁም_በበህላዌነ_እስከ_ንረክቦ_ለአምላክነ - “አይዞአችሁ ፈጣሪያችን እስክናገኘው፣ እስክናውቀው ድረስ በያለንበት ጸንተን እንቁም፡፡” (አክሲማሮስ ገጽ.35) በማለት
#መላእክትን_ያረጋጋ_መልአክ_ነው፡፡ በተወዳጁ መልአክ በቅዱስ ሚካኤል መሪነት የሰው ልጆች ጠላት የሆነውን ዲያብሎስን ተዋግተው ድል እንዲያደርጉ ወደ ጥልቁ እንዲጣል አድርጓል ራእ12፥7፤ ነቢዩ ኢሳይያስ በሰማያት የሳጥናኤል ትዕቢትና ውድቀት ምን እንደሚመስል ሲጽፍልን “አንተ በንጋት የሚወጣ አጥቢያ ኮከብ ሆይ እንዴት ከሰማይ ወደቅህ! ወደ አሕዛብ መልእክትን የላክ አንተሆይ እንዴት እስከ ምድር ድረስ ተቀጠቀጥህ! አንተም በልብህ ወደ ሰማይ ዐርጋለሁ ዙፋኔንም ከእግዚአብሔር ከዋክብት በላይ ከፍ ከፍ አደረጋለሁ፤… በልዑልም እመሰላለሁ አልህ፡፡ ዛሬ ግን ወደ ሲኦል ትወድቃለህ፤ ወደ ምድር ጥልቅም ትወርዳለህ” (ኢሳ.1416) በማለት ገለጠልን፤ ወደ ምድር የጣሉት በመላእክት አለቃ በቅዱስ ሚካኤል  እና በቅዱስ ገብርኤል  መሪነት   ነበር፡፡

✼ ቅዱስ ገብርኤል ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ ከሊቃነ መላእክት አንዱና በእግዚአብሔር ፊት የሚቆመው ታማኝ መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ነው ብሏል ሉቃ 1፥19፤ ታላቁ ነቢይ ሄኖክም ስለ ነገረ
መላእክት በተናገረበት አንቀጽ እንዲህ ሲል መስክሯል ‹‹በአበቦች ላይ በገነትም በጻድቃን ላይ #በኪሩቤልም ላይ የተሾሙ ከከበሩ መላእክት አንዱ #ገብርኤል ነው፡፡›› ሄኖክ 6፥7፤ ‹‹በሦስተኛውም በመላእክት ሁሉ ላይ የተሾመ ቅዱስ ገብርኤል ነው››ሄኖክ 10፥14 እያለ የመልአኩን ክብር ተናግሯል፡፡

ቅዱስ ገብርኤል ቅዱሳን ይሆኑ ዘንድ ለተጠሩት መንፈሳዊ እውቀቱን የሚያካፍላቸው መልአክ ብቻ አይደለም፤ ለእግዚአብሔር በመገዛታቸው ምክንያት ከአላውያን ገዢዎች ከሚደርስባቸው መከራም የሚታደጋቸው መልአክም ነው፡፡ ነገር ግን ያደረጋቸው ተዓምራቶች በመጽሐፍ ቅዱስ፣ በመልክኡ፣ በድርሳኑ፣ በገድሉ፣ በተዓምሩ የተጻፉ ቢሆንም ሐምሌ 19 እና ታኅሣሥ 19 ያደረጋቸውን ተራዳኢነት  ፡-

✤✤✤ ሐምሌ 19 ቀን ሕፃኑ ቅዱስ #ቂርቆስና እናቱ ቅድስት #እየሉጣ በሰማዕትነት መከራ የተቀበሉበት፤ ሊቀ መላእክት  ቅዱስ #ገብርኤል ደግሞ #ከእቶን እሳት ያዳናቸው እለት ነው::
✤✼፠ #ታኅሣሥ_19 አናንያና(ሚሳቅ)፣ አዛርያ(ሲድራቅ) እና ሚሳኤል(አብደናጎ) ያዳናቸው ቅዱስ ገብርኤል ነው፡፡ አናንያና(ሚሳቅ)፣ አዛርያ(ሲድራቅ) እና ሚሳኤል(አብደናጎ) የፋርስ ባቢሎን ንጉሥ የነበረው ናብከደነፆር በዱራ(አዱራን) በሚባል ስፍራ ላይ ላቆመው ጣዖት አንሰግድም በማለታቸው ወደ እቶን እሳት እንዲጣሉ አድርጓቸዋል ፤ በመልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ተራዳኢነት ግን ከእቶን እሳቱ የልብሳቸው ዘርፍ እንኳን እሳት ሳይነካው ድነዋል፡፡ (ይህንን በዓል የምናከብረው ታኅሣሥ 19 ስለሆነ ታሪኩን በስፋት ለመረዳት የታኅሳስ 19 ስንክሳርን ወይም የታኅሣሥ ወር ልጥፈችንን ወደ ሃሏ  በመመለስ ይመልከቱ ፡፡)
✤ ቅዱስ #ቂርቆስ እድሜው የሦስት ዓመት ሳለ እናቱ ቅድስት እየሉጣ ከሮሜ ወደ ሌላ ሃገር ሸሽታ ይዛው ሄደች በዚያም የሸሸችውን መኮንኑን አገኘችው። የሚያውቋትም ሰዎች ሸሽታ እንደመጣች ስለተረዱ ለመኮንኑ ነገር ሰሩባት። መኮንኑም ቅድስት አየሉጣን አስጠራትና ስለ አምልኮ ጠየቃት። ቅድስት ኢየሉጣም መኮንን ሆይ፡ እድሜው ሦስት አመት የሆነው ሕፃን አለ አማልክቶችህን ማምለክ መልካም እንደሆነ ወይም እንዳልሆነ ያስረዳን ዘንድ እርሱን ጠይቅ አለችው። መኮንኑም ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስም ወደ አለበት ጭፍራውን ልኮ ወደ እርሱ አስመጣው ሕፃኑንም ፊቱ ብሩህና ደስተኛ እንደሆነ አየውና አንተ ደስተኛ ሕፃን ሆይ እንዴት ነህ አለው። ሕጻን ቅዱስ ቂርቆስም መለሰለት እንዲህም አለው። አዎ እኔ በጣም ደስተኛ ነኝ ደስታየም ተጠብቆልኛል ላንተ ግን ኀዘንና ለቅሶ ጥርስ ማፋጨትም ነው፤ መጽሐፍ ቅዱስም ለዝንጉዎች ተድላ ደስታ የላቸውም ብሏልና አለው። እግዚአብሔር አምላክ ኃይልንና ንግግርን ሰጥቶታልና በዚያ ለተሰበሰቡት ሰዎች እስኪደነግጡ ድረስ ብዙ ተናገረ። ሕፃን ቅዱስ ቂርቆስም ንጉሱን መኳንንቱንና ጣዖታቱን ረገማቸው ከብርታቱም የተነሳ አደነቁ። መኮንኑም በአፈረ ጊዜ በየአይነቱ በሆነ ስቃይ፡ ታላላቆች አንኳ የማይችሉትን ታላቅ አስጨናቂ የሆነ ስቃይን አሰቃየው። እናቱ ቅድስት እየሉጣንምከእርሱ ጋር እንደ እርሱ በጣሙን አሰቃያት። እግዚአሔብሔር ግን ያለ ምንም ጉዳት ያነሳቸው ነበር። ብዙዎች አህዛብም ይህን አይተው አደነቁ ክብር ይግባውና በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነት አምነው በሰማእትነት ሞቱ የሰማእትነትንም አክሊል ተቀበሉ። በሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስ ላይም የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ አደረበት። ታላላቅ ድንቅ ተአምራቶችንም ያደርግ ነበር። ብዙዎች በሽተኞችንም ያድናቸው ይፈውሳቸው ነበር

። ይህንን ያየ መኮንን በታላቅ የነሃስ ጋን ውስጥ ውሃ ጨምረው በእሳት ያፈሉት ዘንድ አዘዘ። የፍላቱም ድምጽ እንደ ክረምት ነጎድጓድ ሆነ ድምጹም በጣም ያስተጋባ ነበር። ይህን ያየችና የሰማች እናት ቅድስት እየሉጣም ፍርሃትና የሃይማኖት ጉድለት ታየባት። ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስ ግን እናቱ ቅድስት እየሉጣን ሁኔታዋን አይቶ ወደ አምላኩ እግዚአብሔር ጸለየ። ያን ጊዜ ልዑል እግዚአብሔር ልቧን ወደ ሰማይ አሳርጎ ለቅዱሳን ሰማዕታት የተዘጋጁ የብርሃን ማደሪያዎችን አሳያት። ቅድስት እየሉጣም እንደገና በሃይማኖቷ ጸናች። እግዚአብሔር አምላኳንም አመሰገነችው። ልጇን ሕፃኑን ቅዱስ ቂርቆስንም ልጄ ሆይ አንተ ከእንግዲህ አባቴ ነህ እኔም ልጅህ ነኝ አለችው። ቅድስት እየሉጣም ለልጇ ያች የተወለድክባት እለት ቀኗ የተባረከችና የተቀደሰች ናት አለችው። የመኳንንቱ ጭፍሮችም እሳት ወደ አለበት ጋኖች ውስጥ ቅዱስ ቂርቆስንና እናቱን ቅድስት እየሉጣን በጨመሯቸው ጊዜ የውሃው ፍላት ወደያውኑንቀዘቀዘ። ከእግዚአብሔር የታዘዘ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል ከሰማይ ወርዶ የእሳቱን ኃይል አቀዝቅዞታልና። ይህን ያየ መኮንን ሥጋቸው ተቆራርጦ እስከሚወድቅ ድረስ በመቃጥን ውስጥ አድርገው አንዲጎትቷቸው አዘዘ። ከእግዚአብሔርም የታዘዘ መልአክ ቅዱስ ገብርኤል አዳናቸው። መኮንኑም በታላቅ ስቃይ ያሰቃያቸው ዘንድ አስቦ እስኪመክር ድረስ በወህኒ ቤት ዘጋባቸው። በዚህን ጊዜ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕጻኑ ቅዱስ ቂርቆስን አረጋጋው አጽናናው። ስሙን ጠርተው መታሰቢያ ለሚያደርጉለትም በረከትን እንደሚያገኝ ቃል ኪዳን ሰጠው ። እግዚአብሔር አምላካችን የሕጻኑ ቅዱስ ቂርቆስና የእናቱ የቅድስት ኢየሉጣን በረከታቸውንና ረድኤታቸውን ያድለን አሜን።

ቅዱስ ቂርቆስና ቅድስት ኢየሉጣ በእግዚአብሔር ቸርነት በቅዱስ ገብርኤል ተራዳኢነት በእሳት ከመጣል በንፍር ውሃ ከመለብለብ ከዳኑ በኋላ እለስክንድሮስ መከራውን ፈርተው ይመለሳሉ ብሎ በሀብለ ሰናስል እያሰረ በችንካር እየቸነከረ ሲያሰቃያቸው ቆየ፡፡ የማይሆንለት ሲሆን እጅ እግራቸውን አስሮ ከዝግ ቤት አስቀመጣቸው፡፡ ጌታም የመከራቸውን ጽናት የትዕግስታቸውን ብዛት አይቶ ከመከራ ሊያሳርፋቸው ሽቶ በመንፈቀ ሌሊት ተገልጾ፤ በመጣ ጊዜ “ሰላም ለከ ኦ ፍቁርየ ቂርቆስ” ወዳጄ ቂርቆስ ሆይ ሰላም ላንተ ይሁን፤ ብሎ ሠላምታ ከሰጠው በኋላ የመከራህን ጽናት፣ የትዕግስትህን ብዛት አይቼ ቃል ኪዳን ልገባልህ ነው።” “ዘመጠነዝ ገድለ ተጋዲልየ ምንተኑ ትዔስየኒ” በሕፃንነቴ ይህን ያህል ተጋድዬ የምትሰጠኝ ምንድነው?” አለው። “አዐሥየከ ዘሀሎ ውስተ መልብከ” በልብህ ያለውን ሁሉ እሰጥሃለሁ አለው። እንኪያስ በስሜ ቤተ ክርስቲያን ከታነጸበት ረሃብ፣ ቸነፈር፣ የሰው በሽታ፣ የከብት እልቂት፣ የእኅል የውሃ ጥፋት፣ አይሁን አለ። ጌታም ይሁንልህ በማለት ቃል ኪዳን ገብቶላታል፡፡ ደግሞም “ኢትቅብር ሥጋየ በዲበ ምድር” ሥጋዬ በምድር አይቀበር አለው። “አልቦ ዘይፈደፍደከ ዘእንበለ መንበረ መንግሥትየ ወማርያም ወላዲትየ ወዮሐንስ መጥምቅየ” (ከመንበረ መንግስቴ፣ ከማርያም እናቴ ከዮሐንስ መጥምቅም በቀር በመንግሥተ ሰማያት የሚበልጥህ የለም።)
“ወዓዲ ከመ ኢይስማን ሥጋከ ዲበ ሠረገላ ኤልያስ አነብረከ”
(ሥጋህን እንዳይፈርስ በኤልያስ ሠረገላ አኖርልሃለሁ) ብሎ ተስፋውን ነግሮታል። እናቱ ቅድስት ኢየሉጣ በመኮንኑ በሰይፍ ጥር ፲፮ በሰማዕትነት ያረፈች ሲሆን ቅዱስ ቂርቆስን ግን ተመለስ ቢለው አልመለስም እምነቴንም አልክድም ባለው ጊዜ ሰይፍ ጃግሬውን ጠርቶ በጥር ፲፭ አስገድሎት ሰማዕትነትን ተቀብሏል፡፡ የእናቱ የቅድስት ኢየሉጣ መታሰቢያዋ ዕለት በየወሩ በ፲፮ እመቤታችን ቃል ኪዳን በተቀበለችበት ቀን በሚታሰብበት የቅድስት ኪዳነ ምህረት ቀን ይታሰባል።
የመልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ምልጃና ጸሎት፤ የቅዱስ ቂርቆስና የቅድስት ኢየሉጣ በረከታቸው ቃል ኪዳናቸው ይድረሰን በእውነት ይጠብቀን ለዘለዓለሙ አሜን፨

/በቀጨኔ ደ.ሰላም መድኀኔዓለምና ደ.ት.ቅ.ገብርኤል ቤ.ክ ፍኖተ ሕይወት ሰ.ት.ቤት ፤    ትምሕርት ዋና ክፍል ፥ ንዑስ ክፍል /ሕትመት እና ሚዲያ/  የተዘጋጀ ::  ꔰ
  #share
Contact: https://www.tg-me.com/finotehiwot1927
.Facebook...
https://www.facebook.com/FinoteHiwotSundaySchool
.Telegram...  https://www.tg-me.com/medihanaelem 
http://tiktok.com/@finotehiwot 
.YouTube    https://www.youtube.com/channel/UCWVKGH0mSJl47u44uopEb2w
                   www.finotehiwotsundayschool.com
ፍኖተ ሕይወት ሰንበት ት.ቤት .
Telegram (https://www.tg-me.com/finotehiwot1927)
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ሐምሌ_19_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የተነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ዕብራውያን 11
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
³³ እነርሱ በእምነት መንግሥታትን ድል ነሡ፥ ጽድቅን አደረጉ፥ የተሰጠውን የተስፋ ቃል አገኙ፥
³⁴ የአንበሶችን አፍ ዘጉ፥ የእሳትን ኃይል አጠፉ፥ ከሰይፍ ስለት አመለጡ፥ ከድካማቸው በረቱ፥ በጦርነት ኃይለኞች ሆኑ፥ የባዕድ ጭፍሮችን አባረሩ።
³⁵ ሴቶች ሙታናቸውን በትንሣኤ ተቀበሉ፤ ሌሎችም መዳንን ሳይቀበሉ የሚበልጠውን ትንሣኤ እንዲያገኙ እስከ ሞት ድረስ ተደበደቡ፤
³⁶ ሌሎችም መዘበቻ በመሆንና በመገረፍ ከዚህም በላይ በእስራትና በወኅኒ ተፈተኑ፤
³⁷ በድንጋይ ተወግረው ሞቱ፥ ተፈተኑ፥ በመጋዝ ተሰነጠቁ፥ በሰይፍ ተገድለው ሞቱ፥ ሁሉን እያጡ መከራን እየተቀበሉ እየተጨነቁ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ፤
³⁸ ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ፥ በዋሻና በምድር ጕድጓድ ተቅበዘበዙ።
³⁹-⁴⁰ እነዚህም ሁሉ በእምነታቸው ተመስክሮላቸው ሳሉ የተሰጠውን የተስፋ ቃል አላገኙም፥ ያለ እኛ ፍጹማን እንዳይሆኑ እግዚአብሔር ስለ እኛ አንዳች የሚበልጥ ነገርን አስቀድሞ አይቶ ነበርና።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ጴጥሮስ 4
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹² ወዳጆች ሆይ፥ በእናንተ መካከል እንደ እሳት ሊፈትናችሁ ስለሚሆነው መከራ ድንቅ ነገር እንደ መጣባችሁ አትደነቁ፤
¹³ ነገር ግን ክብሩ ሲገለጥ ደግሞ ሐሤት እያደረጋችሁ ደስ እንዲላችሁ፥ በክርስቶስ መከራ በምትካፈሉበት ልክ ደስ ይበላችሁ።
¹⁴ ስለ ክርስቶስ ስም ብትነቀፉ የክብር መንፈስ የእግዚአብሔር መንፈስ በእናንተ ላይ ያርፋልና ብፁዓን ናችሁ።
¹⁵ ከእናንተ ማንም ነፍሰ ገዳይ ወይም ሌባ ወይም ክፉ አድራጊ እንደሚሆን ወይም በሌሎች ጒዳይ እንደሚገባ ሆኖ መከራን አይቀበል፤
¹⁶ ክርስቲያን እንደሚሆን ግን መከራን ቢቀበል ስለዚህ ስም እግዚአብሔርን ያመስግን እንጂ አይፈር።
¹⁷ ፍርድ ከእግዚአብሔር ቤት ተነሥቶ የሚጀመርበት ጊዜ ደርሶአልና፤ አስቀድሞም በእኛ የሚጀመር ከሆነ ለእግዚአብሔር ወንጌል የማይታዘዙ መጨረሻቸው ምን ይሆን?
¹⁸ ጻድቅም በጭንቅ የሚድን ከሆነ ዓመፀኛውና ኃጢአተኛው ወዴት ይታይ ዘንድ አለው?
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 23
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁰ ብዙ ጥልም በሆነ ጊዜ የሻለቃው ጳውሎስን እንዳይገነጣጥሉት ፈርቶ ጭፍሮቹ ወርደው ከመካከላቸው እንዲነጥቁት ወደ ሰፈሩም እንዲያገቡት አዘዘ።
¹¹ በሁለተኛውም ሌሊት ጌታ በአጠገቡ ቆሞ፦ ጳውሎስ ሆይ፥ በኢየሩሳሌም ስለ እኔ እንደ መሰከርህ እንዲሁ በሮሜም ትመሰክርልኝ ዘንድ ይገባሃልና አይዞህ አለው።
¹² በጠባም ጊዜ አይሁድ ጳውሎስን እስኪገድሉት ድረስ እንዳይበሉና እንዳይጠጡ በመሐላ ተስማሙ።
¹³ ይህንም ሴራ ያደረጉት ሰዎች ከአርባ ይበዙ ነበር፤
¹⁴ እነርሱም ወደ ካህናት አለቆችና ወደ ሽማግሌዎቹ መጥተው፦ ጳውሎስን እስክንገድል ድረስ ምንም እንዳንቀምስ ተረጋግመን ተማምለናል።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ሐምሌ_19_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የተነበበው_የተዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
   "ይትኀፈሩ ኵሎሙ እለ ይሰግዱ ለግልፎ። ወእለ ይትሜክሑ በአማልክቲሆሙ። ወይሰግዱ ሎቱ ኵሎሙ መላእክቲሁ"። መዝ 96፥7።
“ለተቀረጸ ምስል የሚሰግዱ ሁሉ፥ በጣዖቶቻቸውም የሚመኩ ይፈሩ፤ መላእክቱ ሁሉ፥ ስገዱለት።” መዝ 96፥7።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ሐምሌ_19_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ማቴዎስ 11
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²⁵ በዚያን ጊዜ ኢየሱስ መልሶ እንዲህ አለ፦ አባት ሆይ፥ የሰማይና የምድር ጌታ፥ ይህን ከጥበበኞችና ከአስተዋዮች ሰውረህ ለሕፃናት ስለ ገለጥህላቸው አመሰግንሃለሁ፤
²⁶ አዎን፥ አባት ሆይ፥ ፈቃድህ በፊትህ እንዲህ ሆኖአልና።
²⁷ ሁሉ ከአባቴ ዘንድ ተሰጥቶኛል፤ ከአብ በቀር ወልድን የሚያውቅ የለም፥ ከወልድም በቀር ወልድም ሊገለጥለት ከሚፈቅድ በቀር አብን የሚያውቅ የለም።
²⁸ እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ።
²⁹ ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፥ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፥ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤
³⁰ ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️ 
የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #ቅዱስ_ያዕቆብ ዘሥሩግ ቅዳሴ ነው። መልካም የቅዱስ ገብርኤል፣ የቅዱሳን ሰማዕታት ቅዱስ ቂርቆስና ቅድስት ኢየሉጣ የሰማዕት የቅዱስ በጥላን ዓመታዊ በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ሐምሌ_20

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ሐምሌ ሃያ በዚህች ቀን #እመቤታችን_ድንግል_ማርያም ከተወለደች በኋላ በሰማንያ ቀን ከርግብ ገላግልቶች ጋራ ወደ ቤተ መቅደስ የገባችበት ነው፣ ታላቅና ክቡር የሆነው የሠራዊት አለቃ #ቅዱስ_ቴዎድሮስ በሰማዕትነት ሞተ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#በዓታ_ለእግዝእትነ_ማርያም

ሐምሌ ሃያ በዚህች ቀን እመቤታችን #ድንግል_ማርያም ከተወለደች በኋላ በሰማንያ ቀን ከርግብ ገላግልቶች ጋራ ወደ ቤተ መቅደስ የገባችበት ነው፣

ለስም አጠራሯ ክብር ይሁንና እመ ብርሃን #ድንግል_ማርያም በዚህች ቀን ወደ ቤተ መቅደስ ገብታለች:: በዓሉ ከሰላሳ ሦስቱ የእመቤታችን በዓላት እንደ አንዱ አይቆጠርም:: ምክንያቱም ቅዱሳን ሊቃውንት በዓታ ከበዓታ ጋር ይስማማል ብለው የታኅሣሥ ሦስትን በዓል ከሰላሳ ሦስቱ ደምረውታል::

#እመቤታችን ወደ ቤተ መቅደስ የገባችው ሁለት ጊዜ ሲሆን:-

1.ዛሬ የምናከብረውና በተወለደች በሰማንያ ቀኗ የገባችበት ነው:: (ከግንቦት 1 ጀምረን እናስላው 80 ቀን ይመጣል::)

ኦሪት እንዳዘዘው ቅዱሳን ኢያቄምና ሐና ንጽሕት ሕፃን #ድንግል_ማርያምን ታቅፈው የርግብ ልጆች (ግልገሎች) ዋኖስም ይዘው ወደ ቤተ መቅደስ ሒደዋል::

ካህናቱ ዘካርያስና ስምዖን ወጥተው በደስታ ተቀብለዋቸዋል:: እመቤታችን ለወላጆቿ ማኅጸን የከፈተች በኩር ናትና በእግዚአብሔር ፊት አቅርበዋታል::

2.ከሦስት ዓመታት በኋላ እንደ ስዕለታቸው ወደ ቤተ መቅደስ ወስደው #ለእግዚአብሔር ሰጥተዋት ተመልሰዋል::

#እግዚአብሔር ዛሬ ያልቃል ነገ ይደቃል የማይባለውን የድንግል እናቱን ፍቅር አብዝቶ ያድለን:: በረከቷም በእኛ ላይ ጸንቶ ይኑር::

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ቴዎድሮስ

ዳግመኛም በዚህች ቀን ታላቅና ክቡር የሆነው የሠራዊት አለቃ ቅዱስ ቴዎድሮስ በሰማዕትነት ሞተ። የዚህ ቅዱስ አባት ስሙ ዮሐንስ ይባል ነበር። እርሱም ከላይኛው ግብጽ ሰጥብ ከምትባል መንደር ነበር። ወደ አንጾኪያ ከተማም ከሠራዊቱ ጋራ ወሰዱትና በዚያ ኖረ ከዚያች ከተማ መኳንንቶችም ያንዱን ልጅ አገባ እርሷም ጣዖትን ታመልክ ነበር። ባሏ ዮሐንስ የሚያመልከውን ግን አታውቅም ነበር።

ከዚህም በኋላ ይህን ቅዱስ ቴዎድሮስን በወለዱት ጊዜ እናቱ ወደ ጣዖቷ አቅርባ አምልኮትዋን ልታስተምረው ፈለገች አባቱ ግን አስተወው ስለዚህም ተቆጥታ ባሏ ዮሐንስን አባረረችው ሕፃኑ ቴዎድሮስም በእናቱ ዘንድ ቀረ።

አባቱ ዮሐንስም ልጁ ቴዎድሮስን ወደ እውነተኛ መንገድ ይመራው ዘንድ ወደ #እግዚአብሔር ይጸልይና ይማልድ ነበር። ሕፃኑ ቴዎድሮስም በአደገ ጊዜ ጥበብን ተማረ ጌታችንም ልቡን ብሩህ አደረገለት ስሙ አውላኪስ ወደሚባል ኤጲስቆጶስም ሒዶ የክርስትና ጥምቀትን ተጠመቀ። እናቱም ታላቅ ኅዘንን አዘነች።

ከዚህም በኋላ ስለ አባቱ በሕይወት እንዳለ ወይም እንደሌለ ጠየቀ ከአገልጋዮቹም አንዱ የአባቱን ሥራ በሥውር ነገረው። ቅዱስ ቴዎድሮስም ጐለመሰ እጅግም ብርቱ ሆነ ንጉሡም የሠራዊት አለቃ አድርጎ ሾመው።

የፋርስ ሰዎችንም ሊወጋቸው በወጣ ጊዜ ይህ ቅዱስ ቴዎድሮስ በረታ የፋርስ ንጉሥንም ልጅ ይዞ ማረከው ከእርሱም ጋር ምሥራቃዊው ቴዎድሮስ ነበር የፋርስንም ሠራዊት አሳደዱአቸው።

ከጥቂት ወራቶች በኋላም የፋርስና የበርበር ስዎች በሮማውያን ላይ ተነሡ። ብዙ ከተሞችንም አጠፉ ዲዮቅልጥያኖስም በሰማ ጊዜ እጅግ ፈራ ቴዎድሮስንም ጠርቶ ምን እናድርግ ሠራዊትህን ሁሉ የጦር መሣሪያህንም ሁሉ ይዘህ ወደ ሰልፍ ውጣ አለው።

ቅዱስ ቴዎድሮስም እንዲህ ብሎ መለሰለት አንተ የጦር መሣሪያህን ወስደህ ለአሽከሮችህ ስጣቸው እኔ ክብር ይግባውና በፈጣሪዬ #ኢየሱስ_ክርስቶስ ርዳታ እተማመናለሁና የጦር መሣሪያ አልሻም እኔም ብቻዬን ወደ ጦርነቱ እሔዳለሁ ከወታደሮችም አንድ እንኳ ከእኔ ጋራ አልወስድም። በእጄ ውስጥ ያለ ይህ ጦር የተቀመጥኩበትም ፈረስ ይበቃኛል ከእኔ ጋራ የሚወጣ ፈጣሪዬ እርሱ ይረዳኛልና። ንጉሡም እነሆ ጠላቶቻችን ወደእኛ ቀርበዋልና የወደድከውን አድርግ አለው።

በማግሥቱም ቅዱስ ቴዎድሮስ ወደ ሰልፍ ወጣ ንጉሡም የበርበርን ሰዎች ትወጋቸው ዘንድ ምን ኃይል አለህ እነርሱ ብዙ ወገኖች ናቸውና አለው። ቅዱሱም ለንጉሡ እንዲህ ብሎ መለሰለት አንተ ከሠራዊትህ ጋራ በዚህ ቁም እኔም ወደ እነርሱ ብቻዬን እሔዳለሁ በነርሱም ላይ የሚደርሰውን ታያለህ። እኔ በ #እግዚአብሔር ኃይል እንደማጠፋቸው አውቃለሁና። ከእነርሱም አንዱ እንኳ ወደቤቱ አይመለስም። ንጉሡም አደነቀ ከእርሱ ጋር ያሉትም አደነቁ።

ከዚህም በኋላ ቅዱስ ቴዎድሮስ ወደ ጦርነቱ ብቻውን ሔደ ንጉሡንም ከእርሱ ሩቅ በሆነ ቦታ ተወው። ወደ በርበር ሰዎችም ደርሶ ትዋጋላችሁን ወይስ በሰላም ወደ አገራችሁ ትመለሳላችሁ አላቸው። እነርሱም ከአንተ በቀር ለሰልፍ የመጣ አናይምና ከማን ጋር እንዋጋለን አሉት እርሱም ማንም ከእኔ ጋር እንዲመጣ አልሻም። እኔ ብቻዬን በ #ፈጣሪዬ ኃይል አጠፋችኋለሁ አላቸው።

ምናልባት ውሻ ልታባርር መጥተህ ይሆናል ከፈቀድህ ግን ወደ አንተ ይመጣ ዘንድ ከእኛ ውስጥ አንዱን ምረጥና ሁለታችሁ ተጋጠሙ አሉት።

ያን ጊዜ ቅዱስ ቴዎድሮስ ከፈረሱ ላይ ወረደና ፊቱን ወደ ምሥራቅ መልሶ እንዲህ እያለ ጸለየ ጣዖታትን እስከ አጠፋቸውና የባቢሎንን ከተማ ዘንዶ እስከ ገደለው ድረስ ነቢዩ ዳንኤልን ያጸናኸው ጌታዬ አምላኬ ሆይ እንዲሁም ዛሬ ከእኔ ጋራ ሁን በረድኤትህም አጽናኝ #አብ_ወልድ_መንፈስ_ቅዱስ ሆይ ምስጋና ይገባሀል ለዘላለሙ አሜን።

ጸሎቱንም በፈጸመ ጊዜ ጦሩን አንሥቶ በላዩ በመስቀል ምልክት አማተበ በፈረሱ ላይም ተቀምጦ በበርበር ሰዎች ላይ እንዲህ እያለ ጮኸ እንዋጋ ዘንድ ወደኔ ኑ ክብር ይግባውና ለ #እግዚአብሔር_ኢየሱስ_ክርስቶስ እኔ ባሪያው ነኝ እንዲህም እያለ በመካከላቸው ገብቶ የበርበርን ሰዎች አጠፋቸው ከእነርሱም ፈረሰኛንም ሆነ እግረኛን ምንም አላስቀረም የመኳንንቶቻቸውንም ቸብቸቦ ቆርጦ ወደ ንጉሡ አቀረበ። ንጉሡም ተቀበለው ሠራዊቱም ሁሉ ሰገዱለት። የአንጾኪያም ከተማ ሰዎች ሁሉም ወጥተው የበርበርን አገር ማረኩ።

አውኪስጦስ በሚባል አገርም ሰዎች የሚያመልኩት ታላቅ ዘንዶ ነበረ ይበላቸውም ዘንድ በየዕለቱ ሁለት ሁለት ሰዎችን ይሰጡት ነበር ሁለት ልጆችም ያሏት አንዲት ክርስቲያናዊት መበለት ነበረች። እንዲበላቸውም ልጆችዋን ወሰደው ለዘንዶው አቀረቧቸው።

በዚያን ጊዜም ቅዱስ ቴዎድሮስ ወደዚያ አገር ደረሰ ያች መበለትም በፊቱ ቆመች ልጆቿን ወስደው እንዲበላቸው ለዘንዶው እንዳቀረቧቸው በእርሷ ላይ የሆነውን ሁሉ አልቅሳ ነገረችው።

ክርስቲያን እንደሆነችም ባወቀ ጊዜ በልቡ ይችን ሴት በድለዋታል #እግዚአብሔርም ይበቀልላታል አለ። ወዲያውኑም ከፈረሱ ወረደና ፊቱን ወደ ምሥራቅ መልሶ ጸለየ። ከዚህም በኋላ ወደ ዘንዶው ቀረበ የከተማው ሰዎችም ሁሉ ወደርሱ ይመለከቱ ነበር። በጦሩም ወግቶ ያንን ዘንዶ ገደለው። ርዝመቱም ሃያ አራት ክንድ ሆነ የመበለቷንም ልጆች አዳናቸው።

ከዚህም በኋላ አባቱን ይፈልገው ዘንድ ወደ ላይኛው ግብጽ ሔደ አባቱንም አገኘው አባቱም ልጁ እንደሆነ በምልክቶቹ አወቀው ቅዱሱም አባቱ እስከ አረፈ ድረስ በዚያ ኖረ።

ከዚህም በኋላ ወደ አንጾኪያ ከተማ ተመለሰ ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስንም ክብር ይግባውና #ክርስቶስን እንደካደና ጣዖትን እንደአመለከ ክርስቲያኖችንም ሲአሠቃያቸው አገኘው።
ከዚህም አስቀድሞ የከተማው ሰዎች የሚያመልኩትን ዘንዶ እርሱ እንደ ገደለው የአውኪስጦስ አገር ሰዎች ወደ ንጉሥ ከሰውት ነበርና ስለዚህ ንጉሥ ልኮ አስቀረበው።

ቅዱስ ቴዎድሮስም ወደ ንጉሡ በቀረበ ጊዜ ንጉሡን እንዲህ ብሎ ዘለፈው አንተ የክፉ ሥራ ሁሉ መገኛ የሆንክ ሰማይንና ምድርን የፈጠረ የክብር ባለቤትን ትተህ የረከሱ ጣዖታትን ያመለክ የኃጢአት ልጅ ሆይ ወዮልህ #እግዚአብሔርም ፈጥኖ መንግሥትህን ያጠፋታል።

በዚያን ጊዜም ንጉሡ ተቆጥቶ ከመሬት ላይ ጥለው ይገርፉት ዘንድ ወታደሮችን አዘዛቸው። ይህንንም አደረጉበት ደሙም እንደ ውኃ ፈሰሰ። እጆቹንና እግሮቹንም ከግንድ ጋር ቸነከሩት።

በሥቃይም ውስጥ ሳለ ከ #እግዚአብሔር የታዘዘ የመላእክት አለቃ #ቅዱስ_ሚካኤል ወደርሱ ወረደ እንዲህም አለው ጽና እነሆ የገድልህ ፍጻሜ ቀርቦአል ሥጋህ በውስጡ በሚኖርበትም ቦታ ድንቆችና ተአምራቶች ይገለጣሉ እነሆ ክብር ይግባውና #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ እንዲህ ብሎ ቃል ኪዳን ሰጠህ መታሰቢያህን ለሚያደርግ ሁሉ፣ ወይም በስምህ የተራበ ለሚያጠግብ፣ የተጠማውን ለሚያጠጣ፣ ወይም ለቤተክርስቲያንህ መባን መጻሕፍትንም ለሚሰጥ እኔ ኃጢአቱን ሁሉ እደመስስለታለሁ። ገድልህንም የሚጽፈውን፣ ወይም የሚያነበውን፣ የሚሰማውን፣ ወይም የሚገዛውን እኔ ስሙን በሕይወት መጽሐፍ እጽፋለሁ።

ከዚህም በኋላ ብዙዎች ከንጉሥ ሠራዊትና ከሕዝቡ ተሰብስበው በንጉሡ ላይ እንዲህ ብለው ጮኹበት አንተ ከሀዲ #እግዚአብሔር ያጥፋህ ከጠላቶቻችን ያዳነንን ኃያልና ጽኑዕ የሆነውን የከበረ ቴዎድሮስን ታሠቃየዋለህና ይህንንም ብለው በክብር ባለቤት #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ታመኑ ያን ጊዜም ንጉሥ ተቆጥቶ ሁሉንም አስገደላቸው ሰማዕትም ሆኑ የሰማዕትነት አክሊልንም ተቀበሉ።

ከዚህም በኋላ ንጉሡ አዘዘ የብረት ዐልጋም አምጥተው ቅዱሱን በላዩ አስተኙት ከበታቹም እሳትን አነደዱ ቅዱስ ቴዎድሮስም እንዲህ ብሎ ጸለየ አቤቱ ፈጣሪዬ ሠለስቱ ደቂቅን ከእሳት ምድጃ እንደ አዳንካቸው አድነኝ። ወዲያውኑም ያ እሳት ጠፋ እንደ ንጋት ጊዜ ቊርም ሆነ።

ከሰማይም እንዲህ የሚል ቃል መጣ ክብር ይግባውና ከ #ጌታ_ኢየሱስ_ክርስቶስ ኃይል የተሰጠህ ሆይ ጽና በርታ ያን ጊዜም ቅዱሱ ተነሥቶ በንጉሡ ፊት ቆመ እንዲህም አለው ክብር ይግባውና #ጌታዬ_ኢየሱስ_ክርስቶስ አድኖኛልና አንተ ከሀዲ እፈር አለው። የንጉሡም የጭፍራ አለቃ ይህን በአየ ጊዜ ክቡር ቴዎድሮስ ከሚያመልከው ክብር ይግባውና ከ #ጌ_ ከኢየሱስ_ክርስቶስ በቀር ሌላ አምላክ የለም ብሎ ጮኸ ርሱንም ራሱን አስቆረጠውና በሰማዕትነት ሞተ።

ቅዱስ ቴዎድሮስንም ብዙ ከአሠቃየውና ማሠቃየቱ ከሰለቸው በኋላ ራሱን በሰይፍ እንዲቆርጡ ሥጋውንም እንዲአቃጥሉ አዘዘ። በ #ጌታችንም ፈቃድ ከእናቱ ደጅ ወስደው እራሱን ቆረጡ ከእርሱም ደም፣ ወተትም ፈሰሰ ታላቅ እሳትም አንድደው ሥጋውን በውስጡ ጨመሩ እሳቱም ከቶ አልነካውም። እናቱም ለወታደሮች ብዙ ወርቅ ሰጥታ ሥጋውን ወሰደች በአማሩ ልብሶችም ገነዘችው እስከ መከራው ፍጻሜም በቤቷ ውስጥ አኖረችው።

ከዚያ በኋላም አብያተ ክርስቲያናት ተሠሩለት ስብጥ በሚባል በአባቱ አገርም በተሠራች ገዳም ሥጋውን አኖሩ ከሥጋውም ድንቆችና ተአምራቶች ተደረጉ ታላቅ ፈውስም ሆነ።

#ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ሐምሌ_20 እና #ዲያቆን_ዮርዳኖስ_አበበ)
2024/09/23 01:37:19
Back to Top
HTML Embed Code: