Telegram Web Link
ንጉሡም ሰይፍን አምጡ ደኅነኛውንም ልጅ ከሁለት ቆርጣችሁ እኵሌታውን ለዚች እኵሌታውን ለዚያች ስጡ አለ። ስለ ልጅዋ ማሕፀኗ ታውኳልና ልጅዋ ደኅና የሆነ ያቺ ሴት መልሳ ንጉሡን ጌታዬ አይደለም መግደልስ አትግደሉት ደኅነኛውን ልጅ ለሷ ስጧት አለችው ያቺ ሴት ግን አካፍሉን እንጂ ለእኔም ለእሷም አይሁን አለች።

ንጉሡም መግደልስ አትግደሉት እሱን ለእሷ ስጧት ላለችው ለዚች ሴት ደኅነኛውን ሕፃን ስጧት እርስዋ እናቱ ናትና አለ። እስራኤልም ሁሉ ንጉሡ የፈረደውን ይህን ፍርድ ሰምተው ቅን ፍርድን ይፈርድ ዘንድ የእግዚአብሔር ጥበቡ በሱ ላይ እንዳለ አይተዋልና በንጉሡ ፊት ፈሩ።

ከዚህም በኋላ የእስራኤል ልጆች ከግብጽ ከወጡ አራት መቶ ሰማንያ አራት ዘመን በሆነ ጊዜ ሰሎሞን በእስራኤል ላይ በነገሠ በአራተኛው ዓመት በሁለተኛው ወር የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ሊያንፅ ጀመረ።

በዐሥራ አንደኛውም ዘመነ መንግሥቱ ወሩ ባዕድ በሚባል በስምንተኛው ወር ቤቱንና ሥርዓቱን ሁሉ ፈጸመ በሰባት ዓመትም ውስጥ ሠራው የራሱንም ቤት በዐሥራ ሦስት ዓመት ሠርቶ ጨረሰ። ከዚህ በኋላ ሰሎሞን የእግዚአብሔርን ቤትና የራሱን ቤት በሃያ ዘመን ሠርቶ በጨረሰ ጊዜ የእግዚአብሔርን ታቦተ ሕግ ከዳዊት ከተማ ከጽዮን ያመጣት ዘንድ ያን ጊዜ የእስራኤልን ሽማግሌዎችና የነገድ አለቆች የአባቶቻቸውንም ቤት አለቆች ሁሉ በኢየሩሳሌም ሰበሰባቸው።

የእስራኤልም ሰዎች ሁሉ ወደ ንጉሡ ወደ ሰሎሞን በሰባተኛው ወር በጥቅምት ተሰበሰቡ። የእስራኤልም ሽማግሌዎች ሁሉ መጡ ካህናቱም ታቦትዋንና የምስክሩን ድንኳን በምስክሩ ድንኳን ውስጥ ያለ ንዋየ ቅድሳቱንም ሁሉ ተሸከሙ። ንጉሡና እስራኤል ሁሉ በታቦትዋ ፊት ሥፍር ቍጥር የሌላቸው በጎችና ላሞችን ይሠዉ ነበር። ካህናቱም ታቦቷን ከኪሩቤል ክንፎች በታች በቤቱ ውስጥ ወዳለው ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ቦታዋ አገቧት።

ኪሩቤል በታቦትዋ ቦታ ላይ ክንፋቸውን ጋርደዋልና ኪሩቤልም በስተላይ በኩል በቅድስተ ቅዱሳን ላይ ታቦትዋን ጋርደዋት ነበር። ከቅድስተ ቅዱሳንም ጋራ የተያያዙ ነበሩ። ቅዱሳን ኪሩቤል ከፍ ብለው ከቅድስተ ቅዱሳኑ አንጻር ላይ ሁነው ያያሉ በውጭ ግን አይታይም ነበር። ከግብጽ አገር በወጡ ጊዜ እግዚአብሔር ከእስራኤል ልጆች ጋራ ቃል ኪዳን ከገባባቸው ሙሴም በዚያ በኮሬብ ከአኖራቸው ከሁለቱ ጽላቶች በቀር በታቦቱ ውስጥ ሌላ አልነበረም።

ከዚህ በኋላ ካህናቱ ከቤተ መቅደስ በወጡ ጊዜ ቤተ መቅደሱን ሁሉ ብርሃን መላው። የእግዚአብሔር ብርሃን በማደሪያው ቤተ መቅደስ መልቷልና ከብርሃኑ መገለጥ የተነሣ ካህናቱ ሥራቸውን መሥራትና ከፊቱ መቆም ተሳናቸው።

ያን ጊዜ ሰሎሞን እግዚአብሔር በደመና ውስጥ እኖራለሁ ብሏል። እኔም ለዘላለም የምትኖርበት ማደሪያህ ቤተ መቅደስን በእውነት ሠራሁልህ አለ። ንጉሡም ፊቱን መልሶ የእስራኤልን ጉባኤ ሁሉ መረቃቸው ወደ እግዚአብሔርም ረዥም ጸሎትን ጸለየ። ሰሎሞንም ይህን ሁሉ ልመና ወደ እግዚአብሔር ለምኖ በጨረሰ ጊዜ በጉልበቱ ተንበርክኮ ከሰገደበት እጆቹንም ከዘረጋበት ከመሠዊያው ፊት ተነሣ።

ቆሞም የእስራኤልን ማኅበር እንደተናገረው ሁሉ ለወገኖቹ ለእስራኤል ዕረፍትን የሰጣቸው እግዚአብሔር ይክበር ይመስገን ብሎ በታላቅ ቃል መረቃቸው። ከዚህ በኋላ ንጉሡና የእስራኤል ልጆች ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት መሥዋዕትን ሠዉ።

ንጉሡ ሰሎሞንም ለእግዚአብሔር ስለ ሰላም መሥዋዕት የሠዋቸው ሃያ ሁለት ሽህ ላሞችና አንድ መቶ ሃያ ሽህ በጎች ናቸው ንጉሡ ሰሎሞንና የእስራኤል ልጆች ሁሉ ያንጊዜ ለእግዚአብሔር ማደሪያ ለቤተ መቅደስ ቅዳሴ ቤት አደረጉ።

ቀድሞ በገባዖን እንደታየው ዳግመኛ እግዚአብሔር ለሰሎሞን ታየው በፊቴ የለመንኸኝ ልመናህንና ጸሎትህን ሰማሁ። እንደ ልመናህም ሁሉ አደረግሁልህ ስሜ በዚያ ለዘላለሙ ጸንቶ ይኖር ዘንድ የሠራኸውንም ቤተ መቅደስ አከበርሁት ልቡናዬም ዐይኖቼም በዘመኑ ሁሉ በዚያ ጸንተው ይኖራሉ አለው። ሰሎሞንም አርባ ዘመን ነገሠ ከመንገሡም በፊት ዐሥራ ሁለት ዓመት ኖረ መላ ዕድሜውም ሃምሳ ሁለት ዓመት ነበር በሰላም አረፈ።

ይህም ጥበብ የተሰጠው ንጉሥ ሰሎሞን ጥቅም ያላቸው ብዙዎች መጻሕፍትን ደርሶአል። እሊህም ትንቢትና ትምህርት ያለባቸው ምሳሌዎችና መኃልዮች ናቸው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አባ_ኖብ

በዚህችም ቀን ደግሞ በክብር ባለቤት ክርስቶስ የታመነ አባ ኖብ አረፈ። ይህም ቅዱስ መነኰስ በላይኛው ግብጽ ከሚገኙ ገዳማት በአንዱ ገዳም ውስጥ የሚጋደል ጽሙድ ነበር።

ዲዮቅልጥያኖስም ብዙዎች ሰማዕታትን ሊአሠቃይና ደማቸውን ሊያፈስስ በጀመረ ጊዜ በአንዲት ቀን ሰማንያ ሰማዕታትን አቅርቦ ደማቸውን አፈሰሰ። በዚያን ጊዜ አባ ኖብን አስታወሱት የእንዴናው ገዥ ወደሆነው ወደ አርያኖስ አቀረቡት። እርሱም ለአማልክት ዕጠን ሠዋ ይህንንም የምንኵስና ልብስ ከላይህ አውጥተህ ጣል አለው።

አባ ኖብም ይህ ሥራ ከቶ ከእኔ ዘንድ አይደረግም የክብር ባለቤት ፈጣሪዬ ኢየሱስ ክርስቶስንም አልተውም የረከሱ ጣዖታትንም አላመልክም አለ። መኰንኑም በየራሱ በሆነ ሥቃይ እጅግ አሠቃየው ያም አባ ኖብ ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ኃይል ታግሦ ተቀበለ።

ከዚህም በኋላ ወደ አምስቱ አህጉር ሰደደው በዚያም በጉድጓድ ውስጥ ጣሉት በውስጡም ጌታችን ከሀዲው ዲዮቅልጥያኖስን አጥፍቶ ደግ ንጉሥ ቈስጠንጢኖስን እስከሾመው ድረስ ሰባት ዓመት ኖረ።

ቈስጠንጢኖስም በነገሠ ጊዜ ክብር ይግባውና ስለ ክርስቶስ የታሠሩትን ሁሉ ፈትተው ወደርሱ እንዲአቀርቧቸውና ከእርሳቸው እንዲባረክ ወደ አገሮች ሁሉ ደብዳቤዎችን ላከ። ለመልእክተኞችም እንዲህ አላቸው ሁሉንም ወደ እኔ ማድረስ ካልተቻላችሁ እጆቻቸውን በራሴ ላይ ጭነው ይባርኩኝ ዘንድ ክብር ያላቸውን ታላላቆችንና መምህራኑን አምጡአቸው።

ከእነርሱም ውስጥ የታወቁ አህናህ ከተባለ አገር አባ ዘካርያስ ከፍዩም መክሲሞስ ከሀገረ ድኂን አጋብዮስ ከሀገረ በላኦስ አባ ኖብ ናቸው የንጉሥ መልእክተኞችም በየአገሮች ሁሉ እየዞሩ የታሠሩ ቅዱሳንን ከእሥር ያወጡአቸው ነበር እነርሱም ደስ ይላቸው ነበር የተመሰገነ እግዚአብሔርንም ያመሰግኑት ነበር ይዘምሩለትም ነበር።

የንጉሥ መልእክተኛም አባ ኖብን ከአምስቱ አገሮች ፈልጎ የአገሩ አንጻር ወደ ሆነች ወደ ሀገረ በሰላ ወሰደው። በዚያም የብረት ልብስ ለብሶ ተቀምጦ ነበር የንጉሡ መልእከተኛም አገኘውና ከእርሱ ጋራ ወሰደው ወደ እንዴናውም እስከ ደረሱ በመርከብ ተሳፈሩ ክርስቲያኖችም ተሰበሰቡ ከውስጣቸውም አራት ኤጲስቆጶሳት ነበሩ አባ ኖብንም ያለ ውዴታው ቅስና ሾሙትና የቊርባን ቅዳሴን ቀደሰ።

በቅዳሴውም ፍጻሜ ቅድሳት ለቅዱሳን ብሎ ጮኸ ይህም ማለት ንጹሕና ቅዱስ የሆነ ከሥጋው ከደሙ ይቀበል ማለት ነው በዚያን ጊዜም ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በመሠዊያው ላይ ተቀምጦ ንስሐ የገቡትን ኃጢአታቸውን ይቅር ሲላቸው አየው ሥጋውንና ደሙንም ከአቀበላቸው በኋላ ወደ ንጉሡ ለመሔድ ተዘጋጁ ቍጥራቸውም ሰባ ሁለት ነበር ሠላሳ ሰባት ሠረገላም አዘጋጅተውላቸው እየአንዳንዳቸው በሠረገላው ተቀመጡ።

በአለፉም ጊዜ የደናግል ገዳማት ካሉበት ደረሱ ደናግሉም ወጥተው ተቀበሏቸው ቍጥራቸው ሰባት መቶ ነበር ከእነርሱ ጋራም እስከሚሰበሰቡ በቅዱሳን ፊት ይዘምሩ ነበር።

ወደ ንጉሡ ከተማም በደረሱ ጊዜ ወደ ንጉሡ ከመግባታቸው በፊት በውኃ ያጥቧቸውና አዳዲስ ልብሶችን ያለብሷቸው ጀመሩ እንዲሁም ለሁሉ አደረጉ ቅዱስ አባ ኖብ ግን አልታጠበም ልብሱንም አልለወጠም ።
ወደ ንጉሡም በገቡ ጊዜ ከእነርሱ ቡራኬ ተቀበለ ቁስላቸውንም ሳመ እጅግም አከበራቸው ብዙ ገንዘብም ሰጣቸው እነርሱ ግን ለቤተ ክርስቲያን ከሚሆን ንዋየ ቅድሳት በቀር ምንም ምን አልተቀበሉም ከዚህም በኋላ ሰላምታ ሰጥቶ ወደየሀገራቸው በሰላም አሰናበታቸው። አባ ኖብም ወደ ቦታው ተመልሶ አረፈና ወደ ወደደው ክርስቶስ ሔደ።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ሰኔ_23)
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ሰኔ_23_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ኤፌሶን 4
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ እንግዲህ በጌታ እስር የሆንሁ እኔ በተጠራችሁበት መጠራታችሁ እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እለምናችኋለሁ፤
² በትሕትና ሁሉና በየዋህነት በትዕግሥትም፤ እርስ በርሳችሁ በፍቅር ታገሡ፤
³ በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ።
⁴ በመጠራታችሁ በአንድ ተስፋ እንደ ተጠራችሁ አንድ አካልና አንድ መንፈስ አለ፤
⁵ አንድ ጌታ አንድ ሃይማኖት አንዲት ጥምቀት፤
⁶ ከሁሉ በላይ የሚሆን በሁሉም የሚሠራ በሁሉም የሚኖር አንድ አምላክ የሁሉም አባት አለ።
⁷ ነገር ግን እንደ ክርስቶስ ስጦታ መጠን ለእያንዳንዳችን ጸጋ ተሰጠን።
⁸ ስለዚህ፦ ወደ ላይ በወጣ ጊዜ ምርኮን ማረከ ለሰዎችም ስጦታን ሰጠ ይላል።
⁹ ወደ ምድር ታችኛ ክፍል ደግሞ ወረደ ማለት ካልሆነ፥ ይህ ወጣ ማለትስ ምን ማለት ነው?
¹⁰ ይህ የወረደው ሁሉን ይሞላ ዘንድ ከሰማያት ሁሉ በላይ የወጣው ደግሞ ያው ነው።
¹¹ እርሱም አንዳንዶቹ ሐዋርያት፥ ሌሎቹም ነቢያት፥ ሌሎቹም ወንጌልን ሰባኪዎች፥ ሌሎቹም እረኞችና አስተማሪዎች እንዲሆኑ ሰጠ፤
¹²-¹³ ሁላችን የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኝ አንድነት፥ ሙሉ ሰውም ወደ መሆን፥ የክርስቶስም ሙላቱ ወደሚሆን ወደ ሙላቱ ልክ እስክንደርስ ድረስ፥ ቅዱሳን አገልግሎትን ለመሥራትና ለክርስቶስ አካል ሕንጻ ፍጹማን ይሆኑ ዘንድ።
¹⁴ እንደ ስሕተት ሽንገላ ባለ ተንኮል በሰዎችም ማታለል ምክንያት በትምህርት ነፋስ ሁሉ እየተፍገመገምን ወዲያና ወዲህም እየተንሳፈፍን ሕፃናት መሆን ወደ ፊት አይገባንም፥
¹⁵ ነገር ግን እውነትን በፍቅር እየያዝን በነገር ሁሉ ወደ እርሱ ራስ ወደሚሆን ወደ ክርስቶስ እንደግ፤
¹⁶ ከእርሱም የተነሣ አካል ሁሉ እያንዳንዱ ክፍል በልክ እንደሚሠራ፥ በተሰጠለት በጅማት ሁሉ እየተጋጠመና እየተያያዘ፥ ራሱን በፍቅር ለማነጽ አካሉን ያሳድጋል።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ዮሐንስ 2
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ ልጆቼ ሆይ፥ ኃጢአትን እንዳታደርጉ ይህን እጽፍላችኋለሁ። ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።
² እርሱም የኃጢአታችን ማስተስሪያ ነው፥ ለኃጢአታችንም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን ለዓለሙ ሁሉ ኃጢአት እንጂ።
³ ትእዛዛቱንም ብንጠብቅ በዚህ እንዳወቅነው እናውቃለን።
⁴ አውቄዋለሁ የሚል ትእዛዛቱንም የማይጠብቅ ውሸተኛ ነው እውነትም በእርሱ ውስጥ የለም።
⁵ ቃሉን ግን የሚጠብቅ ሁሉ በእርሱ የእግዚአብሔር ፍቅር በእውነት ተፈጽሞአል። በእርሱ እንዳለን በዚህ እናውቃለን፤
⁶ በእርሱ እኖራለሁ የሚል እርሱ እንደ ተመላለሰ ራሱ ደግሞ ሊመላለስ ይገባዋል።
⁷ ወንድሞች ሆይ፥ ከመጀመሪያ የነበረቻችሁ አሮጌ ትእዛዝ እንጂ የምጽፍላችሁ አዲስ ትእዛዝ አይደለችም፤ አሮጌይቱ ትእዛዝ የሰማችኋት ቃል ናት።
⁸ ዳግመኛ አዲስ ትእዛዝን እጽፍላችኋለሁ፥ ይህም ነገር በእርሱ በእናንተም እውነተኛ ነው፤ ጨለማው ያልፋልና እውነተኛውም ብርሃን አሁን ይበራል።
⁹ በብርሃን አለሁ የሚል ወንድሙንም የሚጠላ እስከ አሁን በጨለማ አለ።
¹⁰ ወንድሙንም የሚወድ በብርሃን ይኖራል ማሰናከያም የለበትም፤
¹¹ ወንድሙን የሚጠላ ግን በጨለማ አለ፥ በጨለማም ይመላለሳል፥ የሚሄድበትንም አያውቅም፥ ጨለማው ዓይኖቹን አሳውሮታልና።
¹² ልጆች ሆይ፥ ኃጢአታችሁ ስለ ስሙ ተሰርዮላችኋልና እጽፍላችኋለሁ።
¹³ አባቶች ሆይ፥ ከመጀመሪያ የነበረውን አውቃችኋልና እጽፍላችኋለሁ። ጎበዞች ሆይ፥ ክፉውን አሸንፋችኋልና እጽፍላችኋለሁ። ልጆች ሆይ፥ አብን አውቃችኋልና እጽፍላችኋለሁ።
¹⁴ አባቶች ሆይ፥ ከመጀመሪያ የነበረውን አውቃችኋልና እጽፍላችኋለሁ። ጐበዞች ሆይ፥ ብርቱዎች ስለ ሆናችሁ የእግዚአብሔርም ቃል በእናንተ ስለሚኖር ክፉውንም ስለ አሸነፋችሁ እጽፍላችኋለሁ።
¹⁵-¹⁶ ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ፤ በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት ከዓለም ስለ ሆነ እንጂ ከአባት ስላልሆነ፥ ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም።
¹⁷ ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 2
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ በዓለ ኀምሳ የተባለውም ቀን በደረሰ ጊዜ፥ ሁሉም በአንድ ልብ ሆነው አብረው ሳሉ፥
² ድንገት እንደሚነጥቅ ዓውሎ ነፋስ ከሰማይ ድምፅ መጣ፥ ተቀምጠው የነበሩበትንም ቤት ሁሉ ሞላው።
³ እንደ እሳትም የተከፋፈሉ ልሳኖች ታዩአቸው፤ በያንዳንዳቸውም ላይ ተቀመጡባቸው።
⁴ በሁሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው፥ መንፈስም ይናገሩ ዘንድ እንደ ሰጣቸው በሌላ ልሳኖች ይናገሩ ጀመር።
⁵ ከሰማይም በታች ካሉ ሕዝብ ሁሉ በጸሎት የተጉ አይሁድ በኢየሩሳሌም ይኖሩ ነበር፤
⁶ ይህም ድምፅ በሆነ ጊዜ ሕዝብ ሁሉ ተሰበሰቡ፥ እያንዳንዱም በገዛ ቋንቋው ሲናገሩ ይሰማ ስለ ነበር የሚሉትን አጡ።
⁷ ተገርመውም ተደንቀውም እንዲህ አሉ፦ እነሆ፥ እነዚህ የሚናገሩት ሁሉ የገሊላ ሰዎች አይደሉምን?
⁸ እኛም እያንዳንዳችን የተወለድንበትን የገዛ ቋንቋችንን እንዴት እንሰማለን?
⁹ የጳርቴና የሜድ የኢላሜጤም ሰዎች፥ በሁለት ወንዝም መካከል በይሁዳም በቀጰዶቅያም በጳንጦስም በእስያም፥
¹⁰ በፍርግያም በጵንፍልያም በግብፅም በቀሬናም በኩል ባሉት በሊቢያ ወረዳዎች የምንኖር፥ በሮሜም የምንቀመጥ፥ አይሁድም ወደ ይሁዲነትም የገባን፥
¹¹ የቀርጤስና የዓረብ ሰዎች፥ የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ በልሳኖቻችን ሲናገሩ እንሰማቸዋለን።
¹² ሁሉም ተገረሙና አመንትተው እርስ በርሳቸው፦ እንጃ ይህ ምን ይሆን? አሉ።
¹³ ሌሎች ግን እያፌዙባቸው፦ ጉሽ የወይን ጠጅ ጠግበዋል አሉ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ሰኔ_23_ቀን_የዕለቱ_የቅዳሴ_ምስባክ👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"ዐርገ ውስተ አርያም ፄዊወከ ፄዋ። ወወሀብከ ጸጋከ ለእጓለ እመሕያው። እስመ ይክሕዱ ከመ ይኅድሩ"። መዝ 67፥18-19።
"ወደ ላይ ዓረግህ፥ ምርኮን ማረክህ፥ ስጦታንም ለሰዎች ሰጠህ፥ ደግሞም ለዓመፀኞች በዚያ ያድሩ ዘንድ።
እግዚአብሔር አምላክ ቡሩክ ነው እግዚአብሔር በየዕለቱ ቡሩክ ነው የመድኃኒታችን አምላክ ይረዳናል"። መዝ. 67፥18-19።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ሰኔ_23_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ዮሐንስ 14
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ ልባችሁ አይታወክ፤ በእግዚአብሔር እመኑ፥ በእኔም ደግሞ እመኑ።
² በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ፤ እንዲህስ ባይሆን ባልኋችሁ ነበር፤ ስፍራ አዘጋጅላችሁ ዘንድ እሄዳለሁና፤
³ ሄጄም ስፍራ ባዘጋጅላችሁ፥ እኔ ባለሁበት እናንተ ደግሞ እንድትሆኑ ሁለተኛ እመጣለሁ ወደ እኔም እወስዳችኋለሁ።
⁴ ወደምሄድበትም ታውቃላችሁ፥ መንገዱንም ታውቃላችሁ።
⁵ ቶማስም፦ ጌታ ሆይ፥ ወደምትሄድበት አናውቅም፤ እንዴትስ መንገዱን እናውቃለን? አለው።
⁶ ኢየሱስም፦ እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም።
⁷ እኔንስ ብታውቁኝ አባቴን ደግሞ ባወቃችሁ ነበር። ከአሁንም ጀምራችሁ ታውቁታላችሁ አይታችሁትማል አለው።
⁸ ፊልጶስ- ጌታ ሆይ፥ አብን አሳየንና ይበቃናል አለው።
⁹ ኢየሱስም አለው፦ አንተ ፊልጶስ፥ ይህን ያህል ዘመን ከእናንተ ጋር ስኖር አታውቀኝምን? እኔን ያየ አብን አይቶአል፤ እንዴትስ አንተ፦ አብን አሳየን ትላለህ?
¹⁰ እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ አታምንምን? እኔ የምነግራችሁን ቃል ከራሴ አልናገረውም፤ ነገር ግን በእኔ የሚኖረው አብ እርሱ ሥራውን ይሠራል።
¹¹ እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ እመኑኝ፤ ባይሆንስ ስለ ራሱ ስለ ሥራው እመኑኝ።
¹² እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ በእኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ሥራ እርሱ ደግሞ ያደርጋል፤ ከዚህም የሚበልጥ ያደርጋል፥
¹³ እኔ ወደ አብ እሄዳለሁና፤ አብም ስለ ወልድ እንዲከበር በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ አደርገዋለሁ።
¹⁴ ማናቸውንም ነገር በስሜ ብትለምኑ እኔ አደርገዋለሁ።
¹⁵-¹⁶ ብትወዱኝ ትእዛዜን ጠብቁ። እኔም አብን እለምናለሁ ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፤
¹⁷ እርሱም ዓለም የማያየውና የማያውቀው ስለ ሆነ ሊቀበለው የማይቻለው የእውነት መንፈስ ነው፤ ነገር ግን ከእናንተ ዘንድ ስለሚኖር በውሥጣችሁም ስለሚሆን እናንተ ታውቃላችሁ።
¹⁸ ወላጆች እንደ ሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም፤ ወደ እናንተ እመጣለሁ።
¹⁹ ገና ጥቂት ዘመን አለ ከዚህም በኋላ ዓለም አያየኝም፤ እናንተ ግን ታዩኛላችሁ፤ እኔ ሕያው ነኝና እናንተ ደግሞ ሕያዋን ትሆናላችሁ።
²⁰ እኔ በአባቴ እንዳለሁ እናንተም በእኔ እንዳላችሁ እኔም በእናንተ እንዳለሁ በዚያን ቀን ታውቃላችሁ።
²¹ ትእዛዜ በእርሱ ዘንድ ያለችው የሚጠብቃትም የሚወደኝ እርሱ ነው፤ የሚወደኝንም አባቴ ይወደዋል እኔም እወደዋለሁ ራሴንም እገልጥለታለሁ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #ቅዱስ_ዲዮስቆሮስ ቅዳሴ ነው። መልካም ዕለት ሰንበትና የጾም ጊዜ። ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ሰኔ_24

#ቅዱስ_ሙሴ_ጸሊም_ኢትዮጵያዊው

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ሰኔ ሃያ አራት በዚች ቀን አባ ሙሴ ጸሊም በሰማዕትነት ሞተ። ሰዎች ከገድሉ የተነሣ ይህን ቅዱስ ያደንቁታል እርሱ አስቀድሞ መንግሥተ ሰማያትን ገፍቷት ነበረና እርሱ በሥጋው ጠንካራ በሥራውም ኃይለኛ ነበር ይበላና ይጠጣ ይቀማና ያመነዝር ነበር ይገድልም ነበር ማንም ሊቋቋመው አይችልም ነበር።

አንድ በግ በአንድ ጊዜ ጨርሶ እንደሚበላና አንድ ፊቀን ወይን ጠጅ እንደሚጠጣ ስለ እርሱ ተነግሮአል። እርሱም ፀሐይን ለሚያመልኩ ሰዎች አገልጋይ ነበረ ብዙ ጊዜም ወደ ፀሐይ እያንጋጠጠ ፀሐይ ሆይ አንተ አምላክ ከሆንክ አነጋግረኝ ይል ነበር ደግሞም በልቡ የማላውቅህ ሆይ ራስህን አሳውቀኝ ይል ነበር።

ከዚህም በኋላ በአስቄጥስ ገዳም ያሉ መነኰሳት እግዚአብሔርን ያውቁታል ያዩታልም እያሉ ሲነጋገሩ ሰዎችን ሰማቸው። ያን ጊዜም ተነሣ ሰይፉንም ታጥቆ ወደ አስቄጥስ ገዳም ሔደ በደረሰም ጊዜ አባ ኤስድሮስን አገኘው። አባ ኤስድሮስም ፈራው ሙሴ ጸሊምም እውነተኛውን አምላክ ታሳውቁኝና ታስረዱኝ ዘንድ ወደ እናንተ መጣሁ አለው። አባ ኤስድሮስም ወደ አባ መቃርስ ወስዶ አገናኘው።

እርሱም ተቀብሎ ሃይማኖትን አስተማረው እንዲህም አለው ታግሠህ የማስተምርህን ከጠበቅህ እግዚአብሔርን ታየዋለህ። ከዚህም በኋላ የክርስትና ጥምቀትን አጥምቆ አመነኰሰው ከብዙዎች ገድለኞች ቅዱሳን ይልቅ ብዙና ጽኑዕ ገድልን መጋደል ጀመረ።

ሰይጣንም ቀድሞ ሲሠራው በነበረ በመብሉና በመጠጡ በዝሙቱም ይዋጋው ነበረ እርሱም በራሱ ላይ የሚደርስበትን ሁሉ ለአባ ኤስድሮስ ይነግረው ነበር እርሱም አጽናንቶ ሊሠራው የሚገባውን ያስተምረው ነበር።

ከገድሉ ብዛትም የተነሣ አረጋውያን መነኰሳት በሚተኙ ጊዜ ቤቶቻቸውን በመዞር ውኃ መቅጃዎችን ወስዶ ውኃ መልቶ በየቤታቸው ደጃፍ ያኖር ነበር። ውኃው ከእነርሱ ሩቅ ነበረና እንዲህም እያደረገ በመጋደል ለብዙ ዘመናት ኖረ።

ሰይጣንም በእርሱ ቀንቶ በእግሩ ውስጥ አስጨናቂ የሆነ አመታትን መታው ተኝቶም እየተጨነቀ ብዙ ቀን ታመመ። ከዚህም በኋላ የመታውና የሚፈታተነው ሰይጣን እንደሆነ ዐውቆ ሥጋው በእሳት ተለብልቦ እንደ ደረቀ ዕንጨት እስቲሆን ድረስ ተጋድሎውንና አገልግሎቱን አበዛ። እግዚአብሔርም ትዕግስቱን አይቶ ከደዌው ፈወሰው የሰይጣንንም ጦር ከእርሱ አራቀለት የመንፈስ ቅዱስም ጸጋ አደረበት ወደርሱም አምስት መቶ ወንድሞች መነኰሳት ተሰበሰቡ በእነርሱም ላይ አበ ምኔት ሆነ።

ከዚህ በኋላ ቅስና ሊሾሙት መረጡት በቤተ መቅደስም በሊቀ ጳጳሳቱ ዘንድ በአቆሙት ጊዜ ሊቀ ጳጳሳቱም አልፈቀደም ነበር አረጋውያኑንም ይህን ጠቋራ ለምን አመጣችሁት ከዚህ አውጡት አላቸው እርሱም መልክህ የከፋ ጠቋራ ሆይ መልካም አደረጉብህ በማለት ራሱን እየገሠጸ ወጣ ከዚህ በኋላ ዳግመኛ ሊቀ ጳጳሳቱ ጠራውና እጁን በላዩ ጭኖ ቅስና ሾመው እንዲህም አለው ሙሴ ሆይ እነሆ በውስጥም በውጭም ሁለመናህ ነጭ ሆነ።

በአንዲትም ዕለት ቅዱሳን አረጋውያን ወደርሱ መጡ በእርሱም ዘንድ ውኃ አልነበረም እርሱም ከበዓቱ ብዙ ጊዜ ወጣ ገባ ይል ነበር ከዚህ በኋላም ብዙ ዝናም ዘንሞ ጕድጓዶችን ሁሉ ሞላ። አረጋውያንም ለምን ብዙ ጊዜ ወጣ ገባ ትል ነበር ብለው ጠየቁት እርሱም እግዚአብሔርን ውኃ ካልሰጠኸኝ ቅዱሳን አገልጋዮችህን ምን አጠጣቸዋለሁ እለው ነበር በቸርነቱም ዝናምን ልኮልን ውኃን አገኘን አላቸው።

በአንዲትም ዕለት አባ ሙሴ ከአረጋውያን ጋራ ወደ አባ መቃርስ ሔደ አባ መቃርስም የሰማዕትነት አክሊል ያለው ከእናንተ ውስጥ አንዱን እነሆ አያለሁ አላቸው አባ ሙሴም አባቴ ሆይ ምናልባት እኔ እሆናለሁ በሰይፍ የገደለ በሰይፍ ይገደል ዘንድ አለው የሚል ጽሑፍ አለና ብሎ መለሰ።

ከዚህም በኋላ የበርበር ሰዎች መጡ አባ ሙሴም ከእርሱ ጋራ ያሉትን መነኰሳት እነሆ የበርበር ሰዎች ደረሱ መሸሽ የሚፈልግ ይሽሽ አላቸው እነርሱም አባታችን አንተስ አትሸሽምን አሉት እርሱም በሰይፍ የገደለ በሰይፍ ይገደላል ስለሚለው የእግዚአብሔር ቃል እነሆ ያቺን ቀን ለብዙ ዘመናት ስጠብቃት ኖሬአለሁ አላቸው።

ወዲያውኑም የበርበር ሰዎች ገብተው በሰይፍ ገደሉት መሸሽ ስለ አልፈለጉ ከእርሱ ጋራ ሰባት መነኰሳትም ተገደሉ አንዱ ግን ከምንጣፍ ውስጥ ተሠወረ የእግዚአብሔርንም መልአክ አየ በእጁም አክሊል ነበር እርሱም ቆሞ ይጠብቅ ነበር። ይህንንም በአየ ጊዜ ከተሠወረበት ወጣ የበርበር ሰዎችም ገደሉት የሰማዕትነትንም አክሊል ተቀበለ።

ወንድሞች ሆይ ከሀዲና ነፍሰ ገዳይ ቀማኛና ዘማዊ የነበረውን ለውጣ ደግ አባት መምህርና የሚያጽናና ለመነኰሳትም ሥርዓትን የሠራ ካህን እንዳደረገችው በሁሉም አብያተ ክርስቲያን ስሙ እንዲጠራ እንዳደረገችው የንስሐን ኃይሏን ተመልከቱ። ሥጋውም በአስቄጥስ ገዳም ደርምስ በተባለ ቦታ ለዘላለም ይኖራል ከእርሱም ብዙዎች ድንቆችና ተአምራት ይታያሉ።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ሰኔ_24)
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

✞✞✞ እንኩዋን ከዘመነ ጸደይ ወደ ዘመነ ክረምት መሸጋገሪያ ለሆነችው ዕለትና ለቅዱሳኑ ዓመታዊ ክብረ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞

=>ስንዱ እመቤት ቤተ ክርስቲያን (ሃገራችን) ሁሉ ነገሯ በሥርዓት ነውና ዓመቱን በዘመናት ከፍላ ትጠቀማለች:: እሊሕም ዘመናት መጸው (ጽጌ): ሐጋይ (በጋ): ጸደይ (በልግ)ና ክረምት ናቸው:: ዘመናቱ ወቅቶችን ከመለየትና ማሳወቅ ባሻገር የእኛ ሕይወትም ምሳሌዎች ናቸውና ልብ ልንላቸው ይገባል::

+በተለይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለስም አጠራሩ ጌትነት ይሁንና "ሽሽታችሁ (ስደታችሁ) በክረምትና በሰንበት እንዳይሆን ጸልዩ" ብሎናልና (ማቴ. 24:20) ልንጸልይ ይገባናል:: በዘመነ ክረምት ቅጠል እንጂ ፍሬ የለበትምና ፍሬ ምግባር ሣናፈራ ሞት እንዳይመጣ: አንድም ክረምት የዝናብና የጭቃ ጊዜ በመሆኑ እንኩዋንስ ለስደት ለኑሮም አይመችምና እንደ ሊቃውንት እንዲህ ብለን እንጸልይ:-

"በዝንቱ ክረምት በመዋዕሊነ:
እንበለ ፍሬ እንዘ በቆጽል ኀሎነ:
ናስተበቁዐከ እግዚኦ ኢይኩን ጉያነ::"
(ክረምት በተባለ በእኛ እድሜ:
ፍሬ ሳናፈራ በቅጠል /ያለ መልካም ሥራ/ ሳለን:
አቤቱ ጌታ ሆይ ስደትን አታምጣብን)

=>ቸሩ አምላካችን ከዘመነ መጸው በሰላም ያድርሰን:: ተረፈ ዘመኑንም የንስሃ: የፍሬና የበረከት ያድርግልን::

=>በዚሕች ዕለት እነዚህ ቅዱሳን ይከበራሉ:-

+" ቅዱስ ይሁዳ ሐዋርያ "+

+በዘመነ ሐዋርያት ይሁዳ ተብለው ይጠሩ ከነበሩት አንዱ የሆነው ቅዱሱ የአረጋዊው ቅዱስ ዮሴፍ ልጅ ሲሆን እናቱ ማርያም ትባል ነበር:: እናቱ ስትሞትበት ተጎድቶ የነበረ ቢሆንም ገና በልጅነቱ ድንግል ማርያም አግኝታው በፍጹም ጸጋ አሳድጋዋለች:: አስተዳደጉም ከጌታችን ጋር በአንድ ቤት ነበር::
ጌታችን እርሱንና ወንድሞቹን (ያዕቆብና ስምዖንን) ከ72ቱ አርድእት ቆጥሯቸዋል:: ቅዱስ ይሁዳ ወንጌል ላይ ከጌታችን ጋር መነጋገሩን ዮሐንስ ወንጌላዊ መዝግቧል:: (ዮሐ. 14:22)

+ቅዱስ ይሁዳ ከጌታችን እግር 3 ዓመት ተምሮ: መንፈስ ቅዱስንም ተቀብሎ ብዙ አሕጉራትን ዙሯል:: አይሁድንም አረማውያንንም ወደ ክርስቶስ ይመልስ ዘንድ ብዙ ድካምና ስቃይን በአኮቴት ተቀብሏል:: አንዲት አጭር (ባለ አንድ ምዕራፍ) መልእክትም ጽፏል:: አጭር ትምሰል እንጂ ምሥጢሯ እጅግ የሠፋ ነው:: ቅዱስ ይሁዳን በዚህች ቀን አረማውያን ገድለውት በሐዋርያነቱ ላይ የሰማዕትነትን ካባ ደርቧል::

+" ቅዱሳን ዺላጦስና አብሮቅላ "+

=>ብዙዎቻችን መስፍኑን ዺላጦስ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጌታችን እንዳይሰቀል ከአይሁድ ጋር ሲከራከር እናውቀዋለን:: የጌታችን ሞቱ በፈቃዱ ነበርና አይሁድ እንቢ ሲሉት የክርስቶስን ንጽሕና መስክሮ: እጁንም ታጥቦ ሰጥቷቸዋል:: የዺላጦስ ታሪክ ግን እዚህ ላይ አያበቃም::

+ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጐ ከተነሳ በሁዋላ ትንሳኤውን በራዕይ ገልጦለት አይሁድን ተከራክሯቸዋል:: ውሸታም ወታደሮችንም ቀጥቷል:: በመጨረሻ ግን በሮም ቄሳር ተጠርቶ ከእሥራኤል እስከ ሮም ድረስ ሰብኮ በሮም አደባባይ አንገቱ ተሠይፏል::

+ቅድስት እናታችን አብሮቅላም የዺላጦስ ሚስት ስትሆን ቁጥሯ ከ36ቱ ቅዱሳት አንስት ነው:: ጌታችንን ተከትላ: ቤቷን ለሐዋርያት አስረክባ: ቤተ ክርስቲያንንም በዘመኗ አገልግላ ዐርፏለች:: ዛሬ ሁለቱም ቅዱሳን ይታሠባሉ::

=>ጌታችን ከሐዋርያው ይሁዳ: ከዺላጦስና አብሮቅላም ጸጋ በረከትን ያድለን::

=>ሰኔ 25 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ይሁዳ ሐዋርያ (ከ72ቱ አርድእት)
2.ሰማዕቱ ዺላጦስ መስፍን
3.ቅድስት አብሮቅላ (ሚስቱ)
4.አባ ዼጥሮስ ሊቀ ዻዻሳት
5.የጸደይ መውጫ / የክረምትመግቢያ

=>ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ መርቆሬዎስ ሰማዕት
2.ቅድስት ቴክላ ሐዋርያዊት
3.ቅዱስ አበከረዙን ሰማዕት
4.ቅዱስ ዱማድዮስ ሶርያዊ
5.አቡነ አቢብ /አባ ቡላ/
6.ቅዱስ አባ አቡፋና ጻድቅ

=>+"+ የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ: የያዕቆብም ወንድም የሆነ ይሁዳ በእግዚአብሔር አብ ተወደው: ለኢየሱስ ክርስቶስም ተጠብቀው ለተጠሩ:
ምሕረትና ሰላም: ፍቅርም ይብዛላችሁ::
ወዳጆች ሆይ! ስለምንካፈለው ስለ መዳናችን ልጽፍላችሁ እጅግ ተግቼ ሳለሁ ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኩዋችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ:: +"+ (ይሁዳ. 1:1)

✞✞✞ ወስብሐት ለእግዚአብሔር ✞✞✞

" ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"::/የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ) እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል:: አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ /መጽሐፈ ምሥጢር/
https://www.tg-me.com/zikirekdusn
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

✞✞✞ እንኩዋን ለሐዋርያው #ቅዱስ_ታዴዎስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞

+"+ #ቅዱስ_ታዴዎስ_ሐዋርያ +"+

=>#ቅዱሳን_ሐዋርያት አባቶቻችን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በተከተሉበት ሰዓት እድሜአቸው በ3 ደረጃ የተከፈለ እንደ ነበር የቤተ ክርስቲያን ትውፊት ያሳያል::

¤እንደ #ዮሐንስ_ወንጌላዊ ያሉት በ20ዎቹ ውስጥ:
¤#ቅዱስ_ታዴዎስን የመሰሉት ደግሞ በ30ና በ40ዎቹ ውስጥ የነበሩ ሲሆን
¤እነ #ቅዱስ_ዼጥሮስ ደግሞ በ50ዎቹ ውስጥ የሚገኙ ነበሩ:: ደቀ መዛሙርቱ ከወጣቶችም: ከጐልማሶችም ከአረጋውያንም የተዋቀሩ ነበሩ ማለት ነው::

+ቅዱስ ታዴዎስ በቀደመ ስሙ #ልብድዮስ ይባል የነበረ ሲሆን በአንዳንድ መጻሕፍት ውስጥ (በተለይ በምሥራቅ ኦርቶዶክሶች) #ስምዖን እና #ይሁዳ እየተባለም ተጠርቷል::

+ቅዱሱ ጌታችን ተከትሎ:
¤ከ12ቱ አንዱ ሆኖ በፈጣሪው ተመርጦ:
¤3 ዓመት ከ3 ወር ከጌታ እግር ተምሮ:
¤በዕርገቱ ተባርኮ:
¤በበዓለ ሃምሳም 71 ልሳናትን ተቀብሎ:
¤#ሐዋርያት ዕጣ ሲጣጣሉ የበኩሉን አሕጉረ ስብከት ተካፍሎ ዓለምን ዙሯል::

+ቅዱስ ታዴዎስ አንድ ቀን ከሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ዼጥሮስ ጋር ወደ አንዲት ሃገር ይገባሉ:: ታዲያ ለቀናት ያለ ምግብ ወንጌልን ሲሰብኩ ቆይተው ነበርና ደጐቹ ሐዋርያት ራባቸው:: ወደ ከተማዋ ሳይገቡ አንድ ሽማግሌ ሲያርስ አይተው ሰላምታን ሰጡትና "እባክህ እርቦናልና አብላን" አሉት:: እርሱም ምንም ወገኑ ከአሕዛብ ቢሆነ አሳዝነውት በሬዎቹን ሳይፈታ እየሮጠ ሄደ::

+ያን ጊዜ ቅዱስ ታዴዎስ ሊቀ ሐዋርያትን "እርሱ እስኪመጣ ለምን አናርስም" አለው:: 2ቱ ተነስተው ታዴዎስ ሞፈር: ዼጥሮስ ደግሞ ስንዴውን ያዘ:: ቅዱሳኑ እየዘሩ ያረሱት ሰውየው ምግብ ይዞ እስኪመጣ አድጐ: አፍርቶ: እሸት ሆኖ ቆየው::

+ገበሬው የተደረገውን ተአምራት ባየ ጊዜ ደነገጠ:: ሊያመልካቸውም ወደደ:: እነርሱ ግን "እኛ የልዑል ባሮች ነን" ብለው በክርስቶስ ማመንን አስተማሩት:: "ልከተላችሁ" ቢላቸው "የለም! ከእሸቱ ይዘህ ወደ ከተማ ግባና ራት አዘጋጅልን:: እኛ እንመጣለን" አሉት::

+እርሱ ወደ ቤቱ ሲመለስ አሕዛብ ነገሩን ተረዱ:: ተሠብሥበውም "እነዚህ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እሳትም ሰይፍም አይበግራቸውም" ብለው ወደ ከተማ እንዳይገቡ ከበሩ ላይ ራቁቷን የሆነች ዘማ አቆሙ::

+ቅዱስ ታዴዎስ ገና ከርቀት ስላያት ቀና ብሎ #ቅዱስ_ሚካኤልን "እርዳን" አለው:: ሊቀ መላእክትም ድንገት ወርዶ ዘማዋን ሴት በጸጉሯ በዓየር ላይ ሰቀላት:: በከተማዋ ያሉ አሕዛብም ይህንና ሌሎች ተአምራትን አይተው ሁሉም በጌታችን አምነው ተጠመቁ:: ለሐዋርያቱም ሰገዱላቸው::

+አንድ ቀን ግን አንድ ጐረምሳ ባለ ጠጋ ቅዱስ ታዴዎስ "ሀብት ንብረታችሁን መጽውቱ" ሲል ሰምቶት ዘሎ የሐዋርያውን ጉሮሮ አንቆ ከሞት አድርሶት ነበር:: ያን ጊዜ "ጌታየ! ለካ ሀብታም ከሚጸድቅ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀላል ያልክ ለዚህ ነው!" ብሏል:: ባለ ጠጋው "እንዴት ይሆናል?" ቢለው መርፌ አሠርቶ ግመሉን ከነ ባለቤቱ በሰው ሁሉ ፊት 3 ጊዜ አሳልፎታል::

+ያም ማለት ጌታችን እንዳለው "በሰው ዘንድ የማይቻለው በእግዚአብሔር ዘንድ ይቻላል::" (ማር. 10:23) በዚህ ምክንያትም ያ ክፉ ባለ ጸጋ ወደ ልቡናው ተመልሶ ከቅዱስ ታዴዎስ እግር ሥር ወደቀ:: ሐዋርያውም አለው "ሀብትህን ለነዳያን ስጥ:: ይህንንም በትር እንካና እየዞርክ ወንጌለ መንግስትን ስበክ::" ባለ ጸጋውም የተባለውን ሁሉ ፈጽሞ በክብር ዐርፏል::

+ቅዱሳኑ ታዴዎስና ዼጥሮስ ግን በሃገሪቱ አብያተ ክርስቲያናትን አንጸው: ካህናትን ሹመው: ያቺን በዓየር ላይ የሰቀሏትን ዘማም የተባረከች መበለት አድርገው: በሌሎች አሕጉራት ወንጌልን ለማዳረስ ወጥተዋል::

+ቅዱስ ታዴዎስም እስከ እርጅናው ድረስ ለወንጌል ሲተጋ ኑሯል:: ጌታችንም በየጊዜው በአካል እየተገለጸ አጽናንቶታል:: ከብዙ የድካምና የመከራ ዘመናት በሁዋላም በዚህች ቀን ዐርፏል::

=>ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅዱሱ ሐዋርያ በረከት ይክፈለን::

=>ሐምሌ 2 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ታዴዎስ ሐዋርያ (ከ12ቱ ሐዋርያት)

=>ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት
2.ቅዱስ ኢዮብ ጻድቅ ተአጋሲ
3.ቅዱስ አቤል ጻድቅ
4.ቅዱስ አባ ዻውሊ ገዳማዊ (ታላቁ)
5.ቅዱስ ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ
6.አባ ሕርያቆስ ዘሃገረ ብሕንሳ

=>+"+ ጌታ ኢየሱስም ዘወር ብሎ አይቶ ደቀ መዛሙርቱን "ገንዘብ ላላቸው ወደ እግዚአብሔር መንግስት መግባት እንዴት ጭንቅ ይሆናል!" አላቸው:: ደቀ መዛሙርቱም እነዚህን ቃሎች አደነቁ:: ጌታ ኢየሱስም ደግሞ መልሶ "ልጆች ሆይ! በገንዘብ ለሚታመኑ ወደ #እግዚአብሔር መንግስት መግባት እንዴት ጭንቅ ነው! ባለ ጠጋ ወደ እግዚአብሔር መንግስት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀላል" አላቸው:: +"+ (ማር. 10:23-28)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>

" ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"::/የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ) እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::  አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ /መጽሐፈ ምሥጢር/
https://www.tg-me.com/zikirekdusn
2024/10/01 17:21:41
Back to Top
HTML Embed Code: