Telegram Web Link
ሥዕልም አፍ አውጥቶ ‹‹በመጀመሪያ አይሁድ በኢየሩሳሌም ራቁቴን ሰቀሉኝ፣ አሁን ደግሞ አንተ ድጋሚ በሮም ራቁቴን ትሰቅለኝን?›› ብሎ ተናገረው፡፡ ዮሐንስም እጅግ ደንግጦ ‹‹እንዴት አድርጌ ልሳልህ?›› ብሎ የሳለውን ሥዕል ቢጠይቀው ሥዕሉም ‹‹ከለሜዳ አልብሰህ ሳለኝ›› አለው፡፡ ዮሐንስም እንዳለው ከለሜዳ አልብሶ ከሳለው በኋላ ሥዕሉን ትኩር ብሎ ተመልክቶ ቢስመው ከንፈሩ አንድ ቀን ተኩል ያህል ተጣብቆ ቆይቷል፡፡ ዛሬም ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የምትጠቀምባቸውን የ #ጌታችንን ስነ ስቅለት የሚያሳዩ ሥዕሎች መገኛቸው ይህ ወንጌላዊው ዮሐንስ የሳለው ሥዕል ነው፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ በተለያዩ ስሞች ይጠራል፡፡ በሕይወቱና በኑሮው ሁሉ #ጌታችንን ለመምሰል ይጥር ነበርና ጌታችንም እጅግ ይወደው ስለነበር ‹‹ፍቁረ እግዚእ›› ተባለ፡፡ የታላቁ ያዕቆብ ታናሽ ወንድም ስለሆነና አባቱም ዘብድዮስ ስለሚባል ‹‹ዮሐንስ ወልደ ዘብድዮስ›› ተባለ፡፡ ለ #ጌታችን ባለው ቅናትና ከወንድሙ ጋር ሆነው ባሳዩት የኃይል ሥራ እንዲሁም የ #ጌታችንን አምላክነት በመግለጡ ‹‹ወልደ ነጎድጓድ›› ተብሏል፡፡ ነገረ መለኮትን ከሌሎቹ በበለጠ ሁኔታ አስፍቶና አምልቶ በማስተማሩ ‹‹ነባቤ መነኮት ወይም ታኦሎጎስ›› ተብሏል፡፡ ኃላፊውንና መጻዒውን ጊዜ በራእዩ ስለገለጠ ‹‹አቡቀለምሲስ›› ተባለ፣ ይህም በግሪክኛ ባለራእይ ማለት ነው፡፡ የጌታችንን መከራ መስቀሉን እያስታወሰ 70 ዘመን ሙሉ እያለቀሰ ስለኖረና ፊቱም በሀዘን ስለተቋጠረ ‹‹ቁዱረ ገጽ›› ተብሏል፡፡ ረድኤት በረከቱ ይደርብን፣ በጸሎቱ ይማረን፡፡  (ምንጭ፡- ስንክሳር ዘወርሃ ጥር፣ ቤተ ክርስቲያንህን ዕወቅ፣ የቅዱሳን ታሪክ-30)

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ በከበረ ሐዋርያ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘለዓለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ኢያሱ_ሲራክ_ነቢይና_ጠቢብ

በዚህች ቀን ዕውቀትን ከልቡ ያፈለቀ የኢየሩሳሌሙ ሰው የአልዓዛር ልጅ ኢያሱ ሢራክ አረፈ። እርሱም በጥንተ ትንቢቱ የባሕር አሸዋን የዝናም ጠብታን የዘመንን ቁጥር ማን ቈጠረ አለ።

#አብ ጋራ ስለ አለው አንድነት የጥበብ አኗኗር ከዓለም መፈጠር በፊት ነው ለጥበብ መገኛዋ ለማን ተገለጠ የጥበብ ምክሯንስ ማን አወቀ በ #እግዚአብሔር ዙፋን ላይ የምትቀመጥ እጅግ የምታስፈራ ናት አለ።

ሁለተኛም እኔ ከልዑል አፍ ወጥቼ ምድርን አንደ ጉም ሸፍንኋት በሰማያትም እኖራለሁ ዙፋኔንም በደመና ምሰሶ ላይ ዘረጋሁ ብቻዬን በሰማይ ዳርቻ ዞርኩ በውቅያኖስም ጥልቅ ውስጥ ማረፊያ እየፈለግሁ በባሕሩ ውኃ ላይ ሁሉ ተመላለስኩ አለች አለ።

ስለ ወልደ #እግዚአብሔርም ሰው መሆን እንዲህ አለ #እግዚአብሔር በያዕቆብ ዘንድ እደሪ በእስራኤልም ዘንድ ተዋረሺ አለኝ አለች። ደግሞ ስለ #መድኃኒታችን ሞትና ስለ አይሁድ መጥፋት በወጥመዱ ይጠመዳሉ የመሞቻቸው ጊዜም ሳይደርስ ይሠጥማሉ አለ። ስለ ንስሓና ከንስሓ በኋላ ወደ ኃጢአት ስለ መመለስ እንዲህ አለ ከታጠቡ በኋላ ቆሻሻን መዳሰስ ምን ይጠቅማል።

ደግሞ ስለ ቤተክርስቲያን መታነፅና ስለ ሕዝብ እንዲህ አለ። አቤቱ በስምህ የተጠሩና በበረከት ያባዛኃቸውን ወገኖችህን ይቅር በል መመስገኛህና ማደሪያህ የሆነች ሀገርህ ኢየሩሳሌምንም ይቅር በል። የቃልህንም በረከት በጽዮንና በልጆቿ ላይ ምላ።

ስለሹማምንትና ስለ ሰባቱ መዐርጋት ሲናገር እንዲህ አለ ሰባቱን ኃይሎች የተቀበለች የሰው ሰውነቱ ጉበኛ ናት። ከዚህም ሁሉ ጋር መንገድህን ያቀናልህ ዘንድ ወደ ልዑል #እግዚአብሔር ጸልይ። ስለ ጻድቃንም እንዲህ አለ የጻድቃን ልጆች በዱር ጠል የዱር አበባ እንዲ አብብ እንዲሁ ብቀሉ አብቡም እንደ ሊባኖስም መዓዛ መዓዛችሁ እንዲሁ የጣፈጠ ይሁን።

ዳግመኛም የ #እግዚአብሔርን ሥራ ሲያስብ እንዲህ አለ የሰማይን ንጽሕናውንና ጽናቱን ብርሃኑንም ያሳይ ዘንድ በሰማይ ገጽ ላይ ፀሐይን ማውጣቱን በቀትርም ጊዜ አገሩን ማቃጠሉን አስቦ። እንደ ምድጃ እሳት የሚነድ ላቦቱን ማን ይቃወመዋል የፀሐይ ዋዕይ ሦስተኛውም ተራሮችን ያቃጥላቸዋል ከእርሱም የእሳት ወላፈን ይወጣል አለ።

ጨረቃም ለዓለም ምልክቱ ነው በእርሱም የዘመናት የበዓላት ምልክት ይታወቃል። ስለ ከዋክብትም የሰማይ ጌጦቿ የከዋክብት ብርሃናቸው ነው በ #እግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃድ እንዲሁ ያበራሉና በሥርዓታቸውም ጸንተው ከልካቸውም ሳይፋለሱ ሳይሳሳቱ ጸንተው ይኖራሉና አለ።

ስለ ቀስተ ደመናም ተናገረ ቀስቱን አየሁ ፈጣሪውንም አከበረ ብርሃኑ መልካም ነውና የልዑል ሥልጣንም ያዘጋጀዋል። ስለ በረድና መብረቅም ተናገረ ስለ እርሱ ትእዛዝም በረድ ይዘንማል በቃሉም መብረቅ ይፈጥናል ደመናትም እንደ አዕዋፍ ይበራሉ ነፋስም በእርሱ ፈቃድ ይነፍሳል የነጐድጓድ ድምፅና ብልጭልጭታው ምድርን ያስፈራታል ዐውሎውና ውርጩ ነፍስን ያስጨንቃታል።

ሰማይን እንደ ብረት ልብስ የሚሸፍነው እንደ ስለታም የብርጭቆ ስባሪ ይብለጨለጫል አለ። ስለ ዝናምም ተናገረ ዝናም የወረደ እንደሆነ ምድርን ድስ ያሰኛታል በትእዛዙም ባሕር ይደርቃል አለ። አባቶችንም በተሰጣቸው ሀብት ሲያመሰግናቸው ኄኖክ #እግዚአብሔርን ደስ እንዳሰኘው። ኖኅም ጻድቅ ሁኖ እንደተገኘ።

አብርሃም ታማኝ እንደሆነ ይስሐቅም ለሰው ሁሉ የሚጠቅም በረከት እንደተሰጠው ለያዕቆብም በቸርነቱ እንደ ተገለጠለት ዐሥራ ሁለቱንም ነገድ እንደወለዳቸው በሰውና በ #እግዚአብሔርም ዘንድ እንደ ተወደዱ። ሙሴንም ስም አጠራሩ የከበረ የምላእክትም ብርሃን መልኩና ስም አጠራሩ የሆነ አለ። ወንድሙ አሮንንም የዘላለም ሕግን እንደ ሠራለት በልብሰ ተክህኖና በወርቅ አክሊል እንዳስደነቀው አለ። ሹመቱ ሦስተኛ የሚሆን የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስንም ወደሰ።

የነዌ ልጅ ኢያሱን ለእስራኤል ልጆች የርስታቸውን ምድር እንዳወረሳቸው እጁንም በአነሣ ጊዜ እንደተመሰገነ። ሳሙኤልንም በ #እግዚአብሔር ዘንድ የተወደደ እንደሆነ ናታንንም በዳዊት ዘመን ትንቢት እንደተናገረ። ዳዊትንም ታናሽ ሁኖ ሳለ አርበኛውን ጎልያድን እንደገደለው አምስግኖታል ሰሎሞንንም በሰላም ወራት እንደነገሠ።

ኤልያስንም ሙት እንዳስነሣ እሳትንም ከሰማይ እንዳወረደ ራሱም በእሳት ሠረገላና በእሳት ፈረሶች እንደዐረገ። ኤልሳዕንም በዘመኑ ጠላቶች እንዳስደነገጡት ሁለት ሙታኖችንም እንዳስነሣ አንዱን በሕይወት ሳለ አንዱን ከሞተ በኋላ።

ሕዝቅያስንም አገሩን አጽንቶ እንደ ጠበቀ የፋርስንም ሠራዊት በጸሎቱ አጥፍቶ ስለ ሀገራቸው ጽዮን የሚያለቅሱትን ደስ እንዳሰኛቸው ርኵሰትንና ኃጢአትንም እንደ አስወገደ ኢዮስያስንም የኢዮስያስ ስም አጠራሩ መልካም ነው እንዳለው።

ኤርምያስንም ከእናቱ ማሕፀን ጀምሮ እንዳከበረው። ሕዝቅኤልም የእግዚአብሔርን ጌትነቱን እንዳየ። ዘሩባቤልንም በቀኝ እጅ እንዳለ ኀቲም ቀለበት ነው እንዳለው።

ዐሥራ ሁለቱ ነቢያትንም በየቦታቸው ዐፅማቸው እንደሚለመልም። ሆሴዕና ነህምያንም የወደቀች ቅጽርን አንሥተው ጠቃሚ ሥራ እንደሠሩ። ዮሴፍንም እርሱን የመሰለ ደግ ሰው እንዳልተወለደ። ኖኅና ሴምንም ክብራቸው ከሰው ሁሉ እንደሚበልጥ። አዳምንም በፍጥረት ሁሉ ላይ ንጉሥ እንደ ሆነ።

ስምዖንን በዘመኑ ቤተ መቅደስ እንደታነፀ በሕዝቡ ከምርኮ መመለስም እንደ ተመሰገነ በመጽሐፉ መጨረሻም። በሁሉ ቦታ ታላላቅ ሥራ የሚሠራና ዕድሜያችንን የሚያስረዝም #እግዚአብሔር አምላክን አመስግኑት አለ። ይህንንም ተናግሮ በፍቅር አንድነት አረፈ።

#ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘለዓለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
#አቡነ_ሐዋርያ_ክርስቶስ

በዚህች ቀን ኢትዮጵያዊው ጻድቅ ለአቡነ ሐዋርያ ክርስቶስ ከዚህ ዓለም ከሞት ተሰወሩ፡፡   አቡነ ሐዋርያ ክርስቶስ የትውልድ ሀገራቸው ሸዋ መርሐ ቤቴ ነው፡፡ እንደ እነ ኤልያስና ሄኖክ ተሰውረዋል እንጂ በምድር ላይ ሞትን አልቀመሱም፣ ገና ወደፊት መጥተው በሰማዕትነት ይሞታሉ፡፡ ልደታቸው ሐምሌ 16 ቀን ነው፡፡ የነበሩበት ዘመንም በጻድቁ ንጉሥ በዐፄ ገብረ ማርያም ሐርበይ ዘመን ነው፡፡ ጻድቁን መልአኩ ከሚያገለግሉበት ከወሎ የህላ ሚካኤል ወደ ደብረ በንኮል ገዳም ወስዷቸው እንዲመነኩሱ አድርጓቸዋል፡፡ የቆረቆሩት ‹‹አቡነ ሐዋርያ ክርስቶስ ገዳም›› ወሎ መሐል ተከዜ ውስጥ ይገኛል፡፡ የበዛው ገድላቸው በዝርዝር ተጽፎ አይገኝም፡፡ ተከዜ በረሃ ላይ እጅግ አስደናቂ ትልቅ የአንድነት ገዳም አላቸው፡፡ 12 ክንፍ የተሰጣቸው ታላቁ ጻድቅ አቡነ ሐዋርያ ክርስቶስ በዛሬዋ ዕለት ነው የተሠወሩት፡፡

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

#ግንቦት_16_ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

1.ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ (ስብከቱና ቅዳሴ ቤቱ)
2.ቅዱስ ኢያሱ ሲራክ ነቢይና ጠቢብ (መጽሐፈ ሲራክን የጻፈ)
3.ቅድስት እናታችን ዐስበ ሚካኤል (ኢትዮዽያዊት)
4. አቡነ ሐዋርያ ክርስቶስ ከዚህ ዓለም ከሞት የተሰወሩበት


#ወርኀዊ_በዓላት

1.ኪዳነ ምሕረት (የሰባቱ ኪዳናት ማሕተም)
2.ቅድስት ኤልሳቤጥ (የመጥምቁ ዮሐንስ እናት)
3.ቅዱስ ገብረ ማርያም ጻድቅ ንጉሠ ኢትዮዽያ
  (የቅዱስ ላሊበላ ወንድም)
4.ቅዱስ አኖሬዎስ ንጉሥ ጻድቅ
5.አባ አቡናፍር ገዳማዊ
6.አባ ዮሐንስ ወንጌሉ ዘወርቅ
7.አባ ዳንኤል ጻድቅ

📖"በጌታ ኢየሱስ መስቀል አጠገብ እናቱ፡ የእናቱም እህት፡ የቀለዮዻም ሚስት ማርያም፡ መግደላዊትም ማርያም ቆመው ነበር። ጌታ ኢየሱስም እናቱን፡ ይወደው የነበረውንም ደቀ መዝሙር በአጠገቡ ቆሞ ባየ ጊዜ እናቱን 'አንቺ ሆይ! እነሆ ልጅሽ' አላት። ከዚህ በሁዋላ ደቀ መዝሙሩን 'እናትህ እነሁዋት' አለው። ከዚህም ሰዓት ጀምሮ ደቀ መዝሙሩ ወደ ቤቱ ወሰዳት።"
(ዮሐ. 19:25)

ወስብሐት ለእግዚአብሔር


(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ግንቦት እና #ከገድላት_አንደበት)
🌿እንኳን ለታላቁ የቤተ ክርስቲያን ጠበቃ ቅዱስ ኤዺፋንዮስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።

በስመ አብ፡ ወወልድ፡ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ

♱ቅዱስ ኤዺፋንዮስ

📝ሊቁ ቅዱስ ኤዺፋንዮስ ጽድቅ ከቅድስና : ድርሰት ከጥብቅና የተሳካለት አባት ነው:: "ኤዺፋንያ" ማለት የመለኮት መገለጥ ሲሆን "ኤዺፋንዮስ" ማለት ደግሞ ምሥጢረ መለኮት የተገለጠለት ማለት ነው።

💡ቅዱስ ኤዺፋንዮስ የተወለደው ክርስቶስን ከሚጠሉ አይሁዳውያን ቤተሰቦች ቤተ ገብርኤል ውስጥ ነው። ቤተሰቦቹ ከአንድ አህያ በቀር ምንም የሌላቸው ድሆች ነበሩ። በዚያ ላይ በልጅነቱ አባቱ በመሞቱ ከእናቱና ከአንዲት እህቱ ጋር በረሃብ ሊያልቁ ሆነ። ሕጻኑ ኤዺፋንዮስ በአህያው እንዳይሠራ አህያው ክፉ ነበርና ሊሸጠው ገበያ አወጣው።

📝ፊላታዎስ ከሚባል ክርስቲያን ጋር ለግዢ ሲደራደሩ አህያው የኤዺፋንዮስን ኩላሊቱን ረግጦት ለሞት አደረሰው:: በዚህ ጊዜ አብሮት ያለው ክርስቲያኑ በትእምርተ መስቀል አማትቦ አዳነው:: በፈንታው ግን አህያው ሞተ:: ሕጻኑ ኤዺፋንዮስ እያደነቀ ሔደ።

📝ከቆይታ በኋላ ሀብታም አጎቱ ገንዘቡን አውርሶት በመሞቱ ገና በ16 ዓመቱ ባለጠጋ ሆነ:: ያቺ ገበያ ላይ ያያት ተአምር ግን በልቡ ውስጥ ትመላለስ ነበር።

💡አንድ ቀን ደግሞ ሉክያኖስ ከሚባል ክርስቲያን ጋር ሲሔዱ ነዳይ አገኙ:: ባለጠጋው ኤዺፋንዮስ አለፈው:: ያ ድሃ ክርስቲያን ግን የለበሳትን አውልቆ መጸወተው:: በዚሕ ጊዜ መልዐኩ መጥቶ የብርሃን ልብስ ሲያለብሰው ኤዺፋንዮስ ተመለከተ።

📝ኤዺፋንዮስ ጊዜ አላጠፋም:: ከእህቱ ጋር በክርስቶስ አምኖ ተጠመቀ:: ሃብት ንበረቱን ግማሹን መጸወተ:: በተረፈው ደግሞ መጻሕፍትን ገዝቶ ወደ አባ ኢላርዮን ገዳም ገባ:: በዚያም መናንያኑ እስኪያደንቁት ድረስ በፍጹም ትጋትና ቅድስና ተጋደለ። በጸሎቱ ዝናም አዘነመ : ድውያንን ፈወሰ : ብዙ ተአምራትንም አደረገ።

📝 እግዚአብሔርም ደግሞ ለሌላ አገልግሎት ሽቶታልና በቆዽሮስ ደሴት ላይ ዻዻስ ሆኖ ተሾመ:: ብሉይ ከሐዲስ የወሰነ ሊቅ ነውና ብዙ መጻሕፍትን ተረጎመ:: በሺሕ የሚቆጠሩ ድርሳናትን ደረሰ:: በአፍም በመጽሐፍም ብሎ መናፍቃንንና አይሁድን ምላሽ በማሳጣቱ ቤተ ክርስቲያን "ጠበቃየ" ትለዋለች።

📝ከደረሳቸው መጻሕፍት መካከል "ሃይማኖተ አበው ዘኤዺፋንዮስ : መጽሐፈ ቅዳሴውና አክሲማሮስ (ስነ ፍጥረት)" ዛሬም በቅርብ ይገኛሉ:: ሊቁ ቅዱስ ኤዺፋንዮስ በመልካም እረኝነትና በሚደነቅ ቅድስና ተመላልሶ በ406 ዓ.ም. ዐርፏል:: እድሜውም 96 ዓመት ያህል ነበር።

🤲አምላካችን ከቅዱሱ ሊቅ በረከት ያድለን!

🗓 ግንቦት 17 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

1. ቅዱስ ኤዺፋንዮስ ሊቅ (ዘደሴተ ቆዽሮስ)
2. ቅዱስ ኢላርዮን ገዳማዊ
3. አባ ሉክያኖስ ጻድቅ
4. ቅዱስ ፊላታዎስ ክርስቲያናዊ

🗓 ወርኀዊ በዓላት

1. ቅዱስ እስጢፋኖስ ሊቀ ዲያቆናት (ቀዳሜ ሰማዕት)
2. ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ወልደ ዘብዴዎስ)
3. ቅዱሳን አበው መክሲሞስና ዱማቴዎስ
4. አባ ገሪማ ዘመደራ
5. አባ ዸላሞን ፈላሢ
6. አባ ለትጹን የዋህ

📖"የሚታገልም ሁሉ በነገር ሁሉ ሰውነቱን ይገዛል። እነዚያም የሚጠፋውን አክሊል ሊያገኙ ነው። እኛ ግን የማይጠፋውን። ስለዚህ እኔ ያለ አሳብ እንደሚሮጥ ሁሉ እንዲሁ አልሮጥም። ነፋስን እንደሚጐስም ሁሉ እንዲሁ አልጋደልም። ነገር ግን ለሌሎች ከሰበክሁ በኋላ ራሴ የተጣልሁ እንዳልሆን ሥጋዬን እየጐሰምሁ አስገዛዋለሁ።'' (1ቆሮ. 9:25)

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ግንቦት_17_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
  1ኛ ጢሞቴዎስ 3
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ ማንም ኤጲስ ቆጶስነትን ቢፈልግ መልካምን ሥራ ይመኛል የሚለው ቃል የታመነ ነው።
² እንግዲህ ኤጲስ ቆጶስ እንዲህ ሊሆን ይገባዋል፤ የማይነቀፍ፥ የአንዲት ሚስት ባል፥ ልከኛ፥ ራሱን የሚገዛ፥ እንደሚገባው የሚሰራ፥ እንግዳ ተቀባይ፥ ለማስተማር የሚበቃ፥
³ የማይሰክር፥ የማይጨቃጨቅ ነገር ግን ገር የሆነ፥ የማይከራከር፥ ገንዘብን የማይወድ፥
⁴ ልጆቹን በጭምትነት ሁሉ እየገዛ የራሱን ቤት በመልካም የሚያስተዳድር፤
⁵ ሰው ግን የራሱን ቤት እንዲያስተዳድር ባያውቅ፥ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን እንዴት ይጠብቃታል?
⁶ በትዕቢት ተነፍቶ በዲያብሎስ ፍርድ እንዳይወድቅ፥ አዲስ ክርስቲያን አይሁን።
⁷ በዲያብሎስ ነቀፋና ወጥመድም እንዳይወድቅ፥ በውጭ ካሉት ሰዎች ደግሞ መልካም ምስክር ሊኖረው ይገባዋል።
⁸ እንዲሁም ዲያቆናት ጭምቶች፥ በሁለት ቃል የማይናገሩ፥ ለብዙ ወይን ጠጅ የማይጎመጁ፥
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ጴጥሮስ 5
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ እንግዲህ እኔ፥ ከእነርሱ ጋር ሽማግሌ የክርስቶስም መከራ ምስክር ደግሞም ሊገለጥ ካለው ክብር ተካፋይ የሆንሁ፥ በመካከላቸው ያሉትን ሽማግሌዎች እመክራቸዋለሁ፤
² በእናንተ ዘንድ ያለውን የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ፤ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በውድ እንጂ በግድ ሳይሆን፥ በበጎ ፈቃድ እንጂ መጥፎውን ረብ በመመኘት ሳይሆን ጐብኙት፤
³ ለመንጋው ምሳሌ ሁኑ እንጂ ማኅበሮቻችሁን በኃይል አትግዙ፤
⁴ የእረኞችም አለቃ በሚገለጥበት ጊዜ የማያልፈውን የክብርን አክሊል ትቀበላላችሁ።
⁵ እንዲሁም፥ ጐበዞች ሆይ፥ ለሽማግሌዎች ተገዙ፤ ሁላችሁም እርስ በርሳችሁ እየተዋረዳችሁ ትሕትናን እንደ ልብስ ታጠቁ፥ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማልና፥ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል።
⁶ እንግዲህ በጊዜው ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከኃይለኛው ከእግዚአብሔር እጅ በታች ራሳችሁን አዋርዱ፤
⁷ እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት።
⁸ በመጠን ኑሩ ንቁም፥ ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና፤
⁹ በዓለም ያሉት ወንድሞቻችሁ ያን መከራ በሙሉ እንዲቀበሉ እያወቃችሁ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት።
¹⁰ በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዘላለም ክብሩ የጠራችሁ የጸጋ ሁሉ አምላክ ለጥቂት ጊዜ መከራን ከተቀበላችሁ በኋላ ራሱ ፍጹማን ያደርጋችኋል ያጸናችሁማል ያበረታችሁማል።
¹¹ ለእርሱ ክብርና ኃይል እስከዘላለም ድረስ ይሁን፤ አሜን።
¹² እየመከርኋችሁና የምትቆሙባት ጸጋ እውነትኛ የእግዚአብሔር ጸጋ እንድትሆን እየመሰከርሁላችሁ፥ የታመነ ወንድም እንደ ሆነ በቈጠርሁት በስልዋኖስ እጅ በአጭሩ ጽፌላችኋለሁ።
¹³ ከእናንተ ጋር ተመርጣ በባቢሎን ያለች ቤተ ክርስቲያን ልጄም ማርቆስ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል።
¹⁴ በፍቅር አሳሳም እርስ በርሳችሁ ሰላምታ ተሰጣጡ። በክርስቶስ ላላችሁ ለሁላችሁ ሰላም ይሁን። አሜን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 20
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²⁸ በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።
²⁹-³⁰ ከሄድሁ በኋላ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኩላዎች እንዲገቡባችሁ፥ ደቀ መዛሙርትንም ወደ ኋላቸው ይስቡ ዘንድ ጠማማ ነገርን የሚናገሩ ሰዎች በመካከላችሁ እንዲነሡ እኔ አውቃለሁ።
³¹ ስለዚህ ሦስት ዓመት ሌሊትና ቀን በእንባ እያንዳንዳችሁን ከመገሠጽ እንዳላቋረጥሁ እያሰባችሁ ትጉ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ግንቦት_17_ቀን_የዕለቱ_የቅዳሴ_ምስባክ👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"እስመ መምህረ ሕግ ይሁብ በረከተ። ወየሐውር እምኃይል ውስተ ኃይል። ወያስተርኢ አምላከ አማልክት በጽዮን"። መዝ. 83፥6-7።
"በልቅሶ ሸለቆ ውስጥ በወሰነው ስፍራ የሕግ መምህር በረከትን ይሰጣልና። ከኃይል ወደ ኃይል ይሄዳሉ፤ የአማልክት አምላክ በጽዮን ይታያል"። መዝ. 83፥6-7።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ግንቦት_17_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሉቃስ 19
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹¹ እነርሱም ይህን ሲሰሙ፥ ወደ ኢየሩሳሌም መቅረቡ ስለ ሆነ የእግዚአብሔርም መንግሥት ፈጥኖ ሊገለጥ እንዳለው ስለ መሰላቸው ምሳሌ ጭምር ተናገረ።
¹² ስለዚህም እንዲህ አላቸው፦ አንድ መኰንን ለራሱ መንግሥትን ይዞ ሊመለሰ ወደ ሩቅ አገር ሄደ።
¹³ አሥር ባሪያዎችንም ጠርቶ አሥር ምናን ሰጣቸውና፦ እስክመጣ ድረስ ነግዱ አላቸው።
¹⁴ የአገሩ ሰዎች ግን ይጠሉት ነበርና፦ ይህ በላያችን ሊነግሥ አንወድም ብለው በኋላው መልክተኞችን ላኩ።
¹⁵ መንግሥትንም ይዞ በተመለሰ ጊዜ፥ ገንዘብ የሰጣቸውን እነዚህን ባሪያዎች ነግደው ምን ያህል እንዳተረፉ ያውቅ ዘንድ እንዲጠሩለት አዘዘ።
¹⁶ የፊተኛውም ደርሶ፦ ጌታ ሆይ፥ ምናንህ አሥር ምናን አተረፈ አለው።
¹⁷ እርሱም፦ መልካም፥ አንተ በጎ ባሪያ፥ በጥቂት የታመንህ ስለ ሆንህ በአሥር ከተማዎች ላይ ሥልጣን ይሁንልህ አለው።
¹⁸ ሁለተኛውም መጥቶ፦ ጌታ ሆይ፥ ምናንህ አምስት ምናን አተረፈ አለው።
¹⁹ ይህንም ደግሞ፦ አንተም በአምስት ከተማዎች ላይ ሁን አለው።
²⁰ ሌላውም መጥቶ፦ ጌታ ሆይ፥ በጨርቅ ጠቅልዬ የጠበቅኋት ምናንህ እነሆ፤
²¹ ፈርቼሃለሁና፥ ጨካኝ ሰው ስለ ሆንህ፤ ያላኖርኸውን ትወስዳለህ ያልዘራኸውንም ታጭዳለህ አለው።
²² እርሱም፦ አንተ ክፉ ባሪያ፥ አፍህ በተናገረው እፈርድብሃለሁ። እኔ ያላኖርሁትን የምወስድና ያልዘራሁትን የማጭድ ጨካኝ ሰው እንደ ሆንሁ አወቅህ፤ ምን ነው ገንዘቤን ለለዋጮች አደራ ያልሰጠኸው?
²³ እኔም መጥቼ ከትርፉ ጋር እወስደው ነበር አለው።
²⁴ በዚያም ቆመው የነበሩትን፦ ምናኑን ውሰዱበት አሥሩ ምናን ላለውም ስጡት አላቸው።
²⁵ እርሱም፦ ጌታ ሆይ፥ አሥር ምናን አለው አሉት።
²⁶ እላችኋለሁ፥ ላለው ሁሉ ይሰጠዋል፥ ከሌለው ግን ያው ያለው ስንኳ ይወሰድበታል።
²⁷ ነገር ግን እነዚያን በላያቸው ልነግሥ ያልወደዱትን ጠላቶቼን ወደዚህ አምጡአቸው በፊቴም እረዱአቸው።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️  የ #ሚቀደሰው_ቅዳሴ የቅዱስ ኤጲፋንዮስ ቅዳሴ ነው፡፡ መልካም የቅዱስ ኢጲፋንዮስ የዕረፍት በዓልና የበዓለ ሃምሳ ጊዜ ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ግንቦት_21_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ቆሮንቶስ 7
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁹ ነገር ግን በምኞት ከመቃጠል መጋባት ይሻላልና ራሳቸውን መግዛት ባይችሉ ያግቡ።
¹⁰-¹¹ ሚስትም ከባልዋ አትለያይ፥ ብትለያይ ግን ሳታገባ ትኑር ወይም ከባልዋ ትታረቅ፥ ባልም ሚስቱን አይተዋት ብዬ የተጋቡትን አዛቸዋለሁ፥ እኔ ግን አላዝም፥ ጌታ እንጂ።
¹² ሌሎችንም እኔ እላለሁ፥ ጌታም አይደለም፤ ከወንድሞች ወገን ያላመነች ሚስት ያለችው ቢኖር እርስዋም ከእርሱ ጋር ልትቀመጥ ብትስማማ፥ አይተዋት፤
¹³ ያላመነ ባል ያላት ሚስትም ብትኖር ይህ ከእርስዋ ጋር ሊቀመጥ ቢስማማ፥ አትተወው።
¹⁴ ያላመነ ባል በሚስቱ ተቀድሶአልና፥ ያላመነችም ሚስት በባልዋ ተቀድሳለች፤ አለዚያ ልጆቻችሁ ርኵሳን ናቸው፤ አሁን ግን የተቀደሱ ናቸው።
¹⁵ የማያምን ግን ቢለይ ይለይ፤ ወንድም ቢሆን ወይም እኅት እንዲህ በሚመስል ነገር አይገዙም፤ እግዚአብሔር ግን በሰላም ጠርቶናል።
¹⁶ አንቺ ሴት፥ ባልሽን ታድኚ እንደ ሆንሽ ምን ታውቂአለሽ? ወይስ አንተ ሰው፥ ሚስትህን ታድን እንደ ሆንህ ምን ታውቃለህ?
¹⁷ ብቻ ለእያንዳንዱ እግዚአብሔር እንደ ከፈለለት እያንዳንዱም እግዚአብሔር እንደ ጠራው እንዲሁ ይመላለስ። እንዲሁም በአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እደነግጋለሁ።
¹⁸ ማንም ተገርዞ ሳለ ተጠርቶ እንደ ሆነ፥ ወደ አለመገረዝ አይመለስ፤ ማንም ሳይገረዝ ተጠርቶ እንደ ሆነ አይገረዝ።
¹⁹ መገረዝ ቢሆን አለመገረዝም ቢሆን ከንቱ ነው፥ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ መጠበቅ ነው እንጂ።
²⁰ እያንዳንዱ በተጠራበት መጠራት እንደዚሁ ይኑር።
²¹ ባሪያ ሆነህ ተጠርተህ እንደ ሆነ አይገድህም፤ አርነት ልትወጣ ቢቻልህ ግን አርነትን ተቀበል።
²² ባሪያ ሆኖ በጌታ የተጠራ የጌታ ነጻ ነውና፤ እንዲሁም ነጻ ሆኖ የተጠራ የክርስቶስ ባሪያ ነው።
²³ በዋጋ ተገዝታችኋል፤ የሰው ባሪያዎች አትሁኑ።
²⁴ ወንድሞች ሆይ፥ እያንዳንዱ በተጠራበት እንደዚሁ ሆኖ በእግዚአብሔር ዘንድ ይኑር።
²⁵ ስለ ደናግልም የጌታ ትእዛዝ የለኝም፥ ነገር ግን የታመንሁ እሆን ዘንድ ከጌታ ምሕረትን የተቀበልሁ እንደ መሆኔ ምክር እመክራለሁ።
²⁶ እንግዲህ ስለ አሁኑ ችግር ይህ መልካም ይመስለኛል፤ ሰው እንዲህ ሆኖ ቢኖር መልካም ነው።
²⁷ በሚስት ታስረህ እንደ ሆንህ መፋታትን አትሻ፤ በሚስት አልታሰርህ እንደ ሆንህ ሚስትን አትሻ።
²⁸ ብታገባ ግን ኃጢአት አትሠራም ድንግሊቱም ብታገባ ኃጢአት አትሠራም፤ ነገር ግን እንዲህ በሚያደርጉ በሥጋቸው ላይ መከራ ይሆንባቸዋል፥ እኔም እራራላችሁ ነበር።
²⁹ ዳሩ ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ይህን እናገራለሁ፤ ዘመኑ አጭር ሆኖአል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሚስቶች ያሉአቸው እንደሌላቸው ይሁኑ፥
³⁰ የሚያለቅሱም እንደማያለቅሱ፥ ደስ የሚላቸውም ደስ እንደማይላቸው፥
³¹ የሚገዙም ምንም እንደሌላቸው፥ በዚችም ዓለም የሚጠቀሙ በሙሉ እንደማይጠቀሙባት ይሁኑ፤ የዚች ዓለም መልክ አላፊ ነውና።
³² ነገር ግን ያለ አሳብ ልትኖሩ እወዳለሁ። ያላገባው ጌታን እንዴት ደስ እንዲያሰኘው የጌታን ነገር ያስባል፤
³³ ያገባው ግን ሚስቱን እንዴት ደስ እንዲያሰኛት የዓለምን ነገር ያስባል፥ ልቡም ተከፍሎአል።
³⁴ ያልተጋባች ሴትና ድንግል በሥጋም በነፍስም እንዲቀደሱ የጌታን ነገር ያስባሉ፤ የተጋባች ግን ባልዋን እንዴት ደስ እንድታሰኘው የዓለምን ነገር ታስባለች።
³⁵ ይህንም ለራሳችሁ ጥቅም እላለሁ፤ በአገባብ እንድትኖሩ ሳትባክኑም በጌታ እንድትጸኑ ነው እንጂ ላጠምዳችሁ ብዬ አይደለም።
³⁶ ዳሩ ግን ማግባት ወደሚገባው ዕድሜ በደረሰ ጊዜ ስለ ድንግልናው ያፈረ ሰው ቢኖር፥ የወደደውን ያድርግ፤ ኃጢአት የለበትም፤ ይጋቡ።
³⁷ ሳይናወጥ በልቡ የጸና ግን ግድ የለበትም፥ የወደደውን እንዲያደርግ ተፈቅዶለታል፤ ድንግልናውንም በልቡ ይጠብቅ ዘንድ ቢጸና፥ መልካም አደረገ።
³⁸ እንዲሁም ድንግልን ያገባ መልካም አደረገ ያላገባም የተሻለ አደረገ።
³⁹ ሴት ባልዋ በሕይወት ሳለ የታሰረች ናት፤ ባልዋ ቢሞት ግን በጌታ ይሁን እንጂ የወደደችውን ልታገባ ነጻነት አላት።
⁴⁰ እንደ ምክሬ ግን እንዳለች ብትኖር ደስተኛ ናት፤ እኔም ደግሞ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ያለ ይመስለኛል።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ራእይ 12
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ ታላቅ ምልክትም በሰማይ ታየ ፀሐይን ተጐናጽፋ ጨረቃ ከእግሮችዋ በታች ያላት በራስዋም ላይ የአሥራ ሁለት ከዋክብት አክሊል የሆነላት አንዲት ሴት ነበረች።
² እርስዋም ፀንሳ ነበር፥ ምጥም ተይዛ ልትወልድ ተጨንቃ ጮኸች።
³ ሌላም ምልክት በሰማይ ታየ፤ እነሆም ታላቅ ቀይ ዘንዶ፤ ሰባት ራሶችና አሥር ቀንዶችም ነበሩት በራሶቹም ላይ ሰባት ዘውዶች ነበሩ፥
⁴ ጅራቱም የሰማይን ከዋክብት ሲሶ እየሳበ ወደ ምድር ጣላቸው። ዘንዶውም ሴቲቱ በወለደች ጊዜ ሕፃንዋን እንዲበላ ልትወልድ ባላት ሴት ፊት ቆመ።
⁵ አሕዛብንም ሁሉ በብረት በትር ይገዛቸው ዘንድ ያለውን ልጅ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ልጅዋም ወደ እግዚአብሔርና ወደ ዙፋኑ ተነጠቀ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 7
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁴⁴ እንዳየው ምስል አድርጎ ይሠራት ዘንድ ሙሴን ተናግሮ እንዳዘዘው፥ የምስክር ድንኳን ከአባቶቻችን ዘንድ በምድረ በዳ ነበረች፤
⁴⁵ አባቶቻችንም ደግሞ በተራ ተቀብለው እግዚአብሔር በፊታቸው ያወጣቸውን የአሕዛብን አገር በያዙት ጊዜ ከኢያሱ ጋር አገቡአት፥ እስከ ዳዊት ዘመንም ድረስ ኖረች።
⁴⁶ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ አግኝቶ ለያዕቆብ አምላክ ማደሪያን ያገኝ ዘንድ ለመነ።
⁴⁷ ነገር ግን ሰሎሞን ቤት ሠራለት።
⁴⁸-⁵⁰ ነገር ግን ነቢዩ፦ ሰማይ ዙፋኔ ነው ምድርም የእግሬ መረገጫ ናት፤ ለእኔ ምን ዓይነት ቤት ትሠራላችሁ? ይላል ጌታ፥ ወይስ የማርፍበት ስፍራ ምንድር ነው? ይህንስ ሁሉ እጄ የሠራችው አይደለምን? እንዳለ፥ ልዑል የሰው እጅ በሠራችው አይኖርም።
⁵¹ እናንተ አንገተ ደንዳኖች ልባችሁና ጆሮአችሁም ያልተገረዘ፥ እናንተ ሁልጊዜ መንፈስ ቅዱስን ትቃወማላችሁ፤ አባቶቻችሁ እንደ ተቃወሙት እናንተ ደግሞ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ግንቦት_21_ቀን_የዕለቱ_የቅዳሴ_ምስባክ👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"ሰወረከኒ በዕለተ ቀትል መልዕልተ ርእስየ። ኢትመጥወኒ እግዚኦ እምፍትወትየ ለኃጥአን። ተማከሩ ላዕሌየ ኢትኅድገኒ ከመ ኢይዘኀሩ"። መዝ 139፥7-8
አቤቱ፥ ጌታዬ፥ የመድኃኒቴ ጕልበት፥ በሰልፍ ቀን ራሴን ሸፈንህ። አቤቱ፥ ከምኞቴ የተነሣ ለኃጢአተኞች አትስጠኝ፤ በላዬ ተማከሩ፤ እንዳይጓደዱ አትተወኝ። መዝ 139፥7-8
ወይም👉ልቤን ወደ ክፉ ነገር አትመልሰው፥ ዓመፅን ከሚያደርጉ ሰዎች ጋር ለኃጢአት ምክንያት እንዳልሰጥ፤ ከምርጦቻቸውም ጋር አልተባበር። ጻድቅ በምሕረት ይገሥጸኝ፥ ይዝለፈኝም፥ የኃጢአተኛ ዘይት ግን ራሴን አይቅባ፤ ጸሎቴ ገና በክፋታቸው ላይ ነውና። መዝ.104÷4-5
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ግንቦት_21_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ማቴዎስ 18
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁶ በእኔም ከሚያምኑ ከነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን የሚያሰናክል ሁሉ፥ የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ታስሮ ወደ ጥልቅ ባሕር መስጠም ይሻለው ነበር።
⁷ ወዮ ለዓለም ስለ ማሰናከያ፤ ማሰናከያ ሳይመጣ አይቀርምና፥ ነገር ግን በእርሱ ጠንቅ ማሰናከያ ለሚመጣበት ለዚያ ሰው ወዮለት።
⁸ እጅህ ወይም እግርህ ብታሰናክልህ፥ ቈርጠህ ከአንተ ጣላት፤ ሁለት እጅ ወይም ሁለት እግር ኖሮህ ወደ ዘላለም እሳት ከምትጣል ይልቅ አንካሳ ወይም ጉንድሽ ሆነህ ወደ ሕይወት መግባት ይሻልሃል።
⁹ ዓይንህ ብታሰናክልህ አውጥተህ ከአንተ ጣላት፤ ሁለት ዓይን ኖሮህ ወደ ገሃነመ እሳት ከምትጣል ይልቅ አንዲት ዓይን ኖራህ ወደ ሕይወት መግባት ይሻልሃል።
¹⁰ ከነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን እንዳትንቁ ተጠንቀቁ፤ መላእክቶቻቸው በሰማያት ዘወትር በሰማያት ያለውን የአባቴን ፊት ያያሉ እላችኋለሁና።
¹¹ የሰው ልጅ የጠፋውን ለማዳን መጥቶአልና።
¹² ምን ይመስላችኋል? ለአንድ ሰው መቶ በጎች ቢኖሩት ከእነርሱም አንዱ ቢባዝን፥ ዘጠና ዘጠኙን በተራራ ትቶ ሄዶም የባዘነውን አይፈልግምን?
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️#ሚቀደሰው_ቅዳሴ የእመቤታች የማርያም ቅዳሴ ነው፡፡ መልካም የደብረ ምጥማቅ በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ግንቦት_21

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ግንቦት ሃያ አንድ በዚች ዕለት #አምላክ_ለወለደች_ለእናታች ለእመቤታችን #ለቅድስት_ድንግል_ማርያም #በደብረ_ምጥማቅ በስሟ በተሰራች ቤተ ክርስትያን ጉልላት ላይ በብርሃን መርከብ ተቀምጣ ፊቷ በግልጥ #ለአምስት_ተካታታይ_ቀን_ስለመታየቱ የክርስቲያን ወገኖች በዓልን አደረጉ፣ ዳግመኛ በዚህች ቀን #በአንድ_ገዳም_ስልሳ_ሰባት_ዓመት ለተጋደሉ አባት ገሃነመ እሳት በማሰብ በዝሙትም ላለመውደቅ ብለው ሰውነታቸውን የሚነድ እሳት ውስጥ በመጨመር ዘማዊቷን ሴት ለንስሓ ላበቋት #ለአባ_መርትያኖስና #አንበሶች_ውሃ_ይቀዱላቸው ለነበረ፤ ሊፈታተናቸው የመጣውን ሰይጣን በዓታቸው ውስጥ አስገብተው በላዩ ዋሻውን ደፍነው ታላቅ የቋጥኝ ደንጊያም ለዘጉበት #ለአባ_አሮን_ሶርያዊ ዕረፍታቸው በዓል ነው፣ በተጨማሪ በዚህ ከሚታሰቡት፦ #ከነቢዩ_አሞጽ_ከመርዶላ ከመታሰቢያ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ደብረ_ምጥማቅ

ግንቦት ሃያ አንድ በዚች ዕለት አምላክን የወለደች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በደብረ ምጥማቅ በስሟ በተሠራች ቤተ ክርስቲያን ጉልላት ላይ በብርሃን መርከብ ተቀምጣ ፊቷ በግልጥ ስለመታየቱ የክርስቲያን ወገኖች ሁሉም ታላቅ በዓልን ያደርጋሉ።

እርሷም በልጅዋ የመለኮት ብርሃን የተጐናጸፈች ናት በዙሪያዋም የመላእክት ሠራዊት የመላእክት አለቆችም በየማዕረጋቸው ክንፋቸውን ዘርግተው ይቆሙ ነበር ይጋርዷታልም። ሱራፌልም ማዕጠንታቸውን ይዘው ለንግሥዋ ገናናነት ይሰግዳሉ በየስግደታቸውም እንዲህ እያሉ ያመሰግኗታል። አብ በሰማይ ሁኖ ተመለከተ እንደ አንቺ ያለ አላገኘም አንድ ልጁንም ልኮ ከአንቺ ሰው ሆነ።

ሁለተኛ ሰማዕታትም በየማዕርጋቸው ረቂቃን በሆኑ ፈረሶቻቸው ተቀምጠው እየመጡ መጀመሪያ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአምባላይ ፈረሱ ወርዶ ይሰግድላታል እንዲሁም ባልንጀሮቹ ሰማዕታት መጥተው ይሰግዱላታል ።

ከእርሱ በኋላ የሚመጣው በዱሪ ፈረስ የሚቀመጥ ይህ መርቆሬዎስ ነው። ከዚህም በኋላ ሰማዕታት ሁሉ በመከታተል መጥተው ይሰግዱላታል ምስጋናም ያቀርቡላታል። ሁለተኛም ደግሞ የጻድቃን አንድነታቸው መጥተው በፊቷ ሰግደው ይመላለሳሉ።

ሄሮድስ የገደላቸው ሕፃናትም መጥተው ይሰግዱላታል በፊቷም እየዘለሉ አንዱ በአንዱ ላይ እየዘለለ በመተቃቀፍም ይጫወታሉ የተሰበሰቡትም በአዩ ጊዜ ደስታ ይመላባቸዋል በሰማይም ያሉ ይመስላቸው ነበር።

እናትና አባቱም የሞቱበት ቢኖር ወይም ከዘመዶቹ ወይም ባልንጀራዉ ቅድስት ድንግል እመቤቴ ሆይ ዕገሌን አሳዪኝ ብሎ በሚለምናት ጊዜ ቀድሞ በነበረበት መልኩ ያን ጊዜ ታመጣዋለች። ደግሞ መሀረባቸውን ወደላይ ይወረውሩላታል የወደደችውንም በእጇ ተቀብላ መልሳ ትጥልላቸዋለች ለበረከትም በየጥቂቱ ይካፈሉታል።

እንዲህም አምስት ቀን ሁሉ ክርስቲያንም እስላሞችም አረማውያንም ያይዋታል። ወደ ቤታቸውም ለመሔድ ሲሹ በፊቷ ሰግደው ይሰናበቷታል እርሷም ትባርካቸውና ይመለሳሉ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አባ_መርትያኖስ

በዚህችም ዕለት የከበረ አባት አባ መርትያኖስ አረፈ። ይህም አባት በልጅነቱ ከአንድ ቅዱስ የሆነ አረጋዊ አባት ዘንድ መንኵሶ ታላቅ ገድልን ተጋደለ። ከዚህም በኋላ ሐመረ ኖኅ ወደምትባል በቂሣርያ ወደአለች ገዳም ሔደ በዚያም እጅግ በጣም የበዛ ገድልን ተጋደለ።

በጸሎት በጾም በስግደትም በሌሊትና በመዓልት በመትጋት እየተጋደለ ስድሳ ሰባት ዓመት በኖረ ጊዜ የገድሉና የትሩፋቱ ወሬ በቦታው ሁሉ ተሰማ ። እነሆ አንዲት በክፉ ሥራዋና በዝሙቷ የታወቀች ኃጢአተኛ አመንዝራ ሴት ሰማች። ጽድቁንና ቅድስናውን በመናገር የሚያመሰግኑትን እንዲህ አለቻቸው።እናንተ ታመሰግኑታላችሁ እርሱ የሚኖረው በዱር ነው የሴት ገጽ ከቶ አያይም እኔን ቢያይ ድንግልናውን አጥፍቼ ቅዱስናውን በአረከስኩት ትኀርምቱንም ባፈረስኩት ነበር። እነርሱ ግን ጥንክርናውን ስለ ሚያውቁ ተከራከሩዋት።

ስለዚህም በመካከላቸው ክርክር ሆነ ሔጄ ከእኔ ጋራ በኃጢአት ብጥለው ምን ትሰጡኛላችሁ አለቻቸውና ገንዘብ ሊሰጡአት ተስማሙ። ያን ጊዜም ተነሥታ ጌጦቿን ልብሶቿንና ሽቱዎቿን ያዘች መልኳም እጅግ ውብ ነበረች ፊቷንም ተከናንባ ጨርቅ ለብሳ ወደ በዓቱ ሔደች። ልብሷንና ጌጦቿንም ለብቻቸው በከረጢት አሥራ ያዘች። ከበዓቱም ቅርብ በሆነ ቦታ ተሠውራ እስከ ሚመሽ ቆይታ የበዓቱን ደጃፍ አንኳኳች። አራዊት እንዲበሉኝ በውጭ አትተወኝ እኔ መጻተኛ ነኝና መንገድንም ተሳስቼ ወደዚህ ደረስኩ አለችው። እርሱም በልቡ አሰበ በውጭ ብተዋት አራዊት ይበሏታል ባስገባትም ስለርስዋ ጦር በኔ ላይ ይነሣብኛል አለ።

ከዚህም በኋላ ከፈተላት በዚያችም በዓት ውስጥ ትቷት ወደ ሌላ ቦታ ፈቀቅ አለ። እርሷ ግን ልብሶቿን ለብሳ ጌጦቿንም ተሸልማ ሽቱዎቿን ተቀብታ ወደርሱ ገባች ከርሷ ጋርም እንዲተኛ ፈልጋ ከዚህ ማንም የሚያየን የለም አለችው።

ቅዱሱም የሰይጣን ማጥመጃው እንደሆነች አውቆ ጥቂት ታገሺኝ መንገድን እስታይ እግዚአብሔርን የማንፈራው ከሆነ እንደእኛ ያሉ ሰዎችን ላንፈራቸው ይገባናል አላት። ይህንንም ብሎ ከእርሷ ዘንድ ወጣ ታላቅ እሳትም እንድዶ እግሩን ከውስጡ ጨመረ ነፍሱንም የሲኦልን እሳት የምትችዪ ከሆንሽ ኃጢአትን ሥሪያ አላት።

በዘገየ ጊዜ ወደርሱ ሔደች በእሳት ውስጥም እግሩን ሲያቃጥል አይታው እጅግ ደነገጠች። ከእሳትም ውስጥ ጐትታ አወጣችው ልቧም ወደ ንስሓ ተመለሰ። ልብሷንና ጌጦቿን ከላይዋ አውጥታ ጣለች ከእግሩ በታች ሰገደች ስለነፍሷ ድኅነትም እንዲረዳት ለመነችው።

እርሱም ይህ ዓለም ፍላጎቱ ሁሉ ኀላፊ እንደ ሆነ ያስተምራትና ይመክራት ልብ ያስደርጋትም ጀመር እርሷም በጨከነ ልብ ንስሓ ገባች። ከዚህም በኋላ በአንድነት መኖር አግባብ አይደለም ብሎ ወደ ደናግል ገዳም ወሰዳት ትጠብቃትም ዘንድ እመ ምኔቷን አደራ አላት። በቀረው ዕድሜዋም በገድል ተጠምዳ እግዚአብሔርን አገለገለችው ወደ በጎ ሽምግልናም ደረሰች የመፈወስ ሀብትም አድሮባት ብዙዎች በሽተኞችን አዳነች።

የከበረ አባ መርትያኖስ ግን ሌላ ሴት እንዳያመጣበት ፈርቶ በባሕር መካከል ወዳለች ደሴት ገብቶ በዚያ የሚኖር ሆነ። አንድ ባለ ታንኳም የእጅ ሥራውን እየሸጠ ምግቡን ያመጣለት ነበር። ከብዙ ዘመናትም በኋላ መርከብ ተሰብራ ሰጠመች አንዲት ሴትም በመርከብ ስባሪ ተጣብቃ አባ መርትያኖስ ወደ አለበት ደሴት የባሕሩ ማዕበል አደረሳት በአያትም ጊዜ ደነገጠ አደነቀም። ከእርሷ ጋር በአንድነት ስለ መኖሩም አዘነ የእግዚአብሔርንም ቃል አስተምሮ የምንኲስና ልብስ አለበሳት ምግቧንም አዘጋጀላትና ለእኛ በአንድነት መኖር አግባብ አይደለም አላት። ያንንም ደሴት ትቶላት ወደ ባሕሩ ተወርውሮ ገባ አንበሪም ተሸክሞ ወደ የብስ አወጣው።

መቶ ስምንት አገሮችንም እስቲአዳርስ በአገሮች በአሉ ገዳማት ሁሉ ከዚያች ቀን ጀምሮ የሚዞር ሆነ በአንድ ቦታ እንዳይቀመጥ አስቦ ነው። ከዚህ በኋላም የዕረፍቱ ጊዜ እንደ ቀረበ አውቆ በበዓት ውስጥ ራሱን እሥረኛ አደረገ። ኤጲስቆጶሱንም ጠርቶ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ገድሉን ሁሉ ነገረው ኤጲስቆጶሱም ከጸጋው ገናናነት የተነሣ አደነቀ።

ከዚህም አስቀድሞ የእግዚአብሔር መልአክ ለኤጲስቆጶሱ ስለአባ መርትያኖስ ሥጋ እንዲአስብ ነግሮት ነበር። ከዚህም በኋላ ነፍሱን በእግዚአብሔር እጅ ሰጠ ኤጲስቆጶሱም በታላቅ ክብር ገንዞ ቀበረው።

ያቺን ሴት ግን እስከ ዕረፍቷ ቀን ባለ መርከብ የሚጎበኛት ሆነ በአረፈችም ጊዜ ሥጋዋ እንደ በረዶ ነጥቶ አገኛት ሥጋዋንም ወደ ሀገሩ ተሸክሞ ወስዶ ቀበራት።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አሮን_ሶርያዊ

በዚችም ዕለት ከልጅነቱ ጀምሮ ተጋዳይ የሆነ አባ አሮን ሶርያዊ አረፈ። ለዚህ ቅዱስም የመፈወስና ድንቆች ተአምራትን የማድረግ ሀብት ተሰጥቶታል። ይኸውም እንግዶች መነኰሳት ወደ ርሱ በመጡ ጊዜ የርግብ ግልገሎችን አብስሎ አቀረበላቸው።

ሥጋ አንበላም ባሉት ጊዜ በላያቸው አማትቦ ርግቦቹን አድኖ እንዲበሩ አደረጋቸው። ደግሞ በተራራ ላይ ገዳም ሠራ ውኃው ከተራራው በታች የራቀ ነበረ በጸለየና በእጁ ባማተበ ጊዜ ስቦ ከተራራው ላይ አወጣው።

በአንዲት ቀንም ሰይጣን በክፋቱ ሊአጠፋው ወደርሱ መጣ እርሱ ግን በላዩ በአደረ መንፈስ ቅዱስ ተንኰሉን አውቆ ና ወደ በዓት ግባ አለው። በገባ ጊዜም በላዩ ዋሻውን ደፈነው ታላቅ የቋጥኝ ደንጊያም ጫነበት ሰይጣንም አፈረ።

ደግሞም ሁለተኛ የአካ አገረ ገዥ በሞተ ጊዜ በጸሎቱ አስነሣው። ደግሞ ውኃ የሚቀዳባቸውን አራት እንስራዎችን በአንበሳ እየጫነ በመውሰድ ዐሥር ዓመት ያህል ኖረ።

ከዚህ በኋላም ወደ ዘላለም ሕይወት ሔደ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በከበረች ጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አሞጽ_ነቢይ

በዚችም ቀን ከዐሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት አንዱ አሞጽ ነቢይ መታሰቢያው ነው። አሞጽ ማለት "እግዚአብሔር ጽኑዓ ባሕርይ ነው: አንድም እግዚአብሔር ያጸናል::" ማለት ነው:: "ተወዳጅ ሰው" ተብሎም ይተረጐማል:: የነበረውም ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በስምንት መቶ ዓመት ሲሆን አባቱ ቴና እናቱ ሜስታ ይባላሉ:: ትውልዱም ከነገደ ስምዖን ነው:: በትውፊት ይህ ነቢይ የነቢዩ ኢሳይያስ አባት ነው የሚሉ ቢኖሩም ሁለቱ አሞጾች የተለያዩ መሆናቸውን ሊቃውንት ይናገራሉ::

ይህ ዕውነተኛ ነቢይ በእስራኤል ነገሥታት በኢዮአስና በኦዝያ ዘመን አስተማረ የእስራኤልንም ልጆች የእስራኤልንና የይሁዳንም ነገሥታት ይገሥጻቸው ነበር ።

ስለ ክብር ባለቤት ስለ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መከራ ስለመቀበሉ በዚያችም ቀን ስለ ፀሐይ መጨለም ከዚያም በኋላ እስራኤልን ስለሚደርስባቸው መከራ፣ ኀዘን፣ ልቅሶ፣ ረድኤትም እንደሚአጡ፣ የእግዚአብሔርንም ቃል መስማትን ከማጣት የተነሣ እንደሚራቡና እንደሚጠሙ። በሀገሩ ሁሉ በአሕዛብም መካከል እንደሚበተኑ አሕዛብም እንደ አጃ ሸክሽከው እንደሚአጓልቧቸው ትንቢትን ተናገረ ትንቢቱም በላያቸው ተፈጸመ።

ቅዱሱ ነቢይ ወገኖቹን አብዝቶ ይገስጻቸው ነበር፤ ስለኃጢአታቸውና ስለ ክፉ ሥራቸው፣ ስለ ዘለፋቸው እነርሱ እንደ ገደሉት ተነገረ። የትንቢቱም ዘመን ከጌታችን ሥጋዌ በፊት በስምንት መቶ ዓመት ነው ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን ለአባት እናቶቻችን የተገለጠች እመቤታችን ለእኛም በረድኤት ትገለጽልን:: ጣዕመ ስሟ በአንደበታችን: ጣዕመ ፍቅሯ በልባችን ይደርብን አሜን::

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ግንቦት#ዘወርኀ_ጳጉሜን_5 እና #ዲያቆን_ዮርዳኖስ_አበበ)
#ግንቦት_23

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ግንቦት ሃያ ሦስት በዚች ቀን #ሐዋርየ_ቅዱስ_ዮልዮስ አረፈ፣ ዳግመኛ በዚህች ቀን ኢትዮጵያዊው ጻድቅ እንደ ሐዋርያው ታዴዎስ ግመልን በመርፌ ቀዳዳ ያሾለኩት አባት #አቡነ_ታዴዎስ ዘጽላልሽ ልደታቸው ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ሐዋርያው_ቅዱስ_ዮልዮስ

የዚህም ቅዱስ ትውልዱ ከይሁዳ ነገድ ከእስራኤል ልጆች ከቤተ ገብርኤል ነው የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም መረጠው።

ከሰባ ሁለቱ አርድእትም የተቆጠረ ሆነ የመንፈስ ቅዱስንም ሀብት ከሐዋርያት ጋራ ተቀበለ ከእርሳቸውም ጋራ ታላቅ መከራ ደርሶበታል።

ከዚህ በኋላ ሐዋርያት በአንብሮተ እድ ኤጲስቆጶስነት ሹመው ከእንድራኒቆስ ጋራ በአገሮች ውስጥ እንዲሰብክ ላኩት።

እንድራኒቆስም በአለፈው ዕለት በአረፈ ጊዜ ይህ ቅዱስ ዮልዮስ ገንዞ ቀበረው ። ከዚህ በኋላ ከርሱ እንዳይለይ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ በማግሥቱ ዛሬ አረፈ።

እነሆ የከበረ ሐዋርያ ጳውሎስም እሊህን ሐዋርያት በሮሜ ክታቡ እንድራኒቆስንና ዮልዮስን ሰላም በሏቸው ሲል አስታውሷቸዋል።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አቡነ_ታዴዎስ_ዘጽላልሽ

#አቡነ_ታዴዎስ_ዘጽላልሽ፡- አባታቸው ካህኑ ሮማንዮስ የደብረ ሊባኖሱ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት አጎት ሲሆኑ እናታቸው ማርታ ይባላሉ፡፡ የትውልድ ቦታቸው ጽላልሽ ዞረሬ ነው፡፡ ሲወለዱ ዓምደ ብርሃን ተተክሎ የታየ ሲሆን እርሳቸውም በብርሃን ልብስ ተጠቅልለው ታይተዋል፡፡ ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ ለሊቀ ካህናቱ ለሕይወት ብነ በጽዮን ተሰጥተው ሃይማኖትን በሚገባ ተምረዋል፡፡

አቡነ ተክለ ሃይማኖት ዳሞት ተሻግረው ሞተሎሚን አስተምረው ካሳመኑት በኋላ አቡነ ታዴዎስን ወደ እርሳቸው እንዲመጡ ልከውባቸው ሄደው አቡነ ተክለ ሃይማኖትን እያገለገሉ ዘጠኝ ዓመት ተቀመጡ፡፡ ከዘጠኝ ዓመት በኋላ ግን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ወደ አባ በጸሎተ ሚካኤል ሲሄዱ አቡነ ታዴዎስም ወደ ጽላልሽ ተመልሰዋል፡፡ ሁለቱም ከ32ዓመት በኋላ ተመልሰው በጽላልሽ ተገናኘተው አቡነ ተክለ ሃይማኖት ለአቡነ ታዴዎስ ማዕረገ ምንኩስናን ሰጥተዋቸዋል፡፡

አቡነ ታዴዎስም በሥጋ ዕድሜ ታላቅ ቢሆኑም እንደታናሽ ብላቴና አቡነ ተክለ ሃይማኖትን እያገለገሉ በደብረ ሊባኖስ ተቀምጠዋል፡፡ ከዚህ በኋላ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አቡነ ታዴዎስን ወደ ጽጋጋ እንዲሄዱ ነገሯቸው ምክንያቱም አቡነ አኖሬዎስ በዚያ ሲያስተምሩ ከሃዲያን ደብድበው አስረዋቸው ነበር፡፡ እሳቸውም ታስረው ሳለ ወደ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ዘንድ የሚላካቸው ሲያስቡ ቁራ መጥቶ "እኔ እላክሃለሁ" ቢላቸው "ክፋትህ እንደ መልክህ ነው"ብለው እምቢ አሉት፡፡ ፀአዳ ኦፍ መጥቶ እኔ ከሀገራችሁ ኮዞረሬ የመጣሁ ነኝ "እኔ እላክሃለሁ" ብትላቸው "መጥተህ አድነኝ" ብለው በክንፏ ላይ ጽፈው ልከዋት እርሷም መልእክቱን ለአቡነ ተክለ ሃይማኖት አድሳ ነበር፡፡ ስለዚህም ነው አቡነ ታዴዎስን ሕዝቡን ከኃጢአት ግዞት አኖሬዎስን ከእስራት እንንዲያስፈቱ የላኳቸው፡፡

አቡነ ታዴዎስም ከደብረ ሊባኖስ ወደ ደብረ ማርያም በሠረገላ ነፋስ ተጭነው በአንድ ሰዓት ደርሰው መዩጥ ከተባለውና አኖርዮስን ካሰራቸው ንጉሥ ፊት ቢደርሱ ንጉሡ በግንጋጤ መልአክ የመጣበት መስሎት ሲፈራ ከሰው ወገን መሆናቸውን ነግረው ክርስትናን አስተማሩት፡፡ ጋኔን ከእሳት ጥሎት ሲሠቃይ የሚኖርና ሊሞት የደረሰ ልጁን ቢፈውሱለት በትምህርታቸውና በተአምራታቸው አምኖ ሕዝቡ ክርስትናን እንዲቀበል በአዋጅ አስነገረ፡፡ አፍጃል የሚባለው ባለጸጋ ወደ አቡነ ታዴዎስ ቀርቦ ሲማር "ባለጸጋ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ይልቅ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢሾልክ ይቀላል" ማቴ 19፥24፣ ማር10፥25፣ ሉቃ18፥25) የሚለውን የወንጌል ቃል ሲሰማ ለአእምሮው ረቆበት "እስቲ አድርገህ አሳየኝ?" አላቸው፡፡ አቡነ ታዴዎስም እናቲቱን ግመል ከነጇ ቀጥሎም 28ግመሎችን በየተራ በመርፌ ቀዳዳ እያሾለኩ አሳይተውታል፡፡ ሕዝቡ ሁሉ በእጅጉ ሲገረምና "በአምላከ ታዴዎስ ስም አምናለሁ" ሲል የባለጸጋው ልጅ ሙሳ ግን "በምትሀት አሳይቶን ነው እንጂ የእውነት አይደለም" በማለት አባቱንም እንዳያምን ይናገር ጀመር፡፡ ይህንንም ሲናገር በመጀመሪያ ያለፈችው እናቲቱ ግመል እረግጣ ገደለችው፡፡

አቡነ ታዴዎስም ንጉሡን፣ አባቱን አፍጃልንና ሕዝቡን የሞተ እንደሚነሣ ሲያስምሯቸው "የሞተ ይነሣልን? እስኪ ይህ የሞተው ልጅ ይነሳና ሁሉም አይቶ ይመን" አሏቸው፡፡ እሳቸውም "ዛሬ ተቀብሮ ይዋልና ነገ በሦስተኛው ቀን ይነሣል" ብለዋቸው ተቀብሮ ዋለ፡፡ በማግሥቱም አፍጃልን ጠርተው "አልዓዛርን ከሞት ባስነሣው በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ልጄ ሆይ ና ውጣ" ብለህ ከልጅህ መቃብር ላይ አኑረው" ብለው ዘንጋቸውን ሰጡት፡፡ ሄዶም እንዳሉት ቢያደርግ ልጁ አፈፍ ብሎ ተነሥቷል፡፡ ይህንን ያዩ የአገሩ ሰዎች ሁሉም አምነው ተጠምቀዋል፡፡ እሳቸውም 12አብያተ ክርስቲያናትን አሳንጸው ሞቶ የተነሳውን ሙሳን ሙሴ ብለው ሰይመው አስተምረው ሊቀ ካህናት አድርገው ሾመውት አቡነ አኖሬዮስን ይዘው ወደ ጽላልሽ ዞረሬ ተመልሰዋል፡፡

አቡነ ተክለ ሃይማኖት ካረፉ በኋላ አባ ያዕቆብ የተባሉ ጳጳስ ከግብፅ መጡ፡፡ የአቡነ ታዴዎስን ዜና ሲሰሙ ተደስተው ከአቡነ ፊሊጶስ ጋር ሆነው አስጠርተዋቸው "የአባታችሁን ዜና ገድል ንገሩኝ" አላቸው፡፡ አቡነ ታዴዎስም ጨዋታ በአስተርጓሚ አይሰምርም" ብለው ወደ ጌታችን ቢጸልዩ የጳጳሱ ቋንቋ ለአቡነ ታዴዎስ፣ የአቡነ ታዴዎስም ቋንቋ ለጳጳሱ ተገልጦላቸው የመሸ የነጋ ሳይመስላቸው40 ጾምን ሲጨዋወቱ ቆይተዋል፡፡ ከዚህ በኋላ ጳጳሱ ከንጉሡ ተማክረው "ሊቀ ካህናት ዘጽላልሽ" ብለው ሾመዋቸዋል፡፡

በነግህና በሰርክ ቤተ ክርስቲያንን እያገለገሉ፣ ቀን ወንጌልን እየሰበኩ፣ ሌሊት ከባሕር ገብተው ሲጸልዩ እያደሩ በታላቅ ተጋድሎ እየኖሩ ሳለ ከ10ዓመት በኋላ ሰይጣን በንጉሡ በዓምደ ጽዮን ፍቅረ ዝሙት አሳድሮበት በክፉዎችም ምክር አታሎት የአባቱን ቅምጥ አገባ አቡነ ታዴዎስም ይህን ሲሰሙ እንደ ነቢዩ ኤልያስና እንደ መጥምቁ ዮሐንስ በቀጥታ ሄደው ንጉሡን ገሥጸው አወገዙት፡፡ ገሥጸውና አውግዘው አቡነ ማትያስን አስከትለው ሲመለሱ ቅምጧ የንጉሡ ሚስት በፈረስ ተከትላ ደርሳ የኋሊት አሳስራ ዛሬ "ማርያም ገዳም" ከሚባለው ቦታ ፊት ለፊት ካለው ትልቅ ገደል ውስጥ ሁለቱንም ጣለቻቸውና ጥር29 ቀን በሰማዕትነት ዐረፉ፡፡

በሰማዕትነት ዐርፈው ደማቸው ከፈሰሰበት ከገደሉ ስር በፈለቀው ጸበላቸው "ታዴዎስ ወማትያስ" እያለ ሦስት ጊዜ ብቅ ጥልቅ እያለ የተጠመቀ ሰ እንደ 40 ቀን ሕፃን እንደሚሆን ጌታችን ቃል ኪዳን ገብቶላቷቸዋል፡፡ ይህ ሰማዕትነት በተቀበሉበት አካባቢ የተሠራው ቤተ ክርስቲያናቸው በጠላት ወረራ ጊዜ ፈርሶ ቦታው ጠፍ ሆኖ የኖረ ቢሆንም የአካባቢው ሕዝብ ቦታውን ከልሎ በክብር ሲጠብቀው ስለኖረ ፈቃደ እግዚአብሔር ሆኖ የአቡነ ታዴዎስ ታቦታቸው በ2005ዓ.ም ከኢቲሣ ተክለ ሃይማኖት ገዳም ወጥቶ ጻድቁ ሰማዕትነት በተቀበሉበት አካባቢ በተሠራው መቃኞ ቤተ ክርስቲያናቸው በታላቅ ክብር ገብቷል፡፡ ቤተ ክርስቲያኑም ከኢቲሣ በእግር የአንድ ሰዓት ተኩል ርቀት ላይ ይገኛል። ምንጭ፦ መዝገበ ቅዱሳንና የጣና ሐይቅ ደብረ ማርያም ገዳም አጭር ታሪክ ከምትላው መጸሐፍ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ዕለት ሰማዕታት የሆኑ የአንስያ ከሰባ ሁለቱ አርድዕት የአንዱ የአፍሮዲጡ የዮልያና የቀሲስ ታኦድራጦስ የጳጳስ ታድሮስ የዮልያኖስን የእናቱ የእስክንድርያ የሆኑ ደግሞ የኤስድሮስ የሚስቱና የሁለት ወር ልጅዋ እኔ ከእናቴ ጋራ ክርስቲያን ነኝ ብሎ የተናገረና ዲዮቅልጥያኖስ የገደላቸው ለእነርሱም ማኅበር መታሰቢያቸው ሆነ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በአባቶቻችን ሐዋርያት ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

#ግንቦት_23 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ዮልዮስ (ዮልያን) ሐዋርያ (ከ72ቱ አርድእት)
2.ቅዱስ አፍሮዲጡ ሐዋርያ (ከ72ቱ አርድእት)
3.ቅዱሱ ሕጻን ሰማዕት (በዘመነ ሰማዕታት ገና የ2 ወር ሕጻን ቢሆንም ጌታችን አፉን ከፍቶለት ክርስቲያን ነኝ በማለቱ ከእናቱ ጋር ተሠይፏል)
4.አባ አንስያ ሰማዕት
5.ቅዱስ ታኦድራጦስ

#ወርኀዊ_በዓላት
1.ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት
2.ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማዕታት
3.ቅዱስ ሰሎሞን ንጉሠ እስራኤል
4.አባ ጢሞቴዎስ ገዳማዊ
5.አባ ሳሙኤል
6.አባ ስምዖን
7.አባ ገብርኤል

=>+"+ ስለ እናንተ ብዙ ለደከመች ለማርያ ሰላምታ አቅርቡልኝ:: በሐዋርያት መካከል ስመ ጥሩዎች ለሆኑ: ደግሞም ክርስቶስን በማመን ለቀደሙኝ: አብረውኝም ለታሰሩ ለዘመዶቼ ለአንድራኒቆንና ለዮልያን (እንድራኒቆስና ዮልዮስ) ሰላምታ አቅርቡልኝ:: +"+ (ሮሜ. 16:6)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ግንቦት_23)
2024/06/26 04:13:16
Back to Top
HTML Embed Code: