Telegram Web Link
Audio
"" እንደ ጨረቃ የተዋበች . . . ይህች ማን ማን ናት? "" (መሓ. ፮:፲)

"የእመቤታችን ልደት (ክፍል ፩)

(ግንቦት 1 - 2016)

መምህር ዲ/ዮርዳኖስ አበበ

💦https://www.youtube.com/@ZikereKedusan

💦https://www.tg-me.com/zikirekdusn
††† እንኳን ለእናታችን ቅድስት እሌኒ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† እሌኒ ንግሥት †††

††† ቅድስት እሌኒ የታላቁ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ እናቱና እግዚአብሔር ለበጐ አገልግሎት የጠራት ቡርክት ሴት (ንግሥት) ናት::
ጥንተ ነገሩስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-
የቅድስቲቱ ሃገረ ሙላዷ ሮሃ (ሶርያ) አካባቢ ነው:: ነገዷ ከእሥራኤል ዝርዋን እንደሆነም ይነገራል:: ጣልያኖች "Helena" : በእንግሊዝኛው "Helen" ይሏታል:: እኛ ደግሞ "እሌኒ" እንላታለን:: ትርጓሜው "ጥሩ ምንጭ" : አንድም "ውብና ደግ ሴት" ማለት ነው::

ቅድስት እሌኒ በመልካም ክርስትና አድጋ እንደ ቤተ ክርስቲያን መተርጉማን ተርቢኖስ የሚባል ነጋዴ አግብታ ነበር:: ወቅቱም ዘመነ ሰማዕታት ነበር:: በማይሆን ነገር ጠርጥሮ ባሕር ላይ ጥሏት ንጉሥ ቁንስጣ አግኝቷታል:: እርሱም የበራንጥያ (የኋላዋ ቁስጥንጥንያ) ንጉሥ ነበር::

ቅድስት እሌኒ ከቁንስጣ የተባረከ ልጅን ወለደች:: ቆስጠንጢኖስ አለችው:: በልቡናው ፍቅርን : ርሕራሄን : መልካምነትን እየዘራች አሳደገችው:: ቅዱሱ አባቱ በሞተ ጊዜ ተተክቶ ነገሠ::

ቅድስት እሌኒንም ንግሥት አደረጋት:: ያንን የአርባ ዓመት ግፍ በአዋጅ አስቀርቶ ለክርስቲያኖች ነፃነትን : ክብርን በይፋ ሰጠ:: አንድ : ሁለት ብለን የማንቆጥረውን ውለታ ለምዕመናን ዋለ:: ከነዚህ መልካም ምግባራቱ ጀርባ ታዲያ ቅድስት እናቱ ነበረች::

ቅድስት እሌኒ ጾምን : ጸሎትን ከማዘውተሯ ባሻገር አጽመ ሰማዕታትን ትሰበስብ : አብያተ ክርስቲያንን ታሳንጽ : ለነዳያንም ትራራ ነበር:: በኢየሩሳሌምና አካባቢው ብቻ ከሰማንያ በላይ አብያተ መቃድስ አሳንጻለች:: እነዚህንም በወርቅና በእንቁ ለብጣቸዋለች::

በዘመኗ መጨረሻም የጌታችንን ቅዱስ ዕፀ መስቀል ከተቀበረበት አውጥታ ለዓለም በረከትን አስገኝታለች::

እናታችን ቅድስት እሌኒ እንዲህ በቅድስና ተመላልሳ በሰማንያ ዓመቷ በ330ዎቹ አካባቢ ዐርፋለች:: ቤተ ክርስቲያናችንም ስለ ቅድስናዋና ውለታዋ በዓል ሠርታ : ታቦት ቀርፃ ስታከብራት ትኖራለች::

††† ከቅድስት እናታችን ምልጃና በረከት አምላካችን ያድለን::

††† ግንቦት 9 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅድስት እሌኒ ንግሥት
2.ቅዱስ ስልዋኖስ

††† ወርኀዊ በዓላት
1.አባ በርሱማ ሶርያዊ (ለሶርያ መነኮሳት ሁሉ አባት)
2.አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ (ኢትዮጵያዊ)
3.ሦስት መቶ አሥራ ስምንቱ ቅዱሳን ሊቃውንት (ርቱዐነ ሃይማኖት ዘኒቅያ)
4.የብሔረ ብፁዐን ጻድቃን
5.አባ መልከ ጼዴቅ ዘሚዳ (ኢትዮጵያዊ)
6.ቅዱስ ዞሲማስ ጻድቅ (ዓለመ ብፁዐንን ያየ አባት)

††† "ነገር ግን ለበጐ ነገር ጥበበኞች : ለክፉትም የዋሆች እንድትሆኑ እወዳለሁ:: የሰላምም አምላክ ሰይጣንን ከእግራችሁ በታች ፈጥኖ ይቀጠቅጠዋል:: የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን::" †††
(ሮሜ. ፲፮፥፲፱)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††

https://www.tg-me.com/zikirekdusn
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ
አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

❖ እንኳን አደረሳችሁ ❖

❖ ግንቦት 12 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ °+

=>ለቤተ ክርስቲያን የብርሃን ምሰሶ ስለሆነላት ስለ ታላቁ
ሐዋርያዊ ሊቅ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ምን እላለሁ?
ምንስ
እናገራለሁ? እንደ እኔ ያለ ኃጥእ: ለባሴ ሥጋና ገባሬ ንስሃ
ስለሱ ሊናገር አይቻለውምና:: አባቶቻችን እንደ ነገሩን ስለ
አፈ ወርቅ ለመናገር አፈ ወርቅ መሆን ያስፈልጋል:: ግን
እስኪ በቅዱሱ አባት ምልጃ ጥቂት ልሞክር::

<< ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ማን ነው? >>

+ነገዱ ከሶርያ: የተወለደው በ347 ዓ/ም በእስክንድርያ
ሲሆን አባቱ አስፋኒዶስ እናቱ ደግሞ አትናስያ ይባላሉ::
እነርሱ
ደግ ቢሆኑ ይህንን እንቁ ልጅ እግዚአብሔር ሰጣቸው::
ዮሐንስ ለክርስቲያን እንደሚገባ በትምሕርትና በጥበብ
አደገ:: ገና
በሕጻንነቱ ወደ ግሪክ ሔዶ የዘመኑን ሳይንስ (ፍልስፍና)
ከአፉ እስከ ገደፉ ተምሮ ተመልሷል::

+ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅን ለየት ከሚያደርጉት ነገሮችም
አንዱ ይሔው ነው:: በዘመናዊም ሆነ በመንፈሳዊ
ትምሕርት ይህ
ቀረህ የማይሉት ሊቅ የሆነው ገና በ15 ዓመቱ ነበር:: በ2
ወገን የተሳለ ሰይፍ በመሆኑ ስንኳን በሕይወተ ሥጋ እያለ
ዛሬም ለንፉቃን ትልቅ የራስ ምታት ነው::

+ቅዱሱ ገና በ16 ዓመቱ ሃብት: ንብረት: ውበት: ክብርና
እውቀት የሞላለት ቢሆንም ያለውን ሁሉ ለነዳያን ሰጥቶ
መጻሕፍትን ብቻ ሰብስቦ ከባልንጀራው ቅዱስ ባስልዮስ
ጋር በርሃ ገባ:: ሰውነቱን በጾምና በጸሎት እየቀጣ በበርሃ
ሲኖር
ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስና ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ
ዼጥሮስ ወደ እርሱ መጡ::
ሊቀ ሐዋርያት የመንግስተ ሰማያትን መክፈቻ ስልጣን
ቅዱስ ዮሐንስ ደግሞ ወንጌሉን ሰጥተው ተሰወሩት::

+ከዚህች እለት በኋላ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ባሕረ
ምስጢራት ሆነ:: ብሉይ ከሐዲስ: ከኦሪት ዘፍጥረት እስከ
ራዕየ
ዮሐንስ ድረስ በአንድምታ ትርጉዋሜ ተነተናቸው:: በተለይ
ሐዲስ ኪዳንን እየመላለሰ አመሰጠረው:: ቅዱስ ሕሊናው
ሳይታክት:
ንጹሕ እጆቹ ሳይዝሉ የጻፋቸው ድርሳናት: መልዕክታትና
ትርጉዋሜያት ቢቆጠሩ አሥር ሺህ ሞሉ:: በእውነት ለዚህ
አንክሮ
ይገባል! የሚገርመው ይህን ሁሉ ሲሰራ እድሜው ገና
ለጋ: ማዕርጉም ዲቁና ነበር::

+ከዚህ በኋላ በእግዚአብሔር ትእዛዝ ቅስና ተሹሞ
በስብከተ ወንጌል ብዙ ቦታዎችን አዳረሰ:: በቅድስናው
ወደውታልና
የቁስጥንጥንያ ፓትርያርክ አድርገው ሾሙት:: አፈ ወርቅ
ሲናገርም ሆነ ሲያስተምር እንኳን የሚያወራ ኮሽ የሚል
የለም::
ከጣዕመ ትምሕርቱ የተነሳ ሕዝቡ በተደሞ ይሰሙት ነበር::

+ሲያስተምር ምድራዊው ሰው ይቅርና ልዑላኑ መላእክት
ተሰብስበው ያደንቁት ነበር:: አንዴም እመቤታችን በሕዝብ
መካከል "
አፈ-ወርቅ" ብላ ጠርታዋለች:: ለዛም ነው አፈ-ወርቅ
የሚባለው:: ቅዱሱ በሥልጣነ ቃሉ መልዐከ ሞትን ገስፆ
10 ዓመት
አቁሞታል::

+ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ለሰው ፊት አያደላም:: በርሱ
ዘንድ ንጉሥና ደሃ ነዳይ እኩል ነው:: ለሞት ያበቃውም
ይሔው
ነበር:: ምክንያቱም የወቅቱ ንግስት አውዶክስያ ያንዲት
ድሃ መበለትን መሬት ቀምታ አልመልስም በማለቷ መክሮ
አወገዛት::
እርሷ ግን ከኃጥአንና መናፍቃን ጋር መክራ 2 ጊዜ
አጋዘችው::

+በተሰደደበት ፍሬ አፍርቶ: አስተምሮና አሳምኖ በ407 ዓ/
ም አርፏል:: ቤተ ክርስቲያንና ምእመናን ሳይጠግቡት
እንደናፈቁት በ60 ዓመቱ አጡት:: በወቅቱ ታላቅ ሐዘንና
ለቅሶ ተደረገ::

+አንድ ቀን የዘመኑ ደግ ንጉሥ አርቃድዮስ ግብር አገባ
(ግብዣ አዘጋጀ):: በዚያች ሌሊት ደግሞ ቅዱሱ ሊቅ
ታጥቆ ሲጸልይ
ሳለ: አባ ማርዳሪ የሚባል ጻድቅ ደግሞ ከሰማይ 12ቱ
ሊቃነ መላእክት (እነ ቅዱስ ሚካኤል) በግርማ ሲወርዱ
ተመለከተ::

+ደንግጦ "ወዴት ናችሁ ጌቶቼ" ቢላቸው "ቁስጥንጥንያ:
ወደ ዮሐንስ አፈ ወርቅ እንሔዳለን:: እርሱ እመቤታችንን
እንደሚያመሰግናት ጌታ ነግሮናልና" አሉት:: "እባካችሁ
እኔም የአፈ ወርቅ ምስጋናው እንገለጥልኝ መርቁኝ"
አላቸው::
ሊቃነ መላእክቱም መርቀውት ጐዳናቸውን ቀጠሉ::

+በማግስቱ በቤተ መንግስት ውስጥ ሊቃውንቱ:
መሳፍንቱ: ዻዻሳቱ: ሕዝቡ ሁሉ ተሰብስበው ከድግሱ
በሉ:: ቅዱስ ዮሐንስ አፈ
ወርቅ ግን በመንበሩ ተቀምጦ ነበር እንጂ አልበላም::
ድግሱ ሲጠናቀቅ ንጉሡ አርቃድዮስ ሊቁን "ጥያቄ አለኝ"
ብሎ በጉባኤ
መካከል ጠየቀው::

+"ምነው ወንጌላዊ ማቴዎስ 'ኢያዕመራ ዮሴፍ እስከ አመ
ወለደት ወለደ ዘበኩራ-የበኩር ልጇን እስክትወልድ ድረስ
አላወቃትም'
ማለቱ (ማቴ. 1:25) ስለ ምን ነው?" ቢለው ቅዱሱ
ተነስቶ: በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ ይተረጉምለት ጀመር::

+"ድንግል ማርያም ንጹሕ ብርሌን ትመስላለች:: ብርሌ
የተለያየ ቀለም ያለው ፈሳሽ ቢያስገቡበት ቀለሙ አብሮ
ይቀያየራል::
እመቤታችንም ጌታን ጸንሳለችና ሕብረ መለኮቱ ሲለዋወጥ
መልኳ አብሮ ሲለዋወጥ እያየ ዮሴፍ ይደነግጥ ነበር::

+'እርሷ ማን ናት? በማሕጸኗ ያለውስ ማን ነው' እያለ
ይጨነቅ ነበር:: ጌታን ከወለደች በኋላ ግን አንድ ሕብረ
መልክ
ሆናለችና:: አስቀድሞ ማን እንደ ነበረች አላወቀም::

+አሁን ግን እርሷም ወላዲተ አምላክ: ልጇም አምላክ
ዘበአማን መሆኗን አወቀ ማለት ነው" እያለ ሲተረጉም
ሰምተው ሁሉም
ሲያደንቁ: በዚያ የነበረች ስዕለ አድኅኖ "አፈ ወርቅ! ልሳነ
ወርቅ! አፈ በረከት!" ስትል ተናገረች::

+ያን ጊዜ አርቃድዮስ የወርቅ ልሳን በሊቁና በስዕሏ ላይ
አደረገ:: አፈ ወርቅ ግን ባጭር ታጥቆ "እሰግድ ለኪ!
እሰግድ
ለኪ! ወእዌድሰኪ . . ." ብሎ ዛሬ በተአምረ ማርያም
የምናውቀውን ምስጋና ሰተት አድርጐ አደረሰላት:: ይህንን
ምስጋናም
ሊቃነ መላእክቱ ሰምተው እያደነቁ ወደ ሰማይ
ወጥተዋል::

+ሊቁ ባረፈ በ35 ዓመቱ: በትንሹ ቴዎዶስዮስ ዘመን:
ሥጋው ፈልሷል:: ወደ ቁስጥንጥንያ ሲደርስም ከናፍቆት
የተነሳ ታላቅ
ዝማሬና እንባ ተደርጓል:: አፈ ወርቅም ቀና ብሎ ሕዝቡን
ባርኳል::

ቅዱሱ ሲጠራ እንዲሕ ነው:-
*ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ
*አፈ በረከት
*አፈ መዐር (ማር)
*አፈ ሶከር (ስኳር)
*አፈ አፈው (ሽቱ)
*ልሳነ ወርቅ
*የዓለም ሁሉ መምሕር
*ርዕሰ ሊቃውንት
*ዓምደ ብርሃን (የብርሃን ምሰሶ)
*ሐዲስ ዳንኤል
*ሊቀ ዻዻሳት ዘበርትዕ (እውነተኛው)
*መምሕር ወመገስጽ ዘኢያደሉ ለገጽ
*ጥዑመ ቃል - - -

+እግዚአብሔር ከቅዱሱ በረከት አብዝቶ: አብዝቶ: አብዝቶ
ይክፈለን::

+ዳግመኛ በዚህ ቀን ታላቁ ጻድቅ አቡነ ተክለ ሃይማኖት
ሥጋቸው ፈልሷል:: ይሕ የተደረገው ጻድቁ ከረፉ ከ56
ዓመታት
በኋላ ነው:: በዕለቱም ድንቅ ድንቅ ተአምራት
ተፈጽመዋል::

+እናታችን ርሕርሕቷ ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ደግሞ
በዚሕ ቀን ስሟን ለጠራና መታሠቢያዋን ላደረገ የምሕረት
ቃል ኪዳን
ተቀብላለች::

❖ቸር አምላካቸው ከሁለቱም ብሩሃን ቅዱሳኑ ክብር
ያድለን::
❖ግንቦት 12 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ (የዓለም ሁሉ መምሕር)
2አቡነ ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ጻድቅ (ፍልሠታቸው)
3.ቅድስት እናታችን ክርስቶስ ሠምራ (ቃል ኪዳን
የተቀበለችበት)
4.አባ አብርሃም ዘደብረ ሊባኖስ
5.ቅዱስ ዕንባቆም ነቢይ
6.እስክንድር ንጉሠ ኢትዮዽያ
7.ቅዱስ መስቀል (የተአምር በዓሉ)
8.አባታችን ያሬድ (የማቱሳላ አባት)
9.ቅዱስ ሚናስ ዲያቆን❖ወርኃዊ በዓላት
1፡ ቅዱስ ሚካኤል ሊቀ መላእክት2፡ ቅዱስ ድሜጥሮስ
3፡ ቅዱስ ማቴዎስ ሐዋርያ
4፡ ቅዱስ ቴዎድሮስ በናድሌዎስ
5፡ አባ ሳሙኤል ዘዋልድባ
6፡ ቅዱስ ላሊበላ
7፡ ቅድስት መስቀል ክብራ

++"+ እናንተ የምድር ጨው ናችሁ . . . እናንተ የዓለም
ብርሃን ናችሁ:: በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሠወር
አይቻላትም:: መብራትንም አብርተው በዕንቅብ በታች
አይደለም እንጂ በመቅረዙ ላይ ያናሩታል:: በቤት ላሉት
ሁሉም ያበራል::
መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን
አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት
ይብራ:: +"+ (ማቴ.
5:13-16)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>

https://www.tg-me.com/zikirekdusn
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

❖ ግንቦት 13 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

+"+ ቅዱስ አርሳኒ +"+

=>ቅድስት ሃይማኖት እዚህ ዛሬ እኛ ጋር የደረሰችው
በበርካታ ሰማዕታትና ጻድቃን ደም ነው:: ቅድስት ቤተ
ክርስቲያን
ግድግዳዎቿ እንጨትና ድንጋይ እንዳይመስሏችሁ:: አጽመ
ቅዱሳን ነው እንጂ::

+ቅዱሳን ልዑለ ባሕርይ ክርስቶስን እንደ እኔ እና እንደ
ዘመኑ ትውልድ በከንፈራቸው የሚሸነግሉ አልነበሩም::
እነርሱ
በፍጹም ልባቸው ስለ ፍቅሩ ሕይወታቸውን አሳልፈው ሰጡ
እንጂ:: በቅድስናቸው ከተመሰከረላቸው ቀደምት ቅዱሳን
አንዱ ደግም
ቅዱስ አርሳንዮስ ነው::

+ቅዱሱ የተወለደው በ345 ዓ/ም ሮም ውስጥ ነው::
በወጣትነቱ ይሕ ቀረህ የማይሉት የጥበብና የፍልስፍና
ሰው ነበር::
በተለይ በትልቁ የሮም ቄሳር ቴዎዶስዮስ ዘመን በቤተ
መንግስት አካባቢ የተከበረና የንጉሡ ልጆች መምሕር
ነበር::
አኖሬዎስና አርቃዴዎስን ቀጥቶ ያሳደጋቸውም እርሱ ነበር::

+በድንግልና እስከ 40 ዓመቱ ድረስ ሮም ውስጥ ቆየ::
ከዚህ በኋላ ግን ስለ ሰማያዊ ነገሮች ሲያስብ መልዐኩ
በሕልም ወደ
ግብፅ ሒድ አለው:: በመጀመሪያ ወደ እስክንድርያ ቀጥሎ
ወደ ገዳመ አስቄጥስ ሒዶ መነኮሰ:: በቆይታ ግን
ብሕትውና ምርጫው
ሆነ::

+ቅዱስ አርሳኒ በእነዚሕ ነገሮቹ ይታወቃል:-

1.በምንም ምክንያት ከማንም ጋር አያወራም:: (ለ60
ዓመታት በአርምሞ ኑሯል)

2.በቤተ መቅደሱ ግድግዳ ተጠግቶ እንባውን ሲያፈስ
የርሱን አካል አርሶ በመሬት ላይ ሲፈስ ይታይ ነበር::
ከእንባው ብዛት
ቅንድቦቹ ተላልጠው አልቀው ነበር::

3.በርካታ ድርሳናትን ደርሷል:: ብዙዎቹ ዛሬም ግብጽ
ውስጥ አሉ::

4.ሸንጎበቱን ወደ ደረቱ አዘንብሎ ስለሚቆም ማንንም ቀና
ብሎ አያይም ነበር::

5.ለጸሎት አመሻሽ 11:00 አካባቢ ላይ ይቆምና ጸሎቱን
የሚጨርስ ፀሐይ ግንባሩን ስትመታው ነው::

6.ሁል ጊዜ ራሱን "አንተ ሰነፍ (ሐካይ) እያለ ይገስጽ
ነበር::

7.በገዳማውያን ታሪክ የርሱን ያሕል በቁመቱ ረዥም
አልተገኘም ይባላል:: የራሱ ጸጉር በጀርባው የወረደ ሲሆን
ጽሕሙን
በስዕሉ ላይ እንደምታዩት ነጭና እስከ መታጠቂያው
የወረደ ነበር::

+እነዚህ ግን በጣም ጥቂቶቹ ናቸው::

+ቅዱስ አርሳንዮስ አካሉ በተጋድሎ ደቆ: ለ60 ዓመታት
በግሩም መንፈሳዊነት ኑሮ በ100 ዓመቱ በዚሕች ዕለት
ዐርፏል::

❖አምላካችን እግዚአብሔር ከታላቁ የቅድስና ሰው አርሳኒ
በረከት አይለየን::

=>ግንቦት 13 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ አርሳንዮስ - አርሳኒ (ጠቢብ ገዳማዊ)

=>ወርኀዊ በዓላት
1.እግዚአብሔር አብ
2.ቅዱስ ሩፋኤል ሊቀ መላዕክት
3."99ኙ" ነገደ መላዕክት
4.ቅዱስ አስከናፍር
5."13ቱ" ግኁሳን አባቶች
6.አቡነ ዘርዐ ቡሩክ

=>+"+ የፍጥረት ወገን ሁሉ በሰው ይገራል:: ደግሞ
ተገርቷል:: ነገር ግን አንደበትን ሊገራ ማንም ሰው
አይችልም:: የሚገድል መርዝ የሞላበት ወላዋይ ክፋት
ነው:: በእርሱ ጌታንና አብን እንባርካለን:: በእርሱም እንደ
እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠሩትን ሰዎች እንረግማለን::
ከአንድ አፍ በረከትና መርገም ይወጣሉ:: ወንድሞቼ ሆይ
ይህ እንዲህ ሊሆን አይገባም:: +"+ (ያዕ. 3:7-11)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>

https://www.tg-me.com/zikirekdusn
የቅዱስ መስቀል ዓመታዊ የተአምር በዓል ነው።
በመስቀሉ አጥርነት ይጠብቀን።
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

❖ ግንቦት 1 5 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

+"+ ቅዱስ ናትናኤል +"+

+በቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት ከቅዱሳን ሐዋርያት
መካከል ዘግይቶ ሰማዕትነትን የተቀበለ ይህ ቅዱስ
ሐዋርያ ነው::

+ቅዱሱ ሐዋርያ የተወለደው ከእሥራኤላውያን ወላጆቹ
ጌታችን በተወለደበት ዘመን አካባቢ ነው:: ይህ በምን
ይታወቃል ቢሉ
እርሱ ሕጻን እያለ ሔሮድስ 144,000 ሕጻናትን ሲፈጅ
እርሱ ግን በእግዚአብሔር ጥበብ ተርፏል:: እናቱ
በቅርጫት ውስጥ
አድርጋ የበለስ ዛፍ ላይ አስቀምጣው ተደብቃ ታጠባው
ነበር::

+ለሐዋርያው ወላጆቹ ያወጡለት ስም ስምዖን ሲሆን
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ ናትናኤል ብሎታል::
በባልንጀሮቹ
ሐዋርያት ደግሞ የቃናው ስምዖን (ገሊላ ቃና አካባቢ
ስላደገ): አንዳንዴም ቀናተኛው ስምዖን ይሉት ነበር::
ምሑረ ኦሪት
ነበርና ዘወትር ለሕግ ይቀና ነበር::

+በገሊላ ቃና ሰርግ የደገሰው ዶኪማስ የቅዱስ ናትናኤል
የአጎት ልጅ ነው:: ጌታና ደቀ መዛሙርቱን ዶኪማስ
የጠራበት አንዱ
ምክንያትም ይሔው ነው::

+ቅዱስ ናትናኤል ኦሪትን ከገማልያል ተምሮ: ከበለስ ቁጭ
ብሎ ይተክዝ ነበር:: "መሲሕ ምነው ቀረህ" እያለም
ይተክዝ
ነበር:: ማዕምረ ኅቡዓት አምላካችን ክርስቶስ ይህንን
አውቆ በፊልዾስ አማካኝነት ጠርቶታል::

+ናትናኤል ለጊዜው ተከራክሮ ነበር:: በኋላ ግን የጌታችንን
ማንነት በደቂቃዎች ተረድቶ አምኗል:: ጌታችንም "ክዳት
ሽንገላ በልቡ ውስጥ የሌለበት ንጹሕ እሥራኤላዊ" ሲል
አመስግኖታል::

+ሐዋርያው ቅዱስ ናትናኤል ከጌታችን እግር ሥር
ምስጢረ መንግስተ ሰማያትን ተምሮ: በጸጋ መንፈስ
ቅዱስም ሰክሮ ብዙ
አሕዛብን ከጨለማ (ጣኦት አምልኮ) ወደ ብርሃን (አሚነ
ክርስቶስ) መልሷል:: እጅግ ብዙ መከራንም ተቀብሏል::

+የጌታችን ወንድም የተባለ ቅዱስ ያዕቆብ በአይሁድ
ከተገደለ በኋላም ቅዱስ ናትናኤል የኢየሩሳሌም 2ኛ
ኤዺስ ቆዾስ ሆኖ
አገልግሏል:: ከአይሁድም ዘንድ ብዙ መከራ ደርሶበታል::
በመጨረሻም በዚህች ዕለት በሰማዕትነት አልፏል::
በገድለ
ሐዋርያት ላይ እንደተጠቀሰው ቅዱሱ ሰማዕት የሆነው
በ150 ዓመቱ ነው:: ያ ማለት ደግሞ ከሐዋርያት አባቶች
በመጨረሻ
ያረፈው እርሱ ነው ያሰኛል::

❖እግዚአብሔር በቅዱስ ናትናኤል ምልጃ ሃገራችንን
ከጥፋት: ሕዝቦቿንም ከመቅሰፍት ይሰውርልን::
ከበረከቱም አይለየን::

=>ግንቦት 15 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ናትናኤል ሐዋርያ (ቀናተኛው ስምዖን)
2.ቅዱስ ሚናስ ባሕታዊ
3.ቅዱስ ቀርጢኖስ ሰማዕት
4."400" ቅዱሳን ሰማዕታት

=>ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ቂርቆስና እናቱ ኢየሉጣ
2.ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ (አፈ በረከት)
3.ቅዱስ ሚናስ ግብፃዊ
4.ቅድስት እንባ መሪና
5.ቅድስት ክርስጢና

=>+"+ ጌታ ኢየሱስ ናትናኤልን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ ስለ እርሱ 'ተንኰል የሌለበት በእውነት የእሥራኤል ሰው እነሆ' አለ:: ናትናኤልም 'ከወዴት ታውቀኛለህ?' አለው:: ጌታ ኢየሱስም መልሶ 'ፊልዾስ ሳይጠራህ ከበለስ በታች ሳለህ አየሁህ' አለው:: ናትናኤልም መልሶ 'መምሕር ሆይ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ:: አንተ የእስራኤል ንጉሥ ነህ' አለው:: +"+ (ዮሐ. 1:48-51)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>

https://www.tg-me.com/zikirekdusn
2024/10/01 15:46:05
Back to Top
HTML Embed Code: