Telegram Web Link
† እንኳን ለታላቁ ነቢይና ጻድቅ ቅዱስ ዳንኤል ዓመታዊ በዓለ ዕረፍት በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱስ ዳንኤል †††

††† ነቢይ ማለት በቁሙ ኃላፍያትን (አልፎ የተሠወረውን ምሥጢር): መጻዕያትን (ለወደ ፊት የሚሆነውን) የሚያውቅ ሰው ማለት ነው:: ሃብተ ትንቢት የእግዚአብሔር የባሕርይ ገንዘቡ ሲሆን እርሱ ለወደደው በጸጋ ይሰጠዋል:: እነዚህም ከጌታ ሃብተ ትንቢት የተሰጣቸው አባቶችና እናቶች "ቅዱሳን ነቢያት" በመባል ይታወቃሉ::

ዘመነ ነቢያት ተብሎ የሚታወቀው ብሉይ ኪዳን ቢሆንም እስከ ምጽዓት ድረስ ጸጋውን እግዚአብሔር ለፈቀደላቸው አይነሳቸውም:: በሐዋርያት መካከልም ቅዱስ አጋቦስን የመሰሉ ነቢያት ነበሩ:: (ሐዋ. 11:27) ቅዱሳን ነቢያት ከእግዚአብሔር እየተላኩ ሰውን ከፈጣሪው እንዲታረቅ ይመክራሉ: ይገስጻሉ::

ከበጐ ሃይማኖታቸውና ንጽሕናቸው የተነሳም እግዚአብሔርን በተለያየ አርአያና አምሳል አይተውታል::
"እስመ በአንጽሖ መንፈስ ርዕይዎ ነቢያት ለእግዚአብሔር: ወተናጸሩ ገጸ በገጽ" እንዳለ አባ ሕርያቆስ:: (ቅዳሴ ማርያም)

የብዙ ነቢያት ፍጻሜአቸው መከራን መቀበል ነው:: እውነትን ስለ ተናገሩ: አንዳንዶቹም በእሳት: አንዳንዶቹም በሰይፍ: አንዳንዶቹም በመጋዝ ተፈትነዋል:: ሌሎቹ ለአናብስት ሲጣሉ ቀሪዎቹ ደግሞ በድንጋይ ተወግረዋል::

ስለዚህም መከራቸው ለቤተ ክርስቲያን መሠረት ተብለዋል:: ጌታም ለደቀ መዛሙርቱ "ሌሎች ደከሙ: እናንተ በድካማቸው ገባችሁ" ብሎ የነቢያቱን መከራ ተናግሯል:: (ዮሐ. 4:36)

ነቢያት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስና እና ድንግል እናቱን ለማየት ብዙ ጥረዋል: ሽተዋልም:: "ብዙ ነቢያትና ጻድቃን እናንተ የምታዩትን ሊያዩ ሹ" እንዳለ ጌታ በወንጌል:: (ማቴ. 13:16, 1ጴጥ. 1:10) ዛሬ ግን በሰማያት ጸጋ በዝቶላቸው: ክብር ተሰጥቷቸው ሐሴትን ያደርጋሉ::

††† ቅዱሳን ነቢያት በዋነኝነት አሥራ አምስቱ አበው ነቢያት: አራቱ ዐበይት ነቢያት: አሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያትና ካልአን ነቢያት ተብለው በአራት ይከፈላሉ::

††† "አሥራ አምስቱ አበው ነቢያት" ማለት:-
*ቅዱስ አዳም አባታችን
*ሴት
*ሔኖስ
*ቃይናን
*መላልኤል
*ያሬድ
*ኄኖክ
*ማቱሳላ
*ላሜሕ
*ኖኅ
*አብርሃም
*ይስሐቅ
*ያዕቆብ
*ሙሴና
*ሳሙኤል ናቸው::

††† "አራቱ ዐበይት ነቢያት"
*ቅዱስ ኢሳይያስ ልዑለ ቃል
*ቅዱስ ኤርምያስ
*ቅዱስ ሕዝቅኤልና
*ቅዱስ ዳንኤል ናቸው::

††† "አሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት"
*ቅዱስ ሆሴዕ
*አሞጽ
*ሚክያስ
*ዮናስ
*ናሆም
*አብድዩ
*ሶፎንያስ
*ሐጌ
*ኢዩኤል
*ዕንባቆም
*ዘካርያስና
*ሚልክያስ ናቸው::

††† "ካልአን ነቢያት" ደግሞ:-
*እነ ኢያሱ
*ሶምሶን
*ዮፍታሔ
*ጌዴዎን
*ዳዊት
*ሰሎሞን
*ኤልያስና
*ኤልሳዕ ሌሎችም ናቸው::

††† ነቢያት በከተማም ይከፈላሉ::
*የይሁዳ (ኢየሩሳሌም):
*የሰማርያ (እሥራኤል)ና
*የባቢሎን (በምርኮ ጊዜ) ተብለው ይጠራሉ::

††† በዘመን አከፋፈል ደግሞ:-
*ከአዳም እስከ ዮሴፍ (የዘመነ አበው ነቢያት):
*ከሊቀ ነቢያት ሙሴ እስከ ነቢዩ ሳሙኤል (የዘመነ መሳፍንት ነቢያት)
*ከቅዱስ ዳዊት እስከ ዘሩባቤል ያሉት (የዘመነ ነገሥት ነቢያት):
*ከዘሩባቤል ዕረፍት እስከ መጥምቁ ዮሐንስ ያሉት ደግሞ (የዘመነ ካህናት ነቢያት) ይባላሉ::
ስለ ቅዱሳን ነቢያት በጥቂቱ ይህንን ካልን ወደ ዕለቱ በዓል እንመለስ::

ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳንኤል ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በ600 ዓመታት አካባቢ ከይሁዳ ነገሥታት ዘር ተወለደ:: ገና በሕፃንነቱ ናቡከደነጾር ኢየሩሳሌምን አቃጥሎ : ሕዝቡን ማርኮ ወደ ባቢሎን ሲያወርዳቸው አብሮ ወርዷል::

ከሕፃንነቱ ጀምሮ በአምላኩ ፍቅር የታሠረ : ከሦስቱ ጓደኞቹ (አናንያ : አዛርያና ሚሳኤል) ጋር ጾምና ጸሎትን ያዘወትር ነበር:: በዘመኑ እንደርሱ ያለ መተርጉመ-ሕልም አልተገኘምና ለወገኖቹ ሞገሳቸው ነበር::

ኃይለኛውን ንጉሥ ናቡከደነጾርን ጨምሮ የባቢሎንና ፋርስ ነገሥታት ያከብሩት : ይወዱትም ነበር::

ቅዱስ ዳንኤል በጥበብና በሃይማኖት የአሕዛብን አማልክት ድል ነስቷል:: አሕዛብ በተንኮል ወደ አናብስት ጉድጓድ ውስጥ ቢያስጥሉት እግዚአብሔር የአናብስቱን አፍ ዘግቷል:: ዕንባቆምንም አምጥቶ መግቦታል::

ቅዱስ ዳንኤል የብሉይ ኪዳኑ "አቡቀለምሲስ" ይባላል:: ስለ ጌታችን የማዳን ሥራና ስለ ዳግም ምጽዐቱ በግልጥ ተናግሯል:: ሐረገ ትንቢቱም 12 ምዕራፍ ነው:: የዘመኑ አይሁድ ክርስቶስ ገና አልተወለደም ለማለት ዳንኤልን ጠልተውታል::

ታላቁ ነቢይና ጻድቅ ቅዱስ ዳንኤል እስራኤል ወደ ሃገራቸው ሲመለሱ አብሯቸው አልመጣም:: ከ70 ዓመታት በላይ በጸጋ ትንቢት ኑሮ እዛው ባቢሎን ውስጥ አርፏል::

††† ፈጣሪ ከበረከቱ ለሁላችን ያድለን::

††† በዚህች ቀን ክፉዎች አይሁድ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ይገድሉ ዘንድ በቤተ ቀያፋ መከሩ::

††† እርሱ ቸሩ አምላክ ከክፉ መካሪዎች ይሠውረን::

††† መጋቢት 23 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳንኤል (የስሙ ትርጓሜ- እግዚአብሔር ፈራጅ ነው ማለት ነው::)

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት
2.ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማዕታት
3.ቅዱስ ሰሎሞን ንጉሠ እስራኤል
4.አባ ጢሞቴዎስ ገዳማዊ
5.አባ ሳሙኤል
6.አባ ስምዖን
7.አባ ገብርኤል

††† "የዚያን ጊዜም ንጉሡ አዘዘ:: ዳንኤልንም አምጥተው በአንበሶች ጉድጓድ ጣሉት . . . ድንጋይም አምጥተው በጉድጓዱ አፍ ላይ ገጠሙት . . . በነጋውም ንጉሡ ማልዶ ተነሳ . . . ወደ ዳንኤል በቀረበ ጊዜ በኀዘን ቃል ጠራው . . . ዳንኤልም ንጉሡን . . . በፊቱ ቅንነት ተገኝቶብኛልና . . . አምላኬ መልዐኩን ልኮ የአንበሶቹን አፍ ዘጋ:: አንዳችም አልጐዱኝም አለው . . . ዳንኤልም ከጉድጓድ ወጣ:: በአምላኩም ታምኖ ነበርና አንዳች ጉዳት አልተገኘበትም::" ††† (ዳን. ፮፥፲፮-፳፫)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
ቅዱስ ዳንኤል በአንበሶች ጉድጓድ እንዲጣል ያደረገው ንጉሥ ማን ይባላል?
Anonymous Quiz
68%
ንጉሥ ናቡከደርፆር
21%
ንጉሥ ዳርዮሥ
10%
ንጉሥ ባቢሎን
1%
ንጉሥ ሰለሞን
ነብዩ ዳንኤል ከ12ቱ ደቂቀ ነብያት ውስጥ ነው የሚመደበው?
Anonymous Quiz
49%
እውነት
51%
ሐሰት
ነብዩ ዳንኤል በየዕለቱ ስንት ጊዜ ይጸልይ ነበር?
Anonymous Quiz
82%
7 ጊዜ
5%
5 ጊዜ
11%
3 ጊዜ
2%
1 ጊዜ
ከነቢዩ ዳንኤል ጋር በፋርስ በስደት ትኖር የነበረች ሴት ማን ትባላለች?
Anonymous Quiz
13%
ማርታ
38%
ዲቦራ
17%
ሊያ
32%
ሶስና
ነብዩ ዳንኤል የእስራኤል ልጆች ወደ ኢየሩሳሌም እስከሚመለሱበት ጊዜ በባቢሎን ስንት ዘመን ኖረ?
Anonymous Quiz
74%
70 ዘመን
9%
75 ዘመን
11%
25 ዘመን
6%
55 ዘመን
† እንኳን ለጻድቁ አባታችን ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ዓመታዊ በዓለ ፅንሰት በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ሐዋርያዊ †††

††† ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ዐይን ናቸው:: ጻድቁን መንካት የቤተ ክርስቲያንን ዐይኗን መጠንቆል ነው::

ተክለ ሃይማኖት እንደ ሊቃውንት ሊቅ: እንደ ሐዋርያት ሰባኬ ወንጌል: እንደ ሰማዕታት ብዙ ግፍ የተቀበሉ: እንደ ጻድቃን ትሩፋት የበዛላቸው: እንደ ደናግል ንጽሕናን ያዘወተሩ: እንደ ባሕታውያን ግኁስ: እንደ መላዕክትም ባለ ክንፍ አባት ነበሩ:: ለዚሕ ነው ተክለ ሃይማኖትን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ዐይኔ የምትላቸው::

††† ልደት †††

††† መልካም ዛፍ መልካም ፍሬን ያፈራልና ተክለ ሃይማኖትን የወለዱት ደጋጉ: ጸጋ ዘአብ ካህኑና እግዚእ ኃረያ ናቸው:: እርሱ በክህነቱ: እርሷ በደግነቷ: በምጽዋቷ ጸንተው ቢኖሩ እግዚአብሔር ጣፋጭ ፍሬን ሰጥቷቸዋል::

በዳሞቱ ገዢ በሞተለሚ አደጋ ቢደርስባቸው ቅዱስ ሚካኤል: ጸጋ ዘአብን ከሞት: እግዚእ ኃረያን ከትድምርተ አረሚ (ከአረማዊ ጋብቻ) አድኗቸዋል:: በኋላም የቅዱሱን መወለድ አብስሯቸዋል::

ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የተጸነሱት መጋቢት 24 ቀን በ1206 ዓ/ም ሲሆን የተወለዱት ደግሞ ታኅሣሥ 24 ቀን በ1207 ዓ/ም ነው:: በተወለዱበት ቀንም ብዙ ተአምራት ተገልጸዋል:: ቤታቸውም በበረከት ሞልቷል::

ዕድገት

የጻድቁ የመጀመሪያ ስማቸው "ፍሥሃ ጽዮን" ይሰኛል:: ይሕንን ስም ይዘው: አባታቸው ጸጋ ዘአብን ተከትለው አድገዋል:: በተለይ ቅዱሳት መጻሕፍትን (ብሉያት: ሐዲሳትን) ተምረዋል:: በሥጋዊው ጐዳናም ብርቱ አዳኝ እንደ ነበሩ ይነገራል:: ዲቁናም ከወቅቱ ጳጳስ አባ ጌርሎስ ተቀብለዋል::

መጠራት

አንድ ቀን ፍሥሃ ጽዮን ለአደን ወጥቶ ሲያነጣጥር ድንገት ከሰማይ አስደንጋጭ ድምጽ ተሰማ:: የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አእላፍ መላእክት እያመሰገኑት በሚካኤል ክንፍ ተቀምጦ ወረደ::

የወጣቱን አዳኝ ፍርሃቱን አርቆ ጌታችን ተናገረ:: "ከዛሬ ጀምሮ ስምህ ተክለ ሃይማኖት (ተክለ ሥላሴ) ይሁን:: ከዚህ በኋላ አራዊትን ሳይሆን ነፍሳትን ታድናለህ:: ዘወትር ካንተ ጋር ነኝ" ብሎ በግርማ ዐረገ:: ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ከዚህ ጊዜ በኋላ ሰዓትን አላጠፉም:: ንብረታቸውን ለነዳያን በትነው በትር ብቻ ይዘው ቤታቸው እንደ ተከፈተ ወደ ምናኔ ወጡ::

አገልግሎት

ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ከጳጳሱ ቅስና ተቀብለው የወንጌል አገልግሎትን ጀመሩ:: በመጀመሪያ ስብከታቸው እዚያው ሽዋ (ጽላልሽ) አካባቢ ብቻ በ10ሺ የሚቆጠሩ ሰዎችን አሳምነው አጠመቁ:: ያን ጊዜ ኢትዮጵያ 2 መልክ ነበራት::

1ኛ. ዮዲት (ጉዲት) በፈጠረችው ጣጣና በእስላሞች ተጽዕኖ ወደ ደቡብ አካባቢ ያለው ነዋሪ አንድም ሃይማኖቱን ክዷል: ወይም በባዕድ አምልኮ ተጠምዷል::
2ኛ. በዛግዌ ነገሥታት ጥረት ክርስትናና ምናኔ ተነቃቅቶ ነበር::

ግማሹ ሃገር በጨለመበት ወቅት የደረሱት ሐዲስ ሐዋርያ አባ ተክለ ሃይማኖት በወጣት ጉልበታቸውና በኃይለ መንፈስ ቅዱስ ብዙ ቦታዎችን አደረሱ:: ሕዝቡን: መሣፍንቱን ወደ ሃይማኖት መልሰው: ማርያኖችን (ጠንቋዮችን) አጥፍተዋል::

ገዳማዊ ሕይወት

ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት በወንጌል ብርሃን ኢትዮጵያን ከማብራታቸው ባለፈ ገዳማዊ ሕይወትንም አስፋፍተዋል:: እርሳቸው ከሁሉ የተሻሉ ሳሉም በ3 ገዳማት በረድዕነት አገልግለዋል::

እነዚህም በአቡነ በጸሎተ ሚካኤል ገዳም ለ12 ዓመታት: በአቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ ገዳም ለ7 ዓመታት: በደብረ ዳሞ ከአቡነ ዮሐኒ ጋር ለ7 ዓመታት: በአጠቃላይ ለ26 ዓመታት አገልግለዋል::

በአቡነ ኢየሱስ ሞዐ ከመነኮሱ በኋላም ወደ ምድረ ሽዋ (ዞረሬ) ተመልሰው በአንዲት በዓት ውስጥ ለ22 ዓመታት ቆመው ጸልየዋል:: በተሰበረ እግራቸውም 6 ጦሮችን በግራና በቀኝ ተክለው ለ7 ዓመታት ጸልየዋል::

ስድስት ክንፍ

ኢትዮጵያዊው ጻድቅና ሐዋርያ ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ከኢትዮጵያ ወደ ኢየሩሳሌም ተጉዘው ከቅዱሳት መካናት ተባርከዋል:: ጻድቁ ምድረ እሥራኤል የገቡት በየመንገዱ መንፈሳዊ ዘርን እየዘሩ: እያስተማሩና እያሳመኑ ነበር::

የወቅቱ ሊቀ ጳጳሳት አባ ሚካኤል ጋርም ተገናኝተው ቡራኬን ተሰጣጥተዋል:: ዋናው ጉዳይ ግን ከዚህ በኋላ ነው:: ጻድቁ እመቤታችንና ጌታችን ከጽንሰታቸው እስከ ዕርገታቸው የረገጧቸውን ቦታዎች ሲመለከቱ በፍጹም ተደሞ እንባቸው ይፈስ ነበር::

ምክንያቱም እግዚአብሔር ስላበቃቸው ተክለ ሃይማኖት የሚያዩት ቦታውን አልነበረም:: በገሃድ:-
-በቤተ መቅደስ ብስራቱን
-በቤተ ልሔም ልደቱን
-በቤተ ዮሴፍ ግዝረቱን
-በፈለገ ዮርዳኖስ ጥምቀቱን
-በቤተ አልዓዛር ተአምራቱን ይመለከቱ ነበር::

የጉብኝታቸው የመጨረሻ ክፍል ወደ ሆነው ቀራንዮ ደርሰው ጌታቸውን እንደ ተሰቀለ ሆኖ ቢመለከቱት ከዓይናቸው ይፈስ የነበረው ቁጡ እንባ መልኩን ቀየረና ዓይናቸው ጠፋ::
በዚያች ቅጽበት ስም አጠራሯ የከበረ እመቤታችን ድንግል ማርያም ፈጥና ደርሳ ቅዱስ ተክለ ሃይማኖትን ወደ ሰማይ አሳረገቻቸው::

በዚያም:-
*የብርሃን ዐይን ተቀብለው
*ስድስት ክንፍ አብቅለው
*የወርቅ ካባ ላንቃ ለብሰው
*ማዕጠንተ ወርቁን ይዘው
*ከሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይም ተደምረው
*ሥላሴን በአንድነቱና ሦስትነቱ ተመልክተው
*"ስብሐት ወክብር ለሥሉስ ቅዱስ ይደሉ" ብለው መንበረ ጸባኦትን አጥነው ወደ መሬት ተመልሰዋል::

ተአምራት

የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ተአምራት እንደ ሰማይ ከዋክብት የበዛ ነው::
*ሙት አንስተዋል
*ድውያንን ፈውሰዋል
*አጋንንትን አሳደዋል
*እሳትን ጨብጠዋል
*በክንፍ በረዋል
*ደመናን ዙፋን አድርገዋል::

ብዙ ደቀ መዛሙርትን አፍርተው ደብረ ሊባኖስን መሥርተዋል:: በዚያም ሴትና ወንድ መነኮሳት እንደ ሕፃናት አብረው ኑረዋል:: በዘመናቸው ሰይጣን ታሥሯልና::

ዕረፍት

ጻድቅ: ሰማዕትና ሐዋርያ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ብርሃን ሆነው መከራን በብዙ ተቀብለው: እልፍ አእላፍ ፍሬን አፍርተው: በተወለዱ በ99 ዓመት: ከ8 ወር: ከ1 ቀናቸው ነሐሴ 24 ቀን በ1306 ዓ/ም ዐርፈዋል:: ጌታ: ድንግል ማርያምና ቅዱሳን ከሰማይ ወርደው ተቀብለዋቸዋል:: 10 ትውልድ የሚያስምር ቃል ኪዳንም ተቀብለዋል::

=>ይህች ዕለት ለጽንሰታቸው መታሰቢያ በዓል ናት፡፡
††† አምላከ ቅዱሳን ከጻድቁ አባታችን በረከትን ይክፈለን::

††† መጋቢት 24 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት (ጽንሰቱ)
2.ቅዱሳን እግዚእ ኃረያና ጸጋ ዘአብ
3.ቅዱስ አባ መቃርስ ሊቀ ጳጳሳት

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ አጋቢጦስ ጻድቅ
2.ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ
3.ቅዱስ ሙሴ ፀሊም
4.ቅዱስ ቶማስ ዘመርዐስ
5.ቅዱስ አብላርዮስ ታላቁ
6.ሃያ አራቱ ካኅናተ ሰማይ

††† "በረከት በጻድቅ ሰው ራስ ላይ ነው:: የኀጥአንን አፍ ግን ግፍ ይከድነዋል:: የጻድቅ መታሰቢያ ለበረከት ነው:: የኀጥአን ስም ግን ይጠፋል::" †††
(ምሳሌ ፲፥፮)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
ጻድቁ አባታችን አቡነ ተክለ ሐይማኖት መጋቢት 24 ቀን ተጸንሰው ጥር 24 ቀን ነው
Anonymous Quiz
49%
እውነት
51%
ሐሰት
ጻድቁ አቡነ ተክለ ሐይማኖት ከ24ቱ ካህናተ ሰማይ ጋር 25ኛ ሆነው የ#ሥላሴ ን መንበር ያጠኑበት ቀን_______ነው።
Anonymous Quiz
25%
ግንቦት 24
30%
ታህሳስ 24
23%
ነሐሴ 24
22%
ኅዳር 24
Channel name was changed to «ቅዱሳን ኅሩያን»
††† እንኳን ለዘመነ ሐጋይ (በጋ) የመጨረሻ ዕለትና ለሐዋርያው ቅዱስ አንሲፎሮስ በዓለ ዕረፍት በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† አምላካችን እግዚአብሔር ሁሉን ስነ ፍጥረት የፈጠረ ለሰው ልጆች ጥቅም ነው:: ጌታ አዝማናትን : ወሮችን : ሳምንታትን : ቀኖችንና ሰዓታትን ፈጥሮ : ወስኖ ሰጥቶናል:: የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጥንታዊት እንደ መሆኗ ሁሉ ነገሯ በሥርዓት ይፈፀማል::

በራሷ የዘመን ቀመር ስሌት መሠረትም አንድ ዓመት በአራት ወቅቶች ይከፈላል:: አባታችን ሊቁ ቅዱስ ያሬድም እነዚህን ወቅቶች መሠረት አድርጎ መንፈሳዊ ድርሰቶችን ደርሷል::

እነዚሕ አዝማናት (ወቅቶች):-
1.ዘመነ ክረምት (ከሰኔ 26 እስከ መስከረም 25)
2.ዘመነ መፀው (ከመስከረም 26 እስከ ታኅሣሥ 25)
3.ዘመነ ሐጋይ (ከታኅሣሥ 26 እስከ መጋቢት 25)
4.ዘመነ ፀደይ (ከመጋቢት 26 እስከ ሰኔ 25) መሆናቸው ይታወቃል::

ዘመነ ሐጋይ (በጋን) የባረከ አምላክ ዘመነ ፀደይ (መከርን) እንዲባርክልን : የንስሐ ጊዜም እንዲያደርግልን ቅዱስ ፈቃዱ ይሁን::

††† ቅዱስ አንሲፎሮስ †††

††† በዚህች ዕለት ጌታችንን በሃገረ ናይን የተከተለ : ከዋለበት ውሎ : ካደረበት ያደረ : ከሰባ ሁለቱ አርድእት የተቆጠረ ሐዋርያው ቅዱስ አንሲፎሮስ አርፏል::

††† ዳግመኛ በዚህ ዕለት አይሁድ ለመጨረሻ ጊዜ ጌታችንን ሊገድሉት ተስማሙ:: ይሁዳም በ30 ብር ይሸጠው ዘንድ ከአይሁድ ጋር ተዋዋለ::

††† የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይቅርታውና ምሕረቱ ከሁላችን ጋር ይሁን::

††† መጋቢት 25 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ አንሲፎሮስ ሐዋርያ (ከሰባ ሁለቱ አርድእት)

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ መርቆሬዎስ ሰማዕት
2.ቅድስት ቴክላ ሐዋርያዊት
3.ቅዱስ አበከረዙን ሰማዕት
4.ቅዱስ ዱማድዮስ ሶርያዊ
5.አቡነ አቢብ (አባ ቡላ)
6.ቅዱስ አባ አቡፋና ጻድቅ

††† "ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጐዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ: ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዘመናትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን:: እርሱም . . . ኃጢአታችንን በራሱ ካነጻ በኋላ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ::" †††
(ዕብ. ፩፥፩)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
2024/09/29 19:35:28
Back to Top
HTML Embed Code: