Telegram Web Link
እንኳን ለነነዌ ጾም አደረሳችሁ።
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ :: አሜን ::

+*" ጾመ ነነዌ ወቅዱስ ዮናስ ነቢይ "*+

=>ዮናስ ማለት 'ርግብ: የዋህ' ማለት ሲሆን ከ12ቱ ደቂቀ ነቢያት አንዱ ነው:: በሰራፕታ ተወልዶ ያደገው ነቢዩ በልጅነቱ ታሞ ሙቶ ነበር:: ታላቁ ነቢይ ኤልያስ ግን 7 ጊዜ ጸሎት አድርጐ ከሞት አስነስቶታል:: (1ነገ. 17:17) እናቱ የሰራፕታዋ መበለትም ደግ ሴት ነበረች::

+ቅዱስ ዮናስ በእድሜው ከፍ ሲል የቅዱስ ኤልያስ ደቀ መዝሙር ሆነ:: የነ ኤልሳዕና አብድዩም ባልንጀራ ነበረ:: ነቢየ እግዚአብሔር ኤልያስ ካረገ በሁዋላ: ቅ/ል/ክርስቶስ በ800 ዓመት አካባቢ የነነዌ ሰዎች ኃጢአት ከመሥፈርቱ በማለፉ የእግዚአብሔር ቃል ወደ አማቴ ልጅ ወደ ዮናስ መጣ::

+"ሒድና ለነነዌ ሰዎች ንስሃን ስበክላቸው" አለው:: ከነቢያት ወገን ከሙሴና ከዳዊት ቀጥሎ የዮናስን ያህል የዋህ (ገራገር) የለምና እንቢ አለ (ሰምቶ ዝም አለ):: እግዚአብሔር እየደጋገመ ሲናገረው ግን "እንዲህ የሚዘበዝበኝ ከፊቱ ብቀመጥ አይደል!" ብሎ ወደ ተርሴስ ኮበለለ::

+ወገኖቼ አንድ ነገርን ልብ እንበል:: እንኩዋን ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዮናስ እኛ ክፉዎችም ከጌታ ፊት መሸሸት እንደማይቻል ጠንቅቀን እናውቃለን:: ታዲያ ለምን ሸሸ ቢሉ:- ጥበበ እግዚአብሔር በውስጡ ስለ ነበረበት ነው::

+ምክንያቱም ዮናስ በአሣ አንበሪ ሆድ 3 ቀን ሌሊት ኖሮ: ሙስና (ጥፋት) ሳያገኘው መውጣቱ ለጌታ ትንሳኤ ጥላ (ምሳሌ) ነው:: ለዚህም ምስክሩ ራሱ ጌታችን ነው::

"ወበከመ ነበረ ዮናስ ውስተ ከርሠ አንበሪ ሠሉሰ ዕለተ ወሠሉሰ ለያልየ: ከማሁ ይነብር ወልደ እጉዋለ እመ ሕያው ውስተ ልበ ምድር ሠሉሰ ዕለተ: ወሠሉሰ ለያልየ" እንዲል:: (ማቴ. 12:39)

+ቅዱስ ዮናስ በገንዘቡ ዋጅቶ ወደ መርከብ በገባ ጊዜ ታላቅ ማዕበል ሆነ:: የእምነት ሰው ነውና እንዲያ እየተናወጡ እርሱ በእርጋታ ተኝቷል:: እነርሱ ግን ቀስቅሰው ቢጠይቁት (እጣ ወድቆበታልና) "የእኔ ጥፋት ስለ ሆነ ወደ ማዕበሉ ጣሉኝ" አላቸው::

+እያዘኑ ቢጥሉት ታላቅ ጸጥታ ሆነ:: እነዚያ አሕዛብም እግዚአብሔርን በመስዋዕትና በስዕለት አከበሩ:: ዮናስ ግን በማዕበልና በአሣ አንበሪ ሆድ ውስጥ ለ3 ቀናት ጸለየ:: አሣ አንበሪው በ3ኛው ቀን ወደ ነነዌ ተፋው::

+ቅዱሱም "እስከ ሠሉስ ዕለት ትትገፈታእ #ነነዌ ዐባይ ሃገር" እያለ ንስሃን ሰበከ:: የነነዌ ሰዎች ኃጢአታቸውን አምነው ቢጸጸቱ ከሰማይ ወርዶ ከደመና ደርሶ የነበረው የእሳት ማዕበል ተመልሶላቸዋል::

+የነቢዩ ትንቢት ግን አልቀረምና ታላቁዋ ነነዌ ከ300 ዓመታት በሁዋላ ጠፍታለች:: ቅዱስ ዮናስ ግን በቀሪ ዘመኑ ፈጣሪውን እያገለገለ ኑሯል:: ጠቅላላ እድሜውም 170 ዓመት ነው::

+ዛሬ ያለን ሁላችን ሃገራችን ነነዌን ሕዝቦቿም ሕዝቦቻቸውን ከመሰልን ሰንብተናል:: በእርግጥ እንደ ነነዌ እሳት አይዘንብብን ይሆናል:: ግን የዘለዓለም እሳት ይጠብቀናል:: ንስሃ ካልገባን የሚመጣብን ቅጣት የሚከፋ ይሆናል::

=>አምላከ ቅዱስ ዮናስ እድሜ ለንስሃ: ዘመን ለፍስሃ አይንሳን:: ጾሙንም የበረከት ያድርግልን::

=>+"+ ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይሻል:: ከነቢዩም ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም:: ዮናስ በአሣ አንበሪ ሆድ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደ ነበረ: እንዲሁ የሰው ልጅ በምድር ልብ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይኖራል:: የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነስተው ይፈርዱበታል:: በዮናስ ስብከት ንስሃ ገብተዋልና:: እነሆም ከዮናስ የሚበልጥ ከዚህ አለ:: +"+ (ማቴ. 12:39)

   <<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞

❖የካቲት ፲፰ (18) ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

+*" ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ "*+

=>ቅዱስ ያዕቆብ ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ያደገ:
የአረጋዊው ቅ/ዮሴፍ የመጨረሻ ልጅ : በንጽሕናውና
ድንግልናው የተመሠከረለት : ከጸሎትና ገድል ብዛት እግሩ
ያበጠ : የመጀመሪያው የኢየሩሳሌም ኤዺስ ቆዾስ ሲሆን
ቁጥሩም ከ72ቱ አርድዕት ነው:: ይሕስ እንደ ምን ነው
ቢሉ:-

=>ይህ ቅዱስ ሐዋርያ በአባቶቻችን ሐዋርያት መካከል
ትልቅ ሞገስ የነበረውና የጌታችን ወንድም ተብሎ የተጠራ
ነው:: ቅዱስ ያዕቆብ ወላጅ አባቱ አረጋዊው ቅዱስ ዮሴፍ
(የእመቤታችን ጠባቂ) ሲሆን በልጅነቱ ጥላው የሞተችው
እናቱ ደግሞ ማርያም ትባላለች:: በቤት ውስጥም
ስምዖን: ዮሳና ይሁዳ የተባሉ ወንድሞችና ሰሎሜ
የምትባል እህትም ነበረችው::

+እናቱ ማርያም ከሞተች በሁዋላ ዕጉዋለ ማውታ (ደሃ
አደግ) ሆኖ ነበር:: ነገር ግን በፈቃደ እግዚአብሔር አረጋዊ
ዮሴፍ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ከቤተ
መቅደስ ሊጠብቃት (ሊያገለግላት) ተቀብሎ ሲመጣ ያ
ቤተሰብ ተቀየረ:: የበረከት: የምሕረትና የሰላም እመቤት
የአምላክ እናቱ ገብታለችና ያ የሐዘን ቤት ደስታ ሞላው::

+እመ ብርሃን ግን ገና ወደ ዮሴፍ ልጆች ስትደርስ
አለቀሰች:: የአክስቷ ልጆች የሚንከባከባቸው አጥተው
ቆሽሸው ነበር:: በተለይ ደግሞ ትንሹ ቅዱስ ያዕቆብ
ያሳዝን ነበር:: እመ ብርሃን ማረፍ አልፈለገችም::
ወዲያው ማድጋ አንስታ ወደ ምንጭ ወርዳ ውሃ አምጥታ
የሕጻኑን ገላ አጠበችው:: (በአምላክ እናት የታጠበ
ሰውነት ምስጋና በጸጋ ይገባዋል!)

+እመቤታችን ጌታ ከመወለዱ በፊት ለ9 ወራት: ከተወለደ
በሁዋላ ደግሞ ለ2 ዓመታት ሕጻኑን ያዕቆብን
ተንከባከበችው::

ለ3 ዓመታት ከ6 ወራት ግን ድንግል ማርያም አምላክ
ልጇን ይዛ ተሰዳለችና ተለያዩ:: ከስደት መልስ ግን ለ25
ዓመታት ቅዱስ ያዕቆብ ከጌታችን ጋር ሲያድግ ወላጅ እናቱ
ትዝ ብላው አታውቅም:: አማናዊቷ እናት ከጐኑ ነበረችና::

+ሊቃውንት እንደ ነገሩን እመቤታችን ለቅዱስ ያዕቆብ
ያልሰጠችው ነገር ቢኖር ሐሊበ ድንግልናዌ (የድንግልና
ወተትን) ብቻ ነው::

ስለዚህም:-
"እመ ያዕቆብ በጸጋ ማርያም ንግሥተ ኩሉ" ይላል
መጽሐፍ:: (መልክዐ ስዕል)

+ቅዱስ ያዕቆብ "የጌታ ወንድም" ተብሎ በተደጋጋሚ
በሐዲስ ኪዳን ተጠርቷል:: ለዚህ ምክንያቱ:-
1.ለ30 ዓመታት ሳይነጣጠሉ አብረው በማደጋቸው፡፡
2.የጌታችን የሥጋ አያቱ (የቅድስት ሐና) የእህት ልጅ
በመሆኑ፡፡
3.በዮሴፍ በኩልም የአንድ ቅድመ አያት ልጆች
በመሆናቸው፡፡
4.ጌታችን ከትህትናው የተነሳ ደቀ መዛሙርቱን
"ወንድሞች" ይላቸው ስለ ነበር ነው:: (ሥጋቸውን ተዋሕዶ
ተገኝቷልና)

+ራሱ ቅዱስ ያዕቆብ ግን "የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ
ባሪያ ነኝ" ብሎ በፈጣሪና በፍጡር መካከል ያለውን ልዩነት
ገልጧል:: (ያዕ. 1:1) ቅዱስ ያዕቆብ ጌታችን ሲያስተምር
ተከተለው::

¤ከ72ቱ አርድእት ተቆጠረ
¤3 ዓመት ከ3 ወር ወንጌልን ተማረ
¤ለመጀመሪያ ጊዜ ከድንግል ማርያምና ከቅዱስ ዮሐንስ
ጋር ሆኖ "የጌታን ትንሳኤ ሳላይ እሕል አልቀምስም" ብሎ
ማክፈልን አስተማረ
¤መንፈስ ቅዱስን ተሞልቶ ወንጌልን አስተማረ
¤የኢየሩሳሌም የመጀመሪያው ሊቀ ዻዻስ ሆኖ አገለገለ
¤በመጀመሪያዎቹ የክርስትና ዘመናት የሐዋርያት
ሲኖዶሶችን በሊቀ መንበርነት መራ
¤ሙታንን አስንስቶ: ድውያንን ፈውሶ: የመካኖችን ማሕጸን
ከፍቶ: አጋንንትንም አስወጥቶ ብዙ ተእምራትን ሠራ::
እጅግ ብዙ አይሁዳውያንን ወደ አሚነ ክርስቶስ መልሶ
መልካሙን ገድል ተጋደለ::

+በመጨረሻ ዘመኑ ያላመኑ የአይሁድ አለቆች ወደ ቤቱ
ተሰብስበው "የናዝሬቱ ኢየሱስ ማነው? የማንስ ልጅ
ነው?" ሲሉ ጠየቁት:: እነርሱ ሰይጣን በሰለጠነበት
ልቡናቸው "የዮሴፍ ልጅ ነው: የእኔም ወንድሜ ነው"
እንዲላቸው ጠብቀው ነበር:: (ሎቱ ስብሐት ወአኮቴት!)

+በልቡናቸው ያሰቡትን ተንኮል የተረዳው ሐዋርያ ወደ ቤቱ
ጣራ ወጥቶ መናገር ጀመረ:: "ለስም አጠራሩ ጌትነት
ይሁንና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ ወልደ አምላክ:
ወልደ አብ ወልደ ማርያም: ሥግው ቃል: እግዚአብሔር
ነው:: እኔም ፍጡሩና ባሪያው እንጂ እንደምታስቡት
ወንድሙ አይደለሁም" አላቸው::

+ንዴታቸውን መቆጣጠር ያልቻሉት አይሁድ ከላይ
ወጥተው ወደ መሬት ወረወሩት:: በገድል የተቀጠቀጠ
አካሉንም እየተፈራረቁ ደበደቡት:: አንዱ ግን ከእንጨት
የተሠራ ትልቅ ገንዳ አምጥቶ የቅዱሱን ራስ ደጋግሞ
መታው:: ጭንቅላቱም እንዳልነበር ሆነ:: ሰማዕቱ ሐዋርያ
ቅዱስ ያዕቆብ ወደ ወደደው ክርስቶስ በዚህች ቀን ሔደ::

+ቅዱሱ ሐዋርያ ያዕቆብ ቤቱን እንደ ቤተ መቅደስ አበው
ሐዋርያት ይጠቀሙባት ነበር:: በመላ ዘመኑ የሚያገድፍ
ነገር (ጥሉላት) ቀምሶ: ጸጉሩን ተላጭቶ: ገላውን ታጥቦና
ልብሱን ቀይሮ አያውቅም::

"ወዝንቱ ጻድቅ እኅወ እግዚእነ::
ኢያብአ ውስተ አፉሁ ሥጋ ወወይነ::
ወኢገብረ ሎቱ ክልኤተ ክዳነ::" እንዲል::

+ከጾም: ከጸሎትና ከመቆሙ ብዛትም እግሩ አብጦ
አላራምድህ ብሎት ነበር:: ስለዚህም አበው "ጻድቁ
(ገዳማዊው) ሐዋርያ" ይሉታል:: ቅዱሱ ሐዋርያ
"የያዕቆብ መልዕክት" የሚለውን ባለ 5 ምዕራፍ
መልዕክት ጽፏል::

=>ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወንድሙ ይባል ዘንድ
ካደለው ሐዋርያ በረከትን ያድለን:: በምልጃውም
ምሕረትን ይላክልን::

=>የካቲት 18 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (የቅዱስ ዮሴፍ ልጅ : ከ72ቱ
አርድእት አንዱ)
2.ቅዱስ አባ መላልዮስ ጻድቅ ሊቀ ዻዻሳት (በአንጾኪያ
ሊቀ ዽዽስና ተሹሞ በአርዮሳውያን ብዙ ግፍ የደረሰበትና
በስደት ያረፈ አባት ነው)

=>ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ፊልዾስ ሐዋርያ
2.አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ሰባኬ ሃይማኖት
3.አቡነ አኖሬዎስ ዘደብረ ጽጋጋ
4.ማር ያዕቆብ ግብፃዊ

=>+"+ የእግዚአብሔርና የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ
ያዕቆብ: ለተበተኑ ለአሥራ ሁለቱ ወገኖች:: ሰላም ለእናንተ
ይሁን:: ወንድሞቼ ሆይ! የእምነታችሁ መፈተን ትዕግስትን
እንዲያደርግላችሁ አውቃችሁ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ
እንደ ሙሉ ደስታ ቁጠሩት:: ትዕግስትም ምንም
የሚጐድላችሁ ሳይኖር ፍጹማንና ምሉዓን ትሆኑ ዘንድ
ሥራውን ይፈጽም:: +"+ (ያዕ. 1:1)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
🛑 አዲስ የንስሃ መዝሙር "እንደ እኔ የማርከው ማንን ነው" | ዘማሪ ዲያቆን አቤል መክብብ
🙏 '' እንደ እኔ የማርከው ''🙏


እንደኔ የማርከው ማንን ነው
እንደኔ ይቅር ያልከው ማንን ነው
ሀጢያቱ በዝቶበት በደሉ በዝቶበት
የማርከው እንደኔ ከቶ ማነው/2/



በሞገስ አስጊጠህ በዜማ ቃኘኸኝ
ፊትህ ምታቆመኝ ጌታዬ እኔ ማነኝ
ለኔ ያደረከው አቤት ደግነትህ
ምረኸኝ ምረኸኝ አያልቅም ምህረትህ
        አይተኸኝ በምህረት/2/
        ዛሬ አለሁኝ በህይወት

አዝ__

የምስጋና መስዋዕት ማቅረቢያ መሰዊያ
ልቤ ንጹህ ባይሆን ጸጋዬን አለቀማህ
ትቀበለኛለህ ሞልተኽ በጎደለው
እኔን የወደደ እንዳንተ ማን አለ
         አይተኸኝ በምህረት/2/
         ዛሬ አለሁኝ በህይወት

አዝ__

በምኞት ተስቤ ለሀጢያት ተሽጬ
በመስቀልህ ስራ ከሞት ጣር አምልጬ
አንተ እንዳዳንከው ሰው መሆን ቢያቅትም
እኔ ተስፋ ብቆርጥ ተስፋ አትቆጥርብኝም
         አይተኸኝ በምህረት/2/
         ዛሬ አለሁኝ በህይወት

አዝ___

በኖርኩበት ዘመን የቁጣ ልጅ ሆኜ
ምዕራፉ ተዘጋ በአንተ በአዳኜ
ከኔ ምንም ሳይኖር አንተ ሁሉን ሆነህ
ሰገነት ታየሁኝ ስለኔ ተንቀህ
         አይተኸኝ በምህረት/2/
         ዛሬም አለሁኝ በህይወት

አዝ___

እኔን ማረኝ ከምል ከፊትህ ወድቄ
በሌላው ፈራጅ ነኝ እራሴን አጽድቄ
መመልከት ባልችልም የአይኔን ምሰሶ
ያኖረኝ ፍቅርህ ነው ይህ ሁሉ ታግሶ
         አይተኸኝ በምህረት/2/
         ዛሬም አለሁኝ በህወት



🛑 አዲስ የንስሃ መዝሙር
"እንደ እኔ የማርከው ማንን ነው"
| ዘማሪ ዲያቆን አቤል መክብብ
✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን። ✞

† ታላቁ አባ መርትያኖስ †

=>አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም የካቲት ዐሥራ ዘጠኝ በዚች ዕለት የተጋዳይ መነኰስ የአባ መርትያኖስ ሥጋው ከአቴና አገር ወደ አንጾኪያ የፈለሰበት ሆነ። እርሱም ሽንግላ በኃጢያት ልትጥለው በወደደች ጊዜ ከአመንዝራ ሴት ከተፈተነ በኋላ እርሱ ግን መንኵሳ በገድል እስከ ተጸመደች ድረስ ስቦ ወደ ንስሓ መልሷታል።

«« ከዚህም በኋላ መኖሪያውን ትቶላት ከሀገር ወደ ሀገር የሚዞር ሆነ ከአቴና አገርም ደርሶ በዚያ ጥቂት ቀን ኖረ ጥቂትም ታመመና በሰላም አገፈ ዜናው በግንቦት በሃያ አንድ ቀን እንደተጻፈ።

የከበረ ቴዎድሮስም ለአንጾኪያ ሀገር በከሀዲው የፋርስ ንጉሥ ዘመን ሊቀ ጵጵስና በተሾመ ጊዜ ይህ አባት የካህናት አለቆችንና ምእመናንን ልኮ ሥጋውን ከአቴና አፍልሰው ወደ አንጾኪያ ከተማ አመጡት በምስጋናም እየዘመሩ አክብረው ተቀበሉት ሊቀ ጳጳሳቱም ተሳለመው በሣጥንም አድርጐ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አኖረው። በዚችም ዕለት በዓልን አደረጉለት።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

=>የካቲት 19 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ታላቁ አባ መርትያኖስ (በዝሙት ላለመሰናከል እግራቸውን በእሳት ያቃጠሉ አባት)

=>ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ገብርኤል ሊቀ መላእክት
2.ቅዱስ ኤስድሮስ ሰማዕት
3.አቡነ ዓቢየ እግዚእ ጻድቅ
4.አቡነ ስነ ኢየሱስ
5.አቡነ ዮሴፍ ብርሃነ ዓለም

=>+"+ . . . በእስራትና በወኅኒ ተፈተኑ:: በድንጋይ ተወግረው ሞቱ:: ተፈተኑ:: በመጋዝ ተሰነጠቁ:: በሰይፍ ተገድለው ሞቱ:: ሁሉን እያጡ መከራን እየተቀበሉ: እየተጨነቁ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ:: ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ: በዋሻና በምድር ጉድጉዋድ ተቅበዘበዙ:: +"+ (ዕብ. 11:36)

✞ ወስብሐት ለእግዚአብሔር ✞
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

✞✞✞ እንኩዋን ለጻድቁ "አቡነ ክፍለ ማርያም" እና ለሰማዕቱ ቅዱስ "ፊልሞን መዓንዝር" ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞

+*" አቡነ ክፍለ-ማርያም "*+

=>ኢትዮዽያዊው ጻድቅ አቡነ ክፍለ-ማርያም በሐዋርያዊ አገልግሎቱ የተመሠከረለት: ለበርካታ ዓመታት በጾምና በጸሎት በአቱን አጽንቶ የኖረ: ከቅድስናው የተነሳ መላዕክት ሰማያዊ ኅብስት ይመግቡት: ውሃም ከአለት ላይ ይፈልቅለት የነበረ አባት ነው::

+በዘመኑም ረሃብ ነበርና እርሷ ሳታውቀው እናቱን በረሃብ ጠውልጋ ቢያያት በጣም በማዘኑ እንዲባርከው ከቀረበለት የሰንበት ቁርስ ለእናቱ አድልቶ ብዙ ሰጣት:: በዚሕ ምክንያት መልዐኩም ሰማያዊ ኅብስቱን አስቀረበት: ምንጩም ደረቀች::

+ጥፋቱ የገባው አባ ክፍለ-ማርያም ለ11 ዓመታት ንስሃ ገብቶ እግዚአብሔር መልሶለታል:: ከብዙ የገድል ዓመታት በሁዋላም በዚህች ቀን ተሠውሯል::

+*" ቅዱስ ፊልሞን ሰማዕት "*+

=>ይህን ቅዱስ "ፊልሞን መዓንዝር" ብሎ መጥራቱ
የተለመደ ነው:: እርሱ በቀደመ ሕይወቱ አዝማሪ (ዘፋኝ)
ነበርና:: ዘፋኝነት (አዝማሪነት) ደግሞ በክርስትና
ከተከለከሉ ተግባራት አንዱና ዋነኛው በመሆኑ ዘፈን
(ሙዚቃ) መስማትም ሆነ ማድመጡ ኃጢአት ነው::

+ነገር ግን ሁሉ እንዲድን የሚፈቅድ ጌታችን ጥሪውን ወደ
ሁሉም ሰው በየጊዜው ይልካል:: ቅዱስ ፊልሞንም
የክርስቶስ ጥሪ የደረሰው በከንቱ የዘፋኝነት (የአዝማሪነት)
ኑሮ ውስጥ ሳለ ነው:: ነገሩ እንዲህ ነው:-

+በ3ኛው ክ/ዘ መጨረሻ (በ290ዎቹ) አርያኖስ የሚባል
ሹም በግብጽ (እንዴናው) ክርስቲያኖችን ጨፈጨፈ::
ባለማወቅም ክርስቶስን የሚያመልኩ ሚሊየኖችን በሰይፍ
በላቸው:: ከዚህ ድርጊቱ መልስ ደግሞ በጣዖቱ (አዽሎን)
ፊት እያስዘፈነ ከንቱነትን ይሰዋ : ይዝናናም ነበር::

+ከዘፋኞቹ መካከል ደግሞ ይህ ፊልሞን አንዱ ሆኖ
ለዘመናት በፊቱ ተጫወተለት:: አንድ ቀን ግን እንዲህ
ሆነ:: አስቃሎን የሚባል ቅዱስ ክርስቲያን ለጣዖት
እንዲሰዋ ታዘዘ::

+ይህ አስቃሎን (አብላንዮስም ይባላል) ወንድሙን
ፊልሞንን ያድነው ዘንድ ተጠበበ:: ወደ ፊልሞን ሒዶ "እኔ
ገንዘብ እሰጥሃለሁ:: የእኔን ልብስ ለብሰህ : እኔን መስለህ
ለጣዖት ሰዋልኝ" አለው:: አስቃሎን ይህንን ያለው
ለጥበቡ ሲሆን ፊልሞን ግን "ገንዘብ ካገኘሁ" ብሎ
የባልንጀራውን ልብስ ተሸፋፍኖ ወደ ጣዖቱ ፊት ቀረበ::

+ያን ጊዜ ተሸፍኖ መስዋዕት ማቅረብ ክልክል ነውና ሹሙ
አርያኖስ ግለጡት ሲል አዘዘ:: ቢገልጡት ፊልሞን ሁኖ
ተገኘ:: መኮንኑ ገርሞት "ምን እያደረክ ነው?" ቢለው "እኔ
ክርስቲያን ነኝ" ሲል አሰምቶ ተናገረ::

+ለጊዜው ሁሉም እየቀለደ መስሏቸው ነበር:: ፊልሞን
ግን ይህንን ያለው ከልቡ ነው:: ምክንያት በቅዱስ
አስቃሎን ልብስ ተመስሎ መንፈስ ቅዱስ ልቡን ለውጦለት
ነበር:: ተገልጦ ቀና ሲልም ቅዱሳን መላእክት ከበውት
አይቶ ልቡ ጸንቶለታል::

+ሹሙ አርያኖስም የቀልዱን እንዳልሆነ ሲያውቅ
"ታብዳለህ?" ቢለው ፊልሞን "ምን አብዳለሁ! ዛሬ ገና
ከእብደቴ ሁሉ ዳንሁ እንጂ" ሲል መልሶለታል:: አሕዛብ
ሁሉ እያዩም በዚያች ቅጽበት መንፈስ ቅዱስ በደመና
አምሳል ወርዶ አጥምቆታል::

+በሆነው ሁሉ የተበሳጨው ሹሙም ቅዱስ ፊልሞንን
ከክርስቶስ ፍቅር ይለየው ዘንድ ደበደበው : ገረፈው :
ጥርሱን አረገፈው : ደሙንም መሬት ላይ አፈሰሰው::
በዚህ ሁሉ ግን ጸና:: ቅዱስ አስቃሎንም ፈጥኖ መጥቶ
በመከራው መሰለው::

+በመጨረሻም 2ቱም ቅዱሳን በቀስት ተነድፈው ይገደሉ
ዘንድ ተፈረደባቸው:: ነገር ግን ለእነሱ የተወረወረ ቀስት
መንገዱን ስቶ የሹሙን (የአርያኖስን) ዐይን በማጥፋቱ
ወታደሮቹ በንዴት 2ቱንም ሰይፈው ገድለዋቸዋል::

+ዐይኑ የጠፋበት አርያኖስም ስቃዩ ሲበዛበትና
ከሚያመልካቸው የረከሱ ጣዖታት መፍትሔ ሲያጣ
ከቅዱሳኑ ደም ተቀባ:: ዐይኑም ፈጥኖ በራለት:: በዚህም
ምክንያት ምድራዊ ሹመቱን : ሃብት ንብረቱን : ትዳርና
ቤቱን : ጣዖት አምልኮውን ትቶ በክርስቶስ አምኖ
ለሰማዕትነት በቅቷል::

=>አምላከ ቅዱሳን በወዳጆቹ አማላጅነት
የምናስተውልበትን አዕምሮ አይንሳን:: በረከታቸውንም
ያድለን::

=>የካቲት 20 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.አቡነ ክፍለ-ማርያም ዘዲባጋ (የተሰወረበት)
2.አቡነ ገብረ-መርዐዊ ዘአግዶ (ኢትዮዽያዊ)
3.ቅዱስ ፊልሞን መዐንዝር (ከአዝማሪነት በክርስቶስ አምኖ ለሰማዕትነት የበቃ ቅዱስ ሰው)
4.ቅዱስ አስቃሎን አናጉንስጢስ (ሰማዕት)
5.ቅዱስ ዼጥሮስ ሊቀ ዻዻሳት (የታላቁ ሐዋርያዊ አትናቴዎስ ደቀ መዝሙር)

=>ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ቴዎድሮስ ሊቀ ሠራዊት (ሰማዕት)
2.ቅዱስ ዮሐንስ ሐፂር
3.ቅዱስ አክሎግ ቀሲስ
4.ቅዱስ አፄ ካሌብ ጻድቅ
5.አባ አሞንዮስ ዘሃገረ ቶና
6.ቅድስት ሳድዥ የዋሒት

=>+"+ ስትጦሙም እንደ ግብዞች አትጠውልጉ . . . አንተ ግን ስትጦም በስውር ላለው አባትህ እንጂ እንደ ጦመኛ ለሰዎች እንዳትታይ ራስህን ተቀባ: ፊትህንም ታጠብ:: በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ያስረክብሃል:: +"+ (ማቴ. 6:16)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
☞አርኬ ዘአባ መርትያኖስ (መነኮስ ኃያል) የካቲት ፲፱፦

ሰላም ለፍልሠተ ሥጋከ እምሃገረ አቴና ሰቂማ፤
ኀበ አንጾኪያ መካነ ሰማዕት እስመ ከማሁ ስማ፤
መርትያኖስ ኃያል ልቡሰ ዐቢይ ግርማ፤
በከመ አድኃንካ ለፎጢና እምነ ርጉም መስቴማ፤
ሥረይ ኃጢአታ ለነፍስየ ዘማ!

(ዝክረ ቅዱሳን ፥ ርቱዓነ ሃይማኖት)
ዝክረ ቅዱሳን ማኅበረ ቅዱስ ዳዊት

ዝክረ ቅዱሳንን ተማሩ ብለን እንለምናችኋለን!!

" ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"::/የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ) እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::
       አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ /መጽሐፈ ምሥጢር/
https://www.tg-me.com/zikirekdusn

በዩቲብለመከታተል👉https://www.youtube.com/@ZikereKedusan
2024/09/30 07:28:28
Back to Top
HTML Embed Code: