Telegram Web Link
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ፩ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡

=>+"+ እንኩዋን ለአበው "ቅዱሳን አባ አብርሃም ወአባ ገዐርጊ" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ +"+

+*" ቅዱሳን አብርሃም ወገዐርጊ "*+

+*" ተጋድሎተ ቅዱሳን "*+

=>ቅዱሳኑን የመሰሉ አባቶች "መስተጋድላን" ይባላሉ በግእዙ:: ለሃይማኖታቸው እስከ ደም ጠብታና እስከ መጨረሻዋ ህቅታ ድረስ መጋደላቸውን የሚያሳይ ነው:: መጋደል ጐዳናው ብዙ ዓይነት ነው::

+ከራሱ ጋር የሚጋደል አለ:: ከዓለም ጋር የሚጋደልም አለ:: የቅዱሳኑ ተጋድሎ ግን በዋነኝነት ከ2 አካላት ጋር ነው:: በመጀመሪያ ፍትወታት እኩያትን (ኃጣውዕን) ከሚያመጡ አጋንንት ጋር ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ "ሃይማኖቸታችሁን ካዱ: ለጣዖትም ስገዱ" ከሚሉ ከሃድያን ጋር የሚደረግ ትግል ነው::

+በተለይ 2ኛው እስከ ሞት የሚያደርስ ውሳኔን ይጠይቃል:: የዚህን ቅዱስ ሕይወት ለመረዳት ግን አንድ ነገርን ልብ እንድትሉልኝ እፈልጋለሁ::

+ያለንበት ዘመን ክርስትና በራድ (ቀዝቃዛ) በመሆኑ የቀደሙ አባቶች የጸና ተጋድሎ አንዳንዴ ግራ ሲያጋባን ተመልክቻለሁ:: ቅዱሳኑ ሁሌም አንድ ነገርን እያሰቡ ይኖራሉ:: ይኼውም በዘመኑ በርካቶቻችን የረሳነው: ወይም ማስታወስ የማንፈልገው ነገር ይመስላል::

+ሰማያዊው አምላክ ከዙፋኑ ወርዶ በተዋሐደው ሥጋ በቃል ሊገለጽ የማይችል መከራን ስለ እኛ ተቀብሏል:: ክርስትና ማለት ቀራንዮን በልብ ውስጥ መሳል ነው:: ፍቅረ መስቀሉን: የጌታንም ውለታ የሚያስብ ማንኛውም ሰው: የትኛውም ዓይነት መከራ ቢመጣበት አይታወክም::

+ቅዱሳኑም የፍቅራቸውና የትእግስታቸው ምሥጢር ይኼው ነው:: ጌታችን "የሚወደኝ ቢኖር የሞቱን መስቀል ተሸክሞ ይከተለኝ" (ማቴ. 16:18) እንዳለው ቅዱሳኑ ይህንን ቃል በቃል ሲፈጽሙት እነሆ እንመለከታለን::

+*" ገዳማዊ ሕይወት "*+

=>ገዳማዊ ሕይወት ጥንቱ ብሉይ ኪዳን ነው:: በቀዳሚነትም በደብር ቅዱስ አካባቢ ይኖሩ የነበሩ ደቂቀ ሴት እንደ ጀመሩት ይታመናል:: ሕይወቱ በጐላ: በተረዳ መንገድ የታየው ግን በታላቁ ጻድቅ ሄኖክ: ከዚያም በቅዱሱ ካህን መልከ ጼዴቅ አማካኝነት ነው::

+ቀጥሎም እነ ቅዱስ ኤልያስ ነቢይ: እነ ኤልሳዕ ደቀ መዝሙሩ ኑረውበታል:: በሐዲስ ኪዳን ደግሞ ሙሉ ሕይወቱን በገዳም (በበርሃ) ያሳለፈው መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ቅድሚያውን ይይዛል::

+ለስም አጠራሩ ስግደት ይሁንና መድኃኒታችን ክርስቶስ በገዳመ ቆረንቶስ ለ40 ቀናት በትሕርምት ኑሮ ገዳማዊ ሕይወትን ቀድሷል: አስተምሯል:: በዘመነ ስብከቱም ያድርባት የነበረችው የደብረ ዘይቷ በዓቱ (ኤሌዎን ዋሻ) በራሷ ለዚህ ሕይወት ትልቅ ማሳያ ናት::

+ከጌታ ዕርገት በሁዋላም ክርስቲያኖቹ የዓለም ሁካታ ሲሰለቻቸው: አንድም በንጹሕና በተሸከፈ ልቡና ለፈጣሪያቸው መገዛትን ሲሹ ከከተማ ወጣ እያሉ ይኖሩ እንደ ነበር የታሪክ መዛግብት ያሳያሉ:: አኗኗራቸውም በቡድንም: በነጠላም ሊሆን ይችላል::

+ዋናው ነገር ግን በጾምና በጸሎት መትጋታቸው ነው:: ይሕም ሲያያዝ እስከ 3ኛው መቶ ክ/ዘመን ደረሰ:: በዚህ ዘመን ግን አባ ዻውሊ የሚባል አንድ ንጹሕ ክርስቲያን ይሕንን ሕይወት ወደ ሌላ ደረጃ ከፍ አደረገው:: ለ80 ዓመታት ሰው ሳያይ ተጋድሎ "የባሕታውያን አባት" ተባለ:: ደንብ ያለው ተባሕትዎም ጀመረ::

+ይህ ከሆነ ከ20 ዓመታት በሁዋላ ደግሞ አባ እንጦንስ የሚባሉ ደግ ክርስቲያን ይህንን ገዳማዊ ሕይወት በሌላ መንገድ አጣፈጡት:: በቅዱስ ሚካኤል አመንኩዋሽነት ገዳማዊ ሕይወት በምንኩስና ተቃኘ:: ስለዚህም አባ እንጦንስ የመነኮሳት አባት ተባሉ::

+እርሳቸውም ሕይወቱን ለማስፋፋት ከተለያዩ አሕጉር ደቀ መዛሙርትን እየተቀበሉ አመንኩሰዋል:: ቅዱሳን የአባ እንጦንስ ልጆችም ወደየ ሃገራቸው ተመልሰው: ሕይወቱን በተግባር አሳይተው ገዳማዊነትን አስፋፍተዋል::

+አባ እንጦንስ አባ መቃርስን: አባ መቃርስ አባ ዮሐንስን ወልደዋል:: አባ ዮሐንስም የታላቁ ገዳመ አስቄጥስ አበ ምኔት ሆነው በጸጋ አገልግለዋል:: አስቄጥስ በምድረ ግብጽ የሚገኝ: በስፋቱና ብዙ ቅዱሳንን በማፍራቱ ተወዳዳሪ የሌለው የዓለማችን ቁጥር አንድ ገዳም ነው::

+ሕይወተ ምንኩሰናም ወደ መላው ዓለም የተስፋፋ በዚህ ገዳም መናንያን አማካኝነት ነው:: በዚህ ገዳም ላይ የሚሾሙ አበው ደግሞ በብዛት መንፈስ ቅዱስ ያደረባቸውና አባታቸውን ቅዱስ መቃርስ ታላቁን የመሰሉ ናቸውና ኃላፊነቱ እጅግ ከባድ ነው::

+በ5ኛው መቶ ክ/ዘመን በምድረ ግብጽ ተወልደው ያደጉት አባ ዮሐንስ ከመነኑባት ዕለት ጀምረው በፍጹም ተጸምዶና ተጋድሎ ለፈጣሪያቸው ስለ ተገዙ የታላቁ ገዳም አበ ምኔት ሊሆኑ ተገባቸው::

+በአበ ምኔትነት ዘመናቸውም መንጋውን ይጠብቁ ዘንድ ብዙ ደከሙ:: በተለይ ቅዱስ ቃሉን ያስተምሩ ዘንድ ተጉ:: ሕይወተ መላእክትንም ያሳዩ ዘንድ በቃል ብቻ ያይደለ በተግባር ሆነው : ከመንፈሳዊ አብራካቸው ብዙ ቅዱሳንን ወለዱ::

+ከዋክብቱ አባ ገዐርጊ: አባ አብርሃም: አባ ሚናስ: አባ ዘካርያስ . . . የአባ ዮሐንስ ፍሬዎች ናቸውና:: ጻድቁ በዘመናቸው ብዙ ተአምራትን ሠርተዋል:: ከዕረፍታቸው በሁዋላ እንኩዋ መግነዛቸውና የልብሳቸው እራፊ ብዙ ድውያንን ፈውሷል::

+*" ቅዱሳን አብርሃም ወገዐርጊ "*+

=>እነዚህ 2 ቅዱሳን በግብጽ በርሃ ያበሩ የቅዱሱ አባ ዮሐንስ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቹ ናቸው:: አስቀድሞ ወደ በርሃ የወጣ አባ አብርሃም ሲሆን እርሱም በምድረ ግብጽ የተባረኩ ሰዎች ልጅ ነው::

+ወላጆቹ በፈቃደ እግዚአብሔር እርሱን ከወለዱ በሁዋላ ብዙ በጐነትን አሳይተዋል:: ዘመኑ ዘመነ ዐጸባ (የችግርና የረሃብ ጊዜ) ነበርና ሃብታቸውን በምጽዋት ጨርሰዋል:: የሚገርመው የቅዱሱ አባት "ነዳያን እየተራቡ ዝም አልልም" ብሎ እየተበደረ ያበላቸው ነበር::

+እርሱ ባረፈ ጊዜም የተባረከች ሚስቱ መልካምን እየሠራች ብዙ ተፈትናለች:: ለባርነት ተማርካ እስክትሔድ ድረስም ታግሣለች:: ቅዱሱን ልጇን አብርሃምንም እንደሚገባ አሳድጋ "ሚስት ላጋባህ" አለችው::

+እርሱ ግን "እናቴ ሆይ! እኔ ይህንን ዓለም አልፈልገውም" ሲል መለሰላት:: ይህንን ስትሰማም ሐሴትን አድርጋ አብርሃምን ወደ በርሃ ሸኘችው:: አባ አብርሃምም ወደ ገዳመ አስቄጥስ ሔዶ በደብረ አባ መቃርስ መነኮሰ:: ተጋድሎንም በዚያው ጀመረ::

+ሲጾም: ሲጸልይ: ሲጋደልም ዘመናት አለፉ:: በዚህ ጊዜም ታላቁ አባ ገዓርጊ ከዓለም ወደ በርሃ መጥቶ መነኮሰ:: የአባ ዮሐንስ የመንፈስ ልጆች ውስጥም እንደ አንዱ ተቆጠረ:: አባ ገዐርጊን የተመለከተው አባ አብርሃምም ስለ ወደደው አብረው መኖር ጀመሩ::

+2ቱ ቅዱሳንም "በግቢግ" በምትባል በዓታቸው በፍቅር ለፈጣሪያቸው ሲገዙ ዘመናት አለፉ:: በነዚህ ዘመናትም በርካታ ቅዱሳን ከመንፈሳዊ አብራካቸው አፈሩ ከቅድስናቸው ብዛትም ከሰንበት በቀር እህልን አይቀምሱም ነበር::

+የክብር ባለቤት መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም አንድ ቀን ከዓለት በተወቀረች በዓታቸው ውስጥ በጸሎት ላይ ሳሉ ወረደላቸው:: የበዓታቸውን ዓለት ሰንጥቆ ሲገባ ታላቅ ግርማና ብርሃን አካባቢውን ዋጠው:: ቅዱሳኑም ለመድኃኒታችን ተደፍተው ሰገዱ::

+እርሱ አነጋግሯቸው: ባርኩዋቸው ዐርጉዋል:: ለምልክትም በዓታቸው እንደ ተሰነጠቀ ቀርቷል:: ዘወትርም በዕለተ ሰንበት ይገለጥላቸው ነበር:: ቅዱሳን አባ ገዐርጊና አባ አብርሃም በርካታ ተአምራትን ሲሠሩ ኑረዋል::
+አባ አብርሃም ጥር 9 ቀን ሲያርፉ አባ ገዐርጊ ግንቦት 18 ቀን ዐርፎ ተቀብሯል:: በዓታቸው በግቢግም ዛሬ ድረስ በምድረ ግብጽ አለች::

=>አምላከ ቅዱሳን አበው በፍቅሩ ይገለጥልን:: ከአባቶቻች ጸጋ በረከትም አይለየን::

=>ጥር 9 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.አባ አብርሃም ገዳማዊ
2.አባ ገዐርጊ ጻድቅ
3.ቅዱስ ዲዮስቅርስ ዘሮሜ
4.አባ ኪናፎርያ

=>ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱሳን 318ቱ ሊቃውንት
2.አባ በርሱማ ሶርያዊ (ለሶርያ መነኮሳት ኁሉ አባት)
3.አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ
4.የብሔረ ብፁዐን ጻድቃን
5.አባ መልከ ጼዴቅ ዘሚዳ
6.ቅዱስ ዞሲማስ ጻድቅ

=>+"+ በረከት በጻድቅ ሰው ራስ ላይ ነው:: የኀጥአንን አፍ ግን ግፍ ይከድነዋል:: የጻድቅ መታሰቢያ ለበረከት ነው:: የኀጥአን ስም ግን ይጠፋል:: +"+ (ምሳሌ 10:6)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ፩ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞

እንኩዋን "ለጾመ ገሃድ" እና "አባ ታውብንስጦስ" ዓመታዊ የእረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ

+*" ጾመ ገሃድ "*+

=>ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በአዋጅ ምዕመናን እንዲጾሟቸው የሠራቻቸው 7 አጽዋማት አሏት:: "ጾም" ማለት "መከልከል" ነው:: የምንከለከለው ደግሞ ከኃጢአትና ከክፋት ሲሆን አንድም ሰውነትን ወደዚያ ከሚወስዱ መባልዕት መከልከልን ይመለከታል::

+"7ቱ" አጽዋማት:-
1.ዓቢይ ጾም
2.ጾመ ፍልሠታ
3.ጾመ ሐዋርያት
4.ጾመ ነቢያት
5.ጾመ ድኅነት
6.ጾመ ነነዌ እና
7.ጾመ ገሃድ ይሰኛሉ::

+በእነዚህ አጽዋማት ከዓቢይ ጾም በቀር እስከ 9 ሰዓት ድረስ መጾም ይገባል:: ዓቢይ ጾም ግን የተለየ ሥርዓት አለውና ይቆየን:: ስለ ጾም ሲነሳ አስቀድሞ የሚመጣው ጥያቄ አስፈላጊነቱ ነው:: "ጾም ለምን ያስፈልጋል?" ብሎ ከመጠየቅ "ሃይማኖት ለምን ያስፈልጋል?" ብሎ መጠየቁ ይቀላል::

+ምክንያቱም ከሃይማኖታዊ ትዕዛዛት ትልቁ በመሆኑ እርሱን መቃወም ሃይማኖትንና አዛዡን እግዚአብሔርን መቃወም ነውና:: እኛ ሃገር ላይ የተለመደች ክፉ ልማድ አለች:: የከበደችንን ነገር "አያስፈልግም" በሚል እንከራከራለን::

+ደግሞ ጾምን ለመሻር ጥቅስ የሚጠቅሱ ወገኖች በጣም ይገርሙኛል:: ኃጢአትን ለመሥራት: ጾምንም ለመሻር ጥቅስን መጥቀስ አያስፈልግም:: እኛ ግን ከፈጣሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጀምሮ (ማቴ. 4:2) አበው ቅዱሳን ጾመው (ዘዳ. 9:19, ነገ. 19:8, ሐዋ. 13:3, ቆሮ. 4:11) አሳይተውናልና እንደ አቅማችን እንጾማለን::

=>"ገሃድ" የሚለው ቃል በቁሙ "መገለጥን : መታየትን : ይፋ መሆንን" የሚያመለክት ሲሆን በምሥጢሩ ግን "የማይታይ አምላክ መታየቱን : የማይዳሰሰው መዳሰሱን" ያመለክታል::

+ወይም በሌላ ልሳን ወልደ እግዚአብሔር ከድንግል ማርያም በተዋሕዶ ሰው ከሆነ በሁዋላ ለ30 ዓመታት ራሱን ሳይገልጥ ቆይቶ ነበርና በ30 ዓመቱ ራሱን ለእሥራኤል በዚህ ሰሞን መግለጡን ልብ የምንልበት በዓል ነው::

+መድኃኒታችን ሁሉን ነገር የሚሠራው በጊዜው ነውና ከሥጋዌው በሁዋላ ለ30 ዓመታት: ከስደት መልስ ደግሞ ለ25 ዓመታት የሰውነቱን ምሥጢር በይፋ ሳይገልጥ ቆይቷል:: ያም ሆኖ የሰውነቱን ምሥጢር እርሱ: የባሕርይ አባቱና ቅዱስ መንፈሱ ለድንግል ማርያም ገልጠውላት ታውቀው ነበር:: እርሷ ግን መዝገበ ምሥጢር ናትና ሁሉን ነገር በልቧ ትጠብቀው ነበር:: (ሉቃ. 2:52)

+መድኃኒታችን ከሥጋዌው (ሰው ከሆነባት) ደቂቃ ጀምሮ መግቦቱን አላቁዋረጠም:: ምንም በግዕዘ ሕጻናት ቢኖርም እርሱ በዘባነ ኪሩብ የሚሠለስ ቸር ጌታ ነውና መግቦናል::

+እንደ እሥራኤል ባህል 30 ዓመት በሞላው ጊዜ ግን ሥግው አምላክ መሆኑን ገለጠ:: የተገለጠውም በጥምቀቱ ሲሆን በዕለቱ ከአብ: ከመንፈስ ቅዱስ የባሕርይ ልጅነቱን አስመስክሯል:: በባሪያው በዮሐንስ እጅም ተጠምቆ ሥርዓተ ጥምቀትን ሠርቶልናል::

+የእዳ ደብዳቤአችን ቀዶ ልጅነታችንን መልሶልናል:: ይህ ሁሉ የተደረገ ለእኛ ነውና በዓለ ኤዺፋንያን (እለተ አስተርእዮቱን) በድምቀት እናከብራለን::

+ነገር ግን ልክ በቅርብ ጊዜ እያየነው እንደሚገኘው በዘፈንና ከአምልኮ ባፈነገጠ መንገድ እንዳይሆን ቤተ ክርስቲያን አበክራ ታሳስባለች:: የመድኃኒታችንን የማዳን ሥራ ከማዘከርና ለእርሱ ከመገዛት ይልቅ ራስን ዘፈን በሚመስል መዝሙር መቃኘቱና ለልብስ ፋሽን መጨነቁ የሚጠቅም አይደለም::

+በዓላት በሚዲያ ታዩ: ተመዘገቡ ብለን ከመዝናናት ትውፊታችንን እያጠፉ ያሉ ድርጊቶቻችን ብንታዘባቸውና ብናርማቸው ይመረጣል:: ስኬታችን ሁሉም ክርስቲያን ለእግዚአብሔር መንግስት መብቃቱ እንጂ በዓል አከባበራችን ዝነኛ መሆኑ አይደለም::

+ጉዳዩ መለኮታዊ እንጂ ፓለቲካዊ አይደለምና ጥንቃቄን ይሻል:: ዛሬ ለታቦተ እግዚአብሔር ክብርን የማይሰጥና ተጋፊ ትውልድን እየፈጠርን ነው:: ካህናትን አለመስማትና ታቦታትን አግቶ አላስገባም ማለት በክርስትና ትርጉሙ ከሰይጣን መወዳጀት ነው:: ስለዚህም በዓል አከከባበራችንን እንታዘብ:: ደግሞም እናርመው::

+*" ጾመ ገሃድ "*+

=>ቤተ ክርስቲያን ጾመ ገሃድን የደነገገች ለ3 ምክንያት ነው:-

1.የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን መገለጥ በጥሙና እያሰብን በጾም እንድናመልከው::
2.በዓል አከባበራችን እንደ አሕዛብ በተድላ ሥጋ: በመብልና በመጠጥ ብቻ እንዳይሆንና ሰውነታችንን በጾም እንድንገራው::
3.ልደትና ጥምቀት ረቡዕና ዐርብ ሲውሉ እህል በነግህ (በጧት) መቀመስ ስላለበት የእርሱ ቅያሪ (ተውላጥ) እንዲሆን ነው::

+ጾመ ገሃድን የሠሩት አባቶቻችን ቅዱሳን ሐዋርያት ሲሆኑ ያጸኑት ደግሞ ቅዱሳን ሊቃውንት ናቸው:: አጿጿሙም ጥምቀት ከማክሰኞ እስከ ቅዳሜ ከዋለ በዋዜማው "እስከ ይሠርቅ ኮከብ" እንዲሉ አበው እስከ ምሽት 1 ሰዓት ድረስ ይጾማል::

+በዓለ ጥምቀት እሑድ ሲሆን ዐርብን አዘክሮ: በዕለተ ቅዳሜ ደግሞ ከጥሉላት ተከልክሎ መዋል ይገባል:: በመሳሳይ ሰኞ ቢውል ዐርብን አዘክሮ: ቅዳሜና እሑድን ከጥሉላት (ከሚያገድፉ ምግቦች) ሁሉ ተከልክሎ መዋል ይገባል::

+ከ7ቱ አጽዋማት አንዱ ነውና የተለየ ግለሰባዊ ችግር እስከሌለ ድረስ ሊጾም ግድ ይላል:: ችግር ካለ ደግሞ ከንስሃ አባት ጋር ሊመክሩ ይገባል::

+*" አባ ታውብንስጦስ ዘሲሐት "*+

=>በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን በሮም የተነሳ
+ከልጅነቱ መጻሕፍትን የተማረ:
+በክህነት አገልግሎቱ ለብዙዎች አባት የሆነ:
+በምናኔ ወደ ግብጽ የወረደ:

+በእስክንድርያ አካባቢ አበ ምኔት ሆኖ ብዙ መነኮሳትን የመራ::
+በዘመነ ሰማዕታት የተሰደደ:
+ብዙ አሕጉራትን ዞሮ ያስተማረ:

+በትምሕርተ ክርስቶስ ያላመኑትን አሳምኖ : ያመኑትን ያጸና:
+ሽፍቶችን እየገሠጸ ለንስሃ ያበቃ የነበረ ታላቅ አባት ነው::

+በዘመነ ሰማዕታት ስደትን ታግሦ: በሁዋላም በደብረ ሲሐት ተወስኖ ኑሯል:: በዚህች ቀንም በመልካም ሽምግልና ዐርፏል::
=>አምላከ ቅዱሳን ፍቅሩን: ምሥጢሩን ይግለጥልን:: ከጾመ ገሃድ በረከትም አይለየን::

=>ጥር 10 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

1.ጾመ ገሃድ
2.አባ ታውብንስጦስ ዘሲሐት
3.ቅዱስ ኪናርያ
4.ቅድስት ጠምያኒ

=>ወርሐዊ በዓላት

1.ቅዱስ ናትናኤል ሐዋርያ
2.ቅዱስ ኒቆላዎስ ዘሃገረ ሜራ
3.አቡነ መልክዐ ክርስቶስ
4.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ወልደ እልፍዮስ)
5.ቅድስት ዕሌኒ ንግስት
6.ታላቁ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ
7.ቅዱስ እፀ መስቀል

=>+"+ እነርሱ እሥራኤላውያን ናቸውና:: ልጅነትና ክብር: ኪዳንም: የሕግም መሰጠት: የመቅደስም ሥርዓት: የተስፋውም ቃላት ለእነርሱ ናቸውና:: አባቶችም ለእነርሱ ናቸውና:: ከእነርሱም ክርስቶስ በሥጋ መጣ:: እርሱም ከሁሉ በላይ ሆኖ ለዘላለም የተባረከ አምላክ ነው:: አሜን:: +"+ (ሮሜ. 9:4)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
....✣...✣.....ከተራ .....✣....✣... ከተራራ ማለት ከተረ ከተረ ከበበ  አጠረ አገደ አቆመ ከሚለው የግዕዝ ቃል የተገኘ ሲሆን  ከተራራ ማለት ማገድ ማቆም መክብብ ማጠር ማለት ነው ።
.......✣........✣......✣......

@@✣@@@✣@@@✣@@@@✣@@✣@@@@✣@@
.......✣.........✣........✣.....
ከተራ ስንል ሁለት ነገሮችን ለማሳታዎስ ነው

@@✣@@@✣@@@@✣@@✣@@@✣@@@@✣@@
..........✣........✣......✣.......
አንደኛ በክርስቶስ ጥምቀት ጊዜ የተደረገውን የታሪክ ክንዋኔ ለማስታወስ ነው ።

ክርስቶስ ሲጠመቅ  ነቢዩ ዳዊት " ባሕርኒ ርእየት ወጎየት ወዮርዳኖስኒ ገብአት ድኅሬሁ፦ባሕርይ አይታህ ሸሸች ዮርዳኖስስም ወደኋላ ተመለሰ " ብሎ እንደተናገረ መዝ ፻፲፫
ዮርዳኖስ ከሁለት ተከፍሎ ቁሞ ነበርና የዮርዳኖስ ውሃ መቆሙን ለማስታወስ  "ከተራ" ክርስቶስ ሲጠምቅ ሰማያውያን መላእክት  ምድራውያን ዓሣ አንበሬዎች አዞት ጉማሬዎች ለማመስገን ለምስጋና ከበውት ቁመው ነበር ዮርዳኖስ ከዚህ በፊት የበጎች መኛ የነበረ ሲሆን አሁን ግን ውቅያኖስን የፈጠረው አምላክ ሲጠመቅ ዮርዳኖስ በብርሃን ተከባ ስለነበር"ከተራ" እንለዋለን ።


@@✣@@✣@@@@✣@@@✣@@✣@@@@@✣@@
........✣......✣..............✣....
ሁለተኛ ለጥር ዓሥራ አንድ ቀን  የበረከተ ጥምቀት መጠመቂያ ውሃ
በገጠር ያሉ ክርስቲያኖች ወራጁን ውሃ ገድበው፥ አቁመው ፥ከትረው
በከተማ የሚኖሩ ክርስቲያኖች እንደ ጃንሜዳ እንደ ጎንደር በሰው ሠራሺ ገንዳዎች ውሃ አቁረው የሚያመሹበት ቀን ስለሆነ ከተራ በማለት እናስታውሳለን ።

@@✣@@@✣@@@✣@@@@✣@@✣@@@@✣@@
.......✣.......✣........✣........
ታቦታቱ ከመንበረ ክብራቸው ተነሥተው ወደ ባሕረ ጥምቀቱ  መሄዳቸው " አሚሃ መጽአ እግዚእ ኢየሱስ እምገሊላ ውስተ ዮርዳኖስ ፦ያን ጊዜ ክርስቶስ ከዮሐንስ ሊጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መጣ"ብሎ እንደተናገረ  ማቴ ፫÷፲፫ 

@@✣@@@✣@@@@✣@@@✣@@✣@@@✣@@@
........✣.....✣......✣............
ታቦታቱ ከቤተክርስቲያን ተነሥተው ወደ ባሕረ ጥምቀት መሄዳቸው ክርስቶስ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ የመሄዱ ምሳሌ ነው ።

@✣@@✣@@@@✣@@@
@@✣@@@@✣@@@✣@
..........✣......✣..........✣......
ታቦታቱ የክርስቶስ ምሳሌዎች ናቸው። ታቦቱን የተሸከሙ ካህናት የዮሐንስ መጥምቅ ምሳሌዎች ናቸው ።



@@✣@@@@✣@@@✣@@@@@@✣@@@@✣@✣
........✣..............✣.............✣
ታቦቱን አክብረው የሚሄዱ ካህናት የዮሐንስ መጥምቅ ደቀመዛሙርት ምሳሌዎች ናቸው ምእመናንን ከዮሐንስ ለመጠመቅ ሲሄዱ የነበሩ ምእመናን ምሳሌ ናቸው በዋዜማው መውረዳችን ክርስቶስ ወደ ዮርዳኖስ የሄደው በዋዜማው ነበርና የዚያ ምሳሌ ነው።
ድንኳን ጥለን ማደራችን ከዮሐንስ ለመጠመቅ የሚመጡት ምእመናንን ድንኳን ጥለው አጎበር ተከለው በዮርዳኖስ ዙሪያ ያድሩ ነበርና የዚያ ምሳሌ ሲሆን ከድንኳኑ ውጭ ሲጸልዩ እና ውርጩን ታግሰሠው ሲዘምሩ የሚያድሩ ምእመናን ክርስቶስ ተራው እስኪደርስ ድረስ እየጠበቀ  እርሱ ሲጠመቅ የነበረውን የክረምት ብርድና ቅዝቃዜውን ታሦ የማደሩ ምሳሌ ነው ።
......................................
እንኳን ለ፳፻፲፮ ለከተራ በዓል በሰላም አደረሳችሁ !!!
............................................
መምህር ናትናኤል ባየ የብሉይ እና የሐዲስ መምህር የሊቅ ደቀመዝሙር
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ
እንኳን ለመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓመታዊ የጥምቀት በዓል (ኤጲፋንያ) በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

በዓለ ኤጲፋንያ

††† "ኤጲፋንያ" የሚለው ቃል ከግሪክ (ጽርዕ) ልሳን የተወሰደ ሲሆን በቁሙ "አስተርእዮ: መገለጥ" ተብሎ ይተረጐማል:: በነገረ ድኅነት ምሥጢር ግን ኤጲፋንያ ማለት "የማይታይ መለኮት የታየበት: እሳተ መለኮት በተዋሐደው ሥጋ የተገለጠበት" እንደ ማለት ነው::
"ዘኢያስተርኢ ኅቡዕ እስመ አስተርአየ ለነ::
እሳት በላዒ አምላክነ::" እንዲል:: (አርኬ)

አንድም: ምሥጢር ሆኖ የቆየ አንድነቱ: ሦስትነቱ የተገለጠበት ቀን ነውና ዕለተ ጥምቀቱ ኤጲፋንያ ይሰኛል:: መድኃኒታችን ክርስቶስ አዳምንና ልጆቹን ያድን ዘንድ ከሰማያት ዙፋኑ ወርዶ: እንደ ሰውነቱ በሥጋ ማርያም ለ33 ዓመታት ተመላልሷል::

ጊዜው ሲደርስም በፈለገ ዮርዳኖስ: ከዮሐንስ ዘንድ ሊጠመቅ ሔደ:: መድኃኒታችን ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ የወረደው ጥር 10 ቀን አመሻሽ ላይ ሲሆን በፍጹም ትሕትና ተራ ሲጠብቅ አድሮ ሌሊት 10 ሰዓት ላይ ደረሰውና ሊጠመቅ ቀረበ::

አሥር ሰዓት መሆኑም ርግብ (መንፈስ ቅዱስ) ሲወርድ ሰዎች ሥጋዊት ርግብ ናት ብለው እንዳይጠራጠሩ ነው:: ርግብ በሌሊት መንቀሳቀስ አትችልምና::

መድኃኒታችን ወደ ቅዱስ ዮሐንስ ሲጠጋ አምላክነቱን ተረድቶ "እንዴት ፈጣሪየ ወደ እኔ ትመጣለህ? እንዴትስ በእኔ እጅ ትጠመቃለህ?" አለው:: ትህትና ለእናትና ልጅ ልማዳቸው ነውና:: ጌታ ግን "ጽድቅን ሁሉ ልንፈጽም ይገባል" ሲል እንዲያጠምቀው ፈቀደለት::

ቅዱስ ዮሐንስም "ስመ አብ በአንተ ሕልው ነው:: ስመ ወልድ ያንተ ነው:: ስመ መንፈስ ቅዱስም በአንተ ዘንድ ሕልው ነው:: በማን ስም አጠምቅሃለሁ?" ሲል ጠየቀው::

ጌታ "ወልዱ ለቡሩክ ከሣቴ ብርሃን ተሣሐለነ:: አንተ ካህኑ ለዓለም በከመ ሲመቱ ለመልከ ጼዴቅ" እያልክ አጥምቀኝ አለው:: ትርጉሙም "የቡሩክ አብ የባሕርይ ልጁ : ብርሃንን የምትገልጥ ሆይ ይቅር በለን! አንተ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት የዓለም ካህኑ ነህና" እንደ ማለት ነው::

ከዚያም ጌታ ወደ ዮርዳኖስ ሲገባ ባሕር አይታ ደነገጠች : ሸሸችም:: (መዝ. 76:16, 113:3) ዮርዳኖስ ጨንቆት ግራ ቀኝ ተመላለሰ:: እሳተ መለኮት ቆሞበታልና ውኃው ፈላ:: በጌታ ትዕዛዝ ግን ጸና::

ጌታ ተጠምቆ: ሥርዓተ ጥምቀትን ሠርቶ: ዮርዳኖስን ብርህት ማሕጸን አድርጐ: የእዳ ደብዳቤአችንንም ቀዶ ከወጣ በኋላ ሰማያት ተከፈቱ:: ማለትም አዲስ ምሥጢር ተገለጠ::

አብ በደመና ሆኖ "የምወደው: የምወልደው: ሕልው ሆኜ ልመለክበት የመረጥኩት የባሕርይ ልጄ ይህ ነው!" ሲል በአካላዊ ቃሉ ፍጹም ተዋሕዶን መሰከረ:: መንፈስ ቅዱስም በአምሳለ ርግብ ወርዶ በራሱ ላይ ተቀመጠ:: ራሱንም ቆንጠጥ አድርጐ ያዘው:: በዚህም የሥላሴ አንድነቱ: ሦስትነቱ ታወቀ: ተገለጠ::

ቅዱስ ዮሐንስ "መጥምቀ መለኮት" የሚባልበትን ታላቁን ክብር ሲያገኝ ዮርዳኖስ የልጅነት መገኛ ቅዱስ ባሕር ሆነ::

<<< ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ >>>

ቅዱስ ወንጌል ላይ ቅዱስ ሉቃስ "ዘካርያስ ካህኑና ቅድስት ኤልሳቤጥ በሰውና በእግዚአብሔር ፊት ያለ ነቀፋ የሚኖሩ ጻድቃን ነበሩ" ይላቸዋል:: (ሉቃ. 1:6)

እሊህ ቅዱሳን ባልና ሚስት ግን መካኖች በመሆናቸው ልጅ ሳይወልዱ ዘመናቸው አልፎ ነበር:: እንደ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት ዕድሜአቸው የኤልሳቤጥ 90 የዘካርያስ ደግሞ 100 ደርሶ ነበር::

ፍጹም መታገሳቸውን የተመለከተ ጌታ ግን በስተ እርጅናቸው ከሰው ሁሉ በላይ የሆነ: ትንቢት ለብቻው የተነገረለት (ኢሳ. 40:3, ሚል. 3:1) ታላቅ ነቢይን ይሰጣቸው ዘንድ መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤልን ላከላቸው::

ቅዱስ ዘካርያስ ሰው ነውና ከደስታ ብዛት በመከራከሩ ድዳ ሆነ:: ቅድስቲቷ ግን መስከረም 26 ቀን ታላቁን ሰው ጸንሳ ለ6 ወራት ራሷን ሠወረች:: በ6ኛው ወር የፍጥረት ሁሉ ጌታ በተጸነሰ ጊዜ የአርያም ንግሥት ድንግል እመቤታችን ደጋ ደጋውን ወደ ኤልሳቤጥ መጣች:: ሁለቱ ቅዱሳት የእህትማማች ልጆች ናቸው::

የአምላክ እናቱ ስትደርስና "ሰላም" ስትላቸው መንፈስ ቅዱስ በእናትና ልጅ ወርዶ ኤልሳቤጥ በምስጋና: ዮሐንስ ደግሞ ገና በማሕጸን ሳለ በደስታ ዘለለ (ሰገደ):: ከዚህ በኋላ ሰኔ 30 ተወልዶ: አባቱ ዘካርያስ "ዮሐንስ" ሲለው አንደበቱ ተፈትቶለታል::

ቅዱስ ዮሐንስ ከተወለደ 2 ዓመት ከ6 ወር በሆነው ጊዜ ሰብአ ሰገል በመምጣታቸው በእሥራኤል ምድር የሚገኙ ሕፃናትን ሔሮድስ ቁዝ አስፈጀ:: ትንሽ ቆይቶም አይሁድ ለሔሮድስ ስለ ቅዱሱ ሕፃን ነገሩት:: "ሲጸነስ የአባቱን አንደበት የዘጋ: ሲወለድ ደግሞ የከፈተ 'ዮሐንስ' የሚባል ሕፃን አለና እሱንም ግደል" አሉ::

እናቱ ቅድስት ኤልሳቤጥ ይዛው ስትሸሽ ካህኑን ዘካርያስን ግን በቤተ መቅደስ መካከል ገድለውታል:: አረጋይት ኤልሳቤጥም ሕፃኑን እያሳደገች በገዳመ ዚፋታ ለ3 (5) ዓመታት ቆይታለች:: ቅዱስ ዮሐንስ 5 (7) ዓመት ሲሞላው ግን እዚያው በበርሃ እናቱ ዐረፈች:: ከሰማይ ዘካርያስና ስምዖን ወርደው ቀበሯት::

ሕፃኑ ዮሐንስ ሲያለቅስ ድንግል ማርያም ስንት አገር አልፋ ሰማችው:: እርሷም ስደት ላይ ነበረችና:: ከጌታ ጋር በደመና ሒደው ድንግል አቅፋ አጽናናችው:: ጌታንም "እንውሰደው ይሆን?" አለችው:: ጌታችን ግን "ለአገልግሎት እስክጠራው እዚህ ይቆይ" አላት:: ባርካው: አጽናንታውም ተለያዩ::

ቅዱስ ዮሐንስ ከዚህ በኋላ በዚያ ቆላ የግመል ጠጉር ለብሶ: ጠፍር ታጥቆ ተባሕትዎውን ቀጠለ:: ለ25 (23) ዓመታትም በንጽሕና ሲኖር ከምድር አራዊትና ከሰማይ መላእክት በቀር ማንንም አላየም:: ይሕችን ዐመጸኛ ዓለምም አልቀመሳትም::

ከዚህ በኋላ 30 ዘመን ሲሞላው እግዚአብሔር ከሰማይ ተናገረው:: "ሒድ! የልጄን ጐዳና ጥረግ" አለው:: ነቢያት ስለዚህ ነገር ተናግረው ነበርና:: (ኢሳ. 40:3, ሚል. 3:1) አባቱ ዘካርያስም "ወአንተኒ ሕፃን ነቢየ ልዑል ትሰመይ: እስመ ተሐውር ቅድመ እግዚአብሔር ከመ ትጺሕ ፍኖቶ" (ሉቃ. 1:76) ብሎ መንገድ ጠራጊነቱን ተናግሮ ነበርና::

ቅዱስ ዮሐንስ በዚያ ጊዜ በኃይለ መንፈስ ቅዱስ እየገሰገሰ ከበርሃ ወደ ይሁዳ መጣ:: ያዩት ሁሉ ፈሩት: አከበሩት:: ቁመቱ ቀጥ ያለ: ጽሕሙ እንደ ተፈተለ ሐር የወረደ: ጸጉሩ የቁራ ያህል የጠቆረ: መልኩ የተሟላ: ግርማው የሚያስፈራ ገዳማዊ ነውና::

ፈጥኖም ሕዝቡን ለንስሐ ሰበከ: ለንስሐም በርካቶችን አጠመቃቸው:: በዚህ አገልግሎት ለ6 ወራት ቆይቶ ጌታችን ወደ እርሱ ዘንድ መጣ:: ዮሐንስ ሰማይን ከነግሱ: ምድርን ከነልብሱ የያዘ ፈጣሪ "አጥምቀኝ" ብሎ ሲመጣ ደነገጠ:: የሚገባበትም ጠፋው::

"እንቢ ጌታየ! አንተ አጥምቀኝ" አለው:: ጌታ ግን "ፈቅጄልሃለሁ" አለው: አጠመቀው:: በዚህ ምክንያት ይሔው እስከ ዛሬም "መጥምቀ መለኮት" ሲባል ይኖራል:: ቅዱስ ዮሐንስ በመጨረሻ ሔሮድስን ገሰጸው:: ንጉሡም ተቀይሞ ለ7 ቀናት አሠረው::

ልደቱን ባከበረ ጊዜ ወለተ ሔሮድያዳ በዘፈን አጥምዳ አስማለችው:: እርሱም የታላቁን ነቢይ ራስ አስቆርጦ በወጪት አድርጐ ሰጣት:: አበው "እምሔሶ ለሔሮድስ ይብላዕ መሐላሁ - ሔሮድስ መሐላውን በበላ በተሻለው ነበር" ይላሉ:: የቅዱስ ዮሐንስ ራሱ በርራ ስትሔድ አካሉን ግን ደቀ መዛሙርቱ ቀብረውታል:: (ማቴ. 3:1, ማር. 6:14, ሉቃ. 3:1, ዮሐ. 1:6)
=>"አስማተ-ዮሐንስ መጥምቅ /የመጥምቁ ዮሐንስ ስሞች"
1.ነቢይ
2.ሐዋርያ
3.ሰማዕት
4.ጻድቅ
5.ካሕን
6.ባሕታዊ / ገዳማዊ
7.መጥምቀ መለኮት
8.ጸያሔ ፍኖት (መንገድ ጠራጊ)
9.ድንግል
10.ተንከተም (የብሉይና የሐዲስ መገናኛ ድልድይ)
11.ቃለ አዋዲ (አዋጅ ነጋሪ)
12.መምሕር ወመገሥጽ
13.ዘየዐቢ እምኩሉ (ከሁሉ የሚበልጥ)

=>አምላከ ቅዱሳን በጥምቀቱ ይቀድሰን:: ከበረከተ ጥምቀቱም ያድለን::

=>ጥር 11 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ በዓላት
1.በዓለ ኤጲፋንያ
2.ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ
3.አቡነ ሐራ ድንግል ጻድቅ
4.አባ ወቅሪስ ገዳማዊ
5.አባ ዮሐንስ ሊቀ ጳጳሳት
6.ቅዱስ እንጣልዮስ ሰማዕት

=>ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ያሬድ ካህን
2.ማር ገላውዴዎስ ሰማዕት
3.ቅዱስ ፋሲለደስ ሰማዕት
4.ቅድስት ሐና ቡርክት

=>"ጌታ ኢየሱስም ከተጠመቀ በኋላ ወዲያው ከውኃ ወጣ:: እነሆም ሰማያት ተከፈቱ:: የእግዚአብሔርም መንፈስ እንደ ርግብ ሲወርድ: በእርሱ ላይም ሲመጣ አየ:: እነሆም ድምጽ ከሰማያት መጥቶ:- 'በእርሱ ደስ የሚለኝ: የምወደው ልጄ ይህ ነው' አለ::"
(ማቴ. ፫፥፲፮)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
2024/09/30 23:46:53
Back to Top
HTML Embed Code: