Telegram Web Link
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

✞✞✞ ታኅሳስ24 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ✞✞✞

✞✞✞ እንኩዋን ለቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት: ቅዱስ አግናጥዮስ እና ቅድስት አስቴር ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ  ✞✞✞

+*" ቅዱስ  #‎ተክለ_ሃይማኖት  ሐዋርያዊ "*+

*ልደት*

=>መልካም ዛፍ መልካም ፍሬን ያፈራልና ተክለ ሃይማኖትን የወለዱት ደጋጉ:  #‎ጸጋ_ዘአብ  ካህኑና  #‎እግዚእ_ኃረያ  ናቸው:: እርሱ በክህነቱ: እርሷ በደግነቷ: በምጽዋቷ ጸንተው ቢኖሩ እግዚአብሔር ጣፋጭ ፍሬን ሰጥቷቸዋል::

+በዳሞቱ ገዢ በሞተለሚ አደጋ ቢደርስባቸው  #‎ቅዱስ_ሚካኤል : ጸጋ ዘአብን ከሞት: እግዚእ ኃረያን ከትድምርተ አረሚ (ከአረማዊ ጋብቻ) አድኗቸዋል:: በኋላም የቅዱሱን መወለድ አብስሯቸዋል::

+አቡነ ተክለ ሃይማኖት የጸነሱት መጋቢት 24, በ1206 (1196) ሲሆን የተወለዱት ታሕሳስ 24, በ1207 (1197) ዓ/ም ነው:: በተወለዱበት ቀንም ብዙ ተአምራት ተገልጸዋል:: ቤታቸውም በበረከት ሞልቷል::

*ዕድገት*

=>የጻድቁ የመጀመሪያ ስማቸው " #‎ፍሥሃ_ጽዮን " ይሰኛል:: ይሕንን ስም ይዘው: አባታቸው ጸጋ ዘአብን ተከትለው አድገዋል:: በተለይ ቅዱሳት መጻሕፍትን (ብሉያት: ሐዲሳትን) ተምረዋል:: በሥጋዊው ጐዳናም ብርቱ አዳኝ እንደ ነበሩ ይነገራል:: ዲቁና ከወቅቱ ዻዻስ  #‎አባ_ጌርሎስ  ተቀብለዋል::

*መጠራት*

=>አንድ ቀን ፍሥሃ ጽዮን ለአደን ወጥቶ ሲያነጣጥር ድንገት ከሰማይ አስደንጋጭ ድምጽ ተሰማ:: የክብር ባለቤት  #‎ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ  አእላፍ መላእክት እያመሰገኑ በሚካኤል ክንፍ ተቀምጦ ወረደ::

+የወጣቱን አዳኝ ፍርሃቱን አርቆ ጌታችን ተናገረ:

"ከዛሬ ጀምሮ ስምህ ተክለ ሃይማኖት (ተክለ ሥላሴ) ይሁን:: አራዊትን ሳይሆን ነፍሳትን ታድናለህ:: ዘወትር ካንተ ጋር ነኝ" ብሎ በግርማ ዐረገ:: ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ከዚህ ጊዜ በኋላሰዓትን አላጠፉም:: ንብረታቸውን ለነዳያን በትነው በትር ብቻ ይዘው ቤታቸው እንደ ተከፈተ ወደ ምናኔ ወጡ::

*አገልግሎት*

=>ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ከዻዻሱ ቅስና ተቀብለው የወንጌል አገልግሎትን ጀመሩ:: በመጀመሪያ ስብከታቸው እዚያው ሽዋ ( #‎ጽላልሽ ) አካባቢ ብቻ በ10ሺ የሚቆጠሩ ሰዎችን አሳምነው አጠመቁ:: ያንጊዜ  #‎ኢትዮዽያ  2 መልክ ነበራት::

1.ዮዲት (ጉዲት) በፈጠረችው ጣጣና በእስላሞች ተጽዕኖ ወደ ደቡብ አካባቢ ያለው ነዋሪ አንድም ሃይማኖቱን ክዷል: ወይም በባዕድ አምልኮ ተጠምዷል::

2.ደግሞ በዛግዌ ነገሥታት ጥረት ክርስትናና ምናኔ ተነቃቅቶ ነበር::

+ግማሹ ሃገር በጨለመበት ወቅት የደረሱት  #‎ሐዲስ_ሐዋርያ  አባ ተክለ ሃይማኖት በወጣት ጉልበታቸውና በኃይለ መንፈስ ቅዱስ ብዙ ቦታዎችን አደረሱ:: ሕዝቡን: መሣፍንቱን ወደ ሃይማኖት መልሰው: ማርያኖችን (ጠንቁዋዮችን) አጥፍተዋል::

*ገዳማዊ ሕይወት*

=>ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት በወንጌል ብርሃን ኢትዮዽያን ከማብራታቸው ባለፈ ገዳማዊ ሕይወትንም አስፋፍተዋል:: እርሳቸው ከሁሉ የተሻሉ ሳሉም በ3 ገዳማት በረድዕነት አገልግለዋል::

+እነዚህም በአቡነ  #‎በጸሎተ_ሚካኤል  ገዳም ለ12 ዓመታት: በአቡነ  #‎ኢየሱስ_ሞዐ_ዘሐይቅ  ገዳም ለ7 ዓመታት: በደብረ ዳሞ ከአቡነ  #‎ዮሐኒ  ጋር ለ7 ዓመታት: በአጠቃላይ ለ26 ዓመታት አገልግለዋል::

+በአቡነ ኢየሱስ ሞዐ ከመነኮሱ በኋላም ወደ ምድረ ሽዋ  #‎ዞረሬ  ተመልሰው በአንዲት በዓት ውስጥ ለ22 ዓመታት ቆመው ጸልየዋል:: በተሰበረ እግራቸውም 6 ጦሮችን በግራና በቀኝ ተክለው ለ7 ዓመታት ጸልየዋል::

*ስድስት ክንፍ*

=>ኢትዮዽያዊው ጻድቅና ሐዋርያ ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ከኢትዮዽያ ወደ ኢየሩሳሌም ተጉዘው ከቅዱሳት መካናት ተባርከዋል:: ጻድቁ ምድረ  #‎እሥራኤል  የገቡት በየመንገዱ መንፈሳዊ ዘርን እየዘሩ: እያስተማሩና እያሳመኑ ነበር::

+የወቅቱ ሊቀ ዻዻሳት  #‎አባ_ሚካኤል  ጋርም ተገናኝተው ቡራኬን ተሰጣጥተዋል:: ዋናው ጉዳይ ግን ከዚህ በኋላ ነው:: ጻድቁ እመቤታችንና ጌታችን ከጽንሰታቸው እስከ ዕርገታቸው የረገጧቸውን ቦታዎች ሲመለከቱ በፍጹም ተደሞ እንባቸው ይፈስ ነበር::

+ምክንያቱም እግዚአብሔር ስላበቃቸው ተክለ ሃይማኖት የሚያዩት ቦታውን አልነበረም:: በገሃድ:-
¤በቤተ መቅደስ ብስራቱን
¤በቤተ ልሔም ልደቱን
¤በቤተ ዮሴፍ ግዝረቱን
¤በፈለገ ዮርዳኖስ ጥምቀቱን
¤በቤተ አልዓዛር ተአምራቱን ይመለከቱ ነበር::

+የጉብኝታቸው የመጨረሻ ክፍል ወደሆነው  #‎ቀራንዮ  ደርሰው ጌታቸውን እንደ ተሰቀለ ሆኖ ቢመለከቱት ከዓይናቸው ይፈስ የነበረው ቁጡ እንባ መልኩን ቀየረና ዓይናቸው ጠፋ::
በዚያች ቅጽበት ስም አጠራሯ የከበረ  #‎እመቤታችን_ድንግል_ማርያም  ፈጥና ደርሳ ጻድቁን ወደሰማይ አሳረገቻቸው::

+በዚያም:-
¤የብርሃን ዐይን ተቀብለው
¤6 ክንፍ አብቅለው
¤የወርቅ ካባ ላንቃ ለብሰው
¤ማዕጠንተ ወርቁን ይዘው
¤ከ24ቱ ካህናተ ሰማይም ተደምረው
¤ሥላሴን በአንድነቱና ሦስትነቱ ተመልክተው
¤"ስብሐት ወክብር ለሥሉስ ቅዱስ ይደሉ" ብለው መንበረ ጸባኦትን አጥነው ወደ መሬት ተመልሰዋል::

*ተአምራት*

=>የጻድቁ ተአምራት እንደ ሰማይ ከዋክብት የበዛ ነው::
*ሙት አንስተዋል
*ድውያንን ፈውሰዋል
*አጋንንትን አሳደዋል
*እሳትን ጨብጠዋል
*በክንፍ በረዋል
*ደመናን ዙፋን አድርገዋል::

+ብዙ ደቀ መዛሙርትን አፍርተው ደብረ ሊባኖስን መሥርተዋል:: በዚያም ሴትና ወንድ መነኮሳት እንደ ሕጻናት አብረው ኑረዋል:: በዘመናቸው ሰይጣን ታሥሯልና::

*ዕረፍት*

=>ጻድቅ: ሰማዕትና ሐዋርያ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ብርሃን ሆነው መከራን በብዙ ተቀብለው: አእላፍ ፍሬን አፍርተው: በተወለዱ በ99 ዓመት: ከ8 ወር: ከ1 ቀናቸው ነሐሴ 24, በ1306 (1296) ዓ/ም ዐርፈዋል:: ጌታ: ድንግል ማርያምና ቅዱሳን ከሰማይ ወርደው ተቀብለዋቸዋል:: 10 ትውልድ የሚያስምር ቃል ኪዳንም ተቀብለዋል::

=>የጻድቁ አባታችን ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት የቅድስናና የክብር ስሞች :-

1.ተክለ አብ: ተክለ ወልድ: ተክለ መንፈስ ቅዱስ
2.ፍስሐ ፅዮን
3.ሐዲስ ሐዋርያ
4.መምሕረ ትሩፋት
5.ካህነ ሠማይ
6.ምድራዊ መልዐክ
7.እለ ስድስቱ ክነፊሁ (ባለስድስት ክንፍ)
8.ጻድቅ ገዳማዊ
9.ትሩፈ ምግባር
10.ሰማዕት
11.የኢትዮዽያ መነኮሳት አለቃ
12.ፀሐይ ዘበፀጋ
13.የኢትዮዽያ ብርሃኑዋ
14.ብእሴ እግዚአብሔር (የእግዚአብሔር ሰው)
15.መናኒ
16.ኤዺስ ቆዾስ (እጨጌ)

=>እነዚህ የአባታችን ስሞች እንደዘመኑ ሰው ለመሞጋገስ የወጡ ሳይሆኑ ሁሉም በትክክል ሥራዎቹንና ለቤተ ክርስቲያን የሆነላትን የሚያዘክሩ ናቸው:

+" ቅዱስ አግናጥዮስ "+

=>ይህ ቅዱስ ሰው ከመንፈስ ቅዱስ ጸጋ የጠገበ በመሆኑ በመላው ዓለም ዝነኛ ነው:: እርሱ:-
*በክርስቶስ እጅ ተባርኩዋል
*ፈጣሪውን ፊት ለፊት አይቷል
*ሐዋርያትን አገልግሏል
*ከምሥጢር አባት ከዮሐንስ ወንጌላዊ እግር ተምሯል
*ስለ ክርስትና ለአንበሶች ተጥሎ በመገደሉ "ምጥው ለአንበሳ" ይባላል::
+ቅዱስ አግናጥዮስ የተወለደው በክርስቶስ አምላካችን መዋዕለ ስብከት (በ30 ዓ/ም አካባቢ) እንደ ሆነ ይታመናል:: በትውፊትም በማቴ. 18:1 ላይ ያለው ሕጻን እርሱ ነው ይባላል::+ሐዋርያት ከመካከላቸው ማን እንደሚበልጥ ሲጠይቁት አንድ ሕጻንን (አግናጥዮስን) ከመሃል አቁሞ "ካልተመለሳችሁ: እንደዚህም ሕጻንካልሆናችሁ ከቶውንም ወደ እግዚአብሔር መንግስት አትገቡም" ብሏቸዋል::

+ከጌታ ዕርገት በሁዋላም ሐዋርያት ለወንጌል ሲፋጠኑ ሕጻኑ ቅዱስ አግናጥዮስ እየተከተለ አገልግሏል: ተምሯል:: ኢየሩሳሌም በጥጦስ አስባስያኖስ ቄሣር በጠፋችበት ዓመት (በ70 ዓ/ም) ቅዱሱ የአንጾኪያ ሊቀ ዻዻሳት ሆኖ ተሹሟል::

+ከዚህ በሁዋላም ለ2 እና 3 አሠርት ዓመታት ከወንጌላዊ ዮሐንስ ጋር አብሮ ወንጌልን ሰብኩዋል:: የዚህ ቅዱስ ተጋድሎ ጫፍ የደረሰው ከ100 ዓ/ም በሁዋላ ሁሉም ሐዋርያት ሰማዕት በመሆናቸውና ትልቁን ኃላፊነት እርሱ በመሸከሙ ነው:: የወቅቷን ቤተ ክርስቲያን ከቅዱሳኑ ቀሌምንጦስ ዘሮምና ፖሊካርፐስ ዘሰርምኔስ ጋር ሆኖ እስከ ደም ጠብታ ጠብቁዋል::

+ከዚህ በሁዋላ ቅዱስ አግናጥዮስ ለዘመናት ወንጌልን እየሰበከ በሕይወቱና በትምሕርቱ አስተማረ:: ብዙ መልእክቶችን (ድርሳናትንም) ጻፈ:: በመጨረሻው ግን በጠራብሎስ ቄሣር ተይዞ: በብረት ሰንሰለት ታስሮ: ከአንጾኪያ (ሶርያ) ወደ ሮም (ጣልያን) ተወሰደ::

+ደሙ እስኪፈስም ገረፉት:: ዛሬ በሮም ከተማ ግማሽ አካሉ ፈርሶ በሚታየው ስታዲየም (በአባቶቻችን አጠራር ተያጥሮን) እንዲገደል ተወሰነበት:: በወቅቱ ባደረገው ንግግርም ቄሣሩና ሕዝቡ ድፍረቱን አደነቁ:: በመጨረሻም ለአንበሳ እንዲሰጥ ተደርጐ በዚህች ቀን ሰማዕት ሆነ::

+" ቅድስት አስቴር "+

=>ይህቺ ቅድስት እናት:-
*እሥራኤል በባቢሎን ምርኮ ሳሉ የነበረች
*አባቷ አሚናዳብ ባለ መኖሩ በአጐቷ መርዶክዮስ እጅ ያደገች
*እጅግ ውብ በመሆኗ የአርጤክስስ ሚስት (ንግሥት) ለመሆን የበቃች
*ራሷን መስዋዕት አድርጋ ወገኖቿን አይሁድን ከሞት ያተረፈች
*ለመርዶክዮስ ክብርን: ለአማሌቃዊው ሐማ ደግሞ ስቅላትን ያስፈረደች እና
*እግዚአብሔር ሞገስ የሆናት እናት ናት::
*ዛሬ ዕረፍቷ ነው::

=>አምላከ ቅዱሳን ወዳጆቹን ባጸናበት ቅዱስ መንፈሱ እኛንም ያጽናን:: ከበረከታቸውም ይክፈለን::

=>ታሕሳስ 24 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት
2.ቅዱሳን ጸጋ ዘአብና እግዚእ ኃረያ
3.ቅዱስ አግናጥዮስ ሐዋርያ
4.ቅድስት አስቴር
5.አባ ፊሎንጐስ ሊቀ ዻዻሳት
6.አባ ዻውሊ ጻድቅ
7.ጻድቃን ቅዱሳን ዘከዲህ

=>ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ቶማስ ዘመርዐስ
2.አቡነ ዘዮሐንስ ጻድቅ ዘክብራን
3.ቅዱስ አጋቢጦስ (ጻድቅ ኤዺስቆዾስ)
4.ቅዱስ አብላርዮስ ታላቁ
5."24ቱ" ካኅናተ ሰማይ (ሱራፌል)
6.ቅዱስ አባ ሙሴ ጸሊም (ኢትዮዽያዊ)
7.ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ

=>+"+ ንግሥቲቱም አስቴር መልሳ:- 'ንጉሥ ሆይ! በአንተ ዘንድ ሞገስን አግኝቼ እንደ ሆነ: ንጉሡንም ደስ ቢያሰኘው: ሕይወቴ በልመናዬ: ሕዝቤም በመሻቴ ይሰጠኝ:: እኔና ሕዝቤ ለመጥፋትና ለመገደል: ለመደምሰስም ተሸጠናልና:: +"+ (አስቴር. 7:3)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
እንኩዋን ለ5ቱ "ቅዱሳን መቃብያን" እና "ቅዱስ ዮሐንስ ከማ" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ

+*" 5ቱ መቃብያን "*+

=>እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን: 22ቱን ሥነ ፍጥረትን ፈጥሮ አዳምን ገዢ አደረገው:: አክሎም በነፍስ ሕያው አድርጐ: በመንፈስ ቅዱስ አክብሮ: ነቢይና ካህን አድርጐ: ካንዲት ዕፀ በለስ በቀር በፍጥረት ሁሉ ላይ አሰለጠነው::

+አባታችን አዳም ግን ስሕተት አግኝቶት ከገነት ወጣ:: መከራና ፍዳም አገኘው:: በሁዋላም ለ100 ዓመት አልቅሶ ንስሃ ገባ:: ጌታም ንስሃውን ተቀብሎ "ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ" የሚል ተስፋ ድህነትን ሰጠው::

+ስለዚህም ምክንያት ለ5,500 ዓመታት ትንቢት ሲነገር: ሱባኤ ወደ ታች ሲቆጠር: ምሳሌም ሲመሰል ኖረ:: ከደግ ፍጥረት አዳም እስከ ኖኅ ድረስ: የሴት ልጆች እግዚአብሔርን በንጽሕና ሁነው በደብር ቅዱስ አመለኩ::

+ትንሽ ቆይተው ግን ስለተቀላቀሉ ከቃየን ልጆች ጋር በማየ ድምሳሴ ጠፉ:: በጻድቅ ሰው ኖኅ የተጀመረው ትውልድም እግዚአብሔርን ለመዘንጋት ጊዜ አልፈጀበትም:: ነገር ግን ከሴም ዘር ቅንና ጻድቅ ሰው አብርሃም ተገኘ::

+ከእርሱም ይስሐቅ: ከዚያም ያዕቆብ ደጋጉ ተገኙ:: ያዕቆብም "እሥራኤል" ተብሎ በልጆቹ "ሕዝበ እግዚአብሔር" የተባለ ነገድ ተመሠረተ:: በተስፋይቱ ምድር በከነዓን እንዳይኖሩም ረሃብ ምድረ ግብጽ አወረዳቸው::

+በዚያም ለ215 ዓመታት በጭንቅ የባርነትን ሕይወትን አሳለፉ:: እግዚአብሔርም ስለ ወዳጁ አብርሃም ሲል እሥራኤልን አሰባቸው:: የዋሕና ጻድቅ ሰው ሙሴን አስነስቶ እሥራኤልን ከግብጽ ባርነት አዳናቸው::

+ይኸውም በጸናች እጅ: በበረታችም ክንድ: በ9 መቅሰፍት: በ10ኛ ሞተ በኩር: በ11ኛ ስጥመት ግብጻውያንን አጥፍቶ ነው:: በየመንገዱም ጠላቶቻቸውን እየተበቀለላቸው ነው:: ከዚህ ዘመን ጀምሮም እሥራኤል በመሳፍንትና በካህናት የሚተዳደሩ ሆኑ::

+አስቀድሞ ሙሴ በምስፍና: አሮን በክህነት መሯቸው:: ቀጥሎም በቅዱስ ሙሴ ኢያሱ: በአሮን አልዓዛር ተተኩ::

+ከዚህ በሁዋላ ለ300 ዓመታት ያህል መሣፍንት እየተቀያየሩ አስተዳደሩዋቸው:: ሲበድሉ ጠላት እየገዛቸው: ሲጸጸቱ በጐ መሥፍን እየመጣላቸው ከነቢዩ ሳሙኤል ደረሱ::

+በዚህ ጊዜም ሕዝቡ እንደ አሕዛብ ሥርዓት ንጉሥ በመፈለጋቸው ክፉው ሳዖል ለ40 ዓመት ገዛቸው:: ቀጥሎ ግን እንደ አምላክ ልብ የሆነ ቅዱስ ሰው ዳዊት ነግሦላቸው እሥራኤል ከፍ ከፍ አሉ:: ከቅዱስ ዳዊት እስከ ሮብዓም ቆይተው ግን እሥራኤል ከ2 ተከፈሉ::

+10ሩ ነገድ በሰማርያ ሲኖሩ ግፍን ስላበዙ ስልምናሶር ማርኮ አሦር አወረዳቸው:: ባሮችም አደረጋቸው:: 2ቱ ነገድ ደግሞ ከብረው: ገነው በኢየሩሳሌም ቢኖሩም እነርሱም አመጸኞች ነበሩና ናቡከደነጾር ወስዶ የባቢሎን ባሪያ አደረጋቸው::

+እግዚአብሔር ግን እንደ ነቢያቱ ቃል 70ው ዘመን ሲፈጸም በኃይል ወደ ርስታቸው መለሳቸው:: በዚያም ዘሩባቤል የሚባል ደግ ንጉሥ ነግሦላቸው: ቤተ መቅደስ ታንጾላቸው ኖሩ:: ክፋታቸው ግን ማብቂያ አልነበረውምና ከዘሩባቤል በሁዋላ ቅን ንጉሥን ማግኘት አልቻሉም::

+እግዚአብሔር ግን ምሕረቱንና መግቦቱን አይተውምና አልዓዛርን የመሰሉ ደጋግ ካህናትን እያስነሳ ሰው እስከሚሆንባት ቀን ድረስ አቆይቷቸዋል:: በዚህም ምክንያት ይህ ዘመን "ዘመነ ካህናት" ተብሏል::

+በዚህ በዘመነ ካህናት ውስጥ ደግሞ በጐነታቸው የታወቀላቸው: ግን ደግሞ መከራው የበዛባቸው እሥራኤላውያን ነበሩ:: ብዙ ጊዜ የሚጠሩት "መቃብያን" በሚል ስም ነው::

+በያዕቆብ እሥራኤል: በዔቦር ዕብራውያን: በይሁዳ አይሁድ: በፋሬስ ፈሪሳውያን: በሳዶቅ ሰዱቃውያን እንደተባሉት ሁሉ እነዚህም በአባታቸው በመቃቢስ ምክንያት መቃብያን ተብለዋል:: ታሪካቸው ሰፊና በመጽሐፈ መቃብያን የተጻፈ ሲሆን እኛ ግን በአጭሩ አንዷን የታሪክ ዘለላ ብቻ እንመለከታለን::

+በዘመኑ መቃቢስ የሚባል ደግ ሰው 5 (3) ወንዶች ልጆችን (መቃብያንን) ወልዶ ነበር:: እነዚህም በመልክ ይህ ቀራችሁ የማይባሉ: በጠባይ እጅግ የተመሰገኑ: በኃይላቸው ጽናትም የተፈሩ ነበሩ::

+በተለይ 3ቱ ከግሩማን አራዊት አንበሳና ድብ ታግለው ያሸነፉ: በጦርነትም ጠላትን ያንበረከኩ ነበሩ:: ታዲያ ይህ ሁሉ የተሰጣቸው ከእግዚአብሔር እንደ ሆነ ያውቁ ነበርና ፈጣሪያቸውን በንጹሕ ልብ ያመልኩት ነበር::

+በዘመኑ ደግሞ ሞዐባውያንና ሜዶናውያን አካባቢውን ያስገብሩ ነበር:: በተለይ የሞዐቡ ንጉሥ ጺሩጻይዳን ከክፋቱ ብዛት 70 ጣዖታት በወንድና በሴት ምሳሌ አስቀርጾ ያመልክ ነበር:: ከዚያም አልፎ ሕዝቡን "አምልኩ" እያለ ያውክ: ይቀጣ: ይገድልም ነበር::

+ቅዱሳን መቃብያን ይህንን ሲሰሙ ወደ እርሱ ገሰገሱ:: ምንም እንኩዋ ሊያጠፉት ኃይል ቢኖራቸውም አላደረጉትም:: ይልቁኑ ቀርበው ዘለፉት እንጂ::

+እርሱም "ጣዖትን አናመልክም" ስላሉ ለአንበሳ ጣላቸው:: አንበሶቹም ለቅዱሳኑ ሰግደው የንጉሡን ወታደሮች ፈጇቸው:: እርሱም 3ቱን ወደ እሥር ቤት ጣላቸው:: በዚህ ጊዜ 2ቱ ወንድሞቻቸው መጥተው ተቀላቀሉ::

+ቀጥሎም 5ቱንም አስወጥቶ በሰይፍ አስመታቸው:: ከተገደሉ በሁዋላም ወደ ውሃ ጥሏቸው: በእሳት አቃጥሏቸው ነበር:: ባይሳካለት ስለ ተቆጣ ሳይቀበሩ እንዲጣሉ አዘዘ:: ከ14 ቀናት በሁዋላም የቅዱሳኑ አካል እንደ መብረቅ እያብለጨለጨ ተገኝቶ በክብር እንዲቀበር ሆኗል::

<< ቀሪው ታሪካቸው በመጽሐፈ መቃብያን የተጻፈ አይደለምን !! >>

+*" አባ ዮሐንስ ከማ "*+

=>ቅዱስ ዮሐንስ ከማ በዘመነ ጻድቃን (በተለይም በ5ኛው መቶ ክ/ዘመን) ከተነሱ አበው አንዱ ነው:: ቅዱሱ ድንቅ ሕይወት ስለ ነበረው በዜና አበው በስፋት ተጠቅሷል:: መጽሐፈ ስንክሳር "ከማ" የሚለውን ቃል "ከማ ብሒል ካም - 'ከማ' ማለት 'ካም' ማለት ነው" ይላል::

+"ካም" የሚለው ቃል ደግሞ ብዙ ጊዜ መልካቸው ጠቆር ላሉ ሰዎች የሚሰጥ ስም ነው:: ምናልባት የድሮ የኢትዮዽያ ግዛት በነበረው ደቡብ ግብጽ የነበረ አባት እንደ መሆኑ የዘር ሐረጉ ከኢትዮዽያ የተመዘዘ ሊሆን እንደሚችል ይታመናል::

+ቅዱሱ በስፋት የሚታወቀው በድንግልና ሕይወቱ ነው:: መልካም ቤተሰቦቹ በሥርዓት አሳድገው "እንዳርህ" አሉት:: እንቢ ቢላቸው ብቸኛ ልጃቸው ነውና ፈጽሞ ሊያዝኑበት ነው:: ደስታውን ለቤተሰቦቹ ሰውቶ በተክሊል ተዳረ::

+እርሱ የሚሻው በድንግልና መኖርን ነውና ጥበበኛ እግዚአብሔር ሚስቱ የተቀደሰች እንድትሆን አደረጋት:: በሠርጋቸው ምሽት ቅዱስ ዮሐንስ ከማ መልከ መልካሟን ሙሽራ በድንግልና ይኖሩ ዘንድ ቢጠይቃት በደስታ አነባች::

+ምክንያቱም እርሷም ያገባችው ቤተሰብን ለማስደሰት እንጂ ፈቃዷ በድንግልና መኖር ነበርና:: 2ቱም ስላደረገላቸው ፈጣሪን እያከበሩ የድንግልና ሕይወት ተጋድሎን ቀጠሉ:: ቅዱሳኑ በአንድ አልጋ ላይ እየተኙ: አንዲት ምንጣፍን እያነጠፉ: አንድ ልብስንም በጋራ ለብሰው እያደሩ ድንግልናቸውን ጠበቁ::

+አምላከ ድሜጥሮስም ቅዱስ መልአኩን ልኮላቸው በመካከላቸው ያድር: ክንፉንም ያለብሳቸው ነበር:: ክብራቸውን ይገልጥ ዘንድም በቤታቸው መካከል ታላቅ ዛፍን ያለ ማንም ተካይነት አበቀለ::
+በዚህ ጊዜ ግን ቅዱስ ዮሐንስ ከማ ድንግሊቱን ሚስቱን "የከተማ ኑሮ ይብቃን: ወደ በርሃ እንሒድ" አላት:: እርሷም "ፈቃድህ ፈቃዴ ነው" ስላለችው እርሷን ወደ ደናግል ገዳም አስገብቶ እርሱ ወደ ገዳመ አስቄጥስ ተጉዋዘ::+ቅድስቲቱ አስቀድማ ጸጋው በዝቶላት ነበርና ድውያንን ትፈውስ ነበር:: የገዳሙ እመ ምኔት ሆና መርታ በክብር አረፈች:: ቅዱስ ዮሐንስ ከማም በቅዱስ መልአክ መሪነት መጀመሪያ ወደ አባ ዳሩዲ ሔዶ መነኮሰ::

+በመጨረሻም በቅዱስ ዮሐንስ ሐጺር ገዳም ጐን ማደሪያን አነጸ:: በዚያም በመቶ የሚቆጠሩ ደቀ መዛሙርትን አፍርቶ በአበ ምኔትነት አገለገለ:: ለእመቤታችንና ለቅዱስ አትናቴዎስ ልዩ ፍቅር የነበረው ቅዱሱ ከበርካታ የቅድስና ዘመናት በሁዋላ በዚህች ቀን በክብር ዐርፎ ተቀብሯል::

=>አምላከ ቅዱሳን ይራዳን: ይባርከን: ይቀድሰን:: ከወዳጆቹ በረከትም ያሳትፈን::

=>ታሕሳስ 25 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱሳን 5ቱ መቃብያን
2.ቅዱስ ዮሐንስ ከማ (እና የተቀደሰች ሚስቱ)
3.ቅዱስ ዳንኤል መነኮስ
4.ቅዱስ ኒቆላዎስ መኮንን

=>ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ መርቆሬዎስ ሰማዕት
2.ቅድስት ቴክላ ሐዋርያዊት
3.ቅዱስ አበከረዙን ሰማዕት
4.ቅዱስ ዱማድዮስ ሶርያዊ
5.አቡነ አቢብ (አባ ቡላ)
6.ቅዱስ አባ አቡፋና ጻድቅ
7.ታላቁ አባ ቢጻርዮን ገዳማዊ

=>+"+ ቃሌን የሚጠብቅ: በትዕዛዜም ጸንቶ የሚኖር: በረከቴን የሚያገኝ: በእኔ ዘንድ የሚከብር እርሱ ነው::
ቃሌን የሚጠብቅ: በትዕዛዜም ጸንቶ የሚኖር ሰው ሁሉ ከምድር የተገኘውን ድልብ ይበላል:: ቅን ልቡና ያላቸው ደጋጎች ነገሥታት ወደ ገቡበት ወደ ገነትም ገብቶ ይኖራል:: +"+ (መቃ. 12:43)

   <<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>

https://www.tg-me.com/zikirekdusn
<<< በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ፩ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ >>>

<<< ታሕሳስ 26 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት >>>

+" ቅድስት አንስጣስያ "+

=>እስኪ ዛሬ በጥቂቱ የተባረኩ (ቡሩካት) እናቶቻችን
እንዘክር:: "ቅድስት" የሚለው ቃል ለሁሉም ቅዱሳት
እናቶች ቢሰጥም
ቅሉ ለድንግል ማርያም ሲሰጥ ግን ትርጉሙ ይለያል::
እርሷ 'ቅድስተ ቅዱሳን: ንጽሕተ ንጹሐን: ቡርክት
እምቡሩካን:
ኅሪት እምኅሩያን ናትና::

+ከሰው ልጆችም ሁሉ ትበልጣለች:: ይቅርና የሰው ልጅን
ንጹሐን መላእክትንም በንጽሕናና በቅድስና
ትበልጣቸዋለች:: እርሷ
እመ ብርሃን: የአምላክ እናቱ: የሰውነታችን መመኪያ
ናትና::

+እመቤታችንን "ቅድስት" ስንል "ጽንዕት: ንጽሕት: ክብርት:
ልዩ" ማለታችን ነው:: 1."ንጽሕት" ትባላለች:: ሌሎች
ሰዎች (ቅዱሳን) ቢነጹ ከገቢር: ከነቢብ ኃጢአት ነው
እንጂ ከኃልዮ ኃጢአት አይደለም:: እርሷ ግን ከነቢብ:
ከገቢር:
ከኃልዮ ንጽሕት ናት::

"ለመኑ ተውኅቦ ተደንግሎ ኅሊና: ለመላእክትሂ
ኢተክህሎሙ-ኃጢአትን ከማሰብ መጠበቅ ከሰው ልጆች
ለማን ተሰጠው: ይህስ
ለመላእክትም አልተቻላቸውም" እንዲል:: (ተአምረ
ማርያም)

2."ጽንዕት" እንላታለን:: ሴቶች ቢጸኑ ለጊዜው ነው እንጂ
በኋላ በጊዜው ተፈትሆ አለባቸው:: እመቤታችን ግን
ቅድመ
ጸኒስ: ጊዜ ጸኒስ: ድኅረ ጸኒስ: ቅድመ ወሊድ: ጊዜ
ወሊድ: ድኅረ ወሊድ ድንግል ናትና::
"ጽንዕት በድንግልና አልባቲ ሙስና" እንዳላት:: (ቅዱስ
ያሬድ) ታላቁ ቅዱስ ባስልዮስም "ወትረ ድንግል ማርያም-
ማርያም
ዘለዓለማዊት ድንግል ናት" እንዳለ:: (መጽሐፈ ቅዳሴ)

3.ድንግልን "ክብርት" እንላታለን:: ሌሎች ሴቶች ቢከብሩ
ጻድቃን ሰማዕታትን: ነቢያት ሐዋርያትን ወልደው ነው::
እመቤታችንን ግን የምናከብራት "ወላዲተ አምላክ-
የአምላክ እናቱ" ብለን ነውና::

4.እመቤታችንን "ልዩ" እንላታለን:: ከእርሷ በቀር እናት ሁና
ድንግል: እመቤት ሁና አገልጋይ የሆነች: በድንግልና
ወልዳ ወተትን (ሐሊበ ድንግልናዌን) ያስገኘች ሌላ ሴት
የለችምና::

+የእመ ብርሃን ይቆየንና ደግሞ ሌሎች ቅዱሳት
እናቶቻችንን እንመልከት:: እናቶቻችን ስናከብር
የምንጀምረው በቅድስት
ሔዋን ነው:: ብዙ ጊዜ የእናታችን ሔዋን ጥፋቷ እንጂ
በጐ ነገሯ: ደግነቷ: ንስሃዋ አይነገርላትም:: ሆኖም
እናታችን
ቅድስት ሔዋን ክብር የሚገባት ሴት ናት::

*ክርስቶስ ሰው የሆነ እርሷንና ልጆቿን ለመቀደስ ነውና::
"ከመ ይስዓር መርገማ ለሔዋን ዲበ ዕፅ ተሰቅለ"
እንዲል::
(ድጉዋ)

+ቀጥሎ በብሉይ ኪዳን እነ ሐይከል: እድና: ሣራ: ርብቃ:
አስኔት: ሲፓራ: ሐና: ቤርሳቤህን የመሰሉ እናቶቻችን
በበጐው
መንገድ ፈጣሪን ደስ አሰኝተዋል:: በዘመነ ሥጋዌም
ቅዱሳቱ ሐና: ኤልሳቤጥ: ማርያም: ሶፍያ: ሰሎሜ: ዮሐና
እና 36ቱ
ቅዱሳት አንስት በጐነታቸው ያበራል::

+ከዚያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ለ2,000 ዓመታት የተነሱ
አእላፍ ቅዱሳት እናቶቻችንን ግን ዘርዝረን አንዘልቃቸውም::
በቅድስናቸው አራዊትን ያሰገዱ: ነገሥታትን ያንቀጠቀጡ:
አጋንንቸትን የረገጡ: በዘንዶ ላይ የተጫሙ ብዙ እናቶችን
ቤተ
ክርስቲያን አፍርታለች::

+ዛሬም ቢሆን በበርሃና በከተማ በጐውን ጐዳና የተከተሉ
ብዙ እናቶች እንዳሉን እናውቃለን:: አንድም እናምናለን::
ግን
ግን በከተሞች የምንመለከተው ሥርዓቱን የለቀቀው
የበርካታ እህቶቻችን አካሔድ ለሃገርም ለቤተ
ክርስቲያንም ትልቅ ስጋት
ነው:: ክብርና ነውር የማይለይበት ዘመን ይመስላል::

+ይህንን እያነበባችሁ ያላችሁ እህቶቼ! አንድ ነገር
ልንገራችሁ:: በመልካቸው ብዙዎችን ያጋጩ: አጊጠው
በመታየታቸው ብዙዎችን ያሰናከሉ: ለብዙ ምዕመናንም
የጥፋት ምክንያት የሆኑ ብዙ ሴቶች በታሪክ ነበሩ::

+የሚያሳዝነው ግን ዛሬ ያሉት ከመሬት በታች ነው:: አፈር
በልቷቸዋል:: ስም አጠራራቸውም ጠፍቷል:: በጣም
የሚያሳዝነው
ደግሞ ዛሬ በዘለዓለማዊው እሳት እየተቃጠሉ በሲኦል:
በጥልቁ ውስጥ አሉ::

+እናም ወገኖቼ! ይህን አውቀን እንንቃ:: ይህ ዓለም
ጠፊም: አጥፊም ነውና:: እድሜአችን ቢረዝምና ከዚህ
በኋላ ለ100
ዓመታት ብንኖርም እርሱም ማለቁ አይቀርምና::
ምርጫችን ዘለዓለማዊው ሕይወት ይሁን ትላለች ቅድስት
ቤተ ክርስቲያን::

+" ቅድስት አንስጣስያ "+

+ይህች ቅድስት እንደ በርካቶቹ ቅዱሳት እናቶቻችን ሁሉ
የዘመነ ሰማዕታት ፍሬ ናት:: በቀደመችው ታናሽ እስያ
አካባቢ
ተወልዳ: የነገሥታት ዘር በመሆኗ ያደገችው በቤተ
መንግሥት ነው:: አባቷ ከክቡራኑ አንዱ ቢሆንም ሙያው
ጣዖትን ማምለክ
ነበር::

+ጊዜው የመከራ በመሆኑ ብዙ ሴቶች የሚኖሩት
ክርስትናቸውን ደብቀው ነው:: ከእነዚህ መካከል አንዷ
ደግሞ የቅድስት
አንስጣስያ እናት ናት:: ማንን እንደምታመልክ አረሚ ባሏ
አያውቅም ነበር::

+አንስጣስያን በወለደች ጊዜም በድብቅ አስጠመቀቻት::
ከሕጻንነቷ ጀምሮም ፍቅረ ክርስትና እንዲያድርባት ነገረ
ሃይማኖትን
አስተማረቻት:: ቅድስት አንስጣስያ ወጣት በሆነች ጊዜ
ግን ከውበቷ የተነሳ ተመልካቿ በዛ:: እርሷ ግን ይህ ሁሉ
የዓለም
ኮተት አይገባትም ነበር::

+በፈጣሪዋ ፍቅር ከመጠመዷ የተነሳ ለመሰል ነገሮች
ትኩረት አልነበራትም:: ትጾማለች: ትጸልያለች: ነዳያንና
እሥረኞችን
ትጐበኛለች:: በዚህም ዘወትር ደስ ይላት ነበር:: ነገር ግን
አባቷ ባላሰበችው ጊዜ ለአንድ አረማዊ አጋባት:: በጣም
አዘነች: ግን ተስፋ አልቆረጠችምና መፍትሔ ፈለገች::

+ድንግልናዋን እንዳያረክስ በጫጉላዋ ቀን ታመምኩ ብላ
ተኛች:: ከዚያ በኋላም አንዴ በልማደ አንስት: አንዴ
በሕመም
እያመካኘች አላስቀርብ አለችው:: እርሱ የጦር አለቃ
በመሆኑ ወደ ጦርነት ሲሔድ እርሷ ታጥቃ ስለ ቀናች
እምነት የታሠሩ
ክርስቲያኖችን ታገለግል ነበር::

+ቁስላቸውን እያጠበች: አንጀታቸውን በምግብ እየደገፈች
ደስ ታሰኛቸውም ነበር:: ባሏ ሲመለስ ግን ይህንን
በመስማቱ
ድጋሚ እንዳትወጣ ቆልፎባት ወደ ጦርነት ተመለሰ::
ፈጽማ ስላዘነችበትም እግዚአብሔር በጠላቶቹ እጅ
አሳልፎ ሰጠውና ሞተ::

+እርሷም ከነ ድንግልናዋ ቀሪ ሕይወቷን ስትመራ
መከራው ወደ እርሷ ደረሰ:: ተይዛ ቀርባ በአረማውያን እጅ
ብዙ
ተሰቃየች:: በዚህች ቀንም ስለ ክርስቶስ ተገድላ ክብረ
ሰማዕታትን ተቀዳጀች::

ቅዱስ አቦሊ ጻድቅ

+ቅዱሱ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ የክርስቶስን ሕማማት
ለመሳተፍ ሲተጉ ከኖሩ ጻድቃን አንዱ ነው:: መሉ ጊዜውን
በበርሃ
ሲያሳልፍ ብዙ ተጋድሎን ፈጽሟል:: በተለይ ሲጸልይ
እግሩን ከዛፍ ላይ አስሮ: ቁልቁል ከባሕር ውስጥ ሰጥሞ
ነው:: ዛሬ
ቤተ ክርስቲያን ዕረፍቱን ታስባለች::

=>አምላከ ቅዱሳን ጸጋውን: ክብሩን ያድለን:: ከወዳጆቹ
በረከትም አይለየን::

=>ታሕሳስ 26 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅድስት አንስጣስያ ሰማዕት
2.ቅዱስ አቦሊ ጻድቅ
3.ቅድሰት ዮልያና ሰማዕት

=>በ 26 የሚከበሩ ወርኀዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ
2.አቡነ ሐብተ ማርያም ጻድቅ
3.አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ
4.ቅዱሳን ሰማዕታተ ናግራን
5.ቅዱስ አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን

++"+ ለእናንተም ጠጉርን በመሸረብና ወርቅን
በማንጠልጠል ወይም ልብስን በመጐናጸፍ በውጭ የሆነ
ሽልማት አይሁንላችሁ::
ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ
የዋህና ዝግተኛ መንፈስ ያለውን የማይጠፋውን ልብስ
ለብሶ የተሰወረ
የልብ ሰው ይሁንላችሁ:: +"+ (1ዼጥ. 3:3)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
2024/09/26 23:26:06
Back to Top
HTML Embed Code: