Telegram Web Link
''' እንኩዋን ለቅዱሳን *አቡነ ኪሮስ *ዮሐንስ ዘደማስቆ *ሳሙኤል ዘቀልሞን *ተክለ አልፋ *ኤሲ *በርባራ *እንባ መሪና እና *ገብረ ማርያም ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ! '''

=>ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በዚሁ ቀን የምታከብራቸው ብዙ ቅዱሳን አሏት:: ሁሉን ለመዘርዘር ይከብዳል:: ግን የጥቂቱን ዜና ለበረከት እንካፈል ዘንድ የጌታ ፈቃዱ ይሁንና ስለ እያንዳንዱ በጥቂቱ እናንሳ::

+*" አቡነ ኪሮስ ጻድቅ "*+

=>የጻድቁን ስም የሚጠራ አፍ ንዑድ ነው: ክቡር ነው:: በእውነት የቅዱሱን አባት ክብር ለማግኘት መፋጠን ይበጃል:: አቡነ ኪሮስ የተወለዱት በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን ሲሆን ወላጆቻቸው ነገሥታት ናቸው::

+ተወልደው ባደጉባት ሃገር ቁስጥንጥንያ ገና በልጅነት ምቾት ሳያሳሳቸው መጻሕፍትንና ትሕርምትን ተምረዋል:: ወንድማቸው (ታላቁ ቴዎዶስዮስ) በነገሠባቸው የመጀመሪያ ዓመታት በቤተ መንግስቱ ዙሪያ ግፍ በዝቶ ነበርና አቡነ ኪሮስ ከኃጢአት ለመራቅና ለጌታ ለመገዛት ከከተማው ጠፍተው: አሕጉር አቁዋርጠው ወደ ግብፅ (ገዳመ አስቄጥስ) መጡ::

+እርሳቸውን ለመፈለግ የተደረገው ሙከራ አልተሳካም:: ይባስ ብሎ የንጉሡ ልጅ ገብረ ክርስቶስ ሙሽርነቱን ጥሎ ወደ ሌላ ሃገር መነነ:: "የቅኖች ትውልድ ይባረካል" እንዳለ ቅዱስ ዳዊት አቡነ ኪሮስ ለሙሽራው ገብረ ክርስቶስ አጎቱ ናቸው:: አቡነ ኪሮስ በገዳም ውስጥ የታላቁ አቡነ በብኑዳ ደቀ መዝሙር ሆነው ለዘመናት ቆይተዋል::

+ቅዱስ በብኑዳን አንበሳ በበላው ጊዜ በጣም አዝነው "ለምን ጌታ ሆይ?" በሚል መሬት ላይ ወድቀው አለቀሱ:: "ምክንያቱ ካልተነገረኝ አልነሳም" ብለው ከወደቁበት መሬት ላይ ሳይነሱ ለ40 ዓመታት አልቅሰዋል:: በዚህ ምክንያት ግማሹ አካላቸው አፈር ሆኖ ሣር በቅሎበታል::
ጌታችን ተገልጦ ምክንያቱን ነግሯቸዋል:: አካላቸውንም እንደነበረ መልሶላቸዋል::

+አንድ ቀን ጻድቁ ለቅዱስ በብኑዳ ሞት ምክንያት የሆነው መነኮስ ታንቆ መሞቱን ሰምተው በጣም አዘኑ:: ሱባዔ ገብተው: ፍጹም አልቅሰው: ከጌታም አማልደው: የዛን ኃጥእ ነፍስ ከሲዖል አውጥተዋል:: በሌላ ጊዜ ደግሞ ኃጥአን የሞሉበት አንድ ገዳም በግብጽ ነበርና መቅሰፍት ወርዶ ሁሉንም ባንድ ቀን ሲያጠፋቸው አዩ::

+ጻድቁ በዚህም ምክንያት ለ30 ዓመታት አልቅሰው: ሙታኑን አስነስተው: ንስሃ ሰጥተው: ገዳሙን የጻድቃን: ሕይወታቸውንም የፍቅር አድርገውታል:: ጻድቁ እመቤታችንን ከመውደዳቸው የተነሳ በስዕሏ ፊት አብዝተው ይሰግዱና ያለቅሱ ነበር:: እመ አምላክም ተገልጣ ትባርካቸው ነበር::

+ከዚህ በሁዋላ ወደ ምዕራብ አቅጣጫ ሒደው ለ57 ዓመታት ማንንም ሳያዩ ተጋደሉ:: ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ (ለስም አጠራሩ ስግደት ይሁንና) በየቀኑ ይጐበኛቸው: ቁጭ ብሎም ያወራቸው ነበር::

+በመጨረሻም ጌታ አእላፍ መላእክትን: ጻድቃን ሰማዕታትን: ድንግል እመቤታችንና ቅዱስ ዳዊትን አስከትሎ ወረደ::

+ቅዱስ ዳዊት ቀርቦ እያጫወታቸው: በበገናው እየደረደረላቸው: ከዝማሬው ጣዕም የተነሳ ነፍሳቸው ከሥጋቸው በፍቅር ተለየች:: ጌታችንም ታቅፎ: ስሞ ይዟቸው አረገ::

+ሥጋቸውን አባ ባውማ ቀበሩት:: የአቡነ ኪሮስ ቁመታቸው ቀጥ ያለ: ጽሕማቸውም የተንዠረገገ ነበር:: እድሜአቸውን ግን መገመት የሚቻል አይመስለኝም:: (ጻድቁ የተወለዱት በዚሁ ቀን ነው)

+*" አባ ሳሙኤል ዘቀልሞን "*+

=>በ5ኛው መቶ ክ/ዘመን በግብጽ ደብረ ቀልሞን የነበሩ:
*ከዓበይት ጻድቃን የሚቆጠሩ:
*ቀውስጦስ የሚባለውን መልአክ አማልደው ክንፈ ረድኤቱ እንዲመለስ ያደረጉ::
*መልአክን እንኩዋ ማማለድ የቻሉ::

*የታላቁ አባ አጋቶን ደቀ መዝሙር የሆኑ:
*ስለ ቀናች ሃይማኖት የተደበደቡ:
*መናፍቃን አንድ ዐይናቸውን ያጠፉባቸው:
*በፍጹም ትሕርምት የኖሩ:
*እልፍ ደቀ መዛሙርትን ያፈሩ::

*ተአምራትን የሠሩ:
*ደብረ ቀልሞን ገዳምን የመሠረቱና
*እመቤታችንን በፍጹም ልባቸው የወደዱ ቅዱስ አባት ናቸው:: (ዛሬ ዕረፍታቸው ነው)

+*" ቅዱስ ዮሐንስ ዘደማስቆ "*+

=>በ6ኛው መቶ ክ/ዘመን በሶርያ ደማስቆ የተነሳ:
*ፍልስፍናንም: ትምሕርተ ቤተ ክርስቲያንንም ያጠና:
*ስለ ስዕለ አድኅኖ ክብር ከነገሥታቱ ዘንድ የተዋጋ:
*በጦማር (በደብዳቤ) ለዓለም የሰበከ:
*ስለ እመቤታችን ተናገርክ ብለው ቀኝ እጁን የቆረጡት::

*እመ ብርሃን ግን እንደ ገና የቀጠለችለት:
*በበርሃ ውስጥ ለዘመናት በገድልና በጽሙና የኖረ:
*ከ10ሺ በላይ ድርሳናትን የደረሰ:
*ከዐበይት ሊቃውንት የሚቆጠር ቅዱስ አባት ነው:: (ዛሬ ዕረፍቱ ነው)

+*" ቅድስት በርባራ "*+

=>በዘመነ ሰማዕታት (በ3ኛው ክ/ዘ) የነበረች:
*በአረማዊ ንጉሥ አባቷ ጣዖት እንድታመልክ ብትገደድ "እንቢ" ያለች:
*ከባልንጀራዋ ዮልያና ጋር በፍጹም ትእግስት የታገለች:

*የአባቷን ምድራዊ ክብር ንቃ ስለ ክርስቶስ መከራን የተቀበለች:
*በአባቷ እጅ ከቅድስት ዮልያና ጋር የተገደለች:
*እጅግ ብዙ ተአምራትንም የሠራች ቅድስት: ወጣት ሰማዕት ናት:: (ዛሬ ዕረፍቷ ነው)

+" አባ ኤሲ "+

=>በዘመነ ሰማዕታት በግብጽ (ቡጺር) ከደጋግ ክርስቲያኖች የተወለደ:
*ከልጅነቱ ጀምሮ ዓለምን የናቀ:
*በወጣትነቱ የነዳያንና የእሥረኞች አባት የተባለ:
*ቅድስት ቴክላ የተባለችና እመቤታችን የምታነጋግራት እህት የነበረችው:

*ቅዱስ ዻውሎስ ከሚባል ባልንጀራው ጋር ሰማዕታትን በመንከባከብ ያገለገለ:
*በመንፈሳዊ ቅናት ከዻውሎስና ቴክላ ጋር ለሰማዕትነት የቀረበ::

*እጅግ ብዙ መከራዎቸን የተቀበለ::

*ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሱርያል ወደ ሰማይ አሳርጐ ክብረ ቅዱሳንን ያሳየው::

*ቅዱሳንን የሚዘክሩ ሰዎችን ክብር አይቶ የተደነቀና::
*ከብዙ ተከታዮቹና ቅድስት እህቱ ጋር የተሰየፈ ታላቅ ሰማዕት ነው:: (ዛሬ ዕረፍቱ ነው)

+*" ቅድስት እንባ መሪና "*+

=>በዘመነ ጻድቃን በምድረ ግብጽ የተወለደች::

*ከአባቷ ጋር መንና ወደ ወንዶች ገዳም የገባች::

*ወንድ መስላ የወንዶችን ቀኖና በምንኩስና የተቀበለች::

*ያለ አበሳዋ (ወንድ መስላቸው) "ዝሙት ሰርተሻል" ተብላ ወደ በርሃ የተባረረች::

*ያልወለደችውን ልጅ ያሳደገች::

*ያለ ምግብና ውሃ ለ3 ዓመታት የተሰቃየች::

*ብርድና ፀሐይ የተፈራረቀባትና:

*ስታርፍ ክብሯ የተገለጠላት ቡርክት እናት ናት:: (ዛሬ ልደቷ ነው)

+*" አቡነ ተክለ አልፋ "*+

=>በ14ኛው መቶ ክ/ዘመን በኢትዮዽያ የተነሱ::

*ደብረ ድማሕን / ዲማን (ጎጃም) የመሠረቱ::

*በፍጹም ተጋድሎ የኖሩ::

*ምድረ ጎጃምን በስብከተ ወንጌል ያበሩ::

*በሊቅነታቸው የተመሠከረላቸው::

*መልክአ ኢየሱስን እንደ ደረሱ የሚነገርላቸው::

*ብዙ ተአምራትን የሠሩ (ዛሬም ድረስ የሚሠሩ)::

*የሃገራችን ትምክህት የሆኑ ታላቅ ሐዋርያዊ አባት ናቸው:: (ዛሬ ዕረፍታቸው ነው)

+*" ቅዱስ ገብረ ማርያም "*+

=>በ16ኛው መቶ ክ/ዘ በምድረ ኢትዮዽያ የተወለደ::
*ስም አጠራሩ ያማረ:
*ዛሬ እናንተና እኔ ለምናደርገው የቅዱሳን መታሰቢያ መሠረት የጣለ
*በዓመቱ የሚከበሩ ሁሉን ቅዱሳን የሚዘክር

*365ቱን ቀናት በምጽዋት የተጠመደ:
*የነዳያን አባት የሆነ:
*በአፄ ልብነ ድንግል ግራኝ አህመድ መምጣቱን ሲሰማ ያልደነገጠ:
*ሃብት ንብረቱን ለነዳያን አካፍሎ: ነጭ ልብስ ለብሶ ገዳዮቹን የጠበቀ::

*እንዲያ እንዳማረበት የግራኝ ወታደሮች የሰየፉትና ሞገስ የሆነን አባት ነው:: (ዛሬ ዕረፍቱ ነው)
=>እነዚህንና ስማቸውን ያልጠራናቸውን ሌሎች ቅዱሳንን ዜና ማንበብ: በስማቸው መልካሙን ማድረግና መዘከር ዋጋው በሰማያት ታላቅ መሆኑን ገድለ አባ ኤሲ እና ታላቁ ቅዱስ መጽሐፍ ይናገራል:: (ማቴ. 10:41, ዮሐ. 4:36, ዕብ. 6:10)

=>አምላከ ከዋክብት ቅዱሳን ከዓመጸኛው ትውልድ ይሰውረን:: በረድኤታቸው ጥላ ጋርዶ: ለበረከታቸው ያብቃን::

=>ታሕሳስ 8 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ታላቁ አቡነ ኪሮስ
2.አባ ሳሙኤል ዘደብረ ቀልሞን
3.አባ ዮሐንስ ዘደማስቆ (ሊቁ)
4.አባ ኤሲና ቅድስት ቴክላ
5.ቅዱሳት በርባራና ዮልያና
6.ቅድስት እንባ መሪና
7.አባ ተክለ አልፋ ዘደብረ ድማሕ
8.ቅዱስ ገብረ ማርያም ተአማኒ
9.አባ ያሮክላ ሊቀ ዻዻሳት
10.አቡነ እስትፋሰ ክርስቶስ (ልደታቸው)

=>ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ሙሴ ሊቀ ነቢያት
2.አባ ብሶይ (ቢሾይ)
3.ቅዱሳን 4ቱ እንስሳ (ኪሩቤል)
4.ቅዱስ ማትያስ ሐዋርያ (ከ12ቱ ሐዋርያት)

=>+"+ እግዚአብሔር ቅዱሳንን ስላገለገላችሁ: እስከ አሁንም ስለምታገለግሏቸው ያደረጋችሁትን ሥራ: ለስሙም ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዓመጸኛ አይደለምና:: በእምነትና በትእግስትም የተስፋውን ቃል የሚወርሱትን እንድትመስሉ እንጂ ዳተኞች እንዳትሆኑ ተስፋ እስኪሞላ ድረስ እያንዳንዳችሁ ያን ትጋት እስከ መጨረሻ እንድታሳዩ እንመኛለን::+"+ (ዕብ. 6:10)

<ወስብሐት ለእግዚአብሔር>

https://www.tg-me.com/zikirekdusn
ታኅሣሥ 9

እንኩዋን ለጻድቅና ሰማዕት "ቅዱስ በአሚን" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ

+*" ቅዱስ አባ በአሚን "*+

=>የቤተ ክርስቲያን ታሪክ የተጻፈው በብራናና በብዕር አይደለም:: ይልቁኑ:-
¤እንደ ቀለም የሰማዕታት ደማቸው::
¤እንደ ብዕር አጥንታቸው::
¤እንደ ብራና ቆዳቸው ሆኖ ተጽፏል እንጂ:: ሰማዕታት ለሃይማኖታቸው የከፈሉት ዋጋ እጅግ ታላቅ ነው::

+ስለዚህም "ተጋዳዮች : የሚያበሩ ኮከቦች : የቤተ ክርስቲያን ሻማዎች" ተብለዋል:: እነሱ እየቀለጡ አብርተዋልና::

+ሰማዕትነት በብሉይ ኪዳን የጀመረና እስከ ዳግም ምጽዐተ ክርስቶስም የሚቀጥል ቢሆንም "ዘመነ ሰማዕታት" የሚባለው ከ150 እስከ 312 ዓ/ም ድረስ ያለው ዘመን ነው::

+በተለይ ግን ከ270ዎቹ እስከ 312 ዓ/ም ድረስ ያሉ ዓመታት እጅግ የከፉ ነበሩና የክርስቲያኖች ደም በምድር ላይ ፈሷል:: የሰማዕታት ምሥጢራቸው ቃለ ወንጌል: የጌታ ስብከትና ሕይወት እንጂ ሌላ አይደለም:: (ማቴ. 10:16, ማር. 13:9, ሉቃ. 12:4, ዮሐ. 16:1, ሮሜ. 8:35, ራዕይ. 2:9)

+የቅዱሳን ሰማዕታት መነሻቸው ቅዱስ እስጢፋኖስ ሲሆን ፍጻሜአቸው ደግሞ ቅዱስ ዼጥሮስ ሊቀ ዻዻሳት ነው::

=>ከዓበይት ሰማዕታትም አንዱ ቅዱስ በአሚን ነው:: በቤተ ክርስቲያን "ሰማዕት ዘእንበለ ደም (ሰይፍ)" የሚባሉ ቅዱሳን አሉ:: ሰማዕት ዘእንበለ ደም ማለት "እንደ ሰማዕታት መከራውን ሁሉ ተቀብለው ሳይሰየፉ (ሳይገደሉ) የመከራውን ዘመን ያለፉ" ናቸው::

+ለምሳሌ ከሠለስቱ ምዕት (ከ318ቱ ሊቃውንት) አብዛኞቹ እንደዚህ ባለ ሕይወት ያለፉ ናቸው:: ቅዱስ በአሚንም እንዲሁ ዓይነት ዜና ሕይወት ያለው አባት ነው::

¤ጥንተ ነገሩስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-

+ቅዱስ በአሚን ተወልዶ ያደገው በደቡብ ግብጽ በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን ነው:: ቅዱሱ ከልጅነቱ ክርስትናን የተማረ ነበርና ሰው ሁሉ የሚወደው ታማኝ ሰው ሆነ:: ምንም ሃብታም ሰው ባይሆንም ተቀጥሮ ሠርቶ በሚያገኛት ገቢው መልካምን ይሠራ ነበር::

+በዘመኑም ከቅንነቱ የተነሳ "መታመንስ እንደ በአሚን" ይባል ነበር:: ቅንነቱን የወደዱ ሁሉ ይሹት ነበር:: በከተማው ውስጥ እጅግ ብዙ ሃብት የነበራቸው ባል እና ሚስትም ወደ ቤታቸው ወስደው መጋቢ (ተቆጣጣሪ) አደረጉት::

+ጠባዩን ከተረዱ በሁዋላ ግን ሙሉ ሃብት ንብረታቸውን በእጁ አስረክበውት ያስተዳድርላቸው ነበር:: ሲወጡና ሲገቡም እያዩት ደስ ይሰኙበት ነበር:: እርሱ ግን ልቡ በክርስቶስ ፍቅር የተመሰጠ ነበርና ለዚህ ዓለም ጉዋዝ ትኩረትን አይሰጥም ነበር:: ይጾም ይጸልይ ነበር እንጂ::

+አንድ ቀን ግን የቤቱ ባለቤቶች (ባልና ሚስት) ሲመጡ ቤታቸው እንደሚገባ ተደራጅቶ: ቁልፉ ተቀምጦ አገኙት:: ወዳጃቸው በአሚን ግን የለም:: ደንግጠው ቢያፈላልጉት ሊያገኙት አልቻሉም:: በመጨረሻ ግን መንኖ ገዳም መግባቱን ሰምተው ፈጽመው አዘኑ::

+ከእርሱ መለየትን አይፈልጉም ነበርና:: አልቅሰው ወደ ቤታቸው ሊመለሱ ሲሉ ሚስት "አይሆንም! ሔደን እናምጣው" ስላለች ወደ መነነበት ገዳም ሔደው: እያለቀሱ ይመለስላቸው ዘንድ ለመኑት::

+እርሱ ግን "ለሰማያዊ ሠርግ ታጭቻለሁና ከእንግዲህ የክርስቶስ ነኝ" አላቸው:: እንዳልተሳካላቸው ሲያውቁ ፈጽመው እያዘኑ ወደ ቤታቸው ተመለሱ:: ቅዱስ በአሚን ግን ገዳማዊ ሕይወትን በተጋድሎ ጀመረ::

+ይጾማል: ይጸልያል: ይሰግዳል: ይታዘዛል:: በዚህ መንገድ ሥርዓተ ገዳምን በበርሃ ሆኖ ሲፈጽም በዓለም እነ ዲዮቅልጢያኖስ ክርስቲያኖችን ይገድሉ ነበር::

ዜና ሰማዕታትም ቀስ እያለ ቅዱሱ ወዳለበት ገዳም ደረሰ::

+ነገሩን ሲሰማ ደስ አለው:: እርሱ ስለ ክርስቶስ ሲሉ ደምን ማፍሰስና መከራን መቀበል ከሁሉም ነገር የተሻለ እንደ ሆነ ያውቅ ነበርና:: ቀጥሎም ወደ ከተማ ሒዶ ደሙን ለማፍሰስ በቁርጥ ወስኖ ዘለቀ::

+በዚያም የንጉሥ ወታደሮች አግኝተውት ለጣዖት ይሰዋ ዘንድ ታዘዘ:: ቅዱስ በአሚን ግን "መስዋዕት የሚገባው ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ: ለባሕርይ አባቱ ለአብና ለመንፈስ ቅዱስ ነው:: ለፍጡር አልሰዋም" ሲል መለሰላቸው:: በዚህም ምክንያት ወታደሮች እየተፈራረቁ ደበደቡት::

+ደሙንም አፈሰሱት:: ምንም እንዳልተለወጠ ሲያውቁ ወደ እስር ቤት ጨመሩት:: ከዚያም በቀን በቀን እያወጡ ይደበድቡት: በእሳት ያቃጥሉት: በተለያዩ ማሰቃያዎች በመከራ ያውሉት ነበር:: እርሱ ግን ክርስቶስን ከመቀደስ በቀር አንዳች አይመልስላቸውም ነበር::

+በብዙ አሰቃይተው እንቢ ቢላቸው ወስደው በጨለማ ቤት ዘጉበት:: በዚያም ጥለውት ዓመታት አለፉ:: ሁሉንም በጊዜው የሚሠራ ጌታ ግን እነዚያን የመከራ ዘመናት አሳልፎ ዲዮቅልጢያኖስና መክስምያኖስን አጠፋቸው::

+በፈንታቸውም መፍቀሬ ክርስቶሳውያን ቅዱስ ቆስጠንጢኖስን አነገሠ:: አብያተ ክርስቲያናት ታነጸ:: ስለ ክርስቶስ የታሠሩ ሁሉ ነጻ ወጡ:: በዚህ ጊዜ ምዕመናን መጥተው ቅዱስ በአሚንን ከወደቀበት አነሱት::

+በወቅቱም ንጉሡ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ "አጽመ ሰማዕታትን ሰብስቡ: በመከራው አልፈው በእድሜ ካሉትም መካከል መምጣት የሚችሉትን አምጡልኝ" ብሏልና ቅዱስ በአሚንን የመሰሉ 72 ክቡራን ተገኙ:: ከእነርሱም መካከል ታላቁ አባ ኖብና አባ ዘካርያስ ይገኙበታል::

+እነዚህ አበው ቅዱሱን ንጉሥ ባርከውት ሲመለሱ ቅዱስ በአሚን ወደ እስሙናይን ተጉዞ በበዓቱ ተቀመጠ:: በዚያም ደቀ መዛሙርት በዝተውለት እንደ ገና ገዳማዊ ሕይወቱን ቀጠለ:: በበዚያም ሳለ ብዙ ተአምራትን ሠራ::

+ድውያንን ፈወሰ:: መናፍቃንንም በጸሎቱ ከአካባቢው አራቀ:: አንድ ቀንም የሮም ንጉሠ ነገሥት ሚስት ወደ እርሱ ዘንድ መምጣቷን ሰማ:: ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ገብተው "አባ! ንግሥቲቱ ትፈልግሃለች" አሉት::

+እርሱ ግን "እኔ ከምድራዊ ንግሥት ዘንድ ምን አለኝ! አልወጣም" አላቸው:: ደቀ መዛሙርቱ ግን መልሰው "አባ! እዘንላት: በመከራ ውስጥ ናት" ሲሉት "እሺ" ብሎ ወጣ::

+ንግሥቲቱ ምንም ብዙ ሠራዊት ብታስከትል አንጀቷ ታጥፎ ተጐንብሳ ነበር የምትሔደው:: እርሱም በጀሮዋ ጠጋ ብሎ የሕመሟን ምሥጢር ሲነግራት ተገርማ እግሩ ሥር ወድቃ ተማጸነችው:: ነገሩ እንዲህ ነው:-

+ከ15 ዓመታት በፊት አንድ የተባረከ ዲያቆን በቤተ መንግስቷ አካባቢ ይኖር ነበር:: እርሱም (ዮሐንስ ይባላል) የዮሐንስን ራዕይ ቁሞ ዘወትር ያነብላታል:: በዚህ የቀኑ የንጉሡ ባለሟሎች በሃሰት "ሚስትህን ዲያቆኑ እያማገጠ ነው" ሲሉ ለንጉሡ ነገሩት::

+ንጉሡም ነገሩ እውነት ስለ መሰለው ወታደሮቹን ዮሐንስን ከነ ሕይወቱ ባሕር እንዲያሰጥሙት አዘዘ:: ይሕንን የሰማችው ንግስት ለቀናት ስታለቅስ አንጀቷ በመቃጠሉ ታመመች:: እየቆየም ሆዷ ታጠፈ:: ለ15 ዓመትም የሚያድናት አጥታ ተንከራተተች::

+በሁዋላ ግን ሰዎች ስለ ቅዱስ በአሚን ቅድስና ሲናገሩ ሰምታ መጣች:: ለዛ ነው ቅዱስ በአሚን ምሥጢሯን ሹክ ያላት:: ቀጥሎም 2 በጐ ነገርን ፈጸላት:: መጀመሪያ ጸሎት አድርጐ ሆዷን ቢዳስሳት በቅጽበት ድና ቀና አለች::

+2ኛው ግን "ያ የምትወጂው የተባረከ ዲያቆን ዮሐንስ አልሞተም:: መላዕእክት ከባሕር አውጥተው እገሌ በሚባል ደሴት አኑረውታል" አላት::
እርሷም ተመልሳ በደስታ ለባሏ ነገረችው::
+ንጉሡም ተጸጽቶ ዮሐንስን ካለበት አስመጣው:: አበውም የሮሜ ሊቀ ዻዻሳት አድርገውት ብዙ መጻሕፍትን ተርጉሟል:: ቅዱስ በአሚን ግን በቅድስና ኑሮ በዚህች ቀን ዐርፎ በዝማሬ ተቀብሯል::=>አምላከ ቅዱስ በአሚን በጸሎቱ ይማረን:: ከትእግስቱ ይክፈለን:: ከበረከቱም ያሳትፈን::

=>ታሕሳስ 9 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ አባ በአሚን (ጻድቅና ሰማዕት)
2.ቅድስት አርምያ
3.ቅዱስ ዘካርያስ

=>ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱሳን 318ቱ ሊቃውንት
2.አባ በርሱማ ሶርያዊ (ለሶርያ መነኮሳት ኁሉ አባት)
3.አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ
4.የብሔረ ብፁዐን ጻድቃን
5.አባ መልከ ጼዴቅ ዘሚዳ
6.ቅዱስ ዞሲማስ ጻድቅ

=>+"+ አባቶች ሆይ! ከመጀመሪያ የነበረውን አውቃቹሃልና እጽፍላቹሃለሁ:: ጐበዞች ሆይ! ክፉውን አሸንፋቹሃልና እጽፍላቹሃለሁ:: ልጆች ሆይ! አብን አውቃቹሃልና እጽፍላቹሃለሁ:: አባቶች ሆይ! ከመጀመሪያ የነበረውን አውቃቹሃልና እጽፍላቹሃለሁ:: ጐበዞች ሆይ! ብርቱ ስለ ሆናችሁ: የእግዚአብሔርም ቃል በእናንተ ስለሚኖር: ክፉውንም ስላሸነፋችሁ እጽፍላቹሃለሁ:: +"+ (1ዮሐ. 2:13)

   <<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
" ታኅሣሥ 10 "

<<< እንኩዋን ለቅዱሳን ሊቃውንት "አባ ኒቆላዎስ" : "አባ ሳዊሮስ" እና "ቅድስት ሱርስት" ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ >>>

+*" ቅዱስ ኒቆላዎስ ሊቅ "*+

=>ቅዱስ ኒቆላዎስ:-
*ሃይማኖቱ የቀና::
*ምግባሩ የጸና ሊቅ::
*ብዙ መከራን የተቀበለ ሰማዕት::
*ብዙዎችን ያሳመነ ሐዋርያ::
*በበርሐ ለዘመናት የተጋደለ ጻድቅ::
*በዽዽስና ያገለገለ እረኛ እና:
*ከ318ቱ ሊቃውንት አንዱ ነው::

+የተወለደው በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን ሲሆን ሃገሩ ሜራ ትባላለች:: ይህች ሃገር ዛሬ የት እንዳለች ማወቅ ባንችልም ታሪክ ግን የቀድሞዋ ሮም ግዛት እንደ ነበረች ይነግረናል:: የቅዱስ ኒቆላዎስ ወላጆች የዘመኑ ጥሩ ክርስቲያኖች ነበሩ::

+በሕጉ: በሥርዓቱ: በሥጋ ወደሙና በምጽዋት ቢኖሩም ልጅ አልነበራቸውም:: እግዚአብሔርን ሲለምኑ የጉብዝናቸው ዘመን አልፎ አረጁ:: ልጅ መጠየቁንም ተውት:: ልክ እነሱ መጠየቁን ሲያቆሙ ግን እግዚአብሔር ይሕንን ቅዱስ ፍሬ በዮና ማሕጸን ላይ ፈጠረ::

+እነርሱም ተገርመው ፈጣሪን እያመሰገኑ ተወለደ:: እንደ ተወለደ ግን ዓይናቸው ድንቅ ነገርን ተመለከቱ:: አትበው ሊያነሱት ሲጐነበሱ በራሱ ጊዜ ብደግ ብሎ ፈጣሪውን ሲያመሰግን ሰሙት::

+ለ2 ሰዓት ያሕልም ምንነቱን ያላወቁትን ጸሎት ሲያደርስ ቆየ:: መቼም የዕለት ሕጻን ይሕንን ማድረጉ እጅግ ድንቅ ነው:: ከዚህ በሁዋላም የሕጻኑ ቅዱስ ኒቆላዎስ አስገራሚ ነገሮቹ ቀጠሉ::

+ለምሳሌ:- በአጽዋማት: በረቡዕና በዓርብ ዕለታት 9 ሰዓት ካልሆነ የእናቱን ጡት አይጠባም:: ሁሌም ደግሞ የፈለገውን ያህል ቢፈስ የእናቱን የግራ ጡት አይጠባም ነበር:: ሁሌም የሚጠባው በስተቀኝ ያለውን ጡቷን ብቻ ነበር እንጂ::

+እንዲህ እንዲህ እያለ ቅዱስ ኒቆላዎስ አደገ:: እርሱ ወጣት በሆነ ጊዜ አረጋውያን ወላጆቹ ብዙ ሃብት: 400 የወርቅ ዲናርና የመሳሰለውን ትተውለት ዐረፉ:: እርሱ ግን ሁሉንም ትቶት በ16 ዓመቱ በርሃ ገባ::

+በዚያ ሲጾም: ሲጸልይ: ሲሰግድ ያዩ አበው ሁሉ ይገረሙ ነበር:: ሲሠራም: ሲታዘዝም: ሲሰግድም እንደ መንኮራኩር ፈጣን ነበርና:: በሕጻን ገላው ይሕንን ማድረጉ በእርግጥ ይደነቃል:: የቀናውን የሃይማኖት ትምሕርትንም ቶሎ በማጠናቀቁ ገና በ19 ዓመቱ ቀሲስ አድርገው ሾሙት::

+ቅስናን ከተሾመ በሁዋላ ተጋድሎውንም: አገልግሎቱንም አስፋፋ:: ካለበት ገዳም እየተነሳ ብዙ አካባቢዎችን በስብከት ያደርስ ነበር:: በወንጌል አገልግሎቱ ጊዜም ብዙ ተአምራትን ሲሠራ በተለይ በአንድ ቀን የአንድን አካባቢ ሕዝብ ጥቂት ሕብስትን እንደ ፈጣሪው አበርክቶ አብልቷል::

+የተረፈውም ብዙ መሶብ ተነስቷል:: (ዮሐ. 6:5) ጌታችን "በእኔ የሚያምን እኔ የምሠራውን እርሱ ደግሞ ይሠራል" ብሏልና:: (ዮሐ. 14:12) በተረፈም ፈዋሴ ዱያን: መንስኤ ሙታን ሆኖ ዘመናትን አሳልፏል::

+አንድ ቀን ግን በበአቱ እያለ የአንድ ሰውና የ4 ሴት ልጆቹ ነፍስ ሊጠፋ መሆኑ ይታወቀዋል:: ይሔውም በአቅራቢያው ባለ ከተማ የሚኖር አንድ ባለ ጠጋ ሃብቱ አልቆበት ተቸግሯልና ሰይጣን ክፉን እንዲሠራ ሹክ አለው:: ሰውየውም ለ4 ሴት ልጆቹ 4 ቤት አሰናድቶ በዝሙት ሊሸጣቸው ተዘጋጀ::

+ይሕንን በጸጋ ያወቀው ቅዱስ ኒቆላዎስ "ከመገስጽ መርዳት ይቀድማል" ብሎ: ማንም ሳያየው ወላጆቹ ከተውለት 400 የወርቅ ዲናር 100ውን ከፍሎ በሌሊት ከሰውየው በር ላይ ጥሎለት ተሰወረ:: ሰውየውም ተገርሞ የኃጢአት ሃሳቡን ተወ::

+ያ ሥራ ፈት ሰው ግን እንደ ገና ገንዘቡን በልቶ ተመሳሳይ ድርጊት ሊፈጽም ማሰቡን ቅዱሱ አወቀ:: አሁንም ተደብቆ 100 የወርቅ ዲናር ጣለለት:: ይህ ነገር 3ኛና 4ኛም ተደገመ:: በ4ኛው ግን ሰውየው ወደ ልቡናው ተመልሶ ይሕንን ያሕል ቸርነት የሚያደርግለትን ሰው ተደብቆ አየው::

+ሩጦም ሒዶ ከቅዱስ ኒቆላዎስ እግር ላይ ወደቀ:: "አባቴ! ነፍሴን ከእሳት አወጣሃት" አለው:: ቅዱሱም መልሶ መክሮ: ምሥጢሩን ግን ለማንም እንዳይናገር አሳስቦት ተመለሰ:: ያ ሰው ከዚያ በሁዋላ በጐ ክርስቲያን መሆን ችሏል::

+ለቅዱስ ኒቆላዎስ ግን አንድ ቀን ጌታችን: እመቤታችን: ቅዱስ መልአክ መጥተው ስጦታን አበረከቱለት:: መልአኩ ዙፋን: እመ ብርሃን የክብር ልብስን ሲሰጡት ጌታ ደግሞ ወንጌሉን ሰጠው::

+ወዲያውም አበው ካለበት በርሃ መጥተው የሜራ ዻዻስ እንዲሆን ሾሙት:: የተሾመበት ጊዜ ዘመነ ሰማዕታት ነበርና የሜራን ሕዝብ አጽንቶ ለሰማዕትነት በማብቃት ትልቁ ሃላፊነትም ተወጥቷል::

+ነገር ግን ዜና ሕይወቱ በነገሥታቱ ዘንድ ሲሰማ ለፍርድ አቀረቡት:: ስለ ክርስቶስ ሰብከሃል በሚል ስቃይና ሞት ተፈረደበት:: ወደ አውደ ስምዕ (የሰማዕታት አደባባይ) ወስደው ገረፉት: በእሳት አቃጠሉት: ደሙንም አፈሰሱት::

+ነገር ግን እግዚአብሔር ለሌላ ሙያ ይፈልገዋልና አልሞተም:: እነርሱ ግን በጭካኔ ለዘመናት አሰቃዩት:: በመጨረሻም እስር ቤት ውስጥ ጣሉት:: እርሱ በእስር ቤት ሳለም ዘመነ ሰማዕታት ተፈጸመ:: ቆስጠንጢኖስ ነገሠ::

+በዚህ ጊዜም ምዕመናን ቅዱስ አባታቸውን ከእስር ፈትተው በመንበሩ ላይ አኖሩት:: ለ13 ዓመታት ሕዝቡን ሲመራ ቆይቶ አርዮስ በካደ ጊዜ ወደ ኒቅያ አመራ:: በዚያም ለቅዱሳን ሊቃውንት 318ኛ ሆኖ ተቆጠረ:: በጉባኤው ፊትም ተአምራትን አሳየ::

+በኒቅያ ከባልንጀሮቹ ጋር አርዮስን አውግዞ: ሥርዓትን ሠርቶ: መጻሕፍትን ጽፎም ወደ ሃገሩ ተመልሷል:: በመንበሩ ላይ 40 ዓመታት ሲሞሉትም ዐርፎ በዚህች ቀን ተቀብሯል::
<<ኒቆላዎስ ማለት "መዋኤ ሕዝብ - ሕዝብን የሚያሸንፍ" ማለት ነው>>

+"+ ቅድስት ሱርስት +"+

=>ይህቺ ቅድስት እናት በዘመነ ጻድቃን ከተነሱ ስመ ጥር እናቶች አንዷ ናት:: ገና ከልጅነቷ በቤተ መንግስት ውስጥ ብታድግም ከመልካም እናቷ መልካምነትን ወርሳለች:: እጅግ በተቀማጠለ ኑሮ ውስጥ ሆና ሕይወቷን ክርስቶስን አልዘነጋችውም::

+ደም ግባቷ እጅግ የተወደደ ነበርና ገና በ12 ዓመቷ ለነገሥታቱ ልጆች ሚስት ትሆን ዘንድ ታጨች:: መቼም ሃብትን: ክብርን እንኩዋን እንዲህ በለጋ እድሜ አርጅተንም ቢሆን መናቁ አይሳካም::

+ቅድስት ሱርስት ግን አንድ ቅን ሃሳብ መጣላት:: ወደ አባቷ ዘንድ ሔዳም "ወደ አድባራት ሔጄ ከሠርጌ በፊት እንድሳለም ፍቀድልኝ" ስትል ጠየቀችው:: እርሱ ግን "ከሠርግሽ በሁዋላ ይደርሳል" ቢላት "በድንግልናየ ሳለሁ መቃብርህን እስማለሁ ብዬኮ ለፈጣሪየ ተስያለሁ" አለችው::

+አባቷም ከ300 ዲናር ወርቅና ከብዙ ሠራዊት ጋር ወደ ኢየሩሳሌም ላካት:: ቅድስቷ ሕጻንም በዚያ የጌታን መቃብር ተሳልማ ወታደሮችን ጠፋቻቸው:: ከዚያ በሁዋላ የት እንደ ደረሰች ያወቀ የለም:: ሱርስት ግን ከኢየሩሳሌም ግብጽ ወርዳ ወርቁ ገዳም እንዲታነጽበት አደረገች::

+እርሷ ግን መንኩሳ ወደ በርሃው ገባች:: በዚያም 27 ዓመት ሙሉ ማንንም ሳታይ: በጭንቅ: በመከራ: በአርምሞ ተጋደለች:: አንድ ቀን ግን ባሕታውያንን የሚመግብ ሲላስ የሚሉት ካህን አግኝቶ ዜናዋን ከነገረችው በሁዋላ ሰግዳ ዐርፋለች:: በ39 ዓመቷም በዚህች ቀን ቀብሯታል::
+*" ታላቁ ቅዱስ ሳዊሮስ "*+
=>ቅዱስ ሳዊሮስ በ6ኛው መቶ ክ/ዘመን መጀመሪያ አካባቢ በሶርያ አንጾኪያ የተነሳ አባት ነው:: ወቅቱ መለካውያን (2 ባሕርይ ባዮች) የሰለጠኑበት እንደ መሆኑ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ምእመናን ያነሱበትና የሚሰደዱበት ጊዜ ነበር:: በዚህ ጊዜ ነበር ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ሳዊሮስ በሥላሴ ፈቃድ ለቤተ ክርስቲያን የተነሳው:: ሊቃውንት አንበሳ ሲሉ ይጠሩታል::

+ቅዱሱ ለተዋሕዶ ብዙ ሆኖላታል:: የመናፍቃን ጸር በመሆኑ ብዙ ድርሰቶችን ደርሷል:: ንጉሡን ዮስጢያኖስን (Justinian) ሳይቀር በይፋ ይገስጸው ነበርና ንጉሡ ሊገድለው ቆረጠ::

+ሃይማኖቷ የቀና ንግሥቲቱ ታኦድራ ግን ይህንን ስትሰማ በሌሊት ወደ ሊቁ ሒዳ "እባክህን ሽሽ" አለችው:: እርሱ ግን "ሞት ለእኔ ክብር ነውና አልሔድም" ሲል መለሰላት:: አባቶችን ሰብስባ "ስለ ቤተ ክርስቲያን ስትል" ብለው ለምነው ወደ ግብጽ ሸኙት::

+እርሱ እየሔደ ገዳዮቹ ያሳድዱት ገቡ:: መንገድ ላይ ቢደርሱበትም ተሰወረባቸው:: ለብዙ ቀናትም አብሯቸው ተጉዋዘ:: እነርሱ ተስፋ ቆርጠው ሲመለሱ እርሱ ግን ምድረ ግብጽ ደረሰ::

+በምድረ ግብጽም የዽዽስና ልብሱን ትቶ የመነኮሳትን አሮጌ ልብስ ለብሶ ሕዝቡንና መነኮሳቱን አስተማረ: አጸና:: በየቦታውም ብዙ ተአምራትን ሠራ::

+አባቶች መነኮሳትም ማንነቱን ባወቁ ጊዜ ሰገዱለት:: ዶርታኦስ (ዱራታኦስ) በሚባል አንድ ደግ ሰው ቤትም በ6ኛው መቶ ክ/ዘ አጋማሽ አካባቢ የካቲት 14 ቀን ዐርፏል:: ዛሬ የታላቁ ሊቅ በዓለ ፍልሠቱ ነው::

=>አምላከ ቅዱሳን ይርዳን: ይቅርም ይበለን:: ከበረከታቸውም ያሳትፈን::

=>ታሕሳስ 10 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ኒቆላዎስ ሊቅ
2.ቅዱስ ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ
3.ቅድስት ሱርስት ገዳማዊት
4.ቅዱስ ጥዋሽ ሕጽው
5.ቅዱሳን ተላስስና አልዓዛር

  ወርኀዊ  የቅዱሳን  በዓላት
1.ቅዱስ ናትናኤል ሐዋርያ
2.አቡነ መልክዐ ክርስቶስ
3.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ወልደ እልፍዮስ)
4.ቅድስት ዕሌኒ ንግስት
5.ቅዱስ ዕፀ መስቀል
6.ታላቁ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር
2024/09/27 07:20:52
Back to Top
HTML Embed Code: