Telegram Web Link
#ታኅሣሥ_16 #አቡነ_መርቆሬዎስ
ዘደብረ ድማኅ +

በውስጡ አጋንንት ያደሩበት ቁመቱ 170 ክንድ ወርዱ 9 ክንድ ከስንዝር የሆነ ሰይጣን ያደረበት ዘንዶ ቢመጣባቸው በጸሎት ወደ ፈጣሪያቸው አመልክተው #ቅዱስ_ሚካኤል በሰጣቸው #መስቀል ዘንዶውን የገደሉት አቡነ መርቆሬዎስ ዘደብረ ድማኅ ዕረፍታቸው ነው።

የአቡነ መርቆሬዎስ ወላጆቻቸው ካህኑ ቶማስ ስምዖን እና ሰሎሜ #እግዚአብሔርን የሚያገለግሉ ቅዱሳን ስለነበሩ በየወሩም ዝክረ ቅዱስ ሰማዕት መርቆሬዎስ (ፒሉፓዴር) እያደረጉ ሲኖሩ በእለተ ቀኑ ተኣምር ስለተደረገላቸው የልጃቸውን ስም መርቆሬዎስ ብለው ሰየሙት፡፡

አቡነ መርቆሬዎስ ከተወለዱበት ጊዜ ጀምሮ ሲያሳዩት የነበው ተግባራት ሁሉ የትልቅ ሰው እንጂ የአንድ ሕፃን ጠባይ ስላልሆነ ወላጆቻቸው በአንክሮ ያስተውሉ ነበር፡፡ አቡነ መርቆሬዎስም ፊደል በመቁጠር የጀመሩት መንፈሳዊ ትምህርት 22 ዓመት ሲሞላቸው የብሉይ ኪዳንና የሐዲስ ኪዳን እንዲሁም የሁሉም መጻሕፍት ምሥጢር ተገለጠላቸው፡፡ ከአቡነ ኤዎስጣቴዎስ ደግሞ በ33 ዓመታቸው በደብረ ሸማና እያሉ ምንኵስናን እና አስኬማን መላእክትን ተቀበሉ፡፡ ከዚህኽም በኋለ አቡነ መርቆሬዎስ ለረጅም ጊዜ በምናኔ ኖረው ወንጌልን በመስበክና ክርስትናን በማስፋፋት ወደ ተለያዩ ሀገሮች እየተዘዋወሩ እያስተማሩ በርካታ ተኣምራትንም እያደረጉ ለ67 ዓመታት ያህል በታላቅ ተጋድሎ ኖሩ፡፡ አቡነ መርቆሬዎስ የመንፈስ አባታቸው የሆኑት አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ወደ ኤርትራ ሀገር እንደሚሔዱ በ #መንፈስ_ቅዱስ ዐውቀው በራቂት የምትባል ቦታ ላይ ኹለቱ ቅዱሳን ተገናኙ፡፡ ኹለቱም ቅዱሳን አብረው ወንጌል እየሰበኩ ማይምነ ሲደርሱ ግን ሕዝቡን ከ #እግዚአብሔር ሕግ ርቆ በኀጢአት ወድቆ አገኙት፤ በዚያ ያሉ ክፉዎች ሰዎችም
በሰይጣን ምክር ተመርተው አባቶቻችን ተኝተውባት የነበረችውን ጎጆ በእሳት አቃጠሏት።

ቅዱሳኑ አቡነ መርቆሬዎስና አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ግን በዛ እሳት ሳይነኩ በ #እግዚአብሔር ተኣምር ዳኑ፡፡ ከዚኽም በኋላ እነዚህ ቅዱሳን አባቶች በአሁኑ ደብረ ደናግል ደብረ ድማኅ በሚባለው ቦታ ላይ ሱባኤ ገብተው አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ለሰባት ዓመት፣ አቡነ መርቆሬዎስ ደግሞ ለአራት ዓመት ባእት አበጅተው በጽኑ ተጋድሎ ኖሩ፡፡ ከሰባት ዓመት ሱባኤ በኋላ ከ #እግዚአብሔር ባዘዛቸውና ራእይ ባዩት መሠረት አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ወደ አርማንያ እንዲሔዱ ሲነገራቸው አቡነ መርቆሬዎስን ደግሞ አንዲት ወፍ እየመራቻቸው ዛሬ ላይ በስማቸው ወደሚጠራው ታላቁ ገዳም ደብረ ድማኅ አደረሰቻቸው፡፡ አቡነ መርቆሬዎስም ቦታዋን እንዳዩአት ‹‹ይህቺ ለዘለዓለም ማረፊያየ ናት›› አሉ፡፡ የክብር ባለቤት #መድኀኔዓለምም በአካል ተገልጦላቸው መጥቶ በአራቱ ማዕዘን ባረከላቸው፡፡ በዚህ ቦታ ላይ ይኖሩ የነበሩት ሰዎችም አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ወደ አርማንያ እንደሚሔዱ ሲሰሙ ‹‹የእናንተ ረድኤት እንዲሆንልን ቀድሳችሁ አቊርቡን›› ሲሏቸው ሁለቱ ቅዱሳን በጋራ ጥር 18 ቀን ቅዳሴ ቀድሰው ሕዝቡን አቊርበዋል፡፡

አቡነ መርቆሬዎስም አባታቸውን አቡነ ኤዎስጣቴዎስን ተከትለው ኹለቱም እስከ ሱዳን ድረስ ሔደው ወንጌልን በመስበክ ሰፊ ሐዋርያዊ አገልግሎት ሰጥተዋል፡፡ ከዚኽም በኋላ በግብፅ ተሻግረው አርማንያ ደርሰው ወደ ኢየሩሳሌም በመሔድ ቅዱሳት መካናትን ተሳልመዋል፡፡ ከዚያም አቡነ መርቆሬዎስ ወደ ገዳም ተመልሰው ሲመጡ ዉጡሕ በተባለ ቦታ ላይ በኣት አጽንተው ሱባኤ ያዙ፡፡ እርሳቸውም በዕለተ ዐርብ መጋቢት 12 ቀን የ #ቅዱስ_ሚካኤል በዓል ዕለት በኣታቸው ውስጥ እየጸለዩ ሳሉ ድንገት ቁመቱ 170 ክንድ ጎኑ ደግሞ 9 ክንድ ከስንዝር የሚሆን ሰይጣን ከነጭፍሮቹ በውስጡ ያደረበት ታላቅ ዘንዶ ይውጣቸው ዘንድ መጣ፡፡ ነገር ግን #እግዚአብሔር ከእርሳቸው ጋር ስለነበር ጸሎታቸውን ሰምቶ #ቅዱስ_ሚካኤልን ላከላቸው፡፡ መልአኩም ድል የሚያደርጉበትን #መስቀል ሰጣቸው፡፡

ጻድቁም ከመልአኩ በተቀበሉት# ቅዱስ_መስቀል በ #ሥላሴ ስም ቢያማትቡበት ዘንዶው ተሰንጥቆ በውስጡ አድረውበት የነበሩት አጋንንት ከዘንዶው ወጥተው ሮጠው ሊያመልጡ ሲሉ አባታችን አወገዟቸው፡፡ ዘንድውንም ወስደው ዱበና በሚባል በረሓ ውስጥ ጣሉት፡፡ ጻድቁም ዘንዶውን ስለገደሉላቸው ለአካባቢው ሰዎችም ሆነ ለፍጥረታት ሁሉ ሰላምና ዕረፍት ሆነላቸው፡፡ ይኽንንም መሠረት በማድረግ በየአመቱ መጋቢት 12 ቀን መነኰሳት አባቶች ከገዳም ታቦት ይዘው ወደዚህ ቦታ በመሔድ ይቀድሳሉ፣ በዓሉንም ያከብራሉ፡፡ በወቅቱ ሊቀ መላእክት #ቅዱስ_ሚካኤል የሰጣቸው ረጅም# መስቀልም እስከ አሁን ድረስ የተለያየ ተኣምራት እያደረገ በገዳሙ ይገኛል፡፡ አቡነ መርቆሬዎስ ከብዙ ተጋድሎ በኋላ ‹‹ሥጋየ የሚያርፍበትን ቦታ ግለጽልኝ›› ብለው ወደ #እግዚአብሔር ቢጸልዩ በአሁኑ ጊዜ ቅዱስ ዐፅማቸው በክብር ያረፈበት ገዳም ደብረ ድማኅ እንደሆነ ገለጸላቸው፡፡ በ1340 ዓ.ም ስድስት መቶ መነኰሳትና ሦስት መቶ መነኰሳያይት ወደ አባታችን መጥተው መንኵሰዋል፡፡ አቡነ መርቆሬዎስም ሥርዐተ ምንኵስና ሠርተው ገዳም ገድመው ልጆቻቸውን በቅድስና ሲጠብቁ ኖሩ፡፡ አቡነ መርቆሬዎስ ገዳማቸው ሳሉ በአርማንያ ሀገር የአቡነ ኤዎስጣቴዎስ የዕረፍታቸው ነገር በራእይ ስለተገለጠላቸው ከ25 መነኰሳት ጋር ወደ አርማንያ ሔዱ፡፡ ነገር ግን ለመርከብ የሚከፍሉት ገንዘብ ስላልነበራቸው አስቀድመው ከአባታቸው ጋር በአጽፋቸው የተሻገሩትን ባሕር በደመና ተጭነው በማለፍ አርማንያ ሀገር ደርሰው አቡነ ኤዎስጣቴዎስን አገኟቸው፡፡ ኹለቱም ቅዱሳን ሲነጋገሩ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ‹‹…ምሰሶ ተሰበረ›› አሉ፡፡ አቡነ መርቆሬዎስም ‹‹ምሰሶው ምንድነው?›› ብለው ሲጠቋቸው ‹‹የኢትዮጵያው ንጉሥ ዓምደ ጽዮን ሞተ›› አሏቸው፡፡ አቡነ ኤዎስጣቴዎስም እንደተናገሩት በዚያን ጊዜ ንጉሡ በኢትዮጵያ ምድር እንደ ሞተ ተረጋገጠ፡፡ ከዚኽም በኋላ አቡነ መርቆሬዎስ አባታቸው አቡነ ኤዎስጣቴዎስን አሟሙተው ማለትም ገንዘው ቀብረው ወደ ገዳማቸው ሲመለሱ ዳግመኛም ታናሽ ወንድማቸው አቡነ አብሳዲም ዐርፈው ስለደረሱ እጅግ አዘኑ፡፡አቡነ መርቆሬዎስ ከአርማንያ ተመልሰው ሲመጡ ተኸላ የሚባል ቦታ ገዳም መሥርተው ዐሥር ዓመታት ኖረዋል፡፡ ቅዱስ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ወደ አርማንያ ሲሔዱ ‹‹እንደ እኔ ሁናቸው›› ብለው የእጅ መስቀላቸውን የሰጡት ለአቡነ አብሳዲ ነበር፡፡ ከአቡነ አብሳዲ ዕረፍት በኋላ የገዳሙን ኀላፊነት የተረከቡት አቡነ መርቆሬዎስ ሆኑ፡፡ በአቡነ መርቆሬዎስ ገዳም በደብረ ድማኅ አበ ምኔት ሆነው የተሾሙት አባቶች ሁሉ በዚህ መንበር ነው የሚሾሙት፡፡ አቡነ መርቆሬዎስ ተጋድሏቸውን ፈጽመው ዕድሜያቸውም እየገፋ ሔዶ 130 ዓመት ሲደርሱ ለልጆቻቸው መሪ ይሆኑ ዘንድ በእርሳቸው ምትክ አባ ገብር ኄርን ሾሙላቸው፡፡ የክብር ባለቤት #ጌታችንም ተገልጦላቸው ታላቅ ቃልኪዳን ከገባላቸው በኋላ ታኅሣሥ 16 ቀን 1411 ዓ.ም በ130 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሥጋ ሞት ተለዩ፡፡

ደብረ ድማኅ አቡነ መርቆሬዎስ ገዳም ከጥንታዊ ገዳማት ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ገዳሙ ታላቅ የምናኔ ቦታ ከመሆኑም ባሻገር በርካታ ሊቃውንት የሚወጡበት ነው፡፡ የትርጓሜ መጻሕፍት፣ የብሉይና ሐዲስ፣ የቅኔ፣ የምዕራፍ፣ የጾመ ድጓ እና የመዝገበ ቅዳሴ መምህራን ከዚህ ገዳም ታጥተው አያውቁም፡፡ በደቡብ ዞን ዓረዛ ቆላ ሠራየ በሚባል ቦታ የሚገኝ ሲሆን ከአስመራ 102 ኪ.ሜ ርቀት ላይ እንዲሁም ከባሕር ወለል በላይ 2075 ሜትር ከፍታ ላይ የሚገኝ ታላቅ ገዳም ነው።

የጻድቁ አቡነ መርቆሬዎስ በረከታቸው ይደርብን🙏
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ታኅሣሥ_16_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ዕብራውያን 11
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
³² እንግዲህ ምን እላለሁ? ስለ ጌዴዎንና ስለ ባርቅ ስለ ሶምሶንም ስለ ዮፍታሔም ስለ ዳዊትና ስለ ሳሙኤልም ስለ ነቢያትም እንዳልተርክ ጊዜ ያጥርብኛልና።
³³ እነርሱ በእምነት መንግሥታትን ድል ነሡ፥ ጽድቅን አደረጉ፥ የተሰጠውን የተስፋ ቃል አገኙ፥
³⁴ የአንበሶችን አፍ ዘጉ፥ የእሳትን ኃይል አጠፉ፥ ከሰይፍ ስለት አመለጡ፥ ከድካማቸው በረቱ፥ በጦርነት ኃይለኞች ሆኑ፥ የባዕድ ጭፍሮችን አባረሩ።
³⁵ ሴቶች ሙታናቸውን በትንሣኤ ተቀበሉ፤ ሌሎችም መዳንን ሳይቀበሉ የሚበልጠውን ትንሣኤ እንዲያገኙ እስከ ሞት ድረስ ተደበደቡ፤
³⁶ ሌሎችም መዘበቻ በመሆንና በመገረፍ ከዚህም በላይ በእስራትና በወኅኒ ተፈተኑ፤
³⁷ በድንጋይ ተወግረው ሞቱ፥ ተፈተኑ፥ በመጋዝ ተሰነጠቁ፥ በሰይፍ ተገድለው ሞቱ፥ ሁሉን እያጡ መከራን እየተቀበሉ እየተጨነቁ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ፤
³⁸ ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ፥ በዋሻና በምድር ጕድጓድ ተቅበዘበዙ።
³⁹-⁴⁰ እነዚህም ሁሉ በእምነታቸው ተመስክሮላቸው ሳሉ የተሰጠውን የተስፋ ቃል አላገኙም፥ ያለ እኛ ፍጹማን እንዳይሆኑ እግዚአብሔር ስለ እኛ አንዳች የሚበልጥ ነገርን አስቀድሞ አይቶ ነበርና።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ጴጥሮስ 3
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁵ እንዲህ በቀድሞ ዘመን በእግዚአብሔር ተስፋ ያደረጉት ቅዱሳት ሴቶች ደግሞ ለባሎቻቸው ሲገዙ ተሸልመው ነበርና፤
⁶ እንዲሁም ሣራ ለአብርሃም፦ ጌታ ብላ እየጠራችው ታዘዘችለት፤ እናንተም ከሚያስደነግጥ ነገር አንዳች እንኳ ሳትፈሩ መልካም ብታደርጉ ልጆችዋ ናችሁ።
⁷ እንዲሁም፥ እናንተ ባሎች ሆይ፥ ደካማ ፍጥረት ስለ ሆኑ ከሚስቶቻችሁ ጋር በማስተዋል አብራችሁ ኑሩ፤ ጸሎታችሁ እንዳይከለከል አብረው ደግሞ የሕይወትን ጸጋ እንደሚወርሱ አድርጋችሁ አክብሩአቸው።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 13
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²⁰ ከዚህም በኋላ እስከ ነቢዩ እስከ ሳሙኤል ድረስ አራት መቶ አምሳ ዓመት ያህል መሳፍንትን ሰጣቸው።
²¹ ከዚያም ወዲያ ንጉሥን ያነግሥላቸው ዘንድ ለመኑ፥ እግዚአብሔርም ከብንያም ወገን የሚሆን ሰው የቂስን ልጅ ሳኦልን አርባ ዓመት ሰጣቸው፤
²² እርሱንም ከሻረው በኋላ ዳዊትን በእነርሱ ላይ እንዲነግሥ አስነሣው፥ ሲመሰክርለትም፦ እንደ ልቤ የሆነ ሰው ፈቃዴንም ሁሉ የሚያደርግ የእሴይን ልጅ ዳዊትን አገኘሁ አለ።
²³ ከዚህም ሰው ዘር እግዚአብሔር እንደ ተስፋው ቃል ለእስራኤል መድኃኒትን እርሱም ኢየሱስን አመጣ።
²⁴ ከመምጣቱ በፊት ዮሐንስ አስቀድሞ ለእስራኤል ሕዝብ ሁሉ የንስሐን ጥምቀት ሰብኮ ነበር።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ታኅሣሥ_16_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"አዋልደ ንግሥት ለክብርከ። ወትቀውም ንግሥት በየማንከ። በአልባሰ ወርቅ ዑጽፍት ወኊብርት"። መዝ.44፥9።
“የንጉሦች ሴት ልጆች ለክብርህ ናቸው፤ በወርቅ ልብስ ተጐናጽፋና ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች።” መዝ.44፥9
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ታኅሣሥ_16_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ዮሐንስ 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ በመጀመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ።
² ይህ በመጀመሪያው በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ።
³ ሁሉ በእርሱ ሆነ፥ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም።
⁴ በእርሱ ሕይወት ነበረች፥ ሕይወትም የሰው ብርሃን ነበረች።
⁵ ብርሃንም በጨለማ ይበራል፥ ጨለማም አላሸነፈውም።
⁶ ከእግዚአብሔር የተላከ ስሙ ዮሐንስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤
⁷ ሁሉ በእርሱ በኩል እንዲያምኑ ይህ ስለ ብርሃን ይመሰክር ዘንድ ለምስክር መጣ።
⁸ ስለ ብርሃን ሊመሰክር መጣ እንጂ፥ እርሱ ብርሃን አልነበረም።
⁹ ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም ይመጣ ነበር።
¹⁰ በዓለም ነበረ፥ ዓለሙም በእርሱ ሆነ፥ ዓለሙም አላወቀውም።
¹¹ የእርሱ ወደ ሆነው መጣ፥ የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትም።
¹² ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤
¹³ እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም።
¹⁴ ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፥ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነው ክብሩን አየን።
¹⁵ ዮሐንስ ስለ እርሱ መሰከረ እንዲህም ብሎ ጮኸ፦ ከእኔ በኋላ የሚመጣው እርሱ ከእኔ በፊት ነበረና ከእኔ ይልቅ የከበረ ሆኖአል፤ ስለ እርሱ ያልሁት ይህ ነበረ።
¹⁶ እኛ ሁላችን ከሙላቱ ተቀብለን በጸጋ ላይ ጸጋ ተሰጥቶናልና ሕግ በሙሴ ተሰጥቶ ነበርና፤
¹⁷ ጸጋና እውነት ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ሆነ።
¹⁸ መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው።
¹⁹ አይሁድም፦ አንተ ማን ነህ? ብለው ይጠይቁት ዘንድ ከኢየሩሳሌም ካህናትንና ሌዋውያንን በላኩበት ጊዜ፥ የዮሐንስ ምስክርነት ይህ ነው።
²⁰ መሰከረም አልካደምም፤ እኔ ክርስቶስ አይደለሁም ብሎ መሰከረ።
²¹ እንኪያስ ማን ነህ? ኤልያስ ነህን? ብለው ጠየቁት። አይደለሁም አለ። ነቢዩ ነህን? አይደለሁም ብሎ መለሰ።
²² እንኪያስ፦ ማን ነህ? ለላኩን መልስ እንድንሰጥ፤ ስለራስህ ምን ትላለህ? አሉት።
²³ እርሱም፦ ነቢዩ ኢሳይያስ እንዳለ፦ የጌታን መንገድ አቅኑ ብሎ በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ እኔ ነኝ አለ።
²⁴-²⁵ የተላኩትም ከፈሪሳውያን ነበሩና፦ እንኪያስ አንተ ክርስቶስ ወይም ኤልያስ ወይም ነቢዩ ካይደለህ፥ ስለ ምን ታጠምቃለህ? ብለው ጠየቁት።
²⁶ ዮሐንስ መልሶ፦ እኔ በውኃ አጠምቃለሁ፤ ዳሩ ግን እናንተ የማታውቁት በመካከላችሁ ቆሞአል፤
²⁷ እኔ የጫማውን ጠፍር ልፈታ የማይገባኝ፥ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ከእኔ ይልቅ የሚከብር ይህ ነው አላቸው።
²⁸ ይህ ነገር ዮሐንስ ያጠምቅበት በነበረው በዮርዳኖስ ማዶ በቢታንያ በቤተ ራባ ሆነ።
²⁹ በነገው ዮሐንስ ኢየሱስን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ እንዲህ አለ፦ እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️ የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #እመቤታችን_የማርያም_ቅዳሴ ነው። መልካም የቅዱስ ጌዴዎን፣ የአቡነ መርቆሬዎስ የዕረፍት በዓልና የቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ በዓል። ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ለቀራንብትኪ

#እመቤቴ_ኪዳነ_ምህረት_ሆይ የዓይኖችን እይታና አገላለጥ ለመጠበቅና ለመንከባከብ ለተፈጠሩ ቀራንብቶሽ ሰላምታ ይገባል።

#የቃል_ኪዳኗ_እመቤት_ሆይ ያለዘርዓ ብእሲ የወለድሽውን ልጅሽን ኃጥአን እንኳን ቢሆኑ ስምሽን ከጠሩ እምርልሻለሁ ስትል የገባህልኝ ቃል ኪዳን ወዴት አለ ብለሽ አሳስቢው።
#ጸምር_ዘጌዴዮን

#እመቤታችን_ቅድስት_ድንግል_ማርያም  የጌዴዮን ፀምር ትባላለች። እስራኤል በምድያማውያን ተደጋጋሚ መከራ ሲደርስባቸው በነበረበት ዘመን መልአከ #እግዚአብሔር ለጌዴዮን ተገልጦ  ጌታ ባንተ አድሬ እስራኤልን ከምድያም ሰዎች አድናቸዋለሁ ብሎሃል  ሔደህ ተዋጋ አለው። ጌዴዎንም ጽኑ እምነት ነበረውና እንግዲያስ  አስቀድሜ ለ #እግዚአብሔር መሥዋዕት ልሰዋ ብሎት ሊሠዋ ሔደ። መሥዋዕት ሠውቶ፣ ሥጋውን በቅርጫት፣ ደሙን በብርት አድርጎ አቀረበ። ድንጋዩን ጠፍጥፎ፣ እንጨቱን ረብርቦ ሥጋውን ከዚያ ላይ አደረገ።  ጌዴዮን ያዘጋጀውን መሠዋዕት መልአኩ በዘንግ ቢነካው ተቃጥሏል።

እሳት የመቅሠፍተ #እግዚአብሔር፣ ሥጋው የአሕዛብ፣ ሕለት(ዘንግ) የኵናተ ጌዴዎን ምሳሌ ነው። ሁለተኛ ፀምር ልዘርጋና ጠል ከብዝት ላይ ይውረድ፤ ዳርና ዳሩ ግን ደረቅ ይሁን አለው። መልአኩም እንዳልከው ይሁንልህ አለው። ለሦስተኛ ጊዜ ፀምር ልዘርጋ፤ የምዘረጋው ፀምር ደረቅ ሆኖ በዳርና በዳሩ ግን ጠል ይውረድበት አለው። መልአኩም መልሶ እንዳሰብከው ይሁንልህ በማለት መለሰለት። ለጌዴዎን ሁሉም እንዳሰበው ሆኖለታል።

ለጊዜው ፀምር የእስራኤል፣ ጠል የረድኤተ #እግዚአብሔር ምሳሌ። ጠል ከፀምሩ ላይ መውረዱ #እግዚአብሔር እስራኤልን የመርዳቱ፣ ጠል በዳርና በዳር አለመውረዱ አሕዛብን ያለመርዳቱ ምሳሌ ነው። አንድም ፀምር  አይለወጥም የእስራኤል፤ ጠል የመቅሰፍተ #እግዚአብሔር፣ ጠል ከፀምር አለመውረዱ እስራኤልን ያለማጥፋቱ፣ በዳርና በዳር መውረዱ አሕዛብን የማጥፋቱ ምሳሌ ነው።  ፍጻሜው ግን ፀምር የ #እመቤታችን፣ ጠል የ #ጌታ ምሳሌ ነው።  ጠል ከፀምር መውረዱ #ጌታችን_መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ#እመቤታችን የማደሩ ምሳሌ ነው።  ጠል በፀምሩ ዳርና በዳር አለመውረዱ #ጌታችን በሌሎች ሴቶች ያለማደሩ፣ ፀምር ደረቅ መሆኑ #እመቤታችን ካለ ወንድ ዘርዕ  #ጌታችንን የመውለዷ ምሳሌ ነው። ጠል በዳርና ዳር መውረዱ ሌሎች ሴቶች በዘር በሩካቤ የመውለዳቸው ምሳሌ ነው። ሊቃውንት #እመቤታችንን የጌዴዎን ፀምር የሚሏትም ለዚህ ነው። ለጌዴዎን ጸወን እንደሆነው እኛንም ከመከራ ሥጋ፣ ከመከራ ነፍስ ታድነን። አሜን!!

#ታኅሣሥ_16_በዓለ_ዕረፍቱ_ለቅዱስ_ጌዴዎን ስንክሳር ዘወርኃ ታኅሣሥ 16 ይነበብ

@ ማኅበረ ቅዱሳን ዋናው ማዕከል
#ታኅሣሥ_17

#ቅዱስ_ሉቃስ_ዘዓምድ

አንድ አምላክ በሚሆን በ #አብ#ወልድ#መንፈስ_ቅዱስ ስም
ታኅሣሥ ዐስራ ሰባት በዚች ቀን ጻድቁ አቡነ ሉቃስ ዘዓምድ ፍልሠተ ሥጋው ሆነ፡፡ እርሱም ከፋርስ አገር ነው በመጀመሪያ በመቶ ጭፍራ ላይ መኰንን ሁኖ ተሹሞ ነበር ከዚህም በኋላ ሹመቱን ትቶ የምንኵስና ልብስን ለበሰ። በምሥራቅ አገር ከአሉ ገዳማትም በአንዱ ገዳም እየተጋደለ ብዙ ወራት ኖረ የምንኵስናንም ሥራ ተጋድሎንና ትሩፋትንም በፈጸመ ጊዜ በዚያ ገዳም ውስጥ ቅስና ተሾመ። በተሾመም ጊዜ በዚያ በኖረበት መጠን የብረት ልብስ ለበሰ ከዚያቺም ወዲህ ስድስት ቀን የሚጾም ሆነ በክርስቲያን ሰንበት ቀንም ቀድሶ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ይቀበላል ከዚህም በኋላ ከጐመን ጋር አንድ የዳቦ ለከት ይመገባል።

ከዚህም በኋላ ከዓምድ ላይ ወጥቶ በላዩ ሦስት ዓመት ቆመ በስሙም ሲጠራውና ከዚያም ዓምድ ላይ እንዲወርድ ሲያዝዘው የመልአክን ቃል ሰማ የብርሃን #መስቀል ተከተለው ከገዳማት ወደ አንዱ ገዳም እስከ አደረሰውም ድረስ መራው በዚያም የሚኖር ሆነ ሰዎችም ሁሉ ወደርሱ እየመጡ በትምህርቱ ይረጋጉ ነበር።

ከዚህም በኋላ የማይናገር ሆነ ከሰው ጋር ከቶ እንዳይናገር ከአፉ ውስጥ ደንጊያ ጐረሰ ዳግመኛም ወደ የቊስጥንጥንያ አገር ዳርቻ ይሔድ ዘንድ መልአክ አዘዘው ለእርሷም አቅራቢያ ወደ ሆነች ወደ አንዲት ቦታ ሔደ ከምሰሶ ላይም ወጥቶ ታላቅ ተጋድሎን እየተጋደለ በላዩ አርባ አምስት ዓመት ኖረ #እግዚአብሔርም የመፈወስን ሀብት ሰጠው አስደናቂዎች ተአምራትን በማድረግ ወደርሱ የሚመጡትን ከብዙዎች በሽተኞችን ፈወሳቸው።

#እግዚአብሔርም ከዚህ ዓለም ድካም ሊአሳርፈው በፈቀደ ጊዜ በዚህ ወር በዐሥራ አምስተኛው ቀን ዐረፈ የሚያገለግለውም ረድ ለጳጳሳት አለቆችና ለካህናት አለቆች ስለ ዕረፍቱ ነገራቸው እነርሱም መስቀሎችን፣ ጽንሐዎችን፣ መብራቶችን፣ ከመያዝ ጋር በዚያን ጊዜ ተነሠሰተው ወደመኖሪያው ሔዱ በላዩም ጸልየው ተሸክመው ወደ ቊስጥንጥንያ ከተማ ወሰዱት በዐረፈ በሦስተኛው ቀን ታኅሣሥ ዐሥራ ሰባት በዚች ቀን አደረሱት ወደ ቤተ መቅደስም አስገብተው የከበረ ሥጋው በአለበት እንደሚገባ ጸሎትን ፈጸሙ። ከእርሱም ተባረኩ የተሰበሰቡትም ሁሉ ተባረኩ ከዚህም በኋላ ከርሱ አስቀድሞ የቅዱሳን ሥጋቸው ወዳለበት ሣጥን ውስጥ ጨመሩት #እግዚአብሔርም እጅግ ጠቃሚ የሆኑ አስደናቂዎች ተአምራትን አብዝቶ ገለጠ አምነው በሚመጡ በብዙዎች በሽተኞች ላይ ታላቅ ፈውስ ሁኗልና።

#እግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ታኅሣሥ_17)
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ታኅሣሥ_17_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሮሜ 8
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁸ ለእኛም ይገለጥ ዘንድ ካለው ክብር ጋር ቢመዛዘን የአሁኑ ዘመን ሥቃይ ምንም እንዳይደለ አስባለሁ።
¹⁹ የፍጥረት ናፍቆት የእግዚአብሔርን ልጆች መገለጥ ይጠባበቃልና።
²⁰ ፍጥረት ለከንቱነት ተገዝቶአልና፥ በተስፋ ስላስገዛው ነው እንጂ በፈቃዱ አይደለም፤
²¹ ተስፋውም ፍጥረት ራሱ ደግሞ ከጥፋት ባርነት ነፃነት ወጥቶ ለእግዚአብሔር ልጆች ወደሚሆን ክብር ነፃነት እንዲደርስ ነው።
²² ፍጥረት ሁሉ እስከ አሁን ድረስ አብሮ በመቃተትና በምጥ መኖሩን እናውቃለንና።
²³ እርሱም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን የመንፈስ በኵራት ያለን ራሳችን ደግሞ የሰውነታችን ቤዛ የሆነውን ልጅነት እየተጠባበቅን ራሳችን በውስጣችን እንቃትታለን።
²⁴ በተስፋ ድነናልና፤ ነገር ግን ተስፋ የሚደረግበቱ ነገር ቢታይ ተስፋ አይደለም፤ የሚያየውንማ ማን ተስፋ ያደርገዋል?
²⁵ የማናየውን ግን ተስፋ ብናደርገው በትዕግሥት እንጠባበቃለን።
²⁶ እንዲሁም ደግሞ መንፈስ ድካማችንን ያግዛል፤ እንዴት እንድንጸልይ እንደሚገባን አናውቅምና፥ ነገር ግን መንፈስ ራሱ በማይነገር መቃተት ይማልድልናል፤
²⁷ ልብንም የሚመረምረው የመንፈስ አሳብ ምን እንደ ሆነ ያውቃል፥ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ስለ ቅዱሳን ይማልዳልና።
²⁸ እግዚአብሔርንም ለሚወዱት እንደ አሳቡም ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን።
²⁹ ልጁ በብዙ ወንድሞች መካከል በኵር ይሆን ዘንድ፥ አስቀድሞ ያወቃቸው የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ደግሞ ወስኖአልና፤
³⁰ አስቀድሞም የወሰናቸውን እነዚህን ደግሞ ጠራቸው፤ የጠራቸውንም እነዚህን ደግሞ አጸደቃቸው፤ ያጸደቃቸውንም እነዚህን ደግሞ አከበራቸው።
³¹ እንግዲህ ስለዚህ ነገር ምን እንላለን? እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ማን ይቃወመናል?
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ያዕቆብ 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁷ በጎ ስጦታ ሁሉ ፍጹምም በረከት ሁሉ ከላይ ናቸው፥ መለወጥም በእርሱ ዘንድ ከሌለ በመዞርም የተደረገ ጥላ በእርሱ ዘንድ ከሌለ ከብርሃናት አባት ይወርዳሉ።
¹⁸ ለፍጥረቱ የበኵራት ዓይነት እንድንሆን በእውነት ቃል አስቦ ወለደን።
¹⁹ ስለዚህ፥ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፥ ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ ለመናገርም የዘገየ ለቍጣም የዘገየ ይሁን፤
²⁰ የሰው ቍጣ የእግዚአብሔርን ጽድቅ አይሠራምና።
²¹ ስለዚህ ርኵሰትን ሁሉ የክፋትንም ትርፍ አስወግዳችሁ፥ ነፍሳችሁን ማዳን የሚችለውን በውስጣችሁም የተተከለውን ቃል በየዋህነት ተቀበሉ።
²² ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ እንጂ ራሳችሁን እያሳታችሁ የምትሰሙ ብቻ አትሁኑ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 15
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁰ እንግዲህ አባቶቻችንና እኛ ልንሸከመው ያልቻልነውን ቀንበር በደቀ መዛሙርት ጫንቃ ላይ በመጫን እግዚአብሔርን አሁን ስለ ምን ትፈታተናላችሁ?
¹¹ ነገር ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ እንደ እነርሱ ደግሞ እንድን ዘንድ እናምናለን።
¹² ሕዝቡም ሁሉ ዝም አሉ፥ በርናባስና ጳውሎስም እግዚአብሔር በእጃቸው በአሕዛብ መካከል ያደረገውን ምልክትና ድንቅ ሁሉ ሲተርኩላቸው ይሰሙ ነበር።
¹³ እነርሱም ዝም ካሉ በኋላ ያዕቆብ እንዲህ ብሎ መለሰ፦ ወንድሞች ሆይ፥ ስሙኝ።
¹⁴ እግዚአብሔር ለስሙ የሚሆንን ወገን ከአሕዛብ ይወስድ ዘንድ አስቀድሞ እንዴት እንደ ጐበኘ ስምዖን ተርኮአል።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ታኅሣሥ_17_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"ተቀነዩ ለእግዚአብሔር በፍርሃት። ወተኀሠዩ ሎቱ በረዓድ። አጽንዕዋ ለጥበብ ከመ ኢይትመዐዕ እግዚአብሔር"። መዝ 2፥11-12።
"ለእግዚአብሔር በፍርሃት ተገዙ፥ በረዓድም ደስ ይበላችሁ። ተግሣጹን ተቀበሉ ጌታ እንዳይቈጣ እናንተም በመንገድ እንዳትጠፉ፥ ቍጣው ፈጥና ትነድዳለችና። በእርሱ የታመኑ ሁሉ የተመሰገኑ ናቸው"። መዝ 2፥11-12።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ታኅሣሥ_17_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሉቃስ 11
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ እርሱም በአንድ ስፍራ ይጸልይ ነበር፥ በጨረሰም ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ፦ ጌታ ሆይ፥ ዮሐንስ ደቀ መዛሙርቱን እንዳስተማረ እንጸልይ ዘንድ አስተምረን አለው።
² አላቸውም፦ ስትጸልዩ እንዲህ በሉ፦ በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፤ ስምህ ይቀደስ፤ መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን፤
³ የዕለት እንጀራችንን ዕለት ዕለት ስጠን፤
⁴ ኃጢአታችንንም ይቅር በለን፥ እኛ ደግሞ የበደሉንን ሁሉ ይቅር ብለናልና፤ ከክፉ አድነን እንጂ ወደ ፈተና አታግባን።
⁵ እንዲህም አላቸው፦ ከእናንተ ማናቸውም ወዳጅ ያለው፥ በእኩል ሌሊትስ ወደ እርሱ ሄዶ፦ ወዳጄ ሆይ፥ ሦስት እንጀራ አበድረኝ፥
⁶ አንድ ወዳጄ ከመንገድ ወደ እኔ መጥቶ የማቀርብለት የለኝምና ይላልን?
⁷ ያም ከውስጥ መልሶ፦ አታድክመኝ፤ አሁን ደጁ ተቈልፎአል ልጆቼም ከእኔ ጋር በአልጋ ላይ አሉ፤ ተነሥቼ ልሰጥህ አልችልም ይላልን?
⁸ እላችኋለሁ፥ ወዳጅ ስለ ሆነ ተነሥቶ ባይሰጠው እንኳ፥ ስለ ንዝነዛው ተነስቶ የሚፈልገውን ሁሉ ይሰጠዋል።
⁹ እኔም እላችኋለሁ፦ ለምኑ፥ ይሰጣችሁማል፤ ፈልጉ፥ ታገኙማላችሁ፤ መዝጊያን አንኳኩ፥ ይከፈትላችሁማል።
¹⁰ የሚለምን ሁሉ ይቀበላልና፥ የሚፈልግም ያገኛል፥ መዝጊያውንም ለሚያንኳኳው ይከፈትለታል።
¹¹ አባት ከሆናችሁ ከእናንተ ከማንኛችሁም ልጁ እንጀራ ቢለምነው፥ እርሱም ድንጋይ ይሰጠዋልን? ዓሣ ደግሞ ቢለምነው በዓሣ ፋንታ እባብ ይሰጠዋልን?
¹² ወይስ እንቍላል ቢለምነው ጊንጥ ይሰጠዋልን?
¹³ እንኪያስ እናንተ ክፉዎች ስትሆኑ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠት ካወቃችሁ፥ በሰማይ ያለው አባት ለሚለምኑት እንዴት አብልጦ መንፈስ ቅዱስን ይሰጣቸው?
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️ የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #ሠለስቱ_ምዕት_ቅዳሴ ነው። መልካም በዓልና የጾም ለሁላችንም ይሁንልን።

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ታኅሣሥ_18

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ታኅሣሥ ዐስራ ስምንት በዚህች ቀን #አቡነ_ሰላማ_ከሣቴ_ብርሃን ጵጵስና የተሾሙበት ዕለት ነው፣ #የሐዋርያው_ቅዱስ_ቶማስ እና የቅዱስ ጳውሎስ ደቀ መዝሙር የሆነው #የቅዱስ_ቲቶ የሥጋቸው ፍልሰት ነው፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አቡነ_ሰላማ_ከሣቴ_ብርሃን

ታኅሣሥ ዐስራ ስምንት በዚህቸ ቀን #አቡነ_ሰላማ_ከሣቴ_ብርሃን ጵጵስና የተሾሙበት ዕለት ነው፡፡ ቅዱስ አባታችን አባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ከ #ጌታችን_ከኢየሱስ_ክርስቶስ ልደት በኋላ በ245 ዓ.ም በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም ህዳር 26 ቀን ሲወለዱ ታላቅ ብርሃን ከሰማይ ወርዶ ለ7 ቀናት አብርቷል፡፡ ቅዱሳን መላእክትም ወደ ምድር ወርደው በመወለዳቸው ታላቅ ደስታን አድርገዋል፡፡ በተወለዱም ጊዜ ‹‹ለ #አብ ስግደት ለ ወልድ ስግደት ለ #መንፈስ_ቅዱስ ስግደት ይገባል፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን ለአወጡኝ ቅድመ ዓለም ለነበሩ ዛሬም ላሉ ዓለምን አሳልፈው ለሚኖሩ ለ #አብ#ወልድ#መንፈስ_ቅዱስ ምስጋና ይገባል ብለው ዳግመኛም አሐዱ #አብ ቅዱስ አሐዱ #ወልድ ቅዱስ አሐዱ ውእቱ #መንፈስ_ቅዱስ›› ብለው ፈጣሪያቸውን በአንድነት በሦስትነት አመስግነዋል፡፡

ቅዱስ አባታችን በሌላኛው ስማቸው ፍሬምናጦስ እየተባሉ ይጠራሉ፡፡ በ40 ቀናቸው #ጌታ በተጠመቀበት በዮርዳኖስ ያጠመቋቸውና ስመ ክርስትና የሰጧቸው ሊቀ ጳጳስ ‹‹ይህ ሕፃን ለኢትዮጵያውን ሁሉ ብርሃን ይሆንላቸዋል›› በማለት ትንቢት ተናግረዋል፡፡ በሊቀ ጳጳሱ በቅዱስ አትናቴዎስ በሚገባ ተምረው ካደጉ በኋላ በ257 ዓ.ም ከኢየሩሳሌም ወደ ኢትዮጵያ ስሙ ሜርጵዮስ ከሚባል ከአንድ ነጋዴ ጋር መጡ፡፡ ከእነሱም ጋር አድስዮስ የሚባል ልጅ ነበር፡፡ ወደ ሀገራችንም ሊመጡ የቻሉት እንዴት ነው? ቢሉ መጀመሪያ ለሰባት ወር በአንድ ሌላ አገር ኖረው ወደ ኢየሩሳሌም ሊመለሱ ሲሉ የበረሃ ሽፍቶች ሜርጵዮስንና ሌሎች መንገደኞችን ገደሏቸውና ሁለቱን ልጆች ማርከው ወስደው ስሙ አልአሜዳ ለሚባል ለአክሱም ንጉሥ ሰጡት፡፡ እርሱም አድስዮስን የቤተክርስቲያን የአልባሳትና የዕቃ ቤት ጠባቂ አድርጎ ሲሾመው ፍሬምናጦስን ደግሞ የቤተክርስቲያንና የሕግ ጠባቂ አደረገው የቤተክርስቲያንን ሥርዓቷንና አገልግሎቷን ጠንቅቆ ያውቅ ነበርና፡፡

በአክሱምም በተጋድሎና በትጋት ኖረ፡፡ ቅዳሜና እሁድ የዛፍ ቅጠሎችን ከመመገብ በቀር ሌላ ምግብ አይቀምስም ነበር፡፡ በየቀኑም አምስት ሺህ ስግደትን ይሰግድ ነበር፡፡ በእርሱም የተጋድሎ ዘመን ደጋግ የሆኑ ነገሥታት አብርሃና አጽብሓ ነገሡ፡፡ እነርሱም ሆኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍሬምናጦስን በጣም ይወዱት ነበር፡፡ አንድ ቀን ፍሬምናጦስ የአክሱሙን ኤጲስ ቆጶስ ቅዱስ ሚናስን ‹‹ግዝረትና እምነት በእናንተ ዘንድ አለ ነገር ግን ጥምቀትና ሥጋ ወደሙ መቀበል በእናንተ ዘንድ የለም›› አለው፡፡ ቅዱስ ሚናስም ‹‹ግዝረትንስ አባቶቻችን ሌዋውያን አመጡ፣ በ #ክርስቶስ ማመንን ሕንኬ የተባለች የኢትዮጵያ ንግሥት ጃንደረባ አመጣልን፡፡ ስለ ጥምቀትና ሥጋ ወደሙ ሐዋርያ ወደ እኛ አልተላከም ነገር ግን ያልከውን ሁሉ የሚያደርግልን የሚባርከንና የሚቀድሰን ጳጳስን ታመጣልን ዘንድ ሊቀ ጳጳሱ ወዳለበት ወደ እስክንድሪያ አገር አንተ ሂድ›› አለው፡፡ ጥምቀትስ በጃንደረባው በኩል አገራችን ገብቶ ነበር ነገር ግን ገና ስላልተጠናከና ብዙ ሕዝብም አልተጠመቀም ነበርና አባታችን ፍሬምናጦስ አጠናክሮ ያልተጠመቀውን ሁሉ አጥምቆአል፡፡

ፍሬምናጦስም ወደ እስክንድሪያ ለመሄድ አስቦ ሳለ እንደተኛ #ድንግል_ማርያም ተገልጣለት ‹‹ዲቁናና ቅስናን መቀበል ይገባሃል፣ ለጵጵስና ተዘጋጅ፣ #እግዚአብሔር ይህችን ከፍ ያለችውን ማዕረግ ሰጥተሃልና የልጄ ወዳጅ ሆይ በጸሎትህና በልመናህ በስብከትህም የኢትዮጵያ ሰዎች ሁሉ ይድናሉ፣ በእጅህ ጥምቀትንና ሥጋ ወደሙን ይቀበላሉ›› አለችው፡፡ #ጌታችንም እንዲሁ ተገልጦለት ‹‹ወደ ሊቀ ጳጳሳት ወደ አትናቴዎስ ሄደህ ከፍ ያለችውን ማዕረግ ተቀብለህ የኢትዮጵያን ሰዎች አጥምቅልኝ፣ ነቢዩ ዳዊት ስለ እነርሱ ‹ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ #እግዚአብሔር ትዘረጋለች› ብሎ ተናግሯልና›› አለው፡፡ እርሱም ቅዱሳኑን ነገሥታት አብርሃንና አጽብሓን አግኝቶ ከእነርሱም ጋር ተማክሮ ወደ እስክንድሪያ ሄዶ በቅዱስ አትናቴዎስ እጅ በአገራችን ላይ የመጀመሪያው ሊቀ ጳጳስ ሆኖ ታኅሳስ 18 ቀን ተሾመ፡፡ ስሙንም ሰላማ ከሣቴ ብርሃን አለው፡፡ ሰላማ ማለት #እግዚአብሔርንና ሰውን የሚያስታርቅ ማለት ነው፡፡ ከሣቴ ብርሃን ማለትም ሃይማኖትን ገልጦ የሚያስተምር ማለት ነው፡፡ ቅዱስ አትናቴዎስም ከሾመው በኋላ ታቦትና በጣም ብዙ ንዋያተ ቅድሳትንና መገልገያ ዕቃዎችን ሰጥቶ መርቆ በሰላም ወደ ኢትዮጵያ ላከው፡፡ ይህች ዕለት አባታቸን በ330 ዓ.ም በሐዋርያው ቅዱስ አትናቴዎስ እጅ ጵጵስና የተሾሙባት ዕለት ናት፡፡

#እግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሱ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

#አርኬ✍️ሰላም ለከ ሰላማ እዙዝ። ለከሢተ ትምህርት ግኑዝ። ሶበ ውስቴታ ሠረቀ በአምሳለ ቤዝ። በብርሃንከ አዳም ወበስንከ ሐዋዝ። እስከ ዮም ትትፌሣሕ ወትትኃሠይ ግዕዝ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ቶማስ

በዚህች ዕለት የሐዋርያው የቅዱስ ቶማስ የሥጋው ፍልሰት ሆነ፡፡ ቶማስ ማለት ፀሐይ ማለት ሲሆን ቀዳሚ ስሙ ‘ዲዲሞስ’ ነው ‘ዲዲሞስ’ ማለት ጨለማ ማለት ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ ከ12 ሐዋርያት አንዱ ነው ሲሆን #ጌታች_ መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ ከተነሣ በኋላ ያየው በ8ኛው ቀን እሁድ ነው ያየውም በጦር የተወጋ ጐኑን ዳስሶ ነው እንዲሁም የእመ አምላክን ዕርገቷን አስቀድሞ ያየውም እርሱ ነው፡፡

ሀገረ ስብከቱ ሕንደኬ ሲሆን ለምክንያት ይሁነኝ ብሎ በ30 ብር ተሽጦ ከመስፍነ ብሔሩ ክሉክዮስ ቤት እያገለገለ ይኖር ነበር ምን ምን መሥራት ትችላለህ ቢለው ሕንፃ ማነጽ ሐውልት መቅረጽ እችላለሁ አለው እንኪያስ ሠርተህ ቆየኝ ብሎ ብዙ ወርቅ እና ብር ሰጥቶት አሕዛብ ምኩሀን ናቸውና እንዲህ ያለ ጠቢብ አገኘሁ ለማለት ወደ ንጉሥ ሄደ፡፡ እሱም ሕንጻ ማነጽ ሐውልት መቅረጽ ከዚህ የበለጠ አለን ብሎ ለነዳያን መጸወተው ከዚያውም ዘንድ አስተምሮ አሳምኗቸዋል የሉክዮስም ሚስት አርሶንዋ ከነልጆቿ ከአገልጋዮቿ አምና ተጠምቃለች፡፡ ሉክዮስ ከሄደበት ሲመለስ ያነጽከው ሕንጻ የቀረጽከው ሐውልት ወዴት ነው? አለው በወርቅና በብርህ ያነጽኳቸው ሕንጻዎች እኒህ ናቸው ብሎ ያመኑትን አገልጋዮች አሳየው ይህ ክፉ ባሪያ ተጫወተብኝ ብሎ እጅ እግሩን አሥሮ ቆዳውን አስገፍፎ ስልቻ አስፍቶ በአሸዋ መልቶ አሸክሞ ገበያ ለገበያ ሲያዞረው ሚስቱ አርሶንዋ አይታ በድንጋጤ ወድቃ ሞተች ሚስቴ የሞተችው ባንተ ምክንያት አይደለምን ካዳንካት እኔም በአምላክህ አምናለሁ ቢለው #ጌታ ቁስሉን እንደ ውኃ አቀዝቅዞለት ካለችበት ሄዶ ስልቻውን ቢያስነካት ተነሥታለች በዚህም ሉክዮስ አምኖ ተጠምቋል፡፡
ከዚህም በኋላ ስልቻውን ተሸክሞ ከቦታ ወደ ቦታ እየተዘዋወረ ሙት እያነሣ ድውይ እየፈወሰ አሕዛብን አሳምኖ አጠመቀ፡፡ ቀንጦፍያ ሲደርስ አንድ ሽማግሌ ሰባት ልጆቹን ገድለውበት ሲያዝን አግኝቶ ስልቻውን እያስነካ ሰባቱን አስነሥቶለታል፡፡ በኢናስም የቃሉን ትምህርት የእጁን ተአምራት አይተው ከንጉሱ ሚስት ከንግሥቲቱ ጀምሮ እስከ ተራ ገባር ድረስ ያሉት ሁሉ አምነው ተጠመቁ ኋላ ግን ካህናተ ጣኦት ጥቅም የሚቀርባቸው ቢሆን በተንኮል ከንጉሥና መኳንንቱ አጣልተው ግንቦት 26 በዚህ ዕለት አንገቱን በሰይፍ አስመትተውታል፡፡

ዛሬም ድረስ ሕንድ ውስጥ በመንበሩ ላይ የቅዱስ ቶማስ ቀኝ እጁ በሕይወት እንዳለች ሆና ትታያለች፡፡ መለኮትን (የ #ጌታችንን የተወጋ ጎኑን) የዳሰሰች ቅድስት እጅ ናትና ዛሬም ድረስ ሕያው ናት፡፡ በሕንድ ኦርቶዶክስ ቤ/ክ ፓትርያርክ ሲሾሙም የቅዱስ ቶማስን ቀኝ እጅ በሚሾመው ፓትርያርክ ላይ ጭነው ነው፡፡ አንድ ወቅት አንድ ሰው ቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ገብቶ የቅዱስ ቶማስ ቀኝ እጅ እጨብጣለሁ ብሎ እጁን ቢዘረጋ የቶማስ እጅ ተሰወረችባቸው፡፡ እንደገና ብዙ እግዚኦታና ኪሪያላይሶን ካደረሱ በኋላ የቅዱስ ቶማስ እጅ በቦታዋ ተመልሳላቸዋለች፡፡

ይህች ዕለት የሥጋው ፍልሰት መታሰቢያ እንድትሆን አባቶች ሥርዓት ሠሩልን፡፡

#እግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ቲቶ

ዳግመኛም በዚህች ዕለት የሐዋርያው የቅዱስ ቲቶ የሥጋው ፍልሰት ሆነ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ቲቶ ቀርጤስ ከሚባል አገር ሲሆን ለዮናናውያን ወገን ለሆነ ለአገረ ገዥው እኅት ልጇ ነው፡፡ ሐዋርያው ከታናሽነቱ ጀምሮ የዮናናውያንን ትምህርትና ፍልስፍና ተምሮ እጅግ አዋቂ ሆነ፡፡ በጠባዩም ቅን፣ ሥራው ያማረ፣ ለድኆችና ጦም አዳሪዎች መራራት የሚወድ ነው፡፡

ከዕለታትም በአንዲቱ ዕለት ‹‹ቲቶ ሆይ ስለነፍስህ ድኅነት ተጋደል፣ ይህ ዓለም አይጠቅምምና›› የሚለውን በራእይ ተመለከተ፡፡ ምን እንደሚሠራም አላወቀምና ከእንቅልፉ በነቃ ጊዜ ደነገጠ፡፡ ከዚህም በኋላ የ #ጌታችንን ተአምራት እያነሡ ሰዎች ሲነጋገሩ የአክራጥስ መኮንን ሰማ፡፡ መኮንኑም የሰማውቸው የ #ጌታችን ተአምራቶች እውነት መሆናቸውን ወይም የሥራይ ሥራ እንደሆነ ያረጋግጥ ዘንድ የሚልከውን ብልህና አዋቂ ሰው ፈለገ፡፡ ከእርሱ የሚሻል አዋቂ የለምና መኮንኑ የእኅቱን ልጅ ቲቶን መርጦ ስለ #ጌታችን ተአምራቶች ጥልቅ ምርምር ያደርግለት ዘንድ አዘዘው፡፡ ቅዱስ ቲቶም ከይሁዳ ምድር በደረሰ ጊዜ የ #መድኃኒታችን_የኢየሱስ_ክርስቶስን ድንቅ ድንቅ ተአምራት በዐይኑ ተመለከተ፡፡ ትምህቶቹንም ሰማና የ #ጌታንን ትምህርቶች ከዮናናውያን ትምህርትና ፍልስፍና ጋር አነጻጸረ፡፡ የዮናናውያንም ትምህርት የቀናች እንዳልሆነች ለይቶ ዐወቀ፡፡ ከዚህም በኋላ ቅዱስ ቲቶ በ #ጌታችን አመነ፣ ደቀ መዝሙሩም ሆኖ ተከተከለው፡፡

ቅዱስ ቲቶ ወደ እናቱ ወንድም ወደ አገረ ገዥው መልእክትና ላከና #ጌታችን የሚያደርጋቸው ተአምራቶችና የሚያስተምራቸው ትምህርቶች እውነት እንደሆኑ ነገረው፡፡ #ጌታችንም ቅዱስ ቲቶን ቁጥሩን ከ72ቱ አርድእት ወገን አደረገው፡፡ ቅዱስ ቲቶም ከ #ጌታችን ዕርገት በኋላ ከከበሩ ቅዱሳን ሐዋርያት ጋር የ #መንፈስ_ቅዱስን ጸጋ ተቀብሎ በሀገሮች ሁሉ ዞሮ የከበረች ወንጌልን አስተማረ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም በ #ጌታችን ተጠርቶ ወንጌልን መስበክ ሲጀምር ቅዱስ ቲቶ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስን ተከትሎት በብዙ አገሮች ወንጌልን ሰበከ፡፡ የከበረ ቅዱስ ጳውሎስም በሮሜ ከተማ ሰማዕት ከሆነ በኋላ ቅዱስ ቲቶ ወደ ሀገረ አክራጥስ ተመለሰ፡፡ በዚያም ቤተ ክርስቲያን ሠርቶ ቀሳውስትንና ዲያቆናትን ሾመላቸው፡፡ በዙሪያቸው ባሉ ሀገሮችም እንዲሁ አደረገ፡፡ በመጨረሻም ሐዋርያዊ አገልግሎቱን ፈጽሞ ወደ ወደደው #እግዚአብሔር ጷግሜ 2 ቀን ሄደ፡፡

ጻድቁ ንጉሥ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ ከ470,000 በላይ ክርስቲያኖችን በግፍ የገደለውን የሃዲውን ንጉሥ የዲዮቅልጥያኖስን መንግሥት ካጠፋ በኋላ የታሰሩትን ቅዱሳን አስፈትቶ በሚገዛቸው አገሮች ሁሉ አብያተ ክርስቲያናትን አሳነጸ፡፡ ይልቁንም ቁስጥንጥንያ መናገሻ ከተማው ናትና ብዙ አብያተ ክርስቲያናትን ካሳነጸባት በኋላ የቅዱሳን ሐዋርያን እና የቅዱሳን ሰማዕታትን ሥጋቸውን ከየቦታው እየሰበሰበ በክብር በማምጣት በውስጣቸው አኖረ፡፡ የሐዋርያውም የቅዱስ ቲቶ ሥጋ አቅራጥስ በሚባል አገር መኖሩን ሲሰማ የካህናት አለቆችን ከብዙ ገንዘብና ሠራዊት ጋር ልኮ ወደ ቁስጥንጥንያ በክብር አስመጣው፡፡

ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ የቅዱስ ቲቶ ሥጋ አቅራጥስ በሚባል አገር አፍልሶ ወደ ቁስጥንጥንያ ከተማ በክብር ካስመጣው በኋላ ያማረች ቤተ ክርስቲያን ሠርቶለት የቅዱስ ቲቶን ሥጋ በውስጧ በክብር አኖረ፡፡ ከሥጋውም ብዙ አስገራሚ ተአምራት ተፈጽመው ታዩ፡፡ ይኸውም የሆነው ታኅሣሥ 18 ቀን ነው፡፡ የቅዱሱን ሥጋ ከከበረ እምነበረድ በተሠራው ሣጥን ውስጥ አድርገው ተሸክመው ሲወስዱ ከሰው ግፊያ የተነሣ ሣጥኑ ወድቆ የአንዱን ሰው እግር ሰበረው፡፡ እርሱም የቅዱስ ቲቶ ሥዕል ካለበት የመብራት ቅባት ላይ ወስዶ የተሰበረ እግሩን ቀባውና ሲያመው እየጮኸ አሰረው፡፡ ወደ ቤቱም መሄድ ባልቻለ ጊዜ የቅዱስ ቲቶ ሥጋ ሣጥን ባለበት በዚያው አደረ፡፡ በማግሥቱም አይቶ መድኃኒት ሊያደርግ ተሰብሮ የታሰረ እግሩን በፈታው ጊዜ ከቶ ምንም ምን ሕማም እንዳላገኘው ደህና ሆነ፡፡ ለምልክት ይሆን ዘንድ ግን ደም ነበረበት፡፡ ሰውየውም ተነሥቶ እየሮጠ በመሄድ የተደረገለትን ተአምር ለሰው ሁሉ ተናገረ፡፡ ያዩትም ሁሉ የቅዱስ ቲቶን አምላክ ልዑል #እግዚአብሔርን አመሰገኑት፡፡

#እግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በሐዋርያው ቅዱስ ቲቶ ጸሎት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

#አርኬ✍️ሰላም እብል ለፍልሰተ ሥጋሁ በዘምሮ። ለረድአ ጳውሎስ ቲቶ እግዚአብሔር እንተ አፍቀሮ። ሣፁነ ሥጋሁ ዘዕብን አመ ለብእሲ ሰበሮ። ረከበ ፈውሰ ወጥዒና ከመ መንፈስ ቅዱስ አምከሮ። እምቅብዐ ማኅቶት ዘገጸ ሥዕሉ ሶበ ቀብዐ እግሮ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

📌 ታኅሣሥ 18 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ (ፍልሠቱ)
2.ቅዱስ ቲቶ ሐዋርያ (ፍልሠቱ)
3.አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን
4.ቅዱስ ፊልሞና ባሕታዊ
5.ቅዱስ ኢርቅላ

📌 ወርኀዊ በዓላት
1.አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ረባን
2.አቡነ አኖሬዎስ ዓቢይ
3.ማር ያዕቆብ ግብጻዊ
4.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ከ72ቱ)
5.ቅዱስ ፊልዾስ ሐዋርያ (ከ12ቱ)

✍️" የእግዚአብሔር ባሪያና የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ የሆነ ዻውሎስ ፥ በእግዚአብሔር ለተመረጡት እምነት እንዲሆንላቸው በዘላለምም ሕይወት ተሰፋ እንደ አምልኮት ያለውን እውነት እንዲያውቁ የተላከ ፤ . . . መድኃኒታችን እግዚአብሔር እንዳዘዘ ፥ ለእኔ አደራ በተሰጠኝ ስብከት ቃሉን ገለጠ ፤ በሃይማኖት ኅብረት እውነተኛ ልጄ ለሚሆን ለቲቶ፤ ከእግዚአብሔርም አብ ከመድኃኒታችንም ከጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ምሕረት ሰላምም ይሁን"
📖ቲቶ 1፥1-4
#ዘአቅረብኩ ማኅሌተ አዘኪርየ አእላፈ። እምእለ ተጸምዱከ ዘልፈ። ለለአነብብ ተወከፍ ዘንዴትየ መጽሐፈ። እንተ ረሰይከ እግዚኦ ጸሪቀ መበለት ውኩፈ። እምእለ አብኡ ብዑላን ዘተርፈ።
ነቢያት ቅዱሳን ወሐዋርያት ሰባኪያን። ሰማዕት ወጻድቃን ወመላእክት ትጉሃን። ደናግል ዓዲ ወመነኰሳት ኄራን። ባርኩ ባርኮ ጉባኤ ዛቲ መካን። እስከ አረጋዊ ልሒቅ ወንኡስ ሕፃን።

ለዘጸሐፎ በክርታስ ወለዘአጽሐፎ እንዘ ይደርስ። ለዘአንበቦ ወለዘተርጐሞ በልሳን ሐዲስ። ወለዘሰምዐ ቃሎ በዕዝነ መንፈስ። በጸሎተ እሙ ማርያም ዐራቂተ ኵሉ እምባእስ። ኅቡረ ይምሐረነ ኢየሱስ ክርስቶስ።

#ጌታ_ሆይ ከብልጽግናቸው ብዛት የተነሳ ብዙ መባ ካገቡት ይልቅ የደሀዪቱን አነስተኛ መባ እንደተቀበልህ ለሁል ጊዜ የሚያገለግሉህ አእላፍ መላእክትን እያሳሰብሁ በችግሬ ጊዜ የማቀርብልህን ምስጋና ተቀበል።
እናንተም ቅዱሳን ነቢያት የወንጌል ሰባኪያን ሐዋርያት ሰማዕታትና ጻድቃን ትጉሃን መላእክት ፍጹማን ደናግል እንዲሁም ደጋጎች መነኰሳት ሆይ ልጅ አዋቂ ሳይለይ የምንሰበሰብበትን የጉባኤ ቦታ ባርኩ።

ይህን መጽሐፍ ወረቀት አዘጋጅቶ ብራና ደምጦ የጻፈውና ያጻፈውም ከግዕዝ ወደ አማርኛ የተረጐመውን ቃለ ንባቡን በእርጋታ መንፈስ እና በተመስጦ ሕሊና ያዳመጠ በደለኛን ሁሉ የምታስምር የጌታ እናቱ በማርያም ጸሎት ኢየሱስ ክርስቶስ በአንድነት ይማረን። አቡነ ዘበሰማያት......

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ታኅሣሥ_18_ግንቦት እና #ከገድላት_አንደበት)
2024/12/29 07:38:17
Back to Top
HTML Embed Code: