Telegram Web Link
#ከታኅሣሥ 14-20 ያለው ጊዜ " #ዕለተ_ብርሃን" ይባላል ። ፦ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስንና የቅዱስ ያሬድን አስተምሕሮ መሠረት አድርጋ ታኅሣሥ 14 ቀን "ዕለተ ብርሃን" ትለዋለች። ሳምንቱን (ከታኅሣሥ 14-20 ነው)። በእነዚህ ዕለታት እሑድ በዋለበትን ቀን ማኅሌት ተቁሞ ብርሃን ተብሎ ይከበራል።  ደግሞ "ሰሙነ ብርሃን" ስትል ታስባለች::

"ብርሃን" በቁሙ የ #እግዚአብሔር ስሙ፤ አንድም የባሕርይ ገንዘቡ ነው። " #እግዚአብሔር ብርሃን ነውና:: ጨለማም በእርሱ ዘንድ የለችምና።" (ዮሐ 1፥4)

በዚህ ዕለት "ብርሃን" በሚል መነሻ ቤተ ክርስቲያን እነዚህን ታስተምሠራለች:-

1. #እግዚአብሔር ብርሃን መሆኑን። (ዮሐ 1፥5)

2.አምላካችን በመጀመሪያው የፍጥረት ቀን (በዕለተ እሑድ) ዲያብሎስ ቅዱሳን መላእክትን ሲረብሽ "ለይኩን ብርሃን" ብሎ ብርሃንን መፍጠሩን። (ዘፍ. 1፥2 አክሲማሮስ)

3.ነቢያት አበው በጨለማው ዓለም ሆነው መከራ ሲበዛባቸው "ፈኑ ብርሃነከ - ብርሃንህን ላክልን" እያሉ መጮሃቸውን። (መዝ 42፥3)

4.ጩኸታቸውን የሰማ ከሦስቱ አካላት አንዱ #ወልድ (እውነተኛው ብርሃን) ወደዚህ ዓለም መምጣቱን። (ሉቃ 1፥26)

5."እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ" ሲል የባሕርይ ብርሃንነቱን እንደ ነገረን። (ዮሐ 8፥12)

6.ብርሃነ መለኮቱን በገሃድ መግለጡን። (ማቴ 17፥1)

7.ብርሃን የሆነችውን ሕግ፤ ወንጌልን እንደ ሠራልን:: (1ዮሐ 2፥9)

8.ድንግል #እመቤታችን ብርሃን፤ የብርሃንም እናቱ መሆኗን። (ሉቃ 1፥26፣ ራዕ 12፥1)

9.ቅዱሳኑ ብርሀን መባላቸውን። (ማቴ. 5፥14)

10.እኛ በሰው ፊት ሁሉ እንድናበራ መታዘዛችን። (ማቴ 5፥16) ሁሉ ይታሰባል።

እርሱ ፈጣሪያችን #ክርስቶስ ጨለማውን በምሕረቱ አርቆልናልና ዳግመኛ ወደ ጨለማ እንዳንሄድ እየለመንን እናመስግነው።

" #ክርስቶስ ብርሃን ዘአሰሰልከ ጽልመተ።
ላዕለ ኪሩቤል ነቢረከ ዘትሬኢ ቀላያተ።
ስቡሕኒ ወልዑል አንተ"። (መልክአ ኢየሱስ) ምንጭ፦ ከዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ ፔጅ የተወሰደ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ታኅሣሥ_14_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ቆሮንቶስ 11
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እኔን ምሰሉ።
² ወንድሞች ሆይ፥ በሁሉ ስለምታስቡኝና አሳልፌ እንደ ሰጠኋችሁ ወግን ፈጽማችሁ ስለ ያዛችሁ አመሰግናችኋለሁ።
³ ነገር ግን የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ፥ የሴትም ራስ ወንድ፥ የክርስቶስም ራስ እግዚአብሔር እንደ ሆነ ልታውቁ እወዳለሁ።
⁴ ራሱን ተከናንቦ የሚጸልይ ወይም ትንቢት የሚናገር ወንድ ሁሉ ራሱን ያዋርዳል።
⁵ ራስዋን ሳትሸፍን ግን የምትጸልይ ወይም ትንቢት የምትናገር ሴት ሁሉ ራስዋን ታዋርዳለች፤ እንደ ተላጨች ያህል አንድ ነውና።
⁶ ሴትም ራስዋን ባትሸፍን ጠጉርዋን ደግሞ ትቆረጥ፤ ለሴት ግን ጠጉርዋን መቆረጥ ወይም መላጨት የሚያሳፍር ከሆነ ራስዋን ትሸፍን።
⁷ ወንድ የእግዚአብሔር ምሳሌና ክብር ስለ ሆነ ራሱን መከናነብ አይገባውም፤ ሴት ግን የወንድ ክብር ናት።
⁸ ሴት ከወንድ ናት እንጂ ወንድ ከሴት አይደለምና።
⁹ ሴት ስለ ወንድ ተፈጠረች እንጂ ወንድ ስለ ሴት አልተፈጠረምና።
¹⁰ ስለዚህ ሴት ከመላእክት የተነሣ በራስዋ ሥልጣን ሊኖራት ይገባል።
¹¹ ነገር ግን በጌታ ዘንድ ሴት ያለ ወንድ ወንድም ያለ ሴት አይሆንም።
¹² ሴት ከወንድ እንደ ሆነች እንዲሁ ወንድ ደግሞ በሴት ነውና፤ ሁሉም ከእግዚአብሔር ነው።
¹³ በእናንተ በራሳችሁ መካከል ፍረዱ፤ ሴት ራስዋን ሳትሸፍን ወደ እግዚአብሔር ልትጸልይ ይገባታልን?
¹⁴-¹⁵ ወንድ ጠጉሩን ቢያስረዝም ነውር እንዲሆንበት፥ ሴት ግን ጠጉርዋን ብታስረዝም ክብር እንዲሆንላት ተፈጥሮ እንኳ አያስተምራችሁምን? ጠጉርዋ መጎናጸፊያ ሊሆን ተሰጥቶአታልና።
¹⁶ ዳሩ ግን ማንም ሊከራከር ቢፈቅድ፥ እኛ ወይም የእግዚአብሔር አብያተ ክርስቲያናት እንዲህ ያለ ልማድ የለንም።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ጴጥሮስ 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹³ ስለዚህ የልቡናችሁን ወገብ ታጥቃችሁና በመጠን ኖራችሁ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲገለጥ የምታገኙትን ጸጋ ፈጽማችሁ ተስፋ አድርጉ።
¹⁴ እንደሚታዘዙ ልጆች ባለማወቃችሁ አስቀድሞ የኖራችሁበትን ምኞት አትከተሉ።
¹⁵-¹⁶ ዳሩ ግን፦ እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ ተብሎ ስለ ተጻፈ የጠራችሁ ቅዱስ እንደ ሆነ እናንተ ደግሞ በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ።
¹⁷ ለሰው ፊትም ሳያደላ በእያንዳንዱ ላይ እንደ ሥራው የሚፈርደውን አባት ብላችሁ ብትጠሩ በእንግድነታችሁ ዘመን በፍርሃት ኑሩ።
¹⁸-¹⁹ ከአባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከከንቱ ኑሮአችሁ በሚያልፍ ነገር በብር ወይም በወርቅ ሳይሆን፥ ነውርና እድፍ እንደ ሌለው እንደ በግ ደም በክቡር የክርስቶስ ደም እንደ ተዋጃችሁ ታውቃላችሁ።
²⁰-²¹ ዓለም ሳይፈጠር እንኳ አስቀድሞ ታወቀ፥ ነገር ግን እምነታችሁና ተስፋችሁ በእግዚአብሔር ይሆን ዘንድ፥ ከሙታን ባስነሣው ክብርንም በሰጠው በእግዚአብሔር በእርሱ ስለምታምኑ ስለ እናንተ በዘመኑ መጨረሻ ተገለጠ።
²² ለእውነት እየታዘዛችሁ ግብዝነት ለሌለበት ለወንድማማች መዋደድ ነፍሳችሁን አንጽታችሁ እርስ በርሳችሁ ከልባችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ።
²³ ዳግመኛ የተወለዳችሁት ከሚጠፋ ዘር አይደለም፥ በሕያውና ለዘላለም በሚኖር በእግዚአብሔር ቃል ከማይጠፋ ዘር ነው እንጂ።
²⁴ ሥጋ ሁሉ እንደ ሣር ክብሩም ሁሉ እንደ ሣር አበባ ነውና፤ ሣሩ ይጠወልጋል አበባውም ይረግፋል፤
²⁵ የጌታ ቃል ግን ለዘላለም ይኖራል። በወንጌልም የተሰበከላችሁ ቃል ይህ ነው።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 8
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁸ ሲሞንም በሐዋርያት እጅ መጫን መንፈስ ቅዱስ እንዲሰጥ ባየ ጊዜ፥ ገንዘብ አመጣላቸውና።
¹⁹ እጄን የምጭንበት ሁሉ መንፈስ ቅዱስን ይቀበል ዘንድ ለእኔ ደግሞ ይህን ሥልጣን ስጡኝ አለ።
²⁰ ጴጥሮስ ግን እንዲህ አለው፦ የእግዚአብሔርን ስጦታ በገንዘብ እንድታገኝ አስበሃልና ብርህ ከአንተ ጋር ይጥፋ።
²¹ ልብህ በእግዚአብሔር ፊት የቀና አይደለምና ከዚህ ነገር ዕድል ወይም ፈንታ የለህም።
²² እንግዲህ ስለዚህ ክፋትህ ንሰሐ ግባ፥ ምናልባትም የልብህን አሳብ ይቅር ይልህ እንደ ሆነ ወደ እግዚአብሔር ለምን፤
²³ በመራራ መርዝና በዓመፅ እስራት እንዳለህ አይሃለሁና።
²⁴ ሲሞንም መልሶ፦ ካላችሁት አንዳች እንዳይደርስብኝ እናንተው ወደ ጌታ ለምኑልኝ አላቸው።
²⁵ እነርሱም ከመሰከሩና የጌታን ቃል ከተናገሩ በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ በሳምራውያን በብዙ መንደሮችም ወንጌልን ሰበኩ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ታኅሣሥ_14_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"ወሌሊትኒ ብሩህ ከመ መዓልት። በአምጣነ ጽልመታ ከማሁ ብርሃና። እስመ አንተ ፈጠርከ ኵልያትየ እግዚኦ"። መዝ 138፥12-13።
"ጨለማ በአንተ ዘንድ አይጨልምምና፥ ሌሊትም እንደ ቀን ታበራለችና፤ እንደ ጨለማዋ እንዲሁ ብርሃንዋ ነው። አቤቱ፥ አንተ ኵላሊቴን ፈጥረሃልና፥ በእናቴም ሆድ ሰውረኸኛል"። መዝ 138፥12-13።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ታኅሣሥ_14_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ማቴዎስ 10
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁶ እነሆ፥ እኔ እንደ በጎች በተኵላዎች መካከል እልካችኋለሁ፤ ስለዚህ እንደ እባብ ልባሞች እንደ ርግብም የዋሆች ሁኑ።
¹⁷ ነገር ግን ወደ ሸንጎ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፥ በምኩራቦቻቸውም ይገርፉአችኋልና ከሰዎች ተጠበቁ፤
¹⁸ ለእነርሱና ለአሕዛብም ምስክር እንዲሆን፥ ስለ እኔ ወደ ገዥዎች ወደ ነገሥታትም ትወሰዳላችሁ።
¹⁹ አሳልፈውም ሲሰጡአችሁ፥ የምትናገሩት በዚያች ሰዓት ይሰጣችኋልና እንዴት ወይስ ምን እንድትናገሩ አትጨነቁ፤
²⁰ በእናንተ የሚናገር የአባታችሁ መንፈስ ነው እንጂ፥ የምትናገሩ እናንተ አይደላችሁምና።
²¹ ወንድምም ወንድሙን፥ አባትም ልጁን ለሞት አሳልፎ ይሰጣል፥ ልጆችም በወላጆቻቸው ላይ ይነሣሉ ይገድሉአቸውማል።
²² በሁሉም ስለ ስሜ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፤ እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል።
²³ በአንዲቱ ከተማም መከራ ቢያሳዩአችሁ ወደ ሌላይቱ ሽሹ፤ እውነት እላችኋለሁና፥ የሰው ልጅ እስኪመጣ ድረስ የእስራኤልን ከተማዎች አትዘልቁም።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️ የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #ሠለስቱ_ምዕት_ቅዳሴ ነው። መልካም በዓልና የነቢያት (የገና) የጾም ጊዜ ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ታኅሣሥ_15

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ታኅሣሥ ዐስራ አምስት በዚህች እለት #ቅዱስ_ጎርጎርዮስ_ዘአርማንያ ዕረፍታቸው ነው፣ ታላቁ ኢትዮጵያዊ ጻድቅ #አቡነ_ኤዎስጣቴዎስ_ከፋሌ_ባህር ልደታቸው ነው፣ #የቅዱስ_አቡነ_ሉቃስ_ዘዓምድ ዕረፍታቸው ነው፣ የእኔ ቢጤ የነበሩትና ጽድቃቸውን ማንም ሳያውቅባቸው የኖሩት #የአባ_ቆራይ ዕረፍታቸው ነው፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ጎርጎርዮስ_ዘአርማንያ

ታኅሣሥ ዐስራ አምስት በዚህች እለት የአርማንያ አገር ኤጲስቆጶስ አባ ጎርጎርዮስ ዕረፍታቸው ነው፡፡ ይህንንም ቅዱስ የንጉሡን ትእዛዝ ስለመተላለፍና ለአማልክት አልሠዋም ስላለ የአርማንያ ንጉሥ ድርጣድስ አሠቃይቶ ጥልቅ ወደ ሆነ ደረቅ ጒድጓድ ውስጥ ጨመረው በዚያ ዐሥራ አምስት ዓመት ኖረ። #እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነበር አንዲቷን አሮጊትም ሁል ጊዜ ምግቡን እንድታመጣለት አደረጋት ሕያው እንደሆነም የሚያውቅ የለም።

ንጉሥ ድርጣድስም ቅድስት አርሴማን ለማግባት ሽቶ ነበርና በእርሷ ምክንያት ደናግሎችን ገደላቸው። የእሊህ ደናግልም ሥጋቸው በተራራ ላይ እንደ ወደቆ ነበር ንጉሡም ስለ ገደላቸው ደናግል ይልቁንም ውበቷንና ደም ግባቷን እያሰበ ስለ ቅድስት አርሴማ አብዝቶ የሚያዝንና የሚጸጸት ሆነ።

ከዚህም በኋላ ወገኖቹ ለመኑት እንዲህም አሉት አውሬ ታድን ዘንድ በፈረስ ተቀመጥና ወደ ዱር እንውጣ የልብህም ኀዘን ይወገድልሃል። በዚያንም ጊዜ አውሬ ለማደን በፈረሱ ተቀምጦ ወደ ዱር ወጣ። የሚነክስ ሆነ ወገኖቹንም ነከሳቸው #እግዚአብሔርም መልኩን ለውጦ እንደ እሪያ አደረገው ያገኘውን ሁሉ የሚነክስ ሆነ። እንዲሁም ከቤተ መንግሥት ሰዎች በብዙዎቹ ላይ ሰይጣን አደረባቸው ታላቅ ድንጋጤም ሆነ ይህም ሁሉ የሆነ ስለ ቅዱሳት ደናግልና ስለ ቅድስት አርሴማ ነው።

የንጉሡ እኅት ግን "ጎርጎርዮስን ከጒድጓድ ካላስወጣችሁት ድኅነት የላችሁም" የሚላት ሰው በራእይ አየች ይህንንም ለወገኖቿ ነገረች እርሱ አስቀድሞ በጒድጓድ ውስጥ የሞተ ስለ መሰላቸው ደነገጡ። በዚያንም ጊዜ ወደ ጒድጓድ ሔዱ በሕይወት እንዳለም ያወቁ ዘንድ ወደ ጒድጓዱ ውስጥ ገመዶችን አወረዱና ገመዶቹን እንዲይዝ ወደርሱ ጮኹ እርሱም ገመዶችን ያዘ ስበው አወጡት አጥበውም ንጹሕ ልብስን አለበሱት በበቅሎም አስቀምጠው ወደ ቤተ መንግሥት አደረሱት። በዚያንም ጊዜ በሰማዕትነት ስለሞቱ ደናግል ሥጋ ጠየቀ እነርሱም የደናግሉ ሥጋቸው ወዳለበት መርተው አደረሱት የዱር አራዊትና አዕዋፍ ሳይበሏቸው በደኅና አገኛቸው ያማሩ ቦታዎችን አዘጋጅተው በውስጣቸው ያኖሩዋቸው ዘንድ አዘዘ እንዳዘዛቸውም አደረጉ።

ከዚህም በኋላ ንጉሡን ያድነው ዘንድ ሕዝቡ ለመኑት ንጉሡም ወዳለበት ዱር አደረሱት እርሱም "ከክፉ ሥራህ ትመለሳለህን? ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ታምናለህን?" አለው። እሪያ የሆነውም ንጉሥ አዎን እንደሚል ራሱን ዘንበል አድርጎ አመለከተ በዚያንም ጊዜ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ጸለየ ከንጉሡም ላይ በእሪያ አምሳል ሰይጣንን አስወጣው። የንጉሡም አእምሮውና መልኩ እንደ ቀድሞው ተመለሰለት ነገር ግን ዳግመኛ እንዳይታበይ ከእግሩ ላይ የእሪያ ጥፍር አስቀረ ፈጣሪውም ተገዢ ይሆን ዘንድ ዳግመኛም የቤተ መንግሥት ሰዎችን ሁሉንም አዳናቸው ከላያቸውም አጋንትን አስወጥቶ ሰደዳቸው።

ከዚህም በኋላ የአርማንያን ሰዎች ሁሉንም ሰበሰባቸውና ሥርዓትን ሠራላቸው ስምንት ቀንም እንዲጾሙ አዘዛቸው እንዳዘዛቸውም አደረጉ የ #እግዚአብሔርንም ሕግ እያስተማራቸው ኖረ። ዳግመኛም ክብር ይግባውና #መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ሰው መሆኑን አስተማራቸው ታላላቆችም ታናናሾችም ትምህርቱን ተቀበሉት ለአርማንያ ሰዎች ሃይማኖትን የመቀበላቸው ምክንያት ይህ ነው።

ከዚህም በኋላ የክርስትና ጥምቀትን ያጠምቃቸው ዘንድ ቅዱስ ጎርጎርዮስን ለመኑት እርሱም "እኔ ካህን ስለአልሆንኩ አይገባኝም ነገር ግን የሚያጠምቃችሁን ካህን ይልክላችሁ ዘንድ ወደሮሜ ሊቀ ጳጳሳት መልክተኞችን ላኩ" አላቸው። በዚያንም ጊዜ ከርሱ ጋር ወደ ንጉሥ አኖሬዎስና ወደ ሊቀ ጳጳሳቱ መልክተኞችን ልከው የአርማንያ ሰዎች ወደ #እግዚአብሔር እንደተመለሱ አስረዱአቸው ንጉሡም ሊቀ ጳጳሳቱም ሰምተው ደስ አላቸው ከዚህም በኋላ ሊቀ ጳጳሳቱ ለአርማንያ አገር ሊቀ ጳጳሳት ይሆን ዘንድ ቅዱስ ጎርጎርዮስን ሾመው ወደ አርማንያን ንጉሥ ወደ ድርጣድስም በክብር ላከው።

ቅዱስ ጎርጎርዮስም ተሹሞ ወደ አርማንያ አገር በደረሰ ጊዜ በመምጣቱ ደስ ተሰኙበት እርሱም የአርማንያን ሰዎች ሁሉንም አጠመቃቸው በእመቤታችን በቅድስት ድንግል #ማርያምም ስም ያማረች ቤተ ክርስቲያን ሠራላቸው ሃይማኖንትም ከአጸናቸውና መልካም ጉዞንም ከፈጸመ በኋላ ታኅሣሥ 15 ቀን በሰላም በፍቅር ዐረፈ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አቡነ_ኤዎስጣቴዎስ_ከፋሌ_ባህር

ዳግመኛም በዚህች ዕለት አጽፋቸውን እንደጀልባ ተጠቅመው የኢያሪኮን ባሕር የተሻገሩት ታላቁ ኢትዮጵያዊ ጻድቅ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ከፋሌ ባሕር ልደታቸው ነው፡፡ ኢትዮጵያዊው ጻድቅ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ አባታቸው ክርስቶስ ሞዐ ሲሆን እናታቸው ስነ ሕይወት ይባላሉ፡፡ ደጋግ የሆኑ ወላጆቻቸው በሃይማኖትና በምግባር ኮትኩተው አሳደጓቸው፡፡ በአደጉም ጊዜ ከአባ ዘካርያስ እጅ መነኮሱ፡፡ ታላላቅ ቅዱሳን እስኪያደንቋቸው ድረስ በጽኑ ተጋደሎ ሲኖሩ #ጌታችን ከቅዱሳን መላእክቱ ጋር ተገልጦላቸው በንፍሐት #መንፈስ_ቅዱስን አሳደረባቸው፡፡ ‹‹ከእናትህ ማኅፀን የመረጥኩህ ወዳጄ ኤዎስጣቴዎስ ሆይ ለብዙዎች ወንጌልን ትሰብክ ዘንድ ከኢትዮጵያ እስከ አርማንያ ድረስ መምህር አደረግሁህ፡፡ አንተን የሰማ እኔን ሰማ፣ አንተንም ያልሰማ እኔን ያልሰማ ነው›› ካለቸው በኋላ ወደ ሰማይ በክብር ዐረገ፡፡

አባታችን ቅስናን ከተሸሾሙ በኋላ ወንጌልን መስበክ ጀመሩ፡፡ እነ አቡነ አብሳዲን ጨምሮ ብዙዎችንም አመንኩሰው ደቀ መዛሙርቶቻቸው አደረጓቸው፡፡ እጅግ አስገራሚ ተአምራትን በማድረግ ለብዙ ሕሙማን መድኃኒት ሆኗቸው፡፡ ልጆቻቸውን ሰብስበው ከመናፍቃን ጋር በፍጹም እንዳይቀላቀሉ በመምከር አቡነ አብሳዲን ሾመውላቸው ወደ ኢየሩሳሌም በመሄድ ቅዱሳት ቦታዎችን ተሳለሙ፡፡ በመንገዳቸውም የ #ክርስቶስን ወንጌል እየሰበኩ ብዙዎችን ወደ ቀናች ሃይማኖት መለሷቸው፡፡ ወደ አርማንያም ሄደው ወደ ኢያሪኮ ባሕር በደረሱ ጊዜ መርከበኞችን እንዲያሳፍሯቸው ቢለምኗቸው እምቢ አሏቸው፡፡ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ግን አጽፋቸውን በባሕሩ ላይ ዘርግተው በስመ #ሥላሴ አማትበው አጽፋቸውን እንደመርከብ አድርገው ልጆቻቸውን ይዘው ባሕሩን ተሻገሩ፡፡ ልጆቻቸውን ‹‹ልጆቼ በልባችሁ ቂምንና ሽንገላን እንዳታኖሩ ተጠበቁ፣ ለእኔ ግን ከእናንተ አንዱ እንደሚጠፋ ይመስላኛል›› አሏቸው፡፡ ይህንንም እንዳሉ ከመካከላቸው አንዱ የቂም በቀል መከማቻ ነበርና ወዲያው ሰጠመ፡፡

አባታችን አርማንያ ደርሰው ከሊቀ ጳጳሳቱ ጋር ቡራኬን ከተሰጣጡ በኋላ ማስተማር ጀመሩ፡፡ የአርማንያ ሰዎች ሁሉም በሃይማኖት አንድ እስኪሆኑ ድረስ ታላላቅ ተአምራትን እያደረጉ አስተምረው አጠመቋቸው፡፡ አባታችን ጊዜ ዕረፍታቸው ሲደርስ #ጌታችን ተገልጦላቸው ታላቅ ቃልኪዳን ከሰጣቸው በኋላ መስከረም 18 ቀን ዐርፈው ሊቀ ጳጳሳቱና ካህናቱ በታላቅ ክብር ገንዘው በሰማዕቱ በቅዱስ መርምህናም ቤተ ክርስቲያን ቀብረዋቸዋል፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አቡነ_ሉቃስ_ዘዓምድ
በዚህች እለት በአንዲት ምሰሶ ላይ ወጥተው ከዚያ ሳይወርዱ በላይዋ ላይ ሆነው ታላቅ ተጋድሎን እየተጋደሉ 45 ዓመት የኖሩት አቡነ ሉቃስ ዘዓምድ ዕረፍታቸው ነው፡፡ ይኸውም ሀገሩ ፋርስ ሲሆን በመቶ የንጉሡ ጭፍራ ላይ መኰንን ሆኖ ተሹሞ ነበር፡፡ በኋላም ሹመቱን ትቶ ገዳም ገብቶ መነኮሰ፡፡ በምሥራቅ ካሉ ገዳማት ውስጥ በአንዱ ገብቶ ብዙ ዘመን ሲጋደል ኖረ፡፡ ልብሱንም የብረት ልብስ በማድረግ እስከ 6 ቀን የሚጾም ሆነ፡፡ ከዚህም በኋላ ከዓምድ ላይ ወጥቶ በዚያ ላይ ሦስት ዓመት ለጸሎት ቆመ፡፡ የታዘዘ መልአክም መጥቶ ከዚያ ዓምድ ላይ እንዲወርድ ነግሮት በብርሃን #መስቀል እየመራው ወስዶ አንድ ገዳም አደረሰው፡፡ በዚያም ብዙ ተአምራት እያደረገ ኖረ፡፡

ከዚህም በኋላ አቡነ ሉቃስ አርምሞ ያዘ፡፡ ከቶ እንዳይናገርም በአፉ ውስጥ ድንጋይ ነክሶ ያዘ፡፡ አሁንም መልአኩ ወደ ቍስጥንጥንያ ዳርቻ ቦታ ይዞት እየመራ ወስዶት በዚያም አንዲት ምሰሶ ላይ ወጥቶ ታላቅ ተጋድሎን እየተጋደለ በላይዋ ላይ 45 ዓመት ኖረ፡፡ በዚያም አስደናቂ ተአምራትን እያደረገ ብዙዎችን በመፈወስና ወንጌልን በማስተማር ብዙ ደከመ፡፡ ታኅሣሥ 15 ቀን ካረፈ በኋላ ሊቀ ጳጳሳቱና ካህናቱ መጥተው በክብር ወደ ቍስጥንጥንያ ከተማ ወሰዱት፡፡ በዚህም ጊዜ በድውያን ላይ ታላቅ ፈውስ ሆነ፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#የእኔ_ቢጤው_አባ_ቆራይ

በዚህች እለት ጻዱቁ አባ ቆራይ ዕረፍታቸው ነው፡፡ እጅና እግር የሌላቸውና የእኔ ቢጤ የነበሩት ጽድቃቸውን ማንም ሳያውቅባቸው የኖሩት አባ ቆራይ ጻድቅ መሆናቸው ካረፉ በኋላ ነው የታወቀው፡፡ ገዳማቸው ትግራይ ተንቤን ውስጥ ይገኛል፡፡ ቅዱሱ በዐፄ ልብነ ድንግል ዘመነ መንግሥት በትግራይ ተንቤን አውራጃ አዲ ራእሶት-የራሶች (የታላላቅ ሰዎች አገር) በሚባለው ቦታ የእግርና የእጅ ጣቶች የሌሏቸው አባ ቆራይ ወንበር በምትመስል ድንጋይ ላይ ተቀምጠው ተገለጡ፡፡

አንድ የአካባቢው ሰው በመንገድ ሲያልፍ አባ ቆራይ ድንጋይ ላይ ተቀምጠው ጸሎት ሲያደርጉ አያቸውና በሁኔታው ተገርሞ ወደ እርሳቸው ጠጋ ብሎ ስማቸውንና የመጡበትን አገር ጠየቃቸው፡፡ እርሳቸውም "ስሜ አባ ቆራይ ይባላል፣ አገር ግን የለኝም" አሉት፡፡ እርሱም "እባክዎን ወደ መንደር እንሂድና የጸሎትና ቤት ሠርተንልዎት በዚያ ይቀመጡ" አላቸው፡፡ አባ ቆራይ ግን "ማረፊያዬ ይህቺ ናት፣ ከዚህች ሥፍራ አልነሣም" አሉት፡፡ አባ ቆራይም በዚያው እንደተቀመጡ ዝናቸው በሁሉ ዘንድ ተሰማና ሰዎች መጥተው በተቀመጡበት ድንጋይ ዙሪያ ጎጆ ቀለሱላቸው፡፡

ከዚህም በኋላ መንደርተኞቹ በየተራ በምግብ ሊረዷቸው ዕጣ ተጣጥለው ወደየቤታቸወ ሄዱ፡፡ በመጀመሪያ ተራ የደረሰው ሰው ከአንድ ሰዓት በኋላ ምግብ ይዞ ቢመለስ የአባ ቆራይ ጎጆ በብርሃን ተሞልታ አገኘ፡፡ ወደ ጎጆዋም ሲጠጋ ነበልባሉ እየፈጀው አላስቀርበው አለ፡፡ እርሱም በድንጋጤ ወደ መንደሩ ተመልሶ ለአካባቢው ሰው ነግሮ ሁሉም ተሰብስበው መጡ፡፡ መንደርተኛውም ካህናትን ይዘው ብዙ የምሕላ ጸሎትና እግዚኦታ ካደረሱ በኋላ #እግዚአብሔር ወደ ጎጆዋ እንዲገቡ ፈቀደላቸውና ገቡ፡፡ ነገር ግን አባ ቆራይን በሕይወት አላገኟቸውም፡፡ አስክሬናቸውን ብርሃን ከቦት አገኙት፡፡ ከአስክሬናቸው አጠገብ "የአባ ቆራይን አስክሬን ከዚህች ጎጆ ውስጥ እንድትቀብሩት፤ ወደ ሌላ ቦታ ወይም ቤተ ክርስቲያን ወስደን እንቀብራለን ብላችሁ እንዳታስቡ፡፡ ነገሩን በድፍረት ብትፈጽሙት በሀገሩ ላይ #እግዚአብሔርን ቁጣ ታመጣላችሁ" የሚል ትእዛዝ በብራና ተጽፎ ተገኘ፡፡ በዚሁ ትእዛዝ መሠረት የሀገሩ ሕዝብ ተሰብስቦ አባ ቆራይን ታኅሣሥ 15 ቀን እዚያው ቀበሯቸው፡፡

ከጥቂት ዘመናት በኋላ ባልና ሚስት የሆኑ ሰዎች መቆምም ሆነ መራመድ የማይችል ድውይ ልጃቸውን ይዘው ወደ ጸበል ሲሄዱ መሸባቸውና በአካባቢው ማደሪያ ሲፈልጉ የአባ ቆራይ ጎጆ ክፍት ሆኖ ታያቸውና ልጃቸውን ይዘው ሄደው ገቡ፡፡ ድውይ ልጃቸውን በአባ ቆራይ መቃብር ላይ ቢያስተኙት የኤልሳዕን አጥንት እንደነካውና ፈጥኖ እንደተነሣው ሙት ይህ ድውይ ልጅም በአባ ቆራይ መቃብር ላይ እንዳረፈ ወዲያው አፈፍ ብሎ በመነሣት እንደ እንቦሳ ጥጃ መዝለል ጀመረ፡፡ ወላጆቹም እልልታቸውን አቀለጡት፡፡ ወላጆቹም በነጋ ጊዜ ወደ መንደርተኛው ሄደው የተደረገላቸውን ተአምር ተናገሩ፡፡ ከዚያም ጊዜ ጀምሮ የአባ ቆራይ በዓል በአካባቢውና አጎራባች ቦታዎች ሁሉ ዘንድ መከበር ጀመረ፡፡ የዕረፍታቸውም በዓል ታኅሣሥ 15 ቀን ሆነ፡፡

አባ ቆራይ ራሳቸውን ለ #እግዚአብሔር ለይተው እንደ ቅዱስ አልዓዛር (ሉቃ. 16፡19-35) ለዚህ ዓለም ውዳቂ መስለው ለታላቅ ክብር የበቁ ጻድቅ አባት ናቸው፡፡ ዛሬም ልብሳቸውንና አካላቸውን ብቻ እያየን የምንንቃቸው ሰዎች እንደ አባ ቆራይ ያሉ ቅዱሳን ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ከልዑል #እግዚአብሔር በቀር ማንም ማንንም የሚያውቅ የለም፡፡

#እግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ታኅሣሥ_15 እና #ከገድላት_አንደበት)
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ታኅሣሥ_15_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ፊልጵስዩስ 2
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁵ በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረ ይህ አሳብ በእናንተ ዘንድ ደግሞ ይሁን።
⁶ እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቈጠረውም፥
⁷ ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፥
⁸ በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፥ ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ።
⁹ በዚህ ምክንያት ደግሞ እግዚአብሔር ያለ ልክ ከፍ ከፍ አደረገው፥ ከስምም ሁሉ በላይ ያለውን ስም ሰጠው፤
¹⁰ ይህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ፥
¹¹ መላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደ ሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው።
¹² ስለዚህ፥ ወዳጆቼ ሆይ፥ ሁልጊዜ እንደ ታዘዛችሁ፥ በእናንተ ዘንድ በመኖሬ ብቻ ሳይሆን ይልቁን አሁን ስርቅ፥ በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የራሳችሁን መዳን ፈጽሙ፤
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ያዕቆብ 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁹ ስለዚህ፥ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፥ ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ ለመናገርም የዘገየ ለቍጣም የዘገየ ይሁን፤
²⁰ የሰው ቍጣ የእግዚአብሔርን ጽድቅ አይሠራምና።
²¹ ስለዚህ ርኵሰትን ሁሉ የክፋትንም ትርፍ አስወግዳችሁ፥ ነፍሳችሁን ማዳን የሚችለውን በውስጣችሁም የተተከለውን ቃል በየዋህነት ተቀበሉ።
²² ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ እንጂ ራሳችሁን እያሳታችሁ የምትሰሙ ብቻ አትሁኑ።
²³ ቃሉን የሚሰማ የማያደርገውም ቢኖር የተፈጥሮ ፊቱን በመስተዋት የሚያይን ሰው ይመስላል፤
²⁴ ራሱን አይቶ ይሄዳልና፥ ወዲያውም እንደ ምን እንደ ሆነ ይረሳል።
²⁵ ነገር ግን ነጻ የሚያወጣውን ፍጹሙን ሕግ ተመልክቶ የሚጸናበት፥ ሥራንም የሚሠራ እንጂ ሰምቶ የሚረሳ ያልሆነው፥ በሥራው የተባረከ ይሆናል።
²⁶ አንደበቱን ሳይገታ ልቡን እያሳተ እግዚአብሔርን የሚያመልክ የሚመስለው ማንም ቢኖር የእርሱ አምልኮ ከንቱ ነው።
²⁷ ንጹሕ የሆነ ነውርም የሌለበት አምልኮ በእግዚአብሔር አብ ዘንድ ይህ ነው፤ ወላጆች የሌላቸውን ልጆች ባልቴቶችንም በመከራቸው መጠየቅ፥ በዓለምም ከሚገኝ እድፍ ሰውነቱን መጠበቅ ነው።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 20
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²⁸ በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።
²⁹-³⁰ ከሄድሁ በኋላ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኩላዎች እንዲገቡባችሁ፥ ደቀ መዛሙርትንም ወደ ኋላቸው ይስቡ ዘንድ ጠማማ ነገርን የሚናገሩ ሰዎች በመካከላችሁ እንዲነሡ እኔ አውቃለሁ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ታኅሣሥ_15_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"ቀብፁኒ እምልብ ከመ ዘሞተ። ወኮንኩ ከመ ንዋይ ዘተኀጒለ። እስመ ሰማዕኩ ድምፀ ብዙኃን እለ ዐገቱኒ ዐውድየ"። መዝ 30፥12-13።
"እንደ ሞተ ሰው ከልብ ተረሳሁ፥ እንደ ተበላሸ ዕቃም ሆንሁ። የብዙ ሰዎችን ስድብ ሰምቻለሁና፤ በዙሪያው ፍርሃት ነበረ በላዬ በአንድነት በተሰበሰቡ ጊዜ ነፍሴን ለመንጠቅ ተማከሩ"። መዝ 30፥12-13።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ታኅሣሥ_15_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሉቃስ 15
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹¹ እንዲህም አለ፦ አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት።
¹² ከእነርሱም ታናሹ አባቱን፦ አባቴ ሆይ፥ ከገንዘብህ የሚደርሰኝን ክፍል ስጠኝ አለው። ገንዘቡንም አካፈላቸው።
¹³ ከጥቂት ቀንም በኋላ ታናሹ ልጅ ገንዘቡን ሁሉ ሰብስቦ ወደ ሩቅ አገር ሄደ፥ ከዚያም እያባከነ ገንዘቡን በተነ።
¹⁴ ሁሉንም ከከሰረ በኋላ በዚያች አገር ጽኑ ራብ ሆነ፥ እርሱም ይጨነቅ ጀመር።
¹⁵ ሄዶም ከዚያች አገር ሰዎች ከአንዱ ጋር ተዳበለ፥ እርሱም እሪያ ሊያሰማራ ወደ ሜዳ ሰደደው።
¹⁶ እሪያዎችም ከሚበሉት አሰር ሊጠግብ ይመኝ ነበር፥ የሚሰጠውም አልነበረም።
¹⁷ ወደ ልቡም ተመልሶ እንዲህ አለ፦ እንጀራ የሚተርፋቸው የአባቴ ሞያተኞች ስንት ናቸው? እኔ ግን ከዚህ በራብ እጠፋለሁ።
¹⁸ ተነሥቼም ወደ አባቴ እሄዳለሁና፦ አባቴ ሆይ፥ በሰማይና በፊትህ በደልሁ፥
¹⁹ ወደ ፊትም ልጅህ ልባል አይገባኝም፤ ከሞያተኞችህ እንደ አንዱ አድርገኝ እለዋለሁ።
²⁰ ተነሥቶም ወደ አባቱ መጣ። እርሱም ገና ሩቅ ሳለ አባቱ አየውና አዘነለት፥ ሮጦም አንገቱን አቀፈውና ሳመው።
²¹ ልጁም፦ አባቴ ሆይ፥ በሰማይና በፊትህ በደልሁ፥ ወደ ፊትም ልጅህ ልባል አይገባኝም አለው።
²² አባቱ ግን ባሪያዎቹን አለ፦ ፈጥናችሁ ከሁሉ የተሻለ ልብስ አምጡና አልብሱት፥ ለእጁ ቀለበት ለእግሩም ጫማ ስጡ፤
²³ የሰባውን ፊሪዳ አምጥታችሁ እረዱት፥ እንብላም ደስም ይበለን፤
²⁴ ይህ ልጄ ሞቶ ነበርና ደግሞም ሕያው ሆኖአል፤ ጠፍቶም ነበር ተገኝቶአልም። ደስም ይላቸው ጀመር።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️ የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #ሠለስቱ_ምዕት_ቅዳሴ ነው። መልካም የቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘአርማንያ፣ የአባ ቆራይ የዕረፍታቸ በዓል፣ የአቡነ ኤዎስጣቴዎስ የመታሰቢያቸው በዓልና የነቢያት (የገና) ጾም ጊዜ ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ታኅሣሥ_16

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ታኅሣሥ ዐስራ ስድስት በዚች ቀን የእስራኤል መሳፍንት አንዱ #ቅዱስ_ጌዴዎን_ኃያል ዐረፈ፣ #የሙሴ_እኅት_ማርያም መታሰቢያዋ ነው፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ጌዴዎን_ኃያል

ታኅሣሥ ዐስራ ስድስት በዚች ቀን የእስራኤል መሳፍንት አንዱ ጌዴዎን ዐረፈ፡፡ ይህም ከነገደ ምናሴ የሆነ የአባቱ ስም ዮአስ ይባላል ከ #እግዚአብሔርም የታዘዘ መልአክ ተገለጠለትና ለእስራኤል ሾመው። የጠዖታትንም መሠዊያ እነሰዲያፈርስ ዛፎችንም እንዲቆርጥ አዘዘው መሠዊያም ለ #እግዚአብሔር ሠርቶ በዚያ በሰበረው ዕንጨት እንዲሠዋ አዘዘው ሁሉንም እንዳዘዘው አደረገ። #እግዚአብሔር የላከው መልአክም ተመለከተው "እስራኤልን ከምድያም እጅ ታድናቸዋለህና ከሠራዊትህ ጋር ሒድ እነሆ ላክሁህ" አለው።

ጌዴዎንም "አድናቸዋለሁ እንዳልክ እስራኤልን በእጄ ታድናቸው እንደሆነ እነሆ እኔ በአደባባይ የተባዘተ ፀምርን እዘረጋለሁ ጠል በምድር ላይ ሳይወርድ በፀምሩ ላይ ብቻ ቢወርድ አድናቸዋለሁ እንዳል እስራኤልን በእጄ እንድታድ ናቸው ያን ጊዜ አውቃለሁ" አለ እንዳለውም ሆነ። ጌዴዎንም በማግሥቱ ማልዶ ሒዶ ያንን ጨመቀው ከዚያ ፀምር አንድ መንቀል ሙሉ ውኃ ወጣ።

ጌዴዎን #እግዚአብሔርን "በቊጣህ አትቆጣኝ ዳግመኛ አንድ ጊዜ ልናገር በፀምር ላይ ብቻ ሳይወርድ ጠል በምድር ሁሉ ላይ ይውረድ" አለው። #እግዚአብሔርም በዚያች ሌሊት እንዳለው አደረገ። ፀምሩ ብቻ ደረቅ ሁኖ ጠል በምድር ሁሉ ላይ ወረደ። ጌዴዎንንም የ #እግዚአብሔር መንፈስ ረድኤት አጸናው ነጋሪትንም መታ አብያዜርም በኋላው ሁኖ ደነፋ ወደ ነገደ ምናሴር፣ ወደ ነገደ ዛብሎን፣ ወደ ነገደ ንፍታሌምም መልክተኞችን ላከ ወጥተውም ተቀበሏቸው። ጌዴዎንም ከርሱ ጋር ያሉ ወገኖቹም ሁሉ ሔዱ አሮኤድ በሚባል አገርም ሰፈሩ የመሰድያምና የአማሌቅ ሠራዊትም በእንበሬም ቆላ መሠዊያ ቀኝ ሰፈሩ።

#እግዚአብሔርም ጌዴዎንን "እጃችን አዳነችን ብለው እንዳመኩብኝ የምድያምን ሰዎች በእጃቸው መጣል እንደማልችል ካንተ ጋር ያሉ ሕዝብ ብዙ ናቸው" #እግዚአብሔር ጌዴዎንን እንዲህ አለው "ከእናንተ የሚፈራ የመመደነግጥ ሰው ከሕዝቡ ተለይቶ ይመለስ" ብለህ ለሕዝቡ ንገራቸው። ሕዝቡም ከገለዓድ ተመለሱ ከሕዝቡም ሁለት እልፍ ከሁለት ሽህ ተመልሰው እልፍ ሰዎች ቀሩ።

#እግዚአብሔር ጌዴዎንን "ገና ብዙ ሕዝብ አሉ ወደ ውኃ አውርደህ በዚያ ፈትናቸው እኔ ይሒዱ የምልህ ሰዎች እነርሳቸው ካንተ ጋር ይሒዱ" አለው ሕዝቡንም ወደ ውኃ አወረዳቸው። #እግዚአብሔር ጌዴዎንን "ውሻ በምላሱ ጠለፍ ጠለፍ አድርጎ እንዲጠጣ ከውኃው ጠለፍ ጠለፍ አድርጎ የሚጠጣውን ሁሉ ለብቻው አቁመው ውኃን ይጠጣ ዘንድ በጉልበቱ የተንበረከከውንም ሁሉ ለብቻው አቁመው" አለው። በምላሳቸው ጠለፍ ጠለፍ አድርገው የጠጡ ሰዎች ቊጥራቸው ሦስት መቶ ሆነ የቀሩት ሕዝብ ግን ውኃን ይጠጡ ዘንድ በጉልበታቸው ተንበረከኩ።

#እግዚአብሔርም ጌዴዎንን "እንደዚህ በእጃቸው ውኃን በጠጡት በእነዚህ ሦስት መቶ ሰዎች አድናችኋለሁ የምድያምን ሰዎች ወደ ቤታቸው ይመለሱ" አለው። በዚያችም ሌሊት እሊህ ሦስት መቶ ሰዎች መለከትን ነፉ "ይህ የ #እግዚአብሔር ኃይልና የጌዴዎን ጦር ነው" ብለው ጮኹ። የምድያምም ሰዎች የመለከቱን ድምፅ በሰሙ ጊዜ #እግዚአብሔር በልባቸው ፍርሀትን አሳድሮባቸው ደንግጠው ሸሹ #እግዚአብሔርም ያንዱን ሰይፍ ወዳንዱ ወደ ጓደኛው መለሰ በሠራዊቶቻቸው ሁሉ እርስበርስ መተላለቅ ሆነ መኳንንቶቻቸውን ኄሬብንና ዜብን ነገሥቶቻቸው ዛብሄልንና ስልማናንም ገደሏቸው ከምድያምም ሠራዊት ፈረሰኞችና ጦረኞችን አንድ መቶ ሁለት ሽህ ገደሉ።

ከዚህም በኋላ የምድያም ሰዎች በእስራኤል ፊት ተዋረዱ ዳግመኛም ራሳቸውን ከፍ ከፍ አላደረጉም በጌዴዎንም ዘመን ምድር አርባ ዘመን ዐረፈች። ከዚህም በኋላ በዚች ቀን ታኅሣሥ16 በሰላም በፍቅር ዐረፈ።

#እግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ ጌዴዎን ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ማርያም_እህተ_ሙሴ

ዳግመኛም በዚህች ቀን የሙሴ እኅት ማርያም መታሰቢያዋ ነው፡፡ ይህች እናት የሊቀ ነቢያት ቅዱስ ሙሴና የሊቀ ካህናቱ ቅዱስ አሮን ትልቅ እህት ስትሆን ወላጆቿ እንበረምና ዮካብድ ይባላሉ:: እሥራኤል ከግብጽ ባርነት እንዲወጡ የእርሷን ያህል አስተዋጽኦ ያደረገች ሴት የለችም::

ከመነሻውም ቅዱስ ሙሴን የጠበቀች: በሕግ በሥርዓት እንዲያድግ ከእናቱ ጋር ያገናኘች: ወገኖቿ ከግብጽ ሲወጡም ሴቶችን የመራች እናት ናት:: ወንድሞቿን ሙሴንና አሮንንም ታገለገላቸው ነበር:: በተለይ #እግዚአብሔር ባሕረ ኤርትራን የብስ ሲያደርጋት ከበሮን አንስታ "ንሴብሖ ለ #እግዚአብሔር" ብላ ፈጣሪዋን አመስግናለች:: (ዘጸ. 15:20)

አንድ ጊዜም "ኢትዮዽያዊቷን ሲፓራን ለምን አገባህ" በሚል ስለ ተናገረችው #እግዚአብሔር ተቆጥቶ በለምጽ መቷታል:: (ዘኁ. 12:1) ቆይቶም በቅዱሱ ምልጃ ምሯታል:: ማርያም በመንገድ ሳሉ: ወደ ርስት ሳይደርሱ ዐርፋ ተቀብራለች:: (ዘኁ. 20:1)

#እግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ታኅሣሥ እና #ዲያቆን_ዮርዳኖስ_አበበ)
#ታኅሣሥ_16 #አቡነ_መርቆሬዎስ
ዘደብረ ድማኅ +

በውስጡ አጋንንት ያደሩበት ቁመቱ 170 ክንድ ወርዱ 9 ክንድ ከስንዝር የሆነ ሰይጣን ያደረበት ዘንዶ ቢመጣባቸው በጸሎት ወደ ፈጣሪያቸው አመልክተው #ቅዱስ_ሚካኤል በሰጣቸው #መስቀል ዘንዶውን የገደሉት አቡነ መርቆሬዎስ ዘደብረ ድማኅ ዕረፍታቸው ነው።

የአቡነ መርቆሬዎስ ወላጆቻቸው ካህኑ ቶማስ ስምዖን እና ሰሎሜ #እግዚአብሔርን የሚያገለግሉ ቅዱሳን ስለነበሩ በየወሩም ዝክረ ቅዱስ ሰማዕት መርቆሬዎስ (ፒሉፓዴር) እያደረጉ ሲኖሩ በእለተ ቀኑ ተኣምር ስለተደረገላቸው የልጃቸውን ስም መርቆሬዎስ ብለው ሰየሙት፡፡

አቡነ መርቆሬዎስ ከተወለዱበት ጊዜ ጀምሮ ሲያሳዩት የነበው ተግባራት ሁሉ የትልቅ ሰው እንጂ የአንድ ሕፃን ጠባይ ስላልሆነ ወላጆቻቸው በአንክሮ ያስተውሉ ነበር፡፡ አቡነ መርቆሬዎስም ፊደል በመቁጠር የጀመሩት መንፈሳዊ ትምህርት 22 ዓመት ሲሞላቸው የብሉይ ኪዳንና የሐዲስ ኪዳን እንዲሁም የሁሉም መጻሕፍት ምሥጢር ተገለጠላቸው፡፡ ከአቡነ ኤዎስጣቴዎስ ደግሞ በ33 ዓመታቸው በደብረ ሸማና እያሉ ምንኵስናን እና አስኬማን መላእክትን ተቀበሉ፡፡ ከዚህኽም በኋለ አቡነ መርቆሬዎስ ለረጅም ጊዜ በምናኔ ኖረው ወንጌልን በመስበክና ክርስትናን በማስፋፋት ወደ ተለያዩ ሀገሮች እየተዘዋወሩ እያስተማሩ በርካታ ተኣምራትንም እያደረጉ ለ67 ዓመታት ያህል በታላቅ ተጋድሎ ኖሩ፡፡ አቡነ መርቆሬዎስ የመንፈስ አባታቸው የሆኑት አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ወደ ኤርትራ ሀገር እንደሚሔዱ በ #መንፈስ_ቅዱስ ዐውቀው በራቂት የምትባል ቦታ ላይ ኹለቱ ቅዱሳን ተገናኙ፡፡ ኹለቱም ቅዱሳን አብረው ወንጌል እየሰበኩ ማይምነ ሲደርሱ ግን ሕዝቡን ከ #እግዚአብሔር ሕግ ርቆ በኀጢአት ወድቆ አገኙት፤ በዚያ ያሉ ክፉዎች ሰዎችም
በሰይጣን ምክር ተመርተው አባቶቻችን ተኝተውባት የነበረችውን ጎጆ በእሳት አቃጠሏት።

ቅዱሳኑ አቡነ መርቆሬዎስና አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ግን በዛ እሳት ሳይነኩ በ #እግዚአብሔር ተኣምር ዳኑ፡፡ ከዚኽም በኋላ እነዚህ ቅዱሳን አባቶች በአሁኑ ደብረ ደናግል ደብረ ድማኅ በሚባለው ቦታ ላይ ሱባኤ ገብተው አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ለሰባት ዓመት፣ አቡነ መርቆሬዎስ ደግሞ ለአራት ዓመት ባእት አበጅተው በጽኑ ተጋድሎ ኖሩ፡፡ ከሰባት ዓመት ሱባኤ በኋላ ከ #እግዚአብሔር ባዘዛቸውና ራእይ ባዩት መሠረት አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ወደ አርማንያ እንዲሔዱ ሲነገራቸው አቡነ መርቆሬዎስን ደግሞ አንዲት ወፍ እየመራቻቸው ዛሬ ላይ በስማቸው ወደሚጠራው ታላቁ ገዳም ደብረ ድማኅ አደረሰቻቸው፡፡ አቡነ መርቆሬዎስም ቦታዋን እንዳዩአት ‹‹ይህቺ ለዘለዓለም ማረፊያየ ናት›› አሉ፡፡ የክብር ባለቤት #መድኀኔዓለምም በአካል ተገልጦላቸው መጥቶ በአራቱ ማዕዘን ባረከላቸው፡፡ በዚህ ቦታ ላይ ይኖሩ የነበሩት ሰዎችም አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ወደ አርማንያ እንደሚሔዱ ሲሰሙ ‹‹የእናንተ ረድኤት እንዲሆንልን ቀድሳችሁ አቊርቡን›› ሲሏቸው ሁለቱ ቅዱሳን በጋራ ጥር 18 ቀን ቅዳሴ ቀድሰው ሕዝቡን አቊርበዋል፡፡

አቡነ መርቆሬዎስም አባታቸውን አቡነ ኤዎስጣቴዎስን ተከትለው ኹለቱም እስከ ሱዳን ድረስ ሔደው ወንጌልን በመስበክ ሰፊ ሐዋርያዊ አገልግሎት ሰጥተዋል፡፡ ከዚኽም በኋላ በግብፅ ተሻግረው አርማንያ ደርሰው ወደ ኢየሩሳሌም በመሔድ ቅዱሳት መካናትን ተሳልመዋል፡፡ ከዚያም አቡነ መርቆሬዎስ ወደ ገዳም ተመልሰው ሲመጡ ዉጡሕ በተባለ ቦታ ላይ በኣት አጽንተው ሱባኤ ያዙ፡፡ እርሳቸውም በዕለተ ዐርብ መጋቢት 12 ቀን የ #ቅዱስ_ሚካኤል በዓል ዕለት በኣታቸው ውስጥ እየጸለዩ ሳሉ ድንገት ቁመቱ 170 ክንድ ጎኑ ደግሞ 9 ክንድ ከስንዝር የሚሆን ሰይጣን ከነጭፍሮቹ በውስጡ ያደረበት ታላቅ ዘንዶ ይውጣቸው ዘንድ መጣ፡፡ ነገር ግን #እግዚአብሔር ከእርሳቸው ጋር ስለነበር ጸሎታቸውን ሰምቶ #ቅዱስ_ሚካኤልን ላከላቸው፡፡ መልአኩም ድል የሚያደርጉበትን #መስቀል ሰጣቸው፡፡

ጻድቁም ከመልአኩ በተቀበሉት# ቅዱስ_መስቀል በ #ሥላሴ ስም ቢያማትቡበት ዘንዶው ተሰንጥቆ በውስጡ አድረውበት የነበሩት አጋንንት ከዘንዶው ወጥተው ሮጠው ሊያመልጡ ሲሉ አባታችን አወገዟቸው፡፡ ዘንድውንም ወስደው ዱበና በሚባል በረሓ ውስጥ ጣሉት፡፡ ጻድቁም ዘንዶውን ስለገደሉላቸው ለአካባቢው ሰዎችም ሆነ ለፍጥረታት ሁሉ ሰላምና ዕረፍት ሆነላቸው፡፡ ይኽንንም መሠረት በማድረግ በየአመቱ መጋቢት 12 ቀን መነኰሳት አባቶች ከገዳም ታቦት ይዘው ወደዚህ ቦታ በመሔድ ይቀድሳሉ፣ በዓሉንም ያከብራሉ፡፡ በወቅቱ ሊቀ መላእክት #ቅዱስ_ሚካኤል የሰጣቸው ረጅም# መስቀልም እስከ አሁን ድረስ የተለያየ ተኣምራት እያደረገ በገዳሙ ይገኛል፡፡ አቡነ መርቆሬዎስ ከብዙ ተጋድሎ በኋላ ‹‹ሥጋየ የሚያርፍበትን ቦታ ግለጽልኝ›› ብለው ወደ #እግዚአብሔር ቢጸልዩ በአሁኑ ጊዜ ቅዱስ ዐፅማቸው በክብር ያረፈበት ገዳም ደብረ ድማኅ እንደሆነ ገለጸላቸው፡፡ በ1340 ዓ.ም ስድስት መቶ መነኰሳትና ሦስት መቶ መነኰሳያይት ወደ አባታችን መጥተው መንኵሰዋል፡፡ አቡነ መርቆሬዎስም ሥርዐተ ምንኵስና ሠርተው ገዳም ገድመው ልጆቻቸውን በቅድስና ሲጠብቁ ኖሩ፡፡ አቡነ መርቆሬዎስ ገዳማቸው ሳሉ በአርማንያ ሀገር የአቡነ ኤዎስጣቴዎስ የዕረፍታቸው ነገር በራእይ ስለተገለጠላቸው ከ25 መነኰሳት ጋር ወደ አርማንያ ሔዱ፡፡ ነገር ግን ለመርከብ የሚከፍሉት ገንዘብ ስላልነበራቸው አስቀድመው ከአባታቸው ጋር በአጽፋቸው የተሻገሩትን ባሕር በደመና ተጭነው በማለፍ አርማንያ ሀገር ደርሰው አቡነ ኤዎስጣቴዎስን አገኟቸው፡፡ ኹለቱም ቅዱሳን ሲነጋገሩ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ‹‹…ምሰሶ ተሰበረ›› አሉ፡፡ አቡነ መርቆሬዎስም ‹‹ምሰሶው ምንድነው?›› ብለው ሲጠቋቸው ‹‹የኢትዮጵያው ንጉሥ ዓምደ ጽዮን ሞተ›› አሏቸው፡፡ አቡነ ኤዎስጣቴዎስም እንደተናገሩት በዚያን ጊዜ ንጉሡ በኢትዮጵያ ምድር እንደ ሞተ ተረጋገጠ፡፡ ከዚኽም በኋላ አቡነ መርቆሬዎስ አባታቸው አቡነ ኤዎስጣቴዎስን አሟሙተው ማለትም ገንዘው ቀብረው ወደ ገዳማቸው ሲመለሱ ዳግመኛም ታናሽ ወንድማቸው አቡነ አብሳዲም ዐርፈው ስለደረሱ እጅግ አዘኑ፡፡አቡነ መርቆሬዎስ ከአርማንያ ተመልሰው ሲመጡ ተኸላ የሚባል ቦታ ገዳም መሥርተው ዐሥር ዓመታት ኖረዋል፡፡ ቅዱስ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ወደ አርማንያ ሲሔዱ ‹‹እንደ እኔ ሁናቸው›› ብለው የእጅ መስቀላቸውን የሰጡት ለአቡነ አብሳዲ ነበር፡፡ ከአቡነ አብሳዲ ዕረፍት በኋላ የገዳሙን ኀላፊነት የተረከቡት አቡነ መርቆሬዎስ ሆኑ፡፡ በአቡነ መርቆሬዎስ ገዳም በደብረ ድማኅ አበ ምኔት ሆነው የተሾሙት አባቶች ሁሉ በዚህ መንበር ነው የሚሾሙት፡፡ አቡነ መርቆሬዎስ ተጋድሏቸውን ፈጽመው ዕድሜያቸውም እየገፋ ሔዶ 130 ዓመት ሲደርሱ ለልጆቻቸው መሪ ይሆኑ ዘንድ በእርሳቸው ምትክ አባ ገብር ኄርን ሾሙላቸው፡፡ የክብር ባለቤት #ጌታችንም ተገልጦላቸው ታላቅ ቃልኪዳን ከገባላቸው በኋላ ታኅሣሥ 16 ቀን 1411 ዓ.ም በ130 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሥጋ ሞት ተለዩ፡፡

ደብረ ድማኅ አቡነ መርቆሬዎስ ገዳም ከጥንታዊ ገዳማት ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ገዳሙ ታላቅ የምናኔ ቦታ ከመሆኑም ባሻገር በርካታ ሊቃውንት የሚወጡበት ነው፡፡ የትርጓሜ መጻሕፍት፣ የብሉይና ሐዲስ፣ የቅኔ፣ የምዕራፍ፣ የጾመ ድጓ እና የመዝገበ ቅዳሴ መምህራን ከዚህ ገዳም ታጥተው አያውቁም፡፡ በደቡብ ዞን ዓረዛ ቆላ ሠራየ በሚባል ቦታ የሚገኝ ሲሆን ከአስመራ 102 ኪ.ሜ ርቀት ላይ እንዲሁም ከባሕር ወለል በላይ 2075 ሜትር ከፍታ ላይ የሚገኝ ታላቅ ገዳም ነው።

የጻድቁ አቡነ መርቆሬዎስ በረከታቸው ይደርብን🙏
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ታኅሣሥ_16_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ዕብራውያን 11
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
³² እንግዲህ ምን እላለሁ? ስለ ጌዴዎንና ስለ ባርቅ ስለ ሶምሶንም ስለ ዮፍታሔም ስለ ዳዊትና ስለ ሳሙኤልም ስለ ነቢያትም እንዳልተርክ ጊዜ ያጥርብኛልና።
³³ እነርሱ በእምነት መንግሥታትን ድል ነሡ፥ ጽድቅን አደረጉ፥ የተሰጠውን የተስፋ ቃል አገኙ፥
³⁴ የአንበሶችን አፍ ዘጉ፥ የእሳትን ኃይል አጠፉ፥ ከሰይፍ ስለት አመለጡ፥ ከድካማቸው በረቱ፥ በጦርነት ኃይለኞች ሆኑ፥ የባዕድ ጭፍሮችን አባረሩ።
³⁵ ሴቶች ሙታናቸውን በትንሣኤ ተቀበሉ፤ ሌሎችም መዳንን ሳይቀበሉ የሚበልጠውን ትንሣኤ እንዲያገኙ እስከ ሞት ድረስ ተደበደቡ፤
³⁶ ሌሎችም መዘበቻ በመሆንና በመገረፍ ከዚህም በላይ በእስራትና በወኅኒ ተፈተኑ፤
³⁷ በድንጋይ ተወግረው ሞቱ፥ ተፈተኑ፥ በመጋዝ ተሰነጠቁ፥ በሰይፍ ተገድለው ሞቱ፥ ሁሉን እያጡ መከራን እየተቀበሉ እየተጨነቁ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ፤
³⁸ ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ፥ በዋሻና በምድር ጕድጓድ ተቅበዘበዙ።
³⁹-⁴⁰ እነዚህም ሁሉ በእምነታቸው ተመስክሮላቸው ሳሉ የተሰጠውን የተስፋ ቃል አላገኙም፥ ያለ እኛ ፍጹማን እንዳይሆኑ እግዚአብሔር ስለ እኛ አንዳች የሚበልጥ ነገርን አስቀድሞ አይቶ ነበርና።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ጴጥሮስ 3
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁵ እንዲህ በቀድሞ ዘመን በእግዚአብሔር ተስፋ ያደረጉት ቅዱሳት ሴቶች ደግሞ ለባሎቻቸው ሲገዙ ተሸልመው ነበርና፤
⁶ እንዲሁም ሣራ ለአብርሃም፦ ጌታ ብላ እየጠራችው ታዘዘችለት፤ እናንተም ከሚያስደነግጥ ነገር አንዳች እንኳ ሳትፈሩ መልካም ብታደርጉ ልጆችዋ ናችሁ።
⁷ እንዲሁም፥ እናንተ ባሎች ሆይ፥ ደካማ ፍጥረት ስለ ሆኑ ከሚስቶቻችሁ ጋር በማስተዋል አብራችሁ ኑሩ፤ ጸሎታችሁ እንዳይከለከል አብረው ደግሞ የሕይወትን ጸጋ እንደሚወርሱ አድርጋችሁ አክብሩአቸው።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 13
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²⁰ ከዚህም በኋላ እስከ ነቢዩ እስከ ሳሙኤል ድረስ አራት መቶ አምሳ ዓመት ያህል መሳፍንትን ሰጣቸው።
²¹ ከዚያም ወዲያ ንጉሥን ያነግሥላቸው ዘንድ ለመኑ፥ እግዚአብሔርም ከብንያም ወገን የሚሆን ሰው የቂስን ልጅ ሳኦልን አርባ ዓመት ሰጣቸው፤
²² እርሱንም ከሻረው በኋላ ዳዊትን በእነርሱ ላይ እንዲነግሥ አስነሣው፥ ሲመሰክርለትም፦ እንደ ልቤ የሆነ ሰው ፈቃዴንም ሁሉ የሚያደርግ የእሴይን ልጅ ዳዊትን አገኘሁ አለ።
²³ ከዚህም ሰው ዘር እግዚአብሔር እንደ ተስፋው ቃል ለእስራኤል መድኃኒትን እርሱም ኢየሱስን አመጣ።
²⁴ ከመምጣቱ በፊት ዮሐንስ አስቀድሞ ለእስራኤል ሕዝብ ሁሉ የንስሐን ጥምቀት ሰብኮ ነበር።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ታኅሣሥ_16_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"አዋልደ ንግሥት ለክብርከ። ወትቀውም ንግሥት በየማንከ። በአልባሰ ወርቅ ዑጽፍት ወኊብርት"። መዝ.44፥9።
“የንጉሦች ሴት ልጆች ለክብርህ ናቸው፤ በወርቅ ልብስ ተጐናጽፋና ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች።” መዝ.44፥9
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ታኅሣሥ_16_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ዮሐንስ 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ በመጀመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ።
² ይህ በመጀመሪያው በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ።
³ ሁሉ በእርሱ ሆነ፥ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም።
⁴ በእርሱ ሕይወት ነበረች፥ ሕይወትም የሰው ብርሃን ነበረች።
⁵ ብርሃንም በጨለማ ይበራል፥ ጨለማም አላሸነፈውም።
⁶ ከእግዚአብሔር የተላከ ስሙ ዮሐንስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤
⁷ ሁሉ በእርሱ በኩል እንዲያምኑ ይህ ስለ ብርሃን ይመሰክር ዘንድ ለምስክር መጣ።
⁸ ስለ ብርሃን ሊመሰክር መጣ እንጂ፥ እርሱ ብርሃን አልነበረም።
⁹ ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም ይመጣ ነበር።
¹⁰ በዓለም ነበረ፥ ዓለሙም በእርሱ ሆነ፥ ዓለሙም አላወቀውም።
¹¹ የእርሱ ወደ ሆነው መጣ፥ የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትም።
¹² ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤
¹³ እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም።
¹⁴ ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፥ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነው ክብሩን አየን።
¹⁵ ዮሐንስ ስለ እርሱ መሰከረ እንዲህም ብሎ ጮኸ፦ ከእኔ በኋላ የሚመጣው እርሱ ከእኔ በፊት ነበረና ከእኔ ይልቅ የከበረ ሆኖአል፤ ስለ እርሱ ያልሁት ይህ ነበረ።
¹⁶ እኛ ሁላችን ከሙላቱ ተቀብለን በጸጋ ላይ ጸጋ ተሰጥቶናልና ሕግ በሙሴ ተሰጥቶ ነበርና፤
¹⁷ ጸጋና እውነት ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ሆነ።
¹⁸ መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው።
¹⁹ አይሁድም፦ አንተ ማን ነህ? ብለው ይጠይቁት ዘንድ ከኢየሩሳሌም ካህናትንና ሌዋውያንን በላኩበት ጊዜ፥ የዮሐንስ ምስክርነት ይህ ነው።
²⁰ መሰከረም አልካደምም፤ እኔ ክርስቶስ አይደለሁም ብሎ መሰከረ።
²¹ እንኪያስ ማን ነህ? ኤልያስ ነህን? ብለው ጠየቁት። አይደለሁም አለ። ነቢዩ ነህን? አይደለሁም ብሎ መለሰ።
²² እንኪያስ፦ ማን ነህ? ለላኩን መልስ እንድንሰጥ፤ ስለራስህ ምን ትላለህ? አሉት።
²³ እርሱም፦ ነቢዩ ኢሳይያስ እንዳለ፦ የጌታን መንገድ አቅኑ ብሎ በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ እኔ ነኝ አለ።
²⁴-²⁵ የተላኩትም ከፈሪሳውያን ነበሩና፦ እንኪያስ አንተ ክርስቶስ ወይም ኤልያስ ወይም ነቢዩ ካይደለህ፥ ስለ ምን ታጠምቃለህ? ብለው ጠየቁት።
²⁶ ዮሐንስ መልሶ፦ እኔ በውኃ አጠምቃለሁ፤ ዳሩ ግን እናንተ የማታውቁት በመካከላችሁ ቆሞአል፤
²⁷ እኔ የጫማውን ጠፍር ልፈታ የማይገባኝ፥ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ከእኔ ይልቅ የሚከብር ይህ ነው አላቸው።
²⁸ ይህ ነገር ዮሐንስ ያጠምቅበት በነበረው በዮርዳኖስ ማዶ በቢታንያ በቤተ ራባ ሆነ።
²⁹ በነገው ዮሐንስ ኢየሱስን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ እንዲህ አለ፦ እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️ የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #እመቤታችን_የማርያም_ቅዳሴ ነው። መልካም የቅዱስ ጌዴዎን፣ የአቡነ መርቆሬዎስ የዕረፍት በዓልና የቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ በዓል። ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ለቀራንብትኪ

#እመቤቴ_ኪዳነ_ምህረት_ሆይ የዓይኖችን እይታና አገላለጥ ለመጠበቅና ለመንከባከብ ለተፈጠሩ ቀራንብቶሽ ሰላምታ ይገባል።

#የቃል_ኪዳኗ_እመቤት_ሆይ ያለዘርዓ ብእሲ የወለድሽውን ልጅሽን ኃጥአን እንኳን ቢሆኑ ስምሽን ከጠሩ እምርልሻለሁ ስትል የገባህልኝ ቃል ኪዳን ወዴት አለ ብለሽ አሳስቢው።
2025/01/01 01:40:33
Back to Top
HTML Embed Code: