Telegram Web Link
በዚችም ዕለት በምዕራባዊ በረሀ የሚኖር ታላቅና ክቡር አባት የሆነው የአባ ኪሮስ የልደቱ መታሰቢያ ሆነ።

ይህም ቅዱስ የታላቁ ንጉሥ ቴዎዶስዮስ ወንድሙ ነበር በከተማ ውስጥ የሚሠራውን ዐመፅ በአየ ጊዜ ገንዘቡን ሁሉ ትቶ ከሀገሩ ወጣ። #ጌታቸንም መርቶ ወደዚች ምዕራባዊት በረሀ አደረሰው በውስጧም ብዙ ዘመናት ብቻውን ኖረ ከሰው ማንም አላየውም በዚህ ሁሉ ዘመን የዱር አራዊትም ቢሆኑ ።

በአስቄጥስም ገዳም ስሙ አባ ባውማ የሚባል አንድ ቄስ ነበረ እርሱም የንጉሥ ዘይኑን ልጅ ቅድስት ኢላርያን ሥጋዋን የገነዘ ነው ። እርሱም እንዲህ አለ በቤተ ክርስቲያን ወስጥ እያለሁ አባ ባውማ ሆይ ተነሥ ወደ በረሀው ውስጥ ገብተህ ወደ ፀሐይ መግቢያ ሒድ ከቅዱሳን ሁሉ አብዝቶ ፈቃዴን የፈጸመውን የአንድ ገዳማዊ ሥጋ ትገንዝ ዘንድ የሚለኝን ቃል ከሰማይ ሰማሁ።

ያን ጊዜም ደስ ብሎኝ ተነሣሁ በበረሀውም ውስጥ ሦስት ቀን ተጉዤ ከአንድ ገዳማዊ በዓት ደርሼ ደጁን አንኳኳሁ አንድ ሽማግሌ ገዳማዊም ከፈተልኝና እርስ በርሳችን ሰላምታ ተለዋወጥን በዚች በረሀ ሌላ ገዳማዊ አለን ብዬ ጠየቅሁት አዎን አለኝ ። ሁለተኛም ስምህ ማነው አባቴ ሆይ በዚችስ በረሀ ውስጥ ምን ያህል ጊዜ ኖርክ አልሁት ስሜ ስምዖን ነው በዚች በረሀ የኖርኩትም ሰባ ዓመታት ነው አለኝ።

ከእርሱ ዘንድም ወጥቼ ሦስት ቀን ተጓዝኩ ሁለተኛም ስሙ ባሞን የሚባል ገዳማዊ አገኘሁ ሰላምታም ሰጠሁትና በዚች በረሀ ሌላ ገዳማዊ አለን አልሁት አዎን አለ አለኝ ። አራት ቀንም ተጓዝኩ ወደ አባ ኪሮስ በዓት ደረስኩ ቅዱስ አባት ሆይ ባርከኝ እያልኩ ደጁን አንኳኳሁ አባ ባውማ ሆይ መምጣትህ መልካም ነው ብሎ ከውስጥ ተናገረኝ ። #እግዚአብሔር ያከበረህ ሰው በሰላም በፍቅር ወደእኔ ግባ አለኝ ያን ጊዜ ገብቼ ከእርሱ ተባረክሁ በፊቱም የ #እግዚአብሔርን ጸጋ ክብር አየሁ የራሱ ጠጉርና ጽሕሙ እንደ በረድ የነጣ ነበር ።

ከዚህም በኋላ ተቀመጥሁ በብብቻውም አቀፈኝ እንዲህም አለኝ እነሆ ይችን ሰዓት እየጠበቅኋት በዚች በዓት ሃምሳ ሰባት ዓመት ኖርኩ ይህንንም ሲል ጥቂት ታመመና ተኛ እየደነገጠ ያቺን ሌሊት አደረ ሲነጋም በበዓቱ ውስጥ ታላቅ ብርሃን በራ ብርሃናዊ ሰውም ገባ በእጁም የብርሃን #መስቀል አለ በአባ ኪሮስ አጠገብም ተቀምጦ ሳመዉ ባረከውም አጽናናው ሰላምን ፍቅርን አንድነትን አደረገለት ከእርሱም ተሠወረ እኔም ፈራሁ እንዲህ የሚበራ ይህን ክብር የተጐናጸፈ ይህ ማነው አልሁት ።

እርሱም ልጄ ሆይ ይህ የ #እግዚአብሔር ልጅ #ጌታ_ኢየሱስ_ክርስቶስ ነው ልማዱ ስለ ሆነ ሁልጊዜ ይመጣል ያጽናናኛልም አለኝ ። በቀዳሚት ሰንበት ዕለትም ዘጠኝ ሰዓት በሆነ ጊዜ እስከ ሰማይ የሚደርስ ታላቅ ጩኸትን ሰማሁ ከጩኸታቸውም ኃይል የተነሣ ምድር ተናወጸች። እኔም ይህ የምሰማው ጩኸት ምንድነው ብዬ ጠየቅሁት እርሱም ልጄ ሆይ ይህ በሲኦል የሚኖሩ የኃጥአን ጩኸት ነው ስለ ቅድስት ትንሣኤው የእሑድ ፀሐይ እስክትጠልቅ ድረስ #እግዚአብሔር ያሳርፋቸዋልና ስለዚህም #እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል አለኝ ።

ሐምሌ ሰባት ቀን ቅዱስ አባ ኪሮስ ጩኾ አለቀሰ ዛሬ በግብጽ አገር ታላቅ ምሰሶ ወደቀ ይኸውም የገዳማውያን አለቃ ቅዱስ አባ ሲኖዳ ነው አለ ።

ከዚህም በኋላ ከደዌው ጽናት የተነሣ እሑድ ሌሊት እጅግ ደነገጠ በበዓቱም ውስጥ እነሆ ታላቅ ብርሃን በራ ክብር ይግባውና #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስም ገብቶ በአባ ኪሮስ ራስ አጠገብ ተቀመጠ ። አባ ኪሮስም #መድኃኒታችንን_ጌታዬ_ሆይ ይህን ሰው ባርከው አለው #መድኃኒታችንም የመረጥሁህ አባ ባውማ ሆይ ጽና አትፍራም ሰላሜ በረከቴም ከአንተ ጋራ ይኑር ። አሁንም ታማኝ አገልጋዬ የሆነ የዚህን የቅዱስ ኪሮስን ያየኸውንና የሰማኸውን ወደፊትም ዳግመኛ የምታየውንና የምትሰማውን ገድሉን ጻፍ አለኝ ።

ከዚህም በኋላ #መድኃኒታችን አባ ኪሮስን እንዲህ አለው እነሆ አንተ ትሞታለህና አትዘን ሞትህ ሞት አይደለም የዘላለም ሕይወት ነው እንጂ ። የገድልህን መጽሐፍ የሚጽፈውን ወይም የሚያነበውን የሚሰማውንም ሁሉ በምድርም መታሰቢያህን የሚያደርገውን ሁሉ በደብረ ጽዮን በሚደረገው የሽህ ዓመት በዓል ምሳ ከእኔ ጋር ይቀመጥ ዘንድ አደርገዋለሁ ከቅዱሳኖቼም ጋራ እቆጥረዋለሁ ። የኃጢአቱንም መጽሐፍ ቀድጄ ስሙን በሕይወት መጽሐፍ እጽፋለሁ ። ለመሥዋዕት የሚገባውንም ዕጣኑንና ወይኑን መብራቱንም መባ አድርጎ ለሚሰጥም በስምህም ለድኆችና ለችግረኞች ምጽዋትን ለሚያደርግ ዓይን ያላየውን ጆሮም ያልሰማውን በሰው ልቡናም ያልታሰበውን በጎ ዋጋ እኔ እጥፍ ድርብ አድርጌ እሰጠዋለሁ ። በበኵር ቤተ ክርስቲያንም ቅዱሴ ሥጋዬንና ክቡር ደሜን አቀብላቸዋለሁ በዚህም ዓለም ቤታቸውን እባርካለሁ ። ልጆቻቸውን አሳድጋለሁ ከበጎ ነገር ሁሉ ምንም ምን አያጡም ።

አሁንም ከዚህ ዓለም ድካም ወደ ዕረፍት የዘላለም ተድላ ደስታ ወዳለበት ወደ ብርሃን ቦታ እወስድህ ዘንድ ጊዜው ደረሰ #መድኃኒታችንም ይህን ሲናገር እነሆ ነቢዩና ዘማሪው ዳዊት መጣ መሰንቆውም ከእርሱ ጋራ ነበረች። ይቺ ዕለት በእርሷ ፈጽሞ ሐሤት እናደርግ ዘንድ #እግዚአብሔር የሠራት ናት እያለ አመሰገነባት።

#መድኃኒታችንም አባ ኪሮስን እነሆ ዘማሪው ዳዊት መጥቷልና ይዘምርልህ ዘንድ የምትሻውን ንገር አለው። ዳዊትም ቅዱስ አባ ኪሮስን በየትኛው አውታር እንድዘምርልህ ትሻለህ ደግሞስ በየትኛው ዜማ በየትኛው ስልት በመጀመሪያው ነውን ወይስ በሁለተኛው ወይስ በሦስተኛው አለው። ቅዱስ አባ ኪሮስም በዐሥሩም አውታር በየስልታቸውና በየዜማቸው ልሰማ እሻለሁ አለ። ያን ጊዜ ቅዱስ ዳዊት መሰንቆውን አዘጋጅቶ የጻድቅ ሞቱ በ #እግዚአብሔር ፊት የከበረ ነው አለ ዳግመኛም ጐለመስሁ አረጀሁም የሚወድቅ ጻድቅን አላየሁም አለ ። ዳዊትም ድምፁን አሣምሮ ዘመረ መሰንቆውንም በስልት መታት ። ያን ጊዜም የቅዱስ አባ ኪሮስ ነፍሱ ወጣች #መድኃኒታችንም ተቀብሎ ሳማት ለመላእክት አለቃ ለቅዱስ ሚካኤልም ሰጣት ።

እኔ አባ ባውማም የቅዱስ አባ ኪሮስን ሥጋውን ቀበርኩ ከበዓቱም በወጣሁ ጊዜ በረሀው በሰማይ ሠራዊት ተመልቶ አየሁ #መድኃኒታችንም የቅዱስ አባ ኪሮስ ሥጋው ባለበት በዓት ላይ #መስቀሉን አኑሮ ዘጋት ። ከዚህም በኋላ #መድኃኒታችን ለኔ ሰላምታ ሰጥቶኝ መላእክትና የመላእክት አለቆች በፊቱ እያመሰገኑና እየዘመሩ በታላቅ ክብር ዐረገ ። የቅዱስ አባ ኪሮስን ነፍስ ከ #መድኃኒታችን ጋራ እንደዚህ አሳረጓት ። እርሷም በተሰጣት ክብር ደስ እያላት ዐረገች ።

እኔም አባ ባውማ በዚያ ቦታ ብቻዬን ቀረሁ ተመልሼም ወደ አባ አሞን በዓት ደረስሁ ። ከዚያም የሦስት ቀን መንገድ ተጉዤ ወደ አባ ስምዖን በዓት ደረስሁ ። ከዚያም ሦስት ቀን ተጉዤ ወደ ቦታዬ ወደ አስቄጥስ ገዳም ደረስኩ። ለመነኰሳቱም ሁሉ ያየሁትንና የሰማሁትን ሁሉ የቅዱስ አባ ኪሮስን ገድሉን ስለ አባ ሲኖዳም ዕረፍት ትንቢት እንደ ተናገረ ነገርኋቸው።

መነኰሳቱም ሰምተው እጅግ አደነቁ የተመሰገነ እግዚአብሔርንም አመሰገኑት ። እኔ አባ ባውማም የቅዱስ አባ ኪሮስን ገድሉን ጽፌ ለሚያነበውና ለሚሰማው ሁሉ መጽናኛ ይሆን ዘንድ ወደ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉና ወደ ገዳማትም ላክሁ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ አቡነ ኪሮስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_በርባራና_ቅድስት_ዮልያና
በዚችም ቀን የከበሩ ሴቶች በርባራና ዮልያና በሰማዕትነት አረፉ ። ይችም ቅድስት በርባራ በከሀዲው መክስምያኖስ ዘመነ መንግሥት በቤተ መንግሥት ውስጥ ታላቅ መስፍን ለሆነ ሰው ልጁ ናት ስሙም ዲዮስቆሮስ ነው እርሱም ለልጁ ለበርባራ ማንም እንዳያያት ታላቅ ጽኑ የሆነ ሕንፃ አሠራ ከዚህም ዳግመኛ መታጠቢያ የውሽባ ቤት በግንብ ሠራ የሚከፈቱ ሁለት መስኮቶችንም በውስጡ እንዲሠሩ አዘዘ ። ቅድስት በርባራም ሁለቱን መስኮቶች በአየች ጊዜ ሦስተኛ መስኮትን እንዲሠሩ ሐናፂዎችን አዘዘቻቸው ከዚህም በኋላ ክብር ይግባውና የ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስን አዳኝ የሆነ የ #መስቀሉን ምልክት በውኃ መታጠቢያው ላይ አሠራች ።

አባቷም ወደዚህ ሕንፃ በገባ ጊዜ ይህን ልጁ ያሠራችውን አይቶ አናፂዎችን ጠየቀ እነርሱም ይህን እንድንሠራ ልጅህ አዘዘችን አሉት እርሷንም ጠርቶ ለምን እንዲህ አደረግሽ አላት። እርሷም አባቴ ሆይ አስተውል ልዩ ሦስት በሆነ በ #ሥላሴ ስም ሥራ ሁሉ ይፈጸማልና ስለዚህ ሦስተኛ መስኮት አሠራሁ ይህም #መስቀል ዓለሙ ሁሉ በእርሱ በዳነበት በ #መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ #መስቀል አምሳል ነው አንተም አባቴ ሆይ ከስሕተትህ ተመልሰህ የፈጠረህን አምላክ አምልከው አለችው ።

አባቷም ከእርሷ ይህን በሰማ ጊዜ ሰይፉን መዝዞ በኋላዋ ሮጠ እርሷም ሸሸች በፊቷም የነበረች ዐለት ተሠንጥቃ በውስጧ ገብታ ሠወረቻት ። ከዚህም በኋላ ወደ አባቷ ተመለሰች እርሱም እንዲአሠቃያት ለሌላ መኰንን አሳልፎ ሰጣት እርሱም ታላቅ ሥቃይን አሠቃያት በዚያም ዮልያና የምትባል ሴት ነበረች ቅድስት በርባራንም አየቻትና የምታጽናናትና የምታረጋጋት ሆነች ክብር ይግባውና #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስም ለቅድስት በርባራ ተገለጸላትና አረጋጋት።

ከዚህም በኋላ አባቷ በሰይፍ ራሷን እንዲቆርጡ የባልንጀራዋ የዮልያናንም ራስ እንዲቆርጡ አዘዘና ቆረጧቸው የሰማዕትነት አክሊልንም ተቀበሉ ። በዚያንም ጊዜ ከሰማይ እሳት ወርዶ አባቷንና ጓደኛው የሆነ መኰንን መርትያኖስን አቃጠላቸው ያም በውሽባ ቤት ውስጥ በ #መስቀል ምልክት ያሠራቸው መታጠቢያ ለታመመ ሁሉ ከእርሱ በታጠበ ጊዜ የሚያድን በውስጡ ታላቅ ፈውስ ያለበት ሆነ ።

ከዚህም በኋላ የቅዱሳት ሰማዕታትን ሥጋቸውን ወስደው ከከተማ ውጭ ባለች ቤተ ክርስቲያን ስሟ ገላልያ በሚባል ቦታ አኖሩአቸው ይህ ሥጋቸውም በቅዱሳን ሰማዕታት በአቡቂርና በዮሐንስ በምስር አገር በአለ ቤተ ክርስቲያናቸው እስከ ዛሬ አለ ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን አንእስት ሰማዕታት ጸሎት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አባት_አባ_ያሮክላ

በዚህች ቀን የእስክንድርያ አገር ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ አባት አባ ያሮክላ አረፈ እርሱም ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ዐሥራ ሦስተኛ ቊጥር ነው ። የዚህም ቅዱስ ወላጆቹ አስቀድሞ አረማውያን ነበሩ በወለዱትም ጊዜ የአረማውያንን ትምህርት መጻሕፍቶቻቸውንም ሁሉ አስተማሩት ።

ከዚህም በኋላ አምነው ተጠመቁ ይህን ልጃቸውንም የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት አስተማሩት የሐዋርያትንም መጻሕፍት አጠና ሊቀ ጳጳሳት ድሜጥሮስም ዲቁና ሾመው ከዚህም በኋላ በእስክንድርያ አገር ቤተ ክርስቲያን ቅስና ሾመው መንጋውንም በመልካም አጠባበቅ ጠበቀ ።

ሥራውንም ፈጸመ የቤተ ክርስቲያንንም ሕግ ጠንቅቆ አወቀ። አባት ድሜጥሮስም በአረፈ ጊዜ ይህን አባት መርጠው በእስክንድርያ አገር ላይ ሊቀ ጵጵስና ሾሙት እርሱም ክብር ይግባውና የ #ክርስቶስን መንጋዎች በቀናች ሃይማኖት አጽንቶ ጠበቀ ከአረማውያንም ብዙዎችን ክብር ይግባውና #ክርስቶስን ወደ ማመን መልሶ የክርስትና ጥምቀትን አጠመቃቸው ።

ለቅዱስ ዲዮናስዮስም ለምእመናን እንዲፈርድ ሥልጣን ሰጠው እርሱ ግን ዓላው ያንን ወደ ቀናች ሃይማኖት እስከሚመልሳቸው ድረስ ያስተምራቸውና ይገሥጻቸው ነበር ። በወንጌላዊ ማርቆስ ወንበርም ዐሥራ ሦስት ዓመት ኑሮ በሰላም አረፈ ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ ቅዱስ አባት ጸሎት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አባ_ሳሙኤል_ዘደብረ_ቀልሞን

በዚችም ቀን ቅዱስ አባት የደብረ ቀልሞን አባ ሳሙኤል አረፈ ይህም ቅዱስ ለግብጽ ደቡብ ከሆነ መጺል ከሚባል አገር ደክሉባ ከሚባል መንደር ነው ። ወላጆቹም ቅዱሳንና ንጹሐን ናቸው ያለ እርሱም ልጅ አልነበራቸውም አባቱም ቄስ ነበር ። በሌሊት በራእይ ፊቱ ብሩህ የሆነ ሰው አየ ። ይህ ልጅህ ለብዙ ሰዎች የታመነ ቸር መምህር ይሆን ዘንድ አለው በዘመኑም ሁሉ ለ #እግዚአብሔር የተመረጠ ይሆናል አለው ።

አባ ሳሙኤልም ከታናሽነቱ ጀምሮ እንደ ነቢዩ ሳሙኤል ንጹሕ ነው ሁልጊዜም የምንኲስና ልብስን ይለብስ ዘንድ ያስብ ነበር ። በአንዲትም ቀን ወደ አስቄጥስ ገዳም ይሔድ ዘንድ ምክንያት አግኝቶ ከአባቱ ዘንድ ወጣ ግን መንገዱን አያውቅም ነበር ። የ #እግዚአብሔርም መልአክ በመነኵሴ አምሳል ሁኖ እየመራው አብሮት ተጓዘ በአደረሰውም ጊዜ በበዓት ውስጥ ለሚኖር ለአንድ ስሙ አባ አጋቶን ለሚባል ሽማግሌ መነኰስ ሰጠው እርሱ እጅግ ጻድቅ ሰው ነውና ። ይህም መልአክ ስለ አባ ሳሙኤል ለአባ አጋቶን እንዲህ ብሎ ነገረው ሳሙኤልን ደስ ብሎህ ተቀበለው የምንኲስናንም ልብስ አልብሰው እርሱ የሽምግልናህን ድካም የሚያጽናና ዕውነተኛ ልጅን ይሆንሃልና አንተም የምንኲስናን ሕግ ሁሉ አስተምረው ይህንንም ከተናገረው በኋላ መልአኩ ከእርሱ ተሠወረ ።

ሳሙኤልም በደረሰ ጊዜ አባ አጋቶን በደስታ ተቀበለው እንዲህም አለው የ #እግዚአብሔር አገልጋይ ሳሙኤል ሆይ መምጣትህ መልካም ነው በሽምግልናዬ ጊዜ ጌታ ወደእኔ ልኮሃልና አለው ወዲያውኑ ወደ ቤተ ክርስቲያን አስገባውና ከፀጉር በተሠራው ቀሚስና በቆቡ ላይ በቅናትና በአስኬማ ላይ ጸለየና ባረከው የአባቶቼ የአባ እንጦንዮስና የአባ መቃርዮስ ፈጣሪ ከአንተ ጋር ይኑር ልጄ ሳሙኤል ሆይ በችግርህ ሁሉ ረዳት ይሁንህ ብሎ እኒያን የምንኲስና ልብሶችን አለበሰው ።
ቅዱስ አጋቶንም ለአባ ሳሙኤል ትሕትናን አርምሞን አስተማረው አባ ሳሙኤልም ቅዱስና ቡሩክ የሆንክ አባቴ ሆይ ይቅር በለኝ ከእኔ ጋርም ፍቅርን አድርግ አስተምረኝም #እግዚአብሔርም የሚወደውን የምሠራ ያደርገኝ ዘንድ በከበረች ጸሎትህ አስበኝ ይለው ነበር ሁልጊዜ መንፈሳዊ የሆነ የምንኲስናን ሥርዓትም ሁሉ ተማረ ። ቅዱስ አባ ሳሙኤልም በሥራው ሁሉ ይራዳው ነበረ የሚያዝዘውንም ሁሉ እየሠራ ከአባ አጋቶን ጋር ሦስት ዓመት ኖረ ከዚህም በኋላ አባ አጋቶን አረፈ ።

አባ ሳሙኤልም ሰባት ሰባት ቀን እየጾመና ታላቅ ተጋድሎን እየታገለ ኖረ ከዚህም በኋላ በአስቄጠስ በአለች በከበረች በአባ መቃርስ ቤተ ክርስቲያን ቅስና ተሾመ ።

ከጥቂት ቀኖች በኋላም የልዮንን ደብዳቤ ወደ አስቄጥስ ገዳም አምጥተው አነበቧት አረጋውያን መነኰሳትም በሰሙ ጊዜ እጅግ አዘኑ አባ ሳሙኤል መንፈሳዊ ቅናትን ቀና ከሰዎችም መካከል ተነሥቶ ያቺን ደብዳቤ ነጥቆ ቀደዳት እንዲህም አለ የቀናች የአባቶቻችንን ሃይማኖት የሚለውጥ ሁሉ የተወገዘ ነው ።
የንጉሥ መልክተኛም በአየ ጊዜ ቁጣን ተመላ አባ ሳሙኤልንም በብረት ዘንጎች እንዲደበዱቡት በክንዱም ሰቅለው ፊቱን እንዲጸፉት አዘዘ በጸፉትም ጊዜ አንዲት ዐይኑ ወለቀች ከዚህም በኋላ ከአስቄጥስ ገዳም እንዲአሳድዱት ሁለተኛ አዘዘ ።

#እግዚአብሔርም የታዘዘ መልአክ ለአባ ሳሙኤል ተገለጸለትና ወደ ቀልሞን ተራራ ሒዶ በዚያ ይኖር ዘንድ አዘዘው ወዲያውኑ ሒዶ በዚያ ኖረ የቀናች ሃይማኖትንም ለሰዎች ሁሉ እያስተማረ ተቀመጠ ። ሊቀ ጳጳሳት የሆነው መለካዊ የእስክንድርያ መኰንን ምቆዝዝም ዜናውን ሰምቶ ወደ ቅዱስ አባ ሳሙኤል መጥቶ ታላቅ ግርፋትንም ገርፎ ከገዳሙ አሳደደው ።

ወደ ቀልሞን ገዳም ቤተክርስቲያንም ሒዶ በዚያ ተቀመጠ በዚያም ወራት የበርበር አረማውያን ወደዚያ መጡ ወደ አገራቸውም ሊወስዱት አባ ሳሙኤልን ያዙት ከእርሳቸውም እጅ ያድነው ዘንድ ክብር ይግባውና #ጌታችንን_ኢየሱስ_ክርስቶስን ለመነው በአንድ ግመል ላይም በጫኑት ጊዜ ያ ግመል መንቀሳቀስ አልቻለም ታላቅ ድብደባም ደበደቡት በተሳናቸውም ጊዜ ትተውት ሔዱ እርሱም ወደ ቀልሞን ገዳሙ ተመልሶ በምንኲስና ሥርዓት በመጠመድ በሁሉ ተጋድሎ እየተጋደለ ኖረ ።

ከዚህም በኋላ የበርበር አረማውያን ዳግመኛ መጡ ከእርሳቸውም የተነሣ ፈራ ሳሙኤል ሆይ አትፍራ ግን ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብተህ ዝም በል ከእርሳቸው ጋር አትናገር እኔም አንዳያዩህ አደርጋቸዋለሁ የሚልን ቃል ሰማ በዚያንም ጊዜ የተመዘዙ ሰይፎቻቸውን ይዘው ወደ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ገቡ እነርሱም እጅግ በሚያስፈራ ድምፃቸው ይጮኹ ነበር ቅዱስ ሳሚኤልም በቤተ መቅደስ ውስጥ ኃጢአትን ሲሠሩ ተመለከተ ስለ ድፍረታቸውም ዝም ማለት አልተቻለውም ተናገራቸው እንጂ #እግዚአብሔርን መፍራት የሌላችሁ እናንተ ከሀድያን #እግዚአብሔር እንደ ክፉ ሥራችሁ ይክፈላችሁ አላቸው ።

እነዚያ አረማውያንም አንተ ከዚህ ነበርክን እኛ ግን አላየንህም አሉት ከዚህም በኋላ ይዘው ከቤተ ክርስቲያኑ ምሰሶ ጋር አሠሩት ለመሞት እስቲቀርብም ገረፉት ከማሠሪያውም ሲፈቱት በግምባሩ ተደፋ ግመሎች እስካሉበትም ቦታ ጉተቱት ራሱንም በጫማ መቱት ከድብደባ ብዛት የተነሣ መንቀሳቀስ አልተቻለውም በግመልም ጫኑት ከሕመሙም ጽናት የተነሣ መሪር ልቅሶን የሚያለቅስ ሆነ ያም ግመል ወደርሱ ተመልሶ በሰው ቋንቋ እንዲህ ብሎ ተናገረው መደብደብህን መልካም አደረጉ ዝም በል አትናገር ያለህን የፈጣሪህን የ #እግዚአብሔርን ትእዛዝ ስለ ተላለፍክ ሞት ይገባሃልና አለው አባ ሳሙኤልም ሲሰማ በእውነት በድያለሁ ነገር ግን #እግዚአብሔር ቻይ ነውና መተላለፌን ይቅር ይበለኝ አለ ።

ከዚህም በኋላ ወደ አገራቸው ወሰዱት በዚያም የአስቄጥስ ገዳም አበ ምኔት የሆነውን ከእርሱ አስቀድሞ የማረኩትን አባ ዮሐንስን አገኘውና እርስበርሳቸው ተጽናኑ ። የአባ ሳሙኤልም ጌታው ፀሐይን እንዲአመልክ ያስገድደው ነበር እርሱ ግን ከቶ አልሰማውም ከዚህም በኋላ ከአንዲት ብላቴና ጋር በሰይጣን ምክር እግሩን አቆራኝቶ ግመሎችን እንዲጠብቁ ወደጫካ ሰደዳቸው ቅዱስ ሳሙኤል ከእርሷ ጋር በኃጢአት እንደ ሚወድቅና ዲያብሎስ በአስተማረውና በመከረው ሁሉ እንደሚታዘዝለት አስቧልና ።

በዚህም ሁሉ ቅዱስ ሳሙኤል ኃይልና ብርታት የሚጨመርለት ሁኖ ጌታው ታሞ ለሞት እስከ ቀረበ ድረስ በዚያ ኖረ ። አባ ሳሙኤልም በላዩ ጸለየና ከደዌው ፈወሰው ዜናውም በሀገሩ ሁሉ ተሰምቶ ደዌ ያለባቸው ሁሉ ወደርሱ የሚመጡ ሆኑ እርሱም በዘይቱ ላይ ጸልዮ ሲቀባቸው ወዲያውኑ ይድናሉ ጌታውም ይህን አይቶ እጅግ አደነቀ በአንተ ላይ ያደረግሁትን በደሌን ሁሉ ይቅር በለኝ ብሎ ሰገደለት እጅግም ወደደው አከበረውም የምትሻውንም ጠይቀኝ አደርግልሃለሁ አለው ። አባ ሳሙኤልም ወደ ሀገሬ እመለስ ዘንድ እሻለሁ አለው ጌታውም እጅ መንሻ ብዙ ገንዘብንና ግመሎችን አዘጋጅቶ በፍቅር በሰላም ሸኘው ።

ልጆቹ መነኰሳትም ወደርሱ ተሰበሰቡ አእላፋትም እስከሆኑ ድረስ እጅግ በዙ ቅድስት ድንግል እመቤታችን #ማርያምም ተገልጻለት ይህ ቦታ ለዘላለም ማደሪያዬ ይሆናል አለችው ። ከዚያቺም ዕለት ወዲህ ወደዚህ ገዳም አረማውያን ተመልሰው አልመጡም ። ይህ አባት ሳሙኤልም ብዙ ድርሳናትን ደረሰ ስለ እስላሞችም መምጣት መንግሥትንም ስለመያዛቸው የክርስቲያን ወገኖችንም በቦታው ሁሉ እንደሚአሠቃዩአቸው ትንቢት ተናገረ እነርሱም የአጋር ልጆች ናቸው ።

ዕረፍቱም በቀረበ ጊዜ መነኰሳት ልጆቹን ሰበሰባቸውና በ #እግዚአብሔር ሕግ ጸንተው እንዲኖሩ እስከ መጨረሻዪቱም ሕቅታ ድረስ ስለ ቀናች ሃይማኖት እንዲጋደሉ አዘዛቸው ። ከዚህም በኋላ ጥቂት ታሞ በሰላም አረፈ ።

ስለርሱም እንዲህ ተባለ አንድ ቀን ከልጆቹ ውስጥ አንዱ አረፈ አባ ሳሙኤልም ወደርሱ በመጣ ጊዜ ነፍሱ ተመልሳለት በመነኰሳቱ ፊት ተነሣ የኃጥአንን ሥቃይ የጻድቃንንም ተድላ ደስታቸውን እንዳየ ተናግሮ ተመልሶ አረፈ ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ አባት ሳሙኤል ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አማን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱሳን_አባ_ኤሲና_እኅቱ_ቴክላ

በዚችም ቀን ለእስሙናይን በስተምዕራብ ካለ አውራጃ ብጺር ከሚባል መንደር ቅዱሳን አባ ኤሲና እኅቱ ቴክላ በሰማዕትነት አረፉ ። ይህም አባ ኤሲ እጅግ ብዙ ገንዘብ ቦታዎችና በጎችም አሉት የበጎቹንም ጠጉር ሽያጭ ለድኆችና ለችግረኞች ምጽዋት አድርጎ ይሰጥ ነበር እርሱ #እግዚአብሔርን እጅግ ይፈራ ነበርና እህቱ ቴክላም እንደርሱ #እግዚአብሔርን የምትፈራ ናት።

የአባታቸውም ስም ኤልያስ የእናታቸውም ማርያም ይባላል እነርሱም ልጃቸውን ኤሲን የተወደድክ ልጃችን ሆይ በሕይወታችን ሳለን ልናጋባህና በአንተ ደስ እንዲለን እንወዳለን ብለው ለመኑት እርሱ ግን ይህን አልወደደም እንዲህም አላችው የተባረካችሁ አባቴና እናቴ ሆይ ጸልዩልኝ የምታዝዙኝም ሁሉ በደስታ እቀበላለሁ ስለጋብቻ ግን አትናገሩኝ አላደርገውምና ከዚያንም ጊዜ ወዲህ ስለ ጋብቻ ከቶ አልተናገሩትም እጅግ ይወዱት ነበርና ።

ከዚህም በኋላ ዕድሜው ሃያ ዓመት ሲሆነው አባቱ ሞተ ከጥቂት ቀኖችም በኋላ እናቱ ሞተች ከሀዲ ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስም በዚያ ወራት ሰው ሁሉ ጣዖት እንዲሰግድ አዘዘ ቅዱስ ኤሲም የንግድ ዕቃውን ይሸጥ ዘንድ ወደ እስክንድርያ ሔደ ።

ለአባ ኤሲም በእስክንድርያ አገር ጳውሎስ የሚባል ወዳጅ አለው እርሱም ጽኑ በሆነ ደዌ ታሞ ነበር ከደዌውም እስከሚድን አባ ኤሲ በርሱ ዘንድ ተቀመጠ በዚያም ወራት በክርስቲያን ወገኖች ላይ ታላቅ መከራ ሁኖ ነበር ። እኒህ የከበሩ ኤሲና ወዳጁ ጳውሎስ ጣፋጭና መልካም የሆነውን መብል በገንዘባቸው እየገዙ በእስክንድርያ አገር ለሚኖሩ ቅዱሳን ይወስዳሉ እንዲሁም ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ስም የታሠሩትን ይጎበኙዋቸዋል ያረጋጓቸዋልም እንደ ባሮችም ያገለግሏቸው ነበር እኒህ ቅዱሳንም የሰማዕትነት አክሊልን እናንተ ትቀበሉ ዘንድ አላችሁ ብለው በእነርሱ ላይ ትንቢት ተናገሩ ።

በዚህም ወራት የህርማኖስ ልጅ ቅዱስ ፊቅጦርን ወደ እስክንድርያ አገር አመጡት አባ ኤሲና ወዳጁ ጳውሎስም በአዩት ጊዜ አደነቁ መንፈሳዊ ቅንአትንም ቀኑበት እርሱ የዚህን የኃላፊውን ዓለም መንግሥት ንቋልና ። ከዚህም በኋላ አባ ኤሲ ወደ መኰንኑ ቀርቦ በክብር ባለቤት በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ታመነ መኰንኑም ያሠቃዩት ዘንድ አዘዘ በአለንጋዎችም ብዙ ግርፋትን ገረፉት ሕዋሳቱንም በሾተሎች ሠንጣጠቁ በሥጋውም የችቦ መብራቶችን አደረጉ በሰንሰለትም አሠሩት ሁለተኛም ነበልባሉ እጅግ ከፍ ከፍ
እስከሚል በማንደጃ ውስጥ እሳትን አነደዱ ። አባ ኤሲንም ከውስጡ ጣሉት እርሱም እንዲህ ብሎ ጸለየ ጌትነት ገንዘብህ የሆነ #ጌታዬ_ኢየሱስ_ክርስቶስ_ሆይ ሠለስቱ ደቂቅን ከነደደ እሳት ዳንኤልን ከአንበሶች አፍ ምስክርህ ፊቅጦርንም ከውሽባ ቤት እሳት ያዳንካቸው አንተ ነህና እንደ እነርሱ አድነኝ የሚረዳኝንም ቸር መልአክ ላክልኝ ለአንተም ምስጋና ይሁን አሜን ።

ይህንንም ጸሎት በጸለየ ጊዜ እነሆ ቅዱስ ሱርያል መልአክ ከሰማይ ወርዶ በአባ ኤሲ ቀኝ ቆመና ጻድቅ ሰው ሆይ ሰላም ላንተ ይሁን #እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነውና ከመከራህም ሁሉ እርሱ ያድንሃልና አትፍራ አለው ።

በዚያንም ጊዜ የእሳቱ ማንደጃ እንደ ቀዝቃዛ ጠል ሆነ መልአኩም የእቶኑን ግድግዳ ሠንጥቆ የከበረ አባ ኤሲን እጁን ይዞ ያለ ጥፋት በጤና አወጣው በዚያንም ጊዜ አባ ኤሲ ወደ መኰንኑ ሒዶ እንዲህ ብሎ ጮኸ አንተ ከከሀዲ ንጉሥህና ከረከሱ ጣዖቶችህ ጋር እፈር ። ሕዝቡም ሕያው ሁኖ ያለ ጉዳት አባ ኤሲን በአዩት ጊዜ እጅግ አደነቁ በአንድ ቃልም እኛ በግልጥ ክርስቲያን ነን በቅዱስ አባ ኤሲ አምላክ እናምናለን ብለው ጮኹ መኰንኑም ራሶቻቸውን በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘ በመንግሥተ ሰማያትም የሰማዕትነት አክልሊን ተቀበሉ ።

ከዚህም በኋላ አባ ኤሲን ወደ እሥር ቤት እንዲወስዱት መኰንኑ አዘዘ እንዳዘዛቸውም አደረጉ ። ለእህቱም ለቴክላ የ #እግዚአብሔር መልአክ ተገልጾላት ወንድሟን አባ ኤሲን ትጎበኘው ዘንድ ወደ እስክንድርያ አገር እንድትሔድ አዘዛት ያን ጊዜ ከእንዴናው ከተማ ተነሥታ ከባሕር ዳርቻ ደረሰች መንፈሳዊት መርከብም ተገለጸችላት ።

እመቤታችን ቅድስት ደንግል #ማርያምም ከመጥምቁ ዮሐንስ እናት ከኤልሳቤጥ ጋር በውስጧ አለች አዝነውም ተመለከተቻቸውና እመቤቶቼ ሆይ የደረሰባችሁ ምንድን ነው አዝናችሁ አያለሁና አለቻቸው ቅድስት ኤልሳቤጥም በእርጅናዬ ወራት የወለድኩት አንድ ልጅ ነበረኝ ወስደው አረዱብኝ አለቻት እመቤታችንም ቅድስት ድንግል #ማርያምም ለእኔም አንድ ልጅ ነበረኝ እርሱንም ወስደው ሰቅለው ገደሉብኝ አለቻት ። ቴክላም እመቤቶቼ ሆይ በእውነት ጽኑዕ ኀዘን አግኝቷችኋል አለቻቸው ይህንንም እየተነጋገሩ ወንድሟ አባ ኤሲ ወዳለበት አደረሷት የተገለጹላት እነማን እንደሆኑ አላወቀችም ነበር ።

አባ ኤሲም እኅቱ ቴክላን በአያት ጊዜ ፈጽሞ ደስ አለው እርሷም ከእርሱ ጋር በሰማዕትነት ትሞት ዘንድ ተስማማች ።

ከዚህም በኋላ የሌሊቱ እኩሌታ በሆነ ጊዜ የ #እግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ሱርያል ለአባ ኤሲ ተገለጸለት በብርሃናውያን ክንፎቹም ተሸክሞ ወደ ሰማይ አወጣው ኢየሩሳሌም ሰማያዊትንም አሳየው ። ቅዱሳንም ሁሉ ወጥተው ሰላምታ ሰጡት የሰው አንደበት ስለርሷ ሊናገር የማይቻለው ልዕልናዋንና ክብርዋን አሳየው በወርቅ በዕንቁ ያጌጡ አደባባዮቿንም ከፀሐይ ብርሃን ሰባት እጅ የሚበልጥ በውስጧ ያለውንም ብርሃን አሳየው ስለ ክብር ባለቤት #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ስም መከራ የተቀበሉ የጻድቃንንና የሰማዕታትን መኖሪያንም ዳግመኛ አሳየው ።

ከዚህም በኋላ የ #እግዚአብሔር መልአክ ወደ ሌላ ቦታ ወስደውና ታላቅ አዳራሽንም አሳየው በውስጡም በወርቅ በዕንቁ የተሸለሙ ሦስት መቶ ምሰሶዎች አሉ ዙፋኖችም በዕንቁ የተሸለሙ አሉ በዚያም አዳራሽ ውስጥ ሁለት መቶ ጭፍሮች ቁመው ነበር ። እነርሱም በወርቅ ዝናር የታጠቁና ያጌጡ ናቸው ከእርሳቸውም እያንዳንዱ ርዝመቱ ዐሥራ አምስት ዐሥራ አምስት ክንድ ይሆናል እኔም ኤሲ ያንን መልአክ ከዓለም ሰዎች ውስጥ በዚህ አዳራሽ አምሳል ማንም ሊሠራ የማይቻለው ይህ አዳራሽ ለማን ነው አልሁት።

መልአኩም እንዲህ አለኝ ወንድሜ አባ ኤሲ ሆይ የምድር ነገሥታት ሁሉም ከዓለሙ ሁሉ ጋር ቢሰበሰቡ ይህን አዳራሽ ከተሸከሙት ከእሊህ ከሦስት መቶ ምሰሶዎች የአንዱን ምሰሶ ሽያጭ ዋጋ አይችሉም አለኝ እኔም አይቼ አደነቅሁ #እግዚአብሔርንም አመሰገንሁት ።

ሁለተኛም ይህ የከበረና ያማረ ታላቅ አዳራሽ ለማን ይሆናል አልሁት ያ መልአክም የሠራዊት አለቃ ለነበረ ለህርማኖስ ልጅ ለሰማዕቱ ቅዱስ ፊቅጦር ይህ ሁሉ ተሰጠ ። እርሱ ምድራዊ መንግሥትን ሽልማቱንና ጌጡን ክብሩን ሁሉ ንቆ ትቶ መከራ መስቀሉን ተሸክሞ የክብር ባለቤት የሆነ #ጌታውን_ክርስቶስን ተከትሎታልና ስለዚህ ስለ ኃላፊው ምድራዊ መንግሥት ፈንታ የማይጠፋ መንግሥትን #እግዚአብሔር ሰጠው አለኝ ።

ዳግመኛም እንዲህ ብዬ ጠየቅሁት እነዚህ ዙፋኖች እነዚህም ፍሬያቸው ያማረ ዕንጨቶች እሊህም የሚያበሩ አክሊሎች ምንድን ናቸው አልሁት ። እርሱም እንዲህ አለኝ አባ ኤሲ ሆይ እሊህ የዕረፍትና የተድላ ቦታዎች የቅዱሳን ሰማዕታትን መታሰቢያቸውን በምድር ላይ ለሚያደርጉት ሰዎች #እግዚአብሔር ያዘጋጀላቸው ነው አባ ኤሲ ሆይ ስማ እኔ ላስረዳህ በሰማዕታት በስማቸው ቤተ ክርስቲያንን የሚሠራ ሰው ሁሉ ወይም ሥጋቸውን የገነዘ ወይም መሥዋዕትን የሰጠ መብራትንም ወይም የተራበ ያበላ የተራቆተም ያለበሰ ወይም ለቤተ ክርስቲያናቸው መጻሕፍትን ገዝቶ የሰጠ ወይም ገድላቸውንና ምስክርነታቸውን የጻፈ በችሎታው መጠን በመታሰቢያቸው ቀን በጎ ሥራ የሠራ ቀዝቃዛ የጽዋ ውኃ የሰጠ ዋጋውን አያጣም ብሎ ክብር ይግባውና #ጌታችን በከበረ ወንጌል እንደ ተናገረ ።

ከሰማዕታት ላንዱ ወይም ከጻድቃን መታሰቢያቸውን ሲያደርግ የነበረ ሰው በሞተ ጊዜ ያ ሰማዕት ወይም ጻድቁ መጥቶ ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ፊት ይሰግዳል #ጌታዬና_ፈጣሪዬ_ሆይ በምድር መታሰቢያየን ስታደርግ ኑራለችና ይቺን ነፍስ ስጠኝ ይላል እርሷንም ይሰጠዋል እርሱም ተቀብሎ ወደዚህ ተድላ ደስታ ወደ አለበት ቦታ ያስገባታል ።

ያቺ ነፍስ እጅግ ኃጢአተኛ ከሆነች ግን ከ #እግዚአብሔር ዘንድ ቃል ይወጣል በመላእክት አለቃ በሚካኤልም አፍ እንዲህ ተብሎ ይነገራል ሁሉን የያዘ #እግዚአብሔር ይቺን ነፍስ ለአንዲት ቅጽበት አንድ ጊዜ እንዲወረውሩዋት አዘዘ ። ከዚያም በኋላ ስለርሷ ለማለደ ለዚያ ሰማዕት ወይም ለጻድቁ ይስጡት ይላል እንደዚህም ለዚያ ሰማዕት ወይም ለጻድቁ ትሰጠዋለች እርሱም ተቀብሎ ይወስዳታል በመጠመቂያም ውስጥ ያጠምቋታል ያማሩ ልብሶችንም አልብሰው ከእነዚህ ከምታያቸው ዙፋኖች በአንዱ ዙፋን ላይ ያስቀምጧታል በማይጠፋ አክሊልም ይጋርዷታል ከቅዱሳን ሁሉ ጋር ደስ እያላት ለዘላለሙ ትኖራለች ።

ከዚህም በኋላ ያ መልአክ ተሸክሞ ወደ እሥር ቤት መለሰኝ ሰላምታም ሰጥቶኝ ወደ ሰማይ ዐረገ እኔም ስለ ከበረ ስሙ ለሚጋደሉ ስለሚሰጥ ታላቅ ሀብት እጅግ አደነቅሁ ።

በነጋም ጊዜ ቅዱስ አባ ኤሲን ከእኅቱ ቴክላ ጋር ያመጡት ዘንድ መኰንኑ አዘዘ አምጥተውም በጽኑ ሥቃይ በተሽከርካሪዎች መሣሪያ በእሳት ቃጠሎ በብረት ችንካሮች የራሳቸውንም ቆዳ በመግፈፍ አሠቃዩአቸው ። #እግዚአብሔርም ያለ ጉዳት በጤና አስነሣቸው ከሥቃያቻውም የተነሣ በሰለቸ ጊዜ ወደ ላይኛው ግብጽ ይወስዳቸው ዘንድ ለእንዴናው አገር መኰንን አሳልፎ ሰጣቸው ስምንት ቀንም ያህል እንደ ተጓዙ መርከቢቱ ከባሕሩ ዳር ቆመች መኰንኑም ራሶቻቸውን በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘ ቅዱሳን አባ ኤሲና እኅቱ ቴክላም እጅግ ደስ አላቸው ጸሎታቸውንም ጸልየው በፈጸሙ ጊዜ በሰይፍ ራሶቻቸውን ቆረጧቸው ።
እግዚአብሔርም ስንጡፍ ከሚባል አገር ስሙ ኦሪ የሚባለውን ቄስ የቅዱሳንን ሥጋቸውን እንዲአነሣ አዘዘው እርሱም አንሥቶ ወስዶ አጥኖ በአማሩ ልብሶች ገነዛቸው የመከራውም ወራት እስቲፈጸም በንጹሕ ቦታ አኖራቸው ከእርሳቸውም ታላላቅ ተአምራት ተገለጡ ከእነርሱም ጋር በሰማዕትነት የሞቱ ቁጥራቸው አራት መቶ ሰባ ሰባት ነፍስ ናቸው ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አባ_ዮሐንስ_ዘደማስቆ (ሊቁ)

በዚችም ቀን በደማስቆ የተከበረ አባት አባ ዮሐንስ አረፈ ። ይህም ቅዱስ ከደማስቆ ከከበርቴዎቿና ከታላላቆቿ ወገን መንሱር ለሚባል ሰው ልጅ ነው በጥበብና በፈሪሀ እግዚአብሔርም አደገ የቀርሊ ፈላስፋ ከሆነ ቅልህፋ ከሚባል ቁልዝማዊ መነኰስ መምህሩ ዘንድ የፍልስፍና ትምህርትን ተማረ ትምርቱንም ሲጨርስ ቁልዝማዊ መምህሩን ተሰናብቶ ወደ ከበረ ሊቅ ሳበ ሰማዕት ገዳም ሔደ ። አባቱም በሞተ ጊዜ ለአገረ ገዢው ጸሐፊ ሆነ ግን ምሥጢሩን አይሠውርም ።

በዚያንም ወራት የከሀዲው ልዮን ልጅ ቁስጠንጢኖስ ተነሥቶ በአምላክ ፈቃድ ስለተሣሉ ሥዕሎች ጸብ በማንሣት አብያተ ክርስቲያናትን አወከ ይህም አባ ዮሐንስ የቤተክርስቲያን ሹመት ሳይኖረው በቀናች ሃይማኖት እያጸናቸው በአምላክ ፈቃድ ለተሣሉ ሥዕሎችም ስግደት እንደሚገባ መስክር ከቅዱሳት መጽሕፍት እያመጣ የሚጽፍና ወደ ምእመናን ሁሉ የሚልክ ሆነ ።

ከሀዲው ቈስጠንጢኖስም በሰማ ጊዜ ጥርሱን አፋጨ በዮሐንስ ብርዕ አምሳል የሚጽፍ ጸሐፊንም ፈልጎ በዮሐንስ ብርዕ አምሳያ እንዲህ ብሎ አጻፈ ከአንተ ዘንድ ያለ ዮሐንስ ከአንተ ጋር ተዋግቼ አገርህን እማርክ ዘንድ ይህን ደብዳቤ ጽፎ ላከልኝ ብሎ በወንጀል ለደማስቆ ገዥ ላከለት በሰማ ጊዜም እውነት ስለ መሰለው የሚጽፍባት ቀኝ እጁን ቆረጠው ።

አባ ዮሐንስም የተቆረጠች እጁን ይዞ ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሥዕል ሒዶ በብዙ ዕንባ እንዲህ ብሎ ለመናት እመቤቴ ሆይ ለሥዕልሽ መስገድ ስለሚገባ በተጣለሁ ጊዜ አይደለምን ይህ መቆረጥ የደረሰብኝ አሁንም በቸርነትሽ ፈውሺኝ አንቺ በሥራው ላይ ሁሉ ችሎታ አለሽና ይህንንም ብሎ ጥቂት አንቀላፋ ። በእንቅልፉም ሳለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተገለጸችለትና እጁን እንደ ቀድሞው መለሰችለት በነቃም ጊዜ ድና አገኛት እግዚአብሔርንም አመሰገነው ቅድስት ድንግል እመቤታችን ማርያምንም አመሰገናት ።

ከዚህም በኋላ ወደ ገዳም ሒዶ መነኰሰ አበ ምኔቱም የምንኩስናን ሥርዓት ያስተምረው ዘንድ ለአንድ ሽማግሌ መንፈሳዊ አባት ሰጠው ሽማግሌውም ልጄ ዮሐንስ ሆይ አፍአዊት ከሆነች ትምርትህ ምንም ምን አታድርግ ግን ዝምታን ተማር አለው ከትሕትናውም ብዛት የተነሣ ሰይጣንን ድል ነሣው ።

ከዕለታትም በአንዲቷ ከመነኰሳቱ አንዱ ሽማግሌ ሞተ መነኰሳቱም ስለ ወንድማቸው ሙሾ እንዲአወጣለት አባ ዮሐንስን ለመኑት አባ ዮሐንስም ከሽማግሌው መምህሬ ትእዛዝ የተነሣ እኔ እፈራለሁ አላቸው ለማንም አይገለጥም አሉት ምልጃንም በአበዙበት ጊዜ ለሚሰማት ሁሉ የምታሳዝን ሙሾ ደረሰ መምህሩም አውቆ በእርሱ ላይ ተቆጣ ከበዓቱም አባረረው እርሱም አባ ዮሐንስ ወደ አረጋውያን ሁሉ ተማጠነ ሽማግሌውንም ይቅርታ እንዲአደርግ ግድ በአሉት ጊዜ የመነኰሳቱን የመፀዳጃ ቤት የጠረገ እንደሆነ እምረዋለሁ አለ አባ ዮሐንስም ሰምቶ መንፈሳዊ መምህሩ እንዳዘዘው አደረገ እርሱም ቅንነቱንና ትሩፋቱን አይቶ በደስታ ተቀብሎ ወደ ማደሪያው አስገባው ።

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም አረጋዊ መምህሩን ድርሳናትን መድረስን እንዳይከለክለው አዘዘችው ከዚህም በኋላ ብዙ ድርሳናት ደረሰ የኢየሩሳሌሙም ሊቀ ጳጳሳት ቅስና ሾመው በአምላክ ፈቃድ ስለ ተሣሉ ሥዕሎች ክብር ስለ ቀናች ሃይማኖትም ነገሥታቱንና መኳንንቱን ሲዘልፋቸው ኖረ ወደ ሽምግልናም በደረሰ ጊዜ ወደ ወደደው ክርስቶስ ሔደ ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አባ_ተክለ_አልፋ_ዘደብረ_ድማሕ

በዚህችም ቀን የደብረ ድማሕ ገዳም አበምኔት ቅዱስ አባት ተክለ አልፋ አረፈ። ዳግመኛም በክርስቶስ የሚታመን የገብረ ማርያም ዕረፍቱ ነው እርሱም የሰማዕታትንና የጻድቃንን በየዕረፍታቸው ቀን ለየአንዳንዱ ርኁባንን በማጥገብ የተራቆቱትን በማልበስ መታሰቢያቸውን የሚያደርግ ነው ።

እንዲህም ባለ ሥራ ላይ እያለ ያንጊዜ እስላሞች ወደ ሸዋ አገር መጡ እርሱም ያማሩ ልብሶችን ለብሶ ወደ ቤተክርስቲያን ሔዶ ገብቶ ጸሎትን ጸለየ ሲጸልይም እስላሞች ወደርሱ መጥተው ራሱን በሰይፍ ቆረጡት የሰማዕትነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለ ።

#ሰማዕቱ_አባ_ገብረ_ማርያም፡- ይህም ቅዱስ የሰማዕታትንና የጻድቃንን በየዕረፍታቸው ቀን ለእያንዳንዳቸው ርኁባንን በማጥገብ የተራቆቱትን በማልበስ መታሰቢያቸውን የሚያደርግ ነው፡፡ እንዲህም ባለ ሥራ ላይ እያለ ይን ጊዜ እስላሞች ወደ ሸዋ አገር መጡ፡፡ እርሱም ያማሩ የክህነት ልብሶቹን ለብሶ ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብቶ ጸሎትን ጸለየ ሲጸልይም እስላሞች ወደርሱ መጥተው ራሱን በሰይፍ ቆረጡት፡፡ የሰማዕትነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለ፡፡ ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ ቅዱስ አባት በቅዱስ ገብረ ማርያም ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የታኅሣሥ 8 ስንክሳር።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ሁሉ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን ።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ታኅሣሥ_8#ከገድላት_አንደበት እና #ዲያቆን_ዮርዳኖስ_አበበ)
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ታኅሣሥ_8_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
2ኛ ቆሮ 12
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ ትምክህት የሚያስፈልግ ነው፤ አይጠቅምም ነገር ግን ከጌታ ወዳለው ራእይና መገለጥ እመጣለሁ።
² ሰውን በክርስቶስ አውቃለሁ፥ በሥጋ እንደ ሆነ አላውቅም ወይም ከሥጋ ውጭ እንደ ሆነ አላውቅም፥ እግዚአብሔር ያውቃል፤ እንዲህ ያለው ሰው ከአሥራ አራት ዓመት በፊት እስከ ሦስተኛው ሰማይ ድረስ ተነጠቀ።
³ እንዲህ ያለውንም ሰው አውቃለሁ፥ በሥጋ እንደ ሆነ ወይም ያለ ሥጋ እንደ ሆነ አላውቅም፥ እግዚአብሔር ያውቃል፤
⁴ ወደ ገነት ተነጠቀ፥ ሰውም ሊናገር የማይገባውን የማይነገረውን ቃል ሰማ።
⁵ እንደዚህ ስላለው እመካለሁ፥ ስለ ራሴ ግን ከድካሜ በቀር አልመካም።
⁶ ልመካ ብወድስ ሞኝ አልሆንም፥ እውነትን እላለሁና፤ ነገር ግን ማንም ከሚያይ ከእኔም ከሚሰማ የምበልጥ አድርጎ እንዳይቆጥረኝ ትቼአለሁ።
⁷ ስለዚህም በመገለጥ ታላቅነት እንዳልታበይ የሥጋዬ መውጊያ፥ እርሱም የሚጎስመኝ የሰይጣን መልእክተኛ ተሰጠኝ፤ ይኸውም እንዳልታበይ ነው።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ጴጥሮስ 3
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁸ በመጨረሻው ሁላችሁ በአንድ ልብ ሁኑ፥ የሌላው መከራ ለእናንተ እንደሚሆን አድርጉ፥ እንደ ወንድሞች ተዋደዱ፥ ርኅሩኆችና ትሑታን ሁኑ፤
⁹ ክፉን በክፉ ፈንታ ወይም ስድብን በስድብ ፈንታ አትመልሱ በዚህ ፈንታ ባርኩ እንጂ፥ በረከትን ልትወርሱ ለዚህ ተጠርታችኋልና።
¹⁰ ሕይወትን ሊወድ መልካሞችንም ቀኖች ሊያይ የሚፈልግ ሰው፥ መላሱን ከክፉ ከንፈሮቹንም ተንኰልን ከመናገር ይከልክል፤
¹¹ ከክፉ ፈቀቅ ይበል፥ መልካምንም ያድርግ፥ ሰላምን ይሻ ይከተለውም፤
¹² የጌታ ዓይኖች ወደ ጻድቃን ናቸውና፥ ጆሮዎቹም ለጸሎታቸው ተከፍተዋል፥ የጌታ ፊት ግን ክፉ ነገርን በሚያደርጉ ላይ ነው።
¹³ በጎንም ለማድረግ ብትቀኑ የሚያስጨንቃችሁ ማን ነው?
¹⁴ ነገር ግን ስለ ጽድቅ እንኳ መከራን ብትቀበሉ ብፁዓን ናችሁ። ማስፈራራታቸውንም አትፍሩ አትናወጡም፥
¹⁵ ዳሩ ግን ጌታን እርሱም ክርስቶስ በልባችሁ ቀድሱት። በእናንተ ስላለ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቁአችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ሁኑ፥ ነገር ግን በየዋህነትና በፍርሃት ይሁን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 21
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ ከእነርሱም ተለይተን ተነሣን፤ በቀጥታም ሄደን ወደ ቆስ በነገውም ወደ ሩድ ከዚያም ወደ ጳጥራ መጣን፤
² ወደ ፊንቄም የሚሻገር መርከብ አግኝተን ገባንና ተነሣን።
³ ቆጵሮስንም ባየናት ጊዜ በስተ ግራችን ተውናት ወደ ሶርያም ሄደን ወደ ጢሮስ ደረስን፥ መርከቡ ሸክሙን በዚያ የሚያራግፍ ነበርና።
⁴ ደቀ መዛሙርትንም ባገኘን ጊዜ በዚያ ሰባት ቀን ተቀመጥን፤ እነርሱም ጳውሎስን ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይወጣ በመንፈስ አሉት።
⁵ ጊዜውንም በፈጸምን ጊዜ ወጥተን ሄድን፤ ሁላቸውም ከሚስቶቻቸውና ከልጆቻቸው ጋር እስከ ከተማው ውጭ ድረስ ሸኙን፥ በባሕሩም ዳር ተንበርክከን ጸለይን፤
⁶ እርስ በርሳችንም ተሰነባብተን ወደ መርከብ ወጣን፥ እነዚያም ወደ ቤታቸው ተመለሱ።
⁷ እኛም የባሕሩን መንገድ ጨርሰን ከጢሮስ ወደ አካ ደረስን፥ ለወንድሞችም ሰላምታ ሰጥተን ከእነርሱ ዘንድ አንድ ቀን ተቀመጥን።
⁸ በነገውም ወጥተን ወደ ቂሣርያ መጣን፥ ከሰባቱም አንድ በሚሆን በወንጌላዊው ፊልጶስ ቤት ገብተን በእርሱ ዘንድ ተቀመጥን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ታኅሣሥ_8_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"እስመ ኀብአኒ ውስተ ጽላሎቱ በዕለተ ምንዳቤየ። ወሠወረኒ በምኅባአ ጽላሎቱ። ወዲበ ኰኵሕ አልዐለኒ"። መዝ 26፥6-7።
"እነሆ፥ አሁን በዙሪያ ባሉ በጠላቶቼ ላይ ራሴን ከፍ ከፍ አደረገ፤ በድንኳኑም የእልልታ መሥዋዕትን ሠዋሁ፥ ለእግዚአብሔር እቀኛለሁ እዘምርለትማለሁ"። መዝ 26፥6-7።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ታኅሣሥ_8_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ማቴዎስ 11
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁶ ነገር ግን ይህን ትውልድ በምን እመስለዋለሁ? በገበያ የሚቀመጡትን ልጆች ይመስላሉ፥ እነርሱም ባልንጀሮቻቸውን እየጠሩ።
¹⁷ እንቢልታ ነፋንላችሁ ዘፈንም አልዘፈናችሁም ሙሾ አወጣንላችሁ ዋይ ዋይም አላላችሁም ይሉአቸዋል።
¹⁸ ዮሐንስ ሳይበላና ሳይጠጣ መጣ፥ እነርሱም፦ ጋኔን አለበት አሉት።
¹⁹ የሰው ልጅ እየበላና እየጠጣ መጣ፥ እነርሱም፦ እነሆ፥ በላተኛና የወይን ጠጅ ጠጭ፥ የቀራጮችና የኃጢአተኞች ወዳጅ ይሉታል። ጥበብም በልጆችዋ ጸደቀች።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️ የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #ያዕቆብ_ዘሥሩግ_ቅዳሴ ነው። መልካም የአቡነ ተክለ አልፋ የአቡነ ሳሙኤል ዘደብረ ቀለሞን፣የሊቀጳጳስ ያሮክላ፣ የቅዱስ ይሐንስ ዘደማስቆ፣የቅዱስ ገብረ ማርያም ሰማዕት የዕረፍት በዓል፣ የአቡነ እስትፋሰ ክርስቶስ፣ የአቡነ ሙሴ ዘድባ፣ የአቡነ ኪሮስ፣ የቅድስት እንባ መሪና የልደት በዓልና የነቢያት (ገና) የጾም ጊዜ። ለሁላችን ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ታኅሣሥ_9

#ቅዱስ_አባት_አባ_በአሚን

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ታኅሣሥ ዘጠኝ በዚች ቀን ያለ ደም መፍሰስ ታማኝ የሆነ ቅዱስ አባት አባ በአሚን በሰማዕትነት አረፈ።

እርሱም በደቡብ ግብጽ በእስሙናይን አውራጃ ለሀገረ ቴርሳ አቅራቢያ ከሆኑ ከሐፂብ ተወላጆች ወገን ነው። ለአንድ ባለጸጋም በጅሮንድ ሆኖ ሳለ ስለ ንጽሕናውና ስለ ቅድስናው በሁሉ ዘንድ ተወዳጅ ሆ። የባለ ጸጋውም ሚስት አባ በአሚንን እጅግ የምትወደውና የምትተማመንበት ሆነች።

እርሱ ግን የዚህን ዓለም ፍጻሜ አሰበ፤ የባለጸጋውንም አገልግሎት ትቶ ወደ ገዳም ሒዶ መነኰሰ። ባለጸጋውም መሔዱን በሰማ ጊዜ እጅግ አዘነ። ሚስቱንም ይዞ አባ በአሚን ወዳለበት በአንድነት ሔዱ። ወደ እርሳቸው እንዲመለስም ለመኑት፤ እንዲህም አሉት "ከአንተ እንለይ ዘንድ ከቶ አንችልም ስለዚህ አንተውህም" አሉት።

አባ በአሚንም "እኔ ራሴን ብፅዓት አድርጌ ለ #እግዚአብሔር ሰጥቻለሁ እኮን" አላቸው። ይህንንም ሲሰሙ ከእርሱ በመለየታቸው እያዘኑ ተትውት ተመለሱ።

ከዚህም በኋላ በአማረ ተጋድሎ ሁሉ ታላቅ ተጋድሎን በመጋደል ብዙ ዘመናት #እግዚአብሔርን አገለገለው ። ከዚህም በኋላ ክብር ይግባውና ስለ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ምስክር ሁኖ ደሙን ሊአፈስ ወዶ ወደ እንዴናው ከተማ ሔደ። ብዙዎች ምእመናንም ሲያሠቃዩአቸው አገኛቸው። እርሱም ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_በኢየሱስ_ክርስቶስ ታመነ፣ ጽኑ ሥቃይንም አሠቃዩት፣ ሥጋውን በእሳት ለበለቡ፣ ሕዋሳቱንም ሠነጣጥቀው ከመንኰራኲር ውስጥ ጨመሩት፣ ዳግመኛም በአጋሏቸው የብረት ዘንጎች አቃጠሉት። በዚህም ሁሉ ጸና ክብር ይግባውና #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስም ያለ ጉዳት በጤና ያስነሣው ነበር።

እንዲህም እየተሠቃየ ሳለ ጣዖት የሚመለክበት ወራት አለፈና ጻድቅ ቈስጠንጢኖስ ነገሠ። ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ስም ዲዮቅልጥያኖስ ያሠራቸውን እሥረኞች ሁሉ እንዲፈቷቸው አዘዘ። #ጌታችንም ለአባ በአሚን ተገለጠና ከሰማዕታት ጋር እንደቆጠረው አስረዳው።

ንጉሥ ቈስጠንጢኖስም ከእሳቸው ቡራኬ ሊቀበል ሽቶ ከውስጣቸው ሰባ ሁለት እሥረኞችን ወደርሱ ያመጡ ዘንድ አዘዘ። አባ ኖብ ከእርሳቸው ጋር በዚያ ነበረ ከእርሳቸውም አንዱ ይህ አባ በአሚን ነው። ከዚህም በኋላ ከእሥሙናይ ነበር ውጭ በሆነች ገዳም የሚኖር ሆነ። #ጌታችንም ታላቅ ጸጋን ሰጥቶት በሽተኞችን ሁሉ የሚፈውሳቸው ሆነ ዜናውም በቦታው ሁሉ ተሰማ።

በዚያም ወራት የሮም ንጉሥ ሚስት የሆነች አንዲት ንግሥት ነበረች። እርሷም ከእርሷ ጋር ስለሚኖር የወንጌላዊውን ዮሐንስ የራእዩን መጽሐፍ ሁልጊዜ የሚፈራ ስለ አንድ ዲያቆን እጅግ የታመመች ናት። ከንጉሥ ሹሞች አንዱ በቀናበት ጊዜ ወደ ንጉሡ ሒዶ "ጌታዬ ንጉሥ ሆይ ዕወቅ ይህ ዲያቆን ዮሐንስ ሁልጊዜ የዮሐንስ የራእዩን መጽሐፍ በማንበብ እያመካኘ ከእመቤቴ ንግሥት ጋር ይተኛል" አለው።

ንጉሡም ይህን በሰማ ጊዜ እጅግ አዘነ በዚያንም ጊዜ ተነሥቶ ንግሥቲቱ ወዳለችበት ቤተ መንግሥት ገባ ያንንም ዲያቆን በፊቷ ቁሞ የዮሐንስን የራእዩ መጽሐፍ ሲያነብ አገኘውና ከነመጽሐፉ ወስደው ዲያቆኑን ከባሕር እንዲአሠጥሙት አዘዘ። ሁለት ሰዎችም በታናሽ ጀልባ ጭነው ወስደው ከባሕር መካከል ወረወሩት። ወዲያውኑ ብርሃንን የለበሰ ሰው ከሰማይ ወርዶ ያንን ዲያቆን ከመጽሐፉ ጋር ነጥቆ ወስዶ ከአንዲት ደሴት ላይ አኖረው። እንዚያ ሁለት ሰዎች ሲያዩ ነበር እጅግም እያደነቁ ተመለሱ ያዩትንም ለንጉሡ አልነገሩትም።

ንግሥቲቱም በዲያቆኑ ላይ የተደረገውን በአየች ጊዜ እጅግ አዘነች። በእርሷም ደዌ ጸናባት ሆድዋም ቆስሎ ዐሥራ አምስት ዓመት ኖረች። ወደርሷም ብዙ ጥበበኞች ባለመድኃኒቶች መጥተው ነበር ግን ሊፈውሷት አልቻሉም። አንድ አዋቂ ሰውም እንዲህ ብሎ መከራት በግብጽ አገር ወደሚኖሩ ቅድሳን ብትሔጂ ከደዌሽ በተፈወስሽ ነበር። በዚያን ጊዜ ተነሣች ከእርሷም ጋር ብዙ ሠራዊት አለ። ወደ ግብጽ አገርም ደርሳ ገዳማቱንና አብያተ ክርስቲያንንም ሁሉ ዞረች ግን አልዳነችም።

ወደ እንዴናው ከተማም በደረሰች ጊዜ ስለ መምጣቷ የአገሩ መኳንንት አደነቁ። እርሷም ችግርዋን ሁሉ ነገረቻቸው። እነሱም ወደ ቅዱስ አባ በአሚን እንድትሔድ መከሩዋት። በመርከብም ተሳፍራ ወዲያውኑ ቅዱስ አባ በአሚን ወዳለበት ገዳም ደረሰች። "እነሆ ንግሥት ወዳንተ መጥታለች ከአንተም ልትባረክ ትሻለች" ብለው ነገሩት። እርሱም ከምድር ንግሥት ጋር ምን አለኝ ብሎ መውጣትን እምቢ አለ። መነኰሳትም ወደርሷ እንዲመጣ አጽንተው ለመኑትና ወጣ በአየችውም ጊዜ ከእግሩ በታች ወድቃ ሰገደችለት። እርሱም በዘይት ላይ ጸልዩ ቀባት በዚያንም ጊዜ ዳነች።

ቅዱስ አባ በአሚንም "ንጉሥ ከባሕር በአሠጠመው በዚያ ዲያቆን ምክንያት ይህ ሁሉ እንደደረሰብሽ ዕወቂ፤ እርሱ ግን በአንዲት ደሴት ውስጥ በሕይወት ይኖራል፤ የአቡቀለምሲስ ዮሐንስ የራእይ መጽሐፍም ከእርሱ ጋር አለ" አላት። ንግሥቲቱም ሰምታ እጅግ አደነቀች ደስ አላትም ስለዚያ ዲያቆን በሕይወት መኖርና እርሷም ፈውስ ስለማግኘቷ ለቅዱስ አባ በአሚንም እጅ መንሻ ብዙ ገንዘብ አቀረበችለት። ከንዋየ ቅዱሳት በቀር ምንም ምን ገንዘብ አልተቀበለም።

ከዚህም በኋላ #እግዚአብሔርን እያመሰገነች ወደ ሮሜ አገር ተመለሰች። በእርሷ ላይ የሆነውን ሁሉ፣ ወደ ባሕር ስለ አሠጠሙት ስለዚያ ዲያቆንም፣ እርሱም እስከ ዛሬ በአንዲት ደሴት ውስጥ በሕይወት እንዳለ ለንጉሡ ነገረችው። ንጉሡም ይህን ነገር ሰምቶ እጅግ አደነቀ ይፈልጉትም ዘንድ መልክተኞችን ላከ። በደሴትም ውስጥ በሕይወት አገኙት መጽሐፉም ከርሱ ጋር አለ። ተመልሰውም ለንጉሡ ነገሩት ሁለተኛም ወደርሱ እንዲመጣ እየማለደ ላከ። ከመልክተኞችም ጋር ወደ ንጉሡ መጣ። ንጉሡም በአየው ጊዜ ታላቅ ደስታ አደረገ ከእግሩ በታችም ወድቆ "በአንተ ላይ ስለአደረግሁት በደል ይቅር በለኝ" አለው እርሱም በአንድነት# እግዚአብሔር ይቅር ይበለን አለ።

ከዚህም በኋላ ያ ዲያቆን በሮሜ ሀገር ላይ ሊቀ ጵጵስና ተሾመ። ያንንም የዮሐንስ አቡቀለምሲስ ራእይ ተረጐመው። ቅዱስ አባ በአሚንም በቀንና በሌሊት ያለማቋረጥ የሚጋደል ሆነ።

በአቅራቢያውም አንድ ደግ ኤጲስቆጶስ አለ። በአንዲት የሰማዕታት ገዳም ከምእመናን ጋር በዓልን ሲያደርግ አርዮሳውያንም ለራሳቸው ሐሰተኛ ኤጲስቆጶስ ይዘው ሕዝብን የሚያስቱ ሆኑ። የሀገሩም ኤጲስቆጶስ ወደ አባ በአሚን መጥቶ ስለ እሊህ ከሀድያን የደረሰበትን ኃዘኑን ሁሉ ነገረው። የሰማዕታትም በዓል በሆነ ጊዜ የእሊህን ከሀድያን ምክር #እግዚአብሔር ይበትን ዘንድ ቅዱስ አባ በአሚን ከሕዝብ ጋር በመለመንና በመስገድ ጸለየ። ከዚህም በኋላ የሽመል በትር ያዘ ሕዝቡም ሁሉ እየአንዳዱ በትሮችን ይዘው ወደእነዚያ ከሀድያን ሔዱ። ከሀድያንም በአዩ ጊዜ ተበተኑ ወደዚያ ዳግመኛ አልተመለሱም #እግዚአብሔር ምክራቸውን በትኖባቸዋልና።

ቅዱስ አባ በአሚንም ፈጽሞ በአረጀ ጊዜ የሞት ደዌን ታመመ። መነኰሳቱንም ሁሉ ሰብስቦ ዕድሜው እንደ ቀረበ ነገራቸውና አጽናናቸው። እነርሱም ከእርሱ ስለመለየታቸው አዘኑ ከዚህም በኋላ በፈጣሪው #እግዚአብሔር እጅ ነፍሱን ሰጠ። መነኰሳቱም እንደሚገባ እያመሰገኑና እየዘመሩ መልካም አገናነዝን ገነዙት ሥጋው በእምነት ወደርሱ ለሚመጣ ሁሉ መጠጊያ ሆነ ወይም በቀናች ሃይማኖት ጸንቶ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሒዶ በስሙ ለሚለምን ሁሉ የለመነው ይሆንለታል።
#እግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ ጻድቅ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
2024/12/26 18:44:00
Back to Top
HTML Embed Code: