Telegram Web Link
ያንንም ሕፃን ይዘው ወደ መኰንኑ ወሰዱት መኰንኑም መልኩ የሚያምርና ደም ግባት ያለው እንደሆነ በአየው ጊዜ "ደስ የምትል ደስተኛ ሕፃን ሰላምታ ይገባሃል" አለው። ሕፃኑም "እኔን ደስተኛ ማለትህ መልካም ተናገርክ፤ ላንተ ግን ደስታ የለህም #እግዚአብሔር ለዝንጉዎች ደስታ የላቸውም ብሏልና።" ብሎ መለሰለት መኰንኑም ሕፃኑን "ሳልጠይቅህ ይህን ያህል ትመልስልኛለህን?" አለው። ሕፃኑም "ገና ከዚህ የሚበዛ ነገርን እመልስልሃለሁ" አለው።

መኰንኑም ሕፃኑን "ስምህ ማን ነው?" አለው። "ከንጹሕ ዐዘቅትና ከማይለወጥ ከማይጠፋ ውኃ የተገኘ ሕፃን ስሜ ክርስቲያን መባል ነው" ብሎ መለሰለት። መኰንኑም "ዳግመኛ እንዳትሞት ስምህን ንገረኝ" አለው። የከበረ ሕፃንም "ስሜ ክርስቲያን መባል እንደሆነ ነገርኩህ ሞክሼ ስም የምትሻ ከሆነ እናቴ የሰየመችኝ ቂርቆስ ነው።"

መኰንኑም ሕፃን ቂርቆስን "እሺ በለኝና ለአማልክት ሠዋ በሥጋህም ስታድግ እሾምሃለሁ በብዙ ወርቅና ብርም አከብርሃለሁ" አለው። ሕፃኑም "የሰይጣን መልእክተኛ ለዕውነትም ጠላቷ የሆንክ ከእኔ ራቅ" አለው።

መኰንኑም ሰምቶ ተቆጣ ደሙ እንደ ውኃ እስከሚፈስ ቆዳውን እንዲጨምቁትና እንዲገፉት አዘዘ። የከበረች ቅድስት ኢየሉጣም የልጅዋን ትዕግሥት ባየች ጊዜ #እግዚአብሔርን አመሰገነችው።

ከዚህም በኋላ መኰንኑ ጨውና ሰናፍጭ አምጡ አለ የሁለቱንም አፍንጮቻቸውን ከፍተው ያንን ጨውና ሰናፍጭ እንዲጨምሩባቸው አዘዘ ያን ጊዜ ሕፃኑ ትእዛዝህ ለጕረሮዬ ጣፋጭ ሆነ ከማርና ከስኳርም ለአፌ ጣመኝ ብሎ ጮኸ።

ሁለተኛም መኰንኑ እንዲህ ብሎ አዘዘ የረዘሙና የተሳሉ በእሳትም እንደ ፍም የጋሉ ዐሥራ አራት የብረት ችንካሮች አምጡ ሰባቱን በእናቱ አካላት ውስጥ ጨምሩ በሕፃኑም ሁለት በጆሮዎቹ ሁለት በዐይኖቹ ሁለት በአፉና በአፍንጫው አንድ በልቡ ጨምሩ እንዲህ ሲጨመርበት ጆሮዎቹ እንዲያኖሩ ዐይኖቹም ይጠፉ ዘንድ አንደበቱም ይቃጠል ዘንድ ወደ ልቡም ጽኑ ሕማም ገብቶ እርሱ ከዚህ ዓለም በሞት እንዲለይ ለእናቱም እንዲሁ አድርጉ። ችንካሮችም በቅዱሳኑ በሥጋቸው ሁሉ ተጨመሩ።

የክብር ባለቤት በሆነ በ #ጌታችን ትእዛዝ የብረቶቹ ግለት ጠፍቶ እንደ በረዶ ቀዘቀዘ ጤነኞችም ሆኑ መኰንኑም ወደ ወህኒ ወስዳችሁ በዚያ አሥራችሁ ዝጉባቸው አለ።

ከዚህም በኋላ መኰንኑ የሥቃይ መሣሪያ ይሠራ ዘንድ አንዳዝዘው ብረትን የሚያቀልጥ ሰው አምጡልኝ አለ። በአመጡለትም ጊዜ ሰይጣኑ ወደ መኰንኑ ልብ ገብቶ አንደበቱን ዘጋውና መናገር ተሳነው ሕፃኑ ፈጥኖ አክሊልን ለመቀበል እንደሚተጋ ሰይጣን ስለ አወቀ ስለዚህ ዘጋው።

ከዚህም በኋላ ሕፃኑ ሠራተኛውን ጠርቶ እኔንና እናቴን የሚያሠቃዩበትን የሥቃይ መሣሪያ መሥራት ትችላለህን ይህ መኰንን ግን ምንም የሚያውቀው ነገር የለም አለው ሠራተኛውም እንደምትሻው በል ንገረኝ እንደምታዝዘኝ እኔ መሥራት እችላለሁ አለው።

ሕፃን ቂርቆስም ሊአዝዝ ጀመረ እንዲህም አለ ሁለት መላጫዎች ስፋታቸው አራት ክንድ የሆነ ለእኔና ለእናቴ ሥራ። ዳግመኛም የሚያስጨንቅ ራስን የሚመታና የሚሰብር አንገትንም የሚያሥር የሚዝቅም ሹካ ዐይንንም የሚያወልቅ አካልንም የሚበሳሳ አፍንጫንም የሚያጣምምና የሚሰብር ጆሮንም የሚልጥ ሕዋሳትን የሚፈታና የሚለያይ እንደ ልጓም ሁኖ ምላስን የሚቆርጥ በሰውነትም ውስጥ ገብቶ የሚንቀሳቀስ ቆላፋ ጉጠትን ጐኖችንም የሚፍቅና የሚቆለምም አስጨናቂ የሆነ ጉልበቶችንና ጭኖችን የሚሰብር ጅማቶችንም የሚቆራርጥ ሥሮችንም የሚመዝ በዚችም አስጨናቂ መሣሪያ ጅማቶችን የሚታታ አድርግ።

ዳግመኛም በላም አምሳል ሰፊ መቀመጫ ከናስ ሥራ ሦስት ቀዳዳዎችንም በዚያ መቀመጫ ውስጥ ቅደድ። በቁመቴም ልክ ሦስት ችንካሮችን ሥራ የችንካሮቹንም ራስ ከናስ አድርገህ በውስጡ ከሚጠሩት ዘንድ ፈጽሞ የማይለይ ልዩ ሦስት ብለህ ጻፍ።

ዳግመኛም ጠምዝዞ ወደ ላይ የሚያወጣ ሁለት መሣሪያ ሁለት መጋዞችን ሁለት የብረት ምጣዶችን ሥራ አሁንም አንድ ታላቅ ጋን ሠርተህ በውስጡ አንገትን የሚጠመዝዝና የሚሠነጥቅ ተሽከርካሪ መሣሪያ አድርግ።

በውስጥ የተሸሸገ የሆድ ዕቃን የሚመረምር እጅን ከብረት ሥራ እኔ የጻዕር ስቃይን የምሠቃይበት ይህ ነው አለ። ብረት ሠሪውም ሰምቶ እጅግ አደነቀ የሚረዱትንም ከሀገር ውስጥ መቶ ሠራተኞችን ሰብስቦ መሥራት ጀመረ በአርባ ቀንም ጨረሰ።

ከዚህም በኋላ መኰንኑ እለእስክንድሮስ ቅዱስ ቂርቆስንና እናቱን ወደ አደባባይ ያመጡአቸው ዘንድ አዘዘ ያን ጊዜ አንደበቱ ተፈትቶ ነበርና እንዲህም አለ ሕፃኑንና እናቱን ከቆዳቸው ጋር ራሳቸውን ላጩአቸውና በላያቸው የእሳት ፍሞችን ጨምሩ እርር ብለው እንዲቃጠሉ ዳግመኛም አራት ችንካሮችን ከትከሻዎቹ እስከ ተረከዙ ድረስ እንዲተክሉበት አዘዘ የ #እግዚአብሔርም መልአክ መጥቶ ሥቃዮችን ከርሱ አራቀ።

ዳግመኛም ከጥዋት እስከ ማታ ከሥቃይ መሣሪያዎች ውስጥ ጨምረው አዋሏቸው ግን ማሠቃየት ተሳናቸው። ከዚህም በኋላ ከማምጠቂያው ውስጥ ጨምረው መገዙአቸውና አመድ እስከሆኑ ከቅባትና ከጨው ጋር በብረት ምጣድ ውስጥ ቆሉአቸው #ጌታችንም ከሞት አስነሥቶ አዳናቸው።

ወደ መኰንኑም በገቡ ጊዜ እንዲህ አላቸው በእውነት ከሙታን ተለይታችሁ የተነሣችሁ ከሆነ ይህ ጫማዬ ከእግሬ ወጥቶ እንደ ቀድሞው ሕያው እንዲሆን አድርጉ ሕፃን ቂርቆስም በጸለየ ጊዜ ያ ጫማ ታለቅ በሬ ሆነ ከአንገቱም ፍየል ወጣ።

በዚያንም ሰዓት ለዐሣራ አንድ ሽህ አራት ሰዎች በሬውንና ፍየሉን አርደው ምሳ እንዲአደርጉላቸው መኰንኑ አዘዘ እንዲህም አለ ይህ በቅቷቸው ከጠገቡ ከዚህም ሌላ ምግብ ካልፈለጉ የተሠራው ሁሉ ዕውነተኛ ነዋሪ ነው። ከዚህም በኋላ አርደው ምሳ አደረጉላቸውና ከፍየሉ ሥጋ ስድስት እንቅብ ከበሬው ሥጋ አራት እንቅብ አተረፉ መኰንኑም የተረፈውን ሥጋ አይቶ ወደ ባሕር እንዲጥሉት አዘዘ።

መኰንኑም ቢያፍር የሕፃኑን ምላስ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ #ጌታችንም ምላሱን መለሰለት። ዳግመኛም በታላቅ ጋን ውኃ እፍልተው ሕፃን ቂርቆስንና እናቱን ኢየሉጣን ይጨምሩአቸው ዘንድ አዘዘ። እናቱም አይታ ፈራች። ልጅዋም ወደ #እግዚአብሔር በጸለየላት ጊዜ አምላካዊ ኃይልን አሳደረባትና ከልጅዋ ጋር ወደ ጋኑ ገባች። እንደ ውርጭም ቀዝቀዛ ሆነ ደግሞም በውስጡ መንኰራኲር ወዳለበት የብረት ምጣድ እንዲጨምሯቸውና ሥጋቸው እሰከሚቦጫጨቅ እንዲስቡአቸው አዘዘ የ #እግዚአብሔርም መልአክ በሕይወት አወጣቸው።

መኰንኑም እነርሱን ማሸነፍ በተሳነው ጌዜ ቸብቸቧቸውን በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ። በዚያን ጊዜ ለስም አጠራሩ ስግደት የሚገባው የክብር ባለቤት #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ወረደ ሕፃን ቂርቆስንም የምትሻውን ለምነኝ አለው።

ሕፃኑም ሥጋዬ በምድር አይቀበር ስሜን ለሚጠራ መታሰቢያዬን ለሚያደርግ ቤተ ክርስቲያኔን ለሚሠራ የተጋድሎዬን መጽሐፍ ለሚጽፍና ለሚያጽፍ ወይም ለሚያነበው ለቤተ ክርስቲያኔ መባ ለሚያገባ በውስጧም ለሚጸልይ ለሁሉም ፍላጎታቸውን ስጣቸው። ኃጢአታቸውንም ይቅር በል ስሜም በሚጠራበት በዚያች ቦታ የከብት ዕልቂት አይምጣ፤ በሰውም ላይ እባር ቸነፈር በእህልም ላይ ድርቅ የውኃም ማነስ አይሁን።

#መድኃኒታችንም የለመንከኝን ሁሉ እሰጥሃለሁ አንተም በቀኜ ትኖራለህ ሥጋህንም ኤልያስ በዐረገበት ሠረገላ ውስጥ አኖራለሁ አለው። ሕፃን ቂርቆስም በሰማ ጊዜ እጅግ ደስ ብሎት #ጌታችንን አመሰገነው። ከዚህም በኋላ በሌሊቱ እኩሌታም ከእናቱ ጋር አንገቱን ተቆረጠ #መድኃኒታችንም በማይጠፋ አክሊል ጋረደው ነፍሶቻቸውንም በታላቅ ክብር ከእርሱ ጋር አሳረገ።
#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ሊቀ_ጳጳስ_ቅዱስ_ሚናስ_ሁለተኛ

በዚህችም ቀን ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ስልሳ አንደኛ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ አባት ሁለተኛው ሚናስ አረፈ።

ይህን ቅዱስ ሚናስንም በታናሽነቱ ያለ ፍላጎቱ ወላጆቹ ሚስት አጋቡት ትእዛዛቸውን መተላለፍ ስለአልፈለገ የጋብቻውን ሥርዓት ሁሉ በቤተ ክርስቲያን ፈጸመ። ለርሱ ይህ ሁሉ ሕልም ይመስለው ነበር ወደ ሙሽሪትም ወደ አዳራሽ በአስገቡት ጊዜ ተቀምጦ እንዲህ ብሎ ተናገራት እኅቴ ሆይ ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱን ካጠፋ ምን ይጠቅመዋል እንደ ተጻፈ ሁሉ ያልፋልና ግን የ #እግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ለዘላለሙ ይኖራል አሁንም ድንግልናችንን እንድንጠብቅ ነይ ቃል ኪዳን እናድርግ እርሷም ቃሉን ተቀብላ ከእርሱ ጋር ተስማማች።

ከዚህም በኋላ ትቷት ወደ አስቄጥስ ገዳም ሒዶ በአባ መቃርስ ገዳም ውስጥ መነኰሰ ብዙ ዘመናትም በገድል ተጠምዶ ኖረ። ከእርሱ በፊት የነበረ ሊቀ ጳጳሳትም በአረፈ ጊዜ ይህን ቅዱስ አባት ሚናስን ያለውዴታው ወስደው ሊቀ ጵጵስና ሾሙት በወንጌላዊ ማርቆስም ወንበር ላይ መንጋዎቹን በቅን ፍርድ እየጠበቃቸው እያስተማራቸውም ዐሥራ ስምንት ዓመት ኑሮ በሰላም አረፈ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ኅዳር_15_እና_ጥር_15)
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ኅዳር_15_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ቆላስይስ 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹² ከደስታም ጋር በሁሉ ለመጽናትና ለመታገሥ እንደ ክብሩ ጉልበት መጠን በኃይል ሁሉ እየበረታችሁ፥ በቅዱሳንም ርስት በብርሃን እንድንካፈል ያበቃንን አብን እያመሰገናችሁ፥ በነገር ሁሉ ደስ ልታሰኙ ለጌታ እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እንለምናለን።
¹³-¹⁴ እርሱ ከጨለማ ሥልጣን አዳነን፥ ቤዛነቱንም እርሱንም የኃጢአትን ስርየት ወዳገኘንበት ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግሥት አፈለሰን።
¹⁵-¹⁶ እርሱም የማይታይ አምላክ ምሳሌ ነው፤ የሚታዩትና የማይታዩትም፥ ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ጌትነት ወይም አለቅነት ወይም ሥልጣናት፥ በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኵር ነው፤ ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል፤
¹⁷ እርሱም ከሁሉ በፊት ነው ሁሉም በእርሱ ተጋጥሞአል።
¹⁸ እርሱም የአካሉ ማለት የቤተ ክርስቲያን ራስ ነው፤ እርሱም በሁሉ ፊተኛ ይሆን ዘንድ፥ መጀመሪያ ከሙታንም በኵር ነው።
¹⁹-²⁰ እግዚአብሔር ሙላቱ ሁሉ በእርሱ እንዲኖር፥ በእርሱም በኩል በመስቀሉ ደም ሰላም አድርጎ በምድር ወይም በሰማያት ያሉትን ሁሉ ለራሱ እንዲያስታርቅ ፈቅዶአልና።
²¹-²² እናንተንም ነውርና ነቀፋ የሌላችሁና ቅዱሳን አድርጎ በእርሱ ፊት ያቀርባችሁ ዘንድ፥ በፊት የተለያችሁትን ክፉ ሥራችሁንም በማድረግ በአሳባችሁ ጠላቶች የነበራችሁትን አሁን በሥጋው ሰውነት በሞቱ በኩል አስታረቃችሁ።
²³ ይህም፥ ተመሥርታችሁና ተደላድላችሁ ከሰማችሁትም ከወንጌል ተስፋ ሳትናወጡ፥ በሃይማኖት ጸንታችሁ ብትኖሩ ይሆናል፤ ያም ወንጌል ከሰማይ በታች ባለው ፍጥረት ሁሉ ዘንድ የተሰበከ ነው፥ እኔም ጳውሎስ የእርሱ አገልጋይ ሆንሁ።
²⁴ አሁን በመከራዬ ስለ እናንተ ደስ ይለኛል፥ ስለ አካሉም ማለት ስለ ቤተ ክርስቲያን በሥጋዬ በክርስቶስ መከራ የጐደለውን እፈጽማለሁ።
²⁵ ስለ እናንተ እንደ ተሰጠኝ እንደ እግዚአብሔር መጋቢነት፥ የእግዚአብሔርን ቃል ፈጽሜ እንድሰብክ እኔ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ሆንሁ፤
²⁶ ይህም ቃል ከዘላለምና ከትውልዶች ጀምሮ ተሰውሮ የነበረ ምሥጢር ነው፥ አሁን ግን ለቅዱሳኑ ተገልጦአል፤
²⁷ ለእነርሱም እግዚአብሔር በአሕዛብ ዘንድ ያለው የዚህ ምሥጢር ክብር ባለ ጠግነት ምን እንደ ሆነ ሊያስታውቅ ወደደ፥ ምሥጢሩም የክብር ተስፋ ያለው ክርስቶስ በእናንተ ዘንድ መሆኑ ነው።
²⁸ እኛም በክርስቶስ ፍጹም የሚሆን ሰውን ሁሉ እናቀርብ ዘንድ ሰውን ሁሉ እየገሠጽን ሰውንም ሁሉ በጥበብ ሁሉ እያስተማርን የምንሰብከው እርሱ ነው፤
²⁹ ለዚህም ነገር ደግሞ፥ በእኔ በኃይል እንደሚሠራ እንደ አሠራሩ እየተጋደልሁ፥ እደክማለሁ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ጴጥሮስ 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹³ ስለዚህ የልቡናችሁን ወገብ ታጥቃችሁና በመጠን ኖራችሁ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲገለጥ የምታገኙትን ጸጋ ፈጽማችሁ ተስፋ አድርጉ።
¹⁴ እንደሚታዘዙ ልጆች ባለማወቃችሁ አስቀድሞ የኖራችሁበትን ምኞት አትከተሉ።
¹⁵-¹⁶ ዳሩ ግን፦ እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ ተብሎ ስለ ተጻፈ የጠራችሁ ቅዱስ እንደ ሆነ እናንተ ደግሞ በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ።
¹⁷ ለሰው ፊትም ሳያደላ በእያንዳንዱ ላይ እንደ ሥራው የሚፈርደውን አባት ብላችሁ ብትጠሩ በእንግድነታችሁ ዘመን በፍርሃት ኑሩ።
¹⁸-¹⁹ ከአባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከከንቱ ኑሮአችሁ በሚያልፍ ነገር በብር ወይም በወርቅ ሳይሆን፥ ነውርና እድፍ እንደ ሌለው እንደ በግ ደም በክቡር የክርስቶስ ደም እንደ ተዋጃችሁ ታውቃላችሁ።
²⁰-²¹ ዓለም ሳይፈጠር እንኳ አስቀድሞ ታወቀ፥ ነገር ግን እምነታችሁና ተስፋችሁ በእግዚአብሔር ይሆን ዘንድ፥ ከሙታን ባስነሣው ክብርንም በሰጠው በእግዚአብሔር በእርሱ ስለምታምኑ ስለ እናንተ በዘመኑ መጨረሻ ተገለጠ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 19
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²¹ ይህም በተፈጸመ ጊዜ ጳውሎስ፦ ወደዚያ ደርሼ ሮሜን ደግሞ አይ ዘንድ ይገባኛል ብሎ በመቄዶንያና በአካይያ አልፎ ወደ ኢየሩሳሌም እንዲሄድ በመንፈስ አሰበ።
²² ከሚያገለግሉትም ሁለቱን ጢሞቴዎስንና ኤርስጦንን ወደ መቄዶንያ ልኮ ራሱ በእስያ ጥቂት ቀን ቆየ።
²³ በዚያም ጊዜ ስለዚህ መንገድ ብዙ ሁከት ሆነ።
²⁴ ብር ሠሪ የሆነ ድሜጥሮስ የሚሉት አንድ ሰው የአርጤምስን ቤተ መቅደስ ምስሎች በብር እየሠራ ለአንጥረኞች እጅግ ትርፍ ያገኝ ነበርና፤
²⁵ እነዚህንም ይህንም የሚመስለውን ሥራ የሠሩትን ሰብስቦ እንዲህ አላቸው፦ ሰዎች ሆይ፥ ትርፋችን በዚህ ሥራ እንደ ሆነ ታውቃላችሁ።
²⁶ ይህም ጳውሎስ፦ በእጅ የተሠሩቱ አማልክት አይደሉም ብሎ፥ በኤፌሶን ብቻ ሳይሆን ከጥቂት ክፍል በቀር በእስያ ሁሉ ብዙ ሕዝብን እንደ አስረዳና እንደ አሳተ አይታችኋል ሰምታችሁማል።
²⁷ ሥራችንም እንዲናቅ ብቻ አይደለም፥ እስያ ሁሉ ዓለሙም የሚያመልካት የታላቂቱ አምላክ የአርጤምስ መቅደስ ምናምን ሆኖ እንዲቆጠር እንጂ፥ ታላቅነትዋም ደግሞ እንዳይሻር ያስፈራል።
²⁸ ይህንም በሰሙ ጊዜ ቍጣ ሞላባቸው፦ የኤፌሶን አርጤምስ ታላቅ ናት እያሉም ጮኹ።
²⁹ ከተማውም በሙሉው ተደባለቀ፥ የመቄዶንያም ሰዎች የጳውሎስን ጓደኞች ጋይዮስንና አርስጥሮኮስን ከእነርሱ ጋር ነጥቀው በአንድ ልብ ሆነው ወደ ጨዋታ ስፍራ ሮጡ።
³⁰ ጳውሎስም ወደ ሕዝቡ ይገባ ዘንድ በፈቀደ ጊዜ ደቀ መዛሙርት ከለከሉት።
³¹ ከእስያም አለቆች ወዳጆቹ የሆኑት አንዳንዶች ደግሞ ወደ እርሱ ልከው ወደ ጨዋታ ስፍራ ራሱን እንዳይሰጥ ለመኑት።
³² ወዲያና ወዲህም እያሉ ይጮኹ ነበር፤ በጉባኤው ድብልቅልቅ ሆኖ የሚበልጡት ስንኳ ስለ ምን እንደተሰበሰቡ አላወቁም ነበርና።
³³ አይሁድም ሲያቀርቡት፥ እስክንድሮስን ከሕዝቡ መካከል ወደ ፊት ገፉት፤ እስክንድሮስም በእጁ ጠቅሶ በሕዝብ ፊት እንዲምዋገትላቸው ወደደ።
³⁴ አይሁዳዊ ግን እንደ ሆነ ባወቁ ጊዜ፥ ሁሉ በአንድ ድምፅ፦ የኤፌሶን አርጤምስ ታላቅ ናት እያሉ ሁለት ሰዓት ያህል ጮኹ።
³⁵ የከተማይቱም ጸሐፊ ሕዝቡን ጸጥ አሰኝቶ እንዲህ አለ፦ የኤፌሶን ሰዎች ሆይ፥ የኤፌሶን ከተማ ለታላቂቱ አርጤምስ ከሰማይም ለወረደው ጣዖትዋ የመቅደስ ጠባቂ መሆንዋን የማያውቅ ሰው ማን ነው?
³⁶ ይህንም የሚክደው ከሌለ፥ ጸጥ እንድትሉና አንዳች በችኮላ እንዳታደርጉ ይገባል።
³⁷ የመቅደስን ዕቃ ያልሰረቁ አምላካችንንም ያልሰደቡ እነዚህን ሰዎች አምጥታችኋቸዋልና።
³⁸ ድሜጥሮስና ከእርሱ ጋር ያሉት አንጥረኞች ግን በሰው ላይ ነገር እንዳላቸው፥ የመጋቢያ ቀንና አገረ ገዢዎች አሉ፤ እርስ በርሳቸው ይምዋገቱ።
³⁹ ስለ ሌላ ነገር እንደ ሆነ ግን አንዳች ብትፈልጉ፥ በተደነገገው ጉባኤ ይፈታል።
⁴⁰ ዛሬ ስለ ተደረገው፦ ሁከት ነው ሲሉ እንዳይከሱን ያስፈራልና፤ ስለዚህም ስብሰባ ምላሽ መስጠት አንችልም፥ ምክንያት የለምና።
⁴¹ ይህንም ብሎ ጉባኤውን ፈታው።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ኅዳር_15_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"ኵሉ ዘፈቀደ ገብረ እግዚአብሔር። በሰማይኒ ወበምድርኒ። በባሕርኒ ወበኵሉ ቀላያት። መዝ.134÷6
"በሰማይና በምድር በባሕርና በጥልቆች ሁሉ፥ እግዚአብሔር የወደደውን ሁሉ አደረገ"። መዝ.134÷6
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ኀዳር_15_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️ዮሐንስ 5
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁶ ስለዚህም በሰንበት ይህን ስላደረገ አይሁድ ኢየሱስን ያሳድዱት ነበር ሊገድሉትም ይፈልጉ ነበር።
¹⁷ ኢየሱስ ግን፦ አባቴ እስከ ዛሬ ይሠራል እኔም ደግሞ እሠራለሁ ብሎ መለሰላቸው።
¹⁸ እንግዲህ ሰንበትን ስለ ሻረ ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን ደግሞ ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር አስተካክሎ፦ እግዚአብሔር አባቴ ነው ስላለ፥ ስለዚህ አይሁድ ሊገድሉት አብዝተው ይፈልጉት ነበር።
¹⁹ ስለዚህ ኢየሱስ መለሰ እንዲህም አላቸው፦ እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ አብ ሲያደርግ ያየውን ነው እንጂ ወልድ ከራሱ ሊያደርግ ምንም አይችልም፤ ያ የሚያደርገውን ሁሉ ወልድ ደግሞ ይህን እንዲሁ ያደርጋልና።
²⁰ አብ ወልድን ይወዳልና፥ የሚያደርገውንም ሁሉ ያሳየዋል፤ እናንተም ትደነቁ ዘንድ ከዚህ የሚበልጥ ሥራ ያሳየዋል።
²¹ አብ ሙታንን እንደሚያነሣ ሕይወትም እንደሚሰጣቸው፥ እንዲሁ ወልድ ደግሞ ለሚወዳቸው ሕይወትን ይሰጣቸዋል።
²²-²³ ሰዎች ሁሉ አብን እንደሚያከብሩት ወልድን ያከብሩት ዘንድ፥ ፍርድን ሁሉ ለወልድ ሰጠው እንጂ አብ በአንድ ሰው ስንኳ አይፈርድም። ወልድን የማያከብር የላከውን አብን አያከብርም።
²⁴ እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ቃሌን የሚሰማ የላከኝንም የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፥ ከሞትም ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይመጣም።
²⁵ እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ሙታን የእግዚአብሔርን ልጅ ድምፅ የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል እርሱም አሁን ነው፤ የሚሰሙትም በሕይወት ይኖራሉ።
²⁶ አብ በራሱ ሕይወት እንዳለው እንዲሁ ደግሞ ለወልድ በራሱ ሕይወት እንዲኖረው ሰጥቶታልና።
²⁷ የሰው ልጅም ስለ ሆነ ይፈርድ ዘንድ ሥልጣን ሰጠው።

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
✝️የሚቀደሰው ቅዳሴ የ የእመቤታቸን #የማርያም ወይም የ #ቅዱስ_አትናቴዎስ_ቅዳሴ ነው። መልካም የጾመ አዳም፣ የጾመ ነቢያት፣ የጾመ ሐዋርያት፣ የጾመ ማርያም፣ የጾመ ፊልጶስ፣ የጾመ ስብከት፣ የጾመ ልደት፣ የቅዱስ ሚናስ ሰማዕት ዕረፍት፣ የሁለተኛው ቅዱስ ሚናስ ዕረፍት፣ የሕጻኑ ቅዱስ ቂርቆስ ልደትና መልካም ዕለተ ሰንበት ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
Forwarded from 💠ኢዮራም ፕሮሞሽን💠
📷 እርግጠኛ ነኝ ፕሮፍይሎን ለመቀየር ፈልገው ፕሮፍይል የሚያደርጉት ጠፍቶ  ተቸግረው ያውቃሉ።

የናንተን ችግር ለመፍታት በአይነቱ ለየት ያለ አዲስ መንፈሳዊ ቻናል ይዘንላችሁ መተናል ከናንተ የሚጠበቀው ከታች ባለው ሊንክ join ማድረግ ብቻ ነው👇👇👇👇👇👇📷

https://www.tg-me.com/addlist/gpX29GzfGs43MWE0
✝️ ጾመ ነብያት ✝️

#ጾመ_ነቢያት (የገና ጾም) ከ"ሰባቱ የአዋጅ አጽዋማት" መካከል አንዱ ሲሆን “ጾመ ነቢያት” የተባለበት ምክንያት ነቢያት ስለጾሙት ነው፡፡

📌“ነቢያት የጾሙት ስለምንድን ነው?” ቢሉ ለአዳም የተሰጠውን “አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ” የሚለውን የተስፋ ቃል በማሰብ ከሰማየ ሰማያት ይወርዳል፣ ከድንግል #ማርያም ይወለዳል፣ በሞቱም ሞት የተፈረደበትን የሰው ልጅ ነፃ ያወጣዋል ብለው ነው፡፡

📌“ይህንን ጾም የትኞቹ ነቢያት ናቸው የጾሙት?” ቢሉ ሊቀ ነቢያት ቅዱስ ሙሴ 40 ቀን ጾሟል (ዘፀ 34፡27)፤ ነቢዩ ኤልያስም 40 ቀን ጾሟል (1ኛ ነገ 19፡1)፡፡ በተጨማሪም በተለያየ ዘመን የነበሩት ነቢዩ ዕዝራ፣ ነቢዩ ነህምያ፣ ነቢዩ ዳንኤል እንዲሁም ክቡር ዳዊት ጾመዋል፡፡

📌"ነቢያት ይወርዳል ይወለዳል ብለው ከጾሙ፤ እኛ እርሱ ወርዶ፣ ተወልዶ ተሰቅሎ ካዳነን በኋላ ያለን የሐዲስ ኪዳን ክርስትያኖች ስለምን የነቢያትን ጾም እንጾማለን?” ቢሉ እኛ የነቢያትን ጾም የምንጾመው እንደቀደሙት ነቢያት ይወርዳል ይወለዳል እያልን ሳይሆን የቀደሙት ነቢያት ይወርዳል ይወለዳል እያሉ የጾሙትን በማሰብ በመጾማችን ድኅነተ ሥጋ፣ ድኅነተ ነፍስ፣ በረከተ ሥጋ፣ በረከተ ነፍስ እንድናገኝበት ነው፡፡”ጾመ ነቢያት (የገና ጾም) ከኅዳር 15 ጀምሮ እስከ ታኅሳስ 29 ቀን (በዘመነ ዮሐንስ እስከ ታኅሳስ 28 ቀን) ድረስ ለ44 ቀናት (በዘመነ ዮሐንስ ለ 43 ቀናት) ይጾማል፡፡ ከእነዚህም መካከል 40 ቀናት ጾመ ነቢያት፣ 3 ቀናት ጾመ አብርሃም ሶርያዊ ሲሆኑ የቀረው 1 ቀን ደግሞ የገሃድ ጾም ነው (ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 15 ቁጥር 565፣ 567)፡፡ ጾመ ነቢያትን ከኅዳር 15 ጀምሮ ሳይጾሙ የልደትን ዋዜማ ብቻ መጾም የቤተክርስቲያን ሥርዓት አይደለም፡፡

➡️ይህንን ጾም በዘመነ ብሉይና በዘመነ ሐዲስ ብዙ ቅዱሳን ጾመውታል፤ በዚህም ምክንያት የሚከተሉት ስያሜዎች አሉት፡፡ እነርሱም፦

፩. ጾመ አዳም
፪. ጾመ ነቢያት
፫. ጾመ ሐዋርያት
፬. ጾመ ማርያም
፭. ጾመ ፊልጶስ
፮. ጾመ ስብከት
፯. ጾመ ልደት

ጾመ አዳም፦ አዳም ዕፀ በለስን በልቶ ከገነት ከተባረረ በኋላ በፈጸመው በደል አዝኖ ፥ ተክዞ ፤ አለቀሰ [እንባ ቢያልቅበት እዥ እስከሚያፈስ ፤ እዥ ቢያልቅበት ደም በዓይኑ እስከሚፈስና ዓይኑ ይቡስ ወይም ደረቅ እስከሚሆን ድረስ አለቀሰ] ፥ ጾመ፣ ጸለየ፡፡ ከልብ የሆነ ጸጸቱን፣ ዕንባውን፣ በራሱ መፍረዱንም #እግዚአብሔር አይቶ ተስፋ ድኅነት ሰጠው፡፡ "ከአምስት ቀን ተኩል በኋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ ፣ በደጅህ ድኼ ፣ በዕፀ #መስቀል ተሰቅዬ፣ ሞቼ አድንሃለሁ፡፡" የሚል ነው፡፡ [ገላ. ፬፥፬፣ መጽ.ቀሌምንጦስ] ስለዚህ ጾሙ የተሰጠው ተስፋ ፥ የተቆጠረው ሱባኤ ስለተፈጸመበት "ጾመ አዳም" ይባላል፡፡

ጾመ ነቢያት፦ ነቢያትም የምሥጢረ ሥጋዌ ነገር ተገለጦ ስለታያቸው ፣ #ክርስቶስ ለሰው ልጅ የሚከፍለውን የፍቅር ዋጋ በትንቢት ተመልክተው ጾመውታልና ጾመ ነቢያት ይባላል፡፡ ይህ ጾም ከአባታችን አዳም እስከ መጥምቁ ዮሐንስ ድረስ የተነሱ አበውና እናቶች : ድኅነትንና ረድኤትን ሲሹ የጾሙት ጾም ነው:: በተለይ አባታችን አዳም : ቅዱስ ሙሴ : ቅዱስ ኤልያስ ፣ ቅዱስ ዳንኤልና ቅዱስ ዳዊት በጾማቸው የተመሰከረላቸው ቅዱሳን ናቸው:: [ዘዳ.፱፥፲፱ ፣ ነገ.፲፱፥፰ ፣ ዳን.፱፥፫ መዝ.፷፰፥፲ ፻፰፥፳፬] ቅዱሳን ነቢያት በጭንቅ በመከራ ሆነው የጾሙት ጾም ወደ መንበረ ጸባኦት ደርሶ: #ወልድን ከዙፋኑ ስቦታል:: ለሞትም አብቅቶታል::

ጾመ ሐዋርያት፦ ሐዋርያት "ትንሣኤን ዐቢይ ጾምን ጾመን እናከብራለን ፣ ልደትን ምን ሥራ ሠርተን እናከብረዋለን?" ብለው ከልደተ #ክርስቶስ በፊት ያሉትን ፵፫ ዕለታት ጾመዋልና፡፡

ጾመ ማርያም፦ እመቤታችን ቅድስት ድንግል #ማርያም #እግዚአብሔር_አምላክ ቅድስናዋን አይቶ በቅዱስ ገብርኤል ብሥራት ወልደ አምላክን ያለ ሰስሎተ ድንግልና በግብረ #መንፈስ_ቅዱስ ጸንሳ እንደምትወልደው ቢነግራትም የትሕትና እናት ናትና "ምን ሠርቼ የሰማይና ምድርን ፈጣሪ እችለዋለሁ?" ብላ #ጌታን ከመውለዷ አስቀድማ ጾማለችና "ጾመ ማርያም" ይባላል፡፡

ጾመ ፊልጶስ (የፊልጶስ ጾም)›› ተብሎ ይጠራል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ፊልጶስ በአፍራቅያና አውራጃዋ ዅሉ እየተዘዋወረ በ #ጌታችን_አምላካችንና_መድኀኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ስም ወንጌልን በማስተማር፣ ድንቅ ድንቅ ተአምራትን በማድረግ ብዙዎችን ወደ አሚነ #እግዚአብሔር ሲመልስ ቆይቶ ትምህርቱን በማይቀበሉ የአፍራቅያ ሰዎች አማካይነት በሰማዕትነት ዐርፏል፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ሥጋውን ሊቀብሩ ሲሉም ስለ ተሰወረባቸው የሐዋርያውን ሥጋ ይመልስላቸው ዘንድ ሱባዔ ይዘው፣ በጾም በጸሎት ተወስነው በለመኑት ጊዜ #እግዚአብሔር ልመናቸውን ተቀብሎ በ፫ኛው ቀን መልሶላቸው ሥጋውን (አስከሬኑን) በክብር አሳርፈውታል፡፡ ደቀ መዛሙርቱ የሐዋርያውን ሥጋ ካገኙ በኋላ እስከ #ጌታችን ልደት ድረስ ጾመዋል፡፡ ስለዚህም ጾመ ነቢያት ‹‹ጾመ ፊልጶስ›› እየተባለ ይጠራል፡፡

ጾመ ስብከት፦ የ #ወልደ_እግዚአብሔርን ሰው መሆን ያስተማሩበት ፥ የሰው ልጆች ተስፋ የተመሰከረበት ፥ የምስራች የተነገረበት ስለሆነ ጾመ ስብከትም ይባላል፡፡

ጾመ ልደት ፦ የጾሙ መጨረሻ [መፍቻ] በዓለ ልደት ስለሆነ "ጾመ ልደት" ይባላል፡፡

#አስተምህሮ_(አስተምሕሮ)

#በወቅቱ /ጊዜው፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የዘመን አከፋፈል መሠረት ከኅዳር 6 ጀምሮ እስከ ታኅሣሥ 7 ወይም 13 ቀን ድረስ ያለው ወቅት ዘመነ አስተምሕሮ (አስተምህሮ) ይባላል፡፡

#አስተምህሮ፡ ቃሉ በሃሌታው “ሀ” (“አስተምህሮ” ተብሎ) ሲጻፍ የቃለ #እግዚአብሔር ማስተማሪያ (የትምህርተ ወንጌል) ዘመን ማለት ነው፡፡ ሥርወ ቃሉም “መሀረ – አስተማረ፤ ለመምህር ሰጠ፤ መራ፤ አሳየ፤ መከረ፤ አለመደ” ወይም “ተምህረ – ተማረ፤ ለመደ” የሚለው የግእዝ ግስ ሲሆን፣ ይኸውም የ #እግዚአብሔር ቸርነቱ፣ ርኅራኄው፣ ትዕግሥቱና የማዳን ሥራው በቤተክርስቲያን በስፋት የሚሰበክበት ጊዜ ነው፡፡

#አስተምሕሮ_ቃሉ በሐመሩ

“ሐ” (“አስተምሕሮ” ተብሎ) ሲጻፍ ደግሞ የምሕረት፣ የይቅርታ ዘመን ማለት ነው፡፡ ሥርወ ቃሉም “መሐረ – ይቅር አለ፣ ዕዳ በደልን ተወ” ወይም “አምሐረ – አስማረ፤ ይቅር አሰኘ፤ አራራ፤ አሳዘነ” የሚለው የግእዝ ግስ ነው፡፡ ዘመነ አስተምሕሮ ስለ #እግዚአብሔር ቸርነትና ርኅራኄ፤ እርሱ በደላችንን ሁሉ ይቅር እንደሚለን እኛ ምእመናንም እርስ በእርስ ይቅር መባባል እንደሚገባን ትምህርት የሚሰጥበት ወቅት ነው፡፡

#ዘመነ_አስተምህ(ሕ)ሮ፡ ዘመነ አስተምሕሮ ስለ #እግዚአብሔር ቸርነትና ርኅራኄ፤ እርሱ በደላችንን ሁሉ ይቅር እንደሚለን እኛ ምእመናንም እርስ በእርስ ይቅር መባባል እንደሚገባን ትምህርት የሚሰጥበት ጊዜ ነው፡፡ ይህ ዘመነ አስተምሕሮ ቤተ ክርስቲያን ስለ ልጆቿ ይቅርታ የምትጠይቅበት፤ ምእመናንንም ስለ በደላቸው ይቅርታ የሚጠይቁበት፤ ስለዚህም በስፋት ትምህርት የሚሰጥበት ዘመን ነው፡፡
📌በዘመነ አስተምሕሮ የሚገኙ ሰንበታት፡
በቅዱስ ያሬድ የዜማ መጻሕፍት እንደተቀመጠው በዘመነ አስተምሕሮ ውስጥ የሚገኙ ሰንበታት (እሑዶች) አስተምሕሮ (ኢተዘኪሮ)፣ ቅድስት (ሎቱ ስብሐት)፣ ምኵራብ (አምላክ ፍጹም በሕላዌሁ)፣ መጻጉዕ (ይቤሉ እስራኤል) እና ደብረ ዘይት (ሠርዐ ሰንበተ ለሰብእ እረፍተ) ተብለው ይጠራሉ፡፡ ሳምንታቱን በዚህ መልክ የከፋፈለውም ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ነው (ድጓ ዘአስተምህሮ)፡፡ ከመጀመሪያው ሳምንት (ከአስተምሕሮ) በቀር የአራቱ እሑዶቹ ስያሜ ከዐቢይ ጾም ሰንበታት ጋር አንድ ዓይነት ነው፡፡

#የሰንበታቱ ስያሜ ከዐቢይ ጾም ጋር ተመሳሳይ ነውን? #የዘመነ አስተምህሮ ሰንበታት (እሑዶች) ስያሜ ከዐቢይ ጾም ሰንበታት ስያሜ ጋር ተመሳሳይ ይሁን እንጂ በእነዚህ ሳምንታት ሌሊት የሚዘመሩ መዝሙራት፣ በቅዳሴ ጊዜ የሚነበቡ ምንባባትና የሚቀርቡ ትምህርቶች ግን በይዘትና በምሥጢር ይለያያሉ፡፡ ትምህርቶቹ በምስጢር ይለያያሉ ስንልም በዚህ ወቅት የሚነገረው ምሥጢርና ይዘት በወቅቱ ላይ የሚያተኩር መሆኑን ለመግለጽ ነው እንጂ በየትኛውም ጊዜ በቤተክርስቲያናችን የሚቀርበው ትምህርት አንዱ የ #እግዚአብሔር ቃል ብቻ ነው።

#ዘመነ_ስብከት

➛በነቢያት ጾም ውስጥ ከታህሳስ 7 እስከ ታህሳስ 26 ቀን ያለው ዘመን ዘመነ ስብከት ይባላል፡፡ ዘመነ ስብከት የተባለበት ምክንያትም ነቢያት የ #ጌታን በሥጋ መምጣት አምልተውና አስፍተው በትንቢትና በትምህርት መስበካቸውን ቤተክርስቲያን እያሰበች ሰውን ለማዳን ወደ ምድር የመጣውን አምላክ የምትሰብክበት ወቅት በመሆኑ ነው፡፡

➛ስብከት: የዘመነ ስብከት የመጀመሪያው ሰንበት (እሑድ) ‹‹ስብከት›› ይባላል፡፡ በዚህ ሰንበት በኦሪተ ሙሴ፣ በነቢያትና በመዝሙራት አስቀድሞ ስለ #ክርስቶስ ሥጋን ተዋሕዶ ሰው መሆን ትንቢት ተነግሮ፣ ምሳሌ ተመስሎ፣ ሱባዔ ተቆጥሮ እንደነበር ይነገራል፤ ይሰበካልም፡፡ ስለዚህ ነቢያቱ አስቀድመው መምጣቱን ሰብከው ስለነበር ያንን ለማሰብ ይህ ሰንበት ‹‹ስብከት›› ተባለ፡፡ ስብከት ማለት ሰውን ከ #እግዚአብሔር ጋር የሚያገናኝ ትምህርት ማለት ሲሆን በዚህ ሳምንት ከልደተ አብርሃም እስከ ልደተ ዳዊት ባለው ትውልድ ወስጥ ስለ #ክርስቶስ ሰው መሆን የተሰበከው ስብከት ይታሰባል፡፡

#የነቢያት_ስብከት፦ በስብከት ሰንበት #ጌታችን_መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ሙሴ በሕግ ነቢያትም በትንቢት እንደጻፉለት የሚናገረው ወንጌል ይነበባል (ዮሐ 1፡44)፡፡ ነቢየ #እግዚአብሔር ዳዊትም ‹‹እጅህን ከአርያም ላክ አድነኝም›› (መዝ 143፡7) በማለት ስለ #ክርስቶስ ማዳን በትንቢት መነጽር ተመልክቶ የዘመረው የመዝሙር ክፍል እንዲሁ ይሰበካል፡፡ ከዐበይት ነቢያት አንዱ የሆነው ነቢየ #እግዚአብሔር ኢሳይያስም ‹‹ሰማዮችን ቀድደህ ምነው ብትወርድ! ተራሮችም ምነው ቢናወጡ›› (ኢሳ 64፡1) ብሎ ስለ #ክርስቶስ ከሰማየ ሰማያት መውረድ፣ ከድንግል #ማርያምም መወለድ የተናገረውን ትንቢት ቤተክርስቲያን ትሰብካለች፡፡

#የቤተክርስቲያናችን_ስብከት: ብርሃናተ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ “እኛስ የተሰቀለውን #ክርስቶስን እንሰብካለን” (2ኛ ቆሮ 4፡5) እንዳለው ቤተክርስቲያን በተለይ በዘመነ ስብከት #ጌታችን_መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ለሰው ልጆች የሰጠውንና የፈጸመውን የማዳን ተስፋ ትሰብካለች፡፡ ቅዱስ ያሬድም በመዝሙሩ “ከዓለም በፊት የነበረውንና #መድኃኒት የሆነውን #ወልድን እንሰብካለን” እንዳለ ቤተክርስቲያናችን መቼም ቢሆን መቼ፣ በጊዜውም አለጊዜውም፣ ሲሞላም ሲያጎድልም ስለ ኃጢአታችን የሞተውንና አምላክ #ወልደ_አምላክ የሆነውን #ክርስቶስን ትሰብካለች።

#ብርሀን

➛የዘመነ ስብከት ሁለተኛው ሰንበት ‹‹#ብርሀን›› ይባላል፡፡ ነቢያት የነፍሳችን ብርሀን ይወለዳል ብለው ስለመስበካቸው፣ እውነተኛ ብርሀን ይመጣል ብለው ስለማስተማራቸው የሚታሰብበት ሲሆን በዚሁ #ኢየሱስ_ክርስቶስ አማናዊ ብርሀን መሆኑ ይሰበካል፤ ይዘመራልም፡፡ ከዚሁ ጋር ዘመነ ብሉይ መከራ ሥጋ፣ መከራ ነፍስ የጸናበት የሰው ልጅ ብርሃን ከሆነው አምላክ ጋር የተራራቀበት ስለነበር ነቢያት ያሉበትን ያን ዘመን ጨለማ ብለው በመግለጥ የነፍሳችን ብርሀን ይወለዳል፣ እውነተኛ ብርሃን ይመጣል ብለው ስለመስበካቸው የሚታሰብበት ቀን/ሳምንት/ ነው። በዚህ ሳምንት ከልደተ ዳዊት እስከ ፍልሰተ ባቢሎን የነበረው 14 ትውልድ ይታሰብበታል፡፡

➛የነቢያት ጸሎት: ነቢያት የአምላክን ማዳን ከጠበቁባቸውና፣ ከገለጡባቸው መንገዶች አንዱ ብርሃን ነው፡፡ ልበ አምላክ ክቡር ዳዊትም ወደ ትክክለኛው መንገድ የሚመራ ብርሃን ወደ ዓለም እንዲመጣ “ብርሃንህንና ጽድቅህን ላክ” (መዝ 42፡3) እንዲህ ብሎ ይጸልይ ነበረ፡፡ ይህም ብርሃን፣ ጽድቅ፣ እውነት የሆነውን ልጅህን (ወልድን) ላክልን፤ እርሱ መርቶ ወደ መንግሥተ ሰማያት ያስገባን ዘንድ ማለት ነው (ኢሳ 49)፡፡

#እውነተኛው_ብርሀን: ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ‹‹ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም መጣ›› ብሎ እንደመሰከረው እውነተኛ ብርሀን ስለሆነው ስለ #ኢየሱስ_ክርስቶስ ብርሀንነት የሚሰበክበት ሰንበት ነው›› (ዮሐ 1፡1-11)፡፡ #ጌታችንም በመዋዕለ ስብከቱ ‹‹እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ በጨለማ አይመላለስም›› (ዮሐ 8:12) ብሎ እንዳስተማረው በዚህ ሰንበት ስለ እርሱ ብርሀንነትና ክርስቲያኖችም እርሱን ብርሀናቸው እንዲያደርጉት ይሰበካል፡፡

#የሕይወታችን_ብርሀን: በዚህ ዕለት ‹‹ከብርሀን የተገኘ ብርሀን›› እንዲሁም ‹‹የማይነገር ብርሃን›› የተባለ #ኢየሱስ_ክርስቶስ እውነተኛ ብርሃን መሆኑ ይሰበካል፡፡ ‹‹ብርሃን ወደ ዓለም መጣ›› እየተባለ በቅዱስ ያሬድ መዝሙር ይመሰገናል። እኛም አባቶቻችንን አብነት አድርገን ቅዱስ ኤፍሬምም በሰኞ ውዳሴ #ማርያም እንዳሰተማረን ‹‹በዚህ አለም ለሚኖሩ ሰዎች ሁሉ የምታበራ እውነተኛ ብርሀን ስለሰው ፍቅር ወደ አለም የመጣህ፤ ፍጥረት ሁሉ በመምጣትህ ደስ አለው፡፡ አዳምን ከስሕተቱ አድነኽዋልና፡፡ ሔዋንንም ከሞት ጻዕረኝነት ነጻ አድርገኃታልና። የምንወለድበትን መንፈስ ሰጠኽን፤ ከመላዕክት ጋርም አመሰገንህ›› በማለት የሕይወታችን ብርሀን የሆነውን #አምላካችን_መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስን እናመሰግናለን፡፡

#ኖላዊ

➛የዘመነ ስብከት ሦስተኛው ሰንበት ‹‹#ኖላዊ›› ይባላል፡፡ ኖላዊ ማለት ‹‹እረኛ›› ወይም ‹‹ጠባቂ›› ማለት ሲሆን በዚህ ዕለት ነቢያት የ #እግዚአብሔር ልጅ እውነተኛ ጠባቂ ሆኖ ይገለጣል ብለው መተንበያቸው እና #ኢየሱስ_ክርስቶስ እውነተኛ ጠባቂ መሆኑ ቤተክርስቲያናችን እያሰበች የምትዘምርበት፣ የምትቀድስበት፣ የምታመሰግንበት ዕለት ነው፡፡

➛የእስራኤል ጠባቂ: ነቢያት ራሳቸውንና ሕዝበ እስራኤልን ብሎም ዓለምን እረኛቸው እንደተዋቸው በጎች በመቁጠር ስለ እውነተኛው እረኛ መምጣት ትንቢት ተናግረዋል። በዚህ ሰንበት ከፍልሰተ ባቢሎን እስከ #ልደተ_ክርስቶስ ድረስ ያለው አሥራ አራት ትውልድ የነበረው ሰንበት ይታሰባል። በዚህ ሰንበት ቤተክርስቲያናችን እረኛ የሌለው በግ ተኵላ ነጣቂ እንዲበረታበት በበደሉ ምክንያት ከትጉህ እረኛው የተለየው የሰው ልጅም ሰብሳቢና የሚያሰማራ ጠባቂ እንዲኖረው ነቢያት ዮሴፍን እንደ መንጋ የምትመራ በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ የእስራኤል ጠባቂ ሆይ አድምጥ (መዝ 79፡1) በማለት ይማፀኑ እንደነበር ታስተምራለች።
#ቸር_ጠባቂ: የትንቢቱ ፍጻሜ ሲደርስ #ጌታችን_መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ‹‹መልካም እረኛ እኔ ነኝ፤ መልካም እረኛ ነፍሱን ስለ በጎቹ ያኖራል›› ዮሐ፣ 10፥11 በማለት እውነተኛ እረኛ እርሱ መሆኑን መልስ ሰጥቷል። ስለራሱም ‹‹መልካም እረኛ እኔ ነኝ፥ #አብም እንደሚያውቀኝ እኔም #አብን እንደማውቀው የራሴን በጎች አውቃለሁ የራሴም በጎች ያውቁኛል፤ ነፍሴንም ስለ በጎች አኖራለሁ።›› ዮሐ 10፡15 በማለት አስተምሯል፡፡

➛በልበ አምላክ ክቡር ዳዊትም “ #እግዚአብሔር እረኛዬ ነው የሚያሳጣኝ የለም በለመለመ መስክ ያሳድረኛል መዝ (22፡1) ተብሎ እንደተጻፈ በዚህ የጾም ወቅት አቤቱ ብርሀንህንና ጽድቅህን ላክ፣ ቸሩ እረኛችን ሆይ ተቅበዝብዘናልና እባክህ አስበን፣ የቀዘቀዘው ፍቅራችንን መልስልን፣ አንተ እውነተኛ ሰላምህን ስጠን እያልን ምንም ወደ ማያሳጣን ወደ እውነተኛው እረኛችን ወደ #መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ በንስሐ ልንመለስ ይገባል።

➛ከተኩላዎች ተጠበቁ፦ ለክርስቲያኖች ሁሉ የታመነ ጠባቂ #ጌታችን_መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ነው፡፡ በተጨማሪም ‹‹በጎቼን ጠብቅ›› ብሎ ቅዱስ በጴጥሮስ በኩል አደራ የተሰጣቸው ካህናተ ቤተክርስቲያን የመንጋው ጠባቂ ናቸው፡፡ ነገር ግን በዚህ ሐሰተኛ በበዛበት ዘመን እውነተኞቹን እረኞች ከተኩላዎቹ መለየት ያስፈልጋል፡፡ የምንለያቸውም በፍሬያቸው ነው (ማቴ 7፡15)፡፡ መልካም ዛፍ መልካም ፍሬ እንዲያፈራ መልካም እረኛም ለበጎቹ መልካምን ያደርጋል፡፡ ተኩላ ግን በጎችን ሊጠብቅ ሳይሆን ሊነጥቅ እንደሚመጣ ሐሰተኞች እረኞችም ምዕመናንን ሊጠብቋቸው ሳይሆን ሊነጥቋቸው ይፍጨረጨራሉ፡፡ ነገር ግን መጨረሻቸው ጥፋት ስለሆነ ልናውቅባቸው ይገባል፡፡

✍️በአጠቃላይ በዚህ በገና ጾም ነቢያትም ሐዋርያትም ጾመው በረከት አግኝተውበታል፡፡ እኛ ምእመናንም እንደ እነርሱ በረከትን እናገኝ ዘንድ ይህንን ጾም መጾም እንደሚገባን የቤተክርስቲያን አባቶች ሥርዓት ሠርተውልናል፡፡ በዚህም መሠረት የነቢያት፣ የሐዋርያት፣ የጻድቃንና የሰማዕታት አምላክ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል #ማርያም፣ ከቅዱሳን ነቢያትና ሐዋርያት በረከት እንዲያሳትፈን፤ መንግሥቱንም እንዲያወርሰን ሁላችንም በዚህ በጾመ ነቢያት ወቅት በጾም በጸሎት ተወስነን #እግዚአብሔርን ልንማጸነው ይገባል፡፡
ጾሙን የኃጢአታችን መደምሰሻ መንግስተ ሰማያተን መውረሻ ያድርግልን። የቅዱሳን ነብያት አባቶቻችንንም በረከት በሁላችንም ላይ ያሳድርብን።🙏

#ወስብሐት_ለእግዚአብሔር!!!
#ኅዳር_16

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ኅዳር ዐሥራ ስድስት በዚህች ቀን #የቅዱስ_አቡናፍር ቤተ ክርስቲያኑ የከበረችበት ነው፣ የእስክንድርያ ሀገር ሊቀ ጳጳሳት #ቅዱስ_ዮሐንስ ያረፈበት ነው፣ #ቅዱስ_ኪስጦስ በሰማዕትነት ያረፈበት ነው፣ #ቅድስት_ጣጡስ በሰማዕትነት ያረፈችበት ነው፣ የመነኰስ #አባ_ዳንኤልና_የንጉሥ_አኖሬዎስ የዕረፍታቸው መታሰቢያ ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አቡናፍር

ይኸውም ቅዱስ አቡናፍር ጥቂት የሰሌን ፍሬዎችን ብቻ እየተመገበ በበረሃ ውስጥ 60 ዓመት የኖረ ታላቅ ጻድቅ ነው፡፡ በእነዚህ ድፍን 60 ዓመታት ውስጥ ከቶ የሰውን ፊት አላየም፡፡ ዛሬ ከምስር ከተማ ውጪ የተሠራች ቤተ ክርስቲያኑ የከበረችበት ዕለት ነው፡፡

አቡነ አቡናፍር መልካም ሽምግልና ያለው ስም አጠራሩ የከበረ በገዳም የሚኖርና በገድል የተጠመደ አባት ነው፡፡ ከላይኛው ግብፅ የተገኘ ሲሆን ታሪኩን የተናገረለት ጻዲቁ አባ በፍኑትዮስ ነው፡፡ ይኸውም አባ በፍኑትዮስ ወደ በረሃ ውስጥ በገባ ጊዜ አንዲት የውኃ ምንጭና አንዲት የሰሌን ምንጣፍ አግኝቶ በዚያ እየተጋደለ ብዙ ዘመን የኖረ ነው፡፡

በአንዲት ዕለት አባ በፍኑትዮስ ወደ እርሱ ሲመጣ አባ አቡናፍር አየው፡፡ አባ በፍኑትዮስም የሰይጣንን ምትሐት የሚያይ መስሎት ደነገጠ፡፡ አባ አቡናፍር ፀጉሩና ጽሕሙ ሰውነቱን ሁሉ ሸፍኖታል እንጂ በላዩ ላይ ልብስ አልነበረውም፡፡ አባ በፍኑትዮስንም በ #መስቀል ምልክት ባርኮ አጽናናው፡፡ አቡነ ዘበሰማያትንም ከጸለየ በኋላ ‹‹አባ በፍኑትዮስ ሆይ ወደዚህ መምጣትህ መልካም ነው›› ብሎ በስሙ ከጠራው በኋላ ፍርሃቱን አራቀለት፡፡

ከዚህም በኋላ ሁለቱም በጋራ ጸልየው የ #እግዚአብሔርን ገናናነት እየተነጋገሩ ተቀመጡ፡፡ አባ በፍኑትዮስም አኗኗሩንና እንዴት ወደዚህ በረሃ እንደመጣ ታሪኩን ይነግረው ዘንድ አባ አቡናፍርን ለመነው፡፡ አባ አቡናፍርም ታሪኩን እንዲህ ብሎ ነገረው፡- "እኔ ደጋጎች እውነተኞች መነኮሳት በሚኖሩበት ገዳም ውስጥ እኖር ነበር፡፡ የገዳማውያንን ልዕልናቸውን ሲናገሩ ሲያመሰግኗቸውም ሰማሁ፡፡ እኔም ‹ከእናንተ የሚሻሉ አሉን?› ብዬ ጠየኳቸው፡፡ እነርሱም ‹አዎን እነርሱ በበረሃ የሚኖሩ በ #እግዚአብሔር ዘንድ የከበሩ ናቸው፤ እኛ ለዓለም የቀረብን ስለሆንን ብንተክዝና ብናዝን የሚያረጋጋን እናገኛለን ብንታመም የሚጠይቀንና የፈለግነውን ሁሉ እናገኛለን፣ በበረሃ የሚኖሩ ግን ከዚህ ሁሉ የራቁ ናቸው› አሉኝ፡፡ ይህንንም ስሰማ ልቤ እንደ እሳት ነደደና ወደ ፈቀደው መንገድ ይመራኝ ዘንድ በእኩለ ሌሊት ተነሥቼ ጸለይኩ፡፡ ከዚህም በኋላ ተነሥቼ ወጥቼ ስጓዝ አንድ አባት አገኘሁና የገዳማውያንን ገድላቸውን እያስተማረኝ ከእርሱ ጋር ተቀመጥኩኝ፡፡ ከዚያም ወደዚህ ቦታ ደረስኩ፡፡ #እግዚአብሔር ያዘጋጀልኝን ይህችን ሰሌን አገኘኋት፡፡ በየዓመቱ 12 ዘለላ ታፈራለች፤ ለየወሩም የምመገበው አንዱ ዘለላ ይበቃኛል ውኃም ከዚህች ምንጭ እጠጣለሁ፡፡ በዚህችም በረሃ እስከዛሬ 60 ዓመት ኖርኩ፡፡ ከአንተም በቀር የሰው ፊት ከቶ አይቼ አላውቅም" ብሎ አቡነ አቡናፍር ጣፋጭ ታሪኩን በዝርዝር ነገረው፡፡ ይህንንም ሲነጋገሩ የታዘዘ መልአክ መጥቶ የ #ጌታችንን ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም አምጥቶ አቆረባቸው፡፡ ቀጥለውም ጥቂት የሰሌን ፍሬ ተመገቡ፡፡ ወዲያውም የአቡነ አቡናፍር መልኩ ተለወጠ፤ እንደ እሳትም ሆነ፡፡ ወደ #እግዚአብሔርም በተመስጦ እየጸለየ ሳለ ቅድስት ነፍሱ ከሥጋው ተለየች፡፡

አቡነ በፍኑትዮስም በፀጉር ልብሱ በክብር ገንዞ ቀበረው፡፡ ከዚህም በኋላ አባ በፍኑትዮስ በዚያች ቦታ ይኖር ዘንድ ወደደ ነገር ግን ያቺ የሰሌን ዛፍ ወደቀች፤ የውኃዋም ምንጭ ደረቀች፡፡ አባ በፍኑትዮስም ወደ ዓለም ተመልሶ የገዳማውያንን ዜና ይልቁንም የአባ አቡናፍርን ዜና ይሰብክ ዘንድ የ #እግዚአብሔር ፍቃድ ሆነ፡፡

የአቡነ አቡናፍር ዕረፍታቸው ሰኔ 16 ቀን ነው፡፡ ኅዳር 16 ደግሞ ከምስር ከተማ ውጪ የተሠራች ቤተ ክርስቲያናቸው የከበረችበት ዕለት ነው፡፡

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አባት_አባ_ዮሐንስ

በዚህችም ቀን ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት አርባ ስምንተኛ የሆነ የእስክንድርያ ሀገር ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ አባት አባ ዮሐንስ አረፈ። ይህም ቅዱስ አባት የቆጵሮስ ሀገር ሰው ነው እጅግም ባለጸጋ ነው በእስክንድርያ አገርም የሚኖር ሆነ አባቱ አገረ ገዥ ነበርና ሚስትም አግብቶ ልጆችን ወለደ ከዚህም በኋላ ሚስቱም ልጆቹም ሞቱ።

በዚያንም ጊዜ ገንዘቡን ሁሉ ለድኆችና ለችግረኞች ሰጠ መጸወተ እርሱም መንኵሶ በታላቅ ገድል የተጠመደ ሁኖ በጎ ሥራዎችን ትሩፋትን ጨምሮ በመሥራት #እግዚአብሔርን ደስ አሰኘው።

ከበጎ ሥራዎቹና ከትሩፋቱም ከቀናች ሃይማኖቱ ከአገልግሎቱና ከደግነቱ ከጽድቁ ማማር የተነሣ በግብጽ አገር የሚኖሩ ኤጲስቆጶሳት ሁሉም ተሰማምተው ይዘው ወሰዱት ያለ ፈቃዱም በእስክንድርያ አገር ላይ ሊቀ ጵጵስና ሾሙትና በወንጌላዊ ቅዱስ ማርቆስ ወንበር ላይ አስቀመጡት ። ያን ጊዜ የከበረ ወንጌልን አነበበ በሹመቱና በክህነቱም ብርሃን ተገለጸ ብዙዎች ድንቆች የሆኑ ተአምራትንም አደረገ።

ለድኆችና ለችግረኞች ሁልጊዜ ያለማቋረጥ የሚሹትን የሚሰጣቸው ሆነ ስለዚህም የሚራራ ዮሐንስ ተብሎ ተጠራ ። በአይሁድና በአረማውያን ዘንድ የሚአስፈራ ሆነ በመጽሐፈ ገድሉ እንደተጻፈ እጅግ ይፈሩትና ያከብሩት ነበርና መንጋዎቹንም በበጎ አጠባበቅ ጠበቃቸው #እግዚአብሔርንም አገልግሎ በሰላም አረፈ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በአባ ዮሐንስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ኪስጦስ

በዚችም ቀን ቅዱስ ኪስጦስ በመኰንኑ በመክሲሞስ እጅ በሰማዕትነት አረፈ ። ይህንንም ቅዱስ ኪስጦስን መኰንኑ በያዘው ጊዜ ጽኑዕ ሥቃይን አሠቃየው ከዚህም በኋላ ራሱን በሰይፍ ቆረጠ የሰማዕትነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_ጣጡስ

በዚችም ዕለት በሮሜ አገር በከሀዲ መኰንን በእስክንድሮስ እጅ ቅድስት ጣጡስ በሰማዕትነት አረፈች። ወደርሱም በአቀረቧት ጊዜ እስክንድሮስ ለአማልክት ሠዊ አላት እርሷም ከፈጠረኝ ከ #ጌታዬ_ከኢየሱስ_ክርስቶስ በቀር አልሠዋም ብላ መለሰች።

መኰንኑም የፊቷን መሸፈኛ እንዲገልጡ አዘዘ ውበቷንም አይቶ አደነቀ ዐይኖቿ እንደ አጥቢያ ኮከብ ናቸውና ቁመቷም እንደ ዘንባባ ደም ግባቷም እንደ ጽጌረዳ ነው በዚያንም ወራት የሚመሳሰላት የለም ነበር።

ንጉሡም በአያት ጊዜ እርሷን በመውደዱ ልቡ ተነጠቀ እንዲህም አላት እሺ በይኝና ለታላቅ አምላክ ለአጵሎን ሠዊ እኔም ለቤተ መንግሥቴ እመቤት አደርግሻለሁ አላት። ቅድስት ጣጡስም እኔ ክብር ይግባውና ከ #ክርስቶስ ከመንጋዎቹ ውስጥ ነኝ ከእርሱ በቀር ለሌላ አልሠዋም ነገር ግን ወደ አማልክቶችህ መሠዊያ ቤት ገብቼ ኃይላቸውን እንዳይ ፍቀድልኝ አለችው።
በዚያንም ጊዜ ወሰዷት በገባችም ጊዜ ጣዖታቱ ይጠፉ ዘንድ ክብር ይግባውና የኃይል ባለቤት ወደ ሆነ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ጸለየች ወዲያውኑ ንውጽውጽታ ሁኖ ጣዖታቱ ከመቀመጫቸው ወድቀው ተሰባበሩ ታላቁ አምላካቸው አጵሎንም ቊልቊል ወድቆ ተቀጠቀጠ ከጣዖቱ አገልጋዮችም ብዙዎች ሞቱ በአጵሎን ላይ አድሮ የሚኖር ርኩስ መንፈስ እንዲህ ብሎ ጮኸ።

ጣጡስ ሆይ እኔ ካንቺ ምን አለኝ አንቺስ ከእኔ ምን አለሽ እነሆ ማደሪያዬን ቀጥቅጠሽ ከእርሱ አውጥተሽኛልና ንጉሡም ይህን አይቶ ተቆጣ በግምባርዋ ደፍተው በበትሮች እንዲደበድቧት በአለንጋዎችም እንዲገርፏት አዘዘ። ከሥጋዋም በወተት አምሳል ነጭ ደም ፈሰሰ ወደ #እግዚአብሔርም በለመነች ጊዜ የሚደበድቧትን የ #እግዚአብሔር መላእክት የሚያሠቃዩአቸው ሆኑ ቅድስት ጣጡስን ግን ሥቃያቸው የማይነካት ሆነ።

ሁለተኛዋም ለተራበ አንበሳ እንዲሰጧት ንጉሡ አዘዘ። አንበሳውም በደረሰ ጊዜ በፊቷ ሰገደ የእግሮቿንም ትቢያ ላሰ ከሰማይም እኔ ካንቺ ጋር ነኝና ንጽሕት ጣጡስ ሆይ ደስ ይበልሽ የሚል ቃል መጣ። ንጉሡም ከክፉ ነገር የደረሰባት እንደሌለ አይቶ ራሷን በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘ ተጋድሎዋንም ፈጸመች።

በሌሊትም የሮሜ ጳጳስ መጥቶ በከበሩ ልብሶች ገነዛት በወርቅና በብር ከተለበጠ የእብነ በረድ ሣጥን ውስጥ ጨመራትና በአማረ ቦታ አኖራት ከሥጋዋም ብዙዎች ተአምራቶች ተገለጡ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ ጣጡስ በጸሎቷ ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#መነኰስ_አባ_ዳንኤልና_ንጉሥ_አኖሬዎስ

በዚህችም ዕለት የመነኰስ አባ ዳንኤልና የንጉሥ አኖሬዎስ የዕረፍታቸው መታሰቢያ ነው። ይህ አባ ዳንኤል ታላቅ ገድለኛ ነው እንጀራን ዓሣንም ቢሆን ማርንም ዘይትንም ቢሆን ከብቻው ቅጠል በቀር ሳይቀምስ አርባ ዓመት ተኩል በአስቄጥስ ገዳም ኖረ።

ከብዙ ዘመንም በኋላ የመመካት ኀሳብ መጣበት በልቡም እንደእኔ ትርሕምትን መቆምን የታገሠ በገዳም በውኑ አለን አለ ። ሰውን የሚወድ #እግዚአብሔርም ብርሃናዊ መልአኩን ላከለት መልአኩም ዳንኤል ሆይ በጎ ያልሆነ እንዲህ ያለ ትምክህትን ለምን ትመካለህ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ከትሕትና በቀር ትምክህትን አይሻምና አለው።

አባ ዳንኤልም መልአኩን ጌታዬ ከኔ የሚሻል ካለ ንገረኝ ወደርሱ ሒጄ አየው ዘንድ በመመካቴም ወደ ፈጣሪዬ እለማመጥ ዘንድ አለው መልአኩም ንጹህ ቅዱስ #እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው የሮሜና የቁስጥንጥንያ ንጉሥ አኖሬዎስ በመንግሥተ ሰማያት ባልንጀራህ ነው አለው።

አባ ዳንኤልም በሰማ ጊዜ በምድር ላይ ተደፋ በራሱም ላይ አመድ ነስንሶ ክብር ይግባውና በአምላካዊ ጥበብ ወደ ሮሜ አገር አድርሶ እርሱን አኖሬዎስን ያሳየው ዘንድ #ጌታችንን ለመነው።

እንዲህ ሲጸልይም ደመና መጣች ተሸከመችውና ከሮሜ ንጉሥ ከአኖሬዎስ ቤተ መንግሥት ደጅ አደረሰችው የንጉሥ አኖሬዎስንም ረዳት አገኘው ረድኡም እጅ ነስቶ ከእርሱ ቡራኬ ተቀበለና አባቴ ሆይ ወደዚህ የመጣህበት ጉዳይህ ምንድን ነው አለው ።

አባ ዳንኤልም ልጄ ሆይ የሚቻልህ ከሆነ ከሀገር መኳንንት ወዳንዱ አድርሰኝና ወደ ንጉሡ እንዲአስገባኝ አለው ። ረዳቱም እኔ ባስገባህ መግባትን አትሻምን አለው ልጄ ሆይ እሻለሁ አስገባኝ #እግዚአብሔር ይባርክህ አለው ። ዳግመኛም ረድኡ አባቴ ሆይ ሟች የሆነ ንጉሥን በማየት ምን ታገኛለህ አለው አባ ዳንኤልም ፈጣሪዬ ባያዘኝ ወደዚህ ባልመጣሁ ነበር አለው ረዳቱም ለጌታዬ የሚያሻውን እስከምገዛ ጥቂት ታገሠኝ አለው ።

በዚያንም ጊዜ አምባሻ ጨውና መጻጻ የጎመን ቅጠልም ገዝቶ ወደ ጌታው ወደ ንጉሡና ወደ መምህሩ አውሎጊስ ወሰደ አባ ዳንኤልንም በውጭ ተወው ። ንጉሡም ረዳቱን አንተ አላዋቂ ነህን አባ ዳንኤልን በውጭ የምታስቆመው አለው ይህንንም ብሎ ንጉሡ ከመምህሩ ከአውሎጊስ ጋር ወጣ ለአባ ዳንኤልም ሰገዱለት ሰላምታም ተሰጣጥተው ወደ ቤተ መንግሥት አስገቡትና በአንድነት ተቀመጡ ።

ዘጠኝ ሰዓትም በሆነ ጊዜ ረዳቱ የሚበሉትን አቀረበላቸው በአንድነትም ተነሥተው ጸለዩ አባ ዳንኤልም እንዳይታመም እንጀራ መብላትን ፈርቶ ጌቶቼ እንጀራ ባለመብላቴ በእኔ ላይ አታጒረምርሙ እንዳልታመም ፈርቼ ነው እንጂ በትዕቢት አይደለም አላቸው ። ቅጠልንም ሰጡት ማዕዳቸውንም ፈጽመው ጸሎትን ጸለዩ ከዚህም በኋላ ንጉሥ አኖሬዎስ አባ ዳንኤልን ስለ አመጣጡ መረመረው አባ ዳንኤልም ወንድሜ ሆይ የሚቻልህስ ከሆነ ወደ ንጉሡ አሰገባኝ በ #ጌታ_ክርስቶስ ትእዛዝ መጥቻለሁንና አለው ንጉሡም ነገ አስገባሃለሁ አለው ።

በማግሥቱም ቅዱስ አኖሬዎስ ዐይን የሚበዘብዝ ልብሰ መንግሥቱን ለብሶ በዙፋኑ ላይ ተቀመጠ አባ ዳንኤልንም አስገቡት በአየውም ጊዜ ፈርቶ ተንቀጠቀጠ ረዳቱም መፍራቱን አይቶ ወደ ማደሪያው መለሰው ንጉሡም ችሎቱን ሲጨርስ ልብሰ መንግሥቱን ጥሎ የምንኲስናውን ልብስ ለብሶ አባ ዳንኤል ወዳለበት ገባ አባ ዳንኤልም በአየው ጊዜ ወንድሜ ሆይ በልቤ ያለውን ነግሬው ወደ ቦታዬ እመለስ ዘንድ ወደ ንጉሥ ለምን አላስገባኝም አለው ቅዱስ አኖሬዎስም አባቴ ሆይ አልገባህምን ለዚች ምድር ንጉሥ ብለው የሰየሙኝ በኃላፊ ዙፋንም ላይ ተቀምጨ ያየኸኝ እኔ አኖሬዎስ ነኝ አለው።

አባ ዳንኤልም በሰማ ጊዜ ከእግሩ በታች ሰገደለት አኗኗሩን ሁሉ ይነግረው ዘንድ ክብር ይግባውና በ #ጌታችን ስም አማፀነው ንጉሥ አኖሬዎስም በእጅ ሥራው ደክሞ ከሚያገኘው በቀር ይህም ሰሌን መታታት ነው ሳይበላ ሳይለብስ አርባ ዓመት እንደሆነው የሚተርፈውንም ለድኆች እንደሚሰጥ ምግቡም እንጀራና ጨው ቅጠል መጻጻ እንደሆነ የማንንም ገንዘብ ለመቀማት እዳልደፈረ ድንግልናውንም እንደጠበቀ ነገረው።

አባ ዳንኤልም ከእግሩ በታች ወድቆ በአንተ ላይ ስለተመካሁ ይቅር በለኝ አለው ከዚህም በኋላ አባ ዳንኤል ፈጽሞ እያዘነ ወደ ቦታው ተመለሰ።

ከሁለት ወሮችም በኋላ መምህሩ አውሎጊስን ተሰናብቶ ቅዱስ አኖሬዎስ ከቤተ መንግሥቱ ውስጥ ወጣ #እግዚአብሔርም መልአኩን ላከለትና ተሸክሞ ወደ አባ ዳንኤል አደረሰው። በተጋድሎም በመጠመድ ኑረው ገድላቸውንም ፈጸመው በአንዲት ዕለት አረፉ። እንዲሁም አውሎጊስና ረዳቱ በዚያች ዕለት በአንድነት አረፉ።

#ለእግዚአብሔርም ምሰጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን ።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ኅዳር_16 እና #ከገድላት_አንደበት)
2025/01/08 16:47:24
Back to Top
HTML Embed Code: