Telegram Web Link
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ኅዳር_10_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሮሜ 2
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ ስለዚህ፥ አንተ የምትፈርድ ሰው ሁሉ ሆይ፥ የምታመካኘው የለህም፤ በሌላው በምትፈርድበት ነገር ራስህን ትኰንናለህና፤ አንተው ፈራጁ እነዚያን ታደርጋለህና።
² እንደዚህም በሚያደርጉት ላይ የእግዚአብሔር ፍርድ እውነተኛ እንደ ሆነ እናውቃለን።
³ አንተም እንደዚህ በሚያደርጉ የምትፈርድ ያንም የምታደርግ ሰው ሆይ፥ አንተ ከእግዚአብሔር ፍርድ የምታመልጥ ይመስልሃልን?
⁴ ወይስ የእግዚአብሔር ቸርነት ወደ ንስሐ እንዲመራህ ሳታውቅ የቸርነቱንና የመቻሉን የትዕግሥቱንም ባለጠግነት ትንቃለህን?
⁵ ነገር ግን እንደ ጥንካሬህና ንስሐ እንደማይገባ ልብህ የእግዚአብሔር ቅን ፍርድ በሚገለጥበት በቍጣ ቀን ቍጣን በራስህ ላይ ታከማቻለህ።
⁶ እርሱ ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው ያስረክበዋል፤
⁷ በበጎ ሥራ በመጽናት ምስጋናንና ክብርን የማይጠፋንም ሕይወት ለሚፈልጉ የዘላለምን ሕይወት ይሰጣቸዋል፤
⁸ ለዓመፃ በሚታዘዙ እንጂ ለእውነት በማይታዘዙትና በአድመኞች ላይ ግን ቍጣና መቅሠፍት ይሆንባቸዋል።
⁹ ክፉውን በሚያደርግ ሰው ነፍስ ሁሉ መከራና ጭንቀት ይሆንበታል፥ አስቀድሞ በአይሁዳዊ ደግሞም በግሪክ ሰው፤
¹⁰ ነገር ግን በጎ ሥራ ለሚያደርጉ ሁሉ ምስጋናና ክብር ሰላምም ይሆንላቸዋል፥ አስቀድሞ ለአይሁዳዊ ደግሞም ለግሪክ ሰው።
¹¹ እግዚአብሔር ለሰው ፊት አያዳላምና።
¹² ያለ ሕግ ኃጢአት ያደረጉ ሁሉ ያለ ሕግ ደግሞ ይጠፋሉና፤ ሕግም ሳላቸው ኃጢአት ያደረጉ ሁሉ በሕግ ይፈረድባቸዋል፤
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ጴጥሮስ 3
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹-² እንዲሁም፥ እናንተ ሚስቶች ሆይ፥ ከባሎቻችሁ አንዳንዱ ለትምህርት የማይታዘዙ ቢኖሩ፥ በፍርሃት ያለውን ንጹሑን ኑሮአችሁን እየተመለከቱ ያለ ትምህርት በሚስቶቻቸው ኑሮ እንዲገኙ ተገዙላቸው።
³ ለእናንተም ጠጕርን በመሸረብና ወርቅን በማንጠልጠል ወይም ልብስን በመጎናጸፍ በውጭ የሆነ ሽልማት አይሁንላችሁ፥
⁴ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ የዋህና ዝግተኛ መንፈስ ያለውን የማይጠፋውን ልብስ ለብሶ የተሰወረ የልብ ሰው ይሁንላችሁ።
⁵ እንዲህ በቀድሞ ዘመን በእግዚአብሔር ተስፋ ያደረጉት ቅዱሳት ሴቶች ደግሞ ለባሎቻቸው ሲገዙ ተሸልመው ነበርና፤
⁶ እንዲሁም ሣራ ለአብርሃም፦ ጌታ ብላ እየጠራችው ታዘዘችለት፤ እናንተም ከሚያስደነግጥ ነገር አንዳች እንኳ ሳትፈሩ መልካም ብታደርጉ ልጆችዋ ናችሁ።
⁷ እንዲሁም፥ እናንተ ባሎች ሆይ፥ ደካማ ፍጥረት ስለ ሆኑ ከሚስቶቻችሁ ጋር በማስተዋል አብራችሁ ኑሩ፤ ጸሎታችሁ እንዳይከለከል አብረው ደግሞ የሕይወትን ጸጋ እንደሚወርሱ አድርጋችሁ አክብሩአቸው።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 17
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
³⁰ እንግዲህ እግዚአብሔር ያለማወቅን ወራት አሳልፎ አሁን በየቦታቸው ንስሐ ይገቡ ዘንድ ሰውን ሁሉ ያዛል፤
³¹ ቀን ቀጥሮአልና፥ በዚያም ቀን ባዘጋጀው ሰው እጅ በዓለሙ ላይ በጽድቅ ሊፈርድ አለው፤ ስለዚህም እርሱን ከሙታን በማስነሣቱ ሁሉን አረጋግጦአል።
³² የሙታንንም ትንሣኤ በሰሙ ጊዜ እኵሌቶቹ አፌዙበት፥ እኵሌቶቹ ግን፦ ስለዚህ ነገር ሁለተኛ እንሰማሃለን አሉት።
³³ እንዲሁም ጳውሎስ ከመካከላቸው ወጣ።
³⁴ አንዳንዶች ወንዶች ግን ተባብረው አመኑ፤ ከእነርሱ ደግሞ በአርዮስፋጎስ ያለው የፍርድ ቤት ፈራጅ ዲዮናስዮስ ደማሪስ የሚሉአትም አንዲት ሴት ሌሎችም ከእነርሱ ጋር ነበሩ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ኅዳር_10_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇🌹

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"ወቀጻዕክዋ በጾም ለነፍስየ። ወኮነኒ ጽዕለተ። ለበስኩ ሠቀ ወኮንክዎሙ ነገረ"። መዝ 68፥10-11።
"ነፍሴን በጾም አስመረርሁአት፥ ለስድብም ሆነብኝ። ማቅ ለበስሁ ምሳሌም ሆንሁላቸው"። መዝ.68፥10-11።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ኀዳር_10_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ማቴዎስ 25
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ በዚያን ጊዜ መንግሥተ ሰማያት መብራታቸውን ይዘው ሙሽራውን ሊቀበሉ የወጡ አሥር ቆነጃጅትን ትመስላለች።
² ከእነርሱም አምስቱ ሰነፎች አምስቱም ልባሞች ነበሩ።
³ ሰነፎቹ መብራታቸውን ይዘው ከእነርሱ ጋር ዘይት አልያዙምና፤
⁴ ልባሞቹ ግን ከመብራታቸው ጋር በማሰሮአቸው ዘይት ያዙ።
⁵ ሙሽራውም በዘገየ ጊዜ ሁሉ እንቅልፍ እንቅልፍ አላቸውና ተኙ።
⁶ እኩል ሌሊትም ሲሆን፦ እነሆ፥ ሙሽራው ይመጣል፥ ትቀበሉት ዘንድ ውጡ የሚል ውካታ ሆነ።
⁷ በዚያን ጊዜ እነዚያ ቆነጃጅት ሁሉ ተነሡና መብራታቸውን አዘጋጁ።
⁸ ሰነፎቹም ልባሞቹን፦ መብራታችን ሊጠፋብን ነው፤ ከዘይታችሁ ስጡን አሉአቸው።
⁹ ልባሞቹ ግን መልሰው፦ ምናልባት ለእኛና ለእናንተ ባይበቃስ፤ ይልቅስ ወደሚሸጡት ሄዳችሁ ለራሳችሁ ግዙ አሉአቸው።
¹⁰ ሊገዙም በሄዱ ጊዜ ሙሽራው መጣ፥ ተዘጋጅተው የነበሩትም ከእርሱ ጋር ወደ ሰርግ ገቡ፥ ደጁም ተዘጋ።
¹¹ በኋላም ደግሞ የቀሩቱ ቈነጃጅት መጡና፦ ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ፥ ክፈትልን አሉ።
¹² እርሱ ግን መልሶ፦ እውነት እላችኋለሁ፥ አላውቃችሁም አለ።
¹³ ቀኒቱንና ሰዓቲቱን አታውቁምና እንግዲህ ንቁ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
✝️✝️✝️ 🌹
 የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #ቅዱስ_ዮሐንስ_ወልደ_ነጎድጓድ ነው። መልካም የሠላሳ ስድስቱ ቅዱሳት አንስት በዓል። ለሁላችንም ይሁንልን።
🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ኅዳር_11

#ቅድስት_ሐና

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ኅዳር ዐሥራ አንድ በዚች ዕለት አምላክን ለወለደች ለእመቤታችን ቅድስት #ድንግል_ማርያም እናቷ የሆነች የተመሰገነች የቅድስት #ሐና የዕረፍቷ መታሰቢያ ነው።

ይችም ቅድስት ከኢየሩሳሌም አገር ከሌዊ ነገድ ከካህኑ አሮን ትውልድ የሌዊ የሜልኪ ልጅ ለሆነ ለማጣት ልጁ ናት። ለማጣትም ሦስት ሴቶች ልጆች አሉት የታላቂቱም ስሟ ማርያም ናት ሁለተኛዋም ስሟ ሶፍያ ሦስተኛዪቱም ስሟ ሐና ናት ታላቂቱ ማርያምም ለባል ተድራ አዋላጅ የሆነች ሰሎሜን ወለደቻት እርሷም #መድኃኒታችንን ከወለደችበት ጊዜ ጀምሮ በስደቷም ወራት ከአረጋዊ ቅዱስ ዮሴፍ ጋር እመቤታችንን #ድንግል_ማርያምን ያገለገለቻት ናት።

ሶፍያም ለባል ተድራ ለመጥመቁ ቅዱስ ዮሐንስ እናቱ የሆነች ቅድስት ኤልሳቤጥን ወለደቻት። ይችንም ቅድስት ሐናን ከይሁዳ ነገድ ለሆነ ጻድቅ ስሙ ኢያቄም ለሚባል አጋቧትና እመቤታችንን ቅድስት #ድንግል_ማርያምን ወለደቻት እሊህም ሰሎሜና ኤልሳቤጥ ለቅድስት ሐና የእኅትማማች ልጆች ናቸው።

የዚችንም የቅድስት ሐናን በሥውር የምትሠራውን ገድሏንና ትሩፋቷን እንዳናስታውሰው አናውቀውም ግን ከሴቶች ሁሉ እንደምትበልጥና እንደምትከብር እናውቃለን እንረዳለን እርሷ አምላክን በሥጋ ለወለደችው ወላጅዋ ትሆን ዘንድ የተገባት ሁናለችና ከሴቶች ሁሉ የሚበልጥና የሚበዛ ትሩፋትና ተጋድሎ ባይኖራት ይህ ታላቅ ጸጋ ባልተገባት ነበር።

ይህችም ጻድቅት ሐና መካን በመሆንዋ ልጅን ይሰጣት ዘንድ ወደ #እግዚአብሔር ዘወትር በጸሎት ትማልድ ነበር #እግዚአብሔርም በእርሷ ለዓለም ሁሉ ድኅነት የተደረገባትን ይቺን የተባረከችና የከበረች ልጅን ሰጣት እርሷም አምላክን የወለደች እመቤታችን #ድንግል_ማርያም ናት።

ስለዚህም ይህን ታላቅ ጸጋ ስለሰጣት የበዓሏን መታሰቢያ በደስታ ልናከብር ይገባናል።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን በጸሎቷ የሚገኝ በረከቷም ከእኛ ጋር ይሁን ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ኅዳር_11)
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ኅዳር_11_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ጢሞቴዎስ 5
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁵ ብቻዋንም ኖራ በእውነት ባልቴት የምትሆን በእግዚአብሔር ተስፋ ታደርጋለች፥ ሌትና ቀንም በልመና በጸሎትም ጸንታ ትኖራለች፤
⁶ ቅምጥሊቱ ግን በሕይወትዋ ሳለች የሞተች ናት።
⁷ ያለ ነቀፋ እንዲሆኑ ይህን ደግሞ እዘዝ።
⁸ ነገር ግን ለእርሱ ስለ ሆኑት ይልቁንም ስለ ቤተ ሰዎቹ የማያስብ ማንም ቢሆን፥ ሃይማኖትን የካደ ከማያምንም ሰው ይልቅ የሚከፋ ነው።
⁹ ባልቴት በመዝገብ ብትጻፍ ዕድሜዋ ከስድሳ ዓመት እንዳያንስ፥ የአንድም ባል ሚስት የነበረች እንድትሆን ያስፈልጋል፤
¹⁰ ልጆችን በማሳደግ እንግዶችንም በመቀበል፥ የቅዱሳንንም እግሮች በማጠብ፥ የተጨነቁትንም በመርዳት በጎንም ሥራ ሁሉ በመከተል፥ ይህን መልካም ሥራ በማድረግ የተመሰከረላት ልትሆን ይገባል።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ጴጥሮስ 3
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁵ እንዲህ በቀድሞ ዘመን በእግዚአብሔር ተስፋ ያደረጉት ቅዱሳት ሴቶች ደግሞ ለባሎቻቸው ሲገዙ ተሸልመው ነበርና፤
⁶ እንዲሁም ሣራ ለአብርሃም፦ ጌታ ብላ እየጠራችው ታዘዘችለት፤ እናንተም ከሚያስደነግጥ ነገር አንዳች እንኳ ሳትፈሩ መልካም ብታደርጉ ልጆችዋ ናችሁ።
⁷ እንዲሁም፥ እናንተ ባሎች ሆይ፥ ደካማ ፍጥረት ስለ ሆኑ ከሚስቶቻችሁ ጋር በማስተዋል አብራችሁ ኑሩ፤ ጸሎታችሁ እንዳይከለከል አብረው ደግሞ የሕይወትን ጸጋ እንደሚወርሱ አድርጋችሁ አክብሩአቸው።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 16
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁴ ከትያጥሮን ከተማም የመጣች ቀይ ሐር ሻጭ እግዚአብሔርን የምታመልክ ልድያ የሚሉአት አንዲት ሴት ትሰማ ነበረች፤ ጳውሎስም የሚናገረውን ታዳምጥ ዘንድ ጌታ ልብዋን ከፈተላት።
¹⁵ እርስዋም ከቤተ ሰዎችዋ ጋር ከተጠመቀች በኋላ፦ በጌታ የማምን እንድሆን ከፈረዳችሁልኝ፥ ወደ ቤቴ ገብታችሁ ኑሩ ብላ ለመነችን፤ በግድም አለችን።
¹⁶ ወደ ጸሎት ስፍራም ስንሄድ፥ የምዋርተኝነት መንፈስ የነበረባት ለጌቶችዋም እየጠነቈለች ብዙ ትርፍ ታመጣ የነበረች አንዲት ገረድ አገኘችን።
¹⁷ እርስዋ ጳውሎስንና እኛን እየተከተለች፦ የመዳንን መንገድ የሚነግሩአችሁ እነዚህ ሰዎች የልዑል አምላክ ባሪያዎች ናቸው ብላ ትጮኽ ነበር።
¹⁸ ይህንም እጅግ ቀን አደረገች። ጳውሎስ ግን ተቸገረና ዘወር ብሎ መንፈሱን፦ ከእርስዋ እንድትወጣ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አዝሃለሁ አለው፤ በዚያም ሰዓት ወጣ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ኅዳር_11_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"አዋልደ ንግሥት ለክብርከ። ወትቀውም ንግሥት በየማንከ። በአልባሰ ወርቅ ዑጽፍት ወኊብርት"። መዝ.44÷9
“የንጉሦች ሴት ልጆች ለክብርህ ናቸው፤ በወርቅ ልብስ ተጐናጽፋና ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች።” መዝ.44÷9
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ኅዳር_11_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሉቃስ 18
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ ሳይታክቱም ዘወትር ሊጸልዩ እንዲገባቸው የሚል ምሳሌን ነገራቸው፥
² እንዲህ ሲል፦ በአንዲት ከተማ እግዚአብሔርን የማይፈራ ሰውንም የማያፍር አንድ ዳኛ ነበረ።
³ በዚያችም ከተማ አንዲት መበለት ነበረች፥ ወደ እርሱም እየመጣች፦ ከባላጋራዬ ፍረድልኝ ትለው ነበር።
⁴ አያሌ ቀንም አልወደደም፤ ከዚህ በኋላ ግን በልቡ፦ ምንም እግዚአብሔርን ባልፈራ ሰውንም ባላፍር፥
⁵ ይህች መበለት ስለምታደክመኝ ሁልጊዜም እየመጣች እንዳታውከኝ እፈርድላታለሁ አለ።
⁶ ጌታም አለ፦ ዓመፀኛው ዳኛ ያለውን ስሙ።
⁷ እግዚአብሔር እንኪያስ ቀንና ሌሊት ወደ እርሱ ለሚጮኹ ለሚታገሣቸውም ምርጦቹ አይፈርድላቸውምን?
⁸ እላችኋለሁ፥ ፈጥኖ ይፈርድላቸዋል። ነገር ግን የሰው ልጅ በመጣ ጊዜ በምድር እምነትን ያገኝ ይሆንን?
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️ የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #እመቤታችን_የማርያም_ቅዳሴ ነው። መልካም የ #ቅድስት_ሐና የዕረፍት በዓል። ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#የአያቶች_ቀን - #ኅዳር_11

እናትነት ጸጋ ነው:: አባትነትም ደስታ ነው:: ከሁለቱ በላይ ደግሞ አያት መሆን ይበልጣል:: ልጅን ከማየት የበለጠ የልጅ ልጅን የማየት ደስታ እጅግ ትልቅ ነው:: እናት ለልጅዋ ከምታሳየው ፍቅር የአያት ፍቅር የሚበልጠው በአያት እጅ ያደጉ ልጆች ስስትና እንክብካቤ የሚበዛባቸው ለዚህ ነው:: ወላጆች የሚቆጡት ልጅ አያት ሥር የሚደበቀው ለዚህ ነው::

የአባቶችና የእናቶች ቀን እንደሚታሰበው ሁሉ አብልጦ ሊታሰብ የሚገባው የአያቶች ቀን ነው:: ዕድሜ ቢጫናቸው እንኳን ለልጅ ልጆቻቸው ፈገግታቸው የማይደበዝዝ በዕድሜያቸው ፀሐይ መጥለቂያ ሳይደክማቸው ፍቅር የሚሠጡ የፍቅር ጥግ ማሳያዎች አያቶች ናቸው::

ዛሬ በቤተ ክርስቲያን የአያቶች ቀን በታላቅ ድምቀት እየተከበረ ነው:: በምድር ካሉ አያቶች ሁሉ የሚበልጡት አያቶች ቅድስት ሃና እና ቅዱስ ኢያቄም የሚታሰቡበት ክብረ በዓል ነው:: #ድንግል_ማርያም ከእናቶች ሁሉ እንደምትበልጥ ወላጆችዋም ከአያቶች ሁሉ ይበልጣሉ:: እርስዋን የ #አምላክ_እናት ብለን እንደምናከብር እነርሱንም የ #አምላክ_አያቶች ብለን እናከብራቸዋለን::
በመለኮቱ አባት እንጂ አያት ለሌለው ለ #መድኃኔ_ዓለም_ክርስቶስ አያቶቹ የሆኑ ቅዱሳን ሐና እና ኢያቄም እጅ ክቡራን ናቸው::

ሐና ሰማይን ወለደች ልጅዋ ፀሐይን ወለደች:: ሐና ምንጭን ወለደች ልጅዋ የሕይወትን ውኃ ወለደች:: በ #ጌታ የዘር ሐረግ ውስጥ የተቆጠሩ ሁሉ ክቡራን ናቸው የመጨረሻዎቹ አያቶቹ ደግሞ የመጨረሻው ክብር ይገባቸዋል::

ቅዱሳን ሃና እና ኢያቄም የልጅ ልጄ የሚሉት ፈጣሪያቸውን ነው:: እርግጥ ነው በሕይወት ቆይተው ቀድሞ በሕልም አይተው ያልተረዱትን የልጃቸውን ልጅ #ክርስቶስን አቅፈው ለመሳም አልታደሉም:: ሆኖም ድል አድራጊው የልጅ ልጃቸው የሲኦልን መዝጊያ ሰብሮ ነፍሳትን ሲያወጣ አያቶቹንም አውጥቶአቸዋልና ልጃቸው የወለደችውን ፀሐይ በሲኦል ሲያበራ አይተው ሕልማቸው ተፈትቶአል::

(ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ)
#ቅድስት_ሐና
ሐና የሚለውን ስም እስከ #ክርስቶስ መምጣት በቅዱሳት መጻሕፍቱ ለአራት የከበሩ አንስት በስመ ተጸውኦነት መጠሪያ ሆኖ መገለጹን እንረዳለን።
① እመ ሳሙኤል ፣ ብእሲተ ኤፍሬማዊ ሕልቃና ሐና ፣
② እመ ጦቢያ ፣ ብእሲተ ጦቢት (ዘእምነገደ ንፍታሌም) ሐና፣
③ ወለተ ፋኑኤል (ዘእምነገደ አሴር) ነቢይት ሐና ፣ እና
④ ወለተ ማጣት (ዘእምነገደ ሌዊ) ብእሲተ ቅዱስ ኢያቄም ቅድስት ሐና
ከእኒህ ሐናት («ሐናውያት») ሁሉ እጅግ የከበረችውና ለወላዲተ አምላክ እናቷ ለ #ክርስቶስ የሥጋ ልደት አያቱ የሆነችው ቅድስት ሐና የማርያም (የቅድስት ሰሎሜ እናት) እና የሶፍያ (የቅድስት ኤልሳቤጥ እናት) እሕታቸው ናት።
ሐና ለሚለው ስም የእብራይስጡ ሐናህ ( חַנָּה) መነሻ ነው ጸጋ ሥጦታ ፣ ሀብት በረከት ማለት ነው።
መጻሕፍቱም ይሕችን የአዳም ዘር ሀብት የፍጹም በረከት የበጎ ሥጦታ መገኛ እንዲህ እየገለጡ በምስጋና ተባብረው ያከብሯታል ፦
🍀 "ወለዛቲ ቅድስት ሐና ኢያእመርነ ገድላቲሃ ወትሩፋቲሃ ዘትገብሮን በኅቡእ ከመንዝክሮን ዳእሙ ነአምር ወንጤይቅ ከመ ይእቲ ተአቢ ወትከብር እምኩሎን አንስት እስመ ለዛቲ ደለዋ ትኩን ወላዲታ ለወላዲተ አምላክ በሥጋ ወለእመ ኢኮና ላቲ ትሩፋት ብዙኃት ወገድል ዐቢይ ዘይፈደፍድ እምገድለ ኵሎን አንስት እምኢደለዋ ዝንቱ ጸጋ ዐቢይ"
.(ስንክሳር ዘሕዳር ፲፩)
የዚህችን ቅድስት ሐናን በስውር የምትሠራውን ገድሏንና ትሩፋትዋን እንዳናስታውሰው አናውቀውም። ግን ከሴቶች ሁሉ እንደምትበልጥና እንደምትከብር እናውቃለን እንረዳለን እርሷ አምላክን በሥጋ ለወለደች ወላጅዋ ትሆን ዘንድ የተገባች ሁናለችና ከሴቶች ሁሉ የሚበልጥና የሚበዛ ትሩፋትና ተጋድሎ ባይኖራት ይህ ታላቅ ጸጋ ባልተገባት ነበር
━━━━━━━━━✦✿✦━━━━━━━━
🍀 ሰላም ለኪ ለጸሎተ ኵሉ ምዕራጋ፡
ከመ አስካለ ወይን ዲበ ሐረጋ፡
ሐና ብፅዕት ተፈሥሒ እንበለ ንትጋ፡
እስመ ረከብኪ ሞገሰ ወአድማዕኪ ጸጋ፡
እምሔውተ አምላክ ትኩኒ በሥጋ፡፡
(ዐርኬ ዘሕዳር ፲፩)
ሰላም ላንቺ ይሁን ሐና : መንገድ ለሁሉ ጸሎት
ልክ እንደ ወይን ነሽና : በሐረጓ ላይ ፍሬ እንዳላት ብፅዕት ሐና ሆይ ደስ ይበልሽ : ያለ ነቀፋ ያለ ጉድለት ሞገስን ብታገኚ ከአምላክ : ጸጋው ቢሆንሽ ጉልላት ለመሆን የበቃሽ ሆነሻል : በሥጋ የአምላክ አያት
━━━━━━━━━✦✿✦━━━━━━━━
🍀 ወኮና ኤልሳቤጥ ወሰሎሜ ወሐና አዋልደ አሐቲ ብእሲት። ወዛቲ ቅድስት ሐና እስመ ኮነት ክብርተ እምኔሆን ኵሎን አንስተ ዓለም እስመ ኮነት ድሉተ ከመ ትለዳ ለወላዲተ አምላክ በሥጋ ወአዕሚሮ ጽድቃ ወክብራ እምኵሎን አንስት
.(ድርሳነ ኢያቄም ወሐና ዘረቡዕ ቁ ፶፩)
ኤልሳቤጥ ሰሎሜና ሐናም የእኅትማማች ልጆች ናቸው ይህች ቅድስት ሐናን ግን ጽድቋንና ከሴቶች የሚበልጥ ክብሯን አውቆ በሥጋ አምላክን ለወለደች ለ #ድንግል_ማርያም እናት ለመሆን የተገባች አደረጋት። ከሴቶች ሁሉ የተከበረች ናት።
━━━━━━━━━✦✿✦━━━━━━━━
🍀 ሰላም ለፀአተ ነፍስኪ እምኀላዌ ሥጋ ተዋህዶታ ኀበ ተስፋ ሕይወት ተሠርዓ ወተደለወ በበፆታ ሊተ ሐና ለነፍስየ አመ ፀዓታ
አስተዳልዊ አስበ ዚአየ ከመ ታስተዳሉ ማርታ
ማዕደ ፈቃድ ለክርስቶስ በቤታ
.(መልክአ ሐና)
በሥጋ ተዋሕዶ በዚህ ዓለም ከመኖር በየክፍሉ ወደተዘጋጀ ተስፋ ሕይወት ለነፍስሽ መውጣት ሰላም እላለሁ
#ቅድስት_ሐና_ሆይ ነፍሴ ከሥጋዬ በተለየች ጊዜ ማርታ ለ #ክርስቶስ ማዕድን በቤትዋ እንዳዘጋጀች ለእኔም በአማላጅነትሽ ዋጋዬን አዘጋጂልኝ
━━━━━━━━━✦✿✦━━━━━━━━
🍀 ሰላም ለነፍሳቲክም እለ እም ሥጋ ፈለሳ
ከመ በሰማያት ይንግሣ ኢያቄም ወሐና ብርሃናት ዘደወለ ምሕሳ በረከተ ሥጋክሙ ወነፍስክሙ ዘኢይበጽሖ ኀሠሣ ለነፍሰ ዚአየ አንብሩ በርእሳ
.(መልክአ ኢያቄም ወሐና)
ከሥጋችሁ የተለየች ትነግሥ ዘንድ በሰማያት
ለነፍሳችሁ ሰላም እላለሁ ነፍሳችሁ ክብርት ናት ወሰንና መስፈሪያ ኢያቄምና ሐና ብርሃናት
ፍለጋው የማይደረስበት የሥጋና የነፍሳችሁ በረከት በኔም ላይ እንዲያድርብኝ በነፍሴ ራስ ላይ አኑሩት
━━━━━━━━━✦✿✦━━━━━━━━
ሰላም ለሕፅንከ ምርፋቀ ንጽሕና ወቅድስና
አዕዳዊከኒ ዘርኅቁ እምርስሐተ ጌጋይ ወሙስና ኢያቄም አቡነ መራሔ ሕይወት ዖፈ ብርጋና አበዊነ እስራኤል ከመ ተሴሰዩ መና
ሴስዩነ ከመ እሉ ኢያቄም ወሐና
.(መልክአ ኢያቄም)
የቅድስናና የንጽሕና ማረፊያ ለሆነው ፡ ሰላም እላለሁ ላንተ እቅፍ እጆችህ የራቁ ናቸው ፡ ከጥፋትና በበደል ከማደፍ ወደሕይወት የምትመራን ፡ ኢያቄም የብርጋና ወፍ
መና እንደበሉ አባቶቻንን ፡ የሲናን በረሀ ለማለፍ ኢያቄምና ሐናም እንደነርሱ ፡ መግቡን ነፍሳችን እንድታርፍ
━━━━━━━━━✦✿✦━━━━━━━━
🍀 ወበዛቲ ዕለት በዓልኪ ንበል በልሳነ ሥጋ ወኅሊና፡ እንዘ ናነክር በዜና፡ እመሰ ተመክሐት ብእሲቱ ለሕልቃና፡ በረኪበ ሳሙኤል ፍሬ ማኅፀና፡ እፎኬ ፈድፋደ ይሤኒ ትምክሕት በእምኪ ሐና፡ ዘፈረየት ኪያኪ ተስፋ ልቡና፡
እስመ ኢያቄም አቡኪ ዘሐፀና፡ አኮ ዘረከበኪ እምኔሃ በውርዝውና፡
አላ እምድኅረ ልህቀት ወርስዕና፡ አሜን፡
(ነገረ ማርያም ዜና ጽንሰታ ብራና)
በዚች በበዓልሽ ቀን : በሥጋና በኅሊና አንደበት በነገሩ እንደነቅበት የማፀኗ ፍሬ ሳሙኤል : ልጇ ሆኖ ስለተሰጣት ለሕልቃና ሚስት ለሐና : መመኪያዋ ሆናት መመካትስ እጅግ የሚልቀው : በቅድስት ሐና ነው ባንቺ እናት የልባችን ተስፋ የምትሆኝ : አንቺ ፍሬዋ ሆንሻት አባትሽ ኢያቄም : ጠብቆ ያሳደጋት
ከእርሷ የተቀበለሽ : መች ሆነና በወጣትነት
ካረጀች በኋላ ነው እንጂ : ሙቀት ልምላሜ ከተለያት ።
━━━━━━━━━✦✿✦━━━━━━━━
#መድኃኔዓለም አያት
#ድንግል_ማርያም እናት
ለቅድስት ሶፍያና ለቅድስት ማርያም እሕት
ለቅድስት ሰሎሜና ለቅድስት ኤልሳቤጥ አክስት ከምትኾን ከቅድስትና ብፅዕት #ሐና ከዕረፍቷ መታሰቢያ ረድዔትና በረከት ያሳድርብን።

☞ መጋቤ ሐዲስ ቴዎድሮስ በለጠ (ዶክተር)
#ኅዳር_12

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ኅዳር ዐሥራ ሁለት በዚች ቀን የመላእክት አለቃ #ቅዱስ_ሚካኤል የበዓሉ መታሰቢያ ነው፣
#ቅዱስ_ሚካኤል_ኢያሱን እንደ የተረዳበት ቀን ነው፣ #ለቅዱሳኑ_ዱራታኦስ_እና_ቴዎብስታ #ቅዱስ_ሚካኤል ተዓምር ያደረገበት ነው፣ #የባህራን_ቀሲስ መታሰቢያ ነው፣ የኢትዮጵያ ንጉሥ #የጻድቁ_በእደ_ማርያም የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው፣ የሊቀ ጳጳሳት #ቅዱስ_አባት_ፊላታዎስ እረፍቱ ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ሚካኤል_ሊቀ_መላዕክት

ኅዳር ዐሥራ ሁለት በዚች ቀን ለሰው ወገን የሚያዝንና የሚራራ በ #እግዚአብሔር ጌትነት ዙፋን ፊት ሁልጊዜ በመቆም ለፍጥረቱ ሁሉ የሚማልድ የመላእክት አለቃ በሰማያትም ለሚኖሩ ኃይሎች ሁሉ አለቃቸው ለሆነ ለ #ቅዱስ_ሚካኤል የበዓሉ መታሰቢያ ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ኢያሱ_ወልደ_ነዌ

ዳግመኛ በዚህች ዕለት #ቅዱስ_ሚካኤል ኢያሱን የተረዳበት ቀን ነው።

ይህም በንጉሥ ጭፍራ አምሳል በታላቅ ክብር ሁኖ የነዌ ልጅ ኢያሱ ያየው ነው ከእኛ ሰዎች ወገን ነህን ወይስ ከጠላቶቻችን ወገን ነህ አለው። እኔስ የ #እግዚአብሔር ሠራዊት አለቃ ነኝ አሁንም ወዳንተ መጥቻለሁ አለው ።

ኢያሱም ወደ ምድር በግንባሩ ተደፍቶ ሰገደለትና በእኔ በባሪያህ ዘንድ ምን አቁሞሃል አለው ። የ #እግዚአብሔር የሠራዊቱም አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ኢያሱን የቆምክባት ምድር የከበረች ቦታ ናትና ጫማህን ከእግርህ አውልቅ አለው ቅዱስ ኢያሱም እንዳለው አደረገ ።

#እግዚአብሔርም ኢያሱን እንዲህ አለው በውስጧ ያለውን ንጉሧን ከኃያላኑና ከአርበኞቹ ጋር በእጃችሁ ኢያሪኮን እነሆ አስገባታለሁ ። ይህም የከበረ መልአክ ከቅዱሳን ሰማዕታት ጋር በመሆን ገድላቸውን እስከ ሚፈጽሙ የሚያጸናቸውና የሚያስታግሣቸው ነው ።

ስለዚህም ስለ ልዕልናውና ስለ አማላጅነቱ በየወሩ በዐሥራ ሁለት ቀን ለመታሰቢያው በዓል ተሠራለት እርሱ ስለ እኛ የምድሩን ፍሬ ይባርክልን ዘንድ ዝናሙንም በጊዜው እንዲአወርድልን የወንዙንም ውኃ እንዲመላልን ነፋሱንም የምሕረት ነፋስ እንዲአደርግልን ሁሉንም የተስተካከለ እንዲአደርግልን ወደ #እግዚአብሔር በጸሎት ይማልድልናልና።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱሳን_ዱራታኦስና_ቴዎብስታ

ቅዱሳኑ ዱራታኦስ እና ቴዎብስታ የቅዱስ ሚካኤል ወዳጆች ናቸውና በዚህች ዕለት ይታሰባሉ።

እንዲህም ሆነ የ #እግዚአብሔር ወዳጅ የሆነ ስሙ ዱራታዎስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ የሚስቱም ስም ቴዎብስታ ነው እነርሱም ሁልጊዜ ያለ ማቋረጥ የዚህን የከበረ መልአክ የ ቅዱስ ሚካኤልን የበዓሉን መታሰቢያ ያደርጉ ነበር ከዚህም በኋላ በሀገር ውስጥ ችግር በሆነ ጊዜ ገንዘባቸው አለቀ ለዚህም የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ለበዓሉ መታሰቢያ የሚያደርጉት አጡ ዱራታዎስም ሽጦ ለበዓሉ መታሰቢያ ያደርገው ዘንድ የእርሱን ልብስና የሚስቱን ልብስ ይዞ ወጥቶ ሔደ ።

የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልም በታላቅ መኰንን አምሳል ለዱራታዎስ ተገለጠለት ወደ ባለ በጎች ሒዶ በእርሱ ዋስትና በአንድ ዲናር አንድ በግ እንዲወስድ ሁለተኛም ወደ ዓሣ አጥማጅ ሒዶ አንድ ዓሣ እንዲወስድ ግን መልአኩ ወደ ቤቱ ሳይደርስ የዓሣውን ሆድ እንዳይቀድ ወደ ባለ ሥንዴም እንዲሔድና የሚሻውን እንዲሁ በርሱ ዋስትና እንዲወስድ አዘዘው ዱራታዎስም ቅዱስ ሚካኤል እንዳዘዘው አደረገ ።

ወደ ቤቱም በተመለሰ ጊዜ በረከትን ሁሉ ቤቱ ተመልቶ አገኘው ። እጅግም አደነቀ የዚህንም የከበረ መልአክ የበዓሉን መታሰቢያ እንዳስለመደ አደረገ ። የተራቡ ድኆችን ሁሉንም ጠርቶ መገባቸውና ወደየቤታቸው አሰናበታቸው።

ከዚህም በኃላ ለዱራታዎስና ለሚስቱ ቅዱስ ሚካኤል ሁለተኛ ተገለጠላቸው ። ዱራታዎስንም የዓሣውን ሆድ እንዲሠነጥቅ አዘዘው ። በሠነጠቀውም ጊዜ ሦስት መቶ የወርቅ ዲናር በዓሣው ሆድ ተገኘ ። ቅዱስ ሚካኤልም ዱራታዎስንና ቴዎብስታን እንዲህ አላቸው ከዚህ ዲናር ወስዳችሁ ለባለ በጉ ለባለ ዓሣውና ለባለ ሥንዴው ዕዳችሁን ክፈሉ የቀረውም ለፍላጎታችሁ ይሁናችሁ #እግዚአብሔር አስቧችኋልና በጎ ሥራችሁን መሥዋዕታችሁንና ምጽዋታችሁን አስቦ በዚህ ዓለም አሳመረላችሁ ። በኋላኛውም መንግሥተ ሰማያትን አዘጋጅቶላችኋል ።

እነርሱም ሲሰሙ ስለዚህ ነገር ደነገጡ። እርሱም ከመከራችሁ ሁሉ ያዳንኳችሁ የመላእክት አለቃ እኔ ሚካኤል ነኝ መሥዋዕታችሁንና ምጽዋታችሁን ወደ #እግዚአብሔር ፊት ያሳረግሁ እኔ ነኝ አሁንም በዚህ ዓለም ከበጎ ነገር እንድታጡ አላደርጋችሁም አላቸው ። ይህንንም ብሎ ወደ ሰማያት ወጣ ። እነርሱም ሰገዱለት ተአምራቱም የማይቁጠር ብዙ ነው ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በከበረ መልአክ ጸሎትና አማላጅነት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ባህራን_ቀሲስ

ዳግመኛም በዚህች እለት የባህራን ቀሲስ መታሰቢያ ነው።
የዚህ የከበረ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ተአምራቱ ብዙዎች ናቸው ። ከእነርሱም አንዱ ይህ ነው ። #እግዚአብሔርን የሚፈራ አንድ ሰው ነበረ አርሱም የከበረ የሚካኤልን የበዓሉን መታሰቢያ በየወሩ በዐሥራ ሁለተኛው ቀን ይልቁንም በሰኔና በኅዳር ወር አብልጦ ያከብር ነበር ። በጐረቤቱም ርኅራኄ የሌለው አንድ ባለጠጋ ሰው ነበረ ። ይህን #እግዚአብሔርን የሚፈራውን ሰው የከበረ መልአክ የሚካአልን በዓል በሚያደርግበት ጊዜ ይጠላውና ያቃልለው ነበር ለድኆች ስለ መራራቱም ይዘባበትበት ነበረ ። የሕይወቱ ዘመንም ተፈጽሞ የሚሞትበትና ከዚህ ከኃላፊው ዓለም ድካምም የሚያርፍበት ጊዜ ሲቀርብ የክብር መልአክ ቅዱስ ሚካኤልን የበዓሉን መታሰቢያ ታደርግ ዘንድ ምጽዋት ሰጭም ትሆን ዘንድ ሚስቱን አዘዛት ።

ከዚህም በኋላ አረፈና ገንዘው ቀበሩት ሚስቱም ፀንሳ ነበረች የመውለጃዋ ጊዜም ደርሶ ምጥ ያዛት በታላቅ ጭንቀት ውስጥ ሳለችም እንዲህ ብላ ጸለየች የ #እግዚአብሔር መልአኩ ሆይ ራራልኝ በእርሱ ዘንድ ባለሟልነት አለህና በ #እግዚአብሔር ዘንድ ስለ እኔ ለምንልኝ ። ይህንንም በአለች ጊዜ በቤቷ ውስጥ ብርሃን በራ ከችግርም ዳነች መልኩ ውብ የሆነ ወንድ ልጅንም ወለደች የ #እግዚአብሔርም መልእክተኛ ቅዱስ ሚካኤል ከሰማይ ወርዶ ሕፃኑን እንዲህ ብሎ ባረከው ርኅራኄ የሌለውን የዚህን ባለጸጋ ገንዘብና ሀብት ጥሪቱንም ሁሉ ይህ ሕፃን እንዲወርስ #እግዚአብሔር አዝዟል ባለጸጋውም በቤቱ በዐልጋው ላይ ሳለ #ጌታ ጆሮውን ከፍቶለት ይህን ነገር ከመልአኩ ሰማ ።

ይህንንም በሰማ ጊዜ ታላቅ ኀዘን ደረሰበት ሕፃኑንም የሚገድልበትን ምክንያት ይፈልግ ጀመረ ነገር ግን ክብር ይግባውና #ጌታ ይጠብቀው ነበር ። ከዚህም በኋላ ያ ባለጸጋ ምክንያት አዘጋጅቶ የሚያገለግለኝ ልጅ ይሆነኝ ዘንድ ልጅሽን ስጪኝ እኔም እየመገብኩና እያለበስኩ አሳድገዋለሁ ለአንቺም ሃያ ወቄት ወርቅ እሰጥሻለሁ አላት ።

ይህንንም ነገር ከባለጸጋው በሰማች ጊዜ ስለችግሯ እጅግ ደስ አላት ልጅዋንም ሰጠችው እርሱም ሃያውን ወቄት ወርቅ ሰጣት ልጅዋንም ወሰደው የምሻው ተፈጸመልኝ ብሎ ደስ አለው ።

ከዚህም በኋላ በልጁ ቁመት ልክ ሣጥን አሠርቶ ሕፃኑን በሣጥኑ ውስጥ አስገብቶ ዘጋበት እስከ ባሕርም ተሸክመው ወስደው በባሕር ጣሉት ክብር ይግባውና በ #ጌታችን ፈቃድ ያ ሣጥን ሳይሠጥም ከዚያች አገር የሃያ ቀን መንገድ ያህል ርቃ ወደምትገኝ ወደ አንዲት አገር ወደብ እስከሚደርስ በባሕሩ ላይ ተንሳፈፈ ።
በባሕሩም አካባቢ በጎቹን አሰማርቶ የሚጠብቅ አንድ ሰው ነበረና ሣጥኑን በውኃ ላይ ተንሳፎ አየው እርሱም ከባሕሩ አውጥቶ ወደ ቤቱ ወሰደው ይህንም ሣጥን እንዴት እንደሚከፍተው ያስብ ጀመረ ይህንም ሲያስብ ወደ ባሕሩ ይሔድ ዘንድ #ጌታችን በልቡናው ኃሳብ አሳደረበት ወዲያውኑም ተነሥቶ ወደ ባሕሩ ሔደና አንድ ዓሣ የሚያጠምድ ሰው አገኘ ።

ዓሣ አጥማጁንም መረብህን በኔ ስም ጣል ለሚያዘውም ዓሣ ዋጋውን እሰጥሃለሁ አለው አጥማጁም እንዳለው አደረገ ያን ጊዜም ታላቅ ዓሣ ተያዘ ዋጋውንም ሰጥቶ ዓሣውን ተቀበለ ዓሣውንም ይዞ ወደቤቱ ሔደ ለራትም ይጠብሰው ዘንድ አረደው በሆዱም ውስጥ መክፈቻ አገኘ ። በልቡም ይህ መክፈቻ ይህን ሣጥን ይከፍተው ይሆን አለ በሣጥኑ ቀዳዳም በአስገባው ጊዜ ፈጥኖ ተከፈተ በውስጡም ይህን ታናሽ ብላቴና አገኘ ። ልጅ የለውም ነበርና ታላቅ ደስታ ደስ አለው #ጌታችንንም አመሰገነው። ሕፃኑንም በመልካም አስተዳደግ አሳደገው ሕፃኑም አድጎ ጐልማሳ ሆነ ።

ከብዙ ዘመናትም በኋላ ያ ባለ ጸጋ ተነሥቶ ወደዚያ አገር ሔደ በመሸም ጊዜ ወደ በግ ጠባቂው ደጅ ደረሰ በግ ጠባቂውን እስከ ነገ የምናድርበት ማደሪያ በአንተ ዘንድ እናገኛለን ኪራዩንም እሰጥሃለሁ አለው በግ አርቢውም እንዳልክ ይሁንና እደር አለው ባለጸጋውም በዚያ አደረ ።

ራት በሚቀርብም ጊዜ ሕፃኑን ባሕራን ብሎ ጠራው ባለጸጋውም ሰምቶ ልጅህ ነውን ብሎ ጠየቀው በግ ጠባቂውም አዎን ታናሽ ሕፃን ሆኖ ሳለ ከባሕር አግኝቼዋለሁና #እግዚአብሔር የሰጠኝ ልጄ ነው አለው ባለጸጋውም በምን ዘመን አገኘኸው አለው እርሱም ከሃያ ዓመት በፊት ብሎ መለሰለት ። ያን ጊዜም እርሱ ወደ ባሕር የጣለው መሆኑን አውቆ እጅግ አዘነ ።

በማግሥቱም ጎዳናውን ሊጓዝ በተነሣ ጊዜ ሰይጣናዊ ምክንያት አመካኝቶ በግ ጠባቂውን እንዲህ አለው ዕገሊት ወደምትባል አገር በቤቴ የረሳሁት ጉዳይ ስለ አለ እንድልከው ልጅህን ትሰጠኝ ዘንድ እሻለሁ እኔም የድካም ዋጋውን ሃያ ወቄት ወርቅ እሰጥሃለሁ አለው ። የብላቴናውም አባት ስለ ገንዘቡ ደስ ብሎት ልጁ ባሕራንን ሰጠው እንዲህም ብሎ አዘዘው ልጄ ባሕራን ይህ የከበረ ሰው ስለ ጉዳዩ ወደ ቤቱ ይልክህ ዘንድ ና ወደ ቤትህም በሰላም ትመለሳለህ ። ባሕራንም አባቴ ሆይ እሽ በጎ ያዘዝከኝን ሁሉ አደርጋለሁ አለ ።

ያን ጊዜም ባለጸጋው ወደ መጋቢው እንዲህ ብሎ ደብዳቤ ጻፈ ይችን ደብዳቤ በምታነባት ጊዜ ደብዳቤዋን ይዞ የመጣውን ገድለህ በጉድጓድ ውስጥ ጣለው ማንም አይወቅ በመካከላቸውም የሚተዋወቁበትን ምልክት ጽፎ አሸጋት ። ለባሕራንም ሰጠው ለመንገዱም የሚሆነውን ስንቅ ሰጠው ባሕራንም ተነሥቶ ጉዞውን ጀመረ ሲጓዝም ሰንብቶ የአንዲት ቀን ጐዞ ሲቀረው እነሆ የመላእክት አለቃ የከበረ መልአክ ቅዱስ ሚካኤል በንጉሥ ጭፍራ አምሳል በነጭ ፈረስ ላይ ተቀምጦ አንተ ጐልማሳ የያዝኸው ምንድነው አለው ወደ ዕገሌ አገር ወደ ቤቱ ለማድረስ ከአንድ ባለጸጋ የተጻፈች መልእክት ናት አለው ያቺን ደብዳቤ አሳየኝ አለው እርሱም ስለ ፈራ ሠጠው ።

በዚያን ጊዜም የከበረው መልአክ ቅዱስ ሚካኤል ያቺን የሞት መልእክት ደመሰሳት በእርሷ ፈንታም በንፍሐት ለውጦ እንዲህ ብሎ ጻፈ ይቺን ደብዳቤ ይዞ ለመጣ ባሕራን ለሚባል ሰው ይቺ ደብዳቤ ደርሳ በምትነበብበት ጊዜ ልጄ እገሊትን አጋቡት በውስጥና በውጭ ያለ ንብረቴንና ጥሪቴን ወንዶችና ሴቶች ባሮቼን ጠቅላላ ንብረቴንም አውርሼዋለሁና የፈለገውንም ሊያደርግ ሥልጣን ሰጥቼዋለሁና እኔን አትጠብቁኝ ። እኔ ብዙ እዘገያለሁ የኔ ሹም ዕገሌ ሆይ በእኔና በአንተ መካከል ይቺ ምልክት እነኋት ከዚህ በኋላ አሽጐ ለባሕራን ሰጠውና ወደ ባለጸጋው ቤት ሒደህ ይቺን ደብዳቤ ለሹሙ ሰጠው በጎዳናም እኔ እንደ ተገናኘሁህ አትንገረው እንዳይገድልህም ይህን የሞት ደብዳቤ ለውጬልሃለሁ አለው ። ባሕራንም እሺ ጌታዬ ያዘዝኽኝን ሁሉ አደርጋለሁ አለ ።

ባሕራንም ወደ ባለጸጋው ቤት በደረሰ ጊዜ ያቺን ደብዳቤ ለሹሙ ሰጠው በአነበባትም ጊዜ በመካከላቸው ያለውን ምልክት አገኘ አስተውሎም አርግጠኛ እንደሆነ አወቀ ። ከዚህም በኋላ ለባሕራን ሠርግ አዘጋጅቶ እንደሚገባ በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት በተክሊል የባለጸጋውን ልጅ አጋቡት ። አርባ ቀን ያህልም ደስታና ሐሴት እያደረጉ ኖሩ ።

ከዚህ በኋላ ባለጸጋው ከሔደበት መመለሻው ጊዜ ሁኖ በደስታ የሆነውን የመሰንቆና የእንዚራ ድምፅ ሰምቶ ይህ የምሰማው ምንድነው ብሎ ጠየቀ እነርሱም ስሙ ባሕራን ለተባለ የአንተን ደብዳቤ ላመጣ ጐልማሳ ሰው ልጅህ ዕገሊትን አጋቡት እነሆ ለአርባ ቀናት በሠርግ ላይ ነው ። ገንዘብህንና ጥሪትህን ሁሉ ወንዶችና ሴቶች ባሮችህን አንተ እንዳዘዝክ ሰጥተውታል አሉት ። ይህንንም በሰማ ጊዜ ደንግጦ ከፈረሱ ላይ ወደቀ በድንገትም ሞተ ።

ባሕራንም በጎ ሥራዎችን የሚሠራ ሆነ የተገለጸለትና ከመገደል ያዳነው የመላእክት አለቃ የከበረ መልአክ ቅዱስ ሚካኤል እንደሆነ ሊገድለው የሚሻውን የባለጸጋውን ጥሪቱን ሁሉ ያወረሰውም እርሱ እንደ ሆነ ተረዳ የዚህንም የከበረ መልአክ የመላእክት አለቃ ሚካኤልን መታሰቢያ በየወሩ ያደርግ ጀመረ ቤተ ክርስቲያንም ሠራለት የቅዱስ ሚካኤልንም ሥዕሉን አሥሎ በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ አደረገው ከእርሱም ብዙዎች ድንቆች ተአምራቶች ተገለጡ ባሕራንም ቅስና ተሹሞ እስከ ዕለተ ሞቱ በዚያች ቤተክርስቲያን ውስጥ የሚያገለግል ሁኖ ኖረ በዚህ በከበረ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል አማላጅነት ከእናቱና ከአባቱ ከልጆቹም ጋራ የዘላለም ሕይወትን ወረሰ ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ጻድቁ_በእደ_ማርያም

በዚችም ቀን የኢትዮጵያ ንጉሥ የጻድቁ በእደ ማርያም የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው ።

በዕደ ማርያም" ማለት "በማርያም እጅ" እንደ ማለት ነው:: እኒህ ሰው የኢትዮዽያ ንጉሥ ሲሆኑ የነገሡትም በ1460 ዓ/ም ነው:: ደጉ አባታቸው አፄ ዘርዓ ያዕቆብ ሲያርፉ በመንግስቱ ተተክተው ሃገራችንን አስተዳድረዋል:: ድርሰት ደርሰዋል:: አብያተ መቅደስ አንጸዋል::

በተለይ ለቅኔ ትምሕርት ማበብ ልዩ የሆነ አስተዋጽኦ እንዳደረጉ ይነገራል:: ልክ በነገሡ በ10 ዓመታቸው ግን መንግስተ ምድር በቃኝ ብለው በምናኔ በርሃ ገብተዋል:: በዙፋናቸውም አፄ እስክንድር ተተክተዋል:: ጻድቁ ንጉሥ ግን ቅዱስ ሚካኤልን ይወዱት ነበርና በዚህች ቀን ዐርፈዋል::

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አባት_ፊላታዎስ

በዚችም ቀን ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ስልሳ ሦስተኛ የሆነ የእስክንድርያ አገር ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ አባት ፊላታዎስ አረፈ። በሹመቱ ወራትም የኢትዮጵያ ንጉሥ ወደ ኖባ ንጉሥ ወደ ጊዮርጊስ እንዲህ ብሎ የመልእክት ደብዳቤ ጻፈ ወንድሜ ሆይ ከሊቀ ጳጳሳት ቆዝሞስ ጊዜ ጀምሮ ለረጅም ጊዜ ጳጳስ ስለ ሌለን እኛ በታላቅ ችግር ውስጥ እንዳለን ዕወቅ ።

ይህም የሆነው ተንኰለኛው ሚናስ በተንኰልና በሐሰት ነገር የከበረ ጳጳሳችንን ጴጥሮስን ከሹመቱ ወንበር እንዲሰደድ ስለ አደረገው ነው። ስለዚህ አምስት ሊቃነ ጳጳሳት እስቲአልፉ ለሀገራችን ጳጳስ አልተላከልንም ።
አሁንም ስለ #እግዚአብሔር ብለህ ስለ ቀናች ሃይማኖትም በድካም ከእኛ ጋር አንድ በመሆን ስለእኛ ወደ ግብጽ ሊቀ ጳጰሳት ወደ ቅዱስ ፊላታዎስ ጳጳስ ይልክልን ዘንድ ከራስህ ደብዳቤ እንድትጽፍለት እለምንሃለሁ የሚል ነበር ።

በዚያንም ጊዜ የኖባ ንጉሥ ጊዮርጊስ ለኢትዮጵያ አገር ጳጳስን ይሾምላቸው ዘንድ የልመና ደብዳቤ ወደ አባ ፊላታዎስ ጻፈ ይህ ቅዱስ ፊላታዎስም ልመናውን ተቀብሎ ከአስቄጥስ ገዳም ስሙ ዳንኤል የሚባል አንድ ጻድቅ መነኰስ አስመጣ እርሱን ጵጵስና ሹሞ ወደ ኢትዮጵያ አገር ላከው ወደ እነሱም በደረሰ ጊዜ የኢትዮጵያ ሰዎች በታላቅ ደስታ ተቀበሉት ። በዚህም አባት ፊላታዎስ ዘመን ብዙ ተአምራት ተገልጠዋል በሰላምም አረፈ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በሊቀ መላእክት #ቅዱስ_ሚካኤል እና በቅዱሳን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ኅዳር_12 እና #ዲያቆን_ዮርዳኖስ_አበበ)
2024/12/28 20:11:29
Back to Top
HTML Embed Code: