Telegram Web Link
🌹#ጥቅምት_28 #እንኳን_ለአምላክ_ወሰብእ#ቅዱስ_አማኑኤል አመታዊ በዓል በሰላም አደረሰን!!🌹

"የምስራቁ ነፋስ አንበጣዎችን አመጣ።"
ዘጸአት 10፤13
የበዓሉ መሰረትና ታሪክ ይህ ነው
በወርሐ ጥቅምት እንዲህ ሆነ በሱዳን በኩል የመጣ አንበጣ የኢትዮጵያን ምድር ከል መስሎ ወረሳት የተዘራው ሳይሰበሰብ  የአንበጣ እራት ሊሆን ሆነ። ንጉሠ ሸዋ ሣህለ ሥላሴ ወደ ታላቁና ተአምረኛው ሚጣቅ #ቅዱስ_አማኑኤል  ደብር ሄደው እንባቸውን በእጃቸው አቁተው አዝነው አምላኬ #ቅዱስ_አማኑኤል የመጣው የአንበጣ መንጋ ከጠፋ ሕዝቤ ከሰቀቀን ድኖ የዘራውን አጭዶ ከጎተራ ካገባ በአዋጅ ነጋሪት ጎስሜ ቀንደ መለከት አስነፍቼ ድብ አንበሳ ነጋሪት አስመትቼ ታቦትህን በካህናቱ አስወጥቼ አከብራለሁ ብለው ስዕለት ያደርጋሉ የአንበጣው መንጋ ሰማይ ያርግ ምድር ይስረግ ሳይታወቅ አንድ ሰብል ሳያጠፋ ከኢትዮጵያ ምድር ይጠፋል በዓሉም በዚያ ምክንያት ተጀመረ የአባቶቻችን ስም ላለመጥራት ታሪክ አናድበስብስ መሰረቱ ይህ ነው።

በበዓሉ የሚከብረው ስሙ የሚወደሰውም  ወሰብእ #ቅዱስ_አማኑኤል ነው ቸርነቱ የተገለጠበት ተአምራቱ የታየባት እምርት እለት።

አምላካችን በቸርነቱ ይመልከተን ምድራችንን የወረረውን የዘረኝነት አንበጣ ያጥፋልን በየልቦናችን ያቆምነውን የዘረኝነት ጣኦት በኃይለ መለኮቱ ያቅልጥልን አስተዋይ ለሕዝብ የሚያስብ መሪ አይንሳን እኛንም ገባርያነ ሰላም ያድርገን ከዘረኝነት ደዌ ከፍቅር ረሐብ ከዝሙት እሳት ከምንፍቅና አሽክላ ይሰውረን በፈቃዳቸው ላበዱ ፈውስን ብረት ላነሱ ትዕግስቱን ያድልልን አሜን አሜን አሜን!
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ጥቅምት_28_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ዕብራውያን 6
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁹ ስለ እናንተ ግን፥ ወዳጆች ሆይ፥ ምንም እንኳ እንዲሁ ብንናገር፥ አብልጦ የሚሻለውና ለመዳን የሚሆነው እንዲሆንላችሁ ተረድተናል።
¹⁰ እግዚአብሔር፥ ቅዱሳንን ስላገለገላችሁ እስከ አሁንም ስለምታገለግሉአቸው፥ ያደረጋችሁትን ሥራ ለስሙም ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዓመፀኛ አይደለምና።
¹¹-¹² በእምነትና በትዕግሥትም የተስፋውን ቃል የሚወርሱትን እንድትመስሉ እንጂ ዳተኞች እንዳትሆኑ፥ ተስፋ እስኪሞላ ድረስ እያንዳንዳችሁ ያን ትጋት እስከ መጨረሻ እንድታሳዩ እንመኛለን።
¹³-¹⁴ እግዚአብሔርም ለአብርሃም ተስፋ በሰጠው ጊዜ፦ በእውነት እየባረክሁ እባርክሃለሁ እያበዛሁም አበዛሃለሁ ብሎ፥ ከእርሱ በሚበልጥ በማንም ሊምል ስላልቻለ፥ በራሱ ማለ፤
¹⁵ እንዲሁም እርሱ ከታገሰ በኋላ ተስፋውን አገኘ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ጴጥሮስ 4
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹² ወዳጆች ሆይ፥ በእናንተ መካከል እንደ እሳት ሊፈትናችሁ ስለሚሆነው መከራ ድንቅ ነገር እንደ መጣባችሁ አትደነቁ፤
¹³ ነገር ግን ክብሩ ሲገለጥ ደግሞ ሐሤት እያደረጋችሁ ደስ እንዲላችሁ፥ በክርስቶስ መከራ በምትካፈሉበት ልክ ደስ ይበላችሁ።
¹⁴ ስለ ክርስቶስ ስም ብትነቀፉ የክብር መንፈስ የእግዚአብሔር መንፈስ በእናንተ ላይ ያርፋልና ብፁዓን ናችሁ።
¹⁵ ከእናንተ ማንም ነፍሰ ገዳይ ወይም ሌባ ወይም ክፉ አድራጊ እንደሚሆን ወይም በሌሎች ጒዳይ እንደሚገባ ሆኖ መከራን አይቀበል፤
¹⁶ ክርስቲያን እንደሚሆን ግን መከራን ቢቀበል ስለዚህ ስም እግዚአብሔርን ያመስግን እንጂ አይፈር።
¹⁷ ፍርድ ከእግዚአብሔር ቤት ተነሥቶ የሚጀመርበት ጊዜ ደርሶአልና፤ አስቀድሞም በእኛ የሚጀመር ከሆነ ለእግዚአብሔር ወንጌል የማይታዘዙ መጨረሻቸው ምን ይሆን?
¹⁸ ጻድቅም በጭንቅ የሚድን ከሆነ ዓመፀኛውና ኃጢአተኛው ወዴት ይታይ ዘንድ አለው?
¹⁹ ስለዚህ ደግሞ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ መከራን የሚቀበሉ፥ መልካምን እያደረጉ ነፍሳቸውን ለታመነ ፈጣሪ አደራ ይስጡ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 3
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹² ጴጥሮስም አይቶ ለሕዝቡ እንዲህ ሲል መለሰ፦ የእስራኤል ሰዎች ሆይ፥ በዚህ ስለ ምን ትደነቃላችሁ? ወይስ በገዛ ኃይላችን ወይስ እግዚአብሔርን በመፍራታችን ይህ ይመላለስ ዘንድ እንዳደረግነው ስለ ምን ትኵር ብላችሁ ታዩናላችሁ?
¹³ የአብርሃምና የይስሐቅ የያዕቆብም አምላክ፥ የአባቶቻችን አምላክ፥ እናንተ አሳልፋችሁ የሰጣችሁትንና ሊፈታው ቈርጦ ሳለ በጲላጦስ ፊት የካዳችሁትን ብላቴናውን ኢየሱስን አከበረው።
¹⁴ እናንተ ግን ቅዱሱን ጻድቁንም ክዳችሁ ነፍሰ ገዳዩን ሰው ይሰጣችሁ ዘንድ ለመናችሁ፥
¹⁵ የሕይወትንም ራስ ገደላችሁት፤ እርሱን ግን እግዚአብሔር ከሙታን አስነሣው፥ ለዚህም ነገር እኛ ምስክሮች ነን።
¹⁶ በስሙም በማመን ይህን የምታዩትንና የምታውቁትን የእርሱ ስም አጸናው፥ በእርሱም በኩል የሆነው እምነት በሁላችሁ ፊት ይህን ፍጹም ጤና ሰጠው።
¹⁷ አሁንም፥ ወንድሞቼ ሆይ፥ እናንተ እንደ አለቆቻችሁ ደግሞ ባለማወቅ እንዳደረጋችሁት አውቄአለሁ፤
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ጥቅምት_28_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇🌹

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
  "ትውልደ ጻድቃን ይትባረኩ። ክቡር ወብዕል ውስተ ቤቱ። ወጽድቁኒ ይነብር ለዓለም"። መዝ.111፥9
“በተነ ለችግረኞችም ሰጠ፤ ጽድቁ ለዘላለም ዓለም ይኖራል፤ ቀንዱ በክብር ከፍ ከፍ ይላል።” መዝ.111፥9
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ጥቅምት_28_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሉቃስ 20
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
³⁶ ሊሞቱም ወደ ፊት አይቻላቸውም፥ የትንሣኤም ልጆች ስለ ሆኑ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው።
³⁷ ሙታን እንዲነሡ ግን ሙሴ ደግሞ በቍጥቋጦው ዘንድ ጌታን የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ በማለቱ አስታወቀ፤
³⁸ ሁሉ ለእርሱ ሕያዋን ስለ ሆኑ፥ የሕያዋን አምላክ ነው እንጂ የሙታን አይደለም።
³⁹ ከጻፎችም አንዳንዶቹ መልሰው፦ መምህር ሆይ፥ መልካም ተናገርህ አሉት።
⁴⁰ ወደ ፊትም አንድ ነገር ስንኳ ሊጠይቁት አልደፈሩም።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️  🌹
 የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #ሠለስቱ_ምዕት_ቅዳሴ ነው። መልካም የ #ቅዱስ_አማኑኤል በዓል፣ የአቡነ ይምአታ የዕረፍት በዓልና የጽጌ ጾም ለሁላችንም ይሁንልን።
🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ጥቅምት_29

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ጥቅምት ሃያ ዘጠኝ በዚህች ቀን #አቡነ_ሳሙኤል_ዘደብረ_ወገግ አረፉ፣ በከሀዲው ንጉሥ በመክስምያኖስ ዘመን #ቅዱስ_ድሜጥሮስ ዘተሰሎንቄ በሰማዕትነት አረፈ፣ የደብረ ዘኸኝ #መምህር_ጸቃውዐ_ድንግል አረፈ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አቡነ_ሳሙኤል_ጻድቅ (ዘደብረ ወገግ)

ጥቅምት ሃያ ዘጠኝ በዚህች ቀን ታላቁ ኢትዮጵያዊ ጻድቅ አቡነ ሳሙኤል ዘደብረ ወገግ አረፉ፡፡

ጻድቁ አቡነ ሳሙኤል እንድርያስና አርሶንያ ከሚባሉ የበቁ ደጋግ አባትና እናታቸው የተወለዱት በሸዋ ሀገረ ስብከት ቀድሞ ጽላልሽ ዛሬ ቡልጋ በሚባለው አውራጃ ነው፡፡ የወላጆቻቸው በጎ ምግባርና ሃይማኖት ቅዱስ ተክለሃይማኖትን ከደብረ ሊባኖስ አነሣስቶ በቤታቸው ሄደው እንዲስተናገዱ አድርጓል፡፡ ልጅ ስላልነበራቸው ያዝኑ ነበርና አቡነ ተክለሃይማኖትም በጸጋ #እግዚአብሔር ተገልጾላቸው " #እግዚአብሔር ጣዖታትን የሚሰብር፣ አጋንንትን በጸሎቱ የሚያርቅ፣ ሕዝብን ከኃጢአት በሽታ የሚያድን፣ ፈጣሪውን የሚያስደስት ደግ ልጅ ትወልዳላችሁ" ብለው ትንቢት ነግረዋቸዋል፡፡ በትንቢቱም መሠረት አቡነ ሳሙኤል ሐምሌ 10 ቀን 1248 ዓ.ም ሲወለዱ መልካቸው በአራት ልዩ ልዩ ሕብረ መልክ እየተለዋወጠ አንድ ጊዜ እንደ በረዶ፣ አንድ ጊዜ እንደ እሳት፣ አንድ ጊዜ እንደ ልምላሜና ቢጫ ሆነው ታይተዋል፡፡

አቡነ ተክለሃይማኖትም በአባቱ እንድሪያስ በኩል የሥጋ ዘመዱ ሲሆኑ የመንፈስ ቅዱስም አባት ሆኑትና በ40 ቀን ክርስትና አንስተው ስመ ክርስትናውን "ሳሙኤል" አሉት፡፡ ትርጓሜውም " #እግዚአብሔር ጸሎቴን ሰማኝ" ማለት ነው፡፡ ከሕፃንነትም ጀምረው በምግባር በሃይማኖት ኮትኩተው አሳድገው ለዲቁና አብቅተው በኋላም አመንኩሰውታል፡፡ "ደብረ ወገግ" የሚለው ስያሜ የተገኘው ከመላእክት ነው፡፡ ድርሳነ ዑራኤል በሰፊው እንደሚያትተው ቅዱስ ዑራኤል የ #ጌታችንን ደም በብርሃን ጽዋ ተቀብሎ ዓለምን እየረጨ ሲቀድሳት የያዘውን ጽዋ በደብረ አስቦ ቆሞ ሳለ ነው ጨልጦ ያንጠፈጠፈው፡፡ ያንጊዜም ደብረ አስቦን የብርሃን ውጋጋን ሲያጥለቀልቀው መላእክትም "ቦታውን ደብረ ወገግ" (የብርሃን ተራራ) ብለው ሰይመውታል፡፡ ቅዱስ ሚካኤልም "ወደፊት ፈጣሪውን የሚያገለግል ታላቅ ጻድቅ ይወጣባታልና ይህችን ቦታ ባርካት" ብሎ ቅዱስ ዑራኤልን በነገረው መሠረት ባርኳት እንዳረገ ድርሳነ ዑራኤል ላይ በሰፊው ተጽፏል፡፡

በቦታው ላይ ብዙ ጊዜ የብርሃን ምሰሶ ተተክሎ መታየቱን የበቁ ገዳማውያን ብቻ ሳይሆኑ በከተማ ያሉና ለመሳለም ወደ ቦታው የሄዱ ደገኛ ሰዎችም በዐይናቸው ያዩትን ይናገራሉ፡፡ በገዳሙ ዙሪያ እጅግ በጣም ብዙ ስውራን ቅዱሳን እንዳሉ በግልጽ ይታወቃል፡፡

ንጉሥ ዓምደ ጽዮን በክፉዎች ምክር የአባቱን ሚስት እንጀራ እናቱን በማግባቱ ምክንያት አቡነ ፊሊጶስ ጋር ሆነው ያወገዙትን የቅዱስ ተክለሃይማኖትን ወገኖች በየአውራጃው በተናቸው፡፡ አቡነ ፊሊጶስንም ደሙ በምድር ላይ እስከሚንጣለል ድረስ ገርፈው ወደነበረበት ቤቱ ወሰዱት፤ ፊሊጶስም በሚሄድበት ቦታ ላይ ሳይደርስ በመንገድ ሞተ፡፡ እንድርያስ፣ አኖሬዎስና ተክለ ጽዮን ሁላቸው ከተከታዮቻቸው ጋር በሰማዕትነት አርፈው እነስድስተይ በምትባል ምድር ተቀበሩ፡፡ ጳጳሱን አቡነ ያዕቆብንም ደሙ በምድር ላይ እንደውኃ እስኪወርድ ድረስ ገርፈው ወደ ሀገሩ እንዲሰደደ አደረጉት፡፡ ከዚያም በኋላ ሃይማኖቱ የቀና ደግ ጻድቅ ንጉሥ ዳዊት በነገሠ ጊዜ አባታችን ሳሙኤል ዘወገግን አገኘውና ‹‹መማጸኛ እንዲሆነኝ በእንድርያስ መቃብር ላይ ቤተክርስቲያን ሥራልኝ›› ብሎ ለመነውና የ ቅዱስ ሩፋኤልን ቤተ ክርስቲያን ሠራለት፡፡ የእንድርያስንም አጽም ከመቅደሱ ስር አኖረው፡፡ ንጉሡም በዚያ በእንደግብጦን አውራጃ ሁሉ ላይ ፓትርያርክ አድርጎ ሾመው፡፡ በእነስድስታይ አገር ላሉ ሰዎችም ሁሉ አባት ሆናቸውና የ #መንፈስ_ቅዱስ ልጁንም ታዲዮስን መምህርና አባት አድርጎ ሾመላቸውና ጽላልሽ ሄዶ እናቱን ይዞ ጽጋጋ ምድረ ወገግ ወስዶ አመነኮሳት፡፡

አቡነ ሳሙኤል ወደ ምድረ ርስቱ ደብረ ወገግ እየሄደ በዚያ ያሉ ልጆቹን እያጽናና ወደ እንደግብጦን አውራጃም እየተመለሰ ድንቅ ድንቅ ተአምራትን እያደረገ፣ ወንጌልን እያስተማረ፣ ጣዖት አምላኪዎችን ወደ ክርስትና እየቀየረ፣ አጋንንትንና መመለኪያ ቦታዎቻቸውን እያጠፋ፣ አብያተ ክርስቲያናትን እያነጸ በብዙ ተጋድሎ ኖረ፡፡ በቅዱስ ገድሉ ውስጥ በጣም አስገራሚ በሆነ መልኩ እጅግ ብዙ ታሪኮች ተጠቅሰዋል፡፡ እነዚህም ታሪኮች ውስጥ አቡነ ሳሙኤል በሀገራችን በጣም ብዙ ጣዖታትንና መመለኪያ ቤቶቻቸውን እያጠፉ፣ በሰዎች (በጠንቋዮች) ላይ፣ በዛፍና በባሕር ውስጥ አድሮ ይመለኩ የነበሩ ሰይጣናት አጋንንትን በሚያመልኳቸው ሰዎች ፊት እያጋለጡና እያዋረዱ ሰዎቹን አስተምረው አጥምቀው ወደ አምልኮተ #እግዚአብሔር እየመለሷቸው ቤተክርስቲያንም በመሥራት ሐዋርያትን መሰሉ፡፡

ሰይጣን አድሮባቸው የነበሩ ጠንቋዮች ይጠቀሙባቸው የነበሩ ዕቃዎችን ጻድቁ እየባረኩና እየቀደሱ ለቤተክርስቲያን መሥሪያና መጠቀሚያነት ያውሉት ነበር፡፡ ይህም ገና ሳይወለዱ በአቡነ ተክለሃይማኖት ትንቢት ተነግሮላቸው ነበር፡፡ አቡነ ተክለሃይማኖት ‹‹ጣዖታትን የሚሰብር፣ አጋንንትን በጸሎቱ የሚያርቅ፣ ሕዝብን ከኃጢአት በሽታ የሚያድን፣ ፈጣሪውን የሚያስደስት ደግ ልጅ ይሆናል›› ብሎው ትንቢት እንደተናገሩላቸው አቡነ ሳሙኤል በሰዎች፣ በባሕርና በዛፍ ላይ እያደሩ ይመለኩ የነበሩ በጣም ብዙ አጋንንትን አጠፏቸው፡፡ ጠንቋዮችንም በውስጣቸው ካደረባቸው ሰይጣን እያላቀቁ የ #እግዚአብሔር አገልጋይ ያደርጓቸውና ያመነኩሷቸው ነበር፡፡

ጻድቁ አባታችን አባ ሳሙኤል ወንጌልን ዞረው በማስተማር ሐዋርያትን መሰሉ፣ ከዓላውያን ጋር ለመዋጋት ሰውነታቸውን ለሞት በመስጠት ሰማዕታትን መሰሉ፣ በጾም በጸሎት በስግደት በተጋድሎ ቅዱሳን ጻድቃንን መሰሉ፣ ይህን ኃላፊና ጠፊ ዓለም ንቀው በመተው ባሕታውያንን መሰሉ፣ በደልንና ኃጢአትን በማስተሠረይ ካህናትን መሰሉ፣ በጽሕናና በቅድስና መላእክትን መሰሉ እንደዚሁም ሌሎች ብዙ አስደናቂ ተአምራትንም በማድረግ ይታወቃሉ፡፡ በትእምርተ #መስቀል አድርገው እንደሙሴ ባሕርን ለሁለት ከፍለዋል፣ እንደ ኢያሱ በጸሎታቸው ፀሐይን አቁመዋል፡፡ አቡነ ሳሙኤል ተጋድሎአቸውን ፈጽመው ከ #ጌታችን ታላቅ ቃኪዳን ተቀብለው በዚህች ዕለት በሰላም ዐርፈዋል፡፡

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጻድቁ አቡነ ሳሙኤል ጸሎት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ድሜጥሮስ_ሰማዕት

በዚህችም ቀን በከሀዲው ንጉሥ በመክስምያኖስ ዘመን ቅዱስ ድሜጥሮስ በሰማዕትነት አረፈ። ይህም ቅዱስ ከተሰሎንቄ ሀገር ነው የከበረች የቤተ ክርስቲያንንም ትምህርት ተምሮ በቀናች ሃይማኖት ጸና ሕዝቡንም የሚያስተምር ሆነ ክብር ይግባውና የ #ጌታችን_የኢየሱስ_ክርስቶስ ሃይማኖት በመስበክ ብዙዎችን ከስሕተት መለሳቸው።

ስለዚህም በከሀዲው ንጉሥ ዘንድ ወነጀሉት ንጉሡም ወደርሱ እንዲአመጡት አዘዘ በንጉሡም ዘንድ አንድ ሥጋው የደነደነ የጸና ዐጥንቱ የሰፋ ሰው ነበረ ለሰዎችም ሁሉ እሱ ሁሉን የሚያሸንፍ እሱን የሚያሸንፈው የሌለ ይመስላቸው ነበር ንጉሡም ይወደዋል ይመካበታል እንዲህም ይል ነበር ይህን አካሉ ግዙፍ የሆነ ሰው ለሚያሸንፍ እኔ ብዙ ገንዘብ እሰጠዋለሁ።
በዚያንም ጊዜ ስሙ በስጥዮስ የሚባል አንድ ክርስቲያናዊ ሰው ተነሥቶ ወደ ቅዱስ ድሜጥሮስ ሔደ እንዲጸልይለትና በሥጋውም ሁሉ አሸናፊ በሆነ በ #መስቀል ምልክት እንዲአማትብበት ለመነው። እርሱም በላዩ ጸለየለት በሥጋውም ሁሉ ላይ በ #መስቀል አማተበበት ከዚህም በኋላ ወደ ንጉሥ ገብቶ ከዚያ ሥጋው ግዙፍ ከሆነው ጋር ያታግለው ዘንድ ለመነው ንጉሡም ፈቀደለት በታገሉም ጊዜ ሥጋው የደነደነውን ያ ክርስቲያናዊ ሰው አሸንፎ ጣለው ንጉሡም አዘነ አደነቀም ሥጋው የደነደነውም በመሸነፉ አፈረ ተመክቶበት ነበርና።

ንጉሡም ስለዚህ ነገር ወታደሮቹን ጠየቀ እነርሱም ቅዱስ ድሜጥሮስ በላዩ እንደጸለየለትና በሥጋውም ላይ በ #መስቀል ምልክት እንዳማተበበት ነገሩት።

ንጉሡም ይህን በሰማ ጊዜ በቅዱስ ድሜጥሮስ ላይ እጅግ ተቆጣ ለአማልክትም ዕጣን እስከሚአሳርግ ድረስ እንዲገርፉት አዘዘ ንጉሡም እንዳዘዘ እንዲሁ አደረጉበት የንጉሡንም ትእዛዝ ባልሰማ ጊዜ እስከሚሞት በጦሮች እንዲወጉት ሁለተኛ አዘዘ።

ለቅዱስ ድሜጥሮስም ይህን ፍርድ ነገሩት ሃይማኖቱን ትቶ ለአማልክት የሚሰግድ መስሏቸው ነበርና ቅዱስ ድሜጥሮስም እኔ ከዕውነተኛ አምላክ ከሕያው #እግዚአብሔር ልጅ ከ #ጌታዬ_ኢየሱስ_ክርስቶስ በቀር ለረከሱ አማልክት እሰግድ ዘንድ ዕጣን ማሳረግም አልፈቅድም የወደዳችሁትን አድርጉ አላቸው።

በዚያንም ጊዜ ንጽሕት ነፍሱን በ #እግዚአብሔር እጅ እስከ ሚሰጥ በጦር ወጉት ሥጋውንም በጣሉት ጊዜ ምእመናን ወደ ርሳቸው ወሰዱት የስደቱም ወራት እስከሚያልፍ በሣጥን አድርገው በቤታቸው ውስጥ ሠውረው አኖሩት።

የስደቱም ወራት ከአለፈ በኋላ #እግዚአብሔር ገለጠውና ከዚያ አወጡት ያማረች ቤተ ክርስቲያንንም በተሰሎንቄ አገር ሠሩለት ሥጋውንም በውስጧ አኖሩ ድንቅ የሆነ ታላቅ ተአምርን እያደረገ እስከ ዛሬ አለ።

ሽታውም እጅግ ጣፋጭ የሆነ የሽቱ ቅባት ከእርሱ ይፈሳልና በእምነት የሚቀቡትን በሽተኞች ሁሉንም ያድናቸዋል። ይልቁንም በዕረፍቱ መታሰቢያ ቀን ከሌሎቹ ዕለታት ተለይቶ በብዛት ይፈሳል ከአውራጃው ሁሉ ብዙዎች ሰዎችም ይመጣሉ ከዚህም ቅባት ወስደው በማሰሮቻቸው ያደርጋሉ ይቺ ምልክትም እስከ ዓለም ፍጻሜ በመኖር እንደምትገኝ ደጋጎች ካህናት ምስክሮች ሆኑ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጻድቁ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ኮእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አባ_ጸቃውዐ_ድንግል (ዘደብረ ዘኸኝ)

በዚህችም ቀን የተመሰገነና የከበረ የደብረ ዘኸኝ መምህር ጸቃውዐ ድንግል አረፈ። የዚህም ቅዱስ አባቱ ካህን ነው በጥበብና በበጎ ተግሣጽም አሳደገው መለኮታዊ ትምህርትን ሁሉ አስተማረው አድጎ አርባ ዓመትም በሆነው ጊዜ አባቱ ከአንድ ገዳም ውስጥ መነኰሰ ለመምህርነትም ተመርጦ በአባ ገብረ ማርያም ወንበር ላይ ተሾመ።

በዚያንም ጊዜ አባቱ ለልጁ የምንኵስና ልብስ አለበሰው ስሙንም ጸቃውዐ ድንግል ብሎ ሰየመው ከዚያችም ጊዜ ጀምሮ ያለ ማቋረጥ በጾም በጸሎት ብዙ በመስገድም ታላቅ ተጋድሎን ተጋደለ ። ከዚህም በኋላ አባቱ በአረፈ ጊዜ በአባቱ ፈንታ ተሾመ መንጋዎቹንም እንደ ሐዋርያት ሥርዓት በመልካም አጠባበቅ ጠበቃቸው።

በሌሊቱም ሁሉ ከባሕር ውስጥ ቁሞ ያድራል ከባሕሩም ሲወጣ ወዙ በምድር ላይ እስከሚንጠፈጠፍ ስግደትን ያዘወትራል ምግቡም ደረቅ እንጀራ ነው ጠጅ ወይም ጠላ አይጠጣም #እግዚአብሔርም በእጆቹ ላይ ተአምራትን አደረገ በጐዳናም ሲጓዝ ከታናሽነቱ ጀምሮ ሒዶ የማያውቅ መፃጉዕን አገኘ በስመ #አብ #ወወልድ#መንፈስ_ቅዱስ ብሎ የተጸለየበትን ውኃ በላዩ ረጨ በ #መስቀልም ምልክት አማተበው በዚያንም ጊዜ ዳነ ። ከዚህም ዓለም የሚለይበት ሰዓት በደረሰ ጊዜ ጥቂት ታሞ በሰላም አረፈ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምት_29 እና #ከገድላት_አንደበት)
"በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"።

  #ጥቅምት ፳፱ (29) ቀን።

እንኳን #ለኢትዮጵያዊው_ጻድቅ_ኤርትራ_አገር የሚገኘውን #ገዳመ_ደብረ_ኣንገብ ለመሰረቱት እንደ ሙሽራው #ቅዱስ_ገብረ_ክርስቶስ መናኔ መንግሥት ወብእሲት ለሆኑት ለታላቁ አባት #ለአቡነ_ዕንቈ_ብርሃን ለዕረፍታቸው እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።

#የአቡነ_ዕንቈ_ብርሃንን፦ ገድላቸውን በሰፊው ማግኘት ባንችልም ከኤርትራ አባቶች ያገኘነው ማስታወሻ እንደሚናገረው ጻድቁ የንጉሥ ልጅ ናቸው። የአባታቸውን ንግሥና ንቀው ዓለምን ከነግሳንግሷ እንደትቢያ ቆጥረው በመተው በረኀብ በጥም በጾም በጸሎት በታላቅ ተጋድሎ መኖርን ስለመረጡ እንደሙሽራው ገብረ ክርስቶስ መናኔ መንግሥት ወብእሲት ናቸው።

አቡነ ዕንቈ ብርሃን በምንኩስና #እግዚአብሔርን ለማገልገል ከአባታቸው ቤተ መንሥት ወጥተው ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ ሔደው ገዳም ገብተው ትምህርተ ሃይማኖትን ተማሩ። በገዳም ውስጥ አባቶችን በጉልበት ሥራ እያገለገሉ በትምህርታቸውም ብሉይንና ሐዲስን እንዲሁም የቅዱሳት መጻሕፍትን ምሥጢር ሁሉ አጠናቀው ተማሩ። ከዚኸም በኋላ የገዳሙ አበ ምኔት አባታችንን "ስምህ ማን ይባላል? ሲሏቸው አባታችንም ስማቸው ዕንቈ ብርሃን እንደሚባል ነገሯቸው። አበ ምኔቱም "በእኛ ዘንድ እንደ ደማቅ ብርሃን ደምቀህ አብርተሃልና ከዚኽም በኋላ እንደ ድሮው ስምህ ዕንቈ ብርሃን ይባል፣ አማን በአማን ዕንቈ ብርሃን ነህ" አሏቸው። አቡነ ዕንቈ ብርሃን ከመነኰሱ በኋላ በገድል ላይ ገድል በመጨመር በታላቅ ተጋድሎ ኖሩ። እርሳቸውም በነበሩበት አካባቢ በጣዖት አምልኮ ውስጥ የነበሩትን ብዙ ሰዎች የከበረች ወንጌልን አስተምረው #ክርስቶስን ወደማመን መለሷቸው።

ከዚኽም በኋላ አቡነ ዕንቈ ብርሃን በ16ኛው መ.ክ.ዘ ወደ ኤርትራ በመምጣት ልዩ ስሙ "ደብረ ኣንገብ ደቂ ሻሓይ" በሚባል ቦታ ተቀመጡ፣ ይኸም ቦታ ከአስመራ 30 ኪሜ ርቀት ላይ በምዕራብ ዞን ጋሽ ባርካ በንዑስ ዞን ሎጎ ዓንሰባ ላይ ይገኛል። አቡነ ዕንቈ ብርሃን በዚኸ ቦታ ላይ ብዙዎች ቅዱሳንን አስተምረው ከብቃት ደረጃ ያደረሱና በምንኲስና በርካታ ቅዱሳን የወለዱ አንጋፋ አባት ናቸው። ከልጆቻቸውም ውስጥ የፀዓዳ ዓምባው ታላቁ ጻድቅ አቡነ ሰይፈ ሚካኤል አንዱ ናቸው።

ጻድቁ በገዳማቸው በደብረ ኣንገብ ውስጥ በርካታ ተኣምራትን በማድረግ የሚታወቁ ሲሆን ምድርን ባርከው ያፈለቁት ፈዋሽ ጠበል በርካታ ሕሙማንን እየፈወሰ ይገኛል። ዳግመኛም ለሰውም ለእንስሳትም የሚሆን ውኃን አፈለቁ።

የአቡነ ዕንቈ ብርሃን የዕረፍታቸው ጊዜ ሲደርስ #ጌታችን_መድኀኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ከእልፍ አእላፍ ቅዱሳን መላእክቱ ጋር ተገለጠላቸውና "ስምህን የጠሩትን፣ ዝክርህን የዘከሩትን ደብርህን ያነጹትን፣ ገድልህን የጻፉትንና ያነበቡትን የሰሙትን ሁሉንም እምርልሃለሁ" የሚል ታላቅ የምሕረት ቃልኪዳን ገባላቸው። ከዚኽም በኋላ የጸሎት በኣታቸው ተከፈተችና አባታችንም እዚያው ሲያርፉ ከሰማይ ብርሃን ወረደላቸው፤ ወዲያውም በኣታቸው እንደቀድሞው ተዘጋች።

ከአቡነ ዕንቈ ብርሃን ዕረፍት በኋላም ገዳማቸው ለብዙ ባሕታውያን መኖሪያ ሆነ። እንዲሁም በግራኝ አህመድ የ15 ዓመት የመከራ ዘመን ወቅትም ለ79 ታቦታትና ለበርካታ ቅዱሳት መጻሕፍት መሠወሪያ (መሽሽጊያ) ቦታ ሆኖ አገልግሏል። የመከራውም ዘመን ካለፈ በኋላ ታቦታቱ ወጥተው ለተለያዩ ገዳማትና አድባራት ተሰጡ። አሁን ላይ ግን በዚህ ታሪካዊ ገዳም ውስጥ የሚኖሩት መነኰሳት ጥቂት ከመሆናቸውም በላይ ገዳሙ እየተዳከመ ስለሆነ መነኰሳቱ የገዳሙን ክብር ለመጠበቅ ብዙ እየደከሙ ይገኛሉ። የአቡነ ዕንቈ ብርሃን የዕረፍታቸው መታሰቢያ በዓል ጥቅምት 29 ቀን በገዳማቸው ደብረ ኣንገብ በታላቅ ድምቀት ይከበራል። #ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን ረድኤት በረከታቸው ይደርብን፣ በጸሎታቸው ይማረን ለዘላለሙ አሜን!!!


ምንጭ፦ በእንተ ኅሩይ ቅዱሳን ከሚለው መጽሐፍ የተወሰደ።
"በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"።

         ጥቅምት ፳፱ (29) ቀን።

እንኳን #ለኢትዮጵያኑ_ጻድቃን ለታላቁ አባት #ለአቡነ_ታዴዎስ_ዘጽላልሽ_ግመልን_በመርፌ_ቀዳዳ አሳልፈው ሙት አስነስተው ብዙ ሕዝብ ላሳመኑበት ለተአምራት በዓላቸው፣  እግዚአብሔር በሰላምና በጤና አደረሰን።

                          
#አቡነ_ታዴዎስ_ያደረጉት_ተአምር_ይህ_ነው፦ በአቡነ ታዴዎስ አላምንም የሚል ኢሳ የሚባል አንድ የእስላም ንጉሥ ተነሳ እና እንዲህ አላቸው "ስም ታዴዎስ ነው ሐዋርያው ታዴዎስ ግመል በመርፌ ቀዳዳ አስወጥቷል ይባላል አስወጣና ልመንብህ" አላቸው። ይህን ቃል ሲናገራቸው አቡነ ታዴዎስ ሳቁበት "በል ግመልና መርፌ አምጣ እኔ አሳይሃለው" ሲሉት ሠላሳ ግመል አመጣ አቡነ ታዴዎስም "በል መርፌውን በእጅህ ያዘው ቀዳዳውን ወደ ግመሊቱ አዙረህ" አሉት ወደ ግመሊቱ ቀርበው "በ #አብ#ወልድ#መንፈስ_ቅዱስ ስም አዝዝሻለሁ" ሲሏት አንገቷን በመርፌው አስገብታ ከልጇ ጋር ወጣችና ሃያ ስምንቱን መጀመሪያ የወጣችቱ ግመል እንደ ሰው እየጠራቻቸው ወጡ ይህንን ድንቅ ስራ ያየ መርዩጥም ሆነ ሰራዊቱ የደብረ ማርያም ህዝብ ሲያደንቁ።

በዚያን ጊዜ የኢሳ ልጅ ሙሳ ሳቀ "በምትሃት እንጂ በብቃት አላወጣም" ብሎ ሲጠራጠር አንዲቱ ግመል ሆዱን በእርግጫ ስትመታው ሞተ አንጀቱ ተጎለጎለ በዚያን ጊዜ ሰው ሁሉ ደነገጠ ንጉሡም ደነገጠ ወዲያ ወዲህ እየሮጠ "አባቴ ሆይ እማፀንሃለው ማረኝ እንደ ሙሳ አልሳቅሁም" አቡነ ታዴዎስም "መዩጥ ሆይ ከልብህ እመን ከዚህ በላይ ታያለህ ከ #እግዚአብሔር የሚሆንን ነገር ምንም የሚያገኝህ ነገር የለም አትፍራ ከልብህ ካመንክ የሞተው ይነሳል ስላንተ አምላኬ ያነሳዋል" በዚህ ጊዜ መዩጥ አቡነ ታዴዎስን "እንዴት ሆኖ የሞተ ሰው ይነሳል በል አንተ አስነሳው የደራ ህዝብ ያምን ዘንድ በአምላክህ" አቡነ ታዴዎስ መዩጥን "ይቅበሩት እዘዝ ነገ ያነሳዋል ከተቀበረ በኋላ ነገ ሁሉ ሰው ከዳር እስከ ዳር ወንድ ሴት ትልቅ ትንሽ ሳይባል ይሰብሰብ ይህ ሬሳ የተነሳ እንደሆነ በአምላኬ እንድታምኑ ካልተነሳ እኔን ግደለኝ ከዚህ በኋላ ቅበሩት በዚች ቀን ጠዋት ከደብረ ማርያም ያልተገኘ ክፉ ሞት ይሞታል" አለ በዚች ሌሊት አቡነ ታዴዎስ ከደብረ ማርያም ቤተ ክክርስቲያን ውስጥ ከቅድስት ሆነው በየሰዓቱ መቶ መቶ ስግደት እየሰገዱ "ከመቃብር አላዓዛርን እንዳስነሳህ ይህንንም ሙት አንሳው" መዩጥ እንዲምን ብሎ እየጸለዩ ሳሉ ከሌሊቱ 11ሰዓት ጥቅምት 29 ቀን መልአከ #እግዚአብሔር ወርዶ "የሞተው ይነሳል ስለ አንተ ጸሎት ብሎ ይችን ደብረ ማርያምን አሥራት አድርጌ ሰጥቸሃለሁ በእኔም ስም ስላገኘህ ችግር በጾም በጸሎት ሃይማኖትን በማስተማር ከአጋንንት ጋር በመጋደልህ ከክፉ ሰዎች ጋር በመጋደልህ ደብረ ማርያምን የልጆችህ ርስት አድርጌ ሰጥችሀለሁ እስከ መጨረሻው ድረስ" ብሎት መልአከ #እግዚአብሔር ወደ ሰማይ አረገ።

አቡነ ታዴዎስም እስከ ከቀኑ ሦስት ሰዓት ሲጸልዩ አደሩ ህዝቡ ተሰብስበው ሳለ መዩጥ መጣና ከሰራዊቱ መካከል ተቀመጠ አቡነ ታዴዎስም ጠራቸው "አባቴ ሆይ ትናት እዳልከኝ አድርግ በህዝቤ መካከል የሰበሰብኋቸው ስላንተ ነውና" ሲላቸው "በል የሙቱን አባት አምጣው ወደ እኔ" ሲሉ አቀረቡላቸው አቡነ ታዴዎስም ለአባቱ #መስቀላቸውን ሰጡትና እንደ "አላዓዛር ተነስ በለው ይነሳልሃል" አሉትና የአቡነ ታዴዎስን #መስቀል ይዞ ተነሳ ሲለው ሙቱ ተነስቷል ከዚህም በኋላ የደራ ህዝብ በመላው አምኖ በ #አብ#ወልድ#መንፈስ_ቅዱስ ስም አጥምቀው ሃይማኖትን አስተምረው 12 ቤተ ክርስቲያን አሳነጹ።

ከአባታችን አቡነ ታዴዎስ #እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን በጸሎታቸውም ይማረን።

ምንጭ፦ የጣና ሐይቅ ደብረ ማርያም ገዳም አጭር ታሪክ ከምትላው መጸሐፍ።
2024/12/25 07:20:00
Back to Top
HTML Embed Code: