Telegram Web Link
ዳግመኛም #ጌታችን ለቅድስት ጸበለ ማርያም ሦስት በትሮችን ሰጥቷት በእነርሱ እየተመረኮዘች እስከሲኦል ድረስ ትሄድና ነፍሳትን ታወጣና ታስምር እንደነበር ራሷ ተናገረች፡፡ ዳግመኛም ስትናገር "ሰማያውያን ብዙ ስሞች አወጡልኝ፣ 'የወይን ፍሬ' እያሉ ይጠሩኛል፣ 'የበረከት ፍሬ' የሚሉኝም አሉ፣ 'የገነት ፍሬም' ይሉኛል" አለች፡፡ ዳግመኛም ከልዑል ዘንድ ብዙ ጸጋዎች እንደተሰጣት በሕይወት ሳለች ለአንደ ደገኛ ቄስ ነገረችው፡፡

ከዕለታትም በአንደኛው ቀን አምላክን በድንግልና የወለደች ክብርት #እመቤታችን ለቅድስት ጸበለ ማርያም ተገለጠችላትና "ስሜን የተሸከምሽ ጸበለ ማርያም ሆይ! ሰላም ለአንቺ ይሁን" አለቻት፡፡ #እመቤታችንም ብዙ ምሥጢርን ከነገረቻት በኋላ ጡቶቿንም አጠባቻትና በጸጋ የከበረች አደረገቻት፡፡ በስሟም ብዙ ተአምራትን የምታደርግ ሆነች፡፡

ቅድስት እናታችን ጸበለ ማርያም ከነቢያት፣ ከሐዋርያትና ከሰማዕታት ዕድል የተሰጣት እናት ናት፡፡ እንደነቢያት የሚመጣውን ሁሉ እንዳለፈ አድርጋ ትናገራለች፡፡ ዳግመኛም የትምህርታቸውን ፍለጋ ስለተከተለችና ለሕጋቸው ስለተገዛች ከሐዋርያት ጋር ዕድል ተሰጣት፡፡ ሦስተኛ ግድ ሳይሏት በፈቃዷ ስለተቀበለቻቸው ግርፋቶቿና ስላገኛት መከራ የሰማዕታት ዕድል ተሰጣት፡፡ ከደናግል መነኮሳትም ዕድል ተሰጣት መነኩሲትም ድንግልም ናትና፡፡ ቅድስት እናታችን ጸበለ ማርያም መልካም የሆነውን ተጋድሎዋን ከፈጸመችና #ጌታችን ታላቅ ቃልኪዳን ከገባላት በኋላ በሰላም ዐርፋለች፡፡ እንደ ንግሥት ዕሌኒም የሞቷን #መስቀል ተሸክማ ተጠብቆላት ወዳለ ተስፋዋ በክብር ሄደች፡፡

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅድስት ጸበለ ማርያም ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አባ_አብላርዮስ

ዳግመኛም በዚህች ቀን መስተጋድል መነኰስ አባ አብላርዮስ አረፈ። ይህም ቅዱስ ጋዛ ከሚባል አገር ነው ወላጀቹም አረማውያን ናቸው የዮናናውያንንም ትምህርታቸውንና ፍልስፍናቸውን አስተማሩት ሰውነቱ ለጥበብ ማደሪያዋ እስከሆነ ድረስ በዕውቀቱ ከጓደኞቹ በላይ ሆነ።

ከዚህም በኋላ ከሀገሩ የሌለ መልካም የሆነ ጥበብን ከውጭ አገር መማርን ወዶ ተነሥቶ ወደ እስክንድርያ ሀገር ሔደ መምህራንም ሁሉ ከሚኖሩበት ቦታ ገብቶ ከእሳቸው ዘንድ ብዙ ትምህርትን ተማረ በዚያንም ጊዜ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ለመማር ተነሣሥቶ ቸኰለ የቤተ ክርስቲያንንም መጻሕፍት ብዙዎቹን አነበበ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት አባ እለእስክንድሮስም ይተረጕምለትና ያስረዳው ነበር።

ከዚህም በኋላ ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ አምኖ የክርስትናን ጥምቀት ተጠመቀ ከዚያም መንኵሶ በምንኵስና ሕግ ጸንቶ ገድልን ተጋደለ ወደ አባ እንጦንዮስም ሔዶ መንፈሳዊ የሆነ የትሩፋትን ሥራ እየተማረ በእርሱ ዘንድ ብዙ ወራት ኖረ።

ወላጆቹም እንደሞቱ በሰማ ጊዜ ሒዶ የተዉለትን ገንዘባቸውን ሁሉንም ወስዶ ለድኆችና ለችግረኞች መጸወተ ከዚህም በኋላ ከሶርያ ገዳማት ወደ አንዱ ገዳም ገባ በዚያም በጾም በጸሎት በስግደት በመትጋት ፍጹም ገድልን ተጋደለ በየሰባት ቀን እስቲመገብ ድረስ ምግቡም የዱር ሣር ነበር።

#እግዚአብሔርም ሀብተ ትንቢትን ሰጥቶት ልቡናው ብሩህ ሆነ ድንቆች ተአምራትንም የሚያደርግ ሆነ ኤጲፋንዮስንም ያመነኰሰውና ለደሴተ ቆጵሮስም ኤጲስቆጶስ እንደሚሆን ትንቢት የተናገረለት እርሱ ነው።

የዚህም አባት መላ ዕድሜው ሰማንያ ዓመት ነው ከክርስትናውና ከምንኵስናው በፊት ዐሥራ ሰባት ዓመት በምንኵስናም ስልሳ ሦስት ዓመት ነው ክብር ይግባውና #እግዚአብሔርንም ካገለገለ በኋላ በሰላም አረፈ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም አመስግኖታል ሁለተኛም ቅዱስ ባስልዮስ በመጻሕፍቱ አመስግኖታል።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሱ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#መፍቀሬ_ነዳያን_አባ_ዘግሩም

ዳግመኛም በዚህች ቀን የመፍቀሬ ነዳያን አባ ዘግሩም ዓመታዊ መታሰቢያ በዓላቸው ነው፡፡ አባታቸው ገርዜነ ጸጋ የተባለ ደገኛ ካህን ሲሆን እናታቸው ደግሞ ነፍስተ እግዚእ ትባላለች፡፡ እነዚህም ደገኛ ክርስቲያኖች በ #እግዚአብሔር ሕግ ጸንተው ብዙ ዘመን ሲኖሩ የተባረከ ልጅ ይሰጣቸው ዘንድ #እግዚአብሔርን ይለመኑት ነበር፡፡ ልዑል #እግዚአብሔርም መልአኩን ልኮ የተባረከ ልጅ እንደሚወልዱ አበሰራቸው፡፡ አባ አብርሃምም በመልአኩ ብሥራት ግንቦት ሃያ አራት ቀን በተወለዱ ጊዜ ወላጆቻቸው ብርሃነ መስቀል ብለው ጠሩት፡፡ በኋላ የተጠራበት ስመ ጥምቀቱ ግን ማኅፀንተ ሚካኤል ነው፡፡ ወላጆቹም በመንፈሳዊ አስተዳደግ ስላሳደጉት ከልደቱ ጀምሮ ጸጋ #እግዚአብሔር አደረበት፡፡ በ #መንፈስ_ቅዱስ አደገ፡፡ ወደ ቤተ ክርስቲያንም መሄድን አላስታጎለም፡፡ እንደ ነቢዩ ሳሙኤል ከታናሽነቱ ጀምሮ በ #እግዚአብሔር ቤት አድጓልና፡፡

አድጎ ለትምህርት በደረሰ ጊዜ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን፣ መጻሕፍተ ነቢያትን፣ መዝሙረ ዳዊትን ይማር ዘንድ አባቱ ለመምህር ሰጠው፡፡ ሕፃኑም በትምህርቱ አስተዋይ ሆነ፡፡ ሳያቋርጥ ሁልጊዜ ከመምህሩ መረዳትን ያበዛ ነበር፡፡ በ #መንፈስ_ቅዱስም ኃይል የጸና ሆነ፡፡ ዲቁናም ከተሾመ፡፡

ከዚህም በኋላ እናቱና አባቱ ያለ ፈቃዱ ሚስት ያጩለት ዘንድ ወደዱ፡፡ በመጽሐፍ ‹‹የልጅ ልጅህን ታያለህ፣ አንተ ብፁዕ ነህ፣ መልካምም ይሆንልሃል›› የሚል በመጽሐፍ ተጽፏልና፡፡ ስለዚህም ያጋቡት ዘንድ አቻኮሉት፤ እርሱ ግን ዓለመን ፍጹም ንቆ በምንኩስና በተጋድሎ መኖርን ወደደ፡፡

ለምንኩስናም ስሙ አባ ክርስቶስ ይባርከነ ወደተባለ አንድ መነኩሴ ወዳለበት ገዳም ሲሄድ በመንገድ መደራ በተባለች ቦታ በታላቅ ገዳም ውስጥ ከእንግዶች ጋር አደረ፤ በሌሊት በነቃ ጊዜ አንድ ድኃ በዚያች ቤት ውስጥ አገኘ፤ የድኃውን ልብስ ወስዶ የእርሱን ልብስ ሰጥቶተ በሌሊት ወጥቶ መንገዱን ሔደ፡፡ በነጋም ጊዜ ያ ድኃ ያደረገለትን ለሰዎቹ ተናገረ፡፡ ‹‹በእንግዳ ማደሪያ ከእኔ ጋር አብሮ ያደረ አንድ ሰው እኔ የለበስሁትን ልብስ ወስዶ የእርሱን መልካም ልብስ ተወልኝ›› አላቸው፡፡ እነርሱም ‹‹… የ #እግዚአብሔር ሰው ነውና መልካም ሥራ አደረገልህ አንተ ግን ሔደህ ስለ እርሱ ጸልይለት›› አሉት፡፡

አባ አብርሃም ግን ከአባ ክርስቶስ ይባርከነ ከቀድሞ ቤቱ በደረሰ ጊዜ በዚያም አላገኘውም፤ ውኃ ከሌለበት፤ ፀጥታ ከሰፈነበት ምድረ በዳም ሔደ፡፡ የፀሐይ ወቅት ነበረና በዚያ ሲመላለስ ሳለ ውኃ ጥም ያዘው፡፡ ያን ጊዜም በገዳሙ ውስጥ ባዶ ወጭት አገኘና በፊቱ አስቀምጦ ወደ #እግዚአብሔር በጸለየ ጊዜ ወዲያው ብዙ ዝናም ዘነመ፤ በወጭቷም አጠራቀመና እስኪበቃው ድረስ ከእርሷ ጠጣ፡፡ ከዚያም አባታችን ክርስቶስ ይባርከነን አገኘውና ሊያደርግ የሚፈልጋቸውን ምሥጢሩን ሁሉ ነገረው፡፡ የ #እግዚአብሔር መልአክ መጥቶ አባታችንን ‹‹…በደመና ተጭነህ ወደ ዳሞት አገር ሂድ›› አለው፤ አባታችንም በደመና ተጭኖ ፍራጽ ከተባለ ገዳም ደረሰ፤ በዚያም ምድርን ባረኮ ውሃ አፈለቀ፤ መልአኩም ወደ ቀኝህ ተመልከት አለው፡፡ ወደ ቀኙ ሲያይ ዐደልን ብርሃን ከቧት ተመለከተ፤ ዕፅዋትም ጭፍቅ ያሉ ነበሩ፤ አባ ዘግሩምም ይህች ቦታየ ናት አለ፤ የጻሕናንን ምድር እየባረከም ይሄድ ዘንድ ወደደ፡፡ ብዙ ውሃ አፈለቀ፤ ዐደልም ደረሰ፤ በዚያም ውሃ አፈለቀ፤ አባታችን ዘግሩም ወደ ውስጧ ገባ በዚያም ተቀመጠ፣ የገዳሙ አራዊትም በዚህ ተደሰቱ፡፡ ሙሴ ጽላትን እንደተቀበለ ሁሉ ጥቅምት ሃያ አራት ቀን የ
#እግዚአብሔር መልአክ ከሰማይ አመጥቶ የብርሃን #መስቀልና#መድኃኔዓለምን ታቦት ሰጠው፡፡ ዳግመኛም የ #እግዚአብሔር መልአክ የተዘጋጀ ኅብስትና የተቀዳ ጽዋን፤ ለመሥዋዕት የሚሆነውንም ሁሉ ሰጠው፤ አባታችንም ከካህናት ጋር በዚያች ቤተ ክርስቲያን ቀድሶ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ሰጣቸው፡፡

በቤተ ክርስቲያን አጠገብ አንዲት የዋንዛ ዛፍ ነበረች፤ ሕዝቡም ይሰበሰቡባትና በሥሯ ተቀምጠው ክፉ ሥራ ይሠሩ ነበር፤ አባታችንም ‹‹ለምን እንዲህ የማይገባ ሥራ ትሠራላችሁ? ሲላቸው እነርሱ ግን አልሰሙም፡፡ በዚህም ጊዜ አባታችንም ያቺን ዛፍ ‹‹ከበታችሽ ካሉት ሕዝብ ጋር ተነሥተሽ ሒጂ›› ብሎ በቃሉ አዘዛት፡፡ ያን ጊዜም ያች ዛፍ ከሕዝቡ ጋር ተነሥታ የሁለት ጦር ውርወራ ያህል ሔደች፡፡ #ጌታችን በቅዱስ ወንጌሉ ‹‹የሰናፍጭ ቅንጣት ታህል እምነት ቢኖራችሁና ይችን ሾላ ተነስተሽ ወደዚህ ነይ ብትሏት ትመጣለች፤ ይህን ተራራ ከዚህ ሂድ ብትሉት ይሄዳል›› እንዳለ አባታችን አባ ዘግሩምም ይህንን አደረጉ፡፡

ከአባታችን ይባረኩ፤ እጅ ይነሡም ዘንድ አርባ አራት ቅዱሳን በደመና ተጭነው አባታችን ካለበት ቦታ ወደ ዐደል መጡ፡፡ ሶምሶን ከአህያ መንጋጋ፤ ሙሴ ከዐለት ውሃ እንዳፈለቁ ሁሉ ለሚያስፈልጋቸው ነገር ይጠቀሙበት ዘንድ አባታችንም በጸሎቱ በአንድ ጊዜ አርባ አራት የውሃ ምንጮችን አፍልቆ ሰጣቸው፡፡ እነርሱም ይህን አይተው አደነቁ፤ ስምህ ዘግሩም ይሁን አሉት፤ ስለዚህም አባታችን አባ ዘግሩም ተባለ፤ ምንጮቹም ድውያንንና ሕሙማንን የሚፈውሱ ሆኑ፡፡

ዳግመኛም ለአባታችን የሚገለገልበት አንድ አህያ ነበረው፤ የሚጭነው ሰው ሳይከተለው ለሁለት ቀናት ሔዶ ወደ ጫነው ሰው ቤት ይመለስ ነበር፤ የአገሩ ሰዎችም ይህን አይተው ያላቸውን ሁሉ ይጭኑትና ብቻውን ሔዶ ወደ አባታችን ይመለስ ነበር፡፡

የአቡነ ብርሃነ መስቀልን ተአምራቱን ዜናውን በሰማ ጊዜ ከንጉሡ ባለሟሎች አንዱ መጣ፡፡ ሌላም በቤቱ አጠገብ የሚኖር አንድ ሰው መጣና ‹‹ጨው ጭኜ ወደ ገበያ እወስድበት ዘንድ አህያህን ስጠኝ›› ብሎ ለመነው፡፡ የተቸገሩትን ለመርዳት የሚልከው አንድ አህያ ነበረውና አባ አብርሃምም ‹‹የጨው መጠን ምን ያህል ነው?›› አለው፡፡ ያ ሰውም ‹‹በሰቅል ስሳ ይሆናል›› አለው፡፡ አባታችን አብርሃምም ‹‹ውሰደው ከተናገርኸው በላይ ግን አትጫነው›› አለው፡፡ ሰውየውም አህያውን ወስዶ አባታችን እንዳለው ጫነው፤ ለአባታችን ያልነገረውን በቤቱ የተረፈውን ግን ያ ሰውና ወንድሙ ተሸከሙት፡፡ እነርሱም ተካፍለው ተሸክመው መንገዳቸውን እየሄዱ ሳለ ከአገር ብዙ በራቁ ጊዜ ወንድሙን ‹‹ና አህያውን እንጫነውና እንደፈቀድነው እንሒድ የሚያየን የለምና›› አለው፡፡ በዚሀመ ምክራቸው መሠረት ተሸክመውት የነበረውነ በአህያው ላይ ጫኑት፡፡ ነገረ ግን አህያው መንቀሳቀስን ፈጽሞ እምቢ አለ፤ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አላለም፤ ሲገፉትና ሲደበድቡት ብዙ ደከሙ፤ እንዲህ እያደረጉ ሳሉ አንድ አገልጋይ የንጉሥ መልእክት ይዞ መጣ፡፡ እኒህን ስሕተተኞችም አገኛቸውና ‹‹ጌቶቼ ለምን ትደክማላችሁ?›› አላቸው፡፡ እነርሱም ‹‹ይህ አህያ አልሄድም አለን›› አሉት፤ የንጉሡ መልእክተኛም #መንፈስ_ቅዱስ አነሳሳውና ከፊታቸው ቆመና ‹‹የዚህ ነገር ምክንያቱ ምንድን ነው?›› አላቸው፡፡ እነርሱም ‹‹ይህን አህያ ከአንድ #መንፈስ_ቅዱስ ካደረበት ቀሲስ አመጣነው፤ በዚህ ቀሲስ ቃል ላይ በጨመርን ጊዜ መሔድን እምቢ አለን›› በማለት የሠሩትን ነገሩት፡፡ ‹‹እስኪ የጨመራችሁትን ቀንሱለት›› አላቸው፤ ቀነሱለትና ያን ጊዜ አህያው ተነሥቶ እነርሱም ወደሚፈልጉበት ቦታ ሔዱ፡፡ ይህንንም ሁለት ጊዜ ሦስት ጊዜ ደጋግመው አደረጉ እምቢም አላቸው፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው የቅዱሱን ቃል በመተላለፋቸው እንደሆነ አወቁ፤ ያም የንጉሡ አገልጋይ ተደንቆ ‹‹ኑ ይህ ቅዱስ ካለበት አድርሱኝ›› አላቸው፡፡ አባታችን ካለበት ቦታም ደርሶ ከእርሱ ዘንድ ተባረከ፡፡

ያም አህያውን የወሰደው ሰው ከአቡነ ብርሃነ መስቀል እግር ሥር ተንበርክኮ ‹‹በፊትህ በድያለሁና ቃልህንም አሳብያለሁና አባቴ ሆይ ይቅር በለኝ፤ አህያውም መሄድን እምቢ አለ፤ የጨመርንበትን ሸክም በቀነስንለት ጊዜ ግን ይሄዳል›› አለው፡፡ ዳግመኛም ‹‹…እኔ ግን እንደ እኔ አይነት ሰው ነህ መስሎኝ ቃልህን አፈረስሁ፤ አንተ ግን በፍቅርህ ገመድ ሳብኸኝ›› አለው፡፡ አባታችን ብርሃነ መስቀልም ‹‹ለምን ሐሰት ተናገርህ? መጽሐፍ ‹ሐሰት የኀጢአት መጀመሪያ ናት፤ ሐሰተኞችም የ #እግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም› ይል የለምን?›› በማለት ከመከረው በኋላ በሰላም ወደቤቱ እንዲሔድ ነገረው፡፡

ያም ሰው ከአቡነ ብርሃነ መስቀል ዘንድ ወጥቶ መንገዱን ሔደ፤ ያ የንጉሡ መልእክተኛም አብርሃም ከተባለ ከአቡነ ዘግሩም ዘንድ ተባርኮ ወጣ፤ የቤተ ክርስቲያኗንም አሠራር አይቶ የአባታችን የአብርሃምን ተአምር አደነቀ፤ የንጉሡን ትእዛዝ ይፈጽም ዘንድም መንገዱን ሄደ፡፡ ከብዙ ቀናት በኋላ ያ መልእክተኛ ከንጉሡ ዘንድ ደረሰ፤ ስመ መንግሥቱ ቆስጠንጢኖስ ለተባለ የ #እግዚአብሔር ወዳጅ ለሆነ ለንጉሥ ዳዊት ነገሩን ነገረው፡፡ ‹‹ጻድቅ ንጹሕ የሆነ ቀሲስ አለ፤ በዚህ ዘመን በመንግሥትህ ሀገር ሁሉ እንደርሱ ያለ ሰው የለም፤ ሥራው ሁሉ እንደቀደሙት አባቶች ነውና›› አለው፡፡

በዐይኑ ያየውን፤ በጆሮው የሰማውን ሁሉ ስለሠራት ቤተ ክርስቲያንም ነገረው፤ ንጉሡም ይህን ሁሉ በሰማ ጊዜ በልቡ ተደሰተ፤ በመንፈሱም ሐሴትን አደረገ፤ #እግዚአብሔርንም አመሰገነው፤ እንዲህም አለ፡- ‹‹በዘመነ መንግሥቴ የተሰወረውን የሚያውቅ፤ ተአምራትን የሚያደርግ እንዲህ ያለ ጻድቅ ሰውን የሰጠኝ የእስራኤል አምላክ #እግዚአብሔር ስሙ ይክበር፡፡ አባቴ ቤተ ክርስቲያን ማነጽ በፈለግህ ጊዜ ወደ እኔ ለምን አልላክህም ብሎ ላከበት፤ እኔ ከደቀ መዛሙርትህ እንደ አንዱ አይደለሁምን በረከትህን በተቀበልሁ ነበር አለ፡፡ በዚህ የመንግሥት ዙፋን ላይ ያለሁ በ #እግዚአብሔር ፈቃድ ነው እንጂ በራሴ ፈቃድ ይመስልሃልን በእስረኞች መካከል ሳለሁ ከእስረኞች መካከልም ተኝቼ ሳለ ከዚያ አውጥቶ በአባቶቼ በሰይፈ አርዕድና በዐምደ ጽዮን ዙፋን ላይ አስቀመጠኝ፡፡ አንተ ግን በኀጢአቴ አትናቀኝ፤ ለቤተ ክርስቲያን የምትፈልገውን ይህን ገንዘብ ውሰድ፡፡›› ዳግመኛም ለአባታችን ልብስ ላከለት፤ ሚስቱም እንዲሁ ላከች ‹‹በጸሎትህ አትርሳን›› አሉት፡፡

ከዚህም በኋላ ይመነኩስ ዘንድ ወደደ፤ የመላእክትና የቅዱሳን ልብስ የምትሆን የምንኩስና ልብስን ያለብሰው ዘንድ የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ረድእ ወደ ሆነው ወደ አባ ብሶይ መጣ፡፡ ወደ እርሱ ደርሶ ሥርዐተ ምንኩስና ከፈጸመለት በኋላ አባታችን አብርሃም ‹‹የቀድሞ ስሜን ተውልኝ›› አለው፤ አባ ብሶይም ‹‹ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የደቀ መዛሙርቱን ስም እንደ ለወጠላቸው ስምህን እለውጣለሁ እንጂ አይሆንም›› አለው፡፡ ‹‹ስምህንም አብርሃም፣ ጳውሎስ፣ ዮሐንስ ከሚሉት መካከል ዕጣ በማጣጣል እሰይምሃለሁ›› አለው፡፡

ሦስት ጊዜም ዕጣ ጣሉ፤ አብርሃም የሚለውም ስም ወጣ፤ ይህ ነገር ከ #እግዚአብሔር እንደሆነ አወቀ፡፡ ከታናሽነቱ ጀምሮ የአብርሃም ምግባር የሆነውን እንግዳ መቀበልን፣ እግር ማጠብንና የተራበውን ማብላት ጀመረ፤ ስለዚህ አብርሃም መባል ተገባው፡፡ ‹‹ከታናሽነቴ ጀምሮ የአብርሃምን ሃይማኖት እንደወደድሁ፣ እንግዳ በመቀበል እንደ ኖርሁ ይህን ስም የሰጠኝ #እግዚአብሔር ይመስገን›› አለ፡፡ መንኩሶ በፈቃዱ አብርሃም ተብሎ ተጠርቷልና በብዙ ገድልና በትሕርምት በዚያች ቦታ ኖረ፡፡
የነዳያን ፍቅር በልቡ ውስጥ አለ፤ ሁል ጊዜ ስለ ምግባቸውና ስለ ልብሳቸው ያስብ ነበር፤ ለሚያስፈልጋቸው ነገርም ገንዘብ ይሰጣቸው ነበር፡፡ ለድኆች ልብሱን ያካፍላል፤ ለእነርሱም ሰጥቶ እርሱ ራቁቱን ይቆማል፤ ልጆቹም ይመጣሉ፤ ‹‹ልብስህ ወዴት ነው?›› ይሉት ነበር፤ እርሱም ‹‹ሌቦች በማያገኙበት ቦታ አለ›› ይላቸው ነበር፡፡ ልጆቹ ግን ሥራውን አያውቁም ነበር፤ ውዳሴ ከንቱ እንዳይሆንበት ሁሉን ይሠውር ነበር፤ አይገልጥላቸውም ነበር፤ ድኃ ባየ ጊዜ አጽፉን ይሰጥ ነበር፤ አጽፉን ይቅርና ምንም ልብስ አያስቀርም ነበር፡፡

አንድ ቀን አንድ ድኃ መጥቶ ስለ #እግዚአብሔር ስም ምግብና ልብስ ለመነው፡፡ አባታችን ያን ድኃ ባየው ጊዜ አጽፉን ሰጠው፤ ዳግመኛ አንድ ድኃ መጣ፤ በቤቱም የሚሰጠውን አጣ፤ መጠምጠሚያውን አውርዶ እርሷንም ለድኃው ሰጠውና በቤቱ ተቀመጠ፡፡ አንድ ደቀ መዝሙሩ ወደ ቤቱ መጥቶ ራቁቱን አገኘውና ተቆጣበት፤ ‹‹ክቡር አባቴ ሆይ! ለምን እንዲህ ትሆናለህ? አለው፡፡ ‹‹ለምትበላውና ለምትለብሰው ሳታስቀር ያለ አቅምህ ለምን ምጽዋት ትሰጣለህ? ልብስህንና መጎናጸፊያህን ሰጥተህ አንተ ራቁትህን ትሆናለህ፡፡›› አባታችንም ‹‹ልጄ ሆይ! ፈጽሞ ስለሚያረጅና ስለሚጠፋ የዚህ ዓለም ልብስ ፈንታ የብርሃን መጎናጸፊያ የሚያለብሰኝ አምላኬ አለልኝ›› አለ፤ ልጆቹም ሌላም ልብስ አምጥተው አለበሱ፡፡ ‹‹ይህንም እንደ ቀደመው አታድርግ›› አሉት፤ እርሱ ግን ስለ ድኆችና ስለ ችግረኞች ፍቅር ብዙ ጊዜ ምጽዋት ያደርግ ነበር፤ ቅብዓት በሰውነት፣ ውሃ በአንጀት እንዲገባ የነዳያን ፍቅር ወደ ልቡ ገባ፡፡

የነዳያንን የጩኸት ድምፅ በሰማ ጊዜ ከልቡ ደስታ የተነሣ ለመነሣት ይፈልጋል፤ ከማእድ ላይ ቢሆንም እንኳን ድምፃቸውን ከሰማ እጁን ወደ ማእድ አያወርድም ነበር፤ ይሰጣል እንጂ ምንም ነገር አያተርፍም ነበር፡፡ ነዳያን ግን ዘወትር ጩኸትና ልመናን አያቋርጡም ነበር፤ አባታችን ስለ ምግባቸውና ስለ ልብሳቸው እንደሚያስብ አውቀው ከቤቱ አይርቁም ነበር፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን ወደ አንዲት ታላቅ ሀገር ሔዶ ከዚያ ደረሰ፤ በሰንበት ምሽት ለእሑድ አጥቢያ ከዚያ አደረ፤ ሥርዓተ ቁርባን ከተፈጸመ በኋላ ደቀ መዝሙሩን ‹‹ልጄ የምንበላው ነገር አለህ ወይስ የለህም?›› አለው፤ ያ ደቀ መዝሙርም ‹‹አባቴ አዎን አለኝ›› አለው፡፡ በቤተ ክርስቲያን ያያቸውን ታላላቅ መነኮሳት ሰበሰበ፤ ቁጥራቸውም ዐራት መምህራን ነበሩ፡፡ የተዘጋጀ ምግብና ጠላ ያን ጊዜ እነርሱም ከቤታቸው እንጀራ አመጡ፤ ሁለት ያመጣ አለ፤ ሦስትም ያመጣ አለ፤ ሁላቸውም እንደ አቅማቸው አመጡ፤ አባታችንም ጸሎት ያደርግ ዘንድ ተነሣ፤ ባረከላቸውም፡፡

ደቀ መዝሙሩንም ‹‹ጠላውን አምጣው›› አለው፤ ሁለት መነኮሳትም እንሥራውን አመጡት፤ ከመካከላቸው አንዱን ጠጣ አለው፤ ቀምሶም ለአባታችን ሰጠው፤ ጣዕሙ ደስ ባሰኘው ጊዜ አባታችን ከሩቅ ሀገር የመጡ የተራቡ ሰዎች ከቤቱ ደጃፍ እንዳሉ አወቀ፡፡ መነኮሳቱንም ‹‹አባቶቼ፣ ወንድሞቼና ልጆቼ ፈቃዳችሁ ከሆነስ ለ #ክርስቶስ እንሰጠው ዘንድ ለነዳያንና ለችግረኞች እንስጣቸው›› አላቸው፡፡

በቤተ ክርስቲያን የተሰበሰቡ ወንድሞች መነኮሳት፣ ክቡራን ካህናት፣ ዲያቆናትና ሕዝቡ የ #መንፈስ_ቅዱስ ማደሪያ የሆነ፣ በወንጌል ወተት ያደገ፣ የ #እግዚአብሔር ሰው የሆነ የአባታችንን ትሕትና፣ ትሩፋትና ቅድስና ባዩ ጊዜ አዘኑበት፡፡ ምንም ቃል አልመለሱለትም፤ በቦታቸው ወይም በቤታቸው አልነበሩምና፤ በልባቸው ‹‹እኛስ ከሩቅ ሀገር የመጣን አይደለምን?›› አሉ፡፡ እነርሱ ግን ከዚያው ይኖሩ ነበር፤ አባታችን ግን ነዳያንን ሰብስቦ ያንን ምግብ ሰጣቸው፡፡

ወደ ቤቱ ተጠርተው የመጡ እነዚያ መነኮሳትም አንዲት ቃል አልተናገሩም፤ ነገር ግን በልባቸው ተቆጡ፤ በጣምም አዘኑ፤ አባታችን ግን ደቀ መዛሙርቱን ሌላ ማእድ ያቀርቡ ዘንድ አዘዘ፤ ከመንገድ ስንቅ ይመገቡ ነበርና ጥቂት አመጡ፡፡ ገና ሳይቀምሱም ከሕዝብ አንዱ ‹‹አባቴ ሆይ! ጸልይልኝ፤ ይህን ጥቂት በረከትም ተቀበል›› ብሎ ብዙ ጠላ ላከ፤ እነዚህ መነኮሳት ግን ይህን ባዩ ጊዜ ፈጽመው ተደነቁ፤ ፈጽመው ፈሩ፤ ተንቀጠቀጡም፡፡ አባታችንም ተነሥቶ ለ #ክርስቶስ ሰጠሁት፤ ለተራቡትም አስቀደምሁ፤ ለድኆች የሚሰጥ ለ #እግዚአብሔር ያበድራል የሚል ተጽፏልና አላቸው፡፡

እነዚህ መነኮሳትም ‹‹አባታችን መምህራችን ሆይ! ይቅር በለን አንተ ብዙ ሐዘንን ታውቃለህና፤ እኛ ስለሆዳችንና ስለልብሳችን አዘንን፤ አንተ ግን እንደ ጌታህ #ክርስቶስ የድኆችና የችግረኞች ወዳጅ ነህና›› አሉት፡፡ ‹‹አላወቅንምና አባታችን ይቅር በለን፤ አንተ ፈቃደ #እግዚአብሔርን ትፈጽማለህ፤ እርሱም ልመናህን ይሰማልና›› አሉት፡፡ ‹‹እንዲሰጥህ አላወቅንም፤ ነገር ግን ጎተራህን ሁሉ እንደሚሞላልህ ሰምተን ነበር፤ የተዘጋጀ ምግብንም እንዳወረደልህ ሰምተን ረሳን፤ አሁንም አባታችን ይቅር በለን፤ ባንተ ላይ ተቆጥተን ነበር፤ #እግዚአብሔር ከአንተ ጋር እንደሆነ አላወቅንም፤ አንተ ግን አስቀድመህ ለተራቡት ሰጠህ፤ ቀጥሎም ከአምላክህ በረከት ለእኛ ለመብላት ለተዘጋጀን ሰጠኸን›› አሉት፡፡ አባታችን ዘግሩምም ‹‹ወንድሞቼና ልጆቼ ይህን የማደርገው ለሰው ልታይ ብዬ አይደለም፤ ለትምክህትም አይደለም፤ #እግዚአብሔር የሰጠኝ ሀብት ነው እንጂ›› አላቸው፡፡ ‹‹እኔ እሰጣለሁ፤ እርሱም የሚያስፈልገኝን ነገር አላሳጣኝም›› አላቸው፤ እነርሱም ከእርሱ ተባረኩ፤ ከዚህም በኋላ ታላላቅ ተአምራትና ድንቅ ነገርን የሚያደርግ የ #እግዚአብሔርን ገናናነት ተነጋገሩ፡፡

ከዕለታት አንድ ቀንም አባ ዘግሩም ቆሞ ሳለ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ወደ እርሱ መጣ፤ ቅድስት የሆነች የጎኑን መወጋትና ቁስሎቹን ሁሉ አሳየው፡፡ በደሙ መፍሰስም ተደሰተ፤ ሰግዶም እንዲህ አለ፤ ‹‹#ጌታየ የሚፈሰውን ደምህን እዳስስ ዘንድ ፍቀድልኝ›› አለው፤ #ጌታችንም ቅዱስ የሆነ ደሙን ይዳስስ ዘንድ ፈቀደለት፤ እንደ ቅዱስ ቶማስም ጎኑን ዳሰሰ፤ ቅዱስ ቶማስስ ደቀ መዛሙርቱን ስላላመነ ነበር፤ ይህ አባታችን ግን #ጌታችን ‹‹ሳያዩኝ የሚያምኑኝ ብፁዓን ናቸው›› ብሎ እንደተናገረው ሳያይ ያመነ ነው፡፡ ይህ አባታችን ግን ሳያይ አመነ፤ በቅዱስ ደሙ መፍሰስም ደስ አለው፤ ወንድሞቼ ሆይ ለአባታችን የተሰጠውን ጸጋ ተመልከቱ፤ የ #መድኃኒታችንን ቁስሎች ዳስሷልና፤ ለድኆች የማዘን ፍሬው ይህ ነው፤ ‹‹ለድኆች የሚራራ ለ #እግዚአብሔር ያበድራል›› ተብሏልና፡፡

ለሰው ልጅ የሚሰጥ ታላቅ ጸጋን አገኘ፤ ከሀገሮች ሲመለስም ወደ ደብረ ጽዮን ለመሄድ ግባ ከተባለ ታላቅ ወንዝ ደረሰ፤ ከፈሳሹ ብዛት የተነሣ ስትበረታታ አገኛት፡፡ ብዙ ሰዎች ከእርሱ ጋር ነበሩ፤ የሚያደርጉትንም አጡ፤ ብፁዕ አባታችን ግን ከወንዙ ዳር ቆመ፤ በምርጉዙም በባሕሩ ላይ አማተበ፤ ያን ጊዜ ወንዙ ወዲያና ወዲህ ተከፈለ፤ በዚያ የነበሩ ሰዎች ሁሉ ተሻገሩ፡፡ ነቢዩ ሙሴ የኤርትራን ባሕር በከፈላት ሕዝቡንም በመራ ጊዜ እንደ ተሻገሩ ሁሉ ተሻግረዋልና #እግዚአብሔርን አመሰገኑ፡፡ ይህም አባታችን ባሕርን በየብስ አሻገራቸው፤ ከዚህ በኋላ በሰላም ወደ ቤቱ ደረሰ፡፡

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ገድለ_ቅድስት_ጸበለ_ማርያም#ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምት_24 እና #ከገድላት_አንደበት)
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ጥቅምት_24_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሮሜ 11
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹³-¹⁴ ለእናንተም ለአሕዛብ እናገራለሁ። እኔ የአሕዛብ ሐዋርያ በሆንሁ መጠን ሥጋዬ የሆኑትን አስቀንቼ ምናልባት ከእነርሱ አንዳንዱን አድን እንደሆነ አገልግሎቴን አከብራለሁ።
¹⁵ የእነርሱ መጣል ለዓለም መታረቅ ከሆነ ከሙታን ከሚመጣ ሕይወት በቀር መመለሳቸው ምን ይሆን?
¹⁶ በኵራቱም ቅዱስ ከሆነ ብሆው ደግሞ ቅዱስ ነው፤ ሥሩም ቅዱስ ከሆነ ቅርንጫፎቹ ደግሞ ቅዱሳን ናቸው።
¹⁷ ነገር ግን ከቅርንጫፎች አንዳንዱ ቢሰበሩ አንተም የበረሀ ወይራ የሆንህ በመካከላቸው ገብተህ ከእነርሱ ጋር የወይራ ዘይት ከሚወጣው ሥር ተካፋይ ከሆንህ፥ በቅርንጫፎች ላይ አትመካ፤
¹⁸ ብትመካባቸው ግን ሥሩ አንተን ይሸከምሃል እንጂ ሥሩን የምትሸከም አንተ አይደለህም።
¹⁹ እንግዲህ፦ እኔ እንድገባ ቅርንጫፎች ተሰበሩ ትል ይሆናል።
²⁰ መልካም፤ እነርሱ ከአለማመን የተነሣ ተሰበሩ አንተም ከእምነት የተነሣ ቆመሃል። ፍራ እንጂ የትዕቢትን ነገር አታስብ።
²¹ እግዚአብሔር እንደ ተፈጠሩት ለነበሩት ቅርንጫፎች የራራላቸው ካልሆነ ለአንተ ደግሞ አይራራልህምና።
²² እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቸርነትና ጭከና ተመልከት፤ ጭከናው በወደቁት ላይ ነው፥ በቸርነቱ ግን ጸንተህ ብትኖር የእግዚአብሔር ቸርነት በአንተ ላይ ነው፤ ያለዚያ አንተ ደግሞ ትቆረጣለህ።
²³ እነዚያም ደግሞ በአለማመናቸው ጸንተው ባይኖሩ በዛፉ ውስጥ ይገባሉ፤ እግዚአብሔር መልሶ ሊያገባቸው ይችላልና።
²⁴ አንተ በፍጥረቱ የበረሀ ከነበረ ወይራ ተቆርጠህ እንደ ፍጥረትህ ሳትሆን በመልካም ወይራ ከገባህ፥ ይልቁንስ እነዚያ በፍጥረታቸው ያሉት ቅርንጫፎች በራሳቸው ወይራ እንዴት አይገቡም?
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ራእይ 12
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹³ ዘንዶውም ወደ ምድር እንደ ተጣለ ባየ ጊዜ ወንድ ልጅ የወለደችውን ሴት አሳደዳት።
¹⁴ ከእባቡም ፊት ርቃ አንድ ዘመን፥ ዘመናትም፥ የዘመንም እኵሌታ ወደ ምትመገብበት ወደ ስፍራዋ ወደ በረሀ እንድትበር ለሴቲቱ ሁለት የታላቁ ንሥር ክንፎች ተሰጣት።
¹⁵ እባቡም ሴቲቱ በወንዝ እንድትወሰድ ሊያደርግ ወንዝ የሚያህልን ውኃ ከአፉ በስተ ኋላዋ አፈሰሰ።
¹⁶ ምድሪቱም ሴቲቱን ረዳቻት፥ ምድሪቱም አፍዋን ከፍታ ዘንዶው ከአፉ ያፈሰሰውን ወንዝ ዋጠችው።
¹⁷ ዘንዶውም በሴቲቱ ላይ ተቈጥቶ የእግዚአብሔርን ትእዛዛት የሚጠብቁትን የኢየሱስም ምስክር ያላቸውን ከዘርዋ የቀሩትን ሊዋጋ ሄደ፤
¹⁸ በባሕርም አሸዋ ላይ ቆመ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 11
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ ሐዋርያትና በይሁዳም የነበሩት ወንድሞች አሕዛብ ደግሞ የእግዚአብሔርን ቃል እንደ ተቀበሉ ሰሙ።
² ጴጥሮስም ወደ ኢየሩሳሌም በወጣ ጊዜ ከተገረዙት ወገን የሆኑት ሰዎች ከእርሱ ጋር ተከራክረው፦
³ ወዳልተገረዙ ሰዎች ገብተህ ከእነርሱ ጋር በላህ አሉት።
⁴ ጴጥሮስ ግን ከመጀመሪያው ጀምሮ በተራ ገለጠላቸው እንዲህም አለ፦
⁵ እኔ በኢዮጴ ከተማ ስጸልይ ሳለሁ ተመስጬ ራእይን አየሁ፤ ታላቅ ሸማ የመሰለ ዕቃ በአራት ማዕዘን ተይዞ ከሰማይ ወረደና ወደ እኔ መጣ፤
⁶ ይህንም ትኵር ብዬ ስመለከት አራት እግር ያላቸውን የምድር እንስሶች አራዊትንም ተንቀሳቃሾችንም የሰማይ ወፎችንም አየሁ።
⁷ ጴጥሮስ ሆይ፥ ተነሣና አርደህ ብላ የሚለኝንም ድምፅ ሰማሁ።
⁸ እኔም፦ ጌታ ሆይ፥ አይሆንም፤ ርኵስ ወይም የሚያስጸይፍ ከቶ ወደ አፌ ገብቶ አያውቅምና አልሁ።
⁹ ሁለተኛም፦ እግዚአብሔር ያነጻውን አንተ አታርክሰው የሚል ድምፅ ከሰማይ መለሰልኝ።
¹⁰ ይህም ሦስት ጊዜ ሆነ እንደ ገናም ሁሉ ወደ ሰማይ ተሳበ።
¹¹ እነሆም፥ ያን ጊዜ ሦስት ሰዎች ከቂሣርያ ወደ እኔ ተልከው ወዳለሁበት ቤት ቀረቡ።
¹² መንፈስም ሳልጠራጠር ከእነርሱ ጋር እሄድ ዘንድ ነገረኝ። እነዚህም ስድስቱ ወንድሞች ደግሞ ከእኔ ጋር መጡ ወደዚያ ሰውም ቤት ገባን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ጥቅምት_24_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇🌹

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"ዓጸደ ወይን አፍለስከ እምግብፅ። ሰደድከ አሕዛበ ወተከልከ ኪያሃ። ወፄሕከ ፍኖተ ቅድሜሃ"። መዝ 79፥8-9።
"ከግብጽ የወይን ግንድ አመጣህ፤ አሕዛብን አባረርህ እርስዋንም ተከልህ። በፊትዋም ስፍራን አዘጋጀህ፥ ሥሮችዋንም ተከልህ ምድርንም ሞላች"። መዝ 79፥8-9።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ጥቅምት_24_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ማቴዎስ 21
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
³³ ሌላ ምሳሌ ስሙ። የወይን አትክልት የተከለ ባለቤት ሰው ነበረ፤ ቅጥርም ቀጠረለት፥ መጥመቂያም ማሰለት፥ ግንብም ሠራና ለገበሬዎች አከራይቶ ወደ ሌላ አገር ሄደ።
³⁴ የሚያፈራበትም ጊዜ ሲቀርብ፥ ፍሬውን ሊቀበሉ ባሮቹን ወደ ገበሬዎች ላከ።
³⁵ ገበሬዎቹም ባሮቹን ይዘው አንዱን ደበደቡት አንዱንም ገደሉት ሌላውንም ወገሩት።
³⁶ ደግሞ ከፊተኞች የሚበዙ ሌሎች ባሮችን ላከ፥ እንዲሁም አደረጉባቸው።
³⁷ በኋላ ግን፦ ልጄንስ ያፍሩታል ብሎ ልጁን ላከባቸው።
³⁸ ገበሬዎቹ ግን ልጁን ባዩ ጊዜ እርስ በርሳቸው፦ ወራሹ ይህ ነው፤ ኑ፥ እንግደለውና ርስቱን እናግኝ ተባባሉ።
³⁹ ይዘውም ከወይኑ አትክልት አወጡና ገደሉት።
⁴⁰ እንግዲህ የወይኑ አትክልት ጌታ በሚመጣ ጊዜ በእነዚህ ገበሬዎች ምን ያደርግባቸዋል?
⁴¹ እነርሱም፦ ክፉዎችን በክፉ ያጠፋቸዋል፥ የወይኑንም አትክልት ፍሬውን በየጊዜው ለሚያስረክቡ ለሌሎች ገበሬዎች ይሰጠዋል አሉት።
⁴² ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ ግንበኞች የናቁት ድንጋይ እርሱ የማዕዘን ራስ ሆነ፤ ይህም ከጌታ ዘንድ ሆነ፥ ለዓይኖቻችንም ድንቅ ነው የሚለውን ከቶ በመጽሐፍ አላነበባችሁምን?
⁴³ ስለዚህ እላችኋለሁ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት ከእናንተ ትወሰዳለች ፍሬዋንም ለሚያደርግ ሕዝብ ትሰጣለች።
⁴⁴ በዚህም ድንጋይ ላይ የሚወድቅ ይቀጠቀጣል፤ ድንጋዩ ግን የሚወድቅበትን ሁሉ ይፈጨዋል።
⁴⁵ የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያንም ምሳሌዎቹን ሰምተው ስለ እነርሱ እንደ ተናገረ አስተዋሉ፤
⁴⁶ ሊይዙትም ሲፈልጉት ሳሉ ሕዝቡ እንደ ነቢይ ስላዩት ፈሩአቸው።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️ 🌹
 የሚቀደሰው የ #እመቤታችን_የማርያም_ቅዳሴ ነው። መልካም የፀበለ ማርያምና የአባ ዘግሩም የመታሰቢያ በዓልና ዕለተ ሰንበትና የጽጌ ጾም ጊዜ ለሁላችንም ይሁንልን።
🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ጥቅምት_25

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ጥቅምት ሃያ አምስት በዚህች ቀን #ቅዱስ_አቡነ_አቢብ (አባ ቡላ) አረፈ፣ የመላእክት አምሳል የሆነ #አባ_እብሎይ አረፈ፣ የከበረ #ቅዱስ_ዮልዮስ_ሰማዕት ቤተ ክርስቲያኑ የከበረችበት ነው፣ የደብረ ሊባኖሱ #አባ_ሕፃን_ሞዐ ቃልኪዳን የተቀበሉበት ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አቡነ_አቢብ (አባ ቡላ)

ጥቅምት ሃያ አምስት በዚህች ቀን ታላቅና ክብር የሆነ አቢብ የተባለ መስተጋድል አባ ቡላ አረፈ።

የዚህም ቅዱስ የአባቱ ስም አብርሃም የእናቱም ስም ሐሪክ ነው እነርሱም ከሮሜ አገር ሉፊ ከሚባል አውራጃ ናቸው በዘመናቸውም ከሀዲው ንጉሥ መክስምያኖስ በክርስቲያን ወገኖች ላይ መከራ ስለ አመጣ ስደት ሁኖ ነበርና እነርሱም በስደት ብዙ ዘመን ኖሩ።

ልጅንም በአጡ ጊዜ የተባረከ ልጅን ይሰጣቸው ዘንድ በጾም በጸሎት ተወስነው ወደ #እግዚአብሔር ለመኑ የ #እግዚአብሔርም መልአክ በሕልም ተገለጠላቸውና ፍሬ የመላበትን ዘለላ ሰጣቸው።

ይህም ቅዱስ በተፀነሰ ጊዜ በቤታቸው አጠገብ ታላቅ ዛፍ በቀለ በቅጠሉም ላይ በሮማይስጥ ቋንቋ ቡላ የ #እግዚአብሔር አገልጋይ በጽዮንም አድሮ የሚኖር የያዕቆብ ፈጣሪ ያከበረው የሚል ጽሑፍ ነበረበት።

በተወለደም ጊዜ ክርስትና ሳያስነሡ ዓመት ሙሉ አኖሩት እመቤታችን #ማርያምም ለሮሜ ሊቀ ጳጳሳት ለሰለባስትርዮስ ተገልጣ ወደ አብርሃም ቤት ሒዶ ሕፃኑን እንዲአጠምቀው አዘዘችው እርሱም ሒዶ የክርስትና ጥምቀትን አጠመቀው ስሙንም ቡላ ብሎ ሰየመው እናትና አባቱም ሳይነግሩት ቡላ ስለ ሰየመው አደነቁ ዕፁብ ዕፁብ አሉ።

ከዚህም በኋላ ሊቀ ጳጳሳቱ በጸለየ ጊዜ የቊርባን ኅብስትና ወይን የተመላ ጽዋ ከሰማይ ወረደ እርሱም ቀድሶ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ከሕፃኑ ጋር አቀበላቸው በዚያንም ጊዜ ሕፃኑ የአንድ ዓመት ልጅ ሲሆን በባሕርይ በህልውና በመለኮት ከ #ወልድ#መንፈስ_ቅዱስ ጋር አንድ የሆነ #አብ በግብር በአካል በስም ልዩ ነው በባሕርይ በህልውና በመለኮት ከ #አብ#መንፈስ_ቅዱስ ጋር አንድ የሆነ #ወልድ በግብር በአካል በስም ልዩ ነው በባሕርይ በህልውና በመለኮት በ #አብ#ወልድ ጋር አንድ የሆነ #መንፈስ_ቅዱስ በግብር በአካል በስም ልዩ ነው ብሎ ተናገረ።

ከጥቂት ዘመንም በኋላ አባትና እናቱ ኅዳር ሰባት ቀን ሙተው ሕፃኑ ብቻውን ቀረ።

ሕፃኑም ዐሥር ዓመት በሆነው ጊዜ ለጣዖት መስገድን የሚያዝ ከሀዲ መኰንን መጣ ቅዱስ ቡላም በሰማ ጊዜ ወደ መኰንኑ ሒዶ የረከሱ አማልክቶቹን ረገመ መኰንኑም በአካል ታናሽነቱን አይቶ እጅግ አደነቀ በዚያንም ጊዜ በችንካር እንዲቸነክሩት ሥጋውንም እንዲሠነጣጥቁት ቆዳውንም ከዐጥንቱ እንዲገፉ እጆቹንና እግሮቹንም በመጋዝ እንዲቆርጡ ጀርባውንም እንዲገርፉ በሾተሎችና በጦሮች መካከል አድርገው ከመንኰርኵር ውስጥ እንዲጨምሩት ዳግመኛም በመንገድ ላይ እንዲጐትቱት አዘዘ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልም መጥቶ አዳነው ያለ ጉዳትም ጤነኛ አደረገው።

ከዚህም በኋላ ወደ ሌላ መኰንን ሒዶ እርሱንና የረከሱ ጣዖቶቹን ረገመ መኰንኑም ተቆጥቶ በሚያዝያ ወር ዐሥራ ስምንት ቀን ራሱን በሰይፍ ቆረጠው ቅዱስ ሚካኤልም ከሰማይ ወርዶ ከሙታን ለይቶ አስነሣው ወደ አንድ ገዳምም ወስዶ የምንኲስና ልብስንና አስኬማን በ #መስቀልም ምልክት አለበሰው። እንዲህም አለው ከቅዱሳን ጻድቃን አንድነት ትሆን ዘንድ #እግዚአብሔር አዝዞሃል።

ያን ጊዜም ቅዱስ አባ ቡላ ከደረቅ ተራራ ላይ ወጣ ያለ ማቋረጥም በውስጧ እየተጋደለ ኖረ። የ #ጌታችን_የኢየሱስ_ክርስቶስን መከራውንና ስቅለቱን በአሰበ ጊዜ ከረጅም ዕንጨት ላይ በመውጣት ራሱን ወደታች ሁል ጊዜ ይወረውር ነበር።

በአንዲትም ቀን ከዛፍ ላይ በተወረወረ ጊዜ ሰይጣን ሊገድለው ስለ በረታበት ሞተ ያን ጊዜም ክብር ይግባውና #መድኃኒታችን ከሞት አነሣውና እንዲህ አለው ከእንግዲህ ስምህ ቡላ አይሁን አቢብ ይባል እንጂ የብዙዎች አባት ትሆናለህና።

እርሱም የ #ክርስቶስን ፍቅር እጅግ ጨመረ ፊቱንም እየጸፋ ሥጋውን በየጥቂቱ እየቆረጠ ጀርባውንም ሰባት መቶ ጊዜ እየገረፈ ኖረ #ጌታችንም ይፈውሰው ነበር በየእሑድም ቀን ከቅድስት ድንግል እመቤታችን #ማርያም እንደተወለደ በሌሎች ቀኖችም እንደተያዘና ከአይሁድ መከራ እንደ ተቀበለ ሁኖ ይገለጽለት ነበር።

ስለዚህም ሳይበላ ሳይጠጣ አርባ ሁለት ዓመት ኖረ ዳግመኛም ናላው ፈስሶ እስቲአልቅ ዐሥራ ሁለት ወር በራሱ ተተክሎ ኖረ። በአንዲትም ቀን የ #ጌታችንን መከራ በአሰበ ጊዜ ሰይፉን በአንጻሩ ተከለ ከዕንጨት ላይም ወጥቶ በላዩ ወድቆ ሞተ ቅድስት ድንግል እመቤታችን #ማርያምም ከአእላፍ መላእክት ጋር መጥታ የእኔና የልጄ ወዳጅ ሰላምታ ይድረስህ አለችው ። ከበድኑም ቃል ወጥቶ የሰማይና የምድር ንግሥት #እመቤቴ ሰላምታ ይገባሻል አላት እርሷም በከበሩ እጆቿ ዳሥሣ ከሞት አስነሣቸው።

ዕድሜውንም ፈጽሞ ከዚህ ዓለም የሚወጣበት ጊዜ ሲደርስ ክብር ይግባውና #ጌታችን_መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ በእጁ ልዩ የሆኑ አክሊሎችን የሚያበሩ ልብሶችንም ይዞ ተገለጠለት ወዳጄ አቢብ ሆይ በማያልቅ ተድላ ደስታ ደስ አሰኝህ ዘንድ ወደእኔ ና ስምህን ለሚጠራ መታሰቢያህን ለሚያደርግ እኔ ኃጢአቱን አስተሠርይለት ዘንደ በራሴ ማልኩልህ ወይም ለተራቆተ የሚያለብሰውን ለተራበም የሚያጠግበውን ለተጠማ የሚያጠጣውን የገድልህን መጽሐፍም የሚጽፈውን ወይም የሚያነበውንና የሚሰማውን በጸሎትህም የሚታመኑትን ሁሉ እስከ ዐሥር ትውልድ እምራቸዋለሁ ይህንም ብሎ አፉን ሳመው በደረቱም ላይ አድርጎ ወደአየር አወጣው የመላእክትንም ምስጋና በሰማች ጊዜ ነፍሱ ከሥጋው ተለየች ወደ ሰማያዊት ኢየሩሳሌም ገባች።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ አቡነ አቢብ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አባ_እብሎይ

ዳግመኛም በዚህችም ቀን ደግሞ አክሚም ከሚባል አገር የመላእክት አምሳል የሆነ አባ እብሎይ አረፈ። የዚህም ቅዱስ የአባቱ ስም አሞኒ የእናቱ ስም ሙስያ ነው ሁለቱም በ #እግዚአብሔር ፊት ጻድቃን የሆኑ በሕጉ ጸንተው የሚኖሩ ድኆችንና መጻተኞችን የሚወዱ የሚረዱ ናቸው።

ነገር ግን ልጅ አልነበራቸውም ሙስያም ዕንጨት የያዘ ብርሃናዊ ሰው በቤቷ ውስጥ ሲተክለውና ወዲያውኑ ለምልሞ አብቦ ሲያፈራ ያ ብርሃናዊው ሰውም ከዚህ ፍሬ የሚበላ ሁሉ ለዘላለም ይኖራል ሲላት እርሷም ከፍሬው ወስዳ ስትበላና በአፏ ውስጥ ጣፋጭ ሲሆንላት በልቧም ፍሬ ይሆንልኝ ይሆን ስትል ራእይን አየች።

ከእንቅልፏም በነቃች ጊዜ ራእይን እንዳየች ለባሏ ነገረችው እርሱም እርሷ እንዳየችው ያለ ማየቱን ነገራት #እግዚአብሔርንም አብዝተው አመሰገኑት ትሩፋትንና ተጋድሎን በመጨመር በየሁለት ቀን የሚጾሙ ሆኑ ምግባቸውም እንጀራና ጨው ነው።

ይህን ቅዱስ እብሎይን በፀነሰችው ጊዜ እናቱ በገድል ወንዶችን እስከምታሸንፍ ድረስ በየሌሊቱ ሁሉ አንድ ሽህ ስግደትን ትሰግዳለች ሕፃኑን እስከ ወለደችው ድረስ ዘጠኝ ወር ያህል እንዲህ ስትጋደል ኖረች።

በወለዱትም ጊዜ እብሎይ ብለው ሰየሙት በጐለመሰም ጊዜ የምንኩስናን ልብስ ሊለብስ ወደደ ምክንያትም እስቲያገኝ እንዲህ ኖረ አቢብ የሚባል ወዳጅ ነበረውና እርሱ በሌሊት ወሰደው ከላዕላይ ግብጽ በሚገኙ ገዳማት በአንዱ ገዳም ውስጥ መነኰሰ በገድልም በመጠመድ ታላቅ ተጋድሎን ተጋደለ።
ከጥቂት ወራትም በኋላ በጥቅምት ወር ሃያ አምስት ቀን አባ አቢብ አረፈ ያን ጊዜ አባ እብሎይ አብሎግ ወደሚባል ገዳም ሔደ ወደርሱም ብዙ ሰዎች ተሰበሰቡ እርሱም በበጎ አምልኮ #እግዚአብሔርን መፍራትን የሚያስተምራቸው ሆነ።

ቅዱስ አቢብም በአረፈበት ቀን መታሰቢያውን ሲያደርጉ ይህ ቅዱስ አባ አብሎይ ወንድሞች ሆይ በአባ አቢብ ስም ዛሬ ጸሎትን የሚጸልየውን ኃጢአቱን #እግዚአብሔር ያስተሰርይለታል በዕረፍትህ መታሰቢያ ቀን የአባ አቢብ ፈጣሪ ሆይ ኃጢአቴን ሁሉ ተውልኝ ብሎ አንዲት ጸሎትን የሚጸልየውን ሁሉ እኔ ኃጢአቱን እተውለታለሁ ሲል ቃል ኪዳን ሰጥቶታልና አላቸው።

በዚያችም ሰዓት ከመነኰሳት አንዱ አረፈ እነርሱም ሊገንዙት በዚያ ቁመው ሳሉ አባ እብሎይ ስለ ተናገረው ቃል ከመነኰሳት አንዱ ተጠራጠረ በዚያንም ጊዜ ያ የሞተው ተነሥቶ ይናገር ዘንድ ጀመረ አባ እብሎይ ስለተናገረው ቃል ለምን ትጠራጠራላችሁ ለአባታችን አቢብ በመታሰቢያው ቀን በዚህ ቃል ኪዳን #እግዚአብሔር ሰጥቶናልና አላቸው ። ይህንንም ብሎ ተመልሶ አረፈ መነኰሳቱም አደነቁ ምስጉን #እግዚአብሔርንም አመሰገኑት።

ይህ አባ እብሎይም ብዙ ዘመናት ኖረ ልጆቹ መነኰሳትም በዙ ብዙ ገዳማትም ተሠሩለት። የኖረበትም ዘመኑ በታላቁ አባ መቃርስ ዘመን ነው የአባ እብሎይንም የትሩፋቱን ዜና አባ መቃርስ በሰማ ጊዜ እጅግ ደስ ተሰኘበት እርሱን እያጽናና እያረጋጋ መነኰሳት ልጆቹንም #እግዚአብሔር የሚወደውን በመሥራት ያጸናቸው ዘንድ መልእክትን ጻፈለት።

ይህንንም በአስቄጥስ ገዳም ሁኖ አባ መቃርስ ሲጽፍ አባ እብሎይ በላዕላይ ግብጽ ሳለ በ #መንፈስ_ቅዱስ አውቆ በዙሪያው ያሉትን መነኰሳት እንዲህ አላቸው። እነሆ ማጽናናትን የተመላች መልእክትን አባ መቃርስ ጻፈልን። ከዚህም በኋላ ከአባ መቃርስ ዘንድ የተላኩትን መነኰሳት ሁሉ ወጥተው በደስታ ተቀብለው አስገቧቸው መልእክቱንም በመነኮሳቱ ሁሉ ፊት አነበቡ በታላቅ ደስታም ደስ አላቸው።

ይህም አባ እብሎይ ወደ አባ አሞንዮስ የሔደ ከእርሱ ዘንድም የምትኖረውን ስሟ የዋሂት የተባለችውን የተቀደሰች ሴት ያየ ነው። ክብር ይግባውና #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስም ከዚህ ዓለም ድካም ሊአሳርፈው ወዶ በየካቲት ወር በአምስተኛው ቀን አረፈ እኛ ግን የአባ እብሎይን ዜና ከወዳጁ ከአባ አቢብ ጋር ጻፍን።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ አባ እብሎይ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ዮልዮስ_ሰማዕት

በዚህችም ቀን ዳግመኛ አቅፋሐስ ከሚባል አገር ሰማዕት ለሆነ ለቅዱስ ዮልዮስ ቤተ ክርስቲያኑ የከበረችበት ነው።

ይህም ቅዱስ ዮልዮስ በሀገረ ጥዋ በሰማዕትነት በአረፈ ጊዜ በገድሉ እንደተጻፈ ዲዮቅልጥያኖስ ከጠፋ በኋላ ጻድቅ ሰው ቈስጠንጢኖስ ሳይጠመቅ ነገሠላቸው በጥቂት ወራትም የክርስትና ጥምቀትን ተጠመቀ የቤተ ክርስቲያንም ሥልጣን ከፍ ከፍ አለ ከሀድያን ነገሥታት ለገደሏቸው ንጹሐን ሰማዕታት በስማቸው አብያተ ክርስቲያናት ታነፁ።

ስለ ቅዱሳን ሰማዕታትም ስለ ሥጋቸው እንዲአስብ ገንዞ በመሸከም ወደ አገራቸው እንዲአደርሳቸው ከአገልጋዮቹም ጋር ገድላቸውን እንዲጽፍ #እግዚአብሔር እንደአቆመውና እንደጠበቀው ከዚህም እርሱ ራሱ በሰማዕትነት እንዴት እንደ ሞተ የቅዱስ ዮልዮስን ዜና ንጉሥ ቈስጠንጢኖስ በሰማ ጊዜ ስለበጎ ተጋድሎው ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ቅዱስ ዮልዮስን አመሰገነው ።

ስለዚህም ለቅዱስ ዮልዮስ ያማረች ቤተ ክርስቲያን በግብጽ አገር ሠርተው ሥጋውን በውስጧ ያኖሩ ዘንድ ንጉሡ ወደ ግብጽ አገር ብዙ ገንዘብ ላከ በዚያንም ጊዜ ንጉሡ እንዳዘዘ አነፁለት ። የቅዱስ ዮልዮስንም ሥጋ አፍልሰው በውስጧ አኖሩት ሊቀ ጳጳሳት አባ እለእስክንድሮስም ከኤጲስቆጶሳቱ ጋር አከበራት እንደዛሬዪቱም ቀን በዓል አከበረባት ከሥጋውም ታላላቅ የሆኑ ድንቆች ተአምራት ተገለጡ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ ዮልዮስ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አባ_ሕጻን_ሞዐ_ዘደብረ_ሊባኖስ

በዚህችም ቀን የደብረ ሊባኖሱ አባ ሕፃን ሞዐ ቃልኪዳን የተቀበሉበት ነው። በአባታቸው አርከሌድስ እናታቸው ትቤ ጽዮን ይባላሉ፡፡ የተወለዱት ጥር 25 ነው፡፡ አቡነ ሕፃን ሞዐ እና ከእነ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ጋር የሥጋ ዝምድና አላቸው፡፡ ይኸውም አባታቸው አርከሌድስና ጸጋ ዘአብ ወንድማማቾቸ ናቸው፡፡ አርከሌድስና ጸጋ ዘአብ ሌሎች ሌሎች አራት ወንድሞች አሏቸው፡፡

እነርሱም እንድርያስ፣ ዘርዐ አብርሃም፣ ቀሲስ ዮናስ እና ቀሲስ ዮሐንስ ናቸው፡፡ አርከሌድስ ሕፃን ሞዐን ይወልዳል፣ ጸጋ ዘአብ ተክለ ሃይማኖትን ይወልዳል፣ እንድርያስ ሳሙኤል ዘወገግን፣ ዘርዐ አብርሃም ታላቁ አኖሬዎዮስን፣ ቀሲስ ዮናስ ገላውዲዮስንና የፈጠጋሩን ማትያስን፣ እና ቀሲስ ዮሐንስ ዜናማርቆስን ይወልዳሉ፡፡ እነዚህ የከበሩ ቅዱሳን አባቶቻችን በእናታቸውም ወገን ቢሆን እንዲሁ በዝምድና የተቆራኙ ናቸው፡፡ አቡነ ሕፃን ሞዐ በሌላኛው ስማቸው ሕፃን ዘደብረ በግዕ ተብለውም ይጠራሉ፡፡ ይኸውም የደብረ በግዕን ገዳም የመሠረቱት እርሳቸው ስለሆኑ ነው፡፡

ከ47ቱ የሀገራችን ቀደምት ቅዱሳን ውስጥ አንዱ ናቸው፡፡ በመንዝና በተጉለት የሚገኙ ታላላቅ ገዳማትን አብዛኞቹን የመሠረቷቸው አቡነ ሕፃን ሞዐ ናቸው፡፡ ጻድቁ በክፉዎች ወሬና ሴራ ምክንያት ከበሬ ጋር ተጠምደው ሰማዕትነት የተቀበሉ አባት ናቸው፡፡ ከበሬ ጋር ሲታረሱ ውለው በእጅጉ ከደከማቸው በኋላ በኃይል የተነፈሱባት ምድሪቱ ዛሬም ድረስ ልክ እንደሰው የሚሞቅ ትንፋሽ ታወጣለች፡፡ ያም በጻድቁ እስትንፋስ አምሳል ከመሬት ውስጥ የሚወጣው እስትንፋስ ለአስም በሽታ መድኃኒት ሆኖ ብዙዎችን እየፈወሰ ነው፡፡

ገዳማቸው ከደብረ ብርሃን ከተማ በእግር የ2 ሰዓት መንገድ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ይኸውም ከወንይዬ ተክለ ሃይማኖት ገዳም አጠገብ ነው፡፡ ጻድቁ ጥር 25 ቀን ልደታቸው፣ ጥቅምት 25 ቃል ኪዳን የተቀበሉበት ዕለት ሲሆን ሐምሌ 25 ደግሞ ዕረፍታቸው ነው፡፡

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን ።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምት_25 እና #ከገደላት_አንደበት)
2024/12/25 06:49:29
Back to Top
HTML Embed Code: