Telegram Web Link
#ቅዱስ_ቆርኔሌዎስ_ሐዋርያዊ

በዚህችም ቀን የጭፍራ አለቃ የሆነ ትሩፋቱና ገድሉም ያማረ ጻድቅ ሰው ቆርኔሌዎስ የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው እርሱም በቅዱሳን አባቶቻችን ሐዋርያት ዘመን #እግዚብሔርን ያገለገለ ነው።

#እግዚአብሔር መልአክም ተገልጦለት ሐዋርያ ጴጥሮስን ይጠሩት ዘንድ ሰዎችን እንዲልክ ጴጥሮስም ወደርሱ እንዲመጣ ሊሠራው የሚገባውን ከእርሱ ከጴጥሮስ እንዲሰማ አዘዘው።

ጴጥሮስም ወደርሱ በደረሰ ጊዜ የ #እግዚአብሔርን ቃል አስተማረው ለርሱና ከእርሱ ጋር ላሉት ሁሉ ከሁሉ ቤተሰቡ ጋር አምኖ ተጠመቀ። ከዚህ በኋላ ጴጥሮስ ለእስክንድርያ አገር ቅስና ሾመው ወደርሷ በደረሰ ጊዜ የጣዖታትን አምልኮ ተመልታ አገኛትና አስተማራቸው ብዙዎችንም ወደቀናች ሃይማኖት መልሶ አጠመቃቸው መኰንኑ ድሜጥሮስም አምኖ ከወገኖቹ ጋር በእርሱ እጅ ተጠመቀ።

የኑሮውን ዘመንና ሐዋርያዊ ተጋድሎውን አድርሶ በሰላም አረፈ እርሱም ከአሕዛብ አስቀድሞ ያመነ የመጀመሪያ አማኒ ነው።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሱ ጸሎት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_ታዖድራ

በዚህችም ቀን ከእስክንድርያ አገር በንጉሥ ዘይኑን ዘመን ቅድስት ታዖድራ አረፈች።

ይችንም ቅድስት ሌላ ሰው አስገድዶ ከባሏ ወስዶ ከባሏ ጋር ያላትን አንድነት አበላሸ ያን ጊዜም ታላቅ ኀዘን በማዘን ተጸጸተች መሪር ልቅሶንም አለቀሰች የወንዶችንም ልብስ ለብሳ ወንድ መሰላ ከእስክንድርያ በሥውር ወጣች ስሟንም ቴዎድሮስ ብላ ሰየመችና ወደ ወንዶች ገዳም ገባች የምንኲስና ልብስንና የመላእክትን አስኬማ ለበሰች።

የሚያዩዋት ሁሉ እርሷ እንደ ጃንደረባ የሆነች ወንድ ትመስላቸው ነበር እርሷ ግን በረኃብ፣ በጽምዕ ሌሊት በመትጋት ቀን በመቆም ጸንታ በመጋደል ላይ ታገሠች እንዲህም በመጋደል ተጠምዳ ብዙ ዘመን ኖረች።

በዚያም ወራት እንዲህ ሆነ አንድ ሰው ከአንዲት ብላቴና ጋር አመነዘረ እርሷም ፀንሳ ወንድ ልጅን ወለደች ወላጆቿም ድንግልናሽን ያጠፋው ማነው ብለው ጠየቋት እርሷም በገዳም ውስጥ የሚኖር አባ ቴዎድሮስ እርሱ ደፍሮኝ ከእርሱ ፀነስኩ ብላ በዚች ቅድስት ታኦድራ ላይ በሐሰት ተናገረች።

ወላጆቿም በሰሙ ጊዜ እጅግ አዘኑ ሕፃኑንም ወደዚያ ገዳም አበ ምኔት ወሰዱት እንዲህም አሉት ይህ ሕፃን የልጅህ የመነኵሴው የቴዎድሮስ ልጅ ነው ። ያን ጊዜም አበ ምኔቱ ይቺን ቅድስት ታኦድራን ጠራትና እንዲህ አላት ይህን ክፉ ሥራ ለምን ሠራህ በመነኰሳቱም ሁሉ ላይ ኀፍረትንና ጒስቁልናን አመጣህ እርሷ ሴት መሆኗን አላወቀምና እርሷም አባቴ ሆይ በድያለሁና ይቅር በለኝ አለችው።

አበ ምኔቱም ተቆጥቶ ከገዳሙ አስወጥቶ አባረራት በበረሀ ውስጥ ሰባት ዓመት ኖረች ያም ሕፃን ከእርሷ ጋር ሁኖ ከሰይጣናት በሚመጡባት በብዙ መከራዎች ብዙ መከራዎች ላይ ታገሠች ብዙ ሥቃያትንም ፈጽሞ አሠቃዩዋት።

ከዚህም በኋላ ዳግመኛ ተቀብለው ወደ ገዳም አስገቡአት ጥቂት ቀንም ኖረች መልካም ተጋድሎዋንም ፈጽማ በሰላም አረፈች ነፍሷንም በ #እግዚአብሔር እጅ ሰጥታ የዘላለም ሕይወትን አገኘች።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎቷ ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_በነፍዝዝ_ሰማዕት

በዚህች ቀን የስሟ ትርጓሜ ጣፋጭ የሆነ የከበረች በነፍዝዝ በሰማዕትነት አረፈች። ይቺም ቅድስት በእድሜዋ ፈጽማ የሸመገለች ነበረች በፋርስ ንጉሥ በሳቦር ዘመንም መከራ ተቀበለች ከዘጠኝ መቶ ክርስቲያን ጋር ማርከው ወስደው አሠሩዋት የሠራዊቱም አለቃ ታላቅ ሥቃይን አሠቃይቶ ከዚያ በኋላ ራሷን በሰይፍ ቆረጠ።

ራሷንም ከአስቆረጣት በኋላ ከአንገቷ የፈሰሰው ደም እስከ ራቀ ድረስ ወደ ላይ ወጣ ከዚያ የተቀመጡ ጠላቶችም ኃይላቸው ደከመ። የፀሐይ ብርሃንም ጨለመ በዚያም ቦታ ደግሞ ጣፋጭ የሆነ መዐዛ ተመላ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎቷ ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ሦስቱ_ቅዱሳን_ገበሬዎች
(ሱርስ፣ አጤኬዎስ፣ መስተሐድራ)

በዚህችም ቀን ስማቸው ሱርስ፣ አጤኬዎስ፣ መስተሐድራ የሚባል ሦስት ገበሬዎች የእስና አገር ሰዎች በሰማዕትነት አረፉ ። አርያኖስም ከሀገሪቱ በስተደቡብ ምንም ሳያስቀር ወታደሮቹ እስከ ደከሙ ድረስ ሰይፋቸውንም ወደ አፎቱ መልሰው ነበር የአገር ሰዎችን ጨርሶ ገድሎ ሲመለስ እሊህ ሦስቱ ገበሬዎች ከዱር ሲመለሱ በከተማ መካከል በተገናኙት ጊዜ እኛ ክርስቲያኖች ነን ብለው በግልጥ ጮኹ አርያኖስም ሰምቶ ወታደሮቹን እሊህን ገበሬዎች ትገድሏቸው ዘንድ ይገባል አላቸው።

ወታደሮቹም እኛ ደክመናል ሰይፎቻችንንም ወደ አፎታቸው አስገብተናል አሉት እሊህ ቅዱሳንም ሰምተው እነሆ መቆፈሪያዎች ከእኛ ጋራ አሉ በእነርሱ ግደሉን አሉ ከዚያም አንገታቸውን በደንጊያ ላይ አድርገውላቸው ቆረጡአቸው።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ሁሉ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_መስከረም_11)
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#መስከረም_11_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ዕብራውያን 12
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹-² እንግዲህ እነዚህን የሚያህሉ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን፥ እኛ ደግሞ ሸክምን ሁሉ ቶሎም የሚከበንን ኃጢአት አስወግደን፥ የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤ እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና።
³ በነፍሳችሁ ዝላችሁ እንዳትደክሙ፥ ከኃጢአተኞች በደረሰበት እንዲህ ባለ መቃወም የጸናውን አስቡ።
⁴ ከኃጢአት ጋር እየተጋደላችሁ ገና ደምን እስከ ማፍሰስ ድረስ አልተቃወማችሁም፤
⁵-⁶ እንደ ልጆችም ከእናንተ ጋር፦ ልጄ ሆይ፥ የጌታን ቅጣት አታቅልል፥ በሚገሥጽህም ጊዜ አትድከም፤ ጌታ የሚወደውን ይቀጣዋልና፥ የሚቀበለውንም ልጅ ሁሉ ይገርፈዋል ብሎ የሚነጋገረውን ምክር ረስታችኋል።
⁷ ለመቀጣት ታገሡ፤ እግዚአብሔር እንደ ልጆች ያደርግላችኋልና፤ አባቱ የማይቀጣው ልጅ ማን ነው?
⁸ ነገር ግን ሁሉ የቅጣት ተካፋይ ሆኖአልና ያለ ቅጣት ብትኖሩ ዲቃላዎች እንጂ ልጆች አይደላችሁም።
⁹ ከዚህም በላይ የቀጡን የሥጋችን አባቶች ነበሩን እናፍራቸውም ነበር፤ እንዴትስ ይልቅ ለመናፍስት አባት አብልጠን ልንገዛና በሕይወት ልንኖር በተገባን?
¹⁰ እነርሱ መልካም ሆኖ እንደ ታያቸው ለጥቂት ቀን ይቀጡን ነበርና፥ እርሱ ግን ከቅድስናው እንድንካፈል ለጥቅማችን ይቀጣናል።
¹¹ ቅጣት ሁሉ ለጊዜው የሚያሳዝን እንጂ ደስ የሚያሰኝ አይመስልም፥ ዳሩ ግን በኋላ ለለመዱት የሰላምን ፍሬ እርሱም ጽድቅን ያፈራላቸዋል።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ያዕቆብ 3
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ ወንድሞቼ ሆይ፥ ከእናንተ ብዙዎቹ አስተማሪዎች አይሁኑ፥ የባሰውን ፍርድ እንድንቀበል ታውቃላችሁና።
² ሁላችን በብዙ ነገር እንሰናከላለንና፤ በቃል የማይሰናከል ማንም ቢኖር እርሱ ሥጋውን ሁሉ ደግሞ ሊገታ የሚችል ፍጹም ሰው ነው።
³ እነሆ፥ ፈረሶች ይታዘዙልን ዘንድ ልጓም በአፋቸው ውስጥ እናገባለን፥ ሥጋቸውንም ሁሉ እንመራለን።
⁴ እነሆ፥ መርከቦች ደግሞ ይህን ያህል ታላቅ ቢሆኑ በዐውሎ ነፋስም ቢነዱ፥ የመሪ ፈቃድ ወደሚወደው ስፍራ እጅግ ታናሽ በሆነ መቅዘፊያ ይመራሉ።
⁵ እንዲሁም አንደበት ደግሞ ትንሽ ብልት ሆኖ በታላላቅ ነገር ይመካል። እነሆ፥ ትንሽ እሳት እንዴት ያለ ትልቅ ጫካ ያቃጥላል።
⁶ አንደበትም እሳት ነው። አንደበት በብልቶቻችን መካከል ዓመፀኛ ዓለም ሆኖአል፤ ሥጋን ሁሉ ያሳድፋልና፥ የፍጥረትንም ሩጫ ያቃጥላል፥ በገሃነምም ይቃጠላል።
⁷ የአራዊትና የወፎች የተንቀሳቃሾችና በባሕር ያለ የፍጥረት ወገን ሁሉ በሰው ይገራል፥ ደግሞ ተገርቶአል፤
⁸ ነገር ግን አንደበትን ሊገራ ማንም ሰው አይችልም፤ የሚገድል መርዝ የሞላበት ወላዋይ ክፋት ነው።
⁹ በእርሱ ጌታንና አብን እንባርካለን፤ በእርሱም እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠሩትን ሰዎች እንረግማለን፤
¹⁰ ከአንድ አፍ በረከትና መርገም ይወጣሉ። ወንድሞቼ ሆይ፥ ይህ እንዲህ ሊሆን አይገባም።
¹¹ ምንጭስ ከአንድ አፍ የሚጣፍጥንና የሚመርን ውኃ ያመነጫልን?
¹² ወንድሞቼ ሆይ፥ በለስ ወይራን ወይስ ወይን በለስን ልታፈራ ትችላለችን? ከጨው ውኃም ጣፋጭ ውኃ አይወጣም።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 10
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ በቂሣርያም ኢጣሊቄ ለሚሉት ጭፍራ የመቶ አለቃ የሆነ ቆርኔሌዎስ የሚሉት አንድ ሰው ነበረ።
² እርሱም ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር እግዚአብሔርን የሚያመልክና የሚፈራ ለሕዝብም እጅግ ምጽዋት የሚያደርግ ወደ እግዚአብሔርም ሁልጊዜ የሚጸልይ ነበረ።
³ ከቀኑም ዘጠኝ ሰዓት ያህል፦ ቆርኔሌዎስ ሆይ የሚለው የእግዚአብሔር መልአክ ወደ እርሱ ሲገባ በራእይ በግልጥ አየው።
⁴ እርሱም ትኵር ብሎ ሲመለከተው ደንግጦ፦ ጌታ ሆይ፥ ምንድር ነው? አለ። መልአኩም አለው፦ ጸሎትህና ምጽዋትህ በእግዚአብሔር ፊት ለመታሰቢያ እንዲሆን አረገ።
⁵ አሁንም ወደ ኢዮጴ ሰዎችን ልከህ ጴጥሮስ የሚባለውን ስምዖንን አስመጣ።
⁶ እርሱ ቤቱ በባሕር አጠገብ ባለው በቍርበት ፋቂው በስምዖን ዘንድ እንግድነት ተቀምጦአል፤ ልታደርገው የሚገባህን እርሱ ይነግርሃል።
⁷ የተናገረውም መልአክ በሄደ ጊዜ፥ ከሎሌዎቹ ሁለቱን፥ ከማይለዩትም ጭፍሮቹ እግዚአብሔርን የሚያመልክ አንዱን ወታደር ጠርቶ፥
⁸ ነገሩን ሁሉ ተረከላቸው ወደ ኢዮጴም ላካቸው።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#መስከረም_11_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"ወይርአዩ አሕዛብ በቅድመ አዕይንቲነ። በቀለ ደሞሙ፡ለአግብርቲከ፡ዘተክዕወ። ይባዕ ቅድሜከ ገዐሮሙ ለሙቁሓን"። መዝ 78፥10-11።
"አሕዛብ፦ አምላካቸው ወዴት ነው? እንዳይሉ፥ የፈሰሰውን የባሪያዎችህን ደም በቀል በዓይኖቻችን ፊት አሕዛብ ይወቁ።
የእስረኞች ጩኸት ወደ ፊትህ ይግባ፤ እንደ ክንድህም ታላቅነት ሊገደሉ የተፈረደባቸውን አድን"። መዝ 78፥10-11።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#መስከረም_11_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሉቃስ 21
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹² ከዚህም ሁሉ በፊት እጃቸውን በላያችሁ ይጭናሉ ያሳድዱአችሁማል፤ ስለ ስሜም ወደ ምኵራብና ወደ ወኅኒ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፥ ወደ ነገሥታትና ወደ ገዥዎችም ይወስዱአችኋል፤
¹³ ይህም ለምስክርነት ይሆንላችኋል።
¹⁴ ስለዚህ እንዴት እንድትመልሱ አስቀድማችሁ እንዳታስቡ በልባችሁ አኑሩት፤
¹⁵ ወደረኞቻችሁ ሁሉ ሊቃወሙና ሊከራከሩ የማይችሉትን አፍና ጥበብ እሰጣችኋለሁና።
¹⁶ ወላጆችም ስንኳ ወንድሞችም ዘመዶችም ወዳጆችም አሳልፈው ይሰጡአችኋል፥ ከእናንተም አንዳንዱን ይገድላሉ፤
¹⁷ በሁሉም ስለ ስሜ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ።
¹⁸ ከራሳችሁም አንዲት ጠጉር ስንኳ አትጠፋም፤
¹⁹ በመታገሣችሁም ነፍሳችሁን ታገኛላችሁ።
²⁰ ኢየሩሳሌም ግን በጭፍራ ተከባ ስታዩ በዚያን ጊዜ ጥፋትዋ እንደ ቀረበ እወቁ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #ቅዱስ_ባስልዮስ_ቅዳሴ ነው። መልካም የቅዱስ ፋሲለደስ የዕረፍት በዓል፣ የቅድስት ታዖድራ፣ የቅዱስ ቀርኔሌዎስ፣ የቅድስት በነፍዘዝ ሰማዕትና የቅዱሳን ሱርስ፣ አጤኬዎስ፣ መስተሐድራ የዕረፍት በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
2024/09/21 11:32:16
Back to Top
HTML Embed Code: