Telegram Web Link
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#መስከረም_10_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሮሜ 3
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ እንግዲህ የአይሁዳዊ ብልጫው ምንድር ነው? ወይስ የመገረዝ ጥቅሙ ምንድር ነው? በሁሉ ነገር ብዙ ነው።
² አስቀድሞ የእግዚአብሔር ቃላት አደራ ተሰጡአቸው። ታዲያ ምንድር ነው?
³ የማያምኑ ቢኖሩ አለማመናቸው የእግዚአብሔርን ታማኝነት ያስቀራልን?
⁴ እንዲህ አይሁን፤ በቃልህ ትጸድቅ ዘንድ ወደ ፍርድ በገባህም ጊዜ ትረታ ዘንድ ተብሎ እንደ ተጻፈ፥ ሰው ሁሉ ውሸተኛ ከሆነ እግዚአብሔር እውነተኛ ይሁን።
⁵ ነገር ግን ዓመፃችን የእግዚአብሔርን ጽድቅ የሚያስረዳ ከሆነ ምን እንላለን? ቍጣን የሚያመጣ እግዚአብሔር ዓመፀኛ ነውን? እንደ ሰው ልማድ እላለሁ።
⁶ እንዲህ አይሁን፤ እንዲህ ቢሆን እግዚአብሔር በዓለም እንዴት ይፈርዳል?
⁷ በእኔ ውሸት ግን የእግዚአብሔር እውነት ለክብሩ ከላቀ ስለምን በእኔ ደግሞ እንደ ኃጢአተኛ ገና ይፈርድብኛል?
⁸ ስለ ምንስ መልካም እንዲመጣ ክፉ አናደርግም? እንዲሁ ይሰድቡናልና አንዳንዱም እንዲሁ እንድንል ይናገራሉና። የእነርሱም ፍርድ ቅን ነው።
⁹ እንግዲህ ምን ይሁን? ከእነርሱ እንበልጣለንን? ከቶ አይደለም፤ አይሁድም የግሪክ ሰዎችም ሁሉ ከኃጢአት በታች እንደ ሆኑ አስቀድመን ከሰናቸዋልና፤
¹⁰ እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፦
¹¹ ጻድቅ የለም አንድ ስንኳ፤ አስተዋይም የለም፤ እግዚአብሔርንም የሚፈልግ የለም፤ ሁሉ ተሳስተዋል፥
¹² በአንድነትም የማይጠቅሙ ሆነዋል፤ ቸርነት የሚያደርግ የለም፥ አንድ ስንኳ የለም።
¹³ ጕሮሮአቸው እንደ ተከፈተ መቃብር ነው፥ በመላሳቸውም ሸንግለዋል፤ የእባብ መርዝ ከከንፈሮቻቸው በታች አለ፤
¹⁴ አፋቸውም እርግማንና መራርነት ሞልቶበታል፤
¹⁵ እግሮቻቸው ደምን ለማፍሰስ ፈጣኖች ናቸው፤
¹⁶ ጥፋትና ጉስቁልና በመንገዳቸው ይገኛል፥
¹⁷-¹⁸ የሰላምንም መንገድ አያውቁም። በዓይኖቻቸው ፊት እግዚአብሔርን መፍራት የለም።
¹⁹ አፍም ሁሉ ይዘጋ ዘንድ ዓለምም ሁሉ ከእግዚአብሔር ፍርድ በታች ይሆን ዘንድ ሕግ የሚናገረው ሁሉ ከሕግ በታች ላሉት እንዲናገር እናውቃለን፤
²⁰ ይህም የሕግን ሥራ በመሥራት ሥጋ የለበሰ ሁሉ በእርሱ ፊት ስለማይጸድቅ ነው፤ ኃጢአት በሕግ ይታወቃልና።
²¹ አሁን ግን በሕግና በነቢያት የተመሰከረለት የእግዚአብሔር ጽድቅ ያለ ሕግ ተገልጦአል፥
²² እርሱም፥ ለሚያምኑ ሁሉ የሆነ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የሚገኘው የእግዚአብሔር ጽድቅ ነው፤ ልዩነት የለምና፤
²³ ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል፤
²⁴ በኢየሱስ ክርስቶስም በሆነው ቤዛነት በኩል እንዲያው በጸጋው ይጸድቃሉ።
²⁵ እርሱንም እግዚአብሔር በእምነት የሚገኝ በደሙም የሆነ ማስተስሪያ አድርጎ አቆመው፤ ይህም በፊት የተደረገውን ኃጢአት በእግዚአብሔር ችሎታ ስለ መተው ጽድቁን ያሳይ ዘንድ ነው፥
²⁶ ራሱም ጻድቅ እንዲሆን በኢየሱስም የሚያምነውን እንዲያጸድቅ አሁን በዚህ ዘመን ጽድቁን ያሳይ ዘንድ ነው።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ያዕቆብ 3
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹³ ከእናንተ ጥበበኛና አስተዋይ ማን ነው? በመልካም አንዋዋሩ ስራውን በጥበብ የዋህነት ያሳይ።
¹⁴ ነገር ግን መራራ ቅንዓትና አድመኛነት በልባችሁ ቢኖርባችሁ፥ አትመኩ በእውነትም ላይ አትዋሹ።
¹⁵ ይህ ጥበብ ከላይ የሚወርድ አይደለም፤ ነገር ግን የምድር ነው፥ የሥጋም ነው፥ የአጋንንትም ነው፤
¹⁶ ቅንዓትና አድመኛነት ባሉበት ስፍራ በዚያ ሁከትና ክፉ ስራ ሁሉ አሉና።
¹⁷ ላይኛይቱ ጥበብ ግን በመጀመሪያ ንጽሕት ናት፥ በኋላም ታራቂ፥ ገር፥ እሺ ባይ ምሕረትና በጎ ፍሬ የሞላባት፥ ጥርጥርና ግብዝነት የሌለባት ናት።
¹⁸ የጽድቅም ፍሬ ሰላምን ለሚያደርጉት ሰዎች በሰላም ይዘራል።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹² በዚያን ጊዜ ደብረ ዘይት ከሚባለው ተራራ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፥ እርሱም ከኢየሩሳሌም የሰንበት መንገድ ያህል የራቀ ነው።
¹³ በገቡም ጊዜ ወደሚኖሩበት ሰገነት ወጡ፥ ጴጥሮስና ዮሐንስም፥ ያዕቆብም፥ እንድርያስም፥ ፊልጶስም፥ ቶማስም፥ በርተሎሜዎስም፥ ማቴዎስም፥ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብም፥ ቀናተኛ የሚባለው ስምዖንም፥ የያዕቆብ ልጅ ይሁዳም።
¹⁴ እነዚህ ሁሉ ከሴቶችና ከኢየሱስ እናት ከማርያም ከወንድሞቹም ጋር በአንድ ልብ ሆነው ለጸሎት ይተጉ ነበር።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#መስከረም_10_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
  "ወትቀውም ንግሥት በየማንከ። በአልባሰ ወርቅ ዑፅፍት ወኁብርት። ስምዒ ወለትየ ወርእዪ ወአፅምዒ እዝነኪ"። መዝ 44፥9-10።
"የንጉሦች ሴት ልጆች ለክብርህ ናቸው፤ በወርቅ ልብስ ተጐናጽፋና ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች። ልጄ ሆይ፥ ስሚ እዪ ጆሮሽንም አዘንብዪ፤ ወገንሽን ያባትሽንም ቤት እርሺ፤ መዝ 44፥9-10።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#መስከረም_10_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
  ሉቃስ 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁴⁶ ማርያምም እንዲህ አለች፦
⁴⁷ ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች፥ መንፈሴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ሐሴት ታደርጋለች፤
⁴⁸ የባሪያይቱን ውርደት ተመልክቶአልና። እነሆም፥ ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል፤
⁴⁹ ብርቱ የሆነ እርሱ በእኔ ታላቅ ሥራ አድርጎአልና፤ ስሙም ቅዱስ ነው።
⁵⁰ ምሕረቱም ለሚፈሩት እስከ ትውልድና ትውልድ ይኖራል።
⁵¹ በክንዱ ኃይል አድርጎአል፤ ትዕቢተኞችን በልባቸው አሳብ በትኖአል፤
⁵² ገዥዎችን ከዙፋናቸው አዋርዶአል፤ ትሑታንንም ከፍ አድርጎአል፤
⁵³ የተራቡትን በበጎ ነገር አጥግቦአል፤ ባለ ጠጎችንም ባዶአቸውን ሰዶአቸዋል።
⁵⁴-⁵⁵ ለአባቶቻችን እንደ ተናገረ፥ ለአብርሃምና ለዘሩ ለዘላለም ምሕረቱ ትዝ እያለው እስራኤልን ብላቴናውን ረድቶአል።
⁵⁶ ማርያምም ሦስት ወር የሚያህል በእርስዋ ዘንድ ተቀመጠች ወደ ቤትዋም ተመለሰች።

#ወይም

ማቴዎስ 25
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ በዚያን ጊዜ መንግሥተ ሰማያት መብራታቸውን ይዘው ሙሽራውን ሊቀበሉ የወጡ አሥር ቆነጃጅትን ትመስላለች።
² ከእነርሱም አምስቱ ሰነፎች አምስቱም ልባሞች ነበሩ።
³ ሰነፎቹ መብራታቸውን ይዘው ከእነርሱ ጋር ዘይት አልያዙምና፤
⁴ ልባሞቹ ግን ከመብራታቸው ጋር በማሰሮአቸው ዘይት ያዙ።
⁵ ሙሽራውም በዘገየ ጊዜ ሁሉ እንቅልፍ እንቅልፍ አላቸውና ተኙ።
⁶ እኩል ሌሊትም ሲሆን፦ እነሆ፥ ሙሽራው ይመጣል፥ ትቀበሉት ዘንድ ውጡ የሚል ውካታ ሆነ።
⁷ በዚያን ጊዜ እነዚያ ቆነጃጅት ሁሉ ተነሡና መብራታቸውን አዘጋጁ።
⁸ ሰነፎቹም ልባሞቹን፦ መብራታችን ሊጠፋብን ነው፤ ከዘይታችሁ ስጡን አሉአቸው።
⁹ ልባሞቹ ግን መልሰው፦ ምናልባት ለእኛና ለእናንተ ባይበቃስ፤ ይልቅስ ወደሚሸጡት ሄዳችሁ ለራሳችሁ ግዙ አሉአቸው።
¹⁰ ሊገዙም በሄዱ ጊዜ ሙሽራው መጣ፥ ተዘጋጅተው የነበሩትም ከእርሱ ጋር ወደ ሰርግ ገቡ፥ ደጁም ተዘጋ።
¹¹ በኋላም ደግሞ የቀሩቱ ቈነጃጅት መጡና፦ ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ፥ ክፈትልን አሉ።
¹² እርሱ ግን መልሶ፦ እውነት እላችኋለሁ፥ አላውቃችሁም አለ።
¹³ ቀኒቱንና ሰዓቲቱን አታውቁምና እንግዲህ ንቁ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️ 
የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #እመቤታች_ማርያም_ቅዳሴ ነው። መልካም የፄዴንያ ማርያም በዓልና የ #መስቀሉ በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።
#መስከረም_10_ግማደ_መስቀሉ_ወደ_ኢትዮጵያ_የገባበት ቀን፡
የ"ጌታችን ቅዱስ መስቀል" ወደ ኢትዮጵያ ሊመጣ የቻለበት 1394 ዓ.ም. ዐፄ ዳዊት ሁለተኛ በነገሡ በ29ኛ ዓመታቸው የእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን 47ኛው ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሚካኤል  በወቅቱ የነበረው የግብጽ ፈርዖን አሠራቸው ክርስቲያን የሆኑ ዜጎቹን “የእኔን ሃይማኖት ካልተከተላችሁ መኖር በግብጽ መኖር አትችሉም” ብሎ ከአቅማቸው በላይ ግብር ጣለባቸው፡፡ መከራው የጸናባቸው የግብጽ ክርስቲያኖች “ከደረሰብን መከራና ሊቀጳጳሳችንን ታስፈታልን ዘንድ በ #እግዚአብሔር ስም ተማጽነናል” ሲሉ ለአፄ ዳዊት መልእክት ላኩባቸው፡፡ አጼ ዳዊትም ወታደራቸውን ወደ ግብፅ አዘመቱ፡፡ በወታደሩም ኃይል የዓባይን ወንዝ ለመገደብ ተነሱ፡፡ ይህን የሰሙ የወቅቱ የግብጽ መሪ መርዋን እልጋዴን መኳንቱን ሰብስበው “ምን ይሻለናል ብለው ምክር ያዙ” የዐባይን ወንዝ ከምናጣ “ሊቀጳጳሱን አቡነ ሚካኤልን እንፈታለን በክርስቲያኖችም ላይ መከራ አናደርስም” ብለው ቃል በመግባት ብፁዕ አቡነ ሚካኤልን ሁለት እልፍ ወቂት ወርቅ እጅ መንሻ አስይዘው ለዐፄ ዳዊት አማላጅ ላኩ፡፡

ንጉሡ ዐፄ ዳዊትም “ብርና ወርቅ አልፈልግም #የክብር_ባለቤት_ጌታዬ_ኢየሱስ_ክርስቶስ የተሰቀለበትን #መስቀል ነው የምፈልገው” አሏቸው፡፡ የሀገራችን ሕዝብ በውኃ ጥም ከሚያልቅ ብንስማማ ይሻለናል ብለው መስከረም 10 ቀን 1395 ዓ.ም. ከመስቀሉ ጋር ቅዱስ ሉቃስ የሳላት የእመቤታችን ሥዕል ጨምረው ሰጧቸው፡፡ መስከረም 10 ቀን በዐፄ ዳዊት ዘመነ መንግሥት ግማደ #መስቀሉ ከእስክንድርያ ወደ ኢትዮጵያ የመጣበትን የመታሰቢያ በዓል በየዓመቱ ይከበራል፡፡ ዐፄ ዳዊት መስከረም 10 ቀን የ #ጌታችን_መድኀኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስን_መስቀል ከግብፃውያን የተቀበሉበት ቀን በመሆኑ በቤተ ክርስቲያናችን "ተቀጸል ጽጌ" በመባል የሚታወቅ ሲሆን በየዓመቱ በድምቀት ይከበራል፡፡

#ተቀጸል_ጽጌ /#አጼ_መስቀል/

'ተቀጸል ጽጌ' ማለት 'መስቀል ሆይ! በአበባ አጊጥ' እንደ ማለት ሲሆን 'አጼ መስቀል' ደግሞ አጼ ገብረ መስቀልን አንድም አፄ ዳዊት ቀዳማዊን ይመለከታል። ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ፦

በሃገራችን ኢትዮዽያ የነገረ መስቀሉ ትምሕርት ከመጣ ጀምሮ #መስቀል ይከበራል። በአደበባባይ ግን እንዲከበር ያደረጉት የቅዱስ ካሌብ ልጅ አፄ ገብረ መስቀል ናቸው። በወቅቱ ንጉሡ፣ ሠራዊቱ፣ ዻዻሱና ሕዝቡ በተገኙበት ቅዱስ ያሬድ "መስቀል መልዕልተ ኩሉ ነገር ያድኅነነ እምጸር።" "መስቀል ከሁሉ ነገር በላይ ነው: ከጠላትም ያድነናል።" እያለ ይዘምር ነበር።

የአበባ ጉንጉንም ለመስቀሉና ለንጉሡ ይቀርብ ነበር። ከ800 ዓመታት በሁዋላም አፄ ዳዊት ግማደ #መስቀሉን ባስመጡ ጊዜ መስከረም ቀን ተተክሎ ታላቅ በዓልም ሆኖ ተከብሯል።

#መስቀሉ ላዳነን #ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን የ #መድኃኒታችን_የመስቀሉ በረከት ከሁላችን የክርስቲያን ወገኖች ጋር ይኑር ለዘላለሙ አሜን።
በዐርብ ቀን ደም ለአፈሰሱ ጣቶችህና ለጣቶች ጥፍሮች ሰላምታ ይገባል። የ #አብ የቅድምና ስሙ ስምህ የሆነልህ #ኢየሱስ_ክርስቶስ ሆይ በመለኮታዊ ላብ የታጠበው የ #መስቀልህ ክንፍ እንደ ፊያታዊ ዘየማን በራሴ ላይ ይዘርጋልኝ።

#መልክዐ_ቅዱስ_ዕፀ_መስቀል
#በዓለ_ስዕለ_አድኅኖ

፩- የቅዱሳት ሥዕላት ትርጉም፤

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትምህርተ ሃይማኖት እና ትውፊት ቅዱሳት ሥዕላት ማለት፤ በአብያተ ክርስቲያናት ግድግዳ፡ በሸራ፡ በብራና፡ በወረቀት እና በመስቀሎች ላይ በቀለም ወይም በጭረት ባለ ሁለት ጎን ሆነው የሚሠሩ የልዑል #እግዚአብሔርን#የእመቤታችንን፡ የቅዱሳን መላዕክትን፡ የጻድቃንን እና የሰማዕታትን ማንነት የሚገልጥ መንፈሳዊ ጥበብ ነው። ሥጋዊውን ዓለም ከሚያንጸባርቁ መንፈሳዊ መልዕክት ከሌላቸው ሌሎች ሥዕላት ፈጽመው ስለሚለዩ ቅዱሳን ሥዕላት ይባላሉ።

፪- የቅዱሳት ሥዕላት አመጣጥ፤

፪-፩ በብሉይ ኪዳን

ሥዕል በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለያዘው ቦታ መሠረቱ የሁሉ አስገኝ የሆነው አምላካችን #እግዚአብሔር አስቀድሞ ለነቢዩ ሙሴ ሥዕለ ኪሩብን በሥርየት መክደኛው ታቦት ላይ እንዲያዘጋጅ ማዘዙ ነው። ለዚህም መሠረት በዘጸ. ም. ፳፭፡ቁ ፳፪ “በዚያም ካንተ ጋር እገናኛለሁ የእስራኤልንም ልጆች ታዝዝ ዘንድ የምሰጥህን ነገር ሁሉ በምስክሩ ታቦት ላይ ባለው በሁለት ኪሩቤል መካከል በስርየት መክደኛው ላይ ሆኜ አነጋግርሃለሁ” ብሎ መናገሩ ነው። #እግዚአብሔርም የተናገረውን የማያስቀር ነውና ሊቀ ነቢያት ሙሴን በሥዕለ ኪሩብ መካከል ሆኖ ድምጹን አሰምቶታል።

፪-፪ በሐዲስ ኪዳን

ከሐዋርያዊ ተልዕኮውና የሕክምና ሞያው በተጨማሪ የሥዕል ጠቢብ የነበረው ቅዱስ ሉቃስም ምስለ ፍቁር ወልዳን (እመቤታችን ከልጇ ከወዳጇ ጋር ሆና) በመሳል ለትውልድ አቆይቶልናል። በተጨማሪም ቅዱስ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ ለጢባርዮስ ቄሳር የ #ጌታችንን ሥነ-ስቅለት ሥዕል አዘጋጅቶ ሰጥቶታል።

፫- ቅዱሳት ሥዕላት በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የራሷ የሆነ ፊደል፡ ሥነ ጽሁፍ፡ ዜማ፡ ኪነ ህንፃ… ወዘተ እንዳሏት ሁሉ የራሷ የሆነ የሥነ ሥዕል ጥበብም ያላት ስንዱ እመቤት ናት። ከጥንተ ክርስትና የአክሱማውያን ዘመን ጀምሮ ሥዕል በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ቦታ እንደነበረው የአርኪዮሎጂ ግኝቶችና የጥንት አብያተ ክርሰቲያናት ፍርስራሾች ያመለክታሉ። በተለይ በዘመነ አክሱም ተሠርተው በከፊል የፈረሱ እና ከመፍረስ የተረፉ እንደ አብርሃ ወአጽብሐ፡ ውቅሮ ቅዱስ ቂርቆስ፡ ደብረ ዳሞ ገዳም፡ መርጡለ ማርያም፡ ወዘተ ያሉት አብያተ ክርስቲያናት የያዟቸው
ሥዕሎች የዘመኑን የሥዕል ጥበብ አሻራ ያሳያሉ። በተለይ በመካከለኛው መቶ ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የሥዕል ጥበብ ያደገበት ዘመን ነበር። በአሁኑ ወቅት በአብዛኞቹ አብያተ ክርስቲያናት የምናገኛቸው ሥዕላት በዚህ ዘመን የተሠሩ ናቸው።

፬- የቅዱሳት ሥዕላት ጥቅም፡

፬-፩ ለሥርዓተ አምልኮ

ቅዱሳት ሥዕላት ሰውንና #እግዚአብሔርን የሚያገናኙ መንፈሳዊ ሀብቶች ናቸው። በሥዕል ፊት ቆሞ መጸለይ፡ ወይንም መስገድ ሥዕሉን አምላክ ማድረግ አይደለም። ነገር ግን የሥዕሉን ባለቤት በሥዕሉ ፊት ሆኖ በመማጸን በረከቱን ለማግኘት የሚፈጸም ሥርዓት ነው። ሥዕሉ ለባለቤቱ መታሰቢያ ነው። “የጻድቅ መታሰቢያ ለበረከት ነው ተብሎ እንደተጻፈ” ምሳ. ፲፡፯ የሥዕሉን ባለቤት አቅርቦ ያሳየናል። ገድሉን፣ ተአምራቱንና ቃል ኪዳኑን ያስታውሰናል። በመንፈስም ድልድይ ሆኖ ከሥዕሉ ባለቤት ያገናኘናል።

ሙሴና አሮን ወደ ደብተራ ኦሪት ገብተው በታቦቱና ሥዕለ ኪሩብ ፊት እየሰገዱ ከ #እግዚአብሔር ትዕዛዝ ይቀበሉ ነበር ዘኁ. ፲፮፡፵፭

፬-፪ ለትምህርት

ቅዱሳት ሥዕላት ሲሣሉ የሥዕሉን ባለቤት ዐቢይ ገድልና ተአምራት በሚያጎላ መልኩ ነው። ስለሆነም ማንኛውም ምእመን የሥዕሉን ባለቤት መንፈሳዊ ተጋድሎ በቀላሉ እንዲረዳ ያደርገዋል። ለምሳሌ የጻድቁ አባታችን የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ሥዕል ሲሣል ለ22 ዓመታት 8 ጦሮችን ከግራ ከቀኝ ከፊት ከኋላ አስተክለው ሲጸልዩ አንድ እግራቸው በቁመት ብዛት መቆረጡን እንዲሁም ስለ ቅድስናቸው ከተሰጣቸው ስድስት የብርሃን ክንፎች ጋር ተደርጎ ይሣላል። ክህነታቸውን ለመግለጽም የእርፍ መስቀልና ጽና ይዘው ይሣላል። የሥዕሉ ባለቤት እንዲታወቅም በሥዕሉ ላይ አጭር የጽሑፍ መግለጫ ይቀመጣል። ”ዘከመ ጸለየ አቡነ ተክለሃይማኖት” እንዲል። በዚህ ሥዕል ምእመናን የጻድቁን ተጋድሎ ይማሩበታል፤ አርአያም ያደርጉታል።

እንግዲህ ቅዱሳት ሥዕላት ይህን መንፈሳዊ አገልግሎት የሚሰጡን ከሆነ በጥንቃቄ በመያዝ መገልገል እንደሚገባና ዘወትር በጸሎት ሰዓት ከፊት ለፊታችን በማስቀመጥ ልንጸልይ እንደሚገባ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መልዕክቷን ታስተላልፋለች።

ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን!
Media is too big
VIEW IN TELEGRAM
❀እንኳን አደረሳችሁ!

#ማርያም እግዝእት (ጼዴንያ)
#መስቀል ዕጸ ሕይወት
#ማክዳ ንግሥት
#ሐና ዕብራዊት
#ዮዲት ቅድስት
#አትናስያ ቡርክት
#መጥሮንያ ሰማዕት
#ማርታ ብጽዕት
#ኢያቄም ወላዴ በረከት
#ግርማሥሉስ ገባሬ መንክራት
#መስከረም_11

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
መስከረም ዐሥራ አንድ በዚህች ቀን #ቅዱስ_ፋሲለደስ በሰማዕትነት አረፈ፣ #ቅዱስ_ቆርኔሌወስ የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው፣ #ቅድስት_ታዖድራ አረፈች፣ #ቅድስት_በነፍዝዝ የስሟ ትርጓሜ ጣፋጭ የሆነ በሰማዕትነት አረፈች፣ #ሦስቱ_ቅዱሳን_ገበሬዎች (#ሱርስ#አጤኬዎስ#መስተሐድራ) በሰማዕትነት አረፉ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ፋሲለደስ_ሰማዕት

መስከረም ዐሥራ አንድ በዚህች ቀን ለአንጾኪያ ነገሥታት አባታቸውና መካሪያቸው የሆነ ቅዱስ ፋሲለደስ በሰማዕትነት አረፈ።

እርሱም ለሮም ንጉሥ የሠራዊት አለቃ ነው መንግሥቱም ሁለመናዋ በእርሱ ምክር የጸናች ናት። ብዙዎችም ወንዶችና ሴቶች የቤት ውልዶች አገልጋዮች አሉት።

ዝምድናውም እንዲህ ነው ስሙ ኑማርያኖስ የተባለ የሮም ንጉሥ ለቴዎድሮስ በናድሌዎስ እናቱ የሆነች የቅዱስ ፋሲለደስን እኅት አግብቶ ዮስጦስን፣ ገላውዴዎስን፣ አባዲርን ወለደችለት እሊህም ለቅዱስ ፋሲለደስ የእኅቱ ልጆች ናቸው። የቅዱስ ፋሲለደስም ሚስት ለቅዱስ ፊቅጦር እናት እኅት ናት ከእርሷም ስማቸው አውሳብዮስና መቃርስ የተባሉ ሁለት ልጆችን ወለደ።

በዚያም ወራት የቊዝና የፋርስ ሰዎች የሮምን ሰዎች ሊወጓቸው በላያቸው ተነሡ ያን ጊዜ የንጉሥ ልጅ ዮስጦስን የፋሲለደስ ልጅ አውሳብዮስን ከጦር ሠራዊቶቻቸው ጋር ለውጊያ ላኳቸው።

ንጉሡ ኑማርዮስም ሌሎች ጠላቶች በተነሡበት በኩል ለጦርነት ሒዶ በውጊያው ውስጥ ሞተ የሮም መንግሥትም የሚጠብቃትና የሚመራት የሌላት ሆነች።

እንዲህም ሆነ በዚያ ወራት ስለ ጦርነት ለመደራጀት የሮም ሰዎች ከሀገሩ ሁሉ አርበኞች የሆኑ ሰዎችን ሰበሰቡ ከውስጣቸውም ከላይኛው ግብጽ ስሙ አግሪጳዳ የሚባል የፍየሎች እረኛ የሆነ አንድ ሰው አለ። እርሱንም መኳንንቱ ወስደው በመንግሥት ፈረሶች ላይ ባልደራስ አድርገው ሾሙት እርሱም በጠባዩና በሥራው ሁሉ ኃይለኛና ብርቱ ነበር።

ከንጉሥ ኑማርያኖስ ሴቶች ልጆች አንዲቱ ወደርሱ በመስኮት ተመለከተች ወደደችውም መልምላም ወስዳ አገባችው ስሙንም ዲዮቅልጥያኖስ ብላ ሰይማ አነገሠችው። ከጥቂት ቀኖችም በኋላ ሰማይና ምድርን የፈጠረ #እግዚአብሔርን ትቶ ጣዖታትን አመለከ ቅዱስ ፋሲለደስም ሰምቶ እጅግ አዘነ የመንግሥትንም አገልግሎት ተወ።

ከዚህም በኋላ የንጉሥ ኑማርያኖስ ልጅ ዮስጦስና የፋሲለደስ ልጅ አውሳብዮስ ጠላቶቻቸውን ድል አድርገው የጠላቶቻቸውንም አገሮች አጥፍተው ደስ ብሏቸው ተመለሱ። ነገር ግን የነገሠው ዲዮቅልጥያኖስ የክብር ባለቤት #ክርስቶስን ክዶ አምልኮ ጣዖትን አቁሞ አገኙት እጅግም አዘኑ ተቆጥተውም ተነሡ ሰይፎቻቸውን መዝዘው ዲዮቅልጥያኖስን ገድለው የንጉሥ ኑማርያኖስን ልጅ ዮስጦስን ሊያነግሡ ወደዱ ፋሲለደስም ከዚህ ሥራ ከለከላቸው።

ከዚህም በኋላ ቅዱስ ፋሲለደስ ዘመዶቹን፣ ሠራዊቱን፣ አገልጋዮቹንም ሁሉ ሰበሰባቸውና በክብር ባለቤት በክርስቶስ ስም ደሙን ሊያፈስ እንደፈለገ አስረዳቸው ሁሉም እንዲህ ብለው መለሱለት አንተ በምትሞትበት ሞት እኛ ከአንተ ጋር እንሞታለን በዚህም ምክር በአንድነት ተሰማሙ።

ከዚህም በኋላ በንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስ ፊት ቁመው ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ታመኑ ከእርሳቸውም ግርማ የተነሣ ታላቅ ፍርሃትን ፈራ እነርሱ የመንግሥት ልጆች ናቸውና።

የቅዱስ ፊቅጦር አባት ኀርማኖስም ወደ ግብጽ አገር ይልካቸው ዘንድ በዚያም እንዲያሠቃዩዋቸው መከረው ሁሉንም እየአንዳንዳቸውን ለብቻቸው አድርጎ ላካቸው አባዲርንና እኀቱ ኢራኒን ወደ አንዲት አገር፣ አውሳብዮስንና ወንድሙ መቃርስን ወደሌላ ቦታ፣ ገላውዴዎስንም እንዲሁ አደረጉ። በናድሌዎስ ቴዎድሮስም እሼ በሚባል ዕንጨት ላይ በመቶ ሃምሳ ሦስት ችንካር ተቸንክሮ ገድሉን ፈጸመ።

ቅዱስ ፋሲለደስን ግን አምስት ከተማዎች ወዳሉበት ወደ አፍሪካ ምድር ወደ መኰንኑ ወደ መጽሩስ ላከው መጽሩስም በአየው ጊዜ መንግሥቱን ክብሩን ስለ ተወ እጅግ አደነቀ።

ክብር ይግባውና #ጌታችን_ክርስቶስም መልአኩን ልኮ በመንፈስ ወደ ሰማይ አውጥቶ በብርሃን ያጌጠ መንፈሳዊ ማደሪያን አሳየው ነፍሱም እጅግ ደስ አላት ከዚህም በኋላ ወደነበረበት መለሰው። ባሮቹን ግን ነፃ ያወጣቸው አሉ የቀሩትም ከእርሱ ጋር የሰማዕትነት አክሊልን የተቀበሉ ሰባት ሺህ ሠላሳ ሦስት የሚሆኑ አሉ።

ቅዱስ ፋሲለደስንም ታላቅ ስቃይን አሰቃዩት በመንኰራኲርና በተሣሉ የብረት ዘንጎች ሥጋውን ሰነጣጥቀውት ሞተ ክብር ይግባውና #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስም ያለ ጥፋት ከሞት አድኖ አስነሣው አሕዛብም ሁሉ ይህን ድንቅ ተአምር በአዩ ጊዜ አደነቁ ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስም አመኑ መኰንኑንም ረገሙት ጣዖቶቹንም ሰደቡ በእነርሱ ላይም ተቆጥቶ ራሶቻቸውን በሰይፍ ይቆርጧቸው ዘንድ ወታደሮቹን አዘዘ የሰማዕትነት አክሊልንም ተቀበሉ ቊጥራቸውም ዐሥራ አራት ሺህ ሰባት መቶ ወንዶች ሠላሳ ሰባት ሴቶች ናቸው።

ከዚህም በኋላ ቅዱስ ፋሲለደስን ሥጋው ሁሉ ቀልጦ እንደ ውኃ እስከሚሆን በብረት ምጣድ ውስጥ አበሰሉት መኰንኑም በተራራ ላይ ጥልቅ ጒድጓድ ቆፍረው በዚያ እንዲቀብሩት አዘዘ እንዲሁም አደረጉ። ያን ጊዜም ክብር ይግባውና #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ቅዱስ ፋሲለደስን ከሞት ደግሞ አስነሣው ወደ መኰንኑም መጥቶ እንዲህ ብሎ ጮኸ መኰንን መጽሩስ ሆይ እፈር ከሀዲ ንጉሥህም የረከሱ ጣዖቶችህም ይፈሩ እነሆ ክብር ይግባውና #ጌታዬ_ኢየሱስ_ክርስቶስ ያለ ጉዳት ከሞት ጤነኛ አድርጎ አስነሥቶኛልና።

ሕዝቡም ይህን ተአምር በአዩ ጊዜ ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ አምነው በሰማዕትነት ሞቱ ቁጥራቸውም ሁለት ሺህ ሦስት መቶ ሆነ።

ከዚህም በኋላ ቅዱስ ፋሲለደስን በውስጧ መጋዝ ካላት መንኰራኲር ላይ አውጥቶ ታላቅ ሥቃይን አሠቃየው ዳግመኛም በብረት ዐልጋ ላይ በሆዱ አስተኝተው ከበታቹ እሳትን አነደዱ ያን ጊዜም ክብር ይግባውና #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ተገለጠለት ከዚያ ስቃይም ውስጥ አንስቶ ያለ ጉዳት ጤነኛ አደረገው እንዲህም ብሎ ቃል ኪዳን ሰጠው ፋሲለደስ ሆይ ዕውቅ መታሰቢያህን ለሚያደርግ ሁሉ ወይም ለድኆች በስምህ ምጽዋትን ለሚሰጥ ወይም ለተራቈተ ልብስን ወይም በመታሰቢያህ ቀን ለቤተ ክርስቲያን መባ ለሚሰጥ በብዙም ቢሆን በጥቂት መታሰቢያህን ለሚያደርጉ ሁሉ እኔ በደላቸውን ሁሉ እተውላቸዋለሁ መኖሪያቸውንም በመንግሥተ ሰማያት ከአንተ ጋራ አደርጋለሁ።

ጌታችንም ይህን ካለው በኋላ በታላቅ ክብር ወደ ሰማያት ዐረገ ቅዱስ ፋሲለደስም በፍጹም ደስታ ደስ ተሰኘ።

ከዚህም በኋላ መጽሩስ መኰንን ከአማካሪዎቹ ጋር ተማከረ እንዲህም አላቸው ስሙ ፋሲለደስ ስለሚባል ስለዚህ ሰው ምን ላድርግ እርሱን ያላሠቃየሁበት የሥቃይ መሣሪያ ምንም የቀረ የለም ከሐሳቡም አልተመለሰም እነርሱም እንዲህ ብለው መከሩት ራሱን በሰይፍ ቆርጠህ ከእርሱ ተገላገል እነሆ የዚች አገር ሰዎች በእርሱ ምክንያት አልቀዋልና።

በዚያንም ጊዜ የቅዱስ ፋሲለደስን ራስ በሰይፍ እንዲቆርጡ መኰንኑ አዘዘና ቆረጡት የድል አክሊልን ተቀበለ ንቆ ሰለ ተዋት ምድራዊት መንግሥት ፈንታም ሰማያዊት መንግሥት አገኘ። ከሥጋውም ድንቆች የሆኑ ታላላቅ ተአምራት ተገለጡ ከእርሱም ጋር ሰማዕት ሁነው የሞቱ ሁሉም ቊጥራቸው ሃያ ሦስት ሺህ ሰባት መቶ ዘጠና ሦስት ሆነ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ ፋሲለደስና በሰማዕታት ሁሉ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
#ቅዱስ_ቆርኔሌዎስ_ሐዋርያዊ

በዚህችም ቀን የጭፍራ አለቃ የሆነ ትሩፋቱና ገድሉም ያማረ ጻድቅ ሰው ቆርኔሌዎስ የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው እርሱም በቅዱሳን አባቶቻችን ሐዋርያት ዘመን #እግዚብሔርን ያገለገለ ነው።

#እግዚአብሔር መልአክም ተገልጦለት ሐዋርያ ጴጥሮስን ይጠሩት ዘንድ ሰዎችን እንዲልክ ጴጥሮስም ወደርሱ እንዲመጣ ሊሠራው የሚገባውን ከእርሱ ከጴጥሮስ እንዲሰማ አዘዘው።

ጴጥሮስም ወደርሱ በደረሰ ጊዜ የ #እግዚአብሔርን ቃል አስተማረው ለርሱና ከእርሱ ጋር ላሉት ሁሉ ከሁሉ ቤተሰቡ ጋር አምኖ ተጠመቀ። ከዚህ በኋላ ጴጥሮስ ለእስክንድርያ አገር ቅስና ሾመው ወደርሷ በደረሰ ጊዜ የጣዖታትን አምልኮ ተመልታ አገኛትና አስተማራቸው ብዙዎችንም ወደቀናች ሃይማኖት መልሶ አጠመቃቸው መኰንኑ ድሜጥሮስም አምኖ ከወገኖቹ ጋር በእርሱ እጅ ተጠመቀ።

የኑሮውን ዘመንና ሐዋርያዊ ተጋድሎውን አድርሶ በሰላም አረፈ እርሱም ከአሕዛብ አስቀድሞ ያመነ የመጀመሪያ አማኒ ነው።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሱ ጸሎት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_ታዖድራ

በዚህችም ቀን ከእስክንድርያ አገር በንጉሥ ዘይኑን ዘመን ቅድስት ታዖድራ አረፈች።

ይችንም ቅድስት ሌላ ሰው አስገድዶ ከባሏ ወስዶ ከባሏ ጋር ያላትን አንድነት አበላሸ ያን ጊዜም ታላቅ ኀዘን በማዘን ተጸጸተች መሪር ልቅሶንም አለቀሰች የወንዶችንም ልብስ ለብሳ ወንድ መሰላ ከእስክንድርያ በሥውር ወጣች ስሟንም ቴዎድሮስ ብላ ሰየመችና ወደ ወንዶች ገዳም ገባች የምንኲስና ልብስንና የመላእክትን አስኬማ ለበሰች።

የሚያዩዋት ሁሉ እርሷ እንደ ጃንደረባ የሆነች ወንድ ትመስላቸው ነበር እርሷ ግን በረኃብ፣ በጽምዕ ሌሊት በመትጋት ቀን በመቆም ጸንታ በመጋደል ላይ ታገሠች እንዲህም በመጋደል ተጠምዳ ብዙ ዘመን ኖረች።

በዚያም ወራት እንዲህ ሆነ አንድ ሰው ከአንዲት ብላቴና ጋር አመነዘረ እርሷም ፀንሳ ወንድ ልጅን ወለደች ወላጆቿም ድንግልናሽን ያጠፋው ማነው ብለው ጠየቋት እርሷም በገዳም ውስጥ የሚኖር አባ ቴዎድሮስ እርሱ ደፍሮኝ ከእርሱ ፀነስኩ ብላ በዚች ቅድስት ታኦድራ ላይ በሐሰት ተናገረች።

ወላጆቿም በሰሙ ጊዜ እጅግ አዘኑ ሕፃኑንም ወደዚያ ገዳም አበ ምኔት ወሰዱት እንዲህም አሉት ይህ ሕፃን የልጅህ የመነኵሴው የቴዎድሮስ ልጅ ነው ። ያን ጊዜም አበ ምኔቱ ይቺን ቅድስት ታኦድራን ጠራትና እንዲህ አላት ይህን ክፉ ሥራ ለምን ሠራህ በመነኰሳቱም ሁሉ ላይ ኀፍረትንና ጒስቁልናን አመጣህ እርሷ ሴት መሆኗን አላወቀምና እርሷም አባቴ ሆይ በድያለሁና ይቅር በለኝ አለችው።

አበ ምኔቱም ተቆጥቶ ከገዳሙ አስወጥቶ አባረራት በበረሀ ውስጥ ሰባት ዓመት ኖረች ያም ሕፃን ከእርሷ ጋር ሁኖ ከሰይጣናት በሚመጡባት በብዙ መከራዎች ብዙ መከራዎች ላይ ታገሠች ብዙ ሥቃያትንም ፈጽሞ አሠቃዩዋት።

ከዚህም በኋላ ዳግመኛ ተቀብለው ወደ ገዳም አስገቡአት ጥቂት ቀንም ኖረች መልካም ተጋድሎዋንም ፈጽማ በሰላም አረፈች ነፍሷንም በ #እግዚአብሔር እጅ ሰጥታ የዘላለም ሕይወትን አገኘች።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎቷ ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_በነፍዝዝ_ሰማዕት

በዚህች ቀን የስሟ ትርጓሜ ጣፋጭ የሆነ የከበረች በነፍዝዝ በሰማዕትነት አረፈች። ይቺም ቅድስት በእድሜዋ ፈጽማ የሸመገለች ነበረች በፋርስ ንጉሥ በሳቦር ዘመንም መከራ ተቀበለች ከዘጠኝ መቶ ክርስቲያን ጋር ማርከው ወስደው አሠሩዋት የሠራዊቱም አለቃ ታላቅ ሥቃይን አሠቃይቶ ከዚያ በኋላ ራሷን በሰይፍ ቆረጠ።

ራሷንም ከአስቆረጣት በኋላ ከአንገቷ የፈሰሰው ደም እስከ ራቀ ድረስ ወደ ላይ ወጣ ከዚያ የተቀመጡ ጠላቶችም ኃይላቸው ደከመ። የፀሐይ ብርሃንም ጨለመ በዚያም ቦታ ደግሞ ጣፋጭ የሆነ መዐዛ ተመላ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎቷ ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ሦስቱ_ቅዱሳን_ገበሬዎች
(ሱርስ፣ አጤኬዎስ፣ መስተሐድራ)

በዚህችም ቀን ስማቸው ሱርስ፣ አጤኬዎስ፣ መስተሐድራ የሚባል ሦስት ገበሬዎች የእስና አገር ሰዎች በሰማዕትነት አረፉ ። አርያኖስም ከሀገሪቱ በስተደቡብ ምንም ሳያስቀር ወታደሮቹ እስከ ደከሙ ድረስ ሰይፋቸውንም ወደ አፎቱ መልሰው ነበር የአገር ሰዎችን ጨርሶ ገድሎ ሲመለስ እሊህ ሦስቱ ገበሬዎች ከዱር ሲመለሱ በከተማ መካከል በተገናኙት ጊዜ እኛ ክርስቲያኖች ነን ብለው በግልጥ ጮኹ አርያኖስም ሰምቶ ወታደሮቹን እሊህን ገበሬዎች ትገድሏቸው ዘንድ ይገባል አላቸው።

ወታደሮቹም እኛ ደክመናል ሰይፎቻችንንም ወደ አፎታቸው አስገብተናል አሉት እሊህ ቅዱሳንም ሰምተው እነሆ መቆፈሪያዎች ከእኛ ጋራ አሉ በእነርሱ ግደሉን አሉ ከዚያም አንገታቸውን በደንጊያ ላይ አድርገውላቸው ቆረጡአቸው።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ሁሉ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_መስከረም_11)
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#መስከረም_11_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ዕብራውያን 12
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹-² እንግዲህ እነዚህን የሚያህሉ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን፥ እኛ ደግሞ ሸክምን ሁሉ ቶሎም የሚከበንን ኃጢአት አስወግደን፥ የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤ እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና።
³ በነፍሳችሁ ዝላችሁ እንዳትደክሙ፥ ከኃጢአተኞች በደረሰበት እንዲህ ባለ መቃወም የጸናውን አስቡ።
⁴ ከኃጢአት ጋር እየተጋደላችሁ ገና ደምን እስከ ማፍሰስ ድረስ አልተቃወማችሁም፤
⁵-⁶ እንደ ልጆችም ከእናንተ ጋር፦ ልጄ ሆይ፥ የጌታን ቅጣት አታቅልል፥ በሚገሥጽህም ጊዜ አትድከም፤ ጌታ የሚወደውን ይቀጣዋልና፥ የሚቀበለውንም ልጅ ሁሉ ይገርፈዋል ብሎ የሚነጋገረውን ምክር ረስታችኋል።
⁷ ለመቀጣት ታገሡ፤ እግዚአብሔር እንደ ልጆች ያደርግላችኋልና፤ አባቱ የማይቀጣው ልጅ ማን ነው?
⁸ ነገር ግን ሁሉ የቅጣት ተካፋይ ሆኖአልና ያለ ቅጣት ብትኖሩ ዲቃላዎች እንጂ ልጆች አይደላችሁም።
⁹ ከዚህም በላይ የቀጡን የሥጋችን አባቶች ነበሩን እናፍራቸውም ነበር፤ እንዴትስ ይልቅ ለመናፍስት አባት አብልጠን ልንገዛና በሕይወት ልንኖር በተገባን?
¹⁰ እነርሱ መልካም ሆኖ እንደ ታያቸው ለጥቂት ቀን ይቀጡን ነበርና፥ እርሱ ግን ከቅድስናው እንድንካፈል ለጥቅማችን ይቀጣናል።
¹¹ ቅጣት ሁሉ ለጊዜው የሚያሳዝን እንጂ ደስ የሚያሰኝ አይመስልም፥ ዳሩ ግን በኋላ ለለመዱት የሰላምን ፍሬ እርሱም ጽድቅን ያፈራላቸዋል።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ያዕቆብ 3
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ ወንድሞቼ ሆይ፥ ከእናንተ ብዙዎቹ አስተማሪዎች አይሁኑ፥ የባሰውን ፍርድ እንድንቀበል ታውቃላችሁና።
² ሁላችን በብዙ ነገር እንሰናከላለንና፤ በቃል የማይሰናከል ማንም ቢኖር እርሱ ሥጋውን ሁሉ ደግሞ ሊገታ የሚችል ፍጹም ሰው ነው።
³ እነሆ፥ ፈረሶች ይታዘዙልን ዘንድ ልጓም በአፋቸው ውስጥ እናገባለን፥ ሥጋቸውንም ሁሉ እንመራለን።
⁴ እነሆ፥ መርከቦች ደግሞ ይህን ያህል ታላቅ ቢሆኑ በዐውሎ ነፋስም ቢነዱ፥ የመሪ ፈቃድ ወደሚወደው ስፍራ እጅግ ታናሽ በሆነ መቅዘፊያ ይመራሉ።
⁵ እንዲሁም አንደበት ደግሞ ትንሽ ብልት ሆኖ በታላላቅ ነገር ይመካል። እነሆ፥ ትንሽ እሳት እንዴት ያለ ትልቅ ጫካ ያቃጥላል።
⁶ አንደበትም እሳት ነው። አንደበት በብልቶቻችን መካከል ዓመፀኛ ዓለም ሆኖአል፤ ሥጋን ሁሉ ያሳድፋልና፥ የፍጥረትንም ሩጫ ያቃጥላል፥ በገሃነምም ይቃጠላል።
⁷ የአራዊትና የወፎች የተንቀሳቃሾችና በባሕር ያለ የፍጥረት ወገን ሁሉ በሰው ይገራል፥ ደግሞ ተገርቶአል፤
⁸ ነገር ግን አንደበትን ሊገራ ማንም ሰው አይችልም፤ የሚገድል መርዝ የሞላበት ወላዋይ ክፋት ነው።
⁹ በእርሱ ጌታንና አብን እንባርካለን፤ በእርሱም እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠሩትን ሰዎች እንረግማለን፤
¹⁰ ከአንድ አፍ በረከትና መርገም ይወጣሉ። ወንድሞቼ ሆይ፥ ይህ እንዲህ ሊሆን አይገባም።
¹¹ ምንጭስ ከአንድ አፍ የሚጣፍጥንና የሚመርን ውኃ ያመነጫልን?
¹² ወንድሞቼ ሆይ፥ በለስ ወይራን ወይስ ወይን በለስን ልታፈራ ትችላለችን? ከጨው ውኃም ጣፋጭ ውኃ አይወጣም።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 10
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ በቂሣርያም ኢጣሊቄ ለሚሉት ጭፍራ የመቶ አለቃ የሆነ ቆርኔሌዎስ የሚሉት አንድ ሰው ነበረ።
² እርሱም ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር እግዚአብሔርን የሚያመልክና የሚፈራ ለሕዝብም እጅግ ምጽዋት የሚያደርግ ወደ እግዚአብሔርም ሁልጊዜ የሚጸልይ ነበረ።
³ ከቀኑም ዘጠኝ ሰዓት ያህል፦ ቆርኔሌዎስ ሆይ የሚለው የእግዚአብሔር መልአክ ወደ እርሱ ሲገባ በራእይ በግልጥ አየው።
⁴ እርሱም ትኵር ብሎ ሲመለከተው ደንግጦ፦ ጌታ ሆይ፥ ምንድር ነው? አለ። መልአኩም አለው፦ ጸሎትህና ምጽዋትህ በእግዚአብሔር ፊት ለመታሰቢያ እንዲሆን አረገ።
⁵ አሁንም ወደ ኢዮጴ ሰዎችን ልከህ ጴጥሮስ የሚባለውን ስምዖንን አስመጣ።
⁶ እርሱ ቤቱ በባሕር አጠገብ ባለው በቍርበት ፋቂው በስምዖን ዘንድ እንግድነት ተቀምጦአል፤ ልታደርገው የሚገባህን እርሱ ይነግርሃል።
⁷ የተናገረውም መልአክ በሄደ ጊዜ፥ ከሎሌዎቹ ሁለቱን፥ ከማይለዩትም ጭፍሮቹ እግዚአብሔርን የሚያመልክ አንዱን ወታደር ጠርቶ፥
⁸ ነገሩን ሁሉ ተረከላቸው ወደ ኢዮጴም ላካቸው።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#መስከረም_11_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"ወይርአዩ አሕዛብ በቅድመ አዕይንቲነ። በቀለ ደሞሙ፡ለአግብርቲከ፡ዘተክዕወ። ይባዕ ቅድሜከ ገዐሮሙ ለሙቁሓን"። መዝ 78፥10-11።
"አሕዛብ፦ አምላካቸው ወዴት ነው? እንዳይሉ፥ የፈሰሰውን የባሪያዎችህን ደም በቀል በዓይኖቻችን ፊት አሕዛብ ይወቁ።
የእስረኞች ጩኸት ወደ ፊትህ ይግባ፤ እንደ ክንድህም ታላቅነት ሊገደሉ የተፈረደባቸውን አድን"። መዝ 78፥10-11።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#መስከረም_11_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሉቃስ 21
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹² ከዚህም ሁሉ በፊት እጃቸውን በላያችሁ ይጭናሉ ያሳድዱአችሁማል፤ ስለ ስሜም ወደ ምኵራብና ወደ ወኅኒ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፥ ወደ ነገሥታትና ወደ ገዥዎችም ይወስዱአችኋል፤
¹³ ይህም ለምስክርነት ይሆንላችኋል።
¹⁴ ስለዚህ እንዴት እንድትመልሱ አስቀድማችሁ እንዳታስቡ በልባችሁ አኑሩት፤
¹⁵ ወደረኞቻችሁ ሁሉ ሊቃወሙና ሊከራከሩ የማይችሉትን አፍና ጥበብ እሰጣችኋለሁና።
¹⁶ ወላጆችም ስንኳ ወንድሞችም ዘመዶችም ወዳጆችም አሳልፈው ይሰጡአችኋል፥ ከእናንተም አንዳንዱን ይገድላሉ፤
¹⁷ በሁሉም ስለ ስሜ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ።
¹⁸ ከራሳችሁም አንዲት ጠጉር ስንኳ አትጠፋም፤
¹⁹ በመታገሣችሁም ነፍሳችሁን ታገኛላችሁ።
²⁰ ኢየሩሳሌም ግን በጭፍራ ተከባ ስታዩ በዚያን ጊዜ ጥፋትዋ እንደ ቀረበ እወቁ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #ቅዱስ_ባስልዮስ_ቅዳሴ ነው። መልካም የቅዱስ ፋሲለደስ የዕረፍት በዓል፣ የቅድስት ታዖድራ፣ የቅዱስ ቀርኔሌዎስ፣ የቅድስት በነፍዘዝ ሰማዕትና የቅዱሳን ሱርስ፣ አጤኬዎስ፣ መስተሐድራ የዕረፍት በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#መስከረም_12

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
መስከረም ዐሥራ ሁለት መላእክት አለቃ #የቅዱስ_ሚካኤል የበዓሉ መታሰቢያ ነው፣ #ጉባኤ_ኤፌሶን የቅዱሳን የሁለት መቶ ኤጲስቆጶሳት ስብሰባ ሆነ

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ሚካኤል_ሊቀ_መላእክት

መስከረም ዐሥራ ሁለት በዚች ቀን የመላእክት አለቃ የቅዱስ ሚካኤል የበዓሉ መታሰቢያ ነው።

በዚችም ቀን ክብር ይግባውና #እግዚአብሔር ወደ አሞጽ ልጅ ወደ ነቢይ ኢሳይያስ ላከው ይቅርም ብሎት ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ ሕዝቅያስ ሒዶ #እግዚአብሔር ይቅር እንዳለውና ከደዌው እንዳዳነው በዕድሜውም ላይ ዐሥራ አምስት ዓመት እንደ ጨመረለት ይነግረው ዘንድ አዘዘው። ንጉሱም ሚስት አግብቶ ምናሴን እስከወለደው ድረስ እንዲሁ ሆነ።

ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ለንጉሥ ሕዝቅያስ ያደረገለት ተአምር፡-

ከጻድቁ ንጉሥ ከቅዱስ ዳዊት በኋላ በእስራኤል እንደ ሕዝቅያስ ያለ ሌላ ጻድቅ ንጉሥ አልተነሣም፡፡ ከሕዝቅያስ በኋላ የተነሡት ሁሉም ጣዖትን አምልከዋል፣ ለጣዖታቱም የሚሆን መሠዊያ ሠርተዋል፡፡ ንጉሡ ሕዝቅያስ በነገሠ ጊዜ ግን ጣዖታትን ሰባብሯቸዋል፣ የእስራኤል ልጆች ያመልኩት የነበረውን የነሐስ እባብ ቆራርጦታል፡፡ #እግዚአብሔርንም በማመኑ መንግሥቱ እጅግ ሰምሮለታል፡፡ #እግዚአብሔርም ያሳጣው በጎ ነገርም የለም፡፡

ሕዝቅያስ በነገሠ በ14ኛው ዘመን የፋርሱ ነጉሥ ሰናክሬም መጥቶ ኢየሩሳሌምን ከበባት፡፡ ይህም ሰናክሬም በወቅቱ እንደ እርሱ ያለ ኃይለኛ የለም ነበርና ሁሉም የምድር ነገሥታት ይፈሩትና ይገዙለት ነበር፡፡ ሕዝቅያስም ከሰናክሬም ግርማና የጦሩ ብዛት የተነሣ ፈርቶ ኢየሩሳሌምን እንዳያጠፋት ብዙ ወርቅና ብር እጅ መንሻ ቢልክለትም ሰናክሬም ግን እጅ መንሻውን አልቀበልም ብሎ ኢየሩሳሌምን ያጠፋ ዘንድ ተነሣ፡፡ ለሕዝቅያስም ‹‹አምላካችሁ #እግዚአብሔር ከእኔ እጅ ሊያደናችሁ ከቶ አይችልም›› የሚል የስድብን ቃል ላከለት፡፡

ሁለተኛም በልዑል #እግዚአብሔር ላይ የስድብን ቃል ጽፎ ደብዳቤ ላከለት፡፡ ሕዝቅያስም ይህን ሲሰማ ወደ #እግዚአብሔር ቤት ገብቶ አለቀሰ፡፡ ልብሱንም ቀዶ ማቅ በመልበስ የሰናክሬምን ድፍረትና በኢየሩሳሌምና በሕዝቧ ላይ ሊያደርስ ያሰበውንም ጥፋት ወደ #እግዚአብሔር አሳሰበ፡፡ ቀጥሎም ሕዝቅያስ ሰናክሬም የተናገረውን ይነግሩት ዘንድ ስለ ሕዝቡም እንዲጸልይ ለነቢዩ ኢሳይያስ መልእክት ላከበት፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስም ወደ #እግዚአብሔር አመለከተ፡፡

ከዚህም በኋላ ቅዱስ ሚካኤል ስለ ንጉሡ ለነቢዩ መልእክትን አመጣለት፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስም የመጣለትን መልስ እንዲህ ብሎ ለሕዝቅያስ ላከለት፡- ‹‹ልብህን አጽና፣ አትፍራ፡፡ በዓለሙ ሁሉ እንደ እርሱ ያለ ያልተሰማ ዕፁብ ድንቅ የሆነ ሥራ በሰናክሬም ላይ #እግዚአብሔር ይሠራል›› አለው፡፡ ከዚህም በኋላ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ከ #እግዚአብሔር ዘንድ ተልኮ መጥቶ 185,000 (መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ) የፋርስ ሠራዊቶችን በአንድ ሌሊት ገደላቸው፡፡ 2ኛ ነገ 17፣19፡፡ የለኪሶ ሰዎችም ሲነጋ በተነሡ ጊዜ ምድሪቱን በእሬሳ ተሞልታ ስላገኟት በድንጋጤና በፍርሃት ከንጉሣ ጋር ሸሽተው ነነዌ አገር ገቡ፡፡

ንጉሡ ሰናክሬምም ወደ አምላኩ ወደ ጣዖቱ ቤት ገብቶ ሲጸልይ የገዛ ልጆቹ በሰይፍ መትተው ገደሉትና ወደ አራራት ኩበለሉ፡፡2ኛ ነገ ምዕራፍ 19፡፡ ንጉሥ ሕዝቅያስም ከሰናክሬም እጅ ያዳነውን #እግዚአብሔርን አመሰገነ፡፡

ከዚህም በኋላ ሕዝቅያስ ታሞ ለሞት በደረሰ ጊዜ ነቢዩ ኢሳይያስ ወደ እርሱ መጥቶ ‹‹ #እግዚአብሔር ‹ትሞታለህ እንጂ አትድንም› ብሎሃል›› አለው፡፡ ነገር ግን ሕዝቅያስ አሁንም ልብሱንም ቀዶ ማቅ በመልበስ ጸሎቱን ወደ #እግዚአብሔር አቀረበ፡፡ በዚህ ጊዜ ነው ቅዱስ ሚካኤል #እግዚአብሔር ዘንድ ተልኮ መጥቶ ነቢዩ ኢሳይያስን ወደ ንጉሡ ሕዝቅያስ ሄዶ በዕድሜው ላይ 15 ዓመት እንደተጨመረለት እንዲነግረው ያዘዘው፡፡

መልአኩ እንዳዘዘው ነቢዩ ኢሳይያስ ንጉሥ ሕዝቅያስን " #እግዚአብሔር የአባትህ የዳዊት አምላክ ጸሎትህን ሰማሁ፣ ዕንባህንም አየሁ፣ እነሆ እኔ አድንሃለሁ፡፡ በዘመኖችህም 15 ዓመት ጨምሬልሃለሁ፡፡ ከፋርስ ንጉሥ እጅም አድንሃለሁ፡፡ ይህችን አገር ስለ እኔና ስለ ባለሟሌ ዳዊት አጽንቼ እጠብቃታለሁ›› ብሎሃል ብሎ የተላከውን ነገረው፡፡ ከዚህም በኃላ ንጉሥ ሕዝቅያስ የ #እግዚአብሔር ኃይል ስላደረበት የምድር ነገሥታት ሁሉ ፈርተውት እየተገዙለት እጅ መንሻን ያገቡለት ጀመር፡፡ ንጉሡም ዕድሜው ከተጨመረለት በኃላ ሚስት አግብቶ ምናሴን እስኪወልድ ድረስ ቆየ፡፡ በመንበረ መንግሥቱም 29 ዓመት ነግሦ ከኖረ በኋላ #እግዚአብሔርን አገልግሎ በሰላም ዐረፈ፡፡

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ ሚካኤል አማላጅነት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ጉባኤ_ኤፌሶን

በዚችም ቀን ደግሞ በኤፌሶን ከተማ የቅዱሳን የሁለት መቶ ኤጲስቆጶሳት ስብሰባ ሆነ ይህም ለታላላቆች ጉባኤያት ሦስተኛ ነው።

ስብሰባቸውም የተደረገው የታላቁ ቴዎዶስዮስ ልጅ አርቃድዮስ የወለደው ታናሹ ቴዎዶስዮስ በነገሠ በሃያ ዓመት ነው። የስብሰባቸውም ምክንያት የቊስጥንጥንያ ሊቀ ጳጳሳት በሆነ በንስጥሮስ ነው። እርሱ ስቶ እንዲህ ብሏልና እመቤታችን #ድንግል_ማርያም አምላክን በሥጋ አልወለደችውም እርሷ ዕሩቅ ሰውን ወልዳ ከዚህ በኋላ በውስጡ የ #እግዚአብሔር ልጅ አደረበት ከሥጋ ጋር በመዋሐድ አንድ አልሆነም በፈቃድ አደረበት እንጂ። ስለዚህም ክርስቶስ ሁለት ጠባይ ሁለት ባህርይ አሉት የተረገመ የከ*ሐዲ ንስጥሮስ የከፋች ሃይማኖቱ ይቺ ናት።

ስለ እርሱም የተሰበሰቡ እሊህ አባቶች ከእርሱ ጋር ተከራከሩ ከቅድስት #ድንግል_ማርያም የተወለደው አምላክ እንደሆነ ቅዱስ ገብርኤል መልአክ በአበሠራት ጊዜ ከተናገረው ቃል ምስክር አመጡ። እንዲህ የሚል #እግዚአብሔር ከአንቺ ጋር ነው ከአንቺ የሚወለደውም ጽኑዕ ከሀሊ ነው የልዑል #እግዚአብሔር ልጅም ይባላል ።

ዳግመኛም እነሆ #ድንግል በድንግልና ፀንሳ ወንድ ልጅን ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ትለዋለች ብሎ በትንቢቱ ከተናገረው ከኢሳይያስ ቃል ሁለተኛም ከእሴይ ዘር ይተካል ከእርሱም ለአሕዛብ ተስፋቸው ይሆናል።

ዳግመኛም የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ ቄርሎስ ገሠጸው መከረው ስለዚህም እንዲህ ሲል አስረዳው ክብር ይግባውና የ #ክርስቶስ የመለኮቱና የትስብእቱ ባሕርያት በመዋሐድ አንድ ከሆኑ በኋላ አይለያዩም አንድ ባሕርይ በመሆን ጸንተው ይኖራሉ እንዲህም አምነን ሰው የሆነ #እግዚአብሔር ቃል አንዲት ባሕርይ ነው እንላለን።

ከ*ሀዲ ንስጥሮስ ግን ከክፉ ሐሳቡ አልተመለሰም ከሹመቱም ሽረው እንደሚአሳድዱትም ነገሩት። እርሱ ግን የጉባኤውን አንድነት አልሰማም ስለዚህም ከሹመቱ ሽረው ረግ*መው ከቤተ ክርስቲያን ለይተው አሳደ*ዱት ወደ ላይኛውም ግብጽ ሒዶ በዚያ ምላሱ ተጎልጒሎ እንደ ውሻ እያለከለከ በክፉ አሟሟት ሞተ።

እሊህም ሁለት መቶ ኤጲስቆጶሳት አባቶች ሃይማኖትን አጸኑዋት በዚህም ጉባኤ ውስጥ እንዲህ ብለው ጻፉ እመቤታችን ቅድስት #ድንግል_ማርያም ከእርሷ ሰው የሆነውን የ #እግዚአብሔርን አካላዊ ቃል በሥጋ ወለደችው።

ከዚህም በኋላ ሥርዓትን ሠርተው ሕግንም አርቅቀው በእጆቻቸው ጽፈው ለምእመናን ሰጡ። እኛም የሕይወትንና የድኅነትን መንገድ ይመራን ዘንድ #እግዚአብሔርን እንለምነው። ለእርሱም ክብር ምስጋና ይሁን ለዘላለሙ አሜን።
በተጨማሪ በዚች ሰማዕት #ቅዱስ_አፍላሆስ መታሰቢያውና የሥጋው ፍልሰት ነው። የእስክድርያ አገር የሆኑ ባልንጀሮቹ ሰማዕታትም መታሰቢያቸው ነው። #የሰማዕታት_ቅዱሳን_ሉዩራስና_ባሌኒኮስ#ቅዱስ_ኢያቄምና_ቅድስት_ሐናም መታሰቢያቸው ነው።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳን አማላጅነት ይማረን ለዘላለሙ አሜን ።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_መስከረም_12 እና #ከገድላት_አንደበት)
2024/09/25 07:25:21
Back to Top
HTML Embed Code: