Telegram Web Link
➛አንዳንድ የስነ መለኮት ምሁራን ትንቢተ ኢሳይያስን ከይዘቱ አንጻር በአጭር አገላለጽ ሲገልጹት “በአራት ርእሰ አንቀጾች መጠቃለል የሚችል ነው” ይላሉ፡፡ እነርሱም #እግዚአብሔር፣ ሰው፣ ዓለምና ድኅነት በሚሉ ናቸው፡፡ ይኽን ሐሳብ በአንድ ዓረፍተ ነገር እንግለጸው ቢባል እንደሚከተለው ይኾናል፡- “የእስራኤል ቅዱስ #እግዚአብሔር ኃጢአትን ይጸየፋል፤ ይኽ ኃጢአትም የሰውን ልጅ በሙሉ ያደከመና መላውን ዓለም ከፍርድ በታች እንዲኾኑ ያደረገ ነው፡፡ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ግን ይኽን ፍርድ በራሱ ተሸክሞ ይቀድሰንና ያከብረን ዘንድ ፍጹም ሰው ኾነ፡፡”

ትንቢተ ኢሳይያስን በሦስት ክፍል መክፈል እንችላለን፡፡
1, የመዠመሪያው ክፍል (ምዕራፍ ፩-፴፭) በኢሳይያስ ዘመን በኾኑት ድርጊቶች ምክንያት የተጻፈ ነው፡፡ ይኽ ክፍል #እግዚአብሔር የሰው ልጆችን (ሕዝብንም አሕዛብንም) በሙሉ እንደተቈጣ፤ የሰው ልጅ በሙሉ ጽቅድ ስለጐደለውም መለኮታዊ ቅድስና እንደሚያስፈልገው የሚገልጽ ነው፡፡

2, ኹለተኛው ክፍል (ምዕራፍ ፴፮-፴፱) ከኢሳይያስ ዘመን በኋላ በኾነው በባቢሎን ምርኮ ምክንያት ተጽፏል፡፡ ይኽ ክፍል ቅዱስ #እግዚአብሔር በጠላቶቹ (ዲያብሎስና ሠራዊቱ) ድል እንደሚያደርጋቸው የሚናገር ነው፡፡ ይኽ ክፍል በዳዊት ልጅ፣ በሚመጣውና በሚነሣው (በሞተውና በተነሣው) መሲሕ እኛ የምንቀዳጀውን ድል አብሮ ይናገራል፡፡ ንጉሥ ሕዝቅያስ ትሞታለኽ ተብሎ እንደገና ፲፭ ዓመት በዕድሜው ላይ መጨመሩ ይኽን ምስጢር የሚያስረዳ ነው።

3, ሦስተኛው ክፍል (ምዕራፍ ፵-፷፮) ደግሞ የጽዮንን ዘለዓለማዊ ክብርን ያሳያል፡፡ በዚኽም በ #ጌታችን_በኢየሱስ_ክርስቶስ የሚገኘው ድኅነት እንደምን ለሰው ልጆች ዕረፍትን እንደሚሰጥ የሚናገር ነው፡፡

#ነቢዩ_ኢሳይያስና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤት ክርስቲያን

ነቢዩ ኢሳይያስንና ኢትዮጵያውያን ነጣጥሎ ማየት ፈጽሞ አይቻልም፡፡ ኢትዮጵያውያን እንኳንስ በሃገራቸው በሌላ ሃገር ሲሔዱም ከልብሳቸውና ከስንቃቸው ጋር ይዘዉት እየሔዱ ያነቡት እንደነበር ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ምስክራችን ነው /ሐዋ.፰፡፳፮-፵/፡፡ በዘወትር ጸሎታችን ውስጥ፡- “ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ #እግዚአብሔር ጸባዖት ፍጹም ምሉዕ ሰማያተ ወምድረ ቅድሳተ ስብሐቲከ” የምንለውም ከትንቢተ ኢሳይያስ በቀጥታ የተወሰደ ነው /ኢሳ.፮/፡፡ በየቀኑ ለ #እግዚአብሔር በቤተ ክርስቲያን በሚቀርበው የቅዳሴ፣ የሰዓታት፣ የማኅሌት ምስጋናና ጸሎት ትንቢተ ኢሳይያስን ሳያነሣ አያልፍም፡፡ ሥርዓተ ቅዳሴአችን፡- “አሐዱ #አብ_ቅዱስ አሐዱ #ወልድ_ቅዱስ አሐዱ ውእቱ #መንፈስ_ቅዱስ” ብሎ መዠመሩ፤ በፍሬ ቅዳሴአችን ዲያቆኑ፡- “አውሥኡ” ሲል “ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ” ሳይል የሚያልፍ ሊቅ የለም፡፡ ሰዓታቱ በብዛት “ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ ዘበተዋሕዶ ይሤለስ” እያለ ይፈጽማል፡፡ የማኅሌቱ ምስጋና መዠመሪያም ካህኑ ከማዘከሩ በፊት “ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ” ብሎ አመስግኖ አዘክሮ ይዠምራል፡፡ ኪዳንም “ #ቅዱስ_እግዚአብሔር#ቅዱስ_ኃያል#ቅዱስ_ሕያው_ዘኢይመውት” ብሎ ይዠምራል፡፡ በአጠቃላይ ትንቢተ ኢሳይያስና ኢትዮጵያውያን የአንድ ሳንቲም ኹለት ገጽታ ናቸው፡፡

➛የነቢዩ የመጨረሻ ዕረፍቱ

ነቢዩ ኢሳይያስ በዚኽ አገልግሎቱ፥ የአይሁድ ትውፊት እንደሚያስረዳው እስከ ፮፻፹፰ ዓ.ዓ. ቀጥሏል፡፡ ይኽም ማለት በነቢይነት ከ፶፪ ዓመት በላይ አገልግሏል ማለት ነው፡፡ መስከረም ፮ ቀን የሚነበበው ስንክሳርም “ትንቢት እየተናገረ የኖረበት ዘመን ፸ ዘመን ከዚያም በላይ ይኾናል” ይላል፡፡
ስንክሳሩ እንደሚነግረን ነቢዩ ኢሳይያስ የሞተው በሕዝቅያስ ልጅ በንጉሡ ምናሴ ላይ ትንቢት ስለተናገረ ነው፡፡ ንጉሡ ጣዖትን ስለማቆሙና ስለማምለኩ ስለገሠፀው ተቈጥቶ በዕንጨት መሰንጠቂያ መጋዝ በራሱና በእግሮቹ መካከል ሰነጠቀው፡፡ ምስክርነቱንም በዚኽ ፈጸመ፡፡ ሊቃውንት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡- “በመጋዝ ተሰነጠቁ” ያለው ነቢዩ ኢሳይያስን ነው/ዕብ.፲፩፡፴፯/፡፡

#ለእግዚአብሔር ምስጋና ይኹን፤ እኛንም በጸሎቱ ይማረን፤ በረከቱም ከኹላችን ጋር ትኑር ለዘለዓለሙ አሜን!!!

ዋቢ ድርሳናት፡-
© የትንቢተ ኢሳይያስ አንድምታ መቅድም፣ በሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ሐዲስ የተዘጋጀ፤
© የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት፣
© ስንክሳር፣
© A Patristic Commentary on The Book of Isaiah by Fr. Tadros Y. Malaty፡፡
#መስከረም_7

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
መስከረም ሰባት በዚህች ቀን አምላክን የወለደች የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እናት #የቅድስት_ሐና ልደቷ ነው፣ የመጥምቁ ዮሐንስ እናት የከበረች #ቅድስት_ኤልሳቤጥ አረፈች፣ የእስክንድርያ አገር ሊቀ ጳጳሳት #ቅዱስ_ዲዮስቆሮስ አረፈ፣ የከበረ አባት #ቅዱስ_ሳዊርያኖስ አረፈ፣ የከበሩ #አጋቶንና_ጴጥሮስ_ዮሐንስና_አሞን እናታቸውም ራፈቃ በሰማእትነት አረፉ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_ሐና_እመ_እግዝእትነ_ማርያም

መስከረም ሰባት በዚህች ቀን አምላክን ለወለደች ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል #ማርያም እናቷ የሆነች የተመሰገነች የቅድስት ሐና ልደቷ ነው።

ይችም ቅድስት ከኢየሩሳሌም አገር ከሌዊ ነገድ ከካህኑ አሮን ትውልድ የሌዊ የሜልኪ ልጅ ለሆነ ለማጣት ('ጣ' ጠብቆ ይነበብ) ልጁ ናት። ለማጣትም ሦስት ሴቶች ልጆች አሉት የታላቂቱም ስሟ ማርያም ናት ሁለተኛዋም ስሟ ሶፍያ ሦስተኛዪቱም ስሟ ሐና ናት ታላቂቱ ማርያምም ለባል ተድራ አዋላጅ የሆነች ሰሎሜን ወለደቻት እርሷም መድኃኒታችንን ከወለደችበት ጊዜ ጀምሮ በስደቷም ወራት ከአረጋዊ ዮሴፍ ጋር እመቤታችንን ድንግል #ማርያምን ያገለገለቻት ናት።

ሶፍያም ለባል ተድራ ለመጥመቁ ዮሐንስ እናቱ የሆነች ቅድስት ኤልሳቤጥን ወለደቻት። ይችንም ቅድስት ሐናን ከይሁዳ ነገድ ለሆነ ጻድቅ ስሙ ኢያቄም ለሚባል አጋቧት። (ሰሎሜና ኤልሳቤጥ ለቅድስት ሐና የእኅትማማች ልጆች ናቸው።)

ቅድስት ሐና ኢያቄምን አግብታ ስትኖር የቴክታና እና የጴጥሪቃ ምክነት በዘር ወርዶ መክና በመኖሯ የዐይኗ ማረፊያ የልቧ ተስፋ የሚሆን ልጅ እንዲስጣት ፈጣሪዋን ስትማጸን ኖራለች።

የነገሩትን የማይረሳ የለመኑትን የማይነሳ አምላክ ልመናዋን ሰምቶ ሐምሌ ፴ ራእይ አየች። ራእዩንም ከባሏ ከኢያቄም ጋር ተወያየተው ምንጣፍ ለይተው ሱባኤ ገቡ።

ከአንድ ሱባኤ በኋላ ነሐሴ ፯ ቀን #ጌታ ቅዱስ ገብርኤልን ልኮ እንደሚወልዱ አበሠራቸው። ከዚያም #እመቤታችን ጸንሳ ልዩ ልዩ ተአምራትን አድርጋለች። ሳምናስን ከሞት አስነስታለች። በርሴባን ዐይኗን አብርታለች። ከዚያም በአይሁድ ተንኮልና አሳዳጅነት ወደ ሊባኖስ ተራራ ተሰዳ ድንግል ማርያምን ወልዳለች። በመውለዷም ሕዳሴ አካል አግኝታ ከኖረች በኋላ ዐርፋለች።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_ኤልሳቤጥ

በዚችም ቀን የመጥምቁ ዮሐንስ እናት የከበረች ኤልሳቤጥ አረፈች። ቅድስት ኤልሳቤጥ ትውልዷ ከነገደ ሌዊ ነው:: ሐረገ ሙላዷም ከቅዱስ አሮን ካህን ወገን ይመዘዛል:: ከአሮን በቴክታና በጥሪቃ ወርዶ ሔርሜላ ላይ ይደርሳል::

ይህቺ ሔርሜላ የምትባል ደግ ሴት ማጣት ("ጣ" ጠብቆ ይነበብ) የሚባል የተባረከ ሰው አግብታ 3 ቡሩካት ልጆችን ወለደች:: የመጀመሪያዋን 'ማርያም' አሏት:: እርሷ ቅድስት ሰሎሜን ወለደች:: ሁለተኛዋን 'ሶፍያ' አሏት:: እርሷ ደግሞ ቅድስት ኤልሳቤጥን ወለደች:: ሦስተኛዋ ግን የተለየች ናት:: 'ሐና' ብለው ሰየሟት:: እርሷም የሰማይና የምድር ንግሥት የሆነችውን ድንግል #ማርያምን ወለደች:: በዚህም መሠረት ድንግል ማርያም: ቅድስት ኤልሳቤጥና ቅድስት ሰሎሜ የእህትማማች ልጆች ናቸው::

ቅድስት ኤልሳቤጥ እድሜዋ በደረሰ ጊዜ ስም አጠራሩ የከበረ: ደግ ካህን ለሆነ: ለቅዱስ ዘካርያስ አጋቧት:: እነርሱም ልጅ አልነበራቸውም ነበርና በብስራተ መልአክ ቅድስት ኤልሳቤጥ 90 ካህኑ ዘካርያስ 100 ሳሉ መስከረም 26 ቀን ታላቁን ሰው ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቁን ጸንሰች ለ6 ወራት ራሷን ሠወረች::

ድንግል እመቤታችን የኤልሳቤጥን መጽነስ በሰማች ጊዜ ለሰላምታ ሄዳ ነበር። በዚያም ወቅት ቅድስት ኤልሳቤጥ መንፈስ ቅዱስ ስለ ሞላባት እመ ብርሃንን አመስግናታለች:: በማሕጸኗ ያለ የ6 ወር ጽንስም የእመ አምላክን ድምጽ ቢሰማ በደስታ ዘሏል:: ለፈጣሪውም ስግደተ-ስባሔ አቅርቧል::

ቅዱስ ዮሐንስ ከተወለደ 2 ዓመት ከ6 ወር በሆነው ጊዜ ሰብአ ሰገል በመምጣታቸው በእሥራኤል ምድር የሚገኙ ሕጻናትን ሔሮድስ አስፈጀ:: በዚህ ጊዜም እናቱ ቅድስት ኤልሳቤጥ ይዛው ስትሸሽ ካህኑን ዘካርያስን ግን በቤተ መቅደስ መካከል ገድለውታል:: አረጋይት ኤልሳቤጥም ሕጻኑን እያሳደገች በገዳመ ዚፋታ ቆይታለች:: ቅዱስ ዮሐንስ በልጅነቱ እዚያው በበርሃ እንዳለ በዚህች ቀን አርፋለች።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ዲዮስቆሮስ_ሊቅ

በዚህችም ቀን የከበረና የተመሰገነ የእስክንድርያ አገር ሊቀ ጳጳሳት አባ ዲዮስቆሮስ አረፈ። እርሱም ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ሃያ አምስተኛ ነው።

ስለ ቀናች ሃይማኖትም ታላቅ ተጋድሎን ከተጋደለ በኋላ ዕረፍቱ በተሰደደበት በደሴተ ጋግራ ሆነ። ይህም እንዲህ ነው ንጉሥ መርቅያኖስ ወደ ሰበሰበው ጉባኤ በጠሩት ጊዜ ሲደርስ ብዛታቸው ስደስት መቶ ሠላሳ ስድስት የሆነ ታላቅ ጉባኤን አየ። እንዲህም አለ ይህ ታላቅ ጉባኤ እስቲሰበሰብ ድረስ በሃይማኖት ላይ የተገኘው ጉድለት ምንድን ነው።

ይህ ጉባኤ የተሰበሰበው በንጉሥ ትእዛዝ ነው አሉት። እንዲህም አላቸው ይህ ጉባኤ ስለ ክብር ባለቤት #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ቢሆን ኖሮ እኔ ተቀምጬ #እግዚአብሔር በሰጠኝ በአንደበቴ እናገር ነበር ግን የዚህ ጉባኤ መሰብሰብ በንጉሥ ትእዛዝ ከሆነ የሰበሰበውን ጉባኤ ንጉሡ እንዳሻው ይምራ።

ከዚህም በኃላ አንዱን #ክርስቶስን ከተዋሕዶ በኋላ ሁለት ባሕርይ ሁለት ምክር የሚያደርግ የክህደት ቃል በውስጡ የተጻፈበትን የሮሜ ሊቀ ጳጳሳት ልዮን የላከውን ደብዳቤ የከበረና የተመሰገነ ዲዮስቆሮስ ቀደደ።

በመንፈስ ቅዱስ የሚናገር የከበረ ዲዮስቆሮስም በጉባኤው ፊት እንዲህ ብሎ አስረዳ ሰው እንደመሆኑ ወደ ሠርግ ቤት የጠሩት #ጌታችን_ክርስቶስ_አምላክ እንደመሆኑ ውኃውን ለውጦ ወይን ያደረገው ከሀሊ ስለሆነ ሰውነቱና መለኮቱ በሥራው ሁሉ የማይለይ አንድ ነው።

ደግሞ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት አባ ቄርሎስ ከተናገረው የአካላዊ ቃል ተዋሕዶ እንደ ነፍስና ሥጋ እንደ እሳትና ብረት ተዋሕዶ ነው ያለውን ቃል ምስክር አድርጎ በማምጣትም አስረዳ። እሌህም የተለያዩ ሁለቱ ጠባዮች ስለ ተዋሕዷቸው አንድ ከሆኑ እንዲሁም የክብር ባለ ቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱ አንድ መሲሕ አንድ ጌታ አንድ ባሕርይ አንድ ምክር ነው እንጂ ወደ ሁለት አይከፈልም አላቸው።

ከዚያም ከተሰበሰበው ጉባኤ ውስጥ ማንም ሊከራከረው የደፈረ የለም ከውስጣቸውም የእግዚአብሔር ጠላት ስለሆነው ስለ ከሀዲው ንስጥሮስ በኤፌሶን ጉባኤ አስቀድሞ ተሰብስበው የነበሩ አሉ።

ወደ ንጉሥ መርቅያኖስና ወደ ሚስቱ ንግሥት ብርክልያ ከእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ከአባ ዲዮስቆሮስ በቀር ስለ ሃይማኖት ትእዛዛችሁን የሚቃወም የለም ብለው ነገር ሠሩበት።

ቅዱስ ዲዮስቆሮስንም ወደ ንጉሥ አቀረቡት ከእርሱም ጋር ታላላቅ ሊቃነ ጳጳሳትና ኤጲስቆጶሳት ከጉባኤው የሆኑ ነበሩ ከጥዋትም እስከማታ እርስበርሳቸው ሲከራከሩ ዋሉ። የከበረ ዲዮስቆሮስም የቀናች ሃይማኖቱን አልለወጠም ንጉሡና ንግሥቲቱ በእርሱ ተቆጥተው እንዲደበድቡት አዘዙ ስለዚህም ደበደቡት ጽሕሙን ነጩ ጥርሶቹንም ሰበሩ እንዲህም አደረጉበት።
ከዚህም በኃላ የተነጨውን ጽሕሙን ያወለቁትንም ጥሩሱን ሰብስቦ ወደ እስክንድርያ አገር ላካቸው እነሆ የቀናች ሃይማኖት ፍሬ ይህ ነው አላቸው። ለጉባኤውም የተሰበሰቡ ኤጲስቆጶሳት በዲዮስቆሮስ ላይ የደረሰውን መከራ በአዩ ጊዜ እጅግ ፈሩ በእርሱ የደረሰ በእነርሱ ላይ እንዳይደርስ ስለዚህም ከመናፍቁ ንጉሥ ከመርቅያኖስ ጋር ተስማሙ።

በሲኦል ውስጥ ይቆርጡት ዘንድ ባለው ምላሳቸውም ለክርስቶስ ሁለት የተለያዩ ባሕርያት አሉት ብለው በንጉሡ መዝገብ ላይ በእጆቻቸው ጽፈው ፈረሙ። ቅዱስ ዲዮስቆሮስም ተመልሶ ያን በውስጡ የጻፉበትን ደብዳቤ ያመጡለት ዘንድ ወደእሳቸው ላከ እነርሱም ላኩለት እነርሱ እንደጻፉ በውስጡ እርሱ የሚጽፍ መስሏቸዋልና።

እርሱ ግን አባቶቻችን ሐዋርያት ከአስተማርዋት ከቀናች ሃይማኖት በኒቅያ የተሰበሰቡ ሃይማኖታቸው የቀና ሦስት መቶ ዐሥራ ስምንት ኤጲስቆጲሳት አባቶቻችን ከሠሩት ሕግ የሚወጣውን ሁሉ በደብዳቤው ግርጌ ጽፎ አወገዘ።

መና*ፍቁ ንጉሥም ተቆጥቶ ጋግራ ወደም ትባል ደሴት እንዲአግዙት አዘዘ ወደዚያም ወሰዱት።ከእርሱም ጋር የሀገረ ቃው ኤጲስቆጶስ አባ መቃርስ አብሮ ተሰደደ። ሌሎችም አራት መነኰሳት የሸሹ አሉ።

እሊህም ስድስት መቶ ሠላሳ ስድስት ኤጲስቆጶሳት ተቀምጠው በኬልቄዶን ለራሳቸው መመሪያ የሚሆናቸውን ሥርዓት ሠሩ።

የከበረ ዲዮስቆሮስንም በአጋዙት ጊዜ ከዚያች አገር ኤጲስቆጶስ ጭንቅ የሆነ መከራ ደረሰበት ኤጲስቆጶስ ንስጥሮሳዊ ስለሆነ ታላቅ ጉስቁልናንም አጎሳቁለው በእጆቹ ላይ ድንቆች ታላላቅ ተአምራቶችን እግዚአብሔር እስከገለጠ ድረስ።

የደሴቱም ሰዎች ሁሉ ሰገዱለት አከበሩት ከፍ ከፍም አደረጉት እግዚአብሔርም የመረጣቸውን በቦታው ሁሉ ያከብራቸዋልና።አባ ዲዮስቆሮስም አባ መቃርስን አንተ በእስክንድርያ አገር የሰማዕትነት አክሊልን ትቀበል ዘንድ አለህ አለው። ከዚህም በኃላ ከምእመናን ነጋዴዎች ጋር ወደ እስክንድርያ ላከው በእርሱ ላይ ትንቢት እንደተናገረ ገድሉን በዚያ ፈጸመ።

የከበረ አባት ዲዮስቅሮስ ግን መልካም ተጋድሎውን በፈጸመ ጊዜ ክብር ይግባውና እግዚአብሔርንም አገልግሎ ከዚች ኃላፊት ከሆነች ኑሮው ወጥቶ ሔደ የሃይማኖቱንም ዋጋ አክሊልን ተቀብሎ ወደ ዘላለም ዕረፍት ገባ ያረፈውም በዚያች በደሴተ ጋግራ ነው ሥጋውንም በዚያው አኖሩ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ሳዊርያኖስ

በዚህችም ቀን የገብላ ኤጲስቆጶስ የከበረ አባት ሳዊርያኖስ አረፈ። የዚህም ቅዱስ የአበባቱ ስም አብስርያኖስ ይባላል የሀገረ አቴናንም ፍልስፍና ተማረ ከዚያም ወደ ቂሣርያ ሔዶ አሸወቀታቸውን ሁሉ ተማረ።

ዳግመኛም ወደ ሮሜ ከተማ ተመልሶ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ተማረ ከጥቂት ዘመናት የብሉይንና የሐዲስን መጸሕፍት አጠና።

ከዚህም በሗላ ቁጥር የሌለው ብዙ ገንዘብን ትተውለት ወላጆቹ አረፉ ስለርሱ ፈንታ መቶ ዕጥፍ ይቀበል ዘንድ ወዶ ያንን ገንዘብ ለክብር ባለቤት ለክርስቶስ ሊሰጥ ወደደና ድሆችን መጸተኘኞችን ምስኪኖችን ችግረኞችንም በውስጥ ይቀበል ዘንድ የእንግዳ ረቀበያ ቤትን ሠራ።

አታእልትም ተከለ ፍሬዎችን ተሸክመው የሚያመጡላቸውን ሠራተኞችን አደረገ እነዚያም ስለ ድሆችና ስለ ችግረኞች የተሠሩ ቦታወች እስከ ዛሬ በስሙ የሚጠሩ ሆኑ።

አገረ ገዥ የሆነ አጎቱን በሮሜው ንጉሥ በአኖሬዎስ ዘንድ እንዲህ ሲል ወነጀለው በከበረ ወንጌል ቃል ኪዳን እነደገባ ከእርሱ ዘንድ ስለ ርሱ መቶ እጥፍ እቀበላለሁና እኔ ገንዘቤን ክብር ይግባውና ለክርስቶስ እሰጠዋለሁ በማለት ሳዊርያሮስ ገንዘቡን ሁሉ እንደበተነ ።

ይህም ነገር ለንጉሡ ደስ አሰኘው ፈጸሞም በእርሱ ደስ አለው እጅግም ወደደው ከእርሱም ከቤተ መንግስቱ እንዳይለይ ንጉሡ አኖሬዎስ አዘዘው ከእርሱም ጋር ሁል ጊዜ ወደ ቤተክርስቲያን በመሔድ ሌሊቱን ሁሉ ቁመው ያድራሉ ንጉሥ አኖሬዎስም የመነኰሳትን ስራዎች ስለሚሠራ ከልብሰ መንግሥቱ በታች በሥጋው ላይ ማቅ ይለብስ ነበር።

በዚህም ወራት ለሮሜ አገር ሊቀ ጳጳሳት ሁኖ የነበረ አባ ዮናክንዲኖስ ነው ለእርሱም ሳዊርያኖስ በብዙ ሕዝብ ላይ ኤጲስቆጶስ መሆን እንዲ ገባው እግዚአብሔር ገለጸለት።

ሊቀ ጳጳሳቱም እጅግ የሚወደውና የሚያከብረው ሆነ ከቶ እንድለየውም አይሻም ነበር በሁሉም ዘንድ ተወዳድ ሆነ ዜናውም በቁስጥንያው ንጉሥ በቴዎዶስዮስ ዘንድ ተሰማ።

ሰዎች ሁሉ እንደሚያከብሩት በአየ ጊዜ ድካሙ በውዳሴ ከንቱ እንዳይጠፍ ከዚያች ቦታ በሥውር ሊወጣ ወደደ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክም ተገለጸለት ወደ ሀገረ ገብሪ ሔዶ ለብዙ ነፍሳት የገዳም አባት እንዲሆን አዘዘው አበሌሊትም ወጥቶ ሔደ የምንኰስና ለብስን ከለበሰ በሗላ ደቀመዝሙር ቴዎድሮስ ከእርሱ ገር ነበር ክብር ይግባውና እግዚአብሔር ወደ ገብላ ገዳም እስከሚደርስ በፊቱ የምትሔድና የምትመራው በመኰራኩር አምሰል የብርሃን ሠረገላ ላከለት።

በዚያም ገዳም አበ ምኔት የሆነ ጻድቅ ሰው ነበር የቅዱስ ሳዊርያኖስንም መምጣት ጌታችን በራእይ አስረዳው ወደርሱ መጥቶ ተቀበለው ሰላምታም ሰጠውና ስለእርሱ ጌታችን በራእይ ተገልጾለት እንዳስረዳው ነገረው የጌታንም ቸርነት እጅግ አደነቁ።

ዜናውም በሀገሮች ሁሉ ተሰማ የማይቁጠሩ ብዚ ሰዎች ወደርሱ ተሰበሰቡ። ንጉሥ ቴዎዶስዮስም ለከበረ ሳዊርያኖስ ገዳማትን የሚሠሩለት ብዙዎች ሰዎችን ሹሞችንም ከእርሱ ዘነድ ላከ የእግዚአብሔርም መልአክ በውስጣቸው ገደም የሚሠሩባቸውን ቦታዎች ወሰነላቸው ብዙ መፍሳትን የሚያጽናና የሚያረጋጋ ሆነ።

ክብር ይግባው እና እግዚአብሔርም በእጆቹ ላይ ድንቆች የሆኑ ብዙዎች ተአምራትን አደረገ ከእርሳቸውም በሀገር ገብላ መኰንን ልጅ ሰይጣን እንደደረባትና መኮንኑም ሳዊርያኖስን ከዚህ አገር ካላበረርክ ከልጅህ አልወጣም የለው ነው።መኰንኑም ይህን ገነር በሰማ ጊዜ ተነሥቶ ወደ ከበረ ሳዊርያኖስ ሒዶ ሰይጣን ያለውን ነገረው ደሞም ልጅን ያድናት ዘንድ ለመነው።

ቅዱስ ሳዊርያኖስም እንድህ ብሎ ደብዳቤን ጻፈለት ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሰሱስ ክርስቶስ ስም ከእሷ ወጥተህ ሒድ አባቷም ያንን ደብዳቤ ተቀብሎ ወደልጁ ሱደ ያን ጊዜም ከመኰንኑ ልጅ ሰይጣን ወጥቶ ሔደ ልጅቷም ዳነች።

ዳግመኛም ታላቅ ሠራዊት እስቲሆኑ ድረስ ብዙዎች ወንጀለኞች ሰዎች ተሰበሰቡ ወደ ከበረ ሳዊርያኖስም ገዳም ገብተው ሊያፈረርሱት ፈለጉ ክብር ይግባውና እግዚአብሔርም በላያቸው ጨለማን አመጣ ምንም ምን ሳያዩ ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት ኖሩ ቅዱስ ሳዊርያኖስንም ይቅር ይለቸው ዘንድ ብዙ ዕንባ በመፍሰሰ ለመኑት እርሲም ወደ ቦታዎቻቸው መልሶ ሰደዳቸው።

ዳግመኛም በገዳማቱ ውስጥ ያለ በእርሱ የሚተዳደሩ መነኰሳት ሁሉ ከእነርሱ የታመመ ቢኖር በላያቸው በመጸለይ ያድናቸዋው የሚያጸናናቸውና ሁሉም እንደ እግዚአብሔር መላእክት እስቲሆኑ ፈረሀ እግዚአብሔር የሚያስተምራቸው ሆነ።

እንዲህም ሆነ ስሙ ፈላታዎስ የሚባል የዚያች አገር ኤጲስቆጶስ ከእግዚአብሔር ዘንድ የሆነ እራይ ተገልጦለት ቅዱስ ሳዊርያኖስ በእርሱ ፈንታ ኤጲስቆጶስነት ይሾም ዘንድ እንዳለው አወቀ ያን ጊዜም ወደ ሕዝቡ ሁሉ ላከ ቅዱስ ሳዊርያኖስንም ኤጲስቆጶስነት እንዲሾሙት አዘዛቸው ለዚች ሹመት እግዚአብሔር መርጦታና።

ወዲያውኑ ደጋጏች ነገሥታት አኖሬዎስና አርቃዴዎስ ወስደው ገብላ በሚባል አገር ላይ ኢጶስቆጶስነት ሹሙት ስለ መንጋዎቹና ስለ ወገኖቹም አጠባበቅ ታላቅ ተጋድሎ ተጋደለ።

በዚያችም አገር እጅግ አዋቂ የሆነ የሙሴን ሕግ በማወቁ የሚመካ አንድ ስሙ ስቅጣር የሚባል ይሁዳዊ ነበር።
እርሱም ወደ ቅዱስ ሳዊርያኖስ መጥቶ ከእርሱ ጋር ተከራከረ ግን ከቅዱስ ሳዊርያኖስ አንደበት የሚመጣውን ቃል ይሰማ ዘንድ አልተቻለውም።

ከዚህም በሗላ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሲስ ክርስቶስ ለቅዱስ ሳዊርያኖስ በራእይ ተገልጦለት ይህ አይሁዳዊ እርሱ ራሱ ክርስቶስ ከአከበራቸውና ከባረካቸው ወገን ውስጥ ሊሆን እንዳለው አስረዳው።

ያ አይሁዴዊውም ወደ ቤቱ በገባ ጊዜ አስጨናቂዎች የሆኑ የስቃይ ቦታዎች በሕልሙ በማየት እንዲህ የሚለውን ቃል ታላቅ በሆነ የዘላለም ሥቃይ ውስጥ የሚኖሩ እሊህን ከሀዲዎች ዘመዶችህ አይሁድን እነሆ እይ እነርሱም ክብር ይግባውና በክርስቶስ ያላመኑ ናቸው።

በማግሥቱም ያ አይሁዳዊ ወደ ቅዱስ ሳዊርያኖስ መጥቶ ከእግሩ በታች ወድቆ ሰገደለት ክርስቲያንም ያደርገው ዘንድ ለመነው ያን ጊዜም እርሱንና ቤተሰቦቹን የሀገር ሰዎችንም ሁሉ የክርስትና ጥምቀትን አጠመቃቸው።

የቀሩትም አይሁድ ሁሉ አለቃቸው ክርስቲያን እንደሆነ በሰሙ ጊዜ አምነው ተጠምቀው ክርስቲያኖች ሆኑ።

እንዲሁም ኒሞንጦስ የሚባሉ ሌሎች ሥራየኞች ሰዎችን ወደ ክርስቲያን ሃይማኖት እንዲገቡ ቅዱስ ሳዊርያኖስ ለመናቸው እነርሱ ግን በሥራያቸው ስለሚታበዩ ከእርሱ ቃሉን አልሰሙም እነርሱም በዕድ ወደ እነርሱ የመጣ እንደሆነ በፊቱ አረርን ይበትናሉ ምንም ምን ማየት አይችልም።

ቅዱስ ሳዊርያኖስንም ወደ ቀናት ሃይማኖቱ እሊህን ሥራየኞች ሰዎች ያስገባቸው ዘንድ ዕንባን በማፍሰስ ክብር ይግባውና ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ለመነው እግዚአብሔርም በእርሱ ላይ ብቻ ጽኑዕ ደዌ አመጣ ወደ ክርስቲያን ወገኖች ግን ምንም ምን አልደረሰም። በግብጽ አገር በፈርዖንና በሠራዊቱ በግብጻውያንም ላይ መቅሠፍት ሲታዘዝ ወደ እስራኤል ወገን እንዳልደረሰ እንዲሁ ሆነ።

በዚያም ወራት እንዚያ ሥራየኞች የቅዱስ ሳዊርያኖስን ቃል ሰምተው ትእዛዙን ስለ አልተቀበሉ ስለዚህም ይህ ጽኑ ደዌ በላያቸው እንደመጣ አወቁ። ወደ ቅዱስ ሳዊርያኖስም መጥተው በደላቸውን ይቅር ይላቸው ዘንድ ክርስቲያኖችም ያደርጋቸው አስተምሮ አጥምቆ ክብር ይግባውና ከክርስቶስ መንጋዎች ጋር አንድ አደረጋቸው።ያቺ አገር ሁለመናዋ አንድ ማኅበር አንድ መንጋ ሆነች።

ሰይጣንም ልብሱ በተቀደደ ሽማግሌ አማሳል ሆኖ ፈጽሞ የሚጮህ ሆነ እንዲህም አለ። ከጽንፍ እስከ ጽንፍ በአለው ቦታ ሁሉ ጨነቀኝ በግብጽ አገርም ጠንካሮች መነኰሳት ተመሉባት በሮሜ አገርም ሊቀ ጳጳሳት ዮናክንዲኖስ በውስጧ ይኖራል ደግሞ በቁስጥንጥንያ ዮሐንስ አፈወርቅ አለ ይህ ቦታ ለእኔ ቀረልኝ ብዬ ነበር እነሆ ሳዊርያኖስ ከእጄ ውስጥ ነጠቀኝ አለ።

እንዲህም ሆነ የፋርስ ሰዎች ሊወጉአቸው ሽተው ወደ አኖሬዎስና ወደ አርቃዴዎስ መልእክትን ላኩ እሊህ ደጋጎች ነገሥታትም የፋርስ ሰዎች የላኩትን ደብዳቤ ወደ ቅዱስ ሳዊሮያኖስ ላኩት። እርሱም ያቺን ደብዳቤ በአነበባት ጊዜ የደብዳቤውን መልስ ወደ ነገሥታት አኖሬዎስና አርቃዴዎስ እያስረዳ እንዲህ ብሎ ጻፈ እኛ የክርስቶስ ከሆን መንግሥታችንም የክርስቶስ ነው እንዲህም ከሆነ የጦር መሣሪያን የጦር ሠራዊትንም አንሻም። እግዚአብሔርም ከቀደሙ ነገሥታት ጋር ሁኖ ያደረገውን እንዴት እንዳዳናቸው ጸላቶቻቸውንም እንዴት ድል እንዳደረጓቸው አስታወሳቸው።

ታላቁም ጾም ሳይደርስ የፋርስ ሰዎች አፍረው ከእነርሱ ዘንድ ተመልሰው ሔዱ። ስለ ዮሐንስ አፈወርቅም ከኤጲስቆጶሳት ጋር በአመጡት ጊዜ ንግሥት አውዶክስያን በምክሩ ሁሉ መክሮዋትና ገሥጿት ነበር። ስለ ዮሐንስ መሰደድም እርሱ ምንም ምን ያደረገው ስምምነት የለም ንግሥቲቱም ምክሩን ባልሰማች ጊዜ ወደ አገሩ ተመለሰ።

ብዙዎች ድርሳናትንና ተግሣጻትንም ደረሰ እሊህም ሃይማኖታቸው የቀናች ሰዎች በአሉባቸው አብያተ ክርስቲያናት እስከ ዛሬ ይኖራሉ። ቅዱስ ሳዊርያኖስም ሸመገለ ዕድሜውም መቶ ዓመት ሆነው ከሥጋውም ከመለየቱ በፊት በዐሥር ቀን የእግዚአብሔር መልአክ ተገልጾለት ከዚህ ዓለም ከድካምም ወደ እረፍት እንደ ሚወጣ ነገረው።

ከዚህም በኃላ ሕዝቡን ጠራቸው ክብር ይግባውና የእግዚአብሔርን ሕግ በመጠበቅ ጸንተው እንዲኖሩ አዘዛቸውና በሰላም በፍቅር አረፈ። ነፍሱንም በፈጣሪው ክርስቶስ እጅ ሰጠ። ዕረፍቱም የቆጵሮስ ኤጲስቆጶስ ኤጲፋንዮስ በአረፈ በሁለት ዓመት ዮሐንስ አፈወርቅ በአረፈ በአንድ ዓመት ነው። ሥጋውንም እንደ ሚገባ በንጹሕ ልብስ ገነዙ ብዙ መዝሙራትንና ምስጋናዎችን አድርገውለት በክብር ቀበሩት።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱሳን_አጋቶን_ዼጥሮስ_ዮሐንስና_አሞን

በዚህች እለት የከበሩ አጋቶንና ጴጥሮስ ዮሀንስና አሞን እናታቸውም ራፈቃ በሰማእትነት አረፉ። እሊህ ቅዱሳንም በላይኛው ግብፅ ቁስ ከሚባል አውራጃ ከቆንያ ከተማ ናቸው። ለእርሳቸውም ክብር ይግባውና ጌታችን ክርስቶስ ተገልፆላቸው። ከእነርሱ የሚሆነውን ስብራ በምትባል ከተማ እርሷም ወደ እስክንድርያ ክፍል ናት በዚያ የምስክርነት አክሊል እንደሚቀበሉ ስጋቸውንም ወደ ግብፅ ደቡብ ነቅራሀ ወደሚባል አገር እንደሚወስዱ አስረዳቸው ቅዱሳኑም በዚች ራእይ ደስ አላቸው።

በማለዳም ተነስተው ገንዘባቸውን ሁሉ ለድሆችና ለችግረኞች ሰጡ ከእነርሱም የሚበልጥ ወንድማቸው አጋቶን በሀረጉ ሹም ነበር በሁሉም ዘንድ የተወደደ ነው ራፊቃ እናታቸውም ክብር ይግባውና ስለ ክርስቶስ በመከራ ስቃይ ላይ የሚፀኑና የሚታገሱ እንዲሆኑ ታበረታታቸው ነበር።

ከዚህም በኃላ ቊስ ወደ ሚባል አገር ሲደርሱ በመኰንኑ በዲዮናሲዮስ ፊት ቁመው ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመኑ። ከእነርሱም አስቀድሞ እናታቸው ራፊቃን አሰቃያት እርሷም በስቃይ ውስጥ በመታገስ ደስተኛ ነበረች ከዚህም በኃላ አራቱን ልጆቿን አሰቃያቸው።

እነርሱንም በማሰቃየት በሰለቸ ጊዜ ወደ እስክንድርያ እንዲልካቸው ወገኖቹ መከሩት በእነርሱ ምክንያት ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ህዝቡ እንዳያምን ፈርተዋልና። እነርሱ በሁሉ ዘንድ የተወደዱ ስለሆነ በእርሳቸውም ምክንያት ከዚህ በፊት ብዙዎች ሰዎች በክብር ባለቤት በክርስቶስ አምነው በሰማእትነት ሙተዋልና የሰማእትነት አክሊልንም ተቀብለዋልና።

ወደ እስክንድርያም ገዥ ወደ አርማንዮስ ቅዱሳኑን በአመጡአቸው ጊዜ በዚያን ወቅት ስሟ ስብራ በምትባል አገር በዚያ ነበር። የተጋድሎአቸውንም ፅናት አውቆ ፅኑ ስቃይን አሰቃያቸው ስጋቸውንም ቆራርጦ ከመንኮራኩር ውስጥ ጨመራቸው።

ዳግመኛም ዘቅዝቀው ሰቀሉአቸው በዚህም ሁሉ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መኮንኑና የርሱ ሰዎች ሁሉ እስቲአፍሩ ያለ ምንም ጥፋትና ጉዳት የሚያነሳቸው ሆነ።

ከዚህም በኃላ ራሶቻቸውን ይቆርጡ ዘንድ ስጋቸውንም በባህር ሊጥሉ በታናሽ ታንኳ ጫኑአቸው። በዚያንም ጊዜ ከግብፅ በስተደቡብ መፂል ከሚባል አውራጃ ነቅራሀ ከምትባል መንደር ወደ አንድ ባለ ፀጋ እግዚአብሄር መልአኩን ላከ።

የቅዱሳኑንም ስጋ እንዲወስድ አዘዘው። እርሱም ወሰዳቸው የፃድቃን ማደሪያቸው ይህ ነወወ የሚል ቃልን ሰማ የመከራውም ወራት እስከሚአልፍ በዚያ አኖሩአቸው።

ከዚህም በኃላ ገለጡአቸው ውብ የሆነች ቤተ ክርስቲያንንም ሰርተውላቸው ስጋቸውን በውስጧ አኖሩ። እግዚአብሔርም ከስጋቸው ድንቆች የሆኑ ታላላቅ ተአምራትን ገለጠ በዚያም ወራት ስጋቸውን ስሙንጥያ ወደሚባል አገር አፈለሱ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ይኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_መስከረም_7 እና #ከገድላት_አንደበት)
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#መስከረም_7_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ዕብራውያን 13
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹³ እንግዲህ ነቀፌታውን እየተሸከምን ወደ እርሱ ወደ ሰፈሩ ውጭ እንውጣ፤
¹⁴ በዚህ የምትኖር ከተማ የለችንምና፥ ነገር ግን ትመጣ ዘንድ ያላትን እንፈልጋለን።
¹⁵ እንግዲህ ዘወትር ለእግዚአብሔር የምስጋናን መሥዋዕት፥ ማለት ለስሙ የሚመሰክሩ የከንፈሮችን ፍሬ፥ በእርሱ እናቅርብለት።
¹⁶ ነገር ግን መልካም ማድረግን ለሌሎችም ማካፈልን አትርሱ፤ እንዲህ ያለው መሥዋዕት እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘዋልና።
¹⁷ ለዋኖቻችሁ ታዘዙና ተገዙ፤ እነርሱ ስሌትን እንደሚሰጡ አድርገው፥ ይህንኑ በደስታ እንጂ በኃዘን እንዳያደርጉት፥ ይህ የማይጠቅማችሁ ነበርና፥ ስለ ነፍሳችሁ ይተጋሉ።
¹⁸ ጸልዩልን፤ በነገር ሁሉ በመልካም እንድንኖር ወደን፥ መልካም ሕሊና እንዳለን ተረድተናልና።
¹⁹ ይልቁንም ፈጥኜ እንድመለስላችሁ ይህን ታደርጉ ዘንድ አጥብቄ እለምናችኋለሁ።
²⁰ በዘላለም ኪዳን ደም ለበጎች ትልቅ እረኛ የሆነውን ጌታችንን ኢየሱስን ከሙታን ያወጣው የሰላም አምላክ፥
²¹ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በፊቱ ደስ የሚያሰኘውን በእናንተ እያደረገ፥ ፈቃዱን ታደርጉ ዘንድ በመልካም ሥራ ሁሉ ፍጹማን ያድርጋችሁ፤ ለእርሱ እስከ ዘላለም ድረስ ክብር ይሁን፤ አሜን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ጴጥሮስ 3
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁴ ነገር ግን ስለ ጽድቅ እንኳ መከራን ብትቀበሉ ብፁዓን ናችሁ። ማስፈራራታቸውንም አትፍሩ አትናወጡም፥
¹⁵ ዳሩ ግን ጌታን እርሱም ክርስቶስ በልባችሁ ቀድሱት። በእናንተ ስላለ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቁአችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ሁኑ፥ ነገር ግን በየዋህነትና በፍርሃት ይሁን።
¹⁶ በክርስቶስ ያለውን መልካሙን ኑሮአችሁን የሚሳደቡ ሰዎች ክፉን እንደምታደርጉ በሚያሙበት ነገር እንዲያፍሩ በጎ ሕሊና ይኑራችሁ።
¹⁷ የእግዚአብሔር ፈቃድ እንዲህ ቢሆን፥ ክፉ ስለ ማድረግ ሳይሆን በጎ ስለ ማድረግ መከራን ብትቀበሉ ይሻላችኋልና።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 16
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁶ ወደ ጸሎት ስፍራም ስንሄድ፥ የምዋርተኝነት መንፈስ የነበረባት ለጌቶችዋም እየጠነቈለች ብዙ ትርፍ ታመጣ የነበረች አንዲት ገረድ አገኘችን።
¹⁷ እርስዋ ጳውሎስንና እኛን እየተከተለች፦ የመዳንን መንገድ የሚነግሩአችሁ እነዚህ ሰዎች የልዑል አምላክ ባሪያዎች ናቸው ብላ ትጮኽ ነበር።
¹⁸ ይህንም እጅግ ቀን አደረገች። ጳውሎስ ግን ተቸገረና ዘወር ብሎ መንፈሱን፦ ከእርስዋ እንድትወጣ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አዝሃለሁ አለው፤ በዚያም ሰዓት ወጣ።
¹⁹ ጌቶችዋም የትርፋቸው ተስፋ እንደ ወጣ ባዩ ጊዜ ጳውሎስንና ሲላስን ይዘው ወደ ገበያ በሹማምት ፊት ጐተቱአቸው፤
²⁰ ወደ ገዢዎችም አቅርበው፦ እነዚህ ሰዎች አይሁድ ሆነው ከተማችንን እጅግ ያናውጣሉ።
²¹ እኛም የሮሜ ሰዎች ሆነን እንቀበላቸውና እናደርጋቸው ዘንድ ያልተፈቀደልንን ልማዶች ይናገራሉ አሉ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#መስከረም_7_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"እስመ መምህረ ሕግ ይሁብ በረከተ። ወየሐውር እምኀይል ውስተ ኃይል። ወያስተርኢ አምላከ አማልክት በጽዮን"። መዝ.83፥6-7።
"በልቅሶ ሸለቆ ውስጥ በወሰነው ስፍራ የሕግ መምህር በረከትን ይሰጣልና። ከኃይል ወደ ኃይል ይሄዳሉ፤ የአማልክት አምላክ በጽዮን ይታያል"። መዝ.83፥6-7።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#መስከረም_7_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ማርቆስ 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²³ በዚያን ጊዜም በምኩራባቸው ርኵስ መንፈስ ያለው ሰው ነበረ፤
²⁴ እርሱም፦ የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለን? ልታጠፋን መጣህን? ማን እንደ ሆንህ አውቄአለሁ፥ የእግዚአብሔር ቅዱሱ ብሎ ጮኸ።
²⁵ ኢየሱስም፦ ዝም በል ከእርሱም ውጣ ብሎ ገሠጸው።
²⁶ ርኵሱም መንፈስ አንፈራገጠውና በታላቅ ድምፅ ጮኾ ከእርሱ ወጣ።
²⁷ ሁሉም፦ ይህ ምንድር ነው? በሥልጣን ርኵሳን መናፍስትን ያዝዛል፤ እነርሱም ይታዘዙለታልና ይህ አዲስ ትምህርት ምንድር ነው? ብለው እስኪጠያየቁ ድረስ አደነቁ።
²⁸ ዝናውም ወዲያው በየስፍራው ወደ ገሊላ ዙሪያ ሁሉ ወጣ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #እመቤታች_ማርያም_ቅዳሴ ነው። መልካም የቅድስት ሐና የልደት በዓል፣ የአባ ዲዮስቆሮስ የዕረፍት በዓል፣ የቅድስት ኤልሳቤጥ የዕረፍት በዓል፣ የቅዱስ ሳዊርያኖስ የዕረፍት በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#መስከረም_8

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
መስከረም ስምንት በዚህች ቀን የነቢያት አለቃ #ነቢዩ_ቅዱስ_ሙሴ ዕረፍቱ ነው፣ የበራክዩ ልጅ ካህንና ነቢይ የሆነ #ቅዱስ_ዘካርያስ በሰማዕትነት አረፈ፣ የከበረ #ቅዱስ_ዲማድዮስ በሰማእትነት አረፈ፣ የካህኑ #ቅዱስ_አሮን በትሩ ለምልማ የተገኘችበት ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ሙሴ_ሊቀ_ነቢያት

መስከረም ስምንት በዚህች ቀን የ #እግዚአብሔር ሰው የሆነ የዋህ ቅን ጻድቅ የነቢያት አለቃ የሙሴ ዕረፍቱ ነው። ይህ ነቢይ ነፍሱን ስለእሳቸው አሳልፎ እስከ መስጠት ከ #እግዚአብሔር ወገኖች ጋር የደከመ ነው እርሱም በግብጽ አገር በኤርትራ ባሕርም ድንቆች ተአምራትን ያደረገ ነው።

ይህም ስለ ፈርዖን ትእዛዝ ወላጆቹ በግብጽ ወንዝ ውስጥ በጣሉት ጊዜ አውጥታ ላሳደገችው ለፈርዖን ልጅ ለተርሙት ልጅዋ መባልን አልወደደም። እርሱ ፈርዖን የዕብራውያንን ወንዶች ልጆች ይገድሏቸው ዘንድ አዝዞ ነበርና። በአገኘችውም ጊዜ ለርሷ ልጅ ሊሆናት ወስዳ በመልካም አስተዳደግ አሳደገችው።

አርባ ዓመትም በሆነው ጊዜ አንዱን ዕብራዊ የግብጽ ሰው የሆነ ሲያጠቃው አየ ለዕብራዊውም ተበቅሎ ግብጻዊውን ገደለው። በማግሥቱ ደግሞ ሁለት ዕብራውያን እርስ በርሳቸው ሲጣሉ አያቸው ሊአስታርቃቸውና በመካከላቸው ሰላምን ሊአደርግ ወደደ። አንዱ ዐመፀኛም ትላንት ግብጻዊውን እንደገደልከው ልትገድለኝ ትሻለህን አለው።

ስለዚህም ነገር ሙሴ ፈርቶ ወደ ምድያም አገር ሸሸ በዚያም ሚስት አግብቶ ሁለት ልጆችን ወለደ በዚያም አርባ ዓመት ኖረ በጳጦስ ቍጥቋጦ ውስጥም እሳት እየነደደ ራእይን አየ። አይቶ ሊረዳ በቀረብ ጊዜ ጳጦስ በተባለ ቊጥቋጦ ውስጥ #እግዚአብሔር ተናገረው። ወደ ግብጽ አገርም ሒዶ የእስራኤልን ልጆች ከዚያ እንዲአወጣቸው አዘዘው።

ከዚህን በኋላ #እግዚአብሔር በሙሴ እጅ በግብጻውያን ላይ ዐሥር መቅሠፍቶችን አመጣ። መጀመሪያው የወንዙን ውኃ ደም ማድረግ የመጨረሻው የግብጻውያንን የበኵር ልጅ መግደል ነው።

ከዚህም በኋላ ሕዝቡን ከግብጽ አገር አወጣቸው የኤርትራንም ባሕር ከፍሎ በውስጡ አሳለፋቸው የባሕሩንም ውኃ በጠላቶቻቸው በፈርዖንና በሠራዊት ላይ ገልብጦ አሠጠማቸው።

ከዚህም በኋላ በምድረ በዳ ውስጥ አርባ ዓመት ሙሉ መና አወረደላቸው ውኃንም ከአለት አፈለቀላቸው ይህን ሁሉ በጎ ሥራ በዚህ በደግ ነቢይ ሙሴ እጅ #እግዚአብሔር አደረገላቸው እነርሱ ግን ይዘልፉት ነበር ብዙ ጊዜም በድንጊያ ሊወግሩት ሽተው ነበር።

እርሱ ግን በእነርሱ ላይ ልቡን አስፍቶ በመታገሥ ስለርሳቸው ወደ #እግዚአብሔር ይማልዳል። እነርሱንም አብዝቶ ከመውደዱ የተነሣ #እግዚአብሔርን አቤቱ የዚህን ሕዝብ በደሉን ይቅር ካላልክ ከሕይወት መጽሐፍህ ሰርዘኝ አለው።

ሰው ከወዳጁ ጋር እንደሚነጋገር አምስት መቶ ሰብዓ ቃላትን ከ #እግዚአብሔር ጋር እንደተነጋገረ መጽሐፍ ምስክር ሆነ። የእስራኤል ልጆችም በሚያዩት ጊዜ እንዳይሞቱ ፊቱን እስከ ሸፈነ ድረስ በ #እግዚአብሔር በጌትነቱ ብርሀን ፊቱ በራ።

መቶ ሃያ ዓመት የሆነ ዕድሜውም በተፈጸመለት ጊዜ ለአገልጋዩ ለነዌ ልጅ ለኢያሱ ሕዝቡን እርሱ እንደጠበቃቸው እንዲጠብቃቸው በእጁ ውስጥ እንዲአስረክበው #እግዚአብሔር ሙሴን ለኢያሱ አስረክብ ብሎ አዘዘው።

ሙሴም ኢያሱን ጠርቶ የ #እግዚአብሔርን ትእዛዝ አዘዘው ሕጉንም እንዲጠብቅ ሕዝቡንም ለኢያሱ በእጁ አስረከባቸው ወደ ምድረ ርስትም እርሱ እንደ ሚአስገባቸው አረጋገጠለት። ሙሴም #እግዚአብሔር እንዳዘዘው በምስክሩ ድንኳን ውስጥ የሚሠራውን ሁሉ ሠርቶ ከአዘጋጀ በኋላ በተራራ ውስጥ አረፈ በዚያም በመላእክት እጅ በሥውር ተቀበረ። የእስራኤል ልጆች ወስደው እንዳያመልኩት #እግዚአብሔር የሙሴን ሥጋ ሠወረ።

በእስራኤል ልጆች ውስጥ እንደ ሙሴ ያለ ደግ የዋህ ቅን የሆነ ነቢይ እንደማይነሣ መጽሐፍ ምስክር ሆነ። ሰይጣንም የሙሴን ሥጋ ለእስራኤል ሊገልጥላችው በወደደ ጊዜ ሐዋርያው ይሁዳ በጻፈው መጽሐፉ እንደመሰከረ የመላእክት አለቃ ሚካኤል ገሠጸው ከዚህም ሥራ ከለከለው የእስራኤል ልጆችም አርባ ቀን አለቀሱለት።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ ሙሴ ጸሎት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ዘካርያስ_ካህን_ወነቢይ

በዚህችም ቀን የበራክዩ ልጅ ካህንና ነቢይ የሆነ የከበረ ዘካርያስ በንጉሥ ሄሮድስ እጅ በሰማዕትነት አረፈ። ይህም ካህን ስለ ልጁ ዮሐንስ መወለድ የመላእክት አለቃ ገብርኤል በነገረው ጊዜ ነገሩን አምኖ አልተቀበለም ። ስለዚህም ሕፃኑ እስቲወለድ ዲዳ ትሆናለህ አለው። በተወለደም ጊዜ አንደበቱ ተፈትቶ #እግዚአብሔርን አመሰገነው የልጁንም ስም ዮሐንስ ነው ብሎ ጻፈ። እርሱና ሚስቱ በ #እግዚአብሔር ሕግ ያለ ነቀፋ የጸኑ ደጎች እንደሆኑ የከበረ ወንጌል ስለዚህ ምስክር ሆኗል።

ክብር ይግባውና #ጌታችን_ክርስቶስም በተወለደ ጊዜ ሊሰግዱለት የጥበብ ሰዎች መጡ። ሄሮድስም ስለ መንግሥቱ ፈራ ደነገጠም። ስለዚህም ጭፍሮቹን ልኮ በይሁዳ አገር የቤተ ልሔምንና የገሊላን ሁሉንም ሕፃናት ዕድሜያቸው ሁለት ዓመት የሚሆናቸውን ከዚያም የሚያንሱትን ገደላቸው ሰነፍ የሆነ ሄሮድስ #ክርስቶስን ከሕፃናት ጋር እንደ ሚገድለው አስቦ ነበርና።

ከዚህም በኋላ የ #እግዚአብሔር መልአክ ለዮሴፍ በሕልም ተገልጾለት ስለአዘዘው #ጌታችን ሕፃኑንና እናቱን እመቤታችንን ድንግል #ማርያምን ይዞ ወደ ግብጽ አገር መጡ። ኤልሳቤጥ ግን ሕፃኗን ዮሐንስን ይዛ ወደ ዱር ወጣች ወደ ሲና በረሃም ሸሸች በዚያም ሕፃኗን እያሳደገች ሰባት ዓመት ኖረች ከዚህም እርሷ አረፈች ሕፃኑም በመምህርነት ለእሥራኤል እስከሚገለጥበት ጊዜ ድረስ በበረሀ ውስጥ ብቻውን ኖረ።

ሕፃናትንም ከገደላቸው በኋላ ዮሐንስ #ክርስቶስ እንደሆነ ሄሮድስ አሰበ ተጠራጠረ ከአባቱ ከዘካርያስ ዘንድ ሕፃኑን ይሹ ዘንድ ወታደሮቹን ላከ ዘካርያስም ሕፃኑ ያለበትን ወይም እናቱ ያለችበትን እኔ አላውቅም አለ። ሄሮድስም ልጅህን ካላመጣህልኝ እኔ እገድልሃለሁ አለው። ዘካርያስም ከእርሱ ዛቻ የተነሣ አልፈራም ወታደሮቹንም አዝዞ በቤተ መቅደሱና በመሠዊያው መካከል ገደሉት ክብር ይግባውና #እግዚአብሔርም ሥጋውን ሠወረ ደሙ ግን እንደ ደንጊያ ሆነች።

ካህናቱና ሕዝቡ እንደ ልማዳቸው ለጸሎት በመጡ ጊዜ ከካህናት አንዱ ወደ ቤተ መቅደስ ውስጥ ገባ። የረጋ ደምን አገኘ ከመጠዊያውም እንዲህ የሚል ቃልን ሰማ እነሆ የበራክዩ ልጅ ዘካርያስ ተገደለ የሚበቀልም እስሚመጣ ደሙ ስትጮኽ ትኖራለች።

እንዲህ የሚልም አለ ከዐሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት የሆነ የበራክዩ ልጅ ዘካርያስ ይህ አይደለም ያ አልተገደለም በዕድሜው ኡረት በሚባል አገር ሞተ እንጂ ሥጋውም በዚያ ያለ ጥፋት ተገኝቶ ቤተ ክርስቲያን ሠርተውለታል። የዚህ ዘካርያስ ግን ሥጋው አልተገኘም ስለ መገደሉ የደሙ ድምፅ ምስክር ሆነ እንጁ።

ደግሞ እንዲህ ተባለ ሄሮድስ ሕፃናትን በገደላቸው ጊዜ ከአይሁድ አንድ ሰው መጥቶ የ #እግዚአብሔር መልአክ ትወልዳለህ ብሎ ነግሮት ለዘካርያስ ልጅ ተወልዶለታል ምናልባት እርሱ #ክርስቶስን ይሆን አለው። ስለዚህ ሄሮድስ ሕፃኑን ዮሐንስን ይገድሉት ዘንድ ወታደሮችን ላከ።
ዘካርያስም ወታደሮችን እንዲህ አላቸው ሕፃኑን እኔ ወደሌላ ቦታ ወስጄዋለሁ ከእኔ ጋራ መጥታችሁ ራሳችሁ ከዚያ ቦታ ውሰዱት ወደ ቤተ መቅደስም እስከ አስገባቸው ድረስ ወታደሮቹ አብረውት መጡ። እርሱም ሕፃኑን ልጁን በመሠዊያው ጠርዝ ላይ አኑሮ ጸለየበት ይህም የልጁን መወለድ የ #እግዚአብሔር መልአክ ለእርሱ የነገረበት ነው።

ያን ጊዜም የ #እግዚአብሔር መልአክ ሕፃኑን ዚፈታ ወደሚባል በረሀ ነጥቆ ወሰደው ሕፃኑንም ባላገኙት ጊዜ አባቱን ዘካርያስን ገደሉት። ስለዚህም #ጌታችን አይሁድን በቤተ መቅደሰ መካከል የገደላችሁት የዘካርያስ ደም በላያችሁ ይደርሳል አላቸው ለመገደሉ ምክንያት አይሁድ ናቸውና እንዲህ አለ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎቱ ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ዲማድዮስ

በዚህች ቀን የከበረ ዲማድዮስ ከግብጽ ደቡብ ደንጡ ከሚባል አውራጃ ደርሰባ ከሚሏት ከተማ በሰማእትነት አረፈ። እርሱ ሁል ጊዜ ወደ ቤተ ክርስቲያን ይገሠግሣል ድኆችንና በሽተኞችን መጐብኘትንም ይወዳል።

ብርሃናዊ ሰውም ተገልጦለት ሒዶ የሰማእትነት አክሊልን እንዲቀበል አዘዘው ሰማያዊ የሆነ ቃል ኪዳንንም ገባለት በዚህም እጅግ ደስ አለው።

አባቱንና እናቱንም ትቶ ከሀረጉ ወጣ ስለ ከበረ ስሙ በሚቀበለው መከራ ውስጥ ርዳታ እንዲሰጠው እንዲአጸናው ወደ #እግዚአብሔር ጸለየ ወደ ሀገር አትሪብም ሔዶ በመኰንኑ ፊት ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ታመነ።

መኰንኑም ታላቅ ስቃይን አሰቃይቶ የእስክንድርያ አገረ ገዥ ወደ ሆነ ወደ ሉክያኖስ ሰደደው። በመርከብም ውስጥ ሳለ ክብር ይግባውና #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ተገለጠለት በብዙ ደስታም አረጋግቶትና አጽናንቶ ቃል ኪዳንን ሰጠው ልቡናውም ፈጽሞ እጅግ ደስ አላት።

መኰንኑ ሉክያኖስም በጽኑዕ ስቃይ አሰቃይቶ ራሱን በሰይፍ ቆረጠ የሰማዕትነት አክሊልንም በመንግስተ ሰማያት ተቀበለ። የሀገሩ ሰዎችም መጥተው ስጋውን ወሰዱ ታላቅ ክብርንም አከበሩት ከስጋውም ታላላቅ የሆኑ ድንቆችና ተአምራት ተገለጡ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎቱ ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አሮን_ካህን

በዚህች ቀን የካህኑ አሮን በትሩ ለምልማ የተገኘችበት ነው። በቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት የቅዱሱ ካህን የአሮን በትር ሳይተክሏትና ውሃ ሳያጠጧት ለምልማ፣ አብባ፣ አፍርታ የተገኘችው በዚህ ቀን ነው። ዳታን፣ አቤሮንና ቆሬ ከተከታዮቻቸው ጋር በፈጠሩት ሁከት ምድር ተከፍታ ከዋጠቻቸው በሁዋላ #እግዚአብሔር የ12ቱን ነገደ እሥራኤል በትር ሰብስቦ ሲጸልይበት እንዲያድር ሙሴን አዞት እንዲሁ ሆነ።

በነጋም ጊዜ ይህቺ ደረቅ የነበረች በትረ አሮን 12 ፍሬ (ለውዝ፣ ገውዝ፣ በኩረ ሎሚ) አፍርታ ተገኘች። (ዘኁ. 17፥1-11) ለጊዜው ክህነት ከቤተ አሮን እንዳይወጣ ምልክት ሆናለች። ለፍጻሜው ግን ምሳሌነቷ ለ #ድንግል_"ማርያም ነው። እመ ብርሃን የወንድ ዘር ምክንያት ሳይሆናት አምላክን ወልዳ ተገኝታለችና።

"ጸናጽል ዘውስተ ልብሱ ለአሮን ካህን ወዓዲ በትር እንተ ሠረጸት ወጸገየት ወፈረየት" እንዳለ #አባ_ሕርያቆስ። (#ቅዳሴ_ማርያም)

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም ቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_መስከረም_8)
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#መስከረም_8_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ዕብራውያን 11
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²³ ሙሴ ከተወለደ በኋላ ወላጆቹ ያማረ ሕፃን መሆኑን አይተው በእምነት ሦስት ወር ሸሸጉት የንጉሥንም አዋጅ አልፈሩም።
²⁴ ሙሴ ካደገ በኋላ የፈርዖን የልጅ ልጅ እንዳይባል በእምነት እምቢ አለ፤
²⁵-²⁶ ከግብፅም ብዙ ገንዘብ ይልቅ ስለ ክርስቶስ መነቀፍ እጅግ የሚበልጥ ባለ ጠግነት እንዲሆን አስቦአልና ለጊዜው በኃጢአት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራ መቀበልን መረጠ፤ ብድራቱን ትኵር ብሎ ተመልክቶአልና።
²⁷ የንጉሡን ቍጣ ሳይፈራ የግብፅን አገር የተወ በእምነት ነበር፤ የማይታየውን እንደሚያየው አድርጎ ጸንቶአልና።
²⁸ አጥፊው የበኵሮችን ልጆች እንዳይነካ ፋሲካንና ደምን መርጨትን በእምነት አደረገ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ይሁዳ 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁹ የመላእክት አለቃ ሚካኤል ግን ከዲያብሎስ ጋር በተከራከረ ጊዜ ስለ ሙሴ ሥጋ ሲነጋገር፦ ጌታ ይገሥጽህ አለው እንጂ የስድብን ፍርድ ሊናገረው አልደፈረም።
¹⁰ እነዚህ ግን የማያውቁትን ሁሉ ይሳደባሉ፥ አእምሮም እንደሌላቸው እንስሶች በፍጥረታቸው በሚያውቁት ሁሉ በእርሱ ይጠፋሉ።
¹¹ ወዮላቸው፥ በቃየል መንገድ ሄደዋልና ስለ ደመወዝም ለበለዓም ስሕተት ራሳቸውን አሳልፈው ሰጥተዋል በቆሬም መቃወም ጠፍተዋል።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 7
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
³⁰ አርባ ዓመትም ሲሞላ የጌታ መልአክ በሲና ተራራ ምድረ በዳ በቍጥቋጦ መካከል በእሳት ነበልባል ታየው።
³¹-³² ሙሴም አይቶ ባየው ተደነቀ፤ ሊመለከትም ሲቀርብ የጌታ ቃል፦ እኔ የአባቶችህ አምላክ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ ነኝ ብሎ ወደ እርሱ መጣ። ሙሴም ተንቀጥቅጦ ሊመለከት አልደፈረም።
³³ ጌታም፦ የቆምህባት ስፍራ የተቀደሰች ምድር ናትና የእግርህን ጫማ አውልቅ።
³⁴ በግብፅ ያሉትን የሕዝቤን መከራ ፈጽሜ አይቼ መቃተታቸውንም ሰምቼ ላድናቸው ወረድሁ፤ አሁንም ና፥ ወደ ግብፅ እልክሃለሁ አለው።
³⁵ ሹምና ፈራጅ እንድትሆን የሾመህ ማን ነው? ብለው የካዱትን፥ ይህን ሙሴን በቍጥቋጦው በታየው በመልአኩ እጅ እግዚአብሔር ሹምና ቤዛ አድርጎ ላከው።
³⁶ ይህ ሰው በግብፅ ምድርና በኤርትራ ባሕር በምድረ በዳም አርባ ዓመት ድንቅና ምልክት እያደረገ አወጣቸው።
³⁷ ይህ ሰው ለእስራኤል ልጆች፦ እግዚአብሔር ከወንድሞቻችሁ እንደ እኔ ያለ ነቢይ ያስነሣላችኋል፤ እርሱን ስሙት ያላቸው ሙሴ ነው።
³⁸ ይህ ሰው በሲና ተራራ ከተናገረው መልአክና ከአባቶቻችን ጋር በምድረ በዳ በማኅበሩ ውስጥ የነበረው ነው፤ ይሰጠንም ዘንድ ሕይወት ያላቸውን ቃላት ተቀበለ፤
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#መስከረም_8_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"ካህናቲከ ይለብሱ ጽድቀ። ወጻድቃኒከ ትፍሥሕተ ይትፌሥሑ። በእንተ ዳዊት ገብርከ"። መዝ 131፥9-10
"ካህናቶችህ ጽድቅን ይልበሱ፥ ቅዱሳንህም ደስ ይበላቸው። ስለ ዳዊት ስለ ባሪያህ የቀባኸውን ሰው ፊት አትመልስ"። መዝ 131፥9-10
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#መስከረም_8_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ማቴዎስ 23
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²⁹ እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ የነቢያትን መቃብር ስለምትሠሩ የጻድቃንንም መቃብር ስለምታስጌጡና፦
³⁰ በአባቶቻችን ዘመን ኖረን በሆነስ በነቢያት ደም ባልተባበርናቸውም ነበር ስለምትሉ፥ ወዮላችሁ።
³¹ እንግዲያስ የነቢያት ገዳዮች ልጆች እንደሆናችሁ በራሳችሁ ላይ ትመሰክራላችሁ።
³² እናንተ ደግሞ የአባቶቻችሁን መስፈሪያ ሙሉ።
³³ እናንተ እባቦች፥ የእፉኝት ልጆች፥ ከገሃነም ፍርድ እንዴት ታመልጣላችሁ?
³⁴ ስለዚህ፥ እነሆ፥ ነቢያትንና ጥበበኞችን ጻፎችንም ወደ እናንተ እልካለሁ፤ ከእነርሱም ትገድላላችሁ ትሰቅሉማላችሁ፥ ከእነርሱም በምኵራባችሁ ትገርፋላችሁ ከከተማም ወደ ከተማ ታሳድዳላችሁ፤
³⁵ ከጻድቁ ከአቤል ደም ጀምሮ በቤተ መቅደስና በመሠዊያው መካከል እስከ ገደላችሁት እስከ በራክዩ ልጅ እስከ ዘካርያስ ደም ድረስ በምድር ላይ የፈሰሰው የጻድቅ ደም ሁሉ ይደርስባችሁ ዘንድ።
³⁶ እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ በዚህ ትውልድ ላይ ይደርሳል።
³⁷ ኢየሩሳሌም ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ነቢያትን የምትገድል ወደ እርስዋ የተላኩትንም የምትወግር፥ ዶሮ ጫጩቶችዋን ከክንፎችዋ በታች እንደምትሰበስብ ልጆችሽን እሰበስብ ዘንድ ስንት ጊዜ ወደድሁ! አልወደዳችሁምም።
³⁸ እነሆ፥ ቤታችሁ የተፈታ ሆኖ ይቀርላችኋል።
³⁹ እላችኋለሁና፥ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው እስክትሉ ድረስ ከእንግዲህ ወዲህ አታዩኝም።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱስ ኤጲፋንዮስ ቅዳሴ ነው። መልካም የነቢዩ ቅዱስ ሙሴ የዕረፍት በዓል፣ የካህኑ ቅዱስ ዘካርያስ የዕረፍት በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#መስከረም_9

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
መስከረም ዘጠኝ በዚህች የመላእክት አለቃ #ቅዱስ_ሚካኤል በሮም አገር ፍሩምያ በምትባል ከተማ ላደረገው ተአምር መታሰቢያ ነው፣ #ቅዱስ_አባት_አባ_ቢሶራ በሰማዕትነት አረፈ፣ #ቅዱስ_ያሳይ_ንጉሥ እረፍቱ ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ሊቀ_መላእክት_ቅዱስ_ሚካኤል

መስከረም ዘጠኝ በዚህች ቀን በሮም አገር ፍሩምያ በምትባል ከተማ ለሆነው ተአምር መታሰቢያ ሆነ። ይህም እንዲህ ነው የሰማይ ሠራዊት አለቃ በሆነ በከበረ መልአክ በሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሚታዩ ድንቆችና ተአምራቶች ምክንያት ዮናናውያን ሰዎች ሰይጣናዊ ቅናትን እንደ ቀኑ ከመቅናታቸውም ብዛት የተነሣ በዚያ አካባቢ የሚወርደውን የወንዝ ውኃ በዚያች ቤተ ክርስቲያን ላይ ሊመልሱትና ከሚጠብቃት መጋቢዋ ጋር በውኃ ስጥመት ሊአጠፉአት ፈልገው መለሱት።

የሰማያውያን ሠራዊት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልም ለቤተ ክርስቲያኑ መጋቢ ለናርጢኖስ ተገለጠለት ወደርሱም ቀርቦ ጽና አትፍራ አለው ይህንን ብሎ በእጁ ውስጥ ባለ በትር አለቱን መታው አለቱም ተሰንጥቆ እንደ በር ሆነ የዚያ ወንዝ ውኃም በውስጡ አልፎ ሔደ።

ይህንንም ያዩ ምስጉን #እግዚአብሔርን አመሰገኑት የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልንም አከበሩት። ከዚያች ቀን እስከ ዛሬ የወንዙን ውኃ በዚያች በተሠነጠቀች አለት ውስጥ አልፎ ሲሔድ ያዩታል ወደ መላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ከቶ አይቀርብም።

#ለእግዚአብሔርም ምሽጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ ሚካኤል አማላጅነት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አባት_አባ_ቢሶራ

በዚህችም ቀን መጺል የምትባል አገር ኤጲስቆጶስ ቅዱስ አባት አባ ቢሶራ በሰማዕትነት አረፈ።

ይህም ቅዱስ በግብጽ አገር #እግዚአብሔርን በምትወድ መጺል በምትባል ከተማ ኤጲስቆጶስ ሆነ። ዲዮቅልጥያኖስም ነግሦ ክርስቲያኖችን በሚያሠቃያቸው ጊዜ ክብር ይግባውና በ #ክርስቶስ ስም ደሙን ያፈስ ዘንድ ይህ አባት ወደደ።

ሕዝቡንም ሀሉ ሰብስቦ በቤተ መቅደሱ ፊት በዐውደ ምሕረቱ አቆማቸው ሊጠብቁት የሚገባውን ለጽድቅ የሚያበቃቸውን ትእዛዝ ሁሉ አዘዛቸው። ከዚህም በኋላ ክብር ይግባውና በ #ክርስቶስ ስም ደሙን ማፍሰስ እንደሚሻ ነገራቸው ይህንንም በሰሙ ጊዜ ታላቆችም ታናሾችም በላዩ አለቀሱ።

የሙት ልጆች እንሆን ዘንድ የምትተወን ምን ያደርግልሃል እኛስ እንድትሔድ አንለቅህም አሉት ሊይዙትም ቃጡ ግን አልተቻላቸውም ተውትም እርሱም ወደ ክብር ባለቤት #ክርስቶስ አደራ አስጠበቃቸውና ሰላምታ ሰጥቷቸው ከእነርሱ ዘንድ ወጥቶ ተጓዘ። እነርሱም መሪር ልቅሶን እያለቀሱ ሸኙት።

ስማቸው ቢስኮስ ፊናቢክስ ቴዎድሮስ የሚባሉ ኤጲስቆጶሳት አብረውት ሔድ መኰንኑ ወደ አለበት አገርም ደርሰው የክብር ባለቤት በሆነ በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ታመኑ። እርሱም መኰንኑ አሠቃያቸው ኤጲስቆጶሳትም እንደሆኑ አውቆ ሥቃያቸውን አበዛ እሊህ አባቶች ግን በታላቅ ትዕግሥት የጸኑ ናቸው። ክብር ይግባውና ጌታችን ክርስቶስ ያጸናቸዋልና።

ከዚህም በኋላ መኰንኑ ራሶቻቸውን በሰይፍ ይቆርጧቸው ዘንድ አዘዘ የሕይወት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበሉ። የቅዱስ ቢሶራ ሥጋው ግን ንሲል በሚባል አገር እስከ ዛሬ ይኖራል።

#ለእግዚአብሔርም ምሽጋና ይሁን እኛንም በቅዱሱ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ያሳይ_ንጉሥ

በዚችም ቀን ተጋድሎውን በዛፍ ላይ ሆኖ የፈጸመ እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘ ንጉሥ ያሳይ አረፈ።

በቀደመው ዘመን መንግስታቸውን ትተው ከመነኑ ነገሥታት አንዱ ቅዱስ ያሳይ ነው። ምናኔ በቁሙ ከባድ ነው። መንግስትን፣ ዙፋንን፣ ክብርን ትቶ መመነንን ደግሞ ከማድነቅ በቀር እንዲህ ብለው ሊገልጹት ይከብዳል።

ቅዱስ ያሳይም መንግስቱን ትቶ ልምላሜ ወደሌለበት ደረቅ በርሃ ሔደ። በዚያም ከአንዲት ዛፍ በቀር ምንም ነገር አላገኘም። በዚያች ደረቅ ዛፍ ላይ ወጥቶ ለዓመታት በጾምና በጸሎት ተጋደለ።

በዘመነ ተጋድሎው ከዛፏ አልወረደም ሰውም አይቶ አያውቅም። በመጨረሻም ስለ ቅድስናው ዛፏ ለምልማለች። እርሱም በዚህች ቀን ዐርፏል።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም
በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_መስከረም_9_ዲያቆን_ዮርዳኖስ_አበበ)
2024/09/21 05:35:48
Back to Top
HTML Embed Code: