Telegram Web Link
#ነሐሴ_27

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ነሐሴ ሃያ ሰባት በዚህችም ቀን #የመላእክት_አለቃ_ሱርያል የበዓሉ መታሰቢያ ነው፣ #የቅዱስ_ብንያሚንና_እኅቱ_አውዶክስያ በሰማዕትነት ሞቱ፣ በሊቀ ካህናት ኤሊ ዘመን #ነቢይ_ሳሙኤል ለመጠራቱ መታሰቢያ ሆነ፣ታላቁ ሰማዕት #ቅዱስ_ፊቅጦርና_እናቱ_ቅድስት_ሣራ መታሰቢያቸው ነው፣ አባቶቻችን #12ቱ_የያዕቆብን_ልጆች ያስቧቸዋል፣ ታላቁ ጻድቅ ተአምረኛው #አቡነ_ዘርዐ_ቡሩክ ልደታቸው ነው፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ሱርያል_ሊቀ_መላእክት

ነሐሴ ሃያ ሰባት በዚህችም ቀን ከሰባቱ ሊቃነ መላእክት አራተኛ የሆነ የመላእክት አለቃ የሱርያል የበዓሉ መታሰቢያ ነው።

ከታላላቅ ሊቃናት አንዱ የሆነው ቅዱስ ሱርያል ክብሩ ብዙ ቢሆንም ብዙ ምዕመናን አያውቁትም። የመላእክት መዓርግ ሲነገር ሚካኤል፣ ገብርኤል፣ ሩፋኤል ብሎ ቀጥሎ የሚመጣው ሱርያል ነው።

በ3ቱ ሰማያት ካሉት 9ኙ ዓለመ መላእክት የአንዱ (የሥልጣናት) መሪ (አለቃ) ነው። መልአኩ እጅግ ርሕሩሕ እና ተራዳኢ ነውና አንዘንጋው። ለኖኅ መርከብርን ያሳራው ከጥፋት ውሃም ያዳነው ይህ ቅዱስ መልአክ ነው።

በገድለ ሰማዕታትም ላይ እንደተጠቀሰው የሰማዕታት ረዳትና አዳኝም ነው። ቅዱስ ሱርያል በሌላ ስሙ "እሥራልዩ" ይባላል። "የእሥራኤል ረዳት" እንደ ማለት::

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን አማላጅነቱም ከእኛ ጋር ይኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ብንያሚንና_እህቱ_አውዶከስያ

በዚህች ቀን ሰብሲር ከሚባል አገር ብንያሚንና እኅቱ አውዶክስያ በሰማዕትነት ሞቱ።

የእነዚህም ቅዱሳን ወላጆቻቸው እንግዳና መጻተኛን የሚወዱ ደጎች ክርስቲያኖች ናቸው ደግሞ ለክርስቲያኖች በሚገባ በበጎ ሥራ ሁሉ የተጠመዱ ቅድስና ያላቸው ናቸው። እሊህንም ቅዱሳን በወለዱዋቸውና በአሳደጓቸው ጊዜ ክርስቲያናዊት ትምህርትን አስተማሩአቸው።

ከዚህም በኋላ ወደዚያች አገር ከሀዲ መኰንን መጣ ቅዱስ ብንያሚንም በሰማ ጊዜ የክብር ባለቤት ስለሆነ #ክርስቶስ ደሙን ያፈስ ዘንድ ወደደ። በመኰንኑም ፊት ቁሞ በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ታመነ ጽኑ የሆነ ሥቃይንም አሠቃይቶ ከዚያ በኋላ አሠረው።

ወላጆቹና እኅቱ በሰሙ ጊዜ ወደርሱ መጡ አለቀሱ እጅግም አዘኑ እርሱም የዚህ ዓለም ኑሮ እንደ ጥላ ፈጥኖ ያልፋል የወዲያኛው ኑሮ ግን ፍጻሜ የለውም እያለ ያጽናናቸው ጀመረ።

እኅቱ አውዶክስያም ይህን መልካም ትምህርቱን ከወንድሟ ሰምታ ወንድሜ ሆይ ካንተ እንዳልለይ #እግዚአብሔር ሕያው ነው አንተ የምትሞተውንም ሞት እኔም ከአንተ ጋራ እሞታለሁ አለችው።

ይህንንም ብላ ወደ መኰንኑ ሒዳ በክብር ባለቤት #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ በመኰንኑ ፊት ታመነች መኰንኑም ያሠቃያት ጀመረ። ከዚህ በኋላም ያለ መብልና ያለ መጠጥ በጨለማ ቤት ሃያ ቀን ከወንድሟ ጋር አሥረው እንዲያኖሩዋት አዘዘ።

ከዚህም በኋላ ከዚያ አውጥቶ ከባድ የሆኑ ደንጊያዎችን በአንገታቸው አንጠልጥሎ ከጥልቅ ባሕር ጣላቸው የ #እግዚአብሔር መልአክም ወርዶ ከአንገታቸው ደንጊያዎቹን ፈታላቸው እነርሱም ከወደብ እስቲደርሱ በባሕሩ ላይ ዋኝተው ብጥራ ከምትባል ቦታ ደረሱ አንዲት ብላቴና ድንግልም አግኝታቸው ስባ አወጣቻቸው።

ያን ጊዜም ወደ መኰንኑ ሔደው እርሱንና የረከሱ አማልክቶቹን ረገሙ ብዙ ቀኖችም ጭንቅ የሆነ ሥቃይን አሠቃያቸው። ሥቃያቸውም በአደከመው ጊዜ ራሳቸውን በሰይፍ እንዲቆርጧቸው አዘዘና ቆረጡአቸው። የሰማዕትነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበሉ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸው ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ሳሙኤል_ነቢይ

በዚችም ቀን በሊቀ ካህናት ኤሊ ዘመን ነቢይ ሳሙኤል ለመጠራቱ መታሰቢያ ሆነ።

የዚህ ቅዱስ አባቱ ሕልቃና ይባላል የእናቱም ስሟ ሐና ነው። እነርሱም ከሌዊ ነገድ ከካህኑ አሮን ወገን ናቸው። ሐናም መካን ነበረች ክብር ይግባውና ወደ #እግዚአብሔር እያለቀሰች አዘውትራ ስለ ማለደች ይህን የተባረከ ልጅ ሰጣት በቤቷም ሦስት ዓመት አሳደገችው።

ከዚህም በኋላ ገና ስትፀንሰው እንደተሳለች ወደ #እግዚአብሔር መቅደስ አቀረበችው ካህኑ ኤሊንም በመላላክ የሚያገለግለው ሆነ። የካህኑ የኤሊ ልጆች ግን ክፉዎች ነበሩ #እግዚአብሔርንም አይፈሩም ነበር በቅዱስ መሥዋዕቱም ላይ በደሉ። ይህ ሕፃን ሳሙኤል ግን በኤሊ ፊት ለ #እግዚአብሔር ሲያገለግል ኖረ በነዚያ ወራቶችም ቃለ #እግዚአብሔር ውድ ነበር የሚታይ ራእይም አልነበረም።

ከዚህም በኋላ በአንዲት ሌሊት እንዲህ ሆነ ኤሊ በመኝታው ተኝቶ ሳለ ዐይኖቹም መፍዘዝ ጀምረው ነበር ማየትም አይችልም ነበር። የ #እግዚአብሔርንም መብራት አብርቶ ለማሳደር ገና አላዘጋጁም ነበር ሳሙኤል ግን በቤተ መቅደስ በ #እግዚአብሔር ማደሪያ ታቦት አጠገብ ተኝቶ ነበር።

#እግዚአብሔርም ሳሙኤልን ሳሙኤል ሳሙኤል ብሎ ጠራው እነሆ እኔ አለሁ አለ። ወደ ኤሊም ፈጥኖ ሔደ ስለጠራኸኝ እነሆ እኔ መጣሁ አለው ኤሊም አልጠራሁህም ተመልሰኽ ተኛ አለው ሔዶም ተኛ።

#እግዚአብሔርም ዳግመኛ ሳሙኤል ሳሙኤል ብሎ ጠራው ሳሙኤልም ተነሥቶ ወደ ኤሊ ሔደ ስለጠራኸኝ እነሆ መጣሁ አለው። ኤሊም አልጠራሁህም ተመልሰህ ተኛ አለው። ሳሙኤልም ከዚህ አስቀድሞ #እግዚአብሔርን በራእይ ገና አላወቀውም ነበር ቃለ #እግዚአብሔርም አልተገለጠለትም ነበር።

ዳግመኛም #እግዚአብሔር ሳሙኤልን ሦስተኛ ጊዜ ጠራው ተነሥቶም ወደ ኤሊ ሔደ ስለጠራኸኝ እንሆ መጣሁ አለው ኤሊም ያንን ልጅ #እግዚአብሔር እንደጠራው አሰበ። ልጄ ተመልሰህ ተኛ የሚጠራህ ካለ እኔ ባርያህ እሰማለሁና #ጌታዬ ተናገር በለው አለው ሳሙኤልም ሒዶ በመኝታው ተኛ።

#እግዚአብሔርም መጥቶ እንደ መጀመሪያው በፊቱ ቁሞ ጠራው። ሳሙኤልም እኔ ባሪያህ እሰማሃለሁና #ጌታዬ በል ተናገር አለው #እግዚአብሔርም ሳሙኤልን የሰማው ሁሉ ሁለቱን ጆሮዎቹን ይይዝ ዘንድ እነሆ እኔ በእስራኤል ላይ የተናገርሁት ቃሌን አደርጋለሁ።

በዚያችም ቀን በኤሊና በወገኑ ላይ የተናገርኹትን ሁሉ አጸናለሁ እጀምራለሁ እፈጽማለሁም። ልጆቹ የ #እግዚአብሔርን ቃል አቃልለዋልና እርሱም አልገሠጻቸውምና በልጆቹ ኃጢአት እኔ ወገኑን ለዘላለም እንደምበቀለው ነገርሁት። ስለዚህም ነገር በዕጣንም ቢሆን በመሥዋዕትም ቢሆን የኤሊ የወገኑ ኃጢአት እስከ ዘላለሙ ድረስ እንዳይሠረይ ራሴ እንዲህ ብዬ ማልሁ። በኤሊ ወገኖችና ልጆች ላይ #እግዚአብሔር የተናገረው ሁሉ ተፈጸመ።

ከዚህም በኋላ የቂስ ልጅ ሳኦልን ቀብቶ ለእስራኤል ልጆች ያነግሠው ዘንድ #እግዚአብሔር ሳሙኤልን አዘዘው እንዲአነግሥላቸው ለምነዋልና። ሳኦልም የልዑልን ትእዛዝ በተላለፈ ጊዜ ዳግመኛ ለእስራኤል ንጉሥ ሊሆን የዕሴይ ልጅ ዳዊትን ይቀባው ዘንድ ይህን ነቢይ ሳሙኤልን ዳግመኛ አዘዘው። ይህም ነቢይ ሳሙኤል በሕይወት በኖረበት ዘመን ሁሉ እስራኤልን አስተዳደራቸው። ከዚህም በኋላ ሰኔ ዘጠኝ ቀን በሰላም አረፏል።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እና በቅዱስ ሳሙኤል ነብይ ጸሎት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ፊቅጦርና_እናቱ_ሣራ

በዚህች ቀን ታላቁ ሰማዕት ቅዱስ ፊቅጦርና እናቱ ቅድስት ሣራ መታሰቢያቸው ነው፡፡
የከሃዲው ንጉሥ የዲዮቅልጥያኖስ ባለሟል በነበረው በገዛ አባቱ እጅግ ተሠቃይቶ ምስክርነቱን የፈጸመው ታላቁ ሰማዕት ቅዱስ ፊቅጦር፡- ኅርማኖስ የተባለው ወላጅ አባቱ የክርስቲያኖችን ደም እንደ ውኃ ያፈስ የነበረው የዲዮቅልጥያኖስ ልዩ አማካሪና የሠራዊቱ አለቃ ነበር፡፡ እናቱ ሣራ ግን በ #ክርስቶስ አምና የተጠመቀች ክርስቲያን ነበረች፡፡

እንዲያውም ልጇን ቅዱስ ፊቅጦርን ከመውለዷ በፊት የአምላክ እናት የቅድስት #ድንግል_ማርያም ሥዕል ወዳለበት ሄዳ "እመቤቴ ማርያም ለ #ኢየሱስ_ክርስቶስ ደስ የሚያሰኘውን ልጅ ስጪኝ፡፡ #ኢየሱስ_ክርስቶስን ደስ የማያሰኝ ልጅ ከሆነ ግን ማኅፀኔን ዝጊልኝ" ብላ በጸለየችው ጸሎት ነው ቅዱስ ፊቅጦርን ያገኘችው፡፡

ሰማዕቱ ቅዱስ ፊቅጦር በዓለም ላይ ያሉ በ #ክርስቶስ ያመኑ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ክርስቲያኖችን ንጉሡ ዲዮቅልጥያኖስ በግፍ ያስገድል በነበረበት ወቅት የተገኘ ታላቅ ሰማዕት ነው፡፡ ፊቅጦርን ገና 15 ዓመት እንደሆነው ንጉሡ ዲዮቅልጥያኖስ "ከፍ ባለ ስልጣን አስቀምጥሃለሁ፣ እጅግ ብዙ ወርቅና ንብረትም እሰጥሃለሁ፣ በእስክንድርያም ላይ ገዥ አድርጌ እሾምሃለሁ #ክርስቶስን ማመንህን ተውና ወደ ቤተ መንግሥቴ ግባ" ቢለውም ቅዱስ ፊቅጦር ግን ብዙ መከራንና ሥቃይን ተቀብሎ ሰማዕት መሆንን መረጠ፡፡ ቅዱስ ፊቅጦርም ዲዮቅልጥያኖስን " #ክርስቶስን በምታፈቅረው ጊዜ አፈቀርኩህ ወደ አንተም መጣሁ፤ #ክርስቶስን በጠላኸው ጊዜ ግን እኔም ጠላሁህ፣ ቤትህንም ጠላሁ" ብሎታል፡፡

ከብዙ ጊዜም በኋላ ዲዮቅልጥያኖስ ቅዱስ ፊቅጦርን በመንግሥቱ ውስጥ ሦስተኛ ማዕረግ አድርጎ ሾመው፡፡ እርሱ ግን ይጾማል ይጸልያል እንጂ በንጉሡ ቤት አይበላ አይጠጣም ነበር፡፡ ዕድሜውም 27 ነበር፡፡ አባቱንም ከጣዖት አምላኪነቱ እንዲመለስ ቢመክረው ሄዶ ለንጉሡ ከሰሰው፡፡ ፊቅጦርም "ለአንተ ለጣዖት አምላኩ አገልጋይ አልሆንም" በማለት በንጉሡ ፊት ትጥቁን ፈቶ ጣለ፡፡ የቅዱስ ፊቅጦር ወላጅ አባቱ ኅርማኖስ የከሃዲው ንጉሥ የዲዮቅልጥያኖስ የቅርብ እንደራሴና መስፍን ስለነበር ልጁ ፊቅጦርን የንጉሡን ሹመትና ልመና እንዲቀበል ብዙ ሲያግባባው ነበር፤ አባቱም ልጁ በሀሳቡ እንዳልተስማማለት ሲያውቅ ከዲዮቅልጥያኖስ ጋር ተማክሮ ልጁን ቅዱስ ፊቅጦርን ወደ እስክንድርያና ወደ ተለያዩ ሀገሮች በግዞት ተልኮ በዚያም ተሠቃይቶ እንዲሞት ፈደበት፡፡

ወደ ግብፅም ልከው በዚያ እጅግ አሠቃዩት፡፡ መልአክም ነጥቆ ወስዶ በሰማያት የሰማዕታትን ክብር አሳይቶት ወደ ምድር መለሰው፡፡ ክፉዎቹም በብረት አልጋ አስተኝተው ከሥሩ እሳት አነደደዱበት፡፡ በሌላም ልዩ ልዩ በሆኑ ማሠቃያዎች እጅግ አሠቃዩት፡፡ መልአክም ተገልጦ ፈወሰው፡፡ ወደ እንዴናም አጋዙትና በዚያም ብዙ አሠቃዩት፡፡ ምላሱን ቆረጡት፤ በችንካርም ጎኖቹን በሱት፤ ቁልቁል ሰቅለውም ቸነከሩት፤ በእሳትም ውስጥም ጨመሩት፤ ዐይኖቹን አወጡት፤ እሬትና መራራ ሐሞትንም አጠጡት፡፡ ደግመውም ዘቅዝቀው ሰቀሉት፡፡ ጌታችንም ተገልጦ ካጽናናው በኋላ ፈወሰውና ፍጹም ጤነኛ አደረገው፡፡ ፊቅጦር፣ ፋሲለደስ፣ ቴዎድሮስ በናድልዮስ፣ አውሳብዮስና መቃርዮስ እነዚህ ሰማዕታት በአንድነት በአንድ ዘመን አብረው ኖረው ተሰውተው ሰማዕት የሆኑ የሥጋም ዝምድና ያላቸው የነገሥታት ልጆች ናቸው። ዲዮቅልጥያኖስም የቅዱስ ፊቅጦርን ዐይኑን አስወለቀው፣ ነገር ግን የታዘዘ መልአክ መጥቶ የዓይኑን ብርሃን መልሶለታል፡፡ ሰማዕቱ በመዝለል ባሕር የሚሻገር እንደ አሞራ የሚመስል ፈረስ ነበረው፡፡ ከዚህም በኋላ ማሠቃየቱ ቢሰለቻቸው ሚያዝያ 27 ቀን አንገቱን ሰይፈው በሰማዕትነት እንዲያርፍ አድርገውታል፡፡

ሰማዕቱ ቅዱስ ፊቅጦር አንድ የሚነገር ትልቅ ታሪክ አለው፡፡ እርሱም በሰማዕትነት ካረፈ ከብዙ ዘመን በኋላ በራእይ ተገልጦ በ8ኛው ሺህ ዘመን በሀገራችን በኢትዮጵያና በግብፅ እንዲሁም በቁስጥንጥንያና በሮም ወደፊት የሚሆነውን ነገር ሁሉ በግልጽ የተናገረ መሆኑ ነው፡፡ ‹‹ስለ ሃይማኖት ቅዱስ ፊቅጦር ያየው ራእይ›› የሚል መጠሪያ ያለው ይህ ራእይ በሀገራችን ጎጃም ደብረ ጽሞና ገዳም ውስጥ ይገኛል፡፡

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን ሰማዕታት ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#12ቱ_ደቂቀ_ያዕቆብ

በዚችም ቀን ዳግመኛ አባቶቻችን ዐሥራ ሁለቱን የያዕቆብን ልጆች ያስቧቸዋል።

እነዚህ አበው የአብርሃምና የይስሐቅ የልጅ ልጆች የያዕቆብ ደግሞ ልጆች ናቸው። ትውልድ ከአዳም እስከ ቅዱስ ያዕቆብ አንድ ሐረግ ይዞ መጥቶ እዚህ ላይ ሲደርስ ይበተናል። አባታችን ያዕቆብን #እግዚአብሔር ሲባርከው እሥራኤል አለው። ትርጉሙም "ሕዝበ #እግዚአብሔር ወልድ ዘበኩር (የበኩር ልጅ) ከሃሊ ነጻሪ (አስተዋይ) እንደ ማለት ነው።

ይህ ቅዱስ አባት ለ #ድንግል_ማርያም ቅድመ አያት ከመሆኑ ባሻገር ነቢያትን፣ ካህናትን፣ ነገሥታትንና መሣፍንትን ወልዷል። ከወንድሙ ኤሳው ጋር ተጣልቶ ወደ ሶርያ በሔደ ጊዜ ከ2ቱ ሚስቶቹ (ልያና ራሔል) 8 ልጆችን፣ ከ2ቱ የሚስቶቹ ደንገጥሮች (ዘለፋና ባላ) 4 ልጆችን በድምሩ 12 ልጆችን ወልዷል።

#ከልያ የተወለዱት፦ ሮቤል፣ ስምዖን፣ ሌዊ፣ ይሁዳ፣ ይሳኮር እና ዛብሎን ይባላሉ።
#ከራሔል የተወለዱት፦ ዮሴፍና ብንያም ይባላሉ።
#ከባላ የተወለዱት፦ ዳን እና ንፍታሌምን ሲሆኑ
#ከዘለፋ የተወለዱት ደግሞ፦ጋድ እና አሴር ይባላሉ። 12ቱ ደቂቀ እሥራኤል (ያዕቆብ) ማለት እኒህ ናቸው::

ከ12ቱ በቅድስና ዮሴፍ ከፍ ቢልም #እግዚአብሔር ለክህነት ሌዊን፣ ለመንግስት ደግሞ ይሁዳን መርጧል። ከእነሱ ዘርም ዓለምን ለማዳን ተወልዷል። 10ሩ አበው በተለይ በዮሴፍ ላይ ግፍ ሠርተው የነበረ ቢሆንም በኋላ ተጸጽተዋል።
እነሆ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዛሬ ታስባቸዋለች (ዘፍጥረት ከምዕራፍ 28 እስከ 31)

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም ቅዱሳን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አቡነ_ዘርዐ_ቡሩክ

በዚህች ቀን ታላቁ ጻድቅ ተአምረኛው አቡነ ዘርዐ ቡሩክ ልደታቸው ነው፡፡ ከመወለዳቸው አስቀድሞ ትንቢት ተነግሮላቸው ነበር፡፡ አባታቸው ደመ ክርስቶስ ዐይነ ሥውር የነበረ ሲሆን አቡነ ዘርዐ ቡሩክ በተወለዱ ጊዜ ግን የአባታቸውን ዐይን አብርተውለታል፡፡ አባታችን ዘርዐ ቡሩክ ገና በሰባት ዓመታቸው ነው ረቡዕና ዓርብ መጾም የጀመሩት፡፡ በዚሁ በሰባት ዓመታቸውም ‹‹ይህን ዓለም ክፋቱን እንዳላይ ዐይኖቼን አሳውርልኝ›› በማለት ዐይናቸውን እንዲያጠፋላቸው አምላካቸውን ለምነው እንደፈቃዳቸው ዐይነ ሥውር ሆነዋል፡፡ ነገር ግን ከሰባት ዓመት በኋላ በ12 ዓመታቸው #ጌታችን "ለዓለም የምታበራ ብርሃን አደርግሃለሁና ዐይንህም ይብራ" በማለት ዐይነ ብርሃናቸውን መልሶላቸው እንዲያዩ አድርጓቸዋል፡፡ በዚህም ዕድሜያቸው (በ12 ዓመታቸው) ሰባቱንም አጽዋማት ይጾሙ ነበር፡፡

ከዚህም በኋላ #ጌታችን የቅዱሳት መጻሕፍትን ምሥጢር ሁሉ ገለጠላቸው፡፡ መጻሕፍተ ብሉያትን፣ መጻሕፍተ ሐዲሳትን፣ መጻሕፍተ ሊቃውንትን፣ መጻሕፍተ መነኮሳትን፣ አዋልድ መጻሕፍትን ሁሉ ገልጦላቸዋል፡፡ ከሟርት መጻሕፍት በቀር ያስቀረባቸው ነገር አልነበረም፤ የቅዱስ ያሬድንም ዜማ እንዲሁ ገለጠላቸው፡፡
ጻድቁ ከሁሉ ቅዱሳን በበለጠ ሁኔታ ዐሥራ ሁለት ክንፍ የተሰጣቸው ሲሆን በ12 ክንፎቻቸውም የሰማይን ደጆች ሁሉ ገሃነመ እሳትንም አልፈው በመሄድ ቀጥታ በሥሉስ ቅዱስ ዙፋን ፊት ይቆሙ እንደነበር ቅዱስ ገድላቸው ይናገራል፡፡ እጅግ በሚደንቅና ከአእምሮ በላይ በሆነ ሁኔታ አባታችን ለሰባት ቀናት በየቀኑ ለሰባት ሰዓት ያህል በሲኦል ውስጥ ቆመው ይጸልዩ ነበር፡፡ ብዙዎቹ ቅዱሳን በምልጃቸው ነፍሳትን ከሲኦል ሲያወጡ ነው የምናውቀው እንጂ እንደ አቡነ ዘርዐ ቡሩክ በሲኦል ውስጥ ገብቶ ጸሎት የጸለየ ጻድቅ እስካሁን እኔ አላጋጠመኝም፡፡

አቡነ ዘርዐ ቡሩክ እንደ አባታችን ተክለሃይማኖት ለጸሎት በመቆም ብዛት አንድ እግራቸው እስኪሰበር ድረስ በብዙ መከራ ተጋድለዋል፡፡ ከሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ ጋር መንበሩን ያጥኑ ዘንድ ከፈጣሪአቸው ታዘው አጥነዋል፡፡ #ጌታችን ለአቡነ ዘርዐ ቡሩክ ፍጥረታትን ከመፍጠር በቀር ያልሰጣቸው ሥልጣን የለም፡፡ " #እግዚአብሔር ብፁዕና ቅዱስ ለሚሆን አባታችን ዘርዐ ቡሩክ "እኔ ከሥልጣኔ ሥልጣንን፣ ከክብሬም ክብርን፣ ከጥበቤም ጥበብን፣ ከተአምራቴም ተአምራትን፣ ከስጦታዬም ስጦታን፣ ከትዕግስቴም ትዕግስትን፣ ከፍቅሬም ፍቅርን፣ ከትሕትናዬም ትሕትናን፣ ከባለሟልነቴም ባለሟልነትን ሰጥቼሃለሁና ሁሉ ከሥልጣንህ በታች ሆኖ ይታዘዝልህ" የሚል እጅግ ድንቅ ቃልኪዳን ነው የሰጣቸው፡፡ ልዩ ልዩ ሀብታትን ሁሉ ሰጣቸው፡፡ "ለሥላሴ ከሚገባ ከስግደትና በቃልና በሥልጣን ፍጥረታትን ለመፍጠር በቀር ምንም ያልሰጠሁህ የለም" ብሎ ጌታችን በማይታበል ቃሉ እንደነገራቸውና ቃል እንደገባላቸው በቅዱስ ገድላቸው ላይ ተጽፏል፡፡ (የአባታችን ገድላቸው ከመጥፋቱ የተነሣ በአሁኑ ሰዓት አንዳንድ ነጋዴዎች አንዱን ፍሬ ከ3 ሺህ ብር በላይ እየሸጡት ነበር፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ ቲሊሊ የሚገኘው ገዳማቸው በድጋሚ አሳትሞታል፡፡

አቡነ ዘርዐ ቡሩክ በወቅቱ በነበረው ገዥ ፊት በሐሰት ተከሰው ለ5 ዓመታት ያህል በእስርና በእንግልት ሲኖሩ በእነዚህ ጊዜያት ሁሉ ምግብ የሚባል አይቀምሱም ነበርና ከእስር ሲፈቱ አምስት ዓመት ሙሉ ሲሰጣቸው ያጠራቅሙት የነበረው ምግብ ትኩስ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ያሳሰራቸውንም ንጉሥ ገና ሕፃን ሳለ እናቱ ልታስባርከው ወደ አባታችን ዘንድ ወስዳው ነበር፡፡ አቡነ ዘርዐ ቡሩክም ሕፃኑን ከባረኩት በኋላ ለእናቱ "ይህ ልጅሽ ወደፊት ይነግሣል በንግሥናው ዘመንም እኔን ያስርና ያንገላታኛል" ብለው ይህ እንደሚሆን አስቀድመው ትንቢት ተናግረው ነበር፡፡ እንዳሉትም ልጁ አድጎ ሲነግሥ ጭፍሮቹ "ንጉሥ ሆይ አንተን የማይወድ ለቃልህም የማይታዘዝ አንድ መነኩሴ አለ" በማለት ምንም እንኳን ንጉሡ ባያውቃቸውም በሐሰት ነገር ስለከሰሱለት በግዞት እንዲኖሩና እንዲታሰሩ አድርጓቸዋል፡፡ ጻድቁ በግዞት ሲወሰዱ "እነዚህን መጻሕፍቶቼን ለሰዎች አደራ ብሰጣቸው ይክዱኛል፣ ቤተ ክርስቲያን ባስቀምጣቸው ይጠፉብኛል" በማለት ሰባት መጽሐፎቻቸውን ለግዮን (ለዓባይ) ወንዝ አደራ የሰጡ ሲሆን ከ5 ዓመት በኋላ ከእስር ተፈተው ሲመለሱ በወንዙ አጠገብ እንደደረሱ ጸሎት ካደረጉ በኋላ "ግዮን ሆይ በ #እግዚአብሔር ፊት በአደራ የሰጠሁሽን መጽሐፎቼን ግሺ (ትፊ)" ብለው እጃቸውን ወደ ወንዙ ሰደው መጽሐፎቻቸው ሳይረጥቡና ሳይበሰብሱ ከወንዙ ውስጥ አውጥተዋቸል፡፡ እንዲያውም አቧራውን ከመጻሕፍቶቻቸው ላይ እፍ ብለው አራግፈውታል፡፡

በመጽሐፍ ቅዱስ እንደተጠቀሰው የጠለቀው ምሳር እየተንሳፈፈ ወደ ኤልሳዕ እንደመጣ ሁሉ አሁንም እንዲሁ የቅዱስ አባታችን መጽሐፎች አብሯቸው ከነበረውና ዘሩባቤል ከሚባለው ደቀ መዝሙራቸው ጋር ወዳሉበት ተንሳፈው ሊመጡ ችለዋል፡፡ መጽሐፎቻቸውንም አብሯቸው ለነበረው ደቀ መዝሙራቸው ካሳዩት በኋላ እንዲይዛቸው ሰጥተውታል፡፡

የግዮን ወንዝ "ግሺ ዓባይ" ወይም "ዓባይ" እየተባለ መጠራት የጀመረው አቡነ ዘርዐ ቡሩክ "ግዮን ሆይ በእግዚአብሔር ፊት በአደራ የሰጠሁሽን መጽሐፎቼን ግሺ (ትፊ)" ብለው እጃቸውን ወደ ወንዙ ሰደው መጽሐፎቻቸው ሳይረጥቡና ሳይበሰብሱ ከወንዙ ውስጥ ካወጡበት ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ አባታችን በቦታው ላይ 30 ዓመት ሙሉ ቆመው ጸልየው ቦታውን የባረኩት ሲሆን ጌታችንም በቦታው ላይ ትልቅ ቃልኪዳን ሰጥቷቸዋል፡፡ "ብፁዕ አባታችን ለግዮን ወንዝ መጽሐፎቹን በአደራ ሰጥተው በኋላም ከደቀ መዝሙራቸው ከዘሩባቤል ጋር መጽሐፎቹን ከግዮን ምንጭ ውስጥ ከተቀበለ በኋላ "በግዮን ውኃ ውስጥ ሳይረጥቡ በደረቅ መጽሐፎቼን የጠበቀ እግዚአብሔር ይመስገን" ብሎ ፈጣሪውን አመሰገነ፡፡ "ያንጊዜም በውስጥሽ ታላቅ ድኅነት ይደረግብሽ፣ ሕመምተኞች ሁሉ ይዳኑብሽ፣ መካኖች ይውለዱብሽ" ብሎ ግዮንን በቃሉ መረቃት፣ በእጁም ባረካት፡፡ ብፁዕ አባታችንም በዚህች ቦታ ላይ ፈውስ፣ ረድኤት፣ በረከት ይደረግብሽ ብሎ ብዙ ዘመን ቆሞ ጸለየ፡፡ እግዚአብሔርም ጸሎቱን ሰምቶ "ይህ በረከት፣ ረድኤት፣ ሀብት፣ ፈውስ እንደወደድህ እስከዘለዓለሙ በዚህ ቦታ ይሁንልህ" አለው" ተብሎ ነው በቅዱስ ገድላቸው ላይ የተጻፈው፡፡

ጻድቁ አቡነ ዘርዐ ቡሩክ ሌላው የሚታወቁበት "ብሄሞትና ሌዋታን" የተባሉ እጅግ ግዙፍ የሆኑ ሁለት ዘንዶዎችን ጥርሳቸውን ቆጥረው ምላሳቸው ሲጣበቅ የዓለም ፍጻሜ እንደሚሆን አስቀድመው ያወቁ ድንቅ ነቢይ የሆኑ አባት በመሆናቸው ነው፡፡ እነዚህም እጅግ ግዙፍ የሆኑ ሁለት እንስሳት ሴትና ወንድ ሆነው ምድርን እንደመቀነት ከበው የያዙ ናቸው፡፡ ዝርዝር ታሪካቸው በመጽሐፈ አክሲማሮስ (ሥነ ፍጥረትን በሚያስረዳው መጽሐፍ) ላይ በስፋት ተጠቅሰዋል፡፡

አቡነ ዘርዐ ቡሩክ ሳይጠመቁ ለሚሞቱ አሕዛብም ጭምር ትልቅ ቃልኪዳን የተሰጣቸው ታላቅ አባት ናቸው፡፡ ይኸውም በቅዱስ ገድላቸው ላይ እንዲህ ተብሎ ተጽፏል- "በሥራው ሁሉ ፍጹም የሆነና ገድሉ ያማረ ቅዱስ አባታችንን በአድማስ ራስ ቆሞ ምሥራቁንና ምዕራቡን፣ ሰሜኑንና ደቡቡን እንዲባርክ በአፉ እስትንፋስም የምሕረት እስትንፋስን እፍ እንዲል እስትንፋሱንም ከአድማስ እስከ አድማስ ጽንፍ እስከ ጽንፍ ይደርስ ዘንድ እግዚአብሔር አዘዘው፡፡ በእግዚአብሔር በቅዱስ ስሙ ያልተጠመቁ አሕዛብ በእስትንፋሱ ምክንያትና የምሕረት እስትንፋስን እፍ እንዲል እስትንፋሱንም ከአድማስ እስከ አድማስ ጽንፍ እስከ ጽንፍ ይደርስ ዘንድ እግዚአብሔር አዘዘው፡፡ በእግዚአብሔር በቅዱስ ስሙ ያልተጠመቁ አሕዛብ በእስትንፋሱ ምክንያት ልጅነት አግኝተው እንዲከብሩ በቃል ኪዳኑ ተማፅነው ሳይጠመቁ በሚሞቱበት ጊዜ "ይህ ከእኔ የተቀበልከው ቃልኪዳን ከጎኔና ከሰውነቴ እንደፈሰሰው ደሜ ይሁንላቸው" በማለት ለዓለም መድኃኒት አድርጎ ቃልኪዳን ሰጠው፡፡

ዳግመኛም በቅዱስ አባታችን ዘርዐ ቡሩክ ስም ከእግዚአብሔር ምሕረትን ለምነው በሚሞቱበት ጊዜ በውኃና በመንፈስ ቅዱስ እንደተጠመቁ ይሁንላቸው ብሎ ነገረው፡፡ በከበረና በገናና ስሙ የተጠመቁ ሕዝቡም በኃጢአታቸው በወደቁ ጊዜ በሥራቸውም በረከሱ ጊዜ በጻድቁ ጸሎት ቢማጸኑ በቃልኪዳኑ ቢያምኑ ይህ እስትንፋሱ የኃጢአት ማስተሠርያ ይሁናቸው ብሎታል፡፡ ጻድቁ አባታችንም የእግዚአብሔርን ትእዛዝ በሰማ ጊዜ ከዚያ በፊት ለሌሎች ያልተሰጠ ቃልኪዳን ተቀብሎ በአድማስ ላይ ቆመ፡፡ በዚያም ቆሞ መንፈሳዊ እስትንፋሱን በምድር ላይ እፍ አለ፡፡ ያም የሕይወት እስትንፋስ በአራቱ ማዕዘን ደርሶ በኃጢአታቸው መከራ የተቀበሉ ለበደላቸውም የተገዙ ሰዎች በፈጣሪያቸው ስም እንዲከብሩ ዓለሙን ሁሉ ባረከ" ይላል ቅዱስ ገድላቸው፡፡ ይህም የሚያሳያየው መድኃኔዓለም ክርስቶስ የሰውን ልጆች ምን ያህል እንደወደዳቸውና በትንሽ ምክንያት የመዳንን
መንገድ ያዘጋጀላቸው መሆኑን ነው፡፡

ሌላው አቡነ ዘርዐ ቡሩክ እሳቸው በባረኳት ምድርና በልጆቻቸው ላይ ችግርና ርኀብ እንደማይደርስባቸው ቃልኪዳን የተሰጣቸው ድንቅ አባት ናቸው፡፡ ይኸውም በቅርቡ እንኳን በ1977ቱ የርሃብ ዘመን በግልጽ ስለታየ ታሪክ ይመሰክረዋል፡፡ በዚህ ወቅት ከወሎና ከሌሎችም ቦታዎች በርሃብ ተሰዶ ጎጃም ለመጣው የሀገራችን ሕዝብ የአቡነ ዘርዐ ቡሩክ በረከት ከበቂ በላይ ነበር፡፡

ጻድቁ በጎጃም ባሕር ዳር አካባቢ ሁለት ቤተ ክርስቲያን አላቸው፡፡ የዓባይ ምንጭ መነሻ የሆነው ፈለገ ግዮን ግሽ ዓባይ ከባሕር ዳር ከተማ 174 ኪ.ሜ የሚርቅ ሲሆን ከባሕር ዳር ቲሊሊ፣ ከቲሊሊ ሠከላ በመሳፈር በቦታው ላይ ለብዙ ዘመን ቆመው በመጸለይ ታላቅ ቃልኪዳን የተቀበሉበትን እጅግ ተአምረኛና ፈዋሽ የሆነውን ጸበላቸውን ማግኘት ይቻላል፡፡ ቦታው መጽሐፋቸውን ለዓባይ ወንዝ አደራ የሰጡበት ነው፡፡

ሌላኛው ቤተ ክርስቲያናቸው ከባሕር ዳር የሁለት ሰዓት የመኪና መንገድ ርቀት ላይ በምትገኘውና አዴት በምትባለው ቦታ የሚገኘው ነው፡፡ የአቡነ ዘርዐ ቡሩክ መካነ መቃብራቸውና ከሰማይ የወረደላቸው መስቀል እዚህ ይገኛሉ፡፡ ቦታውን የረገጠ ሁሉ ከመካነ መቃብራቸው ላይ እምነት ይወስዳል፣ በመስቀሉም ይባረካል፡፡ ነገር ግን ጻድቁ በቃል ኪዳናቸው መሠረት በዚህ መስቀላቸው የተባረከ ሁሉ ዲቁናን፣ ክህነትን መቀበል ስለሚችል ሴቶች አይባረኩበትም፡፡ መካነ መቃብራቸው ቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ከመቅደሱ ውጭ የሚገኝ ሲሆን ከመቃነ መቃብራቸው ላይ ያለው አፈር ሁልጊዜ እየፈላ መጠኑ ይጨምራል፡፡ ይህን የእምነቱን አፈር ቢዝቁት አያልቅም፣ ባዶ እንኳን ቢደረግ በተአምራት ሞልቶ ይገኛል፡፡ ለብዙ ሕመምተኞች ፍጹም ፈውስ የሆነው ይህ እምነት አጠቃላይ ሁኔታው ለዕይታ አመቺ ስለሆነ ይህንን ማንኛውም ሰው ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ማየትና እምነቱን ወስደው መጠቀም ይችላሉ፡፡

ጻድቁ አባታችን በ482 ዓመታቸው በዚህች ዕለት ጥር 13 ቀን በታላቅ ክብር ያረፉበት በዓላቸው በድምቀት ይከበራል፡፡ በዕረፍታቸው ዕለት ከቤተ ክርስቲያኑ አደባባይ ላይ አትሮንስ ወጥቶ ገድላቸው ይነበባል፡፡ ገድላቸው ሲነበብም ከአትሮንሱ ሥር ሰባት ጠርሙሶችና አንድ ማሰሮ ይቀመጥና በጠርሙሶቹ ውስጥ አንድ አንድ ስኒ ውኃ ይደረግባቸዋል፡፡ የአባታችን ቅዱስ ገድላቸው ሲነበብ ውኃው ይፈላል፣ ገድሉ ተነቦ እንዳለቀ ጠርሙሶቹና ማሰሮው በተአምራት ተሞልተው ይገኛሉ፡፡

ጌታችን ለአቡነ ዘርዐ ቡሩክ ትንባሆን ስለሚጠጡ ሰዎች ታላቅ ምሥጢርን እንደነገራቸው በቅዱስ ገድላቸው ላይ ተጽፏል፡፡ ቅዱስ አባታችን በየቀኑ ለሰባት ሰዓት ያህል በሲኦል ውስጥ ቆመው በመጸለይ ብዙ ነፍሳትን ከእሳት ያወጡ ነበር፡፡ አንድ ቀን ብዙ ነፍሳትን ካወጡ በኋላ አንዲት ነፍስ ግን ከሲኦል ግደግዳ ጋር እንደ ሰም ተጣብቃ እምቢ አለቻቸው፡፡ አባታችንም ያቺን ነፍስ አወጣለሁ ሲሉ ቆመው ይጸልዩበት የነበረው የሲኦል እሳት አሁን ያችን ነፍስ አወጣላሁ ባሉ ሰዓት ግን አቃጠላቸው፡፡ እሳቸውም ያችን ነፍስ እዚያው ሲኦል ጥለው በመውጣት ጌታችንን "የዚያች ነፍስ ኃጢአቷ ምንድን ነው?" አሉት፡፡ የዚህን ጊዜ ነው ጌታችን ትንባሆን ስለሚጠጡ ሰዎች ታላቅ ምሥጢርን የነገራቸው፡፡ ይኸውም አባ ሐዊ የሚባሉ ጻድቅ ያስተላለፉትን ውግዘትና ግዝት የጸና እንደሆነ ነው ጌታችን ለአቡነ ዘርዐ ቡሩክ የነገራቸው፡፡

ዝርዝር ታሪኩም በድርሳነ መድኃዓለም ላይ እንዲህ ተጽፎ ይገኛል፡- ትንባሆ የሚጠጡ ሰዎች ለምን ለማቆም እንደሚቸገሩና መጨረሻቸውም ምን እንደሆነ፡- "ይቅርታውና ምሕረቱ ከሁላችን የጥምቀት ልጆች ጋር ይሁንና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መድኃኔዓለም ያደረገው ተአምር ይህ ነው፡- አባታችን ዘርዓ ቡሩክ መድኃኔዓለምን እንደወደደውና በየወሩ በሃያ ሰባት ቀን በዓሉን እንደሚያከብር በአሥራ ስድስት ቀንም ኪዳነ ምሕረትን እንደሚያከብር እነሆ እንነግራችኋለን፡፡ ባለሟልነትን ባገኘ ጊዜና መድኃኔዓለም የእሳት ፈረስንና የመስቀል ምልክት ያለበት የወርቅ በትርን በሰጠው ጊዜ "ወደ ሲዖል ሂድና መሸከም የምትችለውን ያህል ነፍሳትን አውጣ› አለው፡፡ ሄዶም ወደ ሲዖል ገባ፣ ነፍስ በነፍስ ላይ እንደ ንብ እየተጨናነቁ በሰውነቱ ላይ ታዘሉ፡፡ ነፍሳትንም ይዞ ሲወጣ አንድ ኃጢአተኛ ‹ዘርዓ ቡሩክ ብቻዬን ቀረሁ፣ አውጣኝ" አለው፡፡ ዘርዓ ቡሩክም ወደ እርሱ ተመልሶ ሳበው፡፡ ሰም ከፈትል ጋራ እንደሚጣበቅ ከሲዖል ጥልቅ ጋራ ተጣብቆ እምቢ አለው፡፡ የእሳቱ ነበልባልም ዘርዓ ቡሩክን አቃጠለው፣ እርሱም ተወው፡፡ ክብር ይግባውና እነዚያን ነፍሳት ይዞ ወደ ጌታው ወደ መድኃኔዓለም ሄደ፡፡

ሄዶም "ጌታዬ ሆይ! አንዲት ነፍስ ስሜን እየጠራች ቀርታለች ማርልኝ" አለው፡፡ መድኃኔዓለምም "ዘርዓ ቡሩክ ሆይ! በእኔ ዘንድ ባለሟልነትን ብታገኝ ትንባሆ የሚጠጣውን ማርልኝ ትለኛለህን?" አለው፡፡ እርሱም "ጌታዬ ሆይ! ይህቺ እንጨት በምን ትከፋለች?፣ ከሁሉ ኃጢአትስ በምን ትበልጣለች?" አለው፡፡ ወይቤሎ መድኅን ኢሰማዕከኑ ግብራ ለዛቲ ዕፅ ዘከመ ዘርዓ ሰይጣን ውስተ ገራህተ ዓለም፡፡ መድኃኔዓለምም "የዚህችን እንጨት ሥራ በዓለም እርሻ ሰይጣን እንደዘራት አልሰማህምን?" አለው፡፡ እነሆም እንነግራችኋለን፣ ስሙ ሐዊ የሚባል የፈጣሪውንም ሕግ የሚጠብቅ አንድ መምህር ነበረ፡፡ በዓርብ ቀንም ወደ ሰማይ ይሔዳል፤ በቀዳሚት ሰንበትና በእሑድ ከፈጣሪው ጋር ይነጋገራል፡፡ በሰኞ ቀንም ወደ ቦታው ይመለሳል፡፡ ለሀገር ሰዎችም በጉባኤ ይነግራቸዋል፣ በአዋጅ ነጋሪ ቃልም ይሰበሰባሉ፡፡ ይህቺ ሀገር ትልቅ ናትና እስከ ዓርብም ያስተምራቸዋል፡፡ በዚያን ጊዜ ሰይጣን ቀና፡፡ አባ ሐዊም እንደልማዱ በዕለተ ዓርብ ወደ ሰማይ በሄደ ጊዜ ያ ሰይጣን በመቀመጫው ተቀምጦ በእርሱ በሐዊ ተመስሎ በቀዳሚት ሰንበት ቀንም ተገልጦ "ፈጣሪያችን የሚወዳትን ነገር እነግራችሁ ዘንድ ሁላችሁም ተሰብሰቡ" አለ፡፡ ሁላቸውም ተሰበሰቡ፡፡ "አባት ሆይ! ያለ ልማድህ ዛሬ ለምን መጣህና ጠራኸን?" አሉት፡፡ ያ ጠላት ዲያብሎስም "ጌታዬ ለሕዝቦቼ የዚያችን በቤትህ አንፃር ያለችውን እንጨት ቅጠል በጥርሳቸው ይጨምሩ ዘንድ፣ በአፋቸውም ያጤሱ ዘንድ ዛሬ ካልነገርሃቸው ወዳጄ አይደለህም አለኝ" አላቸው፡፡ ይህችንም እንጨት ባያት ጊዜ እንዲህ አደረገ፣ ሔዋንን በእንጨት እንዳሳታት አሳታቸው፡፡ ዛሬ እንደሚያደርጉትም የጥንባሆ ዕቃን አደረጉ፡፡ ቅጠሏንም አምጥተው ቀጥቅጠው በእሳት አጢሰው ትንሹም ትልቁም፣ የከበረውም የጎሰቆለውም ሁላቸውም ጠጡ፡፡

ሐዊም በሰማይ ሳለ በጸጋ አውቆ አዘነ፣ ነገር ግን ስለ ሰንበታት ክብር ብሎ አደረ፡፡ ሰኞ በነግህም ሐዊ መጣ፣ ሰይጣንም እንደ ጢስ በኖ ጠፋ፡፡ እርሱም ሰዎቹን ሰብስቦ "ይህን ማን አስተማራችሁ?" አላቸው፡፡ "አንተ ነህ" አሉት፡፡ "ሰይጣን ነው እንጂ እኔ አይደለሁም፣ ከዛሬ ጀምሮ ተው" አላቸው፡፡ "ትናንት ጠጡ፣ ዛሬ ተው" ይለናል ብለው እምቢ አሉት፡፡ እርሱም አወገዛቸው፡፡ "በእርሻው የዘራት፣ በአፉም የጠጣት፣ በእጁም የያዛት የተረገመ ይሁን" አላቸው፡፡ ጋኔኑም በቅሉ ውስጥ ሆኖ ይነጋገራል፣ በውጭ ያሉትንም አጋንንት ይጠራቸዋል፡፡ በዚህን ሰዓት የተውም አሉ፣ እምቢም ያሉ አሉ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ያቺ እንጨት ተረገመች፡፡ ሰውም በጠጣት ጊዜ የአምስት ቀፎ ሙሉ ንቦችን የሚያህሉ አጋንንት ይመጣሉ፡፡ በሁለቱ ዓይኖቹ ውስጥ፣ በሁለቱ አፍንጫዎቹም፣ በሁለቱ ጆሮዎቹም፣ በአፉም፣ በታች በሰገራ መውጫም በእነዚህ ሁሉ እንደ ቀፎ ንብ ይገባሉ፣ ይወጣሉ፡፡ ትምክህትን፣ ትዕቢትን፣ መግደልን፣
ሥርቆትንም፣ ክፉውንም ሁሉ ይመሉታል፡፡ ወሶበ ይሰትያ ብእሲ ይመጽኡ አጋንንት ዘየአክሉ መጠነ ፭ቱ ቀፈዋት ዘመልኡ አንህብት ወይበውኡ ውስቴቱ፡፡ በ፪ አዕይንቲሁ፣ ወበ፪ አዕናፊሁ፣ ወበ፪ አዕዛኒሁ ወበመንፈሱ ዘታህት በአፉሁ በዝንቱ ኵሉ ከመ ንህብ ዘቀፎ ይበውኡ ወይወጽኡ፡፡ ወይመልእዎ ትምክህተ፣ ወትዕቢተ፣ ቀትለ፣ ወሠሪቀ ወኵሎ ዕከያተ እንዲል መጽሐፍ፡፡

አባታችን ዘርዓ ቡሩክም ይህን ሰምቶ እጆቹን በትከሻው አመሳቅሎ አለቀሰ፣ በሥዕሉም አለ፣ በዚያን ጊዜ ወደ ዓለም ወጣ፡፡ ይህችን የተረገመች እንጨት እንዲህ ብሎ አወገዛት፡- "በአፉ የጠጣት፣ በእጁም የያዛት፣ የዘራት፣ የሸጣት፣ የገዛትም የጥምቀት ልጅ አይደለም፤ በሥጋው አይጠቀምም፣ ነፍሱም ወደ ሲዖል ትወርዳለች፡፡ ልጄ የሆነ ግን መድኃኔዓለምንና ኪዳነ ምሕረትን ያክብር፡፡ ጥንባሆንም አይጠጣ› አለ፡፡ የዚህ ጻዲቅ በረከቱ ያልታዘዝንውን ከመብላት ይጠብቀን አሜን" በማለት ተአምረ መድኃኔዓለም ወገድለ መባዓ ጽዮን ነገረ ጥንባሆን በሰፊው ዘግቦታል፡፡ በሌላም በኩል ትንባሆን በተመለከተ መድኃኔዓለም ክርስቶስ ለአቡነ ዘርዐ ቡሩክ የሰጣቸው ቃልኪዳን በራሳቸው በዘርዐ ቡሩክ ገድል ላይ የተጻፈውን ወደፊት እናያለን፡፡ እንዲሁም ይህችን የተረገመች ዕፅ የሚጠቀሙባት ሁሉ የሰይጣን ማደሪያዎች እንደሚሆኑና ክፉውንም ሁሉ እንደሚያሠሩት በሌላም ቦታ በአቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ገድል ላይ በሰፊው ተጽፏል፡፡

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን ።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ነሐሴ_27 እና #ከገድላት_አንደበት #ዲያቆን_ዮርዳኖስ_አበበ)
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ነሐሴ_27_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ዕብራውያን 5
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ ሊቀ ካህናት ሁሉ ስለ ኃጢአት መባንና መስዋዕትን ሊያቀርብ ከሰው ተመርጦ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ ስለ ሰው ይሾማልና፤
² እርሱ ራሱም ደግሞ ድካምን ስለሚለብስ፥ ላልተማሩትና ለሚስቱት ሊራራላቸው ይችላል፤
³ በዚህም ምክንያት ስለ ሕዝብ እንደሚያቀርብ እንዲሁ ስለ ራሱ ደግሞ መስዋዕትን ስለ ኃጢአት ሊያቀርብ ይገባዋል።
⁴ እንደ አሮንም በእግዚአብሔር ከተጠራ በቀር ማንም ክብሩን ለራሱ የሚወስድ የለም።
⁵ እንዲሁ ክርስቶስ ደግሞ ሊቀ ካህናት ሊሆን ራሱን አላከበረም ነገር ግን፦ አንተ ልጄ ነህ እኔ ዛሬ ወልጄሃለሁ ያለው እርሱ ነው፤
⁶ እንደዚህም በሌላ ስፍራ ደግሞ፦ አንተ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ካህን ነህ ይላል።
⁷ እርሱም በስጋው ወራት ከሞት ሊያድነው ወደሚችል ከብርቱ ጩኸትና ከእንባ ጋር ጸሎትንና ምልጃን አቀረበ፥ እግዚአብሔርንም ስለ መፍራቱ ተሰማለት፤
⁸ ምንም ልጅ ቢሆን፥ ከተቀበለው መከራ መታዘዝን ተማረ፤
⁹-¹⁰ ከተፈጸመም በኋላ በእግዚአብሔር እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ሊቀ ካህናት ተብሎ ስለ ተጠራ፥ ለሚታዘዙለት ሁሉ የዘላለም መዳን ምክንያት ሆነላቸው።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ጴጥሮስ 3
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁴ ነገር ግን ስለ ጽድቅ እንኳ መከራን ብትቀበሉ ብፁዓን ናችሁ። ማስፈራራታቸውንም አትፍሩ አትናወጡም፥
¹⁵ ዳሩ ግን ጌታን እርሱም ክርስቶስ በልባችሁ ቀድሱት። በእናንተ ስላለ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቁአችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ሁኑ፥ ነገር ግን በየዋህነትና በፍርሃት ይሁን።
¹⁶ በክርስቶስ ያለውን መልካሙን ኑሮአችሁን የሚሳደቡ ሰዎች ክፉን እንደምታደርጉ በሚያሙበት ነገር እንዲያፍሩ በጎ ሕሊና ይኑራችሁ።
¹⁷ የእግዚአብሔር ፈቃድ እንዲህ ቢሆን፥ ክፉ ስለ ማድረግ ሳይሆን በጎ ስለ ማድረግ መከራን ብትቀበሉ ይሻላችኋልና።
¹⁸ ክርስቶስ ደግሞ ወደ እግዚአብሔር እንዲያቀርበን እርሱ ጻድቅ ሆኖ ስለ ዓመፀኞች አንድ ጊዜ በኃጢአት ምክንያት ሞቶአልና፤ በሥጋ ሞተ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ፥
¹⁹ በእርሱም ደግሞ ሄዶ በወኅኒ ለነበሩ ነፍሳት ሰበከላቸው፤
²⁰ ጥቂቶች ማለት ስምንት ነፍስ በውኃ የዳኑበት መርከብ ሲዘጋጅ፥ የእግዚአብሔር ትዕግሥት በኖኅ ዘመን በቈየ ጊዜ ቀድሞ አልታዘዙም።
²¹ ይህም ውኃ ደግሞ ማለት ጥምቀት ምሳሌው ሆኖ አሁን ያድነናል፥ የሰውነትን እድፍ ማስወገድ አይደለም፥ ለእግዚአብሔር የበጎ ሕሊና ልመና ነው እንጂ፥ ይህም በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ነው፤
²² እርሱም መላእክትና ሥልጣናት ኃይላትም ከተገዙለት በኋላ ወደ ሰማይ ሄዶ በእግዚአብሔር ቀኝ አለ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 3
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁷ አሁንም፥ ወንድሞቼ ሆይ፥ እናንተ እንደ አለቆቻችሁ ደግሞ ባለማወቅ እንዳደረጋችሁት አውቄአለሁ፤
¹⁸ እግዚአብሔር ግን ክርስቶስ መከራ እንዲቀበል አስቀድሞ በነቢያት ሁሉ አፍ የተናገረውን እንዲሁ ፈጸመው።
¹⁹-²⁰ እንግዲህ ከጌታ ፊት የመጽናናት ዘመን እንድትመጣላችሁ አስቀድሞም ለእናንተ የመረጠውን ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲልክላችሁ፥ ኃጢአታችሁ ይደመሰስ ዘንድ ንስሐ ግቡ ተመለሱም።
²¹ እግዚአብሔር ከጥንት ጀምሮ በቅዱሳን ነቢያቱ አፍ የተናገረው፥ ነገር ሁሉ እስከሚታደስበት ዘመን ድረስ ሰማይ ይቀበለው ዘንድ ይገባልና።
²² ሙሴም ለአባቶች፦ ጌታ አምላክ እኔን እንዳስነሣኝ ነቢይን ከወንድሞቻችሁ ያስነሣላችኋል፤ በሚነግራችሁ ሁሉ እርሱን ስሙት።
²³ ያንም ነቢይ የማትሰማው ነፍስ ሁሉ ከሕዝብ ተለይታ ትጠፋለች አለ።
²⁴ ሁለተኛም ከሳሙኤል ጀምሮ ከእርሱም በኋላ የተናገሩት ነቢያት ሁሉ ደግሞ ስለዚህ ወራት ተናገሩ።
²⁵ እናንተ የነቢያት ልጆችና እግዚአብሔር ለአብርሃም፦ በዘርህ የምድር ወገኖች ሁሉ ይባረካሉ ብሎ፥ ከአባቶቻችን ጋር ያደረገው የኪዳን ልጆች ናችሁ።
²⁶ ለእናንተ አስቀድሞ እግዚአብሔር ብላቴናውን አስነሥቶ፥ እያንዳንዳችሁን ከክፋታችሁ እየመለሰ ይባርካችሁ ዘንድ፥ ሰደደው።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ነሐሴ_27_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"ወሳሙኤልኒ ምስለ እለ ይጼውዑ ስሙ። ይጼውዕዎ ለእግዚአብሔር ውእቱኒ ይሰጠዎሙ። ወይትናገሮሙ በዐምደ ደመና"። መዝ 98፥6-7።
"ሙሴና አሮን በካህናቱ ዘንድ፥ ሳሙኤልም ስሙን በሚጠሩት ዘንድ ናቸው፤ እግዚአብሔርን ጠሩት፥ እርሱም መለሰላቸው። በደመና ዓምድም ተናገራቸው፤ ምስክሩንና የሰጣቸውን ትእዛዝ ጠበቁ"። መዝ 98፥6-7።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ነሐሴ_27_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ዮሐንስ 12
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²⁶ የሚያገለግለኝ ቢኖር ይከተለኝ፥ እኔም ባለሁበት አገልጋዬ ደግሞ በዚያ ይሆናል፤ የሚያገለግለኝም ቢኖር አብ ያከብረዋል።
²⁷ አሁን ነፍሴ ታውካለች ምንስ እላለሁ? አባት ሆይ፥ ከዚህ ሰዓት አድነኝ። ነገር ግን ስለዚህ ወደዚህ ሰዓት መጣሁ።
²⁸ አባት ሆይ፥ ስምህን አክብረው። ስለዚህም፦ አከበርሁት ደግሞም አከብረዋለሁ የሚል ድምፅ ከሰማይ መጣ።
²⁹ በዚያ ቆመው የነበሩትም ሕዝብ በሰሙ ጊዜ፦ ነጐድጓድ ነው አሉ፤ ሌሎች፦ መልአክ ተናገረው አሉ።
³⁰ ኢየሱስም መለሰ፥ እንዲህ ሲል፦ ይህ ድምፅ ስለ እናንተ መጥቶአል እጂ ስለ እኔ አይደለም።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈ_ወርቅ ቅዳሴ ነው። መልካም የመልአኩ የቅዱስ ሱርያል በዓልና የአቡነ ዘርዐ ቡሩክ የልደት በዓል። ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ነሐሴ_28

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ነሐሴ ሃያ ስምንት በዚች ቀን የአባቶቻችን #የአብርሃም #የይስሐቅና #የያዕቆብን መታሰቢያቸው ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አበ_ብዙሃን_አብርሃም

ነሐሴ ሃያ ስምንት በዚች ቀን የአባቶቻችን የአብርሃም የይስሐቅና የያዕቆብን መታሰቢያቸውን እናደርግ ዘንድ የቤተ ክርስቲያን መምህራን አባቶቻችን አዘዙን ከእርሳቸው ለዘላለም የሚኖር ርስትን ተቀብለናልና።

የእሊህንም አባቶች ትሩፋታቸውንና ጽድቃቸውን ከሰው መናገር የሚችል ማነው?

ከሁሉ ነገር አስቀድሞ #እግዚአብሔር አብርሃምን ጠርቶ እንዲህ አለው ከአገርህ ወጥተህ ከዘመድህ ከአባትህ ወገን ተለይተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ሒድ። ታላቅ ሕዝብ አደርግሃለሁ ስምህንም ከፍ ከፍ አደርገዋለሁ የተባረክህም ትሆናለህ።

የሚአከብሩህንም አከብራቸዋለሁ የሚረግሙህንም እረግማቸዋለሁ የዚህ ዓለም አሕዛብም ሁሉ በአንተ ይከብራሉ። አብርሃምም #እግዙአብሔር እንዳዘዘው ሔደ የወንድሙን ልጅ ሎጥንና ሚስቱ ሣራንም ከርሱ ጋር ወሰደ።

አብርሃምም ከካራን በወጣ ጊዜ ዕድሜው ሰባ አምስት ዘመናት ሁኖት ነበር በካራንም ያጠራቀሙትን ገንዘባቸውን ሁሉ ይዘው ወደ ከንዓን ምድር ደረሱ። አብርሃምም ያቺን አገር ረጅም ዕንጨት እስከ አለበት እስከ ሴኬም ድረስ ዞራት የከነዓን ሰዎች ግን የዚያን ጊዜ በዚያች አገር ነበሩ።

#እግዚአብሔርም ለአብርሃም ተገልጦለት ይችን አገር ለልጆችህ እሰጣታለሁ አለው አብርሃምም በዚያ ለተገለጠለት ለ #እግዚአብሔር መሥዋዕትን አዘጋጀ። ከዚያም ወደ ምሥራቅ ወደ ቤቴል ሔደ በቤተልም በጋይ በኩል በስተምዕራብ ድንኳኑን ተከለና በዚያ ተቀመጠ በዚያም ለ #እግዚአብሔር መሠዊያ ሠራ የ #እግዚአብሔርንም ስም ጠራ።

አብርሃምም ከዚያ ተነሥቶ ሔደ በዚያም ሊኖር ወደ አዜብ ተጓዘ። ባገርም ራብ በጸና ጊዜ አብርሃም በዚያ ሊኖር ወደ ግብጽ ወረደ በአገሩ ራብ ጸንቷልና ። አብርሃምም ወደ ግብጽ ይገባ ዘንድ በቀረበ ጊዜ እንዲህ ሆነ አብርሃም ሚስቱን ሣራን እንዲህ አላት አንቺ መልከ መልካም ሴት እንደሆንሽ አውቃለሁ የግብጽም ሰዎች ካዩሽ ሚስቱ ናት ብለው ይገድሉኛል አንቺንም በሕይወት ያኖሩሻል።

እንግዲህ ስለ አንቺ ይራሩልኝ ዘንድ በአንቺ ዘመንም ነፍሴ ትድን ዘንድ እኔ እኅቱ ነኝ በዮአቸው። አብርሃም ወደ ግብጽ በደረሰ ጊዜ እንዲህ ሆነ የግብጽ ሰዎች ሚስቱን እጅግ መልከ መልካም እንደሆነች አዮዋት ለፈርዖን ወሰዷት ወደ ቤቱም አገቧት።

ስለርሷም ለአብርሃም በጎ ነገርን አደረጉለት ሴቶች አገልጋዮችንና ወንዶች አገልጋዮችን ላሞችንና በጎችን በቅሎዎችንና ግመሎችን አህዮችንም አገኘ። #እግዚአብሔርም በአብርሃም ሚስት በሣራ ምክንያት ፈርዖንንና ቤተሰቡንም ጽኑ ሥቃይን አሠቃያቸው።

ፈርዖንም አብርሃምን ጠርቶ በእኔ ያደረግከው ይህ ነገር ምንድን ነው ሚስትህ መሆኗን ያልነገርከኝ ለምንስ እኅቴ ናት አልከኝ ሚስት ልትሆነኝ ወስጃት ነበር አሁንም ሚስትህ ያቻት ይዘሃት ሒድ አለው። ፈርዖንም አብርሃምንና ሚስቱን ሣራን ከጓዛቸው ሁሉ ጋር እንዲሸኙአቸው ብላቴኖቹን አዘዘ።

ከዚህም በኃላ ለአብርሃም ዘጠና ዘጠኝ ዓመት በሆነው ጊዜ #እግዚአብሔር ለአብርሃም ተገለጠለት እንዲህም አለው በፊትህ የሔድኩ ፈጣሪህ #እግዚአብሔር እኔ ነኝ በፊቴ በጎ ነገርን አድርግ ንጹሕም ሁን።

በእኔና በአንተ መካከል ኪዳኔን አጸናለሁ ፈጽሜም አበዛሃለሁ ለብዙ አሕዛብም አባት ትሆናለህ። እንግዲህም ስምህ አብራም አይባልም አብርሃም እንጂ እጅግም አበዛሃለሁ አሕዛብ ነገሥታትም ከአንተ እንዲወለዱ አደርጋለሁ። አብርሃም በቀትር ጊዜ በድንኳን ደጃፍ ተቀምጦ ሳለ #እግዚአብሔር በወይራ ዛፍ አጠገብ ተገለጠለት።

ዐይኖቹንም አቅንቶ በተመለከተ ጊዜ እነሆ ሦስት ሰዎች በፊቱ ቁመው ነበር አይቶም ከድንኳኑ በር ሊቀበላቸው ሮጠ በምድር ላይም ሰገደ እንዲህም አለው አቤቱ በፊትህ ባልሟልነትን አግኝቼ ከሆነ ባሪያህን አትለፈኝ ውኃ አምጥተን እግራችሁን እንጠባችሁ ከጥላው ዕረፉ።

እንጀራም እናምጣላችሁና ብሎ ከዚህም በኃላ ወደ አሰባችሁት ትሔዳላችሁ እንዳልክ እንዲሁ አድርግ አሉት። አብርሃምም ወደ ሚስቱ ወደ ሣራ ሩጦ ወደ ድንኳን ገብቶ እንዲህ አላት ቶሎ በዬ ሦስቱን መሥፈሪያ ዱቄት አቡክተሽ አንድ ዳቦ ጋግሪ።

አብርሃምም ሁለተኛ ላሞች ወዳሉበት ሮጠ አንድ የሰባ ወይፈን ወሰደና ለብላቴናው ሰጠው እርሱም ፈጥኖ አዘጋጀው። ማርና እርጎ ያዘጋጀውንም ሥጋ አምጥቶ አቀረበላቸውና በሉ እርሱ ግን ቁሞ ያሳልፍላቸው ነበር።

እርሱም ሚስትህ ሣራ ወዴት ናት አለው። እነሆ በድንኳን ውስጥ አለች አለው በተመለስኩ ጊዜ የዛሬ ዓመት እንደዛሬው ወዳንተ እመጣለሁ ሣራም ወንድ ልጅን ታገኛለች አለው ሣራም በድንኳኑ ደጃፍ በስተኃላው ቁማ ሳለች ይህን ሰማች። አብርሃምና ሣራ ግን ፈጽመው አርጅተው ዘመናቸው አልፎ ነበር ሣራንም የሴቶች ልማድ ትቷት ነበር።

ሣራም ለብቻዋ ሳቀች በልቧ እንዲህ ብላለችና እስከ ዛሬ ገና ነኝን ጌታዬም አርጅቷል። #እግዚአብሔርም አብርሃምን እንዲህ አለው ሣራን ለብቻዋ ምን አሳቃት እስከ ዛሬ ገና ነኝን በውነትስ እወልዳለሁን ጌታዬም አርጅቷል እኔም እነሆ አርጅቻለሁ ብላ በውኑ ለ #እግዚአብሔር የሚሳነው ነገር አለን በቀጠርኩህ ዓመት ወደ አንተ በተመለስኩ ጊዜ ሣራ በሰባተኛ ወርዋ ልጅን ታገኛለች።

የዚህም አባት ተጋድሎው ትሩፋቱ ርኅራኄው ጽድቁም ብዙ ነው ሁል ጊዜ እንግዳ ካላገኘ በቀር በማዕዱ አብሮት ካልተቀመጠ አይበላም ነበር ስለዚህም ልዩ ሦስቱ አካላት በማዕዱ እንዲቀመጡ የተገባው ሆነ። አብርሃምም ከዚያ ተነሥቶ ወደ አዜብ ምድር ሔደ በሱሬና በቃዴስ መካከልም ኖረ በጌራራም ተቀመጠ።

አብርሃምም ሚስቱ ሣራን እኃቴ ናት አላቸው አቤሜሌክም ልኮ ሣራን ወሰዳት። በዚያችም ሌሊት አቤሜሌክ ተኝቶ ሳለ #እግዚአብሔር ወደ አቤሜሌክ ገባ በሕልም እንዲህ አለው እሷ የጎልማሳ ሚስት ናትና ስለዚች ስለወሰድካት ሴት እነሆ አንተ ትሞታለህ።

አቤሜሌክ ግን አልነካትም ነበር አቤሜሌክም እንዲህ አለ በውኑ ያላወቀ ሰውን ታጠፋለህን እሱ እኅቴ ናት አለኝ እሷም ወንድሜ ነው አለችኝ ይህንንም ሥራ በንጹህ ልቤ በንጹሕ እጄ አደረግሁት።

#እግዚአብሔርም በሕልም እንዲህ አለው እኔም በየዋህነትህ እንዳደረግከው አውቄአለሁና ራራሁልህ ኃጢአትም እንዳትሠራ ጠበቅሁህ ስለዚህም እንድትቀርባት አልተውኩህም ።

አሁንም ለዚያ ሰው ሚስቱን መልስለት ነቢይ ነውና ስለ አንተ ይፀልይልህ አንተም ትድናለህ ባትመልስለት ግን አንተ ሞትን እንድትሞት ያንተ የሆነው ሁሉ እንዲጠፋ ዕወቅ። አቤሜሌክም አብርሃምን ጠርቶ ይህ በእኔና በመንግሥቴ ላይ ያደረግከው ምንድር ነው ማንም የማይሠራው ታላቅ ኃጢአት ነው ይህንንስ ያደረግህ ምን አይተህ ነው አለው።

አብርሃምም እንዲህ አለ ምናልባት በዚህ ቦታ #እግዚአብሔርን መፍራት የለምና ስለሚስቴ ይገድሉኛል ብዬ ነው። ዳግመኛም በእውነት ከእናቴ ያይደለች ከአባቴ ወገን የሆነች እኅቴ ናት ሚስትም ሆነችኝ #እግዚአብሔርም ከአባቴ ቤት ባወጣኝ ጊዜ ይህንን በጎ ሥራ አድርጊልኝ በገባንበትም ቦታ ሁሉ ወንድሜ ነው በዬ አልኋት።

አቤሜሌክም ሺህ ምዝምዝ ብርን ሴቶች አገልጋዮችን ወንዶች አገልጋዮችን ላሞችና በጎችንም አምጥቶ ለአብርሃም ሰጠው ሚስቱ ሣራንም መለሰለት።
አብርሃምም ወደ #እግዚአብሔር ለመነ #እግዚአብሔርም አቤሜሌክን ፈወሰው ሚስቱንም ባሮቹንና ቤተሰቦቹንም ልጆቹንም ሁሉም ወለዱ ስለ አብርሃም ሚስት ስለሣራ #እግዚአብሔር ማሕፀንን ሁሉ በአፍአ በውስጥ ዘግቶ ነበርና።

ከዚህም በኃላ በጎ ተጋድሎውን ፈጽሞ #እግዚአብሔርንም አገልገሎ በመቶ ሰባ አምስት ዕድሜው ወደ ወደደው #እግዚአብሔር ሔደ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በአባታችን በቅዱስ አብርሃም ጸሎት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ይስሐቅ

በዚህችም ቀን ዳግመኛ የአባቶች አለቃ ለሆነ ለአብርሃም ልጅ ለይስሐቅ የዕረፍቱን መታሰቢያ እንድናደርግ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን መምህራን አባቶቻችን አዘዙን። ይህ ጻድቅ ይስሐቅም በልዑል አምላክ ብሥራት ተወለደ።

ይህንንም ንጹሕ ይስሐቅን #እግዚአብሔር ለልጁ ክርስቶስ ምሳሌው አደረገው። አብርሃምን እንዲህ ብሎታልና የምትወደው ልጅህ ይስሐቅን ከአንተ ጋራ ውሰደውና ወደላይኛው ተራራ ሒደረ እኔ ወደ እምነግርህ ወደ አንዱ ተራራ ላይ አውጥተህ በዚያ ሠዋው።

አብርሃምም በጥዋት ተነሥቶ አህያውን ጫነ ልጁ ይስሐቅንና ሁለቱ ብላቴኖቹንም ወሰደ ለመሥዋዕትም ዕንጨትን ፈልጦ አሸክሞ ሔደ። በሦስተኛም ቀን #እግዚአብሔር ወዳለው ወደዚያ ቦታ ደረሰ አብርሃምም በዐይኑ ቃኘ ቦታውንም ከሩቅ አየ።

አብርሃምም ብላቴኖቹን እናንተ አህያውን ይዛችሁ ከዚህ ቆዮ እኔና ልጄ ግን ወደ ተራራ እንሔዳለን ሰግደንም ወደ እናንተ እንመለሳለን አላቸው። አብርሃምም መሥዋዕት የሚቃጠልበትን ዕንጨት አምጥቶ ለልጁ ለይስሐቅ አሸከመው እሱም ወቅለምቱንና እሳቱን በጁ ያዘ ሁለቱም በአንድነት ሔዱ።

ይስሐቅም አባቱ አብርሃምን አባ አለው እርሱም ልጄ ምነው አለው እነሆ እሳትና እንጨት አለ መሥዋዕት የሚሆነው በጉ ወዴት ነው አለው አብርሃምም መሥዋዕት የሚሆነውን በግ #እግዚአብሔር ያዘጋጃል አለው።

አብረውም ሔደው #እግዚአብሔር ወዳለው ወደዚያ ቦታ ደረሱ አብርሃምም በዚያ መሠዊያን ሠራ ዕንጨቱን ደረደረ ልጁ ይስሐቅንም አሥሮ ጠልፎ በመሠዊያው በዕንጨቱ ላይ በልቡ አስተኛው። አብርሃምም ልጁን ያርደው ዘንድ እጁን ዘርግቶ ወቅለምቱን አነሣ።

#እግዚአብሔርም አብርሃምን አብርሃም አብርሃም ብሎ ጠራው እርሱም አቤት አለ በልጅህ ላይ እጅህን አትዘርጋ ምንም ምን አታድርግበት አንተ #እግዚአብሔርን እንደምትፈራው አሁን አወቅሁ ለምትወደው ለልጅህ አልራራህለትምና አለው።

አብርሃምም በተመለከተ ጊዜ ቀንድና ቀንዱ በዕፀ ሳቤቅ የተያዘ አንድ በግ አየ አብርሃምም ሔደና ወስዶ በልጁ በይስሐቅ ፈንታ ሠዋው። ይህም ንጹህ ይስሐቅ ጎልማሳ ሲሆን አባቱ ሊሠዋው በአቀረበው ጊዜ #እግዚአብሔር በበግ እስከ አዳነው ድረስ ለአባቱ በመገዛት ለመታረድ አንገቱን ዘርግቶ ሰጠ።

እርሱም በአባቱ በአብርሃም ሕሊና ፍጽም መሥዋዕተ ሆነ። ከዚህም በኃላ ይስሐቅን መቸገርና ስደት አግኝቶታል በአባቱ በአብርሃም ዘመን ከሆነው ሌላ በሀገር ረኃብ ሁኖ ነበርና የፍልስጥዔም ንጉሥ አቤሜሌክ ወዳለበት። ወደ ጌራራ ይስሐቅ ሔዶ በዚያ ተቀመጠ።

የአገር ሰዎችም ይስሐቅን የሚስቱን የርብቃን ነገር ጠየቁት እርሱም እኅቴ ናት አላቸው ስለ ሚስቱ ስለ ርብቃ የዚያች አገር ሰዎች እንዳይገድሉት ሚስቴ ናት ብሎ መናገርን ፈርቷልና መልከ መልካም ነበረችና። በዚያም ብዙ ዘመን ኖሩ አቤሜሌክም በመስኮት በተመለከተ ጊዜ ይስሐቅን ከርብቃ ጋር ሲጫወት አየው።

አቤሜሌክም ይስሐቅን ጠርቶ እኅቴ ናት አልከኝ እንጂ እነሆ ሚስትህ ናት አለው ይስሐቅም በርሷ ምክንያት ይገድሉኛል ብዬ ነው አለው። አቤሜሌክም ይህ ያደረግኽብኝ ነገር ምንድን ነው ከዘመዶቼ የሚሆን አንድ ሰው ከሚስትህ ጋር ሊተኛ ጥቂት ቀርቶት ነበር ባለማወቅም ኃጢአትን ልታመጣብኝ ነበር።

ንጉሡም የዚህን ሰው ሚስቱን የነካ ሁሉ ፍርዱ ይሙት በቃ ነው ብሎ ሕዝቡን አዘዛቸው። ይስሐቅም በዚያች ምድር ዘርን ዘራ መቶ ዕጽፍም ሆነለት #እግዚአብሔርም ባረከው ከፍ ከፍም አለ እጅግም ገነነ ወንድ ባርያን ሴት ባርያን ላምን በግን አብዝቶ ገዛ የፍልስጥኤም ሰዎችም ቀኑበት።

በአባቱም ዘመን የአብርሃም ብላቴኖች የቆፈሩአቸውን ጉድጓዶች የፍልስጥኤም ሰዎች ደፈኑዋቸው አፈርንም መሏቸው። አቤሜሌክም ይስሐቅን ፈጽመህ በርትተህብናልና ከእኛ ተለይተህ ሒድ አለው።

ይስሐቅም ከዚያ ተነሥቶ በጌራራ ሸለቆ ሰፍሮ በዚያ ተቀመጠ። ይስሐቅም ያባቱ አገልጋዮች የቆፈሩዋቸውን አባቱ አብርሃምም ከሞተ በኃላ የፍልስጥኤም ሰዎች የደፈኗቸውን የውኃ ጉድጓዶች እንደገና ቆፈራቸው አብርሃም እንደጠራቸው ጠራቸው።

የይስሐቅም አገልጋዮች በጌራራ ቆላ ጉድጓድ ቆፍረው የሚጣፍጥ የውኃ ምንጭ አገኙ የይስሐቅ እረኞችና የጌራራ እረኞች ይህ ውኃ የኛ ነው የኛ ነው በማለት ተጣሉ ያችንም የውኃ ጉድጓድ የዓመፅ ጉድጓድ ብሎ ጠራት ዐምፀውበታልና።

ይስሐቅም ከዚያ ተጎዞ ሒዶ በዚያ ሌላ ጉድጓድ ቁፈረ በርሷም ምክንያት ተጣሉት ስሟንም ጠብ ብሎ ምክንያት ተጣሉት ስሟንም ጠብ ብሎ ጠራት። ከዚያም ተጎዞ ሒዶ ሌላ ጉድጓድን ቁፈረ በርሱም ምክንያት ግን አልተጣሉትም ስሙንም ሰፊ አለው ዛሬ #እግዚአብሔር አሰፋልን በምድርም አበዛን ሲል።

ከዚህም በኃላ ሁለት ልጆችን ኤሳውንና ያዕቆብን ወለደ። ይስሐቅም ኤሳውን ጽኑዕ ኃይለኛ ስለሆነ ይወደዋል። ይስሐቅም አርጅቶ ዐይኖቹ ፈዘው የማያይ ከሆነ በኃላ እንዲህ ሆነ ታላቁ ልጁ ኤሳውን ጠርቶ እነሆ አረጀሁ የምሞትበትንም ቀን አላውቅም ማዳኛ መሣሪያህን የፍላፃ መንደፊያህን ይዘህ ወደ በረሃ ውጣ። ሳልሞት ነፍሴ እንድትመርቅህ እበላ ዘንድ እንደምወደው አድርገህ አምጣልኝ አለው።

ርብቃም ልጁ ኤሳውን እንዲህ ሲለው ይስሐቅን ሰማችው ኤሳውም ወደ አደን ሔደ። ርብቃም ታናሹ ልጇ ያዕቆብን እንዲህ አለችው እነሆ አባትህ ወንድምህን ኤሳውን ሳልሞት በ #እግዚአብሔር ፊት እንድመርቅህ ከአደንከው አዘጋጅተህ የምበላውን አምጣልኝ ሲለው ሰምቼዋለሁ።

አሁንም ልጄ ሆይ በማዝህ ነገር እሽ በለኝ ወደ በጎቻችንም ሒደህ ያማሩ ሁለት ጠቦቶችን አምጣልኝና አባትህ እንደሚወደው አዘጋጃቸው ዘንድ ሳይሞት በልቶ እንዲመርቅህ ወስደህ ለአባትህ እንድትሰጠው አለችው።

ያዕቆብም እናቱ ርብቃን እንዲህ አላት እነሆ ወንድሜ ኤሳው ጠጉራም ነው እኔ ግን ጠጉራም አይደለሁም ምናልባት አባቴ ቢዳስሰኝ በፊቱ እንደምዘብትበት እሆናለሁና ምርቃን ያይደለ በላዬ መርገምን አመጣለሁ።

እናቱም ልጄ ሆይ መርገምህ በእኔ ይሁን ቃሌን ብቻ ስማኝ ሒድና የምልህን አምጣልኝ አለችው ሒዶም ለእናቱ አመጣላትና አባቱ እንደሚወደው አድርጋ መብሉን አዘጋጀች።

ርብቃም ከርሷ ዘንድ የነበረ ያማረውን የታላቅ ልጅዋ የኤሳውን ልብስ አምጥታ ለታናሽ ልጅዋ ለያዕቆብ አለበሰችው ያንንም የሁለቱን ጠቦቶች ለምድ በትከሻውና በአንገቱ ላይ አደረገች ያንን ያዘጋጀችውን እንጀራና ጣፋጭ መብልን ለያዕቆብ በእጁ ሰጠችው።

ወደ አባቱ ገብቶ አባቴ ሆይ አለው አባቱም እነሆኝ ልጄ ሆይ አንተ ማነህ አለው ያዕቆብም እኔ የበኩር ልጅህ ኤሳው ነኝ ያልከኝን አዘጋጅቻለሁ ተነሥና ተቀመጥ ከአደንኩልህም ብላና ነፍስህ ትመርቀኝ ዘንድ አለው።
ይስሐቅም ልጁን ልጄ ሆይ ፈጥነህ ያገኘህ ይህ ምንድነው አለው እርሱም ፈጣሪህ #እግዚአብሔር በፊቴ የሰጠኝ ነው አለው። ይስሐቅም ልጄ ቅረበኝ ልዳሥሥህ አንተ ኤሳው እንደሆንክ ወይም እንዳልሆንክ አለው በቀረበም ጊዜ ዳሠሰውም ቃልህ የያዕቆብ እጆችህ አድነህ ያመጣህልኝን በልቼ ነፍሴ ትመርቅህ ዘንድ አምጣልኝ አለው አቅርቦለት በላ ወይንም አመጣለት ጠጣ።

ይስሐቅም ልጄ ቅረበኝና ሳመኝ አለው ቀርቦም ሳመው የልብሱን ሽታ አሸተተው እነሆ የልጄ ልብስ ሽታው #እግዚአብሔር እንደባረከው እንደዱር አበባ ሽታ ነው አለ። እንዲህም ብሎ መረቀው ከሰማይ ጠል ከምድር ስብ ይስጥህ ሥንዴህን ወይንህንና ዘይትህን ያብዛልህ አሕዛብም ይገዙልህ አለቆችም ይስገዱልህ ለወንድሞችህም ጌታ ሁን የአባትህም ልጆች ይስገዱልህ። የሚረግምህም የተረገመ ይሁን ይህም በ #እግዚአብሔር ፈቃድ ሆነ።

ይህም አባት ይስሐቅ ወደ መቶ ሰማንያ ዘመን ደረሰ አባታችን ይስሐቅም እንዲህ ብሎ ተናገረ ከዚህም በኃላ መልአክ ወደ ሰማይ ወሰደኝ አባቴ አብርሃምን አየሁትና ሰገድሁለት እርሱም ሳመኝ ንጹሕን ሁሉ ስለ አባቴ ተሰበሰቡና ወደ ውስጠኛው የአብ መጋረጃ ከበውኝ ከእኔ ጋራ ሔዱ እኔም ወድቄ ከአባቴ ጋራ ሰገድኩ።

የሚያመሰግኑ መላእክት ሁሉ ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ ተብሎ የሚመሰገን አሸናፊ #እግዘአአብሔር ምስጋናው በሰማይና በምድር የመላ ነው እያሉ ጮኹ።

አባቴ አብርሃምን እኔ በቦታዬ ልዩ ነኝ ሰው ሁሉ ልጁን በወዳጄ ይስሐቅ ስም ቢሰይም በቤቱ ውስጥ በረከቴ ለዘላለም ይኖራል የቡሩክ ወገን የሆንክ አንተ ቡሩክ አብርሃም ሆይ መምጣትህ መልካም ነው። አሁንም በወዳጄ በልጅህ ይስሐቅ ስም የሚለምን ሁሉ በረከቴ በቤቱ ውስጥ ለዘላለም እንዲኖር ቃል ኪዳኔን አጸናለታለሁ አለው።

ትሩፋቱን ቅንነቱን ገድሉን የሚጽፍ ካለ ወይም በስሙ የተራበ የሚያጠግብ በመታሰቢያው ቀን የተራቆተ የሚያለብስ እኔ የማያልፈውን መንግሥት እሰጠዋለሁ።

አብርሃምም እንዲህ አለ አቤቱ ዓለሙን ሁሉ የያዝክ #አብ ሆይ ቃል ኪዳኑን ገድሉን ይጽፍ ዘንድ ካልተቻለው ቸርነትህ ትገናኘው አንተ ቸር መሐሪ ነህና አንጀራ የሌለው ችግረኛ ቢሆንም። #ጌታም እንዲህ ብሎ መለሰለት በወዳጄ በይስሐቅ በመታሰቢያው ዕለት ከሌሊት ጀምሮ በጸሎት ይትጋ አይተኛ እኔም መንግሥቴን ከሚወርሱ ጋራ ከበረከቴ እሰጠዋለሁ።

አባቴ አብርሃምም ሁለተኛ እንዲህ አለ በሽተኛ ድውይ ከሆነ ቸርነትህ ታግኘው #ጌታም እንዲህ አለ ጥቂት ዕጣን ያግባ ዕጣንን ካላገኘ የቃል ኪዳኑን መጽሐፍ ፈልጎ በልጅህ በወዳጄ በይስሐቅ መታሰቢያ ቀን ያንብበው። ማንበብም የማያውቅ ከሆነ ወደሚያነቡለት ሒዶ እሷን አስነብቦ ይስማ። ከእነዚህም ይህን ማድረግ ካልቻለ ወደ ቤቱ ገብቶ ደጁን ይዝጋ እየጸለየ መቶ ስግደቶችን ይስገድ እኔም የሰማይ የመንግሥት ልጅ አደረገዋለሁ።

ለቁርባን የሚሆነውንና መብራትን ያገባ እኔ ያልኩትን ሁሉ የሚያደርግ እርሱ የመንግሥተ ሰማያትን ርስት ይቀበላል። ቃል ኪዳኑንና ገድሉን ትሩፋቱን ለመጻፍ ልቡን ያበረታውን እኔ ስሙን በሕይወት መጽሐፍ እጽፋለሁ በሺው ዓመት ምሳ ላይም ይገኛል።

#እግዚአብሔርም ይህን ብዙ ነገርን በተናገረ ጊዜ ያዕቆብ አይቶ በመደንገጥ ነፍሱ ተመሠጠች ይስሐቅም ያዕቆብን አንሥቶ ልጄ ሆይ ዝም በል አትደንግጥ ብሎ ጠቀሰው ከዚህም በኃላ ሳመውና በሰላም አረፈ። ከኤሞር ልጆች በገዛው እናቱ ሣራ በተቀበረችበት በአብርሃም መቃብር ተቀበረ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ ይስሐቅ አማላጅነት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ያዕቆብ

በዚችም ቀን ደግሞ #እግዚአብሔር እስራኤል ብሎ ስም ያወጣለትን የአባቶች አለቃ የሆነ የያዕቆብን የዕረፍቱን መታሰቢያ እናደርግ ዘንድ የቤተ ክርስቲያን መምህራን አባቶቻችን አዘዙን። ይህም ቅዱስ በበጎ ሥራ ሁሉ በመራራት በቅንነት በትሕትና በለጋስነት የአባቶቹን የአብርሃምንና የይስሐቅን መንገድ የተከተለ ሆነ።

ወንዱሙ ኤሳውም ብኩርናውን በምስር ንፍሮ ደግሞ በረከቱን ስለወሰደበት አብዝቶ ስለጠላው ሊገድለው ይፈልግ ነበር ስለዚህም አባቱ ይስሐቅና እናቱ ርብቃ ያዕቆብን ወደ ርብቃ ወንድም ወደ ላባ ሰደዱት።

እየተጓዘም ሳለ በአደረበት በረሀ ከምድር እስከ ሰማይ የሚደርስ መሰላል የ #እግዚአብሔርም መላእክት በውስጡ ሲወርዱ ሲወጡ በሕልሙ አየ እንዲህም አለ ይህ የሰማይ ደጅ ነው ከዚህም የ #እግዚአብሔር ቤት ይሠራል።

በሶርያ ምድር ወደሚኖር ወደእናቱ ወንድም ወደ ላባ በደረሰ ጊዜ ሁለቱን ልጆቹን ልያንና ራሔልን አጋባው በዚያም የላባን በጎች እየጠበቀ ሃያ አንድ ዓመት ያህል ኖረ። ላባም የምሰጥህ ምንድን ነው አለው ያዕቆብም ምንም የምትሰጠኝ የለም አሁን ወደፊት የምነግርህን ነገር ካደረግህልኝ ዳግመኛ በጎችህን ፈጽሜ እጠብቃለሁ።

አሁን በጎችህ በፊት ይለፉና ከበጎችህ ሁሉ ጠጉራቸው ነጫጭ የሆኑትንና መልካቸው ዝንጉርጉር የሆነውንም ስለዋጋዬ ለይልኝ አለው። ዓይነቱ ዝንጉርጉር ያልሆነውና መልኩ ነጭ ያልሆነው ሁሉ ግን ላንተ ይሁን አለው። ላባም እንዳልክ ይሁን አለ።

በዚያችም ቀን ነጩንም ቀዩንም ዝንጉርጉሩንም መልኩ ዳንግሌ የሆነውንም የፍየሉንም አውራ ለይቶ ለልጆቹ ሰጠ። በእነርሱና በያዕቆብ መካከል ሦስት ቀን የሚያስኬድ ጎዳና ርቀው ሔዱ ያዕቆብ ግን የቀሩትን የላባን በጎች ይጠብቅ ነበር።

ያዕቆብም የልምጭ በትርንና ታላቅ የሎሚ በትርን ወስዶ ቅረፍቱን ልጦ ጣለው ያዕቆብ የላጣቸው በትሮች ነጫጭ ሁነው ታዩ። እነዚያንም በትሮች በጎች ከሚጠጡበት ገንዳ ላይ ጣላቸው በጎች ውኃ ሊጠጡ በመጡ ጊዜ እነዚያ በትሮች በፊታቸው ሁነው ይታዩ ዘንድ። መጥተውም በጠጡ ጊዜ እነዚያን በትሮች አስመስለው ፀንሰው ነጩንና ሐመደ ክቦውን ዝንጉርጉሩን ወለዱ።

ያዕቅብም አውራ አውራዎቹን በጎች ለየ አውራ አውራውን ከለየ በኃላ እንስት እንስቶቹን በጎች ለይቶ ዝንጉርጉር ሐመደ ክቦና ነጭ በሆኑ አውራዎች ፊት አቆማቸው የራሱንም በጎች ለያቸው እንጂ ከላባ በጎች ጋራ አልቀላቀላቸውም።

ያዕቆብም እጅግ ፈጽሞ ባለጸጋ ሆነ ሴቶችንም ወንዶችንም አገልጋዩችን ገዛ ብዙ ከብት ላሞችን በጎችን ግመሎችንና አህዮችን ገዛ። ያዕቆብም ወደአገሩ በተመለሰ ጊዜ እስከ ንጋት ድረስ አንድ ሰው ሲታገለው አደረ ከእርሱም ጋራ ሲታገል እንዳልቻለው ባየ ጊዜ እርም የሚሆንበት ሹልዳውን ያዘው ጎህ ቀድዷልና ልቀቀኝ አለው ካልመረቅከኝ አልለቅህም አለው።

ስምህ ማን ይባላል ቢለው ስሜ ያዕቆብ ነው አለው እንግዲህ ስምህ ያዕቆብ አይባል እስራኤል ይባል እንጂ አለው ከ #እግዚአብሔርና ከሰው ጋራ መታገልን ችለሃልና።

ከዚህም በኃላ ስለ ልጁ ዮሴፍ ብዙ ኀዘን አገኘው ወንድሞቹ ወደ ግብጽ ሸጠውታልና በጠየቃቸውም ጊዜ ክፉ አውሬ በልቶታል አሉት ከልቅሶውም ብዛት የተነሣ ዐይኖቹ ታወሩ።

ከዚህም በኃላ ታላቅ ረሀብ ሆነ በግብጽ አገር እህል የሚሸጥ መሆኑን ያዕቆብ ሰማ ሥንዴ ይሸምቱ ዘንድ ልጆቹን ላካቸውና ወደ ዮሴፍ ደረሱ ንጉሥ ሆኖም አግኘተውት ሰገዱለት ወንድማቸው እንደሆነም አላወቁትም እርሱ ግን አውቋቸዋል ሥንዴውንም ሰጥቶ አስናበታቸው ሁለተኛም በተመለሱ ጊዜ ራሱን ገለጠላቸውና ወደዚህ ስለ ሸጣችሁኝ አትፍሩ እመግባችሁ ዘንድ በፊታችሁ #እግዚአብሔር ለሕይወት ልኮኛልና አላቸው።

አሁንም ፈጥናችሁ ሒዱና ለአባቴ ንገሩት ልጅህ ዮሴፍ እንዲህ ይላል በሉት ለግብጽ አገር ሁሉ #እግዚአብሔር ጌታ አድርጎኛል ፈጥነህ ና በዚያ ልኑር አትበል።
ስለዚህም እስራኤል ወደግብጽ አገር ከቤተሰቡ ሁሉና ከጓዙ ከገንዘቡ ጋር ወርዶ በዚያ የሚኖር ሆነ። ዕረፍቱም በቀረበ ጊዜ ልጆቹን ጠርቶ እየአንዳንዳቸውን መረቃቸው ትንቢትንም ተናገረላቸው የዮሴፍንም ልጆች ኤፍሬምንና ምናሴን እጆቹን አመሳቅሎ ባረካቸው መረቃቸውም። ከዚህም በኃላ በመቶ ሠላሳ ሰባት ዕድሜው በሰላም በፍቅር አረፈ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በአባቶቻችን በአብርሃም፣ በይስሐቅ እና በያዕቆብ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን ።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ነሐሴ_28)
#ነሐሴ_28_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ማቴዎስ 22
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²³ በዚያን ቀን፦ ትንሣኤ ሙታን የለም የሚሉ ሰዱቃውያን ወደ እርሱ ቀረቡ፥
²⁴ እንዲህም ብለው ጠየቁት፦ መምህር ሆይ፥ ሙሴ አንድ ሰው ልጅ ሳይወልድ ሲሞት ወንድሙ ሚስቱን አግብቶ ለወንድሙ ዘር ይተካ አለ።
²⁵ ሰባት ወንድማማች በእኛ ዘንድ ነበሩ፤ ፊተኛውም ሚስት አግብቶ ሞተ፥ ዘርም ስለሌለው ሚስቱን ለወንድሙ ተወለት፤
²⁶ እንዲሁ ደግሞ ሁለተኛው ሦስተኛውም፥ እስከ ሰባተኛው ድረስ።
²⁷ ከሁሉም በኋላ ሴቲቱ ሞተች።
²⁸ ሁሉ አግብተዋታልና በትንሣኤ ቀንስ፥ ከሰባቱ ለማናቸው ሚስት ትሆናለች?
²⁹ ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኃይል አታውቁምና ትስታላችሁ።
³⁰ በትንሣኤስ እንደ እግዚአብሔር መላእክት በሰማይ ይሆናሉ እንጂ አያገቡም አይጋቡምም።
³¹-³² ስለ ትንሣኤ ሙታን ግን፦ እኔ የአብርሃም አምላክ፥ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ ነኝ የሚል ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ እናንተ የተባለውን አላነበባችሁምን? የሕያዋን አምላክ ነው እንጂ የሙታን አይደለም።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
መልካም የአርእስተ አበው የቅዱሳን የ #አብርሃም#ይስሐቅ#ያዕቆብ የዕረፍት በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"#ሰላም_ለአብርሃም_ዘበዘርዑ_ተባረከ ኵሉ ዓለም ርእሰ አበው ግሩም ዘይቤሎ እግዚአብሔር ክቡር አንተ ዘከመ ስብሐትየ። ትርጉም፦ እግዚአብሔር እንደ ጌትነቴ ያከበርኹኽ አንተ የከበርኽ ነኽ ያለው፤ የተወደደ የአባቶች አለቃ ዓለም ኹሉ በዘሩ የተባረከለት ለኾነ #ለቅዱስ_አብርሃም_ሰላምታ_ይገባል#ሊቁ_አባ_ጊዮርጊስ_ዘጋስጫ_በተአምኆ_ቅዱሳን_ላይ
"#ሰላም_ለይሥሐቅ_ንጹሕ_ወጻድቅ ዘኮነ መሥዋዕተ ኅየንቴሁ ኢየሱስ ሊቅ በአምሳለ በግዕ ዘስቁል በዕፀ ሳቤቅ"። ትርጉም፦ በዕፀ ሳቤቅ ላይ በተሰቀለው በግ አምሳል መምህር ኢየሱስ በርሱ ፈንታ መሥዋዕት የኾነለት ለኾነ #ለንጹሕና_ለጻድቅ_ለቅዱስ_ይሥሐቅ_ሰላምታ_ይገባል#ሊቁ_አባ_ጊዮርጊስ_ዘጋስጫ_በተአምኆ_ቅዱሳን_ላይ
"#ሰላም_ለያዕቆብ_ምንዙህ_ዘኮነ_በረከቱ_ብዙኀ እምጠሉ ለሰማይ ወእምስፍሓ ለምድር፤ ዘአስተርአዮ እግዚአብሔር ገጸ በገጽ ወተናገሮ በምድረ ሎዛ፤ ወሰመየ ስሞ እስራኤል"። ትርጉም፦ ከሰማይ ጠልና ከምድርም ስፋት ይልቅ በረከቱ የበዛ የኾነ እግዚአብሔር ፊት ለፊት የተገለጸለት (የታየው) በሎዛ ምድርም የተናገረው፤ ስሙንም እስራኤል ብሎ ለሰየመለት ቅምጥል ድልድል ለኾነ #ለቅዱስ_ያዕቆብ ሰላምታ ይገባል። #ሊቁ_አባ_ጊዮርጊስ_ዘጋስጫ_በተአምኆ_ቅዱሳን_ላይ
2024/09/24 17:20:38
Back to Top
HTML Embed Code: