Telegram Web Link
የጻድቁ አቡነ ተክለ ሐይማኖትን ስም ለሚጠራ መታሰቢያ ለሚያደርግ ለተራበ የሚያበላ ለተጠማ የሚያጠጣውን.... እስከ ስንት ትውልድ ነው እምርልኃለሁ ያላቸው?
Anonymous Quiz
31%
እስከ 15 ትውልድ
53%
እስከ 10 ትውልድ
6%
እስከ 25 ትውልድ
9%
እስከ 35 ትውልድ
የቅዱስ ቶማስ ዘመርዓስን ሥጋ ወደ ጉባኤ ነቂያ በቅርጫት እስከሚወስዱት ድረስ ከሃዲያኖች ሰውነቱን እየቆራረጡ ለስንት ዓመት አሰቃዩት?
Anonymous Quiz
60%
22 ዓመት
13%
25 ዓመት
10%
27 ዓመት
17%
30 ዓመት
ቅዱስ ቶማስ ዘመርዓስ ማን ቅዱስ ክርስቲያን እስከ ነገሠና ነፃ እስከ ወጣ ድረስ ነው ለብዙ አመታት ከሃዲያኖች ሰውነቱን ሲያሰቃዩት?
Anonymous Quiz
12%
ጻድቅ ንጉሥ ካሌብ
68%
ጻድቅ ንጉሥ ቁስጠንጢኖስ
8%
ጻድቅ ንጉሥ ገብረ መስቀል
12%
ጻድቅ ንጉሥ ቴዎዶስዮስ
#ነሐሴ_26

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ነሐሴ ሃያ ስድስት በዚህች ቀን ለአብርሃም ሚስት ለተመሰገነች #ቅድስት_ሣራ መታሰቢያዋ ነው፣ የከበረ #አባ_ሞይስስና_እኅቱ_ሣራ በሰማዕትነት ሞቱ፣ የከበሩ መነኰሳት #ቅዱሳን_አጋቦስና_ቴክላ በሰማዕትነት ሞቱ፣ የከበሩ አባቶቻችን #አቡነ_ኢየሱስ_ሞዐ እና #አቡነ_ሀብተ_ማርያም የተፀነሱበት ዕለት ነው፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_ሣራ

ነሐሴ ሃያ ስድስት በዚህች ቀን ለአብርሃም ሚስት ለተመሰገነች ሣራ መታሰቢያዋን እናደርግ ዘንድ የቤተ ክርስቲያን መምህራን አባቶች አዘዙ።

ይቺንም ክብርተ ማሕፀን የሆነች ጡቶቿም የተባረኩ ክብርት ሣራን የጌራራ ንጉሥ አቤሜሌክ ባል እንዳላት ሳያውቅ በወሰዳት ጊዜ እንዳይቀርባት #እግዚአብሔር ገሠጸው በደዌም ቀሠፈው ባሏ አብርሃምም በጸለየለት ጊዜ ከደዌው ተፈወሰ ከዚህም በኋላ ከብዙ ገንዘብ ጋራ ወደ ባሏ መለሳት።

ከዚህም በኋላ #እግዚአብሔር በሦስትነቱ ተገልጦ ወደ ቤቷ እንግድነት በመጣ ጊዜ ለአብርሃምም የይስሐቅን መወለድ በነገረው ጊዜ ሣራም በድንኳኑ ውስጥ ሳቀች እንዲህ ስትል እስከ ዛሬ ገና ነኝን ጌታዬም አርጅቷል።

#እግዚአብሔርም አብርሃምን እንዲህ አለው ሣራን ለብቻዋ ምን አሳቃት እስከ ዛሬ ገና ነኝን ጌታዬም አርጅቷል እኔም አሁን አርጅቻለሁ ብላ በውኑ ለ #እግዚአብሔር የሚሳነው ነገር አለን። ከዚህም በኋላ ሣራ ፀንሳ #እግዚአብሔር ባለው ወራት በርጅናዋ ለአብርሃም ወንድ ልጅን ወለደች።

ይስሐቅም በአደገ ጊዜ ልጅዋ ይስሐቅን ከእስማኤል ጋራ ሲጫወት አየችው። አብርሃምንም ሣራ እንዲህ አለችው ይቺን ባሪያ ከነልጅዋ አባራት የባሪያ ልጅ ከልጄ ከይስሐቅ ጋራ አይወርስምና። ይህም ነገር ለአብርሃም ስለ ልጁ እስማኤል እጅግ ጭንቅ ሆነበት።

#እግዚአብሔርም አብርሃምን እንዲህ አለው የዚህ ልጅ የዚችም ባሪያ ነገር በፊትህ ጭንቅ አይሁንብህ የምትልህን ሁሉ ሣራን ስማት ከይስሐቅ ዘር ይተካልሃልና።

ይህም ነገር ታላቅ ምሥጢር አለው የተመሰገነ ጳውሎስ ቅድስት ሣራን የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ አድርጓታልና። ከዚህም በኋላ በበጎ እርጅና በአረፈች ጊዜ ከኬጢያዊ ኤሞር ልጆች በገዛው ቦታ ቀበራት።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱሳን_ሞይስስና_እህቱ_ሣራ

በዚህች ቀን የከበረ አባ ሞይስስና እኅቱ ሣራ በሰማዕትነት ሞቱ። የእሊህም ቅዱሳን ወላጆቻቸው ደጎች እጅግም ባለጸጎች ናቸው። የከበረ ሞይስስ ወላጆቹ ከአረፉ በኋላ እኅቱ ሣራን ሊአጋባትና ወላጆቹ የተዉትን ገንዘብም ሊሰጣት እርሱም ወደ ገዳም ሒዶ ሊመነኵስ አሰበ።

ይህን አሳቡንም በነገራት ጊዜ እንዲህ ብላ መለሰችለት እኔን ልታጋባኝ ከወደድክ አስቀድሞ አንተ አግባ አርሱም እንዲህ አላት እኔ ብዙ ኃጢአት ሠርቻለሁ ስለዚህ ኃጢአቴን ለመደምሰስ እመነኵስ ዘንድ እሻለሁ ማግባት አይቻለኝም የነፍሴን መዳኛ አስባለሁ እንጂ ።

ሁለተኛም እንዲህ ብላ መለሰችለት አንተ ነፍስህን ስታድን እኔን በዓለም ወጥመድ ውስጥ እንዴት ትጥለኛለህ። እርሱም እንዲህ አላት ምንኵስና ከፈለግሽ ስለ ራስሽ የምታውቂ አንቺ ነሽ እኔም የወደድሺውን አደርግልሻለሁ።

እንዲህም አለችው ለነፍስህ የምታደርገውን ለኔም እንዲሁ አድርግ እኛ ሁለታችን ከአንድ ባሕርይ ከአንድ አባት ከአንዲት እናት የተገኘን ነንና የልቧንም ቆራጥነት አይቶ ወዲያውኑ ከእርሷ ጋራ ተነሣ ገንዘባቸውንም ሁሉ ለድኆችና ለምስኪኖች በተኑ።

ከዚህም በኋላ እኅቱ ሣራን ወሰዳት ከእስክንድርያ ከተማ ውጭ ወዳለ የደናግል ገዳም ውስጥ አስገባት እርሱም ከወንዶች ገዳም ገብቶ በዚያ ተጋድሎን ተጋደለ። እንዲሁ እኅቱም ጽኑዕ በሆነ ገድል ተጠምዳ እየተጋደለች ሁለቱም ሳይገናኙ ዐሥር ዓመት ኖሩ።

በሊቀ ጳጳሳት አባ ድሜጥሮስ የሹመት ዘመን ሳዊርያኖስ የሚባል ከሀዲ ተነሥቶ የክርስቲያንን ወገኖች ማሠቃየት ጀመረ። ከመነኰሳት ገዳማትም ብዙዎች በሰማዕትነት ሞቱ። አባ ሞይስስም ተነሣ ሊሰናበታትም ወደ እኅቱ ሣራ ላከ በሰማዕትነት መሞት እንደሚሻም ነገራት።

ሣራ እኅቱም በሰማች ጊዜ ወዲያውኑ ተነሣች ሒዳ በሰማዕትነት ትሞት ዘንድ እንድታሰናብታት እመ ምኔቷን ለመነቻት እመ ምኔቷም ጸለየለችላት ሰላምታም ሰጥታ አሰናበተቻት እርሷም ደናግሉን ሁሉ ተሰናበተቻቸው።

ከዚህም በኋላ ወደ ወንድሟ ሔደች በጐዳናም አገኘችውና እርስ በርሳቸው ሰላም ተባባሉ ወደ እስክንድርያ ከተማም ገብተው በመኰንኑ ፊት ቁመው በክብር ባለቤት በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ታመኑ መኰንኑም ጽኑዕ ሥቃይን አሠቃያቸው ከዚህም በኋላ ራሳቸውን በሰይፍ አስቆረጠ። በመንግሥተ ሰማያትም የሰማዕትነት አክሊልን ተቀበሉ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#መነኰሳት_አጋቦስና_እህቱ_ቅድስት_ቴክላ

በዚህችም ቀን የከበሩ መነኰሳት አጋቦስና ቴክላ በሰማዕትነት ሞቱ። እሊህም ቅዱሳን በከሀዲው ሉልያኖስ ዘመን መከራ በመቀበል ተጋደሉ ። ከመኳንንቶቹም አንዱ ጽኑዕ ሥቃይን አሠቃያቸው ። ሥቃያቸውም በአሰለቸው ጊዜ ለአንበሶች ጣላቸውና ገድላቸውን ፈጽመው የሰማዕትነት አክሊልን ተቀበሉ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አቡነ_ኢየሱስ_ሞዐ

በዚህች ቀን አባታቻን አቡነ ኢየሱስ ሞዐ የተፀነሱበት ዕለት ነው፡፡ ቅዱሱ አባት ሀገራቸው ጎንደር ክፍለ ሀገር ስማዳ ወረዳ ሲና ዳኅና በሚባል ቦታ ነሐሴ 26 ቀን ተፀንሰው ግንቦት 26 ቀን 1210 ዓ.ም ከአባታቸው ዘክርስቶስና ከእናታቸው እግዚእ ክብራ ተወለዱ። የተወለዱትም በቅዱስ ነአኲቶ ለአብ ዘመነ መንግስት ነው፡፡ አቡነ ኢየሱስ ሞዐ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት የቆብ አባት ሲሆኑ ታላቁን ሐይቅ ቅዱስ እስጢፋኖስን ገዳም የቆረቆሩ ደገኛ አባት ናቸው፡፡

ዕድሜያቸው 30 ዓመት እስከሚደርስ ድረስ ከቤተሰቦቻቸው ትምህርተ ሃይማኖትንና ግብረ ገብን ሲማሩ ከቆዩ በኋላ በ1240 ዓ.ም ይህንን ዓለም በመተው ወደ ደብረ ዳሞ ገዳም ገቡ፡፡ በደብረ ዳሞ ገዳም መነኰሳቱን እየረዱ፣ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት እያጠኑ፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን እየገለበጡ ለሰባት ዓመታት ከቆዩ በኋላ የደብረ ዳሞ 3ኛ አበ ምኔት ከሆኑት ከአባ ዮሐኒ እጅ ምንኩስናን በ1247 ዓ.ም ተቀበሉ፡፡

አንድ ቀን ሌሊት መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ወደርሳቸው መጥቶ ‹‹የስምህ መክበርያ ወደሆነው ሐይቅ ወደ ተባለው ሥፍራ ሂድ›› አላቸው፡፡ አባታችንም ‹‹ቦታውን እንዴት ዐውቀዋለሁ?›› በማለት መልአኩን ቢጠይቁት ‹‹ተነሥ! ጉዞህን ጀምር ቦታውን እኔ አሳይሃለሁ›› አላቸው፡፡ አባ ኢየሱስ ሞዓ በመልአኩ እንደታዘዙት ከበዓታቸው ተነሥተው ተከተሉት፡፡ የብዙ ወራት መንገድ የሆነውን ጐዳናም በስድስት ሰዓት አደረሳቸው፡፡ በዚያን ወቅት ከሐይቅ ገዳም በስተ ሰሜን ወደነበረው ጴጥሮስ ወጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን ደረሱ፡፡ ወደ ሐይቅ እስጢፋኖስ ከመግባታቸው በፊት ለ6 ወራት ያህል በጴጥሮስ ወጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን አገልግለዋል፡፡ ያገለግሉበት በነበረው ቤተ ክርስቲያን ቀን ቀን ሕዝቡን ሲያስተምሩ በመዋል ሲመሽ ወደ ሐይቁ በመግባት ሲጸልዩ ያድሩ ነበር፡፡ በሐይቅ እስጢፋኖስና በዙርያው ለነበሩ አበውም ማታ ማታ አንድ ብርሃን ወደ ሐይቁ ሲገባ ጠዋት ጠዋትም ሲወጣ ይታያቸው ነበር፡፡ ከዚህም በኋላ አባታችን በገዳሙ አባቶች ልመናና በልዑል #እግዚአብሔር ትዕዛዝ ወደ ሐይቅ ገዳም ገብተው አበምኔት ሆኑ፡፡
ሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም ከደሴ 30 ኪሎ ሜትር ርቆ የሚገኝ ሲሆን የመሠረቱት ካልዕ ሰላማ የተባሉ ግብፃዊ ጻድቅ ናቸው፡፡ ሐይቅን አባ ሰላማ ካልዕና ዐጼ ድል ነአድ በ862 ዓ.ም ነው የቆረቆሩት። ገዳሙን ካቀኑት በኋላ ‹‹የማንን ታቦት እናስገባ?›› ብለው ሲያስቡ ቶራ የምትባል እንስሳ ጭነት ተጭና ከመካከላቸው ተገኘች፤ ጭነቱን አውርደው ቢያዩት በሐር ጨርቅ የተጠቀለለ የቅዱስ እስጢፋኖስንና የቅዱስ ጊዮርጊስን ሁለት ታቦት አገኙ፡፡ በላዩም ላይ ‹‹ይህንን ታቦት በኢየሩሳሌም የሚኖሩ የተሰወሩ ቅዱሳን ከ #እግዚአብሔር ታዘው የላኩት ነው›› የሚል ጽሑፍ አገኙ፡፡

ይህ ከሆነ ከ400 ዘመን በኋላ ነው አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ወደዚህ ቦታ የመጡት፡፡ አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ለ52 ዓመት ቀን ቀን መንፈሳዊ ሥራቸውን እየሠሩ ሌሊት ሌሊት ሐይቁ ውስጥ ቆመው ሲጸልዩ ያድራሉ፡፡ አባ ኢየሱስ ሞዐ በሐይቅ እስጢፋኖስ በአበ ምኔትነት በቆዩባቸው 45 ዓመታት ከየገዳማቱ ቅዱሳን መጻሕፍትን በመገልበጥና በማሰባሰብ የመጀመርያው ዘመናዊ የቤተ ክርስቲያን ቤተ መጻሕፍት በሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም እንዲቋቋም አድርገዋል፡፡ በዚሁ ገዳም ውስጥ የመጀመርያውን የቤተ ክርስቲያን ቋሚ ትምህርት ቤት በማቋቋም 800 መነኮሳትን በትምህርተ ሃይማኖት አሠልጥነው በንቡረ ዕድነት ማዕረግ ሾመው በመላ ሀገራችን እንዲሠማሩ አድርገዋቸዋል፡፡

ከእነዚህም ተማሪዎቻቸው መካከል አቡነ ተክለ ሃይማኖት (ደብረ ሊባኖስ)፣ አቡነ ኂሩተ አምላክ (ጣና ሐይቅ ዳጋ እስጢፋኖስ)፣ አቡነ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ (ቦረና)፣ አባ በጸሎተ ሚካኤል (ቦረና)፣ አቡነ ገብረ እንድርያስ (ቦረና)፣ አቡነ ሕዝቅያስ (ቦረና)፣ አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ (ዳውንት)፣ አቡነ አሮን (መቄት- ጣራው ክፍት የሆነው)፣ አቡነ ተክለ ኢየሱስ ሞዐ (ሐይቅ)፣ አቡነ አላኒቆስ (ትግራይ)፣ አቡነ በግዑ (ሐይቅ)፣ አቡነ ሠረቀ ብርሃን (ሐይቅ)፣ አቡነ ብስጣውሮስ (ሐይቅ)፣ አቡነ ዮሴፍ (ላስታ) ዋና ዋናዎቹና በጣም ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ጻደቁን ንጉሥ ዐፄ ይኩኖ አምላክንም በትምህርተ ሃይማኖት አንጸውና ኮትኩተው ያሳደጉት ጻድቁ አባታችን ናቸው፡፡ እነዚህም ልጆቻቸው እያንዳንዳቸው እጅግ አስገራሚ ገድል ያላቸው የከበሩ ቅዱሳን ናቸው፡፡

አቡነ ተክለ ሃይማኖት ወደ አቡነ ኢየሱስ ሞዐ መጥተው በሐይቁ ዳር ቆመው ሳለ ቅዱስ ሚካኤል መጥቶ በእግሩ በውኃው ላይ እየሄደ እያሳያቸው ተከትለውት እንዲሄዱ ነገራቸው። አባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖትም ሐይቁን በእግራቸው ተራምደው ተሻግረው አቡነ ኢየሱስ ሞዐን አገኟቸው፡፡ እርሳቸውም አቡነ ተክለ ሃይማኖት ወደ እርሳቸው እየመጡ እንደሆነ በመንፈስ ዐውቀው ነበርና ሲያገኟቸው በጣም ተደስተው ከተቀበሏቸው በኋላ አመነኩሰዋቸዋል፡፡ አቡነ ኢየሱስ ሞዐ እጅግ በጣም ብዙ መነኮሳትን አፍርተዋል፡፡ የመጀመሪያው መነኩሴ አባ እንጦንስ ነው፡፡ እንጦንስ መቃርስን፣ መቃርስ ጳጉሚስን፣ ጳጉሚስ ቴዎድሮስን፣ አቡነ አረጋዊንና 8ቱን ቅዱሳን አመነኮሱ፡፡ አቡነ አረጋዊም ወደ ኢትዮጵያ በ460 ዓ.ም መጥተው ክርስቶስ ቤዛን፣ አባ ክርስቶስ ቤዛም መስቀለ ሞዐን፣ መስቀለ ሞዐም አባ ዮሐኒን፣ አባ ዮሐኒም አባ ኢየሱስ ሞዐን፣ አባ ኢየሱም ሞዐም አቡነ ተክለ ሃይማኖትን አመነኮሱ፡፡ አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ምን ያህል ቀደምትና ባለ ታሪክ አባት እንደሆኑ ከዚህ መረዳት ይቻላል፡፡

በዮዲት ጉዲት እጅጉን ተጐድታ የነበረችው ሀገራችን ዳግም የወንጌሉ ብርሃን እንዲበራባት ሊቃውንት፣ እንዳይታጡባት፣ ቅዱሳት መጻሕፍት እንዳይቆነጻጸሉ፣ መነኮሳት አባቶች ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ ወርደው ገዳማትን እንዲያስፋፉ ያደረጉት አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ለቤተ ክርስቲያናችንና ለሀገራችን ትልቅ ባለውለታ ናቸው፡፡ በተለይም በሐይቅ እስጢፋኖስ ያፈሯቸውን 800 ሊቃውንት በመላዋ ኢትዮጵያ በመሰማራታቸው ዛሬ የምናያቸውን አብዛኛዎቹን ገዳማትና ቅዱሳት መጻሕፍት አቆይተውልናል፡፡ አባታችን ለ45 ዓመታት ሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳምን በአበ ምኔትነት እያስተዳደሩ ከቆዩ በኋላ ኅዳር 26 ቀን 1292 ዓ.ም በዕለተ እሑድ ዐርፈዋል፡፡ ባረፉበት ዕለትም በወቅቱ በቦታው የታየው ብርሃን ሀገሪቱን መልቶ ታይቷል፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አቡነ_ሀብተ_ማርያም

ዳግመኛም በዚህች ቀን ቅዱስ አባታችን አቡነ ሀብተ ማርያም ፅንሰታቸው ነው። አባታቸው ፍሬ ቡሩክ እናታቸው ዮስቴና የሚባሉ በሕገ እግዚአብሔር፣ በሃይማኖት፣ በትሩፋትና በምግባር ጸንተው የሚኖሩ ደጋግ ክርስቲያኖች ናቸው፡፡ ቅዱስ አባታችን ፅንሰታቸው ነሐሴ 26፣ ልደታቸው ግንቦት 26፣ ዕረፍታቸው ኅዳር 26 ነው፡፡ አቡነ ሀብተ ማርያምን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ‹‹አምስት መቅሰፍታት እንዲጠፉ በደጄ በደብረ ሊባኖስ ተቀበርልኝ›› ብለው የለመኗቸው ታላቅ አባት ናቸው፡፡

የአቡነ ሀብተ ማርያም እናት ቅድስት ዮስቴና ጻድቁ አቡነ ሀብተ ማርያምን ከመውለዷ በፊት ‹‹ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢገዛ ነፍሱን ካጣ ምን ይጠቅመዋል?›› የሚለውን የወንጌል ቃል አስባ መንና ወደ በረሃ የገባች ቢሆንም በበረሃ ውስጥ ከሰው ተለይቶ የሚኖር የበቃ ባሕታዊ በዋሻ ውስጥ አገኘችና ለምነና ወደ በረሃው እንደመጣች ነገረችው፡፡ ባሕታዊውም በጸሎት ወደ እግዚአብሔር ካመለከተ በኋላ ‹‹ምንኩስና ለአንቺ አልተፈቀደልሽም፣ ወደ ቤትሽ ግቢ፣ ከሕጋዊ ባልሽ ወንድ ልጅ ትወልጃለሽ እርሱም ለዓለም ሁሉ የሚጠቅም፣ ሰው ሁሉ የሚማፀነው፣ ገድሉ ትሩፋቱ በዓለም የሚነገርለት፣ በነፍስም በሥጋም የሚያማልድ፣ እንደ መልአክትም ክንፈ ጸጋ የሚሰጠው በምድር ሆኖ መንበረ ጸባኦትን የሚያይ ወንድ ልጅ ትወልጃለሽ›› በማለት ትንቢት ከነገራት በኋላ ቅድስት ዮስቴና ወደ ቤቷ ተመለሰች፡፡ እርሷም ሀብተ ትንቢት እስከመሰጠት ድረስ የደረሰች በሃይማኖት በምግባር በትሩፋት ያጌጠች ሆነች፡፡

ቅድስት ዮስቴናም ወደ ቤቷ ከተመለሰች በኋላ አቡነ ሀብተ ማርያም ተወለዱና ወላጆቻቸው ፈሪሃ እግዚአብሔርን እያስተማሩ አሳደጓቸው፡፡ ከዕለታት በአንድ ቀን ካህናቱ በቤተ ክርስቲያን ምህላ ሲያደርሱ ‹‹እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ›› እያሉ ሲጸልዩ ሰምተው በልቡናቸው ‹‹ይህች ጸሎት በጣም ጥሩ መልካም ጸሎት ናት፤ እኔ ይህችን ጸሎት መርጫታለሁ፤ በዚህ ጸሎት ዓለም ከአሳችነት ኅሊና በሚመጣውም ዓለም ከገሃነም እሳት እንድንድንባት አውቃለሁ›› አሉ፡፡ ይህችንም ጸሎት ማዘውተር ጀመሩ፡፡ እናትና አባታቸውም በተኙ ጊዜ ሌሊት ለጸሎት ተነሥተው በዚህ ጸሎት ፈጣሪአቸውን ያመሰግኑ ነበር፤ ስግደትን ይሰግዳሉ ነገር ግን እናትና አባታቸው ከእንቅልፋቸው በነቁ በጊዜ ሮጠው ወደ መኝታቸው ሄደው ይተኛሉ፡፡ የጽድቅ ሥራቸውንም ከአምላካቸው በቀር ማንም አያውቅባቸውም ነበር፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ አባታቸው ፍሬ ብሩክ የበግ ጠባቂ አደረጋቸው፡፡ እግዚአብሔር ግን በኋላ ለብዙዎች ስውራን ቅዱሳንና በዓለም ለሚኖሩ ምዕመናን በጎች ጠባቂ ያደርገው ዘንድ ወዶ መርጦታልና ያ ቀን እስኪደርስ ድረስ ፈጣሪያችን አቡነ ሀብተ ማርያምን ይጠብቃቸው ነበር፡፡
ከዕለታትም በአንደኛው ዕለት አባታቸን በጎችን ሲጠብቁ ሌሎች እረኞች በአመጻ ከሰው ሰርቀው ቆርጠው ያመጡትን እሸት ‹‹ና እንብላ›› አሏቸው፡፡ አባታችን ግን ‹‹ከየት እንዳመጣቸሁት ምንም ስለማላውቅ አልበላም›› አሏቸው፡፡ እረኞቹም ሀብተ ማርምን በቁጣ ዐይን እያዩአቸው ተቀምጠው ሲበሉ አባታችን ‹‹የማንችለው ዝናብ መጥቷልና ተነሡ በፍጥነት ወደቤታችን እንሂድ›› አሏቸው፡፡ እረኞቹም ‹‹ሰማዩ ብራ ነው ምንም ደመና የለውም፤ ነፋስም አይነፍስም፡፡ እኛ የማናየው አንተ ብቻ የምታየው ምን ነገር አለ?›› እያሉ በአባታችን ላይ ተዘባበቱባቸው፡፡ አባታችን ግን በጎቻቸውን እያስሮጡ በፍጥነት ወደ ቤታቸው ሄዱ፡፡ ወዲያውም በጣም ኃይለኛ ዝናብ ዘነበ፡፡ የጥፋት ውኃው በላያቸው እስኪፈጸምባቸው ድረስ እነዚያን እረኞች ከቦታቸው አልተነቃነቁም ነበርና በጥፋቱ ውኃ አለቁ፡፡ በዚያችም ሌሊት አቡነ ሀብተ ማርያን ከሰማይ ሦስት ጊዜ ‹‹ሀብተ ማርያም ሀብተ ማርያም›› የሚል ድምፅ ጠራቸው፡፡ አባታችንም እንደ ሳሙኤል ‹‹ጌታዬ ባሪያህ ይሰማሃል ተናገር›› ሲሉ ጌታችን አናገራቸው፡፡ ‹‹ከዚህ በኋላ ለሚሰሙህ ለመረጥኳቸው ቃሌን ትነግራቸው ዘንድ ከእኔም ጋር በምሥጢር በባለሟልነት ትነጋገር ዘንድ መርጨሃለሁ›› አላቸው፡፡

ከጥቂት ቀንም በኋላ አባታችን በጎችን እየጠበቁ ሳሉ አንድ አመጸኛ መጣና በትራቸውን በኃይል ነጥቆ ወሰደባቸው፡፡ አቡነ ሐብተ ማርያምም ‹‹በሕያው እግዚአብሔር አምልሃለሁ እቋቋምህ ዘንድ ኃይል የለኝምና በትሬን መልስልኝ›› ቢሉት የትዕቢትን ቃል ተናገራቸው፡፡ አባታችንም ‹‹እምቢ ካልክስ እሺ የእግዚአብሔርን ኃይል ታያለህ›› አሉት፡፡ ወዲያም ያ አመጸኛ ላዩ ታች፣ ታቹ ላይ፣ ግራው ቀኝ፣ ቀኙ ግራ ሆኖ በአየር ላይ ተሰቅሎ ዋለና እየጮኸ አባታችንን ለመናቸው፡፡ አባታችንም ‹‹የቀጣህ እግዚአብሔር ይቅር ይበልህ›› ባሉት ጊዜ ከተሰቀለበት ወርዶ በእግሩ ቆመ፡፡ በዚያ የነበሩና ይህንን ተአምር ያዩ እረኞችም እጅግ ፈርተው ሄደው ለወላጆቻቸው ያዩትን ተናገሩ፡፡ የሀገሩ ሰዎችም ‹‹ቀድሞ እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ እያለ ሲጸልይ ሲሰግድ አይተነዋል አሁንም ጠላቱን በነፋስ የሚቀጣ ይህ ልጅ ወደፊት ምን ይሆን!›› እያሉ አደቁ፡፡ ወላጆቻቸውም ይህን በሰሙ ጊዜ በግ ጠባቂነቱን አስተዋቸውና ወስደው ለመምህር ሰጧቸው፡፡ አቡነ ሀብተ ማርያምም የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ሁሉ በሚገባ ተማሩ፡፡

ከዚህም በኋላ አባታቸው ከሀገሪቱ ታላላቅ ሰዎች አንዷን እጮኛ አጨላቸው፡፡ ነገር ግን አቡነ ሀብተ ማርያም ‹‹አባቴ ሆይ እኔ ራሴን ለክርስቶስ በድንግልና ለመኖር አጭቻለሁ፣ ተራክቦዬም ቃለ ወንጌልን መስማት እንጂ ሌላ አይደለምና ለምን እንዲህ ትለኛለህ?›› አሉት፡፡ አባታቸውም ይህን ሲሰማ ተቆጥቶ ያለ አቡነ ሀብተ ማርያም ፈቃድ ሙሽራይቱን ለማምጣት ሄደ፡፡ አባታችን ግን ሀገር ጥለው ለመሰደድ ከቤት ተደብቀው ወጡ፡፡ መንፈስ ቅዱስም በመብረቅ አምሳል አባታቸውን ገስጻቸውና በዚህ ድንጋጤ ምክንያት ከዚህ ኃላፊ ዓለም ዐረፈ፡፡

አባታችንም የአባታቸውን ዕረፍት ሳያዩ አፋር ወደምትባል ሀገር ሄደው አባ ሳሙኤል ከሚባል ደግ መነኩሴ ቦታ ገብተው መነኩሴውን እያገለገሉት ኖሩ፡፡ አንድ ቀን አባታችን እንስራ ተሸክመው ውኃ ይቀዱ ዘንድ ወደ ወንዝ ወረዱና ውኃውን ቀድተው ሲመለሱ ድንጋይ አደናቀፋቸውና እንስራው ከላያቸው ላይ ወደቀ፡፡ ነገር ግን መሬት ከመድረሱ በፊት አባታችን ፈጥነው የጌታችን ስም በጠሩ ጊዜ እንስራው ወድቆ ሳይሰበር ተመልሶ በትከሻቸው ላይ ተቀመጠ፡፡ አባ ሳሙኤልም ይከተሏቸው ነበርና ይህን ጽኑ ተዓምር አይተው እጅግ አደነቁ፡፡

እንዲሁ ከዕለታት በአንድ ቀን በሌሊት መብራት ለአባ ሳሙኤል እያበሩ ሳለ መብራቱ ከእጃቸው ላይ ወድቆ ጠፋ፡፡ መምህሩም አባ ሳሙኤል ቁጡ ነበረና ስለ መምህራቸው ቁጣ በጣም ደንግጠው ወድቆ የጠፋውነ መብራት ፈጥነው ባነሱት ጊዜ መብራቱ በእግዚአብሔር ተዓምር ራሱ በርቶ ታየ፡፡ አባ ሳሙኤልም ይህን ተዓምራት አይቶ እጹብ እጹብ በማለት ‹‹የዚህ ቅዱስ ልጅ መጨረሻ ምን ይሆን?›› ብሎ ካደነቀ በኋላ ‹‹የዓለም ሁሉ የጥበብ መብራት ይሆናል›› ሲል ትንቢት ተናገረላቸው፡፡ እመቤታችን ለአባ ሳሙኤል ተገልጣላቸው የአቡነ ሀብተ ማርያምን ክብር ነግራዋለች፡፡ አባታችንም አባ ሳሙኤልን 12 ዓመት ከትሕትና ጋር እየታዘዙ ቤተ ክርስቲያንን እያገለገሉ ኖረው ከዚህ በኋላ በእግዚአብሔር ፈቃድ ወጥተው ሄደው እለ አድባር በተባለ ገዳም መኖር ጀመሩ፡፡ ከቦታውም ደርሰው ጥቂት ከቆዩ በኋላ እግዚአብሔር ከመረጣቸው ከአባ መልኬጼዴቅ እጅ የምንኩስናን ስርዓት ተቀበሉ፡፡ ይኸውም የሚዳው አቡነ መልኬጼዴቅ በደጃቸው የተቀበረውን ሰው አፈር የማያስበሉት ጻዲቅ ናቸው፡፡ ይህንንም የጻድቃኑን አባትና ልጅነታቸውን መሠረት በማድረግ የይሰበይ አቡነ ሀብተ ማርያም ገዳም ካህናት፣ መሪጌቶችና ዲያቆናት ግንቦት 4 ቀን ወደ ሚዳ መራቤቴ በመሄድ የአቡነ መልኬጼዴቅን በዓል እጅግ በደማቅ ሁኔታ ያከብራሉ፡፡

አቡነ ሀብተ ማርያምም ምንኩስናን ከተቀበሉ በኋላ ገድላቸውንና ትሩፋታቸውን በማብዛት በሳምንት አንድ ጊዜ ቅጠልን ብቻ የሚመገቡ ሆኑ፡፡ አርባ አርባ ቀን ሰማንያ ሰማንያ ቀንም የሚጾሙበት ጊዜ ነበር፡፡ በሌሊትም ወደ ጥልቅ ባሕር እየገቡ መዝሙረ ዳዊት፣ አራቱን ወንጌላትና ሌሎች የጸሎት መጽሐፍትን ይደግሙ ነበር፡፡ ፊታቸውም እንደ ንጋት ምሥራቅ ኮከብ ያበራ ጀመር፡፡

ከዚህም በኋላ ወደ ምሥራቅ ሄደው ጎሐርብ ወደምትባል ሀገር ደረሱ፡፡ በዚያም በዓት አጽንተው ሲጸልዩ ጌታችን ቅዱስ ገብርኤልንና ቅዱስ ሚካኤልን በቀኝና በግራ አስከትሎ ተገለጠላቸውና ‹‹ወዳጄ ሀብተ ማርያም ሆይ ሰላም ላንተ ይሁን›› አላቸው፡፡ ያን ጊዜ አባታችን ከፈጣሪአቸው ግርማ የተነሳ ደንግጠው ከመሬት ወድቀው እንደ በድን ሆኑ፡፡ ጌታችንም አንስቶ ክቡራን በሆኑ እጆቹ አጸናቸውና ‹‹የመጣሁት ለጸናህ ነው ሰውነትህንም እንደ ንስር ላድሳት ነው እንጂ ላጠፋህ አይደለም፡፡ ድካምህና ገድልህ ሁሉ ለዘለዓለም መታሰቢያ ሊሆን በኢየሩሳሌም ሰማያዊት ተጽፎልሃል ብዬ በእውነት እነግርሃለሁ፡፡ ለአንተ ለወደድኩህና ለመረጥኩህና ወዳጄ የማቴዎስንና የማርቆስን ወንጌል ባነበብክ ጊዜ ተጭነህ ወደምትሄድበት ቦታ የሚያደርስህ የብርሃን ሰረገላ ሰጥቼሃለሁ፡፡ እንደ አንተም ካሉ በዋሻ በመሬት ፍርኩታ ከሚኖሩ ከመረጥኳቸው ቅዱሳን ጋር ትገናኝ ዘንድ ወደ አራቱም አቅጣጫ ትበር ዘንድ የብርሃን ሠረገላ ሰጥቼሃልሁ፡፡ ዳግመኛም የሉቃስንና የዮሐንስን ወንጌል ባነበብክ ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም ትሄድ ዘንድ የእሳት ሠረገላ ሰጥቼሃለሁ›› አላቸው፡፡ ዳግመኛም ‹‹በጸሎትህ አምኖ በጎ ሥራ ለሚሠራ ሁሉ፣ ስምህን የጠራውን ዝክርህን ያዘከረውን ሁሉ የሀብተ ማርያም አምላክ ሆይ ከጠላት እጅ አድነኝ ያለኝን በኅሊና ያሰበውን በልቡናው የወሰነውን እፈጽምለታለሁ፡፡ አንተን ገድልህንና ቃል ኪዳንህን የናቀውን ያቃለለውን ሁሉ ፍጹም መበቀልን እበቀለዋለሁ፡፡ እንደ ወዳጄ እንደ ፊቅጦርም በእናቴ በማርያም ድንግል አተምኩህ›› ካላቸው በኋላ ቅዱስ ሚካኤል ከእርሳቸው እንዳይለይ የዘወትር ጠባቂ አድርጎ ሰጣቸውና በታላቅ ግርማ ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡
አባታችንም ከጌታችን ይህን ቃል ኪዳን ከተቀበሉ በኋላ ነፍሳቸውን ‹‹ነፍሴ ሆይ ከፈጣሪሽ ከእግዚአብሔር ጋር ፊት ለፊት አፍ ለአፍ ትነጋገሪ ዘንድ ደፍረሻልና በጎም ሥራ ሳይኖርሽ ከፈጣሪሽ ቃልኪዳን ተቀብለሻልና ከዛሬ ጀምሮ እንደ መላእክት ዘወትር አትተኝ›› እያሉ ተጋድሏቸውን አብዝተው ቀጠሉ፡፡ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤልም አባታችንን እንደ ጓደኛ ሆኖ ዘወትር ይጎበኛቸው ነበር፡፡ ቅዱሳን አባታቸንን ሊጎበኟቸው መጥተው ከደጅ ቆመው እንደሆነ ቅዱስ ሚካኤል አባታችንን ‹‹እከሌ ጉዳዩ እንዲህ ነው እንዲህ ብለህ ተናገረው…›› እያለ ያማክራቸው ነበር፡፡ እሳቸውም ቅዱስ ሚካኤል ካዘዛቸው በቀር ምንም አይሠሩም ነበር፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍትንም ባነበቡ ጊዜ ኃይለ ቃሉን እየተረጎመ ምሥጢራትን ይነግራቸዋል፤ የተሰወረውንም ይገልጥላቸዋል፡፡ ከእንስሳት ጩኸት ጀምሮ ከዱር አራዊት ድምፅና እስከ አእዋፍ ቋንቋ ያለውን ያስረዳቸው ነበር፡፡

ይኸውም መልአክ አንድ ቀን አቡነ ሀብተ ማርያምን ወደ ቤተ ክርስቲያን አስገብቷቸው ሥጋ ወደሙን ለመቀበል ተዘጋጅተው ሳለ ወንጌል የሚነበብበት ሰዓት ሲደርስ ያልተማረ ቄስ የክርስቶስ ጌትነቱን የምትናገር ወንጌልን ሲያነብ ‹‹ወዮሴፍ ብእሲሃ ለማርያም ጻድቅ ውእቱ›› የሚል ከቄሱ አፍ ይህን ንባብ አባታችን ሲሰሙ እጅግ ደንግጠው ወንጌል ወደሚነበብበት ስፍራ ሄደው የሚያነበውን ቄስ ገሠጹት፡፡ ‹‹ወዮሴፍሰ ፈሃሪሃ ለማርያም ጻድቅ ውእቱ በል እንጂ ብእሲሃ አትበል›› ብለው መከሩት፡፡ ቄሱም አቡነ ሀብተ ማርያም እንዳዘዙት ከስህተቱ ወደ ቀና ንባቡ ተመለሰ፡፡ ይህን ጊዜ ጌታችን ለአባታችን ድጋሚ ተገልጦላቸው ‹‹ሀብተ ማርያም ሆይ ይህን ትምህርትህን ወድጄ አመሰገንኩህ፣ የእናቴን የድንግል ማርያምን የድንግልናዋን ንጽሕና ስለ አከበርክ እኔም በመንግስተ ሰማያት ፈጽሜ አከብርሃለሁ›› አላቸው፡፡ ዳግመኛም ጌታችን ‹‹አሁንም ዮሴፍ ብእሲሃ ለማርያም የሚሉትን ሁሉ ለያቸው እንጂ አትተዋቸው፤ እንዲህ የሚል ጽሑፍም ብታገኝ እንዳይኖር እርሱን ፍቀህ ፈሃሪሃ ለማርያም የሚለውን ጻፍ›› ብሎ አባታችንን ካዘዛቸው በኋላ ሰላምታ ሰጥቷቸው ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡ አባታችንም በዚህ ጊዜ ፊታቸው ላይ ብርሃን ስለተሳለባቸውና እንደ ፀሐይ ስላበራ ሰዎችም አይተው ባደነቁ ጊዜ ወደ በዓታቸው ገቡና ጌታችንን ‹‹አቤቱ ጌታዬ ሆይ በሰው ፊት ክብሬን አትግለጥብኝ ሰውርልኝ፣ በቸርነትህም አድነኝ›› ብለው ጸለዩ፡፡ እንዲህም ብለው በጸለዩ ጊዜ ፊታቸው መልኩ ተለውጦ እንደ ቀድሞው ሆነ፡፡

ከዕለታትም በአንደኛው ቀን አባታችን ታመው ተኝተው ሳለ ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ጳውሎስ መጥተው ሥጋ ወደሙን አቀብለዋቸዋል፡፡፡ አባታችን በጸሎት ላይ ሳሉ ቅዱስ ሚካኤል ነጥቆ ወደ ሰማይ ወስዶ ቅዱሳን የሚኖሩባቸውን ዓለማት፣ መንግስተ ሰማያትን እንዲሁም ኃጥአን የሚኖሩበትን ሲኦልን አሳያቸው፡፡ በገነት ያሉትንም ከአዳም ጀምሮ እሳቸው እስካሉበት ጊዜ እስከ አቡነ መርሐ ክርስቶስ ድረስ ያሉትን ቅዱሳን አሳያቸው፡፡ ከዚህም በኋላ በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት ቆመው ሳለ ሰይጣንም መጥቶ በእግዚአብሔር ፊት ቆመና ‹‹አቤቱ ጌታዬ ሆይ በሀብተ ማርያም ላይ እንደ ኢዮብ ብዙ መከራ አጸናበት ዘንድ ፍቀድልኝ›› ብሎ እየጮኾ ሲናገር አባታችን እጅግ ፈርተው አለቀሱ፡፡ እግዚአብሔር ግን በሰይጣን ላይ ተቆጥቶ ‹‹በነፍሱም በሥጋውም መከራ ታጸናበት ዘንድ አልፈቅድም›› አለው፡፡ ‹‹እኔ ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ መርጨዋለሁና በንጽሕናና በቅድስና ኃጢአት እንዳይሠራ ዘወትር እጠብቀዋለሁ፤ በእርሱ ላይ ማሰልጠንስ ይቅርና በሀብተ ማርያም ጸሎት በተማጸነኝ ሁሉ ላይ እንኳን አላሠለጥንህም›› አለው፡፡ ሰይጣንም ይህን ቃል ሰምቶ አፍሮ እያዘነ ሄደ፡፡

አቡነ ተክለ ሃይማኖትም ከእርሳቸው በኋላ በመንበራቸው ከተሾሙት ከስምንቱ መምህራን ጋር ለሀብተማርያም ተገለጡላቸው፡፡ እነርሱም ኤልሳዕ፣ ፊሊጶስ፣ ሕዝቅያስ፣ ቴዎድሮስ፣ ዮሐንስ፣ ዮሐንስ ከማ፣ እንድርያስና መርሐ ክርስቶስ ናቸው፡፡ እነዚህም መልካቸው እንደ ፀሐይ ያበራ ልብሳቸው እንደ መብረቅ ያንጸባርቅ ነበር፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖትም ልብሳቸው የእሳት ላንቃ የከበበው መልኩም ነጭ የሆነ የሚያስደንቅ ሆኖ ‹‹በቅድምና ለነበረ ለአብ በቅድምና ለነበረ ለወልድ በቅድምና ለነበረ ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይገባል›› እያለ ልብሳቸው በሰው አንደበት ያመሰግን ነበር፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖትም አቡነ ሀብተ ማርያምን ‹‹ልጄ ሀብተ ማርያም ሆይ! ፈጣሪዬ እግዚአብሔር ስለወደደህ ብዙ ምርኮ እንዳገኘህ በአንተ ፈጽሞ ደስ ይለኛል፡፡ ነገር ግን የምለምንህ ነገር አለና እሺ በለኝ›› አሏቸው፡፡

አቡነ ሀብተ ማርያምም ‹‹ጌታዬ ነገሩ ምንድን ነው?›› ሲሏቸው አቡነ ተክለሃይማኖት ‹‹ከተቀበርኩበት ቦታ እንድትቀበር ቃል ኪዳን ግባልኝ›› አሏቸው፡፡ አቡነ ሀብተማርያምም ‹‹አባቴ ሆይ ይህንን አደርግ ዘንድ ስለምን ትወዳለህ?›› አሏቸው፡፡ አቡነ ተክለሃይማኖትም በሀገሬ ላይ የታዘዙ አምስት መቅሰፍቶች አሉና ስለዚህ ነው እነዚህም አንዱ መብረቅ ነው፤ ሁለተኛውም ቸነፈር ነው፤ ሦስተኛውም ረሃብ ነው፤ አራተኛውም ወረርሽኝ ነው፤ አምስተኛውም የእሳት ቃጠሎ ነው፡፡ የአንተ አጽም በውስጡ የተቀበረ እንደሆነ አጥንቴ የተቀበረባት ሀገሬ ከነዚህ መቅሰፍታት ትድናለች›› አሏቸው፡፡

አቡነ ሀብተ ማርያምም ‹‹ንዑድ ክቡድ የምትሆን አባቴ ሆይ ልዩ ክቡር በሚሆን በአንተ አጽም መቀበር ያልዳነች በእኔ አጽም መቀበር ድኅነት ታገኛለችን? ይህንስ ተወው›› ብለው በተከራከሯቸው ጊዜ አቡነ ተክለ ሃይማኖትም መልሰው ‹‹ልጄ ሀብተ ማርያም ሆይ አንተ የማታውቀው ከፈጣሪያችን ከእግዚአብሔር የተሰጠህ እኔ የማውቀው ክብር አለህና ስለዚህ ነው፡፡ ይልቁንስ እንዳልኩህ በተቀበርኩበት ቦታ እንድትቀበርልኝ ቃልኪዳን ግባልኝ›› ብለው ማለዷቸው፡፡ ይህንንም ሲባባሉ እንዲህ የሚል ቃል መጣላቸው፡- ‹‹ከወዳጄ ከሀብተ ማርያም አንደበት ይህ ቃልኪዳን አይወጣም፣ ዳግመኛም ወዳጄ ተክለ ሃይማኖት ሆይ! እርሱ በወደደው የሚቀበር አይደለምና እኔ ከተቀበርኩበት እንድትቀበር ብለህ የምታስገድደው ለምንድን ነው? እኔ በወደድሁት ቦታ ይቀበራል እንጂ›› የሚል ቃል ተነገረ፡፡ አቡነ ተክለሃይማኖትም እየለመኑናና እየሰገዱ ከሥላሴ ዙፋን ፊት ተንበረከኩ፡፡ ሦስተኛውም ‹‹ይሁን እንዳልከው ይቀበርልህ›› የሚል ቃል ተሰማ፡፡ ዳግመኛም ‹‹በአንተም አጽም በሀብተ ማርያምም አጽም ቦታህ ከመቅሰፍታት ትዳንልህ፤ ልጆችህ ግን በቸነፈር ደዌ ቢሞቱ ከሰማዕትነት ተቆጥሮላቸው ወደ መንግሥተ ሰማያት እንዲገቡ በራሴ ምዬ ቃልኪዳን ገብቼልሃለሁ›› አላቸው፡፡ በዚህም ጊዜ አቡነ ተክለሃይማኖት እጅግ ደስ ተሰኝተው ሦስት ጊዜ ሰገዱ፡፡

ከዚህም በኋላ መልአኩ ለአቡነ ሀብተ ማርያም ክብሯ እንደ ጽርሐ አርያም የሆነች አገርን አሳያቸው፡፡ ሥፍር ቁጥር የሌላቸውም ቅዱሳን መላእክት በውስጧ ተድላ ደስታ ያደርጉባት ነበር፡፡ አባታችንም መልአኩን ‹‹ይህች ክብሯ ፍጹም የሆነችን አገር ማን ትባላለች በውስጧ ለመኖር በእጅጉ ወድጃለሁና›› ብለው ሲጠይቁት መልአኩም ‹‹ይህችማ አገር የአባትህ የተክለ ሃይማኖት አጽም ያረፈባት ደብረ ሊባኖስ ናት፤ ከእርሱም ጋር በክብር እስክትነሣ ድረስ በውስጧ ትቀበርባት ዘንድ ለአንተም ተሰጥታሃለችና ደስ ይበልህ፡፡ አባትህም እንደ ኢየሩሳሌም እንደትሆንለት ቃልኪዳን ተቀብሎባታል›› አላቸው፡፡
በአንደኛውም ቀን አቡነ ሀብተ ማርያም ከሌሎች ቅዱሳን ጋር ሆነው ሲሄዱ ብዙ አጋንንት እየተደነባበሩ ወደ ታች ሲወርዱ ተመለከቱና አባታችን ሥራቸውን ለማየት ተከተሏቸው፡፡ አንዱንም ኃጥእ ይዘው ነፍሱን ከሥጋው ለዩዋትና ወደ ሲኦል አወረዷት፡፡ አባታችንም ከሌሎቹ ቅዱሳን ጋር ሆነው ያችን ነፍስ ይምርላቸው ዘንድ ጌታችንን በጸሎት ማለዱት፡፡ ነገር ግን ‹‹ለጣዖት ስትሰግድ ስለኖረች ይህችን ነፍስ አልምራትምና አትድከሙ›› የሚል ቃል ከልዑል እግዚአብሔር ዘንድ መጣላቸው፡፡ ቅዱሳኑም ‹‹ልመናችንን የማትቀበል ከሆነ በከንቱ ሰብስበኸናል›› ብለው ቢያዝኑ እግዚአብሔርም ‹‹ሕገ እግዚአብሔርን የዘነጉ ሰዎችን ቅጣት እንድታዩ ነው›› አላቸው፡፡ እነርሱም ሕገ እግዚአብሔርን የዘነጉ ሰዎችን ሲቀጣቸው ለደጋጎቹ ሰዎች ደግሞ መልካሙን ዋጋቸውን ሲሰጣቸው አይተው አንድ ሆነው አመስግነውታል፡፡

ከዚህም በኋላ መልአኩ ቅዱስ ራጉኤል አንዱን ሰው በመብረቅ ቀሰፈውና ቅዱስ ሚካኤል ሄዶ ቅዱስ ራጉኤልን ሲከራከረው አባታችን ተመለከቱ፡፡ ቅዱስ ሚካኤል ‹‹የእኔ አገልጋይ ነውና ለምን ገደልከው?›› ሲለው ቅዱስ ራጉኤልም ‹‹ሰንበት ሳይለይ ዝሙትን መሥራት የለመደ ሥራውም ዝሙት ስለሆነ በፈጣሪዬ ታዝዤ ነው የገደልኩት፡፡ ኃጥአንን ሊያጠፋ እንጂ ጻድቃንን ለመቅጣት መብረቅ እንዳይታዘዝ አንተስ ታውቅ የለም እንዴ?›› አለው፡፡ ይህንንም ተባብለው ከሥላሴ ፊት ሰግደው ቅዱስ ሚካኤል የተገባለትን ቃልኪዳን በማሳሰብ ምልጃውን አቀረበ፡፡ እግዚአብሔርም በጎና ክፉ ሥራዋን ባስመዘነ ጊዜ በጎ ሥራዋ ስለበለጠ ቅዱስ ሚካኤል ያችን ነፍስ ታቅፎ ወስዶ ለቅዱስ ገብርኤል ሰጠው፡፡ ሰባቱም ሊቃነ መላእክት እየተቀባበሉ ወስደው ከመስቀል ዘንድ አደረሷት፡፡ ለቅዱስ መስቀልም ካሰገዷት በኋላ አሳልመዋት በቅዱስ ሚኤካል አማላጅነት ወደ ገነት አስገቧት፡፡ አቡነ ሀብተ ማርያምም ይህን በተመለከቱ ጊዜ ቅዱስ ሚካኤልን ‹‹መስቀል ታሳልሟት ዘንድ ያችን ነፍስ ወደ መስቀል ለምን ወሰዳችኋት?›› ብለው ጠየቁት፡፡ መልአኩም ‹‹በትልቅም በትንሽም ነገር ክርስቲያናዊትን ነፍስ የሚቃወም ቢመጣባት ድል የምትነሳበትን በመስቀል ፍርድ ይታይላታልና ስለዚህ ነው፡፡ የሚከራከራት ቢኖር ግን እንዳየኸው ወደ መስቀል ባደረሷት ጊዜ የሚቃወማት ሰይጣን ፈጥኖ ይርቅላታል ዳግመኛም ሊከራከራት አይችልም›› አላቸው፡፡

ከአቡነ ሀብተማርያም በረከት ለመቀበል ብዙ ቅዱሳን ከሮም፣ ከግብፅ፣ ከአስቄጥስና ከሲሐት ገዳም ወደ አባታችን ዘንድ ይመጡ ነበር፤ ከየሀገራቸውም በአንበሳ ተቀምጠው የሚመጡ አሉ፤ ክንፍ ተሰጥቷቸው እንደ ንስር የሚበሩም አሉ፤ ብፁዕ አቡነ ሀብተ ማርያምም የቅዱሳኑን ብቃት አይተው ‹‹ሥራችሁ እንዲህ እንዲህ ሲሆን ለምን ወደኔ መጣችሁ?›› ብለው ሲጠይቋቸው ቅዱሳኑም ‹‹በማንኛውም ሥራ እግዚአብሔርን በለመነው ጊዜ በኢትዮጵያ የሚኖር እንደ ሙሴ ያለ ሀብተ ማርያም የሚባል ወዳጄ አለና ሁሉን ስለሚነግራችሁ ዘወትር እርሱን ጠይቁ ብሎ ስላዘዘን ወደ አንተ መጣን›› አሏቸው፡፡ አባታችንም ቅዱሳኑን ከባረኳቸውና ከእነርሱም ከተባረኩ በኋላ አባታችን ለቅዱሳኑ የሚመጣውን እንዳለፈ የሚደረገውንም እንደተደረገ አድርገው ይነግሯቸዋል፡፡ ቅዱሳኑም ከልጅነታቸው ጀምረው እስከዚያች ቀን ድረስ የሠሩትን ሥራ ሁሉ ይነግሯቸዋል፡፡ እነርሱም እጃቸውን እየሳሙ በረከታቸውን ይቀበሉ ነበር፡፡ እንደዚሁም አቡነ ሀብተ ማርያም ቅዱስ ሚካኤልና ቅዱስ ገብርኤል እየተራዱዋቸው ቀድሰው በሚያቆርቡ ጊዜ ተሰውረው የሚኖሩ 500 ስውራን ቅዱሳን መጥተው ሥጋ ወደሙን ከአባታችን እጅ ተቀበሉ፡፡ ቀድሰውም ወደበዓታቸው እንደገቡ እመቤታችን ተገልጣላቸው ‹‹በነገውም ዕለት ቅዳሴዬን ቀድስ፣ ይህም ቅዳሴ መዓዛ ቅዳሴ ነውና፡፡ የዓለም መሠረት ማርያም ወደኔ ነይ ብለህ በጠራኸኝ ጊዜ ነቢያትን ሐዋርያትን አስከትዬ መጥቼ እባርክሃለሁ›› አለቻቸው፡፡ አባታችንም ‹‹በነገው ዕለት ሌላ ተረኛ ቄስ ይቀድሳልና ይህ እንዴት ይሆንልኛል?›› አሏት፡፡ እመቤታችንም ‹‹ፈቃዴ ስለሆነ አንተ እንድትቀድስ አደርጋለሁ›› አለቻቸው፡፡ በነጋታው ተረኛው ቄስ ከእንቅልፉ በነቃ ጊዜ ቸኩሎ እየተፋጠነ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲገሰግስ ወድቆ ጥርሱ ደማና ስለ ሥጋ ወደሙ ቅዳሴ እጅግ ደንግጦ ወደ አባታችን መጥቶ ‹‹ቅዳሴው በእኔ ስም ከሚታጎል አንተ ቀድስልኝ›› አላቸው፡፡ አባታችንም አስቀድማ እመቤታችን የነገረቻቸውን ነገር አስበው እያደነቁ ሄደው ቀደሱ፡፡ እመቤታችንም ነቢያትን ሐዋርያትን አስከትላ መጥታ ባረከቻቸው፡፡

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን ።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ነሐሴ_26 እና #ከገድላት_አንደበት)
#ነሐሴ_27

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ነሐሴ ሃያ ሰባት በዚህችም ቀን #የመላእክት_አለቃ_ሱርያል የበዓሉ መታሰቢያ ነው፣ #የቅዱስ_ብንያሚንና_እኅቱ_አውዶክስያ በሰማዕትነት ሞቱ፣ በሊቀ ካህናት ኤሊ ዘመን #ነቢይ_ሳሙኤል ለመጠራቱ መታሰቢያ ሆነ፣ታላቁ ሰማዕት #ቅዱስ_ፊቅጦርና_እናቱ_ቅድስት_ሣራ መታሰቢያቸው ነው፣ አባቶቻችን #12ቱ_የያዕቆብን_ልጆች ያስቧቸዋል፣ ታላቁ ጻድቅ ተአምረኛው #አቡነ_ዘርዐ_ቡሩክ ልደታቸው ነው፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ሱርያል_ሊቀ_መላእክት

ነሐሴ ሃያ ሰባት በዚህችም ቀን ከሰባቱ ሊቃነ መላእክት አራተኛ የሆነ የመላእክት አለቃ የሱርያል የበዓሉ መታሰቢያ ነው።

ከታላላቅ ሊቃናት አንዱ የሆነው ቅዱስ ሱርያል ክብሩ ብዙ ቢሆንም ብዙ ምዕመናን አያውቁትም። የመላእክት መዓርግ ሲነገር ሚካኤል፣ ገብርኤል፣ ሩፋኤል ብሎ ቀጥሎ የሚመጣው ሱርያል ነው።

በ3ቱ ሰማያት ካሉት 9ኙ ዓለመ መላእክት የአንዱ (የሥልጣናት) መሪ (አለቃ) ነው። መልአኩ እጅግ ርሕሩሕ እና ተራዳኢ ነውና አንዘንጋው። ለኖኅ መርከብርን ያሳራው ከጥፋት ውሃም ያዳነው ይህ ቅዱስ መልአክ ነው።

በገድለ ሰማዕታትም ላይ እንደተጠቀሰው የሰማዕታት ረዳትና አዳኝም ነው። ቅዱስ ሱርያል በሌላ ስሙ "እሥራልዩ" ይባላል። "የእሥራኤል ረዳት" እንደ ማለት::

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን አማላጅነቱም ከእኛ ጋር ይኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ብንያሚንና_እህቱ_አውዶከስያ

በዚህች ቀን ሰብሲር ከሚባል አገር ብንያሚንና እኅቱ አውዶክስያ በሰማዕትነት ሞቱ።

የእነዚህም ቅዱሳን ወላጆቻቸው እንግዳና መጻተኛን የሚወዱ ደጎች ክርስቲያኖች ናቸው ደግሞ ለክርስቲያኖች በሚገባ በበጎ ሥራ ሁሉ የተጠመዱ ቅድስና ያላቸው ናቸው። እሊህንም ቅዱሳን በወለዱዋቸውና በአሳደጓቸው ጊዜ ክርስቲያናዊት ትምህርትን አስተማሩአቸው።

ከዚህም በኋላ ወደዚያች አገር ከሀዲ መኰንን መጣ ቅዱስ ብንያሚንም በሰማ ጊዜ የክብር ባለቤት ስለሆነ #ክርስቶስ ደሙን ያፈስ ዘንድ ወደደ። በመኰንኑም ፊት ቁሞ በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ታመነ ጽኑ የሆነ ሥቃይንም አሠቃይቶ ከዚያ በኋላ አሠረው።

ወላጆቹና እኅቱ በሰሙ ጊዜ ወደርሱ መጡ አለቀሱ እጅግም አዘኑ እርሱም የዚህ ዓለም ኑሮ እንደ ጥላ ፈጥኖ ያልፋል የወዲያኛው ኑሮ ግን ፍጻሜ የለውም እያለ ያጽናናቸው ጀመረ።

እኅቱ አውዶክስያም ይህን መልካም ትምህርቱን ከወንድሟ ሰምታ ወንድሜ ሆይ ካንተ እንዳልለይ #እግዚአብሔር ሕያው ነው አንተ የምትሞተውንም ሞት እኔም ከአንተ ጋራ እሞታለሁ አለችው።

ይህንንም ብላ ወደ መኰንኑ ሒዳ በክብር ባለቤት #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ በመኰንኑ ፊት ታመነች መኰንኑም ያሠቃያት ጀመረ። ከዚህ በኋላም ያለ መብልና ያለ መጠጥ በጨለማ ቤት ሃያ ቀን ከወንድሟ ጋር አሥረው እንዲያኖሩዋት አዘዘ።

ከዚህም በኋላ ከዚያ አውጥቶ ከባድ የሆኑ ደንጊያዎችን በአንገታቸው አንጠልጥሎ ከጥልቅ ባሕር ጣላቸው የ #እግዚአብሔር መልአክም ወርዶ ከአንገታቸው ደንጊያዎቹን ፈታላቸው እነርሱም ከወደብ እስቲደርሱ በባሕሩ ላይ ዋኝተው ብጥራ ከምትባል ቦታ ደረሱ አንዲት ብላቴና ድንግልም አግኝታቸው ስባ አወጣቻቸው።

ያን ጊዜም ወደ መኰንኑ ሔደው እርሱንና የረከሱ አማልክቶቹን ረገሙ ብዙ ቀኖችም ጭንቅ የሆነ ሥቃይን አሠቃያቸው። ሥቃያቸውም በአደከመው ጊዜ ራሳቸውን በሰይፍ እንዲቆርጧቸው አዘዘና ቆረጡአቸው። የሰማዕትነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበሉ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸው ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ሳሙኤል_ነቢይ

በዚችም ቀን በሊቀ ካህናት ኤሊ ዘመን ነቢይ ሳሙኤል ለመጠራቱ መታሰቢያ ሆነ።

የዚህ ቅዱስ አባቱ ሕልቃና ይባላል የእናቱም ስሟ ሐና ነው። እነርሱም ከሌዊ ነገድ ከካህኑ አሮን ወገን ናቸው። ሐናም መካን ነበረች ክብር ይግባውና ወደ #እግዚአብሔር እያለቀሰች አዘውትራ ስለ ማለደች ይህን የተባረከ ልጅ ሰጣት በቤቷም ሦስት ዓመት አሳደገችው።

ከዚህም በኋላ ገና ስትፀንሰው እንደተሳለች ወደ #እግዚአብሔር መቅደስ አቀረበችው ካህኑ ኤሊንም በመላላክ የሚያገለግለው ሆነ። የካህኑ የኤሊ ልጆች ግን ክፉዎች ነበሩ #እግዚአብሔርንም አይፈሩም ነበር በቅዱስ መሥዋዕቱም ላይ በደሉ። ይህ ሕፃን ሳሙኤል ግን በኤሊ ፊት ለ #እግዚአብሔር ሲያገለግል ኖረ በነዚያ ወራቶችም ቃለ #እግዚአብሔር ውድ ነበር የሚታይ ራእይም አልነበረም።

ከዚህም በኋላ በአንዲት ሌሊት እንዲህ ሆነ ኤሊ በመኝታው ተኝቶ ሳለ ዐይኖቹም መፍዘዝ ጀምረው ነበር ማየትም አይችልም ነበር። የ #እግዚአብሔርንም መብራት አብርቶ ለማሳደር ገና አላዘጋጁም ነበር ሳሙኤል ግን በቤተ መቅደስ በ #እግዚአብሔር ማደሪያ ታቦት አጠገብ ተኝቶ ነበር።

#እግዚአብሔርም ሳሙኤልን ሳሙኤል ሳሙኤል ብሎ ጠራው እነሆ እኔ አለሁ አለ። ወደ ኤሊም ፈጥኖ ሔደ ስለጠራኸኝ እነሆ እኔ መጣሁ አለው ኤሊም አልጠራሁህም ተመልሰኽ ተኛ አለው ሔዶም ተኛ።

#እግዚአብሔርም ዳግመኛ ሳሙኤል ሳሙኤል ብሎ ጠራው ሳሙኤልም ተነሥቶ ወደ ኤሊ ሔደ ስለጠራኸኝ እነሆ መጣሁ አለው። ኤሊም አልጠራሁህም ተመልሰህ ተኛ አለው። ሳሙኤልም ከዚህ አስቀድሞ #እግዚአብሔርን በራእይ ገና አላወቀውም ነበር ቃለ #እግዚአብሔርም አልተገለጠለትም ነበር።

ዳግመኛም #እግዚአብሔር ሳሙኤልን ሦስተኛ ጊዜ ጠራው ተነሥቶም ወደ ኤሊ ሔደ ስለጠራኸኝ እንሆ መጣሁ አለው ኤሊም ያንን ልጅ #እግዚአብሔር እንደጠራው አሰበ። ልጄ ተመልሰህ ተኛ የሚጠራህ ካለ እኔ ባርያህ እሰማለሁና #ጌታዬ ተናገር በለው አለው ሳሙኤልም ሒዶ በመኝታው ተኛ።

#እግዚአብሔርም መጥቶ እንደ መጀመሪያው በፊቱ ቁሞ ጠራው። ሳሙኤልም እኔ ባሪያህ እሰማሃለሁና #ጌታዬ በል ተናገር አለው #እግዚአብሔርም ሳሙኤልን የሰማው ሁሉ ሁለቱን ጆሮዎቹን ይይዝ ዘንድ እነሆ እኔ በእስራኤል ላይ የተናገርሁት ቃሌን አደርጋለሁ።

በዚያችም ቀን በኤሊና በወገኑ ላይ የተናገርኹትን ሁሉ አጸናለሁ እጀምራለሁ እፈጽማለሁም። ልጆቹ የ #እግዚአብሔርን ቃል አቃልለዋልና እርሱም አልገሠጻቸውምና በልጆቹ ኃጢአት እኔ ወገኑን ለዘላለም እንደምበቀለው ነገርሁት። ስለዚህም ነገር በዕጣንም ቢሆን በመሥዋዕትም ቢሆን የኤሊ የወገኑ ኃጢአት እስከ ዘላለሙ ድረስ እንዳይሠረይ ራሴ እንዲህ ብዬ ማልሁ። በኤሊ ወገኖችና ልጆች ላይ #እግዚአብሔር የተናገረው ሁሉ ተፈጸመ።

ከዚህም በኋላ የቂስ ልጅ ሳኦልን ቀብቶ ለእስራኤል ልጆች ያነግሠው ዘንድ #እግዚአብሔር ሳሙኤልን አዘዘው እንዲአነግሥላቸው ለምነዋልና። ሳኦልም የልዑልን ትእዛዝ በተላለፈ ጊዜ ዳግመኛ ለእስራኤል ንጉሥ ሊሆን የዕሴይ ልጅ ዳዊትን ይቀባው ዘንድ ይህን ነቢይ ሳሙኤልን ዳግመኛ አዘዘው። ይህም ነቢይ ሳሙኤል በሕይወት በኖረበት ዘመን ሁሉ እስራኤልን አስተዳደራቸው። ከዚህም በኋላ ሰኔ ዘጠኝ ቀን በሰላም አረፏል።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እና በቅዱስ ሳሙኤል ነብይ ጸሎት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ፊቅጦርና_እናቱ_ሣራ

በዚህች ቀን ታላቁ ሰማዕት ቅዱስ ፊቅጦርና እናቱ ቅድስት ሣራ መታሰቢያቸው ነው፡፡
የከሃዲው ንጉሥ የዲዮቅልጥያኖስ ባለሟል በነበረው በገዛ አባቱ እጅግ ተሠቃይቶ ምስክርነቱን የፈጸመው ታላቁ ሰማዕት ቅዱስ ፊቅጦር፡- ኅርማኖስ የተባለው ወላጅ አባቱ የክርስቲያኖችን ደም እንደ ውኃ ያፈስ የነበረው የዲዮቅልጥያኖስ ልዩ አማካሪና የሠራዊቱ አለቃ ነበር፡፡ እናቱ ሣራ ግን በ #ክርስቶስ አምና የተጠመቀች ክርስቲያን ነበረች፡፡

እንዲያውም ልጇን ቅዱስ ፊቅጦርን ከመውለዷ በፊት የአምላክ እናት የቅድስት #ድንግል_ማርያም ሥዕል ወዳለበት ሄዳ "እመቤቴ ማርያም ለ #ኢየሱስ_ክርስቶስ ደስ የሚያሰኘውን ልጅ ስጪኝ፡፡ #ኢየሱስ_ክርስቶስን ደስ የማያሰኝ ልጅ ከሆነ ግን ማኅፀኔን ዝጊልኝ" ብላ በጸለየችው ጸሎት ነው ቅዱስ ፊቅጦርን ያገኘችው፡፡

ሰማዕቱ ቅዱስ ፊቅጦር በዓለም ላይ ያሉ በ #ክርስቶስ ያመኑ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ክርስቲያኖችን ንጉሡ ዲዮቅልጥያኖስ በግፍ ያስገድል በነበረበት ወቅት የተገኘ ታላቅ ሰማዕት ነው፡፡ ፊቅጦርን ገና 15 ዓመት እንደሆነው ንጉሡ ዲዮቅልጥያኖስ "ከፍ ባለ ስልጣን አስቀምጥሃለሁ፣ እጅግ ብዙ ወርቅና ንብረትም እሰጥሃለሁ፣ በእስክንድርያም ላይ ገዥ አድርጌ እሾምሃለሁ #ክርስቶስን ማመንህን ተውና ወደ ቤተ መንግሥቴ ግባ" ቢለውም ቅዱስ ፊቅጦር ግን ብዙ መከራንና ሥቃይን ተቀብሎ ሰማዕት መሆንን መረጠ፡፡ ቅዱስ ፊቅጦርም ዲዮቅልጥያኖስን " #ክርስቶስን በምታፈቅረው ጊዜ አፈቀርኩህ ወደ አንተም መጣሁ፤ #ክርስቶስን በጠላኸው ጊዜ ግን እኔም ጠላሁህ፣ ቤትህንም ጠላሁ" ብሎታል፡፡

ከብዙ ጊዜም በኋላ ዲዮቅልጥያኖስ ቅዱስ ፊቅጦርን በመንግሥቱ ውስጥ ሦስተኛ ማዕረግ አድርጎ ሾመው፡፡ እርሱ ግን ይጾማል ይጸልያል እንጂ በንጉሡ ቤት አይበላ አይጠጣም ነበር፡፡ ዕድሜውም 27 ነበር፡፡ አባቱንም ከጣዖት አምላኪነቱ እንዲመለስ ቢመክረው ሄዶ ለንጉሡ ከሰሰው፡፡ ፊቅጦርም "ለአንተ ለጣዖት አምላኩ አገልጋይ አልሆንም" በማለት በንጉሡ ፊት ትጥቁን ፈቶ ጣለ፡፡ የቅዱስ ፊቅጦር ወላጅ አባቱ ኅርማኖስ የከሃዲው ንጉሥ የዲዮቅልጥያኖስ የቅርብ እንደራሴና መስፍን ስለነበር ልጁ ፊቅጦርን የንጉሡን ሹመትና ልመና እንዲቀበል ብዙ ሲያግባባው ነበር፤ አባቱም ልጁ በሀሳቡ እንዳልተስማማለት ሲያውቅ ከዲዮቅልጥያኖስ ጋር ተማክሮ ልጁን ቅዱስ ፊቅጦርን ወደ እስክንድርያና ወደ ተለያዩ ሀገሮች በግዞት ተልኮ በዚያም ተሠቃይቶ እንዲሞት ፈደበት፡፡

ወደ ግብፅም ልከው በዚያ እጅግ አሠቃዩት፡፡ መልአክም ነጥቆ ወስዶ በሰማያት የሰማዕታትን ክብር አሳይቶት ወደ ምድር መለሰው፡፡ ክፉዎቹም በብረት አልጋ አስተኝተው ከሥሩ እሳት አነደደዱበት፡፡ በሌላም ልዩ ልዩ በሆኑ ማሠቃያዎች እጅግ አሠቃዩት፡፡ መልአክም ተገልጦ ፈወሰው፡፡ ወደ እንዴናም አጋዙትና በዚያም ብዙ አሠቃዩት፡፡ ምላሱን ቆረጡት፤ በችንካርም ጎኖቹን በሱት፤ ቁልቁል ሰቅለውም ቸነከሩት፤ በእሳትም ውስጥም ጨመሩት፤ ዐይኖቹን አወጡት፤ እሬትና መራራ ሐሞትንም አጠጡት፡፡ ደግመውም ዘቅዝቀው ሰቀሉት፡፡ ጌታችንም ተገልጦ ካጽናናው በኋላ ፈወሰውና ፍጹም ጤነኛ አደረገው፡፡ ፊቅጦር፣ ፋሲለደስ፣ ቴዎድሮስ በናድልዮስ፣ አውሳብዮስና መቃርዮስ እነዚህ ሰማዕታት በአንድነት በአንድ ዘመን አብረው ኖረው ተሰውተው ሰማዕት የሆኑ የሥጋም ዝምድና ያላቸው የነገሥታት ልጆች ናቸው። ዲዮቅልጥያኖስም የቅዱስ ፊቅጦርን ዐይኑን አስወለቀው፣ ነገር ግን የታዘዘ መልአክ መጥቶ የዓይኑን ብርሃን መልሶለታል፡፡ ሰማዕቱ በመዝለል ባሕር የሚሻገር እንደ አሞራ የሚመስል ፈረስ ነበረው፡፡ ከዚህም በኋላ ማሠቃየቱ ቢሰለቻቸው ሚያዝያ 27 ቀን አንገቱን ሰይፈው በሰማዕትነት እንዲያርፍ አድርገውታል፡፡

ሰማዕቱ ቅዱስ ፊቅጦር አንድ የሚነገር ትልቅ ታሪክ አለው፡፡ እርሱም በሰማዕትነት ካረፈ ከብዙ ዘመን በኋላ በራእይ ተገልጦ በ8ኛው ሺህ ዘመን በሀገራችን በኢትዮጵያና በግብፅ እንዲሁም በቁስጥንጥንያና በሮም ወደፊት የሚሆነውን ነገር ሁሉ በግልጽ የተናገረ መሆኑ ነው፡፡ ‹‹ስለ ሃይማኖት ቅዱስ ፊቅጦር ያየው ራእይ›› የሚል መጠሪያ ያለው ይህ ራእይ በሀገራችን ጎጃም ደብረ ጽሞና ገዳም ውስጥ ይገኛል፡፡

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን ሰማዕታት ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#12ቱ_ደቂቀ_ያዕቆብ

በዚችም ቀን ዳግመኛ አባቶቻችን ዐሥራ ሁለቱን የያዕቆብን ልጆች ያስቧቸዋል።

እነዚህ አበው የአብርሃምና የይስሐቅ የልጅ ልጆች የያዕቆብ ደግሞ ልጆች ናቸው። ትውልድ ከአዳም እስከ ቅዱስ ያዕቆብ አንድ ሐረግ ይዞ መጥቶ እዚህ ላይ ሲደርስ ይበተናል። አባታችን ያዕቆብን #እግዚአብሔር ሲባርከው እሥራኤል አለው። ትርጉሙም "ሕዝበ #እግዚአብሔር ወልድ ዘበኩር (የበኩር ልጅ) ከሃሊ ነጻሪ (አስተዋይ) እንደ ማለት ነው።

ይህ ቅዱስ አባት ለ #ድንግል_ማርያም ቅድመ አያት ከመሆኑ ባሻገር ነቢያትን፣ ካህናትን፣ ነገሥታትንና መሣፍንትን ወልዷል። ከወንድሙ ኤሳው ጋር ተጣልቶ ወደ ሶርያ በሔደ ጊዜ ከ2ቱ ሚስቶቹ (ልያና ራሔል) 8 ልጆችን፣ ከ2ቱ የሚስቶቹ ደንገጥሮች (ዘለፋና ባላ) 4 ልጆችን በድምሩ 12 ልጆችን ወልዷል።

#ከልያ የተወለዱት፦ ሮቤል፣ ስምዖን፣ ሌዊ፣ ይሁዳ፣ ይሳኮር እና ዛብሎን ይባላሉ።
#ከራሔል የተወለዱት፦ ዮሴፍና ብንያም ይባላሉ።
#ከባላ የተወለዱት፦ ዳን እና ንፍታሌምን ሲሆኑ
#ከዘለፋ የተወለዱት ደግሞ፦ጋድ እና አሴር ይባላሉ። 12ቱ ደቂቀ እሥራኤል (ያዕቆብ) ማለት እኒህ ናቸው::

ከ12ቱ በቅድስና ዮሴፍ ከፍ ቢልም #እግዚአብሔር ለክህነት ሌዊን፣ ለመንግስት ደግሞ ይሁዳን መርጧል። ከእነሱ ዘርም ዓለምን ለማዳን ተወልዷል። 10ሩ አበው በተለይ በዮሴፍ ላይ ግፍ ሠርተው የነበረ ቢሆንም በኋላ ተጸጽተዋል።
እነሆ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዛሬ ታስባቸዋለች (ዘፍጥረት ከምዕራፍ 28 እስከ 31)

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም ቅዱሳን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አቡነ_ዘርዐ_ቡሩክ

በዚህች ቀን ታላቁ ጻድቅ ተአምረኛው አቡነ ዘርዐ ቡሩክ ልደታቸው ነው፡፡ ከመወለዳቸው አስቀድሞ ትንቢት ተነግሮላቸው ነበር፡፡ አባታቸው ደመ ክርስቶስ ዐይነ ሥውር የነበረ ሲሆን አቡነ ዘርዐ ቡሩክ በተወለዱ ጊዜ ግን የአባታቸውን ዐይን አብርተውለታል፡፡ አባታችን ዘርዐ ቡሩክ ገና በሰባት ዓመታቸው ነው ረቡዕና ዓርብ መጾም የጀመሩት፡፡ በዚሁ በሰባት ዓመታቸውም ‹‹ይህን ዓለም ክፋቱን እንዳላይ ዐይኖቼን አሳውርልኝ›› በማለት ዐይናቸውን እንዲያጠፋላቸው አምላካቸውን ለምነው እንደፈቃዳቸው ዐይነ ሥውር ሆነዋል፡፡ ነገር ግን ከሰባት ዓመት በኋላ በ12 ዓመታቸው #ጌታችን "ለዓለም የምታበራ ብርሃን አደርግሃለሁና ዐይንህም ይብራ" በማለት ዐይነ ብርሃናቸውን መልሶላቸው እንዲያዩ አድርጓቸዋል፡፡ በዚህም ዕድሜያቸው (በ12 ዓመታቸው) ሰባቱንም አጽዋማት ይጾሙ ነበር፡፡

ከዚህም በኋላ #ጌታችን የቅዱሳት መጻሕፍትን ምሥጢር ሁሉ ገለጠላቸው፡፡ መጻሕፍተ ብሉያትን፣ መጻሕፍተ ሐዲሳትን፣ መጻሕፍተ ሊቃውንትን፣ መጻሕፍተ መነኮሳትን፣ አዋልድ መጻሕፍትን ሁሉ ገልጦላቸዋል፡፡ ከሟርት መጻሕፍት በቀር ያስቀረባቸው ነገር አልነበረም፤ የቅዱስ ያሬድንም ዜማ እንዲሁ ገለጠላቸው፡፡
ጻድቁ ከሁሉ ቅዱሳን በበለጠ ሁኔታ ዐሥራ ሁለት ክንፍ የተሰጣቸው ሲሆን በ12 ክንፎቻቸውም የሰማይን ደጆች ሁሉ ገሃነመ እሳትንም አልፈው በመሄድ ቀጥታ በሥሉስ ቅዱስ ዙፋን ፊት ይቆሙ እንደነበር ቅዱስ ገድላቸው ይናገራል፡፡ እጅግ በሚደንቅና ከአእምሮ በላይ በሆነ ሁኔታ አባታችን ለሰባት ቀናት በየቀኑ ለሰባት ሰዓት ያህል በሲኦል ውስጥ ቆመው ይጸልዩ ነበር፡፡ ብዙዎቹ ቅዱሳን በምልጃቸው ነፍሳትን ከሲኦል ሲያወጡ ነው የምናውቀው እንጂ እንደ አቡነ ዘርዐ ቡሩክ በሲኦል ውስጥ ገብቶ ጸሎት የጸለየ ጻድቅ እስካሁን እኔ አላጋጠመኝም፡፡

አቡነ ዘርዐ ቡሩክ እንደ አባታችን ተክለሃይማኖት ለጸሎት በመቆም ብዛት አንድ እግራቸው እስኪሰበር ድረስ በብዙ መከራ ተጋድለዋል፡፡ ከሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ ጋር መንበሩን ያጥኑ ዘንድ ከፈጣሪአቸው ታዘው አጥነዋል፡፡ #ጌታችን ለአቡነ ዘርዐ ቡሩክ ፍጥረታትን ከመፍጠር በቀር ያልሰጣቸው ሥልጣን የለም፡፡ " #እግዚአብሔር ብፁዕና ቅዱስ ለሚሆን አባታችን ዘርዐ ቡሩክ "እኔ ከሥልጣኔ ሥልጣንን፣ ከክብሬም ክብርን፣ ከጥበቤም ጥበብን፣ ከተአምራቴም ተአምራትን፣ ከስጦታዬም ስጦታን፣ ከትዕግስቴም ትዕግስትን፣ ከፍቅሬም ፍቅርን፣ ከትሕትናዬም ትሕትናን፣ ከባለሟልነቴም ባለሟልነትን ሰጥቼሃለሁና ሁሉ ከሥልጣንህ በታች ሆኖ ይታዘዝልህ" የሚል እጅግ ድንቅ ቃልኪዳን ነው የሰጣቸው፡፡ ልዩ ልዩ ሀብታትን ሁሉ ሰጣቸው፡፡ "ለሥላሴ ከሚገባ ከስግደትና በቃልና በሥልጣን ፍጥረታትን ለመፍጠር በቀር ምንም ያልሰጠሁህ የለም" ብሎ ጌታችን በማይታበል ቃሉ እንደነገራቸውና ቃል እንደገባላቸው በቅዱስ ገድላቸው ላይ ተጽፏል፡፡ (የአባታችን ገድላቸው ከመጥፋቱ የተነሣ በአሁኑ ሰዓት አንዳንድ ነጋዴዎች አንዱን ፍሬ ከ3 ሺህ ብር በላይ እየሸጡት ነበር፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ ቲሊሊ የሚገኘው ገዳማቸው በድጋሚ አሳትሞታል፡፡

አቡነ ዘርዐ ቡሩክ በወቅቱ በነበረው ገዥ ፊት በሐሰት ተከሰው ለ5 ዓመታት ያህል በእስርና በእንግልት ሲኖሩ በእነዚህ ጊዜያት ሁሉ ምግብ የሚባል አይቀምሱም ነበርና ከእስር ሲፈቱ አምስት ዓመት ሙሉ ሲሰጣቸው ያጠራቅሙት የነበረው ምግብ ትኩስ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ያሳሰራቸውንም ንጉሥ ገና ሕፃን ሳለ እናቱ ልታስባርከው ወደ አባታችን ዘንድ ወስዳው ነበር፡፡ አቡነ ዘርዐ ቡሩክም ሕፃኑን ከባረኩት በኋላ ለእናቱ "ይህ ልጅሽ ወደፊት ይነግሣል በንግሥናው ዘመንም እኔን ያስርና ያንገላታኛል" ብለው ይህ እንደሚሆን አስቀድመው ትንቢት ተናግረው ነበር፡፡ እንዳሉትም ልጁ አድጎ ሲነግሥ ጭፍሮቹ "ንጉሥ ሆይ አንተን የማይወድ ለቃልህም የማይታዘዝ አንድ መነኩሴ አለ" በማለት ምንም እንኳን ንጉሡ ባያውቃቸውም በሐሰት ነገር ስለከሰሱለት በግዞት እንዲኖሩና እንዲታሰሩ አድርጓቸዋል፡፡ ጻድቁ በግዞት ሲወሰዱ "እነዚህን መጻሕፍቶቼን ለሰዎች አደራ ብሰጣቸው ይክዱኛል፣ ቤተ ክርስቲያን ባስቀምጣቸው ይጠፉብኛል" በማለት ሰባት መጽሐፎቻቸውን ለግዮን (ለዓባይ) ወንዝ አደራ የሰጡ ሲሆን ከ5 ዓመት በኋላ ከእስር ተፈተው ሲመለሱ በወንዙ አጠገብ እንደደረሱ ጸሎት ካደረጉ በኋላ "ግዮን ሆይ በ #እግዚአብሔር ፊት በአደራ የሰጠሁሽን መጽሐፎቼን ግሺ (ትፊ)" ብለው እጃቸውን ወደ ወንዙ ሰደው መጽሐፎቻቸው ሳይረጥቡና ሳይበሰብሱ ከወንዙ ውስጥ አውጥተዋቸል፡፡ እንዲያውም አቧራውን ከመጻሕፍቶቻቸው ላይ እፍ ብለው አራግፈውታል፡፡

በመጽሐፍ ቅዱስ እንደተጠቀሰው የጠለቀው ምሳር እየተንሳፈፈ ወደ ኤልሳዕ እንደመጣ ሁሉ አሁንም እንዲሁ የቅዱስ አባታችን መጽሐፎች አብሯቸው ከነበረውና ዘሩባቤል ከሚባለው ደቀ መዝሙራቸው ጋር ወዳሉበት ተንሳፈው ሊመጡ ችለዋል፡፡ መጽሐፎቻቸውንም አብሯቸው ለነበረው ደቀ መዝሙራቸው ካሳዩት በኋላ እንዲይዛቸው ሰጥተውታል፡፡

የግዮን ወንዝ "ግሺ ዓባይ" ወይም "ዓባይ" እየተባለ መጠራት የጀመረው አቡነ ዘርዐ ቡሩክ "ግዮን ሆይ በእግዚአብሔር ፊት በአደራ የሰጠሁሽን መጽሐፎቼን ግሺ (ትፊ)" ብለው እጃቸውን ወደ ወንዙ ሰደው መጽሐፎቻቸው ሳይረጥቡና ሳይበሰብሱ ከወንዙ ውስጥ ካወጡበት ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ አባታችን በቦታው ላይ 30 ዓመት ሙሉ ቆመው ጸልየው ቦታውን የባረኩት ሲሆን ጌታችንም በቦታው ላይ ትልቅ ቃልኪዳን ሰጥቷቸዋል፡፡ "ብፁዕ አባታችን ለግዮን ወንዝ መጽሐፎቹን በአደራ ሰጥተው በኋላም ከደቀ መዝሙራቸው ከዘሩባቤል ጋር መጽሐፎቹን ከግዮን ምንጭ ውስጥ ከተቀበለ በኋላ "በግዮን ውኃ ውስጥ ሳይረጥቡ በደረቅ መጽሐፎቼን የጠበቀ እግዚአብሔር ይመስገን" ብሎ ፈጣሪውን አመሰገነ፡፡ "ያንጊዜም በውስጥሽ ታላቅ ድኅነት ይደረግብሽ፣ ሕመምተኞች ሁሉ ይዳኑብሽ፣ መካኖች ይውለዱብሽ" ብሎ ግዮንን በቃሉ መረቃት፣ በእጁም ባረካት፡፡ ብፁዕ አባታችንም በዚህች ቦታ ላይ ፈውስ፣ ረድኤት፣ በረከት ይደረግብሽ ብሎ ብዙ ዘመን ቆሞ ጸለየ፡፡ እግዚአብሔርም ጸሎቱን ሰምቶ "ይህ በረከት፣ ረድኤት፣ ሀብት፣ ፈውስ እንደወደድህ እስከዘለዓለሙ በዚህ ቦታ ይሁንልህ" አለው" ተብሎ ነው በቅዱስ ገድላቸው ላይ የተጻፈው፡፡

ጻድቁ አቡነ ዘርዐ ቡሩክ ሌላው የሚታወቁበት "ብሄሞትና ሌዋታን" የተባሉ እጅግ ግዙፍ የሆኑ ሁለት ዘንዶዎችን ጥርሳቸውን ቆጥረው ምላሳቸው ሲጣበቅ የዓለም ፍጻሜ እንደሚሆን አስቀድመው ያወቁ ድንቅ ነቢይ የሆኑ አባት በመሆናቸው ነው፡፡ እነዚህም እጅግ ግዙፍ የሆኑ ሁለት እንስሳት ሴትና ወንድ ሆነው ምድርን እንደመቀነት ከበው የያዙ ናቸው፡፡ ዝርዝር ታሪካቸው በመጽሐፈ አክሲማሮስ (ሥነ ፍጥረትን በሚያስረዳው መጽሐፍ) ላይ በስፋት ተጠቅሰዋል፡፡

አቡነ ዘርዐ ቡሩክ ሳይጠመቁ ለሚሞቱ አሕዛብም ጭምር ትልቅ ቃልኪዳን የተሰጣቸው ታላቅ አባት ናቸው፡፡ ይኸውም በቅዱስ ገድላቸው ላይ እንዲህ ተብሎ ተጽፏል- "በሥራው ሁሉ ፍጹም የሆነና ገድሉ ያማረ ቅዱስ አባታችንን በአድማስ ራስ ቆሞ ምሥራቁንና ምዕራቡን፣ ሰሜኑንና ደቡቡን እንዲባርክ በአፉ እስትንፋስም የምሕረት እስትንፋስን እፍ እንዲል እስትንፋሱንም ከአድማስ እስከ አድማስ ጽንፍ እስከ ጽንፍ ይደርስ ዘንድ እግዚአብሔር አዘዘው፡፡ በእግዚአብሔር በቅዱስ ስሙ ያልተጠመቁ አሕዛብ በእስትንፋሱ ምክንያትና የምሕረት እስትንፋስን እፍ እንዲል እስትንፋሱንም ከአድማስ እስከ አድማስ ጽንፍ እስከ ጽንፍ ይደርስ ዘንድ እግዚአብሔር አዘዘው፡፡ በእግዚአብሔር በቅዱስ ስሙ ያልተጠመቁ አሕዛብ በእስትንፋሱ ምክንያት ልጅነት አግኝተው እንዲከብሩ በቃል ኪዳኑ ተማፅነው ሳይጠመቁ በሚሞቱበት ጊዜ "ይህ ከእኔ የተቀበልከው ቃልኪዳን ከጎኔና ከሰውነቴ እንደፈሰሰው ደሜ ይሁንላቸው" በማለት ለዓለም መድኃኒት አድርጎ ቃልኪዳን ሰጠው፡፡

ዳግመኛም በቅዱስ አባታችን ዘርዐ ቡሩክ ስም ከእግዚአብሔር ምሕረትን ለምነው በሚሞቱበት ጊዜ በውኃና በመንፈስ ቅዱስ እንደተጠመቁ ይሁንላቸው ብሎ ነገረው፡፡ በከበረና በገናና ስሙ የተጠመቁ ሕዝቡም በኃጢአታቸው በወደቁ ጊዜ በሥራቸውም በረከሱ ጊዜ በጻድቁ ጸሎት ቢማጸኑ በቃልኪዳኑ ቢያምኑ ይህ እስትንፋሱ የኃጢአት ማስተሠርያ ይሁናቸው ብሎታል፡፡ ጻድቁ አባታችንም የእግዚአብሔርን ትእዛዝ በሰማ ጊዜ ከዚያ በፊት ለሌሎች ያልተሰጠ ቃልኪዳን ተቀብሎ በአድማስ ላይ ቆመ፡፡ በዚያም ቆሞ መንፈሳዊ እስትንፋሱን በምድር ላይ እፍ አለ፡፡ ያም የሕይወት እስትንፋስ በአራቱ ማዕዘን ደርሶ በኃጢአታቸው መከራ የተቀበሉ ለበደላቸውም የተገዙ ሰዎች በፈጣሪያቸው ስም እንዲከብሩ ዓለሙን ሁሉ ባረከ" ይላል ቅዱስ ገድላቸው፡፡ ይህም የሚያሳያየው መድኃኔዓለም ክርስቶስ የሰውን ልጆች ምን ያህል እንደወደዳቸውና በትንሽ ምክንያት የመዳንን
መንገድ ያዘጋጀላቸው መሆኑን ነው፡፡

ሌላው አቡነ ዘርዐ ቡሩክ እሳቸው በባረኳት ምድርና በልጆቻቸው ላይ ችግርና ርኀብ እንደማይደርስባቸው ቃልኪዳን የተሰጣቸው ድንቅ አባት ናቸው፡፡ ይኸውም በቅርቡ እንኳን በ1977ቱ የርሃብ ዘመን በግልጽ ስለታየ ታሪክ ይመሰክረዋል፡፡ በዚህ ወቅት ከወሎና ከሌሎችም ቦታዎች በርሃብ ተሰዶ ጎጃም ለመጣው የሀገራችን ሕዝብ የአቡነ ዘርዐ ቡሩክ በረከት ከበቂ በላይ ነበር፡፡

ጻድቁ በጎጃም ባሕር ዳር አካባቢ ሁለት ቤተ ክርስቲያን አላቸው፡፡ የዓባይ ምንጭ መነሻ የሆነው ፈለገ ግዮን ግሽ ዓባይ ከባሕር ዳር ከተማ 174 ኪ.ሜ የሚርቅ ሲሆን ከባሕር ዳር ቲሊሊ፣ ከቲሊሊ ሠከላ በመሳፈር በቦታው ላይ ለብዙ ዘመን ቆመው በመጸለይ ታላቅ ቃልኪዳን የተቀበሉበትን እጅግ ተአምረኛና ፈዋሽ የሆነውን ጸበላቸውን ማግኘት ይቻላል፡፡ ቦታው መጽሐፋቸውን ለዓባይ ወንዝ አደራ የሰጡበት ነው፡፡

ሌላኛው ቤተ ክርስቲያናቸው ከባሕር ዳር የሁለት ሰዓት የመኪና መንገድ ርቀት ላይ በምትገኘውና አዴት በምትባለው ቦታ የሚገኘው ነው፡፡ የአቡነ ዘርዐ ቡሩክ መካነ መቃብራቸውና ከሰማይ የወረደላቸው መስቀል እዚህ ይገኛሉ፡፡ ቦታውን የረገጠ ሁሉ ከመካነ መቃብራቸው ላይ እምነት ይወስዳል፣ በመስቀሉም ይባረካል፡፡ ነገር ግን ጻድቁ በቃል ኪዳናቸው መሠረት በዚህ መስቀላቸው የተባረከ ሁሉ ዲቁናን፣ ክህነትን መቀበል ስለሚችል ሴቶች አይባረኩበትም፡፡ መካነ መቃብራቸው ቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ከመቅደሱ ውጭ የሚገኝ ሲሆን ከመቃነ መቃብራቸው ላይ ያለው አፈር ሁልጊዜ እየፈላ መጠኑ ይጨምራል፡፡ ይህን የእምነቱን አፈር ቢዝቁት አያልቅም፣ ባዶ እንኳን ቢደረግ በተአምራት ሞልቶ ይገኛል፡፡ ለብዙ ሕመምተኞች ፍጹም ፈውስ የሆነው ይህ እምነት አጠቃላይ ሁኔታው ለዕይታ አመቺ ስለሆነ ይህንን ማንኛውም ሰው ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ማየትና እምነቱን ወስደው መጠቀም ይችላሉ፡፡

ጻድቁ አባታችን በ482 ዓመታቸው በዚህች ዕለት ጥር 13 ቀን በታላቅ ክብር ያረፉበት በዓላቸው በድምቀት ይከበራል፡፡ በዕረፍታቸው ዕለት ከቤተ ክርስቲያኑ አደባባይ ላይ አትሮንስ ወጥቶ ገድላቸው ይነበባል፡፡ ገድላቸው ሲነበብም ከአትሮንሱ ሥር ሰባት ጠርሙሶችና አንድ ማሰሮ ይቀመጥና በጠርሙሶቹ ውስጥ አንድ አንድ ስኒ ውኃ ይደረግባቸዋል፡፡ የአባታችን ቅዱስ ገድላቸው ሲነበብ ውኃው ይፈላል፣ ገድሉ ተነቦ እንዳለቀ ጠርሙሶቹና ማሰሮው በተአምራት ተሞልተው ይገኛሉ፡፡

ጌታችን ለአቡነ ዘርዐ ቡሩክ ትንባሆን ስለሚጠጡ ሰዎች ታላቅ ምሥጢርን እንደነገራቸው በቅዱስ ገድላቸው ላይ ተጽፏል፡፡ ቅዱስ አባታችን በየቀኑ ለሰባት ሰዓት ያህል በሲኦል ውስጥ ቆመው በመጸለይ ብዙ ነፍሳትን ከእሳት ያወጡ ነበር፡፡ አንድ ቀን ብዙ ነፍሳትን ካወጡ በኋላ አንዲት ነፍስ ግን ከሲኦል ግደግዳ ጋር እንደ ሰም ተጣብቃ እምቢ አለቻቸው፡፡ አባታችንም ያቺን ነፍስ አወጣለሁ ሲሉ ቆመው ይጸልዩበት የነበረው የሲኦል እሳት አሁን ያችን ነፍስ አወጣላሁ ባሉ ሰዓት ግን አቃጠላቸው፡፡ እሳቸውም ያችን ነፍስ እዚያው ሲኦል ጥለው በመውጣት ጌታችንን "የዚያች ነፍስ ኃጢአቷ ምንድን ነው?" አሉት፡፡ የዚህን ጊዜ ነው ጌታችን ትንባሆን ስለሚጠጡ ሰዎች ታላቅ ምሥጢርን የነገራቸው፡፡ ይኸውም አባ ሐዊ የሚባሉ ጻድቅ ያስተላለፉትን ውግዘትና ግዝት የጸና እንደሆነ ነው ጌታችን ለአቡነ ዘርዐ ቡሩክ የነገራቸው፡፡

ዝርዝር ታሪኩም በድርሳነ መድኃዓለም ላይ እንዲህ ተጽፎ ይገኛል፡- ትንባሆ የሚጠጡ ሰዎች ለምን ለማቆም እንደሚቸገሩና መጨረሻቸውም ምን እንደሆነ፡- "ይቅርታውና ምሕረቱ ከሁላችን የጥምቀት ልጆች ጋር ይሁንና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መድኃኔዓለም ያደረገው ተአምር ይህ ነው፡- አባታችን ዘርዓ ቡሩክ መድኃኔዓለምን እንደወደደውና በየወሩ በሃያ ሰባት ቀን በዓሉን እንደሚያከብር በአሥራ ስድስት ቀንም ኪዳነ ምሕረትን እንደሚያከብር እነሆ እንነግራችኋለን፡፡ ባለሟልነትን ባገኘ ጊዜና መድኃኔዓለም የእሳት ፈረስንና የመስቀል ምልክት ያለበት የወርቅ በትርን በሰጠው ጊዜ "ወደ ሲዖል ሂድና መሸከም የምትችለውን ያህል ነፍሳትን አውጣ› አለው፡፡ ሄዶም ወደ ሲዖል ገባ፣ ነፍስ በነፍስ ላይ እንደ ንብ እየተጨናነቁ በሰውነቱ ላይ ታዘሉ፡፡ ነፍሳትንም ይዞ ሲወጣ አንድ ኃጢአተኛ ‹ዘርዓ ቡሩክ ብቻዬን ቀረሁ፣ አውጣኝ" አለው፡፡ ዘርዓ ቡሩክም ወደ እርሱ ተመልሶ ሳበው፡፡ ሰም ከፈትል ጋራ እንደሚጣበቅ ከሲዖል ጥልቅ ጋራ ተጣብቆ እምቢ አለው፡፡ የእሳቱ ነበልባልም ዘርዓ ቡሩክን አቃጠለው፣ እርሱም ተወው፡፡ ክብር ይግባውና እነዚያን ነፍሳት ይዞ ወደ ጌታው ወደ መድኃኔዓለም ሄደ፡፡

ሄዶም "ጌታዬ ሆይ! አንዲት ነፍስ ስሜን እየጠራች ቀርታለች ማርልኝ" አለው፡፡ መድኃኔዓለምም "ዘርዓ ቡሩክ ሆይ! በእኔ ዘንድ ባለሟልነትን ብታገኝ ትንባሆ የሚጠጣውን ማርልኝ ትለኛለህን?" አለው፡፡ እርሱም "ጌታዬ ሆይ! ይህቺ እንጨት በምን ትከፋለች?፣ ከሁሉ ኃጢአትስ በምን ትበልጣለች?" አለው፡፡ ወይቤሎ መድኅን ኢሰማዕከኑ ግብራ ለዛቲ ዕፅ ዘከመ ዘርዓ ሰይጣን ውስተ ገራህተ ዓለም፡፡ መድኃኔዓለምም "የዚህችን እንጨት ሥራ በዓለም እርሻ ሰይጣን እንደዘራት አልሰማህምን?" አለው፡፡ እነሆም እንነግራችኋለን፣ ስሙ ሐዊ የሚባል የፈጣሪውንም ሕግ የሚጠብቅ አንድ መምህር ነበረ፡፡ በዓርብ ቀንም ወደ ሰማይ ይሔዳል፤ በቀዳሚት ሰንበትና በእሑድ ከፈጣሪው ጋር ይነጋገራል፡፡ በሰኞ ቀንም ወደ ቦታው ይመለሳል፡፡ ለሀገር ሰዎችም በጉባኤ ይነግራቸዋል፣ በአዋጅ ነጋሪ ቃልም ይሰበሰባሉ፡፡ ይህቺ ሀገር ትልቅ ናትና እስከ ዓርብም ያስተምራቸዋል፡፡ በዚያን ጊዜ ሰይጣን ቀና፡፡ አባ ሐዊም እንደልማዱ በዕለተ ዓርብ ወደ ሰማይ በሄደ ጊዜ ያ ሰይጣን በመቀመጫው ተቀምጦ በእርሱ በሐዊ ተመስሎ በቀዳሚት ሰንበት ቀንም ተገልጦ "ፈጣሪያችን የሚወዳትን ነገር እነግራችሁ ዘንድ ሁላችሁም ተሰብሰቡ" አለ፡፡ ሁላቸውም ተሰበሰቡ፡፡ "አባት ሆይ! ያለ ልማድህ ዛሬ ለምን መጣህና ጠራኸን?" አሉት፡፡ ያ ጠላት ዲያብሎስም "ጌታዬ ለሕዝቦቼ የዚያችን በቤትህ አንፃር ያለችውን እንጨት ቅጠል በጥርሳቸው ይጨምሩ ዘንድ፣ በአፋቸውም ያጤሱ ዘንድ ዛሬ ካልነገርሃቸው ወዳጄ አይደለህም አለኝ" አላቸው፡፡ ይህችንም እንጨት ባያት ጊዜ እንዲህ አደረገ፣ ሔዋንን በእንጨት እንዳሳታት አሳታቸው፡፡ ዛሬ እንደሚያደርጉትም የጥንባሆ ዕቃን አደረጉ፡፡ ቅጠሏንም አምጥተው ቀጥቅጠው በእሳት አጢሰው ትንሹም ትልቁም፣ የከበረውም የጎሰቆለውም ሁላቸውም ጠጡ፡፡

ሐዊም በሰማይ ሳለ በጸጋ አውቆ አዘነ፣ ነገር ግን ስለ ሰንበታት ክብር ብሎ አደረ፡፡ ሰኞ በነግህም ሐዊ መጣ፣ ሰይጣንም እንደ ጢስ በኖ ጠፋ፡፡ እርሱም ሰዎቹን ሰብስቦ "ይህን ማን አስተማራችሁ?" አላቸው፡፡ "አንተ ነህ" አሉት፡፡ "ሰይጣን ነው እንጂ እኔ አይደለሁም፣ ከዛሬ ጀምሮ ተው" አላቸው፡፡ "ትናንት ጠጡ፣ ዛሬ ተው" ይለናል ብለው እምቢ አሉት፡፡ እርሱም አወገዛቸው፡፡ "በእርሻው የዘራት፣ በአፉም የጠጣት፣ በእጁም የያዛት የተረገመ ይሁን" አላቸው፡፡ ጋኔኑም በቅሉ ውስጥ ሆኖ ይነጋገራል፣ በውጭ ያሉትንም አጋንንት ይጠራቸዋል፡፡ በዚህን ሰዓት የተውም አሉ፣ እምቢም ያሉ አሉ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ያቺ እንጨት ተረገመች፡፡ ሰውም በጠጣት ጊዜ የአምስት ቀፎ ሙሉ ንቦችን የሚያህሉ አጋንንት ይመጣሉ፡፡ በሁለቱ ዓይኖቹ ውስጥ፣ በሁለቱ አፍንጫዎቹም፣ በሁለቱ ጆሮዎቹም፣ በአፉም፣ በታች በሰገራ መውጫም በእነዚህ ሁሉ እንደ ቀፎ ንብ ይገባሉ፣ ይወጣሉ፡፡ ትምክህትን፣ ትዕቢትን፣ መግደልን፣
ሥርቆትንም፣ ክፉውንም ሁሉ ይመሉታል፡፡ ወሶበ ይሰትያ ብእሲ ይመጽኡ አጋንንት ዘየአክሉ መጠነ ፭ቱ ቀፈዋት ዘመልኡ አንህብት ወይበውኡ ውስቴቱ፡፡ በ፪ አዕይንቲሁ፣ ወበ፪ አዕናፊሁ፣ ወበ፪ አዕዛኒሁ ወበመንፈሱ ዘታህት በአፉሁ በዝንቱ ኵሉ ከመ ንህብ ዘቀፎ ይበውኡ ወይወጽኡ፡፡ ወይመልእዎ ትምክህተ፣ ወትዕቢተ፣ ቀትለ፣ ወሠሪቀ ወኵሎ ዕከያተ እንዲል መጽሐፍ፡፡

አባታችን ዘርዓ ቡሩክም ይህን ሰምቶ እጆቹን በትከሻው አመሳቅሎ አለቀሰ፣ በሥዕሉም አለ፣ በዚያን ጊዜ ወደ ዓለም ወጣ፡፡ ይህችን የተረገመች እንጨት እንዲህ ብሎ አወገዛት፡- "በአፉ የጠጣት፣ በእጁም የያዛት፣ የዘራት፣ የሸጣት፣ የገዛትም የጥምቀት ልጅ አይደለም፤ በሥጋው አይጠቀምም፣ ነፍሱም ወደ ሲዖል ትወርዳለች፡፡ ልጄ የሆነ ግን መድኃኔዓለምንና ኪዳነ ምሕረትን ያክብር፡፡ ጥንባሆንም አይጠጣ› አለ፡፡ የዚህ ጻዲቅ በረከቱ ያልታዘዝንውን ከመብላት ይጠብቀን አሜን" በማለት ተአምረ መድኃኔዓለም ወገድለ መባዓ ጽዮን ነገረ ጥንባሆን በሰፊው ዘግቦታል፡፡ በሌላም በኩል ትንባሆን በተመለከተ መድኃኔዓለም ክርስቶስ ለአቡነ ዘርዐ ቡሩክ የሰጣቸው ቃልኪዳን በራሳቸው በዘርዐ ቡሩክ ገድል ላይ የተጻፈውን ወደፊት እናያለን፡፡ እንዲሁም ይህችን የተረገመች ዕፅ የሚጠቀሙባት ሁሉ የሰይጣን ማደሪያዎች እንደሚሆኑና ክፉውንም ሁሉ እንደሚያሠሩት በሌላም ቦታ በአቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ገድል ላይ በሰፊው ተጽፏል፡፡

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን ።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ነሐሴ_27 እና #ከገድላት_አንደበት #ዲያቆን_ዮርዳኖስ_አበበ)
2024/09/21 20:30:38
Back to Top
HTML Embed Code: