Telegram Web Link
ጾመ ፍልሰታ/ጾመ ማርያም/ 
  
   🌺ፍልሰታ ማለት ፈለሰ፤ ተሰደደ፤ ተጓዘ፤ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ሄደ ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ ቃል ሲሆን ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ «ፈለሰት ማርያም እምዘይበሊ ኀበኢይበሊ፤ ድንግል ማርያም ከሚያልፈው ዓለም ወደማያልፈው ዓለም፣ ከምድር ሕይወት ወደ ሰማያዊ ሕይወት፣ ተሻገረች» በማለት ፍልሰታ የሚለውን ቃል ትርጓሜ አመሥጥሮ ገልጾታል፡፡

  🌺ጾመ ፍልሰታ ከእመቤታችን ድንግል ማርያም የዕረፍት ታሪክ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ እመቤታችን በዚህ ዓለም ፷፬ ዓመታትን በሕይወተ ሥጋ ከቆየች በኋላ ጌታችን የእናቱን ተድላ ነፍሷን እንጂ ተድላ ሥጋዋን አይወድምና ጥር ፳፩ ቀን ፵፱ ዓመተ ምሕርት አረፈች፡፡ ዕረፍቷም እንደሌላው ሰው በሕማምና በድካም አይደለም፡፡ በገነት ዕፀዋት መዓዛ ተመስጣ ቅድስት ነፍሷ ከሥጋዋ ተለይታለች፡፡

  🌺ታሪኩ በነገረ ማርያም እንደተጻፈው ሐዋርያት እመቤታችንን በአጎበር አድርገው አክብረው ወደጌቴሴማኒ መካነ መቃብር ይዘዋት ሲሄዱ አይሁድ ለምቀኝነት አያርፉም ነበርና ቀድሞ ልጇን ተነሣ ዐረገ እያሉ ሲያውኩ ኖረዋል፤  እርሷን ደግሞ ተነሣች ዐረገች እያሉ ሊያውኩን ነውና «ኑ የማርያምን ሥጋ በእሳት እናቃጥለው» ብለው በምቀኝነት ተነሱ፡፡ ከመካከላቸው አንድ ታውፋንያ የሚባል አይሁዳዊ ከሐዋርያት እጅ ለመንጠቅ ዘሎ ሄዶ የአልጋውን ሸንኮር ሲይዝ የታዘዘ መልአክ በረቂቅ ሰይፉ እጆቹን ቆረጠው፡፡ እጆቹም በአልጋው ሸንኮር ላይ ተንጠልጥለው ቀሩ፡፡ የምሕረት እናት የሆነችው ድንግል ማርያም ቅዱስ ጴጥሮስ ጸልዮ እጆቹን እንዲመልስለት ነግራው እንደነበረ አድርጎለታል፡፡

  🌺የእመቤታችን ሥጋዋን መላእክት ከዮሐንስ ወንጌላዊ ጋር በገነት ከዕፀ ሕይወት ሥር ወስደው አስቀምጠውታል፡፡ ሥጋዋ ያለበትን ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ አይቶ እነርሱ ባለማየታቸው እመቤታችን ባረፈች በ፮ኛው ወር ከነሐሴ ፩ ቀን እስከ ፲፬ ቀን ድረስ ከጾሙ በኋላ በ፲፬ኛው ቀን ሥጋዋን እንደገና ከጌታ ተቀብለው በጌቴሴማኒ ባለው መቃብር ቀብረውታል፡፡

  🌺ከዚህ በኋላ እንደ ልጇ በ፫ኛው ቀን ተነሥታ መላእክት እየዘመሩላት ወደሰማያት ስታርግ፤ ሐዋርያው ቶማስ ከሀገረ ስብከቱ በደመና ተጭኖ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመለሰ ዕርገቷን በማየቱ መላእክት «እመቤትህ እርሷ ናት፤ስገድላት» አሉት፤ እርሱም «ወፈቀደ ይደቅ እምደመናሁ ይላል፤ከደመናው ሊወድቅ ወደደ» ምክንያቱም ቀድሞ የልጇን ትንሣኤ፤ ዛሬ ደግሞ የእርሷን ትንሣኤ ለማየት ብሎ ነው፡፡ እመቤታችንም «ትንሣኤየን ያየህ አንተ ነህ ሌሎቹ አላዩም» ብላ ሐዋርያት ገንዘው የቀበሩበትን የሐር ግምጃ ሰጥታ አጽናንታ ሰደደችው፡፡

  🌺ቅዱስ ቶማስ ኢየሩሳሌም ሲደርስ የእመቤታችን ነገር እንዴት ሆነ ብሎ ጠየቃቸው፤እነርሱም አግኝተው እንደቀበሯት ነገሩት፤ እርሱም ያየውን ምሥጢር በልቡ ይዞ «ሞት በጥር፤ በነሐሴ መቃብር፤ ለሰሚውም አያምር፤ይህ እንዴት ይሆናል?»፤ ቢላቸው ቅዱስ ጴጥሮስ «ድሮም አንተ ተጠራጣሪ ነህ፤ማን ያርዳ የቀበረ፤ ማን ይናገር የነበረ እንዲሉ፤ ገንዘን የቀበረን እኛ እያለን እንዴት ትጠራጠራለህ» ብለው ወደ መቃብሯ ሄደው መቃብሯን ቢከፍቱት ባዶ ሆኖ አገኙት፡፡ በዚህ ተደናግጠው ተያዩ፤ በዚህ ጊዜ ቅዱስ ቶማስ «አታምኑኝም ብዬ ነው እንጂ እመቤታችን ተነሣች፤ዐረገች፤ ይኸው ምልክቱ» ብሎ ገንዘው የቀበሩበትን ሰበን አሳያቸው፤ እነርሱም አምነው ሰበኗን ለበረከት ተካፈሉት፡፡

  🌺በዓመቱ ነሐሴ ፩ ቀን ሐዋርያት በመንፈሰዊ ቅናት ተነሳስተው «ቶማስ ትንሣኤዋን አይቶ እኛ ሳናይ እንዴት ይቀርብናል» በማለት ነሐሴ ፩ ቀን ሱባኤ ጀምረው በ፲፮ኛው ቀን የሐዋርያትን ሱባኤ ተቀብሎ እመቤታችንን መንበር ጴጥሮስን ተራዳኢ፣ ካህን እስጢፋኖስን ሠራዔ ዲያቆን አድርጉ ቀድሶ አቁርቧቸዋል፡፡ ከዚያ ጊዜ በኋላም ከነሐሴ ፩ እስከ ፲፭ ቀን  ጾመ ፍልሰታ ተብሎ ሁሉም የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታይ ይጾመዋል፡፡

💛የጾሙ እና የትንሣኤዋ በረከት ተካፋይ ያድረገን፤ አሜን💛
#ነሐሴ_2


አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ነሐሴ ሁለት በዚች ቀን መኑፍ ከሚባል አገር #ቅድስት_አትናስያ አረፈች፣ ከነገሥታት ወገን የሆነች #ቅድስት_ኢዮጰራቅስያ አረፈች፣ በተጨማሪ በዚች ቀን #ዲያቆናዊት_ኢዮኤልያና ዕረፍት፣ #ሰማዕቱ_ደሚናና ሰማዕታት የሆኑ ወንድሞቹ መታሰቢያቸው ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_አትናስያ_ቡርክት

ነሐሴ ሁለት በዚች ቀን መኑፍ ከሚባል አገር ቅድስት አትናስያ አረፈች።

የዚችም ቅድስት ወላጆቿ ባለጸጎች ነበሩ እነርሱም በሞቱ ጊዜ ቤቷን ለእንግዳ ማደሪያ ታደርግ ዘንድ በጎ ኃሳብ አሰበች ወደርሷም የሚመጡትን እንግዶች ሁሉ ትቀበላቸው ነበር። በገዳም ለሚኖሩ መነኰሳትም የሚያስፈልጓቸውን ትሰጣቸው ነበር ስለ በጎ ሥራዋም ይወዷት ነበር።

ከዚህም በኋላ ግብራቸው የከፋ ክፉዎች ሰዎች ወደርሷ ተሰብስበው ኃሳቧን ወደ ኃጢአት ሥራ መለሱትና ኃጢአትን አብዝታ ትሠራ ጀመር። በአስቄጥስ ገዳም በሚኖሩ አረጋውያን ቅዱሳን ዘንድም ወሬዋ ተሰማ ስለእርሷም እጅግ አዘኑ አባ ዮሐንስ ሐጺርንም ጠርተው ስለርሷ የሆነውን ነገሩት አስቀድማም ከእነርሱ ጋራ በጎ ስለ ሠራች ወደ እርስዋ ይሔድ ዘንድ ነፍስዋንም ለማዳን ይወድ ዘንድ ለመኑት።

እርሱም ትእዛዛቸውን ተቀበለ በጸሎታቸውም እንዲረዱት ለመናቸው ያን ጊዜም አባ ዮሐንስ ሐጺር ተነሥቶ ሔደ አትናስያ ወዳለችበት ቦታ ደረሰ ለበረኛዋም ለእመቤትሽ ስለእኔ ንገሪ አላት። በነገረቻትም ጊዜ ለረከሰ ሥራ እንደሚፈልጓት ሰዎች ሁሉ የመጣ መሰላትና አጊጣ በዐልጋዋ ላይ ሁና ጠራችው። ወደርሷም ገባ እርሱም እንዲህ እያለ ይዘምር ነበር በሞት ጥላ ውስጥ ብሔድም እንኳ ክፉን አልፈራውም አንተ ከእኔ ጋራ ነህና።

ከእርሷ ጋራም አስቀመጠችው ያን ጊዜም ራሱን ዘንበል አድርጎ አለቀሰ ለምን ታለቅሳለህ አለችው እርሱም ሰይጣናትን በላይሽ ሲጫወቱ አየኋቸው ክብር ይግባውና #ጌታዬ_ኢየሱስ_ክርስቶስን ለምን አሳዘንሺው የቀድሞ በጎ ሥራሽን ትተሽ ወደ ጥፋት ሥራ ተመልሰሻልና አላት።

ቃሉንም ሰምታ ደነገጠችና ተንቀጠቀጠች ምን ይሻለኛል አለችው ንስሐ ግቢ አላት እርሷም #እግዚአብሔር ይቀበለኛልን አለችው እርሱም አዎን አላት እርሷም ወደምትሔድበት ከአንተ ጋራ ውሰደኝ አለችው እርሱም ነዪ ተከተይኝ አላት።

ያን ጊዜም ፈጥና ተነሥታ በኋላው ተከተለችው ከገንዘቧም ምንም ምን አልያዘችም። በመሸም ጊዜ ለማደር ወደ ጫካ ውስጥ ገቡ በዚያም ለእርስዋ ቦታ አዘጋጅቶ እስኪነጋ በዚህ አረፍ ብለሽ ተኚ እኔም ወደዚያ እሆናለሁ አላት። ይህንንም ብሎ ከእርሷ ጥቂት ተገልሎ እየጸለየ ብቻውን ተቀመጠ።

በሌሊቱ እኩሌታም ሊጸልይ ተነሣ ከምድር እስከ ሰማይ የሚደርስ የብርሃን ምሰሶ አየ የ #እግዚአብሔርም መላእክት የከበረች ነፍስን ተሸክመው ሲወጡ አይቶ አደነቀ። በነጋም ጊዜ ወደ ርሷ ሔደ ሙታም አገኛት እጅግም አዘነ ስለ ርሷም ያስረዳው ዘንድ እየሰገደ ወደ #እግዚአብሔር ለመነ።

ወደርሱም እንዲህ የሚል ቃል መጣ ከቤቷ በወጣች ጊዜ #እግዚአብሔር ንስሓዋን ተቀብሎ ኃጢአትሽ ተሠረየልሽ ብሎአታል። ከዚህም በኋላ ሒዶ ለአረጋውያን የሆነውን ሁሉ ነገራቸው እነርሱም እርሱ እንዳያት ማየታቸውን ነገሩት የኃጢአተኛን ወደ ንስሐ መመለሱን እንጂ ሞቱን የማይሻ #እግዚአብሔርን አመሰገኑት።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎቷ ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_ኢዮዸራቅስያ_ድንግል

በዚህችም ቀን ከነገሥታት ወገን የሆነች ቅድስት ኢዮጰራቅስያ አረፈች። የእርስዋም የአባቷ ስም ኢጣጎኖስ ነው የንጉሥም አማካሪ ነበር የእናቷም ስም ኢዮጰራቅስያ ነው እነርሱም ደጎች ነበሩ ጾምና ጸሎትንም ወደ #እግዚአብሔር የሚያቀርቡ ነበሩ። ይችንም ቅድስት በወለዷት ጊዜ በእናቷ ስም ኢዮጰራቅስያ ብለዉ ጠሩዋት።

ከጥቂት ጊዜ በኋላም አባቷ አረፈ ዕድሜዋም ስድስት ዓመት በሆነ ጊዜ እናቷ ወደ ደናግል ገዳም ከእርሷ ጋር ወሰደቻት ይህችም ቅድስት ደናግሉ ሲያገለግሉ አይታ ስለ ምን እንዲህ ደክማችሁ ትሠራላችሁ አለቻቸው እነርሱም ክብር ይግባውና ስለ #ክርስቶስ ነው ብለው መለሱላት ወደ ዲያቆናዊትም ሒዳ ያመነኲሷት ዘንድ ለመነች እነርሱም ለእናቷ ነገሩዋት እናቷም ለዲያቆናዊተዋ ሰጠቻት በደናግሉም ሁሉ ዘንድ አደራ ሰጠቻት ከጥቂትም ቀኖች በኋላ እናቷ አረፈችና ቀበሩዋት።

ከዚህም በኋላ ቅድስት ኢዮጰራቅስያ የምንኲስና ልብስን ለበሰች በጾም በጸሎትና በሰጊድ ተጋድሎ ጀመረች በየሰባት ቀንም ትጾም ነበር ሰይጠንም በእርሷ ላይ ቀንቶ ሊፈትናት ጀመረ ወደ ውኃ ውስጥ እርስዋን የሚጥልበት ጊዜ ነበር እንጨትም ስትፈልጥ በምሳር የሚአቊስልበት ጊዜ ነበር። የፈላ ውኃም በላይዋ የሚያፈሰበት ጊዜ ነበር ነገር ግን ምንም ምን የጐዳት የለም።

ለደነግሎችም ስታገለግል ብዙ ዘመናት ኖረች ምንም አትታክትም ነበር በምድርም ላይ አትተኛም መላዋን ሌሊት ቁማ በጸሎት ታድር ነበር እንጂ ከገድሏ ጽናትም የተነሣ ደናግሉ እስከሚያደንቁ ድረስ አርባ ቀን ቁማ ትፈጽም ነበር።

ከዚህም በኋላ #ጌታችን በሽተኞችን በማዳን አጋንንትን በማስወጣት የዕውሮችን ዐይን በመግለጥ የአንካሶችንም እግር በማስተካከል ድንቆችንና ተአምራቶችን በእጆቿ ገለጠ።

ዲያቆናዊት ኢዮኤልያም ለኢዮጰራቅስያ መጸሐፍትንና የምንኵስናንም ሥርዓት አስተማረቻት በሥራም ሁሉ ትሳተፋት ነበር እጅግም ይፋቀሩ ነበር እርሷም ሰማያዊ ሙሽራ ወደአለበት የመንግሥት አዳራሽ የማያልቅ ተድላ ደስታም ወደአለበት ኢዮጵራቅስያን ሲያወጧት ራእይን አየች።

በነቃችም ጊዜ ለደናግል ነገረቻቸው ወደርሷ ሲሔዱም በትኩሳት በሽታ ታማ አገኟት ስለእነርሱም እንድትጸልይ ለመኑዋት እርሷም ደግሞ በጸሎታቸው እንዲአስቧት ለመነቻቸው ያን ጊዜም ጸሎት አድርጋ መረቀቻቸውና በሰላም አረፈች በእናቷም መቃብር ውስጥ ቀበሩዋት።

ወዳጅዋ ኢዮኤልያም ወደ መቃብርዋ ሒዳ ጸለየችና በሦስተኛው ቀን አረፈች ከእርሷም ጋር ተቀበረች።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ነሐሴ_2)
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ነሐሴ_2_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ጢሞቴዎስ 2
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁸ እንግዲህ ወንዶች በስፍራ ሁሉ አለ ቍጣና አለ ክፉ አሳብ የተቀደሱትን እጆች እያነሱ እንዲጸልዩ እፈቅዳለሁ።
⁹-¹⁰ እንዲሁም ደግሞ ሴቶች በሚገባ ልብስ ከእፍረትና ራሳቸውን ከመግዛት ጋር ሰውነታቸውን ይሸልሙ፤ እግዚአብሔርን እንፈራለን ለሚሉት ሴቶች እንደሚገባ፥ መልካም በማድረግ እንጂ በሽሩባና በወርቅ ወይም በዕንቍ ወይም ዋጋው እጅግ በከበረ ልብስ አይሸለሙ።
¹¹ ሴት በነገር ሁሉ እየተገዛች በዝግታ ትማር፤
¹² ሴት ግን በዝግታ ትኑር እንጂ ልታስተምር ወይም በወንድ ላይ ልትሰለጥን አልፈቅድም።
¹³ አዳም ቀድሞ ተፈጥሮአልና፥ በኋላም ሔዋን ተፈጠረች።
¹⁴ የተታለለም አዳም አይደለም፥ ሴቲቱ ግን ተታልላ በመተላለፍ ወደቀች፤
¹⁵ ነገር ግን በእምነትና በፍቅር በቅድስናም ራሳቸውን እየገዙ ቢኖሩ በመውለድ ትድናለች።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ጴጥሮስ 3
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹-² እንዲሁም፥ እናንተ ሚስቶች ሆይ፥ ከባሎቻችሁ አንዳንዱ ለትምህርት የማይታዘዙ ቢኖሩ፥ በፍርሃት ያለውን ንጹሑን ኑሮአችሁን እየተመለከቱ ያለ ትምህርት በሚስቶቻቸው ኑሮ እንዲገኙ ተገዙላቸው።
³ ለእናንተም ጠጕርን በመሸረብና ወርቅን በማንጠልጠል ወይም ልብስን በመጎናጸፍ በውጭ የሆነ ሽልማት አይሁንላችሁ፥
⁴ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ የዋህና ዝግተኛ መንፈስ ያለውን የማይጠፋውን ልብስ ለብሶ የተሰወረ የልብ ሰው ይሁንላችሁ።
⁵ እንዲህ በቀድሞ ዘመን በእግዚአብሔር ተስፋ ያደረጉት ቅዱሳት ሴቶች ደግሞ ለባሎቻቸው ሲገዙ ተሸልመው ነበርና፤
⁶ እንዲሁም ሣራ ለአብርሃም፦ ጌታ ብላ እየጠራችው ታዘዘችለት፤ እናንተም ከሚያስደነግጥ ነገር አንዳች እንኳ ሳትፈሩ መልካም ብታደርጉ ልጆችዋ ናችሁ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 16
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹³ በሰንበት ቀንም ከከተማው በር ውጭ የጸሎት ስፍራ በዚያ መሆኑን ስላሰብን ወደ ወንዝ አጠገብ ወጣን፤ ተቀምጠንም ለተሰበሰቡት ሴቶች ተናገርን።
¹⁴ ከትያጥሮን ከተማም የመጣች ቀይ ሐር ሻጭ እግዚአብሔርን የምታመልክ ልድያ የሚሉአት አንዲት ሴት ትሰማ ነበረች፤ ጳውሎስም የሚናገረውን ታዳምጥ ዘንድ ጌታ ልብዋን ከፈተላት።
¹⁵ እርስዋም ከቤተ ሰዎችዋ ጋር ከተጠመቀች በኋላ፦ በጌታ የማምን እንድሆን ከፈረዳችሁልኝ፥ ወደ ቤቴ ገብታችሁ ኑሩ ብላ ለመነችን፤ በግድም አለችን።
¹⁶ ወደ ጸሎት ስፍራም ስንሄድ፥ የምዋርተኝነት መንፈስ የነበረባት ለጌቶችዋም እየጠነቈለች ብዙ ትርፍ ታመጣ የነበረች አንዲት ገረድ አገኘችን።
¹⁷ እርስዋ ጳውሎስንና እኛን እየተከተለች፦ የመዳንን መንገድ የሚነግሩአችሁ እነዚህ ሰዎች የልዑል አምላክ ባሪያዎች ናቸው ብላ ትጮኽ ነበር።
¹⁸ ይህንም እጅግ ቀን አደረገች። ጳውሎስ ግን ተቸገረና ዘወር ብሎ መንፈሱን፦ ከእርስዋ እንድትወጣ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አዝሃለሁ አለው፤ በዚያም ሰዓት ወጣ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ነሐሴ_2_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"ወይወስዱ ለንጉሥ ደናግል ድኅሬሃ። ወቢጻሂ ይወስዱ ለከ። ወይወስድዎን በትፍሥሕት ወበኃሤት"። መዝ 44፥14-15
"በኋላዋ ደናግሉን ለንጉሥ ይወስዳሉ፥ ባልንጀሮችዋንም ወደ አንተ ያቀርባሉ፤
በደስታና በሐሴት ይወስዱአቸዋል፥ ወደ ንጉሥ እልፍኝም ያስገቡአቸዋል"። መዝ 44፥14-15
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ነሐሴ_2_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ዮሐንስ 8
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ ኢየሱስ ግን ወደ ደብረ ዘይት ሄደ።
² ማለዳም ደግሞ ወደ መቅደስ ደረሰ ሕዝቡም ሁሉ ወደ እርሱ መጡ። ተቀምጦም ያስተምራቸው ነበር።
³ ጻፎችና ፈሪሳውያንም በምንዝር የተያዘችን ሴት ወደ እርሱ አመጡ በመካከልም እርሱዋን አቁመው፦
⁴ መምህር ሆይ፥ ይህች ሴት ስታመነዝር ተገኝታ ተያዘች።
⁵ ሙሴም እንደነዚህ ያሉት እንዲወገሩ በሕግ አዘዘን፤ አንተስ ስለ እርስዋ ምን ትላለህ? አሉት።
⁶ የሚከሱበትንም እንዲያገኙ ሊፈትኑት ይህን አሉ። ኢየሱስ ግን ጐንበስ ብሎ በጣቱ በምድር ላይ ጻፈ፤
⁷ መላልሰው በጠየቁት ጊዜ ግን ቀና ብሎ፦ ከእናንተ ኃጢአት የሌለበት አስቀድሞ በድንጋይ ይውገራት አላቸው።
⁸ ደግሞም ጐንበስ ብሎ በጣቱ በምድር ላይ ጻፈ።
⁹ እነርሱም ይህን ሲሰሙ ሕሊናቸው ወቀሳቸውና ከሽማግሌዎች ጀምረው እስከ ኋለኞች አንድ አንድ እያሉ ወጡ፤ ኢየሱስም ብቻውን ቀረ ሴቲቱም በመካከል ቆማ ነበረች።
¹⁰ ኢየሱስም ቀና ብሎ ከሴቲቱ በቀር ማንንም ባላየ ጊዜ፦ አንቺ ሴት፥ እነዚያ ከሳሾችሽ ወዴት አሉ? የፈረደብሽ የለምን? አላት።
¹¹ እርስዋም፦ ጌታ ሆይ፥ አንድ ስንኳ አለች። ኢየሱስም፦ እኔም አልፈርድብሽም፤ ሂጂ ከአሁንም ጀምሮ ደግመሽ ኃጢአት አትሥሪ አላት።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #እመቤታች_የማርያም_ቅዳሴ ነው። መልካም የጾም ጊዜና በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ነሐሴ 3

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ነሐሴ ሦስት በዚህች ቀን በገድል የተጠመደ መስተጋድል የከበረ #አባ_ስምዖን_ዘዓምድ አረፈ፣ ከመንግሥት ወገን የሆነች #ቅድስት_ሶፍያ አረፈች።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ታላቁ_አባ_ስምዖን_ዘዓምድ

ነሐሴ ሦስት በዚህች ቀን በገድል የተጠመደ መስተጋድል የከበረ አባ ስምዖን ዘዓምድ አረፈ። ለዚህም ቅዱስ ስድስት ዓመት በሆነው ጊዜ አባቱ የበጎቹ ጠባቂ አደረገው። ወደ ቤተ ክርስቲያንም በመሔድ ሁል ጊዜ ቅዱሳት መጻሕፍትን ይሰማ ነበር የ #እግዚአብሔርም ቸርነት አነሳሥቶት ወደ አንድ ገዳም ሒዶ መነኰሰ ብዙ ዘመናትም በገድል ተጠምዶ ሲጋደልና ሰውነቱን ሲያስጨንቅ ኖረ።

ከዚህም በኋላ ገመዱ ሥጋውን ቆርጦ እስቲገባ ድረስ በወገቡ ላይ ገመድን አሠረ። ሥጋውም ተልቶ ከእርሱ ክፉ ሽታ ይወጣ ነበር ስለ ክፉ ሽታውም መነኰሳቱ አዘኑ ተጸየፉትም ወደ አበ ምኔቱም ተሰብስበው ይህን መነኰስ ስምዖንን ከእኛ ዘንድ ካላወጣኸው አለዚያ አንተን ትተን ወደሌላ እንሔዳለን አሉት እርሱም ምን አደረገ አላቸው እነርሱም ጥራውና አንተ ራስህ እይ አሉት።

ጠርቶትም መጥቶ በፊቱ በቆመ ጊዜ ደም ከመግል ጋራ በእግሮቹ ላይ ሲፈስ አየ አበ ምኔቱንም እጅግ አስጨነቀው። ልብሶቹንም ገልጦ በሥጋው ውስጥ የገባውን ያንን ገመድ አየው አበ ምኔቱም በእርሱ ላይ ተቆጥቶ ይህን ታደርግ ዘንድ እንዴት ደፈርክ አለው በታላቅ ድካምም ያንን ገመድ ከሥጋው ውስጥ አወጡት ቍስሉም እስከሚድን መድኃኒት እያደረጉለት ኃምሳ ቀኖች ያህል ኖረ።

ከዚህም በኋላ አበ ምኔቱ እንዲህ አለው ልጄ ስምዖን ሆይ እንግዲህስ ወደ ፈለግኸው ቦታ ሒድ ከዚያም ወጥቶ ሔደ በደረቅ ጕድጓድ ውስጥም ገብቶ ከእባቦችና ከጊንጦች ጋራ ኖረ።

ከዚህም በኋላ አገልጋዩ ስምዖንን ለምን ሰደድከው አሁንም ፈልገህ መልሰው በፍርድ ቀን እርሱ ከአንተ ይሻላልና ብሎ ሲገሥጸው አበ ምኔቱ ራእይን አየ። አባ ስምዖንንም ከገዳሙ ስለመውጣቱ ገሠጸው።

በነጋም ጊዜ አበ ምኔቱ ራእይን እንዳየ ስለ አባ ስምዖንም እንደገሠጸው ለመነኰሳቱ ነገራቸው ወንድሞችም ደንግጠው እጅግ አዘኑ እስከምታገኙትም ሔዳችሁ በቦታው ሁሉ ፈልጉት አላቸው ሔደውም ፈለጉት ግን አላገኙትም። ከዚህም በኋላ መብራትን አብርተው ወደ ጕድጓድ ውስጥ ገቡ ያለ መብልና መጠጥም ከእባቦችና ከጊንጦች ጋራ ተቀምጦ አዩት።

ገመድም አውረዱለትና ከዚያ አወጡት በፊቱም ሰግደው በአንተ ላይ ያደረግነውን በደላችንን ይቅር በለን አሉት እኔንም ስለ አሳዘንኳችሁ ይቅር በሉኝ አላቸው። ከዚህም በኋላ ወደ ገዳማቸው ወሰዱት በብዙ ገድልም ተጠምዶ ሲያገለግል ኖረ።

ከዚህም በኋላ ከዚያ ገዳም በሥውር ወጥቶ ወደ አንዲት ዐለት ቋጥኝ ደረሰ። በእርስዋም ላይ ሳያረፍና ሳይተኛ ስልሳ ቀን ቆመ። ከዚህም በኋላ የ #እግዚአብሔር መልአክ ስለ ብዙ ሰዎች ድኅነት #እግዚአብሔር እንደ ጠራው ነገረው። ከዚያም ሔዶ ቁመቱ ሠላሳ ክንድ የሚሆን የድንጋይ ምሰሶ አገኘ ድንቅ ተአምራትን እያደረገ በሽተኞችንም እየፈወሰ ወደርሱ የሚመጡትንም እያስተማረ ዐሥራ ሁለት ዓመት በድንጋይ ምሰሶው ላይ ቆመ።

አባቱም ፍልጎት ነበር ግን ሳያየው ሞተ እናቱ ግን ወሬውን ሰምታ ከብዙ ዘመናት በኋላ ወደርሱ መጣች በድንጋይ ምሰሶውም ላይ ቁሞ አገኘችው አይታውም አለቀሰች ከድንጋይ ምሰሶውም በታች ተኛች። ቅዱስ ስምዖንም #ጌታችን በጎ ነገርን ያደርግላት ዘንድ ስለርሷ ለመነ ያን ጊዜም እንደተኛች አረፈችና ከደንጊያው ምሰሶ በታች ቀበሩዋት።

ሰይጣንም በእርሱ ላይ ቀንቶ እግሩን መታው ከእግሩ ትል እየወደቀ በአንዲት እግሩ ብዙ ዓመታት ኖረ። ከዚህም በኋላ የሽፍቶች አለቃ ወደርሱ መጥቶ ንስሐ ገባ ጥቂት ቀኖችም ኑሮ አረፈ በጸሎቱም ሕይወትን ወረሰ። ወደርሱ ስለሚመጡ ብዙ ሕዝቦችም የውኃ ጥማት እንዳያስጨንቃቸው ወደ #እግዚአብሔር ለምኖ ከድንጋይ ምሰሶው በታች ውኃን አፈለቀላቸው።

ዳግመኛም ወደ ሌላ ምሰሶ ተዛወረ በእርሱም ላይ እየተጋደለ ሠላሳ ዓመት ኖረ። ብዙዎች አረማውያንንና ከሀድያንን ካስተማራቸውና ወደ ፈጠራቸው #እግዚአብሔር ከመለሳቸው በኋላ ክብር ይግባውና ወደ ወደደው #ክርስቶስ ሔደ በሰላምም አርፎ የዘላለም ሕይወትን ወረሰ።

ከዚህም በኋላ የአንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ አባ ስምዖን እንዳረፈ በሰማ ጊዜ ካህናትን ዲያቆናትንና የአገሩን መኳንንቶች ከእርሱ ጋራ ይዞ የቅዱስ አባ ስምዖን ሥጋው ወዳለበት ደረሰ በታላቅ ክብርም ተሸክመው እየዘመሩና እያመሰገኑ ወደ እስክንድርያ አድርሰው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አኖሩት ከሥጋውም ድንቆችና ተአምራቶች ታላቅ ፈውስም ተገለጡ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ መስተጋድል ጸሎት ይማረን በረከቱም ትድርሰን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_ሶፍያ_ቡርክትና_ደናግል_ልጆቿ

በዚችም ቀን ከመንግሥት ወገን የሆነች ሶፍያ አረፈች። ለዚችም ቅድስት ብዙ ሀብትና ብዙ ጥሪት ነበራት ክብር ይግባውና ስለ ክርስቶስ ፍቅር የክርስቶስን መከራ መስቀል አንሥታ ትሸከም ዘንድ ከሦስት ሴቶች ልጆቿ ጋራ ወደ ሮም ከተማ ሔደች።

ንጉሥ እንድርያሰኖስም ክርስቲያን እንደ ሆነች አውቆ ከልጆቹ ጋራ ወደ አደባባይ አስቀረባትና ስለ ሀገርዋና ስለ ስሟ ጠየቃት እርሷም የሚቀደመው ስሜ ክርስቲያን ነኝ ወላጆቼ ያውጡልኝ ስም ሶፊያ ነው እኔም በኢጣልያ ባለ ብዙ ወገን ነኝ ክብር ይግባውና በ #ክርስቶስ ፈቃድም ልጆቼን መሥዋዕት አድርጌ ላቀርብ ወደ አገርህ መጣሁ አለችው። ከዚህም በኋላ የከዳተኛው ንጉሥ ሥቃዩ እንዳያስፈራቸው ልጆቿን አበረታቻቸው።

ምስክርነታቸውንም ፈጽመው ከሞቱ በኋላ ገንዛ ከሮሜ ከተማ ውጭ ቀበረቻቸው።

በሦስተኛውም ቀን መታሰቢያቸውን ታደርግ ዘንድ ልጆቿ ወደ ተቀበሩበት ከብዙዎች ከከተማው ሴቶች ጋራ ሔደች እንዲህ ብላም ጸለየች አክሊላትን የተቀዳጃችሁ የምታምሩ ፍጹማት የሆናችሁ ልጆቼ ሆይ እኔንም ከእናንተ ጋራ ውሰዱኝ ይህንንም እንዳለች ወዲያውኑ አረፈች ከልጆቿም ጋር ተቀበረች።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ነሐሴ_3)
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ነሐሴ_3_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ተሰሎንቄ 3
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ ስለዚህ ወደ ፊት እንታገሥ ዘንድ ባልተቻለን ጊዜ፥ በአቴና ብቻችንን ልንቀር በጎ ፈቃዳችን ሆነ።
² ስለ እምነታችሁም እንዲያጸናችሁና እንዲመክራችሁ ወንድማችንን የእግዚአብሔርንም አገልጋይ ከእኛ ጋርም አብሮ በክርስቶስ ወንጌል የሚሠራውን ጢሞቴዎስን ላክነው፤
³ በዚህ መከራ ማንም እንዳይናውጥ፥ ለዚህ እንደ ተመረጥን ራሳችሁ ታውቃላችሁና።
⁴ በእውነት ከእናንተ ጋር ሳለን፥ መከራ እንቀበል ዘንድ እንዳለን አስቀድመን እንነግራችሁ ነበር፤ እንዲሁም ደግሞ ሆነ፥ ይህንም ታውቃላችሁ።
⁵ ስለዚህ እኔ ደግሞ ወደ ፊት እታገሥ ዘንድ ባልተቻለኝ ጊዜ፦ ፈታኝ ምናልባት ፈትኖአቸዋል ድካማችንም ከንቱ ሆኖአል ብዬ እምነታችሁን ለማወቅ ላክሁ።
⁶ አሁን ግን ጢሞቴዎስ ከእናንተ ዘንድ ወደ እኛ መጥቶ ስለ እምነታችሁና ስለ ፍቅራችሁ የምስራች ብሎ በነገረን ጊዜ፥ እኛም እናያችሁ ዘንድ እንደምንናፍቅ ታዩን ዘንድ እየናፈቃችሁ ሁልጊዜ በመልካም እንደምታስቡን በነገረን ጊዜ፥
⁷ ስለዚህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ በእምነታችሁ በኩል በችግራችንና በመከራችን ሁሉ ስለ እናንተ ተጽናናን፤
⁸ እናንተ በጌታ ጸንታችሁ ብትቆሙ፥ አሁን በሕይወት እንኖራለንና።
⁹-¹⁰ ፊታችሁን ልናይ በእምነታችሁም የጎደለውን ልንሞላበት ሌሊትና ቀን ከመጠን ይልቅ እየጸለይን በአምላካችን ፊት ከእናንተ የተነሣ ስለምንደሰተው ደስታ ሁሉ፥ ለእግዚአብሔር በእናንተ ምክንያት ምን ያህል ምስጋና እናስረክብ ዘንድ እንችላለን?
¹¹ አምላካችንና አባታችን ራሱ ጌታችንም ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ እናንተ መንገዳችንን ያቅና፤
¹²-¹³ ጌታችንም ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅዱሳኑ ሁሉ ጋር ሲመጣ፥ በአምላካችንና በአባታችን ፊት በቅድስና ነቀፋ የሌለበት አድርጎ ልባችሁን ያጸና ዘንድ፥ እኛ ደግሞ ለእናንተ እንደምንሆን ጌታ እርስ በእርሳችሁ ያላችሁን ለሁሉም የሚሆን ፍቅራችሁን ያብዛ ይጨምርም።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ጴጥሮስ 3
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁰ ሕይወትን ሊወድ መልካሞችንም ቀኖች ሊያይ የሚፈልግ ሰው፥ መላሱን ከክፉ ከንፈሮቹንም ተንኰልን ከመናገር ይከልክል፤
¹¹ ከክፉ ፈቀቅ ይበል፥ መልካምንም ያድርግ፥ ሰላምን ይሻ ይከተለውም፤
¹² የጌታ ዓይኖች ወደ ጻድቃን ናቸውና፥ ጆሮዎቹም ለጸሎታቸው ተከፍተዋል፥ የጌታ ፊት ግን ክፉ ነገርን በሚያደርጉ ላይ ነው።
¹³ በጎንም ለማድረግ ብትቀኑ የሚያስጨንቃችሁ ማን ነው?
¹⁴ ነገር ግን ስለ ጽድቅ እንኳ መከራን ብትቀበሉ ብፁዓን ናችሁ። ማስፈራራታቸውንም አትፍሩ አትናወጡም፥
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 14
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²⁰ ደቀ መዛሙርት ግን ከበውት ሳሉ፥ ተነስቶ ወደ ከተማ ገባ። በነገውም ከበርናባስ ጋር ወደ ደርቤን ወጣ።
²¹-²² በዚያችም ከተማ ወንጌልን ሰብከው እጅግ ደቀ መዛሙርትን ካደረጉ በኋላ፥ የደቀ መዛሙርትን ልብ እያጸኑ በሃይማኖትም ጸንተው እንዲኖሩ እየመከሩና፦ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በብዙ መከራ እንገባ ዘንድ ያስፈልገናል እያሉ፥ ወደ ልስጥራን ወደ ኢቆንዮንም ወደ አንጾኪያም ተመለሱ።
²³ በየቤተ ክርስቲያኑም ሽማግሌዎችን ከሾሙላቸው በኋላ ጦመውም ከጸለዩ በኋላ፥ ላመኑበት ለጌታ አደራ ሰጡአቸው።
²⁴ በጲስድያም አልፈው ወደ ጵንፍልያ መጡ፥
²⁵ በጴርጌንም ቃሉን ከተናገሩ በኋላ ወደ አጣልያ ወረዱ፥
²⁶ ከዚያም ስለ ፈጸሙት ሥራ ለእግዚአብሔር ጸጋ አደራ ወደ ተሰጡበት ወደ አንጾኪያ በመርከብ ሄዱ።
²⁷ በደረሱም ጊዜ ቤተ ክርስቲያኑን ሰብስበው እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ያደረገውን ሁሉ ለአሕዛብም የሃይማኖትን ደጅ እንደ ከፈተላቸው ተናገሩ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ነሐሴ_3_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"ወይሰግዳ ሎቱ አዋልደ ጢሮስ በአምኃ። ወለገጽኪ ይትመሀለሉ ኵሎሙ አሕዛብ ብዑላነ ምድር። ኵሉ ክብራ ለወለተ ንጉሥ፡ሐሴቦን"። መዝ 44፥12-13።
"የጢሮስ ሴቶች ልጆች እጅ መንሻን ይዘው ይሰግዱለታል። የምድር ባለጠጎች አሕዛብ በፊትህ ይማለላሉ። ለሐሴቦን ንጉሥ ልጅ ሁሉ ክብርዋ ነው፤ ልብስዋ የወርቅ መጐናጸፊያ ነው"። መዝ 44፥12-13።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ነሐሴ_3_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሉቃስ 18
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁹ ጻድቃን እንደ ሆኑ በራሳቸው ለሚታመኑና ሌሎቹን ሁሉ በጣም ለሚንቁ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፥
¹⁰ እንዲህ ሲል፦ ሁለት ሰዎች ሊጸልዩ ወደ መቅደስ ወጡ፥ አንዱ ፈሪሳዊ ሁለተኛውም ቀራጭ።
¹¹ ፈሪሳዊም ቆሞ በልቡ ይህን ሲጸልይ፦ እግዚአብሔር ሆይ፥ እንደ ሌላ ሰው ሁሉ፥ ቀማኞችና ዓመፀኞች አመንዝሮችም፥ ወይም እንደዚህ ቀራጭ ስላልሆንሁ አመሰግንሃለሁ፤
¹² በየሳምንቱ ሁለት ጊዜ እጦማለሁ፥ ከማገኘውም ሁሉ አሥራት አወጣለሁ አለ።
¹³ ቀራጩ ግን በሩቅ ቆሞ ዓይኖቹን ወደ ሰማይ ሊያነሣ እንኳ አልወደደም፥ ነገር ግን፦ አምላክ ሆይ፥ እኔን ኃጢአተኛውን ማረኝ እያለ ደረቱን ይደቃ ነበር።
¹⁴ እላችኋለሁ፥ ከዚያ ይልቅ ይህ ጻድቅ ሆኖ ወደ ቤቱ ተመለሰ፤ ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳልና፥ ራሱን ግን የሚያዋርድ ከፍ ይላል።
¹⁵ እንዲዳስሳቸውም ሕፃናትን ደግሞ ወደ እርሱ አመጡ፤ ደቀ መዛሙርቱም አይተው ገሠጹአቸው።
¹⁶ ኢየሱስ ግን ሕፃናትን ወደ እርሱ ጠርቶ፦ ሕፃናት ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ ተዉአቸው አትከልክሉአቸውም፤ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደ እነዚህ ላሉት ናትና።
¹⁷ እውነት እላችኋለሁ፥ የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደ ሕፃን የማይቀበላት ሁሉ ከቶ አይገባባትም አለ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #እመቤታች_የማርያም_ቅዳሴ ነው። መልካም የጾም ጊዜና በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
2024/09/22 17:25:22
Back to Top
HTML Embed Code: