Telegram Web Link
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

✞✞✞ እንኩዋን ለሐዋርያው #ቅዱስ_ታዴዎስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞

+"+ #ቅዱስ_ታዴዎስ_ሐዋርያ +"+

=>#ቅዱሳን_ሐዋርያት አባቶቻችን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በተከተሉበት ሰዓት እድሜአቸው በ3 ደረጃ የተከፈለ እንደ ነበር የቤተ ክርስቲያን ትውፊት ያሳያል::

¤እንደ #ዮሐንስ_ወንጌላዊ ያሉት በ20ዎቹ ውስጥ:
¤#ቅዱስ_ታዴዎስን የመሰሉት ደግሞ በ30ና በ40ዎቹ ውስጥ የነበሩ ሲሆን
¤እነ #ቅዱስ_ዼጥሮስ ደግሞ በ50ዎቹ ውስጥ የሚገኙ ነበሩ:: ደቀ መዛሙርቱ ከወጣቶችም: ከጐልማሶችም ከአረጋውያንም የተዋቀሩ ነበሩ ማለት ነው::

+ቅዱስ ታዴዎስ በቀደመ ስሙ #ልብድዮስ ይባል የነበረ ሲሆን በአንዳንድ መጻሕፍት ውስጥ (በተለይ በምሥራቅ ኦርቶዶክሶች) #ስምዖን እና #ይሁዳ እየተባለም ተጠርቷል::

+ቅዱሱ ጌታችን ተከትሎ:
¤ከ12ቱ አንዱ ሆኖ በፈጣሪው ተመርጦ:
¤3 ዓመት ከ3 ወር ከጌታ እግር ተምሮ:
¤በዕርገቱ ተባርኮ:
¤በበዓለ ሃምሳም 71 ልሳናትን ተቀብሎ:
¤#ሐዋርያት ዕጣ ሲጣጣሉ የበኩሉን አሕጉረ ስብከት ተካፍሎ ዓለምን ዙሯል::

+ቅዱስ ታዴዎስ አንድ ቀን ከሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ዼጥሮስ ጋር ወደ አንዲት ሃገር ይገባሉ:: ታዲያ ለቀናት ያለ ምግብ ወንጌልን ሲሰብኩ ቆይተው ነበርና ደጐቹ ሐዋርያት ራባቸው:: ወደ ከተማዋ ሳይገቡ አንድ ሽማግሌ ሲያርስ አይተው ሰላምታን ሰጡትና "እባክህ እርቦናልና አብላን" አሉት:: እርሱም ምንም ወገኑ ከአሕዛብ ቢሆነ አሳዝነውት በሬዎቹን ሳይፈታ እየሮጠ ሄደ::

+ያን ጊዜ ቅዱስ ታዴዎስ ሊቀ ሐዋርያትን "እርሱ እስኪመጣ ለምን አናርስም" አለው:: 2ቱ ተነስተው ታዴዎስ ሞፈር: ዼጥሮስ ደግሞ ስንዴውን ያዘ:: ቅዱሳኑ እየዘሩ ያረሱት ሰውየው ምግብ ይዞ እስኪመጣ አድጐ: አፍርቶ: እሸት ሆኖ ቆየው::

+ገበሬው የተደረገውን ተአምራት ባየ ጊዜ ደነገጠ:: ሊያመልካቸውም ወደደ:: እነርሱ ግን "እኛ የልዑል ባሮች ነን" ብለው በክርስቶስ ማመንን አስተማሩት:: "ልከተላችሁ" ቢላቸው "የለም! ከእሸቱ ይዘህ ወደ ከተማ ግባና ራት አዘጋጅልን:: እኛ እንመጣለን" አሉት::

+እርሱ ወደ ቤቱ ሲመለስ አሕዛብ ነገሩን ተረዱ:: ተሠብሥበውም "እነዚህ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እሳትም ሰይፍም አይበግራቸውም" ብለው ወደ ከተማ እንዳይገቡ ከበሩ ላይ ራቁቷን የሆነች ዘማ አቆሙ::

+ቅዱስ ታዴዎስ ገና ከርቀት ስላያት ቀና ብሎ #ቅዱስ_ሚካኤልን "እርዳን" አለው:: ሊቀ መላእክትም ድንገት ወርዶ ዘማዋን ሴት በጸጉሯ በዓየር ላይ ሰቀላት:: በከተማዋ ያሉ አሕዛብም ይህንና ሌሎች ተአምራትን አይተው ሁሉም በጌታችን አምነው ተጠመቁ:: ለሐዋርያቱም ሰገዱላቸው::

+አንድ ቀን ግን አንድ ጐረምሳ ባለ ጠጋ ቅዱስ ታዴዎስ "ሀብት ንብረታችሁን መጽውቱ" ሲል ሰምቶት ዘሎ የሐዋርያውን ጉሮሮ አንቆ ከሞት አድርሶት ነበር:: ያን ጊዜ "ጌታየ! ለካ ሀብታም ከሚጸድቅ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀላል ያልክ ለዚህ ነው!" ብሏል:: ባለ ጠጋው "እንዴት ይሆናል?" ቢለው መርፌ አሠርቶ ግመሉን ከነ ባለቤቱ በሰው ሁሉ ፊት 3 ጊዜ አሳልፎታል::

+ያም ማለት ጌታችን እንዳለው "በሰው ዘንድ የማይቻለው በእግዚአብሔር ዘንድ ይቻላል::" (ማር. 10:23) በዚህ ምክንያትም ያ ክፉ ባለ ጸጋ ወደ ልቡናው ተመልሶ ከቅዱስ ታዴዎስ እግር ሥር ወደቀ:: ሐዋርያውም አለው "ሀብትህን ለነዳያን ስጥ:: ይህንንም በትር እንካና እየዞርክ ወንጌለ መንግስትን ስበክ::" ባለ ጸጋውም የተባለውን ሁሉ ፈጽሞ በክብር ዐርፏል::

+ቅዱሳኑ ታዴዎስና ዼጥሮስ ግን በሃገሪቱ አብያተ ክርስቲያናትን አንጸው: ካህናትን ሹመው: ያቺን በዓየር ላይ የሰቀሏትን ዘማም የተባረከች መበለት አድርገው: በሌሎች አሕጉራት ወንጌልን ለማዳረስ ወጥተዋል::

+ቅዱስ ታዴዎስም እስከ እርጅናው ድረስ ለወንጌል ሲተጋ ኑሯል:: ጌታችንም በየጊዜው በአካል እየተገለጸ አጽናንቶታል:: ከብዙ የድካምና የመከራ ዘመናት በሁዋላም በዚህች ቀን ዐርፏል::

=>ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅዱሱ ሐዋርያ በረከት ይክፈለን::

=>ሐምሌ 2 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ታዴዎስ ሐዋርያ (ከ12ቱ ሐዋርያት)

=>ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት
2.ቅዱስ ኢዮብ ጻድቅ ተአጋሲ
3.ቅዱስ አቤል ጻድቅ
4.ቅዱስ አባ ዻውሊ ገዳማዊ (ታላቁ)
5.ቅዱስ ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ
6.አባ ሕርያቆስ ዘሃገረ ብሕንሳ

=>+"+ ጌታ ኢየሱስም ዘወር ብሎ አይቶ ደቀ መዛሙርቱን "ገንዘብ ላላቸው ወደ እግዚአብሔር መንግስት መግባት እንዴት ጭንቅ ይሆናል!" አላቸው:: ደቀ መዛሙርቱም እነዚህን ቃሎች አደነቁ:: ጌታ ኢየሱስም ደግሞ መልሶ "ልጆች ሆይ! በገንዘብ ለሚታመኑ ወደ #እግዚአብሔር መንግስት መግባት እንዴት ጭንቅ ነው! ባለ ጠጋ ወደ እግዚአብሔር መንግስት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀላል" አላቸው:: +"+ (ማር. 10:23-28)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>

" ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"::/የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ) እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::  አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ /መጽሐፈ ምሥጢር/
https://www.tg-me.com/zikirekdusn
††† እንኳን ለሐዋርያው ቅዱስ መርቄሎስ እና ለነቢዩ ቅዱስ ዕዝራ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱስ መርቄሎስ ሐዋርያ †††

††† ቅዱሱ በነገድ እሥራኤላዊ የሆነ የመጀመሪያው መቶ ክ/ዘመን ሰው ነው:: ጌታችን በመዋዕለ ስብከቱ ሲያስተምር በምሥጢሩና በተአምራቱ ተማርኮ ተከትሎታል:: ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስም ከሰባ ሁለቱ አርድእት አንዱ ይሆን ዘንድ አድሎታል:: ከጌታችን ሕማማትና ስቅለት በፊትም ድውያንን መፈወስና አጋንንትን ማስወጣት ከቻሉ አርድእትም አንዱ ነው::

ቅዱስ መርቄሎስ በበዓለ ሃምሳ ጸጋ መንፈስ ቅዱስን ተቀብሎ ለወንጌል አገልግሎት ተሰማርቷል:: በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ለሰላሳ አራት ዓመታት በማገልገሉ ሐዋርያት ስሙን "ጳውሎስ" ብለውታል:: ጳውሎስ ማለት ብርሃን ማለት ነውና:: ልክ ሳውል "ጳውሎስ" እንደተባለው ማለት ነው::

ስሙ የግብር (በሥራ የሚገኝ) ስም ነው:: በዚህም ምክንያት ዛሬም ድረስ ቤተ ክርስቲያን የምትጠራው "ጳውሎስ የተባለው መርቄሎስ" እያለች ነው::

ቅዱስ መርቄሎስ በ60ዎቹ ዓ/ም አካባቢ ከቅዱስ ጴጥሮስ ጋር በሮም ይሰብክ ነበር:: ኔሮን ቄሳር ሊቀ ሐዋርያትን ዘቅዝቆ ሲሰቅለው የተመለከተና ይህንኑ የጻፈ እርሱ ነበር:: ወታደሮቹ ቅዱስ ጴጥሮስን ገድለውት ሲሔዱ ቅዱስ መርቄሎስ እያነባ ቀርቦ: ችንካሮችንም ነቅሎ: ሊቀ ሐዋርያትን ከተሰቀለበት አወረደው::

በፍጥነት ዋጋው ውድ የሆነ ሽቱ አምጥቶ በቅዱስ ጴጥሮስ ሥጋ ላይ አፈሰሰና በፍቅርና በክብር ሊገንዘው ጀመረ:: በዚህ ጊዜ ሊቀ ሐዋርያት አይኑን ግልጥ አድርጎ መርቄሎስን ተመለከተውና አለው:- "ልጄ! ምነው ለእኔ ይህንን ያሕል ሽቱ አባከንክ?" አለውና ተምልሶ ዐረፈ::

ቅዱስ መርቄሎስም እግዚአብሔርን እያመሰገነ በንጹሕ በፍታ ገንዞ እርሱ በሚያውቀው ቦታ ሠወረው:: ሊቀ ሐዋርያትን በመገነዙ የክብር ክብር ተሰጥቶታል::

ቅዱሱ አሁንም ስብከተ ወንጌልን ቀጠለ:: ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን እርሱም ተይዞ በኔሮን ፊት ቀረበ:: ኔሮን ቄሳር ቅዱስ መርቄሎስን ጠየቀው:: "እንዴት ባለ አሟሟት ልግደልህ? እንደ መምህርሕ ጴጥሮስ ወይስ ሌላ የምትፈልገው ዓይነት አሟሟት አለህ?"

ቅዱስ መርቄሎስ መለሰለት:- "የትኛውም ዓይነት ሞት እኔን አያስፈራኝም:: የምፈልገው ወደ ጌታዬ ቶሎ መሔድ ብቻ ነው::" አለው:: ንጉሡ ኔሮንም ዘቅዝቃችሁ ስቀሉት አላቸው:: ወታደሮቹም በዚህች ዕለት እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ ዘቅዝቀው ሰቅለው ገድለውታል::

††† ቅዱስ ዕዝራ ነቢይ †††

ከክርስቶስ ልደት በፊት በ500 ዓመት አካባቢ የነበረ
¤እሥራኤል ከምርኮ ከተመለሱ በኋላ መጻሕፍት ተቃጥለው ጠፍተው ነበርና ስለ እነሱ አብዝቶ የለመነ
¤ጥበብን ሽቷልና እግዚአብሔር ቅዱስ ዑራኤልን የላከለት
¤በሊቀ መላእክት እጅም ጽዋዐ ልቡናን የጠጣ
¤ብዙ ምሥጢራት የተገለጡለት
¤ለአርባ ቀናት ምግብ ሳይበላ አገልጋዮቹ የጠፉ መጻሕፍትን እየነገራቸው የጻፉለት
¤መጽሐፈ ዕዝራ የተሰኘ መጽሐፍን ያዘጋጀና
¤በብሉይ ኪዳን ከነበሩ ዐበይት ነቢያተ ጽድቅ አንዱ የሆነ ታላቅ የእግዚአብሔር ሰው ነው::

††† ስለ ቅድስናውም ሞትን አልቀመሰም:: በዚህች ዕለት ቅዱሳን መላእክት ብሔረ ሕያዋን ውስጥ አስገብተውታል::

††† እግዚአብሔር ከሐዋርያውና ከነቢዩ በረከትን አይንሳን::

††† ሐምሌ 6 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ መርቄሎስ ሐዋርያ (ከሰባ ሁለቱ አርድእት)
2.ቅዱስ ዕዝራ ነቢይ
3.ቅዱስ በርተሎሜዎስ ሐዋርያ
4.ቅድስት ቴዎዳስያ ሰማዕት
5.ቅድስት ንስተሮኒን ዘኢየሩሳሌም

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ቅድስት ደብረ ቁስቋም
2.አባታችን አዳምና እናታችን ሔዋን
3.አባታችን ኖኅና እናታችን ሐይከል
4.ቅዱስ ኤልያስ ነቢይ
5.ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ
6.ቅዱስ ዮሴፍ አረጋዊ
7.ቅድስት ሰሎሜ
8.አባ አርከ ሥሉስ
9.አባ ጽጌ ድንግል
10.ቅድስት አርሴማ ድንግል

††† "እግዚአብሔርም በቤተ ክርስቲያን አንዳንዶቹን አስቀድሞ ሐዋርያትን: ሁለተኛም ነቢያትን: ሦስተኛም አስተማሪዎችን: ቀጥሎም ተአምራት ማድረግን: ቀጥሎም የመፈወስን ስጦታ: እርዳታንም: አገዛዝንም: የልዩ ልዩ ዓይነት ልሳኖችንም አድርጓል:: ሁሉ ሐዋርያት ናቸውን? ሁሉስ ነቢያት ናቸውን? ሁሉስ አስተማሪዎች ናቸውን? . . . ነገር ግን የሚበልጠውን የጸጋ ስጦታ በብርቱ ፈልጉ::" †††
(፩ቆሮ. ፲፪፥፳፰)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
እግዝእትየ፦

መዝገበ #በረከት
መዝገበ #ቅድሳት
መዝገበ #ንጽሕ
መዝገበ #ርህራሄ
መዝገበ #የዋሃት

✞ባርክኒ በእዴኪ፤ በከመ ባረኪዮ #ለኤፍሬም ፍቁርኪ፤ በበረከተ ወልድኪ ወአቡሁ ወመንፈስ ቅዱስ፡፡

" ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"::/የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ) እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል:: አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ /መጽሐፈ ምሥጢር/
https://www.tg-me.com/zikirekdusn
††† እንኳን ለታላቁ ሊቅና አፈ በረከት ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱስ ማሪ ኤፍሬም ሶርያዊ †††

††† እንደ ቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት ቅዱስ ኤፍሬም የተወለደው ንጽቢን በምትባል የሶርያ ግዛት ውስጥ በ298 / 306 ዓ/ም ነው:: ወላጆቹ በክርስቶስ የማያምኑ አላውያን ነበሩ:: (ምንም አንዳንድ ምንጮች ክርስቲያኖች ነበሩ ቢሉም)

ቅዱሱ ተወልዶ ባደገባት ንጽቢን ጵጵስናን የተሾመ ቅዱስ ያዕቆብ የሚባል ታላቅ ሰው ነበር:: የሰማዕትነት: የሐዋርያነት: የጻድቅነትና የሊቅነት ግብር ያለው አባት ነው:: ታዲያ ቅዱስ ኤፍሬም ይሔ አባት ሁሌ ሲያስተምር ይሰማው ነበርና በስብከቱ ተማርኮ ደቀ መዝሙሩ ለመሆን በቃ::

ቅዱስ ኤፍሬም በቅዱስ ያዕቆብ እጅ ከተጠመቀ በኋላ ሙሉ የወጣትነት ጊዜውን ያሳለፈው በትምሕርት ነው:: የሚገርመው መምሕሩ ቅዱስ ያዕቆብ ዘንጽቢን እመቤታችን ድንግል ማርያምን በፍጹም ልቡ የሚወድና ጠርቷት የማይጠግብ አባት ነውና ለልጁ ለቅዱስ ኤፍሬም ይሕንኑ አጥብቆ አስተምሮታል::

ቅዱስ ኤፍሬም ክርስትናን ሲመረምር የእመቤታችን ፍቅር ይበዛለት ጀመር:: ምክንያቱም እመ ብርሃንን ሳይወዱ ክርስትና የለምና:: እንደ እርሱ የሚወዳት የለም እስኪባል ድረስ ያገለግላት: ይገዛላትም ገባ::

እንዲህ እንደ ዛሬ የድንግል ማርያም ምስጋና በአንደበት እንጂ በመጽሐፍ አይገኝም ነበር:: እርሱ ግን ከወንጌለ ሉቃስ በስድስተኛው ወርን (ይዌድስዋን) እና ጸሎተ ማርያምን(ታዐብዮን) አውጥቶ በየዕለቱ በዕድሜዋ ልክ ስልሳ አራት ስልሳ አራት ጊዜ ያመሰግናት ነበር::

በእንዲህ ያለ ግብር እያለ አርዮስ በመካዱ እርሱን ለማውገዝና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ለማጽናት በ317 (325) ዓ.ም ሦስት መቶ አሥራ ስምንቱ ሊቃውንት በኒቅያ ሲሰበሰቡ አንዱ መምሕረ ኤፍሬም ቅዱስ ያዕቆብ ነበር:: በዚህ ምክንያት ቅዱስ ኤፍሬም ከሊቃውንቱ ትምሕርትና በረከትን አግኝቷል::

ከጉባዔ መልስ መንገድ ላይ በራዕይ የብርሃን ምሰሶ አይቶ "ጌታ ሆይ! ምንድን ነው?" ብሎ ቢጠይቅ "ይሕማ ታላቁ ቅዱስ ባስልዮስ ነው::" አለው:: እርሱም መምሕሩን ቅዱስ ያዕቆብን ተሰናብቶ ወደ ቅዱስ ባስልዮስ (ቂሣርያ) ወረደ:: ተገናኝተውም በአንድ ሌሊት ቋንቋ ተገልጦላቸው ሲጨዋወቱ አድረዋል::

በቦታው ብዙ ተአምራት ተደርጓል:: ቅዱስ ኤፍሬም ከታላቁ ባስልዮስ ከተማረ በኋላ ሃገረ ስብከት ተሰጥቶት ያስተምር ጀመር:: ሁል ጊዜ ታዲያ ጸሎቱ ይሔው ነበር:: "እመቤቴ ሆይ! ምስጋናሽ እንደ ሰማይ ከዋክብት: እንደ ባሕር አሽዋ በዝቶልኝ: እንደ እንጀራ ተመግቤው: እንደ ውኃ ጠጥቼው: እንደ ልብስም ተጐናጽፌው" እያለ ይመኝ ነበር::

አፍጣኒተ ረድኤት: ፈጻሚተ ፈቃድ እመ ብርሃንም በገሃድ ተገልጻ የልቡን ፈቃድ ፈጸመችለት:: ዛሬ ጸጋ በረከት የምናገኝበትን ውዳሴ ማርያምን ደረሰላት:: ሲደርስላትም እርሷ አእላፍ መላእክትን: ጻድቃን ሰማዕታትን አስከትላ ወርዳ: በፊቱም ተቀምጣ ሲሆን እርሱ ደግሞ ባጭር ታጥቆ: በፊቷ ቆሞ: በመንፈስ ቅዱስም ተቃኝቶ ነው::

ውዳሴዋን በሰባት ቀናት ከደረሰላት በኋላ በብርሃን መስቀል ባርካው: ሊቀ ሊቃውንትም እንዲሆን ምሥጢር ገልጣለት ዐረገች:: ከዚህ በኋላ በምሥጢር ባሕር ውስጥ ዋኝቶ አሥራ አራት ሺህ ድርሰቶችንም ደርሷል:: ዛሬ ሶርያ ውስጥ የምንሰማውን ዜማም የደረሰው ይህ ቅዱስ ነው::

እንዲያውም አንድ ቀን የምሥጢር ማዕበል ቢያማታው "አሃዝ እግዚኦ መዋግደ ጸጋከ" ብሎ ጸልዩዋል:: (የጸጋህን ማዕበል ያዝልኝ) እንደ ማለት ነው:: ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ በመጨረሻ ሕይወቱ ተክሪት በምትባል ሃገር ኤጲስ ቆጶስ ሆኖ ተሹሟል::

በጣፋጭ ስብከቱ ብዙዎችን ካለማመን መልሷል:: የምዕመናንንም ሕይወት አጣፍጧል:: ለመናፍቃንና ለአርዮሳውያን ግን የማይጋፉት ግድግዳ ሆኖባቸው ኑሯል:: በዘመኑም ብዙ ተጋድሎ አፍርቷል:: ተአምራትንም ሠርቷል:: በተወለደ በስልሳ ሰባት ዓመቱ በ365 (373) ዓ.ም ዐርፎ ተቀብሯል::

††† ቅዱሱ ለሶርያ ብቻ ሳይሆን እመቤታችንን ለምንወድ የዓለም ክርስቲያኖች ሁሉ ሞገሳችን ሆኗል:: ስለዚህም እንዲህ እያልን እንጠራዋለን:-
1.ቅዱስ ኤፍሬም
2.ማሪ ኤፍሬም
3.አፈ በረከት ኤፍሬም
4.ሊቀ ሊቃውንት ኤፍሬም
5.ጥዑመ ልሳን ኤፍሬም
6.አበ ምዕመናን ኤፍሬም
7.ርቱዐ ሃይማኖት ኤፍሬም . . . አባታችን አንተ ነህ::

††† ጽንዕት በድንግልና: ሥርጉት በቅድስና እመቤታችን ለቅዱስ ኤፍሬም የሰጠሽውን ጸጋውን: ክብሩን: አእምሮውን: ለብዎውን በልቡናችን ሳይብን: አሳድሪብን . . . አሜን::

††† ጴጥሮስ ወጳውሎስ †††

††† ዳግመኛ በዚህ ቀን ብርሃናተ ዓለም ጴጥሮስ ወጳውሎስ ይታሠባሉ::

ቅዱሳኑ ሶርያ አካባቢ ውስጥ ወደምትገኝ አንዲት ሃገር ገብተው ሕዝቡን ከንጉሣቸው ጰራግሞስ ጋር አሳምነው አጥምቀዋል:: ነገር ግን እነርሱ ሲወጡ ሰይጣን አስቶት አጥፊ ሰው ወደ መሆን ተመልሶ ንጉሡ ሐዋርያትን አሰቃይቷቸዋል::

ስለ ቅዱሳኑ ግን ፈረሶቹ ሰግደው: በሰው አንደበት ቅድስናቸውን መስክረዋል:: በመጨረሻም ንጉሡን ከነ ሕዝቡና ሠራዊቱ በዓየር ላይ ሰቅለው ንስሐ ሰጥተውታል:: በእነዚህ ተአምራትም ሁሉም አምነው ለከተማዋና ለሕዝቡ ድኅነት ተደርጓል::

††† ከአባቶቻችን አበው ሐዋርያት በረከት ይክፈለን::

††† ሐምሌ 15 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ማሪ ኤፍሬም ሶርያዊ (አፈ በረከት)
2.ብርሃናተ ዓለም ቅዱሳን ሐዋርያት ጴጥሮስ ወጳውሎስ
3.አባ ሓርዮንና ደቀ መዛሙርቱ (ሰማዕታት)
4.አባ ፍሬምናጦስ መስተጋድል

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ቂርቆስና እናቱ ኢየሉጣ
2.ቅዱስ ሚናስ (ማር ሚና) ሰማዕት
3.ቅድስት እንባ መሪና
4.ቅድስት ክርስጢና

††† "ለምኑ ይሰጣችሁማል:: ፈልጉ ታገኙማላችሁ:: መዝጊያ አንኳኩ ይከፈትላችሁማል:: የሚለምነው ሁሉ ይቀበላልና:: የሚፈልገውም ያገኛል:: መዝጊያንም ለሚያንኳኳ ይከፈትለታል::" †††
(ማቴ. ፯፥፯)

††† "የጻድቅ አፍ ጥበብን ያስተምራል::
አንደበቱም ፍርድን ይናገራል::
የአምላኩ ሕግ በልቡ ውስጥ ነው::
በእርምጃውም አይሰናከልም::" †††
(መዝ. ፴፯፥፴)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"::/የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ) እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል:: አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ /መጽሐፈ ምሥጢር/
https://www.tg-me.com/zikirekdusn
የደብረ ታቦር መዝሙራት

በደብር በደብረ ታቦር
በደብር በደብረ ታቦር (2)
ታቦር ወአርሞንኤም (4)
ትርጉም፦  በታቦር ተራራ የነበረ አርሞንኤምና ታቦር

በደብር በደብረ ታቦር
በደብር በደብረ ታቦር (2)
ሰባሕኩከ በደብር (4)
ትርጉም፦ በታቦር ተራራ አመሰገንኩህ

በስመ  ዚአከ
በስመ ዚአከ ይትፌሥሑ ዮም (2)
ታቦር ወአርሞንኤም (4)
ትርጉም፦ ታቦርና አርሞንኤም በስምህ ዛሬ ደስ ይላቸዋል

አሐደ ለከ
አሐደ ለከ ወአሐደ ለሙሴ (2)
ወአሐደ ለኤልያስ ንግበር ማኅደረ (4)
ትርጉም፦ አንዱንም ላንተ አንዱንም ለሙሴ (2)
    አንዱንም ለኤልያስ እንስራ ዳስ (4)

ደብረ ታቦር አብርሂ
ደብረ ታቦር አብርሂ ኢየሩሳሌም (2)
 ብርሃንኪ (5) እግዚአብሔር (2)
ትርጉም፦ ብርሃንሽ እግዚአብሔር ነውና የታቦር ተራራ በኢየሩሳሌም አብሪ

ደብር ርጉእ
ደብር ርጉእ ወደብር ጥሉል (2) ለምንት ይትነሥኡ ርጉአን አድባር (2)
ደብር ዘሠምሮ እግዚአብሔር የኀድር ውስቴቶ እግዚአብሔር (2)
ትርጉም፦ የጸኑ ተራሮች ለምን ይነሣሉ? እግዚአብሔር ይህን ተራራ ያድርበት ዘንድ ወደደው በእውነት እግዚአብሔር ያድርበታል።

ወተወለጠ
ወተወለጠ ራእዩ በቅድሜሆሙ ራእዩ በቅድሜሆሙ (2)
ወአልባሲሁኒ ኮነ ፀዓዳ ከመ በረድ (2)
ትርጉም፦ መልኩ በፊታቸው ተለወጠ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ ሆነ

ወይቤ ሠመርክዎ
ወይቤ ሠመርክዎ (2)
ወይቤ ሎቱ ስምዕዎ(4)
ትርጉም፦ ወደድከው እርሱንም ስማው አለ
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ሐምሌ_17_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሮሜ 2
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ ስለዚህ፥ አንተ የምትፈርድ ሰው ሁሉ ሆይ፥ የምታመካኘው የለህም፤ በሌላው በምትፈርድበት ነገር ራስህን ትኰንናለህና፤ አንተው ፈራጁ እነዚያን ታደርጋለህና።
² እንደዚህም በሚያደርጉት ላይ የእግዚአብሔር ፍርድ እውነተኛ እንደ ሆነ እናውቃለን።
³ አንተም እንደዚህ በሚያደርጉ የምትፈርድ ያንም የምታደርግ ሰው ሆይ፥ አንተ ከእግዚአብሔር ፍርድ የምታመልጥ ይመስልሃልን?
⁴ ወይስ የእግዚአብሔር ቸርነት ወደ ንስሐ እንዲመራህ ሳታውቅ የቸርነቱንና የመቻሉን የትዕግሥቱንም ባለጠግነት ትንቃለህን?
⁵ ነገር ግን እንደ ጥንካሬህና ንስሐ እንደማይገባ ልብህ የእግዚአብሔር ቅን ፍርድ በሚገለጥበት በቍጣ ቀን ቍጣን በራስህ ላይ ታከማቻለህ።
⁶ እርሱ ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው ያስረክበዋል፤
⁷ በበጎ ሥራ በመጽናት ምስጋናንና ክብርን የማይጠፋንም ሕይወት ለሚፈልጉ የዘላለምን ሕይወት ይሰጣቸዋል፤
⁸ ለዓመፃ በሚታዘዙ እንጂ ለእውነት በማይታዘዙትና በአድመኞች ላይ ግን ቍጣና መቅሠፍት ይሆንባቸዋል።
⁹ ክፉውን በሚያደርግ ሰው ነፍስ ሁሉ መከራና ጭንቀት ይሆንበታል፥ አስቀድሞ በአይሁዳዊ ደግሞም በግሪክ ሰው፤
¹⁰ ነገር ግን በጎ ሥራ ለሚያደርጉ ሁሉ ምስጋናና ክብር ሰላምም ይሆንላቸዋል፥ አስቀድሞ ለአይሁዳዊ ደግሞም ለግሪክ ሰው።
¹¹ እግዚአብሔር ለሰው ፊት አያዳላምና።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ጴጥሮስ 2
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ እንግዲህ ክፋትን ሁሉ ተንኰልንም ሁሉ ግብዝነትንም ቅንዓትንም ሐሜትንም ሁሉ አስወግዳችሁ፥
²-³ ጌታ ቸር መሆኑን ቀምሳችሁ እንደ ሆነ፥ ለመዳን በእርሱ እንድታድጉ አሁን እንደ ተወለዱ ሕፃናት ተንኰል የሌለበትን የቃልን ወተት ተመኙ።
⁴ በሰውም ወደ ተጣለ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ወደ ተመረጠና ክቡር ወደ ሆነው ወደ ሕያው ድንጋይ ወደ እርሱ እየቀረባችሁ፥
⁵ እናንተ ደግሞ እንደ ሕያዋን ድንጋዮች ሆናችሁ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ደስ የሚያሰኝ መንፈሳዊ መሥዋዕትን ታቀርቡ ዘንድ ቅዱሳን ካህናት እንድትሆኑ መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ተሠሩ።
⁶ በመጽሐፍ፦ እነሆ፥ የተመረጠና የከበረን የማዕዘን ራስ ድንጋይ በጽዮን አኖራለሁ በእርሱም የሚያምን አያፍርም ተብሎ ተጽፎአልና።
⁷ እንግዲህ ክብሩ ለእናንተ ለምታምኑት ነው፤ ለማያምኑ ግን አናጢዎች የጣሉት ድንጋይ እርሱ የማዕዘን ራስ የዕንቅፋትም ድንጋይ የማሰናከያም ዓለት ሆነ፤
⁸ የማያምኑ ስለ ሆኑ በቃሉ ይሰናከሉበታልና፤ ለዚህ ደግሞ የተመደቡ ናቸው።
⁹ እናንተ ግን ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእርሱን በጎነት እንድትናገሩ የተመረጠ ትውልድ፥ የንጉሥ ካህናት፥ ቅዱስ ሕዝብ፥ ለርስቱ የተለየ ወገን ናችሁ፤
¹⁰ እናንተ ቀድሞ ወገን አልነበራችሁም አሁን ግን የእግዚአብሔር ወገን ናችሁ፤ እናንተ ምሕረት ያገኛችሁ አልነበራችሁም አሁን ግን ምሕረትን አግኝታችኋል።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 26
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ አግሪጳም ጳውሎስን፦ ስለ ራስህ ትናገር ዘንድ ተፈቅዶልሃል አለው። በዚያን ጊዜ ጳውሎስ እጁን ዘርግቶ መለሰ እንዲህ ሲል፦
²-³ ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፥ የአይሁድን ሥርዓት ክርክርንም ሁሉ አጥብቀህ አውቀሃልና በአይሁድ በተከሰስሁበት ነገር ሁሉ ዛሬ በፊትህ ስለምመልስ ራሴን እጅግ እንደ ተመረቀ አድርጌ እቈጥረዋለሁ፤ ስለዚህ በትዕግሥት ትሰማኝ ዘንድ እለምንሃለሁ።
⁴ ከመጀመሪያ አንሥቶ በሕዝቤ መካከል በኢየሩሳሌም የሆነውን፥ ከታናሽነቴ ጀምሬ የኖርሁትን ኑሮዬን አይሁድ ሁሉ ያውቃሉ፤
⁵ ሊመሰክሩ ይወዱ እንደ ሆነ፥ በአምልኮአችን ከሁሉ ይልቅ ሕግን በመጠንቀቅ እንደሚተጋ ወገን ፈሪሳዊ ሆኜ እንደኖርሁ ከጥንት ጀምረው አውቀውኛልና።
⁶ አሁንም ከእግዚአብሔር ዘንድ ለአባቶቻችን ስለ ተሰጠው ስለ ተስፋ ቃል አለኝታ ልፋረድ ቆሜአለሁ።
⁷ ወደዚህም ወደ ተስፋ ቃል አሥራ ሁለቱ ወገኖቻችን ሌሊትና ቀን በትጋት እያመለኩ ይደርሱ ዘንድ አለኝታ አላቸው፤ ስለዚህም አለኝታ፥ ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፥ ከአይሁድ እከሰሳለሁ።
⁸ እግዚአብሔር ሙታንን የሚያስነሣ እንደ ሆነ ስለ ምን በእናንተ ዘንድ የማይታመን ነገር ሆኖ ይቈጠራል?
⁹ እኔም ራሴ የናዝሬቱን የኢየሱስን ስም የሚቃወም እጅግ ነገር አደርግ ዘንድ እንዲገባኝ ይመስለኝ ነበር።
¹⁰ ይህንም ደግሞ በኢየሩሳሌም አደረግሁት፤ ከካህናት አለቆችም ሥልጣን ተቀብዬ እኔ ከቅዱሳን ብዙዎችን በወኅኒ አሳሰርኋቸው፥ ሲገድሉአቸውም አብሬ ተቸሁ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ሐምሌ_17_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"ወአይቴ እጎይይ እምቅድመ ገጽከ። እመኒ ዐረጉ ውስተ ሰማይ ህየኒ አንተ። ወእመኒ ወረድኩ ውስተ ቀላይ ህየኒ ሀሎከ"። መዝ 138፥7-8።
"ከመንፈስህ ወዴት እሄዳለሁ? ከፊትህስ ወዴት እሸሻለሁ? ወደ ሰማይ ብወጣ፥ አንተ በዚያ ነህ፤ ወደ ሲኦልም ብወርድ፥ በዚያ አለህ"። መዝ 138፥7-8።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ሐምሌ_17_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ማቴዎስ 12
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
³⁸ በዚያን ጊዜ ከጻፎችና ከፈሪሳውያን አንዳንዶቹ መለሱና፦ መምህር ሆይ፥ ከአንተ ምልክት እንድናይ እንወዳለን አሉ።
³⁹ እርሱ ግን መልሶ እንዲህ አላቸው፦ ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይሻል፥ ከነቢዩም ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም።
⁴⁰ ዮናስ በዓሣ አንባሪ ሆድ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደ ነበረ፥ እንዲሁ የሰው ልጅ በምድር ልብ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይኖራል።
⁴¹ የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥተው ይፈርዱበታል፤ በዮናስ ስብከት ንስሐ ገብተዋልና፥ እነሆም፥ ከዮናስ የሚበልጥ ከዚህ አለ።
⁴² ንግሥተ ዓዜብ በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥታ ትፈርድበታለች፤ የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳር መጥታለችና፥ እነሆም፥ ከሰሎሞን የሚበልጥ ከዚህ አለ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
የሚቀደሰው ቅዳሴ የወልደ ነጎድጓድ #ቅዱስ_ዮሐንስ ቅዳሴ ነው። መልካም በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ነብስ_ይማር 😥
ብፁዕ አቡነ አብርሃም በጎፋ ዞን በደረሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ የብዙ ወገኖች ሕይወታቸው በማለፉ ጥልቅ ኀዘናቸውን ገለጹ።

"ትግሁ እንከ እስመ ኢተአምሩ በዓይ ሰዓት ይመጽእ እግዚእክሙ ፤ጌታችሁ በማናቸውም ሰዓት እንዲመጣ አታውቁምና ተግታችሁ ኑሩ።ማቴ ፳፬፥፵፪"

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሳቻ ጎዝዲ ቀበሌ ድንገት በተከሰተው የመሬት መንሸራተት ብዛት ያላቸው ኢትዮጵያውያን ላይ በደረሰው አሰቃቂና አሳዛኝ አደጋ ታላቅ ሀዘን ተሰምቶናል።

በመሆኑም የድንገተኛ አደጋው ተጎጂ ለሆኑ ወገኖቻችን እግዚአብሔር አምላክ በወዲያኛው ዓለም ዕረፍተ ነፍስን፣
ለተጎጂ ቤተሰቦች፣ ለአካባቢው ነዋሪዎችና ለመላው ኢትዮጵያውያንም መጽናናትን እንዲሰጥልን በመለመን
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ስም የተሰማንን ጥልቅ ሀዘን እንገልጻለን።

"አምላካችን እግዚአብሔር ለአገራችንና
ለዓለሙ ሁሉ ሰላምን ይስጥልን!"

አባ አብርሃም
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን
መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ዋና
ሥራ አስኪያጅ፣የባህር ዳርና የሰሜን ጎጃም
አህጉረስብከት ሊቀ ጳጳስ

©የኢኦተቤ ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

✞✞✞ እንኩዋን ለነቢዩ #ቅዱስ_ዮናስ እና ለእናታችን #ቅድስት_አውፎምያ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞

✞✞✞ ቅዱስ ዮናስ ነቢይ ✞✞✞

=>በቤተ ክርስቲያን አስተምሕሮ ከ12ቱ #ደቂቀ_ነቢያት አንዱ የሆነው #ቅዱስ_ዮናስ ከክርስቶስ ልደት 800 ዓመታት በፊት እንደ ነበረ ይታመናል:: #ሊቃውንት እንዳስተማሩን ደግሞ እናቱ #ቅዱስ_ኤልያስን የመገበችው የሰራፕታዋ መበለት ናት:: ቅዱስ ዮናስ ገና ሕጻን ሳለ በእሥራኤል ምድር ዝናብ ለ3 ዓመታት ከ6 ወራት ተከልክሎ ነበር::

+ይሕንንም ያደረገው ደጉ ነቢይ ኤልያስ ለአምልኮተ እግዚአብሔር ቀንቶ ነው:: በወቅቱ ኤልያስ በሰራፕታ ሳለ ሕጻኑ ዮናስ ታሞ ሞተ:: ልጇ የሞተባት መበለትም ኤልያስን ለመነችው:: ኤልያስም ወደ ፈጣሪው ማልዶ ሕጻኑን ዮናስን ከሞት አስነስቶታል:: ትንሽ ከፍ ባለ ጊዜም ከጉዋደኞቹ (ከነቢያቱ) #አብድዩና #ኤልሳዕ ጋር ሆነው ታላቁን ነቢይ ኤልያስን ተከትለውታል::

+ኤልያስ ካረገ በሁዋላ ሁሉም በየተሰጣቸው አገልግሎት ተሠማርተዋል:: ቅዱስ ዮናስን #እግዚአብሔር "ወደ ነነዌ ሒደሕ ንስሃን ስበክ" አለው:: ዮናስ ግን የፈጣሪውን መሐሪነት ጠንቅቆ ያውቃልና አልሔድም አለ:: (ተመልከቱ የየዋሕነት ብዛት)

+እግዚአብሔር እየደጋገመ እንዲሔድ ሲነግረው ነቢዩ "እንዲሕ የሚዘበዝበኝ ከፊቱ ብቀመጥ አይደል" ብሎ ሊኮበልል ወጣ:: ነገር ግን አልቀናውም:: በእርሱ ምክንያት ማዕበል ተነሳ:: ሕዝቡም ሊያልቁ ሆነ:: ከእንቅልፉ የነቃው ዮናስ ከመርከቡ ላሉት አሕዛብ አምልኮተ እግዚአብሔርን ሰብኮላቸው: በእርሱ ጠያቂነት ሐምሌ 15 ቀን ወደ ባሕር ጥለውታል::

+አሣ አንበሪም ተቀብሎታል:: በግዙፉ አሣ ውስጥም ያለ እንቅልፍ በጾም: በጸሎትና በምስጋና 3 ለቀን ቆይቷል::
ሙስና ሳያገኘውም በዚህች ቀን አሣ አንበሪው #ነነዌ ዳር ላይ ተፍቶታል:: ቅዱስ ዮናስ እግዚአብሔር እንዳዘዘው "እስከ ሠሉስ ዕለት ትትገፈታእ ነነዌ ዓባይ ሃገር" /እስከ ሦስት ቀን ድረስ ነነዌ ትገለበጣለች (ዮናስ 3:4)/ ብሎ አሰምቶ ሰበከ::

+የነነዌ ሰዎችም በስብከተ ዮናስ አምነው: ንስሃም ገብተው ድነዋል:: በዚህም ጌታችን በወንጌል ላይ አመስግኗቸዋል:: ቅዱስ ዮናስ መኮብለሉ #በሐዲስ_ኪዳን ለሚደረገው ምስጢረ ትንሳኤ ጥላ (ምሳሌ) ነውና ይደነቃል:: (ማቴ. 12:38) ነቢዩ ግን በተረፈ ሕይወቱ ሕዝቡን ሲያስተምር: ፈጣሪውን ሲያገለግል ኑሮ በመልካም ሽምግልና ዐርፏል::

+"+ ቅድስት አውፎምያ ሰማዕት +"+

=>እናታችን #ቅድስት_አውፎምያ (ስሟ አፎምያ አይደለም:: በስሕተት "ው" መካከል ላይ የገባች እንዳይመስልዎ:: እስመ ከመዝ ስማ-ስሟ እንዲሁ ነው የሚጠራው) በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን ከነበሩ ወጣት ክርስቲያኖች አንዷ ናት:: ገና ከልጅነቷ ልቧ በፍቅረ ክርስቶስ የተነደፈ ነበር::

+በዚህም ምክንያት ራሷን በጾምና በጸሎት ወስና ትኖር ነበር:: እድሜዋ ገና በአሥራዎቹ ቢሆንም በመንኖ ጥሪት መኖር ምርጫዋ ነበር:: ሊቃውንት አበው ከሰማዕትነቷ ደርበው "ጻድቅት አውፎምያ" እያሉም ይጠሯታል::

+አንድ ቀን ግን መንገድ ወጥታ ነበርና ክርስቲያኖች ሲሰቃዩ ተመለከተች:: ምንም ጥፋት ሳይገኝባቸው ክርስቶስን ስላመለኩ ብቻ ይሙት በቃ ተፈርዶባቸው ሊገደሉ እየተወሰዱ ነበር:: አሕዛብ ግብራቸው የአውሬ ነውና ርሕራሔ የላቸውም:: ሰማዕታቱ ደማቸው በየመንገዱ እየፈሰሰ ጥቁር ሰንሰለት በአንገታቸው: በእጃቸውና በእግራቸው ላይ አድርገው ይጐትቷቸው ነበር::

+ቅድስት አውፎምያ የተደረገውን ሁሉ ተመልክታ አምርራ አለቀሰች:: ፈጠን ብላም ወደ መኮንኑ ቀርባ ገሰጸችው::
"አንተ አእምሮ የጎደለህ! እንዴት ክርስቲያኖችን እንዲህ ታሰቃያለህ? አምላካቸው #ጌታ_ክርስቶስ ታጋሽ ባይሆን ኑሮ በቅጽበት ከገጸ ምድር ባጠፋህ ነበር" አለችው::

+በድፍረቷ የተገረመው መኮንኑ "አንቺስ ማንን ታመልኪያለሽ?" ሲል ጠየቃት:: እርሷም "ሰማይና ምድርን የፈጠረውን: ስለ እኛ ሲል በቀራንዮ አንባ የተሠዋውን #ኢየሱስ ክርስቶስን አመልካለሁ" ስትል መለሰችለት:: በዚያች ሰዓት የመኮንኑ ቁጣ በቅድስቷ ላይ ነደደ::

+ነገር ግን ቁጣውን ከቁም ነገር አልቆጠረችውምና እንዲያሰቃዩዋት አዘዘ:: ወታደሮቹ ሥጋዋን በብዙ አሰቃዩ:: ብላቴናዋ አውፎምያ ግን ጽንዕት ናትና አልቻሏትም:: በመጨረሻ በእሳት ተቃጥላ ትሞት ዘንድ ተፈረደባት::

+እሳቱ ከመሬት ከፍ ባለ ጊዜ ወደ ውስጥ ወረወሯት:: በእሳቱ መካከል ቁማ ለረዥም ጊዜ ጸለየች:: ከዚያም ነፍሷን አሳልፋ ሰጠች:: ምዕመናን በክብር ገንዘው ቀብረዋታል::

=>አምላካችን ከነቢዩና ከሰማዕቷ ወዳጆቹ በረከት ይክፈለን::

=>ሐምሌ 17 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ዮናስ ነቢይ (ከአሣ አንበሪ ሆድ የወጣበት)
2.ቅድስት አውፎምያ (ጻድቅትና ሰማዕት)
3.ቅዱስ ዮስጦስ ሰማዕት (ታላቁ)
4.ቅዱስ ዘካርያስ

=>ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ እስጢፋኖስ ሊቀ ዲያቆናት (ቀዳሜ ሰማዕት)
2.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ወልደ ዘብዴዎስ)
3.ቅዱሳን አበው መክሲሞስና ዱማቴዎስ
4.አባ ገሪማ ዘመደራ
5.አባ ዸላሞን ፈላሢ
6.አባ ለትጹን የዋህ
7.ቅዱስ ኤዺፋንዮስ ሊቅ (ዘደሴተ ቆዽሮስ)

=>+"+ በዚያን ጊዜ ከጻፎችና ከፈሪሳውያን አንዳንዶቹ መለሱና:- 'መምሕር ሆይ! ከአንተ ምልክት እንድናይ እንወዳለን' አሉት:: እርሱ ግን መልሶ እንዲህ አላቸው:- 'ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይሻል:: ከነቢዩም ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም:: ዮናስ በአሣ አንበሪ ሆድ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደ ነበረ እንዲሁ የሰው ልጅ በምድር ልብ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይኖራል:: የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነስተው ይፈርዱበታል:: በዮናስ ስብከት ንስሃ ገብተዋልና:: እነሆም ከዮናስ የሚበልጥ ከዚህ አለ:: +"+ (ማቴ. 12:38)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>

" ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"::/የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ) እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::  አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ /መጽሐፈ ምሥጢር/
https://www.tg-me.com/zikirekdusn
††† እንኳን ለሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ †††

††† ይህ ቅዱስ ሐዋርያ በአባቶቻችን ሐዋርያት መካከል ትልቅ ሞገስ የነበረውና "የጌታችን ወንድም" ተብሎ የተጠራ ነው:: ቅዱስ ያዕቆብ ወላጅ አባቱ አረጋዊው ቅዱስ ዮሴፍ (የእመቤታችን ጠባቂ) ሲሆን በልጅነቱ የሞተችው እናቱ ደግሞ ማርያም ትባላለች:: በቤት ውስጥም ስምዖን: ዮሳና ይሁዳ የተባሉ ወንድሞችና ሰሎሜ የምትባል እህትም ነበረችው::

እናቱ ማርያም ከሞተች በኋላ ዕጓለ-ማውታ (ደሃ አደግ) ሆኖ ነበር:: ነገር ግን በፈቃደ እግዚአብሔር አረጋዊ ዮሴፍ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ከቤተ መቅደስ ሊጠብቃት (ሊያገለግላት) ተቀብሎ ሲመጣ ያ ቤተሰብ ተቀየረ:: የበረከት: የምሕረትና የሰላም እመቤት የአምላክ እናቱ ገብታለችና ያ የሐዘን ቤት ደስታ ሞላው::

እመ ብርሃን ግን ገና ወደ ዮሴፍ ልጆች ስትደርስ አለቀሰች:: የአክስቷ ልጆች የሚንከባከባቸው አጥተው ቆሽሸው ነበር:: በተለይ ደግሞ ትንሹ ቅዱስ ያዕቆብ ያሳዝን ነበር:: እመ ብርሃን ማረፍ አልፈለገችም:: ወዲያው ማድጋ አንስታ ወደ ምንጭ ወርዳ ውኃ አምጥታ የሕፃኑን ገላ አጠበችው:: (በአምላክ እናት የታጠበ ሰውነት ምስጋና በጸጋ ይገባዋል::)

እመቤታችን ጌታ ከመወለዱ በፊት ለዘጠኝ ወራት: ከተወለደ በኋላ ደግሞ ለሁለት ዓመታት ሕፃኑን ያዕቆብን ተንከባከበችው:: ለሦስት ዓመት ከስድስት ወር ግን ድንግል ማርያም አምላክ ልጇን ይዛ ተሰዳለችና ተለያዩ:: ከስደት መልስ ግን ለሃያ አምስት ዓመታት ቅዱስ ያዕቆብ ከጌታችን ጋር ሲያድግ ወላጅ እናቱ ትዝ ብላው አታውቅም:: አማናዊቷ እናት ከጐኑ ነበረችና::

ሊቃውንት እንደ ነገሩን እመቤታችን ለቅዱስ ያዕቆብ ያልሰጠችው ነገር ቢኖር ሐሊበ ድንግልናዌ (የድንግልና ወተትን) ብቻ ነው:: ስለዚህም:-
"እመ ያዕቆብ በጸጋ ማርያም ንግሥተ ኩሉ" ይላል መጽሐፍ:: (መልክዐ ስዕል)

††† ቅዱስ ያዕቆብ "የጌታ ወንድም" ተብሎ በተደጋጋሚ በሐዲስ ኪዳን ተጠርቷል:: ለዚህ ምክንያቱ
1.ለሰላሳ ዓመታት ሳይነጣጠሉ አብረው በማደጋቸው
2.የጌታችን የሥጋ አያቱ (የቅድስት ሐና) የእህት ልጅ በመሆኑ
3.በዮሴፍ በኩልም የአንድ ቅድመ አያት ልጆች በመሆናቸው
4.ጌታችን ከትህትናው የተነሳ ደቀ መዛሙርቱን "ወንድሞች" ይላቸው ስለ ነበር ነው:: (ሥጋቸውን ተዋሕዶ ተገኝቷልና::)

ራሱ ቅዱስ ያዕቆብ ግን "የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ ነኝ" ብሎ በፈጣሪና በፍጡር መካከል ያለውን ልዩነት ገልጧል:: (ያዕ. 1:1) ቅዱስ ያዕቆብ ጌታችን ሲያስተምር ተከተለው::
¤ከሰባ ሁለቱ አርድእት ተቆጠረ
¤ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ወንጌልን ተማረ
¤ለመጀመሪያ ጊዜ ከድንግል ማርያምና ከቅዱስ ዮሐንስ ጋር ሆኖ "የጌታን ትንሣኤ ሳላይ እህል አልቀምስም" ብሎ ማክፈልን አስተማረ
¤መንፈስ ቅዱስን ተሞልቶ ወንጌልን አስተማረ
¤የኢየሩሳሌም የመጀመሪያው ሊቀ ጳጳስ ሆኖ አገለገለ
¤በመጀመሪያዎቹ የክርስትና ዘመናት የሐዋርያት ሲኖዶሶችን በሊቀ መንበርነት መራ
¤ሙታንን አስንስቶ
¤ድውያንን ፈውሶ
¤የመካኖችን ማኅጸን ከፍቶ: አጋንንትንም አስወጥቶ ብዙ ተዓምራትን ሠራ:: እጅግ ብዙ አይሁዳውያንን ወደ አሚነ ክርስቶስ መልሶ መልካሙን ገድል ተጋደለ::

በመጨረሻ ዘመኑ ያላመኑ የአይሁድ አለቆች ወደ ቤቱ ተሰብስበው "የናዝሬቱ ኢየሱስ ማነው? የማንስ ልጅ ነው?" ሲሉ ጠየቁት:: እነርሱ ሰይጣን በሰለጠነበት ልቡናቸው "የዮሴፍ ልጅ ነው: የእኔም ወንድሜ ነው" እንዲላቸው ጠብቀው ነበር:: (ሎቱ ስብሐት ወአኮቴት)

††† በልቡናቸው ያሰቡትን ተንኮል የተረዳው ሐዋርያ ወደ ቤቱ ጣራ ወጥቶ መናገር ጀመረ:: "ለስም አጠራሩ ጌትነት ይሁንና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ:-
አምላክ:
ወልደ አምላክ:
ወልደ አብ:
ወልደ ማርያም:
ሥግው ቃል:
እግዚአብሔር ነው:: እኔም ፍጡሩና ባሪያው እንጂ እንደምታስቡት ወንድሙ አይደለሁም" አላቸው::

ንዴታቸውን መቆጣጠር ያልቻሉት አይሁድ ከላይ ወጥተው ወደ መሬት ወረወሩት:: በገድል የተቀጠቀጠ አካሉንም እየተፈራረቁ ደበደቡት:: አንዱ ግን ከእንጨት የተሠራ ትልቅ ገንዳ አምጥቶ የቅዱሱን ራስ ደጋግሞ መታው:: ጭንቅላቱም እንዳልነበር ሆነ:: ሰማዕቱ ሐዋርያ ቅዱስ ያዕቆብ ወደ ወደደው ክርስቶስ በዚህች ቀን ሔደ::

ቅዱሱ ሐዋርያ ያዕቆብ ቤቱን እንደ ቤተ መቅደስ አበው ሐዋርያት ይጠቀሙባት ነበር:: በመላ ዘመኑ የሚያገድፍ ነገር (ጥሉላት) ቀምሶ : ጸጉሩን ተላጭቶ : ገላውን ታጥቦና ልብሱን ቀይሮ አያውቅም::
"ወዝንቱ ጻድቅ እኅወ እግዚእነ::
ኢያብአ ውስተ አፉሁ ሥጋ ወወይነ::
ወኢገብረ ሎቱ ክልኤተ ክዳነ" እንዲል::

††† ከጾም : ከጸሎትና ከመቆሙ ብዛትም እግሩ አብጦ አላራምድህ ብሎት ነበር:: ስለዚህም አበው "ጻድቁ (ገዳማዊው) ሐዋርያ" ይሉታል::

††† ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወንድሙ ይባል ዘንድ ካደለው ሐዋርያ በረከትን ያድለን:: በምልጃውም ምሕረትን ይላክልን::

††† ሐምሌ 18 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ከሰባ ሁለቱ አርድእት-የመጀመሪያው የኢየሩሳሌም ሊቀ ጳጳሳት)
2.ቅዱስ አትናቴዎስ ሰማዕት
3.ቅዱስ እንድራኒቆስ ሰማዕት
4.ዘጠኝ ሺህ ሰማዕታት (የቅዱስ ኤስድሮስ ማኅበር)

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ፊልጶስ ሐዋርያ
2.አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ሰባኬ ሃይማኖት (ረባን)
3.አቡነ አኖሬዎስ ዘደብረ ጽጋጋ
4.ማር ያዕቆብ ግብጻዊ

††† "የእግዚአብሔርና የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ ያዕቆብ: ለተበተኑ ለአሥራ ሁለቱ ወገኖች:: ሰላም ለእናንተ ይሁን:: ወንድሞቼ ሆይ! የእምነታችሁ መፈተን ትዕግስትን እንዲያደርግላችሁ አውቃችሁ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቁጠሩት:: ትዕግስትም ምንም የሚጐድላችሁ ሳይኖር ፍጹማንና ምሉዓን ትሆኑ ዘንድ ሥራውን ይፈጽም::" †††
(ያዕ. ፩፥፩)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††

https://www.tg-me.com/zikirekdusn
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ሐምሌ_18_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ቆሮንቶስ 15
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ ወንድሞች ሆይ፥ የሰበክሁላችሁን ደግሞም የተቀበላችሁትን በእርሱም ደግሞ የቆማችሁበትን በእርሱም ደግሞ የምትድኑበትን ወንጌል አሳስባችኋለሁ፤
² በከንቱ ካላመናችሁ በቀር፥ ብታስቡት፥ በምን ቃል እንደ ሰበክሁላችሁ አሳስባችኋለሁ።
³ እኔ ደግሞ የተቀበልሁትን ከሁሉ በፊት አሳልፌ ሰጠኋችሁ እንዲህ ብዬ፦ መጽሐፍ እንደሚል ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን ሞተ፥ ተቀበረም፥
⁴ መጽሐፍም እንደሚል በሦስተኛው ቀን ተነሣ፥
⁵ ለኬፋም ታየ በኋላም ለአሥራ ሁለቱ፤
⁶ ከዚያም በኋላ ከአምስት መቶ ለሚበዙ ወንድሞች በአንድ ጊዜ ታየ፤ ከእነርሱም የሚበዙቱ እስከ አሁን አሉ አንዳንዶች ግን አንቀላፍተዋል፤
⁷ ከዚያም በኋላ ለያዕቆብ ኋላም ለሐዋርያት ሁሉ ታየ፤
⁸ ከሁሉም በኋላ እንደ ጭንጋፍ ለምሆን ለእኔ ደግሞ ታየኝ።
⁹ እኔ ከሐዋርያት ሁሉ የማንስ ነኝና፥ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ስላሳደድሁ ሐዋርያ ተብዬ ልጠራ የማይገባኝ፤
¹⁰ ነገር ግን በእግዚአብሔር ጸጋ የሆንሁ እኔ ነኝ፤ ለእኔም የተሰጠኝ ጸጋው ከንቱ አልነበረም ከሁላቸው ይልቅ ግን ደከምሁ፥ ዳሩ ግን ከእኔ ጋር ያለው የእግዚአብሔር ጸጋ ነው እንጂ እኔ አይደለሁም።
¹¹ እንግዲህስ እኔ ብሆን እነርሱም ቢሆኑ እንዲሁ እንሰብካለን እንዲሁም አመናችሁ።
¹² ክርስቶስ ከሙታን እንደ ተነሣ የሚሰበክ ከሆነ ግን ከእናንተ አንዳንዶቹ፦ ትንሣኤ ሙታን የለም እንዴት ይላሉ?
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ያዕቆብ 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ የእግዚአብሔርና የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ ያዕቆብ ለተበተኑ ለአሥራ ሁለቱ ወገኖች፤ ሰላም ለእናንተ ይሁን።
²-³ ወንድሞቼ ሆይ፥ የእምነታችሁ መፈተን ትዕግሥትን እንዲያደርግላችሁ አውቃችሁ፥ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቍጠሩት
⁴ ትዕግሥትም ምንም የሚጎድላችሁ ሳይኖር ፍጹማንና ምሉዓን ትሆኑ ዘንድ ሥራውን ይፈጽም።
⁵ ከእናንተ ግን ማንም ጥበብ ቢጎድለው፥ ሳይነቅፍ በልግስና ለሁሉ የሚሰጠውን እግዚአብሔርን ይለምን፥ ለእርሱም ይሰጠዋል።
⁶ ነገር ግን በምንም ሳይጠራጠር በእምነት ይለምን፤ የሚጠራጠር ሰው በነፋስ የተገፋና የተነቃነቀ የባሕርን ማዕበል ይመስላልና።
⁷-⁸ ሁለት አሳብ ላለው በመንገዱም ሁሉ ለሚወላውል ለዚያ ሰው ከጌታ ዘንድ አንዳች እንዲያገኝ አይምሰለው።
⁹-¹⁰ የተዋረደው ወንድም ግን በከፍታው፥ ባለ ጠጋም በውርደቱ ይመካ፤ እንደ ሣር አበባ ያልፋልና።
¹¹ ፀሐይ ከትኵሳት ጋር ይወጣልና፥ ሣርንም ያጠወልጋልና፥ አበባውም ይረግፋልና፥ የመልኩም ውበት ይጠፋልና፤ እንዲሁ ደግሞ ባለ ጠጋው በመንገዱ ይዝላል።
¹² በፈተና የሚጸና ሰው የተባረከ ነው፤ ከተፈተነ በኋላ ለሚወዱት ተስፋ ስለ እርሱ የሰጣቸውን የሕይወትን አክሊል ይቀበላልና።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 15
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹³ እነርሱም ዝም ካሉ በኋላ ያዕቆብ እንዲህ ብሎ መለሰ፦ ወንድሞች ሆይ፥ ስሙኝ።
¹⁴ እግዚአብሔር ለስሙ የሚሆንን ወገን ከአሕዛብ ይወስድ ዘንድ አስቀድሞ እንዴት እንደ ጐበኘ ስምዖን ተርኮአል።
¹⁵ ከዚህም ጋር የነቢያት ቃል ይሰማማል፥ እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፦
¹⁶-¹⁷ ከዚህ በኋላ የቀሩት ሰዎችና በስሜ የተጠሩት አሕዛብ ሁሉ ጌታን ይፈልጉ ዘንድ እመለሳለሁ፥ የወደቀችውንም የዳዊትን ድንኳን እንደ ገና እሠራታለሁ፥ ፍራሽዋንም እንደ ገና እሠራታለሁ እንደ ገናም አቆማታለሁ ይላል ይህን የሚያደርግ ጌታ።
¹⁸ ከጥንት ጀምሮ ሥራው ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ የታወቀ ነው።
¹⁹ ስለዚህ ከአሕዛብ ወደ እግዚአብሔር የዞሩትን እንዳናስቸግራቸው፥
²⁰ ነገር ግን ከጣዖት ርኵሰትና ከዝሙት ከታነቀም ከደምም ይርቁ ዘንድ እንድንጽፍላቸው እቈርጣለሁ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ሐምሌ_18_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"ወኢነበርኩ ውስተ ዐውደ ከንቱ። ወኢቦእኩ ምስለ ዐማፅያን። ጸላዕኩ ማኅበረ እኩያን "። መዝ.25፥4-5።
"በከንቱ ሸንጎ አልተቀመጥሁም፥ ከዓመፀኞችም ጋር አልገባሁም። የክፉዎችን ማኅበር ጠላሁ፥ ከዝንጉዎችም ጋር አልቀመጥም"። መዝ.25፥4-5።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ሐምሌ_18_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ማርቆስ 6
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ ከዚያም ወጥቶ ወደ ገዛ አገሩ መጣ ደቀ መዛሙርቱም ተከተሉት።
² ሰንበትም በሆነ ጊዜ በምኵራብ ያስተምር ጀመር፤ ብዙዎችም ሰምተው ተገረሙና፦ እነዚህን ነገሮች ይህ ከወዴት አገኛቸው? ለዚህ የተሰጠችው ጥበብ ምንድር ናት? በእጁም የሚደረጉ እንደነዚህ ያሉ ተአምራት ምንድር ናቸው?
³ ይህስ ጸራቢው የማርያም ልጅ የያቆብም የዮሳም የይሁዳም የስምዖንም ወንድም አይደለምን? እኅቶቹስ በዚህ በእኛ ዘንድ አይደሉምን? አሉ፤ ይሰናከሉበትም ነበር።
⁴ ኢየሱስም፦ ነቢይ ከገዛ አገሩና ከገዛ ዘመዶቹ ከገዛ ቤቱም በቀር ሳይከበር አይቀርም አላቸው።
⁵ በዚያም በጥቂቶች ድውዮች ላይ እጁን ጭኖ ከመፈወስ በቀር፥ ተአምር ሊያደርግ ምንም አልቻለም።
⁶ ስለ አለማመናቸውም ተደነቀ። በመንደሮችም እያስተማረ ይዞር ነበር።
⁷ አስራ ሁለቱንም ወደ እርሱ ጠራ ሁለት ሁለቱንም ይልካቸው ጀመር፥ በርኵሳን መናፍስትም ላይ ሥልጣን ሰጣቸው፥
⁸ ለመንገድም ከበትር በቀር እንጀራም ቢሆን ከረጢትም ቢሆን መሐለቅም በመቀነታቸው ቢሆን እንዳይዙ አዘዛቸው።
⁹ በእግራችሁ ጫማ አድርጉ እንጂ ሁለት እጀ ጠባብ አትልበሱ አለ።
¹⁰ በማናቸውም ስፍራ ወደ ቤት ብትገቡ ከዚያ እስክትወጡ ድረስ በዚያው ተቀመጡ።
¹¹ ከማይቀበሉአችሁና ከማይሰሙአችሁ ስፍራ ሁሉ፥ ከዚያ ወጥታችሁ ምስክር ይሆንባቸው ዘንድ ከእግራችሁ በታች ያለውን ትቢያ አራግፉ። እውነት እላችኋለሁ፥ ከዚያች ከተማ ይልቅ ለሰዶምና ለገሞራ በፍርድ ቀን ይቀልላቸዋል አላቸው።
¹² ወጥተውም ንስሐ እንዲገቡ ሰበኩ፥ ብዙ አጋንንትንም አወጡ፥
¹³ ብዙ ድውዮችንም ዘይት እየቀቡ ፈወሱአቸው።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #ቅዱሳን_ሐዋርያት ቅዳሴ ነው። መልካም የ #ሐዋርያው_ቅዱስ_ያዕቆብ_ወልደ_ዮሴፍ የዕረፍት በዓል። ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
የያዕቆብ መልእክት (3).pdf
1.3 MB
📚⛪️ የያዕቆብ መልእክት አንድምታ⛪️📚 
#ሐምሌ_19

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ሐምሌ ዐሥራ ዘጠኝ በዚህች ቀን ሕፃኑ #ቅዱስ_ቂርቆስ እና #እናቱ_ቅድስት_ኢየሉጣ በሰማዕትነት መከራ ተቀበሉ፣ #ቅዱሳን_ሱርስ_ኀርማን_ያኑፋና_ስንጣንያ የሚባሉ የእስና ሀገር ሰዎች በሰማዕትነት ሞቱ፣ ብልህ የሆነ #ቅዱስ_በጥላን በሰማዕትነት ሞተ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ቂርቆስና_እናቱ_ቅድስት_ኢየሉጣ

ሐምሌ ዐሥራ ዘጠኝ በዚህች ቀን ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስና እናቱ ኢየሉጣ በሰማዕትነት መከራ ተቀበሉ። ይህም ሕፃን ዕድሜው ሦስት ዓመት ሲሆነው ከሮሜ አገር ወደሌላ ሀገር እናቱ ይዛው ሸሸች በዚያም የሸሸችውን መኰንን አገኘችው።

ሰዎችም ነገር ሠሩባት ወደርሱ አስቀረባትና ስለ አምልኮ ጠየቃት እርሷም መኰንን ሆይ ዕድሜው ሦስት ዓመት የሆነው ሕፃን አለ አማልክቶችህን ማምለክ መልካም እንደሆነ ወይም እንዳልሆነ ያስረዳን ዘንድ እርሱን ጠይቅ አለችው።

ሕፃኑም ወደአለበት ጭፍራውን ልኮ ወደርሱ አስመጣው ሕፃኑንም ፊቱ ብሩህና ደስተኛ እንደሆነ አየውና አንተ ደስተኛ ሕፃን ሆይ እንዴት ነህ አለው። ሕፃኑም መልሶ አዎ ለእኔ ደስታ ተጠብቆልኛል ላንተ ግን ኀዘንና ልቅሶ ጥርስ ማፋጨትም ነው መጽሐፍ ለዝንጉዎች ተድላ ደስታ የላቸውም ብሏልና አለው እግዚአብሔር ኃይልና ንግግርን ሰጥቶታልና ብዙ ተናገረ በዚያም ያሉትን እስከ አስደነገጣቸው ድረስ ንጉሡን መኳንንቱንና ጣዖታቱን ረገማቸው ከብርታቱም የተነሣ አደነቁ።

መኰንኑም በአፈረ ጊዜ በየአይነቱ በሆነ ሥቃይ ታላላቆች የማይችሉትን ታላቅና አስጨናቂ የሆነ ሥቃይን አሠቃየው እናቱንም ከርሱ ጋር እንደ እርሱ አሠቃያት እግዚአብሔርም ያለምንም ጉዳት ያነሣቸው ነበር። ብዙዎች አሕዛብም ይህን አይተው አደነቁ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም አምነው በሰማዕትነት ሞቱ የሰማዕትነትንም አክሊል ተቀበሉ።

በሕፃኑ ላይም የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ አደረበት። ታላላቅ ድንቆችና ተአምራቶችንም አደረገ ብዙዎች በሽተኞችንም አዳናቸው።

ከዚህም በኋላ መኰንኑ በታላቅ የናስ ጋን ውስጥ ውኃ ጨምረው በእሳት ያፈሉት ዘንድ አዘዘ የፍላቱም ድምጽ እንደ ክረምት ነጐድጓድ ሆነ ያን ጊዜም ፍርሀትና የሃይማኖት ጉድለት በእናቱ ላይ ደረሰባት ሕፃኑም ስለ እናቱ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ።

ያን ጊዜ ጌታችን ልቧን ወደ ሰማይ አሳርጎ ለቅዱሳን ሰማዕታት የተዘጋጁ የብርሃን ማደሪያዎችን አየች ከዚህም በኋላ ጸናች እግዚአብሔርንም አመሰገነችው ልጅዋንም ልጄ ሆይ ከእንግዲህ አንተ አባቴ ነህ እኔም ልጅህ ነኝ አለችው።

ያቺ ከኔ የተወለድክባትም ቀን የተባረከች ናት አለች ወደዚያ ወደ ጋኑ ውስጥ በገቡ ጊዜም የውኃው ፍልሐት እንደ ንጋት ጊዜ ውርጭ ቀዘቀዘ ከእግዚአብሔር የታዘዘ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል ከሰማይ ወርዶ የእሳቱን ኃይል አቀዝቅዞታልና።

ከዚህም በኋላ መኰንኑ ሥጋቸው ተቆራርጦ እስከሚወድቅ ድረስ በመቃጥን ውስጥ አድርገው እንዲጐትቷቸው አዘዘ ከእግዚአብሔርም የታዘዘ መልአክ አዳናቸው መኰንኑም በታላቅ ሥቃይ ያሠቃያቸው ዘንድ አስቦ እስኪመክር ድረስ በወህኒ ቤት ዘጋባቸው።

ያን ጊዜም ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሕፃኑ ቂርቆስ ወርዶ አጽናናው አረጋጋውም። ስሙን ለሚጠራና መታሰቢያውን ለሚያደርግ ቃል ኪዳን ሰጠው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱሳን_ሱርስ_ኀርማን_ያኑፋ_እና_ስንጣንያ

በዚህች ቀን ስማቸው ሱርስ፣ ኀርማን፣ ያኑፋ፣ ስንጣንያ የሚባሉ የእስና ሀገር ሰዎች በሰማዕትነት ሞቱ። የሰማዕትነታቸው ምክንያትም እንዲህ ነው መኰንኑ አርያኖስ ወደ እስና ከተማ ሦስት ጊዜ ደረሰ። በመጀመሪያ የተባረከች መስተጋድልት የሆነች ዳላዢን ገደላት። ስማቸውን አስቀድመን የጠራናቸው አራቱን ልጆቿንም ገደላቸው። የሰማዕትነታቸውም ፍጻሜ ግንቦት ሰባት ቀን ሆነ።

በሁለተኛም ጊዜ ስማቸው አውሳፍዮስ፣ ታማን፣ ኀርማን፣ ባኮስ የሚባል አራቱን መኳንንት ገደላቸው። የሰማዕትነታቸውም ፍጻሜ ሰኔ ሰባት ቀን ሆነ። በሦስተኛም ጊዜ በቤቷ ውስጥ በዐልጋዋ ላይ ተኝታ የነበረችውን አሮጊት የአርያኖስ ወታደሮች ስለ እነዚህ ቅዱሳን ከጠየቋት በኋላ ገደሏት።

ከዚህም በኋላ መኰንኑ ከክርስቲያን ወገን ያገኙትን ሁሉ እንዲገድሉ የተክል ማጠጫ በተባለች በከተማዋ ምዕራብም መግደልን እንዳያቋርጡ አዘዘ ወደ ከበረ አባት ወደ ባሕታዊ ይስሐቅም እስኪደርሱ ድረስ በመንገድ ብዙ ሕዝብን አገኙ።

ያን ጊዜም ጠባቂያቸው እንዲህ እያለ ያጽናናቸውና ያረጋጋቸው ነበር። ወደ ሰማያዊት መንግሥት እንድትገቡ ጸንታችሁ ታገሡ። እንዲህም ሲወስዷቸው መኰንኑ ደረሰ በአዩትም ጊዜ ሁሉም በአንድ ቃል እኛ ክርስቲያን ነን እያሉ በግልጽ ጮኹ መኰንኑም ሁሉንም እንደበግ ያርዷቸው ዘንድ አዘዘ።

ጭፍሮች ግን በላያቸው በሰይፎች አጋና ተጫወቱ። በዚችም በሐምሌ ዐሥራ ዘጠኝ ቀን የእስናን ከተማ ሰዎች ከታናሾቻቸው እስከ ታላቆቻቸው ሴቶችንና ወንዶችን ጨረሷቸው። የመላእክት ሠራዊትም ነፍሶቻቸውን ይቀበሉ የብርሃን አክሊሎችንም ያቀዳጁአቸው ነበር።

ከዚህም በኋላ መኰንኑ ከዚያ ወደ እስዋን ከተማ ሔደ ሁለተኛም ወደ እስና ከተማ ተመልሶ ሦስት ገበሬዎችን የእርሻ ዕቃቸውን ተሸክመው አገኘ። መኰንኑንም በአዩት ጊዜ እኛ ክርስቲያን ነን ብለው በግልጥ ጮኹ መኰንኑም ሰምቶ ይገድሏቸው ዘንድ አዘዘ በእርሻ መሣሪያቸውም ገደሏቸው የእነዚህም ስማቸው ሱሩፋስ፣ አንጣኪዮስ፣ ስሐድራ ይባላል የሰማዕትነታቸውም ፍጻሜ መስከረም ዐሥራ አንድ ቀን ነው።

ይህንንም ቅዱስ አባት ኤጲስቆጶስ ይስሐቅን መኰንኑ አሥሮ ለጣዖት እንዲሠዋ አስገደደው። እምቢ ባለውም ጊዜ ወደ እሳት እንዲወረውሩት አዘዘ የሰማዕትነቱም ፍጻሜ ታኅሣሥ ዐሥራ አራት ቀን ነው ምእመናንም ሥጋውን ወስደው ገንዘው ቀበሩት። የስደቱ ወራትም ከአለፈ በኋላ ቤተ ክርስቲያን ሠርተው በስሙ አከበሩዋት።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_በጥላን_ጠቢብ_ሰማዕት

በዚህችም ቀን ትዕማዳን ከምትባል ከተማ ብልህ የሆነ ቅዱስ በጥላን በሰማዕትነት ሞተ። አባቱም አረማዊ ነበረ ስሙም አውሱጢኪዮስ ነበር እናቱ ግን አማኝ ነበረች ስሟም ኤልያና ነበር። በአደገ ጊዜም አባቱ ጥበብን ሁሉ አስተማረው እጅግም አዋቂ ሆነ።

በበጥላን ቤት አቅራቢያም አንድ ቄስ ይኖር ነበር። በጥላንም በፊቱ ሲያልፍ መልኩንና ዕውቀቱን ብልህነቱንና አሰተዋይነቱንም ይመለከት ነበር ከሀዲ ስለመሆኑም ስለርሱ ያዝን ነበር። ቄሱም በጥላንን መንገድ መርቶ ወደ ቀናች ሃይማኖት ያስገባው ዘንድ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ለመነው።

ስለ በጥላንም ልመናውን በአዘወተረ ጊዜ በጥላን በእርሱ እጅ ያምን ዘንድ እንዳለው ጌታችን በራእይ ገለጠለት ቄሱም ደስ አለው ሁልጊዜም በፊቱ ሲያልፍ በጥላንን ያነጋግረውና ሰላምታ የሚሰጠው ነበር። ስለዚህም በመካከላቸው ፍቅር ጸና።

ከዚህም በኋላ በጥላን ወደ ቄሱ ቤት ይገባና ስለ ሃይማኖት ይነጋገር ነበር። ቄሱም ክብር ይግባውና የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሃይማኖት ምን ያህል ክብር እንዳላት ለሚያምኑበትም ሁሉ ዕውቀትና ማስተዋል እንደሚሰጣቸው ድንቆችና ታላላቅ ተአምራቶች እንደሚደረግላቸው ታላቅ ፈውስም እንደሚያደርጉ ገለጠለት።

በጥላንም ክብር ይግባውና በክርስቶስ የሚያምኑ ተአምራትን እንደሚያደርጉ ይህን በሰማ ጊዜ እጅግ ደስ ብሎት በዚያ ቄስ ትምህርት በጌታ አመነ ቄሱም ሁልጊዜ የሃይማኖትን ትምህርት ያስተምረው ጀመር።
2024/09/23 07:22:05
Back to Top
HTML Embed Code: