Telegram Web Link
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ
አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

❖ እንኳን አደረሳችሁ ❖

❖ ግንቦት 12 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ °+

=>ለቤተ ክርስቲያን የብርሃን ምሰሶ ስለሆነላት ስለ ታላቁ
ሐዋርያዊ ሊቅ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ምን እላለሁ?
ምንስ
እናገራለሁ? እንደ እኔ ያለ ኃጥእ: ለባሴ ሥጋና ገባሬ ንስሃ
ስለሱ ሊናገር አይቻለውምና:: አባቶቻችን እንደ ነገሩን ስለ
አፈ ወርቅ ለመናገር አፈ ወርቅ መሆን ያስፈልጋል:: ግን
እስኪ በቅዱሱ አባት ምልጃ ጥቂት ልሞክር::

<< ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ማን ነው? >>

+ነገዱ ከሶርያ: የተወለደው በ347 ዓ/ም በእስክንድርያ
ሲሆን አባቱ አስፋኒዶስ እናቱ ደግሞ አትናስያ ይባላሉ::
እነርሱ
ደግ ቢሆኑ ይህንን እንቁ ልጅ እግዚአብሔር ሰጣቸው::
ዮሐንስ ለክርስቲያን እንደሚገባ በትምሕርትና በጥበብ
አደገ:: ገና
በሕጻንነቱ ወደ ግሪክ ሔዶ የዘመኑን ሳይንስ (ፍልስፍና)
ከአፉ እስከ ገደፉ ተምሮ ተመልሷል::

+ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅን ለየት ከሚያደርጉት ነገሮችም
አንዱ ይሔው ነው:: በዘመናዊም ሆነ በመንፈሳዊ
ትምሕርት ይህ
ቀረህ የማይሉት ሊቅ የሆነው ገና በ15 ዓመቱ ነበር:: በ2
ወገን የተሳለ ሰይፍ በመሆኑ ስንኳን በሕይወተ ሥጋ እያለ
ዛሬም ለንፉቃን ትልቅ የራስ ምታት ነው::

+ቅዱሱ ገና በ16 ዓመቱ ሃብት: ንብረት: ውበት: ክብርና
እውቀት የሞላለት ቢሆንም ያለውን ሁሉ ለነዳያን ሰጥቶ
መጻሕፍትን ብቻ ሰብስቦ ከባልንጀራው ቅዱስ ባስልዮስ
ጋር በርሃ ገባ:: ሰውነቱን በጾምና በጸሎት እየቀጣ በበርሃ
ሲኖር
ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስና ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ
ዼጥሮስ ወደ እርሱ መጡ::
ሊቀ ሐዋርያት የመንግስተ ሰማያትን መክፈቻ ስልጣን
ቅዱስ ዮሐንስ ደግሞ ወንጌሉን ሰጥተው ተሰወሩት::

+ከዚህች እለት በኋላ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ባሕረ
ምስጢራት ሆነ:: ብሉይ ከሐዲስ: ከኦሪት ዘፍጥረት እስከ
ራዕየ
ዮሐንስ ድረስ በአንድምታ ትርጉዋሜ ተነተናቸው:: በተለይ
ሐዲስ ኪዳንን እየመላለሰ አመሰጠረው:: ቅዱስ ሕሊናው
ሳይታክት:
ንጹሕ እጆቹ ሳይዝሉ የጻፋቸው ድርሳናት: መልዕክታትና
ትርጉዋሜያት ቢቆጠሩ አሥር ሺህ ሞሉ:: በእውነት ለዚህ
አንክሮ
ይገባል! የሚገርመው ይህን ሁሉ ሲሰራ እድሜው ገና
ለጋ: ማዕርጉም ዲቁና ነበር::

+ከዚህ በኋላ በእግዚአብሔር ትእዛዝ ቅስና ተሹሞ
በስብከተ ወንጌል ብዙ ቦታዎችን አዳረሰ:: በቅድስናው
ወደውታልና
የቁስጥንጥንያ ፓትርያርክ አድርገው ሾሙት:: አፈ ወርቅ
ሲናገርም ሆነ ሲያስተምር እንኳን የሚያወራ ኮሽ የሚል
የለም::
ከጣዕመ ትምሕርቱ የተነሳ ሕዝቡ በተደሞ ይሰሙት ነበር::

+ሲያስተምር ምድራዊው ሰው ይቅርና ልዑላኑ መላእክት
ተሰብስበው ያደንቁት ነበር:: አንዴም እመቤታችን በሕዝብ
መካከል "
አፈ-ወርቅ" ብላ ጠርታዋለች:: ለዛም ነው አፈ-ወርቅ
የሚባለው:: ቅዱሱ በሥልጣነ ቃሉ መልዐከ ሞትን ገስፆ
10 ዓመት
አቁሞታል::

+ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ለሰው ፊት አያደላም:: በርሱ
ዘንድ ንጉሥና ደሃ ነዳይ እኩል ነው:: ለሞት ያበቃውም
ይሔው
ነበር:: ምክንያቱም የወቅቱ ንግስት አውዶክስያ ያንዲት
ድሃ መበለትን መሬት ቀምታ አልመልስም በማለቷ መክሮ
አወገዛት::
እርሷ ግን ከኃጥአንና መናፍቃን ጋር መክራ 2 ጊዜ
አጋዘችው::

+በተሰደደበት ፍሬ አፍርቶ: አስተምሮና አሳምኖ በ407 ዓ/
ም አርፏል:: ቤተ ክርስቲያንና ምእመናን ሳይጠግቡት
እንደናፈቁት በ60 ዓመቱ አጡት:: በወቅቱ ታላቅ ሐዘንና
ለቅሶ ተደረገ::

+አንድ ቀን የዘመኑ ደግ ንጉሥ አርቃድዮስ ግብር አገባ
(ግብዣ አዘጋጀ):: በዚያች ሌሊት ደግሞ ቅዱሱ ሊቅ
ታጥቆ ሲጸልይ
ሳለ: አባ ማርዳሪ የሚባል ጻድቅ ደግሞ ከሰማይ 12ቱ
ሊቃነ መላእክት (እነ ቅዱስ ሚካኤል) በግርማ ሲወርዱ
ተመለከተ::

+ደንግጦ "ወዴት ናችሁ ጌቶቼ" ቢላቸው "ቁስጥንጥንያ:
ወደ ዮሐንስ አፈ ወርቅ እንሔዳለን:: እርሱ እመቤታችንን
እንደሚያመሰግናት ጌታ ነግሮናልና" አሉት:: "እባካችሁ
እኔም የአፈ ወርቅ ምስጋናው እንገለጥልኝ መርቁኝ"
አላቸው::
ሊቃነ መላእክቱም መርቀውት ጐዳናቸውን ቀጠሉ::

+በማግስቱ በቤተ መንግስት ውስጥ ሊቃውንቱ:
መሳፍንቱ: ዻዻሳቱ: ሕዝቡ ሁሉ ተሰብስበው ከድግሱ
በሉ:: ቅዱስ ዮሐንስ አፈ
ወርቅ ግን በመንበሩ ተቀምጦ ነበር እንጂ አልበላም::
ድግሱ ሲጠናቀቅ ንጉሡ አርቃድዮስ ሊቁን "ጥያቄ አለኝ"
ብሎ በጉባኤ
መካከል ጠየቀው::

+"ምነው ወንጌላዊ ማቴዎስ 'ኢያዕመራ ዮሴፍ እስከ አመ
ወለደት ወለደ ዘበኩራ-የበኩር ልጇን እስክትወልድ ድረስ
አላወቃትም'
ማለቱ (ማቴ. 1:25) ስለ ምን ነው?" ቢለው ቅዱሱ
ተነስቶ: በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ ይተረጉምለት ጀመር::

+"ድንግል ማርያም ንጹሕ ብርሌን ትመስላለች:: ብርሌ
የተለያየ ቀለም ያለው ፈሳሽ ቢያስገቡበት ቀለሙ አብሮ
ይቀያየራል::
እመቤታችንም ጌታን ጸንሳለችና ሕብረ መለኮቱ ሲለዋወጥ
መልኳ አብሮ ሲለዋወጥ እያየ ዮሴፍ ይደነግጥ ነበር::

+'እርሷ ማን ናት? በማሕጸኗ ያለውስ ማን ነው' እያለ
ይጨነቅ ነበር:: ጌታን ከወለደች በኋላ ግን አንድ ሕብረ
መልክ
ሆናለችና:: አስቀድሞ ማን እንደ ነበረች አላወቀም::

+አሁን ግን እርሷም ወላዲተ አምላክ: ልጇም አምላክ
ዘበአማን መሆኗን አወቀ ማለት ነው" እያለ ሲተረጉም
ሰምተው ሁሉም
ሲያደንቁ: በዚያ የነበረች ስዕለ አድኅኖ "አፈ ወርቅ! ልሳነ
ወርቅ! አፈ በረከት!" ስትል ተናገረች::

+ያን ጊዜ አርቃድዮስ የወርቅ ልሳን በሊቁና በስዕሏ ላይ
አደረገ:: አፈ ወርቅ ግን ባጭር ታጥቆ "እሰግድ ለኪ!
እሰግድ
ለኪ! ወእዌድሰኪ . . ." ብሎ ዛሬ በተአምረ ማርያም
የምናውቀውን ምስጋና ሰተት አድርጐ አደረሰላት:: ይህንን
ምስጋናም
ሊቃነ መላእክቱ ሰምተው እያደነቁ ወደ ሰማይ
ወጥተዋል::

+ሊቁ ባረፈ በ35 ዓመቱ: በትንሹ ቴዎዶስዮስ ዘመን:
ሥጋው ፈልሷል:: ወደ ቁስጥንጥንያ ሲደርስም ከናፍቆት
የተነሳ ታላቅ
ዝማሬና እንባ ተደርጓል:: አፈ ወርቅም ቀና ብሎ ሕዝቡን
ባርኳል::

ቅዱሱ ሲጠራ እንዲሕ ነው:-
*ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ
*አፈ በረከት
*አፈ መዐር (ማር)
*አፈ ሶከር (ስኳር)
*አፈ አፈው (ሽቱ)
*ልሳነ ወርቅ
*የዓለም ሁሉ መምሕር
*ርዕሰ ሊቃውንት
*ዓምደ ብርሃን (የብርሃን ምሰሶ)
*ሐዲስ ዳንኤል
*ሊቀ ዻዻሳት ዘበርትዕ (እውነተኛው)
*መምሕር ወመገስጽ ዘኢያደሉ ለገጽ
*ጥዑመ ቃል - - -

+እግዚአብሔር ከቅዱሱ በረከት አብዝቶ: አብዝቶ: አብዝቶ
ይክፈለን::

+ዳግመኛ በዚህ ቀን ታላቁ ጻድቅ አቡነ ተክለ ሃይማኖት
ሥጋቸው ፈልሷል:: ይሕ የተደረገው ጻድቁ ከረፉ ከ56
ዓመታት
በኋላ ነው:: በዕለቱም ድንቅ ድንቅ ተአምራት
ተፈጽመዋል::

+እናታችን ርሕርሕቷ ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ደግሞ
በዚሕ ቀን ስሟን ለጠራና መታሠቢያዋን ላደረገ የምሕረት
ቃል ኪዳን
ተቀብላለች::

❖ቸር አምላካቸው ከሁለቱም ብሩሃን ቅዱሳኑ ክብር
ያድለን::
❖ግንቦት 12 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ (የዓለም ሁሉ መምሕር)
2አቡነ ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ጻድቅ (ፍልሠታቸው)
3.ቅድስት እናታችን ክርስቶስ ሠምራ (ቃል ኪዳን
የተቀበለችበት)
4.አባ አብርሃም ዘደብረ ሊባኖስ
5.ቅዱስ ዕንባቆም ነቢይ
6.እስክንድር ንጉሠ ኢትዮዽያ
7.ቅዱስ መስቀል (የተአምር በዓሉ)
8.አባታችን ያሬድ (የማቱሳላ አባት)
9.ቅዱስ ሚናስ ዲያቆን❖ወርኃዊ በዓላት
1፡ ቅዱስ ሚካኤል ሊቀ መላእክት2፡ ቅዱስ ድሜጥሮስ
3፡ ቅዱስ ማቴዎስ ሐዋርያ
4፡ ቅዱስ ቴዎድሮስ በናድሌዎስ
5፡ አባ ሳሙኤል ዘዋልድባ
6፡ ቅዱስ ላሊበላ
7፡ ቅድስት መስቀል ክብራ

++"+ እናንተ የምድር ጨው ናችሁ . . . እናንተ የዓለም
ብርሃን ናችሁ:: በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሠወር
አይቻላትም:: መብራትንም አብርተው በዕንቅብ በታች
አይደለም እንጂ በመቅረዙ ላይ ያናሩታል:: በቤት ላሉት
ሁሉም ያበራል::
መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን
አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት
ይብራ:: +"+ (ማቴ.
5:13-16)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>

https://www.tg-me.com/zikirekdusn
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

❖ ግንቦት 13 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

+"+ ቅዱስ አርሳኒ +"+

=>ቅድስት ሃይማኖት እዚህ ዛሬ እኛ ጋር የደረሰችው
በበርካታ ሰማዕታትና ጻድቃን ደም ነው:: ቅድስት ቤተ
ክርስቲያን
ግድግዳዎቿ እንጨትና ድንጋይ እንዳይመስሏችሁ:: አጽመ
ቅዱሳን ነው እንጂ::

+ቅዱሳን ልዑለ ባሕርይ ክርስቶስን እንደ እኔ እና እንደ
ዘመኑ ትውልድ በከንፈራቸው የሚሸነግሉ አልነበሩም::
እነርሱ
በፍጹም ልባቸው ስለ ፍቅሩ ሕይወታቸውን አሳልፈው ሰጡ
እንጂ:: በቅድስናቸው ከተመሰከረላቸው ቀደምት ቅዱሳን
አንዱ ደግም
ቅዱስ አርሳንዮስ ነው::

+ቅዱሱ የተወለደው በ345 ዓ/ም ሮም ውስጥ ነው::
በወጣትነቱ ይሕ ቀረህ የማይሉት የጥበብና የፍልስፍና
ሰው ነበር::
በተለይ በትልቁ የሮም ቄሳር ቴዎዶስዮስ ዘመን በቤተ
መንግስት አካባቢ የተከበረና የንጉሡ ልጆች መምሕር
ነበር::
አኖሬዎስና አርቃዴዎስን ቀጥቶ ያሳደጋቸውም እርሱ ነበር::

+በድንግልና እስከ 40 ዓመቱ ድረስ ሮም ውስጥ ቆየ::
ከዚህ በኋላ ግን ስለ ሰማያዊ ነገሮች ሲያስብ መልዐኩ
በሕልም ወደ
ግብፅ ሒድ አለው:: በመጀመሪያ ወደ እስክንድርያ ቀጥሎ
ወደ ገዳመ አስቄጥስ ሒዶ መነኮሰ:: በቆይታ ግን
ብሕትውና ምርጫው
ሆነ::

+ቅዱስ አርሳኒ በእነዚሕ ነገሮቹ ይታወቃል:-

1.በምንም ምክንያት ከማንም ጋር አያወራም:: (ለ60
ዓመታት በአርምሞ ኑሯል)

2.በቤተ መቅደሱ ግድግዳ ተጠግቶ እንባውን ሲያፈስ
የርሱን አካል አርሶ በመሬት ላይ ሲፈስ ይታይ ነበር::
ከእንባው ብዛት
ቅንድቦቹ ተላልጠው አልቀው ነበር::

3.በርካታ ድርሳናትን ደርሷል:: ብዙዎቹ ዛሬም ግብጽ
ውስጥ አሉ::

4.ሸንጎበቱን ወደ ደረቱ አዘንብሎ ስለሚቆም ማንንም ቀና
ብሎ አያይም ነበር::

5.ለጸሎት አመሻሽ 11:00 አካባቢ ላይ ይቆምና ጸሎቱን
የሚጨርስ ፀሐይ ግንባሩን ስትመታው ነው::

6.ሁል ጊዜ ራሱን "አንተ ሰነፍ (ሐካይ) እያለ ይገስጽ
ነበር::

7.በገዳማውያን ታሪክ የርሱን ያሕል በቁመቱ ረዥም
አልተገኘም ይባላል:: የራሱ ጸጉር በጀርባው የወረደ ሲሆን
ጽሕሙን
በስዕሉ ላይ እንደምታዩት ነጭና እስከ መታጠቂያው
የወረደ ነበር::

+እነዚህ ግን በጣም ጥቂቶቹ ናቸው::

+ቅዱስ አርሳንዮስ አካሉ በተጋድሎ ደቆ: ለ60 ዓመታት
በግሩም መንፈሳዊነት ኑሮ በ100 ዓመቱ በዚሕች ዕለት
ዐርፏል::

❖አምላካችን እግዚአብሔር ከታላቁ የቅድስና ሰው አርሳኒ
በረከት አይለየን::

=>ግንቦት 13 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ አርሳንዮስ - አርሳኒ (ጠቢብ ገዳማዊ)

=>ወርኀዊ በዓላት
1.እግዚአብሔር አብ
2.ቅዱስ ሩፋኤል ሊቀ መላዕክት
3."99ኙ" ነገደ መላዕክት
4.ቅዱስ አስከናፍር
5."13ቱ" ግኁሳን አባቶች
6.አቡነ ዘርዐ ቡሩክ

=>+"+ የፍጥረት ወገን ሁሉ በሰው ይገራል:: ደግሞ
ተገርቷል:: ነገር ግን አንደበትን ሊገራ ማንም ሰው
አይችልም:: የሚገድል መርዝ የሞላበት ወላዋይ ክፋት
ነው:: በእርሱ ጌታንና አብን እንባርካለን:: በእርሱም እንደ
እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠሩትን ሰዎች እንረግማለን::
ከአንድ አፍ በረከትና መርገም ይወጣሉ:: ወንድሞቼ ሆይ
ይህ እንዲህ ሊሆን አይገባም:: +"+ (ያዕ. 3:7-11)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>

https://www.tg-me.com/zikirekdusn
የቅዱስ መስቀል ዓመታዊ የተአምር በዓል ነው።
በመስቀሉ አጥርነት ይጠብቀን።
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

❖ ግንቦት 1 5 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

+"+ ቅዱስ ናትናኤል +"+

+በቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት ከቅዱሳን ሐዋርያት
መካከል ዘግይቶ ሰማዕትነትን የተቀበለ ይህ ቅዱስ
ሐዋርያ ነው::

+ቅዱሱ ሐዋርያ የተወለደው ከእሥራኤላውያን ወላጆቹ
ጌታችን በተወለደበት ዘመን አካባቢ ነው:: ይህ በምን
ይታወቃል ቢሉ
እርሱ ሕጻን እያለ ሔሮድስ 144,000 ሕጻናትን ሲፈጅ
እርሱ ግን በእግዚአብሔር ጥበብ ተርፏል:: እናቱ
በቅርጫት ውስጥ
አድርጋ የበለስ ዛፍ ላይ አስቀምጣው ተደብቃ ታጠባው
ነበር::

+ለሐዋርያው ወላጆቹ ያወጡለት ስም ስምዖን ሲሆን
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ ናትናኤል ብሎታል::
በባልንጀሮቹ
ሐዋርያት ደግሞ የቃናው ስምዖን (ገሊላ ቃና አካባቢ
ስላደገ): አንዳንዴም ቀናተኛው ስምዖን ይሉት ነበር::
ምሑረ ኦሪት
ነበርና ዘወትር ለሕግ ይቀና ነበር::

+በገሊላ ቃና ሰርግ የደገሰው ዶኪማስ የቅዱስ ናትናኤል
የአጎት ልጅ ነው:: ጌታና ደቀ መዛሙርቱን ዶኪማስ
የጠራበት አንዱ
ምክንያትም ይሔው ነው::

+ቅዱስ ናትናኤል ኦሪትን ከገማልያል ተምሮ: ከበለስ ቁጭ
ብሎ ይተክዝ ነበር:: "መሲሕ ምነው ቀረህ" እያለም
ይተክዝ
ነበር:: ማዕምረ ኅቡዓት አምላካችን ክርስቶስ ይህንን
አውቆ በፊልዾስ አማካኝነት ጠርቶታል::

+ናትናኤል ለጊዜው ተከራክሮ ነበር:: በኋላ ግን የጌታችንን
ማንነት በደቂቃዎች ተረድቶ አምኗል:: ጌታችንም "ክዳት
ሽንገላ በልቡ ውስጥ የሌለበት ንጹሕ እሥራኤላዊ" ሲል
አመስግኖታል::

+ሐዋርያው ቅዱስ ናትናኤል ከጌታችን እግር ሥር
ምስጢረ መንግስተ ሰማያትን ተምሮ: በጸጋ መንፈስ
ቅዱስም ሰክሮ ብዙ
አሕዛብን ከጨለማ (ጣኦት አምልኮ) ወደ ብርሃን (አሚነ
ክርስቶስ) መልሷል:: እጅግ ብዙ መከራንም ተቀብሏል::

+የጌታችን ወንድም የተባለ ቅዱስ ያዕቆብ በአይሁድ
ከተገደለ በኋላም ቅዱስ ናትናኤል የኢየሩሳሌም 2ኛ
ኤዺስ ቆዾስ ሆኖ
አገልግሏል:: ከአይሁድም ዘንድ ብዙ መከራ ደርሶበታል::
በመጨረሻም በዚህች ዕለት በሰማዕትነት አልፏል::
በገድለ
ሐዋርያት ላይ እንደተጠቀሰው ቅዱሱ ሰማዕት የሆነው
በ150 ዓመቱ ነው:: ያ ማለት ደግሞ ከሐዋርያት አባቶች
በመጨረሻ
ያረፈው እርሱ ነው ያሰኛል::

❖እግዚአብሔር በቅዱስ ናትናኤል ምልጃ ሃገራችንን
ከጥፋት: ሕዝቦቿንም ከመቅሰፍት ይሰውርልን::
ከበረከቱም አይለየን::

=>ግንቦት 15 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ናትናኤል ሐዋርያ (ቀናተኛው ስምዖን)
2.ቅዱስ ሚናስ ባሕታዊ
3.ቅዱስ ቀርጢኖስ ሰማዕት
4."400" ቅዱሳን ሰማዕታት

=>ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ቂርቆስና እናቱ ኢየሉጣ
2.ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ (አፈ በረከት)
3.ቅዱስ ሚናስ ግብፃዊ
4.ቅድስት እንባ መሪና
5.ቅድስት ክርስጢና

=>+"+ ጌታ ኢየሱስ ናትናኤልን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ ስለ እርሱ 'ተንኰል የሌለበት በእውነት የእሥራኤል ሰው እነሆ' አለ:: ናትናኤልም 'ከወዴት ታውቀኛለህ?' አለው:: ጌታ ኢየሱስም መልሶ 'ፊልዾስ ሳይጠራህ ከበለስ በታች ሳለህ አየሁህ' አለው:: ናትናኤልም መልሶ 'መምሕር ሆይ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ:: አንተ የእስራኤል ንጉሥ ነህ' አለው:: +"+ (ዮሐ. 1:48-51)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>

https://www.tg-me.com/zikirekdusn
#ግንቦት_16

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ግንቦት ዐሥራ ስደስት በዚችም ቀን #ወንጌላዊው_ቅዱስ_ዮሐንስ መታሰቢያው ነው፣ ዕውቀትን ከልቡ ያፈለቀ የኢየሩሳሌሙ ሰው #ቅዱስ_ኢያሱ_ሲራክ_ነቢይና_ጠቢብ አረፈ፣ ኢትዮጵያዊው ጻድቅ #ለአቡነ_ሐዋርያ_ክርስቶስ ከዚህ ዓለም ከሞት ተሰወሩ፡፡  

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ዮሐንስ_ወንጌላዊ

ግንቦት ዐሥራ ስደስት በዚችም ቀን የወንጌላዊ ቅዱስ ዮሐንስ መታሰቢያው ነው። በእስያና በኤፌሶን በዙሪያቸው በአሉ አገሮች ሁሉ ስለ መስበኩና ከባሕር በመስጠምም ወደ ፈጣሪያቸው #እግዚአብሔር እስከ መለሳቸውና የክብር ባለቤት #ጌታችን በእጆቹ ላይ የሚያደርገው ተአምራት በትምህርቶቹም ከሰይጣን ወጥመድ እስከ አዳናቸው ድረስ ጣዖታትን ከሚያመልኩ ከክፉዎች ሰዎች ስለደረሰበት መከራ ነው።

በሸመገለም ጊዜ ወንጌልን ጻፈላቸው ሦስቱ ወንጌላውያን ያስቀሩትን እስከሚጽፍ መንፈስ ቅዱስ አነሣሥቶታልና የወልድንም አኗኗሩንና ሰው መሆኑን ዓለም የማይወስነውንም ተአምራቱን። ከዚህ በኋላም ወደ ሰማይ እንደ ወጣና በሰማይ የሚኖሩ የመላእክት ሠራዊት ሥርዓታቸውን አይቶ አቡቀለምሲስ የሚባለውን ጻፈ።

ለስብከቱም የበዓሉ መታሰቢያ ሊሆን ግብጻውያን ይህን ሠሩ ዳግመኛም በእስክንድርያ አገር ውስጥ ቤተ ክርስቲያኑ የከበረችበት ቀን ነው። (ስንክሳር ዘወርኀ ግንቦት 16)

ተጨማሪ ስለ ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ

ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌልን ለመስበክ ዕጣ የደረሰው እስያ ስለነበር ደቀ መዝሙሩን አብሮኮሮስን አስከትሎ ሄደ፡፡ ይኽችውም ኤፌሶን በጥንቱ በታናሽ እስያ በዛሬው የቱርክ ግዛት ውስጥ ከተማ ናት፡፡ ዛሬ ኢያዞሎክ ተብላ የጥንት ታሪኳ ጠፍቷል፡፡ አስቀድሞ ቅዱስ ጳውሎስ ወንጌልን ሰብኮባታል፡፡ ደቀ መዝሙሩን ቅዱስ ጢሞቴዎስንም በከተማዋ ላይ ኤጲስቆጶስ አድርጎ ሾሞት ነበር፡፡ እርሱም በግፍ እስከተገደለበት ጊዜ ድረስ ቅዱስ ዮሐንስን እየረዳው በከተማዋ ብዙ አገልግሏል፡፡ በኋላ ግን በግፍ ገድለውታል፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ ወደ ኤፌሶን ለመሄድ በመርከብ ሲሳፈር መርከቡ በማዕበል ተሰበረ፡፡ ደቀ መዝሙሩን አብሮኮሮስን መዕበሉ ወደ አንዲት ደሴት አደረሰው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ግን በመርከቡ ስባሪ ተንጠልጥሎ በባሕሩ ማዕበል መካከል 40 ቀንና 40 ሌሊት ከኖረ በኋላ ማዕበሉ ተፍቶ አብሮኮሮስ ካለበት ደሴት አደረሰውና ተያይዘው ኤፌሶን ከተማ ገቡ፡፡ የከተማይቱም ሰዎች እጅግ ክፉዎች ስለነበሩ መጀመሪያ ላይ ቅዱስ ወንጌልን መስበክ አልቻሉም ነበር፡፡ እነርሱም እጅግ ክፉዎች መሆናቸውን ስላወቀ ቅዱስ ዮሐንስ ገና ዕጣው ሲደርሰው በሀዘን አልቅሶ ነበር፡፡ አሁንም ከተማው በገቡ ጊዜ ቅዱስ ዮሐንስ ምክንያት በመፍጠር ሮምና ለምትባል ሴት የውሽባ ቤቷ እሳት አንዳጅ ሆኖ አብሮኮሮስም ዕቃ አጣቢ ሆነው ተቀጠሩ፡፡ የቀጠረቻቸው ሴትም እጅግ ታሠቃያቸው ጀመር፡፡ ባሮቿ እንደሆኑ ተስማምተው ስለጻፉላት ትደበድባቸውም ነበር፡፡

እነርሱም በታላቅ ጉስቁልና ውስጥ እየኖሩ እያለ በአንዲት ዕለት የአገረ ገዥው ልጅ ለመታጠብ ወደ ውሽባው ቤት ገባ፡፡ በውሽባ ቤቱም የሰይጣን ኃይል ስለነበረበት የመኰንኑን ልጅ አንቆ ገደለው፡፡ የአገሪቱም ሰዎች ሁሉ ለሞተው የመኰንን ልጅ ሊያለቅሱ ሲሰበሰቡ ቅዱስ ዮሐንስም አብሮ ቆሞ ሲመለከት ሮምና መጥታ ‹‹በጌታዬ ልጅ ሞት ልትደሰት መጣህን›› እያለች ረገመችው፡፡ እርሱም ‹‹አይዞሽ አትዘኚ›› አላትና ወደ ሞተው ልጅ ቀርቦ በመስቀል ምልክት ካማተበበት በኋላ በፊቱ እፍ አለበት፡፡ የሞተውም ልጅ ድኖ ተነሣ፡፡ የሀገሪቱም ሰዎች እጅግ ደነገጡ፡፡ ሮምናም ደንግጣ ‹‹ #እግዚአብሔር የሚሉት #አምላክ አንተ ነህን›› ብላ ጠየቀችው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም ‹‹በፍጹም እኔ #አምላክ አይደለሁም፣ እኔ የእርሱ አገልጋዩና ሐዋርያው ነኝ እንጂ›› አላት፡፡ ሮምናም ስለበደለቻቸው በደል ሁሉ መሪር ዕንባን እያለቀሰች ይቅር እንዲሏት ለመነቻቸው፡፡ እነርሱም አረጋጉዋት፡፡ ከሕዝቡም ውስጥ ብዙዎቹ በጌታችን አመኑ፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም ሌሎች ብዙ ድንቅ ድንቅ ተአምራትን እያደረገ ወንጌልን እየሰበከ ከጣዖት አገልጋዮች በቀር ሁሉንም አሳምኖ አጠመቃቸው፡፡ አገልጋዮችን ኤጲስቆጶሳትን፣ ቀሳውስትንና ዲያቆናትን ከሾመላቸው በኋላ ወደ ሌሎች አቅራቢያ አገሮች ሄደ፡፡

በመጨረሻም በከሃዲውና በጨካኙ በድምጥያኖስ ዘመን በጣዖት አምላኪዎች ተከሶ ለፍርድ ቀረበ፡፡ በፈላ ውኃ ካሠቃዩት በኋለ በፍጥሞ ደሴት አጋዙት፡፡ በዚያም ሳለ ራእዩን ተመልክቶ ጻፈው፡፡ ድምጥያኖስም ከተገደለ በኋላ ከግዞቱ ተመልሶ ሦስቱን መልእክታቱንና ቅዱስ ወንጌሉን ጽፏል፡፡ ጌታችንም አስቀድሞ ሞትን እንደማይቀምስ ለዮሐንስ ቃል ገብቶለት ነበርና (ዮሐ 21፡22) ጥር 4 ቀን እንደ ኤልያስና ሄኖክ ሞትን እንዳያይ ወደ ብሔረ ሕያዋን ወስታል፡፡ ዛሬ ግንቦት 16 ቀንም ዓመታዊ መታሰቢያ በዓሉ ነው፡፡ ይኸውም በእስያና በኤፌሶን በዙሪያቸውም ባሉ አገሮች ሁሉ ወንጌልን ስለመስበኩና ስለደረሰበት መከራ ስላደረጋቸውም ብዙ ተአምራት ነው፡፡ ዳግመኛም በእስክንድርያ አገር ቤተ ክርስቲያኑ የከበረችበት ዕለት ነው፡፡

#ጌታችን ለዮሐንስ ያልነገረው እርሱም ያላስተማረው ምሥጢር የለም፡፡ ወንጌሉን መጻፍ ሲጀምር ‹‹በመጀመሪያ ቃል ነበረ፣ ቃልም በ #እግዚአብሔር ዘንድ ነበረ…›› ብሎ የጌታችን ነገር ተመራምሮ ለመድረስ ሲል በመሀል መልአኩን በዮርዳኖስ ባሕር ላይ ሲሄድ አገኘው፡፡ መልአኩም የዮርዳኖስን ባሕር በእንቁላል ቅርፊት እየጨለፈ ወደ ውጭ ሲያፈስ ተመለከተው፡፡ ዮሐንስም ተገርሞ ‹‹ምን ማድረግህ ነው›› አለው፡፡ መልአኩም ‹‹የዮርዳኖስን ባሕር ቀድቼ እየደፋሁ ልጨርሰው ነው›› ሲለው ዮሐንስም መልሶ ‹‹ታዲያ በእንቁላል ስባሪ ነውን?›› አለው፡፡ መልአኩም ‹‹አዎን›› አለው፡፡ ዮሐንስም ‹‹በከንቱ ደከምክ›› አለው፡፡ ይህን ጊዜ መልአኩም መልሶ ‹‹አንተስ እንጂ ደግሞ የአምላክን መገኘት፣ አኗኗሩንም ተመራምረህ በጥበብ ለማግኘት ብለህ ‹በመጀመሪያ ቃል ነበረ፣ ቃልም በ #እግዚአብሔር ዘንድ ነበረ..› ብለህ ጀምረህ የለምን? አንተ ጌታን ተመራምረህ ካገኘህና ከደረስክበት እኔም የዮርዳኖስን ወንዝ በዚህ እንቁላል ቅርፊት ቀድቼ እጨርሰዋለሁ›› አለው፡፡ ዮሐንስም ይህን ጊዜ ደንግጦ ዝቅ ብሎ ‹‹ስሙ ዮሐንስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ…›› ብሎ ሀሳቡን ለወጠና ሌላ ታሪክ ቀጠለ፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ #ጌታችንን እስከ እግረ መስቀሉ ድረስ በመከተሉ ክርስቲያኖችን ሁሉ ወክሎ #እመቤታችንን በአደራ የተቀበለ እርሱም ለ #እመቤታችን በአደራ የተሰጠ ሲሆን #እመቤታችንን ከወሰዳት በኋላ ለ16 ዓመት እየተንከባከበ ጠብቋታል፡፡ እናቱም በሕፃንነቱ ስለሞተች እመቤታችን ናት እየተንከባከበች ያሳደገችው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ በመልኩም ከጌታችን ጋር ይመሳል ነበር፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ሥዕል የመሳል ተሰጥኦም ነበረው፡፡ #ጌታችን በተሰቀለበት ዘመን የነበረው ጢባርዮስ ቄሳር ልጁ በሽተኛ ነበር፡፡ የጌታችንን የማዳን ሥራ እየሰማ እነ ጲላጦስም ስለጌታችን የሚጽፉለትን ይሰማ ስለነበር ልጁን ከጌታችን መቃብር ላይ እንዲያኖሩለት ላከው፡፡ ልጁም ፈጥኖ ተፈወሰለት፡፡ ጢባርዮስ ቄሳርም በልጁ መዳን ምክንያት የ #ጌታችንን ውለታ ማስቀመጥ ፈልጎ የ #ጌታችንን ሥዕሉን የሚሥልለትን ሲያጠያይቅ ዮሐንስን አገናኙት፡፡ ዮሐንስም #ጌታችንን ልክ በዕለተ ዓርብ እንደተሰቀለ አድርጎ በመሣል ለጢባርዮስ ቄሳር ሰጠው፡፡ ሲሥለውም በመጀመሪያ #ጌታችንን ልክ እንደተሰቀለ ራቁቱን ነበር የሳለው፡፡ ዮሐንስ የሳለው የ #ጌታችን
ሥዕልም አፍ አውጥቶ ‹‹በመጀመሪያ አይሁድ በኢየሩሳሌም ራቁቴን ሰቀሉኝ፣ አሁን ደግሞ አንተ ድጋሚ በሮም ራቁቴን ትሰቅለኝን?›› ብሎ ተናገረው፡፡ ዮሐንስም እጅግ ደንግጦ ‹‹እንዴት አድርጌ ልሳልህ?›› ብሎ የሳለውን ሥዕል ቢጠይቀው ሥዕሉም ‹‹ከለሜዳ አልብሰህ ሳለኝ›› አለው፡፡ ዮሐንስም እንዳለው ከለሜዳ አልብሶ ከሳለው በኋላ ሥዕሉን ትኩር ብሎ ተመልክቶ ቢስመው ከንፈሩ አንድ ቀን ተኩል ያህል ተጣብቆ ቆይቷል፡፡ ዛሬም ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የምትጠቀምባቸውን የ #ጌታችንን ስነ ስቅለት የሚያሳዩ ሥዕሎች መገኛቸው ይህ ወንጌላዊው ዮሐንስ የሳለው ሥዕል ነው፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ በተለያዩ ስሞች ይጠራል፡፡ በሕይወቱና በኑሮው ሁሉ #ጌታችንን ለመምሰል ይጥር ነበርና ጌታችንም እጅግ ይወደው ስለነበር ‹‹ፍቁረ እግዚእ›› ተባለ፡፡ የታላቁ ያዕቆብ ታናሽ ወንድም ስለሆነና አባቱም ዘብድዮስ ስለሚባል ‹‹ዮሐንስ ወልደ ዘብድዮስ›› ተባለ፡፡ ለ #ጌታችን ባለው ቅናትና ከወንድሙ ጋር ሆነው ባሳዩት የኃይል ሥራ እንዲሁም የ #ጌታችንን አምላክነት በመግለጡ ‹‹ወልደ ነጎድጓድ›› ተብሏል፡፡ ነገረ መለኮትን ከሌሎቹ በበለጠ ሁኔታ አስፍቶና አምልቶ በማስተማሩ ‹‹ነባቤ መነኮት ወይም ታኦሎጎስ›› ተብሏል፡፡ ኃላፊውንና መጻዒውን ጊዜ በራእዩ ስለገለጠ ‹‹አቡቀለምሲስ›› ተባለ፣ ይህም በግሪክኛ ባለራእይ ማለት ነው፡፡ የጌታችንን መከራ መስቀሉን እያስታወሰ 70 ዘመን ሙሉ እያለቀሰ ስለኖረና ፊቱም በሀዘን ስለተቋጠረ ‹‹ቁዱረ ገጽ›› ተብሏል፡፡ ረድኤት በረከቱ ይደርብን፣ በጸሎቱ ይማረን፡፡  (ምንጭ፡- ስንክሳር ዘወርሃ ጥር፣ ቤተ ክርስቲያንህን ዕወቅ፣ የቅዱሳን ታሪክ-30)

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ በከበረ ሐዋርያ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘለዓለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ኢያሱ_ሲራክ_ነቢይና_ጠቢብ

በዚህች ቀን ዕውቀትን ከልቡ ያፈለቀ የኢየሩሳሌሙ ሰው የአልዓዛር ልጅ ኢያሱ ሢራክ አረፈ። እርሱም በጥንተ ትንቢቱ የባሕር አሸዋን የዝናም ጠብታን የዘመንን ቁጥር ማን ቈጠረ አለ።

#አብ ጋራ ስለ አለው አንድነት የጥበብ አኗኗር ከዓለም መፈጠር በፊት ነው ለጥበብ መገኛዋ ለማን ተገለጠ የጥበብ ምክሯንስ ማን አወቀ በ #እግዚአብሔር ዙፋን ላይ የምትቀመጥ እጅግ የምታስፈራ ናት አለ።

ሁለተኛም እኔ ከልዑል አፍ ወጥቼ ምድርን አንደ ጉም ሸፍንኋት በሰማያትም እኖራለሁ ዙፋኔንም በደመና ምሰሶ ላይ ዘረጋሁ ብቻዬን በሰማይ ዳርቻ ዞርኩ በውቅያኖስም ጥልቅ ውስጥ ማረፊያ እየፈለግሁ በባሕሩ ውኃ ላይ ሁሉ ተመላለስኩ አለች አለ።

ስለ ወልደ #እግዚአብሔርም ሰው መሆን እንዲህ አለ #እግዚአብሔር በያዕቆብ ዘንድ እደሪ በእስራኤልም ዘንድ ተዋረሺ አለኝ አለች። ደግሞ ስለ #መድኃኒታችን ሞትና ስለ አይሁድ መጥፋት በወጥመዱ ይጠመዳሉ የመሞቻቸው ጊዜም ሳይደርስ ይሠጥማሉ አለ። ስለ ንስሓና ከንስሓ በኋላ ወደ ኃጢአት ስለ መመለስ እንዲህ አለ ከታጠቡ በኋላ ቆሻሻን መዳሰስ ምን ይጠቅማል።

ደግሞ ስለ ቤተክርስቲያን መታነፅና ስለ ሕዝብ እንዲህ አለ። አቤቱ በስምህ የተጠሩና በበረከት ያባዛኃቸውን ወገኖችህን ይቅር በል መመስገኛህና ማደሪያህ የሆነች ሀገርህ ኢየሩሳሌምንም ይቅር በል። የቃልህንም በረከት በጽዮንና በልጆቿ ላይ ምላ።

ስለሹማምንትና ስለ ሰባቱ መዐርጋት ሲናገር እንዲህ አለ ሰባቱን ኃይሎች የተቀበለች የሰው ሰውነቱ ጉበኛ ናት። ከዚህም ሁሉ ጋር መንገድህን ያቀናልህ ዘንድ ወደ ልዑል #እግዚአብሔር ጸልይ። ስለ ጻድቃንም እንዲህ አለ የጻድቃን ልጆች በዱር ጠል የዱር አበባ እንዲ አብብ እንዲሁ ብቀሉ አብቡም እንደ ሊባኖስም መዓዛ መዓዛችሁ እንዲሁ የጣፈጠ ይሁን።

ዳግመኛም የ #እግዚአብሔርን ሥራ ሲያስብ እንዲህ አለ የሰማይን ንጽሕናውንና ጽናቱን ብርሃኑንም ያሳይ ዘንድ በሰማይ ገጽ ላይ ፀሐይን ማውጣቱን በቀትርም ጊዜ አገሩን ማቃጠሉን አስቦ። እንደ ምድጃ እሳት የሚነድ ላቦቱን ማን ይቃወመዋል የፀሐይ ዋዕይ ሦስተኛውም ተራሮችን ያቃጥላቸዋል ከእርሱም የእሳት ወላፈን ይወጣል አለ።

ጨረቃም ለዓለም ምልክቱ ነው በእርሱም የዘመናት የበዓላት ምልክት ይታወቃል። ስለ ከዋክብትም የሰማይ ጌጦቿ የከዋክብት ብርሃናቸው ነው በ #እግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃድ እንዲሁ ያበራሉና በሥርዓታቸውም ጸንተው ከልካቸውም ሳይፋለሱ ሳይሳሳቱ ጸንተው ይኖራሉና አለ።

ስለ ቀስተ ደመናም ተናገረ ቀስቱን አየሁ ፈጣሪውንም አከበረ ብርሃኑ መልካም ነውና የልዑል ሥልጣንም ያዘጋጀዋል። ስለ በረድና መብረቅም ተናገረ ስለ እርሱ ትእዛዝም በረድ ይዘንማል በቃሉም መብረቅ ይፈጥናል ደመናትም እንደ አዕዋፍ ይበራሉ ነፋስም በእርሱ ፈቃድ ይነፍሳል የነጐድጓድ ድምፅና ብልጭልጭታው ምድርን ያስፈራታል ዐውሎውና ውርጩ ነፍስን ያስጨንቃታል።

ሰማይን እንደ ብረት ልብስ የሚሸፍነው እንደ ስለታም የብርጭቆ ስባሪ ይብለጨለጫል አለ። ስለ ዝናምም ተናገረ ዝናም የወረደ እንደሆነ ምድርን ድስ ያሰኛታል በትእዛዙም ባሕር ይደርቃል አለ። አባቶችንም በተሰጣቸው ሀብት ሲያመሰግናቸው ኄኖክ #እግዚአብሔርን ደስ እንዳሰኘው። ኖኅም ጻድቅ ሁኖ እንደተገኘ።

አብርሃም ታማኝ እንደሆነ ይስሐቅም ለሰው ሁሉ የሚጠቅም በረከት እንደተሰጠው ለያዕቆብም በቸርነቱ እንደ ተገለጠለት ዐሥራ ሁለቱንም ነገድ እንደወለዳቸው በሰውና በ #እግዚአብሔርም ዘንድ እንደ ተወደዱ። ሙሴንም ስም አጠራሩ የከበረ የምላእክትም ብርሃን መልኩና ስም አጠራሩ የሆነ አለ። ወንድሙ አሮንንም የዘላለም ሕግን እንደ ሠራለት በልብሰ ተክህኖና በወርቅ አክሊል እንዳስደነቀው አለ። ሹመቱ ሦስተኛ የሚሆን የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስንም ወደሰ።

የነዌ ልጅ ኢያሱን ለእስራኤል ልጆች የርስታቸውን ምድር እንዳወረሳቸው እጁንም በአነሣ ጊዜ እንደተመሰገነ። ሳሙኤልንም በ #እግዚአብሔር ዘንድ የተወደደ እንደሆነ ናታንንም በዳዊት ዘመን ትንቢት እንደተናገረ። ዳዊትንም ታናሽ ሁኖ ሳለ አርበኛውን ጎልያድን እንደገደለው አምስግኖታል ሰሎሞንንም በሰላም ወራት እንደነገሠ።

ኤልያስንም ሙት እንዳስነሣ እሳትንም ከሰማይ እንዳወረደ ራሱም በእሳት ሠረገላና በእሳት ፈረሶች እንደዐረገ። ኤልሳዕንም በዘመኑ ጠላቶች እንዳስደነገጡት ሁለት ሙታኖችንም እንዳስነሣ አንዱን በሕይወት ሳለ አንዱን ከሞተ በኋላ።

ሕዝቅያስንም አገሩን አጽንቶ እንደ ጠበቀ የፋርስንም ሠራዊት በጸሎቱ አጥፍቶ ስለ ሀገራቸው ጽዮን የሚያለቅሱትን ደስ እንዳሰኛቸው ርኵሰትንና ኃጢአትንም እንደ አስወገደ ኢዮስያስንም የኢዮስያስ ስም አጠራሩ መልካም ነው እንዳለው።

ኤርምያስንም ከእናቱ ማሕፀን ጀምሮ እንዳከበረው። ሕዝቅኤልም የእግዚአብሔርን ጌትነቱን እንዳየ። ዘሩባቤልንም በቀኝ እጅ እንዳለ ኀቲም ቀለበት ነው እንዳለው።

ዐሥራ ሁለቱ ነቢያትንም በየቦታቸው ዐፅማቸው እንደሚለመልም። ሆሴዕና ነህምያንም የወደቀች ቅጽርን አንሥተው ጠቃሚ ሥራ እንደሠሩ። ዮሴፍንም እርሱን የመሰለ ደግ ሰው እንዳልተወለደ። ኖኅና ሴምንም ክብራቸው ከሰው ሁሉ እንደሚበልጥ። አዳምንም በፍጥረት ሁሉ ላይ ንጉሥ እንደ ሆነ።

ስምዖንን በዘመኑ ቤተ መቅደስ እንደታነፀ በሕዝቡ ከምርኮ መመለስም እንደ ተመሰገነ በመጽሐፉ መጨረሻም። በሁሉ ቦታ ታላላቅ ሥራ የሚሠራና ዕድሜያችንን የሚያስረዝም #እግዚአብሔር አምላክን አመስግኑት አለ። ይህንንም ተናግሮ በፍቅር አንድነት አረፈ።

#ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘለዓለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
#አቡነ_ሐዋርያ_ክርስቶስ

በዚህች ቀን ኢትዮጵያዊው ጻድቅ ለአቡነ ሐዋርያ ክርስቶስ ከዚህ ዓለም ከሞት ተሰወሩ፡፡   አቡነ ሐዋርያ ክርስቶስ የትውልድ ሀገራቸው ሸዋ መርሐ ቤቴ ነው፡፡ እንደ እነ ኤልያስና ሄኖክ ተሰውረዋል እንጂ በምድር ላይ ሞትን አልቀመሱም፣ ገና ወደፊት መጥተው በሰማዕትነት ይሞታሉ፡፡ ልደታቸው ሐምሌ 16 ቀን ነው፡፡ የነበሩበት ዘመንም በጻድቁ ንጉሥ በዐፄ ገብረ ማርያም ሐርበይ ዘመን ነው፡፡ ጻድቁን መልአኩ ከሚያገለግሉበት ከወሎ የህላ ሚካኤል ወደ ደብረ በንኮል ገዳም ወስዷቸው እንዲመነኩሱ አድርጓቸዋል፡፡ የቆረቆሩት ‹‹አቡነ ሐዋርያ ክርስቶስ ገዳም›› ወሎ መሐል ተከዜ ውስጥ ይገኛል፡፡ የበዛው ገድላቸው በዝርዝር ተጽፎ አይገኝም፡፡ ተከዜ በረሃ ላይ እጅግ አስደናቂ ትልቅ የአንድነት ገዳም አላቸው፡፡ 12 ክንፍ የተሰጣቸው ታላቁ ጻድቅ አቡነ ሐዋርያ ክርስቶስ በዛሬዋ ዕለት ነው የተሠወሩት፡፡

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

#ግንቦት_16_ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

1.ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ (ስብከቱና ቅዳሴ ቤቱ)
2.ቅዱስ ኢያሱ ሲራክ ነቢይና ጠቢብ (መጽሐፈ ሲራክን የጻፈ)
3.ቅድስት እናታችን ዐስበ ሚካኤል (ኢትዮዽያዊት)
4. አቡነ ሐዋርያ ክርስቶስ ከዚህ ዓለም ከሞት የተሰወሩበት


#ወርኀዊ_በዓላት

1.ኪዳነ ምሕረት (የሰባቱ ኪዳናት ማሕተም)
2.ቅድስት ኤልሳቤጥ (የመጥምቁ ዮሐንስ እናት)
3.ቅዱስ ገብረ ማርያም ጻድቅ ንጉሠ ኢትዮዽያ
  (የቅዱስ ላሊበላ ወንድም)
4.ቅዱስ አኖሬዎስ ንጉሥ ጻድቅ
5.አባ አቡናፍር ገዳማዊ
6.አባ ዮሐንስ ወንጌሉ ዘወርቅ
7.አባ ዳንኤል ጻድቅ

📖"በጌታ ኢየሱስ መስቀል አጠገብ እናቱ፡ የእናቱም እህት፡ የቀለዮዻም ሚስት ማርያም፡ መግደላዊትም ማርያም ቆመው ነበር። ጌታ ኢየሱስም እናቱን፡ ይወደው የነበረውንም ደቀ መዝሙር በአጠገቡ ቆሞ ባየ ጊዜ እናቱን 'አንቺ ሆይ! እነሆ ልጅሽ' አላት። ከዚህ በሁዋላ ደቀ መዝሙሩን 'እናትህ እነሁዋት' አለው። ከዚህም ሰዓት ጀምሮ ደቀ መዝሙሩ ወደ ቤቱ ወሰዳት።"
(ዮሐ. 19:25)

ወስብሐት ለእግዚአብሔር


(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ግንቦት እና #ከገድላት_አንደበት)
🌿እንኳን ለታላቁ የቤተ ክርስቲያን ጠበቃ ቅዱስ ኤዺፋንዮስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።

በስመ አብ፡ ወወልድ፡ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ

♱ቅዱስ ኤዺፋንዮስ

📝ሊቁ ቅዱስ ኤዺፋንዮስ ጽድቅ ከቅድስና : ድርሰት ከጥብቅና የተሳካለት አባት ነው:: "ኤዺፋንያ" ማለት የመለኮት መገለጥ ሲሆን "ኤዺፋንዮስ" ማለት ደግሞ ምሥጢረ መለኮት የተገለጠለት ማለት ነው።

💡ቅዱስ ኤዺፋንዮስ የተወለደው ክርስቶስን ከሚጠሉ አይሁዳውያን ቤተሰቦች ቤተ ገብርኤል ውስጥ ነው። ቤተሰቦቹ ከአንድ አህያ በቀር ምንም የሌላቸው ድሆች ነበሩ። በዚያ ላይ በልጅነቱ አባቱ በመሞቱ ከእናቱና ከአንዲት እህቱ ጋር በረሃብ ሊያልቁ ሆነ። ሕጻኑ ኤዺፋንዮስ በአህያው እንዳይሠራ አህያው ክፉ ነበርና ሊሸጠው ገበያ አወጣው።

📝ፊላታዎስ ከሚባል ክርስቲያን ጋር ለግዢ ሲደራደሩ አህያው የኤዺፋንዮስን ኩላሊቱን ረግጦት ለሞት አደረሰው:: በዚህ ጊዜ አብሮት ያለው ክርስቲያኑ በትእምርተ መስቀል አማትቦ አዳነው:: በፈንታው ግን አህያው ሞተ:: ሕጻኑ ኤዺፋንዮስ እያደነቀ ሔደ።

📝ከቆይታ በኋላ ሀብታም አጎቱ ገንዘቡን አውርሶት በመሞቱ ገና በ16 ዓመቱ ባለጠጋ ሆነ:: ያቺ ገበያ ላይ ያያት ተአምር ግን በልቡ ውስጥ ትመላለስ ነበር።

💡አንድ ቀን ደግሞ ሉክያኖስ ከሚባል ክርስቲያን ጋር ሲሔዱ ነዳይ አገኙ:: ባለጠጋው ኤዺፋንዮስ አለፈው:: ያ ድሃ ክርስቲያን ግን የለበሳትን አውልቆ መጸወተው:: በዚሕ ጊዜ መልዐኩ መጥቶ የብርሃን ልብስ ሲያለብሰው ኤዺፋንዮስ ተመለከተ።

📝ኤዺፋንዮስ ጊዜ አላጠፋም:: ከእህቱ ጋር በክርስቶስ አምኖ ተጠመቀ:: ሃብት ንበረቱን ግማሹን መጸወተ:: በተረፈው ደግሞ መጻሕፍትን ገዝቶ ወደ አባ ኢላርዮን ገዳም ገባ:: በዚያም መናንያኑ እስኪያደንቁት ድረስ በፍጹም ትጋትና ቅድስና ተጋደለ። በጸሎቱ ዝናም አዘነመ : ድውያንን ፈወሰ : ብዙ ተአምራትንም አደረገ።

📝 እግዚአብሔርም ደግሞ ለሌላ አገልግሎት ሽቶታልና በቆዽሮስ ደሴት ላይ ዻዻስ ሆኖ ተሾመ:: ብሉይ ከሐዲስ የወሰነ ሊቅ ነውና ብዙ መጻሕፍትን ተረጎመ:: በሺሕ የሚቆጠሩ ድርሳናትን ደረሰ:: በአፍም በመጽሐፍም ብሎ መናፍቃንንና አይሁድን ምላሽ በማሳጣቱ ቤተ ክርስቲያን "ጠበቃየ" ትለዋለች።

📝ከደረሳቸው መጻሕፍት መካከል "ሃይማኖተ አበው ዘኤዺፋንዮስ : መጽሐፈ ቅዳሴውና አክሲማሮስ (ስነ ፍጥረት)" ዛሬም በቅርብ ይገኛሉ:: ሊቁ ቅዱስ ኤዺፋንዮስ በመልካም እረኝነትና በሚደነቅ ቅድስና ተመላልሶ በ406 ዓ.ም. ዐርፏል:: እድሜውም 96 ዓመት ያህል ነበር።

🤲አምላካችን ከቅዱሱ ሊቅ በረከት ያድለን!

🗓 ግንቦት 17 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

1. ቅዱስ ኤዺፋንዮስ ሊቅ (ዘደሴተ ቆዽሮስ)
2. ቅዱስ ኢላርዮን ገዳማዊ
3. አባ ሉክያኖስ ጻድቅ
4. ቅዱስ ፊላታዎስ ክርስቲያናዊ

🗓 ወርኀዊ በዓላት

1. ቅዱስ እስጢፋኖስ ሊቀ ዲያቆናት (ቀዳሜ ሰማዕት)
2. ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ወልደ ዘብዴዎስ)
3. ቅዱሳን አበው መክሲሞስና ዱማቴዎስ
4. አባ ገሪማ ዘመደራ
5. አባ ዸላሞን ፈላሢ
6. አባ ለትጹን የዋህ

📖"የሚታገልም ሁሉ በነገር ሁሉ ሰውነቱን ይገዛል። እነዚያም የሚጠፋውን አክሊል ሊያገኙ ነው። እኛ ግን የማይጠፋውን። ስለዚህ እኔ ያለ አሳብ እንደሚሮጥ ሁሉ እንዲሁ አልሮጥም። ነፋስን እንደሚጐስም ሁሉ እንዲሁ አልጋደልም። ነገር ግን ለሌሎች ከሰበክሁ በኋላ ራሴ የተጣልሁ እንዳልሆን ሥጋዬን እየጐሰምሁ አስገዛዋለሁ።'' (1ቆሮ. 9:25)

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
2024/09/23 17:26:39
Back to Top
HTML Embed Code: