Telegram Web Link
†††እንኳን ለታላቁ ሊቅና ጻድቅ ቅዱስ አንስጣስዮስ እና አቡነ ዓምደ ሥላሴ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱስ አንስጣስዮስ ሊቅ †††

††† ቅዱስ አንስጣስዮስ በ4ኛው ክ/ዘመን የተነሳ ሶርያዊ የነገረ መለኮት ሊቅ: ገዳማዊ ጻድቅና የመንበረ አንጾኪያ ሊቀ ዻዻሳት ነበር:: ቅዱሱ ርጉም አርዮስን ካወገዙ 318ቱ ቅዱሳን ሊቃውንት አንዱ ነው:: በወቅቱ ታላላቅ ሊቃነ ዻዻሳት ሱባኤውንና ጉባኤውን የመሩ ሲሆን አንዱ ይህ ቅዱስ ነው::

ከ 5 ዓመታት በሁዋላም ብዙ ድርሳናትን ጽፎ: ሐዋርያዊ አገልግሎቱን ፈጽሞ በ330 ዓ/ም አርፏል:: ያረፈው ግን አርዮሳውያን ባቀረቡት ክስ በሃሰት ተመስክሮበት በግፍ ተሰዶ ነው:: ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ስለ ውለታው የውዳሴ ድርሳን ጽፎለታል::

††† አቡነ ዓምደ ሥላሴ †††

††† እኒህ ታላቅ ጻድቅ ሐዋርያዊ አባት አቡነ ዓምደ ሥላሴ የትውልድ ሃገራቸው ጎጃም ሲሆን የተወለዱት በዚሁ ዕለት (የካቲት 27) ነው:: ጻድቁ በአጼ ሱስንዮስ (በ17ኛው መቶ ክ/ዘ) የነበሩ ድንቅ ሠሪ : ተአምረኛና ገዳማዊ አባት ናቸው::

የካቲት 16 ቀን መንኩሰው ወደ ተጋድሎ ገብተዋል:: በዋልድባ በነበራቸው ቆይታም እመቤቴ ኪዳነ ምሕረት የካቲት 16 ቀን እንድትከበር ማድረጋቸውም ይነገራል:: ጻድቁ በሌሎች ገዳማትም የነበሩ ሲሆን ዛሬም ድረስ ረድኤታቸው የሚደረግበት : ስማቸው የሚጠራበት ገዳም ግን ማኅበረ ሥላሴ ይባላል::

ገዳሙ የሚገኘው በሃገራችን ሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ : በመተማ በርሃ ውስጥ ነው:: ይህንን ቅዱስ ገዳም የመሠረቱትም ራሳቸው አባ ዓምደ ሥላሴ ናቸው:: ገዳሙ ዛሬም ብዙ ምሑራንና መናንያን ያሉበት : በደህና ሁኔታም የሚገኝ ነው:: ግን በርሃውን የኔ ብጤ ደካማ ሰው የሚችለው አይደለም::

ስለ ጻድቁ ዓምደ ሥላሴ ከሚነገሩ ታሪኮች ቅድሚያውን የሚይዘው የተዋሕዶ ጠበቃነታቸው ነው:: በ1603 ዓ/ም ዼጥሮስ (ፔድሮ) ፓኤዝ የሚባል ካቶሊካዊ እሾህ ወደ ሃገራችን ገብቶ ነበርና ንጉሡን ሱስንዮስን አባብሎ ተዋሕዶን አስካዳቸው:: ነገሩ ውስጥ ለውስጥ ሲበስል ቆይቶ በ1609 ዓ/ም በመገለጡ እነ ራስ ዮልዮስ ለሃይማኖታቸው ጠዳ ላይ ተዋግተው ግንቦት 6 ቀን ተሰው::

ይህ ነገር ሲሰማ ወንድ ሴት : ትልቅ ትንሽ ሳይመረጥ በገጠሩም : በከተማውም : በገዳሙም ያሉት ሁሉ የተዋሕዶ ልጆች መንቀሳቀስ ጀመሩ:: 7 ዓመታት እንዲህ አልፈው በ1616 ዓ/ም ግጭቱ በይፋ ተጀመረ::

"ተዋሕዶን ካልካዳችሁ" በሚል በቀን እስከ 8,000 ሰው በሰይፍ ታረደ:: ይህን ያደረጉት ደግሞ አልፎንሱ ሜንዴዝ : ንጉሡ ሱስንዮስና ጀሌዎቻቸው ነበሩ::

በጊዜውም ከቤተ መንግሥት እነ ንግሥት ወልድ ሰዓላ (የሱስንዮስ ሚስት) : ከጻድቃን አበው ዘርዓ ቡሩክ ዘግሺ : ሐራ ድንግል ዘደራ : ምዕመነ ድንግል ዘጩጊ : ዓምደ ሥላሴ ዘማኅበረ ሥላሴ . . . ከቅዱሳት እነ ፍቅርተ ክርስቶስ : ወለተ ዼጥሮስ : ወለተ ዻውሎስ : እኅተ ዼጥሮስ . . . ለሃይማኖታቸው ተዋሕዶ ጥብቅና ቆመው ሕዝቡን አስተማሩ:: መከራም ተቀበሉ::

ብዙ ኢትዮዽያውያን የመከራ ጽዋን ተጐንጭተው ለክብር ከበቁ በሁዋላ የእግዚአብሔር ፍርድ ተገለጠ:: በጻድቃኑ እነ አባ ዓምደ ሥላሴ ሐዘን ንጉሡ ታመመ:: ምላሱ ተጐልጉሎ ወጣ::

በዚህ ጊዜ አቤቶ ፋሲለደስ ለአባ ዓምደ ሥላሴና ለሌሎቹ ቅዱሳን "አባቴን አድኑልኝ! ተዋሕዶም ትመለስ" አላቸው:: ጻድቁም ከባልንጀሮቻቸው ጋር ጸልየው ንጉሡን አዳኑት:: በፈንታውም ይህንን አሳወጁ::

††† ፋሲል ይንገሥ!
ሃይማኖት (ተዋሕዶ) ይመለስ!
የሮም ሃይማኖት ይፍለስ! †††

ከዚህ በሁዋላ በ1624 ዓ/ም ፋሲል ሲነግሥ አባ ዓምደ ሥላሴ ለገዳማቸው ብዙ ቦታ አስከልለው : በተጋድሎ ኑረው በዚህች ቀን ዐርፈዋል::

††† አምላከ ቅዱሳን በቀናችው እምነት ተዋሕዶ ሁላችንም እስከ ፍጻሜ ዘመናችን ያጽናን:: ከበረከተ ቅዱሳንም ይክፈለን::

††† የካቲት 27 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.አባ አንስጣስዮስ ርቱዓ ሃይማኖት (ዘአንጾኪያ)
2.አቡነ ዓምደ ሥላሴ

††† ወርኀዊ በዓላት
1.የጌታችንና አምላካችን መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ በዓለ ስቅለት
2.አቡነ መብዐ ፅዮን ጻድቅ
3.ቅዱስ መቃርስ (የመነኮሳት ሁሉ አለቃ)
4.ቅዱስ ፊቅጦር ሰማዕት
5.ቅዱስ ያዕቆብ ዘግሙድ
6.ቅዱስ ገላውዴዎስ ሰማዕት (ንጉሠ ኢትዮዽያ)
7.ቅዱስ ቢፋሞን ጻድቅና ሰማዕት

††† "የተጠራችሁለት ለዚህ ነው:: ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሏልና:: እርሱም ኃጢአት አላደረገም:: ተንኮልም በአፉ አልተገኘበትም:: ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም:: መከራንም ሲቀበል አልዛተም . . . እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ::" †††
(1ዼጥ. 2:21-25)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
Audio
""🛑 የዐቢይ ጾም መግቢያ ትምህርት ""

እንዴት እንጹም?

(መጋቢት 1 - 2016)

በዩቲዩብ ለምትፈልጉ👉https://youtu.be/3TJdP3s6PB8?si=6oGh5kG5IFTh0s46


ዝክረቅዱሳን ማኅበረ ቅዱስ ዳዊት

" ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"::/የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ) እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::
       አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ /መጽሐፈ ምሥጢር

https://www.tg-me.com/zikirekdusn
✞ እንኩዋን ለታላቁ "የጌታ ጾም (ጾመ እግዚእ)" በሰላም አደረሳችሁ ✞

+*" ጾመ እግዚእ "*+

=>ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በአዋጅ ምዕመናን
እንዲጾሟቸው የሠራቻቸው 7 አጽዋማት አሏት:: "ጾም" ማለት "መከልከል" ነው:: የምንከለከለው ደግሞ ከኃጢአትና ከክፋት ሲሆን አንድም ሰውነትን ወደዚያ ከሚወስዱ አዝማደ መባልዕት (የምግብና የመጠጥ ዓይነቶች) መከልከልን ይመለከታል::

+"7ቱ" አጽዋማት:-
1.ዓቢይ ጾም
2.ጾመ ፍልሠታ
3.ጾመ ሐዋርያት
4.ጾመ ነቢያት
5.ጾመ ድኅነት
6.ጾመ ነነዌ እና
7.ጾመ ገሃድ ይሰኛሉ::

+በእነዚህ አጽዋማት ከዓቢይ ጾም በቀር እስከ 9 ሰዓት
ድረስ መጾም ይገባል:: ዓቢይ ጾም ግን የተለየ ሥርዓት
አለው:: ስለ ጾም ሲነሳ አስቀድሞ የሚመጣው ጥያቄ
አስፈላጊነቱ ነው:: "ጾም ለምን ያስፈልጋል?" ብሎ
ከመጠየቅ "ሃይማኖት ለምን ያስፈልጋል?" ብሎ
መጠየቁ ይቀላል::

+ምክንያቱም ከሃይማኖታዊ ትዕዛዛት ትልቁ በመሆኑ
እርሱን መቃወም ሃይማኖትንና አዛዡን እግዚአብሔርን
መቃወም ነውና:: እኛ ሃገር ላይ የተለመደች ክፉ ልማድ
አለች:: የከበደችንን ነገር "አያስፈልግም" በሚል
እንከራከራለን::

+ደግሞ ጾምን ለመሻር ጥቅስ የሚጠቅሱ ወገኖች
በጣም ይገርሙኛል:: ኃጢአትን ለመሥራት : ጾምንም
ለመሻር ጥቅስን መጥቀስ አያስፈልግም:: እኛ ግን
¤ከፈጣሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጀምሮ (ማቴ. 4:2)

¤አበው ቅዱሳን ጾመው (ዘዳ. 9:19, ነገ. 19:8, ሐዋ.
13:3, ቆሮ. 4:11) አሳይተውናልና እንደ አቅማችን
እንጾማለን::

+የጾሙ የመጀመሪያው ሳምንት (ዘወረደ) የሚጾመው
እስከ 12 ሰዓት ሲሆን ከቅድስት (ከ2ኛው ሳምንት) እስከ
ተጽኢኖ (የኒቆዲሞስ ዓርብ) ድረስ ደግሞ እስከ 11
ሰዓት ይጾማል::
በሰሙነ ሕማማት ግን የምንጾመው "እስከ ይሠርቅ
ኮከብ" (እስከ ምሽት 1 ሰዓት) ድረስ ይሆናል::

+ነገር ግን ሁሉም እንደ መጠኑ ነውና ከመምሕረ ንስሃ
ጋር ሊጨዋወቱት ይገባል:: በዓቢይ ጾም ለቻለ ቂጣ
በጨው እየበላ: ውሃ እየተጐነጨ ሊጾም ይገባል::
በእነዚህ 55 ቀናትም ከዕለተ ሆሳዕና በቀር ከበሮ
አይጐሰምም:: ጸናጽል አይጸነጸልም:: ተድላ ደስታም
አይደረግም::

+አብዝቶ መብላት : ሳቅ ማብዛትና ጌጥን ማብዛትም
እንዲሁ አይገባም:: ለቻለ ደግሞ በሌሊት ሰዓታቱን፡
በግህ ኪዳንና ስብሐተ ነግሁን : በመዓልት ቅዳሴውን :
በሰርክ (ምሽት) ደግሞ ምሕላውን ሊሳተፍ ይገባል::

+በእነዚህ 55 ቀናት ፈቃደ ሥጋ ሊደክም : ፈቃደ ነፍስ
ልትሰለጥን ግድ ነውና:: ከሌላው ጊዜ በተሻለ ወቅቱ
ምጽዋትና ጸሎት የሚደረግበት ነው:: በዚያውም ላይ
ነገሮችን እያመቻቹ በእነዚህ ዕለታት ቅዱስ ቃሉን
መስማት (ማንበብ) ይገባል:: በትዳር ውስጥ ላሉም
መኝታን መለየት ግድ ነው::

=>ከ7ቱ አጽዋማት አንዱ የሆነው ይህ ጾም=
1.ዐቢይ (ታላቁ) ጾም
2.የጌታ ጾም
3.ጾመ ሑዳድ
4.የድል ጾም
5.የካሳ ጾም
6.አርባ ጾም
7.የፍቅር ጾም . . .
በሚሉ መጠሪያዎችም ይታወቃል::

=>የጾሙ መግቢያ የመጀመሪያ ሳምንት ደግሞ=
1.ጾመ ሕርቃል
2.ጾመ በረከት ዘሐዋርያት
3.ሰሙነ ዘወረደም ይባላል::

=>ጾሙን የሰላም : የፍቅር : የምሕረት : የፀጋ :
የበረከት ያድርግልን:: ጾሞ ለማበርከትም ያብቃን፡፡

=>+"+ አሁንስ ይላል እግዚአብሔር በፍጹም ልባችሁ
በጾምም በልቅሶና በዋይታ ወደ እኔ ተመለሱ:: ልባችሁን
እንጂ ልብሳችሁን አትቅደዱ:: አምላካችሁም
እግዚአብሔር ቸርና መሐሪ: ቁጣው የዘገየ: ምሕረቱም የበዛ: ለክፋትም የተጸጸተ ነውና ወደ እርሱ ተመለሱ:: +"+ (ትን. ኢዩኤል 2:12)

✞ ወስብሐት ለእግዚአብሔር ✞
††† እንኳን ለአባታችን ቅዱስ ቆዝሞስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቆዝሞስ ሊቀ ጳጳሳት †††

††† "ጳጳስ" ማለት "አባት - መሪ - እረኛ" ማለት ነው:: በቅድስት ቤተ ክርስቲያን አስተምሕሮ በሐዲስ ኪዳን የመንፈሳዊ ስልጣን ደረጃዎች በጥቅሉ 3 ናቸው:: እነሱም ዲቁና: ቅስና: ጵጵስና ሲሆኑ በሥራቸው ወደ 9 ያህል ክፍሎች አላቸው:: ከእነዚህም ከፍተኛው ስልጣን ጵጵስና ነው::

ጵጵስና ማለት የክርስቶስን መንጋ እንደ ባለቤቱ አድርጐ መጠበቅ ማለት ነው:: ሥልጣኑ በምድር "ሸክም: ዕዳ" ሲሆን በሰማይ ግን "ክብር" ነው:: ማንም በሥጋው ላይ ካልጨከነ በቀር ጵጵስናን አይመኝም::

ቅዱስ ጳውሎስ "ሠናየ ግብረ ፈተወ - ማንም ጵጵስናን ቢመኝ መልካም ሥራን ተመኘ" (1ጢሞ. 3:1) ማለቱን ይዞ "ሹሙኝ" ማለት ወደ ማይጠፋ እሳት የሚያስጥል ከባድ ውሳኔ ነው:: ምክንያቱም አንድ ክርስቲያን የሚጠየቅ በራሱ ኃጢአት ሲሆን አንድ ካህን ደግሞ ስለ ልጆቹ ይጠየቃል:: የከፋው ግን የጳጳሱ ነው::

አንድ ጳጳስ ቢጾም ቢጸልይም እንኳ ለድኅነቱ በቂ አይደለም:: ምክንያቱም በመንበሩ ላይ ያስቀመጠው መንጋውን እንጂ ራሱን እንዲያድን አይደለምና:: ጌታ እንዳለ መልካም እረኛ "ይሜጡ ነፍሶ ቤዛ አባግኢሁ - መልካሙ እረኛ ስለ በጐቹ ቤዛ ራሱን አሳልፎ የሚሰጥ ነው::" (ዮሐ. 10) ስለዚህም ክህነት ( ጵጵስና) ሐዋርያዊ አገልግሎት ከባድም ኃላፊነት ነው::

አባቶቻችን ሐዋርያትና ተከታዮቻቸው ሐዋርያውያን ታላላቅ የጵጵስና መንበሮችን መሥርተው: ትምሕርቱን ከነ ወንበሩ አስተላልፈዋል:: ከእነዚህ መንበረ ጵጵስናዎች አራቱ የበላይ ናቸው::

እነዚህም የቅዱስ ጴጥሮሱ የሮም: የቅዱስ ዮሐንሱ የአንጾኪያ: የቅዱስ ማርቆሱ የእስክንድርያና የቅዱስ ጳውሎሱ የኤፌሶን መናብርት ናቸው::

እነዚህ መንበሮችም ከክርስቶስ ዕርገት እስከ 443 (451) ዓ/ም: ጉባኤ ኬልቄዶን ድረስ በአንድነት ቆይተው ተለያይተዋል:: ከእነዚህ መናብርት መካከል የእስክንድርያው (የግብጹ) እና የአንጾኪያው (የሶርያው) ዛሬም ድረስ በተዋሕዶ እምነት የጸኑ ናቸው::

የእኛ ቤተ ክርስቲያንም ሐዋርያዊት እንደ መሆኗ ሐዋርያትን መስለው: ሐዋርያትን አህለው የተነሱ አበው ጳጳሳትን በየጊዜው በበዓላት ታስባለች: ታከብራለች::

በተለይ ደግሞ የእስክንድርያና የአንጾኪያ በርካታ አባቶችን እናከብራለን:: እነርሱ ለቀናች ሃይማኖትና ለመንጋው ሲሉ ብዙ መከራን በአኮቴት ተቀብለዋልና:: ከእነዚህም መካከል አንዱ ቅዱስ ቆዝሞስ የእስክንድርያ (የግብጽ) 58ኛ ሊቀ ጳጳሳት የነበረ አባት ነው:: ዘመኑ እስልምና የሰለጠነበት ነበርና በዚያ ጊዜ እረኝነት (ጵጵስና) መመረጥ እንደ ዛሬው ዘመን ሠርግና ምላሽ አልነበረም:: በከሃዲዎች እሳትና ስለት መከራን ለመቀበል መወሰን እንጂ::

ከ6ኛው መቶ ክ/ዘመን በኋላ በዓለማችን ከተነሱ ሊቃነ ጳጳሳት ለግብጻውያኑ ቤተ ክርስቲያን ልዩ ቦታ አላት:: ምክንያቱም በወቅቱ በጎቻቸውን (ምዕመናንን) ለመጠበቅ ከግብጽ ከሊፋዎች የግፍ ጽዋዕን ጠጥተዋልና:: ከነዚህም አንዱ የእመቤታችን ፍቅር የበዛለትና በዚህ ቀን ያረፈው ቅዱስ ቆዝሞስ ነው::

††† አምላከ ቅዱሳን ሊቃውንት በጸሎታቸው እኛንም: ቤተ ክርስቲያናችንንም ከክፉ ጠላት ይጠብቅልን::

††† መጋቢት 3 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ አባ ቆዝሞስ (የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት)
2.አባ በርፎንዮስ ክቡር

††† ወርኀዊ በዓላት
1.በዓታ ለእግዝእትነ ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ
2.ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና
3.ቅዱሳን ሊቃነ ካህናት አበው (ዘካርያስና ስምዖን)
4.አባ ሊባኖስ ዘመጣዕ
5.አቡነ ዜና ማርቆስ
6.አቡነ መድኃኒነ እግዚእ ዘደብረ በንኮል

††† "ነገር ግን ወንድሞች ሆይ! እናንተ የተማራችሁትን ትምህርት የሚቃወሙትን: መለያየትንና ማሰናከያን የሚያደርጉትን ሰዎች እንድትመለከቱ እለምናቹሃለሁ:: ከእነርሱ ዘንድ ፈቀቅ በሉ:: እንዲህ ያሉት ለገዛ ሆዳቸው እንጂ ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ አይገዙምና:: በመልካምና በሚያቆላምጥ ንግግርም ተንኮል የሌለባቸውን ሰዎች ልብ ያታልላሉ::" †††
(ሮሜ ፲፮፥፲፯)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
††† እንኳን ለሐዋርያው ቅዱስ ማትያስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ሐዋርያው ቅዱስ ማትያስ †††

††† በቅድስት ቤተ ክርስቲያን አስተምሕሮ ከእመቤታችን በቀር ከቅዱሳን ሐዋርያት የሚበልጥ አልተነሳም:: "ሐዋርያ" ማለት "ፍንው: ልዑክ: የተላከ: የጽድቅ መንገደኛ" እንደ ማለት ነው:: በምሥጢሩ ግን "ባለሟል" ብለው ሊቃውንቱ ተርጉመውታል::
ይህስ እንደምን ነው ቢሉ:-
¤የፍጥረታት ሁሉ ጌታ: የክብር ባለቤት መድኃኔ ዓለም ከድንግል ማርያም ተወልዶ: አድጐ: ተጠምቆ: ጾሞ: ከገዳመ ቆረንቶስ ሲመለስ ቀዳሚ ሥራው ያደረገው ደቀ መዛሙርቱን መጥራት ነበር::

ከተከተሉት የ5 ገበያ ሕዝብ መካከል "ወሐረየ እምሰብአ ዚአሁ አሠርተ ወክልኤተ ሐዋርያተ" እንዲል በመጀመሪያ 12ቱን ሐዋርያት መረጠ::

††† እሊህም:-
1.ዼጥሮስ የተባለ ስምኦን
2.እንድርያስ (ወንድሙ)
3.ያዕቆብ ወልደ ዘብዴዎስ
4.ዮሐንስ (ወንድሙ)
5.ፊልዾስ
6.በርተሎሜዎስ
7.ቶማስ
8.ማቴዎስ
9.ያዕቆብ ወልደ እልፍዮስ
10.ታዴዎስ (ልብድዮስ)
11.ናትናኤል (ቀናተኛው ስምዖን) እና
12.ማትያስ (በይሁዳ የተተካ) ናቸው:: (ማቴ. 10:1)

††† እነዚህን 12 አርድእቱን ከጠራ በሁዋላ ለ3 ዓመታት ከ3 ወራት ከዋለበት ሲማሩ ይውሉ ነበር:: ሌሊት ደግሞ ምሥጢር ሲያስተረጉሙ ያድሩ ነበር::

ጌታ እንደሚገባ ካስተማራቸው በሁዋላ ከፍ ያለ ኃላፊነትን ሾማቸው:: ለዓለም እረኞች: የእርሱም ባለሟሎች ሆኑ:: እጅግ ብዙ መከራ እንደሚገጥማቸው ነገራቸው:: (ማቴ. 10:16, ዮሐ. 16:33) በዚያው ልክ ክብራቸውንም አከለላቸው:: (ማቴ. 19:28)

ሥልጣናቸው ደግሞ እስከዚህ ድረስ ሆነ:: "በምድር ያሠራችሁት በሰማይ የታሰረ ይሆናል: በምድር የፈታችሁት በሰማይ የተፈታ ይሆናል::" (ማቴ. 18:18) "ይቅር ያላችሁዋቸው ኃጢአታቸው ይቀርላቸዋል: ያላላቹሃቸው ግን አይቀርላቸውም::" (ዮሐ. 20:23)

የመንግስተ ሰማያትን መክፈቻ (ማቴ. 16:19): እረኝነትን (ዮሐ. 21:15) ተቀበሉ:: ጌታ በንጹሕ አንደበቱ ሐዋርያቱን እጅግ ሲያከብራቸው "ጨው: የዓለም ብርሃናት" (ማቴ. 5:13) አላቸው:: ወንድሞቹም ተባሉ:: (ዮሐ. 7:5) ከዚህም በሚበልጥ በሌላ ክብር አከበራቸው::

ከዚህ ሁሉ ነገር በሁዋላ በጌታ ሕማማት ጊዜ ገና ነበሩና አንዳንዶቹ ፈርተው ተበተኑ:: ተመልሰው ግን በጽርሐ ጽዮን ሲጸልዩ ሰንብተው የጌታን ትንሳኤ ተመለከቱ:: እጆቹን: እግሮቹንም ዳስሰው ሐሴትን አደረጉ::

ለ40 ቀናት መጽሐፈ ኪዳንን: ትምሕርተ ኅቡዓት: ሌላም በፍጡር አንደበት የማይነገር ብዙ ምሥጢራትን ተምረው: ጌታ ሊቀ ዽዽስናን ሹሟቸው ዐረገ::

ለ10 ቀናት በእመ ብርሃን ሥር ተጠልለው ሲጸልዩና በአንድ ልብ ሲተጉ ሰንብተው መንፈስ ቅዱስ ወረደላቸው:: በአንዴም ከፍርሃት ወደ ድፍረት ተመልሰው ፍጹማን: ብርሃናውያን ሆኑ:: 71 ልሳናትን ነስተው በአንዲት ስብከት ብቻ 3ሺ ነፍሳትን ማረኩ:: (ሐዋ. 2:41)

ቅዱሳን ሐዋርያት በኅብረት ለአንድ ዓመት ያህል በኢየሩሳሌምና በዙሪያዋ እየተመላለሱ አስተምረው ብዙ እሥራኤላውያንን ወደ ክርስትና ማርከዋል:: ከዚህ በሁዋላ ግን እንደ ትውፊቱ ዓለምን በእጣ ለ12 ተካፈሏት::

ይህ ሲሆን መንፈስ ቅዱስ አብሯቸው ነበርና ለእያንዳንዳቸው እንደሚገባቸው አሕጉረ ስብከቶች ደረሷቸው:: እነርሱም ደቀ መዛሙርቶቻቸውን አስከትለው ለታላቁ መንፈሳዊ ዘመቻ ወረዱ::

በሔዱበት ቦታም ከተኩላ: ከአንበሳና ከነምር ጋር ታገሉ:: በጸጋቸውም አራዊትን (ክፉ ሰዎችን) ወደ በግነት መልሰው ለክርስቶስ አስረከቡ:: በየሃገሩ እየሰበኩ ድውያንን ፈወሱ:: ለምጻሞችን አነጹ:: እውራንን አበሩ:: አንካሶችን አረቱ:: ጐባጦችን አቀኑ:: ሙታንንም አስነሱ:: እልፍ አእላፍ አሕዛብንም ወደ መንጋው ቀላቀሉ::

ስለዚህ ፈንታም ብዙዎቹ በእሳት ተቃጠሉ:: ቆዳቸው ተገፈፈ:: በምጣድ ተጠበሱ:: ደማቸው በምድር ላይ ፈሰሰ:: ከአንድ ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ በቀር ሁሉም ይህችን ዓለም በሰማዕትነት ተሰናበቱ:: ጨው ሆነው አጣፍጠዋልና: ብርሃንም ሆነው አብርተዋልና እናከብራቸዋለን:: "አባቶቻችን: መምሕሮቻችን: ጌቶቻችንና ሊቆቻችን" እንላቸዋለን::

ቅዱስ ማትያስ ስም አጠራሩ ይክበርና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተሰቦቼ ብሎ ከመረጣቸው 120 ቅዱሳን አንዱ: 3 ዓመት ከ3 ወር ከጌታችን እግር ቁጭ ብሎ የተማረ: በይሁዳ ፈንታ ከ12ቱ ሐዋርያት ይቆጠር ዘንድ መንፈስ ቅዱስ የመረጠው ሐዋርያ ነው::

ቅዱሱ ሐዋርያ በዕጣ በደረሰው ሃገረ ስብከቱና በሌሎቹም ዓለማት ለወንጌል አገልግሎት ብዙ ደክሙዋል:: በተለይ የሰውን ሥጋ ወደሚበሉ ሰዎች ሃገር ገብቶ ወንጌልን ቢሰብክላቸው ዓይኖቹን አውጥተው ከብዙ ስቃይ ጋር ለ30 ቀናት ሣር አብልተውታል::

እሱ ግን በትእግስትና በፈጣሪው ኃይል ድንቅ ተአምር አድርጐ አሳምኖ አጥምቋቸዋል:: ከብዙ ተጋድሎና ቅድስና በሁዋላም በዚሕች ቀን በመልካም ሽምግልና አርፏል::

††† አምላከ ቅዱሳን ሐዋርያት ቸርነቱን ያብዛልን:: በምልጃቸው ከክፉ ጠብቆ ከበረከታቸው ይክፈለን::

††† መጋቢት 8 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ማትያስ ሐዋርያ (ከ12ቱ ሐዋርያት)
2.ቅዱስ አርያኖስ ሰማዕት (በዘመነ ሰማዕታት ብዙ ክርስቲያኖችን ያሳድድ የነበረና ጌታ በንስሃ የጠራው)
3.ቅዱስ ዮልዮስ ሊቀ ዻዻሳት

††† ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ሙሴ ሊቀ ነቢያት
2.ኪሩቤል (አርባዕቱ እንስሳ)
3.አባ ብሶይ (ቢሾይ)
4.አቡነ ኪሮስ
5.አባ ሳሙኤል ዘደብረ ቀልሞን

††† ". . . እንዲህም ብለው ጸለዩ:: 'አቤቱ ልብን ሁሉ የምታውቅ አንተ ከእነዚህ ከሁለቱ የመረጥከውን አንዱን ግለጥ?' . . . ዕጣ አጣጣሉአቸው ዕጣውም በማትያስ ላይ ወጣ:: ከዐሥራ አንዱ ሐዋርያት ጋርም ተቆጠረ::" †††
(ሐዋ. 1:24-26)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
††† እንኳን ለሐዋርያው ቅዱስ ኩትን ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ሐዋርያው ቅዱስ ኩትን †††

††† ቅዱስ ኩትን በዘመነ ሐዋርያት የነበረ: ከአሕዛብ ወደ ክርስትና በቅዱስ ዻውሎስ አማካኝነት የተመለሰ: ከቅዱሳን ሐዋርያት እግር ሥር ቁጭ ብሎ ይማር ዘንድ የታደለ: በፍፁም ድንግልናው የተመሰገነ ሐዋርያዊ አባት ነው::

ይህ ቅዱስ ሚስት ነበረችው:: ግን በትዳር ውስጥ ሆኖ ድንግልናን መጠበቅ እንደሚቻል ያሳየ የሐዲስ ኪዳን ሰው ነው:: ቅዱስ ኩትን በንጽሕናው: በአገልግሎቱና በጣዕመ ስብከቱ በሐዋርያትና ምዕመናንም ተወዳጅ ነበር:: ለብዙ ዘመናት በወንጌል አገልግሎት ኑሮ በዚሕች ቀን በመልካም ሽምግልና አርፏል::

††† ፈጣሪ ከበረከቱ ያድለን::

††† መጋቢት 9 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ኩትን ሐዋርያ
2.ቅዱስ እንድርያኖስ ሰማዕት
3.ቅዱስ አውሳብዮስ ሰማዕት
4."2,000" ሰማዕታት (የአባ ኖብ ማሕበር)

††† ወርሐዊ በዓላት
1.አባ በርሱማ ሶርያዊ (ለሶርያ መነኮሳት ኁሉ አባት)
2.አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ (ኢትዮዽያዊ)
3."318ቱ" ቅዱሳን ሊቃውንት (ርቱዐነ ሃይማኖት ዘኒቅያ)
4.የብሔረ ብፁዐን ጻድቃን
5.አባ መልከ ጼዴቅ ዘሚዳ (ኢትዮዽያዊ)
6.ቅዱስ ዞሲማስ ጻድቅ (ዓለመ ብፁዐንን ያየ አባት)

††† ". . . ስለ ድንግልናው ያፈረ ሰው ቢኖር የወደደውን ያድርግ:: ቢያገባም ኃጢአት የለበትም:: ሳይናወጥ በልቡ የጸና ግን ግድ የለበትም:: የወደደውን እንዲያደርግ ተፈቅዶለታል:: ድንግልናውንም በልቡ ይጠብቅ ዘንድ ቢጸና መልካም አደረገ:: እንዲሁም ድንግልን ያገባ መልካም አደረገ:: ያላገባም የተሻለ አደረገ::" †††
(1ቆሮ. 7:36-38)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
እንኩዋን ለዲማው ኮከብ "አቡነ ተከሥተ ብርሃን" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ

+*" አቡነ ተከሥተ ብርሃን ዘድማኅ "*+

=>ደብረ ድማኅ (የአሁኑ ዲማ ጊዮርጊስ) እጅግ የበረከት ቦታ ነው:: ከጻድቃን እነ አቡነ ተክለ አልፋን : ከሊቃውንት የኔታ መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬን የመሰሉ አበው ፍሬ አፍርተውበታል:: ጻድቁ ተከሥተ ብርሃንም ተጋድሏቸውን የፈጸሙት በዚሁ ቦታ ነው::

+ደብሩ (ዲማ ጊዮርጊስ) ያሳተመው መጽሔት እንደሚለው የጻድቁ ስማቸው አባ በኪሞስ ነው:: "ተከሥተ ብርሃን" የተባሉት በቅድስናቸውና ብርሃን ይወርድላቸው ስለነበር ነው::

+የተወለዱት በምድረ ሽዋ በ13ኛው መቶ ክ/ዘመን ሲሆን የታላቁ ኮከብ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ደቀ መዝሙር ሆነው በደብረ ሊባኖስ አገልግለዋል:: ያመነኮሷቸውም ራሳቸው ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ናቸው::

+ቅዱስ ተክለ ሥላሴ በ1296 ዓ/ም ሲያርፉ እርሳቸውን ቀብረው በዓመቱ (ማለትም በ1297 ዓ/ም) በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ወደ ዲማ በርሃ መጥተዋል:: በዲማ (ጐጃም)ም ተጋድሏቸውን ከማስፋታቸው ባለፈ በስብከተ ወንጌል ተግተዋል::

+ጸበል አፍልቀውም ብዙ ድውያንን ፈውሰዋል:: በተለይ ደግሞ በቦታው እናቶችን ታስቸግር የነበረችውን ቡላድን (ዛር ናት) ከአካባቢው አሰድደዋታል:: ዛሬም ድረስ የጻድቁ ጸበል ለእናቶቻችን (ለሁሉም ሰው) ትልቅ ፈውስ እየሰጠ መሆኑን እንሰማለን::

+ጻድቁ አቡነ ተከሥተ ብርሃን ግን ተጋድሏቸውን ፈጽመው በዚያው በዲማ : መጋቢት 10 ቀን ዐርፈዋል:: ዛሬም በዲማ ጊዮርጊስ በዓላቸው ይከበራል::

=>የጻድቁን ክብርና በረከት አይለይብን:: በጸሎታቸው እኛንም : ቤተ ክርስቲያናችንንም ከክፉ ጠላት ይጠብቅልን::

=>+"+ እግዚአብሔር ፍርድን ይወድዳልና::
ቅዱሳኑንም አይጥላቸውምና::
ለዘለዓለምም ይጠብቃቸዋል. . .
ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ::
በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ::
የጻድቅ አፍ ጥበብን ያስተምራል::
አንደበቱም ፍርድን ይናገራል::
የአምላኩ ሕግ በልቡ ውስጥ ነው::
በእርምጃውም አይሰናከልም:: +"+ (መዝ. 36:28-31)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
2024/09/30 07:29:13
Back to Top
HTML Embed Code: