Telegram Web Link
††† እንኳን ለታላቁ ሊቅና የተዋሕዶ ጠበቃ ቅዱስ ሳዊሮስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ታላቁ ቅዱስ ሳዊሮስ †††

††† ቅዱስ ሳዊሮስ በስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ በሶርያ አንጾኪያ የተነሳ አባት ነው። ወቅቱ መለካውያን (ሁለት ባሕርይ ባዮች) የሰለጠኑበት እንደ መሆኑ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ምእመናን ያነሱበትና የሚሰደዱበት ጊዜ ነበር። በዚህ ጊዜ ነበር ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ሳዊሮስ በሥላሴ ፈቃድ ለቤተ ክርስቲያን የተነሳው። ሊቃውንት አንበሳ ሲሉ ይጠሩታል።

ቅዱሱ ለተዋሕዶ ሃይማኖት ብዙ ሆኖላታል። የመናፍቃን ጸር በመሆኑ ብዙ ድርሰቶችን ደርሷል። ንጉሡን ዮስጢያኖስን (Justinian) ሳይቀር በይፋ ይገስጸው ነበርና ንጉሡ ሊገድለው ቆረጠ።

ሃይማኖቷ የቀና ንግሥቲቱ ታኦድራ ግን ይህንን ስትሰማ በሌሊት ወደ ሊቁ ሒዳ "እባክህን ሽሽ።" አለችው። እርሱ ግን "ሞት ለእኔ ክብር ነውና አልሔድም።" ሲል መለሰላት። አባቶችን ሰብስባ "ስለ ቤተ ክርስቲያን ስትል" ብለው ለምነው ወደ ግብጽ ሸኙት።

እርሱ እየሔደ ገዳዮቹ ያሳድዱት ገቡ። መንገድ ላይ ቢደርሱበትም ተሰወረባቸው። ለብዙ ቀናትም አብሯቸው ተጓዘ። እነርሱ ተስፋ ቆርጠው ሲመለሱ እርሱ ግን ምድረ ግብጽ ደረሰ።

በምድረ ግብጽም የጵጵስና ልብሱን ትቶ የመነኮሳትን አሮጌ ልብስ ለብሶ ሕዝቡንና መነኮሳቱን አስተማረ፤ አጸና። በየቦታውም ብዙ ተአምራትን ሠራ።

አባቶች መነኮሳትም ማንነቱን ባወቁ ጊዜ ሰገዱለት። ዶርታኦስ (ዱራታኦስ) በሚባል አንድ ደግ ሰው ቤትም በስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ አካባቢ የካቲት ፲፬ ቀን ዐርፏል።

††† አምላከ ቅዱሳን ሊቃውንት የድንግል እመቤታችንን ጣዕሟን ፍቅሯን ያሳድርብን። የአበውን ሃብትና በረከትም አይንሳን።

††† የካቲት ፲፬ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ
፪.ቅዱስ ቄርሎስ ሊቀ ጳጳሳት
፫.አባ ያዕቆብ ሊቀ ጳጳሳት
፬.ቅዱስ ዳርዮስ
፭.ቅድስት ሊድና

††† ወርኀዊ በዓላት
፩.አቡነ አረጋዊ (ዘሚካኤል)
፪.ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ መርዓዊ
፫.ቅዱስ ፊልጶስ ሐዋርያ
፬.ቅዱስ ሙሴ (የእግዚአብሔር ሰው)
፭.አባ ስምዖን ገዳማዊ
፮.አባ ዮሐንስ ጻድቅ
፯.እናታችን ቅድስት ነሣሒት

††† "ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኋችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ።" †††
(ይሁዳ ፩፥፫)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
† እንኳን ለታላቁ ነቢይ ቅዱስ ዘካርያስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱስ ዘካርያስ ነቢይ †††

††† ነቢይ ማለት በቁሙ ኃላፍያትን (አልፎ የተሠወረውን ምሥጢር): መጻዕያትን (ገና ለወደ ፊት የሚሆነውን) የሚያውቅ ሰው ማለት ነው:: ሃብተ ትንቢት የእግዚአብሔር የባሕርይ ገንዘቡ ሲሆን እርሱ ለወደደው ደግሞ በጸጋ ይሰጠዋል:: እነዚህም ከጌታ ሃብተ ትንቢት የተሰጣቸው አባቶችና እናቶች "ቅዱሳን ነቢያት" በመባል ይታወቃሉ::

ዘመነ ነቢያት ተብሎ የሚታወቀው ብሉይ ኪዳን ቢሆንም እስከ ምጽዓት ድረስ ጸጋውን እግዚአብሔር ለፈቀደላቸው አይነሳቸውም:: በሐዋርያት መካከልም ቅዱስ አጋቦስን የመሰሉ ነቢያት ነበሩ:: (ሐዋ. 11:27) ቅዱሳን ነቢያት ከእግዚአብሔር እየተላኩ ሰውን ከፈጣሪው እንዲታረቅ ይመክራሉ: ይገስጻሉ::

ከበጐ ሃይማኖታቸውና ንጽሕናቸው የተነሳም እግዚአብሔርን በተለያየ አርአያና አምሳል አይተውታል::
"እስመ በአንጽሖ መንፈስ ርዕይዎ ነቢያት ለእግዚአብሔር : ወተናጸሩ ገጸ በገጽ::" እንዳለ አባ ሕርያቆስ:: (ቅዳሴ ማርያም)

የብዙ ነቢያት ፍጻሜአቸው መከራን መቀበል ነው:: እውነትን ስለ ተናገሩ: አንዳንዶቹም በእሳት: አንዳንዶቹም በሰይፍ: አንዳንዶቹም በመጋዝ ተፈትነዋል:: ሌሎቹ ለአናብስት ሲጣሉ ቀሪዎቹ ደግሞ በድንጋይ ተወግረዋል::

ስለዚህም መከራቸው ለቤተ ክርስቲያን መሠረት ተብለዋል:: ጌታም ለደቀ መዛሙርቱ "ሌሎች ደከሙ:: እናንተ በድካማቸው ገባችሁ::" ብሎ የነቢያቱን መከራ ተናግሯል:: (ዮሐ. 4:36)

ነቢያት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እና ድንግል እናቱን ለማየት ብዙ ጥረዋል:: ሽተዋልም:: "ብዙ ነቢያትና ጻድቃን እናንተ የምታዩትን ሊያዩ ሹ" እንዳለ ጌታ በወንጌል:: (ማቴ. 13:16, 1ጴጥ. 1:10) ዛሬ ግን በሰማያት ጸጋ በዝቶላቸው: ክብር ተሰጥቷቸው ሐሴትን ያደርጋሉ::

ቅዱሳን ነቢያት በዋነኝነት "አሥራ አምስቱ አበው ነቢያት" : "አራቱ ዐበይት ነቢያት" : "አሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት" እና "ካልአን ነቢያት" ተብለው በ4 ይከፈላሉ::

††† "አሥራ አምስቱ አበው ነቢያት" ማለት:-
1.ቅዱስ አዳም አባታችን
2.ሴት
3.ሔኖስ
4.ቃይናን
5.መላልኤል
6.ያሬድ
7.ኄኖክ
8.ማቱሳላ
9.ላሜሕ
10.ኖኅ
11.አብርሃም
12.ይስሐቅ
13.ያዕቆብ
14.ሙሴ እና
15.ሳሙኤል ናቸው::

††† "አራቱ ዐበይት ነቢያት"
1.ቅዱስ ኢሳይያስ ልዑለ ቃል
2.ቅዱስ ኤርምያስ
3.ቅዱስ ሕዝቅኤል እና
4.ቅዱስ ዳንኤል ናቸው::

††† "አሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት"
1.ቅዱስ ሆሴዕ
2.አሞጽ
3.ሚክያስ
4.ዮናስ
5.ናሆም
6.አብድዩ
7.ሶፎንያስ
8.ሐጌ
9.ኢዩኤል
10.ዕንባቆም
11.ዘካርያስ እና
12.ሚልክያስ ናቸው::

††† "ካልአን ነቢያት" ደግሞ:-
*እነ ኢያሱ
*ሶምሶን
*ዮፍታሔ
*ጌዴዎን
*ዳዊት
*ሰሎሞን
*ኤልያስ እና
*ኤልሳዕ . . . ሌሎችም ናቸው::

††† ነቢያት በከተማም ይከፈላሉ::
*የይሁዳ (ኢየሩሳሌም):
*የሰማርያ (እሥራኤል) እና
*የባቢሎን (በምርኮ ጊዜ) ተብለው ይጠራሉ::

††† በዘመን አከፋፈል ደግሞ:-
*ከአዳም እስከ ዮሴፍ (የዘመነ አበው ነቢያት):
*ከሊቀ ነቢያት ሙሴ እስከ ነቢዩ ሳሙኤል (የዘመነ መሳፍንት ነቢያት)
*ከቅዱስ ዳዊት እስከ ዘሩባቤል ያሉት (የዘመነ ነገሥት ነቢያት):
*ከዘሩባቤል ዕረፍት እስከ መጥምቁ ዮሐንስ ያሉት ደግሞ (የዘመነ ካህናት ነቢያት) ይባላሉ::

††† ስለ ቅዱሳን ነቢያት በጥቂቱ ይህንን ካልን ወደ ዕለቱ በዓል እንመለስ::

††† ቅዱስ ዘካርያስ ቁጥሩ ከአሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት ሲሆን ዘመነ ትንቢቱም ቅ/ል/ክርስቶስ በ450 ዓ/ዓ አካባቢ ነው:: "ደቂቀ ነቢያት" ማለት በጥሬው "የነቢያት ልጆች" ማለት ነው:: አንድም የጻፏቸው ትንቢቶች ሲበዙ 14 ምዕራፍ: ሲያንስ አንድ ምዕራፍ ያላቸው ናቸውና ደቂቅ ይላቸዋል::

††† ነቢዩ ቅዱስ ዘካርያስ:-
*ከክርስቶስ ልደት 450 ዓመታት በፊት የነበረ::
*በጻድቅነቱ የተመሰከረለት::
*14 ምዕራፎች ያሉት ሐረገ - ትንቢት የተናገረ::
*ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ሥራ በስፋት የተነበየ ነቢይ ሲሆን ከአሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያትም አንዱ ነው::

††† የአባታችን በረከት ይደርብን::

††† የካቲት 15 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ዘካርያስ ነቢይ (ከአሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት አንዱ)
2.ቅዱስ አባ በፍኑትዮስ ገዳማዊ (ከጻድቅነቱ ባሻገር በግብጽ በርሃ የሚኖሩ የብዙ ቅዱሳንን ዜና ሕይወት የጻፈ አባት ነው::)
3.ቅዱሳን አርብዐ ሐራ ሰማይ (40 የሰማይ ጭፍሮች) ለ40 ቀናት ሰብስጥያ በምትባል ሃገር መከራ ተቀብለው በሰማዕትነት ያለፉ ክርስቲያን ጓደኛሞች::

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ቂርቆስና እናቱ ኢየሉጣ
2.ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ (አፈ በረከት)
3.ቅዱስ ሚናስ ግብጻዊ
4.ቅድስት እንባ መሪና
5.ቅድስት ክርስጢና

††† ". . . የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል:: 'ወደ እኔ ተመለሱ . . . እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ::' " †††
(ዘካርያስ ፩፥፫)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
የካቲት 16

እንኩዋን ለእናታችን ቅድስት ኤልሳቤጥ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ

+" ቅድስት ኤልሳቤጥ "+

=>በወንጌላዊው አንደበት የተመሰገነች እናታችን ቅድስት ኤልሳቤጥ ትውልዷ ከነገደ ሌዊ ነው:: ሐረገ ሙላዷም ከቅዱስ አሮን ካህን ወገን ይመዘዛል:: ከአሮን በቴክታና በጥሪቃ ወርዶ ሔርሜላ ላይ ይደርሳል::

+ይህቺ ሔርሜላ የምትባል ደግ ሴት ማጣት ("ጣ" ጠብቆ ይነበብ) የሚባል የተባረከ ሰው አግብታ 3 ቡሩካት ልጆችን ወለደች:: የመጀመሪያዋን 'ማርያም' አሏት:: እርሷ ቅድስት ሰሎሜን ወለደች:: ሁለተኛዋን 'ሶፍያ' አሏት:: እርሷ ደግሞ ቅድስት ኤልሳቤጥን ወለደች::

+ሦስተኛዋ ግን የተለየች ናት:: 'ሐና' ብለው ሰየሟት:: እርሷም የሰማይና የምድር ንግሥት የሆነችውን ድንግል ማርያምን ወለደች:: በዚህም መሠረት ድንግል ማርያም: ቅድስት ኤልሳቤጥና ቅድስት ሰሎሜ የእህትማማች ልጆች ናቸው::

+ቅድስት ኤልሳቤጥ እድሜዋ በደረሰ ጊዜ ስም አጠራሩ የከበረ: ደግ ካህን ለሆነ: ለቅዱስ ዘካርያስ አጋቧት:: እርሷ የሊቀ ካህናቱ ሚስት ናትና ክብሯ ከፍ ያለ ነበር:: ምንም ልጅ ባይኖራትም ዘወትር በጸሎትና በጾም: ምጽዋትንም በማዘውተር: ነዳያንንም በማሰብ የምትኖር እናትም ነበረች::

+ቅዱስ ወንጌል ላይ ከእመቤታችን ቀጥሎ የነዘካርያስን ቤተሰብ ያህል ክብሩ የተገለጠለት ፍጡር ይኖራል ብሎ መናገሩ ይከብዳል:: ቅዱስ ሉቃስ ወንጌሉን የጀመረው በዚህ ቅዱስ ቤተሰብ ነውና መንፈስ ቅዱስ እንዲህ ሲል አጽፎታል::
"ዘካርያስ ካህኑና ቅድስት ኤልሳቤጥ በሰውና በእግዚአብሔር ፊት ያለ ነቀፋ የሚኖሩ ጻድቃን ነበሩ" ይላቸዋል:: (ሉቃ. 1:6)

+የሰውን እንተወውና በእግዚአብሔር ፊት ያለ ነቀፋ መኖር ምን ይረቅ? ለዚህ አንክሮ (አድናቆት) ይገባል! እሊህ ቅዱሳን ባልና ሚስት ግን መካኖች በመሆናቸው ልጅ ሳይወልዱ ዘመናቸው አልፎ ነበር:: እንደ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት ዕድሜአቸው የኤልሳቤጥ 90 የዘካርያስ 100 ደግሞ ደርሶ ነበር::

+ፍጹም መታገሳቸውን የተመለከተ ጌታ ግን በስተ እርጅናቸው ከሰው ሁሉ በላይ የሆነ ታላቅ ነቢይን ይሰጣቸው ዘንድ መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤልን ላከላቸው:: ቅድስቲቷ መስከረም 26 ቀን ታላቁን ሰው ጸንሳ ለ6 ወራት ራሷን ሠወረች::

+ድንግል እመቤታችን ወደ እርሷ መጥታ 'ሰላም' ባለቻት ጊዜ ምንም ያሳደገቻት ልጇ ማለት ብትሆን: መንፈስ ቅዱስ ስለ ሞላባት እመ ብርሃንን አመስግናታለች:: ቡርክት: ብጽእት: ከፍጥረተ ዓለሙ የከበረች መሆኗንም መስክራለች::

+በማሕጸኗ ያለ የ6 ወር ጽንስም የእመ አምላክን ድምጽ ቢሰማ በደስታ ዘሏል:: ለፈጣሪውም ስግደተ-ስባሔ አቅርቧል:: ቅድስት ኤልሳቤጥ አክላም "ወምንትኑ አነ ከመ ትምጽኢ ኀቤየ እሙ ለእግዚእየ-የጌታየ እናቱ ወደ እኔ ትመጪ ዘንድ እንዴት ይገባኛል?" ስትል በትኅትና ተናግራለች:: ከጌታ እናት ጋር ለ3 ወራት በአንድ ቤት ቆይታለች::

+ቅዱስ ዮሐንስ ከተወለደ 2 ዓመት ከ6 ወር በሆነው ጊዜ ሰብአ ሰገል በመምጣታቸው በእሥራኤል ምድር የሚገኙ ሕጻናትን ሔሮድስ ቁዝ አስፈጀ:: ትንሽ ቆይቶም አይሁድ ለሔሮድስ ስለ ቅዱሱ ሕጻን ነገሩት:: "ሲጸነስ የአባቱን አንደበት የዘጋ: ሲወለድ ደግሞ የከፈተ 'ዮሐንስ' የሚባል ሕጻን አለና እሱንም ግደል" አሉ::

+እናቱ ቅድስት ኤልሳቤጥ ይዛው ስትሸሽ ካህኑን ዘካርያስን ግን በቤተ መቅደስ መካከል ገድለውታል:: አረጋይት ኤልሳቤጥም ሕጻኑን እያሳደገች በገዳመ ዚፋታ ለ3 (5) ዓመታት ቆይታለች:: ቅዱስ ዮሐንስ 5 (7) ዓመት ሲሞላው ግን እዚያው በበርሃ እናቱ ዐረፈች:: ከሰማይ ዘካርያስና ስምዖን ወርደው ቀበሯት:: ኤልሳቤጥ ማለት 'እግዚአብሔር መሐላየ ነው': አንድም 'የጌታ አገልጋይ' ማለት ነው::

+ሊቃውንትም:-
+"+ ሰላም ለኤልሳቤጥ እንተ ወደሳ ወአልዓላ:
ሉቃስ ወንጌለ ሶበ ጸሐፈ ለታኦፊላ:
ሐገረ ይሁዳ አሜሃ ሶበ በጽሐት እምገሊላ:
ተሐስየ በውስተ ከርሣ ወአንፈርዓጸ ዕጉዋላ:
ለማርያም ድንግል ሶበ ሰምዓት ቃላ:: +"+ ሲሉ አወድሰዋታል::

=>ከቅድስት እናታችን ክብሯንና በረከቷን ይክፈለን::

   ወስብሐት ለእግዚአብሔር

⛪️ዝክረ ቅዱሳን ጉባኤ
'
" ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"::/የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ) እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::  አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ /መጽሐፈ ምሥጢር/
https://www.tg-me.com/zikirekdusn
ቅዱስ ሐርቤ (ገብረ ማርያም)

ከ4ቱ ቅዱሳን የዛግዌ ነገሥታት አንዱ የሆነው ቅዱስ ሐርቤ /ገብረማርያም/ያረፈው በዚሁ ዕለት (የካቲት 16) ነው::
ለሃገራችን ኩራት : ለቤተ ክርስቲያናችን ደግሞ ሞገስ የሆነ ቅዱስና መናኝ ንጉሥ ነው::

<< አምላክ ከበረከቱ ይክፈለን:: >>

ዝክረቅዱሳን ማኅበረ ቅዱስ ዳዊት'
" ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"::/የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ) እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል:: አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ /መጽሐፈ ምሥጢር/
https://www.tg-me.com/zikirekdusn
† እንኩዋን ለሊቀ ነቢያት ቅዱስ ሙሴ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ †

+"* ቅዱስ ሙሴ ሊቀ ነቢያት *"+

=>ቅዱሳን ነቢያት እጅግ ብዙ ናቸው:: ከፈጣሪያቸው የተቀበሉት ጸጋም ብዙና ልዩ ልዩ ነው:: ያም ሆኖ ከሁሉም ነቢያት ቅዱስ ሙሴ ይበልጣል:: መጽሐፍ እንደሚል ከእርሱም በፊት ቢሆን ከእርሱ በሁዋላ እንደ እርሱ ያለ ነቢይ አልተነሳምና:: ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-

*ዓለም በተፈጠረ በ3,600 ዓመት እሥራኤል በረሃብ ምክንያት 75 ራሱን ወደ ምድረ ግብፅ ወረደ:: በዚያም ልጆቹና የልጅ ልጆቹ ለ215 ዓመታት ተከብረው: ለ215 ዓመታት ደግሞ በባርነት: በድምሩ ለ430 ዓመታት በምድረ ግብፅ ኑረዋል::

*በባርነት ዘመናቸውም 'ራምሴና ጋምሴ' የሚባሉ 2 ከተሞችን (ዛሬ ፒራሚዶች የምንላቸውን) ገንብተዋል:: ግፋቸው እየበዛ ሲሔድ ግን ጩኸታቸው ቅድመ እግዚአብሔር ደረሰ:: ያድናቸውም ዘንድ አንድ ቅዱስ ሰው እንዲወለድ አደረገ:: ይኽም ሰው ሙሴ ይባላል::

*ወላጆቹ መታመናቸውን በፈጣሪያቸው ያደረጉ 'እንበረም'ና 'ዮካብድ' ሲሆኑ ከሌዊ ነገድ ናቸው:: ከሙሴ ውጪም አሮንና ማርያምን ወልደዋል:: ቅዱስ ሙሴ በተወለደበት ወራት ወንድ የእሥራኤል ሕጻናት ይፈጁ ነበር:: ጌታ ግን በገዳዮቹ ልቡና ርሕራሔን አምጥቶ አትርፎታል::

*በሁዋላም በ3 ወሩ ዓባይ ወንዝ ላይ ጥለውት ተርሙት (የፈርኦን ልጅ ናት) ወስዳ በቤተ መንግስት አሳድጋዋለች:: 'ሙሴ' ያለችውም እርሷ ናት:: 'ዕጉዋለ ማይ / እማይ ዘረከብክዎ' (ከውሃ የተገኘ) ለማለት ነው:: ወላጆቹ ያወጡለት ስም ግን 'ምልክአም' ይባላል:: ገና ሲወለድ ፊቱ እንደ መልአክ ያበራ ነበርና::

*ቅዱስ ሙሴ 5 ዓመት በሆነው ጊዜ ፈርኦንን በጥፊ በመማታቱ ለፍርድ ቀርቦ እሳትን በመብላቱ አንደበቱ ኮልታፋ ሆኖ ቀርቷል:: እናቱ ዮካብድ ሞግዚት ሆና ስላሳደገችው 40 ዓመት በሆነው ጊዜ የፈርኦንን ቤት ምቾትና የንጉሥ ልጅ መባልን ናቀ:: ቅዱስ ዻውሎስ እንደሚለው በአሕዛብ ቤት ካለ ምቾት ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራን ሊቀበል ወዷልና:: (ዕብ. 11:24)

*አንድ ቀንም ለዕብራዊ ወገኑ ተበቅሎ ግብጻዊውን ገድሎት ወደ ምድያም ሸሸ:: በዚያም ለ40 ዓመታት የካህኑን ዮቶርን በጐች እየጠበቀ: ኢትዮዽያዊቱን ሲፓራን አግብቶ ኖረ:: ልጆንም አፈራ:: 80 ዓመት በሞላው ጊዜ እግዚአብሔር በደብረ ሲና ተናገረው:: ሕዝቡንም ከባርነት ቀንበር እንዲታደግ ላከው::

*ቅዱስ ሙሴም ከወንድሙ አሮንና ከአውሴ (ኢያሱ) ጋር ግብጻውያንን በ9 መቅሰፍት: በ10ኛ ሞተ በኩር መታ:: እሥራኤልንም ነጻ አወጣ:: ሊቀ ነቢያት የሠራቸው ሥራዎች ተዘርዝረው የሚያልቁ አይደሉም::

>እርሱ ባሕረ ኤርትራን ከፍሎ ሕዝቡን በደረቅ አሻግሯል::
>ግብጻውያንን ከነሠረገሎቻቸው በባሕር ውስጥ አስጥሟል::
>ለሕዝቡ መና ከደመና አውርዷል::
>ውሃን ከጨንጫ (ከዓለት) ላይ አፍልቁዋል::
>በብርሃን ምሰሶ መርቷቸዋል::
>በ7 ደመና ጋርዷቸዋል::
>ጠላቶቻቸውን ሁሉ ድል ነስቶላቸዋል::

*ስለዚህ ፈንታ ግን ወገኖቹ ብዙ አሰቃይተውታል:: እርሱ ግን ደግ: ቅንና የዋህ ሰው ነውና ብዙ ጊዜ ራሱን ለእነሱ አሳልፎ ሰጥቷል:: "ሙሴሰ የዋህ እምኩሎሙ ደቂቀ እሥራኤል" እንዲል:: (ዘኁ. 12:3) ቅዱስ ሙሴ ለ40 ዓመታት ሕዝቡን ሲመራ ከእግዚአብሔር ጋር ለ570 ጊዜ ተነጋግሯል::

*ከጸጋው ብዛትም ፊቱ ብርሃን ስለ ነበር ሰዎች እርሱን ማየት አይችሉም ነበር:: ታቦተ ጽዮንንና 10ሩ ቃላትን ተቀብሎ ጽላቱ ቢሰበሩ ራሱ ሠርቶ በጌታ እጅ ቃላቱ ተጽፈውለታል:: "የቀረው የቅዱሱ ሕይወት በመጻሕፍተ ኦሪት (በብሔረ ኦሪት) ውስጥ የተጻፉ አይደሉምን?"

*እኔ ግን ደካማ ነኝና ይህቺ ትብቃኝ:: ቅዱስ: ክቡር: ታላቅ: ጻድቅ: ነቢይና ደግ ሰው ቅዱስ ሙሴ በ120 ዓመቱ ዐርፎ በደብረ ናባው ሊቃነ መላእክት ቅዱሳን ሚካኤል: ገብርኤልና ሳቁኤል ቀብረውታል:: መቃብሩንም ሠውረዋል:: (ይሁዳ. 1:9)

=>አምላከ ሊቀ ነቢያት ደግነቱን አስቦ ከግራ ቁመት: ከገሃነመ እሳት ይሰውረን:: በረከቱንም አብዝቶ ያድለን::

=>የካቲት 17 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ሙሴ ሊቀ ነቢያት (በ120 ዓመቱ ደብረ ናባው ላይ ተቀብሯል)
2.ቅዱስ ሚናስ ግብፃዊ (ኁለተኛው)

=>ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ እስጢፋኖስ ሊቀ ዲያቆናት (ቀዳሜ ሰማዕት)
2.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ወልደ ዘብዴዎስ)
3.ቅዱስ ኤዺፋንዮስ ዘቆዽሮስ
4.ቅዱሳን አበው መክሲሞስና ዱማቴዎስ
5.አባ ገሪማ ዘመደራ
6.አባ ዸላሞን ፈላሢ
7.አባ ለትጹን የዋህ

††† ሙሴ ካደገ በሁዋላ የፈርኦን የልጅ ልጅ እንዳይባል በእምነት እምቢ አለ:: ከግብጽም ብዙ ገንዘብ ይልቅ ስለ ክርስቶስ መነቀፍ እጅግ የሚበልጥ ባለጠግነት እንዲሆን አስቧልና:: ለጊዜው በኃጢአት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራ መቀበልን መረጠ:: ብድራቱን ትኩር ብሎ ተመልክቷልና:: ††† (ዕብ. 11:24)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
እንኳን ለነነዌ ጾም አደረሳችሁ።
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ :: አሜን ::

+*" ጾመ ነነዌ ወቅዱስ ዮናስ ነቢይ "*+

=>ዮናስ ማለት 'ርግብ: የዋህ' ማለት ሲሆን ከ12ቱ ደቂቀ ነቢያት አንዱ ነው:: በሰራፕታ ተወልዶ ያደገው ነቢዩ በልጅነቱ ታሞ ሙቶ ነበር:: ታላቁ ነቢይ ኤልያስ ግን 7 ጊዜ ጸሎት አድርጐ ከሞት አስነስቶታል:: (1ነገ. 17:17) እናቱ የሰራፕታዋ መበለትም ደግ ሴት ነበረች::

+ቅዱስ ዮናስ በእድሜው ከፍ ሲል የቅዱስ ኤልያስ ደቀ መዝሙር ሆነ:: የነ ኤልሳዕና አብድዩም ባልንጀራ ነበረ:: ነቢየ እግዚአብሔር ኤልያስ ካረገ በሁዋላ: ቅ/ል/ክርስቶስ በ800 ዓመት አካባቢ የነነዌ ሰዎች ኃጢአት ከመሥፈርቱ በማለፉ የእግዚአብሔር ቃል ወደ አማቴ ልጅ ወደ ዮናስ መጣ::

+"ሒድና ለነነዌ ሰዎች ንስሃን ስበክላቸው" አለው:: ከነቢያት ወገን ከሙሴና ከዳዊት ቀጥሎ የዮናስን ያህል የዋህ (ገራገር) የለምና እንቢ አለ (ሰምቶ ዝም አለ):: እግዚአብሔር እየደጋገመ ሲናገረው ግን "እንዲህ የሚዘበዝበኝ ከፊቱ ብቀመጥ አይደል!" ብሎ ወደ ተርሴስ ኮበለለ::

+ወገኖቼ አንድ ነገርን ልብ እንበል:: እንኩዋን ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዮናስ እኛ ክፉዎችም ከጌታ ፊት መሸሸት እንደማይቻል ጠንቅቀን እናውቃለን:: ታዲያ ለምን ሸሸ ቢሉ:- ጥበበ እግዚአብሔር በውስጡ ስለ ነበረበት ነው::

+ምክንያቱም ዮናስ በአሣ አንበሪ ሆድ 3 ቀን ሌሊት ኖሮ: ሙስና (ጥፋት) ሳያገኘው መውጣቱ ለጌታ ትንሳኤ ጥላ (ምሳሌ) ነው:: ለዚህም ምስክሩ ራሱ ጌታችን ነው::

"ወበከመ ነበረ ዮናስ ውስተ ከርሠ አንበሪ ሠሉሰ ዕለተ ወሠሉሰ ለያልየ: ከማሁ ይነብር ወልደ እጉዋለ እመ ሕያው ውስተ ልበ ምድር ሠሉሰ ዕለተ: ወሠሉሰ ለያልየ" እንዲል:: (ማቴ. 12:39)

+ቅዱስ ዮናስ በገንዘቡ ዋጅቶ ወደ መርከብ በገባ ጊዜ ታላቅ ማዕበል ሆነ:: የእምነት ሰው ነውና እንዲያ እየተናወጡ እርሱ በእርጋታ ተኝቷል:: እነርሱ ግን ቀስቅሰው ቢጠይቁት (እጣ ወድቆበታልና) "የእኔ ጥፋት ስለ ሆነ ወደ ማዕበሉ ጣሉኝ" አላቸው::

+እያዘኑ ቢጥሉት ታላቅ ጸጥታ ሆነ:: እነዚያ አሕዛብም እግዚአብሔርን በመስዋዕትና በስዕለት አከበሩ:: ዮናስ ግን በማዕበልና በአሣ አንበሪ ሆድ ውስጥ ለ3 ቀናት ጸለየ:: አሣ አንበሪው በ3ኛው ቀን ወደ ነነዌ ተፋው::

+ቅዱሱም "እስከ ሠሉስ ዕለት ትትገፈታእ #ነነዌ ዐባይ ሃገር" እያለ ንስሃን ሰበከ:: የነነዌ ሰዎች ኃጢአታቸውን አምነው ቢጸጸቱ ከሰማይ ወርዶ ከደመና ደርሶ የነበረው የእሳት ማዕበል ተመልሶላቸዋል::

+የነቢዩ ትንቢት ግን አልቀረምና ታላቁዋ ነነዌ ከ300 ዓመታት በሁዋላ ጠፍታለች:: ቅዱስ ዮናስ ግን በቀሪ ዘመኑ ፈጣሪውን እያገለገለ ኑሯል:: ጠቅላላ እድሜውም 170 ዓመት ነው::

+ዛሬ ያለን ሁላችን ሃገራችን ነነዌን ሕዝቦቿም ሕዝቦቻቸውን ከመሰልን ሰንብተናል:: በእርግጥ እንደ ነነዌ እሳት አይዘንብብን ይሆናል:: ግን የዘለዓለም እሳት ይጠብቀናል:: ንስሃ ካልገባን የሚመጣብን ቅጣት የሚከፋ ይሆናል::

=>አምላከ ቅዱስ ዮናስ እድሜ ለንስሃ: ዘመን ለፍስሃ አይንሳን:: ጾሙንም የበረከት ያድርግልን::

=>+"+ ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይሻል:: ከነቢዩም ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም:: ዮናስ በአሣ አንበሪ ሆድ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደ ነበረ: እንዲሁ የሰው ልጅ በምድር ልብ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይኖራል:: የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነስተው ይፈርዱበታል:: በዮናስ ስብከት ንስሃ ገብተዋልና:: እነሆም ከዮናስ የሚበልጥ ከዚህ አለ:: +"+ (ማቴ. 12:39)

   <<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞

❖የካቲት ፲፰ (18) ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

+*" ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ "*+

=>ቅዱስ ያዕቆብ ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ያደገ:
የአረጋዊው ቅ/ዮሴፍ የመጨረሻ ልጅ : በንጽሕናውና
ድንግልናው የተመሠከረለት : ከጸሎትና ገድል ብዛት እግሩ
ያበጠ : የመጀመሪያው የኢየሩሳሌም ኤዺስ ቆዾስ ሲሆን
ቁጥሩም ከ72ቱ አርድዕት ነው:: ይሕስ እንደ ምን ነው
ቢሉ:-

=>ይህ ቅዱስ ሐዋርያ በአባቶቻችን ሐዋርያት መካከል
ትልቅ ሞገስ የነበረውና የጌታችን ወንድም ተብሎ የተጠራ
ነው:: ቅዱስ ያዕቆብ ወላጅ አባቱ አረጋዊው ቅዱስ ዮሴፍ
(የእመቤታችን ጠባቂ) ሲሆን በልጅነቱ ጥላው የሞተችው
እናቱ ደግሞ ማርያም ትባላለች:: በቤት ውስጥም
ስምዖን: ዮሳና ይሁዳ የተባሉ ወንድሞችና ሰሎሜ
የምትባል እህትም ነበረችው::

+እናቱ ማርያም ከሞተች በሁዋላ ዕጉዋለ ማውታ (ደሃ
አደግ) ሆኖ ነበር:: ነገር ግን በፈቃደ እግዚአብሔር አረጋዊ
ዮሴፍ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ከቤተ
መቅደስ ሊጠብቃት (ሊያገለግላት) ተቀብሎ ሲመጣ ያ
ቤተሰብ ተቀየረ:: የበረከት: የምሕረትና የሰላም እመቤት
የአምላክ እናቱ ገብታለችና ያ የሐዘን ቤት ደስታ ሞላው::

+እመ ብርሃን ግን ገና ወደ ዮሴፍ ልጆች ስትደርስ
አለቀሰች:: የአክስቷ ልጆች የሚንከባከባቸው አጥተው
ቆሽሸው ነበር:: በተለይ ደግሞ ትንሹ ቅዱስ ያዕቆብ
ያሳዝን ነበር:: እመ ብርሃን ማረፍ አልፈለገችም::
ወዲያው ማድጋ አንስታ ወደ ምንጭ ወርዳ ውሃ አምጥታ
የሕጻኑን ገላ አጠበችው:: (በአምላክ እናት የታጠበ
ሰውነት ምስጋና በጸጋ ይገባዋል!)

+እመቤታችን ጌታ ከመወለዱ በፊት ለ9 ወራት: ከተወለደ
በሁዋላ ደግሞ ለ2 ዓመታት ሕጻኑን ያዕቆብን
ተንከባከበችው::

ለ3 ዓመታት ከ6 ወራት ግን ድንግል ማርያም አምላክ
ልጇን ይዛ ተሰዳለችና ተለያዩ:: ከስደት መልስ ግን ለ25
ዓመታት ቅዱስ ያዕቆብ ከጌታችን ጋር ሲያድግ ወላጅ እናቱ
ትዝ ብላው አታውቅም:: አማናዊቷ እናት ከጐኑ ነበረችና::

+ሊቃውንት እንደ ነገሩን እመቤታችን ለቅዱስ ያዕቆብ
ያልሰጠችው ነገር ቢኖር ሐሊበ ድንግልናዌ (የድንግልና
ወተትን) ብቻ ነው::

ስለዚህም:-
"እመ ያዕቆብ በጸጋ ማርያም ንግሥተ ኩሉ" ይላል
መጽሐፍ:: (መልክዐ ስዕል)

+ቅዱስ ያዕቆብ "የጌታ ወንድም" ተብሎ በተደጋጋሚ
በሐዲስ ኪዳን ተጠርቷል:: ለዚህ ምክንያቱ:-
1.ለ30 ዓመታት ሳይነጣጠሉ አብረው በማደጋቸው፡፡
2.የጌታችን የሥጋ አያቱ (የቅድስት ሐና) የእህት ልጅ
በመሆኑ፡፡
3.በዮሴፍ በኩልም የአንድ ቅድመ አያት ልጆች
በመሆናቸው፡፡
4.ጌታችን ከትህትናው የተነሳ ደቀ መዛሙርቱን
"ወንድሞች" ይላቸው ስለ ነበር ነው:: (ሥጋቸውን ተዋሕዶ
ተገኝቷልና)

+ራሱ ቅዱስ ያዕቆብ ግን "የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ
ባሪያ ነኝ" ብሎ በፈጣሪና በፍጡር መካከል ያለውን ልዩነት
ገልጧል:: (ያዕ. 1:1) ቅዱስ ያዕቆብ ጌታችን ሲያስተምር
ተከተለው::

¤ከ72ቱ አርድእት ተቆጠረ
¤3 ዓመት ከ3 ወር ወንጌልን ተማረ
¤ለመጀመሪያ ጊዜ ከድንግል ማርያምና ከቅዱስ ዮሐንስ
ጋር ሆኖ "የጌታን ትንሳኤ ሳላይ እሕል አልቀምስም" ብሎ
ማክፈልን አስተማረ
¤መንፈስ ቅዱስን ተሞልቶ ወንጌልን አስተማረ
¤የኢየሩሳሌም የመጀመሪያው ሊቀ ዻዻስ ሆኖ አገለገለ
¤በመጀመሪያዎቹ የክርስትና ዘመናት የሐዋርያት
ሲኖዶሶችን በሊቀ መንበርነት መራ
¤ሙታንን አስንስቶ: ድውያንን ፈውሶ: የመካኖችን ማሕጸን
ከፍቶ: አጋንንትንም አስወጥቶ ብዙ ተእምራትን ሠራ::
እጅግ ብዙ አይሁዳውያንን ወደ አሚነ ክርስቶስ መልሶ
መልካሙን ገድል ተጋደለ::

+በመጨረሻ ዘመኑ ያላመኑ የአይሁድ አለቆች ወደ ቤቱ
ተሰብስበው "የናዝሬቱ ኢየሱስ ማነው? የማንስ ልጅ
ነው?" ሲሉ ጠየቁት:: እነርሱ ሰይጣን በሰለጠነበት
ልቡናቸው "የዮሴፍ ልጅ ነው: የእኔም ወንድሜ ነው"
እንዲላቸው ጠብቀው ነበር:: (ሎቱ ስብሐት ወአኮቴት!)

+በልቡናቸው ያሰቡትን ተንኮል የተረዳው ሐዋርያ ወደ ቤቱ
ጣራ ወጥቶ መናገር ጀመረ:: "ለስም አጠራሩ ጌትነት
ይሁንና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ ወልደ አምላክ:
ወልደ አብ ወልደ ማርያም: ሥግው ቃል: እግዚአብሔር
ነው:: እኔም ፍጡሩና ባሪያው እንጂ እንደምታስቡት
ወንድሙ አይደለሁም" አላቸው::

+ንዴታቸውን መቆጣጠር ያልቻሉት አይሁድ ከላይ
ወጥተው ወደ መሬት ወረወሩት:: በገድል የተቀጠቀጠ
አካሉንም እየተፈራረቁ ደበደቡት:: አንዱ ግን ከእንጨት
የተሠራ ትልቅ ገንዳ አምጥቶ የቅዱሱን ራስ ደጋግሞ
መታው:: ጭንቅላቱም እንዳልነበር ሆነ:: ሰማዕቱ ሐዋርያ
ቅዱስ ያዕቆብ ወደ ወደደው ክርስቶስ በዚህች ቀን ሔደ::

+ቅዱሱ ሐዋርያ ያዕቆብ ቤቱን እንደ ቤተ መቅደስ አበው
ሐዋርያት ይጠቀሙባት ነበር:: በመላ ዘመኑ የሚያገድፍ
ነገር (ጥሉላት) ቀምሶ: ጸጉሩን ተላጭቶ: ገላውን ታጥቦና
ልብሱን ቀይሮ አያውቅም::

"ወዝንቱ ጻድቅ እኅወ እግዚእነ::
ኢያብአ ውስተ አፉሁ ሥጋ ወወይነ::
ወኢገብረ ሎቱ ክልኤተ ክዳነ::" እንዲል::

+ከጾም: ከጸሎትና ከመቆሙ ብዛትም እግሩ አብጦ
አላራምድህ ብሎት ነበር:: ስለዚህም አበው "ጻድቁ
(ገዳማዊው) ሐዋርያ" ይሉታል:: ቅዱሱ ሐዋርያ
"የያዕቆብ መልዕክት" የሚለውን ባለ 5 ምዕራፍ
መልዕክት ጽፏል::

=>ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወንድሙ ይባል ዘንድ
ካደለው ሐዋርያ በረከትን ያድለን:: በምልጃውም
ምሕረትን ይላክልን::

=>የካቲት 18 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (የቅዱስ ዮሴፍ ልጅ : ከ72ቱ
አርድእት አንዱ)
2.ቅዱስ አባ መላልዮስ ጻድቅ ሊቀ ዻዻሳት (በአንጾኪያ
ሊቀ ዽዽስና ተሹሞ በአርዮሳውያን ብዙ ግፍ የደረሰበትና
በስደት ያረፈ አባት ነው)

=>ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ፊልዾስ ሐዋርያ
2.አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ሰባኬ ሃይማኖት
3.አቡነ አኖሬዎስ ዘደብረ ጽጋጋ
4.ማር ያዕቆብ ግብፃዊ

=>+"+ የእግዚአብሔርና የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ
ያዕቆብ: ለተበተኑ ለአሥራ ሁለቱ ወገኖች:: ሰላም ለእናንተ
ይሁን:: ወንድሞቼ ሆይ! የእምነታችሁ መፈተን ትዕግስትን
እንዲያደርግላችሁ አውቃችሁ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ
እንደ ሙሉ ደስታ ቁጠሩት:: ትዕግስትም ምንም
የሚጐድላችሁ ሳይኖር ፍጹማንና ምሉዓን ትሆኑ ዘንድ
ሥራውን ይፈጽም:: +"+ (ያዕ. 1:1)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
2024/09/25 05:19:27
Back to Top
HTML Embed Code: