Telegram Web Link
✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞

❖ የካቲት 13 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

+*" ማር ፊቅጦር "*+

=>ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በደማቸውና በገድላቸው ያስጌጡ ብዙ ሰማዕታት አሉ:: ነገር ግን ከኮከብም ኮከብ ይበልጣልና ማን እንደ ጊዮርጊስና እስጢፋኖስ! ከእነርሱ ቀጥለው ከሚጠሩ ሰማዕታት ደግሞ አንዱና ዋነኛው ቤተ ክርስቲያን "ማር" የምትለው ቅዱስ ፊቅጦር ነው::

=>እስኪ ከበዛው መዓዛ-ገድሉ ጥቂት እንካፈል:-
+ቅዱስ ፊቅጦር አባቱ ኅርማኖስ ይባላል:: አረማዊና
ጨካኝ ነው:: እናቱ ግን የተመሰገች ቅድስት ማርታ
ትባላለች:: ልጇን እንደሚገባ አሳድጋው 20 ዓመት
ሲሞላው የአንጾኪያ ንጉሥ የሠራዊት አለቃና በመንግሥቱ
3ኛ አድርጐ ሾመው::

+የድሮዋ አንጾኪያ (ሮም) እንደ ዛሬዋ አሜሪካ ዓለምን
የተቆጣጠረች ሃገር ነበረች:: ቅዱስ ፊቅጦር ደም ግባቱ
ያማረ: በጦርነትም ኃይለኛ ስለ ነበር ሁሉ ያከብሩት:
ይወዱትም ነበር::

+እርሱ ግን ቀን ቀን ሲጾም: ነዳያንን ሲያበላ ይውል
ነበር:: ሌሊት ደግሞ እኩሉን ሲጸልይና ሲሰግድ እኩሉን
የእስረኞችን እግር ሲያጥብ ያድር ነበር:: ይህ ሁሉ ሲሆንኮ
እርሱ የንጉሡ 3ኛ: የሠራዊትም አለቃ ነው:: በዘመኑ
የሚያገድፍ ምግብና የወይን ጠጅ በአፉ ዙሮ አያውቅም::

+ከነገር ሁሉ በሁዋላ ንጉሡ ዲዮቅልጢያኖስ ካደ:: ዘመነ
ሰማዕታትም ጀመረ:: አብያተ ክርስቲያናት ተቃጠሉ:: ከ47
ሚሊየን በላይ ክርስቲያኖች በመንኮራኩር ተፈጩ::
በመጋዝ ተተረተሩ:: ለአራዊት ተሰጡ:: በግፍም
ተጨፈጨፉ:: ቀባሪ አጥተውም ወደቁ::

+በዚሕ ጊዜ ማር ፊቅጦር እናቱን ቅድስት ማርታን በዕንባ
ተሰናብቶ ወደ ንጉሡ ቀርቦ በክርስቶስ ስም ታመነ::
ክፉ አባትም በልጁ ላይ ሞትን መከረ::

+ከዚያም ቅዱሱን አፉን በብረት ለጉመው ወደ ምድረ
ግብፅ አወረዱት:: መሪያቸው እንዳልነበረ ወታደሮቹ
መኩዋንንቱ ሁሉ ተዘባበቱበት:: እርሱ ከምድራዊ ንግሥና
ሰማያዊ መንግስትን: በሰዎች ፊት ከመክበር ስለ ክርስቶስ
ሲል መናቅን መርጧልና::

+ለቀናት: ለወራትና ለዓመታት መኩዋንንቱ እየተፈራረቁ
አሰቃዩት:: በርሱ ላይ ያልሞከሩት የስቃይ ዓይነት
አልነበረም:: አካሉን ቆራርጠዋል: ዓይኖቹን አውጥተዋል:
ምላሱንም ቆርጠዋል:: ሚያዝያ 27 ቀን ግን በሰይፍ
አንገቱን ቆርጠውታል:: ስለዚህም እናት ቤተ ክርስቲያን
በታላቅ ማክበር ታከብረዋለች::

❖እግዚአብሔርም ለቅዱስ ፊቅጦር እንዲህ አለው:-
"እንደ አቅሙ ስምህን የጠራ: መታሠቢያህን ያደረገ:
ስምህን ያከበረ: የብርሃን ልብስ አጐናጽፌ ወደ መንግስተ
ሰማያት አስገባዋለሁ::"

❖ይህች ቀን ማር ፊቅጦር የተወለደባት ናት፡፡ እናቱን ቅድስት ማርታ (ሶፍያንም) እናስባለን፡፡

❖ቸሩ አምላከ ፊቅጦር ሁላችንም ይማረን:: ከቃል ኪዳኑ አሳትፎ ለርስቱ ያብቃን::

✞✞ ቅዱስ አውሳብዮስ ካልዕ (ጥዑመ ዜና) ✞✞

=> ቅዱስ አውሳብዮስ በወጣትነቱ ከተባረከች ሚስቱ ጋ
በድንግልና የኖረ; በዘመኑ ባሕር ውስጥ ሰጥሞ ይጸልይ;
4,000
አቡነ ዘበሰማያት በአንድ ቀን ያደርስ የነበረ; ስለ
ሃይማኖትም በቀስት የተወጋ; በእሳት የቃጠለ; አካሉን
ቆራርጠው
የጣሉትና እግዚአብሔር ከሞት ያስነሳው ጻድቅና ሰማዕት
ነው:: ከዚህ ሁሉ ነገር በኋላ ከነሥጋው ወደ ሰማይ
ተነጥቆ ለ14
ዓመታት ቆይቷል:: ወደ ምድርም ተመልሶ ለ40 ዓመታት
በሐዋርያነት ከ85,000 በላይ አሕዛብን ወደ ሃይማኖት
መልሷል::
ጌታም በስምህ የተማጸነውን እስከ 7 ትውልድ
እምርልሃለሁ ብሎታል::"

❖አባቶቻችን ደግሞ 'ስም አጠራሩ የከበረ ዜና ሕይወቱ
ያማረ' ሲሉ ይጠሩታል::

❖ ከበረከቱ ያድለን::

✞ የካቲት 13 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ አውሳብዮስ ጻድቅ (ጥዑመ ዜና)
2.ቅዱስ ፊቅጦር ሰማዕት (ልደቱ)
3.ቅዱስ ሰርግዮስ ሰማዕት
4.ቅዱስ መፁን ቀሲስ
5.ቅዱስ ቴዎድሮስ ሰማዕት (የቅ/ፋሲለደስ ልጅ)
6.አባ ጢሞቴዎስ ሊቀ ዻዻሳት
7.አባ ክፍላ
8.አባ ኅብስ

=>ወርኀዊ በዓላት
1.እግዚአብሔር አብ
2.ቅዱስ ሩፋኤል ሊቀ መላዕክት
3."99ኙ" ነገደ መላዕክት
4.ቅዱስ አስከናፍር
5."13ቱ" ግኁሳን አባቶች
6.ቅዱስ አርሳንዮስ ጠቢብ ገዳማዊ
7.አቡነ ዘርዐ ቡሩክ

=>+"+ እግዚአብሔር ቅዱሳንን ስላገለገላችሁ : እስከ
አሁንም ስለምታገለግሏቸው ያደረጋችሁትን ሥራ :
ለስሙም ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዓመጸኛ
አይደለምና:: በእምነትና በትእግስትም የተስፋውን ቃል
የሚወርሱትን እንድትመስሉ እንጂ ዳተኞች እንዳትሆኑ
ተስፋ እስኪሞላ ድረስ እያንዳንዳችሁ ያን ትጋት እስከ
መጨረሻ እንድታሳዩ እንመኛለን::+"+ (ዕብ. 6:10-13)

✞ ወስብሐት ለእግዚአብሔር ✞
††† እንኳን ለታላቁ ሊቅና የተዋሕዶ ጠበቃ ቅዱስ ሳዊሮስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ታላቁ ቅዱስ ሳዊሮስ †††

††† ቅዱስ ሳዊሮስ በስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ በሶርያ አንጾኪያ የተነሳ አባት ነው። ወቅቱ መለካውያን (ሁለት ባሕርይ ባዮች) የሰለጠኑበት እንደ መሆኑ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ምእመናን ያነሱበትና የሚሰደዱበት ጊዜ ነበር። በዚህ ጊዜ ነበር ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ሳዊሮስ በሥላሴ ፈቃድ ለቤተ ክርስቲያን የተነሳው። ሊቃውንት አንበሳ ሲሉ ይጠሩታል።

ቅዱሱ ለተዋሕዶ ሃይማኖት ብዙ ሆኖላታል። የመናፍቃን ጸር በመሆኑ ብዙ ድርሰቶችን ደርሷል። ንጉሡን ዮስጢያኖስን (Justinian) ሳይቀር በይፋ ይገስጸው ነበርና ንጉሡ ሊገድለው ቆረጠ።

ሃይማኖቷ የቀና ንግሥቲቱ ታኦድራ ግን ይህንን ስትሰማ በሌሊት ወደ ሊቁ ሒዳ "እባክህን ሽሽ።" አለችው። እርሱ ግን "ሞት ለእኔ ክብር ነውና አልሔድም።" ሲል መለሰላት። አባቶችን ሰብስባ "ስለ ቤተ ክርስቲያን ስትል" ብለው ለምነው ወደ ግብጽ ሸኙት።

እርሱ እየሔደ ገዳዮቹ ያሳድዱት ገቡ። መንገድ ላይ ቢደርሱበትም ተሰወረባቸው። ለብዙ ቀናትም አብሯቸው ተጓዘ። እነርሱ ተስፋ ቆርጠው ሲመለሱ እርሱ ግን ምድረ ግብጽ ደረሰ።

በምድረ ግብጽም የጵጵስና ልብሱን ትቶ የመነኮሳትን አሮጌ ልብስ ለብሶ ሕዝቡንና መነኮሳቱን አስተማረ፤ አጸና። በየቦታውም ብዙ ተአምራትን ሠራ።

አባቶች መነኮሳትም ማንነቱን ባወቁ ጊዜ ሰገዱለት። ዶርታኦስ (ዱራታኦስ) በሚባል አንድ ደግ ሰው ቤትም በስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ አካባቢ የካቲት ፲፬ ቀን ዐርፏል።

††† አምላከ ቅዱሳን ሊቃውንት የድንግል እመቤታችንን ጣዕሟን ፍቅሯን ያሳድርብን። የአበውን ሃብትና በረከትም አይንሳን።

††† የካቲት ፲፬ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ
፪.ቅዱስ ቄርሎስ ሊቀ ጳጳሳት
፫.አባ ያዕቆብ ሊቀ ጳጳሳት
፬.ቅዱስ ዳርዮስ
፭.ቅድስት ሊድና

††† ወርኀዊ በዓላት
፩.አቡነ አረጋዊ (ዘሚካኤል)
፪.ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ መርዓዊ
፫.ቅዱስ ፊልጶስ ሐዋርያ
፬.ቅዱስ ሙሴ (የእግዚአብሔር ሰው)
፭.አባ ስምዖን ገዳማዊ
፮.አባ ዮሐንስ ጻድቅ
፯.እናታችን ቅድስት ነሣሒት

††† "ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኋችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ።" †††
(ይሁዳ ፩፥፫)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
† እንኳን ለታላቁ ነቢይ ቅዱስ ዘካርያስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱስ ዘካርያስ ነቢይ †††

††† ነቢይ ማለት በቁሙ ኃላፍያትን (አልፎ የተሠወረውን ምሥጢር): መጻዕያትን (ገና ለወደ ፊት የሚሆነውን) የሚያውቅ ሰው ማለት ነው:: ሃብተ ትንቢት የእግዚአብሔር የባሕርይ ገንዘቡ ሲሆን እርሱ ለወደደው ደግሞ በጸጋ ይሰጠዋል:: እነዚህም ከጌታ ሃብተ ትንቢት የተሰጣቸው አባቶችና እናቶች "ቅዱሳን ነቢያት" በመባል ይታወቃሉ::

ዘመነ ነቢያት ተብሎ የሚታወቀው ብሉይ ኪዳን ቢሆንም እስከ ምጽዓት ድረስ ጸጋውን እግዚአብሔር ለፈቀደላቸው አይነሳቸውም:: በሐዋርያት መካከልም ቅዱስ አጋቦስን የመሰሉ ነቢያት ነበሩ:: (ሐዋ. 11:27) ቅዱሳን ነቢያት ከእግዚአብሔር እየተላኩ ሰውን ከፈጣሪው እንዲታረቅ ይመክራሉ: ይገስጻሉ::

ከበጐ ሃይማኖታቸውና ንጽሕናቸው የተነሳም እግዚአብሔርን በተለያየ አርአያና አምሳል አይተውታል::
"እስመ በአንጽሖ መንፈስ ርዕይዎ ነቢያት ለእግዚአብሔር : ወተናጸሩ ገጸ በገጽ::" እንዳለ አባ ሕርያቆስ:: (ቅዳሴ ማርያም)

የብዙ ነቢያት ፍጻሜአቸው መከራን መቀበል ነው:: እውነትን ስለ ተናገሩ: አንዳንዶቹም በእሳት: አንዳንዶቹም በሰይፍ: አንዳንዶቹም በመጋዝ ተፈትነዋል:: ሌሎቹ ለአናብስት ሲጣሉ ቀሪዎቹ ደግሞ በድንጋይ ተወግረዋል::

ስለዚህም መከራቸው ለቤተ ክርስቲያን መሠረት ተብለዋል:: ጌታም ለደቀ መዛሙርቱ "ሌሎች ደከሙ:: እናንተ በድካማቸው ገባችሁ::" ብሎ የነቢያቱን መከራ ተናግሯል:: (ዮሐ. 4:36)

ነቢያት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እና ድንግል እናቱን ለማየት ብዙ ጥረዋል:: ሽተዋልም:: "ብዙ ነቢያትና ጻድቃን እናንተ የምታዩትን ሊያዩ ሹ" እንዳለ ጌታ በወንጌል:: (ማቴ. 13:16, 1ጴጥ. 1:10) ዛሬ ግን በሰማያት ጸጋ በዝቶላቸው: ክብር ተሰጥቷቸው ሐሴትን ያደርጋሉ::

ቅዱሳን ነቢያት በዋነኝነት "አሥራ አምስቱ አበው ነቢያት" : "አራቱ ዐበይት ነቢያት" : "አሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት" እና "ካልአን ነቢያት" ተብለው በ4 ይከፈላሉ::

††† "አሥራ አምስቱ አበው ነቢያት" ማለት:-
1.ቅዱስ አዳም አባታችን
2.ሴት
3.ሔኖስ
4.ቃይናን
5.መላልኤል
6.ያሬድ
7.ኄኖክ
8.ማቱሳላ
9.ላሜሕ
10.ኖኅ
11.አብርሃም
12.ይስሐቅ
13.ያዕቆብ
14.ሙሴ እና
15.ሳሙኤል ናቸው::

††† "አራቱ ዐበይት ነቢያት"
1.ቅዱስ ኢሳይያስ ልዑለ ቃል
2.ቅዱስ ኤርምያስ
3.ቅዱስ ሕዝቅኤል እና
4.ቅዱስ ዳንኤል ናቸው::

††† "አሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት"
1.ቅዱስ ሆሴዕ
2.አሞጽ
3.ሚክያስ
4.ዮናስ
5.ናሆም
6.አብድዩ
7.ሶፎንያስ
8.ሐጌ
9.ኢዩኤል
10.ዕንባቆም
11.ዘካርያስ እና
12.ሚልክያስ ናቸው::

††† "ካልአን ነቢያት" ደግሞ:-
*እነ ኢያሱ
*ሶምሶን
*ዮፍታሔ
*ጌዴዎን
*ዳዊት
*ሰሎሞን
*ኤልያስ እና
*ኤልሳዕ . . . ሌሎችም ናቸው::

††† ነቢያት በከተማም ይከፈላሉ::
*የይሁዳ (ኢየሩሳሌም):
*የሰማርያ (እሥራኤል) እና
*የባቢሎን (በምርኮ ጊዜ) ተብለው ይጠራሉ::

††† በዘመን አከፋፈል ደግሞ:-
*ከአዳም እስከ ዮሴፍ (የዘመነ አበው ነቢያት):
*ከሊቀ ነቢያት ሙሴ እስከ ነቢዩ ሳሙኤል (የዘመነ መሳፍንት ነቢያት)
*ከቅዱስ ዳዊት እስከ ዘሩባቤል ያሉት (የዘመነ ነገሥት ነቢያት):
*ከዘሩባቤል ዕረፍት እስከ መጥምቁ ዮሐንስ ያሉት ደግሞ (የዘመነ ካህናት ነቢያት) ይባላሉ::

††† ስለ ቅዱሳን ነቢያት በጥቂቱ ይህንን ካልን ወደ ዕለቱ በዓል እንመለስ::

††† ቅዱስ ዘካርያስ ቁጥሩ ከአሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት ሲሆን ዘመነ ትንቢቱም ቅ/ል/ክርስቶስ በ450 ዓ/ዓ አካባቢ ነው:: "ደቂቀ ነቢያት" ማለት በጥሬው "የነቢያት ልጆች" ማለት ነው:: አንድም የጻፏቸው ትንቢቶች ሲበዙ 14 ምዕራፍ: ሲያንስ አንድ ምዕራፍ ያላቸው ናቸውና ደቂቅ ይላቸዋል::

††† ነቢዩ ቅዱስ ዘካርያስ:-
*ከክርስቶስ ልደት 450 ዓመታት በፊት የነበረ::
*በጻድቅነቱ የተመሰከረለት::
*14 ምዕራፎች ያሉት ሐረገ - ትንቢት የተናገረ::
*ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ሥራ በስፋት የተነበየ ነቢይ ሲሆን ከአሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያትም አንዱ ነው::

††† የአባታችን በረከት ይደርብን::

††† የካቲት 15 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ዘካርያስ ነቢይ (ከአሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት አንዱ)
2.ቅዱስ አባ በፍኑትዮስ ገዳማዊ (ከጻድቅነቱ ባሻገር በግብጽ በርሃ የሚኖሩ የብዙ ቅዱሳንን ዜና ሕይወት የጻፈ አባት ነው::)
3.ቅዱሳን አርብዐ ሐራ ሰማይ (40 የሰማይ ጭፍሮች) ለ40 ቀናት ሰብስጥያ በምትባል ሃገር መከራ ተቀብለው በሰማዕትነት ያለፉ ክርስቲያን ጓደኛሞች::

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ቂርቆስና እናቱ ኢየሉጣ
2.ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ (አፈ በረከት)
3.ቅዱስ ሚናስ ግብጻዊ
4.ቅድስት እንባ መሪና
5.ቅድስት ክርስጢና

††† ". . . የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል:: 'ወደ እኔ ተመለሱ . . . እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ::' " †††
(ዘካርያስ ፩፥፫)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
የካቲት 16

እንኩዋን ለእናታችን ቅድስት ኤልሳቤጥ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ

+" ቅድስት ኤልሳቤጥ "+

=>በወንጌላዊው አንደበት የተመሰገነች እናታችን ቅድስት ኤልሳቤጥ ትውልዷ ከነገደ ሌዊ ነው:: ሐረገ ሙላዷም ከቅዱስ አሮን ካህን ወገን ይመዘዛል:: ከአሮን በቴክታና በጥሪቃ ወርዶ ሔርሜላ ላይ ይደርሳል::

+ይህቺ ሔርሜላ የምትባል ደግ ሴት ማጣት ("ጣ" ጠብቆ ይነበብ) የሚባል የተባረከ ሰው አግብታ 3 ቡሩካት ልጆችን ወለደች:: የመጀመሪያዋን 'ማርያም' አሏት:: እርሷ ቅድስት ሰሎሜን ወለደች:: ሁለተኛዋን 'ሶፍያ' አሏት:: እርሷ ደግሞ ቅድስት ኤልሳቤጥን ወለደች::

+ሦስተኛዋ ግን የተለየች ናት:: 'ሐና' ብለው ሰየሟት:: እርሷም የሰማይና የምድር ንግሥት የሆነችውን ድንግል ማርያምን ወለደች:: በዚህም መሠረት ድንግል ማርያም: ቅድስት ኤልሳቤጥና ቅድስት ሰሎሜ የእህትማማች ልጆች ናቸው::

+ቅድስት ኤልሳቤጥ እድሜዋ በደረሰ ጊዜ ስም አጠራሩ የከበረ: ደግ ካህን ለሆነ: ለቅዱስ ዘካርያስ አጋቧት:: እርሷ የሊቀ ካህናቱ ሚስት ናትና ክብሯ ከፍ ያለ ነበር:: ምንም ልጅ ባይኖራትም ዘወትር በጸሎትና በጾም: ምጽዋትንም በማዘውተር: ነዳያንንም በማሰብ የምትኖር እናትም ነበረች::

+ቅዱስ ወንጌል ላይ ከእመቤታችን ቀጥሎ የነዘካርያስን ቤተሰብ ያህል ክብሩ የተገለጠለት ፍጡር ይኖራል ብሎ መናገሩ ይከብዳል:: ቅዱስ ሉቃስ ወንጌሉን የጀመረው በዚህ ቅዱስ ቤተሰብ ነውና መንፈስ ቅዱስ እንዲህ ሲል አጽፎታል::
"ዘካርያስ ካህኑና ቅድስት ኤልሳቤጥ በሰውና በእግዚአብሔር ፊት ያለ ነቀፋ የሚኖሩ ጻድቃን ነበሩ" ይላቸዋል:: (ሉቃ. 1:6)

+የሰውን እንተወውና በእግዚአብሔር ፊት ያለ ነቀፋ መኖር ምን ይረቅ? ለዚህ አንክሮ (አድናቆት) ይገባል! እሊህ ቅዱሳን ባልና ሚስት ግን መካኖች በመሆናቸው ልጅ ሳይወልዱ ዘመናቸው አልፎ ነበር:: እንደ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት ዕድሜአቸው የኤልሳቤጥ 90 የዘካርያስ 100 ደግሞ ደርሶ ነበር::

+ፍጹም መታገሳቸውን የተመለከተ ጌታ ግን በስተ እርጅናቸው ከሰው ሁሉ በላይ የሆነ ታላቅ ነቢይን ይሰጣቸው ዘንድ መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤልን ላከላቸው:: ቅድስቲቷ መስከረም 26 ቀን ታላቁን ሰው ጸንሳ ለ6 ወራት ራሷን ሠወረች::

+ድንግል እመቤታችን ወደ እርሷ መጥታ 'ሰላም' ባለቻት ጊዜ ምንም ያሳደገቻት ልጇ ማለት ብትሆን: መንፈስ ቅዱስ ስለ ሞላባት እመ ብርሃንን አመስግናታለች:: ቡርክት: ብጽእት: ከፍጥረተ ዓለሙ የከበረች መሆኗንም መስክራለች::

+በማሕጸኗ ያለ የ6 ወር ጽንስም የእመ አምላክን ድምጽ ቢሰማ በደስታ ዘሏል:: ለፈጣሪውም ስግደተ-ስባሔ አቅርቧል:: ቅድስት ኤልሳቤጥ አክላም "ወምንትኑ አነ ከመ ትምጽኢ ኀቤየ እሙ ለእግዚእየ-የጌታየ እናቱ ወደ እኔ ትመጪ ዘንድ እንዴት ይገባኛል?" ስትል በትኅትና ተናግራለች:: ከጌታ እናት ጋር ለ3 ወራት በአንድ ቤት ቆይታለች::

+ቅዱስ ዮሐንስ ከተወለደ 2 ዓመት ከ6 ወር በሆነው ጊዜ ሰብአ ሰገል በመምጣታቸው በእሥራኤል ምድር የሚገኙ ሕጻናትን ሔሮድስ ቁዝ አስፈጀ:: ትንሽ ቆይቶም አይሁድ ለሔሮድስ ስለ ቅዱሱ ሕጻን ነገሩት:: "ሲጸነስ የአባቱን አንደበት የዘጋ: ሲወለድ ደግሞ የከፈተ 'ዮሐንስ' የሚባል ሕጻን አለና እሱንም ግደል" አሉ::

+እናቱ ቅድስት ኤልሳቤጥ ይዛው ስትሸሽ ካህኑን ዘካርያስን ግን በቤተ መቅደስ መካከል ገድለውታል:: አረጋይት ኤልሳቤጥም ሕጻኑን እያሳደገች በገዳመ ዚፋታ ለ3 (5) ዓመታት ቆይታለች:: ቅዱስ ዮሐንስ 5 (7) ዓመት ሲሞላው ግን እዚያው በበርሃ እናቱ ዐረፈች:: ከሰማይ ዘካርያስና ስምዖን ወርደው ቀበሯት:: ኤልሳቤጥ ማለት 'እግዚአብሔር መሐላየ ነው': አንድም 'የጌታ አገልጋይ' ማለት ነው::

+ሊቃውንትም:-
+"+ ሰላም ለኤልሳቤጥ እንተ ወደሳ ወአልዓላ:
ሉቃስ ወንጌለ ሶበ ጸሐፈ ለታኦፊላ:
ሐገረ ይሁዳ አሜሃ ሶበ በጽሐት እምገሊላ:
ተሐስየ በውስተ ከርሣ ወአንፈርዓጸ ዕጉዋላ:
ለማርያም ድንግል ሶበ ሰምዓት ቃላ:: +"+ ሲሉ አወድሰዋታል::

=>ከቅድስት እናታችን ክብሯንና በረከቷን ይክፈለን::

   ወስብሐት ለእግዚአብሔር

⛪️ዝክረ ቅዱሳን ጉባኤ
'
" ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"::/የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ) እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::  አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ /መጽሐፈ ምሥጢር/
https://www.tg-me.com/zikirekdusn
ቅዱስ ሐርቤ (ገብረ ማርያም)

ከ4ቱ ቅዱሳን የዛግዌ ነገሥታት አንዱ የሆነው ቅዱስ ሐርቤ /ገብረማርያም/ያረፈው በዚሁ ዕለት (የካቲት 16) ነው::
ለሃገራችን ኩራት : ለቤተ ክርስቲያናችን ደግሞ ሞገስ የሆነ ቅዱስና መናኝ ንጉሥ ነው::

<< አምላክ ከበረከቱ ይክፈለን:: >>

ዝክረቅዱሳን ማኅበረ ቅዱስ ዳዊት'
" ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"::/የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ) እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል:: አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ /መጽሐፈ ምሥጢር/
https://www.tg-me.com/zikirekdusn
2024/11/05 19:07:11
Back to Top
HTML Embed Code: