Telegram Web Link
+*" ቅዱስ አብርሃም ርዕሰ አበው "*+

=>የሃይማኖት: የደግነት: የምጽዋት: የፍቅር አባት የሆነው አብርሃም በቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት አባቱ ታራ ጣዖትን ይጠርብና ይሸጥ ነበር:: ሽጦ ገንዘብ የሚያመጣለት ደግሞ ልጁ አብርሃም ነበር::

*በዚያ ወራት አብርሃም እውነተኛውን አምላክ ፍለጋ ገብቶ ነበር:: አንድ ቀን ጣዖቱን ሊሸጥ ወደ ገበያ እየሔደ የተሸከመውን እንጨት ይመራመረው ገባ:: "አሁን ይሔ ምኑ ነው አምላክ!" እያለም ያደንቅ ገባ:: መንገድ ላይም ደክሞት ካረፈበት "ለምን አልጠይቀውም" በሚል አናገረው::

*"እርቦኛል አብላኝ" አለው:: መልስ የለም:: "እሺ አጠጣኝ" አለው:: አሁንም ያው ነው:: "ባይሆን እሺ አጫውተኝ" አለው:: ጣዖቱ ተራ እንጨት ነውና መልሱ ዝምታ ነበር:: ከዚያ ተነስቶ ወደ ገበያው ሲደርስ "ዐይን እያለው የማያይ: ጀሮ እያለው የማይሰማ አምላክ የሚገዛ" እያለ ይጮህ ጀመር::

*ይህን ሲሰሙ አንዳንዶቹ "የታራ ልጅ አብዶ" ሲሉ ሌሎቹ ደግሞ "እሱ ያቀለለውን ማን ይገዛዋል" ብለውት ሔደዋል:: ከገበያ ሲመለስም ጣዖቱን ተመልክቶ አብርሃም እንዲህ አለ:: "አንተ ቀድሞውን በዕለተ ሠሉስ የተፈጠርክ ዕፅ ነህ" ብሎ ሰባበረው::

*ወደ ቤቱ ሲመለስም ሁሉንም ጣዖታት ሠባበራቸው:: የመንግስተ ሰማያት አበጋዝ: የእግዚአብሔር ወዳጅ: የሕዝብና የአሕዛብ አባት የሆነው አብርሃም እግዚአብሔርን አምልኮ: ጣዖታትን ሰብሮ ወደ ከነዓን ከወጣ በሁዋላ ብዙ ችግርን አሳልፏል:: በረሃብ ምክንያት ከአንድም 2 ጊዜ ወደ ግብጽና ፍልስጥኤም ተሰዷል:: በዚያ ግን ፈጣሪው አክብሮታል::

*2ቱ ነገሥታት (ፈርኦንና አቤሜሌክ) ሣራን እንነካለን ቢሉ ተግሣጽ ደርሶባቸዋል:: ነቢይ ነውና በአብርሃም ጸሎት ተፈውሰዋል:: ቅዱስ አብርሃም ከደግነቱ የተነሳ በኬብሮን (በተመሳቀለ መንገድ) ላይ ድንኩዋን ሠርቶ እንግዳ ይቀበል ነበር:: ምሥክር ሳይይዝም እህል አይቀምስም ነበር::

*ሰይጣን ከፍቶ ለ3 ቀናት እንግዳ ቢያስቀርበት ያለ ምግብ ለ3 ቀናት ቆይቷል:: በፍጻሜውም ሥላሴ በእንግድነት መጥተውለት በክብር ላይ ክብር: በጸጋ ላይ ጸጋ: በጣዕም ላይ ጣዕም ተጨምሮለታል:: እርሱ የሥላሴን እግር ያጥብ ዘንድ: በጀርባውም ይሸከማቸው ዘንድ አድሎታልና:: ሥላሴም በቤቱ ተስተናግደው: ልደተ ይስሐቅን አክብሥረውታል:: ጻድቁ ሰውም በፈጣሪው ፊት ስለ ሰዶምና ገሞራ ለምኗል::

*አብርሃም በአምልኮው ፍጹም ነውና የሚወደውን ልጁን ይስሐቅን ለመስዋዕት አቅርቧል:: በዚህም የነቢያት: የሐዋርያት: የነገሥታት: የካህናት አባት: ሥርወ ሃይማኖት (የሃይማኖት ሥር) ተብሏል:: ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ አያቱም ተብሏል::

*አንድ ቀን እግዚአብሔር መላእክቱን "ብየ አርክ አብርሃም በዲበ ምድር - በምድር ላይ ወዳጄ አብርሃም አለ" አላቸው:: ያን ጊዜ 99ኙ ነገደ መላእክት ፈጣሪያቸውን አመሰገኑ:-
>"አብርሃም አርከ እግዚአብሔር (አብርሃም የእግዚአብሔር ወዳጅ)"
>"አብርሃም ብእሴ እግዚአብሔር (አብርሃም የእግዚአብሔር ሰው)"

>"አብርሃም ገብረ እግዚአብሔር (አብርሃም የእግዚአብሔር አገልጋይ)"
>"አብርሃም ምዕመነ እግዚአብሔር
(አብርሃም የእግዚአብሔር ታማኝ)
>"አብርሃም ፍቁረ እግዚአብሔር (አብርሃም የእግዚአብሔር ተወዳጁ ነው) እያሉ አሰምተው ተናግረዋል::

*አባታችን አብርሃም በክብር: በቅድስናና በሞገስ ከዘፍጥረት እስከ ዮሐንስ ራዕይ ድረስ ተጠቅሷል:: ፈጣሪ በስሙ ለቅዱሳን ተለምኗል:: ስለ ክብሩም በሲዖል ውስጥ እንኩዋ ማረፊያን ሠርቶለታል:: አጋንንትም ሊቀርቡት አልተቻላቸውም:: ያረፈውም ከክርስቶስ ልደት 1,900 ዓመታት በፊት ነው:: እድሜውም 175 ዓመት ነበር::

*ፍቅሩን የተረዱ ሊቃውንት ድንግል ማርያምን "ሐይመቱ (ድንኩዋኑ): ተናግዶቱ (እንግድነቱ) ለአብርሃም" ሲሉ አመስግነዋታል:: ሊቁም:-
"አብርሃም ፍጹም በሒሩት ወበአምልኮ:
እግዚአብሔር አዕበየከ ወባረከከ ባርኮ:
እስከ ሰመየከ ዲበ ምድር አርኮ::" ብሎ በምሥጢር ገልጾታል::

=>አምላከ ቅዱሳን በእነርሱ ላይ የበዛች ፍቅሩን ለእኛም ያድለን:: ፍሬ ትሩፋት: ፍሬ ክብር እንድናፈራም ይርዳን:: ክብራቸውንም አያጉድልብን::

    <ወስብሐት ለእግዚአብሔር>
† እንኳን ለጌታችን አማኑኤል ክርስቶስ ዓመታዊ የተአምር በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

ተአምረ እግዚእ

††† "ተአምር" የሚለውን ቃል በቁሙ "ምልክት" ብሎ መተርጐም ይቻላል:: መሠረታዊ መልዕክቱ ግን ነጮቹ በልሳናቸው Miracle የሚሉት ዓይነት ነው:: ከተፈጥሮ ሕግ ውጪ (በላይ): ከፍጡራንም ችሎታ የላቀ ነገር ሲሠራ (ሲፈጸም) ተአምር ይባላል::

ተአምር የእግዚአብሔር የባሕርይ ገንዘቡ ነው:: እርሱ ዓለምን ከመፍጠሩ ጀምሮ እያንዳንዷ ተግባሩ ለእኛ ተአምራት ናቸው:: ስለዚህም ነው "ኤልሻዳይ - ከሐሌ ኩሉ - ሁሉን ቻይ" እያልን የምንጠራው::

እግዚአብሔር ፍጡራኑን ይወዳልና እርሱ ለወደዳቸውና ደስ ላሰኙት ተአምራት ማድረግን ሰጥቷል:: በብሉይ ኪዳን እነ ሙሴ ባሕር ሲከፍሉ: መና ሲያዘንሙ: ውሃ ሲያፈልቁ (ኦሪትን ተመልከት) እነ ኤልያስ ሰማይን ሲለጉሙ: እሳትን ሲያዘንሙ: ሙታንን ሲያስነሱ (1 ነገሥት) እንደ ነበር ይታወቃል::

እንዲያውም በሙሉ መጽሐፍ ቅዱስ የተአምር መጽሐፍ ነው ብሎ ለመናገርም ያስደፍራል:: በሐዲስ ኪዳንም መድኃኒታችን ብዙ ተአምራትን ሠርቶ ለሐዋርያቱ የተአምራት ጸጋውን ሰጥቷቸዋል:: (ማቴ. 10:8, 17:20, ማር. 16:17, ሉቃ. 10:17, ዮሐ. 14:12)

እነርሱም በተሰጣቸው ሥልጣን ብዙ ተአምራትን ሠርተዋል:: (ሐዋ. 3:6, 5:1, 5:12, 8:6, 9:33-43, 14:8, 19:11)

††† ተአምራተ እግዚእ †††

††† ጌታችን በመዋዕለ ስብከቱ ብዙ ተአምራትን ሰርቷል:: እያንዳንዱ ግን ቢጻፍ ዓለም ለራሷ ባልበቃች ነበር:: ከእነዚህ መካከልም አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው በዚህ ዕለት በ7 እንጀራ እና በጥቂት ዓሣ ሴቶችና ሕፃናትን ሳይጨምር 4,000 ሰዎችን በቸርነቱ አበርክቶ አጥግቡዋል:: ደቀ መዛሙርቱም 7 ቅርጫት ማዕድ አንስተዋል::

ጌታችን በከሃሊነቱ የተራቡትን ሲያጠግብ እንዲሁ አይደለም:: በጊዜው የነበሩ አይሁድ ጠማሞች ነበሩና እነሱን ምላሽ በሚያሳጣ መንገድ ነበር እንጂ:: አይሁድ ላለማመን ብዙ ጥረት ነበራቸውና::

በዚህ ዕለትም እንጀራውን አበርክቶ ሲያበላቸው:-
1.ጊዜው አመሻሽ ላይ ነበር:: ምክንያት:- ጧት ላይ ቢሆን ከቤታችን የበላነው ሳይጐድል ብለው ከማመን ይርቁ ነበርና::

2.ከውሃ ዳር አድርጐታል:: መታጠቢያ ብናጣ በደንብ ሳንበላ ቀረን እንዳይሉ::

3.ሳር የበዛበት ቦታ ላይ አድርጐታል:: ምክንያቱም መቀመጫ ብናጣ በደንብ ሳንበላ ቀረን እንዳይሉ::

4.ከከተማ አርቆ ምድረ በዳ ላይ አድርጐታል:: ያማ ባይሆን "ፈጣን: ፈጣን ደቀ መዛሙርቱ ተሯሩጠው እየገዙ አቀረቡለት" ባሉ ነበርና::

††† ለመድኃኒታችን ክርስቶስ አምልኮና ምስጋና ይሁን!
አማኑኤል አምላካችን ጣዕመ ፍቅሩን ያሳድርብን::

††† ጥር 28 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ቀሌምንጦስ ሰማዕት (ስለ ሃይማኖት 7 ጊዜ ሙቶ የተነሳ, 7 አክሊል የወረደለት)
2.ቅዱስ አካውህ መነኮስ
3."800" ሰማዕታት
4.ቅዱስ ዮሴፍ አይሁዳዊ (የእመቤታችን ወዳጅ)
5.ቅድስት ሳቤላ

††† ወርሐዊ በዓላት
1.አባቶቻችን አብርሃም: ይስሐቅና ያዕቆብ
2.ቅዱስ ቴዎድሮስ ሮማዊ
3.ቅዱስ እንድራኒቆስና አትናስያ
4.ቅድስት ዓመተ ክርስቶስ

††† "ጌታ ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ:- ሕዝቡ ከእኔ ጋር እስከ አሁን ሦስት ቀን ውለዋልና የሚበሉት ስለ ሌላቸው አዝንላቸዋለሁ:: በመንገድም እንዳይዝሉ ጦማቸውን ላሰናብታቸው አልወድም' አላቸው::
ደቀ መዛሙርቱም:- 'ይህን ያህል ሕዝብ የሚያጠግብ ይህን ያህል እንጀራ በምድረ በዳ ከወዴት እናገኛለን?' አሉት:: ጌታ ኢየሱስም:- 'ስንት እንጀራ አላችሁ?' አላቸው:: እነርሱም:- 'ሰባት: ጥቂትም ትንሽ ዓሣ' አሉት::
ሕዝቡም በምድር ላይ እንዲቀመጡ አዘዘ:: ሰባቱንም እንጀራ: ዓሣውንም ይዞ አመሰገነ:: ቆርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ:: ደቀ መዛሙርቱም ለሕዝቡ:: ሁሉም በሉና ጠገቡ:: የተረፈውንም ቁርስራሽ ሰባት ቅርጫት ሙሉ አነሱ:: የበሉትም ከሴቶችና ከልጆች በቀር አራት ሺህ ወንዶች ነበሩ::" †††
(ማቴ. 15:32)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
† እንኳን ለቅዱሳን ጻድቃነ ዴጌ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †

† ጻድቃነ ዴጌ †

† እነዚህ ጻድቃን ኢትዮዽያውያን ባይሆኑም ያበሩት በሃገራችን ነው:: ቅዱሳኑ በቁጥር 3,000 : በዜግነት ሮማውያን ናቸው:: ከሺህ አዝማናት በፊት ከሮም ግዛት ተሰባስበው እንደ ተስዓቱ ቅዱሳን ወደ ኢትዮዽያ (አክሱም) መጥተዋል::

ቀጥለውም እዛው አካባቢ ወደሚገኝ ገዳም ገብተዋል:: ይህ ቦታ ለአክሱም ቅርብ ሲሆን በዘመነ ሐዋርያት የቅዱስ ማቴዎስ ወንጌላዊ በዓት ነበር:: የሐዋርያው በትረ መስቀልም እስካሁን አለች::

ጻድቃነ ዴጌ ሕጋቸው አንዲት : እርሷም ፍቅር ናት:: ለዘመናት በፍቅረ ክርስቶስ ታሥረው : ፍቅርን ለብሰው : በፍቅር ኑረዋል:: ሁሌም በ29 የጌታችንን ስም እየጠሩ ጽዋ ጠጥተዋል:: ስለ ፍቅራቸውም ጌታችን 3,001ኛ ሆኖ : ነዳይ መስሎ አብሯቸው ጠጥቷል::

በመጨረሻም 3ሺው በአንድነት ተሠውረዋል::

††† ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን:: እኛንም በወዳጆቹ ጸሎት ይማረን:: . . .አሜን!

††† ጥር 29 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ጻድቃን ቅዱሳን ማሕበረ ዶጌ (ዴጌ ጻድቃን)
(አክሱም አካባቢ በቁጥር ወደ 3,000 ሲሆኑ ከመድኃኔ ዓለም ጋር ማሕበር ይጠጡ የነበሩና በአንድ ላይ የተሠወሩ ቅዱሳን ናቸው)
2.አባ ገብረ ናዝራዊ ዘቃውንት (ኢትዮዽያዊ)
3.ቅድስት አክሳኒ ፈላሲት
4.ቅዱስ ሰርያኮስ ሰማዕት
5.አባ እስጢፋኖስ ገዳማዊ
6.ከድሮዋ ሮም የተነሱ ቅዱሳት አንስት

††† ወርሐዊ በዓላት
1.ቅድስት አርሴማ ሰማዕት
2.ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ እናታችን
3.ቅዱስ ዼጥሮስ ተፍፃሜተ ሰማዕት
4.ቅዱስ ማርቆስ ዘቶርማቅ
5.ቅዱስ ዘርዐ ክርስቶስ

††† "ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ::
በእርስዋም ለዘለዓለም ይኖራሉ::
የጻድቅ አፍ ጥበብን ያስተምራል::
አንደበቱም ፍርድን ይናገራል::
የአምላኩ ሕግ በልቡ ውስጥ ነው::
በእርምጃውም አይሰናከልም::" †††
(መዝ. 36:29)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
ጥር 29
ወበዛቲ ዕለት አዕረፈ አብ ክቡር አረጋዊ፡ ወሰማዕተ ጽድቅ አቡነ ታዴዎስ ዘጽላልሽ፡፡ በዚህች ዕለት ኢትዮጵያዊው ፃድቅ አቡነ ታዴዎስ አረፉ

#አቡነ_ታዴዎስ_ዘጽላልሽ

ትውልድ ሀገራቸው ጽላልሽ (ዞረ) ነው። አባታቸው ሮማንዮስ እናታቸው ማርታ ይባላሉ። አባታቸው ሮማንዮስ ቄስ ነው። የአቡነ ተክለ ሃይማኖት አጎት ናቸው።
በእናታቸው ማኅፀን ሳሉ በጽላልሽ ረሀብ ፀንቶ ነበር። እሳቸው ግንቦት ፳፫ ቀን በመንፈቀ ሌሊት በልብሰ ብርሃን ተጠቅልለው ተወለዱ። ቤታቸው በበረከት ተመላ። ለሀገሬው ዝናብ ዘንቦለት ህዝቡ ከፃድቁ እናትና አባት የተመፀወቱትን ከፍለው ዘሩ።

አቡነ ታዴዎስ በተወለዱ በ፵ ቀናቸው ሐምሌ ፪ ቀን ሲጠመቁ የተዘራው እህል አንድ ሳይቀር አፍርቶ ተገኝቷል።

ዕድሜአቸው ለትምህርት ሲደርስ ለሊቀ ካህናቱ ለሕይወት ብነ ሰጥተዋቸው ሲማሩ አደጉ። አቡነ ተክለ ሃይማኖት ዳሞት (ወላይታ) ተሻግረው መተሎሚን አስተምረው “በእግዚአብሔር ቸርነት በአንተ ፀሎት መተሎሚን በሃይማኖት ወልጄዋለሁ። በምግባር አሳድጌዋለሁና እህትህን ይዘህ በቶሎ ና፤” ብለው ላኩባቸው።
እህታቸው ትቤጽዮን ትባላለች። የመተሎሚን ወንድም ዝግናን አግብታ አባ ኤልሳዕን ወልዳለች። ከባሏ ተጣልታ ነበርና እሷን ከባሏ አስታርቀው እሳቸው አቡነ ተክለሃይማኖትን እያገለገሉ ፱ አመት ኖረዋል።

በኋላ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ወደ አባ በጸሎተ ሚካኤል ሲሄዱ እሳቸውም ወደ ጽላልሽ ተመልሰው ስለነበር አፄ ይኩኖ አምላክ እንድትመክረኝ እንድትገስፀኝ ከቤቴ ተቀመጥ ብለው ከቤተመንግስት አስቀመጣቸው።
ሰይጣን ለፀብ ለምቀኝነት አያርፍምና ጠላ ቤቷን ክፉ የሚገድል ሽታ አሸተታትና ሞተች። አባ ታዴዎስ ወንዝ ገብተው ሲፀልዩ ሙቷ ተነሥታለች። ከዚህ በኋላ ውዳሴ ከንቱ ይሆንብኛል ብለው ወደ ደብረ ሊባኖስ ተመለሱ።

አቡነ ተክለሃይማኖት ወደ ጽጋጋ (ጅጅጋ) ሂድ አሏቸው። ለምን ቢሉ? አባ አኖሬዎስ ሄደው ሲያስተምሩ ያገሬው ሰዎች ደብድበው አስረዋቸው ነበርና እሳቸውን ለማሰወፈታት ነበር።
የአካባቢው ንጉስ መዩጥ ይባላል። በነፋስ ሰረገላ ተጭነው ሄደው ከፊቱ ወርደው ሲቆሙ ደንግጦ ከሰማይ መላእክት ነህ ወይስ ከሰው ወገን? ቢላቸው። እኔ ከሰው ወገን ነኝ አሉት። ክርስትናንም አስተማሩት ጋኔን ከእሳት ላይ ጥሎት ሲሰቃይ የሚኖር ልጅ ነበረው አድነውለታል።
ይህን አይቶ አምኖ ሕዝቡም እንዲያምኑና ክርስትናን እንዲቀበሉ አዋጅ ነገረ።

እንደ ሐዋርያው ታዴዎስ ፳፭ ግመል በመርፌ ቀዳዳ በተአምራት አሳልፈው በማሳየታቸው አፍጃል የሚባል ያንድ ባለጠጋ ልጅ በምትሐት እንደሚያደርጉት አድርጎ በመናገሩ ከግመሎቹ አንዲቱ ረግጣው ሞተ፤ ይህን ሙሳ የሚባል ልጅም በተቀበረ በሦስተኛው ቀን «አልዓዛርን ከሙታን በአስነሳው በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ልጄ ና ተነስ» ብለህ ይህንን መቋሚያዬን ወስደህ ከመቃብሩ ላይ አኑር ብለው በአፍጃል ሰጥተውት እንዳሉት ቢያደርግ አፈፍ ብሎ ተነስቷል።
ይህን አይተው ህዝቡ ሁሉ አምነዋል። ከዚህ በኋላ ሙሳን ሙሴ ብለው ሊቀ ካህናት አድርገው ፲፪ አብያተ ክርስቲያናት አሳንፀው አኖሬዎስን ይዘው ተመልሰዋል።

አቡነ ተክለሃይማኖትም ከንጉሱ ተማክረው ሊቀካህናት ዘጽላልሽ ብለው ሾመዋቸዋል።
ንጉስ ዓምደ ጽዮን ፍቅረ ዝሙት አድሮበት የአባቱን ቅምጥ ቢያገባት ሄደው ገሰፁት። በዚህ የተናደደች የንጉሱ ሚስት የኋሊት አሳስራ ከጥልቅ ገደል አሰጣለቻቸው።
በዚህ ጊዜ የመቶ ሃያ አመት አረጋዊ ነበሩ።

የታዘዘ መልአክ ገብረ እግዚአብሔርና ውቢት የተባሉ ደጋግ ሰዎችን አስነስቶ ስጋቸውን ወስደው ከበዓታቸው ቀብረው የተሰጣቸውንም ቃል ኪዳን በዳግማዊ አፄ ዳዊት ዘመን በህዝቡ ፊት መስክረዋል።
ንጉስ ዳዊትም ዜና ገድላቸውን አጽፈዋል፤ ስጋቸውንም ወደ ከተማቸው በክብር አፍልሰው በተቀደሰ ስፍራ አኑረውታል።

የፃድቁ አባታችን እረድሄት በረከት ይደርብን አሜን!!!
† እንኳን ለቅዱሳት አንስት ሶፍያ ወአዋልዲሃ: ኦርኒ ወማኅበራኒሃ እና ለሊቁ ቅዱስ ጐርጐርዮስ ነባቤ መለኮት ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †

† ቅድስት ሶፍያና ልጆቿ †

† በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ታዋቂ ከሆኑ የእናቶቻችን ስሞች "ሶፍያ" ቀዳሚው ነው:: ቃሉ በጥሬው ሲተረጐም "ጥበብ (ጥበበ ክርስቶስ) Wisdom of God" ማለት ነው:: ከጻድቃንና ከሰማዕታት ወገን በዚህ ስም የተጠሩ እናቶች አሉ::

ከእነዚህ መካከል አንዷ የሆነችው በዕለቱ የምናስባት እናት ቁጥሯ ከሰማዕታት ነው:: ዋናው ዘመነ ሰማዕታት ከመጀመሩ በፊት የነበረችው ቅድስት ሶፍያ ከሕግ ትዳር 3 ሴቶች ልጆችን አፍርታለች::

ስማቸውንም:- ጲስጢስ (ሃይማኖት) : አላጲስ (ተስፋ) : አጋጲስ (ፍቅር) ስትል ሰይማቸዋለች:: እንደሚገባም በሥርዓቱ አሳድጋ እድሜአቸው 9 : 10 እና 12 ሲደርስ ለሰማያዊ ሙሽርነት አጭታቸዋለች::

በዘመኑ "ክርስቶስን ካዱ" የሚል መሪ ተነስቶ ነበርና ቅዱሳቱ በመድኃኒታችን አምነው : ጣዖትን ዘልፈው አንገታቸውን ሰጥተዋል:: ክብረ ሰማዕትን : ሃገረ ክርስቶስንም ወርሰዋል::

††† ቅድስት ኦርኒ ሰማዕት †††

††† "ኦርኒ" ማለት በምሥራቃውያን ልሳን "ሰላም" ማለት ነው:: ቅድስቲቱ አርበኛ የዘመነ ሐዋርያት የቤተ ክርስቲያን ፍሬ ስትሆን ተወልዳ ያደገችውም በቀድሞው የሮም ግዛት ውስጥ ነው::

ምንም ዛሬ ያለ ትውልድ ቢዘነጋት ቅድስት ኦርኒ ተወዳዳሪ የሌላት ሰማዕት : ሐዋርያዊት : ድንግል ናት:: እርሷ ውበቷን : ንግሥናዋን : ክብሯን : ሃብቷን : ወጣትነቷንና ያላትን ሁሉ ስለ ፍቅረ ክርስቶስ ሰውታለችና ክብርት ናት::

በ1ኛው መቶ ክ/ዘመን መጨረሻ አካባቢ ከሮም ቤተ መንግስት የተወለደችው ቅድስት ኦርኒ እስከ ወጣትነቷ ድረስ ክርስቶስን ልታውቀው አልተቻላትም ነበር:: ምክንያቱ ደግሞ ንጉሡ አባቷ ጣዖትን ማምለኩ ነበር::

ንግሥት እናቷ ምንም ክርስቲያን ብትሆንም ስለ ክርስትና ልትነግራት አልደፈረችም:: ይህን ብታደርግ የሚደርስባትን መከራ ታውቃለችና:: ግን ደግሞ ውስጥ ውስጡን ትጸልይላት ነበርና ፈጣሪ መንገዱን ሊከፍት ጀመረ::

መምለኬ ጣዖት አባቷ ሰው እንዳያያት ቤተ መንግስት ሠርቶ : 12 ሞግዚቶችን መድቦ ጣዖት ከፊቷ አቁሞ ለዘመናት ዘጋት:: የሚገርመው ግን መልኳን እንዳያይ በበር ሆኖ የሚያስተምራት ፈላስፋ ተቀጥሮ ነበርና የዚህ ሰው ማንነቱ ነው::

መምለኬ ክርስቶስ ደግ ሰው ነበርና ፈሊጥን ይሻላት ገባ:: በዚህ መካከል ቅድስት ኦርኒ ራዕይን ታያለች:: የቤቷ መስኮቶች ተከፍተው ሳሉ በስተምሥራቅ ነጭ ርግብ : የዘይት (የወይራ) ዝንጣፊ ይዛ ገብታ : ከማዕዷ ላይ ጥላው ወጣች::

እርሷን ተከትሎ ቁራ በምዕራብ ገባ:: እባቡን ማዕዷ ላይ ጣለው:: በ3ኛው ደግሞ ንስር ገብቶ አክሊል ትቶላት ወጣ:: ቅድስቲቱም እየገረማት አረጋዊ መምህሯን "ተርጉምልኝ" አለችው::

††† እርሱም:-
"•ርግብ=ጥበብ (መንፈስ ቅዱስ)
•ዘይት=ጥምቀት
•ቁራ=ክፉ ንጉሥ
•እባብ=መከራ
•ንስር=ድል ነሺነት (ልዑላዊነት)
•አክሊልም=ክብረ ሰማዕታት ነው" ብሎ ተርጉሞ : ክርስቲያን ሆና ይህ ሁሉ እንደሚደረግ ነግሮ ተሰናበታት::

እርሷም ስትጸልይ ቅዱስ መልአክ ተገልጦ አጽናናት:: ያጠምቃትና ያስተምራት ዘንድም ሐዋርያው ቅዱስ ጢሞቴዎስን ልኮላታል:: ሐዋርያውም የቤተ መንግስቱን ግድግዳ ሰንጥቆ ገብቶ : ለሰማያዊ ሙሽርነት የሚያበቃ ትምህርትና ጥምቀትን ሰጥቷት ሔዷል::

ቅድስት ኦርኒም የአባቷን ጣዖታት ቀጥቅጣ ሰብራ ከአባቷ ጋር ተጣላች:: እርሱም "እገድላታለሁ" ብሎ በእንስሳት ጅራት ላይ ጸጉሯን ሲያስር እንስሶቹ ደንብረው : እጁን ገንጥለው መሬት ላይ ጥለው ገደሉት:: ቅድስት ኦርኒ ግን ጸሎት አድርሳ አባቷን ከሞት አስነሳችው:: እጁንም ቀጠለችለት::

በዚህ ምክንያት በዚያች ዕለት ብቻ አባቷና 30,000 የከተማው አሕዛብ አምነው ተጠምቀዋል:: ቅድስት ኦርኒ ግን ኃይለ መንፈስ ቅዱስ ታጥቃ ክርስትናን ሰበከች:: ብዙም ተሰቃየች:: ንጉሡ ዳኬዎስ : ልጁና ሌሎች 2 ያህል ነገሥታት በእሳት : በአራዊት : በግርፋትና በጦር ፈትነዋታል::

እርሷ ግን ሁሉን በኃይለ ክርስቶስ ድል ነስታለች:: ሙታም የተነሳችበት ጊዜ አለ:: በመጨረሻም በዚህች ቀን ወደ ሰማያዊ ርስት (ገነት) ተመስጣለች:: በዘመነ ስብከቷ ካሳመነቻቸው ባሻገር 130,000 የሚያህሉ ሰዎች ለሰማዕትነት እንዲበቁም ምክንያት ሆናለች::

††† ቅዱስ ጐርጐርዮስ ታኦሎጐስ †††

††† ቅዱሱ:-
•የዘመነ ሊቃውንት ፍሬ:
•የእንዚናዙ ኤጲስ ቆጶስ:
•የቁስጥንጥንያ ፓትርያርክ:
•የጉባዔ ቁስጥንጥንያ (በ381 ዓ/ም) 3ኛ ሊቀ መንበር:
•ባለ ብዙ ድርሳን:
•የቂሣርያ (ቀጰዶቅያ) ኮከብ:
•ብሩህ ገዳማዊ:
•መልካም እረኛ የነበረ አባት ነው::
መጽሐፈ ቅዳሴውን ጨምሮ በጻፋቸው ብዙ መጻሕፍትና በስብከቱ ከሊቃውንት ወገን "ታኦ(ዎ)ሎጐስ" ተብሎ የተጠራ እርሱ ብቻ ነው:: ትርጉሙም በግዕዙ "ነባቤ መለኮት" ማለት ነው:: በአማርኛም "አንድነትን : ሦስትነትን የተናገረ (ያመሠጠረ) እንደ ማለት ነው:: ቅዱሱ ዛሬ ዕረፍቱ ነው::

††† አምላከ ቅዱሳን ከበረከታቸው ይክፈለን፡፡
በመጽናታቸውም ያጽናን፡፡

††† እንዲህ ኃጢአታችን ጽዋዑን ሞልቶ በተረፈበት በዚህ ዘመን አንዲት ሰዓትም ውድ የሆነች የንስሃ ዕድሜ ናት:: እግዚአብሔር ግን ደግ ነውና ይሔው ጥርን አስፈጸመን:: ባይገባን ነው እንጂ በዚሕች ወር ውስጥ ሚሊየኖች በደዌ የአልጋ ቁራኛ ሁነዋል::

ሚሊየኖችም ለንስሃ ሳይበቁ እንዲሁ አንቀላፍተዋል (ሙተዋል):: እስኪ እርሱ አምላካችን ቀሪውን ዘመን ደግሞ ለንስሃና ለመልካም ሥራ ባርኮ ይስጠን::

††† ወርኀ ጥርን በቸር ያስፈፀመ አምላከ ቅዱሳን ወርኀ የካቲትን እንዲባርክልን እንለምነው::

††† ጥር 30 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅድስት ሶፍያና ሦስቱ ሰማዕታት ልጆቿ (ጲስጢስ አላጲስና አጋጲስ)
2.ቅድስት ኦርኒ ሰማዕት ( (በ5 ነገሥታት እጅ የተሰቃየች : የሐዋርያው ጢሞቴዎስ ተከታይና ወደ ብሔረ ሕያዋን የተነጠቀች እናት)
3.ቅዱስ ጐርጐርዮስ ነባቤ መለኮት
4.አባ አክርስጥሮስ
5.አምስቱ ደናግል ሰማዕታት (ጤቅላ: ማርያ: ማርታ: አበያ: ዓመታ)
6.ጻድቃነ ዴጌ (የተሠወሩበት)
7.አባ ሚናስ ሊቀ ጳጳሳት
8."130,000" ሰማዕታት (የቅድስት ኦርኒ ማኅበር)

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ማርቆስ ዘአንበሳ
2.ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት
3.አባ ሣሉሲ ክቡር

††† "ለእናንተም ጠጉርን በመሸረብና ወርቅን በማንጠልጠል ወይም ልብስን በመጐናጸፍ በውጭ የሆነ ሽልማት አይሁንላችሁ:: ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ የዋህና ዝግተኛ መንፈስ ያለውን የማይጠፋውን ልብስ ለብሶ የተሰወረ የልብ ሰው ይሁንላችሁ::" †††
(፩ጴጥ. ፫፥፫)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
††† እንኳን ለተፍጻሜተ ሰማዕት ቅዱስ ዼጥሮስ እና ለ150ው ቅዱሳን ሊቃውንት ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱስ ዼጥሮስ ሰማዕት †††

††† የቅዱሳን ሰማዕታት መነሻቸው ቅዱስ እስጢፋኖስ ሲሆን ፍጻሜአቸው ደግሞ ቅዱስ ዼጥሮስ ሊቀ ዻዻሳት ነው::

ይህ ቅዱስ የሚታወቀው "ተፍጻሜተ ሰማዕት (የሰማዕታት መጨረሻ)" በሚለው ስሙ ነው:: ይሕስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-
የቅዱሱ ሃገረ ሙላዱ ግብጽ ናት:: ዘመኑም 3ኛው መቶ ክ/ዘመን ነው:: ወላጆቹ ካህን ቴዎድሮስና ቡርክት ሶፍያ ልጅ አጥተው ሐምሌ 5 ቀን ወደ ፈጣሪ ቢማጸኑ በራዕይ ዼጥሮስ ወዻውሎስ ተገልጠው ብሥራትን ለሶፍያ ነገሯት:: በወለደችው ጊዜም በራዕዩ መሠረት "ዼጥሮስ" አለችው::

ሰባት ዓመት በሆነው ጊዜም ለቤተ እግዚአብሔር ሰጥተው በሊቀ ዻዻሳቱ ቅዱስ ቴዎናስ እጅ አደገና በወጣትነቱ ሊቅ: ጥዑመ ቃልና በጐ ሰው ሆነ:: ዲቁናና ቅስናን ተሹሞ ሲያገለግል ቅዱስ ቴዎናስ በማረፉ ቅዱስ ዼጥሮስን የግብጽ 17ኛ ፓትርያርክ አድርገው ሾሙት::

ዘመኑ ደግሞ እጅግ ጭንቅ ነበር:: ክርስቲያኖች በተገኙበት ስለሚገደሉ: አብያተ ክርስቲያናትም ስለ ተቃጠሉ የቅዱሱ መከራ የበዛ ነበር:: ለ14 ዓመታት በፍጹም ትጋት ከመንጋው ጋር ተጨነቀ::

አርዮስን (ተማሪው ነበር) አውግዞ ለየው:: ከጌታ ጋርም ብዙ ጊዜ ተነጋገረ:: ብዙ ተአምራትንም ሠራ:: በዚህ ሁሉ ጊዜ አንድም ቀን በመንበረ ዽዽስናው ላይ አልተቀመጠም:: በሁዋላ ግን ጨካኙ ንጉሥ እንዲገደል አዘዘ::

ሕዝቡ "ከእሱ በፊት እኛን ግደሉን" በማለታቸው ሁከት እንዳይነሳ ቅዱስ ዼጥሮስ ተደብቆ ሔደና በፈቃዱ ለወታደሮች ተሰጠ:: በዚያች ሌሊትም የእርሱ ደም የግፍ ማብቂያ እንዲሆን እያለቀሰ ጮኸ:: ከሰማይም "አሜን! ይሁን!" የሚል ቃል መጣ:: ያን ጊዜ የእርሱ አንገት ተሰየፈ:: ዘመነ ሰማዕታትም አለፈ::

††† የቅዱሳንን ዝክር ከማንበብ ባለፈ በስማቸው መጸለይ (ዘፀ. 32:13): በምጽዋትም ማሰብ (ማቴ. 10:41) ይገባል::

††† ወርኀ የካቲትን ይባርክልን!

††† የካቲት 1 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1."150"ቅዱሳን ሊቃውንት ዻዻሳት (በቁስጥንጥንያ ተሠብሥበው መናፍቃንን ያወገዙበት: ትምሕርተ ቤተ ክርስቲያንን ያፀኑበት /ጉባዔ ቁስጥንጥንያ/ በ381 ዓ/ም::
ከወቅቱ ቅዱሳን ሊቃውንት እነዚህ ይጠቀሳሉ:-
*ቅዱስ ጐርጐርዮስ ዘኑሲስ
*ቅዱስ ጐርጐርዮስ ዘእንዚናዙ
*ቅዱስ ጢሞቴዎስ ዘአልቦ ጥሪት
*ቅዱስ ቄርሎስ ዘኢየሩሳሌም)
2.ቅዱስ ዼጥሮስ ተፍጻሜተ ሰማዕት (ቅዳሴ ቤቱ)
3.ታላቁ ቴዎዶስዮስ ጻድቅ (ንጉሠ ቁስጥንጥንያ)

††† ወርሐዊ በዓላት
1.ልደታ ለቅድስት ድንግል ማርያም እግዝእትነ
2.ቅዱስ በርተሎሜዎስ ሐዋርያ
3.ቅዱስ ሚልኪ ቁልዝማዊ
4.ቅዱስ ራጉኤል ሊቀ መላዕክት
5.ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና

††† "ስለዚህ በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያንን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ዻዻሳት አድርጎ ለሾመባት: ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ:: ከሄድሁ በሁዋላ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኩላዎች እንዲገቡባችሁ እኔ አውቃለሁ:: ስለዚህ 3 ዓመት ሌሊትና ቀን በእንባ እያንዳንዳችሁን ከመገሰጽ እንዳላቁዋረጥሁ እያሰባችሁ ትጉ::" †††
(ሐዋ. 20:28)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
2024/09/30 23:42:45
Back to Top
HTML Embed Code: