Telegram Web Link
<<< በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ፩ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ >>>

<<< ታሕሳስ 26 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት >>>

+" ቅድስት አንስጣስያ "+

=>እስኪ ዛሬ በጥቂቱ የተባረኩ (ቡሩካት) እናቶቻችን
እንዘክር:: "ቅድስት" የሚለው ቃል ለሁሉም ቅዱሳት
እናቶች ቢሰጥም
ቅሉ ለድንግል ማርያም ሲሰጥ ግን ትርጉሙ ይለያል::
እርሷ 'ቅድስተ ቅዱሳን: ንጽሕተ ንጹሐን: ቡርክት
እምቡሩካን:
ኅሪት እምኅሩያን ናትና::

+ከሰው ልጆችም ሁሉ ትበልጣለች:: ይቅርና የሰው ልጅን
ንጹሐን መላእክትንም በንጽሕናና በቅድስና
ትበልጣቸዋለች:: እርሷ
እመ ብርሃን: የአምላክ እናቱ: የሰውነታችን መመኪያ
ናትና::

+እመቤታችንን "ቅድስት" ስንል "ጽንዕት: ንጽሕት: ክብርት:
ልዩ" ማለታችን ነው:: 1."ንጽሕት" ትባላለች:: ሌሎች
ሰዎች (ቅዱሳን) ቢነጹ ከገቢር: ከነቢብ ኃጢአት ነው
እንጂ ከኃልዮ ኃጢአት አይደለም:: እርሷ ግን ከነቢብ:
ከገቢር:
ከኃልዮ ንጽሕት ናት::

"ለመኑ ተውኅቦ ተደንግሎ ኅሊና: ለመላእክትሂ
ኢተክህሎሙ-ኃጢአትን ከማሰብ መጠበቅ ከሰው ልጆች
ለማን ተሰጠው: ይህስ
ለመላእክትም አልተቻላቸውም" እንዲል:: (ተአምረ
ማርያም)

2."ጽንዕት" እንላታለን:: ሴቶች ቢጸኑ ለጊዜው ነው እንጂ
በኋላ በጊዜው ተፈትሆ አለባቸው:: እመቤታችን ግን
ቅድመ
ጸኒስ: ጊዜ ጸኒስ: ድኅረ ጸኒስ: ቅድመ ወሊድ: ጊዜ
ወሊድ: ድኅረ ወሊድ ድንግል ናትና::
"ጽንዕት በድንግልና አልባቲ ሙስና" እንዳላት:: (ቅዱስ
ያሬድ) ታላቁ ቅዱስ ባስልዮስም "ወትረ ድንግል ማርያም-
ማርያም
ዘለዓለማዊት ድንግል ናት" እንዳለ:: (መጽሐፈ ቅዳሴ)

3.ድንግልን "ክብርት" እንላታለን:: ሌሎች ሴቶች ቢከብሩ
ጻድቃን ሰማዕታትን: ነቢያት ሐዋርያትን ወልደው ነው::
እመቤታችንን ግን የምናከብራት "ወላዲተ አምላክ-
የአምላክ እናቱ" ብለን ነውና::

4.እመቤታችንን "ልዩ" እንላታለን:: ከእርሷ በቀር እናት ሁና
ድንግል: እመቤት ሁና አገልጋይ የሆነች: በድንግልና
ወልዳ ወተትን (ሐሊበ ድንግልናዌን) ያስገኘች ሌላ ሴት
የለችምና::

+የእመ ብርሃን ይቆየንና ደግሞ ሌሎች ቅዱሳት
እናቶቻችንን እንመልከት:: እናቶቻችን ስናከብር
የምንጀምረው በቅድስት
ሔዋን ነው:: ብዙ ጊዜ የእናታችን ሔዋን ጥፋቷ እንጂ
በጐ ነገሯ: ደግነቷ: ንስሃዋ አይነገርላትም:: ሆኖም
እናታችን
ቅድስት ሔዋን ክብር የሚገባት ሴት ናት::

*ክርስቶስ ሰው የሆነ እርሷንና ልጆቿን ለመቀደስ ነውና::
"ከመ ይስዓር መርገማ ለሔዋን ዲበ ዕፅ ተሰቅለ"
እንዲል::
(ድጉዋ)

+ቀጥሎ በብሉይ ኪዳን እነ ሐይከል: እድና: ሣራ: ርብቃ:
አስኔት: ሲፓራ: ሐና: ቤርሳቤህን የመሰሉ እናቶቻችን
በበጐው
መንገድ ፈጣሪን ደስ አሰኝተዋል:: በዘመነ ሥጋዌም
ቅዱሳቱ ሐና: ኤልሳቤጥ: ማርያም: ሶፍያ: ሰሎሜ: ዮሐና
እና 36ቱ
ቅዱሳት አንስት በጐነታቸው ያበራል::

+ከዚያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ለ2,000 ዓመታት የተነሱ
አእላፍ ቅዱሳት እናቶቻችንን ግን ዘርዝረን አንዘልቃቸውም::
በቅድስናቸው አራዊትን ያሰገዱ: ነገሥታትን ያንቀጠቀጡ:
አጋንንቸትን የረገጡ: በዘንዶ ላይ የተጫሙ ብዙ እናቶችን
ቤተ
ክርስቲያን አፍርታለች::

+ዛሬም ቢሆን በበርሃና በከተማ በጐውን ጐዳና የተከተሉ
ብዙ እናቶች እንዳሉን እናውቃለን:: አንድም እናምናለን::
ግን
ግን በከተሞች የምንመለከተው ሥርዓቱን የለቀቀው
የበርካታ እህቶቻችን አካሔድ ለሃገርም ለቤተ
ክርስቲያንም ትልቅ ስጋት
ነው:: ክብርና ነውር የማይለይበት ዘመን ይመስላል::

+ይህንን እያነበባችሁ ያላችሁ እህቶቼ! አንድ ነገር
ልንገራችሁ:: በመልካቸው ብዙዎችን ያጋጩ: አጊጠው
በመታየታቸው ብዙዎችን ያሰናከሉ: ለብዙ ምዕመናንም
የጥፋት ምክንያት የሆኑ ብዙ ሴቶች በታሪክ ነበሩ::

+የሚያሳዝነው ግን ዛሬ ያሉት ከመሬት በታች ነው:: አፈር
በልቷቸዋል:: ስም አጠራራቸውም ጠፍቷል:: በጣም
የሚያሳዝነው
ደግሞ ዛሬ በዘለዓለማዊው እሳት እየተቃጠሉ በሲኦል:
በጥልቁ ውስጥ አሉ::

+እናም ወገኖቼ! ይህን አውቀን እንንቃ:: ይህ ዓለም
ጠፊም: አጥፊም ነውና:: እድሜአችን ቢረዝምና ከዚህ
በኋላ ለ100
ዓመታት ብንኖርም እርሱም ማለቁ አይቀርምና::
ምርጫችን ዘለዓለማዊው ሕይወት ይሁን ትላለች ቅድስት
ቤተ ክርስቲያን::

+" ቅድስት አንስጣስያ "+

+ይህች ቅድስት እንደ በርካቶቹ ቅዱሳት እናቶቻችን ሁሉ
የዘመነ ሰማዕታት ፍሬ ናት:: በቀደመችው ታናሽ እስያ
አካባቢ
ተወልዳ: የነገሥታት ዘር በመሆኗ ያደገችው በቤተ
መንግሥት ነው:: አባቷ ከክቡራኑ አንዱ ቢሆንም ሙያው
ጣዖትን ማምለክ
ነበር::

+ጊዜው የመከራ በመሆኑ ብዙ ሴቶች የሚኖሩት
ክርስትናቸውን ደብቀው ነው:: ከእነዚህ መካከል አንዷ
ደግሞ የቅድስት
አንስጣስያ እናት ናት:: ማንን እንደምታመልክ አረሚ ባሏ
አያውቅም ነበር::

+አንስጣስያን በወለደች ጊዜም በድብቅ አስጠመቀቻት::
ከሕጻንነቷ ጀምሮም ፍቅረ ክርስትና እንዲያድርባት ነገረ
ሃይማኖትን
አስተማረቻት:: ቅድስት አንስጣስያ ወጣት በሆነች ጊዜ
ግን ከውበቷ የተነሳ ተመልካቿ በዛ:: እርሷ ግን ይህ ሁሉ
የዓለም
ኮተት አይገባትም ነበር::

+በፈጣሪዋ ፍቅር ከመጠመዷ የተነሳ ለመሰል ነገሮች
ትኩረት አልነበራትም:: ትጾማለች: ትጸልያለች: ነዳያንና
እሥረኞችን
ትጐበኛለች:: በዚህም ዘወትር ደስ ይላት ነበር:: ነገር ግን
አባቷ ባላሰበችው ጊዜ ለአንድ አረማዊ አጋባት:: በጣም
አዘነች: ግን ተስፋ አልቆረጠችምና መፍትሔ ፈለገች::

+ድንግልናዋን እንዳያረክስ በጫጉላዋ ቀን ታመምኩ ብላ
ተኛች:: ከዚያ በኋላም አንዴ በልማደ አንስት: አንዴ
በሕመም
እያመካኘች አላስቀርብ አለችው:: እርሱ የጦር አለቃ
በመሆኑ ወደ ጦርነት ሲሔድ እርሷ ታጥቃ ስለ ቀናች
እምነት የታሠሩ
ክርስቲያኖችን ታገለግል ነበር::

+ቁስላቸውን እያጠበች: አንጀታቸውን በምግብ እየደገፈች
ደስ ታሰኛቸውም ነበር:: ባሏ ሲመለስ ግን ይህንን
በመስማቱ
ድጋሚ እንዳትወጣ ቆልፎባት ወደ ጦርነት ተመለሰ::
ፈጽማ ስላዘነችበትም እግዚአብሔር በጠላቶቹ እጅ
አሳልፎ ሰጠውና ሞተ::

+እርሷም ከነ ድንግልናዋ ቀሪ ሕይወቷን ስትመራ
መከራው ወደ እርሷ ደረሰ:: ተይዛ ቀርባ በአረማውያን እጅ
ብዙ
ተሰቃየች:: በዚህች ቀንም ስለ ክርስቶስ ተገድላ ክብረ
ሰማዕታትን ተቀዳጀች::

ቅዱስ አቦሊ ጻድቅ

+ቅዱሱ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ የክርስቶስን ሕማማት
ለመሳተፍ ሲተጉ ከኖሩ ጻድቃን አንዱ ነው:: መሉ ጊዜውን
በበርሃ
ሲያሳልፍ ብዙ ተጋድሎን ፈጽሟል:: በተለይ ሲጸልይ
እግሩን ከዛፍ ላይ አስሮ: ቁልቁል ከባሕር ውስጥ ሰጥሞ
ነው:: ዛሬ
ቤተ ክርስቲያን ዕረፍቱን ታስባለች::

=>አምላከ ቅዱሳን ጸጋውን: ክብሩን ያድለን:: ከወዳጆቹ
በረከትም አይለየን::

=>ታሕሳስ 26 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅድስት አንስጣስያ ሰማዕት
2.ቅዱስ አቦሊ ጻድቅ
3.ቅድሰት ዮልያና ሰማዕት

=>በ 26 የሚከበሩ ወርኀዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ
2.አቡነ ሐብተ ማርያም ጻድቅ
3.አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ
4.ቅዱሳን ሰማዕታተ ናግራን
5.ቅዱስ አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን

++"+ ለእናንተም ጠጉርን በመሸረብና ወርቅን
በማንጠልጠል ወይም ልብስን በመጐናጸፍ በውጭ የሆነ
ሽልማት አይሁንላችሁ::
ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ
የዋህና ዝግተኛ መንፈስ ያለውን የማይጠፋውን ልብስ
ለብሶ የተሰወረ
የልብ ሰው ይሁንላችሁ:: +"+ (1ዼጥ. 3:3)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
ቅድስት አንስጣስያን በድብቅ ያጠመቃት ማን ነው/ናት
Anonymous Quiz
42%
ባሏ
11%
እህቷ
30%
እናቷ
17%
አባቷ
እንኩዋን ለሰማዕቱ "አባ አብሳዲ" እና ለጻድቁ "አባ በግዑ" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ

+"+ ቅዱስ አባ አብሳዲ +"+

=>ቅዱሱን የመሰሉ አባቶች "መስተጋድላን" ይባላሉ በግእዙ:: ለሃይማኖታቸው እስከ ደም ጠብታና እስከ መጨረሻዋ ህቅታ ድረስ መጋደላቸውን የሚያሳይ ነው:: መጋደል ጐዳናው ብዙ ዓይነት ነው::

+ከራሱ ጋር የሚጋደል አለ:: ከዓለም ጋር የሚጋደልም አለ:: የቅዱሳኑ ተጋድሎ ግን በዋነኝነት ከ2 አካላት ጋር ነው:: በመጀመሪያ ፍትወታት እኩያትን (ኃጣውዕን) ከሚያመጡ አጋንንት ጋር ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ "ሃይማኖቸታችሁን ካዱ: ለጣዖትም ስገዱ" ከሚሉ ከሃድያን ጋር የሚደረግ ትግል ነው::

+በተለይ 2ኛው እስከ ሞት የሚያደርስ ውሳኔን ይጠይቃል:: የዚህን ቅዱስ ሕይወት ለመረዳት ግን አንድ ነገርን ልብ እንድትሉልኝ እፈልጋለሁ::

+ያለንበት ዘመን ክርስትና በራድ (ቀዝቃዛ) በመሆኑ የቀደሙ አባቶች የጸና ተጋድሎ አንዳንዴ ግራ ሲያጋባን ተመልክቻለሁ:: ቅዱሳኑ ሁሌም አንድ ነገርን እያሰቡ ይኖራሉ:: ይኼውም በዘመኑ በርካቶቻችን የረሳነው: ወይም ማስታወስ የማንፈልገው ነገር ይመስላል::

+ሰማያዊው አምላክ ከዙፋኑ ወርዶ በተዋሐደው ሥጋ በቃል ሊገለጽ የማይችል መከራን ስለ እኛ ተቀብሏል:: ክርስትና ማለት ቀራንዮን በልብ ውስጥ መሳል ነው:: ፍቅረ መስቀሉን: የጌታንም ውለታ የሚያስብ ማንኛውም ሰው: የትኛውም ዓይነት መከራ ቢመጣበት አይታወክም::

+ቅዱሳኑም የፍቅራቸውና የትእግስታቸው ምሥጢር ይኼው ነው:: ጌታችን "የሚወደኝ ቢኖር የሞቱን መስቀል ተሸክሞ ይከተለኝ" (ማቴ. 16:18) እንዳለው ቅዱሳኑ ይህንን ቃል በቃል ሲፈጽሙት እነሆ እንመለከታለን::

+"+ ቅዱስ አባ አብሳዲ +"+

=>ቅዱሱ ሰማዕት ተወልዶ ያደገው በምድረ ግብጽ : በ3ኛው መቶ ክ/ዘ ነው:: እንደርሱ በቅድስና ያጌጠ ባልንጀራም ነበረው:: ስሙም ቅዱስ አላኒቆስ ነበር::

+እኒህ ክርስቲያኖች በዚያ የመከራ ዘመን ግራ ቀኝ ሳይሉ ትምሕርተ ቤተ ክርስቲያንን ጠንቅቀው ተምረዋል:: በጐውን ጐዳና አጽንተው በመገኘታቸውም መንፈስ ቅዱስ 2ቱንም በአንዴ ለእረኝነት ጠራቸው::

+ዽዽስና ከዚህ በፊት እንደ ተመለከትነው እዳ (ኃላፊነት) እንጂ ምድራዊ ክብርን ማጋበሻ መንገድ: ወይም የሥጋ ድሎትን መፍጠሪያ ዙፋን አይደለም:: ያም ሆኖ ምርጫው የመንፈስ ቅዱስ ሲሆን ደስ ያሰኛል::

+በእርግጥም የክርስቶስን መንጋ እንደሚገባ መምራትና በለመለመው የወንጌል መስክ ማሰማራት የሚያስገኘው ክብር በሰማያት ታላቅ ነው:: ያም ቢሆን ግን ከብዙ መከራ በሁዋላ እንጂ እንዲሁ በዋዛ አይደለም:: የእግዚአብሔር ጸጋውና መንግስቱ ያለ መከራ አትገኝምና::

+ቅዱሳኑ አባ አብሳዲና አባ አላኒቆስም ይህንን ኃላፊነት የተረዱ ነበርና ታጥቀው ሥራቸውን ጀመሩ:: እንደ ሐዋርያት ሥርዓትም ያላመነውን ማሳመን: ያመነውን በሃይማኖቱ ማጽናት: የጸናውን ደግሞ ለምሥጢራተ ቅድሳት (ሥጋ ወደሙ) ማብቃት የዘወትር ተግባራቸው ነበር::

+ቅዱሳኑ በዚህ ተጋድሏቸው ሳሉ ዜናቸው በየቦታው ተሰማ:: ነገር ግን ይህ ዝናቸው የወለደው መከራን ነበር:: በጊዜው አውሬው ዲዮቅልጢያኖስ ክርስቲያኖችን ከዋሉበት አላሳድር: ካደሩበትም አላውል ብሎ ነበር::

+ለክፋቱ እንዲመቸው በየሃገሩ ጨካኝ መኮንኖችን ሾመ:: በምድረ ግብጽም 2 ገዢዎችን ሲያኖር አንዱ አርያኖስ (በሁዋላ አምኖ ሰማዕት ሆኗል): 2ኛው ደግሞ ሔርሜኔዎስ ይባላሉ::

+እነዚህ መኩዋንንት ግብጽን ለ2 ተካፍለው: በሥራቸው ገዥዎችን ሹመው በግፍ ተግባራቸው ክርስቲያኖችን ይቀጡ ገቡ:: የስቃይ ተራው ደግሞ የ2ቱ ቅዱሳን (አባ አብሳዲና አባ አላኒቆስ) ነበርና ተከሰሱ::

+ለፍርድ ይቀርቡ ዘንድም አርያኖስ በማዘዙ ወታደሮች መጡ:: ነገሮችን አስቀድሞ የሚያውቀው ቅዱስ አብሳዲም ምንም ስለ ክርስቶስ ለመሞት ቢቸኩልም መንጋውን እንዲሁ ሊበትን ግን አልወደደም::

+ስለዚህም ወታደሮችን "እባካችሁ ሕዝቡን ልሰናበት : አንድ ቀን ታገሱኝ" አላቸው:: ወታደሮቹ ከፊቱ የሚታየው ግርማው ደንቁዋቸው ነበርና ፈቀዱለት:: ቅዱሱም ከሕይወቱ የቀረችውን 24 ሰዓት ይጠቀምባት ዘንድ ምዕመናን ልጆቹን ሁሉ ጠራ::

+ቅዳሴ ቀድሶ : ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ፈትቶ ለሁሉም አቀበላቸው:: (በጊዜው የማይቆርብ ክርስቲያን አልነበረምና)

+ከቅዳሴ መልስም የተፈጠረውን ሁሉ ነግሮ ወደ ክርስቶስ ሊሔድ እንደ ናፈቀ ነገራቸው:: ሊያስቀሩት እንደማይችሉ ሲረዱ ፈጽመው አዘኑ:: እርሱም በቀናችው እምነት እስከ ሞት ድረስ እንዲጸኑ አስተምሯቸው ከባልንጀራው ቅዱስ አላኒቆስ ጋር በወታደሮች እጅ ወደቀ::

+እነርሱም ቅዱሳኑን ወስደው በመኮንኑ አርያኖስ ፊት ለፍርድ አቀረቧቸው:: አርያኖስም የአባ አብሳዲ የፊቱ ግርማ ቢስበው ላለመግደል ወስኖ ሊያባብለው ወሰነ:: "አንተ ክቡር ሰው ነሕና ለንጉሡ ታዘዝ : ለጣዖትንም እጠን" አለው::

+ቅዱስ አላኒቆስ ግን "ክብሬ ክርስቶስ ነውና ፈጣሪየን በምንም ነገር አልለውጠውም" ሲል እቅጩን ነገረው:: እንደማያሳምነው ሲረዳም ከአባ አላኒቆስ ጋር ያሰቃዩአቸው ዘንድ አዘዘ::

+በምስክርነት አደባባይም በመንኮራኩር (አካልን የሚበጣጥስ ተሽከርካሪ ብረት ነው) አበራዩአቸው:: እግዚአብሔር ግን አዳናቸው:: እንደ ገና እሳት አስነድደው እዚያ ውስጥ ጨመሯቸው:: እሳቱም ግን ሊበላቸው አልቻለም::

+በመጨረሻም መኮንኑ አንገታቸው ይሰየፍ ዘንድ አዘዘ:: ከመሰየፋቸው በፊትም ቅዱሳኑ ጸሎትን አደረሱ:: አባ አብሳዲ ነጭ የቅዳሴ ልብሱን ለብሶ: ወደ ሰይፍ ቀረበ:: ወታደሮች ደግሞ ሁለቱን ቅዱሳን እንደታዘዙት ሰየፏቸው:: በክብርም ዐረፉ::

+"+ አባ በግዑ ጻድቅ +"+

=>እኒህ አባት በመካከለኛው ዘመን የሃገራችን ታሪክ ሰፊ ቦታን ይዘው ይገኛሉ:: ተጋድሏቸውን የፈጸሙት በደብረ ሐይቅ ነው:: ጻድቁ ብዙ ጊዜ የሁዋለኛው ዘመን ሙሴ ጸሊም ይባላሉ:: ብዙ የሕወታቸው ጐዳና ተመሳሳይ ነው::

+ልክ ቅዱስ ሙሴ ጸሊም ከኃጢአት ከሽፍትነት ሕይወት እንደ መጣው ሁሉ አባ በግዑም አስቸጋሪ ሰው እንደ ነበሩ ይነገርላቸዋል:: ከዚያ የከፋ የኃጢአት ኑሮ እግዚአብሔር ሲጠራቸው ግን ክሳደ ልቡናቸውን አላደነደኑም:: "እሺ" ብለው ንስሃ ገቡ እንጂ::

+ከዚያም በደብረ ሐይቅ (ወሎ) በፍጹም ተጋድሎ ኑረዋል:: ያዩ ሁሉም ፍጹም ያደንቁ ነበር:: ስትበላ: ስትጠጣ የኖረችውን ሰውነት ራሳቸውን ውሃ ለዘመናት በመከልከል ቀጥተዋታል:: ስለዚህም "ውሃ የማይጠጣው አባት" ይባሉም ነበር:: ጻድቁ ሲያርፉ ፈጣሪያቸው አክብሯቸዋል::

=>አምላከ አበው ቅዱሳን አሠረ ፍኖታቸውን ይግለጽልን:: ከበረከታቸውም ያድለን::

=>ታሕሳስ 27 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ አብሳዲ ሰማዕት
2.አባ አላኒቆስ ሰማዕት
3.አባ በግዑ ጻድቅ
4.አባ ፊልዾስ

=>ወርኀዊ በዓላት
1.ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ
2.አቡነ መብዓ ጽዮን ጻድቅ
3.ቅዱስ መቃርስ (የመነኮሳት ሁሉ አለቃ)
4.ቅዱስ ያዕቆብ ዘግሙድ
5.ቅዱስ ገላውዴዎስ ሰማዕት (ንጉሠ ኢትዮዽያ)
6.ቅዱስ ቢፋሞን ጻድቅና ሰማዕት
7.ማር ቅዱስ ፊቅጦር ሰማዕት
=>+"+ መቶ በግ ያለው ከእነርሱም አንዱ ቢጠፋ ዘጠና ዘጠኙን በበርሃ ትቶ የጠፋውን እስኪያገኘው ድረስ ሊፈልገው የማይሔድ ከእናንተ ማን ነው? ባገኘውም ጊዜ ደስ ብሎት በጫንቃው ይሸከመዋል:: ወደ ቤትም በመጣ ጊዜ ወዳጆቹንና ጐረቤቶቹን በአንድነት ጠርቶ 'የጠፋውን በጌን አግኝቼዋለሁና ከእኔ ጋር ደስ ይበላችሁ' ይላቸዋል:: እላችሁአለሁ: እንዲሁ ንስሃ ከማያስፈልጋቸው ከዘጠና ዘጠኝ ጻድቃን ይልቅ ንስሃ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በሰማይ ደስታ ይሆናል:: +"+ (ሉቃ. 15:3-7)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
https://www.tg-me.com/zikirekdusn
#ሰማዕት ሊሆኑ ከመሄዳቸው በፊት ምእመኑን #ያቆረቡ አባት
Anonymous Quiz
21%
#አባ_በግዑ
33%
#አባ_አላኒቆስ
18%
#አባ_አብሳዲ
29%
ለ እና ሐ
ከተጋድሎ ብዛት #የጌታችንን_ሥጋ_ና_ደም ለመቀበል በቃሬዛ የወሰዱት #ቅዱስ_አባት
Anonymous Quiz
32%
#አባ_በግዑ
37%
#አባ_ይሥሐቅ
22%
#አባ_አብሳዲ
9%
#አባ_አላኒቆስ
2024/11/15 17:38:07
Back to Top
HTML Embed Code: