Telegram Web Link
††† እንኳን ለቅዱስ እንድርያስ ሐዋርያ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱስ እንድርያስ ሐዋርያ †††

††† ቅዱሱ ሐዋርያ ተወልዶ ያደገው በቤተ ሳይዳ አካባቢ ሲሆን የሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ ትንሽ ወንድም ነው:: አባቱም ዮና ይባላል:: ገና ከልጅነቱ ጀምሮ አሣ ማጥመድን ከትልቅ ወንድሙ ተምሯል:: እድሜው ከፍ ባለ ጊዜ ኦሪትን ተምሮ የመጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ ደቀ መዝሙር ሆኗል::

ከእርሱም እያገለገለ ለ6 ወራት ተምሯል:: በወቅቱ ከወንጌላዊው (ወልደ ዘብዴዎስ) ዮሐንስ ጋር ቅርብ ባልንጀራም ነበር:: ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተጠመቀ ጊዜ ያን ድንቅ ምሥጢረ ሥላሴ ከተመለከቱትም አንዱ ነው::

ጌታ ከጾም (ከገዳመ ቆረንቶስ) በተመለሰ ጊዜ እንድርያስ መንፈስ ቅዱስ አነሳስቶት ተከትሎታል:: መጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ "ነዋ በግዑ ለእግዚአብሔር ዘያዐትት ኃጢአተ ዓለም - የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ እነሆ" ማለቱን ሰምቶ ቅዱስ እንድርያስ ጌታን ተከተለ::

በዚህም የመጀመሪያው የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ለመባል በቃ:: (ዮሐ. 1:47) ሊቁ ማር ገላውዴዎስም እመቤታችንን ሲያመሰግናት:-
"ለሐዋርያ እንድርያስ ቀዳማዊ ማርያም ሃይማኖቱ::
(ለመጀመሪያው ሐዋርያ ለእንድርያስ ሃይማኖቱ ማርያም አንቺ ነሽ)" ብሏል:: (መልክዐ ስዕል)

ቅዱሱ ሐዋርያ ስሉጥ (ፈጣን) አገልጋይ እንደ ነበርም ወንጌል ይነግረናል:: (ዮሐ. 6:9, 12:22) ለ3 ዓመታት ከ3 ወራት ከጌታ እግር ሥር ተምሮ: በበዓለ ሃምሳ መንፈስ ቅዱስን ተቀበሎ ምን ሃገረ ስብከቱ ልዳ ብትሆን ብዙ አሕጉረ ዓለምን ሰብኳል::

ሐዋርያው ከጌታ ጋር በመርከብ ውስጥ ተነጋገረና ቅዱስ ማትያስን ሰውን ከሚበሉ ሰዎች እጅ አዳነ:: ቅዱስ እንድርያስ 30 ቀናት የሚፈጅ የባሕር ላይ ጉዞ ለማድረግ ከአርድእቱ ጋር ወደ ወደብ ቢሔድም መርከበኞች ሁሉ አናሳፍርም በማለታቸው የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወጣት መርከበኛ መስሎ ሐዋርያውንና አርድእቱን የሠላሳውን ቀን መንገድ በሰዓታት ልዩነት እንዲጨርሱ አድርጓል::

ቅዱስ እንድርያስም እንዲሁ ሰው መስሎት ለጌታችን ስለ ጌታችን ሰብኮለታል:: መርቆታልም:: መርከበኛው ጌታችን መሆኑን ሲያውቅም ደንግጦ አልቅሷል::

¤"ሶበ አእመረ ኪያሁ ወጠየቀ አምሳሎ::
ዘተናገርኩ በድፍረት ምስሌከ ኩሎ::
ሥረይ ሊተ ጌጋይየ ወኅድግ ይቤሎ::" እንዲል "ማረኝ?" ብሎታል:: ጌታችንም "አይዞህ እኔ ካንተ ጋር ነኝ" ብሎታል::

እንድርያስ ማለት "ተባዕ" (ደፋር: ብርቱ) ማለት ነው:: ድፍረት ሥጋዊ: ድፍረት መንፈሳዊ አለና:: "ድፍረት ሥጋዊ" በራስ ተመክቶ ሌሎችን ማጥቃት: ለጥቃትም ምላሽ መስጠት ነው::

"ድፍረት መንፈሳዊ" ስለ ክርስቶስ: ስለ ቀናችው ሃይማኖት ሲሉ በራስ ላይ መጨከን: ራስን አሳልፎ መስጠት: መከራንም አለመሰቀቅ ነው:: ይሕንንም አበው "ጥብዓት" ይሉታል::

ቅዱስ እንድርያስም ለጊዜው በቤተ እሥራኤል መካከል ደፋር የነበረ ሲሆን ለፍጻሜው ግን እስከ ሞት ደርሶ ስመ ክርስቶስን በድፍረት ገልጧልና "ተባዕ (ደፋር)" ይለዋል::
"ዘኢያፍርሃከ ምንተ መልአከ ዓመጻ ጽኑዕ::
አንተኑ እንድርያስ ተባዕ" እንዲል:: (መልክዐ ዓቢየ እግዚእ)

የቅዱስ እንድርያስ ሃገረ ስብከቱ ልዳ (ልድያ) ናት:: ይህቺን ሃገር: አስቀድሞ ሊቀ ሐዋርያቱ (ትልቅ ወንድሙ) ቅዱስ ጴጥሮስ አስተምሮባታል:: ቅዱስ ጴጥሮስ ወደ ሮም ሲዘልቅ ቅዱስ እንድርያስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ገብቶ ብዙ ደክሞባታል::

በቀደመው ዘመን ልዳ እንደ ዛሬው ትንሽ ሃገር አልነበረችም:: ቅዱሱ ሐዋርያ ወደ ቦታው ገብቶ: ስመ ክርስቶስን ሰብኮ ብዙዎችን ቢያሳምንም የጣዖቱ ካህናት ግን ተበሳጩ:: በእርግጥ እነርሱ የሚያጥኗቸው ድንጋዮች አማልክት እንዳልሆኑ ጠንቅቀው ያውቃሉ::

ነገር ግን ከብረው: ገነው: ባለ ጠጐችም ሆነው የሚኖሩበት ሐሰት እንዲገለጥ አይፈልጉምና እውነትን ከመቀበል ሐዋርያቱን ማሳደዱን ይመርጡ ነበር:: አሁንም የልዳ ከተማ ሕዝብ ማመናቸውን ሲሰሙ በቁጣ ሠራዊት ሰብስበው: ጦርና ጋሻን አስታጥቀው: ሐዋርያውን ያጠፉ ዘንድ እየተመሙ መጡ::

ቅዱስ እንድርያስ ይህንን ሲያውቅ ከደቀ መዛሙርቱ መካከል "ጥዑመ-ቃል" የሚባለውን ቅዱስ ፊልሞናን (ኅዳር 27 ቀን ያከበርነውን ማለት ነው) ጠርቶ የቅዱስ ዳዊትን መዝሙር ገልጦ ምዕራፍ (113:12) ላይ ሰጠውና "ጮክ ብለህ አንብብ" አለው::

††† ቅዱስ ፊልሞናም በቅዱስ መንፈሱ ተቃኝቶ ያነብ ጀመር::
"አማልክቲሆሙ ለአሕዛብ ዘወርቅ ወዘብሩር::
ዓይን ቦሙ ወኢይሬእዩ::
እዝን ቦሙ ወኢይሰምዑ::
አንፍ ቦሙ ወኢያጼንዉ . . .
የአሕዛብ አማልክት ከወርቅና ከብር የተሠሩ ናቸው::
ዓይን አላቸው: ግን አያዩም::
ጆሮ አላቸው: ግን አይሰሙም::
አፍንጫ አላቸው: ግን አያሸቱም . . ." አለ::

በፍጻሜውም "ከማሁ ለይኩኑ ኩሎሙ እለ ገብርዎሙ / የሚሰሯቸው ሁሉ እንደ እነርሱ ይሁኑ" ብሎ ጸጥ አለ:: ይህንን የሰሙት ካህናተ ጣዖትና ሠራዊታቸው የልባቸው መታጠቂያ ተፈታ:: በደቂቃዎችም የመንፈስ ቅዱስ ምርኮኛ ሆነው በቅዱስ እንድርያስ ፊት ሰገዱ::

እርሱም አጥምቆ ወደ ምዕመናን ማኅበር ቀላቀላቸው:: አንድ ጊዜ ደግሞ ከልዳ አውራጃዎች በአንዱ እንዲህ ሆነ:: በጨዋታ ላይ ሳሉ የክርስቲያኑ ልጅ የአሕዛቡን ቢገፈትረው ወድቆ ሞተ::

የሟቹ አባትም የገዳዩን አባት ዮሐንስን (ቀሲስ ነው) "ልጅህን በፈንታው እገድለዋለሁ" አለው:: ቀሲስ ዮሐንስ ግን "ለመምሕሬ ለእንድርያስ እስክነግር ድረስ ታገሠኝ" ብሎ ሒዶ ለሐዋርያው ነገረው::

በወቅቱ ቅዱስ እንድርያስ የወንጌል አገልግሎት ላይ ስለ ነበር ቅዱስ ፊልሞናን ላከው:: ፊልሞና ወደ አካባቢው ሲደርስ ሁከት ተነስቶ አገረ ገዢው ሕዝቡን ይደበድብ ነበርና ቀርቦ ገሠጸው:: "የተሾምከው ሕዝቡን ልታስተዳድርና ልትጠብቅ ነው እንጂ ልታሰቃይ አይደለም" ስላለው አገረ ገዥው ቅዱሱን አሰቀለው::

ተሰቅሎም ሳለ ይገርፉት ነበርና አለቀሰ:: ምክንያቱም ቅዱስ ፊልሞና ሕጻን ነበርና:: በዚህ ጊዜ ሕዝቡ ሲያለቅሱለት ቁራ: ወፍና ርግብ ቀርበው አጽናኑት:: ከእነርሱም መርጦ ርግብን ወደ ቅዱስ እንድርያስ ላካት::

ርግብ በሰው ልሳን ስትናገር የሰማት አገረ ገዢው ተገርሞ ቅዱሱን ከተሰቀለበት አወረደው:: ሰይጣን ግን በብስጭት በመኮንኑ ሚስት አድሮ ልጁን አስገደለበት:: በሃዘን ላይ ሳሉም ቅዱስ እንድርያስ ደረሰ::

በመኮንኑ ሚስት ያደረውን ሰይጣንን ወደ ጥልቁ አስጥሞ የሞተውን አስነሳው:: መጀመሪያ የሞተውን ሕጻን ደግሞ ፊልሞና አስነሳው:: በእነዚህ ተአምራትም መኮንኑ: ሕዝቡና ሠራዊቱ በክርስቶስ አምነው ተጠመቁ::

ቅዱስ እንድርያስ በእድሜው የመጨረሻ ዘመናት ከልድያ ወጥቶ በብዙ አሕጉራት አስተማረ:: ስሟ ባልተጠቀሰ አንዲት ሃገር ውስጥ ግን በእሳት ሊያቃጥሉት ሲሉ እሳት ከሰማይ ወርዳ በላቻቸው::

ድጋሚ ሌሎች ይዘው አሰሩት: ደበደቡት አሰቃዩት:: በሌሊትም ጌታ መጥቶ አጽናናው:: ታኅሣሥ 4 ቀን በሆነ ጊዜም ወደ ውጭ አውጥተው: ወግረውና ሰቅለው ገድለውታል::
¤እኛም እንደ አባቶቻችን:-
"እዜምር ለከ ወእየብብ በሃሌ ሉያ::
አንቅሃኒ እምሐኬትየ እንድርያስ ሐዋርያ::
ከመ በእዴከ ነቅሐት እሙታን ልድያ::" እያልን ቅዱሱን እንጠራዋለን:: (አርኬ ዘታኅሣሥ 4)††† አምላከ ቅዱስ እንድርያስ ከሞተ ልቡና አንቅቶ ለክብሩ ያድርሰን:: ከበረከቱም ያድለን::

††† ታኅሣሥ 4 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ እንድርያስ ሐዋርያ
2.አባ ጻዕ
3.አባ ያዕቆብ
4.ቅድስት ታኦድራ

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ
2.ቅድስት ሶፍያ ሰማዕት
3.ቅዱስ ዮሐንስ ዘሐራቅሊ (ሰማዕት)

††† "ሁለቱም ደቀ መዛሙርት ሲናገር ሰምተው ጌታ ኢየሱስን ተከተሉት:: ጌታ ኢየሱስም ዘወር ብሎ: ሲከተሉትም አይቶ:- "ምን ትፈልጋላችሁ?" አላቸው:: እነርሱም:- "ረቢ ወዴት ትኖራለህ?" አሉት:: ትርጓሜው "መምህር ሆይ!" ማለት ነው:: "መጥታችሁ እዩ" አላቸው:: መጥተው የሚኖርበትን አዩ:: በዚያም ቀን በእርሱ ዘንድ ዋሉ:: አሥር ሰዓት ያህል ነበረ:: ከዮሐንስ ዘንድ ሰምተው ከተከተሉት ከሁለቱ አንዱ የስምዖን ጴጥሮስ ወንድም እንድርያስ ነበረ::" †††
(ዮሐ. ፩፥፴፯-፵፩)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
https://www.tg-me.com/zikirekdusn
''' እንኩዋን ለቅዱሳን *አቡነ ኪሮስ *ዮሐንስ ዘደማስቆ *ሳሙኤል ዘቀልሞን *ተክለ አልፋ *ኤሲ *በርባራ *እንባ መሪና እና *ገብረ ማርያም ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ! '''

=>ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በዚሁ ቀን የምታከብራቸው ብዙ ቅዱሳን አሏት:: ሁሉን ለመዘርዘር ይከብዳል:: ግን የጥቂቱን ዜና ለበረከት እንካፈል ዘንድ የጌታ ፈቃዱ ይሁንና ስለ እያንዳንዱ በጥቂቱ እናንሳ::

+*" አቡነ ኪሮስ ጻድቅ "*+

=>የጻድቁን ስም የሚጠራ አፍ ንዑድ ነው: ክቡር ነው:: በእውነት የቅዱሱን አባት ክብር ለማግኘት መፋጠን ይበጃል:: አቡነ ኪሮስ የተወለዱት በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን ሲሆን ወላጆቻቸው ነገሥታት ናቸው::

+ተወልደው ባደጉባት ሃገር ቁስጥንጥንያ ገና በልጅነት ምቾት ሳያሳሳቸው መጻሕፍትንና ትሕርምትን ተምረዋል:: ወንድማቸው (ታላቁ ቴዎዶስዮስ) በነገሠባቸው የመጀመሪያ ዓመታት በቤተ መንግስቱ ዙሪያ ግፍ በዝቶ ነበርና አቡነ ኪሮስ ከኃጢአት ለመራቅና ለጌታ ለመገዛት ከከተማው ጠፍተው: አሕጉር አቁዋርጠው ወደ ግብፅ (ገዳመ አስቄጥስ) መጡ::

+እርሳቸውን ለመፈለግ የተደረገው ሙከራ አልተሳካም:: ይባስ ብሎ የንጉሡ ልጅ ገብረ ክርስቶስ ሙሽርነቱን ጥሎ ወደ ሌላ ሃገር መነነ:: "የቅኖች ትውልድ ይባረካል" እንዳለ ቅዱስ ዳዊት አቡነ ኪሮስ ለሙሽራው ገብረ ክርስቶስ አጎቱ ናቸው:: አቡነ ኪሮስ በገዳም ውስጥ የታላቁ አቡነ በብኑዳ ደቀ መዝሙር ሆነው ለዘመናት ቆይተዋል::

+ቅዱስ በብኑዳን አንበሳ በበላው ጊዜ በጣም አዝነው "ለምን ጌታ ሆይ?" በሚል መሬት ላይ ወድቀው አለቀሱ:: "ምክንያቱ ካልተነገረኝ አልነሳም" ብለው ከወደቁበት መሬት ላይ ሳይነሱ ለ40 ዓመታት አልቅሰዋል:: በዚህ ምክንያት ግማሹ አካላቸው አፈር ሆኖ ሣር በቅሎበታል::
ጌታችን ተገልጦ ምክንያቱን ነግሯቸዋል:: አካላቸውንም እንደነበረ መልሶላቸዋል::

+አንድ ቀን ጻድቁ ለቅዱስ በብኑዳ ሞት ምክንያት የሆነው መነኮስ ታንቆ መሞቱን ሰምተው በጣም አዘኑ:: ሱባዔ ገብተው: ፍጹም አልቅሰው: ከጌታም አማልደው: የዛን ኃጥእ ነፍስ ከሲዖል አውጥተዋል:: በሌላ ጊዜ ደግሞ ኃጥአን የሞሉበት አንድ ገዳም በግብጽ ነበርና መቅሰፍት ወርዶ ሁሉንም ባንድ ቀን ሲያጠፋቸው አዩ::

+ጻድቁ በዚህም ምክንያት ለ30 ዓመታት አልቅሰው: ሙታኑን አስነስተው: ንስሃ ሰጥተው: ገዳሙን የጻድቃን: ሕይወታቸውንም የፍቅር አድርገውታል:: ጻድቁ እመቤታችንን ከመውደዳቸው የተነሳ በስዕሏ ፊት አብዝተው ይሰግዱና ያለቅሱ ነበር:: እመ አምላክም ተገልጣ ትባርካቸው ነበር::

+ከዚህ በሁዋላ ወደ ምዕራብ አቅጣጫ ሒደው ለ57 ዓመታት ማንንም ሳያዩ ተጋደሉ:: ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ (ለስም አጠራሩ ስግደት ይሁንና) በየቀኑ ይጐበኛቸው: ቁጭ ብሎም ያወራቸው ነበር::

+በመጨረሻም ጌታ አእላፍ መላእክትን: ጻድቃን ሰማዕታትን: ድንግል እመቤታችንና ቅዱስ ዳዊትን አስከትሎ ወረደ::

+ቅዱስ ዳዊት ቀርቦ እያጫወታቸው: በበገናው እየደረደረላቸው: ከዝማሬው ጣዕም የተነሳ ነፍሳቸው ከሥጋቸው በፍቅር ተለየች:: ጌታችንም ታቅፎ: ስሞ ይዟቸው አረገ::

+ሥጋቸውን አባ ባውማ ቀበሩት:: የአቡነ ኪሮስ ቁመታቸው ቀጥ ያለ: ጽሕማቸውም የተንዠረገገ ነበር:: እድሜአቸውን ግን መገመት የሚቻል አይመስለኝም:: (ጻድቁ የተወለዱት በዚሁ ቀን ነው)

+*" አባ ሳሙኤል ዘቀልሞን "*+

=>በ5ኛው መቶ ክ/ዘመን በግብጽ ደብረ ቀልሞን የነበሩ:
*ከዓበይት ጻድቃን የሚቆጠሩ:
*ቀውስጦስ የሚባለውን መልአክ አማልደው ክንፈ ረድኤቱ እንዲመለስ ያደረጉ::
*መልአክን እንኩዋ ማማለድ የቻሉ::

*የታላቁ አባ አጋቶን ደቀ መዝሙር የሆኑ:
*ስለ ቀናች ሃይማኖት የተደበደቡ:
*መናፍቃን አንድ ዐይናቸውን ያጠፉባቸው:
*በፍጹም ትሕርምት የኖሩ:
*እልፍ ደቀ መዛሙርትን ያፈሩ::

*ተአምራትን የሠሩ:
*ደብረ ቀልሞን ገዳምን የመሠረቱና
*እመቤታችንን በፍጹም ልባቸው የወደዱ ቅዱስ አባት ናቸው:: (ዛሬ ዕረፍታቸው ነው)

+*" ቅዱስ ዮሐንስ ዘደማስቆ "*+

=>በ6ኛው መቶ ክ/ዘመን በሶርያ ደማስቆ የተነሳ:
*ፍልስፍናንም: ትምሕርተ ቤተ ክርስቲያንንም ያጠና:
*ስለ ስዕለ አድኅኖ ክብር ከነገሥታቱ ዘንድ የተዋጋ:
*በጦማር (በደብዳቤ) ለዓለም የሰበከ:
*ስለ እመቤታችን ተናገርክ ብለው ቀኝ እጁን የቆረጡት::

*እመ ብርሃን ግን እንደ ገና የቀጠለችለት:
*በበርሃ ውስጥ ለዘመናት በገድልና በጽሙና የኖረ:
*ከ10ሺ በላይ ድርሳናትን የደረሰ:
*ከዐበይት ሊቃውንት የሚቆጠር ቅዱስ አባት ነው:: (ዛሬ ዕረፍቱ ነው)

+*" ቅድስት በርባራ "*+

=>በዘመነ ሰማዕታት (በ3ኛው ክ/ዘ) የነበረች:
*በአረማዊ ንጉሥ አባቷ ጣዖት እንድታመልክ ብትገደድ "እንቢ" ያለች:
*ከባልንጀራዋ ዮልያና ጋር በፍጹም ትእግስት የታገለች:

*የአባቷን ምድራዊ ክብር ንቃ ስለ ክርስቶስ መከራን የተቀበለች:
*በአባቷ እጅ ከቅድስት ዮልያና ጋር የተገደለች:
*እጅግ ብዙ ተአምራትንም የሠራች ቅድስት: ወጣት ሰማዕት ናት:: (ዛሬ ዕረፍቷ ነው)

+" አባ ኤሲ "+

=>በዘመነ ሰማዕታት በግብጽ (ቡጺር) ከደጋግ ክርስቲያኖች የተወለደ:
*ከልጅነቱ ጀምሮ ዓለምን የናቀ:
*በወጣትነቱ የነዳያንና የእሥረኞች አባት የተባለ:
*ቅድስት ቴክላ የተባለችና እመቤታችን የምታነጋግራት እህት የነበረችው:

*ቅዱስ ዻውሎስ ከሚባል ባልንጀራው ጋር ሰማዕታትን በመንከባከብ ያገለገለ:
*በመንፈሳዊ ቅናት ከዻውሎስና ቴክላ ጋር ለሰማዕትነት የቀረበ::

*እጅግ ብዙ መከራዎቸን የተቀበለ::

*ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሱርያል ወደ ሰማይ አሳርጐ ክብረ ቅዱሳንን ያሳየው::

*ቅዱሳንን የሚዘክሩ ሰዎችን ክብር አይቶ የተደነቀና::
*ከብዙ ተከታዮቹና ቅድስት እህቱ ጋር የተሰየፈ ታላቅ ሰማዕት ነው:: (ዛሬ ዕረፍቱ ነው)

+*" ቅድስት እንባ መሪና "*+

=>በዘመነ ጻድቃን በምድረ ግብጽ የተወለደች::

*ከአባቷ ጋር መንና ወደ ወንዶች ገዳም የገባች::

*ወንድ መስላ የወንዶችን ቀኖና በምንኩስና የተቀበለች::

*ያለ አበሳዋ (ወንድ መስላቸው) "ዝሙት ሰርተሻል" ተብላ ወደ በርሃ የተባረረች::

*ያልወለደችውን ልጅ ያሳደገች::

*ያለ ምግብና ውሃ ለ3 ዓመታት የተሰቃየች::

*ብርድና ፀሐይ የተፈራረቀባትና:

*ስታርፍ ክብሯ የተገለጠላት ቡርክት እናት ናት:: (ዛሬ ልደቷ ነው)

+*" አቡነ ተክለ አልፋ "*+

=>በ14ኛው መቶ ክ/ዘመን በኢትዮዽያ የተነሱ::

*ደብረ ድማሕን / ዲማን (ጎጃም) የመሠረቱ::

*በፍጹም ተጋድሎ የኖሩ::

*ምድረ ጎጃምን በስብከተ ወንጌል ያበሩ::

*በሊቅነታቸው የተመሠከረላቸው::

*መልክአ ኢየሱስን እንደ ደረሱ የሚነገርላቸው::

*ብዙ ተአምራትን የሠሩ (ዛሬም ድረስ የሚሠሩ)::

*የሃገራችን ትምክህት የሆኑ ታላቅ ሐዋርያዊ አባት ናቸው:: (ዛሬ ዕረፍታቸው ነው)

+*" ቅዱስ ገብረ ማርያም "*+

=>በ16ኛው መቶ ክ/ዘ በምድረ ኢትዮዽያ የተወለደ::
*ስም አጠራሩ ያማረ:
*ዛሬ እናንተና እኔ ለምናደርገው የቅዱሳን መታሰቢያ መሠረት የጣለ
*በዓመቱ የሚከበሩ ሁሉን ቅዱሳን የሚዘክር

*365ቱን ቀናት በምጽዋት የተጠመደ:
*የነዳያን አባት የሆነ:
*በአፄ ልብነ ድንግል ግራኝ አህመድ መምጣቱን ሲሰማ ያልደነገጠ:
*ሃብት ንብረቱን ለነዳያን አካፍሎ: ነጭ ልብስ ለብሶ ገዳዮቹን የጠበቀ::

*እንዲያ እንዳማረበት የግራኝ ወታደሮች የሰየፉትና ሞገስ የሆነን አባት ነው:: (ዛሬ ዕረፍቱ ነው)
=>እነዚህንና ስማቸውን ያልጠራናቸውን ሌሎች ቅዱሳንን ዜና ማንበብ: በስማቸው መልካሙን ማድረግና መዘከር ዋጋው በሰማያት ታላቅ መሆኑን ገድለ አባ ኤሲ እና ታላቁ ቅዱስ መጽሐፍ ይናገራል:: (ማቴ. 10:41, ዮሐ. 4:36, ዕብ. 6:10)

=>አምላከ ከዋክብት ቅዱሳን ከዓመጸኛው ትውልድ ይሰውረን:: በረድኤታቸው ጥላ ጋርዶ: ለበረከታቸው ያብቃን::

=>ታሕሳስ 8 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ታላቁ አቡነ ኪሮስ
2.አባ ሳሙኤል ዘደብረ ቀልሞን
3.አባ ዮሐንስ ዘደማስቆ (ሊቁ)
4.አባ ኤሲና ቅድስት ቴክላ
5.ቅዱሳት በርባራና ዮልያና
6.ቅድስት እንባ መሪና
7.አባ ተክለ አልፋ ዘደብረ ድማሕ
8.ቅዱስ ገብረ ማርያም ተአማኒ
9.አባ ያሮክላ ሊቀ ዻዻሳት
10.አቡነ እስትፋሰ ክርስቶስ (ልደታቸው)

=>ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ሙሴ ሊቀ ነቢያት
2.አባ ብሶይ (ቢሾይ)
3.ቅዱሳን 4ቱ እንስሳ (ኪሩቤል)
4.ቅዱስ ማትያስ ሐዋርያ (ከ12ቱ ሐዋርያት)

=>+"+ እግዚአብሔር ቅዱሳንን ስላገለገላችሁ: እስከ አሁንም ስለምታገለግሏቸው ያደረጋችሁትን ሥራ: ለስሙም ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዓመጸኛ አይደለምና:: በእምነትና በትእግስትም የተስፋውን ቃል የሚወርሱትን እንድትመስሉ እንጂ ዳተኞች እንዳትሆኑ ተስፋ እስኪሞላ ድረስ እያንዳንዳችሁ ያን ትጋት እስከ መጨረሻ እንድታሳዩ እንመኛለን::+"+ (ዕብ. 6:10)

<ወስብሐት ለእግዚአብሔር>

https://www.tg-me.com/zikirekdusn
2024/10/01 22:40:50
Back to Top
HTML Embed Code: