Telegram Web Link
#መሸነፍ

በህይወታችሁ ውስጥ አንዳንድ ደግ ሰዎች በደግነታቸው አሸነፈዋችሁ አያውቁም? ወይም ፍቅራቸው ከምትጠብቁት በላይ ሆኖ ተሸንፋችሁ ታውቁ ይሆን? በህይወታችሁ እንዲገቡ የማትፈልጓቸውን ሰዎች እንኳን በቅንነታቸው እና ከሚያሳዩአችሁ ፍቅር የተነሳ ተሸንፋችሁላቸው ታውቁ እንደሆን?

በበትር ያሸነፋችሁት ሰው ቀን ጠብቆ እርሱም በበትር ወይም በጉልበት እናንተን ማሸነፉ አይቀርም በመሃላችሁም የሚኖር በጎ ነገር አይኖርም። በፍቅር የረታችሁት ሰው ግን ወዳጅ ይሆናችኋል እርሱንም ገንዘብ ታደርጉታላችሁ። ላሳያችሁት ፍቅር ምላሽ እየሰጠ ቋሚ ቤተሰብ እንዲሆን ታደርጉታላችሁ።

አንዳንዴ ገጥሟችሁ ያውቃል ለሰው ፍቅር መሸነፍ ሲያቅታችሁ ሰው ተቆጥቷችሁ ለምን ትጠላዋለሁ እርሱ እኮ ይወድሃል ተብላችሁ ታውቆ እንደሆን? አንዳንዶቻችን እንዲው አይመቸኝም የምንለው ብሂል ደግሞ አለችን። ምንም አርጎኝ እኮ አይደለም በድሎኝም አይደለም ግን እንዲህ ሳየው ደስ አይለኝም፣ እንዲው አይመቸኝም ስንል እንሰማለን።

በእንከን ለተሞላው ለሰው ፍቅር ለመሸነፍ አቅማምተን እና አመንትተን ይሆናል። ባለመሸነፋችን እንደየ ምልከታችን እና እንደየ አስተሳሰባችን ልክም ልንሆን ወይም ልንስት እንችላለን። ለሰዎች ፍቅር ባለመሸነፋችን ያጣናቸው እልፍ ጥቅሞች እና ሰዎች ይኖሩ ይሆናል። ነገር ግን የእግዚአብሔር ፍቅር ልቡን ያልረታው ሰው ለምንም አይሸነፍም።

ይህንን ትክክል የሆነውን ፍቅር እምቢ ማለት እና አልሸነፍልህም ማለት እንዴት ያለ ዕድለቢስነት ይሆን? ታላቅ የሆነው እና ምንም ህጸጽ የሌለበት የእግዚአብሔር ፍቅር የማይረታን ከሆነ የትኛውስ የፍጡር ፍቅር ሊረታን? በሰዎች ፍቅር ውስጥ ክፍተት ሰለመኖሩ የሚያሻማ አይደለም ለዛ ነው ህያው የሆነውን የእግዚአብሔርን ፍቅር እምቢ ማለት የከፋ ህመም ነው የምንለው።

ምክንያቱም እግዚአብሔር የወደደን ምንም ውለታ ስለዋልንለት አይደለም ወይም ስላመነውም አይደለም ወይም የተቀመጠ መስፈርት ኖሮ አልፈን አይደለም። እንዲው የሆነውን ይሄን ፍቅር እምቢ ማለት እንዴት ይቻል ይሆን? እንዲው ወዶን፣ በነጻ አፍቅሮን፣ ያለመስፈርት ቀርቦን ይሄን ወዳጅነት መግፋት ለራስ ጉዳት መስራት ነው።

የእግዚአብሔር የፍቅሩ ማብራሪያ በቀራንዮ አንድ ልጁን ኢየሱስን መስቀል ላይ በማዋል ተተንትኖ፣ ከቋንቋ በሚሻገር መናገር ፍቅር ተስርቶልን፣ ከቃላት ባለፈ ያሁሉ ግርፋት ፍቅሩን አሳይቶን፣ የላቀው ያ ፍቅር ለእኛ ሆኖ ሳለ ይሄ እኔን አይመለከትም ብሎ ለዚህ ፍቅር ጀርባ መስጠት እንዴት ያለ ክህደት ይሆን?

ይሄንንስ ፍቅር በሌላ ፍቅር መተካት፣ ለእግዚአብሔር ለመገዛት በተገባ መገዛት ለሌላ መገዛትስ እንደምን ያለ ጠዖተ አምላኮ ይሆን? መሸነፍ ማሸነፍ የሚሆነው ለዚህ ፍቅር መሸነፍ ስንችል ነው። ለሰው ለሆነው መውደድ ልባችን እሺ ብሎ ለእግዚአብሔር ፍቅር ግን አልመረታት ካለብን የፍቅር ትርጉም አረዳዳችን ላይ ትልቅ ክፍተት አለብን ማለት ነው።

የእግዚአብሔር ፍቅሩ ከራሱ የሚመነጭ፣ ከእኛ በሆነ በየትኛውም በጎነታችን ላይ መሰረት ያላደረገ በመሆኑ ጥቅምን መስረት አድርጎ ከሚመጣው ከሰው ፍቅር በእጅጉ የተለየ እና ንጽጽር ውስጥ የማይገባ ነው። መወደድ ሳይገባን ተወደናል፣ መፈቀርም ሳይገባን ተፈቅረናል፣ የማይገባን ብዙ ነገር ተደርጎልናል ይህን መተው ውለታን መብላት ነው።

ይህ ፍቅር ካልረታን የትኛውስ ፍቅር ሊረታን? የቱስ እንክብካቤ ሊያሸንፈን? የቱ በጎነት ልባችንን ሊይዝ? የቱስ መውደድ ከዚህ ፍቅር ጋር ይደረደራል? የቱስ ፍቅር ከዚህ ፍቅር ይልቅ ጎልቶ ታይቶ ህጸጽ አልባ ይሆናል?... የሄ ፍቅር የበላይ ነው፣ ሁሉን ፍቅር በስሩ የሚያይ፣ የፍቅር ልኬቱ እና ቱምቢው ይሄ የእግዚአብሔር ፍቅር ነው።

ከዚህ ፍቅር መጉደል የጉድለት ዋና ነውና ለዚህ ፍቅር በመሸነፍ ውስጥ ያለውን ድል ማጣጣም ሲገባን ለዚህ ፍቅር ደርባ ስንሰጥ እንዳንገኝ አምላክ ማስተዋሉን ያድለን። አሜን

ዲያቆን ተስፋ መሠረት
📆 መስከረም 7 2017 ዓ.ም ተጻፈ

  🇯 🇴 🇮 🇳    ♻️  🇸 🇭 🇦 🇷 🇪

⍟⎓⎓⎓⎓⎓⎓⎓⎓⍟⎓⎓⎓⎓⎓⎓⎓⎓⍟
  ✥     @AtronoseZetewahdo      ✥
  ✥     @AtronoseZetewahdo      ✥
⍟⎓⎓⎓⎓⎓⎓⎓⎓⍟⎓⎓⎓⎓⎓⎓⎓⎓⍟
"አንተ ሐሳብህን ልትመራዉ እንጂ፤ ሐሳብህ አንተን ሊመራ ቦታ አትስጠዉ፥ እዉነተኛ ክርስቲያን ስሜቱ የሚመራዉ ሳይሆን ስሜቱን የሚመራ ነዉ።"

አቡነ ሸኖዳ ሣልሳዊ


  🇯 🇴 🇮 🇳    ♻️  🇸 🇭 🇦 🇷 🇪

⍟⎓⎓⎓⎓⎓⎓⎓⎓⍟⎓⎓⎓⎓⎓⎓⎓⎓⍟
  ✥     @AtronoseZetewahdo      ✥
  ✥     @AtronoseZetewahdo      ✥
⍟⎓⎓⎓⎓⎓⎓⎓⎓⍟⎓⎓⎓⎓⎓⎓⎓⎓⍟
2024/09/21 09:53:00
Back to Top
HTML Embed Code: