Telegram Web Link
"የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ"
ማር 4:3-23

@finote_tsidk  ♻️ 
@finote_tsidk
ጾም እጅግ ግሩም የሆነ ነገር ነው፡፡ ኃጢአታችንን እንደማይጠቅም አረም ከውስጣችን ይነቅለዋል፡፡ እውነተኛው የጽድቅ ተክልም በውስጣችን ልክ እንደ አበባ እንዲያብብ ይረዳዋል፡፡  (ቅዱስ ባስልዮስ)

ከምግባራት ሁሉ ታላቁ ጸሎት ነው ነገር ግን የእርሱ መሠረቱ ጾም ነው፡፡ የምንጾምበት ምክንያት ርኩስ የሆነውን የሰይጣንን መንፈስ በነፍሳችን ውስጥ እንዳያድር ለመጠበቅ ነው፡፡ ሥጋችንን ለጾም ባስገዛነው ጊዜ ነፍሳችን ነፃነትን፤ ጥንካሬን ሰላምን፣ ንጽሕናን እንዲሁም እውቀትን ለመለየት እንድትበቃ ትሆናለች፡፡
(ጻድቁ ዮሐንስ ዘክሮስታንድ)


@finote_tsidk  ♻️ 
@finote_tsidk
"ያለ እግዚአብሔር ብቻ ኃጢአትን ይቅር ማለት ለማን ይቻለዋል? ሥጋን መዋሀዱ ከሰው ወገን ባይሆን ኖሮ የኢያኢሮስን ልጅ ልጄ ብሎ ባልጠራ ነበር፣ በመለኮቱ ፈጣሪ ባይሆን ኖሮ ከሞተች በኋላ ለህይወት ባላስነሳት ነበር፣ ሥጋን መዋሀዱ ከሰው ወገን ባይሆን ምራቁን ከአፈር ላይ ባላደረገ ነበር በመለኮቱ ፈጣሪ ባይሆን ምራቁን በመቀባት ከመወለዱ ጀምሮ ዕውር የሆነውን ሰው ዓይን ባላበራ ነበር ሥጋን መዋሀዱ ከሰው ወገን ባይሆን ማዕበል ሲነሳ በጀልባ ውስጥ ባልተኛ ነበር፣ በመለኮቱ ፈጣሪ ባይሆን ባህሩን ነፋሳትን በመገሰጽ ጸጥ ባላሰኘ ነበር፡፡ ሥጋን መዋሐዱ ከሰው ወገን ባይሆን መንገድ በመሄድ ባለደከመ ነበር፣ በመለኮቱ ፈጣሪ ባይሆን መሄድ የተሳናቸውን ባላዳናቸው እንደጐበዝ ተራማጅ ባላደረጋቸው ነበር፣ ሰው መሆኑ ከሰው ወገን ባይሆን ኖሮ ባልተራበ፣ በመለኮቱ ፈጣሪ ባይሆን አምሰት ሺ ርኁባንን በአምስት ኅብስትና በሁለት ዓሣ ወራት መቶ ርኁባንን በሰባት እንጀራና በጥቂት ዓሣ ባላጠገበ ነበር፣ የክርስቶስ ክብር ከራሱ እንጂ ከሌላ የተገኘ አይደለም፡፡"

(አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ - መጽሐፈ ምስጢር)

@Finote_tsidk @Finote_tsidk
@Finote_tsidk @Finote_tsidk
"ሰዎችን ከፍቅር በላይ በየትኛውም ዓይነት መንገድ ከክፋታቸው ልንመልሳቸው አንችልም፡፡ ፍቅር ግን ሰዎችን ከአውሬነታቸው መልሳ ሰዎች እንዲሆኑ የምታደርግ ታላቅ መምህርት ናት፡፡"

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ

@Finote_tsidk
Please open Telegram to view this post
VIEW IN TELEGRAM
+++ "የምወደው ልጄ ይህ ነው" +++

ጌታችን ከሐዋርያቱ መካከል "አዕማድ መስለው የሚታዩ ያዕቆብና ጴጥሮስ፣ ዮሐንስንም" ወደ ቅዱሱ የታቦር ተራራ ብቻቸውን ይዟቸው ወጣ።(ገላ 2፥9) ከተራራውም ጫፍ ሲደርሱ ሦስቱ ደቀ መዛሙርት የመምህራቸው ፊት እንደ ፀሐይ ሲያበራ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ ሲሆን ተመለከቱ። እነሆም ከቀደሙት ጻድቃን ታላላቆቹ ሙሴና ኤልያስ በታቦር ተገኝተው ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው።

እነዚህ የብሉይ ኪዳን ነቢያት የትንቢታቸው ፍጻሜ ከሆነው ክርስቶስ ጋር ምን ተነጋገሩ? መቼም በጊዜው ከጌታ ጋር ውለው ያድሩ እንደ ነበሩት ተማሪዎቹ ሐዋርያት  "አትሙትብን" አይሉትም። በሺህ ለሚቆጠሩ ዓመታት ሱባኤ የያዙለትና ደጅ የጠኑት የድኅነት ተስፋ እናዳይፈጸም "ይቅር አትሙት" እንዴት ይላሉ? ስለዚህ ከብሔረ ሕያዋን የመጣው ኤልያስና ከብሔረ ሙታን የመጣው ሙሴ በአንድ ላይ "በኢየሩሳሌም ሊፈጸም ስላለው ስለ መውጣቱ (ስለ መከራው፣ ሞቱ)" ያነጋግሩት ነበር።(ሉቃ 9፥31)

በታቦር ተራራ ላይ የብሉይ ኪዳንና የሐዲስ ኪዳን መልእክተኞች ተገናኙ። በባሕር ላይ በእግሩ የተራመደው ጴጥሮስ፣ የኤርትራን ባሕር እጁን ዘርግቶ የከፈለው ሙሴን አየው።(ማቴ 14፥29፣ ዘጸአ 14፥21) የሰማርያ ሰዎች በተቃወሙ ጊዜ "እሳት ከሰማይ ወርዶ ያጥፋቸው" ያሉ ያዕቆብና ዮሐንስ፣ ከሰማይ እሳት አዝንሞ ሃምሳ አንዱን ወታደሮች ያስበላ ኤልያስን ተመለከቱት።(ሉቃ 9፥54፣ 2ኛ ነገ 1፥10)

ሁለቱ ምስክሮች እንደ ተሰወሩም ወዲያው ቅዱስ ጴጥሮስ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው፤ ብትወድስ ሦስት ዳሶች እንሥራ ብሎ ጌታውን ጠየቀ። ሐዋርያው በዚህ ተራራ ላይ መቅረት የፈለገው ያለ ምክንያት አይደለም። መድኃኒታችን አስቀድሞ ወደ ኢየሩሳሌም ይሄድ ዘንድ ከሽማግሎችና ከካህናት አለቆች ከጻፎችም ዘንድ ብዙ መከራ ይቀበልና ይሞት ዘንድ እንዳለው ሲነግራቸው ቅዱስ ጴጥሮስ "አይሁንብህ፤ አይድረስብህ" ሲል ሊከላከለው ሞክሮ ነበር። ለዚህም በጊዜ "ወደ ኋላዬ ሂድ፥ አንተ ሰይጣን፤ የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን አታስብምና ዕንቅፋት ሆነህብኛል" ተብሎ ተገስጾበታል።(ማር 9፥31-33) ይሁን እንጂ አሁንም ቅዱስ ጴጥሮስ ያለውን ሁሉ እድል ተጠቅሞ ጌታን ወደ ኢየሩሳሌም ከመሄድና በካህናት አለቆች እጅ ተላልፎ ከመሰጠት ማስቀረት ስለሚፈልግ "ጌታ ሆይ፦ በዚህ(በታቦር ተራራ) መሆን ለእኛ መልካም ነው" ብሎ ተናገረ።

እርሱም ይህን ገና ሲናገር ሳለ እነሆ፥ ብሩህ ደመና ጋረዳቸው። ከደመናው "በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት" የሚል ድምፅ መጣ። ሐዋርያቱ ይህን ድምጽ የሰሙት ሙሴ እና ኤልያስ ከክርስቶስ ተለይተው ከሄዱ፣ እነርሱም ወድቀው ከነበሩበት ከተነሡ በኋላ ነው። ይህም ከደመናው ውስጥ ሲወጣ ስለ ሰሙት ቃል "ለማን የተነገረ ይሆን?" ብለው እንዳይጠይቁና ምስክርነቱ ለክርስቶስ ብቻ የተሰጠ መሆኑን በማያሻማ ሁኔታ እንዲረዱ ነው። በዚሁም ላይ ደመናው ወርዶ የጋረደው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ብቻ ሳይሆን ሐዋርያቱንም ጭምር ነበር። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንደሚነግረን ደመናው ጌታን ብቻ ጋርዶት ቢሆን ኖሮ፣ ሐዋርያቱ "እርሱን ስሙት" የሚለውን ቃል ራሱ ክርስቶስ ለራሱ የተናገረው ሊመስላቸው በቻለ ነበር። 

ቅዱስ ጴጥሮስ "አትሙት" ያለው መምህሩን በፍጹም ልቡ ስለሚወደው መሆኑ አያጠራጥርም። ነገር ግን ጴጥሮስ ጌታን የቱንም ያህል ቢወደው፣ ፍቅሩ ግን ከወለደው ከባሕርይ አባቱ ከአብ አይደለም ሊበልጥ ሊነጻጸርም አይችልም። ታዲያ አብ በእርሱ ደስ የሚለው፣ የሚወደው፣ አንድያ ልጁ እንዲሞት ፈቃዱ ከሆነ፣ የአብን ያህል ሊወደው የማችለው አረጋዊው ጴጥሮስ ለምን "አትሙት" እያለ ይቃወማል?!

አብ ምትክ የሌለው ልጁ ወልድ ሰው ሆኖ በክፉዎች እጅ ሲንገላታ እና እስከ መስቀል ሞት ሲደርስ እያየ ዝም ያለው ስለማይወደው አይደለም። ዓለም ያለ ልጁ መከራና ሞት ስለማትድን ነው እንጂ። ከዚህ ምን እንማራለን?  ዛሬም ወደ መከራ የምንገባ የጸጋ ልጆቹ የምንሆን እኛ ክርስቲያኖች "እግዚአብሔር እንዲህ ስሆን ዝም ያለኝ  ስለማይወደኝ ነው" አንበል። ባገኘን ጥቂት የሥጋ መከራና ሕመም የሚበልጠውን የነፍስ ጤና የምንሸምት ከሆነ እግዚአብሔር ዝም ይላል። ዝም የሚለው መከራችንን ስለማያይ ሳይሆን ከመከራው ጀርባ ያለው ዓላማ ታላቅና የተቀደሰ እንደ ሆነ ስለሚያውቅ ነው።

(ዲያቆን አቤል ካሳሁን)

@Finote_tsidk
@Finote_tsidk
Please open Telegram to view this post
VIEW IN TELEGRAM
#ዕርገተ_ማርያም (#ነሐሴ_16)

ነሐሴ ዐሥራ ስድስት በዚህች ቀን አምላክን የወለደች የእመቤታችን ድንግል ማርያም ሥጋዋ ወደ ሰማይ ያረገበት መታሰቢያዋ ሆነ። ከዕረፍቷም በኋላ ከእርሳቸው ስለመለየቷ ሐዋርያት ፈጽሞ እያዘኑ ነበር።

ከዚህም በኋላ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ተገለጠላቸው እርሷን በሥጋ ያዩ ዘንድ እንዳላቸውም ተስፋ ሰጣቸው። ወንጌላዊ ዮሐንስም እስያ በሚባል አገር እያስተማረ ሳለ በነሐሴ ወር ዐሥራ ስድስተኛ ቀን ተድላ ደስታ ወደአለባት ገነት በመንፈስ ቅዱስ ተነጠቀ።

የክብር ባለቤት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን የእመቤታችን ማርያም ሥጋዋ ካለበት ከዕፀ ሕይወት ሥር ተቀምጦ አየው። የንጽሕት እናቱንም ሥጋ ታወጣ ዘንድ ምድርን እንዲጠሩዋት ሰባቱን የመላእክት አለቆች አዘዛቸው። እነርሱም የንጽሕት እናቱን ሥጋ ታወጪ ዘንድ እግዚአብሔር አዞሻል አሏት። ያን ጊዜም ከዕፀ ሕይወት በታች ካለ መቃብር የእመቤታችን ማርያም ሥጋዋ ወጣ።

የክብር ባለቤት ጌታችንም እንዲህ እያለ አረጋጋት የተወደድሽ የወለድሽኝ እናቴ ሆይ ዘላለማዊ ወደ ሆነ መንግሥተ ሰማያት አሳርግሽ ዘንድ ነዪ ። ያን ጊዜም በገነት ያሉ ዕፀዋት ሁሉም አዘነበሉ መላእክት የመላእክት አለቆች ጻድቃን ሰማዕታትም እየሰገዱላትና ፈጽሞ እያመሰገኗት አሳረጓት ።

አባቷ ዳዊትም ንግሥት እመቤታችን ወርቀ ዘቦ ለብሳ ደርባ ደራርባ በቀኝህ ትቀመጣለች እያለ በበገና አመሰገናት ። በኪሩቤል ሠረገላ ተቀምጣ ከዐረገች በኋላ በልጁዋና በፈጣሪዋ ቀኝ በታላቅ ክብር ተቀመጠች ።

ወንጌላዊ ዮሐንስም ከእርሷ በረከትን ተቀብሎ ሰግዶላት ተመልሶ ከሰማይ ወረደ ሐዋርያትን ተሰብስበው ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሥጋ ፈጽሞ ሲያዝኑና ሲተክዙ አገኛቸው ። እርሱም እንደ አየ እንደ ሰማ ሥጋዋንም በታላቅ ክብር በምስጋና እንደ አሳረጓት ነገራቸው ።

ሐዋርያትም በሰሙ ጊዜ ዮሐንስ እንዳየና እንደሰማ ባለማየታቸውና ባለመስማታቸው እጅግ አዘኑ ። ከዚህም በኋላ እያዘኑ ሳሉ እነሆ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገለጠላቸውና የፍቅር አንድነት ልጆች ሰላም ይሁንላችሁ ስለ እናቴ ማርያም ሥጋ ለምን ታዝናላችሁ ። እነሆ እኔ እርሷን በሥጋ ላሳያችሁ ልባችሁም ደስ ሊለው ይገባዋል አላቸው ይህንንም ብሎ ከእርሳትው ዘንድ ወደ ሰማያት ዐረገ ።

ሐዋርያትም ዓመት ሙሉ ቆዩ የነሐሴም ወር በባተ ቀን ለሐዋርያት ዮሐንስ እንዲህ አላቸው አምላክን የወለደች የእመቤታችንን ሥጋዋን ለማየት የተዘጋጀን አድርጎ ያሰየን ዘንድ ኑ ይህን ሁለት ሱባዔ በመጾም የክብር ባለቤት ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን እንለምነው በልጅዋ በወዳጅዋ ቀኝ ተቀምጣ አይተን በእርሷ ደስ እንዲለን ።

በዚያን ጊዜም ዮሐንስ እንዳላቸው በጾም በጸሎት ሱባዔ ያዙ የነሐሴ ወር እንደ ዛሬ ዐሥራ ስድስተኛ ቀን በሆነ ጊዜ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉንም ሐዋርያት ወደ ሰማይ አወጣቸው ። በታላቅ ክብር በተወደደ ልጅዋ ቀኝ ተቀምጣ ከሥጋዋ ተዋሕዳ ተነሥታ እመቤታችን ማርያምን አዩዋት። እጆቿንም ዘርግታ የከበሩ ሐዋርያትን እያንዳንዳቸውን ባረከቻቸው በልባቸውም እጅግ ደስ አላቸው።

የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በከበረ ሥጋውና ደሙ ላይ ሠራዒ ካህን ሆነ ። እስጢፋኖስም አዘጋጀ ዮሐንስም በመፍራት ቁሙ አለ ። ሁሉም ሐዋርያት በመሠዊያው ዙሪያ ቆሙ በዚያን ጊዜ ከቶ እንደርሱ ሆኖ የማያውቅ ታላቅ ደስታ ሆነ።

ጌታችንም የቅዳሴውን ሥርዓት በፈጸመ ጊዜ ሥጋውንና ደሙን አቀበላቸው ። ከዚያም በኪሩቤልና በሱራፌል ሠረገላ ተቀምጣ በምታርግ ጊዜ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እናቱ እመቤታችን ማርያምን እንዲህ ብሎ ተናገራት።

በዚች ቀን የሆነ የዕርገትሽን መታሰቢያ በዓለም ውስጥ እንዲሰብኩ ልጆችሽ ሐዋርያትን እዘዣቸው ። መታሰቢያሽን የሚያደርገውን ሁሉ ተጠብቆም በዚች ቀን ቅዱስ ቁርባንን የሚቀበለውን ኃጢአቱን እደመስስለታለሁ ። የእሳትን ሥቃይ ከቶ አያያትም መታሰቢያሽን ለሚያደርግ ሁሉ በዚች ቀን ለድኆች በስምሽ ለሚመጸውት ቸርነቴ ትገናኘዋለች ይህም ሥጋሽ ወደ ሰማይ ያረገበት ነው።

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም ክብር ይግባውና ጌታችንን እንዲህ አለችው ልጄ ሆይ እነሆ በዐይኖቻቸው አዩ በጆሮቻቸውም ሰሙ በእጆቻቸውም ያዙ ሌሎችም ታላላቅ ደንቆች ሥራዎችን አዩ ። እመቤታችንም ይህን ስትናገር ጌታችን ሰላምታ ሰጥቷቸው በታላቅ ደስታ ወደ ደብረ ዘይት ተመለሱ ።

የተወደዳችሁ ወንድሞች ሆይ በፍጹም ደስታ መታሰቢያዋን እናደርግ ዘንድ ይገባናል እርሷ ስለእኛ ወደ ተወደደ ልጅዋ ሁልጊዜ ትማልዳለችና ።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት ይማረን ። በረከቷም ከርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ከአባ ማትያስ ከሁሉም ሊቃነ ጳጳሳትና ኤጲስቆጶሳት ጋራ ሐዋርያት ከሰበሰቧት ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልጆች ከሁላችን ጋራ ይኑር ለዘላለሙ አሜን ።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ነሐሴ)

🇯 🇴 🇮 🇳    ♻️  🇸 🇭 🇦 🇷 🇪

⍟⎓⎓⎓⎓⎓⎓⎓⎓⍟⎓⎓⎓⎓⎓⎓⎓⎓⍟
@Finote_tsidk ♻️ @Finote_tsidk
@Finote_tsidk ♻️ @Finote_tsidk
⍟⎓⎓⎓⎓⎓⎓⎓⎓⍟⎓⎓⎓⎓⎓⎓⎓⎓⍟
ድንግል ሆይ !

❝አንቺን የወለደ ማህጸን እንዴት ያለ ብሩክ ነው❞ አንቺን የታቀፉ ክንዶችስ እንዴት ያሉ ድንቅ ናቸው ! አስራ ሁለት ዓመት ወደ ቤተመቅደስ የተመላለሱ እግሮችሽስ እንዴት የከበሩ ናቸው ! የቅዱሱን መልአክ ብሥራት የሰሙ ጆሮዎችሸስ እንዴት ያሉ ንቁ ናቸው ! ❝የቃልን ሰው መሆን ያመነው ልብሽ እንዴት ያለ ንጹሕ ነወ ! ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ጌታን የተሸከመው ማሕፀንሽ እንዴት ያለ ግሩም ነው ! ይህን ታላቅ አምላክ የታቀፉ ክንዶችሽስ እንዴት ያሉ ጽኑ ናቸው ! ጌታዬን ያጠቡት ጡቶሽን እንዴት የለመለሙ ናቸው ! ድንግል ሆይ ክብርሽ ከፍ ያለ ነውና አከብርሻለሁ❞ ሰላሳ ሶስት ዓመት ከሶሶት ወር ከጌታ ጋር ያኖረሽን እምነት እኔ ልጅሽ ለአንድ ሰዓት እንኳ የለኝምና እጅግ ጎስቋላ ነኝ ። አስራ ሁለት ዓመት ከወንጌላዊው ዮሐንስ ቤት ያኖረሽን ልበ ሰፊነት እኔ ደካማው ልጅሽ ለአንድ ሰዓት እንኳ ከምወደው ጋር ለመሆን አልታደልኩምና እጅግ ደካማ ነኝ ! ቅድስት ሆይ የምልጃሽ በረከት የእግዚአብሔርን እገዛ ይላክልኝ ። ፍልሰትሽ መጪውን የምዕመናንን ትንሳኤ ጎልቶ ያሳያል ።  ዕርገትሽ መጪውን የምዕመናን ዕርገት በግልጥ ያስተምራል ። ከሚታስበው በላይ  ቅድስት ፣ ከሚነገረው በላይ ትሁት ፣ ከምሰማው በላይ ቡሩክት ፣ ከጻፉልሽም በላይ ንጽህት ፣ ከተረኩሽም በላይ ልዕልት ነሽና ልቤ ታመሰግንሻለች !

ዲያቆን እስጢፋኖስ ደጀኔ
ነሐሴ 16 ቀን 2016 ዓ.ም.


🇯 🇴 🇮 🇳    ♻️  🇸 🇭 🇦 🇷 🇪

⍟⎓⎓⎓⎓⎓⎓⎓⎓⍟⎓⎓⎓⎓⎓⎓⎓⎓⍟
@Finote_tsidk ♻️ @Finote_tsidk
@Finote_tsidk ♻️ @Finote_tsidk
⍟⎓⎓⎓⎓⎓⎓⎓⎓⍟⎓⎓⎓⎓⎓⎓⎓⎓⍟
🌹#ቅዱስ_ገብርኤል_ማን_ነው🌹

#ገብርኤል ማለት " እግዚእ ወገብር”፦ የእግአብሔር አገልጋይ ማለት ነው። ፍጥረታት መፈጠር በጀመሩበት በዕለተ እሑድ እግዚአብሔር መላእክትን ከፈጠራቸው በኋላ ተሰወራቸው መላእክትም “መኑ ፈጠረነ፦ማን ፈጠረን” ሲሉ ዲያብሎስ እኔ ፈጠርኳችሁ ብሎ መላእክት በተረበሹ ጊዜ “የፈጠረንን✥አምላካችን እስክናውቅ በያለንበት ጸንተን እንቁም” ብሎ ያረጋጋቸው መልአክ ነው። በዚህም ምክንያት ጌታ “በእንተዝ ይደልዎ ከመ ይጹር ዜናሃ ለማርያም” እንዲል ሥጋዌውን ለድንግል እንዲያበስር አድሎታል።

➯✥ይህ ቅዱስ ገብርኤል ነው✥
ሰጥናኤል ሥላሴን በካደ ጊዜ መላእክትን በቃሉ ያጽናናቸው

➯✥ይህ ገብርኤል ነው✥
ከሰባቱ ሊቃነ መላእክት አንዱና በእግዚአብሔር ፊት የሚቆም

➯✥ይህ ገብርኤል ነው✥
በጨለማና በሞት ጥላ ውስጥ ለሚኖሩ ብርሃን የገለጸና የሰበከ ይህ

➯✥ቅዱስ ገብርኤል ነው✥
የነቢያትን ትንቢት የፈጸመ፤የክርስቶስን ልደት ለድንግል ያበሰረ

➯✥ቅዱስ ገብርኤል ነው✥
ዳንኤልን ከአናብስት ያዳነው

➯✥ይህ ገብርኤል ነው✥
ሠለስቱ ደቂቅን ከእቶን እሳት ያዳነቸው

➯✥ይህ ገብርኤል ነው✥
ወደ ዘካርያስ የተላከ የዮሐንስን ልደት ያበሰረ

➯✥ይህ ገብርኤል ነው✥
ወደ ዮሴፍና ወደ ኒቆዲሞስ የተላከ

➯✥ቅዱስ ገብርኤል ነው✥
ቂርቆስና እናቱ ኢየሉጣን ከእቶን እሳት ያዳናቸው

➯✥ይህ ገብርኤል ነው✥
ሰብአ ሰገልን በኮከብ ምልክት የመራቸው

➯✥ይህ ገብርኤል ነው✥
ድንግል ማርያምና ሕፃኑን ክርስቶስን በምድረ በዳ በስደታቸው የመራ

➯✥ይህ ገብርኤል ነው✥
የብርሃን ራስ ወርቅ የተቀዳጀ

➯✥ገብርኤል ነው✥
የአሸናፊና የኃይል መልአክ

✥ገብርኤል ነው✥
ነበልባላዊ ዖፈ ሰማይ

➯✥ገብርኤል ነው✥
"የመልአኩ ጥበቃ እና ረድኤት አይለየን"
❖አሜን❖

🇯 🇴 🇮 🇳    ♻️  🇸 🇭 🇦 🇷 🇪

⍟⎓⎓⎓⎓⎓⎓⎓⎓⍟⎓⎓⎓⎓⎓⎓⎓⎓⍟
@Finote_tsidk ♻️ @Finote_tsidk
@Finote_tsidk ♻️ @Finote_tsidk
⍟⎓⎓⎓⎓⎓⎓⎓⎓⍟⎓⎓⎓⎓⎓⎓⎓⎓⍟
"ዲያብሎስ ልጅነታችንን እናቆሽሽ ዘንድ በእኛ ላይ የሚተናኰለው ተንኰል በጣም ተደጋጋሚና ኃይለኛ ነው፡፡ ስለዚህ ይህን መንቻካ የዲያብሎስን ደባ ድል እንነሣ ዘንድ ዘወትር ንቁዎችና ጠንቃቆች ልንኾን ይገባናል፡፡ እኛ ይህን ማድረግ ሳንችል ቀርተን እጅግ ጥቂት መግቢያ ቀዳዳ የምንተውለት ከኾነ ግን እርሱ ጥቂቷን ቀዳዳ ሰፊ በር ያደርጋታል፡፡ እንዲህ አድርጎም ኃይሉን ኹሉ ተጠቅሞ ወደ እኛ ይገባል፡፡

ስለዚህ ስለ ድኅነታችን የሚገደን ከኾነ እንደዚህ ጥቂትና ቀልድ በሚመስሉ ነገሮች እንኳን አንዘናጋ፤ እርሱ የሚንቀውና ጥቂት የሚለው ኃጢአት የለምና፡፡ እኛ ጥቃቅን የምንላቸውን ነገሮች መነሻ አድርጎ ልጅነታችንን የምናቆሽሽበትን ታላላቅ ኃጢአቶችን እንድንሠራ አድርጎ እጅግ ይተጋልና፡፡"

(#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ)

🇯 🇴 🇮 🇳    ♻️  🇸 🇭 🇦 🇷 🇪

⍟⎓⎓⎓⎓⎓⎓⎓⎓⍟⎓⎓⎓⎓⎓⎓⎓⎓⍟
@Finote_tsidk ♻️ @Finote_tsidk
@Finote_tsidk ♻️ @Finote_tsidk
⍟⎓⎓⎓⎓⎓⎓⎓⎓⍟⎓⎓⎓⎓⎓⎓⎓⎓⍟
+ ማርያማዊ ደስታ +

ድንግል ማርያም ‘መንፈሴም በመድኃኒቴ በእግዚአብሔር ደስ ይላታል’ አለች፡፡ የድንግሊቱን ጥበብ ተመልከቱ፡፡ ‘በመልአክ በመመስገኔ ደስ ይለኛል ፣ ከሴቶች ሁሉ የተባረከች በመባሌ ደስ ይለኛል ፣ አምላክን ለመውለድ በመመረጤ ደስ ይለኛል’ አላለችም፡፡ የእርስዋ የደስታ ምንጭ ከእግዚአብሔር የተሠጣት ነገር ሳይሆን ራሱ እግዚአብሔር ነው፡፡

እግዚአብሔር የደስታህ ምንጭ ከሆነ በሕይወትህ ምንም ነገር ቢከሰት ደስታህን አይነካብህም፡፡ ድንግሊቱ ከሴቶች ሁሉ የተባረከች በመሆንዋ ደስ ያላት ብትሆን ኖሮ ከዚያ በኋላ ከሴቶች ሁሉ የተንከራተተች ፣ ከሴቶች ሁሉ ያዘነች ፣ ከሴቶች ሁሉ በዲያብሎስና ጭፍሮቹ የተጠላች ፣ በሔሮድስ በአይሁድ የተነቀፈች መሆንዋን ስታይ ደስታዋ በጠፋ ነበር፡፡

እርስዋ ግን ደስታዋ የመነጨው ከአምላክዋ ብቻ ነበር፡፡ ፍጹም የሆነ ውስጣዊ ደስታን ማግኘት የሰው ልጅ ትልቅ ምኞቱ ነው፡፡ ሰዎች ደስታን ፍለጋ ብዙ ይደክማሉ፡፡ ድንግሊቱ ግን የደስታ ሁሉ ምንጭ የሆነው አምላክ ከእርስዋ ጋር ነውና በፍጹም ደስታ ደስ ይላታል፡፡ የድንግል ማርያም ደስታ ልጅዋ ‘ደስታችሁን የሚወስድባችሁ የለም’ ያለው ዓይነት ደስታ ነበር፡፡ ዮሐ. ፲፮፥፳፪

‘ተፈሥሒ ፍስሕት’ (ደስተኛይቱ ሆይ ደስ ይበልሽ) ፤ ሙኃዘ
ፍሥሓ (የደስታ መፍሰሻ ሆይ) ብለን የምናመሰግናት እመቤታችን ከማንም የሚበልጥ ደስታ በእርስዋ ዘንድ ነበረ፡፡ ደስተኛ የነበረችው በምድር በነበራት ቆይታ የሚያስደስት ኑሮ ስለነበራት አይደለም፡፡ እንደ እርስዋ የተሰደደ ፣ ያለቀሰ ፣ የተጨነቀ ፍጡር የለም፡፡ እንደ ክርስቶስ መከራ የተቀበለ እንደሌለ እንደ ድንግል ማርያምም ያዘነ የለም፡፡ እርስዋ ግን ለሌሎች የሚተርፍ ወደ ኤልሳቤጥ የሚሸጋገር ፣ ሆድ ውስጥ ወዳለ
ፅንስ የሚጋባ ጥልቅ ደስታ ነበራት፡፡ ቅዱስ ያሬድ ‘ተፈሢሓ በነፍሳ  ፆረቶ በከርሣ’ ‘በነፍስዋ ደስ ተሰኝታ በሆድዋ ተሸከመችው’ እንዳለ እርስዋ የተደሰተችው ሥጋዊ ደስታን አልነበረም፡፡ (ድጓ ዘቅዱስ ገብርኤል )ከመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎች አንዱ ደስታ ነውና ቅድስቲቱ ማንም ጋር ያልነበረ ደስታ ነበራት፡፡ ገላ. ፭፥፳፪
በእርግጥም ደስታን ወልዳ ደስ ባይላት ይደንቅ ነበር፡፡ እርስዋ የወለደችው ‘የመላእክት ተድላ ደስታቸው’ ነው ፤ እርስዋ የወለደችው መወለዱ ‘ለሰው ሁሉ ደስታ የሚሆን ታላቅ የምሥራች’ የሚሆን ልጅን አይደለምን?

እግዚአብሔር አብ ‘በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወድደው ልጄ ይህ ነው’ ያለውን አንድያ ልጁን ልጅዋ እንዲሆን ሠጥቶአታልና እርስዋም በምትወደው በልጅዋ ደስ ይላታል፡፡ ንጉሥ ዳዊት ‘ወደ እግዚአብሔር ቤት እንሒድ ባሉኝ ጊዜ ደስ አለኝ’ ካለ እግዚአብሔር የዘጠኝ ወር ቤቱ አድርጎ ያደረባት ድንግል ምንኛ ደስ ይላት ይሆን? መወለዱ ሰውና መላእክትን በደስታ እንዲዘምሩ ካደረገ የወለደችው ድንግል ምንኛ ደስ ይላት ይሆን?

ጌታ ለሐዋርያቱ ‘ስማችሁ በሰማይ ስለተጻፈ ደስ ይበላችሁ’ ካላቸው እግዚአብሔር ሁለተኛ ሰማዩ አድርጎ ዙፋን ያደረጋት በምድር ያለች የጠፈር ባልንጀራ ፣ የአርያም እኅት ማርያም ምንኛ ደስ ይላት ይሆን?

እመቤታችን ሆይ እባክሽን በአንቺ ላይ ከፈሰሰው ደስታ ቀድተሽ ወደ እኛ ወደ ኀዘንተኞቹ አፍስሺ፡፡ ኖኅ እንደ ላካት ርግብ የመከራችን ውኃ ጎደለ ብለሽ ታበሥሪን ዘንድ ወደ እኛ ነይ ‘ንዒ ርግብየ ትናዝዝኒ ኀዘነ ልብየ’ ‘ርግቤ ሆይ ከኀዘኔ ታረጋጊኝ ዘንድ ነይ’ እንዳለ ሊቁ፡፡

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ከብርሃን እናት ገጾች
#share


🇯 🇴 🇮 🇳    ♻️  🇸 🇭 🇦 🇷 🇪

⍟⎓⎓⎓⎓⎓⎓⎓⎓⍟⎓⎓⎓⎓⎓⎓⎓⎓⍟
@AtronoseZetewahdo
@AtronoseZetewahdo
⍟⎓⎓⎓⎓⎓⎓⎓⎓⍟⎓⎓⎓⎓⎓⎓⎓⎓⍟
#ደመናው_ባይኖርስ

እንዴት ነው ይዘንባል እንዴ ስትሏቸው ሰዎች ሰማዩን አይተው ደመና ከታያቸው አልያም ጠቆር ካለ አዎ ይዘንባል ይላሉ። ይዘንባል እንዲሉ ያነሳሳቸው የሰማዩ በደመና መሸፈን ነው። ደመናው ባይታይ ወይ አይዘንብም ወይ ደግሞ እንጃ ይሏችሁ ነበረ።

ብዙዎቻችን እግዚአብሔርን ተስፋ አድርጋለሁ እንላለን። ተስፋ የምናደርግበት ልኩ ይለያይ እንጂ ተስፋ መድረጋችን አይቀሬ ነው።  እግዚአብሔር ቢል የሆነ ነገር ሊሳካ ነው መሰለኝ ስንል እነሰማለን። እግዚአብሔርን መቼ ነው ተስፋ ያደርጋችሁት?  የሆነ ነገር እንዲሰጣችሁ ጠይቃችሁት ከቤተሰብ ጥሩ ምላሽ ተሰጥቷችሁ ትንሽ ጊዜ ጠብቅ በተባላችሁ ጊዜ ነውን?

ሁኔታዎች ጥሩ በሆኑ ጊዜያት እግዚአብሔርን ተስፋ ማድረግ ትክክለኛቱ ላይ ግድፈት አለበት ምክንያቱም ደመና ከተያችሁ ወዲህ እንዲዘንብ ተስፋ ማድረግ የተስፋን ተስፋነት ያጠፋዋል። ምክንያቱም የሚታይ ነገር ተስፋ አይደረግምና። "ነገር ግን ተስፋ የሚደረግበቱ ነገር ቢታይ ተስፋ አይደለም፤ የሚያየውንማ ማን ተስፋ ያደርገዋል?" ሮሜ 8:24

እስኪ አሁን እግዚአብሔር ተስፋ ስላደረጋችሁበት ነገር አስተውሉ። ታይቷችሁ ይሆንን ተስፋ ያደረጋችሁት? የታየንን እሰክናገኝ መጠበቅ ትዕግስት እንጂ ተስፋ አይደለም እና እየታገሳችሁ ባለበት ሁኔታ ተስፋ አታድርጉ። የተስፋችሁ ተስፋነት የሚጸናው ነገሩ ያልታያችሁ እሰከሆነ ድረስ ብቻ ነው።

ባልታየን ደመና እግዚአብሔር ይችላል ስለዚህ ይዘንባል ብሎ ተስፋ ማድረግ እንዴት ያለ ተስፋ ነው። ባልታያችሁ ነገር ላይ እግዚአብሔርን ተስፋ ያደረጋችሁ እንደሆነ የእግዚአብሔርን አድራጊነት አምናችሁ ነውና ይህ አይነቱ የተስፋ ሙላት እንዳይጎድልባችሁ በጸሎት ትተጉ ዘንድ እመጸናለሁ። ምክንያቱም ብዙዎቻችን ባልታየን ነገር እግዚአብሔርን ተስፋ ስናደርግ አንታይም።

ክርስቲያን በማየት አያምንም። የሚያመልከውን እግዚአብሔር እንኳን ሳያየው ፈጠሪዬ፣ ገዢዬ፣ አስገኚዬ፣ አምላኬ ብሎ ያመልከዋል። ስለዚህ ነው ክርስቲያን ባልታየ፣ ባልተያዘ እና ባልተጨበጠ ሁኔታ ውስጥ እግዚአብሔርን ተስፋ ማድረግ ያለበት። አይተን ተስፋ ካደረግነው ከአህዛብ/ከማያምኑ መለየታችን በምን ሆነ?

የምናመልከው ሁሉን የሚችለውን ጌታ እስከሆነ ድረስ በነገሮቻችን ሁሉ የሱን ቻይነት ማወጅ እና መኖር የግድ ነው። ይህ ሳይሆን ቀርቶ ባየነው ነገር ተስፋ አድርገን ተስፈኞች ነን ብንል ምስኪን ሆነናል። ደመናውን ሳናይ እግዚአብሔር ተስፋ ማድረግ የምንችልበት አቅም ከራሱ ከእግዚአብሔር ይሰጠን።

ተስፋዬ አንተ ነህ አይደለም ሁኔታ
አይኖቼኝ አያዩም ከአንተ ውጪ ለአፍታ
ደመናን አይቼ ይዘንባል አልልም
አንተን እረስቼህ ሁኔታን አላምንም

ሲመቻች ይሆናል አልያም አይሆንም
ሁኔታን አይቼ እንዲህ ነው አልልም
የሚታየው ነገር የሚጸና አይደለም
ተስፋዬ አንተ ነህ የሚያቅትህ የለም

ከሚታየው በላይ አንተ አይሃለሁ
ምንም በሌለበት ተስፋ አደርግሃለሁ
የተያዘ ነገር አንድ ቀን ይጠፋል
አንተን ያየዘ ግን ዘወትር ያተርፋል

ሰማዩ ሳይጠቆር ይዘንባል እላለሁ
ትችላለሁ እና አንተን አምንሃለሁ
ተስፋ አንተን ማደረጌ በሌለበት ምንም
ጥቅም ብቻ እንጂ ኪሰራ የለውም

ስለማላፍርበት ተስፋነትህ ተመስገን።

ዲያቆን ተስፋ መሠረት
📆 ከአንድ ዓመት በፊት የተጻፈ


🇯 🇴 🇮 🇳    ♻️  🇸 🇭 🇦 🇷 🇪

⍟⎓⎓⎓⎓⎓⎓⎓⎓⍟⎓⎓⎓⎓⎓⎓⎓⎓⍟
@Finote_tsidk ♻️ @Finote_tsidk
@Finote_tsidk ♻️ @Finote_tsidk
⍟⎓⎓⎓⎓⎓⎓⎓⎓⍟⎓⎓⎓⎓⎓⎓⎓⎓⍟
2024/09/21 05:53:43
Back to Top
HTML Embed Code: