Telegram Web Link
#ድንግል__ሆይ!

አንገታቸውን እንደሚያረዝሙ እንደ እብራውያን ሴቶች ልጆች በዋዛ ያደግሽ አይደለሽም ፤
#በቅድስናና #በንጽሕና #በቤተ_መቅደስ ኖርሽ እንጂ ።

#ድንግል__ሆይ!

ምድራዊ ሕብስትን የተመገብሽ አይደለም ፤ ከሰማየ ሰማያት የበሰለ
#ሰማያዊ #ሕብስትን እንጂ ።

#ድንግል__ሆይ!

ምድራዊ መጠጥን የጠጣሽ አይደለም ፤ ከሰማየ ሰማያት የተቀዳ
#ሰማያዊ መጠጥን እንጂ ።
(ቅዳሴ ማርያም)

🌹
#መልካም_ዕለተ_ሰንበት 🌹

አጫጭር ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶች
•➢ 👇 ለማግኘት // 👇

@Enatachn_mareyam
@Enatachn_mareyam
Forwarded from አብሰራ ገብርኤል ለማርያም (♱ ባሕራን ♱)
                        †                             

  †   🕊   ክብርት ሰንበት   🕊   †

❝ የሰው ልጆች ያርፉባት ዘንድ ሰንበትን አዘጋጀ፡፡ ለጻድቃንም ለኃጥአንም ፣ ለሞቱትም በሕይወት ላሉትም ፡ የሰው ልጆች ያርፉባት ዘንድ ሰንበትን አዘጋጀ፡፡

የክርስቶስ ሰንበቱማ እርሷ ናት ፣ ለልዑልም የስሙ ማደሪያ ናት፡፡ ዛሬስ በሰማያት ያለች ተስፋችንና ሕይወታችን በዚህች በተቀደሰች ቀን ነው ፣ በርሷ በሚያርፉባት በሰንበት ቀን፡፡ ❞

[    ቅዱስ ያሬድ    ]

🕊

[ መጽሐፍ እንደተናገረ በፈጣሪ እና በፍጡራን መካከል ለዕረፍት የቃል ኪዳን ማደሪያ [ ምልክት ] የሆንሽ የብርሃን ቀን ሰንበተ ሰንበታት ማርያም ሆይ በገነት ያሉ ጻድቃን በአንቺ ደስ ይላቸዋል፡፡ ኃጥአንም ከደይን በአንቺ ይወጣሉ፡፡ ]

[   አባ ጽጌ ድንግል   ]

†                      †                      †
💖                   🕊                   💖
🕊

[  † እንኳን ለጻድቅ ሊቀ ዻዻሳት አባ ዮሴፍ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን። †  ]

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †


†  🕊 ጻድቅ ሊቀ ዻዻሳት አባ ዮሴፍ 🕊 

† በእስክንድርያ [ግብጽ] ሊቀ ዽዽስናን ከተሾሙና በጐ ሥራን ከሠሩ አበው አንዱ አባ ዮሴፍ ነው:: እርሱ ለግብጽ ፶፪ኛ ፓትርያርክ ነውና በ9ኛው መቶ ክ/ዘመን አካባቢ እንደ ነበር ይታመናል::
ጥንተ ነገሩስ እንደ ምን ነው ቢሉ :-
በግብጽ የሚኖሩ የዘመኑ ክርስቲያን ባልና ሚስት ወደ ፈጣሪ ለምነው ልጅ ሲወልዱ 'ዮሴፍ' አሉት:: እጅግ ሃብታሞች ቢሆኑም እርሱ ገና ልጅ እያለ ሁለቱም ዐረፉ:: ሕጻኑ ዮሴፍም ዕጓለ ሙታን [ወላጅ አልባ] ሆነ:: ሕጻኑ ሲያለቅስ የተመለከተ አንድ ደግ ጐረቤቱ ግን ወደ ቤቱ ወሰደው::

እንደ ልጁ ተንከባክቦ: ክርስትናንም አስተምሮ አሳደገው:: እድሜው ፳ ሲደርስም "የወላጆችህን ንብረት ንሳ" ብሎ አወረሰው:: ወጣቱ ዮሴፍ ግን "አኮኑ ዝንቱ ኩሉ ኃላፊ-ይህ ሁሉ ሃብት ጠፊ አይደለምን" ብሎ ናቀው::

ለነዳያንም በትኖት እያመሰገነ ወደ ገዳመ አስቄጥስ ገሰገሰ:: በዚያም የአሞክሮ ጊዜውን ፈጽሞ መዓርገ ምንኩስናን ተቀበለ:: ለዓመታትም በዲቁና ገዳሙን እያገለገለ: እየተጋደለ ኖረ::

የአባ ዮሴፍን ደግነት የሰማው የወቅቱ ፓትርያርክ አባ ማርቆስም ከገዳም አውጥቶ በመንበረ ዽዽስናው እንዲራዳውና ሕዝቡን እንዲያስተምርለት ወደ ከተማ አመጣው::

ከጥቂት ቆይታ በኋላ ግን አባ ዮሴፍ ወደ ፓትርያርኩ አባ ማርቆስ ቀርቦ "አባቴ! ወደ ገዳሜ አሰናብተኝ:: ለመነኮስ በከተማ መኖር ፍትሕ አይደለምና" ሲል ተማጸነው:: ፓትርያርኩም "እሺ" ብሎ ቅስናን ሹሞ አሰናበተው::

ወደ ገዳመ አስቄጥስ ከተመለሰ ጀምሮ አባ ዮሴፍ በዓት ለየ:: እስከ ፶፱ ዓመቱም ድረስ በጾምና በጸሎት በበዓቱ ጸንቶ ኖረ:: በአጠቃላይ በገዳም የኖረባቸው ዓመታትም ፴፱ ደረሱ::

በዚህ ጊዜ ግን የወቅቱ ፓትርያርክ አባ ስምዖን [ከአባ ማርቆስ በኋላ ፫ ፓትርያርኮች ዐርፈዋል] በማረፉ ግብጽ እረኛን ስትፈልግ ነበር:: 'ማንን እንሹም' እያሉ ሲጨነቁ አንድ ሰው ጉቦ ሰጥቶ ሊሾም መሆኑን አበው ሰሙ:: ይህ ሰው ደግሞ ጭራሹኑ ልጅ ያለው ነው::

አባቶች ተሯሩጠው ያ ጉቦኛ ባለ ሚስት እንዳይሾም አደረጉ:: ቀጥለው ማንን እንደ ሚሾሙ ሲጨነቁ የሁሉም ሕሊና ስለ አንድ ሰው [አባ ዮሴፍ] ያስብ ነበር:: ሁሉም ተሰብሳቢዎች ስለ ነገሩ ተጨዋውተው አባ ዮሴፍን ይሾሙ ዘንድ ቆረጡ::

ተሰብስበው በመንገድ ላይ ሳሉም እንዲህ ተባባሉ:: "ወደ በዓቱ ስንደርስ ቤቱ ክፍት ከቆየን ፈቃደ እግዚአብሔር ነው:: ዝግ ከሆነ ግን ፈጣሪ አልፈቀደም ማለት ነው" ሲሉ ተስማሙ:: ምክንያቱም የአበው በዓት ቶሎ ቶሎ አይከፈትምና::

ነገሩ ጥበበ እግዚአብሔር ነበረበትና ልክ ሲደርሱ እንግዳ ሊሸኝ በዓቱን ከፍቶ አገኙት:: እንዳያመልጣቸው ተረባርበው ያዙት:: ግጥም አድርገው አሥረው "አክዮስ-ይደልዎ-ይገባዋል" እያሉ ሥርዓተ ሲመት አደረሱለት:: እርሱ [አባ ዮሴፍ] ግን "እኔ ኃጢአተኛ ነኝ: አይገባኝም: ልቀቁኝ" እያለ ይጮህ ነበረ::

አበው ግን ሥርዓተ ሢመቱን ፈጽመው ወስደው በመንበረ ዽዽስና: በቅዱስ ማርቆስ ወንጌላዊ ዙፋን ላይ አስቀመጡት:: በቁጥርም ፶፪ኛ ሁኖ ተቆጠረ:: አምላክ ደጉን ሰው ጠቁሟቸዋልና ለቤተ ክርስቲያን ይተጋ ጀመር::

ሕዝቡን እያስተማረ: አብያተ ክርስቲያናትን እያነጸ: መጻሕፍትን እየተረጐመ: ተአምራትን እየሠራ: በመንኖ ጥሪት ለ፲፱ ዓመታት አገልግሏል:: ወቅቱም ተንባላት [አማሌቃውያን] በምድረ ግብጽ የሰለጠኑበት ነበርና ብዙ ችግሮችን አሳልፏል::

የግብጹ ሱልጣንም ሊገድለው ፪ ጊዜ ሞክሮ አልተሳካለትም:: ፪ ጊዜም ለአባ ዮሴፍ የሰነዘረው ሰይፍ በመልአክ እየተመለሰ ተመልክቶ ትቶታል:: አባ ዮሴፍ በዘመኑ ተሰዶ የነበረውን የኢትዮዽያ ዻዻስ አባ ዮሐንስንም ከተሰደደበት ወደ ሃገራችን
እንደ መለሰው በዜና ሕይወቱ ተጽፏል:: አባ ዮሴፍ እንዲህ ተመላልሶ በ፸፰ ዓመቱ በዚህች ቀን ዐርፏል::

† ቸር አምላክ በጻድቁ ሊቀ ዻዻሳት ጸሎት ይማረን:: ከበረከቱም ይክፈለን::

🕊

[  † ጥቅምት ፳፫ [ 23 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት  ]

፩. አባ ዮሴፍ ጻድቅ ሊቀ ዻዻሳት
፪. ቅዱስ ዲዮናስዮስ ሰማዕት
፫. ቅዱስ ኢላርዮስ
፬. ቅድስት እለእስክንድርያ ሰማዕት

[  † ወርኀዊ የቅዱሳን በዓላት   ]

፩. ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት
፪. ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማዕታት
፫. ነቢየ ጽድቅ ቅዱስ ሰሎሞን [ንጉሠ እሥራኤል]
፬. አባ ጢሞቴዎስ ገዳማዊ
፭. ቅዱስ ዳንኤል ነቢይ
፮. አባ ሳሙኤል
፯. አባ ስምዖን
፰. አባ ገብርኤል
 

" ኤዺስ ቆዾስ እንደ እግዚአብሔር መጋቢ የማይነቀፍ ሊሆን ይገባዋልና:: የማይኮራ: የማይቆጣ: የማይሰክር: የማይጨቃጨቅ: ነውረኛ ረብ የማይወድ: ነገር ግን እንግዳ ተቀባይ: በጐ የሆነውን ነገር የሚወድ: ጠንቃቃ: ጻድቅ: ቅዱስ: ራሱን የሚገዛ ይሁን:: " † [ቲቶ.፩፥፯]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
🕊

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †

[  † ጥቅምት ፳፬ [ 24 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት †  ]


† 🕊 ቅዱስ አብላርዮስ ገዳማዊ 🕊 † 

† በቤተ ክርስቲያን አስተምሕሮ "ታላቁ / ዓቢይ / THE GREAT" የሚል ስም የሚሰጣቸው አባቶች የተለዩ ናቸው:: አንድም እጅግ ብዙ ትሩፋቶችን የሠሩ ናቸው:: በሌላ በኩል ደግሞ በተመሳሳይ ስም ከሚጠሩ ሌሎች ቅዱሳን እንለይበታለን::

ታላቁ ቅዱስ አብላርዮስ ደግሞ ካለ ማመን ወደ ማመን: ከማመን ወደ መመንኮስ: ከመመንኮስ ወደ መጋደል: ከመጋደል ወደ ትሕርምት: ከዚያም ወደ ፍጹምነት የደረሰ: በምድረ ሶርያም ገዳማዊ ሕይወትን ያስፋፋ አባት ነው::

ገዳማዊ ሕይወት ጥንቱ ብሉይ ኪዳን ነው:: በቀዳሚነትም በደብር ቅዱስ አካባቢ ይኖሩ የነበሩ ደቂቀ ሴት እንደ ጀመሩት ይታመናል:: ሕይወቱ በጐላ: በተረዳ መንገድ የታየው ግን በታላቁ ጻድቅ ሄኖክ: ከዚያም በቅዱሱ ካህን መልከ ጼዴቅ አማካኝነት ነው::

ቀጥሎም እነ ቅዱስ ኤልያስ ነቢይ: እነ ኤልሳዕ ደቀ መዝሙሩ ኑረውበታል:: በሐዲስ ኪዳን ደግሞ ሙሉ ሕይወቱን በገዳም [በበርሃ] ያሳለፈው መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ቅድሚያውን ይይዛል::

ለስም አጠራሩ ስግደት ይሁንና መድኃኒታችን ክርስቶስ በገዳመ ቆረንቶስ ለ40 ቀናት በትሕርምት ኑሮ ገዳማዊ ሕይወትን ቀድሷል: አስተምሯል:: በዘመነ ስብከቱም ያድርባት የነበረችው የደብረ ዘይቷ በዓቱ [ኤሌዎን ዋሻ] በራሷ ለዚህ ሕይወት ትልቅ ማሳያ ናት::

ከጌታ ዕርገት በኋላም ክርስቲያኖቹ የዓለም ሁካታ ሲሰለቻቸው: አንድም በንጹሕና በተሸከፈ ልቡና ለፈጣሪያቸው መገዛትን ሲሹ ከከተማ ወጣ እያሉ ይኖሩ እንደ ነበር የታሪክ መዛግብት ያሳያሉ:: አኗኗራቸውም በቡድንም: በነጠላም ሊሆን ይችላል::

ዋናው ነገር ግን በጾምና በጸሎት መትጋታቸው ነው:: ይሕም ሲያያዝ እስከ ፫ኛው መቶ ክ/ዘመን ደረሰ:: በዚህ ዘመን ግን አባ ዻውሊ የሚባል አንድ ንጹሕ ክርስቲያን ይሕንን ሕይወት ወደ ሌላ ደረጃ ከፍ አደረገው:: ለ፹ ዓመታት ሰው ሳያይ ተጋድሎ 'የባሕታውያን አባት' ተባለ:: ደንብ ያለው ተባሕትዎም ጀመረ::

ይህ ከሆነ ከ፳ ዓመታት በኋላ ደግሞ አባ እንጦንስ የሚባሉ ደግ ክርስቲያን ይህንን ገዳማዊ ሕይወት በሌላ መንገድ አጣፈጡት:: በቅዱስ ሚካኤል አመንኳሽነት ገዳማዊ ሕይወት በምንኩስና ተቃኘ:: ስለዚህም አባ እንጦንስ የመነኮሳት አባት ተባሉ::

እርሳቸውም ሕይወቱን ለማስፋፋት ከተለያዩ አሕጉር ደቀ መዛሙርትን እየተቀበሉ አመንኩሰዋል:: ቅዱሳን የአባ እንጦንስ ልጆችም ወደየ ሃገራቸው ተመልሰው: ሕይወቱን በተግባር አሳይተው ገዳማዊነትን አስፋፍተዋል:: ከእነዚህም አንዱና ዋነኛው ዛሬ የምናከብረው ታላቁ ጻድቅ አባ አብላርዮስ ነው::

ቅዱስ አብላርዮስ ሶርያዊ ሲሆን የተወለደው በ፫ኛው መቶ ክ/ዘመን መጨረሻ አካባቢ ነው:: በቀደመ ሕይወቱ ክርስትናን ፈጽሞ የማያውቅ ሰው ነበር:: ለዚህ ምክንያቱ የወላጆቹ ኢ-አማንያን መሆን ነው::

ገና በልጅነቱ ወደ ት/ቤት ገብቶ የግሪክን ፍልስፍና: የዮናናውያንን ጥበብ ተምሮ ፈላስፋ ሁኗል:: በ፲፮ ዓመቱም በምድረ ሶርያ አሉ ከሚባሉ የጥበብ ሰዎች አንዱ ሆነ:: ቅዱሱ ማንበብና መጠየቅን አብዝቶ ይወድ ነበር::

የሚያነበው ነገር በሶርያ ቢያጣ በ፲፯ ዓመቱ ተጨማሪ ጥበብን [እውቀትን] ፍለጋ ወደ ግብጽ [እስክንድርያ] ወረደ:: በዚያ ግን ከሰማቸው ትምሕርቶች አንዱ ልቡን ገዛው:: በወቅቱ በግብጽ ላይ ፓትርያርክ የነበረው ቅዱስ እለ እስክንድሮስ ስለ ምድራዊው ያይደለ ስለ ሰማያዊው ጥበብ ሲያስተምር ሰምቶ ተገረመ::

ቅዱስ አብላርዮስ በዚህ ሰዓት የሰበሰባቸውን የፍልስፍና መጻሕፍት ጥሎ ቅዱሳት መጻሕፍትን ያነብ ጀመረ:: ቅዱስ እለ እስክንድሮስም የሚከብድበትን እያፍታታ ተረጐመለት:: በአጭር ጊዜም ክርስቲያን ሆኖ ተጠመቀ::

በዚያው ዓመትም ከከተማ ወጥቶ ወደ በርሃ ገባ:: ከአባ እንጦንስ የመጀመሪያ ደቀ መዛሙርት አንዱ ሆኖ መነኮሰ:: በዚያም በጾምና በጸሎት: በመታዘዝና በትሕትና ለዓመታት ኖረ:: ቀጥሎም ወሬ ነጋሪ መጥቶ ወላጆቹ ማረፋቸውን ነገረው::

በዚህ ጊዜ ቅዱስ አብላርዮስ ከአባ እንጦንስ ዘንድ ተባርኮ: ማኅበሩንም ተሰናብቶ ሶርያ ገባ:: የወላጆቹን ሃብትና ንብረት በሙሉ መጽውቶ ወደ ሶርያ በርሃ ወጣ:: በወቅቱ በአካባቢው ምንኩስና እየተነቃቃ ነበርና የቅዱሱ መምጣት ይበልጥ አጠናከረው::

ታላቁን ሊቅ ቅዱስ ኤዺፋንዮስን ጨምሮ በርካታ ደቀ መዛሙርትንም አፈራ:: በአካባቢውም ታላቅ መካሪ: ናዛዥ: አጽናኝ: መሪ ሆነ:: ከብዙ ተአምራቱ ባለፈ ሃብተ ትንቢት የተሰጠው አባት ነውና እጅግ ክቡር ነበር::

የገድሉን ነገርማ ማን ተናግሮ ይፈጽመዋል!

እርሱ ከዕለተ ሰንበት በቀር እህልን አይቀምስም:: ለዚያውም እሑድ በነግህ [ጧት] ትንሽ ሳር ነጭቶ ከመብላት በቀር ሌላ የሚበላው አልነበረውም:: እንዲህ ባለ የበርሃ ሕይወት ለ፷፫ ዓመታት ኖረ:: በዓለም የኖረበትን ፲፯ ዓመት ብንደምረው ፹ ይሆናል:: ቅዱሱ በተወለደ በ፹ ዓመቱ በ፬ኛው መቶ ክ/ዘመን በዚህች ቀን ዐርፏል::

አምላከ ቅዱስ አብላርዮስ ጥበቡን: ፈሊጡን: ሕይወቱን ይግለጽልን:: ከበረከቱም አይለየን::

🕊

[   † ጥቅምት ፳፬ [ 24 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት  ]

፩. ቅዱስ አብላርዮስ ገዳማዊ
፪. ቅድስት ጸበለ ማርያም
፫. ቅድስት አውስያ
፬. አባ ዻውሎስ ሊቀ ዻዻሳት

[  † ወርኀዊ የቅዱሳን በዓላት  ]

፩. ቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት
፪. ቅዱስ አጋቢጦስ [ጻድቅ ኤዺስቆዾስ]
፫. ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ
፬. ቅዱስ ቶማስ ዘመርዐስ
፭. ቅዱስ አባ ሙሴ ጸሊም [ኢትዮዽያዊ]
፮. "፳፬ቱ" ካኅናተ ሰማይ [ሱራፌል]
፯. ቅዱስ አብላርዮስ ታላቁ
፰. አቡነ ዘዮሐንስ ጻድቅ ዘክብራን

" ወንድሞች ሆይ ! መጠራታችሁን ተመልከቱ:: እንደ ሰው ጥበብ ጥበበኞች የሆኑ ብዙዎች: ኃይለኞች የሆኑ ብዙዎች: ባላባቶች የሆኑ ብዙዎች አልተጠሩም:: ነገር ግን እግዚአብሔር ጥበበኞችን እንዲያሳፍር የዓለምን ሞኝነት መረጠ . . . ሥጋን የለበሰ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት እንዳይመካ:: ነገር ግን:- የሚመካ በእግዚአብሔር ይመካ::" [፩ቆሮ.፩፥፳፮]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
2024/11/06 01:18:55
Back to Top
HTML Embed Code: