Telegram Web Link
🕊

[ † እንኩዋን ለጥንተ በዓለ ዸራቅሊጦስ [ መንፈስ ቅዱስ ] እና ለጻድቁ አባ ገዐርጊ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ † ]


†  🕊  በዓለ ዸራቅሊጦስ  🕊  †

✞ ከዚሕ በፊት እንደተመለከትነው የጌታችን ዓበይት በዓላቱ ፪ [2] ጊዜ [ማለትም ጥንተ በዓልና የቀመር በዓል ተብለው] ይከበራሉ:: ዛሬም ከ፩ ሺህ ፱ መቶ ፸፰ [1,978] ዓመታት በፊት አምላካችን መንፈስ ቅዱስ በቅዱሳን ሐዋርያት ላይ መውረዱን እናስባለን::

† ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ :-

ቸር አምላክ ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ ሲል

- ከልዑል ማዕርጉ ወርዶ:
- በማሕጸነ ድንግል ተጸንሶ:
- በኅቱም ድንግልና ተወልዶ:
- ከኃጢአት በቀር በግዕዘ ሕጻናት አድጐ:
- በ30 ዘመኑ ተጠምቆ:
- ቅድስት ሕግ ወንጌልን አስተምሮ:
- በፈቃዱ ሙቶ:
- በባሕርይ ስልጣኑ ተነስቶ:
- በአርባኛው ቀን ያርጋል::

ታዲያ ደቀ መዛሙርቱን የቅዱስ መንፈሱን ጸጋ ተስፋ እንዲያደርጉ ነግሯቸው ነበርና በተነሳ በ፶ [50] ኛው ቀን: በዐረገ በ፲ [10] ቀን ተስፋውን ፈጸመላቸው::

- እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዶሮ ጫጩቶቿን በክንፎቿ እንድትይዝ በአንድ ላይ ሰብስባ ለክብረ መንፈስ ቅዱስ አብቅታቸዋለች:: ፻፳ [120] ው ቤተሰብ ከጌታችን እናት ጋር ሲጸልዩ መንፈስ ቅዱስ በአውሎ ንፋስ አርአያ ወርዶ በአምሳለ እሳት አደረባቸው::

- ቅዱሳን ሐዋርያት ፈሪዎች የነበሩ ደፋሮች: አሮጌ ሕሊና የነበራቸው ሐዲሶች ሆኑ:: በአዕምሮ ጐለመሱ: ቁዋንቁዋ ተናገሩ: ምሥጢርም ተረጐሙ:: በቅጽበትም ብሉይ ከሐዲስ በልቡናቸው ውስጥ ተሞላ::

- ሐዋርያቱ ቅዱስ መንፈስን ተቀብለው ዓለምን በወንጌል ዕርፈ መስቀል አርሰዋል:: አልጫውን ዓለም ጨው ሆነው አጣፍጠዋል:: ሳይሳሱም አንገታቸውን ለሰይፍ ሰጥተዋል:: "ኪያሁ መንፈሰ ነሢኦሙ ለለአሐዱ: ሐዋርያት ለሰቢክ አሕጉራተ ዓለም ዖዱ: ሰማዕትኒ ለሕማም ነገዱ::" እንዳለ ደራሲ::

- በዚህ ቀን ፪ [ 2 ] ነገሮች በትኩረት ይነገራሉ :-

፩. የመንፈስ ቅዱስ የባሕርይ አምላክነት :-

- እርሱ ከአብ የሠረጸ: ቅድመ ዓለም የነበረ: በባሕርይ ስልጣኑ ከአብና ከወልድ ጋር እኩል የሆነ: የራሱ ፍጹም አካል ያለው ፍጹም አምላካችን ነውና::

፪. 🕊 ቅድስት ቤተ ክርስቲያን 🕊 :-

- አብ ያሰባት: ወልድ በደሙ የቀደሳት: መንፈስ ቅዱስ በጸጋው ያጸናት የክርስቲያኖች አማናዊት አንድነት: አንድም ቤት ናትና:: ዛሬ በጉባዔ ተመስርታለች::

🕊 አባ ገዐርጊ 🕊

በዚችም ዕለት የአባ አብርሃም ጓደኛ የከበረ አባ ገዐርጊ አረፈ።ይህም ቅዱስ የክርስቲያን ወገን ነው ወላጆቹ ደጎች ጻድቃን ናቸው።በአደገም ጊዜ የወላጆቹን ከብቶች የሚጠብቅ እረኛ ሆነ።ሁል ጊዜም የምንኵስና ልብስ ይለብስ ዘንድ በልቡ ይመኝ ነበር።

ዐሥራ አራት ዓመትም በሆነው ጊዜ የእግዚአብሔር ጸጋ አነሣሳችው በጎቹንም ትቶ ወደ አስቄጥስ ገዳም ሔደ። እየተጓዘም ሳለ ከሩቅ የብርሃን ምሰሶ አየ ወደ ወንዝ እስከ ደረሰ ድረስ ወደ ርሱ ሔደ ከዚህም በኃላ ያ የብርሃን ምሰሶ ከእርሱ ተሰወረ።

ያንንም ወንዝ በተሻገረ ጊዜ በሽማግሌ አምሳል ሰይጣን ተገለጠለትና ልጄ ሆይ ዕወቅ ስለ አንተ ልብሱን ቀዶ አባትህን አየሁት እርሱም ያዝናል ያለቅሳል ተመልሰህ የአባትህን ልብ ልትአጽናና ይገባሃል።የዱር አውሬ ነጥቆ የበላህ መስሎታልና አለው።

አባ ገዐርጊም ደንግጦ አንድ ሰዓት ያህል ቆመ ከዚህም በኃላ የከበረ ወንጌል ከእኔ ሊሆን አይገባውም ደቀ መዝሙሬም ሊሆን አይችልም ብሏል ብሎ አሰበ።ይህንንም በአለ ጊዜ ሰይጣን እንደ ጢስ ሆኖ ተበተነ።አባ ገዐርጊም ሰይጣን እንደ ሆነ አወቀ በዚያን ጊዜም ያ የብርሃን ምሰሶ ደግሞ ተገለጠለት የእግዚአብሔርም መልአክ በመነኵሴ አምሳል አብሮት ተጓዘ ቅዱሱም መልአኩን ተከተለው እርሱም ከአባ አርዮን ገዳም አደረሰው።አባ ገዐርጊም ከአንድ ጻድቅ ሰው መነኵሴ ጋራ በዚያ ዐሥራ አራት ዓመት ወጥሳይቀምስ ወይን ሳይጠጣ የአትክልት ፍሬም ቢሆን በዚህ በዐሥራ አራት ዓመት ያህል ከሚቀመጥ በቀር አልተኛም።

ተጋድሎውንም በጨመረ ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ተገለጠለትና እንዲህ አለው ሥጋህ እንዳይደክም በመካከለኛ ገድል ተጋደል ብሎሃል ጌታ።ከዚህም በኃላ ሊሠራው የሚገባውን ሥርዓት ሠራለት ።ሁል ጊዜም እስከሚመሽ እንዲጾም ትንሽም እንጀራን እንዲበላ ከአራት ሰዓት እስከ መንፈቀ ሌሊት ስለ ሥጋው ዕረፍት እንዲተኛ በቀረው ሌሊት እስቲነጋ ተግቶ እንዲጸልይ።

በዚህም ተጋድሎ ብዙ ዘመናት እየተጋደለ በኖረ ጊዜ በበረሀ ውስጥ ብቻውን ሊኖር ወዶ በጫካ ውስጥ እየተመላለሰ ሁለት ዓመት ኖረ።ከዚህም በኃላ ጌታ ተገለጾለት ወደ ቦታው እንዲመለስ አዘዘው።ያን ጊዜም አምላካዊት ኃይል ከከበሩ መክሲሞስና ደማቴዎስ ገዳም አደረሰችው እርሷም ለደብሩ አቅራቢያ ናት።

ወደ ደብሩም በተመለሰ ጊዜ በዚያን ወቅት አብርሃም ከዓለም ወደዚያ ገዳም መጥቶ ሁለቱም ተገናኙና በአንድነት ተስማምተው የአስቄጥስ ገዳም አበ ምኔት ወደ ሆነ ወደ አባ ዮሐንስ ደረሱ።እርሱም ቦታ ሰጥቷቸው በውስጡ ኖሩ ያ ቦታም እስከ ዛሬ ታውቆ ይኖራል ።

ያቺም ዋሻ በግቢግ ትባላለች የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዐለት የሆነ ጣሪያዋን ሠንጥቆ ወደ እነርሱ የወረዳበት ናት ።እነርሱም ሰገዱለት ሰላምታም ሰጥቷቸው አጽናንቷቸው ከእርሳቸው ዘንድ ዐረገ።በዚያችም ጌታችን በወረደበት መስኮት ብርሃንን አዩ እስከ ዛሬም የተከፈተች ሁና ትኖራለች።

እሊህ ቅድሳንም ለመነኰሰኘሳት የሚሆን ብዙ ድርሳናትንና ብዙ ተግሣጻትን ደረሱ።ለአባቶቹ የሚታዘዘውንና የሚገዛውን አመሰገኑት።ከዚህም በኋላ አባ አብርሃም ጥር ሁለት ቀን አረፈ። ከእርሱ በኋላም የከበረ አባ ገዐርጊ በዚች በግንቦት ወር በዐሥራ ስምንት ቀን አረፈ።መላ ዕድሜውም ሰባ ሁለት ዓመት ሆነ።በዓለም ዐሥራ አራት ዓመት በምንኩስና ኃምሳ ስምንት ዓመት ነው። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትሁን አሜን።

በዚችም ዕለት የሰማዕት ሲኖዳ መታሰቢያው ነው በረከቱ ከእኛ ጋራ ለዘላለም ትኑር አሜን።

አምላከ ገዐርጊ ከቅዱስ መንፈሱ ጸጋ ለኃጥአን ባሮቹ ያድለን::

[ † ግንቦት ፲፰ [ 18 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. ቅዱሳን ሐዋርያት ወአርድእት
፪. አባ ገዐርጊ ገዳማዊ
፫. ቅዱስ ሲኖዳ ሰማዕት

[ †  ወርሐዊ በዓላት ]

፩. ቅዱስ ፊልዾስ ሐዋርያ
፪. አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ሰባኬ ሃይማኖት [ረባን]
፫. አቡነ አኖሬዎስ ዘደብረ ጽጋጋ
፬. ማር ያዕቆብ ግብፃዊ

" በዓለ ሃምሳም የተባለው ቀን በደረሰ ጊዜ ሁሉም በአንድ ልብ ሆነው አብረው ሳሉ ድንገት እንደሚነጥቅ አውሎ ነፋስ ከሰማይ ድምጽ መጣ:: ተቀምጠው የነበሩበትንም ቤት ሁሉ ሞላው:: እንደ እሳትም የተከፋፈሉ ልሳኖች ታዩአቸው:: በእያንዳንዳቸውም ላይ ተቀመጡባቸው:: በሁሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው:: መንፈስም ይናገሩ ዘንድ እንደሰጣቸው በሌላ ልሳኖች ይናገሩ ጀመር :: " [ሐዋ.፪፥፩] (2:1-4)

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
ፀሐይ ብርሃን ካልሰጠች ፀሐይ አትባልም፤ ብርሃን ተፈጥሮዋ አይደለምና፡፡ እንስሳት ካልተነፈሱ እንስሳት አይባሉም፤ መተንፈስ ተፈጥሮአቸው ነውና፡፡ ዓሣ ከውኃ ከወጣ ሕይወት ያለው ዓሣ መኾኑ ይቀርና ይሞታል፡፡ #አንድ_ክርስቲያንም እውነተኛ ክርስቲያን የሚባለው፡-

1.
#ሲጸልይ_ነው፡፡ ክርስቲያን ማለት በወልድ ውሉድ በክርስቶስ ክርስቲያን በመንፈስ ቅዱስም መንፈሳዊ መባል ነውና፡፡ ልጅ ከኾኑ ደግሞ አባትን ማናገር ክርስቲያናዊ ተፈጥሮ ነውና፡፡

2.
#ሲያመሰግን_ነው፡፡ ክርስቲያን ማለት እግዚአብሔር ፈጣሬ ዓለማት ነው ብሎ ማመን ነውና፡፡ ስለዚህ ለአንድ ክርስቲያን የሰማይና የምድር ውበት እየተመለከተ እግዚአብሔርን ማመስገኑ ክርስቲያናዊ ተፈጥሮው ነው፡፡

3.
#ሲመጸውት_ነው፡፡ ክርስቲያን ማለት ሀብት ኹሉ ከእግዚአብሔር እንደ ኾነ መመስከር ነውና፡፡ ስለዚህ ራስን እንደ መልእክተኛ አድርጎ በመቁጠር ያለውን ለሌላው ማካፈል ክርስቲያናዊ ተፈጥሮው ነውና፡፡

4.
#ቅዱሳት_መጻሕፍትን_ሲያነብ_ነው፡፡ ክርስቲያን ማለት በመንፈስ ቅዱስ ሀብት ደስ የሚሰኝ ነውና፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ መንፈስ ቅዱስ በቅዱሳት መጻሕፍት በኩል ሲናገር መስማት ለአንድ ክርስቲያን ክርስቲያናዊ ተፈጥሮው ነውና፡፡

#በቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ

#መልካም_ዕለተ_ሰንበት🙏

አጫጭር ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶች
•➢ 👇 ለማግኘት // 👇

@Enatachn_mareyam
@Enatachn_mareyam
🕊

✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞

†  እንኳን አደረሳችሁ  †

[ †  ግንቦት ፲፱ [ 19 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]


†  🕊  አባ ዓቢየ እግዚእ  🕊  †

ጐንደር ከተማ ነዋሪ ከሆኑ: ወይም ከተማዋን የሚያውቁዋት ከሆነ አንድ ጥያቄ ልጠይቅዎ::[እንደ ወትሮው ሁሉ] ከተማዋ ውስጥ ጅብና እባብን የመሠሉ አራዊት ነዋሪውን ሲገድሉ: ወይም ሲያቆስሉ ተመልክተው: ካልሆነም በታሪክ ሰምተው ያውቃሉ?

መልስዎ "በጭራሽ አላውቅም" እንደሚሆን እገምታለሁ:: [ምክንያቱም ሆኖ አያውቅማ!]

ነገሬን እንዲረዱኝ ሌሎች የሃገራችን ዋና ዋና ከተሞችን ልብ ይበሉልኝ:: እንኳን በሌሊት በቀንም አራዊቱ አይጠፉባቸውም::

"ታዲያ ጐንደር ከተማ ውስጥ ጅብ የማይገባው: እባብና ጊንጥ ሰው የማይገድለው ግን ለምን?" ካሉ በጻድቁ በአባ ዓቢየ እግዚእ ቃል ኪዳን ምክንያት ነው:: [ሁሉም የሃገራችን ከተሞች የተባረኩ መሆናቸውን ሳንዘነጋ ማለት ነው]

ጥንተ ነገሩስ እንደ ምን ነው ቢሉ :-

አባ ዓቢየ እግዚእ የተወለዱት በ፲፬ [14]ኛው መቶ ክ/ዘመን ትግራይ ተንቤን [መረታ] ውስጥ ነው:: የተባረኩ ወላጆቻቸው ያፍቅረነ እግዚእና ጽርሐ ቅድሳት ይባላሉ:: አጥምቀው 'ዓቢየ እግዚእ' ሲሉ ስም ያወጡላቸው የወቅቱ ዻዻስ ሰላማ መተርጉመ መጻሕፍት ናቸው:: ትርጉሙም "በጌታ ዘንድ ታላቅ ሰው" ማለት ነው::

ዓቢየ እግዚእ በሕጻንነታቸው ሌሊት ሌሊት ባሕር ውስጥ ሰጥመው ሲጸልዩ አድረው ቀን ቀን እየተማሩ ብሉይ ከሐዲስ ጠነቀቁ:: ገና በወጣትነታቸው ወደ ታላቁ መነኮስ አቡነ መድኃኒነ እግዚእ ደብረ በንኮል ሔደው መንኩሰዋል::

በገዳሙ በጾም: በጸሎትና በስግደት ተወስነው ከኖሩ በኋላ ወደ ዋልድባ ሔደው የተሰወረች ቤተ ክርስቲያን አግኝተዋል:: በጊዜው በ፵ [40] ቀን አንዲት ቅጠል ብቻ ለቁመተ ሥጋ ይበሉ ነበር::

ከዚያም ወደ ሃገራቸው ተንቤን ተመልሰው ዛሬም ድረስ ድንቅ ሆኖ የሚታየውን ገዳም መሥርተው ብዙ መናንያንን አፍርተዋል:: ዓቢየ እግዚእ ገዳማዊና ጻድቅ ብቻ ሳይሆን ሐዋርያዊ አባትም ነበሩ:: ከትግራይ እስከ ደንቢያ ደግሞ ሃገረ ስብከታቸው ነው::

አንድ ጊዜ ደቀ መዛሙርትን አስከትለው ለስብከት ሲንቀሳቀሱ ተከዜ ወንዝ አካባቢ ደረሱ:: ቀኑ ነሐሴ ፲ [10] ነውና ተከዜ እስከ ገደፉ ሞልቶ ለ፫ [3] ቀናት ባለመጉደሉ ከ፩ ሺህ [1,000] በላይ ሰዎች ሲያለቅሱ ደረሱ:: ጻድቁ ባካባቢው የነበሩት ኢ- አማንያን [አሕዛብ] ቢሆኑም ራርተዋልና "አምላከ ሙሴ" ብለው ጸልየው ወደ ጥልቁ ውስጥ ገቡ::

ቅዱስ ሚካኤል አብሯቸው ነበርና ተከዜ ግራና ቀኝ ተከፍሎ መሃሉ የብስ ሆነ:: ይሕን ድንቅ ያዩ ከ፩ ሺህ [1,000] በላይ አሕዛብም አምነው በጻድቁ እጅ ተጠምቀዋል:: ይሕም ዘወትር ነሐሴ ፲ [10] ቀን በቤተ ክርስቲያናቸው [ጐንደር] ይከበራል::

ከዚያም እያስተማሩ ጐንደር ደረሱ:: ያኔ ጐንደር በቀሃና አንገረብ ወንዞች የታጠረች አንዲት መንደር ነበረች:: ጻድቁ ቀን ቀን እየሰበኩ ማታ ዛሬ ቤተ ክርስቲያናቸው የታነጸበት ሥፍራ ላይ ሲጸልዩ ያድሩ ነበር::

በዚያ ዘመን ጐንደር ውስጥ ጅብ: እባብና መሠል አራዊት ገብተው ሕዝቡን ጨረሱት:: ይሕንን የተመለከቱት አባ ዓቢየ እግዚእ ወደ እግዚአብሔር አለቀሱ:: በፍጹም ልባቸውም ስለ ሕዝቡ ለመኑ::

የለመኑትን የማይነሳ ጌታ ወደ ጻድቁ ቀርቦ "በስምሕ የተማጸኑ: በቃል ኪዳንህ ያመኑ: በምድር አራዊት አይሠለጥኑባቸውም:: በሰማይም እሳትን አያዩም:: ጐንደርንም አራዊት ገብተው ሰውን አይጐዱም::" ብሏቸው አርጓል::

ጻድቁም የወንጌል አገልግሎታቸውን ፈጽመው ወደ ገዳማቸው ተንቤን ተመልሰዋል:: ይሔው እኛ ምን ብንከፋ: ጻድቁንም ብንረሳቸው እግዚአብሔር ግን ዛሬም በጻድቁ ምልጃ ከተማዋን ጠብቆ ይኖራል:: ነገን ደግሞ እርሱ ያውቃል:: ዛሬ ቤተ ክርስቲያኑ የታነጸበት ቦታ [ጎንደር ቀበሌ 09 ኪዳነ ምሕረት] ጻድቁ የጸለዩበት ቦታ ነው:: እንኳን በወርሃዊ በዓላቸው በ፲፱ [19] ይቅርና በዓመታዊ በዓላቸው [ግንቦት ፲፱ [19] ለንግስ የሚመጣው ሰው ቁጥር ያስተዛዝባል::

አባ ዓቢየ እግዚእ በገዳማቸው ተንቤን ለብዙ ዘመናት በቅድስና ኑረው: ፫ [3] ሙታንን አስነስተው: ብዙ ድውያንን ፈውሰው: ብሔረ ብጹዓንን ጎብኝተው: የድኅነት ቃል ኪዳንም ተቀብለው: በ፻፵ [140] ዓመታቸው ግንቦት ፲፱ [19] ቀን አርፈዋል:: የጻድቁ ክብር ለሁሉ ነውና እባካችሁ እናስባቸው::

"ተአምሪሁ ለጻድቅ አቡነ ዓቢየ እግዚእ - - - ጸሎቱ ወበረከቱ የሃሉ ምስለ ኩልነ ሕዝበ ክርስቲያን ለዓለመ ዓለም:: አሜን::"

" ከበዙ ተአምራቱ አንዱን "

ጻድቁ አባ ዓቢየ እግዚእ በገዳማቸው ተንቤን
[መረታ] ሳሉ አንዲት መበለት መጥታ "አባቴ! የምጠጣውን ጸበል ባርከህ ስጠኝ?" አለቻቸው:: ጻድቁም በውሃው ላይ ጸሎትን አድርሰው : በመስቀላቸው ባርከው ሰጧት::

ወደ ባልንጀራዋ ስትደርስ ግን ሐሳቧን ቀየረችና "ልጠጣው" ብላ የተቀበለችውን ማይ [ጸበል] ልትጠመቅበት [ልትጸበልበት] ወሰነች:: ባልንጀራዋንም "በላዬ ላይ አፍሺልኝ" ስትል አዘዘቻት::

ባልንጀራዋም "እሺ" ብላ ልታፈስላት [ልትጸብላት] በፋጋ [ግማሽ ቅል] ያለውን ጸበል አነሳች:: ልታፈሰው ስትዘቀዝቀው ግን ከሆነው ነገር የተነሳ ፪ [2] ቱም ደነገጡ:: ጸበሉ የረጋ ደም ወደ መሆን በቅጽበት ተለውጧልና::

ፍጹም ፍርሃት የወደቀባቸው ሴቶቹ እየተሯሯጡ ወደ አባ ዓቢየ እግዚእ በዓት ደረሱ:: ከውጭ ሆነውም "አባ! አባ! የሰጠኸን ጸበልኮ የረጋ ደም ሆነ" አሏቸው:: ጻድቁም እንዳላዋቂ "ምን አጠፋችሁ?" ሲሉ ጠየቁ::

"አባታችን! ምንም አላጠፋንም:: ብቻ አፍሺልኝ ብየ ስሰጣት እንዲህ ሆነ" ስትል አንዷ መለሰች:: ጻድቁ ግን በየውሃት "ልጆቼ! ሁሌም : 'ምንም አላጠፋንም' አይባልም:: ሰው ሆኖ የማይበድል የለምና::

+ . . . አንቺም ልጄ ! እኔን ያልሺኝ 'የምጠጣው ጸበል ስጠኝ' ነበር:: ግን ልትጸበይበት ወደድሽ:: ስሕተትሽ ከዚህ ይጀምራል:: [የቅዳሴ ጸበል ለመጸበል አይሆንምና]
¤በዚያ ላይ "አልቦ ዓቢይ ኃጢአት ከመ ወልጦ ቃል . . . ከውሸት በላይ ከባድ ኃጢአት የለም::" [ዮሐ.፰፥፵፬]

+ . . . በተጨማሪ ደግሞ ያለ ስልጣኗ እህትሽን 'አጥምቂኝ' አልሻት:: ስለነዚህ ነገሮች ጸበሉ ተለውጦባቹሃል" ብለው ወደ ጸበሉ በመስቀል አማተቡ:: "እፍ" ሲሉትም የረጋ ደም የነበረው ማይ ወደ ጸበልነቱ ተመለሰ:: ይህንን ያዩ ሴቶቹ በግንባራቸው ተደፍተው ለጻድቁ ሰገዱ::

ጸሎቱ ወበረከቱ የሃሉ ምስለ ኩልነ ሕዝበ ክርስቲያን ለዓለመ ዓለም:: አሜን::
አምላካችን በወዳጆቹ ምልጃ ሃገራችንን ከክፉው ሁሉ ይሠውርልን::

[  †  ግንቦት ፲፱ [ 19 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት   ]

፩. አባ ዓቢየ እግዚእ ጻድቅ [ ኢትዮዽያዊ ]
፪. አቡነ ዮሴፍ ብርሃነ ዓለም [ የ፲፪ [ 12 ]ቱ ሐዋርያት መቃብር ከጌታ የተገለጠላቸው ኢትዮዽያዊ ]
፫. አቡነ ብስጣውሮስ ዘሐይቅ እስጢፋኖስ [ ኢትዮዽያዊ ]
፬. ቅዱስ ኤስድሮስ ሰማዕት ታላቁ [ ፯ [7 ] ጊዜ ሙቶ የተነሳ ]
፭. "805,007" ሰማዕታት [ በአንድ ቀን ብቻ የተገደሉ ]
፮. አባ ይስሐቅ ገዳማዊ

[   †  ወርኃዊ በዓላት    ]

፩ ፡ ቅዱስ ገብርኤል ሊቀ መላእክት
፪ ፡ ቅዱስ ኤስድሮስ ሰማዕት
፫ ፡ ቅዱስ ይምርሐነ ክርስቶስ
፬ ፡ አባ ስነ ኢየሱስ ጻድቅ

" በተኩላና በእባብ ላይ ትጫማለህ:: አንበሳውንና ዘንዶውን ትረግጣለህ:: በእኔ ተማምኗልና አስጥለዋለሁ:: ስሜንም አውቁዋልና እጋርደዋለሁ:: ይጠራኛል እመልስለትማለሁ:: በመከራውም ጊዜ ከእርሱ ጋር እሆናለሁ:: አድነዋለሁ: አከብረውማለሁ:: ረጅም እድሜን አጠግበዋለሁ:: ማዳኔንም አሳየዋለሁ:: " [መዝ.፺፥፲፫]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
🕊

[ † እንኳን ለመናኙ ንጉሥ ቅዱስ አፄ ካሌብ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። † ]

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ! †


🕊 መናኙ ንጉሥ ካሌብ 🕊

† ቅዱሱን ንጉሥ አፄ ካሌብን በዓለም ያሉ አብያተ ክርስቲያናት በትልቁ ያከብሩታል:: ኢትዮጵያ ውስጥ ግን አክሱም አካባቢ ካልሆነ ከነ ስም አጠራሩ እንኳ እየተዘነጋ ይመስለኛል::

ነገር ግን ውለታው : ምናኔውና ቅድስናው የማይረሳ ነውና እንኳን በእምነት የሚመስሉን ይቅርና የማይመስሉን ምሥራቅ ኦርቶዶክሶችና ካቶሊኮች ዓመታዊ በዓሉን በወርኀ ጥቅምት ያከብራሉ::

ከአክሱም ነገሥታት በኃይሉም ሆነ በሃይማኖታዊ ቅድስናው አፄ ካሌብ ዋናው ነው:: ቅዱሱ የነገሠው በ፬፻፹፭ [485] ዓ/ም አካባቢ ሲሆን እስከ ፭፻፲፭ [515] ዓ/ም ድረስ በዙፋኑ ላይ ቆይቷል:: ከመልካም ትዳሩ አፄ ገብረ መስቀልን ጨምሮ ልጆችን ወልዷል::

† ስለ ቅዱስ አፄ ካሌብ እስኪ እነዚህን ነገሮች ብቻ እናንሳ :-

፩. በንግሥና ዙፋን ከመቀመጡ በፊት የሚገባውን መንፈሳዊ ትምሕርት ጠንቅቆ ተምሯል::

፪. ሃይማኖቱ የጠራና እጅግ የሚደነቅ ነበር:: በእርሱ ዘመን ሃይማኖት ለነገሥታቱ የፖለቲካ ማስፈጸሚያ ነበር:: እርሱ ግን እግዚአብሔርን በፍጹም ልቡ አምልኳል::

፫. ለእመቤታችንና ለቸር ልጇ የነበረው ጥልቅ ፍቅር የተገለጠና የሚያስቀና ነበር::

፬. ገና በዙፋኑ ሳለ ጸሎትን ያዘወትር ነበር::

፭. ዛሬም ድረስ ሁሉም ክርስቲያኖች የማይረሱትን መንፈሳዊ ቅንዓትን አሳይቷል:: ይሕስ እንደ ምን ነው ቢሉ :-

- በወቅቱ ዐመፀኛው የአይሁድ መሪ ፊንሐስ በሃገረ ናግራን [የአሁኗ የመን] ውስጥ የነበሩ ክርስቲያኖችን ክርስቶስን ካዱ በሚል ጨፈጨፋቸው::

ከተማዋንም ለአርባ ቀናት በእሳት አነደዳት:: ዜናው በመላው ዓለም ሲሰማ በርካቶቹ ቢያዝኑም የተረፉትን ለመታደግ የሞከረ አልነበረም::

ቅዱስ አፄ ካሌብ ግን የሆነውን ሲሰማ ወደ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ገብቶ በግንባሩ ሰገደ:: ወደ ፈጣሪም ጸለየ :- "ጌታዬ ሆይ ! የክርስቲያኖችን ደም እመልስ ዘንድ እርዳኝ? እኔ በጦሬ ብዛት አልመካም:: እኔ ተሸንፌ ክርስትና ከሚናቅ እዚሁ ግደለኝ" ብሎ በበርሃ ላሉ መነኮሳት እንዲጸልዩ ላከባቸው::

ጊዜ ሳያጠፋ በመርከብና በፈረስ : በበቅሎና በግመል ናግራን [የመን] ደረሰ:: ፊንሐስን ገድሎ ሠራዊቱንም ማርኮ ክርስቲያኖችን ነጻ አወጣ:: ደምና እንባቸውንም አበሰ:: አብያተ መቅደሶችን አንጾላቸው ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰ::

ወዲያው እንደተመለሰ ወደ አክሱም ጽዮን ገብቶ "ጌታየ ኢየሱስ ክርስቶስ ስላደረክልኝ የምሰጥህ ሰውነቴን እንጂ ሐብቴን አይደለም" ብሎ መንግስቱን ለልጁ ገብረ መስቀል አውርሶ ከዙፋኑ ወጣ:: የወርቅ አክሊሉን ወደ ኢየሩሳሌም ልኮ እርሱ በአባ ጰንጠሌዎን እጅ መንኩሶ መነነ::
[በፎቶው ላይ የምታዩት አፄ ቅዱስ ካሌብ የመነነበት : አክሱም አካባቢ የሚገኝ የአባ ጰንጠሌዎን ገዳም ነው]

ከዚሕች ዓለም ከአንዲት ረዋት [ኩባያ] : ከአንዲት ሰሌንና ከአንዲት ቀሚስ በቀር የወሰደው አልነበረም:: ከዚያም በበዓቱ ውስጥ በጾምና በጸሎት ተወስኖ አንድም ሰው ሳያይ በሰባ ዓመቱ [በ፭፻፳፱ [529] ዓ/ም] ዐርፏል:: ጌታችንም በሰማይ ክብርን አጐናጽፎታል::

† ለቅዱስ አፄ ካሌብ የተለመነ አምላክ ለእኛም ይለመነን:: በጻድቁም ጸሎት ከመከራ ይሠውረን::

[ † ግንቦት ፳ [ 20 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. ቅዱስ አፄ ካሌብ [ መናኙ ንጉሠ ኢትዮጵያ ]
፪. ቅዱስ አሞንዮስ ገዳማዊ [ ታላቁ አሞኒ ዘቶና ]
፫. ቅድስት ሳድዥ የዋሂት
፬. አባ ሖር ጻድቅ
፭. አባ ዳርማ ገዳማዊ
፮. ቅዱስ ዘካርያስ አንጾኪያዊ
፯. አባ በትረ ወንጌል ዘደብረ ሊባኖስ

[ † ወርኀዊ በዓላት ]

፩. ቅዱስ ቴዎድሮስ ሊቀ ሠራዊት [ ሰማዕት ]
፪. ቅዱስ ዮሐንስ ሐፂር
፫. ቅዱስ አክሎግ ቀሲስ

" አቤቱ በኃይልህ ንጉሥ ደስ ይለዋል:: በማዳንህ እጅግ ሐሴትን ያደርጋል:: የልቡን ፈቃድ ሰጠኸው:: የከንፈሩንም ልመና አልከለከልኸውም:: በበጐ በረከት ደርሰህለታልና:: ከከበረ ዕንቁ የሆነ ዘውድን በራሱ ላይ አኖርህ:: ሕይወትን ለመነህ ሰጠኸውም:: ለረጅም ዘመን ለዘላለሙ:: በማዳንህ ክብሩ ታላቅ ነው:: " † [መዝ. ፳፥፩-፭]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
መልእክተ ቅዱስ ፓትርያርክ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
- ብፁዕ አቡነ አብርሃም
የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ
የሰሜን ጎጃምና የባሕር ዳር አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
- ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት!
እግዚአብሔር አምላካችን በቤተ ክርስቲያን ላይ በየጊዜው የሚደርሰውን ፈተና በማስቻል ለዚህ ሲኖዶሳዊ ምልአተ ጉባኤ እንኳን በሰላም አደረሰን!

‹‹አስተብቊዓክሙ አኃዊነ በስሙ ለእግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ ከመ ትበሉ ኵልክሙ አሐደ ቃለ ወአሐደ ነገረ ወትኩኑ ፍጹማነ ወኢትትፋለጡ ወሀልዉ በአሐዱ ምክር ወበአሐዱ ልብ፤ ወንድሞች ሆይ ሁላችሁ አንድ ንግግር እንድትናገሩ፣ በአንድ ልብና በአንድ ሐሳብም የተባበራችሁ እንድትሆኑ እንጂ መለያየት በመካከላችሁ እንዳይሆን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እለምናችኋለሁ›› (፩ቆሮ ፩፥፲)፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን መልእክት ለቆሮንቶስ ሰዎች ለመጻፍ ሲያስብ አንድ ዓቢይ ምክንያት እንዳለው ከመልእክቱ ይዘት መረዳት ይቻላል፤ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች አንድነትንና ሰላምን ፍቅርንና መተባበርን ከምትሰብከው ወንጌለ መንግሥተ እግዚአብሔር ወጥተው ብዙ ርቀት ሂደዋል፤ አንድነቱ፣ ኅብረቱ መረዳዳቱ መተጋገዙና መተባበሩ ከመካከላቸው ጠፍቶአል፤ ሌላው ቀርቶ ቅዱስ ቊርባንን ለመቀበል በሚሰበሰቡበት ጊዜ እንኳ የሀብታምና የድሀ የሚል ክፍፍል ተፈጥሮ ቤተ ክርስቲያኗን አደጋ ላይ ጥሎአል፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን እና ይህንን የመሳሰለ ፈተና በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ሥር እየሰደደ መምጣቱን በእጅጉ አሳስቦታል፤ ይህ የሰላምና የአንድነት ጠንቅ የሆነው የመለያየት አዝማሚያ በጣም ሰፍቶ ቤተ ክርስቲያንን ከማፍረሱ በፊት በትምህርት በምክርና በተግሣጽ ማረም እንዳለበት ቅዱስ ጳውሎስ ተገንዝቦአል፤ እሱ ራሱም በአካል በመካከላቸው ተገኝቶ ሊያስተካክላቸው ፈቃደኛ ነበረ፤ ነገር ግን እሱ በዚህ ጊዜ በሮም ውስጥ እስር ቤት ላይ ስለነበረ አልቻለም፤ የነበረው አማራጭ በጽሑፍ ማስተማርና መምከር ነውና፤ ይህንን መልእክት ጽፎላቸዋል፡፡

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት!

ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ዘላቂው የቤተ ክርስቲያን ፈተና ሲነግረን ‹‹ወበዓለምሰ ሀለወክሙ ትርከቡ ሕማመ፤ በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ›› እንዳለው ቤተ ክርስቲያን ከፈተና ተለይታ አታውቅም፤ ፈተናውም ከተወሰነ አቅጣጫ ብቻ የሚመጣ ሳይሆን ከብዙ አቅጣጫ ይከባታል፤ የቤተ ክርስቲያን መከራ ከውጭ ብቻም አይደለም ከውስጥም እንጂ፤ ከባዕድ ብቻም አይደለም ከወዳጅም እንጂ፣ የወዳጅ ፈታኝ እንደሚብስም ታውቆ ያደረ ነገር ነው፤ ባዕዳውያን አይሁድ ጌታን ይዘው የገደሉ የውስጥ ሰው የሆነው ይሁዳ በሰጣቸው ምልክት ነው፡፡

ከዚህ አንጻር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአሁኑ ጊዜ በከባድ ፈተና ውስጥ እያለፈች ትገኛለች፤ እንደተነገረው የውጭው ፈተና ባይቀርላትም ከሱ በላይ ግን በውስጧ የሚነሡ ፈተናዎች ተልእኮዋን በአግባቡ እንዳትወጣ ዕንቅፋት ሆነውባታል፤ ከጥንት ጀምሮ የነበረ፣ በእግዚአብሔር ቃል የተቃኘ፣ የጸሊአ ሢመትና የጸሊአ ንዋይ መንፈሳዊ ባህሏ ተዘንግቶአል፤ በምትኩም ፍቅረ ሢመትና ፍቅረ ንዋይ ነግሦአል፤ መለያየትና መነቃቀፍ እየሰፉ መጥተዋል፣ ሃይማኖታችንንና ባህላችንን የማይወክሉ ኃይለ ቃላት፣ ኃላፊነት በጐደለው አገላለጽ እየተሰነዘሩ በጎቻችንን አስበርግገዋል፤ ድርጊቶቹ በበጎቻችን ዘንድ የነበረንን ተሰሚነትና ተደማጭነት ሊቀንሱብን እየተንደረደሩ ነው፡፡

እነዚህና እነዚህ የመሳሰሉ ክሥተቶች በውስጣችን ሥር በሰደዱ ቁጥር ጉዳትን እያስከተሉ ነው፤ ሰዎች ከኦርቶዶክሳዊ ቀኖና እና ሥርዓት ባፈነገጠ መልኩ ራስን በራስ የመሾም አባዜ እየተለማመዱ ነው፤ እሽቅድምድሙም በዚህ ዙሪያ አይሎአል፤ በአጠቃላይ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖችን የፈተነ መለያየት በቤተ ክርስቲያናችንም ብቅ ጥልቅ እያለ እየፈተነን ነው፤ የፈተናው መንሥኤ ውጫዊ ሳንካ ባይጠፋበትም የውስጣችን ሰዎች ለሱ ምቹ ሆነው መገኘታቸው አልቀረም፤ በመሆኑም ቤተ ክርስቲያናችን በዚህ ፈተና የማይናቅ ጉዳት እየደረሰባት ነው፤ ከሁሉ በላይ ደግሞ ሰላምዋና አንድነቷ ጥያቄ ላይ ወድቆአል፡፡

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት!

በሀብተ መንፈስ ቅዱስ ወልደን፣ በሀብተ ክህነት ሹመን፣ በመዐርገ ምንኩስና አልቀን በቤተ ክርስቲያን ኃላፊነት ያስቀመጥናቸው ሰዎች በውኑ ‹‹እርስ በርስዋ የምትለያይ ቤት… የሚለውን አምላካዊ አስተምህሮ እንዴት ዘነጉት? ወይስ ድሮውንም ሳያውቁት ነው ኃላፊነቱ የተሰጣቸው? ወይስ ደግሞ ሆን ብለው ቃሉን ቸል ብለውታል? ሁሉም ውሉደ ክህነት ለዚህ መልስ መስጠት ይጠበቅበታል፤ በመልካም አስተዳደርና በቂም በቀል እያሳበቡ ቤተ ክርስቲያንን ለማዳከም ብሎም ለማፍረስ መሮጥ በማናቸውም መመዘኛ ሚዛን አይደፋም፤ ውሃም አያነሣም፡፡
ችግር ሲኖር በመወያየት በጥበብና በሕግ ማረም እንጂ የጋራ ችግርን ለተወሰነ አካል በመለጠፍና እሱን ብቻ ተጠያቂ በማድረግ ንጹህ መሆን አይቻልም፤ ሁሉም ጓዳው ቢፈተሽ ከዚህ የተለየ ነገር አይገኝም፤ አንድነትንና ሰላምን ግቡ ያደረገ ግምገማን መገምገም፣ መወያየትና መመካከር፣ ሕግንና ሥርዓትን ማእከል አድርጎ መሥራት ተመራጭ መፍትሔ ነው፡፡

እንደሚታወቀው ባለፉት ዓመታት አስከፊ በደል ተፈጽሞአል አሁንም አልቆመም፤ ይሁን እንጂ በደል ዛሬ ብቻ የተጀመረ አድርገን አናስብ፤ ይብዛም ይነስ በደል ፊትም ነበረ፤ ዛሬም አለ፤ ነገም የተለየ ነገር ይኖራል ተብሎ አይታሰብም፡፡

በደልን በካሣና በዕርቅ በይቅርታና በምሕረት መዝጋት፣ ተመሳሳይ በደል እንዳይፈጸም አስተማማኝ የሆነ ተቅዋማዊ ሥርዓትን ማበጀት መልካም ፈሊጥ ይሆናል፤ በደልንና ጥፋትን ምክንያት አድርገን እስከ ዘለቄታው መለያየትን መምረጥ ግን ራስን በራስ መጉዳት ይሆናል፤ ስለዚህ ይህ ቅዱስ ጉባኤ በዚህ ዙሪያ በስፋትና በጥልቀት በመወያየት ሁሉንም ሊያስማማ በሚችል መልኩ ወደ ሰላምና ዕርቅ ሊያደርስ የሚችል ስራ መስራት ይኖርበታል፡፡

ብፀዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖስ አባላት!

የማኅበረ ሰባችን ችግር በቤተ ክርስቲያን ብቻ የተወሰነ አይደለም፤ በሀገር ደረጃ እየቀጠለ ያለው አለመግባባትም ለጠቅላላ ማኅበረ ሰባችን ፈተና ከሆነ ውሎ አድሮአል፤ የቤተ ክርስቲያናችን ፈተና ምንጭ ከሆኑትም አንዱና ዕድል ሰጩ ይህ ሀገራዊ አለመግባባት ነው፤ በዚህ አለመግባባት ምክንያት ገዳማውያን መነኮሳት፤ መምህራን ካህናት ምእመናን አብያተ ክርስቲያናት ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ በሰላም ወጥቶ መግባትም አጠራጣሪ ሆኖአል፤ ይህንን ችግር ለመፍታት የሚደረግ ጥረትም ጎልቶ አይታይም፡፡
በመሆኑም ይህ ክሥተት እውን ኢትዮጵያውያን የራሳችንን ችግር በራሳችን መፍታት የማንችል ሰዎች ነን ወይ? ለኛስ ከኛ የበለጠ ማን ይመጣልናል? የሚለውን ጥያቄ ልናነሣ ግድ ነው፤ ስለዚህ ለሀገር ህልውናና ድኅነት የሚበጅ ነገር እንዲመጣ ቤተ ክርስቲያን ባላት ሃይማኖታዊና ሰብአዊ ኃላፊነት ጠንክራ መስራት ይጠበቅባታል፤ ከዚህ በተረፈ ይህ ዓቢይ ጉባኤ ወሳኝና ወቅታዊ እንዲሁም ሐዋርያዊና ቀኖናዊ በሆኑ የቤተ ክርስቲያናችን ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ለቤተ ክርስቲያንና ለሀገር የሚበጁ ነገሮችን በማየት ጠቃሚ ውሳኔዎችን እንዲያሳልፍ በዚህ አጋጣሚ ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡

በመጨረሻም
ዓመታዊው የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በዛሬው ዕለት በእግዚአብሔር ፈቃድ የተጀመረ መሆኑን በመንፈስ ቅዱስ ስም እናበስራለን ፡፡

መልካም ጉባኤ ያደርግልን!
እግዚአብሔር አምላካችን ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!
አሜን፡፡

አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ግንቦት ፳፩ ቀን !፻0፮ ዓ.ም.
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ
🕊

[ † እንኩዋን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የመገለጥ በዓል [ደብረ ምጥማቅ] በሰላም አደረሳችሁ † ]

🕊  †   ደብረ ምጥማቅ  †   🕊

የአርያም ንግሥት: የሰማይና የምድር እመቤት: የሰውነታችንም መመኪያ ቅድስት ድንግል ማርያም በዚሕች ዕለት በምድረ ግብፅ ለተከታታይ ቀናት ተገልጻለች::

ጥንተ ነገሩስ እንደ ምን ነው ቢሉ ፦

ለስም አጠራሩ ስግደት ይሁንና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድረ ግብፅና ኢትዮዽያ በተሰደደ ጊዜ ከድንግል እናቱ: ከዮሴፍና ሰሎሜ ጋር ዛሬ ደብረ ምጥማቅ በሚባለው ቦታ ላይ አርፎ ነበር:: ቦታውን ባርኮ ለዘለዓለም ያንቺ መገለጫ ይሁን ብሎም ቃል ኪዳን ገብቶላት ነበር::

ጊዜው በደረሰ ሰዓት ደብረ ምጥማቅ ተገድሞ የበርካታ መነኮሳት ቤት ሆነ:: እመቤታችንም በልጇ ፈቃድ ግንቦት ፳ [21] ቀን አእላፍ መላእክትን: ጻድቃን ሰማዕታትን አስከትላት መጣች::

በዚያ ሕዝበ ክርስቲያንም: አሕዛብም ተሰብስበው ለ፭ [5] ቀናት ከእመ ብርሃን ጋር ይሰነብታሉ:: እንግዲህ ልብ በሉት :- እንኩዋን የአርያም ንግስት: የአምላክ እናቱ እመቤታችንን ይቅርና በዚሕ ዓለም ሰይጣን ቤቱ ያደረጋቸውን: የመዝናኛው ኢንዳስትሪ ዝነኛ ሰዎችን ለማየት የዘመናችን ሰው እንዴት እንደሚቸኩል::

እመቤታችንን በአካል መመልከት አይደለም ስሟን መጥራት ነፍስን ከሥጋ መለየት የሚችል ጣዕምና ደስታ አለው:: ባይሆን ይሔ ለሚገባውና ላደለው ብቻ ነው::

የደብረ ምጥማቅና የአካባቢዋ ሰዎች ከእመቤታችን ጋር የሚቆዩባቸው ቀናት የዘለዓለም የሕይወት ስንቅ የሚይዙባቸው ናቸው:: ፈልገው የሚያጡት: ጠይቀው የማይፈጸምላቸው ምንም ነገር አልነበረም:: ነቢያት: ሐዋርያት: ጻድቃን: ሰማዕታት: ደናግል: መነኮሳት: መላዕክትና ሊቃነ መላእክት ለድንግል ማርያም ሲሰግዱ ይታዩ ነበርና:: እመ ብርሃንም እየመላለሰች ትባርካቸው ነበር::

እነዚያ እርሷን ያዩ ዐይኖች: በፊቷ የቆሙ እግሮች ክብር ይገባቸዋል:: ፭ [5] ቱ ዕለታት ሲፈጸሙ ሕዝቡ እመቤታችንን በዕንባ ይሰናበቷታል:: እመ ብርሃንም በብርሃን መስቀል ባርካቸው ከቅዱሳኑ ጋር ታርጋለች::


🕊   †  አባ መርትያኖስ   †   🕊

አባ መርትያኖስ በበርሃ ከ ፷፰ [68] ዓመታት በላይ በቅድስና የኖሩ አባት ናቸው:: ሰይጣን እርሳቸውን ፊት ለፊት ተዋግቶ መጣል ቢያቅተው በዝሙት በተለከፉ ሴቶች ያስቸግራቸው ነበር::

አንድ ቀን አንዷ ሽቶ አርከፍክፋ በዝሙት ልትጥላቸው ብትል እግራቸውን እሳት ውስጥ ጨምረው እግራቸው እየተቃጠለ በሚወጣው ጠረን አጋንንትን አርቀዋል:: እሷንም በንስሃ መልሰው ለቅድስና አብቅተዋታል:: ጻድቁ ከፈተና ለመራቅ በ ፻፰ [108] ሃገራት ፻፰ [108] በዓቶች የነበሯቸው ብቸኛ አባት ናቸው::

† ለአባት እናቶቻችን የተገለጠች እመቤታችን ለእኛም በረድኤት ትገለጽልን:: ጣዕመ ስሟ በአንደበታችን: ጣዕመ ፍቅሯ በልባችን ይደርብን:: †

🕊

[ † ግንቦት ፳፩ [ 21 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. ቅድስት ደብረ ምጥማቅ [የእመቤታችን መገለጥ]
፪. አባ መርትያኖስ ጻድቅ [በዝሙት ላለመሰናከል እግራቸውን በእሳት ያቃጠሉ አባት]
፫. ቅዱስ አሮን ሶርያዊ
፬. ቅዱስ አሞጽ ነቢይ

[ † ወርኀዊ በዓላት ]

፩. አበው ጎርጎርዮሳት
፪. አቡነ ምዕመነ ድንግል
፫. አቡነ አምደ ሥላሴ

" የምድር ባለጠጐች አሕዛብ በፊትሽ ይማለላሉ:: ለሐሴቦን ንጉሥ ልጅ ሁሉ ክብሯ ነው:: ልብሷ የወርቅ መጐናጸፊያ ነው:: በሁዋላዋ ደናግሉን ለንጉሥ ይወስዳሉ . . . በአባቶችሽ ፈንታ ልጆች ተወለዱልሽ:: በምድርም ሁሉ ላይ ገዥዎች አድርገሽ ትሾሚያቸዋለሽ:: ለልጅ ልጅ ሁሉ ስምሽን ያሳስባሉ:: " [መዝ.፵፬፥፲፪-፲፯] (44:12-17)

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
2024/06/26 04:25:03
Back to Top
HTML Embed Code: