Telegram Web Link
This media is not supported in your browser
VIEW IN TELEGRAM
                          †                          

[     🕊    ዳግሚያ ትንሳኤ !    🕊      ]

እንኩዋን ለዳግሚያ ትንሳኤ በሰላም አደረሳችሁ !

💖

እሁድ - ዳግም ትንሣኤ ይባላል

በዚህ ዕለት ክርስቶስ ለሦስተኛ ጊዜ ለደቀ መዛሙርቱ ተገልጦ ሰላምን መስበኩ እና ሥልጣንን መስጠቱ ይሰበካል፡፡

---------------------------------------------

"ደጆች ተዘግተው ሳሉ ኢየሱስ መጣ:: በመካከላቸውም ቆሞ 'ሰላም ለእናንተ ይሁን' አላቸው:: ከዚያም በሁዋላ ቶማስን 'ጣትህን ወደዚህ አምጣና እጆቼን እይ:: እጅህንም አምጣና በጐኔ አግባው:: ያመንህ እንጂ ያላመንህ አትሁን' አለው:: ቶማስም 'ጌታዬ አምላኬም' ብሎ መለሰለት:: ኢየሱስም 'ስላየኸኝ አምነሃል:: ሳያዩ የሚያምኑ ብጹዓን ናቸው' አለው::" [ዮሐ.፳፥፳፮-፳፱]

†                       †                        †
💖                    🕊                     💖
🕊

[ † እንኳን ለነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ኤርምያስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን። † ]

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †

†  🕊  ቅዱስ ኤርምያስ  🕊   

† ታላቁ ነቢይ ቅዱስ ኤርምያስ ከዐበይት ነቢያት አንዱ ሲሆን ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በስድስት መቶ አካባቢ የነበረ ነቢይ ነው:: አባቱ ኬልቅዩ ይባላል:: ከካህናተ እስራኤል አንዱ ነበር::

እግዚአብሔር ኤርምያስን የጠራው ገና በሕፃንነቱ ነበር:: "ከእናትህ ማኅጸን ሳትወጣ መርጬሃለሁ: ቀድሼሃለሁ" ሲልም በገሃድ መስክሮለታል:: [ኤር.፩፥፭] (1:5)

ከቅዱሳን ነቢያት እንደ ኤርምያስ የተሰቃየና ያለቀሰ የለም:: ከሰባ ዘመናት በላይ ስለ ወገኖቹ አልቅሷልና ሊቃውንት "ነቢየ ብካይ" [ባለ እንባው ነቢይ] ይሉታል::

ዘመኑ ዘመነ-ኃጢአት [ዘመነ ዐጸባ] ነበር:: እሥራኤላውያን ከመሪዎቻቸው ከነ ሴዴቅያስ ጋር በክፋት ተባብረውም ነበርና ኤርምያስን አልሰሙትም:: ይልቁኑ ክፉ ቦታ ውስጥ አስረው አሰቃዩት:: እግዚአብሔር ግን በኢትዮጵያዊው አቤሜሌክ አማካኝነት ከመከራው አዳነው::

የተሰበከላቸውን የንስሐ ጥሪ አልሰሙምና ስልምናሦር የሚባል የአሕዛብ ንጉሥ መጥቶ አሥሩን ነገድ ማርኮ በ፯፻፳፪ [722] አሦር [ነነዌ] አወረዳቸው:: በኋላ ደግሞ በኃይለኝነቱ የታወቀው የባቢሎን ንጉሥ ይማርካቸው ዘንድ ወደ ሁለቱ ነገድ ኢየሩሳሌም ደረሰ:: ኤርምያስ ወደ ከተማዋ ዳር ወጥቶ ስለ ኢየሩሳሌምና ስለ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አለቀሰ::

ከቤተ መቅደስ ንዋያት እኩሉን ለምድር አደራ ሰጣትና ሸሸገችው:: ነቢዩ የተናገረው አይቀርምና ንጉሡ ናቡከደነጾር እኩሉን ገድሎ: እኩሉንም ማርኮ: ኢየሩሳሌምን አቃጥሎ: የአሕዛብ መዘባበቻ አድርጐ በ፭፻፹፮ [586] ባቢሎን አወረዳቸው::

ቅዱስ ኤርምያስን ግን ትሩፋን [ከመከራው የተረፉት] ይዘውት ወደ ግብጽ ወረዱ እንጂ አልተማረከም:: በዚያም ተአምራትን አድርጐ አራዊትን አጥፍቷቸዋል:: ትንሽ ቆይቶ ግን እውነተኛ አባት : ነቢይ : መምሕርም ነውና ወደ ሕዝቡ [ወደ ባቢሎን] ወረደ:: በዚያም ትንቢትን እየተናገረ : ሕዝቡን ከሰባ ዓመታት በኋላ ወደ ሐገራቸው እንደሚመለሱ እያስተማራቸው በባቢሎን ቆይቷል:: ያለ በደሉም በመከራቸው ተካፋይ ሆኗል::

ሰባው ዘመን ሲፈጸም እግዚአብሔር እንደ ቃል ኪዳኑ በኤርምያስ መሪነት እሥራኤል ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ:: አሁንም ግን ክፋታቸውን ይተው ዘንድ ፈቃደኞች አልነበሩምና ኤርምያስ ገሠጻቸው::

በዚህ ተበሳጭተው ሊወግሩት ሲሉ ጸጋ በዝቶለት : ምሥጢርም ሰፍቶለት ስለ ነገረ ሥጋዌ [ስለ ክርስቶስ የማዳን ሥራ] አምልቶና አጉልቶ ትንቢት ተናገረ:: አንዴ ልቡናቸው ታውሮ ኤርምያስ ነው ብለው ድንጋዩን በድንጋይ ሲወግሩት ውለዋል:: ዘግይቶ ግን ኤርምያስ ራሱን ገለጠላቸው:: ስለ እነርሱ ሲል ሰባ ዘመን ያለቀሰውንና ምትክ የሌለውን አባታቸውን ወግረው ገደሉት::

ታላቁ ነቢይ ቅዱስ ኤርምያስ ሃምሳ ሁለት ምዕራፎች ያሉት ሐረገ ትንቢት ተናግሯል / ጽፏል:: ዜና ሕይወቱ ከራሱ የትንቢት መጽሐፍ በተጨማሪ በተረፈ ኤርምያስ : በመጽሐፈ ባሮክ : በገድለ ኤርምያስ : በዜና ብጹዐን : በመጽሐፈ ስንክሳርም ተጽፏል::

† ቸር እግዚአብሔር በኤርምያስ ምልጃ ሃገራችንን ከጥፋት: ሕዝቦቿን ከስደትና ከመቅሰፍት ይሰውርልን::

🕊

[ † ግንቦት ፭ [ 5 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. ቅዱስ ኤርምያስ ነቢይ [ከታላላቆቹ ነቢያት አንዱ]

[ † ወርኀዊ በዓላት ]

፩. ቅዱስ ጴጥሮስ ሊቀ ሐዋርያት
፪. ቅዱስ ጳውሎስ ሐዋርያ
፫. አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ
፬. ቅዱስ ዮሐኒ ኢትዮጵያዊ
፭. ቅዱስ አሞኒ ዘናሒሶ

" ኢየሩሳሌም ሆይ ነቢያትን የምትገድል : ወደ እርሷ የተላኩትንም የምትወግር : ዶሮ ጫጩቶቿን ከክንፎቿ በታች እንደምትሰበስብ ልጆችሽን እሰበስብ ዘንድ ስንት ጊዜ ወደድሁ! አልወደዳችሁምም:: እነሆ ቤታችሁ የተፈታ ሆኖ ይቀርላቹሃል:: እላችሁአለሁና : በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው እስክትሉ ድረስ እንግዲህ ወዲህ አታዩኝም :: " [ማቴ. ፳፫፥፴፯-፴፱]

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ ]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
🕊

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ †

[ † ግንቦት ፮ [ 6 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]


†  🕊  አባ መቃርስ ካልዕ  🕊  †

ይህ ቅዱስ "መቃርዮስ: መቃርስ: መቃሬም" ይባላል:: ትርጉሙ በ ፫ [3]ቱም መንገድ አይለወጥም:: ምክንያቱም ሥርወ ቃሉ በዮናኒ ልሳን "ብጹዕ: ንዑድ: ክቡር" ማለት ነውና::

ከስሙ ቀጥሎ "ካልዕ-፪ [2] ኛው": አንዳንዴ ደግሞ "እስክንድርያዊ" እየተባለ ይጠራል:: "ካልዕ-፪ [2] ኛው" የሚባለው ከቀዳሚው [ታላቁ መቃርስ] ለመለየት ሲሆን "እስክንድርያ" ደግሞ ተወልዶ ያደገባት ሃገር ናት::

አባ መቃርስ በ ፬ [4]ኛው መቶ ክ/ዘመን የነበረ ገዳማዊ: ጻድቅና ትሩፈ-ምግባር ነው:: በዓለም ለ ፵ [40] ዓመት ሲኖር እንደ ሕጉ ፈጣሪውን ደስ ያሰኘ ሰው ነው:: ጻድቃን እንደ ከዋክብት በበዙበት በዚያ ዘመን የታላቁ መቃርስን ዜና ሰምቷልና ይህቺን ክፉ ዓለም ከነግሳንግሷ ንቋት በርሃ ገብቷል::

እንደሚገባ ሥርዓተ ገዳምን ጠብቆ: ለአበው ታዞ: በጾም: በጸሎት: በትሕትናና በስግደት ተጠምዶ ቢያገኘው ፈጣሪ አከበረው:: በዚያ ጊዜም ለታላቁ ገዳመ አስቄጥስ መናንያን አበ ምኔት ሊሆን መረጡት::

እርሱም እረኝነትን ያውቃልና በጐቹን [መነኮሳትን] ከተኩላ [ሰይጣናት] ይጠብቅ ዘንድ ብዙ ተጋ:: ከብቃቱ የተነሳም ሳያስታጉል: ሳይበላ: ሳይጠጣና ሳይቀመጥ እስከ ፵ [40] ቀን ይጸልይ ነበር:: ሲጸልይ ደግሞ በልቡ እየተቃጠለ በፍቅረ ክርስቶስ ነበርና አጋንንት ይርዱለት ነበር::

እርሱ ጸሎት ሲጀምርም በገዳሙ ዙሪያ ያሉ አጋንንት እየጮሁ ይሸሹ ነበር:: ከተጋድሎው ጽናትና ከትሕትናው ብዛት የተነሳ ያዩት ትዕቢተኞች ሁሉ ይገሠጹ ነበር:: በዘመኑም ብዙ ተአምራትን ሠርቷል::

አንድ ቀን በበዓቱ ሳለ ጅብ መጥታ ተማጸነችው:: አብሯት ወደ ዋሻዋ ቢሔድ ልጆቿ በሙሉ ዓይነ ሥውራን ሆነው አገኛቸው:: እርሱም ወደ መሬት ምራቁን እትፍ ብሎ በጭቃ ለውሶ ቢቀባቸው የሁሉም ዐይናቸው በርቷል::

ስለ ውለታውም ጅቢቱ የበግ ቆዳ እየጐተተች አምጥታ ሰጥታዋለች:: [ከሰው ልጅ በቀር እንስሳት ውለታን አይረሱምና] ቅዱስ መቃርስም ለወትሮው ባዶው መሬት [አፈር] ላይ ይተኛ የነበረው ከዚያ ቀን በኋላ በአጐዛው ላይ የሚተኛ ሁኗል::

በሃገሩ እስክንድርያም ለ ፪ [2] ዓመታት ዝናብ በመጥፋቱ ሕዝቡ ተጨንቆ ነበርና "ናልን" ሲሉ መልዕክት ላኩበት:: እርሱ መጥቶ ሲጸልይም መብረቅ የቀላቀለ ዝናብ ጣለ:: ዝናቡም ያለ ማቆም ለ ፪ [2] ቀናት በመዝነቡ ሕዝቡ ፈርተው "አባታችን ስለ ኃጢአታችን እንዳንጠፋ ለምንልን?" አሉት:: እርሱም በጸሎቱ [በፈጣሪው ኃይል] እንደ ወደዱት ዝናቡን አቁሞላቸዋል::

የአባ መቃርስን ዜና ሕይወትና ተአምራት ተናግሬ አልፈጽመውም:: ግን አንዲት ብቻ ላክል:: ሁሌ ሳስበው ስለሚገርመኝም ነው::

ብዙዎቻችን የጌታችን ሥጋና ደም አንቀበልም:: ለምን ያከበርነውና የፈራነው አስመስለን ኃጢአትን ለመጥገብ ቦታን [አጋጣሚን] ስለምንፈልግ:: በተቃራኒው ደግሞ አንዳንዶቻችን መለኮት የተዋሐደውን የጌታ ሥጋና ደም እንደ ተርታ ነገር [ያለ ጥንቃቄ] ስንቀበል ይታያል:: ፪ [2] ቱም ግን ስሕተት ነው::

ፈርተን [ፍርሃቱ ጤነኛ ባይሆንም] ስለ ራቅን በፍርድ ቀን ማምለጥ አንችልም:: "ሥጋየን ያልበላ: ደሜንም ያልጠጣ የዘለዓለም ሕይወት የለውም" ይለናልና:: [ዮሐ.፮፥፶፪] (6:52)

በድፍረት ለምንቀበልም ሥጋው እሳት ሁኖ እንዳይበላን: ደሙም ባሕር ሆኖ እንዳያሰጥመን ልናከብረው ይገባናል:: "ሳይገባው ከጌታ ሥጋና ደም የተቀበለ የጌታ ሥጋ ዕዳ አለበት" ይለናልና::  [፩ቆሮ.፲፩፥፳፯] (11:27)

"ታዲያ የሚሻለው ለሁላችንም ንስሃ ገብቶ: በፍርሃት ሆኖ መቅረቡ ነው::"

ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና አባ መቃርስ ወደ በርሃ እንደ ገባ ሥጋ ወደሙን ተቀብሎ ነበር:: ቅዱሱ ይህንን እያሰበ ለ ፷ [60] ዓመታት ምራቁን ሳይተፋ ኑሯል:: ለዚያ አይደል አበው "ብታከብሩት ያከብራቹሃል" ያሉት::

ሊቃውንቱም ይህንን ሲያደንቁ :-

"ኢታስተማስልዎ ለቁርባን ከመ ሕብስት ዕራቆ:: አኮኑ ሥጋ መለኮት ዘይትላጸቆ:: መቃርዮስ አብ ዕበየ ቁርባን ለአጠይቆ:: ድኅረ ተወክፈ በአሚን እንበለ ያብዕ ናፍቆ:: መጠነ ዓመታት ስሳ ኢተፍአ ምራቆ::" ብለዋል::

ቅዱስ መቃርስም በ ፻ [100] ዓመቱ በ ፭ [5] ኛው ክ/ዘመን መጀመሪያ አካባቢ በዚህች ቀን ዐርፏል::

ጌታችን ከክብሩ : ከበረከቱ አይለየን::

🕊

[ †  ግንቦት ፮ [ 6 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. ቅዱስ አባ መቃርስ ገዳማዊ
፪. እናታችን ቅድስት ሰሎሜ ኢትዮዽያዊት
፫. አባ ይስሐቅ ጻድቅ
፬. ቅድስት ዲላጊና ፬ [4] ሴት ልጆቿ [ሰማዕታት]
፭. ቅዱስ ዳናስዮስ ሰማዕት
፮. ቅዱስ በንደላዖስ ሰማዕት [የታላቁ ኤስድሮስ አባት]
፯. አባ አሞን ጻድቅ [ዽዽስናን አልፈልግም ብሎ የሸሸ አባት]

[ † ወርኀዊ በዓላት ]

፩. ቅድስት ደብረ ቁስቁዋም
፪. አባታችን አዳምና እናታችን ሔዋን
፫. አባታችን ኖኅና እናታችን ሐይከል
፬. ቅዱስ ኤልያስ ነቢይ
፭. ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ
፮. ቅዱስ ዮሴፍ አረጋዊ
፯. ቅድስት ሰሎሜ
፰. አባ አርከ ሥሉስ
፱. አባ ጽጌ ድንግል
፲. ቅድስት አርሴማ ድንግል

" ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘለዓለም ሕይወት አለው:: እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሳዋለሁ:: ሥጋዬ እውነተኛ መብል: ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነውና:: ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል:: እኔም በርሱ እኖራለሁ:: "  [ዮሐ.፮፥፶፫-፶፮] (6:53-56)

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
🕊

†   🕊   በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡   🕊   †

❖ እንኳን አደረሳችሁ ❖

ግንቦት ፯ [ 7 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት


🕊 †  ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ †  🕊

በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከሐዋርያት ቀጥሎ የቅዱስ አትናቴዎስን ያሕል ስለ ሃይማኖት የተዋጋ ቅዱስ ፈልጐ ማግኘት አይቻልም::

†  ቅዱስ አትናቴዎስ ማን ነው ?

ቅዱስ አትናቴዎስ በቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት በዘመነ ሰማዕታት መጠናቀቂያ በ፫፻ [300] አካባቢ ፪፻፺፮ (296) እስክንድርያ ግብፅ ውስጥ ነው የተወለደው:: ወላጆቹ አረማውያን በመሆናቸው ክርስትናን አልተማረም ነበር::

ሕጻን እያለ ለጭዋታ ከቤቱ ሲወጣ የክርስቲያን ልጆች ሃይማኖታዊ ጨዋታ ሲጫወቱ ተመለከተ:: ሊቀላቀላቸው ቢፈልግም ክርስቲያን ባለመሆኑ ከለከሉት:: አትናቴዎስም ክርስቲያን ልሁንና አጫውቱኝ ብሏቸው እሺ ስላሉት ሕጻናቱ ዕጣ ተጣጣሉ::

ላንዱ ቄስ: ላንዱም ዲያቆን መሆን ሲደርሳቸው ለአትናቴዎስ ፓትርያርክ መሆን ስለ ደረሰው ሌሎቹ ሕጻናት ይሰግዱለት ጀመር:: በአጋጣሚ ሕጻናቱ ይሕንን ሁሉ ሲያደርጉ የወቅቱ ፓትርያርክ ቅዱስ እለ እስክንድሮስ በመገረም ያያቸው ነበርና ለሕጻኑ አትናቴዎስ ትንቢት ተናገረለት::

ከዚያም የአትናቴዎስ አባቱ ሲሞት ሊቀ ዻዻሳቱ ከእናቱ ወስዶ አጥምቆ: የሚገባውን መንፈሳዊ ትምሕርት ሁሉ በልቡናው ላይ ቀረጸበት:: ከዚሕ በኋላ ዲቁናን ሹሞ አስተምር አለው:: ምንም ሕጻን ቢሆንም ከሊቅነቱ: ከአመላለሱና ከአንደበቱ ጣፋጭነት የተነሳ የሰማው ሁሉ ይደነቅ ነበር:: ጸጋ እግዚአብሔር በእርሱ ላይ አድራለችና::

ቅዱስ አትናቴዎስ ሊቀ ዲቁና በተሾመ ወራት አርዮስ ቤተ ክርስቲያንን በመረበሹ ኒቅያ ላይ ፫፻፲፰ [318] ቱ ሊቃውንት ሲሰበሰቡ ጸሐፊ አድርገው ሾሙት:: በጊዜውም በዕድሜ የስንት ጊዜ ትልቁ የሚሆነውን አርዮስን ተከራክሮ ምላሽ አሳጣው::

†  ቅዱስ

አትናቴዎስ ከሊቃውንቱ ጋር ሆኖ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ ወልደ አምላክ: እግዚአብሔር መሆኑን በአደባባይ መሠከረ:: ጸሎተ ሃይማኖትንም ያረቀቀው እርሱ ነው::

ከዚሕ በኋላ የእስክንድርያ [የግብፅ] ፳ [20] ኛ ፓትርያርክ ሆኖ ተሾመ:: ቤተ ክርስቲያንን በመልካም እረኝነት ለ፵፰ [48] ዓመታት ሲመግብ ብዙ መከራዎችን ተቀበለ:: ለ፭ [5] ጊዜ ከመንበሩ አፈናቅለው ወደ በርሃ ሲያግዙት በስደት ከ፲፭ [15] ዓመታት በላይ አሳልፏል::

በተሰደደባቸው ቦታዎች መከራን እየተቀበለ ያላመኑትን አሳምኗል:: በጎቹ እንዳይባዝኑበት ደግሞ በጦማር [በደብዳቤ] ይጠብቃቸው ነበር:: ዛሬ በሃይማኖተ አበው የምናገኘው ቃለ ሃይማኖት በዚሕ ዘመን የተጻፈ ነው::

በወቅቱ የነበረው ንጉሥ [ትንሹ ቆስጠንጢኖስ] የአባቱን [ታላቁ ቆስጠንጢኖስን] ዕረፍት ተከትሎ ነገሠ::

ወዲያውም አርዮሳዊ መናፍቅ ሆነ:: ሃይማኖታቸው የቀና አባቶችንም ያሳድድ ገባ:: ከአበው ቅዱሳን መካከል ግንየዚህ መከራ ቀዳሚው ገፈት ቀማሽ ታላቁ ሊቅ ቅዱስ አንትናቴዎስ ነበር::

በተለይ አንድ ጊዜ ንጉሡ ቅዱሱን ወደ በርሃ አግዞ: መናፍቅ ዻዻስ በግብጽ ሹሞ: ብዙ ክርስቲያኖችን በግፍ ሲያስገድል: ቅዱሱን ለ፮ [6] ዓመታት አሰቃየው:: የወገኖቹ [የልጆቹን] ስቃይ የሰማው ቅዱስ አትናቴዎስ ግን በድፍረት ወደ ቤተ መንግስት ገብቶ ተናገረው::

፪ [2] አማራጭን አቅርቦ "ወይ ግደለኝና እንደ አባቶቼ ሰማዕት ልሁን: ካልሆነ ግን ወደ መንጐቼ [ምዕመናን] መልሰኝ" አለው:: መናፍቁ ንጉሥም ቢገድለው ብጥብጥ እንደሚነሳ ስለሚያውቅ በስልት ሊያጠፋው ወሰነ::

ቀዛፊ: መቅዘፊያ: ምግብና ውሃ በሌላት ጀልባ ውስጥ ከቶም ሜዲትራኒያን ባሕር ውስጥ ጣለው:: ድንገት ግን ከሰማይ ጌታችን መላእክቱን አስከትሎ ወረደ::

ሚካኤልና ገብርኤል ባሕሩን እየቀዘፍ: ሌሎች መላእክት እየመገቡት በዚህች ቀን እስክንድርያ [ግብጽ] አድርሰውት ተሠውረዋል:: ሕዝቡም በታላቅ ሐሴት እየዘመሩ አባታቸውን ተቀብለውታል::

ሐዋርያዊው ቅዱስ ስለ ኦርቶዶክስ ተዋግቶ: ብዙ ስቃይንም ተቀብሎ በ፫፻፹፫ [373] ዓ/ም አካባቢ አርፏል:: ቤተ ክስርቲያን ፦
- "ሊቀ ሊቃውንት:
- ርዕሰ ሊቃውንት:
- የቤተ ክርስቲያን
- [ የምዕመናን ] ሐኪም [ Doctor of the Church ]:
- ሐዋርያዊ" ብላ ታከብረዋለች::

አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሊቁ በረከት አይለየን:: በምልጃውም ሃይማኖታችንን ይጠብቅልን::

🕊

[ † ግንቦት ፯ [ 7 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ
፪. የባሕታውያን አለቃ ታላቁ አባ ሲኖዳ [ጽንሰቱ]
፫. ቅዱስ ዮሐንስ ጻድቅ [ሃብቱን: ንብረቱን: ልብሱን
ሳይቀር መጽውቶ ራቁቱን የተገኘ ደግ ሰው ነው]
፬. አባ ሐርስዮስ ገዳማዊ

[ †  ወርሐዊ በዓላት ]

፩. ሥሉስ ቅዱስ [አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ]
፪. አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ
፫. አባ ሲኖዳ [የባሕታውያን አለቃ]
፬. አባ ዳንኤል ዘገዳመ ሲሐት
፭. አባ ባውላ ገዳማዊ
፮. ቅዱስ አግናጥዮስ [ለአንበሳ የተሰጠ]

" ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብጹዐን ናቸው:: መንግስተ ሰማያት የእነርሱ ናትና:: ሲነቅፉአችሁና ሲያሳድዱአችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብጹዓን ናችሁ:: ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ:: ሐሴትም አድርጉ:: ከእናንተ በፊት የነበሩ ነቢያትን እንዲሁ አሳደዋቸዋልና። " [ማቴ.፭፥፲] (5:10)


[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ ]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
🕊

[  † እንኳን ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጥንተ በዓለ ዕርገት እና ለጻድቁ አባ ዳንኤል ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን። †   ]

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ! †


 †  🕊   ዕርገተ እግዚእ   🕊  †  

† ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በዓለ ዕርገትን ፪ [2] ጊዜ ታከብራለች:: አንዱ "ጥንተ በዓል" : ሁለተኛው ደግሞ "የቀመር በዓል" ይሠኛል:: ጥንተ በዓል ማለት ጌታችን በትክክል ያረገበትን ቀን ያመለክታል::

የክብር ባለቤት መድኃኔ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ በኪነ ጥበቡ [በሕማሙ : በሞቱ] ዓለምን አድኖ: ፵ [40] ቀን ለሐዋርያቱ መጽሐፈ ኪዳንን: ትምሕርተ ኅቡዓትን አስተምሯቸዋል::

በ፵ [40] ኛው ቀን ፻፳ [120] ውን ቤተሰብ ይዟቸው ወደ ቢታንያ ወጣ:: በዚያም እስከ ሊቀ ዽዽስና ድረስ ሾሟቸው : ከኢየሩሳሌም እንዳይወጡም አዟቸው የመንፈስ ቅዱስን ተስፋ ጠብቁ ብሏቸዋል:: እየባረካቸው በተዋሐደው ሥጋ ወደ ሰማያዊ ዙፋኑ አርጓል::

ሰማያት: ምድር: ደመናት: ነፋሳት: መባርቅትና መላእክት: ፍጥረት በሙሉ አመስግኗል:: አይሁድ መናፍቃን ዕርገቱን ምትሐት ነው እንዳይሉ: ጌታችን ትንሳኤውን አማናዊ እንደሆነ ለማስረዳት በ፵ [40] ኛው ቀን ዐረገ::

አንድም ራስ ባለበት ሌሎች የሰውነት ክፍሎች ሊኖሩ ይገባልና ጌታችን ዕርገቱን በገሃድ አደረገው:: "ዐርገ እግዚእ ከመ ያለቡ ዕርገተ ጻድቃን ንጹሐን" እንዲል::

† ዐርገ እግዚአብሔር በይባቤ::
ወእግዚእነ በቃለ ቀርን::
ዘምሩ ለአምላክነ ዘምሩ:: † [መዝ.፵፮፥፮] (46:6)


🕊  †  ታላቁ አባ ዳንኤል  †  🕊

† ይህ ቅዱስ አባት ስም አጠራሩ ክቡር ነው:: በሁሉ ነገሩ የተቀደሰ የገዳማውያን መብራትም ነው:: ከተረፈ ንጹሕ ሕይወቱ ጣዕመ መንግስተ ሰማያትን አይቷልና:: አባ ዳንኤል በትውልድ ግብጻዊ ሲሆን ዓለምን ንቆ [መንኖ] ገዳም የገባው ገና በወጣትነቱ ነው::

ጊዜውም ዘመነ ጻድቃን [በ፭ [5] ኛው መቶ ክ/ዘመን] ነበር:: በገዳመ አስቄጥስ እና በደብረ ሲሐት ይታወቃል:: ታላቋ መካነ ቅዱሳን ገዳመ ሲሐት ዛሬም ድረስ በስሙ የምትጠራ ሲሆን ለዚህም ምክንያቱ እጅግ ለብዙ ዘመናት በውስጧ ተጋድሎ ፍሬ ስላፈራባት : ደቀ መዛሙርትን በቅድስና ስለ ወለደባት ነው::

ስለዚህም ዛሬም ድረስ "አባ ዳንኤል ዘደብረ ሲሐት" ተብሎ ሲጠራ ይኖራል:: ሌላኛው ስሙ ደግሞ "ዘገዳመ አስቄጥስ" ይሰኛል:: ገዳመ አስቄጥስ የታላቁ ቅዱስ መቃርስ ርስት ሲሆን በዓለም በስፋትም : ብዙ ቅዱሳንን በማፍራትም አንደኛ የሆነ ገዳም ነው::

በዚህ ገዳም ላይ አበ ምኔት ሆኖ የሚሾሙ አበው ሁሌም የብቃት መዓርግ ላይ የደረሱ ሲሆኑ ክብራቸው ከፓትርያርክ በላይ ነው:: አባ ዳንኤልም ከብዙ የቅድስና ዓመታት በኋላ በአስቄጥስ ገዳም አበ ምኔት ሆኖ ተሹሞ እልፍ አእላፍ መነኮሳትን በጽድቅ መንገድ መርቷል::

ቅዱሱ ከትጋቱ የተነሳ ለምግብና ለእንቅልፍ ጊዜ አልነበረውም:: ቀን ቀን መነኮሳቱን ሲናዝዝ : ድውያንን ሲፈውስ : ሥርዓተ ገዳምን ሲቆጣጠር ይውላል:: ልክ ሲመሽ ጭው ወዳለውና ስውራን ወደ ሚገኙበት በርሃ ይወጣል::

በዚያም ሙሉውን ሌሊት የተሰወሩ አባቶችን ሲፈልግ ያድር ነበር:: በዚህም ምክንያት የብዙ ስውራንን ገድል የጻፈ ሲሆን ባረፉ ጊዜም ገንዞ በመቅበር በረከታቸውን ተሳትፏል:: ታላቅ ሙያንም ፈጽሟል::

እርሱ ገንዞ ቀብሮ : ዜናቸውን ከጻፈላቸው ሥውራን ቅዱሳንም እንደ አብነት እሥራኤላዊቷን ቅድስት ዓመተ ክርስቶስን [ለ፴፰ [38] ዓመት ራቁቷን በሥውር የኖረች] እና ቅድስት በጥሪቃ ንግሥትን [መንግስቷን ትታ በሥውር የኖረች ናት] መጥቀስ እንችላለን::

ከዚህ ባለፈም አባ ዳንኤል በሰው ዘንድ የተናቁትንም ማክበርን ያውቅበታል:: ለምሳሌ በሴቶች ገዳም እብድ ናት ተብላ በበር የተጣለችውን ቅድስት አናሲማን : በእስክንድርያ ከተማ ሊቀ ዻዻሳቱ ሳይቀር "እብድ ነው" ብለው የናቁትን ቅዱስ ምሕርካን: እብድ ሳይሆኑ ራሳቸውን የሠወሩ ቅዱሳን መሆናቸውን ገልጧል::

አባ ዳንኤል ሐዋርያዊም ነበር:: በጊዜው ጦማረ ልዮን የሚባል የኑፋቄ ደብዳቤ ይላክ ነበርና ለዚህ ኬልቄዶናዊ ኑፋቄ በትጋት ምላሽ ይሰጥ ነበር:: አንድ ቀንም በንጉሥ ትዕዛዝ ኑፋቄው በእርሱ ገዳም ሊነበብ ሲል ቅዱሱ ከወታደሩ ቀምቶ ስለ ቀደደው ለሞት እስኪደርስ ደብድበውታል::

ጻድቁ አባ ዳንኤል አንዴ አውሎጊስ የሚባልድሃ ድንጋይ ጠርቦ እንግዳ ሲቀበል ተመልክቶ "ጌታ ሆይ! ይህንን ደግ ሰው ለምን ድሃ አደረከው?" ሲል በፈጣሪ ሥራ ገባ::

ጌታም እንደ ወትሮው በገሃድ ተገልጦ "በነፍስህ ትዋሰዋለህ?" አለው:: "አዎ ጌታየ" ስላለው ጌታችን ለአውሎጊስ ሃብትን ሰጠው:: ግን ወዲያው የጦር አለቃና ጨካኝ ሰው ሆነ::

ጻድቁ ወሬውን ሰምቶ ሊጠይቅ ቢሔድ የአውሎጊስ ወታደሮች ደበደቡት:: ጌታችንም አባ ዳንኤልን ወደ ፍርድ ዙፋኑ አቅርቦ "ወዳጄን መልስልኝ" አለው:: እመ ብርሃን ግን ቀርባ የልጇን እግር ሳመች::

"ልጄ ሆይ ማር!" አለችው:: ጌታም "እሺ" ብሎ ጻድቁን ወደ በአቱ: አውሎጊስን ወደ ቀደመ ግብሩ መለሳቸው:: የአባ ዳንኤል ድንቁ ብዙ ነው::

ሌላው ቢቀር ሽፍታ አባ ዳንኤልን መስሎ ወደ ደናግል ገዳም ሊዘርፍ : በማታለል ገባ:: ደናግሉም ጻድቁ መስሏቸው እግሩን አጥበው ዐይነ ስውሯን ቢቀቧት ዐይኗ በርቷል:: ሽፍታውም ደንግጦ ንስሃ ገብቷል:: አባ ዳንኤል ግን ተጋድሎውን ፈጽሞ በዚህች ቀን ዐርፏል::

† በተረፈው ግን ከቅድስና ሕይወቱ ባሻገር :-

፩. በገዳመ አስቄጥስ [ግብጽ] አበ ምኔት ሆኖ ተሹሞ ባሳየው ትጋት::
፪. በሃይማኖት ጠበቃነቱ በደረሰበት ድብደባና ስደት::
፫. ብዙ የበርሃ ቅዱሳንን በየበአታቸው እየዞረ በመቅበሩ::
፬. የብዙ ስውራን ቅዱሳንን ዜና ሕይወት በመሰብሰቡ::
፭. በየጊዜው በእግዚአብሔር ኃይል ይፈጽማቸው በነበሩ ተአምራት:: እና
፮. ለድንግል እመቤታችን ማርያም በነበረው ልዩ ፍቅር ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ታከብረዋለች::

† ቸር አምላክ ክርስቶስ ከዕርገቱና ከጻድቁ በረከት አይለየን::

🕊

[  † ግንቦት ፰ [ 8 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት  ]

፩. ቅዱሳን የጌታ ቤተሰብ [፻፳ (120) ው]
፪. ቅዱስ አባ ዳንኤል ጻድቅ
፫. ቅዱስ ዮሐንስ ሰማዕት
፬. ቅዱስ መክሲሞስ መስተጋድል
፭. አቡነ ዮሐኒ ዘደብረ ዳሞ [አቡነ ተክለ ሃይማኖትንና አቡነ ኢየሱስ ሞዐን ለምንኩስና ያበቁ]

[    † ወርሐዊ በዓላት    ]

፩. ቅዱስ ሙሴ ሊቀ ነቢያት
፪. ኪሩቤል [ አርባዕቱ እንስሳ ]
፫. አባ ብሶይ [ ቢሾይ ]
፬. አቡነ ኪሮስ
፭. አባ ሳሙኤል ዘደብረ ቀልሞን
፮. ቅዱስ ማትያስ ሐዋርያ [ከ፲፪ [12] ቱ ሐዋርያት]

" እስከ ቢታንያም አወጣቸው:: እጆቹንም አንስቶ ባረካቸው:: ሲባርካቸውም ከእነርሱ ተለየ:: ወደ ሰማይም ዐረገ:: እነርሱም ሰገዱለትና በብዙ ደስታ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ:: ዘወትርም እግዚአብሔርን እያመሰገኑና እየባረኩ በመቅደስ ኖሩ:: " † [ሉቃ.፳፬፥፶-፶፫] [24:50-53]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
🕊

[ † እንኳን ለእናታችን ቅድስት እሌኒ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን። † ]

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ! †


🕊  †   እሌኒ ንግሥት   †   🕊

† ቅድስት እሌኒ የታላቁ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ እናቱና እግዚአብሔር ለበጐ አገልግሎት የጠራት ቡርክት ሴት [ንግሥት] ናት::

ጥንተ ነገሩስ እንደ ምን ነው ቢሉ :-

የቅድስቲቱ ሃገረ ሙላዷ ሮሃ [ሶርያ] አካባቢ ነው:: ነገዷ ከእሥራኤል ዝርዋን እንደሆነም ይነገራል:: ጣልያኖች "Helena" : በእንግሊዝኛው "Helen" ይሏታል:: እኛ ደግሞ "እሌኒ" እንላታለን:: ትርጓሜው "ጥሩ ምንጭ" : አንድም "ውብና ደግ ሴት" ማለት ነው::

ቅድስት እሌኒ በመልካም ክርስትና አድጋ እንደ ቤተ ክርስቲያን መተርጉማን ተርቢኖስ የሚባል ነጋዴ አግብታ ነበር:: ወቅቱም ዘመነ ሰማዕታት ነበር:: በማይሆን ነገር ጠርጥሮ ባሕር ላይ ጥሏት ንጉሥ ቁንስጣ አግኝቷታል:: እርሱም የበራንጥያ [የኋላዋ ቁስጥንጥንያ] ንጉሥ ነበር::

ቅድስት እሌኒ ከቁንስጣ የተባረከ ልጅን ወለደች:: ቆስጠንጢኖስ አለችው:: በልቡናው ፍቅርን : ርሕራሄን : መልካምነትን እየዘራች አሳደገችው:: ቅዱሱ አባቱ በሞተ ጊዜ ተተክቶ ነገሠ::

ቅድስት እሌኒንም ንግሥት አደረጋት:: ያንን የአርባ ዓመት ግፍ በአዋጅ አስቀርቶ ለክርስቲያኖች ነፃነትን : ክብርን በይፋ ሰጠ:: አንድ : ሁለት ብለን የማንቆጥረውን ውለታ ለምዕመናን ዋለ:: ከነዚህ መልካም ምግባራቱ ጀርባ ታዲያ ቅድስት እናቱ ነበረች::

ቅድስት እሌኒ ጾምን : ጸሎትን ከማዘውተሯ ባሻገር አጽመ ሰማዕታትን ትሰበስብ : አብያተ ክርስቲያንን ታሳንጽ : ለነዳያንም ትራራ ነበር:: በኢየሩሳሌምና አካባቢው ብቻ ከሰማንያ በላይ አብያተ መቃድስ አሳንጻለች:: እነዚህንም በወርቅና በእንቁ ለብጣቸዋለች::

በዘመኗ መጨረሻም የጌታችንን ቅዱስ ዕፀ መስቀል ከተቀበረበት አውጥታ ለዓለም በረከትን አስገኝታለች::

እናታችን ቅድስት እሌኒ እንዲህ በቅድስና ተመላልሳ በሰማንያ ዓመቷ በ፫፻፴ [330] ዎቹ አካባቢ ዐርፋለች:: ቤተ ክርስቲያናችንም ስለ ቅድስናዋና ውለታዋ በዓል ሠርታ : ታቦት ቀርፃ ስታከብራት ትኖራለች::

† ከቅድስት እናታችን ምልጃና በረከት አምላካችን ያድለን::

🕊

[ †  ግንቦት ፱ [ 9 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. ቅድስት እሌኒ ንግሥት
፪. ቅዱስ ስልዋኖስ

[ † ወርኀዊ በዓላት ]

፩. አባ በርሱማ ሶርያዊ [ለሶርያ መነኮሳት ሁሉ አባት]
፪. አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ [ኢትዮጵያዊ]
፫. ሦስት መቶ አሥራ ስምንቱ ቅዱሳን ሊቃውንት [ርቱዐነ ሃይማኖት ዘኒቅያ]
፬. የብሔረ ብፁዐን ጻድቃን
፭. አባ መልከ ጼዴቅ ዘሚዳ [ኢትዮጵያዊ]
፮. ቅዱስ ዞሲማስ ጻድቅ [ዓለመ ብፁዐንን ያየ አባት]

" ነገር ግን ለበጐ ነገር ጥበበኞች : ለክፉትም የዋሆች እንድትሆኑ እወዳለሁ:: የሰላምም አምላክ ሰይጣንን ከእግራችሁ በታች ፈጥኖ ይቀጠቅጠዋል:: የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን:: " † [ሮሜ. ፲፮፥፲፱]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
2024/09/28 21:50:44
Back to Top
HTML Embed Code: