Telegram Web Link
ꔰ ꔰꔰእንኳን ለእመቤታችን 2031ኛ ዓመት በዓለ ልደት አደረሳችሁꔰ ꔰꔰ
ꔰ  #ልደታ_ለማርያም  ꔰ
#ልደቷ_መጽሐፍ_ቅዱስ_ላይ_ከሌለ_ተቀባይነት_እንዴት_ይኖረዋል? ꔰ
ሰላም ለልደትኪ እማኀፀነ ድክምት ሥጋ
ድኅረ ኀለፋ ውርዙት ወድኅረ ትክቶ ኃደጋ
#የግንቦት_ልደታ_ለማርያም_ክብረ_በዓልና_የእመቤታችን_በዓላት
በቀደመዉ ዘመን በዘመነ ብሉይ ‹‹የቤተ መቅደስ መታደስ በዓል›› ይከበር እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ያስረዳል፡፡ ይህ በዓል እስከ ጌታችን ዘመንም ይከበር ነበር፡፡ /ዮሐ. 10፥22/ በሐዲስ ኪዳን እውነተኛ የእግዚአብሔር ማደሪያ ቤተ መቅደስ ለሆነችዉ እመቤታችን በስሟ በዓል ሊደረግላት ይገባል፤ ‹‹የጻድቅ መታሰቢያ ለዘላለም ይኖራል›› እንዳለ ቅዱስ ዳዊት መዝ. 111፥7በተአምረ ማርያም ላይ በዝርዝር እንደተቀመጠዉ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም 33ት በዓላት አሏት፡፡ ከእነዚህ በዓላት ሁሉ አስበልጣ የምትወደዉ በዓለ ልደቷን እንደሆነ በአጼ ዘርዓ ያዕቆብ ዘመነ መንግሥት ከዐረብኛ ወደ ግእዝ በተተረጎመዉ እመቤታችን በተለያዩ ሀገራት ያደረገቻችዉን ገቢረ ተአምራት በኢትዮጵያ ከተፈጸሙት ጋር አካቶ የያዘው ተአምረ ማርያም በዝርዝር ያስረዳል፡፡

#ልደቷ_መጽሐፍ_ቅዱስ_ላይ_ከሌለ_ተቀባይነት_እንዴት_ይኖረዋል?
      በመጽሐፍ ቅዱስ ያልተካተቱና ምሉዕነት የሌላቸዉ ታሪኮች በአዋልደ መጻሕፍት እንደሚሟሉ ራሱ መጽሐፍ ቅዱስ ያስረዳል ለምሳሌ ስለ ቅዱስ ዳዊት የሚናገረዉ መጽሐፈ ዜና መዋዕል ‹‹የንጉሡም የዳዊት የፊተኛዉና የኋለኛዉ ነገር በነቢዩ በናታን ታሪክ እንዲሁም በባለ ራእዩም በጋድ ታሪክ ላይ ተጽፏል›› ይላል፡፡ 1ኛ ዜና 29፥29

#የእመቤታችን_የልደቷ_ታሪክ
የእመቤታችን ወላጆች በአብዛኛዉ አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ‹‹ሐና››ና ኢያቄም/ዮአኪን በሚለዉ ስም የሚጠሩ ሲሆን ሐና በቤተልሔም ተወልዳ እንዳደገች ታሪክ ያስረዳል፡፡ በናዝሬት ገሊላ ለመሥዋዕት የሚሆኑ በጎች የሚያቀርብ እንዲሁም እረኛ የነበረዉን ኢያቄምንም አግብታለች፡፡ ቅድስት ሐና ወደ ቤተ መቅደስ ስትሔድ እርግብን አይታ ታለቅስ ነበር፡፡ ከብዙ ልመና በኋላ ቅድስት ድንግል ማርያምን ግንቦት አንድ ቀን በደብረ ሊባኖስ ወልደዋል፡፡
ስለ ሐና መካንነት ወደ ቤተ መቅደስ ሄደዉ መባዕ ሲያቀርቡ ካህኑ ያልተቀበላቸዉ መሆኑን በብስራተ መልአክ ልጅ እንደሚወልዱ እንደተነገራቸዉ በእኛ ቤተ ክርስቲያን የሚተረከዉና በሌሎች ኦርቶዶክሳዊያን አብያተ ክርስቲያናት የሚነገረዉ ታሪክ ተመሳሳይ ነዉ፡፡

#እመቤታችን_የት_ተወለደች?
እመቤታችን ስለተወለደችበት ስፍራ በዓለም የተለያዩ ሐሳቦች ይስተጋባሉ፡፡ ሌላዉ ቀርቶ በዶግማ አንድነት ባላቸዉ አኃት አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ በእንዲህ ዓይነት ታሪክ ነክ ጉዳዮች ላይ ልዩነት መኖራቸዉ የተለመደ ክስተት ነዉ፡፡ የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሁለት ሐሳቦች የሚያነሱ ሲሆን፤ አንደኛዉ ‹‹ድንግል ማርያም ብስራተ መልአክ በሰማችበት ናዝሬት ተወልዳለች›› የሚል ነዉ፡፡ ሁለተኛዉ ሐሳብ ደግሞ ‹‹ከሦስተኛዉ ክ/ዘመን ወዲህ የማርያም መግቢያ ተብሎ በሚታወቀዉ ከኢየሩሳሌም የቅድስት ሐና የክሩሲድ ቤ/ክ በታች ነዉ የተወለደችዉ የሚል ነዉ፡፡
የግብጽ ስንክሳር የእመቤታችን የትዉልድ ስፍራ በናዝሬት ነዉ ይላል፡፡ የኢትዮጵያ ስንክሳር ግን በቀደምትነታቸዉ ተጠብቀዉ የቆዩ ከመሆናቸዉ አንጻር ተአማኒነታቸዉ የጎላ መሆኑን ያሳያል፡፡ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መጻሕፍት የእመቤታችን የትዉልድ ስፍራ ሊባኖስ የተባለዉ ተራራማ ሀገር ነዉ፡፡ ሊባኖስ ከገሊላ በስተ ሰሜንና ከፊንቄ በስተምስራቅ ይገኛል፡፡ ‹‹ሙሽራየ ሆይ ከሊባኖስ ከእኔ ጋር ነይ›› መኃ. 4፥7 የሚለዉ ቃለ ትንቢት ምሥጢርም የአመቤታችን መካነ ልደት የሊባኖስ ተራራ ስለመሆኑ የሚያጠይቅ እንደሆነ ምስክርነታቸዉ የታመነ የቤተ ክርስቲያን ሊቃዉንት ያስረዳሉ፡፡

#የልደታ_ለማርያም_በዓል_መቸ_ነዉ?
እንደተወለደችበት ሥፍራ የእመቤታችን የልደት ቀን እንዲሁ አወዛጋቢ ነዉ፡፡ በ6ኛዉ ና7ኛዉ መቶ/ክ/ዘመን ነዉ የሚሉ የተለያዩ ሃሳቦች የተጻፉ ሲሆን Encyclopaedic of Christian antiquities ደግሞ በ431 ዓ/ም ከተካሄደዉና ንስጥሮስ ከተወገዘበት ከጉባኤ ኤፌሶን በኋላ ነዉ ይላል፡፡ በዓለም ቅዱሳንን የሚያከብሩ አብያተ ክርስቲያናት የቅዱሳንን በዓለ እረፍታቸዉን የሚያከብሩ ሲሆን ልደታቸዉ የሚከበረዉም በሦስተኛ ደረጃ የመጥምቀ መለኮት ቅ/ ዮሐንስ፤ በሁለተኛ ደረጃ የእመቤታችን ቅ/ድንግል ማርያም ልደት ነዉ፡፡ በአንደኛ ደረጃ ለስም አጠራሩ ክብር ይግባዉና የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ነዉ፡፡
የአመቤታችን ልደት በምዕራባዊያን አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ኬ.ክ በመጋገር፡ የአመቤታችን ትንሽ ሀዉልት በማቆም ዐስር ሻማዎችን በማብራት ያከብራሉ፡፡

#የድንግል_ማርያም_ልደት_ለምን_ይከበራል?
* ስለ መጥምቁ ዮሐንስ ልደት በመልአኩ ቅ/ገብርኤል አንደበት‹‹በመወለዱ ብዙዎች ደስ ይላቸዋል›› በማለት ተነግሯል (ሉቃ 1-14)፤ ምክንያቱም ቅ/ዮሐንስ የጌታ መንገድ ጠራጊ፥ የአዋጅ ነጋሪ በመሆኑ ነዉ፡፡ የቅዱስ ዮሐንስ መወለድ ለብዙዎች ደስታ ምክንያት ከሆነ፤ የድንግል ማርያም ልደትማ ምንኛ የሚያስደስት ይሆን!?፡፡ስለሆነም ከጌታ ቀን ቀጥሎ የምንደሰትበት ትልቁ ቀን የእርሷ የልደት ቀን ነዉ፡፡
* የቀርጤሱ ቅ/እንድርያስ ስለ ከበረ ልደቷ እንዲህ ብሏል ‹‹ይህ በዓል በሐዲስና በብሉይ ኪዳን መካከል መገኛ ሆነ፡፡ ምሳሌዎቹ በእዉነታ፣ አሮጌዉ በአዲስ ቃል ኪዳን ተተኩ፡፡ ፍጥረት ሁሉ በደስታ ይዘምራል የዚህን ቀንም ደስታ ይካፈላል፡፡ ይህ መቅደሱን የሰራበት ዕለት ነዉ፡፡ ይህ ዕለት ትልቅ ሕንፃ የታነጸበትና ፍጡር የፈጣሪ ማደሪያ ለመሆን የተዘጋጀበት ዕለት ነዉ፡፡››ብሏል
* እመቤታችን  ለፀሐዩ መምጣት የተዘረጋች ሰማይ፤ በቅድመ አያቶቿ በነ ቴክታና ጰጥሪቃ ሕልም እንደታየችዉ በሌሊት የምታበራ ጨረቃ፤ የብሉይ ኪዳን ማብቂያ የሐዲስ ኪዳን መጀመሪያ ናትና ልደቷ ለሰዉ ልጅ ሁሉ ደስታ ነዉ፡፡
* ነቢያት በብዙ ሕብረ አምሳል የተናገሩላት ‹‹መሠረቶቿ የተቀደሱ ተራራዎች ናቸዉ››፤ ‹‹ከእሴይ ስር በትር ትወጣለች አበባዋም ከግንዱ ይወጣል››፤ ‹‹ሙሽራየ ሆይ ከሊባኖስ ነይ››፤ …. ብለዉ የተናገሩላት ቅ/ድ/ማርያም ልደቷ የትንቢታቸዉ ፍፃሜ ነዉና ታላቅ ደስታቸዉ ደስታችንም ነዉ፡፡ (መዝ. 86፥1፣ ኢሳ. 11፥1፣ መኃ. 4፥7)ጂነአ
* በዓለም ላይ የብዙ ታዋቂ ሰዎች ልደት ከሞቱም በኋላም ጭምር በታላቅ ድምቀት ይከበራል፤ ታዋቂ ያልሆኑ ሰዎች ልደትም እንዲሁ ይታሰባል፡፡ ለሰዉ ልጅ መዳን ምክንያት የሆነች የአምላክ እናት የተወለደችበት ቀን ግን ምንኛ ሊከበር ይገባዉ ይሆን!

#የግንቦት_ልደታ_በዓል_አከባበር
ሐናና ኢያቄም ከአይሁድ ለማምለጥ ተሰደዉ በአድባረ ሊባኖስ ስር  እመቤታችንን ወለዱ በወቅቱ ከቤት የወጡት ለሽሽት ነበርና ስንቅ ስላልያዙ ምግባቸዉ ‹‹ንፍሮና ጥራጥሬ›› ነበር፡፡ ይኼንን ትዉፊት በመያዝ በዓሉ ከቤት ዉጭ ንፍሮ እየተበላ ይከበራል፡፡ ሆኖም ግን በበጎ ነገሮች ሰበብ ክፉ ዓላማዉን ማስፈጸም የሚፈልገዉ ዲያቢሎስ በማር መሃል መርዝን ከሚጨምርባቸዉ መንፈሳውያት በዓላት አንዱ የግንቦት ልደታ የእመቤታችን በዓል ነዉ፡፡ አንዳንዶች በድፍረት ለአድባር ለዉጋር ነዉ ፣ቆሌዉን ለመለመን ነዉ፣ እያሉ ንፍሮ የሚበትኑ፣ ፈንድሻ የሚጥሉ፣ ቡና የሚረጩ፣ ቂቤ የሚቀቡ፣ የከብት ደም የሚያፈሱ፣  እነዚህ በእርግጥም ጣዖት አምላኪዎች ናቸዉ፡፡
🕊

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡

ግንቦት ፪ [ 2 ]

[ ግንቦት ፪ [ 2 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

🕊   ቅዱስ ኢዮብ   🕊

የትዕግስት አባት ቅዱስ ኢዮብ በቅዱስ መጽሐፍ ላይ እንደተመለከትነው ያልተፈተነበት ነገር የለም:: ሐረገ ትውልዱም ከአባታችን አብርሃም ይመዘዛል::

- አብርሃም ይስሐቅን
- ይስሐቅ ኤሳውን
- ኤሳው ራጉኤልን
- ራጉኤል ዛራን
- ዛራ ኢዮብን ይወልዳሉ::

ቅዱስ ኢዮብ የነበረው እሥራኤል በግብፅ በባርነት ሳሉ ነበር:: ኢዮብ ይሕ ቀረህ የማይሉት ባለጠጋ: ደግና እግዚአብሔርን አምላኪ ነበር:: የኢዮብ ደግነት የተመሰከረው በሰው [በፍጡር] አንደበት አልነበረም:: በራሱ በፈጣሪ አንደበት እንጂ::

በዚህ የቀና ጠላት ዲያብሎስ ግን ኢዮብን ይፈትነው ዘንድ ከአምላክ አስፈቀደ:: ጌታችን የጻድቁን የትዕግስት መጠን ሊገልጥ ወዷልና ሰይጣን ኢዮብን በሐብቱ መጣበት:: በአንድ ጀምበርም ድሃ ሆነ:: እርሱ ግን ፈጣሪውን ባረከ::

ሰይጣን ቀጠለ:- የአብራኩን ክፋዮች [ልጆቹን] አሳጣው:: ኢዮብ አሁንም አመሰገነ::

በሦስተኛው ግን ሰውነቱን በቁስል መታው:: ቁስል ሲባል በዘመኑ እንደምታዩት ዓይነት አልነበረም:: ከሰው ሕሊና በላይ የሆነ አሰጨናቂ ደዌ ነበር እንጂ:: ጻድቁ የአንድ ወጣት እድሜ ያሕል በመከራው ጽናት እየተሰቃየ ገላውን በገል ያከው ነበር:: ከአፉ ግን ተመስገን ማለትን አላቁዋረጠም::

በመጨረሻም ሰይጣን በሚስቱ መጣበት:: "እግዚአብሔርን ተሳደብ" አለችው:: እርሱ ግን መለሰ :- "እግዚአብሔር ሰጠ: እግዚአብሔርም ነሣ: ስሙ የተባረከ ይሁን::"

ከዚሕ ሁሉ ነገር በኋላ እግዚአብሔር ሰይጣንን ከጎዳናው አስወገደው:: ጤናውን: ሐብቱን: ልጆቹን ለኢዮብ መለሰለት:: ካለው እድሜ ላይ ፻፵ [140] ዓመት ጨመረለት:: ጻድቅና የትዕግስት ሰው ቅዱስ ኢዮብ በ፪፻፵፰ [248] ዓመቱ በዚሕች ቀን ዐረፈ::

እግዚአብሔር አምላክ ከጻድቁ ትዕግስትና በረከት
አይለየን::

🕊

[ † ግንቦት ፪ [ 2 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. ቅዱስ ኢዮብ ጻድቅ [ የትእግስት አባት ]
፪. አባ ቴዎድሮስ ሊቀ ምኔት [ የታላቁ ቅዱስ ዻኩሚስ ደቀ መዝሙርና የአቡነ አረጋዊ ጉዋደኛ ]
፫. ፳፪ "22" ሰማዕታት [ የአባ ኤሲ ማሕበር ]

[ †  ወርኃዊ በዓላት ]

፩፡ ቅዱስ ታዴዎስ ሐዋርያ
፪፡ ቅዱስ ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ
፫፡ ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ
፬፡ ቅዱስ አቤል ጻድቅ
፭፡ አባ ጳውሊ ገዳማዊ
፮፡ አባ ሕርያቆስ ዘብሕንሳ

" ወንድሞች ሆይ ! የመከራና የትዕግስት ምሳሌ የሆኑትን በጌታ ስም የተናገሩትን ነቢያትን ተመልከቱ:: እነሆ በትዕግስት የጸኑትን ብጹዓን እንላቸዋለን:: ኢዮብ እንደ ታገሠ ሰምታቹሃል:: ጌታም እንደፈጸመለት አይታቹሃል:: ጌታ እጅግ የሚምር: የሚራራም ነውና::" [ያዕ.፭፥፲] (5:10)

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ ]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
                        †                        

🕊  💖        ሰ ላ ም ታ        💖  🕊

'' ክርስቶስ ተንስአ እሙታን
▸ በዐቢይ ኃይል ወስልጣን ፤
አሠሮ ለሰይጣን
▸ አግዐዞ ለአዳም ፤
ሰላም
▸ እምይእዜሰ ፤
ኮነ
▸ ፍስሐ ወሰላም ''

🕊

'' ክርስቶስ በታላቅ በኃይልና ስልጣን ከሙታን ተነሳ ፤ ሰይጣንን አሰረው አዳምንም ነጻ አወጣው ፤ ስለዚህም ከእንግዲህ ወዲህ ፍፁም ሰላም እና ደስታ ሆነ። ''


†                       †                        †
💖                    🕊                     💖
                        †                        

🕊  💖   እለተ አርብ   💖   🕊

▬▬▬▬▬▬  †  ▬▬▬▬▬▬


†  🕊 ቅድስት ቤተ ክርስቲያን  🕊  †

በእውነት አብያተክርስቲያናትን ቸሩ ይጠብቅልን በቸርነቱ ይማረን።

[ 🕊 ✞ እንኩዋን ለዕለተ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንና ለነፍሳተ ብሉይ ዓመታዊ የመታሠቢያ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞ 🕊 ]

ከትንሳኤ ሳምንት ቀናት ይህች ዕለት ቤተ ክርስቲያን አንድም ነፍሳት በመባል ትታወቃለች::

🕊 ቅድስት ቤተ ክርስቲያን  🕊

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዓለም ሳይፈጠር በአምላክ ልቡና ታስባ : በዓለመ መላእክት ከታየች በኋላ :-

¤ አበው ተስፋ ሲያደርጓት
¤ ነቢያት ትንቢት ሲናገሩላት
¤ ሱባኤ ሲቆጥሩላት
¤ ምሳሌም ሲመስሉላት ኑረዋል::

† ዘመኑ በደረሰ ጊዜ በአምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ :-

¤ በመጸነሱ ተጸንሳ
¤ በመወለዱ ተወልዳ
¤ በጥበብና በሞገስ አብራው አድጋ
¤ በጥምቀቱ ተጠምቃ
¤ በትምሕርቱ ጸንታ
¤ በደሙ ተቀድሳ
¤ በትንሣኤው ከብራ
¤ በዕርገቱ ሰማያዊነቷን አጽንታ
¤ በበዓለ ሃምሳ መንፈስ ቅዱስ ወርዶላት በይፋ ለልጆቿ ተሰጥታለች::

ድንገት የተመሠረተች ሳትሆን ቅድመ ዓለም በአምላክ ልቡና የታሠበች: በዓለመ መላእክት የተወጠነች ናት:: በአማን ጐልታ: ግዘፍ ነስታ የተመሠረተችው ግን በደመ ክርስቶስ ተቀድሳ: በትንሳኤው ከብራ: ንጽሕትና ጽሪት ባደረጋት ጊዜ ነው:: መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ ባይነሳ ኖሮ ቤተ ክርስቲያን ሕልውና አይኖራትም ነበርና ይህች ዕለት ቤተ ክርስቲያን ተብላ ትከበራለች::

†  ነፍሳት   †

በብሉይ ኪዳን የነበሩና ለ ፭ ሺህ ፭ መቶ [ 5500 ] ዓመታት በሲዖል የተጋዙ ሰዎችን ያመለክታል:: እነርሱም ከአባታችን አዳም ጀምሮ በዓመተ ኩነኔ የነበሩ ሰዋች ሲሆኑ ደመ ክርስቶስ ቀድሷቸው: የትንሳኤው ብርሃን ደርሷቸው ወደ ገነት ስለ ገቡ በዚሁ ቀን ይታሠባሉ::

እግዚአብሔር ከአባቶች ነፍስና ከቅድስት ቤቱ በረከት አይለየን::

" መጽሐፍ እንደሚል ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን ሞተ: ተቀበረም:: መጽሐፍም እንደሚል በሦስተኛው ቀን ተነስቷል...  ከዚያም በሁዋላ ለያዕቆብ: ሁዋላም ለሐዋርያት ሁሉ ታየ:: ከሁሉም በሁዋላ እንደ ጭንጋፍ ለምሆን ለእኔ ደግሞ ታየኝ:: እኔ ከሐዋርያት ሁሉ የማንስ ነኝና:: የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ስላሳደድሁ ሐዋርያ ተብየ ልጠራ የማይገባኝ: ነገር ግን በእግዚአብሔር ጸጋ የሆንሁ እኔ ነኝ:: " [፩ቆሮ.፲፭፥፫-፲] (15:3-10)

†  ወስብሐት ለእግዚአብሔር   †

†                       †                        †
💖                    🕊                     💖
🕊

†  በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ
አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡  †

[ † ግንቦት ፫ [ 3 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት  † ]

🕊  ቅዱስ ያሶን ሐዋርያ  🕊 †

ባለንበት ዘመን አሳዛኝ ከሆኑ ነገሮች አንዱ የቅዱሳኑ ስማቸው ከነሥራቸው መዘንጋቱ ነው:: ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ደማቸው እንዳልፈሰሰ: አጥንታቸውም እንዳልተከሰከሰ ይሔው አስታዋሽ አጥተው ስማቸውም ተዘንግቶ ይኖራል::

አንዳንድ ንፉቃን ደግሞ ከዚሁ ብሶ ጭራሹኑ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ስለ ክርስቶስ ትታ ስለ ቅዱሳኑ ብቻ ትሰብካለች ይሉናል::

በእጅጉ ከሚያሳዝኑኝ ነገሮች አንዱ የቅዱሳን ሐዋርያት [የ፻፳ (120) ው ቤተሰብ] መዘንጋት ነው:: ከ፻፳ [120] ው ቤተሰብ የአብዛኞቹ ስም በመዘንጋቱ: ሊቃውንቱም ዝምታን በመምረጣቸው
"ያሶን: አርስጦስ: አፍሮዲጡ: ቆሮስ . . . እያልን የ፸፪ [72]ቱን አርድእት ስም ስንጠራ ግር የሚለው ዓይነት ትውልድ ተፈጥሯል::

እስኪ እንዲያው ቢያንስ ሐዋርያትንና ዐበይት ቅዱሳንን እናስባቸው:: አስበናቸው የሚጨመረልን እንጂ የሚጨመርላቸው የለምና::

ዛሬ የምናስበው ቅዱስ ያሶን ሐዋርያ ከ፸፪ [72] ቱ አርድእት አንዱ ነው:: ጌታችንን ከጥምቀቱ በኋላ ተከትሎ ለ፫ [3] ዓመታት ከእግሩ ሥር ቁጭ ብሎ ተምሯል:: ከጌታችን ዕርገት በኋላ መንፈስ ቅዱስን ተቀብሎ ለስብከተ ወንጌል ወጥቷል::

ለብዙ ጊዜ ከቅዱስ ዻውሎስ ጋር ተመላልሶ ሰብኳል:: በመከራውም ተካፍሎታል:: ታላላቆቹ ሐዋርያት ሰማዕትነትን ከተቀበሉ በኋላ ለመጣው አዲስ ክርስቲያን ትውልድ ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቃል በቃል የሰማውን አስተላልፏል::

ወንጌልን ስለ ሰበከላቸው አሕዛብ ብዙ ጊዜ አስረው ይደበድቡት: ያንገላቱት ነበር:: አንዳንድ ጊዜም እሳት እያነደዱ ያቃጥሉት ነበር:: ፈጣሪው ግን በተአምራት እያዳነው ከርሱ ጋር አልተለየም::

ከከተማ ወጥቶ በዱርና በእስር ቤቶች ብዙ ነፍሳትን: ሽፍቶችንም ሳይቀር ወደ ክርስትና ማርኳል:: ቅዱስ ያሶን ለረዥም ዓመታት ሰብኮ በመልካም ሽምግልና አርፏል::

🕊 ንግሥት ወለተ ማርያም 🕊

ዳግመኛ በዚህ ቀን ኢትዮዽያዊቷ እናታችን ቡርክት ወለተ ማርያም ትታሰባለች::

ወለተ ማርያም ማለት የደጉ አፄ ናኦድ ሚስት: የአፄ ልብነ ድንግልና የቅድስት ሮማነ ወርቅ እናት ናት:: በንግስትነት በቆየችባቸው ዘመናት [ ከ1487-1500 ዓ/ም ] የረሃብ ጊዜ በመሆኑ ብዙ ሕዝብ አልቆ ነበር::

ቡርክት ወለተ ማርያም ከጾምና ከጸሎት ባሻገር የተራቡትን በማብላት ብዙዎችን ታድጋለች:: የንጉሡን ቤተሰብ ወደ መልካም ክርስትና በመምራትም የተመሰገነች ነበረች:: በዚህ ቀንም አርፋ ተቀብራለች::

አምላካችን ከቅዱሳኑ በረከት አይለየን::

🕊

[ †  ግንቦት ፫ [ 3 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. ቅዱስ ያሶን ሐዋርያ [ከ፸፪ [72] ቱ አርድእት አንዱ]
፪. አባ ብሶይ ሰማዕት
፫. ቅዱስ አውሳብዮስ ቀሲስ
፬. ቡርክት ወለተ ማርያም ንግሥት [የዐፄ ልብነ ድንግል እናት]

[ †  ወርኃዊ በዓላት ]

፩፡ በዓታ ለእግዝእትነ ማርያም
፪፡ ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና
፫፡ ካህናት ዘካርያስ ወስምዖን
፬፡ አባ ሊባኖስ ዘመጣዕ
፭፡ አባ ዜና ማርቆስ
፮፡ አቡነ መድኃኒነ እግዚእ
፯፡ ቅዱስ ቄርሎስ ዓምደ ሃይማኖት
፰፡ ቅዱስ ስምዖን ዘዓምድ

" ሰብዓውም በደስታ ተመልሰው ጌታ ሆይ! አጋንንት ስንኳ በስምህ ተገዝተውልናል አሉት:: እንዲህም አላቸው . . . እነሆ እባቡንና ጊንጡን ትረግጡ ዘንድ በጠላትም ኃይል ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጥቻችሁአለሁ:: የሚጐዳችሁም ምንም የለም:: ነገር ግን መናፍስት ስለ ተገዙላችሁ በዚህ ደስ አይበላችሁ:: ስማችሁ ግን በሰማያት ስለ ተጻፈ ደስ ይበላችሁ:: " [ሉቃ.፲፥፲፯] (10:17)

ወስብሐት ለእግዚአብሔር።


[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ ]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
🕊

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †

[ † እንኩዋን ለጻድቁ አቡነ መልከ ጼዴቅ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ † ]


🕊  አቡነ መልከ ጼዴቅ  🕊

ኢትዮዽያዊው ጻድቅ አቡነ መልከ ጼዴቅን ብዙ ሰው ሽዋ [ሚዳ] ውስጥ በሚገኘው አስደናቂ ገዳማቸው ያውቃቸዋል:: ገዳሙ በእድሜ ጠገብ ዛፎች ያጌጠ ከመሆኑ ባሻገር በጻድቁ ቃል ኪዳን ምክንያት በቦታው የሚቀበር ሁሉ አካሉ አይፈርስም:: የጻድቁስ ዜና ሕይወታቸው እንደምን ነው ቢሉ :-

አቡነ መልከ ጼዴቅ በሸዋ ነገሥታት ዘመን የነበሩ: የንጉሱ ዓምደ ጽዮን የቅርብ ዘመድ ነበሩ:: የጻድቁ ወላጆች ፍሬ ጽዮንና ዐመተ ማርያም ይባላሉ:: አቡነ መልከ ጼዴቅ ገና በሕጻንነታቸው ሥርዓተ መንግስትን አጥንተዋል::

በሁዋላ ከመምሕር ዘንድ ገብተው ብሉይ ከሐዲስ ተምረው ሲያጠናቅቁ ይሕንን ዓለም ናቁና ከቤተ መንግስቱ አካባቢ ጠፍተው ወደ አቡነ አሮን መንክራዊ ዘንድ ሔደው መንኩሰዋል::

ነገሩ በቤተ መንግስት አካባቢ ሲሰማ ወላጆች አለቀሱ:: አቡነ አሮንም ተከሰው ነበር:: ነገሩ ግን ከእግዚአብሔር ነበርና አቡነ መልከ ጼዴቅን መልዐክ እየመራ አምጥቶ አሁን ገዳማቸው ያለበት ሸዋ [ሚዳ] አደረሳቸው::

በዚያ ትንሽ በዓት ሰርተው ለዘመናት ተጋድለዋል:: ዋሻዋም ደብረ መድኃኒት ትባላለች:: ጻድቁ ከጾምና ጸሎታቸው በተረፈ ዓርብ ዓርብ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሕማማት በማሰብ ጀርባቸውን ፫፻ [300] ጊዜ ይገርፉ: ደቀ መዛሙርቱንም ግረፉኝ ይሉ ነበር:: አንድ ጊዜም እጃቸውንና እግራቸውን በትልልቅ ችንካሮች ቸንክረውት ደማቸው ሲፈስ ተገኝቷል::

በመጨረሻ አቡነ መልከ ጼዴቅ ጌታን ኢትዮዽያውያንን ማርልኝ አሉት:: ጌታችንም መለሰ:- "በስምህ ያመኑትን: በቃል ኪዳንህ የተማጸኑትን: ገዳምሕን የተሳለሙትን እምርልሃለሁ::"

ጻድቁም ብዙ ተአምራትን ሰርተው በዚሕች ቀን አርፈዋል:: አቡነ አምሃ ኢየሱስም በክብር ገንዘው በበዓታቸው ውስጥ ቀብሯቸዋል::

አምላካችን እግዚአብሔር ከጻድቁ ዋጋና በረከት አይለየን::

🕊

[ † ግንቦት ፬ [ 4 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. አቡነ መልከ ጼዴቅ ካህን [ኢትዮዽያዊ ጻድቅ]
፪. አባ ዮሐንስ ሊቀ ዻዻሳት
፫. ቅዱሳን ሶሲማና ኖዳ ሰማዕታት [የታላቁ ፊቅጦር ተከታዮች የነበሩ]

[ †  ወርኀዊ በዓላት ]

፩. ቅዱስ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጉዋድ [ወንጌላዊው]
፪. ቅዱስ እንድርያስ ሐዋርያ
፫. ቅድስት ሶፍያ ሰማዕት
፬. ቅዱስ ዮሐንስ ዘሐራቅሊ [ሰማዕት]

" ከእናንተ የታመመ ማንም ቢኖር የቤተ ክርስቲያን ቀሳውስትን ወደ እርሱ ይጥራ:: በጌታም ስም እርሱን ዘይት ቀብተው ይጸልዩለት:: የእምነትም ጸሎት ድውዩን ያድናል:: ጌታም ያስነሳዋል:: ኃጢአትም ሠርቶ እንደ ሆነ ይሠረይለታል:: እርስ በርሳችሁ በኃጢአታችሁ ተናዘዙ:: ትፈወሱም ዘንድ እያንዳንዱ ስለ ሌላው ይጸልይ:: የጻድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኃይል ታደርጋለች:: " [ያዕ.፭፥፲፬]  (5:14)

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ ]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
2024/11/05 23:33:18
Back to Top
HTML Embed Code: