Telegram Web Link
🕊

[ ✞ እንኩዋን ለጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞ ]


✞  🕊  አቡነ ተክለ ሃይማኖት 🕊

ኢትዮዽያዊው ጻድቅና ሐዋርያ ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት በዚህች ቀን ከኢትዮዽያ ወደ ኢየሩሳሌም ተጉዘው ከቅዱሳት መካናት ተባርከዋል::

ጻድቁ ምድረ እሥራኤል የገቡት በየመንገዱ መንፈሳዊ ዘርን እየዘሩ: እያስተማሩና እያሳመኑ ነበር:: የወቅቱ ሊቀ ዻዻሳት አባ ሚካኤል ጋርም ተገናኝተው ቡራኬን ተሰጣጥተዋል::
+ዋናው ጉዳይ ግን ከዚህ በሁዋላ ነው::

ጻድቁ እመቤታችንና ጌታችን ከጽንሰታቸው እስከ ዕርገታቸው የረገጧቸውን ቦታዎች ሲመለከቱ በፍጹም ተደሞ እንባቸው ይፈስ ነበር:: ምክንያቱም እግዚአብሔር ስላበቃቸው ተክለ ሃይማኖት የሚያዩት ቦታውን አልነበረም:: በገሃድ:-
- በቤተ መቅደስ ብስራቱን
- በቤተ ልሔም ልደቱን
- በቤተ ዮሴፍ ግዝረቱን
- በፈለገ ዮርዳኖስ ጥምቀቱን
- በቤተ አልዓዛር ተአምራቱን ይመለከቱ ነበር::

የጉብኝታቸው የመጨረሻ ክፍል ወደ ሆነው ቀራንዮ ደርሰው ጌታቸውን እንደ ተሰቀለ ሆኖ ቢመለከቱት ከዓይናቸው ይፈስ የነበረው ቁጡ እንባ መልኩን ቀየረና ዓይናቸው ጠፋ::
በዚያች ቅጽበት ስም አጠራሯ የከበረ እመቤታችን ድንግል ማርያም ፈጥና ደርሳ ተክልየን ወደ ሰማይ አሳረገቻቸው::

በዚያም ፦

- የብርሃን ዐይን ተቀብለው
- ፮ ክንፍ አብቅለው
- የወርቅ ካባ ላንቃ ለብሰው
- ማዕጠንተ ወርቁን ይዘው
- ከ፳፬ቱ ካህናተ ሰማይም ተደምረው
- ሥላሴን በአንድነቱና ሦስትነቱ ተመልክተው
- "ስብሐት ወክብር ለሥሉስ ቅዱስ ይደሉ" ብለው መንበረ ጸባኦትን አጥነው ወደ መሬት ተመልሰዋል::

የተክለ ሃይማኖት አምላክ ከጻድቁ ትሩፋት: ጸጋና በረከት ይክፈለን::

† አባ ይስሀቅ †

በዚች ቀን ከግብፅ ደቡብ ከእብክ አውራጃ ከሆሪን ከተማ የከበረ አባት ይስሀቅ አረፈ። የዚህም ቅዱስ የአባቱ ስም አብርሀም የእናቱም ስም ሶስና ነው ታናሽም ሆኖ ሳለ እናቱ ሙታ ብቻውን ያለእናት አባቱ እያሳደገው ኖረ።

ጥቂት በአደገም ጊዜ የአባቱን በጎች የሚጠብቅ ሆነ አባቱም ሌላ ሚስት አገባ በዚያ ወራትም ታላቅ ረኃብ ሆነ የአባቱም ሚስት ትጠላው ነበረ ከጥቂትም በቀር እንጀራ አትሰጠውም ያንኑም ሁልጊዜ ለእረኞች ሰጥቶ እርሱ ግን እስከምሽት ይፈፀማል።

ምሳውን ለእረኞች እንደሚሰጥና ሁልጊዜ እስከምሽት እንደሚፆም አባቱ ሰምቶ እውነት እንደሆነ ሊያይ ወደርሱ ሄደ። ቅድሱም ህፃን የአባቱን መምጣት አውቆ በልብሱ ሶስት ጭቃ አድበልብሎ አሰረ እንደ ታሰረ በሚያየው ጊዜ ለአባቱ አምባሻ እንዲመስለው ብሎ።

አባቱም በመጣ ጊዜ የልጁን ልብስ ፈትቶ አየ አንባሻም ሆነው አገኛቸው።የነገረውንም ሰው ምግቡን ለእረኞች ከሰጠ በዛሬይቱ ቀን ይህ አምባሻ ከወዴት ተገኘለት ብሎ ጠየቀው እርሱም በእውነት ሰጥቷል አለ ሌሎችም ብዙዎች መጥተው በዚህ ነገር ምስክሮች ሆኑ አባቱም አደነቀ እግዚአብሄርንም አመሰገነ።

ይህም በአደገ ጊዜ አባ ኤልያስ ወደሚባል ሰው ሄዶ መንኩሶ በዚያ እየተጋደለ ብዙ አመታት ኖረ። አባ ኤልያስም በአረፈ ጊዜ በርኑግ ወደሚባል ገዳም ሄደ ስሙ ዘካርያስ ከሚባል አረጋዊ ዘንድ በታላቅ ገድል ተጠምዶ ኖረ።

አባቱም ያገኘው ዘንድ በሀገሮች ሁሉ ይዞር ነበረ በዚህ በበርኑግ ገዳምም በአገኘው ጊዜ ከእርሱ ጋራ እንዲመለስ አባቱ ለመነው አይሆንም አለ አባ ዘካርያስም ከአባቱ ጋራ ይሄድ ዘንድ እስከ ሚአርፍም ከእርሱ ዘንድ እንዲኖር አዘዘው ይህ ቅዱስም ከአባቱ ጋራ ሄዶ እስከሚአርፍ ድረስ ከእርሱ ዘንድ ኖረ።

አባቱም በአረፈ ጊዜ አባቱ የተወውን ገንዘብ ሁሉንም ለድኆችና ለምስኪኖች ሰጠ ከከተማውም ጥቂት ራቅ ብሎ ለራሱ ታናሽ ማደሪያ ሰራ በሰላም እሰከ ሚአርፍባት ቀን ድረስ ያለ ማቋረጥ በበጎ ገድል በፆም በፀሎት በስግደት ኖረ በአረፈ ጊዜም በመልካም ቦታ አኖሩት ከዚያም ተሰወረ።

ከብዙ ዘመናትም በኃላ እግዚአብሄር ሊገልጠው ወዶ በመቃብሩ ላይ መብራት ሲበራ እህል ለሚአጭዱ ሰዎች ሶስት ቀን ያህል ታየ ሊያዩትም ወደቦታው ሲደርሱ ያ መብራት ከእርሳቸው ይሰወራል በሁሉ ዘንድ እስቲሰማም እንዲህ ሆኖ ኖረ።

ከዚህም በኃላ በመቃብሩ ላይ እያበራ ያ መብራት ደግሞ ታያቸው ስጋውም በዚያ እንዳለ ሁለተኛ በህልም ነገራቸው ምእመናንም አክብረው በግመል ጭነው ወደ ሀገሩ መካከል ወደ ሆሪን ወሰዱት ነስሪን ከሚባል ሀገር መካከል ሲደርሱ ግመሉ በዚያ ተንበረከከ እንዲነሳም መቱት መነሳትንም እቢ አለ መኖሪያው በዚያ ይሆን ዘንድ የእግዚአብሄር ፈቃድ እንደሆነ አወቁ።

በዚያም በስሙ ቤተ ክርስቲያን ሰርተው ስጋውን በውስጥዋ አኖሩ ሰርተው ስጋውን በውስጥዋ አኖሩ ከእርሱም ብዙ ድንቆች ተአምራቶች ተገለጡ።

🕊 † ቅዱስ እለእስክንድሮስ   †  🕊

በዚች ቀን የከበረ አባት የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳትም አስራ ዘጠነኛ የሆነ እለእስክንድሮስ አረፈ። ስለርሱም ሀዋርያዊ አባት አትናቴዎስ እንዲህ አለ አባቴ እለእስክንድሮስ ተቀምጦ ወንጌልን አያነብም ቁሞ ያነባል እንጂ ከርሱ ጋራም ብርሀን አለ።

ሁለተኛው ስለርሱ ሲናገር ወደርሱ እመምኔቶች መጥተው በእኛ ዘንድ ሰባት ሰባት ቀን የሚሶሙ ደናግል አሉ ።በእጆቻቸውም ምንም ምን ስራ አይሰሩም ብለው ነገሩት።

እርሱም እህቶቼ ሆይ እኔ ሁለት ቀን እንኳን ከቶ አልፆምኩም ፀሀይ እስኪገባው ቆይቼ አልበላሁም በልክ እበላለሁ በልክም እፆማለሁ በልክ በመጠንም እሰራለሁ በልክ ይበሉ ዘንድ በልክም ይፆሙ ዘንድ በልክም ስራ ይሰሩ ዘንድ ነግሯቸው በበጎ ስራ ሁሉ ይሰለፉ አለ።

የዚህም ቅዱስ ወላጆቹ ደጎች ምእመናን ናቸው እርሱም በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ውስጥ ሆኖ ከታናሽነቱ ጀምሮ በውስጥዋ አደገ።አባ መክሲሞስ አናጒን ስጢስነት አባ ቴዎናስ ዲቁና ተፍፃሜተ ሰማእት ጴጥሮስም ቅስና ሹመውታልና እርሱም ከታናሽነቱ ጀምሮ ንፅህ ድንግል ነው።

አባ ጴጥሮስ በሰማእትነት የሚሞትበት ጊዜ ሲቀርብ በግዞት ቤት ሳለ ይህ እለእስክንድሮስና አኪላስ ከውግዘቱ ይፈታው ዘንድ ስለ አርዮስ ወደርሱ ገብተው ለመኑት ስለርሱ አባ ጴጥሮስን ይማልዱለት ዘንድ ሁለቱን ለምኖአቸዋልና።

አባት ጴጥሮስ ግን በውግዘት ላይ ውግዘትን ጨመረበት እንዲህም ብሎ ነገራቸው የክብር ባለቤት ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ የተቀደደ ልብስ ለብሶ ተገለፀልኝ ልብሴን አርዮስ ቀደዳት አለኝ። ይህም የባህርይ አንድነቴን ለያት ማለት ነው ውግዘቱንም እንድጨምርበት እርሱ አዘዘኝ።

ደግሞ እንዲህ ገለጠላቸው አኪላስ ሊቀ ጵጵስና እንዲሾም ከርሱ በኃላም እለእስክንድሮስ እንደሚሾም አርዮስን እንዳይቀበሉት በምንም ስራው እንዳይተባበሩት አዘዛቸው።

አባ ጴጥሮስም ምስክርነቱን በፈፀመ ጊዜ አኪላስ ሊቀ ጵጵስና ተሾመ የአባት ጴጥሮስንም ትእዛዝ ተላልፎ አርዮስን ከውግዘቱ ፈታው። ቅስናም ሾመው ስለዚህም አኪላስ በመንበረ ሲመቱ ያለ ስድስት ወር አልኖረም በድንገት ሞተ።

ከዚህ በኃላ ይህ አባት እለእስክንድሮስ ሊቀ ጵጵስና ተሹሞ በመንበረ ሲመቱ ላይ ተቀመጠ አርዮስንም ከወገኖቹ ጋራ አውግዞ አሳደደው። የሀገር ታላላቆችም ከህዝቡ መጡ ከውግዘቱ እንዲፈታውም ለመኑት። በውግዘት ላይ ውግዘትን እንዲጨምር እንጂ እንዳይፈታው አባት ጴጥሮስ እንደአዘዘው ነገራቸው።

ከዚህ በኃላ አርዮስ ወደ ንጉስ ቈስጠንጢኖስ ሂዶ በግፍ አወገዘኝ ብሎ እለእስክንድሮስን ከሰሰው። ስለዚህም ንጉሱ ሶስት መቶ አስራ ስምንት የከበሩ አባቶችን በኒቅያ ከተማ ሰበሰበ።
ይህም አባት እለእስክንድሮስ ተመርጦ ለጉባኤው ሊቀ መንበር ሆነ አትናቴዎስ ፀሀፊ ነበር ።አርዮስንም ተከራክረው ክህደቱን ግልፅ አደረጉ ስለ ጌታ

ችን ኢየሱስ ክርስቶስም ከአባቱ ከአብ ጋራ ከህይወቱ መንፈስ ቅዱስም ጋራ በመለኮቱ ትክክል እንደሆነ አስረዱት።

ከክህደቱ ባልተመለሰ ጊዜ አውግዘው ለይተው ከቤተ ክርስቲያን አሳደዱት። በአንድ ቃልም ፀሎተ ሀይማኖትን ከአባቶች ጋራ ሰሩልን ደግሞ በእርሳቸው ቤተ ክርስቲያን ለዘላለም የምትመራባቸው ሀያ ቀኖናን ሰርተው ወሰኑ።

ከዚህ በኃላም ይህ አባት እለእስክንድሮስ ወደ መንበረ ሲመቱ ከደል ጋራ ተመለሰ። በበጎ አጠባበቅም መንጋውን ጠበቀ በወንጌላዊ ማርቆስ መንበርም አስራ ሰባት አመት ኖሮ በሰላም አረፈ።

🕊 † አባ ሚካኤል ዘእስክንድርያ † 🕊

በዚችም ቀን የከበረ አባት አባ ሚካኤል የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት አረፈ እርሱም ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ሀምሳ ሶስተኛ ነው። ይህም ቅዱስ ፃድቅ መንኲሶ በአስቄጥስ በቅዱስ ዮሀንስ ገዳም አበ ምኔት ሆኖ ተሾመ ከዚያም ያለ ፈቃዱ ወስደው በግድ ሊቀ ጵጵስና በእስክንድርያ አገር ላይ ኀዳር ሀያ አራት ቀን ሾሙት።

በሊቀ ጵጵስናውም ስራ ተጠምዶ የሚጋደል ሆነ እንደ ሀዋርያትም አጠባበቅ መንጋውን ጠበቀ። ታላቁ ፆምም በደረሰ ጊዜ ወደ አስቄጥስ በዚያ ሊፆም ወጣ ከመሾሙ በፊት በዚያ ገዳም ውስጥ በብህትውና ሆኖ መጠመዱንና የቀድሞ መጋደሉን አሰበ።

ወደ ጌታችንም እንዲህ ብሎ ለመነ አቤቱ እኔ በብቸኛነት መኖርን እንደምሻ አንተ ታውቃለህ ለዚች ለተሾምኩባትም ሹመት ችሎታ የለኝምና የምትገባኝም አይደለችምና በይቅርታህም ብዛት ነፍሴን ወስደህ ከዚህ ድካም ታሳርፈኝ ዘንድ እለምንሀለሁ ጌታም ልመናውን ተቀበለ ከፋሲካ በአል በኃላም በፍቅር አንድነት አረፈ።የሹመቱም ዘመን ሁለት አመት ከአምስት ወር ነው።

[ †  ሚያዝያ ፳፪ [ 22 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት
፪. ቅዱስ እለእስክንድሮስ ሊቅ [ አርዮስን ያወገዘ ]
፫. አባ ይስሐቅ ጻድቅ
፬. አባ ማርቆስ ሐዲስ
፭. አባ ሚካኤል ዘኢየሩሳሌም
፮. አባ ሚካኤል ዘእስክንድርያ

[ † ወርኀዊ በዓላት ]

፩. ቅዱስ ዑራኤል ሊቀ መላእክት
፪. ቅዱስ ሉቃስ ወንጌላዊ
፫. ቅዱስ ደቅስዮስ [ የእመቤታችን ወዳጅ ]
፬. አባ እንጦንዮስ [ አበ መነኮሳት ]
፭. አባ ዻውሊ የዋህ

" ንጉሡ ዖዝያን በሞተበት ዓመት እግዚአብሔርን በረዥምና ከፍ ባለ ዙፋን ላይ ተቀምጦ አየሁት:: የልብሱም ዘርፍ መቅደሱን ሞልቶት ነበር:: ሱራፌል ከእርሱ በላይ ቆመው ነበር:: ለእያንዳንዱ ስድስት ክንፍ ነበረው:: በሁለት ክንፍ ፊቱን ይሸፍን ነበር:: በሁለቱም ክንፍ እግሮቹን ይሸፍን ነበር:: በሁለቱም ክንፍ ይበር ነበር:: አንዱም ለአንዱ 'ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ምድር ሁሉ ከክብሩ ተሞልታለች' እያለ ይጮህ ነበር:: " [ኢሳ.፮፥፩-፬]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
                         †                         

🕊    †    ሰሙነ ሕማማት   †    🕊

▬▬▬▬▬▬  †  ▬▬▬▬▬▬

           [   ሕማማት ዘረቡዕ   ]


[ † ምክረ አይሁድ ይባላል † ]

ረቡዕ እለት የአይሁድ ሊቃነ ካህናትና ጸሐፍት ጌታን እንዴት መያዝ እንዳለባቸው የመከሩበትና ውሳኔ ያሳለፉበት ቀን በመሆኑ ምክረ አይሁድ ይባላል። ወቅቱ የፋሲካን በዓል የሚያከብሩበት ቀን በመሆኑ እና ብዙ ህዝብም ጌታን ይከተለው ስለነበር ሁከት እንዳይነሳ ስጋት ነበራቸው ። ነገር ግን ከአስራ ሁለቱ ሐዋርያት አንዱ የአስቆሮቱ ይሁዳ አሳልፎ እንደሚሰጣቸው ስለነገራቸው [ ሉቃ ፳፪፥፩-፮ ] ጭንቀታቸው ተወግዶ በጌታ መያዝ ተስማምተዋል።

[ † የመልካም መዓዛ ቀንም ይባላል † ]

ጌታችን በዚህ ዕለት በለምጻሙ በስምዖን ቤት ተቀምጦ ሳለ መላ ሕይወቷን ለዝሙት አስገዝታ ትኖር የነበረችው ማርያም እንተ እፍረት [ ባለሽቶዋ ማርያም] ዋጋው እጅግ ውድ የሆነ የአልባጥሮስ ሽቱ አምጥታ በራሱ ላይ በማርከፍከፍ ስለቀባቸው [ ማቴ ፳፮፥፮-፯ ] የመዓዛ ቀን ይባላል።

[ † የእንባ ቀን ይባላል † ]

ባለሽቱዋ ሴት [ ማርያም እንተ እፍረት ] ኃጢአቷን ይቅር እንዲላት እየለመነች በእግሩ ስር ተደፍታ በእንባዋ እግሩን አርሳለችና [ ማር ፲፬፥፱ ] የእንባ ቀን ይባላል።

▬▬▬▬▬▬  †  ▬▬▬▬▬▬

- [  ብፁዕ አቡነ እንድርያስ ስለ ሰሙነ ሕማማት ያስተማሩት ትምህርት [ ክፍል - ፩ - ]


- [  የሰሙነ ሕማማት ዘረቡዕ [ በሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ]

💖    ድንቅ ትምህርት   💖

         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
                        👇
🕊

[ † እንኩዋን  ለታላቁ ሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ ዓመታዊ የሰማዕትነት በዓል በሰላም አደረሳችሁ † ]

🕊   †  ዐቢይ ወክቡር : ጊዮርጊስ: ሰርዌ አዕላፍ : ወመክብበ ሰማዕታት  †     🕊


መጽሐፈ ገድሉ እንደሚለው የሰማዕታት አለቃቸው: አንድም ሞገሳቸው ታላቅና ክቡር ሰማዕት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ፯ [7] ዓመታት ስቃይ በሁዋላ በዚህ ቀን ተሰይፏል:: ይሕስ ጥንተ ነገሩ እንደምን ነው ቢሉ :-

- ቅዱሱ የተወለደው ከአባቱ ዘረንቶስ [አንስጣስዮስ] እና ከእናቱ ቴዎብስታ የድሮው ፋርስ ግዛት ፍልስጥኤም [ልዳ] ውስጥ ነው:: የተባረኩ ወላጆቹ ክርስትናን ጠንቅቀው አስተምረውት አባቱ ይሞታል::

ቅዱስ ጊዮርጊስ ፳ [20] ዓመት ሲሞላው የአባቱን ስልጣን እጅ ለማድረግ ሲሔድ የቢሩት [የአሁኗ ቤይሩት-ሊባኖስ] ሰዎች ዘንዶ [ደራጎን] ሲያመልኩ አገኛቸው:: እርሱ ግን የከተማውን ሕዝብ አስተምሮ: አሳምኖ: ደራጎኑንም በፈጣሪው ኃይል ገድሎ መንገዱን ቀጥሏል::

ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ዱድያኖስና ፸ [70] ነገሥታት ዘንድ ሲደርስ ክርስቶስ ተክዶ ለጣዖት ይሠገድ ነበር:: በዚያች ሰዓት ድንግል እመቤታችን ወደ ሰማዕቱ መጥታ መከራውንና ክብሩን ነገረችው:: እርሱም በክርስቶስ ስም መሞት ምርጫው ነበርና ከእመቤታችን ተባርኮ ወደ ምስክርነት አደባባይ [ዐውደ ስምዕ] ደረሰ::

ከዚያም ለተከታታይ ፯ [7] ዓመታት ብዙ ጸዋትወ መከራዎችን ተቀበለ:: ፫ [3] ጊዜ ሙቶ ተነሳ:: ከሰው ልጅ የተፈጥሮ ትዕግስት በላይ የሆነ ስቃይን ስለ ቀናች ሃይማኖት ሲል በመቀበሉ የሰማዕታት አለቃቸው: ፀሐይና የንጋት ኮከብ በሚል ይጠራል::

"ተውላጠ ጻማሁ ወሕማሙ:
ዘተለዐለ ሞገሰ ስሙ" እንዲል መጽሐፍ::

ቅዱስ ጊዮርጊስን ለዘመናት በብዙ ስቃያት ሲያስጨንቁት ኖረው በጽናቱ አሸነፋቸው:: ፸ [70] ነገሥታትን ከነ ሠራዊታቸው ከማሳፈሩ ባሻገርም በርካታ [በመቶ ሺ የሚቆጠሩ] አሕዛብን ማርኮ ለሰማዕትነት አበቃ::

በዚህ የተበሳጨ ዱድያኖስም ኮከበ ፋርስ ቅዱስ ጊዮርጊስን እንዲቆራርጡት አዘዘ:: ወታደሮቹም ቅዱሱን ቆራርጠው: በብረት ምጣድ ላይ ጠበሱት:: ያለ ርሕራሔም አካሉን አሳረሩት:: ቀጥለውም ፈጭተው አመድ አደረጉት::

በአካባቢው ወደ ነበረው ትልቅ ተራራ ጫፍ [ደብረ ይድራስ)] ወጥተውም በነፋስ በተኑት::
"ሐረድዎ ወገመድዎ: ወዘረዉ ሥጋሁ ከመ ዓመድ" እንዲል:: [ምቅናይ]

እነርሱ ይህንን ፈጽመው ዘወር ሲሉ ግን የቅዱሱ ዓጽም ባረፈባቸው ዛፎች: ቅጠሎችና ድንጋዮች ሁሉ "ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማዕታት" የሚል ጽሑፍ ተገኘ::

ወዲያው ግን ኃያል ሰማዕት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከተበተነበት ተነስቶ ወታደሮችን አገኛቸውና "በክርስቶስ እመኑ" ብሎ: አስደንቆ ወደ ሕይወት መራቸው:: ፸ [70] ው ነገሥታት ግን አፈሩ::
ከ፯ [7] ዓመታት መከራ በሁዋላም በዚሕች ቀን ከብዙ ተዓምራት ጋር ተሰይፎ ደም: ውሃና ወተት ከአንገቱ ፈሷል:: ፯ [7] አክሊላትም ወርደውለታል::

በ፫፻፺ [390] ዎቹ አካባቢ [ሰማዕት ከሆነ ከጥቂት ዓመታት በሁዋላ] በዚያው በሃገሩ ደብር አንጸው: አጽሙን አፍልሠው ቀድሰዋታል::
ቅዱሱ ሰማዕት ከሰማዕትነቱ በፊትም ሆነ በሁዋላ ተአምረኛ ነው:: በዘመኑ የክርስቲያኖችን ደም ሲያፈሱ ከነበሩ አራዊት [ነገሥታት] መካከል አንዱ የሆነው ዲዮቅልጢያኖስ ርጉም የ፵፯ [47] ሚሊየን ክርስቲያኖችን ደም አፍስሶ ነበርና ፈጣሪ ደመ ሰማዕታትን የሚበቀልበት ጊዜ ደረሰ::

በ፫፻፭ [305] ዓ/ም አካባቢ አረመኔው ንጉሥ ስለ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ተአምረኛነት ሰምቶ እንዲያፈርሱት ሠራዊት ላከ:: የሠራዊቱ አለቃም ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ገብቶ በቅዱስ ጊዮርጊስ ስዕል ላይ ተሳለቀ::

ከፊቱ የነበረውን ቀንዲል በሰይፍ እመታለሁ ሲል ግን ቀንዲሉ ተገልብጦ መሐል አናቱን መታው:: እንደ እብድ ሆኖ ሞተ:: ሠራዊቱም ሰምቶ ወደ ንጉሡ ሸሸ:: ይሕን ሰምቶ የተበሳጨው ዲዮቅልጢያኖስ ግን ራሱ ሊያፈርሰው ሔደ:: ከቤተ ክርስቲያኑ በር ላይ ሲደርስ ሚካኤልና ገብርኤል ዐይኑን አጠፉት::

እገባለሁ ሲል ቅዱስ ጊዮርጊስ ከላይ መረዋውን [ደወሉን] ለቀቀበት:: ራሱን ቢመታው ደነዘዘ:: የብዙ ቅዱሳንን ደም የጠጣው ርጉሙ ንጉሥም አብዶ ለ፯ [7] ዓመታት ፍርፋሪ ሲለምን ኑሮሰ ይጣን ከገደል ጫፍ ወርውሮ ገድሎታል::

አምላካችን እግዚአብሔር ከኃያሉ ሰማዕት ጽናትና ትእግስት: ከበረከቱም ይክፈለን::

🕊

[ † ሚያዝያ ፳፫ [ 23 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማዕታት
፪. ቅዱስ ሮቆ ጻድቅ [በስሙ ለተማጸነ ከወባ በሽታ እንዲጠብቀው ጌታ ቃል ኪዳን ገብቶለታል]

[ † ወርኀዊ በዓላት ]

፩. ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት
፪. ቅዱስ ሰሎሞን ንጉሠ እስራኤል
፫. አባ ጢሞቴዎስ ገዳማዊ
፬. አባ ሳሙኤል
፭. አባ ስምዖን
፮. አባ ገብርኤል

" የሚበልጠውን ትንሳኤ እንዲያገኙ እስከ ሞት ድረስ ተደበደቡ:: ሌሎችም መዘበቻ በመሆንና በመገረፍ ከዚህም በላይ በእስራትና በወኅኒ ተፈተኑ:: በድንጋይ ተወግረው ሞቱ:: ተፈተኑ: በመጋዝ ተሰነጠቁ: በሰይፍ ተገድለው ሞቱ:: ሁሉን እያጡ: መከራን እየተቀበሉ: እየተጨነቁ: የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ:: ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ: በዋሻና በምድር ጉድጉዋድ ተቅበዘበዙ:: " [ዕብ.፲፩፥፴፭-፴፰] (11:35-38)

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
#ዕሮብ
#የመልካም_መዓዛ_ቀን ይባላል።
★ ጌታችን በዚህ ዕለት ስምኦን ቤት ተቀምጦ ሳለ፣ መላ ህይወቷን ለዝሙት አስገዝታ ትኖር የነበረችው ማርያም እንተ እፍረት (ባለሽቶዋ ማርያም)፤‹‹ከእንግዲህ ወዲህ በኃጢአት ተበላሽቶ ይኖር የነበረውን ሕይወቴን እንደዚህ መልካም ሽቱ የሚጣፍጥ፣ ኃጢአትን ይቅር የሚል አምላክ መጣ›› ስትል ዋጋው እጅግ በጣም ውድ የሆነ፣ ከሦሰት መቶ ዲናር በላይ የሚያወጣ፣ በአልባስጥሮስ ብልቃጥ የተሞላ ሽቱ ይዛ በመሄድ በጠጉሩ(በራሱ)ላይ በማርከፍከፍ ስለቀባችው ረቡዕ የመዓዛ ቀን ተብሎ ይጠራል፡፡

#የዕንባ_ቀን ይባላል።
★ ማርያም እንተ እፍረት በጌታችን እግር ላይ ተደፍታ፣ መላ ኃጢአቷን ይቅር አንዲላት በእንባዋ እግሩን አጥባዋለችና፣ በጠጉሯም በእንባዋ ያጠበችውን እግሩን አብሰዋለችና፡፡ (ማቴ፳፮፥ ፮፣ ማር ፲፬፥ ፱፣ ዮሐ ፲፪፥ ፰)

#መልካም__ሕማማት🙏

አጫጭር ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶች
•➢ 👇 ለማግኘት // 👇

@Enatachn_mareyam
@Enatachn_mareyam
2024/09/29 17:26:28
Back to Top
HTML Embed Code: