Telegram Web Link
🕊

[ † እንኳን ለአባ መክሲሞስ ሊቀ ዻዻሳት ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን። † ]

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †

🕊  † አባ መክሲሞስ ሊቀ ዻዻሳት †   🕊

† "ዻዻስ" ማለት "አባት - መሪ - እረኛ" ማለት ነው:: በቅድስት ቤተ ክርስቲያን አስተምሕሮ በሐዲስ ኪዳን የመንፈሳዊ ስልጣን ደረጃዎች በጥቅሉ ፫ ናቸው:: እነሱም ፦
- ዲቁና:
- ቅስና:
- ዽዽስና ሲሆኑ በሥራቸው ወደ ፱ ያህል ክፍሎች አላቸው:: ከእነዚህም ከፍተኛው ስልጣን ዽዽስና ነው::

ዽዽስና ማለት የክርስቶስን መንጋ እንደ ባለቤቱ አድርጐ መጠበቅ ማለት ነው:: ሥልጣኑ በምድር "ሸክም" : "ዕዳ" ሲሆን በሰማይ ግን "ክብር" ነው:: ማንም በሥጋው ላይ ካልጨከነ በቀር ዽዽስናን አይመኝም::

ቅዱስ ዻውሎስ "ሠናየ ግብረ ፈተወ - ማንም ዽዽስናን ቢመኝ መልካም ሥራን ተመኘ" [፩ጢሞ.፫፥፩] ማለቱን ይዞ "ሹሙኝ" ማለት ወደ ማይጠፋ እሳት የሚያስጥል ከባድ ውሳኔ ነው:: ምክንያቱም አንድ ክርስቲያን የሚጠየቅ በራሱ ኃጢአት ሲሆን አንድ ካህን ደግሞ ስለ ልጆቹ ይጠየቃል:: የከፋው ግን የዻዻሱ ነው::

አንድ ዻዻስ ቢጾም ቢጸልይም እንኩዋ ለድኅነቱ በቂ አይደለም:: ምክንያቱም በመንበሩ ላይ ያስቀመጠው መንጋውን እንጂ ራሱን እንዲያድን አይደለምና:: ጌታ እንዳለ መልካም እረኛ "ይሜጡ ነፍሶ ቤዛ አባግኢሁ - መልካሙ እረኛ ስለ በጐቹ ቤዛ ራሱን አሳልፎ የሚሰጥ ነው::" [ዮሐ.፲]  ስለዚህም ክህነት [ዽዽስና] ሐዋርያዊ አገልግሎት: ከባድም ኃላፊነት ነው::

አባቶቻችን ሐዋርያትና ተከታዮቻቸው ሐዋርያውያን ታላላቅ የዽዽስና መንበሮችን መሥርተው: ትምሕርቱን ከነ ወንበሩ አስተላልፈዋል:: ከእነዚህ መንበረ ዽዽስናዎች ፬ቱ የበላይ ናቸው::

† እነዚህም ፦
- የቅዱስ ዼጥሮሱ የሮም:
- የቅዱስ ዮሐንሱ የአንጾኪያ:
- የቅዱስ ማርቆሱ የእስክንድርያና
- የቅዱስ ዻውሎሱ የኤፌሶን መናብርት ናቸው::

እነዚህ መንበሮችም ከክርስቶስ ዕርገት እስከ ፬፻፵፫ [፬፻፶፩] ዓ/ም {ጉባኤ ኬልቄዶን} ድረስ በአንድነት ቆይተው ተለያይተዋል:: ከእነዚህ መናብርት መካከል የእስክንድርያው [የግብጹ] እና የአንጾኪያው [የሶርያው] ዛሬም ድረስ በተዋሕዶ እምነት የጸኑ ናቸው::

የእኛ ቤተ ክርስቲያንም ሐዋርያዊት እንደ መሆኗ ሐዋርያትን መስለው: ሐዋርያትን አህለው የተነሱ አበው ዻዻሳትን በየጊዜው በበዓላት ታስባለች: ታከብራለች::

በተለይ ደግሞ የእስክንድርያና የአንጾኪያ በርካታ አባቶችን እናከብራለን:: እነርሱ ለቀናች ሃይማኖትና ለመንጋው ሲሉ ብዙ መከራን በአኮቴት ተቀብለዋልና:: ከእነዚህም መካከል አንዱ አባ መክሲሞስ ነው::

አባ መክሲሞስ የእስክንድርያ [ግብጽ] ፲፭ኛ ፓትርያርክ ሲሆን በ፫ኛው መቶ ክ/ዘመን ቤተ ክርስቲያንን ለ፲፭ ዓመታት አገልግሏል:: ቅዱሱ ከልጅነቱ ጀምሮ ምስጢረ ሃይማኖትን የተማረ ሲሆን መናኝ ሰው እንደ ነበርም ይነገርለታል::

በደቀ መዝሙርነትም ለአባ ያሮክላ [፲፫ኛው ሊቀ ዻዻሳት] እና ለአባ ዲዮናስዮስ [፲፬ኛው ሊቀ ዻዻሳት] በትህትና አገልግሏል:: ዲቁናና ቅስና ሹመት ያገኘውም በዚህ ጊዜ ነው::

ፓትርያርክ ሆኖ ከተመረጠ በሁዋላም ምዕመናንን በአፍም : በመጣፍም ብሎ አስተምሯል:: በዚህም መንጋውን ከተኩላ የመጠበቅ ተግባርን ከውኗል:: በተለይ ደግሞ ዓለማቀፍ መናፍቃን የሆኑትን ማኒንና ሳምሳጢን ተዋግቷል:: ትግሉም ተሳክቶ መናፍቃኑ ተወግዘዋል::

ቅዱሱ አባት አባ መክሲሞስ [ ማክሲሙስ ] ከዚህም የሚበልጥ ብዙ በጐ ሥራ ሠርቶ በበጐ ዕረፍት በዚህች ቀን ዐርፏል::

† አምላከ ቅዱሳን ስለ አባቶቻችን ብሎ ለመንጋው የሚራራ እረኛን ይስጠን:: ከቅዱሱ በረከትንም ይክፈለን::

🕊

[ † ሚያዝያ ፲፬ [ 14 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. አባ መክሲሞስ ሊቀ ዻዻሳት

[ † ወርሐዊ በዓላት ]

፩. አቡነ አረጋዊ [ ዘሚካኤል ]
፪. ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ መርዓዊ
፫. ቅዱስ ፊልዾስ ሐዋርያ
፬. ቅዱስ ሙሴ [የእግዚአብሔር ሰው]
፭. አባ ስምዖን ገዳማዊ
፮. አባ ዮሐንስ ጻድቅ
፯. እናታችን ቅድስት ነሣሒት

" ስለዚህ በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያንን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ዻዻሳት አድርጎ ለሾመባት: ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ:: ከሄድሁ በሁዋላ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኩላዎች እንዲገቡባችሁ እኔ አውቃለሁ:: ስለዚህ ፫ ዓመት ሌሊትና ቀን በእንባ እያንዳንዳችሁን ከመገሰጽ እንዳላቁዋረጥሁ እያሰባችሁ ትጉ:: " † [ሐዋ.፳፥፳፰]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
#ኒቆዲሞስ

በአይሁድ አደባባይ ፍርድ ስትጓደል
ሌት ተቀን ሲመክሩ “ሺ’ዎች አንድ” ለመግደል
ጸሐፍት ልሂቃኑ ምሁራን በሙሉ
ሕግ ተርጉመናል ‘ፈራጆች’ ነን ያሉ
በጨለማ ምክር ‘መምህሩን’ ሊገድሉ
የሚይዙበትን ስልት መንገድ ሲቀይሱ
ተግቶ የሚፈልግ ሐቅን በመንፈሱ
ሌት እየጠበቀ እየተነጠለ
ከእውነተኛው መምህር ‘እግር ሥር የዋለ’
ከተመከረበት ተሰቅሎ እንዲገደል
ሲረዳ የነበር ምሥጢር ሲያደላድል
በፍትሕ መጓደል ልቡ እየታመመ
ኹሉ አውቀው ሲክዱ ለእውነት የቆመ
ኒቆዲሞስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ
ብቻውን ቢቀርም ሐቅ የመሰከረ
የተሰቀለውን በክብር የቀበረ!

የሰው ልጆች ኹሉ በሐሰት ቢቆሙ
እውነትን ለመቅበር ሌት ተቀን ቢደክሙ
ምን ብዙ ቢመከር ምን ብዙ ቢለፋም
ሐቁን የሚናገር አንድ ሰው አይጠፋም
ቁጥሩን አንድ ብለን በአሃዝ ሳንበይነው
ሐቁን ያወጣው 'ለት "አንድ ሰው" ስንት ነው
???
                   
             #_ሰናይ__ቀን🙏

ለመቀላቀል 👇👇👇👇
@Enatachn_mareyam  
@Enatachn_mareyam
🕊

[ ✞ እንኩዋን ለታላቁ ነቢይና ሰማዕት "ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞ ]

🕊  † ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ  †   🕊

ቅዱስ ወንጌል ላይ ከእመቤታችን ቀጥሎ የነዘካርያስን ቤተሰብ ያህል ክብሩ የተገለጠለት ፍጡር ይኖራል ብሎ መናገሩ ይከብዳል:: ቅዱስ ሉቃስ ወንጌሉን የጀመረው በዚህ ቅዱስ ቤተሰብ ነውና መንፈስ ቅዱስ እንዲህ ሲል አጽፎታል:: "ዘካርያስ ካህኑና ቅድስት ኤልሳቤጥ በሰውና በእግዚአብሔር ፊት ያለ ነቀፋ የሚኖሩ ጻድቃን ነበሩ" ይላቸዋል:: [ ሉቃ.፩፥፮ ]

የሰውን እንተወውና በእግዚአብሔር ፊት ያለ ነቀፋ መኖር ምን ይረቅ? ለዚህ አንክሮ [አድናቆት] ይገባል! እሊህ ቅዱሳን ባልና ሚስት ግን መካኖች በመሆናቸው ልጅ ሳይወልዱ ዘመናቸው አልፎ ነበር:: እንደ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት ዕድሜአቸው የኤልሳቤጥ ፺ [90] የዘካርያስ ፻ [100] ደግሞ ደርሶ ነበር::

ፍጹም መታገሳቸውን የተመለከተ ጌታ በስተእርጅናቸው ከሰው ሁሉ በላይ የሆነ: ትንቢት ለብቻው የተነገረለት [ኢሳ.፵፥፫ (40:3) , ሚል.፫፥፩ (3:1) ] ታላቅ ነቢይን ይሰጣቸው ዘንድ መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤልን ላከላቸው::

ቅዱስ ዘካርያስ ሰው ነውና ከደስታ ብዛት በመከራከሩ ድዳ ሆነ:: ቅድስቲቷ ግን መስከረም ፳፮ [26] ቀን ታላቁን ሰው ጸንሳ ለ፮ [6] ወራት ራሷን ሠወረች:: በ፮ [6] ኛው ወር የፍጥረት ሁሉ ጌታ በተጸነሰ ጊዜ የአርያም ንግሥት ድንግል እመቤታችን ደጋ ደጋውን ወደ ኤልሳቤጥ መጣች:: ሁለቱ ቅዱሳት የእህትማማች ልጆች ናቸው::

የአምላክ እናቱ ስትደርስና "ሰላም" ስትላቸው መንፈስ ቅዱስ በእናትና ልጅ ወርዶ ኤልሳቤጥ በምስጋና: ዮሐንስ ደግሞ ገና በማሕጸን ሳለ በደስታ ዘለለ [ሰገደ]:: ከዚህ በሁዋላ ሰኔ ፴ [30] ተወልዶ: አባቱ ዘካርያስ "ዮሐንስ" ሲለው አንደበቱ ተፈትቶለታል::

ቅዱስ ዮሐንስ ከተወለደ ፪ [2] ዓመት ከ፮ [6] ወር በሆነው ጊዜ ሰብአ ሰገል በመምጣታቸው በእሥራኤል ምድር የሚገኙ ሕጻናትን ሔሮድስ ቁዝ አስፈጀ:: ትንሽ ቆይቶም አይሁድ ለሔሮድስ ስለ ቅዱሱ ሕጻን ነገሩት:: "ሲጸነስ የአባቱን አንደበት የዘጋ: ሲወለድ ደግሞ የከፈተ 'ዮሐንስ' የሚባል ሕጻን አለና እሱንም ግደል" አሉ::

እናቱ ቅድስት ኤልሳቤጥ ይዛው ስትሸሽ ካህኑን ዘካርያስን ግን በቤተ መቅደስ መካከል ገድለውታል:: አረጋይት ኤልሳቤጥም ሕጻኑን እያሳደገች በገዳመ ዚፋታ ለ፫ [3] ፭ [5] ዓመታት ቆይታለች:: ቅዱስ ዮሐንስ ፭ [5] ፯ (7) ዓመት ሲሞላው ግን እዚያው በበርሃ እናቱ ዐረፈች:: ከሰማይ ዘካርያስና ስምዖን ወርደው ቀበሯት::

ሕጻኑ ዮሐንስ ሲያለቅስ ድንግል ማርያም ስንት አገር አልፋ ሰማችው:: እርሷም ስደት ላይ ነበረችና:: ከጌታ ጋር በደመና ሒደው ድንግል አቅፋ አጽናናችው:: ጌታንም "እንውሰደው ይሆን?" አለችው:: ጌታችን ግን "ለአገልግሎት እስክጠራው እዚህ ይቆይ" አላት:: ባርካው: አጽናንታውም ተለያዩ::

ቅዱስ ዮሐንስ ከዚህ በኋላ በዚያ ቆላ የግመል ጠጉር ለብሶ: ጠፍር ታጥቆ ተባሕትዎውን ቀጠለ:: ለ ፳፭ [25] ፳፫ [23 ዓመታትም በንጽሕና ሲኖር ከምድር አራዊትና ከሰማይ መላእክት በቀር ማንንም አላየም:: ይሕችን ዐመጸኛ ዓለምም አልቀመሳትም::

ከዚህ በኋላ ፴ [30] ዘመን ሲሞላው እግዚአብሔር ከሰማይ ተናገረው:: "ሒድ! የልጀን ጐዳና ጥረግ" አለው:: ነቢያት ስለዚህ ነገር ተናግረው ነበርና::[ኢሳ.፵፥፫ (40:3) , ሚል.፫፥፩ (3:1)] አባቱ ዘካርያስም "ወአንተኒ ሕጻን ነቢየ ልዑል ትሰመይ: እስመ ተሐውር ቅድመ እግዚአብሔር ከመ ትጺሕ ፍኖቶ" [ሉቃ.፩፥፸፮ (1:76) ብሎ መንገድ ጠራጊነቱን ተናግሮ ነበርና::

ቅዱስ ዮሐንስ በዚያ ጊዜ በኃይለ መንፈስ ቅዱስ እየገሰገሰ ከበርሃ ወደ ይሁዳ መጣ:: ያዩት ሁሉ ፈሩት: አከበሩት:: ቁመቱ ቀጥ ያለ: ጽሕሙ እንደ ተፈተለ ሐር የወረደ: ጸጉሩ የቁራ ያህል የጠቆረ: መልኩ የተሟላ: ግርማው የሚያስፈራ ገዳማዊ ነውና::

ፈጥኖም ሕዝቡን ለንስሃ ሰበከ: ለንስሃም በርካቶችን አጠመቃቸው:: በዚህ አገልግሎት ለ፮ [6] ወራት ቆይቶ ጌታችን ወደ እርሱ ዘንድ መጣ:: ዮሐንስ ሰማይን ከነግሱ: ምድርን ከነልብሱ የያዘ ፈጣሪ 'አጥምቀኝ' ብሎ ሲመጣ ደነገጠ:: የሚገባበትም ጠፋው::

"እንቢ ጌታየ! አንተ አጥምቀኝ" አለው:: ጌታ ግን "ፈቅጄልሃለሁ" አለው: አጠመቀው:: በዚህ ምክንያት ይሔው እስከ ዛሬም "መጥምቀ መለኮት" ሲባል ይኖራል:: ቅዱስ ዮሐንስ በመጨረሻ ሔሮድስን ገሰጸው:: ንጉሡም ተቀይሞ ለ፯ [7] ቀናት አሠረው::

በዚህች ቀንም ልደቱን ባከበረ ጊዜ ወለተ ሔሮድያዳ በዘፈን አጥምዳ አስማለችው:: እርሱም የታላቁን ነቢይ ራስ አስቆርጦ በወጪት አድርጐ ሰጣት:: አበው "እምሔሶ ለሔሮድስ ይብላዕ መሐላሁ - ሔሮድስ መሐላውን በበላ በተሻለው ነበር" ይላሉ:: የቅዱስ ዮሐንስ ራሱ በርራ ስትሔድ አካሉን ግን ደቀ መዛሙርቱ ቀብረውታል:: [ማቴ.፫፥፩ (3:1) , ማር.፮፥፲፬ (6:14) , ሉቃ.፫፥፩ (3:1) , ዮሐ.፩፥፮ (1:6)]

ርጉም ሔሮድስ አንገቱን ካስቆረጠው በኋላ የመጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ ራሱ የጸጋ ክንፍ ተሰጥቷት ጌታችን ወዳለበት ደብረ ዘይት ሔዳ በፊቱ ሰገደች:: ቅዱሳን ሐዋርያትበኋላ በአዩት ነገር ተገርመው ራሱን እጅ ነሷት::

ከዚሕ በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱስ ዮሐንስ ራስ የማስተማር ስልጣን ሰጥቶ አሰናበታት:: በመላው ዓለም ለ፲፭ [15] ዓመታት ስትሰብክ ኑራ በዚህች ቀን ዓረቢያ ውስጥ ዓርፋለች::

" አስማተ-ዮሐንስ መጥምቅ/ የመጥምቁ ዮሐንስ ስሞች"

፩. ነቢይ
፪. ሐዋርያ
፫. ሰማዕት
፬. ጻድቅ
፭. ካሕን
፮. ባሕታዊ/ገዳማዊ
፯. መጥምቀ መለኮት
፰. ጸያሔ ፍኖት [መንገድ ጠራጊ]
፱. ድንግል
፲. ተንከተም [የብሉይና የሐዲስ መገናኛ ድልድይ]
፲፩. ቃለ አዋዲ [ አዋጅ ነጋሪ ]
፲፪. መምሕር ወመገሥጽ
፲፫. ዘየዐቢ እምኩሉ [ ከሁሉ የሚበልጥ]

ጌታችን መድኃኔ ዓለም የመጥምቁ ዮሐንስን ምትረት አስቦ ይቅር ይበለን:: ጸጋውን: በረከቱንና ክብሩንም ያሳድርብን::

🕊

[ ሚያዝያ ፲፭ [ 15 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት [ጸዐተ ነፍሱ]
፪. ቅዱስ ኒቆላዎስ ዘሃገረ ሜራ [ከ፫፻፲፰ [318] ቱ ሊቃውንት]
፫. ቅዱስ አጋቦስ ሐዋርያ [ከ፸፪ [72] ቱ አርድእት]
፬. ቅድስት እለእስክንድርያ ሰማዕት
፭. አቡነ አቢብ ጻድቅ

" ጌታ ኢየሱስ ለሕዝቡ ስለ ዮሐንስ ሊናገር ጀመረ . . . ምን ልታዩ ወጣችሁ? ነቢይን? አዎን እላችሁአለሁ ከነቢይም የሚበልጠውን . . . እውነት እላቹሃለሁ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሳም. . . ነቢያት ሁሉና ሕጉ እስከ ዮሐንስ ድረስ ትንቢት ተናገሩ:: ልትቀበሉትስ ብትወዱ ይመጣ ዘንድ ያለው ኤልያስ ይሕ ነው:: የሚሰማ ጀሮ ያለው ይስማ:: " [ማቴ.፲፩፥፯ (11:7-15) ]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †


[  ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


🕊                     💖                       🕊
🕊

[ † እንኳን ለቅዱስ አንቲቦስ ሐዋርያ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን። † ]

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ! †

🕊   †  ቅዱስ አንቲቦስ  †   🕊

† በዚህ ቀን ታላቁ ሐዋርያና ሰማዕት ቅዱስ አንቲቦስ ይታሰባል:: ቅዱሱ በአርማ በምትባል ሐገር በእረኝነት (ጵጵስና) ያገለገለ የቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ደቀ መዝሙር ነው::

ቅዱሱ ስለ ክርስቶስ መንጋ ብዙ መከራን ተቀብሏል:: በእሥር ቤት ሳለም ከቅዱስ ዮሐንስ ነባቤ መለኮት [ወንጌላዊ] ክታብ [መልእክት] ደርሶታል:: በክታቡም ከሐዋርያትና ሰማዕታት መቆጠሩን ነግሮታል:: ጊዜው 1ኛው ክ/ዘ ሲሆን ክታቧ ከእኛ አልደረሰችም::

ከቅዱስ ዮሐንስ እግር ቁጭ ብሎ በመማሩ እንደ መምሕሩ የንጽሕና ሰው ነበር:: ከብዙ ዓመታት አገልግሎት በኋላ ስለ ፍቅረ ክርስቶስ በዚሕች ቀን በሰማዕትነት አልፏል::

በታላቁ ቅዱስ መጽሐፍ ደግሞ የዚህ ቅዱስ ስም መጠቀሱን ምስራቅ ኦርቶዶክሶች ያምናሉ:: በዮሐንስ ራዕይ.፪፥፲፪ [2:12] ላይ የእኛው [ግዕዙ] "ጻድቅየ መሃይምን" ሲለው የግሪኩ ግን በቀጥታ በስሙ "አንቲጳስ [አንቲቦስ] ብሎ ይጠራዋል፡፡ እርሱም በታናሽ እስያ ከነበሩት 7 አብያተ ክርስቲያናት የአንዱ [የጴርጋሞን] አለቃ የነበረ ሲሆን ሰማዕት መሆኑም በዚሁ ምዕራፍ ላይ ተጠቅሷል ፡፡

"በጴርጋሞንም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ:: በሁለት ወገን የተሳለ ስለታም ሰይፍ ያለው እንዲህ ይላል:: የሰይጣን ዙፋን ባለበት የምትኖርበትን አውቃለሁ ፤ ስሜንም ትጠብቃለህ ፥ ሰይጣንም በሚኖርበት ፥ በእናንተ ዘንድ የተገደለው የታመነው ምስክሬ አንቲጳስ በነበረበት ዘመን እንኳ ሃይማኖቴን አልካድህም:: ዳሩ ግን ለጣዖት የታረደውን እንዲበሉና እንዲሴስኑ በእስራኤል ልጆች ፊት ማሰናከያን ሊያኖርባቸው ባላቅን ያስተማረ የበልዓምን ትምህርት የሚጠብቁ በዚያ ከአንተ ጋር ስላሉ ፥ የምነቅፍብህ ጥቂት ነገር አለኝ:: እንዲሁ የኒቆላውያንን ትምህርት እንደ እነዚህ የሚጠብቁ ሰዎች ከአንተ ጋር ደግሞ አሉ:: እንግዲህ ንስሐ ግባ ፤ አለዚያ ፈጥኜ እመጣብሃለሁ፥ በአፌም ሰይፍ እዋጋቸዋለሁ:: መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ:: ድል ለነሣው ከተሰወረ መና እሰጠዋለሁ ፥ ነጭ ድንጋይንም እሰጠዋለሁ ፥ በድንጋዩም ላይ ከተቀበለው በቀር አንድ ስንኳ የሚያውቀው የሌለ አዲስ ስም ተጽፎአል:: [ራዕይ.፪፥፲፪] [2:12-17]

† አምላካችን ከቅዱስ አንቲቦስ በረከትን ያሳትፈን::

[ † ሚያዝያ ፲፮ [ 16 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. ቅዱስ አንቲቦስ ዘሃገረ በአርማ [ሐዋርያዊ ጳጳስና ሰማዕት]
፪. ቅዱስ ሳባ ሰማዕት

[ † ወርኀዊ በዓላት ]

፩. ኪዳነ ምሕረት [ የሰባቱ ኪዳናት ማሕተም ]
፪. ቅድስት ኤልሳቤጥ [ የመጥምቁ ዮሐንስ እናት ]
፫. ቅዱስ ገብረ ማርያም ጻድቅ ንጉሠ ኢትዮጵያ [ የቅዱስ ላሊበላ ወንድም ]
፬. ቅዱስ አኖሬዎስ ንጉሥ ጻድቅ
፭. አባ አቡናፍር ገዳማዊ
፮. አባ ዮሐንስ ወንጌሉ ዘወርቅ
፯. አባ ዳንኤል ጻድቅ

" የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሯችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ:: የኑሯቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነት ምሰሏቸው:: ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትና ዛሬ: እስከ ዘለዓለምም ያው ነው:: ልዩ ልዩ ዓይነት በሆነ በእንግዳ ትምሕርት አትወሰዱ:: ልባችሁ በጸጋ ቢጸና መልካም ነው እንጂ በመብል አይደለም:: በዚህ የሚሠሩባት አልተጠቀሙምና:: " † [ዕብ. ፲፫፥፯]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
🕊

[ † እንኩዋን ለታላቁ "ሐዋርያ ቅዱስ ያዕቆብ" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ † ]


🕊  †  ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ †  🕊

በቅድስት ቤተ ክርስቲያን አስተምሕሮ ከእመቤታችን በቀር ከቅዱሳን ሐዋርያት የሚበልጥ አልተነሳም:: "ሐዋርያ" ማለት "ፍንው: ልዑክ: የተላከ: የጽድቅ መንገደኛ" እንደ ማለት ነው:: በምሥጢሩ ግን "ባለሟል" ብለው ሊቃውንቱ ተርጉመውታል::

ይህስ እንደምን ነው ቢሉ  ፦

¤ የፍጥረታት ሁሉ ጌታ: የክብር ባለቤት መድኃኔ ዓለም ከድንግል ማርያም ተወልዶ: አድጐ: ተጠምቆ: ጾሞ: ከገዳመ ቆረንቶስ ሲመለስ ቀዳሚ ሥራው ያደረገው ደቀ መዛሙርቱን መጥራት ነበር::

ከተከተሉት የ ፭ ገበያ ሕዝብ መካከል "ወሐረየ እምሰብአ ዚአሁ አሠርተ ወክልኤተ ሐዋርያተ" እንዲል በመጀመሪያ ፲፪ቱን ሐዋርያት መረጠ::

እሊህም ፦

፩. ዼጥሮስ የተባለ ስምኦን
፪. እንድርያስ [ ወንድሙ ]
፫. ያዕቆብ ወልደ ዘብዴዎስ
፬. ዮሐንስ [ ወንድሙ ]
፭. ፊልዾስ
፮. በርተሎሜዎስ
፯. ቶማስ
፰. ማቴዎስ
፱. ያዕቆብ ወልደ እልፍዮስ
፲. ታዴዎስ [ ልብድዮስ ]
፲፩. ናትናኤል [ ቀናተኛው ስምዖን ] እና
፲፪. ማትያስ [ በይሁዳ የተተካ ] ናቸው:: [ማቴ.፲፥፩]

እነዚህን ፲፪ አርድእቱን ከጠራ በሁዋላ ለ፫ ዓመታት ከ፫ ወራት ከዋለበት ሲማሩ ይውሉ ነበር:: ሌሊት ደግሞ ምሥጢር ሲያስተረጉሙ ያድሩ ነበር::

ጌታ እንደሚገባ ካስተማራቸው በሁዋላ ከፍ ያለ ኃላፊነትን ሾማቸው:: ለዓለም እረኞች: የእርሱም ባለሟሎች ሆኑ:: እጅግ ብዙ መከራ እንደሚገጥማቸው ነገራቸው:: [ማቴ.፲፥፲፮, ዮሐ.፲፮፥፴፫] በዚያው ልክ ክብራቸውንም አከለላቸው:: [ማቴ.፲፱፥፳፰]

ሥልጣናቸው ደግሞ እስከዚህ ድረስ ሆነ:: "በምድር ያሠራችሁት በሰማይ የታሰረ ይሆናል: በምድር የፈታችሁት በሰማይ የተፈታ ይሆናል::" [ማቴ.፲፰፥፲፰]  "ይቅር ያላችሁዋቸው ኃጢአታቸው ይቀርላቸዋል: ያላላቹሃቸው ግን አይቀርላቸውም::" [ዮሐ.፳፥፳፫]

የመንግስተ ሰማያትን መክፈቻ [ማቴ.፲፮፥፲፱] : እረኝነትን [ዮሐ.፳፩፥፲፭] ተቀበሉ:: ጌታ በንጹሕ አንደበቱ ሐዋርያቱን እጅግ ሲያከብራቸው "ጨው: የዓለም ብርሃናት" [ማቴ.፭፥፲፫] አላቸው:: ወንድሞቹም ተባሉ:: [ዮሐ.፯፥፭] ከዚህም በሚበልጥ በሌላ ክብር አከበራቸው::

ከዚህ ሁሉ ነገር በሁዋላ በጌታ ሕማማት ጌዜ ገና ነበሩና አንዳንዶቹ ፈርተው ተበተኑ:: ተመልሰው ግን በጽርሐ ጽዮን ሲጸልዩ ሰንብተው የጌታን ትንሳኤ ተመለከቱ:: እጆቹን: እግሮቹንም ዳስሰው ሐሴትን አደረጉ::

ለ፵ ቀናት መጽሐፈ ኪዳንን: ትምሕርተ ኅቡዓት: ሌላም በፍጡር አንደበት የማይነገር ብዙ ምሥጢራትን ተምረው: ጌታ ሊቀ ዽዽስናን ሹሟቸው ዐረገ::

ለ፲ ቀናት በእመ ብርሃን ሥር ተጠልለው ሲጸልዩና በአንድ ልብ ሲተጉ ሰንብተው መንፈስ ቅዱስ ወረደላቸው:: በአንዴም ከፍርሃት ወደ ድፍረት ተመልሰው ፍጹማን: ብርሃናውያን ሆኑ:: ፸፩ ልሳናትን ነስተው በአንዲት ስብከት ብቻ ፫ ሺ ነፍሳትን ማረኩ:: [ሐዋ.፪፥፵፩]

ቅዱሳን ሐዋርያት በኅብረት ለአንድ ዓመት ያህል በኢየሩሳሌምና በዙሪያዋ እየተመላለሱ አስተምረው ብዙ እሥራኤላውያንን ወደ ክርስትና ማርከዋል:: ከዚህ በሁዋላ ግን እንደ ትውፊቱ በዚህች ቀን ዓለምን በእጣ ለ፲፪ ተካፈሏት::

ይህ ሲሆን መንፈስ ቅዱስ አብሯቸው ነበርና ለእያንዳንዳቸው እንደሚገባቸው አሕጉረ ስብከቶች ደረሷቸው:: እነርሱም ደቀ መዛሙርቶቻቸውን አስከትለው ለታላቁ መንፈሳዊ ዘመቻ ወረዱ::

በሔዱበት ቦታም ከተኩላ: ከአንበሳና ከነምር ጋር ታገሉ:: በጸጋቸውም አራዊትን [ክፉ ሰዎችን] ወደ በግነት መልሰው ለክርስቶስ አስረከቡ:: በየሃገሩ እየሰበኩ ድውያንን ፈወሱ:: ለምጻሞችን አነጹ:: እውራንን አበሩ:: አንካሶችን አረቱ:: ጐባጦችን አቀኑ:: ሙታንንም አስነሱ:: እልፍ አእላፍ አሕዛብንም ወደ መንጋው ቀላቀሉ::

ስለዚህ ፈንታም ብዙዎቹ በእሳት ተቃጠሉ:: ቆዳቸው ተገፈፈ:: በምጣድ ተጠበሱ:: ደማቸው በምድር ላይ ፈሰሰ:: ከአንድ ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ በቀር ሁሉም ይህችን ዓለም በሰማዕትነት ተሰናበቱ:: ጨው ሆነው አጣፍጠዋልና: ብርሃንም ሆነው አብርተዋልና እናከብራቸዋለን:: "አባቶቻችን: መምሕሮቻችን: ጌቶቻችንና ሊቆቻችን" እንላቸዋለን::

🕊  ✞  ቅዱስ ያዕቆብ ✞   🕊

በዚህ ቀን ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ ወልደ ዘብዴዎስ ሰማዕት ሆኗል:: ቅዱሱ ሐዋርያ አባቱ ዘብዴዎስ: እናቱ ማርያም ባውፍልያ: ትንሽ ወንድሙ ደግሞ ዮሐንስ ወንጌላዊ ይባላል::

ከ፲፪ቱ ሐዋርያት አንዱ ሲሆን አሳ አጥማጅነቱን ትቶ: ከጌታችን እግር ተምሮ በዓለም ወንጌልን አስፋፍቷል:: [ማር.፩፥፲፱] ከሌሎቹ ሐዋርያት በተለየም የእንስሳትን ቁዋንቁዋ ያውቅ ነበር::

በመጽሐፍ ቅዱስ በሔሮድስ መገደሉ [ሰማዕትነቱ] የተነገረለት ከ፲፪ቱ ብቸኛው ነው:: ሰማዕት የሆነውም በ፵፬ ዓ/ም : ማለትም ከጌታ ዕርገት ፲ ዓመታት በሁዋላ : ሐዋርያት ለስብከተ ወንጌል ወደ ዓለም ሳይበተኑ ነው:: [ሐዋ.፲፪፥፩]

እግዚአብሔር ከቅዱስ ያዕቆብና ከቅድስት ቤቱ በረከት አይለየን::

🕊

[ † ሚያዝያ ፲፯ [ 17 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ ወልደ ዘብዴዎስ [ከ፲፪ቱ ሐዋርያት]

[ †  ወርኀዊ በዓላት ]

፩. ቅዱስ እስጢፋኖስ ሊቀ ዲያቆናት [ቀዳሜ ሰማዕት]
፪. ቅዱስ ኤዺፋንዮስ ዘቆዽሮስ
፫. ቅዱሳን አበው መክሲሞስና ዱማቴዎስ
፬. አባ ገሪማ ዘመደራ
፭. አባ ዸላሞን ፈላሢ
፮. አባ ለትጹን የዋህ

" በዚያም ዘመን ንጉሡ ሄሮድስ መከራ ያጸናባቸው ዘንድ ከቤተ ክርስቲያኑ በአንዳንዶቹ ላይ እጁን ጫነባቸው:: የዮሐንስንም ወንድም ያዕቆብን በሰይፍ ገደለው:: አይሁድንም ደስ እንዳሰኛቸው አይቶ ጨምሮ ዼጥሮስን ደግሞ ያዘው:: የቂጣ በዓልም ወራት ነበረ:: " [ሐዋ.፲፪፥፩]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
🕊

✞ ሚያዝያ ፲፰ [18] ✞

[ ✞ እንኩዋን ለጻድቅና ሰማዕት "አባ ዼጥሮስ" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞ ]

🕊  ጻድቅና ሰማዕት አባ ዼጥሮስ   🕊

ሰማዕትነት በክርስትና ለሃይማኖት የሚከፈል የመጨረሻው ዋጋ [መስዋዕትነት] ነው:: ሰው ለፈጣሪው ሰውነቱን ሊያስገዛ: ሃብት ንብረቱን ሊሰጥ ይችላል:: ከስጦታ በላይ ታላቅ ስጦታ ግን ራስን አሳልፎ መስጠት ነው::

ራስን መስጠት በትዳርም ሆነ በምናኔ ውስጥ ይቻላል:: የመጨረሻ ደረጃው ግን ሰማዕትነት ነው:: "አማን መነኑ ሰማዕት ጣዕማ ለዝ ዓለም: ወተዓገሡ ሞተ መሪረ በእንተ መንግስተ ሰማያት" እንዳለው ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ ሰማዕትነት ማለት መራራውን ሞት ስለ ፍቅረ እግዚአብሔር ሲሉ መታገስ ነው::

እርሱ ቅሉ መድኃኒታችን ክርስቶስ የሰማይና የምድር ጌታ ሲሆን ኃፍረተ መስቀልን ታግሦ ሙቶልን የለ! በዓለም ያሉ ብዙ እምነቶች ስለ መግደል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ያስተምራሉ:: ክርስትና ግን መሞትን እንጂ መግደልን የሚመለከት ሕግ የለውም::

እርሱ ባለቤቱ "ጠላቶቻችሁን ውደዱ: የሚረግሟችሁን መርቁ: ስለሚያሳድዷችሁ ጸልዩ" ብሎናልና:: [ማቴ.፭፥፵፬]  ነገር ግን ዕለት ዕለት ራሳችንን በሃይማኖትና በምግባር ካልኮተኮትነው ክርስትና በአንድ ጀምበር ፍጹም የሚኮንበት እምነት አይደለምና በፈተና መውደቅ ይመጣል::

በተለይ የዘመኑ ክርስቲያን ወጣቶች ልናስተውል ይገባናል:: የቀደሙ ወጣት ሰማዕታት ዜና የሚነገረን እንድንጸና ነውና::

ቅዱስ አባ ጴጥሮስም ከዘመነ ሰማዕታት ፍሬዎች አንዱ ነው። በዚያ የመከራ ዘመን [፫ኛው መቶ ክ/ዘ] ግብፅና ሶርያ በብዙ መከራ ውስጥ ሳሉ በርካታ ቅዱሳን ተሰውተዋል፡፡ በተለይ በግብፅ ደግሞ ብዙ ንጹሐን አበውና ቅዱሳት አንስት መከራውን ታግሠው ለክብር በቅተዋል፡፡

ከእነዚሁ አንዱ የሆነው አባ ጴጥሮስ ገና ከልጅነቱ ጣዕመ ክርስትናን የተማረው ከአሳዳጊው [ከአክስቱ] ነበር፡፡ በፍፁም ልቡ የሚወደው ወንድም እና ባልንጀራም ነበረው፡፡ ስሙ ደግሞ አባ ብሶይ ይሰኛል፡፡ ሁለቱም በበጎ ምግባር ተኮትኩተው ፡ ዓለምንም ንቀው በርሃ ገብተው ፡ በጾም በጸሎት ተወስነው ብዙጊዜ ኑረዋል፡፡

በመከራው ዘመን ደግሞ ክርስቶስን ስላመለኩ ብቻ ተከሰው ታስረዋል፡፡ ተገርፈው ተደብድበዋል፡፡ ጭንቅ ስቃይንም በትእግስት አሳልፈዋል፡፡ በፍጻሜውም አባ ጴጥሮስ በዚህች ቀን ተሰውቶ ለክብር አክሊል በቅቷል፡፡ ወዳጁና ወንድሙ ቅዱስ ብሶይም በክብር ገንዞ ቀብሮታል፡፡

አምላከ ሰማዕታት ከጸናች ገድላቸው ፡ ከበዛች ትእግስታቸው ፡ ከፍጹም በረከታቸው ያሳትፈን፡፡

🕊

[ † ሚያዝያ ፲፰ [ 18 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. ቅዱስ አውሳብዮስ ሰማዕት
፪. አባ ዼጥሮስ ሰማዕት
፫. ሰማዕታተ ጠርሴስ

[ †  ወርሐዊ በዓላት ]

፩. ቅዱስ ፊልዾስ ሐዋርያ
፪. አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ሰባኬ ሃይማኖት [ረባን]
፫. አቡነ አኖሬዎስ ዘደብረ ጽጋጋ
፬. ማር ያዕቆብ ግብፃዊ

" በድካም : አብዝቼ በመገረፍ: አብዝቼ በመታሠር: አትርፌ በመሞት ብዙ ጊዜ ሆንሁ:: በድካምና በጥረት: ብዙ ጊዜም እንቅልፍ በማጣት: በራብና በጥም: ብዙ ጊዜም በመጦም: በብርድና በራቁትነት ነበርሁ . . . የቀረውን ነገር ሳልቆጥር ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው:: " [፪ቆሮ.፲፩፥፳፫]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
2024/09/29 21:27:37
Back to Top
HTML Embed Code: