Telegram Web Link
                       †                        

🕊       ጳጉሜ / ጾመ ዮዲት         🕊

🌼

በስመ አብ : ወወልድ : ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።

ጳጉሜ ማለት ጭማሪ ማለት ነው፡፡ ይህም በዓመቱ መጨረሻ ላይ አምስት ወይም ስድስት ቀን በመሆን የምትመጣ ናት፡፡ በአራት ዓመት አንዴ ማለትም በዘመነ ዮሐንስ ጳጉሜ ስድስት ቀን ይሆናል፡፡ በዚህም ሐገራችን ኢትዮጵያ የአሥራ ሦስት ወራት ጸጋ / Thirty months of sunshine / በመባል ትታወቃች ፡፡

ጳጉሜ በዘመነ ዮሐንስ ስድስት በምትሆንበት ጊዜ ጾመ ነቢያት /የገና ጾም/ ህዳር ፲፬ [14] ቀን ይገባና ታህሳስ ፳፰ [28] ቀን ጾሙ ተፈቶ የልደት በዓል ይከበራል፡፡

በቅድስት ቤተክርስቲያን ካሉት ሁለት የፈቃድ አጽዋማት መካከል አንዱ በዚህ በጳጉሜ ወር የምንጾመው የፈቃድ ጾም ነው፡፡ ይህም ጾመ ዮዲት በመባል ይታወቃል፡፡ ይህ ግን እንደ አንደኛው የፈቃድ ጾም /ጽጌ ጾም/ በብዙዋኑ ዘንድ የታወቀ አይደለም፡፡ የዮዲት ጾም የሚባለውም እርሷ ስለ ጾመችው ነው፡፡

እዚህ ላይ ዮዲት ተብላ የተጠቀሰችው በቤተክርስቲያን ታሪክ ትምህርት ላይ በጥፋት ሥራዋ በተደጋጋሚ የምትጠቀሰው ዮዲት ጉዲት እንዳልሆነች ለማሳወቅ እንወዳለን፡፡ ወደ ታሪኩ ስንመለስ የፋርስ ንጉስ ናቡከደነጾር በሠራዊቱ ተመክቶ ሹም ጠላት አጥፋ ድንበር አስፋ ካመነው እጅ መንሻ እየተቀበልህ ያላመነውን እያሳመንህ ና ብሎ ለጦር አበጋዙ ለሆሎፎርኒስ ትዕዛዝ ሰጠ፡፡ [ዮዲ.፪፥፯]፡፡ እርሱም እንደታዘዘው በኃይላቸው የታመኑ ፲፪ [12] ሺህ እግረኞችንና በፈረስ የተቀመጡ ፲፪ [12] ሺህ ጦረኞችን እየመራ ዘምቶ ካመነው እጅ መንሻ እየተቀበለ ያላመነውን እያሳመነ ብዙ ሀገሮችን እያጠፋ ሲሔድ ከአይሁድ ከተማ ደረሰ በዚህም ብዙ ጥፋ በመድረሱ የእስራኤል ልጆች አለቀሱ፡፡

ዮዲት ባሏ ሞቶባት ከወንድ ርቃ ንጽሕናዋን ጠብቃ በጾም በቀኖና በሀዘን ተወስና ትኖራለች በተፈጠረው ጥፋት ህዝቡ ላይ ለመጣው መከራ ማቅ ለብሳ በራስዋ ላይ ትብያ ነስንሳ ወደ እግዚአብሔር አለቀሰች፡፡ የፍጥረቱን ጥፋት የማይሻ እግዚአብሔር አምላክም ሕዝቡን የሚያድኑበትን መንገድ ለመጠየቅ ሱባኤ በገባች በሦስተኛው ቀን ገለፀላት፡፡ [ዮዲ.፰፥፪]፡፡

ከዚህ በኋላ ጠላታቸውን በዮዲት ምክንያት እስራኤላውያን እስከ ዮርዳኖስ እየተከተሉ አጥፍተዋቸዋል፡፡ ዮዲት ጠላቷን ለማጥፋት የቻለችው በጾምና በጸሎት ከእግዚአብሔር አምላክ ኃይል አግኝታ ነው፡፡ ስለዚህ ምዕመናን ጥንተ ጠላታችን ሰይጣንን ፈቃደ ሥጋን ለማሸነፍ በጾም ከፈጣሪያችን ኃይልን መጎናጸፍ አለብን ብለው ጳጉሜን በፈቃድ ይጾማሉ፡፡

የጳጉሜ ወር ዕለተ ምጽአት የሚታሰብበትም ወር ነው፡፡ ይህም ጳጉሜ የዓመታት መሸጋገሪያ ጨለማው የክረምት ወቅት ወደ ማብቂያው የምናልፍባት እንደሆነች ሁሉ ምጽአትም ከጊዜያዊው ወደ ዘላለማዊ ከምድራዊ ወደ ሰማያዊ ከዚህ ዓለም ወደ ወዲያኛው መሸጋገሪያ ነውና ነው፡፡

ክርስቲያኖች ሁሉ በየዓመቱ በጳጉሜ ወር ሁሉም ተሰብስበው ከሌሊት ጀምረው በቤተክርስቲያን ተገኝተው ጸበል ይጠመቃሉ፡፡ ይህንን የምናደገውም እግዚአብሔር የተባረከ ዓመት እንዲሰጠን ፣ ባሳለፍነው ዓመት የሰራነውን ኃጢአት ይቅር እንዲለን ነው የምንጠመቀውም ንስሐ ገብተን ነው፡፡ በእግዚአብሔር ስም የተቀደሰው ጸበል ደግሞ ከበሽታችን ያድነናል፣ የተቀደስንም ያደርገናል ፣ መጪውንም ህይወታችን የተባረከ ያደርግልናል፡፡

ስለ ቅድስት ቤተክርስቲያናችንና ስለ ሀገራችን ኢትዮጵያ ወደ እግዚአብሔር በመጮህና በማሳሰብ አጽራረ ቤተክርስቲያንን ያስታግስልን ዘንድ ፡ ሀገራችን ኢትዮጵያም ከመለያየት ፡ ከጥላቻ ፡ ከዘረኝነት ከመከራና ከስቃይ በቃሽ ይላት ዘንድ የምናለቅስበትም ጾም ነው፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ፡ ወለወላዲቱ ድንግል ፡ ወለመስቀሉ ክቡር፡፡

🌼

መልካም የአዲስ ዓመት ዋዜማ [ ጷጉሜ ] ይሁንላችሁ፡፡


🕊                        💖                     🕊
🕊

[  † እንኳን ለርኅወተ ሰማይ: ለቅዱስ ሩፋኤል: መልከ ጼዴቅ: ዘርዓ ያዕቆብና ሰራጵዮን ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን። †  ]

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †


†  🕊    ርኅወተ ሰማይ    🕊   †

† ይህች ዕለት የሰዎች ሁሉ ጸሎት የሚያርግባት: አራተኛው መጋቢ ኮከብ የሚያልፍባት: ለሰው ልጆች ከፈጣሪያቸው ጸጋ በረከት የሚሰጥባት ዕለት ስለሆነች "ርኅወተ ሰማይ-ሰማይ የሚከፈትባት ቀን::" ትባላለች::

አሁን በሰማይ መዘጋት መከፈት ኑሮበት አይደለም:: የሰው ልጆችን ልመና ቅዱሳን መላእክት ያለ ከልካይ የሚያሳርጉበት: አንድም ቅዱስ ሩፋኤል የዓመቱን የጸሎት መዝገብ የሚከፍትበት ቀን ስለሆነ እንዲህ ተባለ እንጂ::

እመቤታችን ድንግል ማርያም ለአጼ ናዖድ እንደ ነገረቻቸው በዚህች ዕለት ሁሉም ቅዱሳን ስለሚታሰቡ: የእግዚአብሔር የምሕረት መዝገቡ ስለሚከፈት: ዕለቷን ክብርት ያሰኛታል:: በቅዱስ ሩፋኤል አበጋዝነት [መሪነት] በዚህች ዕለት ለዓመት የሚበቃ ምሕረት ይገኛል::

ስለዚህም አባቶቻችን በዚህች ሌሊት ሦስት መቶ ስልሳ አምስት አቡነ ዘበሰማያትን ሲጸልዩ ያድራሉ:: በሌላ ወገን ደግሞ የጌታ ዳግም ምጽዓቱ መታሰቢያ እንደ መሆኗ ትልቅ ትኩረትም ይሰጣታል::
ቸሩ ጌታችን ከተከፈተች ገነት ከተነጠፈች ዕረፍት ሁላችንንም ያድርሰን::


†  🕊  ቅዱስ ሩፋኤል ሊቀ መላእክት  🕊  † 

† ቅዱስ ሩፋኤል በቤተ ክርስቲያን አስተምሕሮ ከሰባቱ ሊቃነ መላእክት በደረጃው ሦስተኛ ነው:: በመጀመሪያዋ ዕለተ ፍጥረት እግዚአብሔር መቶ ነገደ መላእክትን ፈጥሮ በአሥር ከተማ ሲያኖራቸው የቅዱስ ሩፋኤል ዕድል ፈንታው ራማ ሆነች::

በዚያም "መናብርት" ተብለው ለሚጠሩ አሥሩ ነገድ አለቃ [መሪ] ሆኖ በፈጣሪው ተሹሟል:: በኋላም "መጋብያን" በሚባሉ በሃያ ሦስቱ ነገድ ላይ ሹሞታል:: ይህች ዕለትም በዓለ ሲመቱ ናት::

አንድ ቀን ጌታችን ክርስቶስ በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ ሐዋርያቱ ቅዱስ ሩፋኤልን እንዲያስተዋውቃቸው ለመኑት:: ጌታም ሦስቱን ሊቃናት [ሚካኤል: ገብርኤል እና ሩፋኤል] ይመጡ ዘንድ አዘዛቸው::

ቀጥሎም ቅዱስ ሩፋኤልን "ክብርህን ንገራቸው::" አለው:: እርሱም ለጌታ ሰግዶ ለሐዋርያት ብዙ ምሥጢር ነገራቸው:: በተለይ ስሙን ለሚጠሩ: መታሰቢያውን ለሚያከብሩ የሚደረገውን ጸጋ አብራርቶላቸው ዐረገ::

በመጽሐፈ ጦቢት ላይ ተጽፎ እንደምናገኘው ቅዱሱ መልአክ ሰው [አዛርያን] መስሎ: ጦብያን ለትዳር አብቅቶ: ሣራን አስማንድዮስ ከሚባል ሰይጣን አድኖ: የጦቢትን ዓይን አብርቷል:: በገድላተ ቅዱሳን እንደምናየውም ለብዙ ቅዱሳን ረዳታቸው ሆኖ ገድላቸውን አስፈጽሟል::

ታሪክ እንደሚለው ይህች ቀን ለቅዱስ ሩፋኤል ቅዳሴ ቤቱም ናት:: በ፬ኛው መቶ ክ/ዘመን በቅዱስ ቴዎፍሎስ ዘእስክንድርያ አማካኝነት ቤቱ ታንጿል:: የሚገርመው ደግሞ የታነጸው በዓሣ አንበሪ ጀርባ: ደሴት ላይ ነው:: በመልአኩ አጋዥነትም ለሦስት መቶ ዓመታት አገልግሏል::


† ቅዱስ ሩፋኤል

¤ መስተፍስሒ [ ልቡናን ደስ የሚያሰኝ ]
¤ አቃቤ ሥራይ [ ባለ መድኃኒት ፈዋሽ ]
¤ መዝገበ ጸሎት [ የጸሎት መዝገብ መክፈቻ የተሰጠው ]
¤ ሊቀ መናብርት [ በዙፋን ላይ በክብር የሚቀመጡ መላእክት መሪ ]
¤ ፈታሔ ማኅጸን [ የሰውንም ሆነ የእንስሳትን ማኅጸን የሚፈታ ]
¤ መወልድ [ አዋላጅ: ምጥን የሚያቀል ] ይባላል::
"ለሰብእ ወለእንስሳ ፈታሔ ማኅጸኖሙ አንተ" እንዲል::


†   🕊   ቅዱስ መልከ ጼዴቅ  🕊   †

† ካህኑ መልከ ጼዴቅን ቅዱስ ጳውሎስ "የትውልድ ቁጥር የለውም: ለዘመኑም ጥንትና ፍጻሜ የለውም::" ይለዋል:: [ዕብ.፯፥፫] ሐዋርያው ይህንን ያለው ለወልደ እግዚአብሔር ምሳሌ ሲያደርገው እንጂ ትውልዱ ከነገደ ካም ነው:: ወላጆቹም "ሚልኪ እና ሰሊማ" ይባላሉ::

ገና ከእናቱ ማኅጸን የተመረጠው ቅዱሱ "ካህነ ዓለም: ንጉሠ ሳሌም" ይባላል:: የዛሬ አምስት ሺ አምስት መቶ ዓመት አካባቢ ሴም ባኖረበት ቦታ [በደብረ ቀራንዮ] ለዘላለም ይኖራል:: ካህኑ መልከ ጼዴቅ ከሰው ወገን እጅግ ክቡርም ነው::


†  🕊   አፄ ዘርዓ ያዕቆብ   🕊  † 

† ሃይማኖቱ የቀና ኢትዮጵያዊው ንጉሥ አፄ ዘርዓ ያዕቆብ በኢትዮጵያ በነገሠባቸው ሠላሳ አራት ዓመታት [ከ1426 እስከ 1460 ዓ/ም] ብዙ በጐ ነገሮችን ሠርቷል:: ላለፉት ሰባ ዓመታት ግን አንዳንድ ጥቃቅን ሰብአዊ ስህተቶችን እየነቀሱ ተሐድሶዎቹ ስሙን ሲያጠፉት ኑረዋል::

ዛሬ ዛሬ ደግሞ የእኛ ቤት ሰዎችም ተቀላቅለዋቸዋል::
እነርሱ ያሉትን ይበሉ እንጂ ለእኛ ግን ዘርዓ ያዕቆብ ማለት :-

፩. ጣዖት አምልኮን ከሃገራችን ለማጥፋት ብዙ ሺህ ካህናትን አሰልጥኖ አሰማርቷል::
፪. የኑፋቄ ችግሮችን ለመቅረፍ ጉባኤያትን አዘጋጅቷል::
፫. ከአሥራ አንድ ያላነሱ መጻሕፍትን በመንፈስ ቅዱስ አጋዥነት ደርሶ ለአገልግሎት አብቅቷል::
፬. ብዙ መጻሕፍትን ከውጪ አስመጥቶ አስተርጉሟል [በተለይ ተአምረ ማርያምን]
፭. ሰው ሁሉ ለእመ ብርሃንና ለመስቀሉ ፍቅር እንዲገዛ ጥረት አድርጓል
፮. እመቤታችንን በፍጹም ልቡ ከመውደዱ የተነሳ ዛሬ ድረስ በሃገራችን ድንግል ማርያም "የዘርዓ ያዕቆብ እመቤት" እየተባለች ትጠራለች::
፯. ብዙ አብያተ ክርስቲያናትን አንጾ: ብዙ ሥርዓቶችም በሊቃውንት እንዲሠሩ አድርጐ: ሌሎች ብዙ በጐ ተግባራትንም ፈጽሞ በዚህች ቀን ዐርፏል::
ቤተ ክርስቲያን ስለውለታቸው ዘርዓ ያዕቆብን: እናታቸው ጽዮን ሞገሳን እና አባታቸው ዳዊትን በክብር ታስባለች::


†  🕊  ቅዱስ ሰራጵዮን ዘሰንዱን  🕊  †

† ይህ ቅዱስ እጅግ የበዛ ሃብቱን ለነዳያን አካፍሎ: ወደ ሌላ ሃገር ሔዶ ለባርነት ተሽጧል:: በተሸጠበት ሃገርም በጸሎት ተግቶ ከክህደት ወደ ሃይማኖት መልሷቸዋል:: ክብሩን ሲያውቁበትም በተመሳሳይ ወደ ሌላ ሃገር ሒዶ አሕዛብን አድኗል:: በፍጻሜው ወደ በርሃ ገብቶ በተጋድሎ ኑሮ በዚህች ቀን ዐርፏል::

† አምላከ ቅዱሳን የወዳጆቹን ሁሉ በረከትና ጸጋ ያብዛልን:: ለዓለምም ሰላሙን ይዘዝልን::

🕊

[  † ጳጉሜን ፫ [ 3 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት  ]

፩ . ርኅወተ ሰማይ [የሰማይ መከፈት]
፪ . ቅዱስ ሩፋኤል ሊቀ መላእክት
፫ . ቅዱስ መልከ ጼዴቅ ካህን
፬ . አፄ ዘርዓ ያዕቆብ ንጉሥ [የእመቤታችን ወዳጅ]
፭ . ቅዱስ ሰራጵዮን ዘሰንዱን
፮ . ቅዱስ አኖሬዎስ
፯ . ቅዱስ ቴዎፍሎስ
፰ . አባ ዮሐንስ
፱ . ቅዱስ ጦቢት
፲ . ቅዱሳን ጦብያና ሣራ

[  † ወርኀዊ በዓላት  ]

-  የለም

† " እውነት እውነት እላችኋለሁ:: ሰማይ ሲከፈት: የእግዚአብሔርም መላእክት በሰው ልጅ ላይ ሲወጡና ሲወርዱ ታያላችሁ::" † [ዮሐ. ፩፥፶፪]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Forwarded from አብሰራ ገብርኤል ለማርያም (♱ ባሕራን ♱)
🕊

[  † እንኳን ለቅዱስ አባ ባይሞን እና ለቅዱስ ሊባርዮስ ሊቅ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን። †  ]

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †


 †  🕊  አባ ባይሞን [ ጴሜን ]  🕊

† ይህ ቅዱስ አባት የ፬ [4]ኛው መቶ ክ/ዘ የቤተ ክርስቲያን ፍሬ ሲሆን ተሰምተው በማይጠገቡ መንፈሳዊ ቃላቱ [ምክሮቹ]ና በቅድስና ሕይወቱ ይታወቃል::

ጥንተ ነገሩስ እንደ ምን ነው ቢሉ :-

በተጠቀሰው ዘመን በምድረ ግብጽ የምትኖር አንዲት ደግ ሴት ነበረች:: አምላክ በፈቀደው ጋብቻ ውስጥ ገብታ ሰባት ወንዶች ልጆችን አፈራች:: ሰባቱም ወንድማማቾች ገና ሕፃን እያሉ አባት በመሞቱ እናት ፈተና ውስጥ ገባች::

ነገር ግን ብርቱ ሴት ነበረችና በወዟ ደክማ አሳደገቻቸው:: ሥጋዊ ማሳደጉስ ብዙም አይደንቅም:: ምክንያቱም ሁሉም እናቶች ይህንን ያደርጉታል ተብሎ ይታመናልና:: የዚህች እናት የሚገርመው ግን ሁሉንም ንጹሐን: የተባረኩ: የክርስቶስ ወዳጆች: የቤተ ክርስቲያንም አለኝታዎች እንዲሆኑ አድርጋ ማሳደጓ ነው::

እነዚህ ሰባቱ ወንድማማቾች :-

፩. አብርሃም
፪. ያዕቆብ
፫. ዮሴፍ
፬. ኢዮብ
፭. ዮሐንስ
፮. ላስልዮስ እና
፯. ባይሞን [ጴሜን] ይባላሉ:: ለእነዚህም ዮሐንስ በኩር ሲሆን ባይሞን መቁረጫ ነው::

ሰባቱም ወጣት በሆኑ ጊዜ ወገባቸውን ታጥቀው እናታቸውን ያገለግሉ: ለፈጣሪያቸው ይገዙ ያዙ:: ያየ ሁሉ "ከዓይን ያውጣችሁ::" የሚላቸው: ቡሩካንም ሆኑ:: አንድ ቀን ግን መንፈስ ቅዱስ በሰባቱ ልብ ውስጥ አንድ ቅን ሃሳብን አመጣ:: ሁሉም እንደ አንድ ልብ መካሪ: እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ስለ ምናኔ አወሱ::

ይህንን ዓለም ከነ ኮተቱ ይተውት ዘንድ መርጠዋልና ወደ በርሃ ለመሔድ ተስማሙ:: እናታቸው ምን መንፈሳዊ ብትሆን የትኛዋም እናት ሁሉን ልጆቿን በአንዴ ማጣትን አትፈልግምና አላማከሯትም:: ይልቁኑ እነርሱ ከሔዱ በኋላ እንዳትቸገር የምትታገዝበትን መንገድ አዘጋጅተውላት ተሰወሩ::

ሰባት ልጆቿን በአንዴ ያጣችው እናት ብቻ አይደለችም: ሁሉም አዘነ:: ተፈለጉ: ግን አየኋቸው የሚል ሰው አልተገኘም:: ሰባቱም ቅዱሳን ከቤታቸው እንደ ወጡ ወደ ገዳም ሔደው አንዲት በዓት ተቀበሉ:: ሰባቱም የሚጸልዩ በጋራ: የሚሠሩ: የሚመገቡ: የሚውሉ: የሚተኙም በጋራ ነው::

በአገልግሎታቸውም ሆነ በፍቅራቸው አበውን ደስ አሰኙ:: "እምኩሉ የዓቢ ተፋቅሮ - እርስ በእርስ መዋደድ ከሁሉ ይበልጣል::" እንዲሉ አበው:: ከዘመናት ተጋድሎ በኋላ ግን ዝናቸው ከገዳሙ አልፎ በከተሞች ተሰማ:: ይህንን የሰማችው እናታቸው የእርሷ ልጆች መሆናቸውን በማወቋ ፈጥና ወደ ገዳሙ ገሰገሰች::

"ልያችሁ ልጆቼ?" ስትልም ላከችባቸው:: እነሱ ግን "እናታችን በመንግስተ ሰማያት እንድታይን በዚህ ይቅርብሽ::" አሏት:: ምክንያቱም ሰባቱም የሴትን ፊት ላያዩ ቃል ገብተው ነበርና:: ይህ ለአንድ እናት ከባድ ቢሆንም እርሷ ግን ተረዳቻቸው:: ፈጥናም ወደ ቤቷ ተመለሰች::

ከኮከብ ኮከብ ይበልጣልና [፩ቆሮ.፲፭፥፵፩] (15:41) ከሰባቱ ቅዱሳን ደግሞ ትንሹ አባ ባይሞን የተለየ አባት ሆነ:: ከንጽሕናው: ቅድስናና ትጋቱ ባሻገር ከአንደበቱ የሚወጡ ቃላት ሕይወትነት ያላቸው ሆኑ:: በዘመኑም ከሕፃን እስከ አዋቂ ድረስ ብዙዎች ከመንፈሳዊ ቃላቱ ተጠቅመዋል::

እነዚህ ምክሮቹ ዛሬ ድረስ ለምዕመናንም ሆነ ለመነኮሳት ጣፋጮች ናቸው::
እልፍ አእላፍ ከሆኑ ምክሮቹ እስኪ አንድ አምስቱን እንጥቀስ :-

፩. "ባልንጀራህ በወደቀ ጊዜ በፍጹም ተስፋ አትቁረጥበት:: ይልቅስ አንቃው: አበረታታው: ሸክሙንም አቅልለት እንጂ::"

፪. "ለጥሩ ባልንጀራህ የምታደርገውን ደግነት ለክፉው በእጥፍ አድርግለት:: መድኃኒትን የሚሻ የታመመ ነውና:: አልያ ግን ለበጐው ያደረከው ከንቱ ነው::"

፫. "ባልንጀራህ በበደለ ጊዜ አትናቀው:: ያንተ ተራ በደረሰ ጊዜ ጌታህ ይንቅሃልና::"

፬. "የማንንም ኃጢአት አትግለጥ [አታውራ]:: ካላረፍክ ጌታ ያንተኑ ይገልጥብሃልና::"

፭. "አንደበትህ የተናገረውን ሁሉ ለመሥራት ታገል:: አልያ ውሸታም ትሆናለህ::"

ሰባቱ ቅዱሳን ወንድማማቾች ለብዙ ዓመታት በፍቅርና በተጋድሎ ኑረው በዚህች ቀን ዐርፈዋል::


†  🕊   ቅዱስ ሊባርዮስ ሊቅ   🕊  †

† ሊቁ ተወልዶ ያደገው በአውሮጳ ሮም ውስጥ ሲሆን የታላቁ ሊቅ ቅዱስ አትናቴዎስ ባልንጀራም ነበር:: በቀደመ ሕይወቱ ምሑርና ገዳማዊ በመሆኑ ሊቃውንት የሮም ፓትርያርክ አድርገው ሾሙት:: ዘመኑ አርዮሳውያን የሰለጠኑበት በመሆኑ ምዕመናንን ከተኩላ ለመጠበቅ እንቅልፍን አልተኛም::

የወቅቱ ንጉሥ ታናሹ ቆስጠንጢኖስ እምነቱ አርዮሳዊ በመሆኑ ቅዱሱን ያሰቃየው: ያሳድደውም ነበር:: ለበርካታ ዓመታትም ከመናፍቃንና ከአጋዥ ነገሥታት ጋር ስለ ሃይማኖቱ ተዋግቶ በዚህች ዕለት ዐርፏል::

† የአባቶቻችን አምላክ መፋቀራቸውንና ማስተዋላቸውን ያድለን:: ከበረከታቸውም ያሳትፈን::

🕊

[  † ጳጉሜን ፬ [ 4 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት  ]

፩. ቅዱስ አባ ባይሞን [ ጴሜን ]
፪. ስድስቱ ወንድሞቹ [ አብርሃም: ያዕቆብ: ዮሴፍ: ኢዮብ: ላስልዮስና ዮሐንስ ]
፫. ቅዱስ ሊባርዮስ ሊቅ

[  † ወርኀዊ በዓላት  ]

- የለም

† " ለእውነት እየታዘዛችሁ: ግብዝነት ለሌለበት ለወንድማማች መዋደድ ነፍሳችሁን አንጽታችሁ እርስ በእርሳችሁ ከልባችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ:: ዳግመኛ የተወለዳችሁት ከሚጠፋ ዘር አይደለም:: በሕያውና ለዘላለም በሚኖር በእግዚአብሔር ቃል: ከማይጠፋ ዘር ነው እንጂ::" † [፩ጴጥ. ፩፥፳፪]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
ዘመነ #ማቴዎስም፣ ዘመነ #ማርቆስም፣ ዘመነ #ሉቃስም ሆነ ዘመነ #ዮሐንስ፤ በአራቱም ዘመናት አስቀድሞ ርእሰ ዓውደ ዓመት ቅዱስ #ዮሐንስ(መጥምቁ) ይዘከራል፡፡ ዮሐንስ የስሙ ትርጉም «ጸጋ እግዚአብሔር» ማለት ነው፡፡ ዘመናት ዘመናትን እየወለዱ፣ ሰዓታት ደቂቃን ቅጽበትን /ሰኮንድን/ ሳይቀር እየሰፈሩ/እየቆጠሩ/ ዕለታት ሳምንታትን፣ ሳምንታት ወራትን፣ ወራት ዓመታትን አሁን ላለንበት ዘመን ደርሰናል፡፡ ዓውደ ዓመት በግእዝ ሲሆን በአማርኛ የዘመን መለወጫ/ ቅዱስ ዮሐንስ፣ #ዕንቁጣጣሽ እየተባለም ይጠራል፡፡

                #ሰናይ__ቀን 🙏

🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼

ለመቀላቀል 👇👇👇👇
@Enatachn_mareyam  
@Enatachn_mareyam
Forwarded from አብሰራ ገብርኤል ለማርያም (♱ ባሕራን ♱)
                          †                          

🌼 [ አዲስ ዓመት ማክበር ማለት ! ] 🌼

▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬

🕊

" እግዚአብሔር የሚወዳችሁ እናንተም የምትወዱት ልጆቼ ! በአዲሱ ዓመት ብቻ ሳይሆን ዘወትር እንዲህ እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ የምንገሥፅ ፣ ወይም የምናመሰግን ከኾነ ሹመት ሽልማታችን ብዙ ነው፡፡

ልጆቼ ! ይህን ሁሉ የምነግራችሁ እንዲኹ ስሜታችሁን ለማርካት አይደለም፡፡ ይልቁንም በአዲሱ ዓመት ብቻ ሳይኾን በየእለቱ አስተሳሰባችንን እንዲህ የምናስተካክል ከኾነና እኛም እንደዚኹ በምግባር በትሩፋት ለማጌጥ የምንሽቀዳደም ከኾነ ሹመት ሽልማታችን ብዙ የብዙ ብዙ እንደኾነ እንድታውቁ ብዬ ነው፡፡

ነብየ እግዚአብሔር ክቡር ዳዊት ስለዚህ ጉዳይ ምን እንደሚል እስቲ አብረን እናዳምጠው ፦

" በአንደበቱ የማይሸነግል ፣ በባልንጀራው ላይ ክፋትን የማያደርግ ፣ ሰርቆ ቀምቶ እናት አባቱን የማያሰድብ ፣ እኩይ ምግባር በፊቱ የተናቀለት ፣ እግዚአብሔርንም የሚፈሩትን የሚያከብር ፣  ለባልንጀራው ምሎ የማይከዳ ፣ ገንዘቡን በአራጣ የማያበድር ፣ ከድኻው መማለጃ የማይቀበል ፣ እንዲህ የሚያደርግ ሰው በመከራ ሥጋ በመከራ ነፍስ ለዘላለም አይታወክም፡፡" [ መዝ.፲፭:፫ ]

ይኽም ማለት ክፋትን በመጸየፍ በጎውን በማመስገን እግዚአብሔርን የሚያከብር ሰው ነፍሱ ለዘላለም አትታወክም ማለት ነው፡፡

ዳግመኛም ክቡር ዳዊት በሌላ ሥፍራ እንዲህ አለ ፦

" አቤቱ ባለሟሎችህ በእኔ ዘንድ እንደምን እጅግ ንዑዳን ክቡራን ናቸው ! አስቀድመው ከነበሩት ባለሟሎችህ ይልቅ እኚህ ፈጽመው ጸኑ ! " [ መዝ.፻፴፱:፲፯ ]                           

እግዚአብሔር ያከበረውን ግን አትገስጹ፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር በጽድቅ በቅድስና ሕያዋን የኾኑትን ያከብራልና፡፡ በሰው ዓይን እዚህ ግቡ የማይባሉ ድኾች ቢኾኑም በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ንዑዳን ክቡራን ናቸውና እነዚህን አትገሥጹ፡፡

እግዚአብሔር ያላከበረውን ግን ገስጹት፡፡ ምንም ያህል በወርቅ ላይ ቆሞ በወርቅ ላይ ቢተኛም ምግባር ትሩፋትን ሳይይዝ በገቢረ ኃጢአት የፀናውን ፣ በሚቀጥለው ዓመትም ይህን ለማድረግ የሚያቅደውን ሰው ገሥጹት፡፡

በአጭር ቃል ስታመሰግኑም ስትገስጹም ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት፡፡ አዲስ ዓመትን ማክበር ማለት እንደዚህ በኹለንተናችን አዲስ ሰው ኾኖ በመዘጋጀት ነውና፡፡ "

🕊

[ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ]


†                       †                        †
🌼                    🍒                     🌼
Forwarded from አብሰራ ገብርኤል ለማርያም (♱ ባሕራን ♱)
🕊

†  በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን †

🌼    እንኳን አደረሳችሁ !    🌼


[  †  መስከረም ፩ [ 1 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት   ]  🌼


†  🕊  ቅዱስ በርተሎሜዎስ ሐዋርያ 🕊

ወንጌል ላይ እንደ ተጠቀሰው ከ፲፪ [12] ቱ ቅዱሳን ሐዋርያት አንዱ ቅዱስ በርተሎሜዎስ ነው:: [ማቴ.፲፥፫] (10:3) ነገር ግን ዜና ሕይወቱ በስፋት ሲተረክ አንሰማም:: ቅዱሱ ሐዋርያ እንደ ሌሎቹ ወንድሞቹ ዓለምን በወንጌል ትምሕርት አብርቷል:: በትውፊት ትምሕርት መሠረት 'በርተሎሜዎስ' የሚለውን ስም ያወጣለት ጌታችን ሲሆን ትርጉሙም 'ተክሎችን የሚያጠጣ' ማለት ነው::

ከሐዋርያትም ጌታ አስቀድሞ የስም ቅያሪ ያደረገለት ለእርሱ እንደ ሆነ ይታመናል:: በርተሎሜዎስ የግብርና ሥራውን ትቶ: የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር ሆኖ: ከዋለበት እየዋለ: ካደረበትም እያደረ ምሥጢረ ወንጌልን ተምሯል::

ጸጋ መንፈስ ቅዱስን ከተቀበለ በኋላም ከሐዋርያት ጋር ዓለምን በዕጣ ተካፍሏል:: ሃገረ ስብከቱም 'እልዋህ' እና 'አርማንያ' ናቸው:: የአርማንያ መንበርም የእርሱ ነው:: ቅዱሱ ገድሉ እንደሚለው አሕዛብን በስብከቱና በሚያስደነግጡ ተአምራቱ አሳምኗል::

ከቅዱስ ዼጥሮስ: ከቅዱስ እንድርያስ: ከክርስቶፎሮስና ከሌሎቹም ሰባክያን ጋር ዓለምን ዙሯል:: ሙታንን አስነስቶ: ድውያንን ፈውሶ: አጋንንትን አውጥቶ: ብዙወችን ወደ ሕይወት መልሷል:: የደረቁ እንጨቶችም በእጁ ላይ እንዳሉ ለምልመው: አብበው ያፈሩ ነበር::

ቅዱስ በርተሎሜዎስ እያስተማረ ወደ ኢትዮዽያም ደርሶ እንደ ነበር ይነገራል:: በመጨረሻም 'ለሚስቶቻችን ንጽሕናን አስተምረሃል' በሚል ተከሶ: ንጉሥ አግሪዻ በሰቅ [ጸጉር] ጠቅልሎ: አሸዋ ሞልቶ: ባሕር ውስጥ ጥሎታል:: በዚያውም ዐርፏል::


†  🕊  ቅዱስ ሚልኪ ቁልዝማዊ  🕊  †

ይህቺ ሃገረ ቁልዝም ግብጽ ውስጥ የምትገኝ ስትሆን ብዙ ቅዱሳንን አፍርታለች:: በተለይ የአባ እንጦንስና የልጆቹ ማረፊያ ከመሆኗ ባሻገር ቅዱስ አባ ሚልኪም ወጥቶባታል:: ቅዱሱ የዘመነ ጻድቃን ፍሬ: የስለት ልጅም ነው:: ጥሩ ክርስቲያኖች የነበሩት ወላጆቹ እጅግ ባለጸጐችም ነበሩ::

በስለት መንታ ልጆችን [ሚልኪና ስፍናን] ወልደው: በሥርዓት አሳድገዋል:: ቅዱስ ሚልኪ በሕጻንነት ወራቱ ስቆና ከሕጻናት ጋር ተጫውቶ አያውቅም:: ብሉያትና ሐዲሳትን ጠንቆቆ ካጠና በኋላ እድሜው ፲፱ [19] ሲደርስ ወላጆቹ "እንዳርህ" አሉት:: የልቡን እያወቀ "እሺ" አላቸው::

ቀጥሎም "ባልንጀሮቼን ልጋብዝበት" ብሎ: ፲፻ [1,000] ወቄት ወርቅ ተቀብሎ: በፈረስ ተቀምጦ ሔደ:: መንገድ ላይ መቶውን ለተከተሉት: ፱ [9] መቶውን ወቄት ለነዳያን: ፈረሱን ደግሞ ለአንድ ደሃ ሰጥቶ: ጡር [ጢር] ወደ ሚባል በርሃ ገሰገሰ::

መጥፋቱ በቤተሰብ ሲሰማ ታላቅ ሐዘንና ለቅሶ ተደረገ:: እናቱም ዐይኗ ተሰወረ:: እርሱ ግን አባ አውጊን ከሚባል ባሕታዊ ሒዶ ደቀ መዝሙሩ ሆነ:: ለ፫ [3] ዓመታትም ተፈትኖ መነኮሰ::

*ከዚያም በጠባቡ ጐዳና ገብቶ በጾም: በጸሎት: በትሩፋት ከፍ ከፍ አለ:: ከቅድስናው ብዛት የተነሳ አጋንንት ገና ከርቀት ሲያዩት ይሸሹት ነበር:: የነካቸውም ሁሉ ይፈወሱለት ነበር:: በእርሱ ጸሎትም በፋርስና በሮም ሰላም ሆነ::

አንድ ቀን የዳዊትን መዝሙር እየዘመረ ሲሔድ የአገረ ገዥውን ልጅ ዘንዶ በልቶት ሲለቀስ ደረሰ:: ጸሎት አድርጐ ዘንዶውን ጠራውና "እንደ ነበረ አድርገህ ትፋው" ሲል አዘዘው:: ዘንዶውም ተፋው: ሰይጣኑም ሸሽቶ አመለጠ::

ሃገረ ገዥው ደስ ቢለው ፫፻ [300] ቤቶች ያሉት ገዳም ለማር ቅዱስ ሚልኪ አነጸለት:: በዚያም ፫፻ [300] መነኮሳት ተሰብስበው ትልቅ ገዳም ሆነ:: ማር ሚልኪ ሁሉን ካሰናዳ በኋላ "ከዚህ አልወጣም" ብሎ በዓቱን ዘጋ:: ሰይጣን ግን "አስወጣሃለሁ" ብሎ ፎክሮ ሒዶ በንጉሡ ልጅ አደረባትና አሳበዳት::

"ከሚልኪ በቀር የሚያሰወጣኝ የለም" አለ:: ንጉሡ ወታደሮቹን ጠርቶ "ሒዳችሁ: አባ ሚልኪን ይዛችሁ ብትመጡ ሽልማት: ካልሆነ ግን ሞት ይጠብቃችሁአል" አላቸው:: እነርሱም በጭንቅ አግኝተው "እንሒድ" አሉት:: "በሮም ከተማ በር ላይ እንገናኝ" አላቸው::

ልክ በዓመቱ እነርሱ ሮም ሲደርሱ ማር ሚልኪ ደመና ጠቅሶ ከተፍ አለ:: ልጅቱንም አቅርቦ ሰይጣንን "እየታየህ ውጣ" አለው:: ወደል ጐረምሳ ሆኖ ወጣ:: ወስዶም አሰረው:: ከቀናት በኋላ ሕዝቡና ንጉሡ እያዩ ማር ሚልኪ ደመና ላይ ተቀምጦ: ሰይጣኑን የድንጋይ ገንዳ አሸክሞ እየነዳ ወሰደው::

ሕዝቡም ደስ ብሏቸው በታላቅ ዝማሬና እልልታ ሸኙት:: ሰይጣኑንም ለዘለዓለም አሰረው:: ቅዱስ ሚልኪ በገዳሙ ለዓመታት ከተጋደለ በኋላ በዚህች ቀን ቅዱሳን አባ እንጦንስ: መቃርስ: ሲኖዳና ሌሎችም መጥተው: በክብር ተቀብለውት ዐርፏል:: አበው 'ትሩፈ ምግባር' ይሉታል::


†  🕊 ቅዱስ ራጉኤል ሊቀ መላእክት 🕊

ከዘጠኙ ሊቃነ መላእክት አንዱ ሲሆን በብርሃናት ላይ ተሹሟል:: ለሃገራችን ልዩ ፍቅር ያለው መልአኩ ከሔኖክ ጀምሮ የብዙ ቅዱሳን ረዳት ነው:: ዛሬ በዓለ ሲመቱ ነው::


†   🕊  ቅዱስ ኢዮብ ጻድቅ   🕊  †

ታላቁ ጻድቅ: የትእግስትም አባቷ ቅዱስ ኢዮብ በጭንቅ ደዌ ለብዙ ዘመናት በመከራ ከኖረ በኋላ በዚህች ቀን በፈሳሽ ውሃ (በዮርዳኖስ) ታጥቦ ሰውነቱ ታድሷል:: ክብርም ተመልሶለታል:: በፈሳሽ ውሃ የምንጠመቅበት አንዱ ምክንያትም ይሔው ነው::

የበርተሎሜዎስ አምላክ ፍቅሩን: የሚልኪ አምላክ ትሩፋቱን: የራጉኤል አምላክ ረድኤቱን: የኢዮብ አምላክ ትእግስቱን ያሳድርብን::

🕊

[  † መስከረም ፩ [ 1 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት  ] 🌼

፩. ርዕሰ ዓውደ ዓመት
፪. ቅዱስ በርተሎሜዎስ ሐዋርያ
፫. ቅዱስ /ማር/ ሚልኪ [ትሩፈ ምግባር]
፬. ቅዱስ ራጉኤል ሊቀ መላእክት
፭. ቅዱስ ኢዮብ ተአጋሲ
፮. ሜልዮስ ሊቀ ዻዻሳት

[   †  ወርኀዊ በዓላት   ] 🌼

፩. ልደታ ለማርያም ድንግል እግዝእትነ
፪. ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና

" የነቢዩንም የኢሳይያስን መጽሐፍ ሰጡት:: መጽሐፉንም በተረተረ ጊዜ :- የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው:: ለድሆች ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ቀብቶኛልና:: ለታሠሩትም መፈታትን: ለዕውሮችም ማየትን እሰብክ ዘንድ: የተጠቁትንም ነጻ አወጣ ዘንድ: የተወደደቺውንም የጌታ ዓመት እሰብክ ዘንድ ልኮኛል::' ተብሎ የተጻፈበትን ሥፍራ አገኘ::" [ሉቃ.፬፥፲፯] (4:17)


† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
2024/09/29 09:31:06
Back to Top
HTML Embed Code: