Telegram Web Link
🕊

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ †

[ ግንቦት ፲፭ [ 15 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]


🕊  ቅዱስ ናትናኤል   🕊

በቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት ከቅዱሳን ሐዋርያት መካከል ዘግይቶ ሰማዕትነትን የተቀበለ ይህ ቅዱስ ሐዋርያ ነው::

ቅዱሱ ሐዋርያ የተወለደው ከእሥራኤላውያን ወላጆቹ ጌታችን በተወለደበት ዘመን አካባቢ ነው:: ይህ በምን ይታወቃል ቢሉ እርሱ ሕጻን እያለ ሔሮድስ ፻፵፬ ሺህ [144,000] ሕጻናትን ሲፈጅ እርሱ ግን በእግዚአብሔር ጥበብ ተርፏል:: እናቱ በቅርጫት ውስጥ አድርጋ የበለስ ዛፍ ላይ አስቀምጣው ተደብቃ ታጠባው ነበር::

ለሐዋርያው ወላጆቹ ያወጡለት ስም ስምዖን ሲሆን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ ናትናኤል ብሎታል:: በባልንጀሮቹ ሐዋርያት ደግሞ የቃናው ስምዖን [ገሊላ ቃና አካባቢ ስላደገ] : አንዳንዴም ቀናተኛው ስምዖን ይሉት ነበር:: ምሑረ ኦሪት ነበርና ዘወትር ለሕግ ይቀና ነበር::

በገሊላ ቃና ሰርግ የደገሰው ዶኪማስ የቅዱስ ናትናኤል የአጎት ልጅ ነው:: ጌታና ደቀ መዛሙርቱን ዶኪማስ የጠራበት አንዱ ምክንያትም ይሔው ነው::

ቅዱስ ናትናኤል ኦሪትን ከገማልያል ተምሮ: ከበለስ ቁጭ ብሎ ይተክዝ ነበር:: "መሲሕ ምነው ቀረህ" እያለም ይተክዝ ነበር:: ማዕምረ ኅቡዓት አምላካችን ክርስቶስ ይህንን አውቆ በፊልዾስ አማካኝነት ጠርቶታል::

ናትናኤል ለጊዜው ተከራክሮ ነበር:: በኋላ ግን የጌታችንን ማንነት በደቂቃዎች ተረድቶ አምኗል:: ጌታችንም "ክዳት ሽንገላ በልቡ ውስጥ የሌለበት ንጹሕ እሥራኤላዊ" ሲል አመስግኖታል::

ሐዋርያው ቅዱስ ናትናኤል ከጌታችን እግር ሥር ምስጢረ መንግስተ ሰማያትን ተምሮ: በጸጋ መንፈስ ቅዱስም ሰክሮ ብዙ አሕዛብን ከጨለማ [ጣኦት አምልኮ] ወደ ብርሃን [አሚነ ክርስቶስ] መልሷል:: እጅግ ብዙ መከራንም ተቀብሏል::

የጌታችን ወንድም የተባለ ቅዱስ ያዕቆብ በአይሁድ ከተገደለ በኋላም ቅዱስ ናትናኤል የኢየሩሳሌም ፪ [2] ኛ ኤዺስ ቆዾስ ሆኖ አገልግሏል:: ከአይሁድም ዘንድ ብዙ መከራ ደርሶበታል:: በመጨረሻም በዚህች ዕለት በሰማዕትነት አልፏል:: በገድለ ሐዋርያት ላይ እንደተጠቀሰው ቅዱሱ ሰማዕት የሆነው በ፻፶ [150] ዓመቱ ነው:: ያ ማለት ደግሞ ከሐዋርያት አባቶች በመጨረሻ ያረፈው እርሱ ነው ያሰኛል::

❖ እግዚአብሔር በቅዱስ ናትናኤል ምልጃ ሃገራችንን
ከጥፋት: ሕዝቦቿንም ከመቅሰፍት ይሰውርልን::
ከበረከቱም አይለየን::

🕊

[ † ግንቦት ፲፭ [ 15 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. ቅዱስ ናትናኤል ሐዋርያ [ቀናተኛው ስምዖን]
፪. ቅዱስ ሚናስ ባሕታዊ
፫. ቅዱስ ቀርጢኖስ ሰማዕት
፬. ፬፻ "400" ቅዱሳን ሰማዕታት

[ †  ወርሐዊ በዓላት ]

፩. ቅዱስ ቂርቆስና እናቱ ኢየሉጣ
፪. ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ [አፈ በረከት]
፫. ቅዱስ ሚናስ ግብፃዊ
፬. ቅድስት እንባ መሪና
፭. ቅድስት ክርስጢና

" ጌታ ኢየሱስ ናትናኤልን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ ስለ እርሱ 'ተንኰል የሌለበት በእውነት የእሥራኤል ሰው እነሆ' አለ:: ናትናኤልም 'ከወዴት ታውቀኛለህ?' አለው:: ጌታ ኢየሱስም መልሶ 'ፊልዾስ ሳይጠራህ ከበለስ በታች ሳለህ አየሁህ' አለው:: ናትናኤልም መልሶ 'መምሕር ሆይ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ:: አንተ የእስራኤል ንጉሥ ነህ' አለው:: "  [ዮሐ.፩፥፵፰] (1:48-51)

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
#ሰው_ሆይ! የሚጎዳህ ሀብትህ አይደለም፤ ድኽነትህም አይደለም። ሰውን የሚጎዳው #ክፉ_ልብ ነው። ክፉ ልብ ደግሞ በሀብትም፣ ሀብት በማጣትም የሚመጣ አይደለም። ክፉ ልብ ሌሎች ክፉ ልቦችን #ይወልዳል። እሳት እሳትን እየወለደ ብዙ እንጨቶችን እንደሚበላ ኹሉ #ክፉ ልብም እንደዚህ ነው።

አንተ ሰው! ይህን ማወቅ ትወዳለህን? ክፉ ምግባር ወይም በጎ ምግባር
#በተፈጥሮ የሚገኙ አይደሉም። እነዚህ ኹለቱ ከክፉ ልብ ወይም #ከመልካም_ልብ የሚገኙ ናቸው።

             #_ሰናይ__ቀን🙏

ለመቀላቀል 👇👇👇👇
@Enatachn_mareyam  
@Enatachn_mareyam
የሮማን_ክፋይ_ኪዳነምህረት16
#ሰላም_ነሽ_ለኔ_ፍቅር_በረከት
#ስምሽ_ሞገሴ_ክብርሽ_ማዕረጌ
#ምን_ብዬ_ልጥራሽ_ድንግል_እናቴ..
#የቃል_ኪዳኗ_እመቤት_ሆይ_አንቺ_እኮ
#የመለኮት__ዙፋን_የአለም_እናት
#ለታመሙት__ፈውስ
#ለተራቡት__ምግብን
#ለታመሙት__እርካታን
#ለተሰደዱ__ጥንካሬን
#ላዘኑ_ዕምነትን
#ለሞቱ_የነፍስ_እረፍትን
#ለአለማችን ሰላምን የምትሰጪ የጭንቅ አማላጅ እናቴ እመቤቴ ቅድስት #ኪዳነምህረት_ሆይ ልጅሽ በገባልሽ ቃል ኪዳን ከመከራ ስጋ ከመከራ ነፍስ ስውሪን ሀገራችንን #ኢትዮጵያን አንቺ በቃል ኪዳንሽ ከውጭም ከሀገር ውስጥ ጠላት ከክፉ ነገር አንቺ ጠብቂልን

#የእናታችን_የቅድስት_ኪዳነምህረት እረድኤት በረከት ምልጃ ፀሎት ልመናዋ ጥበቃ እኛን ህዝበ ክርስትያንን አይለየን/አይለያችሁ አሜን፫ 🙏🙏

#መልካም___ቀን🙏

አጫጭር ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶች
•➢ 👇 ለማግኘት // 👇

@Enatachn_mareyam
@Enatachn_mareyam
🕊

† በስመ አብ: ወወልድ: ወመንፈስ ቅዱስ: አሐዱ አምላክ †

†  ግንቦት ፲፮ [ 16 ] †

🕊 † ቅዱስ ዮሐንስ ፍቁረ እግዚእ † 🕊

አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌሉ እንደነገረን በመንግስተ ሰማያት ታላቁ ሰው ወንጌላዊው ዮሐንስ ነው:: ቅዱሱ ሐዋርያ ከዘብዴዎስና ከማርያም ባውፍልያ ተወልዶ: በገሊላ አካባቢ አድጐ: ገና በወጣትነቱ መድኃኔ ዓለምን ተከትሎታል::

ቅዱስ ዮሐንስ ከሐዋርያት ቀድሞ ጌታን ከመከተሉ ባሻገር በምንም ምክንያት ከጐኑ አይጠፋም ነበር:: ስለ ንጽሕናውና በጐ የፍቅር ሕሊናው ሕጻን ሳለ በወንድሞቹ ሐዋርያት ዘንድ ሞገሱ ከፍ ያለ ነው:: ጌታችንን እስከ እግረ መስቀሉ ድረስ በመከተሉ ድንግል እመቤታችንን ተቀብሏል::

ከእርሷ ጋር ለ፲፭ [15] ዓመታት ቢቀመጥ መዝገበ ምሥጢር ሆነ:: ስንኩዋን ከሰው ልጆች ይቅርና ከልዑላኑ መላዕክትም ማዕረጉ ከፍ አለ:: ሰው ቢበቃ መላእክትን ሊያይ ይቻለዋል:: ቅዱስ ዮሐንስን ግን መላእክት ሊያዩት ይከብዳቸዋል:: ከፍጥረት ወገን ከእመ ብርሃን ቀጥሎ ክቡር እርሱ ነው::

ቅዱስ ዮሐንስ በታናሽ እስያ ለ፯ [7] ቱ አብያተ ክርስቲያናት መስበኩ ይታሰባል:: ቅዱሱ ከጌታችን ዕርገት በሁዋላ ለ፸ [70]  ዓመታት በዚህ ምድር ሲኖር አብዛኛውን ጊዜውን ያሳለፈው በኤፌሶን አካባቢ ነው:: ሕዝቡን ወደ ክርስትና ለማምጣት በአፍም በመጽሐፍም ደክሟል::

፫ [3] መልዕክታት: ራዕዩንና ወንጌልን ጽፎላቸዋል:: ሕይወትን ስለ ሰበከላቸው በፈንታው ብዙ አሰቃይተውታል:: ከእሳት እስከ ስለት: እስከ መጋዝም በስተእርጅና ደርሶበታል:: እርሱ ግን በትእግስቱ ገንዘብ አድርጉዋቸዋል::

††† ቅዱሱ በኤፌሶን †††

ይህቺ ኤፌሶን የሚሏት ሃገር መገኛዋ በቀድሞው ታናሽ እስያ [አሁን ቱርክ አካባቢ] ሲሆን ብዙ ሐዋርያት አስተምረውባታል:: ያም ሆኖ የሚፈለገውን ያህል ለውጥ ያመጣች አልነበረችምና ቅዱስ ዮሐንስ ሊሔድ ተነሳ::

ከደቀ መዛሙርቱ መካከልም ቅዱስ አብሮኮሮስን [ከ፸፪] [72]ቱ አርድእት አንዱ ነው] አስከትሎ እየጸለዩ በመርከብ ላይ ተሳፈሩ:: ሐዋርያት አበው መከረኞች ናቸውና ማዕበል ተነሳባቸው:: በጥቂት አፍታም መርከባቸው በማዕበሉ ተበታተነች::

ቅዱስ አብሮኮሮስ በስባሪ ላይ ተሳፍሮ ወደ አንዲት ደሴት ደረሰ:: ከንጹሑ መምሕሩ ቅዱስ ዮሐንስ ተለይቷልና አለቀሰ:: ፍቁረ እግዚእ ግን ያለ ምግብና ውሃ ማዕበለ ባሕር እያማታው ለ፵ [40] ቀናት ቆየ::

እርሱ በፈጣሪው ፍቅር የተመሰጠ ነበርና አለመመገቡ አልጐዳውም:: በ፵ [40] ኛው ቀን ግን ደቀ መዝሙሩ ወዳለበት ደሴት ማዕበሉ አደረሰው:: ፪ [2] ቱ ቅዱሳን ተፈላልገው ተገናኙ:: እጅግም ደስ ብሏቸው ፈጣሪን አመሰገኑ::

አምላካቸው ወደዚህች ደሴት ያመጣቸው በጥበቡ ነውና ሲዘዋወሩ ፪ [2] ነገርን አስተዋሉ::

፩ኛ የደሴቷ ሁሉም ነዋሪ የሚያመልኩት ጣዖትን ነው::
፪ኛ አብዛኞቹ የቤተ መንግስት ውላጆች ናቸው:: ሮምና የሚሏት አንዲት ሴት ደግሞ እነዚህን ሁሉ እየመገበች ታስተዳድራለች::

ቅዱሳኑ በቦታው በቀጥታ ትምሕርተ ወንጌልን ቢናገሩ እንደ ማይቀበሏቸው ስለ ተረዱ ሌላ ፈሊጥን አሰቡ:: እንዳሰቡትም ወደ እመቤት ሮምና ቤት ሒደው በባርነት ተቀጠሩ::

ለእርሷም "ድሮ የአባትሽ ባሮች የነበርን ሰዎች ነን" ስላሏት ፪ [2]ቱን ቅዱሳን እሳት አንዳጅና ገንዳ አጣቢ አደረገቻቸው:: ለሰማይ ለምድሩ የከበዱ እነዚህ ቅዱሳን የካዱትን ይመልሱ ዘንድ በባርነት ግፍን ተቀበሉ:: የመከር [የማሳመኛ] ጊዜ ሲደርስም አንዳች አጋጣሚ ተፈጠረ::

ቅዱሳኑ ዮሐንስና አብሮኮሮስ ወደ መታጠቢያ ቤቱ ሲገቡ ሰይጣን በውስጥ ኖሮ ደንግጧልና እወጣለሁ ብሎ ሲሮጥ የንጉሡን ልጅ ረግጦ ገደለው:: ሮምናና የአካባቢው ሰዎች ከበው ሲላቀሱ ቅዱሳኑ ቀረቡ::

ሮምና ግን በቁጣ "ልትሣለቁ ነው የመጣችሁ?" በሚል ቅዱስ ዮሐንስን በጥፊ መታችው:: መላእክት እንኩዋ ቀና ብለው ሊያዩት የሚከብዳቸው ሐዋርያ ይህንን ታገሰ:: በጥፊ ወደ መታችው ሴት ቀረብ ብሎም "አትዘኚ! ልጁ ይነሳል" አላትና ጸለየ::

ወደ ሞተውም ቀረብ ብሎ በጌታችን ስም አስነሳው:: በዚህ ጊዜም ሮምናን ጨምሮ በሥፍራው የነበሩ ሰዎች ለቅዱስ ዮሐንስ ሰገዱ:: እርሱ ግን ሁሉንም አስነስቶ ትምሕርተ ሃይማኖትን: ፍቅረ ክርስቶስን ሰበከላቸው::

በስመ ሥላሴ አጥምቆ: ካህናትን ሹሞ: ቤተ ክርስቲያንም አንጾላቸው ወጥቷል:: በሁዋላም ለሮምናና ለደሴቷ ሰዎች ክታብ [መልዕክትን] ጽፎላቸዋል:: ይህች መልዕክት ዛሬ ፪ [2] ኛዋ የዮሐንስ መልዕክት ተብላ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ትታወቃለች::

ቅዱስ ዮሐንስ ቀጥሎ የተጉዋዘው ወደ ኤፌሶን ነው:: በዚህች ከተማ የምትመለክ አርጤምስ [አርጢሞስ] የሚሏት ጣዖት ነበረች:: አርጤምስ ማለት መልክ የነበራት ትዕቢተኛ ሴት ስትሆን አስማተኛ ባሏ ነው እንድትመለክ ያደረጋት::

ቅዱስ ዻውሎስ ብዙ ምዕመናን ከእርሷ እንዲርቁ ማድረግ ችሏል:: ጨርሶ ያጠፋት ግን ቅዱስ ዮሐንስ ነው:: በቦታውም ብዙ ግፍ ደርሶበት: በርካታ ተአምራትን አድርጉዋል:: ቤተ ጣዖቱንም በተአምራት አፍርሶታል::

††† የፍቅር ሐዋርያ †††

ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ዮሐንስን 'የፍቅር ሐዋርያ' ትለዋለች:: ለ፸ [70] ዘመናት በቆየ ስብከቱ ስለ ፍቅር ብዙ አስተምሯል:: ፍቅርንም በተግባር አስተምሯል:: በየደቂቃውም "ደቂቅየ ተፋቀሩ በበይናቲክሙ - ልጆቼ ሆይ! እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ" እያለ ይሰብክ ነበር::

በተለይ ደግሞ ከፈጣሪው ክርስቶስ ጋር የነበረው ፍቅር ፍጹም የተለየ ነበር:: በዚህ ምክንያትም ጌታ ባረገ ጊዜ እንዲህ ብሎታል:- "ለፍጡር ከሚገለጥ ምሥጢር ከአንተ የምሠውረው የለኝም" ብሎታል::

ቀጥሎም በንጹሕ አፉ ስሞታል:: ሊቁ :-

"ሰላም ለአፉከ ለዮሐንስ ዘሰዓሞ:
ንጽሐ ኅሊናሁ ወልቡ ለዐይነ ፍትወትከ ሶበ አደሞ" እንዳለው:: [መልክዐ ኢየሱስ]

ቅዱስ ዮሐንስ ከእመቤታችንም ጋር ልዩ ፍቅር ነበረው:: እርሷ እንደ ልጇ ስትወደው: እርሱ ደግሞ እንደ እናቱ ልቡ እስኪነድ ድረስ ይወዳት ነበር:: እስከ እግረ መስቀሉ ድረስ ተከትሎ ያገኛት እመቤቱ ናትና::

ከዚያ ሁሉ ጸጋና ማዕረግ የመድረሱ ምሥጢርም ድንግል ናት:: ለ፲፭ [15] ዓመታት በጽላሎተ ረድኤቷ [በረዳትነቷ ጥላ] ተደግፎ አብሯት ሲኖር ብዙ ተምሯል:: ከመላእክትም በላይ ከብሯል:: ከንጽሕናዋ በረከትም ተካፍሏል::

ስለ ድንግል ማርያምም "ነገረ ማርያም" የሚል ድርሰት ሲኖረው "የሰኔ ጐልጐታንም" የጻፈው እርሱ ነው::

ድንግል ባረፈችበት ቀንም ልክ እንደ ልጇ ክርስቶስ እርሷም ስማው: ታቅፋው ዐርፋለች:: ሊቃውንቱ ለዚህ አይደል በንጹሕ ከንፈሮቿ መሳምን [መባረክን] ሲሹ :-

"በከመ ሰዓምኪ ርዕሰ ዮሐንስ ቀዳሚ:
ስዒሞትየ ማርያም ድግሚ" ያሉት::

ታላቁ ቅዱስ ሐዋርያ ዕድሜው ፺ [90] ዓመት በሆነው ጊዜ ተሰውሯል:: ከዚያ አስቀድሞም የዓለምን ፍጻሜ ተመልክቷል:: ዛሬ ያለበትን የየሚያውቅ ቸር ፈጣሪው ነው::

† ይሕች ዕለት ለሐዋርያው ቅዳሴ ቤቱ ናት:: †

እናት ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ዮሐንስን ስትጠራው እንዲሕ ነው:-
- ወንጌላዊ
- ሐዋርያ
- ሰማዕት ዘእንበለ ደም
- አቡቀለምሲስ [ምሥጢራትን ያየ]
- ታኦሎጐስ [ነባቤ መለኮት]
- ወልደ ነጐድጉዋድ
- ደቀ መለኮት ወምሥጢር
- ፍቁረ እግዚእ
- ርዕሰ ደናግል [የደናግል አለቃ]
- ቁጹረ ገጽ
- ዘረፈቀ ውስተ ሕጽኑ ለኢየሱስ [ከጌታ ጎን የሚቀመጥ]
- ንስር ሠራሪ
- ልዑለ ስብከት
- ምድራዊው መልዐክ
- ዓምደ ብርሐን
- ሐዋርያ ትንቢት
- ቀርነ ቤተ ክርስቲያን
- ኮከበ ከዋክብት

በቅዱስ ዮሐንስ ላይ ያደረ የእመቤታችን ድንግል ማርያምና የአንድ ልጇ ፍቅር በእኛም ላይ ይደር::

ቅዱስ ዮሐንስን የወደደ ጌታ በፍቅሩ ይጠግነን:: ከእናቱ ፍቅር አድርሶ በሐዋርያው በረከት ያስጊጠን::

[ † ግንቦት ፲፮ [ 16 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ [ ስብከቱና ቅዳሴ ቤቱ ]
፪. ቅዱስ ኢያሱ ሲራክ ነቢይና ጠቢብ [ መጽሐፈ ሲራክን የጻፈ ]
፫. ቅድስት እናታችን ዐስበ ሚካኤል [ ኢትዮዽያዊት ]

[ † ወርኀዊ በዓላት ]

፩. ኪዳነ ምሕረት [የሰባቱ ኪዳናት ማሕተም]
፪. ቅድስት ኤልሳቤጥ [የመጥምቁ ዮሐንስ እናት]
፫. ቅዱስ ገብረ ማርያም ጻድቅ ንጉሠ ኢትዮዽያ [የቅ/ላሊበላ ወንድም]
፬. ቅዱስ አኖሬዎስ ንጉሥ ጻድቅ
፭. አባ አቡናፍር ገዳማዊ
፮. አባ ዮሐንስ ወንጌሉ ዘወርቅ
፯. አባ ዳንኤል ጻድቅ

" በጌታ ኢየሱስ መስቀል አጠገብ እናቱ: የእናቱም እህት: የቀለዮዻም ሚስት ማርያም: መግደላዊትም ማርያም ቆመው ነበር:: ጌታ ኢየሱስም እናቱን: ይወደው የነበረውንም ደቀ መዝሙር በአጠገቡ ቆሞ ባየ ጊዜ እናቱን 'አንቺ ሆይ! እነሆ ልጅሽ' አላት:: ከዚህ በሁዋላ ደቀ መዝሙሩን 'እናትህ እነሁዋት' አለው:: ከዚህም ሰዓት ጀምሮ ደቀ መዝሙሩ ወደ ቤቱ ወሰዳት::" [ዮሐ.፲፱፥፳፭] (19:25)

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
🕊

[ † እንኳን ለታላቁ የቤተ ክርስቲያን ጠበቃ ቅዱስ ኤዺፋንዮስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን። † ]

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †


🕊  †  ቅዱስ ኤዺፋንዮስ  †   🕊

† ሊቁ ቅዱስ ኤዺፋንዮስ ጽድቅ ከቅድስና : ድርሰት ከጥብቅና የተሳካለት አባት ነው:: "ኤዺፋንያ" ማለት የመለኮት መገለጥ ሲሆን "ኤዺፋንዮስ" ማለት ደግሞ ምሥጢረ መለኮት የተገለጠለት ማለት ነው::

ቅዱስ ኤዺፋንዮስ የተወለደው ክርስቶስን ከሚጠሉ አይሁዳውያን ቤተሰቦች ቤተ ገብርኤል ውስጥ ነው:: ቤተሰቦቹ ከአንድ አህያ በቀር ምንም የሌላቸው ድሆች ነበሩ:: በዚያ ላይ በልጅነቱ አባቱ በመሞቱ ከእናቱና ከአንዲት እህቱ ጋር በረሃብ ሊያልቁ ሆነ:: ሕጻኑ ኤዺፋንዮስ በአህያው እንዳይሠራ አህያው ክፉ ነበርና ሊሸጠው ገበያ አወጣው::

ፊላታዎስ ከሚባል ክርስቲያን ጋር ለግዢ ሲደራደሩ አህያው የኤዺፋንዮስን ኩላሊቱን ረግጦት ለሞት አደረሰው:: በዚህ ጊዜ አብሮት ያለው ክርስቲያኑ በትእምርተ መስቀል አማትቦ አዳነው:: በፈንታው ግን አህያው ሞተ:: ሕጻኑ ኤዺፋንዮስ እያደነቀ ሔደ::

ከቆይታ በኋላ ሀብታም አጎቱ ገንዘቡን አውርሶት በመሞቱ ገና በ፲፮ [ 16 ] ዓመቱ ባለጠጋ ሆነ:: ያቺ ገበያ ላይ ያያት ተአምር ግን በልቡ ውስጥ ትመላለስ ነበር::

አንድ ቀን ደግሞ ሉክያኖስ ከሚባል ክርስቲያን ጋር ሲሔዱ ነዳይ አገኙ:: ባለጠጋው ኤዺፋንዮስ አለፈው:: ያ ድሃ ክርስቲያን ግን የለበሳትን አውልቆ መጸወተው:: በዚሕ ጊዜ መልዐኩ መጥቶ የብርሃን ልብስ ሲያለብሰው ኤዺፋንዮስ ተመለከተ::

ኤዺፋንዮስ ጊዜ አላጠፋም:: ከእህቱ ጋር በክርስቶስ አምኖ ተጠመቀ:: ሃብት ንበረቱን ግማሹን መጸወተ:: በተረፈው ደግሞ መጻሕፍትን ገዝቶ ወደ አባ ኢላርዮን ገዳም ገባ:: በዚያም መናንያኑ እስኪያደንቁት ድረስ በፍጹም ትጋትና ቅድስና ተጋደለ::

በጸሎቱ ዝናም አዘነመ : ድውያንን ፈወሰ : ብዙ ተአምራትንም አደረገ::

እግዚአብሔር ደግሞ ለሌላ አገልግሎት ሽቶታልና በቆዽሮስ ደሴት ላይ ዻዻስ ሆኖ ተሾመ:: ብሉይ ከሐዲስ የወሰነ ሊቅ ነውና ብዙ መጻሕፍትን ተረጎመ:: በሺሕ የሚቆጠሩ ድርሳናትን ደረሰ:: በአፍም በመጽሐፍም ብሎ መናፍቃንንና አይሁድን ምላሽ በማሳጣቱ ቤተ ክርስቲያን "ጠበቃየ" ትለዋለች::

ከደረሳቸው መጻሕፍት መካከል "ሃይማኖተ አበው ዘኤዺፋንዮስ : መጽሐፈ ቅዳሴውና አክሲማሮስ [ስነ ፍጥረት]" ዛሬም በቅርብ ይገኛሉ:: ሊቁ ቅዱስ ኤዺፋንዮስ በመልካም እረኝነትና በሚደነቅ ቅድስና ተመላልሶ በ ፬፻፮ [406] ዓ/ም ዐርፏል:: እድሜውም ፺፮ [96] ዓመት ያህል ነበር::

† አምላካችን ከቅዱሱ ሊቅ በረከት ያድለን::

🕊

[ † ግንቦት ፲፯ [ 17 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. ቅዱስ ኤዺፋንዮስ ሊቅ [ ዘደሴተ ቆዽሮስ ]
፪. ቅዱስ ኢላርዮን ገዳማዊ
፫. አባ ሉክያኖስ ጻድቅ
፬. ቅዱስ ፊላታዎስ ክርስቲያናዊ

[ †  ወርኀዊ በዓላት ]

፩. ቅዱስ እስጢፋኖስ ሊቀ ዲያቆናት [ ቀዳሜ ሰማዕት ]
፪. ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ [ ወልደ ዘብዴዎስ ]
፫. ቅዱሳን አበው መክሲሞስና ዱማቴዎስ
፬. አባ ገሪማ ዘመደራ
፭. አባ ዸላሞን ፈላሢ
፮. አባ ለትጹን የዋህ

" የሚታገልም ሁሉ በነገር ሁሉ ሰውነቱን ይገዛል:: እነዚያም የሚጠፋውን አክሊል ሊያገኙ ነው:: እኛ ግን የማይጠፋውን:: ስለዚህ እኔ ያለ አሳብ እንደሚሮጥ ሁሉ እንዲሁ አልሮጥም:: ነፋስን እንደሚጐስም ሁሉ እንዲሁ አልጋደልም:: ነገር ግን ለሌሎች ከሰበክሁ በኋላ ራሴ የተጣልሁ እንዳልሆን ሥጋዬን እየጐሰምሁ አስገዛዋለሁ:: " † [፩ቆሮ.፱፥፳፭] (9:25)

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
🕊

[ † እንኩዋን ለጥንተ በዓለ ዸራቅሊጦስ [ መንፈስ ቅዱስ ] እና ለጻድቁ አባ ገዐርጊ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ † ]


†  🕊  በዓለ ዸራቅሊጦስ  🕊  †

✞ ከዚሕ በፊት እንደተመለከትነው የጌታችን ዓበይት በዓላቱ ፪ [2] ጊዜ [ማለትም ጥንተ በዓልና የቀመር በዓል ተብለው] ይከበራሉ:: ዛሬም ከ፩ ሺህ ፱ መቶ ፸፰ [1,978] ዓመታት በፊት አምላካችን መንፈስ ቅዱስ በቅዱሳን ሐዋርያት ላይ መውረዱን እናስባለን::

† ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ :-

ቸር አምላክ ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ ሲል

- ከልዑል ማዕርጉ ወርዶ:
- በማሕጸነ ድንግል ተጸንሶ:
- በኅቱም ድንግልና ተወልዶ:
- ከኃጢአት በቀር በግዕዘ ሕጻናት አድጐ:
- በ30 ዘመኑ ተጠምቆ:
- ቅድስት ሕግ ወንጌልን አስተምሮ:
- በፈቃዱ ሙቶ:
- በባሕርይ ስልጣኑ ተነስቶ:
- በአርባኛው ቀን ያርጋል::

ታዲያ ደቀ መዛሙርቱን የቅዱስ መንፈሱን ጸጋ ተስፋ እንዲያደርጉ ነግሯቸው ነበርና በተነሳ በ፶ [50] ኛው ቀን: በዐረገ በ፲ [10] ቀን ተስፋውን ፈጸመላቸው::

- እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዶሮ ጫጩቶቿን በክንፎቿ እንድትይዝ በአንድ ላይ ሰብስባ ለክብረ መንፈስ ቅዱስ አብቅታቸዋለች:: ፻፳ [120] ው ቤተሰብ ከጌታችን እናት ጋር ሲጸልዩ መንፈስ ቅዱስ በአውሎ ንፋስ አርአያ ወርዶ በአምሳለ እሳት አደረባቸው::

- ቅዱሳን ሐዋርያት ፈሪዎች የነበሩ ደፋሮች: አሮጌ ሕሊና የነበራቸው ሐዲሶች ሆኑ:: በአዕምሮ ጐለመሱ: ቁዋንቁዋ ተናገሩ: ምሥጢርም ተረጐሙ:: በቅጽበትም ብሉይ ከሐዲስ በልቡናቸው ውስጥ ተሞላ::

- ሐዋርያቱ ቅዱስ መንፈስን ተቀብለው ዓለምን በወንጌል ዕርፈ መስቀል አርሰዋል:: አልጫውን ዓለም ጨው ሆነው አጣፍጠዋል:: ሳይሳሱም አንገታቸውን ለሰይፍ ሰጥተዋል:: "ኪያሁ መንፈሰ ነሢኦሙ ለለአሐዱ: ሐዋርያት ለሰቢክ አሕጉራተ ዓለም ዖዱ: ሰማዕትኒ ለሕማም ነገዱ::" እንዳለ ደራሲ::

- በዚህ ቀን ፪ [ 2 ] ነገሮች በትኩረት ይነገራሉ :-

፩. የመንፈስ ቅዱስ የባሕርይ አምላክነት :-

- እርሱ ከአብ የሠረጸ: ቅድመ ዓለም የነበረ: በባሕርይ ስልጣኑ ከአብና ከወልድ ጋር እኩል የሆነ: የራሱ ፍጹም አካል ያለው ፍጹም አምላካችን ነውና::

፪. 🕊 ቅድስት ቤተ ክርስቲያን 🕊 :-

- አብ ያሰባት: ወልድ በደሙ የቀደሳት: መንፈስ ቅዱስ በጸጋው ያጸናት የክርስቲያኖች አማናዊት አንድነት: አንድም ቤት ናትና:: ዛሬ በጉባዔ ተመስርታለች::

🕊 አባ ገዐርጊ 🕊

በዚችም ዕለት የአባ አብርሃም ጓደኛ የከበረ አባ ገዐርጊ አረፈ።ይህም ቅዱስ የክርስቲያን ወገን ነው ወላጆቹ ደጎች ጻድቃን ናቸው።በአደገም ጊዜ የወላጆቹን ከብቶች የሚጠብቅ እረኛ ሆነ።ሁል ጊዜም የምንኵስና ልብስ ይለብስ ዘንድ በልቡ ይመኝ ነበር።

ዐሥራ አራት ዓመትም በሆነው ጊዜ የእግዚአብሔር ጸጋ አነሣሳችው በጎቹንም ትቶ ወደ አስቄጥስ ገዳም ሔደ። እየተጓዘም ሳለ ከሩቅ የብርሃን ምሰሶ አየ ወደ ወንዝ እስከ ደረሰ ድረስ ወደ ርሱ ሔደ ከዚህም በኃላ ያ የብርሃን ምሰሶ ከእርሱ ተሰወረ።

ያንንም ወንዝ በተሻገረ ጊዜ በሽማግሌ አምሳል ሰይጣን ተገለጠለትና ልጄ ሆይ ዕወቅ ስለ አንተ ልብሱን ቀዶ አባትህን አየሁት እርሱም ያዝናል ያለቅሳል ተመልሰህ የአባትህን ልብ ልትአጽናና ይገባሃል።የዱር አውሬ ነጥቆ የበላህ መስሎታልና አለው።

አባ ገዐርጊም ደንግጦ አንድ ሰዓት ያህል ቆመ ከዚህም በኃላ የከበረ ወንጌል ከእኔ ሊሆን አይገባውም ደቀ መዝሙሬም ሊሆን አይችልም ብሏል ብሎ አሰበ።ይህንንም በአለ ጊዜ ሰይጣን እንደ ጢስ ሆኖ ተበተነ።አባ ገዐርጊም ሰይጣን እንደ ሆነ አወቀ በዚያን ጊዜም ያ የብርሃን ምሰሶ ደግሞ ተገለጠለት የእግዚአብሔርም መልአክ በመነኵሴ አምሳል አብሮት ተጓዘ ቅዱሱም መልአኩን ተከተለው እርሱም ከአባ አርዮን ገዳም አደረሰው።አባ ገዐርጊም ከአንድ ጻድቅ ሰው መነኵሴ ጋራ በዚያ ዐሥራ አራት ዓመት ወጥሳይቀምስ ወይን ሳይጠጣ የአትክልት ፍሬም ቢሆን በዚህ በዐሥራ አራት ዓመት ያህል ከሚቀመጥ በቀር አልተኛም።

ተጋድሎውንም በጨመረ ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ተገለጠለትና እንዲህ አለው ሥጋህ እንዳይደክም በመካከለኛ ገድል ተጋደል ብሎሃል ጌታ።ከዚህም በኃላ ሊሠራው የሚገባውን ሥርዓት ሠራለት ።ሁል ጊዜም እስከሚመሽ እንዲጾም ትንሽም እንጀራን እንዲበላ ከአራት ሰዓት እስከ መንፈቀ ሌሊት ስለ ሥጋው ዕረፍት እንዲተኛ በቀረው ሌሊት እስቲነጋ ተግቶ እንዲጸልይ።

በዚህም ተጋድሎ ብዙ ዘመናት እየተጋደለ በኖረ ጊዜ በበረሀ ውስጥ ብቻውን ሊኖር ወዶ በጫካ ውስጥ እየተመላለሰ ሁለት ዓመት ኖረ።ከዚህም በኃላ ጌታ ተገለጾለት ወደ ቦታው እንዲመለስ አዘዘው።ያን ጊዜም አምላካዊት ኃይል ከከበሩ መክሲሞስና ደማቴዎስ ገዳም አደረሰችው እርሷም ለደብሩ አቅራቢያ ናት።

ወደ ደብሩም በተመለሰ ጊዜ በዚያን ወቅት አብርሃም ከዓለም ወደዚያ ገዳም መጥቶ ሁለቱም ተገናኙና በአንድነት ተስማምተው የአስቄጥስ ገዳም አበ ምኔት ወደ ሆነ ወደ አባ ዮሐንስ ደረሱ።እርሱም ቦታ ሰጥቷቸው በውስጡ ኖሩ ያ ቦታም እስከ ዛሬ ታውቆ ይኖራል ።

ያቺም ዋሻ በግቢግ ትባላለች የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዐለት የሆነ ጣሪያዋን ሠንጥቆ ወደ እነርሱ የወረዳበት ናት ።እነርሱም ሰገዱለት ሰላምታም ሰጥቷቸው አጽናንቷቸው ከእርሳቸው ዘንድ ዐረገ።በዚያችም ጌታችን በወረደበት መስኮት ብርሃንን አዩ እስከ ዛሬም የተከፈተች ሁና ትኖራለች።

እሊህ ቅድሳንም ለመነኰሰኘሳት የሚሆን ብዙ ድርሳናትንና ብዙ ተግሣጻትን ደረሱ።ለአባቶቹ የሚታዘዘውንና የሚገዛውን አመሰገኑት።ከዚህም በኋላ አባ አብርሃም ጥር ሁለት ቀን አረፈ። ከእርሱ በኋላም የከበረ አባ ገዐርጊ በዚች በግንቦት ወር በዐሥራ ስምንት ቀን አረፈ።መላ ዕድሜውም ሰባ ሁለት ዓመት ሆነ።በዓለም ዐሥራ አራት ዓመት በምንኩስና ኃምሳ ስምንት ዓመት ነው። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትሁን አሜን።

በዚችም ዕለት የሰማዕት ሲኖዳ መታሰቢያው ነው በረከቱ ከእኛ ጋራ ለዘላለም ትኑር አሜን።

አምላከ ገዐርጊ ከቅዱስ መንፈሱ ጸጋ ለኃጥአን ባሮቹ ያድለን::

[ † ግንቦት ፲፰ [ 18 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. ቅዱሳን ሐዋርያት ወአርድእት
፪. አባ ገዐርጊ ገዳማዊ
፫. ቅዱስ ሲኖዳ ሰማዕት

[ †  ወርሐዊ በዓላት ]

፩. ቅዱስ ፊልዾስ ሐዋርያ
፪. አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ሰባኬ ሃይማኖት [ረባን]
፫. አቡነ አኖሬዎስ ዘደብረ ጽጋጋ
፬. ማር ያዕቆብ ግብፃዊ

" በዓለ ሃምሳም የተባለው ቀን በደረሰ ጊዜ ሁሉም በአንድ ልብ ሆነው አብረው ሳሉ ድንገት እንደሚነጥቅ አውሎ ነፋስ ከሰማይ ድምጽ መጣ:: ተቀምጠው የነበሩበትንም ቤት ሁሉ ሞላው:: እንደ እሳትም የተከፋፈሉ ልሳኖች ታዩአቸው:: በእያንዳንዳቸውም ላይ ተቀመጡባቸው:: በሁሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው:: መንፈስም ይናገሩ ዘንድ እንደሰጣቸው በሌላ ልሳኖች ይናገሩ ጀመር :: " [ሐዋ.፪፥፩] (2:1-4)

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
ፀሐይ ብርሃን ካልሰጠች ፀሐይ አትባልም፤ ብርሃን ተፈጥሮዋ አይደለምና፡፡ እንስሳት ካልተነፈሱ እንስሳት አይባሉም፤ መተንፈስ ተፈጥሮአቸው ነውና፡፡ ዓሣ ከውኃ ከወጣ ሕይወት ያለው ዓሣ መኾኑ ይቀርና ይሞታል፡፡ #አንድ_ክርስቲያንም እውነተኛ ክርስቲያን የሚባለው፡-

1.
#ሲጸልይ_ነው፡፡ ክርስቲያን ማለት በወልድ ውሉድ በክርስቶስ ክርስቲያን በመንፈስ ቅዱስም መንፈሳዊ መባል ነውና፡፡ ልጅ ከኾኑ ደግሞ አባትን ማናገር ክርስቲያናዊ ተፈጥሮ ነውና፡፡

2.
#ሲያመሰግን_ነው፡፡ ክርስቲያን ማለት እግዚአብሔር ፈጣሬ ዓለማት ነው ብሎ ማመን ነውና፡፡ ስለዚህ ለአንድ ክርስቲያን የሰማይና የምድር ውበት እየተመለከተ እግዚአብሔርን ማመስገኑ ክርስቲያናዊ ተፈጥሮው ነው፡፡

3.
#ሲመጸውት_ነው፡፡ ክርስቲያን ማለት ሀብት ኹሉ ከእግዚአብሔር እንደ ኾነ መመስከር ነውና፡፡ ስለዚህ ራስን እንደ መልእክተኛ አድርጎ በመቁጠር ያለውን ለሌላው ማካፈል ክርስቲያናዊ ተፈጥሮው ነውና፡፡

4.
#ቅዱሳት_መጻሕፍትን_ሲያነብ_ነው፡፡ ክርስቲያን ማለት በመንፈስ ቅዱስ ሀብት ደስ የሚሰኝ ነውና፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ መንፈስ ቅዱስ በቅዱሳት መጻሕፍት በኩል ሲናገር መስማት ለአንድ ክርስቲያን ክርስቲያናዊ ተፈጥሮው ነውና፡፡

#በቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ

#መልካም_ዕለተ_ሰንበት🙏

አጫጭር ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶች
•➢ 👇 ለማግኘት // 👇

@Enatachn_mareyam
@Enatachn_mareyam
2024/06/29 00:45:22
Back to Top
HTML Embed Code: