Telegram Web Link
ዳግማይ_ትንሣኤ (ፈጸምነ)

    በዓለ ትንሣኤ የበዓላት ሁሉ ርዕስ ነው፡፡ ስለሆነም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እስከ በዓለ ዕርገት ድረስ ያለውን ዘመነ ትንሣኤ ብላ ሰይማለች፡፡

ከስምንት ቀን በኋላም ደቀ መዛሙርቱ ደግመው በውስጥ ነበሩ፤ ቶማስም ከእነርሱ ጋር ነበረ፡፡ ደጆች ተዘግተው ሳሉ ኢየሱስ መጣ፤ በመካከላቸውም ቁሞ ‹‹ሰላም ለእናንተ ይሁን›› አላቸው፡፡  ቶማስ ጎኑን ካልዳሰስኩ ብሎ ነበርና ከዚያም በኋላ ቶማስን ‹‹ጣትህን ወደዚህ አምጣና እጆቼን እይ፤ እጅህንም አምጣና በጎኔ አግባው ያመንህ ሁን እንጂ ያላመንህ እትሁን›› አለው፤ (ዮሐ 20 ፥27)፡፡ ቶማስም ቢዳስሰው እጁ ከእሳት እንደ ገባ ጅማት ኩምትርትር አለች፤ እርሱም ጌታዬ አምላኬ ሆይ አለ፡፡ ኢየሱስም ‹‹ስላየኸኝ አምነሃል፤ ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዓን ናቸው›› ብሎ ፈውሶታል፡፡ ጎኑን የዳሰሰችው እጁ ዛሬም በሕያውነት በሕንድ ከታቦቱ ጋር ትኖራለች፤ በዓመት በዓመቱ  በእመቤታችን በዓል (በአስተርእዮ) ሊያጥኑ ሲገቡ ቀድሳ ታቆርባለች፤ የሚሾመውን ወጥታ ቀኝ እጁን ትይዘዋለች፡፡ እንዲህ እያለች እስከ ምጽአት ድረስ ትኖራለች፤ (አንድምታ ዘዮሐንስ ወንጌል 20፥28)፡፡

#መልካም_ዳግማዊ_ትንሣኤ_በዓል🙏

አጫጭር ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶች
      •➢ 👇  ለማግኘት // 👇

@Enatachn_mareyam  
@Enatachn_mareyam
                        †                        

🕊  💖        ሰ ላ ም ታ        💖  🕊

'' ክርስቶስ ተንስአ እሙታን
▸ በዐቢይ ኃይል ወስልጣን ፤
አሠሮ ለሰይጣን
▸ አግዐዞ ለአዳም ፤
ሰላም
▸ እምይእዜሰ ፤
ኮነ
▸ ፍስሐ ወሰላም ''

🕊

'' ክርስቶስ በታላቅ ኃይልና ስልጣን ከሙታን ተነሳ ፤ ሰይጣንን አሰረው ፤ አዳምንም ነጻ አወጣው ፤ ስለዚህም ከእንግዲህ ወዲህ ፍፁም ሰላም እና ደስታ ሆነ። ''

💖

[ †  🕊  ክብርት ሰንበት  🕊 † ]

" ንጉሥ ከእርሱ ርቀን የነበርን እኛ ቤዛችን በሚሆን በልጁ ሕማም ከእርሱ ምን ያህል ክብር እንዳገኘን ዐወቅህን? ሞት ጠፋ ፣ ዲያብሎስም ድል ተነሣ ፣ ሲዖል ታወከ ፣ በኃጢአት የተፈረደው ፍርድ ተፋቀ ፣ ሰይጣን ያመጣው ስሕተት ጠፋ። እንዳልነበረም ሆነ ገነት ተከፈተ ትንሣኤ ተገለጠ"

[ ቅዱስ ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ ]

---------------------------------------------

" ለክርስቶስ ፡ ይደሉ ፡ ስብሐት ፤ ለዘአብጽሐነ ፡ እስከ፡ ዛቲ ፡ ሰዓት ፤ እግዚኣ ፡ ለሰንበት ፤ አኰቴተ ፡ ነዓርግ ለመንግሥትከ ፡ ወመኑ ፡ መሐሪ ፡ ዘከማከ።

ትርጉም ፦

[ እስከዚኽች ሰዓት ለአደረሰን ለክርስቶስ ክብር ምስጋና ይገባል፡፡ የሰንበት ጌታዋ ነው፡፡ ለጌትነትህ ምስጋና እናቀርባለን፡፡ እንዳንተ ያለ ይቅር ባይ ማነው ? ]

[ ቅዱስ ያሬድ ]


†                       †                        †
💖                    🕊                     💖
                        †                        

🕊  💖    ዕለተ ሰንበት   💖   🕊

▬▬▬▬▬▬  †  ▬▬▬▬▬▬

†  🕊 ዳግሚያ ትንሳኤ !   🕊  †



እንኩዋን ለዳግሚያ ትንሳኤ በሰላም አደረሳችሁ።

ለስም አጠራሩ ጌትነት ይድረሰውና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅድስት ትንሳኤው በሁዋላ ለደቀ መዛሙርቱ በጉባኤ ፫ [3] ጊዜ ተገልጦላቸዋል :-

፩. በዕለተ ትንሳኤ ምሽት በፍርሃት ሳሉ
፪. ያላመነ ቶማስን ለማሳመን በተነሳ በ ፰ [ 8 ]ኛው ቀን [ ማለትም ዛሬ ]
፫. ከተነሳ ከ ፳፫ [ 23 ] ቀናት በሁዋላ በጥብርያዶስ ባሕር ዳርቻ ላይ ነው::

ጌታ አርባውን ቀን ለአንዱም: ለሁለቱም በግል ይገለጥላቸው ነበር:: እመቤታችንን ግን ፈጽሞ አይለያትም ነበር::

ጌታችን ከተነሳ በሁዋላ ለሳምንት ተለይቷቸው ስለ ነበር በቤተ ክርስቲያን ውዳሴ ማርያም እንጂ መልክዐ ኢየሱስ በማሕበር አይደገምም::

በዚሕች ዕለት ደቀ መዛሙርቱ በጽርሐ ጽዮን ሳሉ ጌታችን "ሰላም ለእናንተ ይሁን" ብሏቸዋል:: ቶማስንም "ና ዳስሰኝ" ብሎታል:: ሐዋርያው እጁን ከተወጋ ጐኑ ላይ ቢያሳርፍ በመቃጠሉ "ጌታየ አምላኬም" ሲል ጮሆ ምስጢረ ተዋሕዶውን መስክሯል::

ጌታም ቶማስን "እስመ ርኢከኒሁ አመንከኒ" [ማለትም ስላየኸኝ አመንከኝ] ! "ብጹዐንሰ እለ እንዘ ኢይሬእዩኒ የአምኑኒ" [ሳያዩ የሚያምኑ ግን ብጹዐን (ማለትም ንዑዳን ክቡራን) ናቸው ብሎታል:: [ዮሐ.፳፥፳፬] (20:24)

ከጌታችን ከትንሳኤው: ከቅዱሱም ሐዋርያ በረከት አይለየን::

ደጆች ተዘግተው ሳሉ ኢየሱስ መጣ:: በመካከላቸውም ቆሞ 'ሰላም ለእናንተ ይሁን' አላቸው:: ከዚያም በሁዋላ ቶማስን 'ጣትህን ወደዚህ አምጣና እጆቼን እይ:: እጅህንም አምጣና በጐኔ አግባው:: ያመንህ እንጂ ያላመንህ አትሁን' አለው:: ቶማስም 'ጌታዬ አምላኬም' ብሎ መለሰለት:: ኢየሱስም 'ስላየኸኝ አምነሃል:: ሳያዩ የሚያምኑ ብጹዓን ናቸው' አለው:: [ዮሐ.፳፥፳፮-፳፱] (20:26-29)

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †

[  ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


†                       †                        †
💖                    🕊                     💖
This media is not supported in your browser
VIEW IN TELEGRAM
                          †                          

[     🕊    ዳግሚያ ትንሳኤ !    🕊      ]

እንኩዋን ለዳግሚያ ትንሳኤ በሰላም አደረሳችሁ !

💖

እሁድ - ዳግም ትንሣኤ ይባላል

በዚህ ዕለት ክርስቶስ ለሦስተኛ ጊዜ ለደቀ መዛሙርቱ ተገልጦ ሰላምን መስበኩ እና ሥልጣንን መስጠቱ ይሰበካል፡፡

---------------------------------------------

"ደጆች ተዘግተው ሳሉ ኢየሱስ መጣ:: በመካከላቸውም ቆሞ 'ሰላም ለእናንተ ይሁን' አላቸው:: ከዚያም በሁዋላ ቶማስን 'ጣትህን ወደዚህ አምጣና እጆቼን እይ:: እጅህንም አምጣና በጐኔ አግባው:: ያመንህ እንጂ ያላመንህ አትሁን' አለው:: ቶማስም 'ጌታዬ አምላኬም' ብሎ መለሰለት:: ኢየሱስም 'ስላየኸኝ አምነሃል:: ሳያዩ የሚያምኑ ብጹዓን ናቸው' አለው::" [ዮሐ.፳፥፳፮-፳፱]

†                       †                        †
💖                    🕊                     💖
🕊

[ † እንኳን ለነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ኤርምያስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን። † ]

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †

†  🕊  ቅዱስ ኤርምያስ  🕊   

† ታላቁ ነቢይ ቅዱስ ኤርምያስ ከዐበይት ነቢያት አንዱ ሲሆን ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በስድስት መቶ አካባቢ የነበረ ነቢይ ነው:: አባቱ ኬልቅዩ ይባላል:: ከካህናተ እስራኤል አንዱ ነበር::

እግዚአብሔር ኤርምያስን የጠራው ገና በሕፃንነቱ ነበር:: "ከእናትህ ማኅጸን ሳትወጣ መርጬሃለሁ: ቀድሼሃለሁ" ሲልም በገሃድ መስክሮለታል:: [ኤር.፩፥፭] (1:5)

ከቅዱሳን ነቢያት እንደ ኤርምያስ የተሰቃየና ያለቀሰ የለም:: ከሰባ ዘመናት በላይ ስለ ወገኖቹ አልቅሷልና ሊቃውንት "ነቢየ ብካይ" [ባለ እንባው ነቢይ] ይሉታል::

ዘመኑ ዘመነ-ኃጢአት [ዘመነ ዐጸባ] ነበር:: እሥራኤላውያን ከመሪዎቻቸው ከነ ሴዴቅያስ ጋር በክፋት ተባብረውም ነበርና ኤርምያስን አልሰሙትም:: ይልቁኑ ክፉ ቦታ ውስጥ አስረው አሰቃዩት:: እግዚአብሔር ግን በኢትዮጵያዊው አቤሜሌክ አማካኝነት ከመከራው አዳነው::

የተሰበከላቸውን የንስሐ ጥሪ አልሰሙምና ስልምናሦር የሚባል የአሕዛብ ንጉሥ መጥቶ አሥሩን ነገድ ማርኮ በ፯፻፳፪ [722] አሦር [ነነዌ] አወረዳቸው:: በኋላ ደግሞ በኃይለኝነቱ የታወቀው የባቢሎን ንጉሥ ይማርካቸው ዘንድ ወደ ሁለቱ ነገድ ኢየሩሳሌም ደረሰ:: ኤርምያስ ወደ ከተማዋ ዳር ወጥቶ ስለ ኢየሩሳሌምና ስለ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አለቀሰ::

ከቤተ መቅደስ ንዋያት እኩሉን ለምድር አደራ ሰጣትና ሸሸገችው:: ነቢዩ የተናገረው አይቀርምና ንጉሡ ናቡከደነጾር እኩሉን ገድሎ: እኩሉንም ማርኮ: ኢየሩሳሌምን አቃጥሎ: የአሕዛብ መዘባበቻ አድርጐ በ፭፻፹፮ [586] ባቢሎን አወረዳቸው::

ቅዱስ ኤርምያስን ግን ትሩፋን [ከመከራው የተረፉት] ይዘውት ወደ ግብጽ ወረዱ እንጂ አልተማረከም:: በዚያም ተአምራትን አድርጐ አራዊትን አጥፍቷቸዋል:: ትንሽ ቆይቶ ግን እውነተኛ አባት : ነቢይ : መምሕርም ነውና ወደ ሕዝቡ [ወደ ባቢሎን] ወረደ:: በዚያም ትንቢትን እየተናገረ : ሕዝቡን ከሰባ ዓመታት በኋላ ወደ ሐገራቸው እንደሚመለሱ እያስተማራቸው በባቢሎን ቆይቷል:: ያለ በደሉም በመከራቸው ተካፋይ ሆኗል::

ሰባው ዘመን ሲፈጸም እግዚአብሔር እንደ ቃል ኪዳኑ በኤርምያስ መሪነት እሥራኤል ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ:: አሁንም ግን ክፋታቸውን ይተው ዘንድ ፈቃደኞች አልነበሩምና ኤርምያስ ገሠጻቸው::

በዚህ ተበሳጭተው ሊወግሩት ሲሉ ጸጋ በዝቶለት : ምሥጢርም ሰፍቶለት ስለ ነገረ ሥጋዌ [ስለ ክርስቶስ የማዳን ሥራ] አምልቶና አጉልቶ ትንቢት ተናገረ:: አንዴ ልቡናቸው ታውሮ ኤርምያስ ነው ብለው ድንጋዩን በድንጋይ ሲወግሩት ውለዋል:: ዘግይቶ ግን ኤርምያስ ራሱን ገለጠላቸው:: ስለ እነርሱ ሲል ሰባ ዘመን ያለቀሰውንና ምትክ የሌለውን አባታቸውን ወግረው ገደሉት::

ታላቁ ነቢይ ቅዱስ ኤርምያስ ሃምሳ ሁለት ምዕራፎች ያሉት ሐረገ ትንቢት ተናግሯል / ጽፏል:: ዜና ሕይወቱ ከራሱ የትንቢት መጽሐፍ በተጨማሪ በተረፈ ኤርምያስ : በመጽሐፈ ባሮክ : በገድለ ኤርምያስ : በዜና ብጹዐን : በመጽሐፈ ስንክሳርም ተጽፏል::

† ቸር እግዚአብሔር በኤርምያስ ምልጃ ሃገራችንን ከጥፋት: ሕዝቦቿን ከስደትና ከመቅሰፍት ይሰውርልን::

🕊

[ † ግንቦት ፭ [ 5 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. ቅዱስ ኤርምያስ ነቢይ [ከታላላቆቹ ነቢያት አንዱ]

[ † ወርኀዊ በዓላት ]

፩. ቅዱስ ጴጥሮስ ሊቀ ሐዋርያት
፪. ቅዱስ ጳውሎስ ሐዋርያ
፫. አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ
፬. ቅዱስ ዮሐኒ ኢትዮጵያዊ
፭. ቅዱስ አሞኒ ዘናሒሶ

" ኢየሩሳሌም ሆይ ነቢያትን የምትገድል : ወደ እርሷ የተላኩትንም የምትወግር : ዶሮ ጫጩቶቿን ከክንፎቿ በታች እንደምትሰበስብ ልጆችሽን እሰበስብ ዘንድ ስንት ጊዜ ወደድሁ! አልወደዳችሁምም:: እነሆ ቤታችሁ የተፈታ ሆኖ ይቀርላቹሃል:: እላችሁአለሁና : በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው እስክትሉ ድረስ እንግዲህ ወዲህ አታዩኝም :: " [ማቴ. ፳፫፥፴፯-፴፱]

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ ]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
🕊

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ †

[ † ግንቦት ፮ [ 6 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]


†  🕊  አባ መቃርስ ካልዕ  🕊  †

ይህ ቅዱስ "መቃርዮስ: መቃርስ: መቃሬም" ይባላል:: ትርጉሙ በ ፫ [3]ቱም መንገድ አይለወጥም:: ምክንያቱም ሥርወ ቃሉ በዮናኒ ልሳን "ብጹዕ: ንዑድ: ክቡር" ማለት ነውና::

ከስሙ ቀጥሎ "ካልዕ-፪ [2] ኛው": አንዳንዴ ደግሞ "እስክንድርያዊ" እየተባለ ይጠራል:: "ካልዕ-፪ [2] ኛው" የሚባለው ከቀዳሚው [ታላቁ መቃርስ] ለመለየት ሲሆን "እስክንድርያ" ደግሞ ተወልዶ ያደገባት ሃገር ናት::

አባ መቃርስ በ ፬ [4]ኛው መቶ ክ/ዘመን የነበረ ገዳማዊ: ጻድቅና ትሩፈ-ምግባር ነው:: በዓለም ለ ፵ [40] ዓመት ሲኖር እንደ ሕጉ ፈጣሪውን ደስ ያሰኘ ሰው ነው:: ጻድቃን እንደ ከዋክብት በበዙበት በዚያ ዘመን የታላቁ መቃርስን ዜና ሰምቷልና ይህቺን ክፉ ዓለም ከነግሳንግሷ ንቋት በርሃ ገብቷል::

እንደሚገባ ሥርዓተ ገዳምን ጠብቆ: ለአበው ታዞ: በጾም: በጸሎት: በትሕትናና በስግደት ተጠምዶ ቢያገኘው ፈጣሪ አከበረው:: በዚያ ጊዜም ለታላቁ ገዳመ አስቄጥስ መናንያን አበ ምኔት ሊሆን መረጡት::

እርሱም እረኝነትን ያውቃልና በጐቹን [መነኮሳትን] ከተኩላ [ሰይጣናት] ይጠብቅ ዘንድ ብዙ ተጋ:: ከብቃቱ የተነሳም ሳያስታጉል: ሳይበላ: ሳይጠጣና ሳይቀመጥ እስከ ፵ [40] ቀን ይጸልይ ነበር:: ሲጸልይ ደግሞ በልቡ እየተቃጠለ በፍቅረ ክርስቶስ ነበርና አጋንንት ይርዱለት ነበር::

እርሱ ጸሎት ሲጀምርም በገዳሙ ዙሪያ ያሉ አጋንንት እየጮሁ ይሸሹ ነበር:: ከተጋድሎው ጽናትና ከትሕትናው ብዛት የተነሳ ያዩት ትዕቢተኞች ሁሉ ይገሠጹ ነበር:: በዘመኑም ብዙ ተአምራትን ሠርቷል::

አንድ ቀን በበዓቱ ሳለ ጅብ መጥታ ተማጸነችው:: አብሯት ወደ ዋሻዋ ቢሔድ ልጆቿ በሙሉ ዓይነ ሥውራን ሆነው አገኛቸው:: እርሱም ወደ መሬት ምራቁን እትፍ ብሎ በጭቃ ለውሶ ቢቀባቸው የሁሉም ዐይናቸው በርቷል::

ስለ ውለታውም ጅቢቱ የበግ ቆዳ እየጐተተች አምጥታ ሰጥታዋለች:: [ከሰው ልጅ በቀር እንስሳት ውለታን አይረሱምና] ቅዱስ መቃርስም ለወትሮው ባዶው መሬት [አፈር] ላይ ይተኛ የነበረው ከዚያ ቀን በኋላ በአጐዛው ላይ የሚተኛ ሁኗል::

በሃገሩ እስክንድርያም ለ ፪ [2] ዓመታት ዝናብ በመጥፋቱ ሕዝቡ ተጨንቆ ነበርና "ናልን" ሲሉ መልዕክት ላኩበት:: እርሱ መጥቶ ሲጸልይም መብረቅ የቀላቀለ ዝናብ ጣለ:: ዝናቡም ያለ ማቆም ለ ፪ [2] ቀናት በመዝነቡ ሕዝቡ ፈርተው "አባታችን ስለ ኃጢአታችን እንዳንጠፋ ለምንልን?" አሉት:: እርሱም በጸሎቱ [በፈጣሪው ኃይል] እንደ ወደዱት ዝናቡን አቁሞላቸዋል::

የአባ መቃርስን ዜና ሕይወትና ተአምራት ተናግሬ አልፈጽመውም:: ግን አንዲት ብቻ ላክል:: ሁሌ ሳስበው ስለሚገርመኝም ነው::

ብዙዎቻችን የጌታችን ሥጋና ደም አንቀበልም:: ለምን ያከበርነውና የፈራነው አስመስለን ኃጢአትን ለመጥገብ ቦታን [አጋጣሚን] ስለምንፈልግ:: በተቃራኒው ደግሞ አንዳንዶቻችን መለኮት የተዋሐደውን የጌታ ሥጋና ደም እንደ ተርታ ነገር [ያለ ጥንቃቄ] ስንቀበል ይታያል:: ፪ [2] ቱም ግን ስሕተት ነው::

ፈርተን [ፍርሃቱ ጤነኛ ባይሆንም] ስለ ራቅን በፍርድ ቀን ማምለጥ አንችልም:: "ሥጋየን ያልበላ: ደሜንም ያልጠጣ የዘለዓለም ሕይወት የለውም" ይለናልና:: [ዮሐ.፮፥፶፪] (6:52)

በድፍረት ለምንቀበልም ሥጋው እሳት ሁኖ እንዳይበላን: ደሙም ባሕር ሆኖ እንዳያሰጥመን ልናከብረው ይገባናል:: "ሳይገባው ከጌታ ሥጋና ደም የተቀበለ የጌታ ሥጋ ዕዳ አለበት" ይለናልና::  [፩ቆሮ.፲፩፥፳፯] (11:27)

"ታዲያ የሚሻለው ለሁላችንም ንስሃ ገብቶ: በፍርሃት ሆኖ መቅረቡ ነው::"

ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና አባ መቃርስ ወደ በርሃ እንደ ገባ ሥጋ ወደሙን ተቀብሎ ነበር:: ቅዱሱ ይህንን እያሰበ ለ ፷ [60] ዓመታት ምራቁን ሳይተፋ ኑሯል:: ለዚያ አይደል አበው "ብታከብሩት ያከብራቹሃል" ያሉት::

ሊቃውንቱም ይህንን ሲያደንቁ :-

"ኢታስተማስልዎ ለቁርባን ከመ ሕብስት ዕራቆ:: አኮኑ ሥጋ መለኮት ዘይትላጸቆ:: መቃርዮስ አብ ዕበየ ቁርባን ለአጠይቆ:: ድኅረ ተወክፈ በአሚን እንበለ ያብዕ ናፍቆ:: መጠነ ዓመታት ስሳ ኢተፍአ ምራቆ::" ብለዋል::

ቅዱስ መቃርስም በ ፻ [100] ዓመቱ በ ፭ [5] ኛው ክ/ዘመን መጀመሪያ አካባቢ በዚህች ቀን ዐርፏል::

ጌታችን ከክብሩ : ከበረከቱ አይለየን::

🕊

[ †  ግንቦት ፮ [ 6 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. ቅዱስ አባ መቃርስ ገዳማዊ
፪. እናታችን ቅድስት ሰሎሜ ኢትዮዽያዊት
፫. አባ ይስሐቅ ጻድቅ
፬. ቅድስት ዲላጊና ፬ [4] ሴት ልጆቿ [ሰማዕታት]
፭. ቅዱስ ዳናስዮስ ሰማዕት
፮. ቅዱስ በንደላዖስ ሰማዕት [የታላቁ ኤስድሮስ አባት]
፯. አባ አሞን ጻድቅ [ዽዽስናን አልፈልግም ብሎ የሸሸ አባት]

[ † ወርኀዊ በዓላት ]

፩. ቅድስት ደብረ ቁስቁዋም
፪. አባታችን አዳምና እናታችን ሔዋን
፫. አባታችን ኖኅና እናታችን ሐይከል
፬. ቅዱስ ኤልያስ ነቢይ
፭. ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ
፮. ቅዱስ ዮሴፍ አረጋዊ
፯. ቅድስት ሰሎሜ
፰. አባ አርከ ሥሉስ
፱. አባ ጽጌ ድንግል
፲. ቅድስት አርሴማ ድንግል

" ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘለዓለም ሕይወት አለው:: እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሳዋለሁ:: ሥጋዬ እውነተኛ መብል: ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነውና:: ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል:: እኔም በርሱ እኖራለሁ:: "  [ዮሐ.፮፥፶፫-፶፮] (6:53-56)

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
🕊

†   🕊   በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡   🕊   †

❖ እንኳን አደረሳችሁ ❖

ግንቦት ፯ [ 7 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት


🕊 †  ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ †  🕊

በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከሐዋርያት ቀጥሎ የቅዱስ አትናቴዎስን ያሕል ስለ ሃይማኖት የተዋጋ ቅዱስ ፈልጐ ማግኘት አይቻልም::

†  ቅዱስ አትናቴዎስ ማን ነው ?

ቅዱስ አትናቴዎስ በቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት በዘመነ ሰማዕታት መጠናቀቂያ በ፫፻ [300] አካባቢ ፪፻፺፮ (296) እስክንድርያ ግብፅ ውስጥ ነው የተወለደው:: ወላጆቹ አረማውያን በመሆናቸው ክርስትናን አልተማረም ነበር::

ሕጻን እያለ ለጭዋታ ከቤቱ ሲወጣ የክርስቲያን ልጆች ሃይማኖታዊ ጨዋታ ሲጫወቱ ተመለከተ:: ሊቀላቀላቸው ቢፈልግም ክርስቲያን ባለመሆኑ ከለከሉት:: አትናቴዎስም ክርስቲያን ልሁንና አጫውቱኝ ብሏቸው እሺ ስላሉት ሕጻናቱ ዕጣ ተጣጣሉ::

ላንዱ ቄስ: ላንዱም ዲያቆን መሆን ሲደርሳቸው ለአትናቴዎስ ፓትርያርክ መሆን ስለ ደረሰው ሌሎቹ ሕጻናት ይሰግዱለት ጀመር:: በአጋጣሚ ሕጻናቱ ይሕንን ሁሉ ሲያደርጉ የወቅቱ ፓትርያርክ ቅዱስ እለ እስክንድሮስ በመገረም ያያቸው ነበርና ለሕጻኑ አትናቴዎስ ትንቢት ተናገረለት::

ከዚያም የአትናቴዎስ አባቱ ሲሞት ሊቀ ዻዻሳቱ ከእናቱ ወስዶ አጥምቆ: የሚገባውን መንፈሳዊ ትምሕርት ሁሉ በልቡናው ላይ ቀረጸበት:: ከዚሕ በኋላ ዲቁናን ሹሞ አስተምር አለው:: ምንም ሕጻን ቢሆንም ከሊቅነቱ: ከአመላለሱና ከአንደበቱ ጣፋጭነት የተነሳ የሰማው ሁሉ ይደነቅ ነበር:: ጸጋ እግዚአብሔር በእርሱ ላይ አድራለችና::

ቅዱስ አትናቴዎስ ሊቀ ዲቁና በተሾመ ወራት አርዮስ ቤተ ክርስቲያንን በመረበሹ ኒቅያ ላይ ፫፻፲፰ [318] ቱ ሊቃውንት ሲሰበሰቡ ጸሐፊ አድርገው ሾሙት:: በጊዜውም በዕድሜ የስንት ጊዜ ትልቁ የሚሆነውን አርዮስን ተከራክሮ ምላሽ አሳጣው::

†  ቅዱስ

አትናቴዎስ ከሊቃውንቱ ጋር ሆኖ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ ወልደ አምላክ: እግዚአብሔር መሆኑን በአደባባይ መሠከረ:: ጸሎተ ሃይማኖትንም ያረቀቀው እርሱ ነው::

ከዚሕ በኋላ የእስክንድርያ [የግብፅ] ፳ [20] ኛ ፓትርያርክ ሆኖ ተሾመ:: ቤተ ክርስቲያንን በመልካም እረኝነት ለ፵፰ [48] ዓመታት ሲመግብ ብዙ መከራዎችን ተቀበለ:: ለ፭ [5] ጊዜ ከመንበሩ አፈናቅለው ወደ በርሃ ሲያግዙት በስደት ከ፲፭ [15] ዓመታት በላይ አሳልፏል::

በተሰደደባቸው ቦታዎች መከራን እየተቀበለ ያላመኑትን አሳምኗል:: በጎቹ እንዳይባዝኑበት ደግሞ በጦማር [በደብዳቤ] ይጠብቃቸው ነበር:: ዛሬ በሃይማኖተ አበው የምናገኘው ቃለ ሃይማኖት በዚሕ ዘመን የተጻፈ ነው::

በወቅቱ የነበረው ንጉሥ [ትንሹ ቆስጠንጢኖስ] የአባቱን [ታላቁ ቆስጠንጢኖስን] ዕረፍት ተከትሎ ነገሠ::

ወዲያውም አርዮሳዊ መናፍቅ ሆነ:: ሃይማኖታቸው የቀና አባቶችንም ያሳድድ ገባ:: ከአበው ቅዱሳን መካከል ግንየዚህ መከራ ቀዳሚው ገፈት ቀማሽ ታላቁ ሊቅ ቅዱስ አንትናቴዎስ ነበር::

በተለይ አንድ ጊዜ ንጉሡ ቅዱሱን ወደ በርሃ አግዞ: መናፍቅ ዻዻስ በግብጽ ሹሞ: ብዙ ክርስቲያኖችን በግፍ ሲያስገድል: ቅዱሱን ለ፮ [6] ዓመታት አሰቃየው:: የወገኖቹ [የልጆቹን] ስቃይ የሰማው ቅዱስ አትናቴዎስ ግን በድፍረት ወደ ቤተ መንግስት ገብቶ ተናገረው::

፪ [2] አማራጭን አቅርቦ "ወይ ግደለኝና እንደ አባቶቼ ሰማዕት ልሁን: ካልሆነ ግን ወደ መንጐቼ [ምዕመናን] መልሰኝ" አለው:: መናፍቁ ንጉሥም ቢገድለው ብጥብጥ እንደሚነሳ ስለሚያውቅ በስልት ሊያጠፋው ወሰነ::

ቀዛፊ: መቅዘፊያ: ምግብና ውሃ በሌላት ጀልባ ውስጥ ከቶም ሜዲትራኒያን ባሕር ውስጥ ጣለው:: ድንገት ግን ከሰማይ ጌታችን መላእክቱን አስከትሎ ወረደ::

ሚካኤልና ገብርኤል ባሕሩን እየቀዘፍ: ሌሎች መላእክት እየመገቡት በዚህች ቀን እስክንድርያ [ግብጽ] አድርሰውት ተሠውረዋል:: ሕዝቡም በታላቅ ሐሴት እየዘመሩ አባታቸውን ተቀብለውታል::

ሐዋርያዊው ቅዱስ ስለ ኦርቶዶክስ ተዋግቶ: ብዙ ስቃይንም ተቀብሎ በ፫፻፹፫ [373] ዓ/ም አካባቢ አርፏል:: ቤተ ክስርቲያን ፦
- "ሊቀ ሊቃውንት:
- ርዕሰ ሊቃውንት:
- የቤተ ክርስቲያን
- [ የምዕመናን ] ሐኪም [ Doctor of the Church ]:
- ሐዋርያዊ" ብላ ታከብረዋለች::

አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሊቁ በረከት አይለየን:: በምልጃውም ሃይማኖታችንን ይጠብቅልን::

🕊

[ † ግንቦት ፯ [ 7 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ
፪. የባሕታውያን አለቃ ታላቁ አባ ሲኖዳ [ጽንሰቱ]
፫. ቅዱስ ዮሐንስ ጻድቅ [ሃብቱን: ንብረቱን: ልብሱን
ሳይቀር መጽውቶ ራቁቱን የተገኘ ደግ ሰው ነው]
፬. አባ ሐርስዮስ ገዳማዊ

[ †  ወርሐዊ በዓላት ]

፩. ሥሉስ ቅዱስ [አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ]
፪. አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ
፫. አባ ሲኖዳ [የባሕታውያን አለቃ]
፬. አባ ዳንኤል ዘገዳመ ሲሐት
፭. አባ ባውላ ገዳማዊ
፮. ቅዱስ አግናጥዮስ [ለአንበሳ የተሰጠ]

" ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብጹዐን ናቸው:: መንግስተ ሰማያት የእነርሱ ናትና:: ሲነቅፉአችሁና ሲያሳድዱአችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብጹዓን ናችሁ:: ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ:: ሐሴትም አድርጉ:: ከእናንተ በፊት የነበሩ ነቢያትን እንዲሁ አሳደዋቸዋልና። " [ማቴ.፭፥፲] (5:10)


[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ ]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
🕊

[  † እንኳን ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጥንተ በዓለ ዕርገት እና ለጻድቁ አባ ዳንኤል ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን። †   ]

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ! †


 †  🕊   ዕርገተ እግዚእ   🕊  †  

† ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በዓለ ዕርገትን ፪ [2] ጊዜ ታከብራለች:: አንዱ "ጥንተ በዓል" : ሁለተኛው ደግሞ "የቀመር በዓል" ይሠኛል:: ጥንተ በዓል ማለት ጌታችን በትክክል ያረገበትን ቀን ያመለክታል::

የክብር ባለቤት መድኃኔ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ በኪነ ጥበቡ [በሕማሙ : በሞቱ] ዓለምን አድኖ: ፵ [40] ቀን ለሐዋርያቱ መጽሐፈ ኪዳንን: ትምሕርተ ኅቡዓትን አስተምሯቸዋል::

በ፵ [40] ኛው ቀን ፻፳ [120] ውን ቤተሰብ ይዟቸው ወደ ቢታንያ ወጣ:: በዚያም እስከ ሊቀ ዽዽስና ድረስ ሾሟቸው : ከኢየሩሳሌም እንዳይወጡም አዟቸው የመንፈስ ቅዱስን ተስፋ ጠብቁ ብሏቸዋል:: እየባረካቸው በተዋሐደው ሥጋ ወደ ሰማያዊ ዙፋኑ አርጓል::

ሰማያት: ምድር: ደመናት: ነፋሳት: መባርቅትና መላእክት: ፍጥረት በሙሉ አመስግኗል:: አይሁድ መናፍቃን ዕርገቱን ምትሐት ነው እንዳይሉ: ጌታችን ትንሳኤውን አማናዊ እንደሆነ ለማስረዳት በ፵ [40] ኛው ቀን ዐረገ::

አንድም ራስ ባለበት ሌሎች የሰውነት ክፍሎች ሊኖሩ ይገባልና ጌታችን ዕርገቱን በገሃድ አደረገው:: "ዐርገ እግዚእ ከመ ያለቡ ዕርገተ ጻድቃን ንጹሐን" እንዲል::

† ዐርገ እግዚአብሔር በይባቤ::
ወእግዚእነ በቃለ ቀርን::
ዘምሩ ለአምላክነ ዘምሩ:: † [መዝ.፵፮፥፮] (46:6)


🕊  †  ታላቁ አባ ዳንኤል  †  🕊

† ይህ ቅዱስ አባት ስም አጠራሩ ክቡር ነው:: በሁሉ ነገሩ የተቀደሰ የገዳማውያን መብራትም ነው:: ከተረፈ ንጹሕ ሕይወቱ ጣዕመ መንግስተ ሰማያትን አይቷልና:: አባ ዳንኤል በትውልድ ግብጻዊ ሲሆን ዓለምን ንቆ [መንኖ] ገዳም የገባው ገና በወጣትነቱ ነው::

ጊዜውም ዘመነ ጻድቃን [በ፭ [5] ኛው መቶ ክ/ዘመን] ነበር:: በገዳመ አስቄጥስ እና በደብረ ሲሐት ይታወቃል:: ታላቋ መካነ ቅዱሳን ገዳመ ሲሐት ዛሬም ድረስ በስሙ የምትጠራ ሲሆን ለዚህም ምክንያቱ እጅግ ለብዙ ዘመናት በውስጧ ተጋድሎ ፍሬ ስላፈራባት : ደቀ መዛሙርትን በቅድስና ስለ ወለደባት ነው::

ስለዚህም ዛሬም ድረስ "አባ ዳንኤል ዘደብረ ሲሐት" ተብሎ ሲጠራ ይኖራል:: ሌላኛው ስሙ ደግሞ "ዘገዳመ አስቄጥስ" ይሰኛል:: ገዳመ አስቄጥስ የታላቁ ቅዱስ መቃርስ ርስት ሲሆን በዓለም በስፋትም : ብዙ ቅዱሳንን በማፍራትም አንደኛ የሆነ ገዳም ነው::

በዚህ ገዳም ላይ አበ ምኔት ሆኖ የሚሾሙ አበው ሁሌም የብቃት መዓርግ ላይ የደረሱ ሲሆኑ ክብራቸው ከፓትርያርክ በላይ ነው:: አባ ዳንኤልም ከብዙ የቅድስና ዓመታት በኋላ በአስቄጥስ ገዳም አበ ምኔት ሆኖ ተሹሞ እልፍ አእላፍ መነኮሳትን በጽድቅ መንገድ መርቷል::

ቅዱሱ ከትጋቱ የተነሳ ለምግብና ለእንቅልፍ ጊዜ አልነበረውም:: ቀን ቀን መነኮሳቱን ሲናዝዝ : ድውያንን ሲፈውስ : ሥርዓተ ገዳምን ሲቆጣጠር ይውላል:: ልክ ሲመሽ ጭው ወዳለውና ስውራን ወደ ሚገኙበት በርሃ ይወጣል::

በዚያም ሙሉውን ሌሊት የተሰወሩ አባቶችን ሲፈልግ ያድር ነበር:: በዚህም ምክንያት የብዙ ስውራንን ገድል የጻፈ ሲሆን ባረፉ ጊዜም ገንዞ በመቅበር በረከታቸውን ተሳትፏል:: ታላቅ ሙያንም ፈጽሟል::

እርሱ ገንዞ ቀብሮ : ዜናቸውን ከጻፈላቸው ሥውራን ቅዱሳንም እንደ አብነት እሥራኤላዊቷን ቅድስት ዓመተ ክርስቶስን [ለ፴፰ [38] ዓመት ራቁቷን በሥውር የኖረች] እና ቅድስት በጥሪቃ ንግሥትን [መንግስቷን ትታ በሥውር የኖረች ናት] መጥቀስ እንችላለን::

ከዚህ ባለፈም አባ ዳንኤል በሰው ዘንድ የተናቁትንም ማክበርን ያውቅበታል:: ለምሳሌ በሴቶች ገዳም እብድ ናት ተብላ በበር የተጣለችውን ቅድስት አናሲማን : በእስክንድርያ ከተማ ሊቀ ዻዻሳቱ ሳይቀር "እብድ ነው" ብለው የናቁትን ቅዱስ ምሕርካን: እብድ ሳይሆኑ ራሳቸውን የሠወሩ ቅዱሳን መሆናቸውን ገልጧል::

አባ ዳንኤል ሐዋርያዊም ነበር:: በጊዜው ጦማረ ልዮን የሚባል የኑፋቄ ደብዳቤ ይላክ ነበርና ለዚህ ኬልቄዶናዊ ኑፋቄ በትጋት ምላሽ ይሰጥ ነበር:: አንድ ቀንም በንጉሥ ትዕዛዝ ኑፋቄው በእርሱ ገዳም ሊነበብ ሲል ቅዱሱ ከወታደሩ ቀምቶ ስለ ቀደደው ለሞት እስኪደርስ ደብድበውታል::

ጻድቁ አባ ዳንኤል አንዴ አውሎጊስ የሚባልድሃ ድንጋይ ጠርቦ እንግዳ ሲቀበል ተመልክቶ "ጌታ ሆይ! ይህንን ደግ ሰው ለምን ድሃ አደረከው?" ሲል በፈጣሪ ሥራ ገባ::

ጌታም እንደ ወትሮው በገሃድ ተገልጦ "በነፍስህ ትዋሰዋለህ?" አለው:: "አዎ ጌታየ" ስላለው ጌታችን ለአውሎጊስ ሃብትን ሰጠው:: ግን ወዲያው የጦር አለቃና ጨካኝ ሰው ሆነ::

ጻድቁ ወሬውን ሰምቶ ሊጠይቅ ቢሔድ የአውሎጊስ ወታደሮች ደበደቡት:: ጌታችንም አባ ዳንኤልን ወደ ፍርድ ዙፋኑ አቅርቦ "ወዳጄን መልስልኝ" አለው:: እመ ብርሃን ግን ቀርባ የልጇን እግር ሳመች::

"ልጄ ሆይ ማር!" አለችው:: ጌታም "እሺ" ብሎ ጻድቁን ወደ በአቱ: አውሎጊስን ወደ ቀደመ ግብሩ መለሳቸው:: የአባ ዳንኤል ድንቁ ብዙ ነው::

ሌላው ቢቀር ሽፍታ አባ ዳንኤልን መስሎ ወደ ደናግል ገዳም ሊዘርፍ : በማታለል ገባ:: ደናግሉም ጻድቁ መስሏቸው እግሩን አጥበው ዐይነ ስውሯን ቢቀቧት ዐይኗ በርቷል:: ሽፍታውም ደንግጦ ንስሃ ገብቷል:: አባ ዳንኤል ግን ተጋድሎውን ፈጽሞ በዚህች ቀን ዐርፏል::

† በተረፈው ግን ከቅድስና ሕይወቱ ባሻገር :-

፩. በገዳመ አስቄጥስ [ግብጽ] አበ ምኔት ሆኖ ተሹሞ ባሳየው ትጋት::
፪. በሃይማኖት ጠበቃነቱ በደረሰበት ድብደባና ስደት::
፫. ብዙ የበርሃ ቅዱሳንን በየበአታቸው እየዞረ በመቅበሩ::
፬. የብዙ ስውራን ቅዱሳንን ዜና ሕይወት በመሰብሰቡ::
፭. በየጊዜው በእግዚአብሔር ኃይል ይፈጽማቸው በነበሩ ተአምራት:: እና
፮. ለድንግል እመቤታችን ማርያም በነበረው ልዩ ፍቅር ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ታከብረዋለች::

† ቸር አምላክ ክርስቶስ ከዕርገቱና ከጻድቁ በረከት አይለየን::

🕊

[  † ግንቦት ፰ [ 8 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት  ]

፩. ቅዱሳን የጌታ ቤተሰብ [፻፳ (120) ው]
፪. ቅዱስ አባ ዳንኤል ጻድቅ
፫. ቅዱስ ዮሐንስ ሰማዕት
፬. ቅዱስ መክሲሞስ መስተጋድል
፭. አቡነ ዮሐኒ ዘደብረ ዳሞ [አቡነ ተክለ ሃይማኖትንና አቡነ ኢየሱስ ሞዐን ለምንኩስና ያበቁ]

[    † ወርሐዊ በዓላት    ]

፩. ቅዱስ ሙሴ ሊቀ ነቢያት
፪. ኪሩቤል [ አርባዕቱ እንስሳ ]
፫. አባ ብሶይ [ ቢሾይ ]
፬. አቡነ ኪሮስ
፭. አባ ሳሙኤል ዘደብረ ቀልሞን
፮. ቅዱስ ማትያስ ሐዋርያ [ከ፲፪ [12] ቱ ሐዋርያት]

" እስከ ቢታንያም አወጣቸው:: እጆቹንም አንስቶ ባረካቸው:: ሲባርካቸውም ከእነርሱ ተለየ:: ወደ ሰማይም ዐረገ:: እነርሱም ሰገዱለትና በብዙ ደስታ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ:: ዘወትርም እግዚአብሔርን እያመሰገኑና እየባረኩ በመቅደስ ኖሩ:: " † [ሉቃ.፳፬፥፶-፶፫] [24:50-53]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
2024/09/29 09:22:19
Back to Top
HTML Embed Code: