Telegram Web Link
Forwarded from ዝክረ ቅዱሳን zikre kidusan (ɴᴀᴛɴᴀᴇʟ)
Forwarded from ዝክረ ቅዱሳን zikre kidusan (ɴᴀᴛɴᴀᴇʟ)
††† እንኳን ለሐዋርያው ቅዱስ ሐናንያ እና ለሰማዕቱ ቅዱስ ቶማስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱስ ሐናንያ ሐዋርያ †††

††† ሐናንያ ቁጥሩ ከ72ቱ አርድእት ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስማቸው ተመዝግቦ ከተቀመጠልን ከጥቂቶቹ ዋነኛው ነው:: ከነገደ እሥራኤል ተወልዶ : በሕገ ኦሪት አድጐ : ከወጣትነት ዕድሜው ትንሽ እልፍ ሲል ጌታችን ወንጌልን ማስተማር ጀምሯልና ጠራው:: እርሱም በበጐ ፈቃድ ተከትሎታልና ከ72ቱ አርድእት ደመረው::

ለ3 ዓመታት ከጌታ እግር ተምሮ : ከዕለተ ስቅለት በፊት ሀብተ ፈውስም ተሰጥቶት ነበር:: ምክንያቱም ቅዱስ ሉቃስ እንደ ጻፈልን ሰብዐው አርድእት "ጌታ ሆይ! አጋንንት በስምህ ተገዙልን" ማለታቸውን አስቀምጦልናል:: (ሉቃ. 10:17) ቅዱስ ሐናንያ በበዓለ ዕርገት ተባርኮ በ50ኛው ቀንም መንፈስ ቅዱስን ተቀብሎ ለስብከተ ወንጌል ወጥቷል::

በሚያስተምር ጊዜ የሶርያዋን ደማስቆን ማዕከል አድርጐ ነበር:: በሁዋላም አበው ሐዋርያት የዚህች ከተማ የመጀመሪያው ዻዻስ አድርገው ሹመውታል:: ጌታ ባረገ በ8ኛው ዓመት ክርስቲያኖችን ያሰቃይ የነበረው ሳውል (የሁዋላው ቅዱስ ዻውሎስ) ወደ ደማስቆ የተጉዋዘው ክርስቲያኖችን በተለይም ቅዱስ ሐናንያን ለማሠር ነበር::

ለእግዚአብሔር ምርጥ ዕቃ ይሆን ዘንድ መብረቅ ዐይኑን አጠፋው:: ወዲያውም ጌታችን ሳውልን ወደ ሐናንያ እንዲሔድ ነገረው:: ከ3 ቀናት በሁዋላ ጌታችን ለሐናንያ ተገልጦ አነጋግሮታል::

ሳውል (ዻውሎስ) ወደ ሐናንያ የደረሰው በመሪ ነበር:: 2ቱ እንደተገናኙ ቅዱስ ሐናንያ ሳውልን አስተማረው : ፈወሰው : አጠመቀው : በጐ መንገድንም መራው:: በዚህ ምክንያት ቅዱሱ ሐዋርያ የቅዱስ ዻውሎስ የንስሃ አባቱ ይሰኛል:: (ሐዋ. 9:1-19)

ከዚህ በሁዋላ ቅዱስ ሐናንያ ለብዙ ዓመታት በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ወንጌልን አስተማረ:: መከራንም ተቀበለ:: በመጨረሻም በዚህ ቀን ክፉዎች ከብዙ ስቃይ በሁዋላ በድንጋይ ወግረው ገድለውታል::

††† ቅዱስ ቶማስ ዘሰንደላት †††

††† በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን ከነበሩ ሰማዕታት አንዱ የሆነው ቅዱስ ቶማስ ወደ ሰማዕትነት ሕይወት የገባው በ11 ዓመቱ በመላእክት መሪነት ነው:: ገና ወደ ምስክርነት አደባባይ እንደ ቀረበ መኮንኑ "ክርስቶስን ካድና ልሹምህ" ቢለው ሕጻኑ ቅዱስ ቶማስ ተቆጥቶ : "አንተ ሰነፍ መኮንን" ብሎ ገስጾ : በጐችን ይመልስባት በነበረችው ጅራፍ ገርፎታል:: ይሔም በዘመኑ የመጨረሻው የድፍረት ደረጃ ነበር::

††† በዚህም ምክንያት በሕጻን ገላው ላይ የተቀበለው መከራ ሊናገሩት ይከብዳል::
¤ግርፋት:
¤እሳት:
¤አራዊት በእርሱ ላይ አልፈዋል::

አካሉ ተቆራርጧል:: አንድ ጊዜም "ለጣዖታችሁ እንድሰግድ አምጡት" ብሏቸው ልክ ከፊቱ ሲደርሱ ወደ ጌታ ቢጸልይ መሬት ተከፍታ ውጣቸዋለች::

እሱን ያሰቃየው የነበረውን መኮንንም ከደዌው አድኖ ከነ ሠራዊቱ አሳምኖታል:: ሕጻኑን ቅዱስ ቶማስን ግን ያላመኑ አረማውያን በዚህች ቀን አንገቱን ሰይፈውት በሰማዕትነት ወደ ወደደው ክርስቶስ ሔዷል::

††† አምላከ ቅዱሳን ከሐዋርያው በረከት : ከሰማዕቱም ምልጃ አይለየን::

+"+ #ቅዱስ_ያዕቆብ_ዘሥሩግ +"+

=>#በቤተ_ክርስቲያን_ታሪክ በደራሲነታቸው: በወንጌል አገልግሎታቸውና በቅድስናቸው ከተመሠከረላቸው ዐበይት ሊቃውንት አንዱ ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ ነው::

+ሊቁ የተወለደው መጋቢት 27 ቀን በ433 ዓ/ም ሲሆን ሃገሩ ሶርያ ነው:: ወላጆቹ ክርስቲያኖች ለዚያውም አባቱ ሊቀ ካህናት ነበር:: ቅዱስ ያዕቆብ ገና በልጅነቱ ጀምሮ ጸጋ እግዚአብሔር የጠራው ነውና በብዙ ነገሩ የተለየ ነበር::

+አንድ ቀን በዕለተ ሰንበት ገና በ3 ዓመቱ እናቱ አቅፋ ወደ #ቤተ_መቅደስ ወሰደችው:: ምዕመናን #ቅዱስ_ሥጋውንና #ክቡር_ደሙን ሲቀበሉ ሕጻኑ ያዕቆብም ይቆርብ ዘንድ ቀረበ:: ሊቀ ዻዻሱ ደሙን በዕርፈ መስቀል ሊያቀብለው ሲል መልአኩ መጥቶ "በጽዋው ጋተው" አለው:: የጌታን ደም በጽዋ ቢጠጣ ምስጢር ተገለጸለትና "#አንሰ_እፈርሕ_ሠለስተ_ግብራተ-እኔስ 3 ነገሮች ያስፈሩኛል" ሲል አሰምቶ ተናገረ::

+ዻዻሱና ሕዝቡ ወደ ሕጻኑ ያዕቆብ ቀርበው "ምን ምን?" አሉት:: እርሱም:-
1.ነፍሴ ከሥጋየ ስትለይ
2.ቅድመ እግዚአብሔር ለፍርድ ስቀርብ
3.ከፈጣሪየ የፍርድ ቃል ሲወጣ" አላቸው::
ያን ጊዜ ሕዝቡና ሊቀ ዻዻሳቱ "#እግዚአብሔር_በዚሕ_ሕጻን_አድሮ_ዘለፈን" እያሉ ለንስሃ በቅተዋል::

+ቅዱስ ያዕቆብ 7 ዓመት ሲሞላው ይማር ብለው ወደ ጉባዔ አስገቡት:: በ5 ዓመታት ብሉይ ከሐዲስ ጠንቅቆ በ12 ዓመቱ ሊቅ ሆኗል:: በዚህ ወቅት የነበሩ ታላላቅ ሊቃነ ዻዻሳት ወደ እርሱ ተሰበብስበው "እንግዳ ድርሰት ድረስልን: አዲስ ምሥጢር ንገረን" አሉት:: እርሱ ግን ሲቻለው ስለ ትሕትና "አልችልም" አላቸው::

+"እንግዲያውስ #ትንቢተ_ሕዝቅኤልን ተርጉምልን" ቢሉት ባጭር ታጥቆ አመሥጥሮላቸው ተደስተዋል:: ፈጣሪንም አመስግነዋል::

+ቅዱስ ያዕቆብ ከዚህ በሁዋላ ወደ ገዳም ገብቶ ትሕርምተ አበውን: ዕጸበ ገዳምን: ሕይወተ ቅዱሳንን በተግባር ተምሯል:: በድንግልናው ጸንቶ: #ጾምና_ጸሎትን እያዘወተረ ኑሯል:: በፈቃደ እግዚአብሔር የሥሩግ (በኤፍራጥስና ጤግሮስ ወንዞች መካከል የምትገኝ የሶርያ ግዛት ናት) ኤዺስ ቆዾስ ሆኖ ተሹሟል::

+በዘመኑም:-
1.የ451ን የኬልቄዶን ጉባኤ አውግዟል

2.ብዙ መናፍቃንን ተከራክሮ ምላሽ አሳጥቷል

3.በወንጌል አገልግሎት መልካም እረኝነቱን አሳይቷል

4.ዛሬ የምንገለገልበትን መጽሐፈ ቅዳሴውን ጨምሮ በርካታ መንፈሳዊ ድርሰቶችን ደርሷል::

+በመጨረሻም ከብዙ የተጋድሎና የቅድስና ዓመታት በሁዋላ በተወለደ በ72 ዓመቱ በ505 ዓ/ም በዚሕች ቀን አርፏል:: አንዳንድ ምንጮች ደግሞ ሰኔ 27 ቀን እንዳረፈ ይናገራሉ:: #ቅዱስ_ያዕቆብ_ዘሥሩግ ለቤተ ክርስቲያን የቁርጥ ቀን ተወዳጅ ልጇ ነውና በእጅጉ ታከብረዋለች::

=>#አምላከ_ቅዱሳን ከታላቁ ሊቅ በረከት ይክፈለን::

††† ሰኔ 27 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ሐናንያ ሐዋርያ (ከ72ቱ አርድእት)
2.ቅዱስ ቶማስ ሰማዕት (ዘሰንደላት)
3.ቅዱስ አልዓዛር ነዳይ (በነዌ ደጅ የወደቀ : ቀጥሎ ደግሞ በአብርሃም እቅፍ ውስጥ የተገኘ ጻድቅ - ሉቃ. 16:19)
4.ቅዱስ ማማስ

††† ወርኀዊ በዓላት
1.የጌታችንና አምላካችን መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ በዓለ ስቅለት
2.አቡነ መብዐ ፅዮን ጻድቅ
3.ቅዱስ መቃርስ (የመነኮሳት ሁሉ አለቃ)
4.ቅዱስ ያዕቆብ ዘግሙድ
5.ቅዱስ ገላውዴዎስ ሰማዕት (ንጉሠ ኢትዮዽያ)
6.ቅዱስ ቢፋሞን ጻድቅና ሰማዕት
7.ማር ቅዱስ ፊቅጦር ሰማዕት

††† "በደማስቆም ሐናንያ የሚሉት አንድ ደቀ መዝሙር ነበረ:: ጌታም በራዕይ:- "ሐናንያ ሆይ!" አለው:: እርሱም "ጌታ ሆይ! እነሆኝ" አለ:: ጌታም:- ተነስተህ ቅን ወደ ሚባለው መንገድ ሒድ:: በይሁዳ ቤትም ሳውል የሚሉትን አንድ የጠርሴስ ሰው ፈልግ:: እነሆ እርሱ ይጸልያልና:: ሐናንያ የሚሉትም ሰው ገብቶ ደግሞ እንዲያይ እጁን ሲጭንበት አይቷል" አለው::" †††
(ሐዋ. 9:10-18)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
Forwarded from ዝክረ ቅዱሳን zikre kidusan (ɴᴀᴛɴᴀᴇʟ)
Forwarded from ዝክረ ቅዱሳን zikre kidusan (ɴᴀᴛɴᴀᴇʟ)
"" በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ::
አሜን:: ""
+*" ቅዱስ ያዕቆብ ዘእልበረዲ (እል-በረዳይ) "*+
(St. Jacob baradaeus)
(በተለይ በሃገራችን የተዘነጋ የሚመስለው የምሥራቅ ኮከብ -
ኮከበ ጽባሕ)
=>"ያዕቆብ" ለሚል ስም ትርጉምን የሰጡ አበው በ2 መንገድ
ያትቱታል::
1.አኃዜ ሰኮና:: ነገሩ ከወልደ ይስሐቅ ወርብቃው ርዕሰ አበው
ያዕቆብ ጋር የተያያዘ ቢሆንም አበው ግን ለትህትና
ይተረጉሙታል::
2.አእቃጺ / አሰናካይ:: ነገሩ ስድብ (አሉታዊ) ይምሰል እንጂ
በዚህ ስም የተጠሩ አበው ሁሉ ለአጋንንትና ለመናፍቃን ትልቅ
መሰናክል ሆነውባቸው ኑረዋልና አባባሉ ምስጋና እንጂ ነቀፋን
አይወክልም::
+የ6ኛው መቶ ክ/ዘመን ምሥራቃዊ ኮከብ ቅዱስ ያዕቆብም
ለመለካዊ መናፍቃንና ለተዋሕዶ ተገዳዳሪዎች ትልቅ መሰናክል
ሆኖባቸዋል:: የቀናችውን ቀርነ ሃይማኖትንም አጽንቷል::
+ብዙ ጊዜ "ዘ"-እልበረዲ መባሉን ይዘው በ"ዘ" ምክንያት
እልበረዲን እንደ ሃገር የቆጠሯት አልጠፉም:: በረከታቸው
ይድረሰንና ትጉሑ ዻዻስ አቡነ ጐርጐርዮስ ካልዕ ግን ለዚሁ
መላምት "የለም!" ባይ ናቸው::
+'የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ' በተሰኝ ተወዳጅ
መጽሐፋቸው "እል-በረዲ" ማለትን በዓረብኛ ከሠጋር በቅሎ :
ከሥሙር ሠረገላ ጋር አነጻጽረው አስቀምጠውታል:: ለምን ቢባል
- እንደ ሠረገላ በተፋጠነ አገልግሎቱ ወዳጅንም ጠላትንም
አስደምሟልና::
+ቅዱስ ያዕቆብ የተወለደው በ6ኛው መቶ ክ/ዘመን መጀመሪያ
(በ500 አካባቢ) ሲሆን ያረፈው ደግሞ በ578 ዓ/ም እንደሆነ
ይታመናል:: ነገሩን ልብ ስንለው ቅዱስ ማኅሌታይ ያሬድን -
ወዲህ በዘመን : ወዲያ ደግሞ በአገልግሎት ይመስለዋል::
እርግጥ ነው ለውለታው የሶርያ ቤተ ክርስቲያን "ያዕቆባዊት"
ስትባል የእኛዋስ ምናለ "ያሬዳዊት" ብትባል የሚል ቁጭትን
ያመጣል::
+ጊዜው (5ኛውና 6ኛው መቶ ክ/ዘመን) ወዲህ ወርቃማ :
ወዲያ ደግሞ ጨለማ ተብሎ ሊጠራ የሚችል ዘመን ነበር::
¤በብርሃንነቱ በተለይ በምሥራቁ ዓለም ያበሩ አበው እነ ያዕቆብ
ዘስሩግ : ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ : ያዕቆብ ዘእልበረዲን የመሰሉ
አበው ተገኝተውበታል:: ሲያልፍ ደግሞ ዘይኑንና አንስጣስዮስን
የመሰሉ ደጋግ ነገሥታት በዘመኑ መነሳታቸውን እናስባለን::
+በተቃራኒው ግን ዘመኑ ቤተ ክርስቲያን ለ2 የተከፈለችበት :
መለካውያን የነገሥታቱ ደጀን አላቸውና ተዋሕዶ ሃይማኖትን
ከሥሯ ነቅሎ ለማጥፋት ብዙ የሞከሩበት ዘመን ነውና ጨለማነቱ
ይጐላብናል::
+በእርግጥም ከመርቅያን እስከ ዮስጢኖስ ዳግማዊ ዘመን
ድረስ ለ100 ዓመታት መለካውያኑ የልዮን ልጆች 2 ባሕርይ
ማለትን ሊያሰፉ : ተዋሕዶንም ሊያጠፉ የከፈቱት ዘመቻ ሊሳካ
ጫፍ የደረሰ ይመስል ነበር::
+ግን አማናዊት ቤቱን የማይተው አማናዊው ጌታ መድኃኔ
ዓለም አርመኖቹን ስቦ በ490ዎቹ ወደ መንጋው ቀላቀለ::
በግብጽ አባ ቴዎዶስዮስን : በሶርያ ደግሞ ታላቁን ሊቅ ቅዱስ
ሳዊሮስን አስነስቷል:: ከቤተ መንግስትም ስም አጠራሯ ያማረ
ንግሥት ታኦድራን ማርኯል:: በእነዚህ ቅዱሳን ትጋት
የለመለመችው ተዋሕዶ እንደ ቅዱስ ያዕቆብ ዘእልበረዲ ያለ
አርበኛን ግን ያገኘችው በጭንቅ ቀን ነበር::
+ሰው መሆን ሰው በጠፋባቸው ቀናት ነውና : በግብጽና
በቁስጥንጥንያ በትምህርትና ምናኔ ላይ የነበረው ቅዱሱ ታጥቆ
ለአገልግሎት የተሰለፈው በ530ዎቹ አካባቢ ነበር::
+ጊዜው ወዲህ አንበሳው ቅዱስ ሳዊሮስ ከሶርያ ወደ ግብጽ
እንደተሰደደ ያረፈበት ነበር::
ወዲያ ደግሞ ሊቁ አባ ቴዎዶስዮስ የግብጹ ለግዞት የተዳረገበት
ነበርና የተዋሕዶ ምዕመናን ያለ እረኛ ተቅበዘበዙ:: የቤተ
መንግስቱ ተጽዕኖ ደግሞ 2 ባሕርይ በማይሉት ላይ እሥራትና
ግድያን ወደ ማወጅ ተሸጋግሯልና የምእመናን ቁጥር እጅጉን
መመንመኑ ቀጠለ::
+ይህ ዕረፍት የነሳው ቅዱስ ያዕቆብ በበኩሉ ነገሩን በዝምታ
ሊያልፈው አልወደደምና አገልግሎቱን አሰፋ:: ሌሊቱን በጸሎት
ያድራል:: ቀን በቤተ ክርስቲያን አካባቢ ማስተማር ባይችል
በየቦታው እየዞረ ያስተምር ነበር::
+ከትምህርቱ ጣዕምና ከመልእክቱ ሥምረት የተነሳም ምእመናን
እንደገና ተነቃቁ:: እርሱም ከግብጽ እስከ ሶርያ : አልፎም እስከ
ቁስጥንጥንያ ድረስ ያለ ዕረፍት ሲሰብክ 40 ዘመናትን አሳለፈ::
በተለይ አዲስ አማኞችን ያጠምቅ ዘንድ በእሥረኛው ቅዱስ
ቴዎዳስዮስ ኤዺስ ቆዾስነትን ተቀብሏል::
+የሶርያ (አንጾኪያ) የፕትርክና መንበሩ ክፍት ሆኖ እርሱን
ቢጠብቀውም እርሱ ግን የዚህ (የስልጣን) ፈላጊ አልነበረምና
ሌሎች እንዲሾሙበት አድርጉዋል::
+ቅዱስ ያዕቆብ በስብከት አገልግሎት ምሥራቁን ዓለም ሲያበራ
የተባበሩት ደቀ መዛሙርት ቢኖሩም ያሳለፈው ድካምና መከራ
ግን ተወዳዳሪ አልነበረውም:: በተለይ የወቅቱ የአንጾኪያ ኃያላን
መኩዋንንትና ሹመኛ መናፍቃን ብዙ አሳደውታል::
+እርሱ ግን በጥበብና በፈሊጥ እዚያው ደጃቸው ላይ የነበሩ
ምዕመናንን በእረኝነት ጠብቁአል:: ለዚህ ሲባልም ራሱን
እየቀያየረ የመሣፍንቱን አጥሮችና ቅጥሮች አልፏል:: ለቤተ
ክርስቲያን ክብርም እንደ እብድ : እንደ ሴትም መስሎ የወንጌልን
ዘር ዘርቷል::

¤ከብዙ ፈተናና አገልግሎት በሁዋላም በተወለደ በ78 ዓመቱ
(በ578 ዓ/ም) ዐርፎ በክብር ተቀብሯል::

¤ትልቁ መታሰቢያው የሶርያ ቤተ ክርስቲያን "ያዕቆባዊት" :
ምዕመኑ "ያዕቆባውያን" መባላቸው ሲሆን እኛ ደግሞ
በአንገታችን ላይ እንድናስራት ባስተማረን ማዕተብ (ማኅተም)
ዘወትር እናስበዋለን:: ለመጀመሪያ ጊዜ ማዕተብን በአንገት ላይ
ስለ ማሰር ያስተማረ እርሱ ነውና::

¤የምሥራቁን ኮከብ እል-በረዲ ያዕቆብን በየዓመቱ ሰኔ 28 ቀን
በነገረ ቅዱሳን መደበኛ ጉባኤ (ጐንደር) እናከብራለን::
ሶርያውያን ደግሞ July 31 (ሐምሌ 24 ቀን) ያከብሩታል::

=>+"+ እናንተ የምድር ጨው ናችሁ . . . እናንተ የዓለም
ብርሃን ናችሁ:: በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሠወር
አይቻላትም:: መብራትንም አብርተው በዕንቅብ በታች አይደለም
እንጂ በመቅረዙ ላይ ያናሩታል:: በቤት ላሉት ሁሉም ያበራል::
መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን
እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ:: +"+
(ማቴ. 5:13-16)
Forwarded from ዝክረ ቅዱሳን zikre kidusan (ɴᴀᴛɴᴀᴇʟ)
Forwarded from ዝክረ ቅዱሳን zikre kidusan (ɴᴀᴛɴᴀᴇʟ)
=>+"+ እንኩዋን ለቅዱሳን ነገሥታት "#ማርቆስ እና #ቴዎድሮስ" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ +"+

=>ማንኛውም ሰው
¤ቢጾም ቢጸልይ
¤መልካም ቢሠራ
¤ለእግዚአብሔር ቢገዛ
¤አልፎም ቢመንን ይደነቃል:: ይሕንን ሥራ ንጉሥ ሆነው ስለ ሠሩትስ ምን እንላለን? ማድነቅ የሚለው ቃል የሚገልጸው አይመስለኝም::

¤ወርቅና ብር በእግር እየተረገጠ
¤የሚበላውና የሚጠጣው ተትረፍርፎ ሳለ
¤አገር ምድሩ እየሰገደላቸው
¤ሁሉ በእጃቸው
¤ሁሉም በደጃቸው ሳለ...
ይህንን ሁሉ ስለ #ክርስቶስ ፍቅር የተውትን ጻድቃን ነገሥታት የክብር ክብር ይገባቸዋል:: ከእነዚህ መካከል ዛሬ የሚከበሩትን 2ቱን እናዘክር::

+*" ቅዱስ ማርቆስ ንጉሠ ሮም "*+

=>ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ይህንን ቅዱስ ጻድቅ: የዋህ: ንጹሕና ገዳማዊ ብላ ትጠራዋለች:: ሮም እንደ ዛሬ ጠባብ ከተማ ሳትሆን ዓለምን በክንዷ ሥር ቀጥቅጣ የምትገዛ ኃያል ሃገር ነበረች:: ቅዱስ ማርቆስ የልዑላኑ ቤተሰብ ነውና በሮም ተወልዶ በእመቤታችን ቤተ መቅደስ ውስጥ አድጉዋል::

+የየዕለት ሙያው ጾምና ጸሎት: መጻሕፍትንም መመልከት ነበር:: ነባሩ ንጉሥ ሲሞት መሣፍንቱ ቅዱስ ማርቆስን በድንግልናው ገና ወጣት ሳለ በዚያች ታላቅ ሃገር ላይ አነገሡት:: ንጉሥ ቢሆንም ሙሉውን ሌሊት በእመቤታችን ፊት ሲጸልይና ሲያለቅስ ያነጋ ነበር::

+ስለ ፍቅርም ድንግል ማርያም ተገልጻ "ምን ላደርግልህ ትወዳለህ?" አለችው:: ቅዱስ ማርቆስም "ለሕዝቡ ፍቅር አንድነትን ሰላምን ስጪልኝ:: እኔ በማስተዳድርበት ቦታ ሁሉ ጠብ ክርክር ይጥፋልኝ:: ፍቅር ይንገስልኝ" ሲል መለሰላት:: ድንግል እመቤታችንም "እንደ ቃልህ ይሁን" ብላ አጋንንት ወደ ሃገሩ እንዳይገቡ ከለከለችለት:: በዚህም ቅዱስ ማርቆስ ከነገሠ ጀምሮ ለ5 ዓመታት ጠብ ክርክር: ክፋትና ችግር አልነበረም:: ሁሉም ተፋቅሮን ያጸና ነበር እንጂ::

+ከ5 ዓመታት በሁዋላ ግን ሕዝቡና ሹማምንቱ ተሠብስበው አንድ ነገርን መከሩ:: #ቅዱስ_ማርቆስን አጋብተው ለብዙ ጊዜ እንዲመራቸው ማለት ነው:: ምክንያቱም አኗኗሩ እንደ መነኮሳት ነውና ጠፍቶ እንዳይሔድ በመስጋታቸው ነው:: ከዚያም የሕዝቡ አለቆች ተመርጠው ሃሳባቸውን አቀረቡለት:: እርሱ ግን ጭንቅ ሆነበት:: ጭራሹኑ እንዲህ ዓይነት ሃሳብ መጥቶበት አያውቅም::

+"እስኪ በጸሎት ላስብበት" ብሎ መለሳቸው:: እነርሱ ግን ወደውታልና ድጋሚ ተሰብስበው ሌላ ነገርን መከሩ:: እርሱ ሳያውቅ መልካም ሴት መርጠው: ሥርዓተ ተክሊል አዘጋጅተው: ድግሱንም አዘጋጅተው በግድም ቢሆን ሊያጋቡት ቆረጡ:: ቅዱስ ማርቆስ የተደረገውን ሁሉ ፈጣሪ ገልጦለት በጣም ደነገጠ::

+ፈጥኖ ወደ #እመ_ብርሃን ስዕል ቀርቦ አለቀሰ:: "#እመቤቴ! እኔ ካንቺ ጋር እንጂ ከዚህ ዓለም ጋር መኖር አልችልም" አላት:: እመ ብርሃን ከሰማይ ወደ እርሱ ወርዳ "የምነግርህን ስማኝ:: በሌሊት ተነስተህ ወደ ማሳይህ በርሃ ሒድ" ብላው ተሠወረች:: ቅዱስ ማርቆስ ደስ እያለው የንግሥና ልብሱን ጥሎ: ቆሻሻ ጨርቅ ለብሶ በሌሊት ከቤተ መንግስቱ ወጣ::

+ወደ ሁዋላ አልተመለከተም:: እመቤታችን እየመራችው #ደብረ_ቶርማቅ የሚባል በርሃ ውስጥ ባሕር ተከፍሎለት ገባ:: ሕዝቡ መልካም እረኛ መሪን አጥቷልና በሮም ከተማ ታላቅ ለቅሶና ሐዘን ተደረገ:: ቅዱስ ማርቆስ ግን በደብረ ቶርማቅ በጾም: በጸሎትና በተጋድሎ ማንንም ሳያይ ለ60 ዓመታት ኖረ::

+በዚህች ቀንም ዐርፎ ወደ ወደደው ክርስቶስ ሒዷል:: ሥጋውን የሚቀብር አልነበረምና ከሰማይ 12ቱ ሊቃነ መላእክትና 12ቱ ሐዋርያት ወረዱ:: በዝማሬ ሲገንዙትም በድኑ ከመሬት 5 ክንድ ከፍ ብሎ ተንሳፈፈ::
መላእክቱና ሐዋርያቱም በማሕሌት እዚያው ደብረ ቶርማቅ ውስጥ ቀብረውታል::

+"+ #ቅዱስ_ቴዎድሮስ ንጉሠ ኢትዮዽያ +"+

=>በሃገራችን ታሪክ በጣም ተወዳጅ ከነበሩ ነገሥታት #ጻድቁ_ቴዎድሮስ ቅድሚያውን ይወስዳል:: በርግጥ በርካቶቻችን የምናውቀው ስለ ሃገሩ ፍቅር ራሱን የሰዋውን ዳግማዊ ዐፄ ቴዎድሮስን (1845-1860) ነው:: በበጎ ሥራውና በቅድስና ሕይወቱ የተመሠከረለት ግን ዛሬ የምናስበው ቀዳማዊው ነው::

+ቀዳማዊ ዐፄ ቴዎድሮስ የደጉ #ዐፄ_ዳዊት (#ግማደ_መስቀሉን ያመጡት) እና የተባረከችው ሚስታቸው #ፅዮን_ሞገሳ ልጅና የጻድቁ ዐፄ #ዘርዐ_ያዕቆብ ታላቅ ወንድም ነው::

+በኢትዮዽያ ለ3 ዓመታት (ከ1396-1399) ብቻ ነግሦ እያለ እንደ ንጉሥ ሳይሆን
¤ከጠዋት እስከ ማታ ድሃ እንዳይበደል: ፍርድ እንዳይጉዋደል ይታትር የነበር:
¤ጾምና ጸሎትን የሚያዘወትር:
¤ወገቡን ታጥቆ ነዳያንን የሚያበላ:
¤ለአብያተ ክርስቲያናትም የሚጨነቅ ደግ ሰው ነበር::

+ስለዚህም በሕዝቡ እጅግ ተወዳጅ ነበር:: በነገሠ በ3 ዓመቱ ዐርፎ በዝማሬና በለቅሦ ሥጋውን ተሸክመው ሲሔዱ ወንዝ ተከፍሎላቸዋል:: ከመቃብሩም ላይ ጸበል ፈልቁዋል::

=>ቸር አምላክ መልካም መሪ ለሃገራችን: በጐ እረኛንም ለነፍሳችን ያድለን:: ከቅዱሳን ነገሥታቱም ጸጋ በረከትን ይክፈለን::

=>ሰኔ 29 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ማርቆስ ንጉሠ ሮም (ጻድቅ: ንጹሕና ገዳማዊ)
2.ቅዱስ ቴዎድሮስ ጻድቅ (ንጉሠ ኢትዮዽያ)
3.ቅዱስ ዓምደ ሚካኤል ኢትዮዽያዊ (ፍልሠቱ)
4."7ቱ" ቅዱሳን መስተጋድላን (አባ አብሲዳ: አባ ኮቶሎስ: አባ አርድማ: አባ ኒኮላስ: አባ ሙሴ: አባ እሴይ: አባ ብሶይ)
5.ቅዱሳን አባ ሖር: አባ ብሶይ: አባ ሖርሳና እናታቸው ቅድስት ይድራ (ሰማዕታት)

=>ወርኀዊ በዓላት
1.የፈጣሪያችንና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት
2.ቅድስት አርሴማ ድንግል
3.ቅዱስ ዼጥሮስ ተፍጻሜተ ሰማዕት
4.ቅዱስ ማርቆስ ዘቶርማቅ
5.ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ ኢትዮዽያዊት
6.ቅዱስ ዘርዐ ክርስቶስ (ጻድቅና ሰማዕት)

=>+"+ አቤቱ በኃይልህ ንጉሥ ደስ ይለዋል::
በማዳንህ እጅግ ሐሴትን ያደርጋል::
የልቡን ፈቃድ ሰጠኸው::
የከንፈሩንም ልመና አልከለከልኸውም::
በበጐ በረከት ደርሰህለታልና::
ከከበረ ዕንቁ የሆነ ዘውድን በራሱ ላይ አኖርህ::
ሕይወትን ለመነህ ሰጠኸውም::
ለረጅም ዘመን ለዘለዓለሙ::
በማዳንህ ክብሩ ታላቅ ነው:: +"+ (መዝ. 20:1-5)

<ወስብሐት ለእግዚአብሔር>
Forwarded from ዝክረ ቅዱሳን zikre kidusan (ɴᴀᴛɴᴀᴇʟ)
Forwarded from ዝክረ ቅዱሳን zikre kidusan (ɴᴀᴛɴᴀᴇʟ)
††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† እንኳን ለመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ዓመታዊ የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ †††

††† ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ †††

=>ቅዱስ ወንጌል ላይ ከእመቤታችን ቀጥሎ የነዘካርያስን ቤተሰብ ያህል ክብሩ የተገለጠለት ፍጡር ይኖራል ብሎ መናገሩ ይከብዳል:: ቅዱስ ሉቃስ ወንጌሉን የጀመረው በዚህ ቅዱስ ቤተሰብ ነውና መንፈስ ቅዱስ እንዲህ ሲል አጽፎታል:: "ዘካርያስ ካህኑና ቅድስት ኤልሳቤጥ በሰውና በእግዚአብሔር ፊት ያለ ነቀፋ የሚኖሩ ጻድቃን ነበሩ" ይላቸዋል:: (ሉቃ. 1:6)

+የሰውን እንተወውና በእግዚአብሔር ፊት ያለ ነቀፋ መኖር ምን ይረቅ? ለዚህ አንክሮ (አድናቆት) ይገባል!
እሊህ ቅዱሳን ባልና ሚስት ግን መካኖች በመሆናቸው ልጅ ሳይወልዱ ዘመናቸው አልፎ ነበር:: እንደ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት ዕድሜአቸው የኤልሳቤጥ 90 የዘካርያስ 100 ደግሞ ደርሶ ነበር:: ፍጹም መታገሳቸውን የተመለከተ ጌታ ግን በስተ እርጅናቸው ከሰው ሁሉ በላይ የሆነ: ትንቢት ለብቻው የተነገረለት (ኢሳ. 40:3, ሚል. 3:1) ታላቅ ነቢይን ይሰጣቸው ዘንድ መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤልን ላከላቸው::

+ቅዱስ ዘካርያስ ሰው ነውና ከደስታ ብዛት በመከራከሩ ድዳ ሆነ:: ቅድስቲቷ ግን መስከረም 26 ቀን ታላቁን ሰው ጸንሳ ለ6 ወራት ራሷን ሠወረች:: በ6ኛው ወር የፍጥረት ሁሉ ጌታ በተጸነሰ ጊዜ የአርያም ንግሥት ድንግል እመቤታችን ደጋ ደጋውን ወደ ኤልሳቤጥ መጣች:: ሁለቱ ቅዱሳት የእህትማማች ልጆች ናቸው::

+የአምላክ እናቱ ስትደርስና "ሰላም" ስትላቸው መንፈስ ቅዱስ በእናትና ልጅ ወርዶ ኤልሳቤጥ በምስጋና: ዮሐንስ ደግሞ ገና በማሕጸን ሳለ በደስታ ዘለለ (ሰገደ):: ከዚህ በሁዋላ በዚህች ቀን (ሰኔ 30) ተወልዶ: አባቱ ዘካርያስ "ዮሐንስ" ሲለው አንደበቱ ተፈትቶለታል::

=>መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ
+የቅዱሳኑ ዘካርያስና ኤልሳቤጥ ልጅ
+በማሕጸን ሳለ መንፈስ ቅዱስ የሞላበት
+በበርኀ ያደገና በገዳማዊ ቅድስና ያጌጠ
+እሥራኤልን ለንስሃ ያጠመቀ
+የጌታችንን መንገድ የጠረገ
+ጌታውን ያጠመቀና
+ስለ እውነት አንገቱን የተቆረጠ ታላቅ ሰው ነው::

+ስለዚሕም ቤተ ክርስቲያን ነቢይ: ሐዋርያ: ሰማዕት: ጻድቅ: ገዳማዊ: መጥምቀ መለኮት: ጸያሔ ፍኖት: ቃለ ዐዋዲ ብላ ታከብረዋለች::

+" አባ ጌራን ሕንዳዊ "+

=>ዳግመኛ በዚህች ቀን ሕንድ ካፈራቻቸው ታላላቅ ቅዱሳን አንዱ የሆኑት ጻድቁ አባ ጌራን ይታሰባሉ:: የእኒህ ቅዱስ ታሪክ አሳዛኝ ነው:: ቅዱሱ በሕንድ ተወልደው: በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን አድገው: ገና በወጣትነታቸው መንነው: ደሴት ውስጥ ወደሚገኝ አንድ በርሃ ገብተዋል:: ከገድላቸው ጽናት: ከቅድስናቸውም ብዛት የተነሳ በሃገረ ሕንድ ሰይጣን እንዳይገባ: ጠብ ክርክር እንዲጠፋ: ሰው ሁሉ በፍቅርና በሰላም እንዲኖር ማድረግ ችለው በጣም ተወዳጅ ነበሩ::

+በዚህ የተበሳጨ ሰይጣን ግን ባልጠረጠሩት መንገድ መጣባቸው:: አንዲት ሴት ወደ እርሳቸው መጥታ (የንጉሡ ልጅ ነኝ በሚል) አስጠግተዋት ነበር:: አንድ ሌሊት ላይ ግን አውሬ ያባረራት በመምሰል ሩጣ ወደ ቤታቸው ገብታ አቀፈቻቸው:: በዚያ ቅጽበት ፍጡር ደካማ ነውና ታላቁ አባ ጌራን ተሰነካከሉ:: ከአፍታ በሁዋላ የሆነውን ሲያውቁ ደም አለቀሱ::

+ልብሳቸውን ቀደው: እንባቸው እንደ ዥረት እየፈሰሰ አለቀሱ:: ራሳቸውን በትልቅ ድንጋይ እየቀጠቀጡት የጭንቅላታቸውና የደረታቸው አጥንቶች ተሰባበሩ:: እርሱ እግዚአብሔር መሐሪ ነውና ይቅር ብሎ: የቅድስና ስም ሰጥቶ በዚሕች ቀን ወደ ገነት አሳርጉዋቸዋል:: ለዚህ ነው መጽሐፉ "ጻድቅ 7 ጊዜ ይወድቃልና: ይነሣማል" ያለው:: (ምሳ. 24:16)

=>አምላካችን ከቅዱሱ ቤተሰብና ከጻድቁ አባ ጌራን በረከት ይክፈለን::

=>ሰኔ 30 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት (ልደቱ)
2.ቅዱሳን ዘካርያስና ኤልሳቤጥ (ወላጆቹ)
3.አባ ጌራን መስተጋድል (ሕንዳዊ)
4.ቅዱሳት ደናግል ማርያና ማርታ (ከ36ቱ ቅዱሳት አንስት-የአልዓዛር እህቶች)

=>ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ማርቆስ ዘአንበሳ (ሐዋርያ)
2.አባ ሣሉሲ ክቡር
3.ቅዱስ ጐርጐርዮስ ነባቤ መለኮት
4.ቅድስት ሶፍያ ሰማዕት

=>+"+ ደግሞም አንተ ሕጻን ሆይ የልዑል ነቢይ ትባላለህ:: መንገዱን ልትጠርግ በጌታ ፊት ትሔዳለህና:: እንደዚህም የኃጢአታቸው ስርየት የሆነውን የመዳን እውቀት ለሕዝቡ ትሰጣለህ:: ይሕም ከላይ የመጣ ብርሃን በጐበኘበት በአምላካችን ምሕረትና ርኅራኄ ምክንያት ነው:: +"+ (ሉቃ. 1:76)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
Forwarded from ዝክረ ቅዱሳን zikre kidusan (ɴᴀᴛɴᴀᴇʟ)
Forwarded from ዝክረ ቅዱሳን zikre kidusan (ɴᴀᴛɴᴀᴇʟ)
††† እንኳን ለተባረከ ወር ሐምሌ እና ለቅዱሳኑ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

††† እግዚአብሔርን ቸር የምንለው በባሕርዩ ፍጹም ቸር በመሆኑ ነው:: ይሕንን ደግሞ ለማረጋገጥ መቅመስ ይቻላል:: ይገባልም:: (መዝ. 33:7) ይሔው ደግሞ ያን ሁሉ ኃጢአታችንን ታግሶ ከወርኀ ሐምሌ አደረሰን:: ለዚሕ ቸርነቱ አምልኮ : ውዳሴና ስግደት ይገባዋል::
ለወርኀ ነሐሴ ደግሞ እንዲያደርሰን ልንማጸነው ይገባል::

††† ቅዱስ አግናጥዮስ ሐዋርያዊ ሊቅ †††

††† ሐዋርያዊ ጳጳስና ሰማዕት ቅዱስ አግናጥዮስ ገና በልጅነቱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ያየ : ራሱ ጌታችን ትንቢት የተናገረለት (ማቴ.18:1) እና ከጌታ ዕርገት በኋላ ሐዋርያትን የተከተለ አባት ነው:: ጌታ ሲያርግ የአምስት ዓመት ሕፃን ሲሆን ከሰላሳ ስድስት ዓመታት በላይ ሐዋርያትንና ቤተ ክርስቲያንን አገልግሏል::

ዕድሜው ወደ አርባዎቹ ሲደርስ (ኢየሩሳሌም በጠፋችበት ዓመት - በ70 ዓ/ም) እርሱ የአንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳት ሆኖ ተሹሟል:: አስቀድሞ ከወንጌላዊ ቅዱስ ዮሐንስ እግር ምሥጢርና ፍቅርን ጠጥቷልና የተለየ ሰው ነበር:: ቅዱስ አግናጥዮስ ከአንጾኪያ እየተነሳ ምድረ እስያንም በወንጌል ዕርፈ መስቀል አርሷል::

በአካል ያልደረሰባቸውን በጦማር (በክታብ) አስተምሯል:: በአካሉ እንኳ ምንም በጾም በጸሎትና በብዙ ድካም የተቀጠቀጠ ቢሆን ግርማው የሚያስፈራ ነበር:: ከነገር ሁሉ በኋላ የወቅቱ ቄሣር ጠራብሎስ ይዞ አሰቃይቶ ለአንበሳ አስበልቶታል:: በዚህ ምክንያት "ምጥው ለአንበሳ-ለአንበሳ የተሰጠ" እየተባለ ይጠራል::

††† አባ ብዮክ እና አባ ብንያሚን †††

††† እነዚህ ቅዱሳን የሥጋ ወንድማማቾች ናቸው:: ካህን አባታቸው በሚገባ ቢያሳድጋቸው እነሱም ገና በወጣትነት የሚደነቅ የክህነት አገልግሎትን ሰጥተዋል:: ሙሉ ሌሊት ለጸሎት : ሲነጋ ለኪዳን : በሠርክ ደግሞ ለቅዳሴ ይፋጠኑ ነበር:: ሁሌም በየቤቱ እየዞሩ የደከመውን ሲያበረቱ : የታመመውን ሲፈውሱ : ያዘነውን ሲያጽናኑ ውለው ትንሽ ቂጣ ለራት ይመገባሉ::

ሰውነታቸው በፍቅር ሽቱ የታሸ ነበርና ብዙዎችን መለወጥ ቻሉ:: አንዴ ቅዳሴ ሊገቡ ሲሉ "አባታችሁ ሊሞት ነው" ቢሏቸው "ሰማያዊው አባት ይቀድማል" ብለው ቀድሰዋል:: አባታቸውንም ቀብረውታል:: በመጨረሻ ግን አንድ ቀን ለመስዋዕት ብለው ያዘጋጁትን የበረከት ሕብስት እባብ በልቶባቸው አገኙ:: እንደ ምንም ፈልገው እባቡን ገደሉት::

ነገር ግን ያ የተባረከ ሕብስት በሆዱ ውስጥ ነበርና ምን ያድርጉት? ጌታን ስለ ማክበር ሊበሉት ፈልገው ጌታን ቢጠይቁት መልአኩ መጥቶ "ሰማዕትነት ሆኖ ይቆጠርላቹሃል" አላቸው:: ሁለቱ ወንድማማቾች ብዮክና ብንያሚን ፈጣሪያቸውን አመስግነው በሉት:: ምዕመናን ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲገቡ ሁለቱንም እንደተቃቀፉ ዐርፈው አገኟቸው:: መልካም እረኞቻቸው ናቸውና ከታላቅ ለቅሶ ጋር ቀብረዋቸዋል::

††† ቅድስት ቅፍሮንያ ሰማዕት ወጻድቅት †††

††† ይህቺ ቅድስት እናታችን ደግሞ ገና በአሥራ ሁለት ዓመቷ ታላቅ እህቷን ተከትላ ገዳም ትገባለች:: በሚገርም ተጋድሎ በጥቂት ጊዜ አጋንንትን አሳፍራ መነኮሳይያትንም አስገርማቸዋለች:: ትጋቷ ግሩም ነበርና ስትታዘዝ : ስትጸልይና ስትሰግድ ያለ እንቅልፍና ምግብ ቀናት ያልፉ ነበር:: በዚህ የተቆጣ ሰይጣን አረማዊ መኮንንን ይዞባት መጣ::

ሌሎች ደናግል ሲያመልጡ እርሷ ለመከራ ተዘጋጅታ ጠበቀችው:: አዕምሮ የጎደለው መኮንኑም ክርስቶስን ካልካድሽ ብሎ ጽኑዕ ጽኑዕ መከራን አመጣባት:: በተጋድሎ ባለቀ አካሏ ሁሉንም ቻለች:: በዚህች ቀን ግን አንገቷን በሰይፍ አስቆርጧታል::

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የወዳጆቹን ትዕግስትና ጽናት ለእኛም ያድለን:: ከበረከታቸውም ይክፈለን::

††† ቅዱስ ቶማስ †††

ዳግመኛ በዚህ ቀን ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ ይታሰባል::
ይኸውም ከሕንድ አውራጃዎች በአንዱ ወንጌልን ሰብኮ እኩሎቹ ሲያምኑ እኩሎቹ እንቢ አሉ:: ቅዱስ ቶማስም ያመኑትን "ከጣዖት አምልኮና ከዝሙት ሽሹ" ብሎ መከራቸው::

ምክሩን ከሰሙት አንዱ በዚያው ምሽት ሊጠጣ ወደ መሸታ ቤት ይገባል:: ሰው ሁሉ ከወጣ በኋላ ባለ መሸተኛዋ ሴት እንደለመደችው አብረው እንዲተኙ ስትጠይቀው "እንዴት ሐዋርያው ከዝሙት ሽሹ እያለ እንዲህ ትይኛለሽ?" በሚል ሰይፍ አውጥቶ አንገቷን ቆረጣት::

እርሱ መልካም ያደረገ መስሎታል:: የሠራው ሥራ (መግደሉ) ግን አሕዛባዊ ግብር ነው:: በማግስቱ ቅዱስ ቶማስ ነገሩን ሰምቶ ሰዎችን ሰበሰበና "ይህንን የአውሬ ድርጊት የፈጸመ ማነው?" ሲል ጠየቀ:: ፈጻሚው ግን አልታወቅም በሚል ዝም አለ:: ወዲያው ቅዱሱ ሐዋርያ ዳቦ አንስቶ ቆረሰና "ለበረከት እያነሳችሁ ውሰዱ" አለ:: ሰውየው ተራውን ጠብቆ ሊያነሳ ሲል እጁ ሰለለች::

ሐዋርያው "ምነው ልጄ! ምን ሆንክ?" አለው:: እሱም እንዳላመለጠ ሲያውቅ እውነቱን ተናዘዘ:: ቅዱስ ቶማስ ግን ሕዝቡ ሁሉ እንደተሰበሰበ ያን ወጣት ገስጾ "አስከሬኑን አምጡልኝ" አለ::

የወጣቱን እጅ ፈውሶ "በል የገደልኩሽ እኔ:: የሚያስነሳሽ ግን ጌታየ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው:: ብለህ አንገቷን ቀጥለው" አለው:: እንዳለው ቢያደርግ የሞተችው አፈፍ ብላ ተነሳች:: ይህንን ተአምር ያዩ አሕዛብ አምነው ተጠምቀዋል::

††† ከሐዋርያው በረከት ይክፈለን::

††† ሐምሌ 1 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ አግናጥዮስ ሐዋርያዊ ሰማዕት
2.አበው ቅዱሳን ብዮክና ብንያሚን
3.ቅድስት ቅፍሮንያ (ሰማዕት ወጻድቅት)
4.ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ
5.አቡነ ገብረ መድኅን ጻድቅ
6.አባ ክልዮስ ዘሮሜ

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ልደታ ለማርያም ድንግል እግዝእትነ
2.ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና
3.ቅዱስ ራጉኤል ሊቀ መላእክት
4.ቅዱስ በርተሎሜዎስ ሐዋርያ
5.ቅዱስ ሚልኪ ትሩፈ ምግባር

††† "በዚያች ሰዓት ደቀ መዛሙርቱ ወደ ጌታ ኢየሱስ ቀርበው "በመንግስተ ሰማያት ከሁሉ የሚበልጥ ማን ይሆን?" አሉት::
ሕፃንም ጠርቶ በመካከላቸው አቆመ:: እንዲህም አለ:- "እውነት እላቹሃለሁ:: ካልተመለሳችሁ እንደ ሕፃናትም ካልሆናችሁ ወደ መንግስተ ሰማያት ከቶ አትገቡም::
እንግዲህ እንደዚህ ሕፃን ራሱን የሚያዋርድ ሁሉ በመንግስተ ሰማያት የሚበልጥ እርሱ ነው::" " ††
(ማቴ. ፲፰፥፩)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
Forwarded from ዝክረ ቅዱሳን zikre kidusan (ɴᴀᴛɴᴀᴇʟ)
Forwarded from ዝክረ ቅዱሳን zikre kidusan (ɴᴀᴛɴᴀᴇʟ)
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

✞✞✞ እንኩዋን ለሐዋርያው #ቅዱስ_ታዴዎስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞

+"+ #ቅዱስ_ታዴዎስ_ሐዋርያ +"+

=>#ቅዱሳን_ሐዋርያት አባቶቻችን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በተከተሉበት ሰዓት እድሜአቸው በ3 ደረጃ የተከፈለ እንደ ነበር የቤተ ክርስቲያን ትውፊት ያሳያል::

¤እንደ #ዮሐንስ_ወንጌላዊ ያሉት በ20ዎቹ ውስጥ:
¤#ቅዱስ_ታዴዎስን የመሰሉት ደግሞ በ30ና በ40ዎቹ ውስጥ የነበሩ ሲሆን
¤እነ #ቅዱስ_ዼጥሮስ ደግሞ በ50ዎቹ ውስጥ የሚገኙ ነበሩ:: ደቀ መዛሙርቱ ከወጣቶችም: ከጐልማሶችም ከአረጋውያንም የተዋቀሩ ነበሩ ማለት ነው::

+ቅዱስ ታዴዎስ በቀደመ ስሙ #ልብድዮስ ይባል የነበረ ሲሆን በአንዳንድ መጻሕፍት ውስጥ (በተለይ በምሥራቅ ኦርቶዶክሶች) #ስምዖን እና #ይሁዳ እየተባለም ተጠርቷል::

+ቅዱሱ ጌታችን ተከትሎ:
¤ከ12ቱ አንዱ ሆኖ በፈጣሪው ተመርጦ:
¤3 ዓመት ከ3 ወር ከጌታ እግር ተምሮ:
¤በዕርገቱ ተባርኮ:
¤በበዓለ ሃምሳም 71 ልሳናትን ተቀብሎ:
¤#ሐዋርያት ዕጣ ሲጣጣሉ የበኩሉን አሕጉረ ስብከት ተካፍሎ ዓለምን ዙሯል::

+ቅዱስ ታዴዎስ አንድ ቀን ከሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ዼጥሮስ ጋር ወደ አንዲት ሃገር ይገባሉ:: ታዲያ ለቀናት ያለ ምግብ ወንጌልን ሲሰብኩ ቆይተው ነበርና ደጐቹ ሐዋርያት ራባቸው:: ወደ ከተማዋ ሳይገቡ አንድ ሽማግሌ ሲያርስ አይተው ሰላምታን ሰጡትና "እባክህ እርቦናልና አብላን" አሉት:: እርሱም ምንም ወገኑ ከአሕዛብ ቢሆነ አሳዝነውት በሬዎቹን ሳይፈታ እየሮጠ ሄደ::

+ያን ጊዜ ቅዱስ ታዴዎስ ሊቀ ሐዋርያትን "እርሱ እስኪመጣ ለምን አናርስም" አለው:: 2ቱ ተነስተው ታዴዎስ ሞፈር: ዼጥሮስ ደግሞ ስንዴውን ያዘ:: ቅዱሳኑ እየዘሩ ያረሱት ሰውየው ምግብ ይዞ እስኪመጣ አድጐ: አፍርቶ: እሸት ሆኖ ቆየው::

+ገበሬው የተደረገውን ተአምራት ባየ ጊዜ ደነገጠ:: ሊያመልካቸውም ወደደ:: እነርሱ ግን "እኛ የልዑል ባሮች ነን" ብለው በክርስቶስ ማመንን አስተማሩት:: "ልከተላችሁ" ቢላቸው "የለም! ከእሸቱ ይዘህ ወደ ከተማ ግባና ራት አዘጋጅልን:: እኛ እንመጣለን" አሉት::

+እርሱ ወደ ቤቱ ሲመለስ አሕዛብ ነገሩን ተረዱ:: ተሠብሥበውም "እነዚህ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እሳትም ሰይፍም አይበግራቸውም" ብለው ወደ ከተማ እንዳይገቡ ከበሩ ላይ ራቁቷን የሆነች ዘማ አቆሙ::

+ቅዱስ ታዴዎስ ገና ከርቀት ስላያት ቀና ብሎ #ቅዱስ_ሚካኤልን "እርዳን" አለው:: ሊቀ መላእክትም ድንገት ወርዶ ዘማዋን ሴት በጸጉሯ በዓየር ላይ ሰቀላት:: በከተማዋ ያሉ አሕዛብም ይህንና ሌሎች ተአምራትን አይተው ሁሉም በጌታችን አምነው ተጠመቁ:: ለሐዋርያቱም ሰገዱላቸው::

+አንድ ቀን ግን አንድ ጐረምሳ ባለ ጠጋ ቅዱስ ታዴዎስ "ሀብት ንብረታችሁን መጽውቱ" ሲል ሰምቶት ዘሎ የሐዋርያውን ጉሮሮ አንቆ ከሞት አድርሶት ነበር:: ያን ጊዜ "ጌታየ! ለካ ሀብታም ከሚጸድቅ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀላል ያልክ ለዚህ ነው!" ብሏል:: ባለ ጠጋው "እንዴት ይሆናል?" ቢለው መርፌ አሠርቶ ግመሉን ከነ ባለቤቱ በሰው ሁሉ ፊት 3 ጊዜ አሳልፎታል::

+ያም ማለት ጌታችን እንዳለው "በሰው ዘንድ የማይቻለው በእግዚአብሔር ዘንድ ይቻላል::" (ማር. 10:23) በዚህ ምክንያትም ያ ክፉ ባለ ጸጋ ወደ ልቡናው ተመልሶ ከቅዱስ ታዴዎስ እግር ሥር ወደቀ:: ሐዋርያውም አለው "ሀብትህን ለነዳያን ስጥ:: ይህንንም በትር እንካና እየዞርክ ወንጌለ መንግስትን ስበክ::" ባለ ጸጋውም የተባለውን ሁሉ ፈጽሞ በክብር ዐርፏል::

+ቅዱሳኑ ታዴዎስና ዼጥሮስ ግን በሃገሪቱ አብያተ ክርስቲያናትን አንጸው: ካህናትን ሹመው: ያቺን በዓየር ላይ የሰቀሏትን ዘማም የተባረከች መበለት አድርገው: በሌሎች አሕጉራት ወንጌልን ለማዳረስ ወጥተዋል::

+ቅዱስ ታዴዎስም እስከ እርጅናው ድረስ ለወንጌል ሲተጋ ኑሯል:: ጌታችንም በየጊዜው በአካል እየተገለጸ አጽናንቶታል:: ከብዙ የድካምና የመከራ ዘመናት በሁዋላም በዚህች ቀን ዐርፏል::

=>ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅዱሱ ሐዋርያ በረከት ይክፈለን::

=>ሐምሌ 2 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ታዴዎስ ሐዋርያ (ከ12ቱ ሐዋርያት)

=>ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት
2.ቅዱስ ኢዮብ ጻድቅ ተአጋሲ
3.ቅዱስ አቤል ጻድቅ
4.ቅዱስ አባ ዻውሊ ገዳማዊ (ታላቁ)
5.ቅዱስ ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ
6.አባ ሕርያቆስ ዘሃገረ ብሕንሳ

=>+"+ ጌታ ኢየሱስም ዘወር ብሎ አይቶ ደቀ መዛሙርቱን "ገንዘብ ላላቸው ወደ እግዚአብሔር መንግስት መግባት እንዴት ጭንቅ ይሆናል!" አላቸው:: ደቀ መዛሙርቱም እነዚህን ቃሎች አደነቁ:: ጌታ ኢየሱስም ደግሞ መልሶ "ልጆች ሆይ! በገንዘብ ለሚታመኑ ወደ #እግዚአብሔር መንግስት መግባት እንዴት ጭንቅ ነው! ባለ ጠጋ ወደ እግዚአብሔር መንግስት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀላል" አላቸው:: +"+ (ማር. 10:23-28)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
2024/06/29 10:03:50
Back to Top
HTML Embed Code: