Telegram Web Link
Forwarded from ዝክረ ቅዱሳን zikre kidusan (ɴᴀᴛɴᴀᴇʟ)
††† እንኳን ለተባረከ ወር ሐምሌ እና ለቅዱሳኑ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

††† እግዚአብሔርን ቸር የምንለው በባሕርዩ ፍጹም ቸር በመሆኑ ነው:: ይሕንን ደግሞ ለማረጋገጥ መቅመስ ይቻላል:: ይገባልም:: (መዝ. 33:7) ይሔው ደግሞ ያን ሁሉ ኃጢአታችንን ታግሶ ከወርኀ ሐምሌ አደረሰን:: ለዚሕ ቸርነቱ አምልኮ : ውዳሴና ስግደት ይገባዋል::
ለወርኀ ነሐሴ ደግሞ እንዲያደርሰን ልንማጸነው ይገባል::

††† ቅዱስ አግናጥዮስ ሐዋርያዊ ሊቅ †††

††† ሐዋርያዊ ጳጳስና ሰማዕት ቅዱስ አግናጥዮስ ገና በልጅነቱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ያየ : ራሱ ጌታችን ትንቢት የተናገረለት (ማቴ.18:1) እና ከጌታ ዕርገት በኋላ ሐዋርያትን የተከተለ አባት ነው:: ጌታ ሲያርግ የአምስት ዓመት ሕፃን ሲሆን ከሰላሳ ስድስት ዓመታት በላይ ሐዋርያትንና ቤተ ክርስቲያንን አገልግሏል::

ዕድሜው ወደ አርባዎቹ ሲደርስ (ኢየሩሳሌም በጠፋችበት ዓመት - በ70 ዓ/ም) እርሱ የአንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳት ሆኖ ተሹሟል:: አስቀድሞ ከወንጌላዊ ቅዱስ ዮሐንስ እግር ምሥጢርና ፍቅርን ጠጥቷልና የተለየ ሰው ነበር:: ቅዱስ አግናጥዮስ ከአንጾኪያ እየተነሳ ምድረ እስያንም በወንጌል ዕርፈ መስቀል አርሷል::

በአካል ያልደረሰባቸውን በጦማር (በክታብ) አስተምሯል:: በአካሉ እንኳ ምንም በጾም በጸሎትና በብዙ ድካም የተቀጠቀጠ ቢሆን ግርማው የሚያስፈራ ነበር:: ከነገር ሁሉ በኋላ የወቅቱ ቄሣር ጠራብሎስ ይዞ አሰቃይቶ ለአንበሳ አስበልቶታል:: በዚህ ምክንያት "ምጥው ለአንበሳ-ለአንበሳ የተሰጠ" እየተባለ ይጠራል::

††† አባ ብዮክ እና አባ ብንያሚን †††

††† እነዚህ ቅዱሳን የሥጋ ወንድማማቾች ናቸው:: ካህን አባታቸው በሚገባ ቢያሳድጋቸው እነሱም ገና በወጣትነት የሚደነቅ የክህነት አገልግሎትን ሰጥተዋል:: ሙሉ ሌሊት ለጸሎት : ሲነጋ ለኪዳን : በሠርክ ደግሞ ለቅዳሴ ይፋጠኑ ነበር:: ሁሌም በየቤቱ እየዞሩ የደከመውን ሲያበረቱ : የታመመውን ሲፈውሱ : ያዘነውን ሲያጽናኑ ውለው ትንሽ ቂጣ ለራት ይመገባሉ::

ሰውነታቸው በፍቅር ሽቱ የታሸ ነበርና ብዙዎችን መለወጥ ቻሉ:: አንዴ ቅዳሴ ሊገቡ ሲሉ "አባታችሁ ሊሞት ነው" ቢሏቸው "ሰማያዊው አባት ይቀድማል" ብለው ቀድሰዋል:: አባታቸውንም ቀብረውታል:: በመጨረሻ ግን አንድ ቀን ለመስዋዕት ብለው ያዘጋጁትን የበረከት ሕብስት እባብ በልቶባቸው አገኙ:: እንደ ምንም ፈልገው እባቡን ገደሉት::

ነገር ግን ያ የተባረከ ሕብስት በሆዱ ውስጥ ነበርና ምን ያድርጉት? ጌታን ስለ ማክበር ሊበሉት ፈልገው ጌታን ቢጠይቁት መልአኩ መጥቶ "ሰማዕትነት ሆኖ ይቆጠርላቹሃል" አላቸው:: ሁለቱ ወንድማማቾች ብዮክና ብንያሚን ፈጣሪያቸውን አመስግነው በሉት:: ምዕመናን ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲገቡ ሁለቱንም እንደተቃቀፉ ዐርፈው አገኟቸው:: መልካም እረኞቻቸው ናቸውና ከታላቅ ለቅሶ ጋር ቀብረዋቸዋል::

††† ቅድስት ቅፍሮንያ ሰማዕት ወጻድቅት †††

††† ይህቺ ቅድስት እናታችን ደግሞ ገና በአሥራ ሁለት ዓመቷ ታላቅ እህቷን ተከትላ ገዳም ትገባለች:: በሚገርም ተጋድሎ በጥቂት ጊዜ አጋንንትን አሳፍራ መነኮሳይያትንም አስገርማቸዋለች:: ትጋቷ ግሩም ነበርና ስትታዘዝ : ስትጸልይና ስትሰግድ ያለ እንቅልፍና ምግብ ቀናት ያልፉ ነበር:: በዚህ የተቆጣ ሰይጣን አረማዊ መኮንንን ይዞባት መጣ::

ሌሎች ደናግል ሲያመልጡ እርሷ ለመከራ ተዘጋጅታ ጠበቀችው:: አዕምሮ የጎደለው መኮንኑም ክርስቶስን ካልካድሽ ብሎ ጽኑዕ ጽኑዕ መከራን አመጣባት:: በተጋድሎ ባለቀ አካሏ ሁሉንም ቻለች:: በዚህች ቀን ግን አንገቷን በሰይፍ አስቆርጧታል::

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የወዳጆቹን ትዕግስትና ጽናት ለእኛም ያድለን:: ከበረከታቸውም ይክፈለን::

††† ቅዱስ ቶማስ †††

ዳግመኛ በዚህ ቀን ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ ይታሰባል::
ይኸውም ከሕንድ አውራጃዎች በአንዱ ወንጌልን ሰብኮ እኩሎቹ ሲያምኑ እኩሎቹ እንቢ አሉ:: ቅዱስ ቶማስም ያመኑትን "ከጣዖት አምልኮና ከዝሙት ሽሹ" ብሎ መከራቸው::

ምክሩን ከሰሙት አንዱ በዚያው ምሽት ሊጠጣ ወደ መሸታ ቤት ይገባል:: ሰው ሁሉ ከወጣ በኋላ ባለ መሸተኛዋ ሴት እንደለመደችው አብረው እንዲተኙ ስትጠይቀው "እንዴት ሐዋርያው ከዝሙት ሽሹ እያለ እንዲህ ትይኛለሽ?" በሚል ሰይፍ አውጥቶ አንገቷን ቆረጣት::

እርሱ መልካም ያደረገ መስሎታል:: የሠራው ሥራ (መግደሉ) ግን አሕዛባዊ ግብር ነው:: በማግስቱ ቅዱስ ቶማስ ነገሩን ሰምቶ ሰዎችን ሰበሰበና "ይህንን የአውሬ ድርጊት የፈጸመ ማነው?" ሲል ጠየቀ:: ፈጻሚው ግን አልታወቅም በሚል ዝም አለ:: ወዲያው ቅዱሱ ሐዋርያ ዳቦ አንስቶ ቆረሰና "ለበረከት እያነሳችሁ ውሰዱ" አለ:: ሰውየው ተራውን ጠብቆ ሊያነሳ ሲል እጁ ሰለለች::

ሐዋርያው "ምነው ልጄ! ምን ሆንክ?" አለው:: እሱም እንዳላመለጠ ሲያውቅ እውነቱን ተናዘዘ:: ቅዱስ ቶማስ ግን ሕዝቡ ሁሉ እንደተሰበሰበ ያን ወጣት ገስጾ "አስከሬኑን አምጡልኝ" አለ::

የወጣቱን እጅ ፈውሶ "በል የገደልኩሽ እኔ:: የሚያስነሳሽ ግን ጌታየ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው:: ብለህ አንገቷን ቀጥለው" አለው:: እንዳለው ቢያደርግ የሞተችው አፈፍ ብላ ተነሳች:: ይህንን ተአምር ያዩ አሕዛብ አምነው ተጠምቀዋል::

††† ከሐዋርያው በረከት ይክፈለን::

††† ሐምሌ 1 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ አግናጥዮስ ሐዋርያዊ ሰማዕት
2.አበው ቅዱሳን ብዮክና ብንያሚን
3.ቅድስት ቅፍሮንያ (ሰማዕት ወጻድቅት)
4.ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ
5.አቡነ ገብረ መድኅን ጻድቅ
6.አባ ክልዮስ ዘሮሜ

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ልደታ ለማርያም ድንግል እግዝእትነ
2.ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና
3.ቅዱስ ራጉኤል ሊቀ መላእክት
4.ቅዱስ በርተሎሜዎስ ሐዋርያ
5.ቅዱስ ሚልኪ ትሩፈ ምግባር

††† "በዚያች ሰዓት ደቀ መዛሙርቱ ወደ ጌታ ኢየሱስ ቀርበው "በመንግስተ ሰማያት ከሁሉ የሚበልጥ ማን ይሆን?" አሉት::
ሕፃንም ጠርቶ በመካከላቸው አቆመ:: እንዲህም አለ:- "እውነት እላቹሃለሁ:: ካልተመለሳችሁ እንደ ሕፃናትም ካልሆናችሁ ወደ መንግስተ ሰማያት ከቶ አትገቡም::
እንግዲህ እንደዚህ ሕፃን ራሱን የሚያዋርድ ሁሉ በመንግስተ ሰማያት የሚበልጥ እርሱ ነው::" " ††
(ማቴ. ፲፰፥፩)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
Forwarded from ዝክረ ቅዱሳን zikre kidusan (ɴᴀᴛɴᴀᴇʟ)
Forwarded from ዝክረ ቅዱሳን zikre kidusan (ɴᴀᴛɴᴀᴇʟ)
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

✞✞✞ እንኩዋን ለሐዋርያው #ቅዱስ_ታዴዎስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞

+"+ #ቅዱስ_ታዴዎስ_ሐዋርያ +"+

=>#ቅዱሳን_ሐዋርያት አባቶቻችን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በተከተሉበት ሰዓት እድሜአቸው በ3 ደረጃ የተከፈለ እንደ ነበር የቤተ ክርስቲያን ትውፊት ያሳያል::

¤እንደ #ዮሐንስ_ወንጌላዊ ያሉት በ20ዎቹ ውስጥ:
¤#ቅዱስ_ታዴዎስን የመሰሉት ደግሞ በ30ና በ40ዎቹ ውስጥ የነበሩ ሲሆን
¤እነ #ቅዱስ_ዼጥሮስ ደግሞ በ50ዎቹ ውስጥ የሚገኙ ነበሩ:: ደቀ መዛሙርቱ ከወጣቶችም: ከጐልማሶችም ከአረጋውያንም የተዋቀሩ ነበሩ ማለት ነው::

+ቅዱስ ታዴዎስ በቀደመ ስሙ #ልብድዮስ ይባል የነበረ ሲሆን በአንዳንድ መጻሕፍት ውስጥ (በተለይ በምሥራቅ ኦርቶዶክሶች) #ስምዖን እና #ይሁዳ እየተባለም ተጠርቷል::

+ቅዱሱ ጌታችን ተከትሎ:
¤ከ12ቱ አንዱ ሆኖ በፈጣሪው ተመርጦ:
¤3 ዓመት ከ3 ወር ከጌታ እግር ተምሮ:
¤በዕርገቱ ተባርኮ:
¤በበዓለ ሃምሳም 71 ልሳናትን ተቀብሎ:
¤#ሐዋርያት ዕጣ ሲጣጣሉ የበኩሉን አሕጉረ ስብከት ተካፍሎ ዓለምን ዙሯል::

+ቅዱስ ታዴዎስ አንድ ቀን ከሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ዼጥሮስ ጋር ወደ አንዲት ሃገር ይገባሉ:: ታዲያ ለቀናት ያለ ምግብ ወንጌልን ሲሰብኩ ቆይተው ነበርና ደጐቹ ሐዋርያት ራባቸው:: ወደ ከተማዋ ሳይገቡ አንድ ሽማግሌ ሲያርስ አይተው ሰላምታን ሰጡትና "እባክህ እርቦናልና አብላን" አሉት:: እርሱም ምንም ወገኑ ከአሕዛብ ቢሆነ አሳዝነውት በሬዎቹን ሳይፈታ እየሮጠ ሄደ::

+ያን ጊዜ ቅዱስ ታዴዎስ ሊቀ ሐዋርያትን "እርሱ እስኪመጣ ለምን አናርስም" አለው:: 2ቱ ተነስተው ታዴዎስ ሞፈር: ዼጥሮስ ደግሞ ስንዴውን ያዘ:: ቅዱሳኑ እየዘሩ ያረሱት ሰውየው ምግብ ይዞ እስኪመጣ አድጐ: አፍርቶ: እሸት ሆኖ ቆየው::

+ገበሬው የተደረገውን ተአምራት ባየ ጊዜ ደነገጠ:: ሊያመልካቸውም ወደደ:: እነርሱ ግን "እኛ የልዑል ባሮች ነን" ብለው በክርስቶስ ማመንን አስተማሩት:: "ልከተላችሁ" ቢላቸው "የለም! ከእሸቱ ይዘህ ወደ ከተማ ግባና ራት አዘጋጅልን:: እኛ እንመጣለን" አሉት::

+እርሱ ወደ ቤቱ ሲመለስ አሕዛብ ነገሩን ተረዱ:: ተሠብሥበውም "እነዚህ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እሳትም ሰይፍም አይበግራቸውም" ብለው ወደ ከተማ እንዳይገቡ ከበሩ ላይ ራቁቷን የሆነች ዘማ አቆሙ::

+ቅዱስ ታዴዎስ ገና ከርቀት ስላያት ቀና ብሎ #ቅዱስ_ሚካኤልን "እርዳን" አለው:: ሊቀ መላእክትም ድንገት ወርዶ ዘማዋን ሴት በጸጉሯ በዓየር ላይ ሰቀላት:: በከተማዋ ያሉ አሕዛብም ይህንና ሌሎች ተአምራትን አይተው ሁሉም በጌታችን አምነው ተጠመቁ:: ለሐዋርያቱም ሰገዱላቸው::

+አንድ ቀን ግን አንድ ጐረምሳ ባለ ጠጋ ቅዱስ ታዴዎስ "ሀብት ንብረታችሁን መጽውቱ" ሲል ሰምቶት ዘሎ የሐዋርያውን ጉሮሮ አንቆ ከሞት አድርሶት ነበር:: ያን ጊዜ "ጌታየ! ለካ ሀብታም ከሚጸድቅ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀላል ያልክ ለዚህ ነው!" ብሏል:: ባለ ጠጋው "እንዴት ይሆናል?" ቢለው መርፌ አሠርቶ ግመሉን ከነ ባለቤቱ በሰው ሁሉ ፊት 3 ጊዜ አሳልፎታል::

+ያም ማለት ጌታችን እንዳለው "በሰው ዘንድ የማይቻለው በእግዚአብሔር ዘንድ ይቻላል::" (ማር. 10:23) በዚህ ምክንያትም ያ ክፉ ባለ ጸጋ ወደ ልቡናው ተመልሶ ከቅዱስ ታዴዎስ እግር ሥር ወደቀ:: ሐዋርያውም አለው "ሀብትህን ለነዳያን ስጥ:: ይህንንም በትር እንካና እየዞርክ ወንጌለ መንግስትን ስበክ::" ባለ ጸጋውም የተባለውን ሁሉ ፈጽሞ በክብር ዐርፏል::

+ቅዱሳኑ ታዴዎስና ዼጥሮስ ግን በሃገሪቱ አብያተ ክርስቲያናትን አንጸው: ካህናትን ሹመው: ያቺን በዓየር ላይ የሰቀሏትን ዘማም የተባረከች መበለት አድርገው: በሌሎች አሕጉራት ወንጌልን ለማዳረስ ወጥተዋል::

+ቅዱስ ታዴዎስም እስከ እርጅናው ድረስ ለወንጌል ሲተጋ ኑሯል:: ጌታችንም በየጊዜው በአካል እየተገለጸ አጽናንቶታል:: ከብዙ የድካምና የመከራ ዘመናት በሁዋላም በዚህች ቀን ዐርፏል::

=>ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅዱሱ ሐዋርያ በረከት ይክፈለን::

=>ሐምሌ 2 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ታዴዎስ ሐዋርያ (ከ12ቱ ሐዋርያት)

=>ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት
2.ቅዱስ ኢዮብ ጻድቅ ተአጋሲ
3.ቅዱስ አቤል ጻድቅ
4.ቅዱስ አባ ዻውሊ ገዳማዊ (ታላቁ)
5.ቅዱስ ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ
6.አባ ሕርያቆስ ዘሃገረ ብሕንሳ

=>+"+ ጌታ ኢየሱስም ዘወር ብሎ አይቶ ደቀ መዛሙርቱን "ገንዘብ ላላቸው ወደ እግዚአብሔር መንግስት መግባት እንዴት ጭንቅ ይሆናል!" አላቸው:: ደቀ መዛሙርቱም እነዚህን ቃሎች አደነቁ:: ጌታ ኢየሱስም ደግሞ መልሶ "ልጆች ሆይ! በገንዘብ ለሚታመኑ ወደ #እግዚአብሔር መንግስት መግባት እንዴት ጭንቅ ነው! ባለ ጠጋ ወደ እግዚአብሔር መንግስት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀላል" አላቸው:: +"+ (ማር. 10:23-28)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
Forwarded from ዝክረ ቅዱሳን zikre kidusan (ɴᴀᴛɴᴀᴇʟ)
Forwarded from ዝክረ ቅዱሳን zikre kidusan (ɴᴀᴛɴᴀᴇʟ)
††† እንኳን ለጻድቃን ቅዱሳን አባ አጋቶን ወአቡነ ያሳይ ዘመንዳባ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† አባ አጋቶን ዘዓምድ †††

††† ታላቁ ጻድቅ በትውልድ ግብጻዊ ሲሆኑ የነበሩበት ዘመንም ከ4ኛው ክ/ዘመን መጨረሻ እስከ 5ኛው መቶ ክ/ዘመን አጋማሽ አካባቢ ነው:: በእርግጥ 'አጋቶን ' በሚባል ስም የሚጠሩ ብዙ አበው አሉ:: ቅድሚያውን 2ቱ ይወስዳሉ::
አንደኛው አባ አጋቶን ለ30 ዓመታት ድንጋይ ጐርሰው የኖሩት አባት ሲሆኑ ሁለተኛው ደግሞ ዛሬ የምናከብራቸው ናቸው:: እኒህኛው 'ዘዓምድ ' ይባላሉ:: ምክንያቱም ለ50 ዓመታት አንድ ምሰሶ ላይ ያለ ዕረፍት ጸልየዋልና ነው::

አባ አጋቶን ገና ከልጅነታቸው መጻሕፍትን የተማሩ ሲሆኑ ምናኔን አጥብቀው ይፈልጓት ነበር:: በዚህም ራሳቸውን በትሕርምት እየገዙ: በዲቁና ማዕርጋቸውም እያገለገሉ እስከ 35ዓመታቸው ቆዩ:: በዚህ ጊዜ ደግሞ 'ይገባሃል' ብለው ቅስናን ሾሟቸው::

የማታ ማታ የለመኑትን የማይነሳ ጌታ ተምኔተ ልባቸውን ፈጽሞላቸው ወደ በርሃ ሔዱ:: ወቅቱ የግብጽ ገዳማት በቅዱሳን ሕይወት የበሩበት ነውና እዚህም እዚያም አበውና እናቶች ይገኙ ነበር::

አባ አጋቶንም የከዋክብቱ አበው አባ ገዐርጊና አባ አብርሃም ደቀ መዝሙር ሆነው ገቡ:: አስፈላጊውን የምንኩስና ፈተና ካለፉ በኋላም ምንኩስናን ከእነዚህ አባቶች ተቀበሉ:: በዚያው በገዳመ አስቄጥስ በጽኑ ገድል ተጠምደው ለ15 ዓመታት አገለገሉ::

ጻድቁ ከእርሳቸው በፊት የነበሩ ቅዱሳንን ተጋድሎ ጠዋት ማታእያነበቡ መንፈሳዊ ቅናትን ይቀኑ ነበር:: በተለይ የታላቁን ስምዖን ዘዓምድን ገድል ሲያነቡ ሕሊናቸውን ደስ ይለው: ይህንኑ ገድል ይመኙ ነበር:: እድሜአቸው 50 ዓመት በሞላ ጊዜ በልቡናቸው እንደ አባ ስምዖን ዘዓምድ ለመጋደል ወሰኑ:: ይህን ለገዳሙ አባቶች ቢያማክሯቸው አበው:- "ይበል! ሸጋ ምክር ነው:: እግዚአብሔር ያስፈጽምህ!" ብለው መርቀው አሰናበቷቸው:: አባ አጋቶን የዳዊትን መዝሙር እየዘመሩ ከገዳሙ ወጡ:: በጣምም ወደ ዓለም ሳይገቡ: ከዓለም (ከከተማም) በጣም ሳይርቁ አንድ ረዥም ምሰሶ አገኙና ከላዩ ላይ ወጡ::

ከዚህች ዕለት ጀምረው ጻድቁ ለ50 ዓመታት ከዚያች ዓምድ (ምሰሶ) ወርደው: ለሥጋቸውም ዕረፍትን ሰጥተውት አያውቁም:: ማዕከለ ገዳም ወዓለም ናቸውና ለምዕመናንም ሆነ ለመነኮሳት አጽናኝ አባት ሆኑ:: ለአካባቢውም የብርሃን ምሰሶ ሆኑ:: የታመመ ቢኖር ይፈውሱታል:: የበደለውን በንስሃ ይመልሱታል:: ሰይጣን የቋጠረውን ይፈቱታል:: ለራሳቸው ግን ከጸሎት: ከጾምና ከትሕርምት በቀር ምንም አልነበራቸውም:: በተለይ እነዚህ ስራዎቻቸው ይዘከሩላቸዋል::
1.አጥማቂ ነን እያሉ ሕዝቡን ያስቱ የነበሩ ሰዎችን እየጠሩ እንዲህ የሚያስደርጋቸውን ጋኔን ከእነሱ አስወጥተዋል::
2.እርሳቸውን ያልሰሙት ግን መጨረሻቸው ጥፋት ሆኗል::
3.ፍጹም ወንጌልን በሕይወትና በአንደበት መስክረዋል::
4.ሕዝቡን በንስሃ አስጊጠዋል::
5.ተግሳጽ የሚገባውን ገስጸዋል::

ጻድቁ አባ አጋቶን ዘዓምድ ከእነዚህ የቅድስና ዘመናት በኋላበተወለዱ በ100 ዓመታቸው በዚህች ቀን ዐርፈው በክብርና በዝማሬ ተቀብረዋል::

††† አቡነ ያሳይ ዘመንዳባ †††

††† እኒህ ኢትዮዽያዊ ጻድቅ በ14ኛው መቶ ክ/ዘ በጣና ገዳማትውስጥ ያበሩ ኮከብ ናቸው:: ከ7ቱ ከዋክብት (አባ ዮሐንስ፣ አባ ታዴዎስ፣ አባ ያፍቅረነ እግዚእ፣ አባ ሳሙኤል ዘዋልድባ፣ አባ ሳሙኤል ዘቆየጻና አባ ሳሙኤል ዘጣሬጣ ) እርሳቸው አንዱ ናቸው:: እነዚህ አበው ከገዳማዊ ሕይወታቸው ባሻገር በምስጉን የወንጌል አገልግሎታቸው የሚታወቁ ናቸው::

ገድላቸው እንደሚለው አቡነ ያሳይ የዐፄ ዐምደ ጽዮን ቀዳማዊ ልጅ ሲሆኑ የተወለዱትም በ14ኛው መቶ ክ/ዘመን ሽዋ: ተጉለት ውስጥ ነው:: ገና በልጅነታቸው ወደ አባታቸው ቤተ መንግስት የሚመጡ መነኮሳትን እግር እያጠቡ ሥርዓተ ምንኩስናን በድብቅ ያጠኑ ነበር::

ብሉይ ከሐዲስ የጠነቀቁ ናቸውና የአባታቸውን ዙፋን (ልዑልነት) ስለ ፍቅረ ክርስቶስ ንቀውት እየዘመሩ ጠፍተው ወደ ትግራይ ተጓዙ:: በዚህም ምክንያት 'መናኔ መንግስት' ይባላሉ:: በዚያም ወደ ደብረ በንኮል ገዳም ውስጥ ገብተው የታላቁ አባት የአቡነ መድኃኒነ እግዚእ ደቀ መዝሙር ሆኑ::

ቀደም ሲል የጠቀስናቸው 7ቱ አበው በዚያ ነበሩና 7ቱም በአንድ ቀን ሲመነኩሱ ገዳሙ የተቃጠለ እስኪመስል ድረስ ብርሃን ወርዶ ነበር:: አቡነ ያሳይ በረድእነት በቆዩበት ዘመን ዛፎችን መትከል ይወዱ ነበር:: ከትሩፋት መልስም በልብሳቸው ውሃ እየቀዱ ያጠጡ ነበር:: በተለይ "ምዕራገ ጸሎት" የሚባለው ተአምረኛ ዛፍ ዛሬ ድረስ አለ ይባላል::

አቡነ ያሳይ ጊዜው በደረሰ ሰዓት ከአቡነ መድኃኒነ እግዚእ ተባርከው: ከ2ቱ ባልንጀሮቻቸው (አቡነ ሳሙኤል ዘዋሊና አቡነ ያፍቅረነ እግዚእ) ጋር ወደ ጣና ሐይቅ መጡ:: በዚያም አካባቢ ተአምራትን እየሠሩ ሕዝቡንም እያስተማሩ ከቆዩ በኋላ ጌታ ወደየፈቀደላቸው ቦታ ተለያዩ::

አቡነ ሳሙኤል ወደ ዋልድባ: አቡነ ያፍቅረነ እግዚእ ወደ ገሊላ: ከዚያ ወደ ጉጉቤ ሲሔዱ አቡነ ያሳይ መንዳባ ውስጥ ገቡ:: ጻድቁ ወደ አርባ ምንጭ ሒደው ታቦተ መድኃኔ ዓለምን ይዘው ሲመጡ ጣናን የሚሻገሩበት አጡ:: ጌታን ቢማጸኑት:- "ምነው እሷን ድንጋይ ባርከህ አትቀመጥባትም?" አላቸው:: እሳቸውም በእምነት: ድንጋይ ላይ ተቀምጠው ጣናን ተሻገሩት:: ይህንን ከርቀት ያዩ የዘመኑ ሰዎች "ብዙ ተአምር አይተናል: ነገር ግን ማን እንደ አባ! ጣናን በድንጋይ የተሻገረ" ሲሉ አድንቀዋቸዋል::

ጻድቁ ጣናን ተሻግረው: ገዳም መሥርተው: ብዙ አርድእትን አፍርተው: በተጋድሎ ሕይወታቸው ቀጥለዋል:: በተለይ ዛሬ ድረስ የሚተረከው የ'አትማረኝ' ታሪክም የሚገኘው እዚሁ ገዳም ውስጥ ነው:: ታሪኩም በየዋህነት "አትማረኝ" ብለው ጸልየው ጣናን ያለ ታንኳ በእግራቸው የረገጡ አባትን የሚመለከት ሲሆን ከአቡነ ያሳይ ጋርም ወዳጅ ነበሩ::

አባታችን አቡነ ያሳይ ለዘመናት በቅድስና ኑረው: ቅዱሳንንም ወልደው መስከረም 14 ቀን ታመሙ:: "ጌታ ሆይ!" ብለው ቢጠሩት መድኃኔ ዓለም መጣላቸው:: ጣና በብርሃን ተከበበች:: ጌታም "ወዳጄ! ስለ ድካምህ: ደጅህን የረገጠውን: መታሰቢያህን ያደረገውን: በስምህ የተማጸነውን ሁሉ ከነትውልዱ እምርልሃለሁ" ብሏቸው ነፍሳቸውን አሳረገ:: አበውም ሥጋቸውን ገንዘው እዚያው መንዳባ መድኃኔ ዓለም ውስጥ ቀበሩት:: ዐጽማቸው ዛሬም ድረስ ይገኛል::

††† አምላከ ጻድቃን በምልጃቸው የበዛች ኃጢአታችንን ይቅር ይበለን:: በረከታቸውንም ያብዛልን::

††† መስከረም 14 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.አባ አጋቶን ዘዓምድ
2.አቡነ ያሳይ ዘመንዳባ
3.አባ ጴጥሮስ መምሕረ ጻና (ጣና)
4.ቅዱስ ዴግና ቀሲስ

††† ወርሐዊ በዓላት
1.አቡነ አረጋዊ (ዘሚካኤል)
2.ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ መርዓዊ
3.ቅዱስ ፊልጶስ ሐዋርያ
4.ቅዱስ ሙሴ (የእግዚአብሔር ሰው)
5.አባ ስምዖን ገዳማዊ
6.አባ ዮሐንስ ጻድቅ
7.እናታችን ቅድስት ነሣሒት

††† "ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ይወስዳል:: ጻድቅን በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል:: ማንም ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ውሃ ብቻ በደቀ መዝሙር ስም የሚያጠጣ እውነት እላቹሃለሁ ዋጋው አይጠፋበትም::" †††
(ማቴ. ፲፥፵፩)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
Forwarded from ዝክረ ቅዱሳን zikre kidusan (ɴᴀᴛɴᴀᴇʟ)
Forwarded from ዝክረ ቅዱሳን zikre kidusan (ɴᴀᴛɴᴀᴇʟ)
††† "እስጢፋኖስም ጸጋንና ኃይልን ተሞልቶ በሕዝቡ መካከል ድንቅንና ታላቅ ምልክትን ያደርግ ነበር . . . አንዳንዶቹ ተነስተው እስጢፋኖስን ይከራከሩት ነበር:: ይናገርበት የነበረውንም ጥበብና መንፈስ ይቃወሙዘንድ አልቻሉም:: በዚያን ጊዜ በሙሴ ላይ: በእግዚአብሔርም ላይ የስድብን ነገር ሲናገር ሰምተነዋል የሚሉ ሰዎችን አስነሱ . . . በሸንጐም የተቀመጡት ሁሉ ትኩር ብለው ሲመለከቱት እንደ መልአክ ፊት ሆኖ ፊቱን አዩት::" †††
(ሐዋ. ፮፥፰-፲፭)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
Forwarded from ዝክረ ቅዱሳን zikre kidusan (ɴᴀᴛɴᴀᴇʟ)
Forwarded from ዝክረ ቅዱሳን zikre kidusan (ɴᴀᴛɴᴀᴇʟ)
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

✞✞✞ እንኩዋን ለአበው #ቅዱሳን_ኤዎስጣቴዎስ_አኖሬዎስና_ማር_ያዕቆብ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞

✞✞✞ #አቡነ_ኤዎስጣቴዎስ_ረባን ✞✞✞

=>ሐዋርያዊው ጻድቅ ኢትዮዽያዊ (ኤርትራዊ) ሲሆኑ በዓለም ደረጃ የሚታወቅ አገልግሎት ያላቸው አባት ናቸው:: በመካከለኛው ዘመን የኢትዮዽያ ታሪክ የኤወስጣቴዎስንና የተክለ ሃይማኖትን ያህል ስሙ የጐላ ጻድቅ አይገኝም::

+ጻድቁ በ1265 ዓ/ም አካባቢ እንደ ተወለዱ ሲታመን ወላጆቻቸው #ክርስቶስ_ሞዐ እና #ስነ_ሕይወት ይባላሉ:: የጻድቁ የመጀመሪያ ስም #ማዕቀበ_እግዚእ (ለጌታ የተጠበቀ) ነው:: ኤዎስጣቴዎስ የተባሉ በሁዋላ ነው::

+ገና ከልጅነታቸው መንፈሰ እግዚአብሔር አድሮባቸዋልና ለዚህ ዓለም ግድ አልነበራቸውም:: ከመምሕር ዘንድ ገብተው: ቅዱሳት መጻሕፍትን ተምረው: ዲቁናን ተቀብለው ያገለግሉ ገቡ:: በዲቁና አገልግሎታቸው ስሉጥ በመሆናቸውም የዘመኑ አበው 'ዳግማዊ እስጢፋኖስ' እያሉ ይጠሯቸው ነበር::

+ከዚያ በወጣትነት እድሜአቸው ምናኔን መርጠው: ጾምና ጸሎትን ከስግደት ጋር አዘወተሩ:: እንዲህ ባለ ሕይወት ሳሉ አንድ ቀን ለስም አጠራሩ ጌትነት ይሁንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ዘንድ መጣ::

+በዘባነ ኪሩብ: በግርማው ቢያዩት ደነገጡ:: ጌታ ግን "ወዳጄ ኤዎስጣቴዎስ! ገና ከእናትህ ማሕጸን መርጬሃለሁ:: ከኢትዮዽያ እስከ አርማንያም ሐዋርያ ትሆን ዘንድ ሹሜሃለሁ:: 'ዘኪያከ ሰምዐ: ኪያየ ሰምዐ . . . አንተን የሰማ እኔን ሰማ: አንተን እንቢ ያለ እኔን እንቢ አለ" ብሏቸው: ባርኩዋቸው ዐረገ::

+ጻድቁ ፈጣሪያቸውን ስለ ስጦታው እያመሰገኑ ቅስናን ተቀብለው ስብከትን ጀመሩ:: ስም አጠራራቸውም ፈጥኖ በሃገሪቱ ተሰማ:: በየቦታው እየዞሩ ያላመነውን አሳምነው እያጠመቁ: ያመነውን በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን እያጸኑ: ሕይወተ ገዳምን እያስፋፉ ኖሩ::

+አሁን ኤርትራ ውስጥ የሚገኘውንና እርሳቸው የመሠረቱትን ገዳም ጨምሮ ለገዳማዊ ሕይወት መስፋፋት አስተዋጽኦ አድርገዋል:: በገዳማቸውም አባ አብሳዲን ጨምሮ በርካታ አርድእትን አስተምረዋል: አፍርተዋል::

+አቡነ ኤዎስጣቴዎስ በተለይ የሚታወቁት #ቀዳሚት_ሰንበት እንዳትናቅ (እንድትከበር) ባደረጉት ጥረት ነው:: ደግሞም ተሳክቶላቸዋል:: ቅርብ ጊዜ ከምናየው የድፍረት ሥራ በቀር በሃገራችን 2ቱም ሰንበቶች ክቡር ናቸው::

+አቡነ ኤዎስጣቴዎስ 2 ጊዜ በእግራቸው ተጉዘዋል:: መሔዳቸው ግን ለመሳለም ብቻ አይደለም:: ይልቁኑ የወንጌል ዘርን እየዘሩ: ፍሬውንም እየለቀሙ እንጂ:: እርሳቸው መቼም ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን ቸል አይሉምና::

+በመጨረሻ ሕይወታቸውም በገዳማቸው ላይ ደቀ መዝሙራቸውን አባ አብሳዲን ሹመው ለአዲስ ጉዞ ተነሱ:: እኩሎች ልጆቻቸውን በገዳማቸው ትተው እኩሎችን አስከትለው ጉዞ ወደ አርማንያ ተደረገ::

+በመንገድም ወደ ባሕረ #ኢያሪኮ ሲደርሱ የሚሻገሩበት መርከብ አጡ:: ድንቅ አባት ናቸውና በእምነት አጽፋቸውን (ኩታቸውን) አውልቀው ባሕሩ ላይ ጣሉት:: በላዩ ላይም በትእምርተ መስቀል አማትበው ተቀመጡበት::

+ደቀ መዛሙርቶቻቸውም ባሕሩ ላይ በተነጠፈው ኩታ ላይ ከበው ተቀመጡ:: ከሰማይም ጌታችን ወርዶ በመካከላቸው ቆመ:: #ሚካኤል በቀኝ #ገብርኤልም በግራ ቆሙ:: ጻድቁ ደግሞ ልጆቻቸውን ያስተምሯቸው: ይተረጉሙላቸው ገቡ::

+በመካከል ግን አንዱ (የማነ ብርሃን ይሉታል በቅኔ ቤት) በመጠራጠሩ እርሱ የተቀመጠባት ብቻ ተቀዳ ሰጠመ:: በሁዋላ ግን ጻድቁ ተመልሰው አውጥተው: ከሞት አስነስተውታል:: በዚህም ምክንያት 'ዘአደወ ባሕረ-ማዕበልን የተሻገረ' ይባላሉ::

+አቡነ ኤዎስጣቴዎስ በአርማንያ ለዘመናት ሰብከው: ሕይወተ ገዳምን አስፋፍተው: ብዙ ተአምራትን ሠርተው: በተወለዱ በ80 ዓመታቸው: በ1345 ዓ/ም በዚህች ቀን ዐርፈዋል:: በብዙ ዝማሬ በመቅደሰ #መርምሕናም ተቀብረዋል:: ዛሬ #በኢትዮዽያ: #ኤርትራ: #ግብጽና #አርማንያ ይከብራሉ::

+"+ #አቡነ_አኖሬዎስ_ጻድቅ +"+

=>እኒህ ኢትዮዽያዊ ጻድቅ 'ታላቁ አኖሬዎስ' ይባላሉ:: በዚህ ስም ከሚጠሩ አባቶች ዋነኛው እኒህ ናቸው:: ተወልደው ያደጉት #ሙገር አካባቢ ሲሆን ዘመኑም 14ኛው መቶ ክ/ዘመን ነው:: ወላጆቻቸውም #ሰላማ እና #ክርስቶስ_ዘመዳ ይባላሉ::

+ጻድቁ ከአቡነ #ተክለ_ሃይማኖት ደቀ መዛሙርት አንዱ ናቸው:: በወንጌል ትምሕርት ከመሞላታቸው ባሻገር ፍጹም መናኝ ስለ ነበሩ እጅግ ደፋር ነበሩ:: የትኛውንም ስሕተት ፊት ለፊት ይናገሩም ነበር::

+አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሲያርፉ ጌታ "በአንተ ፈንታ አኖሬዎስ ቀሪ ጣዖት አምልኮን ያጠፋል" ብሎ ነግሯቸው ነበር:: ይኸውም አልቀረ ጻድቁ ከ12ቱ ንቡራነ እድ እንደ አንዱ በተመረጡ ጊዜ በደበቡ የሃገራችን አካባቢ ክርስትናን አስፋፍተዋል::

+#ደብረ_ጽጋጋ ገዳምንም የመሠረቱ እርሳቸው ናቸው:: ዛሬ '#ኑራ_ሑሴን' እየተባለ ታሪኩ ጠልሽቶ የሚነገርለት ዋሻ የጻድቁ በዓት ነው:: አቡነ አኖሬዎስ 2ቱን ነገሥታት (#ዓምደ_ጽዮንንና #ሰይፈ_አርእድን) በመገሰጻቸው ብዙ ፈተና ደርሶባቸዋል:: ጻድቁ ብዙ ፍሬ አፍርተው በዚህ ቀን ዐርፈዋል::

+"+ #ማር_ያዕቆብ_ግብጻዊ +"+

=>በግብጽ ገዳማት ውስጥ በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን ተነስተው ካበሩ ቅዱሳን አንዱ ማር ያዕቆብ ነው:: ቅዱሱ ከተባረከ ቤተሰብ ተወልዶ: በሥርዓቱ አድጐ ገና በልጅነቱ ከመምሕሩ ጋር መንኗል:: ከገድሉ ጽናት የተነሳ ሰይጣን በግልጽ ይፈታተነው ነበር::

+በተለይ ለ7 ዓመታት ያህል ይደበድበው: መሬት ላይ ይጐትተው: በጥፊ ይመታው ነበር:: እርሱ ግን በጸሎቱ መብረቅ አውርዶ አባርሮታል:: በበርሃው ምንም የሚበላ ነገር ባለ መኖሩ የዱር እንስሳትን ወተት ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ይጠጣ ነበር::

+ቅዱሱ ሰማዕት ለመሆን ሞክሮም ነበር:: ማር ያዕቆብ ገድሉና ተአምራቱ እጅግ ብዙ ከመሆኑ የተነሳ ስሙ ከፍ ከፍ ብሏል:: እስኪ ጊዜውና እድሉ ካለዎት #መጽሐፈ_ስንክሳር ላይ የተጻፈውን ገድሉን እንዲያነቡ ልጋብዝዎት:: ጻድቁ ያረፈው በዚሁ ዕለት ነው::

=>አምላከ ቅዱሳን ወዳጆቹ ካሉበት ጉባኤ እንደ ምሕረቱ ታላቀነት ያድርሰን:: በረከታቸውንም ይሙላልን::

=>መስከረም 18 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ረባን
2.አቡነ አኖሬዎስ ዓቢይ
3.ማር ያዕቆብ ግብጻዊ
4.ቅዱስ ዕፀ መስቀል
5.ቅድስት እሌኒ ንግሠት
6.ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ
7.ቅዱስ መርቆሬዎስ ካልዕ (ሰማዕት)
8.ቅዱስ ቶማስ ሰማዕት
9.ቅዱስ ኤፍሬም ሰማዕት
10.አባ ፊልሞስ
11.ቅዱስ ሰልሖን ሰማዕት
12.ቅዱስ አክሳኤልስ ሰማዕት
13.ቅዱስ ይስሐቅ ሰማዕት
14.ቅዱስ እስጢፋኖስ ቀሲስ
15.ቅዱስ ነኪጣ ሰማዕት
16.አባ ፊላታውዎስ መንክራዊ
17.አባ ኖብ ባሕታዊ
18.አባ አትናቴዎስ ሊቀ ዻዻሳት
19."60" ሰማዕታት (ማሕበረ ቅዱስ አቦሊ)

=>ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ፊልዾስ ሐዋርያ
2.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ከ72ቱ አርድእት)

=>+"+ እናንተ የምድር ጨው ናችሁ . . . እናንተ የዓለም #ብርሃን ናችሁ:: በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሠወር አይቻላትም . . . መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ:: +"+ (ማቴ. 5:13-16)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
Forwarded from ዝክረ ቅዱሳን zikre kidusan (ɴᴀᴛɴᴀᴇʟ)
Forwarded from ዝክረ ቅዱሳን zikre kidusan (ɴᴀᴛɴᴀᴇʟ)
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

✞✞✞ መስከረም 19 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ✞✞✞

+*" ቅዱስጐርጐርዮስ ዘአርማንያ "°+

✞✞✞ ይህ ቅዱስ አባት ከሰማዕታት: ከጻድቃን: ከሊቃውንትና ከዻዻሳት ዝርዝር
ውስጥ ይገኛል:: በቤተ ክርስቲያንም ዓበይትተጽፎ
ከሚባሉ አበው አንዱ ነው:: ቅዱስ ጐርጐርዮስ ሮማዊ ሲሆን ከክርስቲያን
ወላጆቹ የተወለደው በዘመነ ሰማዕታት (በ3ኛው መቶ
ክ/ዘመን) ነው::

+አበው በትውፊት እንደ ነገሩን ከሆነ ቅዱሱ የታላቁዋ ሰማዕት ቅድስት
አርሴማ ትልቅ ወንድም ነው:: በዜና ሰማዕታት
እንደሚገኘው በዚያ የመከራ ዘመን ቅዱስ ጐርጐርዮስ ሦስት ኃላፊነቶች
ነበሩበት:-

1.ቅድስት አርሴማን ጨምሮ ደናግሉን ማጽናት
2.ትምሕርተ ቤተ ክርስቲያንን በሚገባ ማጥናት
3.የሚመጣውን መከራ ለመቀበል ራሱን ማዘጋጀት::

+ቅዱሱ 3ቱንም ኃላፊነቶች በሚገባ በመወጣቱ ከራሱ አልፎ ለሌሎቹ አርአያ
መሆን ቻለ:: ያቺን ንጽሕት አርበኛ ቅድስት
አርሴማንም አጽንቶ የደናግሉ መሪ አደረጋት:: መከራው በጣም ገፍቶ እስከበመልኩዋ
መጣበት ጊዜ ድረስ በአንድ የደናግል ገዳም ውስጥ
ሆነው ይጸልዩ: ይጾሙ: ገዳማዊ ሥራንም ይሠሩ ነበር::

+ለዚህም ነው ቅድስት አርሴማና ቅዱስ ጐርጐርዮስ ጻድቃን የምንላቸው::
በኋላ ግን ማሕደረ ሰይጣን ዲዮቅልጢያኖስ
ተማርኮ ቅድስት አርሴማን ካላገባሁ በማለቱ ቅዱስ ጐርጐርዮስበጸሎት ድንግሏን
አርሴማን ጨምሮ ክርስቲያኖችን ይዞ ወደ አርማንያ
ተሰደደ::

+በአርማንያም በአንድ ገዳም ውስጥ ተደብቀው በጾምና ለጥቂት
ጊዜ ቆዩ: ነገር ግን ረሃብ ፈጃቸው:: የሚላስ
የሚቀመስ ነገር በአካባቢው ባለ መኖሩ ቅዱስ ጐርጐርዮስ ወደ ከተማ
ለመውጣት ተገደደ::

+በዚያም በድርጣድስ ቤተ መንግስት ውስጥ ባርነት ተቀጠረ:: በሚያገኛት
ገንዘብም ወገኖቹን ይረዳ ነበር:: መከራው ግንእኔ
አለቀቃቸውም:: ርጉም ዲዮቅልጢያኖስ ቅዱሳኑ ወደ አርማንያ መሔዳቸውን
ስለ ሰማ ይዞ እንዲልክለት ድርጣድስን ላከው::

+ድርጣድስ ግን ቅድስት አርሴማን ባያት ጊዜ ከውበቷ የተነሳ መታገስ
ባለመቻሉ "ካላገባሁሽ" አላት:: ድንግሊቱ ግን "
የክርስቶስ ሙሽራ ነኝ: አይሆንም" አለችው:: ሊያስፈራራት ሞከረ:: ዐይኗ እያየ ደናግሉን ጨፈጨፋቸው::

+አልሳካልህ ቢለው በአደባባይ በግድ ሊያገባት ቢሞክር እጁን ጠምዝዛ
በሰው ሁሉ ፊት መሬት ላይ ጣለችው:: እጅግ ስላፈረ
አስገረፋት: አሰቃያት: ዐይኗንም አወጣ:: በመጨረሻም አንገቷን አስቆርጦ
ከሰማዕታቱ ጋር ተራራ ላይ ጣላት::

+ወዲያው ደግሞ የቅዱስ ጐርጐርዮስ ማንነቱ በመታወቁ ይዘው
እስኪያልቅ ገረፉት:: በእሳትም አቃጠሉት:: በብዙሽማግሌ
ስቃይም አሰቃዩት::

+በመጨረሻ ግን ከነ ሕይወቱ እንዲቀበር ተወሰነበት:: ወደ መጸዳጃ ቤት
ወስደውም ከነ ሕይወቱ ቀበሩት:: ነገር ግን
የእግዚአብሔር መልአክ ወርዶ መተንፈሻ ቀዳዳን ሠራለት:: አንዲት
ክርስቲያንም በዚያች ቀዳዳ ቂጣ እየጣለችለት ለ15
ዓመታት ተቀብሮ ኖረ::

+አካሉና አፈሩ ተጣበቀ:: እርሱ ግን ፈጣሪውን እያመሰገነ ቆየ:: ከነገርየንጉሡ ሁሉ በኋላ ድርጣድስና
ባለሟሎቹ ለአደን
በሔዱበት ርኩስ መንፈስ ወደ አውሬነት (እሪያነት) ቀየራቸው::

+የንጉሡ እንስሳ /አውሬ መሆን በአርማንያ ታላቅ ድንጋጤን ፈጠረ::
እህት ስታለቅስ በራዕይ "ለእመ ኢያዕረግምዎ
ለጐርጐርዮስ አልብክሙ ድኂን-ጐርጐርዮስን ከተቀበረበት ካላወጣችሁት
አትድኑም" አላቸው:: ወዲያውም በዚያች ሽማግሌ መሪነት
ቆፍረው አወጡት::

+አካሉንም እግዚአብሔር መለሰለት:: ቅዱሱ እንደ ወጣ ዕረፍትን አልፈለገም::
ለ15 ዓመታት ቀባሪ አጥቶ የተበተነውን
የቅድስት አርሴማንና የሰማዕታቱን አጽም ሰብስቦ በክብር አኖረው::
ድርጣድስና ባለሟሎቹንም ወደ በርሃ ሒዶ ፈወሳቸው::

+ወደ ሰውነትም መልሶ መላ አርማንያን ወደ ክርስትና መለሰ:: የንጉሡን እግር ግን የአውሬ አድርጐት ቀርቷል:: በመጨረሻም
ቅዱስ ጐርጐርዮስ የአርማንያ ሊቀ ዻዻሳት ሆኖ ተሹሞ ብዙ መጻሕፍትን
ደረሰ:: ከ318ቱ ሊቃውንትም አንዱ ሆኖ ተቆጠረ::
ዕረፍቱ ታሕሳስ 15 ቀን ሲሆን ዛሬ ከተቀበረበት የወጣበት ነው::

+" ቅዱስ ቂርቆስ ገዳማዊ "+

+ቅዱሱ የ6ኛው መቶ ክ/ዘመን ጻድቅ ሲሆን በዓለም ከመናፍቃን: በገዳም
ደግሞ ከአጋንንት ብዙ መከራን ተቀብሏል:: በወቅቱ
መለካውያን (የአሁኖቹ ካቶሊኮችና ምስራቅ ኦርቶዶክሶች) አባቶችን
ያሳድዱ ነበር:: ልክ 9ኙ ቅዱሳን በዚህ
ምክንያት ወደ ኢትዮዽያ እንደመጡት ቅዱስ ቂርቆስም ወደ ግብጽ በርሃ ከእርሷ ተሰደደ::

+በበርሃው ውሃም ሆነ ዛፍ ባለመኖሩ በረሃብና በጥም በመሰቃየቱ ወደ ፈጣሪ
ለመነ:: ጌታም አንዲት አጋዘን ልኮለት
ወተትን አልቦ ጠጣ:: እስከ ሕይወቱ ፍጻሜም ምግቡ ይሔው የአጋዘን ወተት
ነበር:: በዚህ ምክንያት ይሔው ዛሬም ድረስ "
ቅዱስ ቂርቆስ ገዳማዊ ዘሲሳዩ ሐሊበ ቶራ" እየተባለ ይጠራል::

+በበርሃው ውስጥ በኖረባቸው ዘመናትም አንድም ሰው አይቶ ካለማወቁስትሆን
ባለፈ አጋንንት በገሃድ እየመጡ ያሰቃዩት ነበር::
ቅዱሱ ግን በትእግስት ኑሮ በዚህች ቀን ሲያርፍ ብዙ ተአምራት በበዓቱ
ውስጥ ተገልጠዋል:: ይህንን ያዩት ደግሞ ከዻዻሱ
ዘንድ ተልከው የቀበሩት አበው ናቸው::

+" ቅድስት ሮማነ ወርቅ "+

+ይህቺ ቅድስት እናት ደግሞ ኢትዮዽያዊት ናት:: የነገሥታቱ ልጅ አባቷ
አፄ ናዖድ: እናቷ ደግሞ እሌኒ /ወለተ
ማርያም ይባላሉ:: ወንድሟ ደግሞ አፄ ልብነ ድንግል ይባላሉ::

+በቤተ መንግስት ውስጥ ብታድግም መንፈሳዊነቷ የገዳም ያህል ነበር::
ከተባረከ ትዳሯም ቅዱስ ላዕከ ማርያምን አፍርታለች::
አብያተ ክርስቲያናትን ከማነጽ ባለፈ የነዳያን እናትም ነበረች:: በክርስትናዋ
ፈጣሪዋን ደስ አሰኝታ በዚህ ቀን ዐርፋለች::

✞✞✞ አምላከ ቅዱሳን ጸጋውን: ክብሩን አይንሳን:: ከወዳጆቹ በረከትም እንደ ቸርነቱ ያድለን::

✞✞✞ መስከረም 19 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ጐርጐርዮስ ዘአርማርያ
2.ቅዱስ ቂርቆስ ገዳማዊ
3.ቅድስት ሮማነ ወርቅ
4.ቅዱስ ዕጸ መስቀል

++"+ ጻድቃን ጮሁ: እግዚአብሔርም ሰማቸው::
ከመከራቸውም ሁሉ አዳናቸው::
እግዚአብሔር ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው::
መንፈሳቸው የተሰበረውንም ያድናቸዋል::
የጻድቃን መከራቸው ብዙ ነው::
እግዚአብሔርም ከሁሉ ያድናቸዋል::
እግዚአብሔር አጥንቶቻቸውን ሁሉ ይጠብቃል:: +"+ (መዝ. 33:17)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
Forwarded from ዝክረ ቅዱሳን zikre kidusan (ɴᴀᴛɴᴀᴇʟ)
2024/10/01 23:28:28
Back to Top
HTML Embed Code: