Telegram Web Link
#ከሐምሌ_22_እስከ_ሐምሌ_28 ቀን 2016 ዓ/ም ድረስ በሁሉም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ገዳማት የምሕላ ጸሎት እንዲፈጸም አወጀ።

በሀገር አስተማማኝ ሰላም ሲጠፋ በጾም በጸሎት በመወሰን ፣ ምሕላ ይታወጃል። ምሕላ የሚታወጀው ልባዊ በሆነ ተማሕጽኖ ሁሉን ማድረግ ወደሚችለው እግዚአብሔር ምልጃን ለማቅረብ ነው።

"ውሎ ማደር፣ ወጥቶ መግባት በአንዳንድ የሀገራችን አካባቢዎች ስጋት ከሆነ ሰነባብቷል " ያለው ቋሚ ሲኖዶስ " በእውነት የሚለምኑትን ሁሉ የሚሰማ እግዚአብሔር ፦
✤ መተላለፋችንን ይቅር እንዲለን፣
✤ ለሀገራችን ዘላቂ ሰላም፣
✤ ለቤተ ክርስቲያናችን ፍቅር አንድነት፣
✤ ለሕዝባችን ደኅንነት እንዲሰጥልን ከአንድነት ገዳማት ኅብረት በቀረበው ጥያቄ መነሻነት ምሕላ ማወጅ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል" ብሏል።
በዚህም በመላ የሀገራችን ክፍልና ሌሎች አህጉራተ ዓለም የሚገኙ መነኰሳትና መነኰሳይያት ከሐምሌ 22 እስከ ሐምሌ 28 ቀን 2016 ዓ/ም ድረስ ለሰባት ተከታታይ ቀናት በቅድስት ቤተ ክርስቲያኗ ሃይማኖታዊና ቀኖናዊ ትውፊት መሠረት የገዳማት ኅብረቱን ጥሪ ተቀብለው የምሕላ ጸሎት እንዲያደርሱ ጥሪ አቅርቧል።

በጤና ችግር ምክንያት ካልሆነ በስተቀርም እስከ ዕርበተ ፀሐይ በመጾም ሱባኤ እንዲይዙ ፣ ቋሚ ሲኖዶስ ከአደራ ጋር አሳስቧል።

ከዚህ በተጨማሪ ሁሉም የቤተክርስቲያን አገልጋዮች እና ምእመናን ሀገራዊ ሰላምን፣  መረጋጋትን እና ፍቅር አንድነትን ለማስፈን ጾምና ጸሎት በታወጀበት የምሕላ ሳምንት ለገዳማውያኑ ፀጥታ ሲባል ወደ ገዳማት የሚያደርጉትን ጉዞ ለጊዜው እንዲቆይ አድርገውት መደበኛው ሥራቸውን በያሉበት ቦታ እየሰሩ እግዚአብሔር የገዳማውያኑን ጸሎት ሰምቶ ለሀገራችንና ለሕዝባችን ምሕረትን እንዲሰጥ በኅሊና ዝግጅት፣ በሐሳብ አንድነት ሆነው በጾም በጸሎት እንድተጉ ጥሪ ተላልፏል።
ስንክሳር ዘወርኀ ሐምሌ 7
 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ሐምሌ ሰባት በዚች ቀን ሥሉስ ቅዱስ በአብርሃም ቤት የተገለጡበት ነው፣ ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ የአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ልደቱና ዕረፍቱ ነው፣ ቅዱስ አባት የባሕታውያን አለቃ የሆነ መስተጋድል አባ ሲኖዳ አረፈ፣ የሮሜ ከተማ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ አግናጥዮስ በሰማዕትነት ሞተ፡፡

ቅድስት ሥላሴ

ሐምሌ ሰባት በዚች ቀን ሥሉስ ቅዱስ በአብርሃም ቤት የተገለጡበት ነው፡፡ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ በስም በአካል በግብር ሦስትነት በባሕርይ በሕልውናና በፈቃድ አንድነት የጸኑ ናቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ተገኙ፣ በዚህ ጊዜ ያልፋሉ አይባሉም መጀመሪያም መጨረሻም እነርሱ ናቸውና፡፡ ርሕሩሐን ናቸውና በእናት ሥርዓት ‹‹ቅድስት ሥላሴ›› እንላቸዋለን፡፡ የሚጠላቸው (የማያምንባቸውን) አይጠሉም፡፡ የሚወዳቸውን ግን እጽፍ ድርብ ይወዱታል፣ በቤቱም መጥተው ያድራሉ፡፡ ከፍጥረታት ወገን ከእመቤታችን ቀጥሎ የአብርሃምን ያህል በሥላሴ ዘንድ የተወደደ ፍጡር የለም፡፡ አባታችን ቅዱስ አብርሃም የደግነት ሁሉ አባት ነውና በኬብሮን በመምሬ ዛፍ ሥር ሥላሴን ተቀብሎ አስተናግዷል፡፡
አባታችን አብርሃም በ99 ዓመቱ እናታችን ሣራ በ89 ዓመቷ ሥላሴን በድንኳናቸው አስተናገዱ፡፡ አብርሃም እግራቸውን አጠበ፡፡ በጀርባውም አዘላቸው፡፡ ምሳቸውንም አቀረበላቸው፡፡ እነርሱም እንደሚበሉ ሆኑለት፡፡ በዚያው ዕለትም የይስሃቅን መወለድ አበሠሩት፡፡ አብርሃም ከደግነቱና እንግዳ ከመውደዱ የተነሣ በተመሳቀለ ጎዳና ላይ ድንኳን ሠርቶ የወጣ የመረደውን፣ የመጣ የሄደውን ሁሉ እየተቀበለ እግዚአብሔርን እያገለገለ የሚኖር ጻድቅ ነበር፡፡ ለዚህም ነው አብርሃም በወይራ ግራር (በመምሬ) ዛፍ ሥር ተቀምጦ ሳለ እግዚአብሔር አንድነቱን ሦስትነቱን የገለጠለት፡፡ ዘፍ 18፡1-25፣ ሮሜ 4፡-3፡፡ ቀትር ሰዓት ላይ በድንኳኑ ደጅ ተቀምጦ እንግዳ ሲጠብቅ እግዚአብሔር ታየው ተነጋገረው፡፡ አንገቱን ቀና አድርጎ ዐይኑን አራምዶ በተመለከተ ጊዜ እነሆ ሦስት ሰዎች ከበላዩ ባለ ተራራ ላይ ቆመው አያቸው፣ ወደ እርሱም ሲወርዱ አይቶ ፈጥኖ ሄዶ ከሰግደላቸው በኋላ ‹‹አቤቱ በፊትህስ ሞገስ አግኝቼ እንደሆነ ባሪያህን አትለፈኝ ብዬ እለምናለሁ፤ ጥቂት ውኃ ይምጣላችሁ እግራችሁን ታጠቡ…›› እያለ በትሕትና በመጋበዝ ወደ ድንኳኑ አስገብቶ በሚገባ ጋበዛቸው፡፡ ‹‹በፊትህስ ሞገስ አግኝቼ›› ብሎ አንድነታቸውን፣ ‹‹ጥቂት ውኃ ይምጣላችሁ እግራችሁን ታጠቡ›› ብሎ የሦስትነታቸውን ምስጢር ገልጾአል፡፡
ያች ሥላሴ የገቡባት የአብርሃም ድንኳን የእመቤታችን ምሳሌ ናት፡፡ ሥላሴ ወደ አብርሃም ድንኳን እንደገቡ ሁሉ በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያምም አብ ለአጽንዖ፣ መንፈስ ቅዱስ ለአንጽሖ፣ ወልድ በተለየ አካሉ ሥጋዋን ለመዋሐድ የማደራቸው ምሳሌ በመሆኑ አማናዊቷ የሥላሴ ማደሪያ የአብርሃም ድንኳን እመቤታችን ናት፡፡ ሉቃ 1፡35፡፡
እግዚአብሔርም አብርሃምን የዛሬ ዓመት ልጅ እንደሚወልድ ነግሮት በዓመቱ ይስሐቅን ወልዷል፡፡ ሁለቱ ሰዎች ከአብርሃም ድንኳን ወጥተው ወደ ሰዶም ወደ ገሞራ ሄዱ፣ አብርሃምም ይሸኛቸው ዘንድ አብሯቸው ሄደ፡፡ የሄዱትም ሁለቱ ሰዎች አብና መንፈስ ቅዱስ ናቸው፡፡ ነገር ግን አንዱ ወልድ በአብርሃም ቤት ቀርቷል ይኸውም ከቤተ አብርሃም ሰው እንደሚሆን ለማጠየቅ ነው፡፡ አብርሃምም ተመልሶ በእግዚአብሔር ፊት ቆመ፡፡ እግዚአብሔርም የሚሠራውን ሁሉ ከአብርሃም አይሠውርም ነበርና የሰዶምን የገሞራን ጥፋት ነገረው፡፡ አብርሃምም ይቅር እንዲላቸው አብዝቶ ለመነላቸው፡፡ ሥሉስ ቅዱስን የአብርሃሙ ሥላሴን በምግባር በሃይማኖት ሆነን እናገለግል ዘንድ የቅዱሳኑ ጸሎት ይርዳን!
++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ሥር በሚገኙ አጥቢያዎች የ፬ [4] ኛ , የ፮ [6] ኛ እና የ፲ [10] ኛ ክፍል ተማሪዎች የ2016 ዓ.ም የማጠቃለያ ምዘና ሐምሌ 21/2016 ዓ.ም ይሰጣል !!!

#የአዲስ_አበባ_ሰንበት_ትምህርት_ቤቶች_አንድነት

++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++
ለተከታታይ 5 ሳምንታት #ዮሐንስን_እንወቅ በሚል ርዕሰ በመጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ ገድል ላይ ባተኮረው ውድድር ላይ ከተሳተፉት ከ200 በላይ የቻናላችንን አባላት መካከል 22/28 በማምጣት አንደኛ የወጣችው እህታችን ቤተልሔም በየነን (@Enulhem) በዛሬው ዕለት ሸልመና።

አገልግሎትሽን እግዚአብሔር አምላክ ይባርክልሽ!

በቀጣይ በሌላ ውድድርና በላቀ ሽልማት እንመለሳለን።
ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን። አሜን።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የማጽናኛ መልእክት አስተላለፉ።

“ምንም እንኳ የመከራ ድሀ ባንሆንም ይህ መከራ ለነጋሪውም ለሰሚውም ከባድ መሆኑን እንገነዘባለን ። “

++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን !

“እግዚኦ ሚ በዝኁ እለ ይሣቅዩኒ፦አቤቱ፥ የሚያስጨንቁኝ ምንኛ በዙ ! ”
(መዝ. 3፡1)

አባታዊ የማጽናኛ መልእክት

በጎፋ ዞን፣ በገዜ ጎፋ ወረዳ፣ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ በደረሰው የመሬት ናዳ እጅግ ብዙ የሚሆኑ ወገኖቻችን በመሞታቸው ታላቅ ኀዘን ተሰምቶናል ። ምንም እንኳ የመከራ ድሀ ባንሆንም ይህ መከራ ለነጋሪውም ለሰሚውም ከባድ መሆኑን እንገነዘባለን ።

ይሁን እንጂ ጭንቀታችን ብዙ ቢሆንም እግዚአብሔር መልካም የምንሰማበትን ዘመን እንደሚያመጣ ተስፋ እናደርጋለን ።

በተለይም ደግሞ እኛ ክርስቲያኖች በወገኖቻችን መጎዳት ብናዝንም በትንሣኤ ሙታን ስለምናምን የምጽናና በመሆኑ የሞቱት ልጆቻችን ዕረፍተ ነፍስ እንዲያገኙ እየጸለይን፤ የመከራው ገፈት ቀማሽ ለሆኑት የአካባቢው ማኅበረሰብእ ሁለንተናዊ ድጋፍ በማድረግ ሁሉም አቅሙ በፈቀደው መጠን እንዲደርስላቸው ስንል አባታዊ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን።

እግዚአብሔር አምላክ ለቤተሰቦቻቸውና ለሕዝቡ መጽናናትን ይስጥልን፤ ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!
አሜን።

አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ
ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም
ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

ሐምሌ 17 ቀን 2016 ዓ.ም. ዋሽንግተን ዲሲ~ አሜሪካ
ቅዱስ ቂርቆስ ወቅድስት ኢየሉጣ
እንኳን ለሊቀ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልና ለቅዱስ ቂርቆስ ወኢየሉጣ ዓመታዊ በዓል (ሐምሌ ፲፱) በሰላም አደረሰን፤ አደረሳችሁ !!!

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በድምቀት ከሚከበሩት በዓላት አንዱ የቅዱስ ገብርኤል በዓል ነው፡፡ ይኽ በዓል ታኅሣሥ ፲፱ እና ሐምሌ ፲፱ ቀን በድምቀት ይከበራል፡፡/መጽሐፈ ስንክሳር የሐምሌ፣ ድርሳነ ገብርኤል እና በገድለ ቂርቆስ ወኢየሉጣ/፡፡ የዛሬው ጽሑፌም ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ሐምሌ ፲፱ ቀን በእግዚአብሔር ቸርነት ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስ እና ቅድስት ኢየሉጣን ያዳነበትን ዕለት የተመለከተ ይሆናል፡፡
ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል
ቅዱስ ገብርኤል የስሙ ትርጓሜ “አምላክ ሰው ሆነ ሰው አምላክ ሆነ” ማለት ነው፡፡ “ገብርኤል ሆይ ተመራምሮ ለማይደረስበት ስም አጠራርህ ሰላም እላለሁ፤ ነገር ግን አምላክ ሰው ሆነ ሰው አምላክ ሆነ ማለት ይመስላል” እንዲል /መልክዐ ቅዱስ ገብርኤል/፡፡ ቅዱስ ገብርኤል የጌታችን መድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ሰው መሆን የምሥራች ዜናን ያበሠረ፤ በጨለማ እና በሞት ጥላ ውስጥ ለሚኖሩት ሁሉ የብርሃን ፋና ያበራ፣ “ጌታ ይወርዳል ይወለዳል” በማለት የነቢያትን ትንቢት ያስፈጸመና የምሥራችን ቃል የተናገረ ነው፡፡ ቅዱስ ሉቃስ እንደጻፈው መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ሁል ጊዜም ለደስታና ለምሥራች የሚላክ መልአክ ነው፤ በተለይም ስለ ልደተ ክርስቶስ ለድንግል ማርያም ለመጀመሪያ ጊዜ የምስጋና እና የክብር ሰላምታ ያበሠረ በመሆኑ “አብሳሬ ትስብእት (መልአከ ብሥራት) መጋቤ ሐዲስ” ተብሎ ይጠራል፡፡

ቅዱስ ገብርኤል ከሌሎች መላእክት ተለይቶ መላእክት ከተፈጠሩ በኋላ አምላካቸውን ለማወቅ “ማነው የፈጠረን?” እያሉ ሲባዝኑ ሳጥናኤል “እኔ ፈጠርኳችሁ” ሲል፤ ቅዱስ ገብርኤል ግን “የፈጠረንን አምላክ እስክናውቅ ድረስ በያለንበት እንቁም እንጽና” በማለት መላእክትን ያረጋጋ መልአክ ነው /አክሲማሮስ. ገጽ ፴፭/፡፡

ቅዱስ ገብርኤል የመላእክት አለቃ ነው፤ በራማ በሠፈሩት ዐሥሩ የነገድ ሠራዊት ላይ የአርባብ አለቃ ነው፡፡ ነቢዩ ሄኖክም “በሠራዊት ሁሉ ላይ የተሾመ መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ነው” ይላል፡፡ በዚህም ምክንያት የራማው መልአክ ተብሎ ይጠራል /ሄኖክ.፲፥፲፬/፡፡ ቅዱስ ገብርኤል ከሌሎች መላእክት ተለይቶ ዘወትር በምንጸልያቸው ጸሎቶች ስሙ የሚጠራ መልአክ ነው፡፡ ይኸውም በዘወትር ጸሎቶች በአቡነ ዘበሰማያት፣ በሰላመ ቅዱስ ገብርኤል፣ በውዳሴ ማርያም፣ በይዌድስዋ መላእክት እና በመሳሰሉት ጸሎቶች ዘወትር ስሙ የሚጠራ መልአክ ነው፡፡

ቅዱስ ገብርኤል የእግዚአብሔር ባለሟል ነው፤ “እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ነኝ” እንዲል፡፡ ቅዱስ ገብርኤል ምእመናንን የሚጠብቅ ጠባቂ መልአክ ነው፤ “በመንገድህ ሁሉ ይጠብቁህ ዘንድ መላእክቱን ስለአንተ ያዛቸዋል፤እግርህም በድንጋይ እንዳትሰናከል በእጆቻቸው ያነሡሃል” እንዲል /መዝ.፺፩፥፲፩/፡፡“የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሠፍራል፤ ያድናቸውማል” /መዝ.፴፬፥፩/፤ “በመንገድህ ይጠብቅህ ዘንድ ወዳዘጋጀሁትም ስፍራ ያገባህ ዘንድ እነሆ እኔ መልአክን በፊትህ እሰድዳለሁ” /ዘጸ.፳፫፥፳/፡፡ቅዱስ ገብርኤል ስእለት ሰሚ እንዲሁም ፈጥኖ ደራሽ መልአክ ነው፡፡ ቅዱስ ገብርኤል ቅዱሳን ይሆኑ ዘንድ ለተጠሩት ለእግዚአብሔር በመገዛታቸው ምክንያት ከአላውያን ገዢዎች ከሚደርስባቸውንም መከራ የሚታደጋቸው መልአክም ነው፡፡ በክርስቲያኖችም ዘንድ እጅግ ተወዳጅ የሆነ ፈጥኖ ደራሹ መልአክ፣ ስእለት ሰሚው መልአክ ይባላል፡፡ በሀገራችንም ክብረ በዓሉ በተለያዩ ቦታዎች እጅግ በርካታ ሕዝበ ክርስቲያን በተገኙበት ይከበራል፡፡ ቅዱስ ገብርኤል ያደረጋቸው ተአምራቶች በመጽሐፍ ቅዱስ፣ በመልክዑ፣ በድርሳኑ፣ በገድሉ፣ በተአምሩ የተጻፉ ቢሆንም፤ ሐምሌ ፲፱ ያደረገውን ተራዳኢነት ከብዙው በጥቂቱ እንደከሚተለው እናያለን፡-
“እናቴ ሆይ አትፍሪ”
“እናቴ ሆይ አትፍሪ” ብሎ የተናገረው ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስ (Cyricus) ነው፡፡ ቅዱስ ቂርቆስ አባቱ ቆዝሞስ እናቱ ቅድስት እያሉጣ (Julitta) ይባላሉ፡፡ የትውልድ ሀገራቸውም በሮም ግዛት በሚገኘው አንጌቤን ነው፡፡
በ303 ዓ.ም ዲዮቅልጥያኖስ በነገሠ በሃያ ዓመት አንድ ዐዋጅ አወጣ፡፡ አብያተ ክርስቲያናት ይዘጉ፤ አብያተ ጣዖታት ይከፈቱ ብሎ፡፡ በዚህ ምክንያት በርካታ ሕዝበ ክርስቲያን ተሰደዱ፡፡ ቅድስት ኢየሉጣም የሦስት ዓመት ልጇን ይዛ ወደ ኢቆንያን ሸሸች፡፡ ይህቺ ቅድስት የዘመኑን አረማዊ መኰንን እለእስክንድሮስን በመፍራቷ ከልጇ
ጋር ከሮም ወደ ጠርሴስ በተሰደደች ጊዜ መኰንኑ እነርሱ ከሚገኙበት አገር ገብቶ ክርስቲያኖችን እያሳደደ መግደል ጀመረ፡፡

በወቅቱም የነበረው ሹም እለስክንድሮስ ኢየሉጣን “ክርስቶስን ካጂ ለጣዖት ስገጂ” አላት፡፡ እርሷም “ዐይን እያለው ለማያይ፣ ጆሮ እያለው ለማይሰማ በእጅህ ሠርተህ ላቆምከው ምስል አልሰግድም” አለች፡፡ አይሆንም ካልሽማ በሰይፍ ትቀጫለሽ ብሎ አስፈራራት፡፡ እስኪ ይህን ሕፃን ጠይቀው አለችው፡፡ አንተ ሕፃን ለዚህ ጣዖት ስገድ አለው፡፡ መንፈስ ቅዱስ አድሮበታልና “ራሳቸውን ማዳን ለማይችሉ ርኩሳን ጣዖታትህ፣ አልሰግድም” አለው፡፡ ተበሳጨ በብረት ጋን ውኃ አፍልታችሁ ከዚያ ውስጥ ጣሏቸው አለ፡፡

የፈላ ውኃ ውስጥ ሊከቷቸው ሲወስዷቸው ኢየሉጣ ልቧ በፍርሃት ታወከ፤ እርሱ ግን ፍርሃቷን አርቅላት እያለ ይጸልይላት ነበር፡፡ እርሷንም “ሁለተኛ ሞት አያገኘንምና እናቴ ሆይ በርቺ፤ በዚያውስ ላይ አናንያ፣ አዛርያ ሚሳኤልን ያዳነ እኛንስ ያድነን የለምን?” እያለ እያጽናናት ልብሷን እየጊተተ ከእሳቱ ቀረቡ፡፡ ከዚህ በኋላ በፍጹም ልብ ኾነው ተያይዘው ከፈላው ውስጥ ገብተዋል፡፡ በዚህ ጊዜም በዐላውያን ነገሥታት ፊት የመሰከሩለት፣ በስሙ መከራ የተቀበሉት፣ ኢየሱስ ክርስቶስ፤ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤልን ልኮ በበትረ መስቀሉ እሳቱን አጥፍቶ፣ የፈላውን ውኃ አቀዝቅዞ ከእሳቱ ሐምሌ ፲፱ ቀን አውጥቶአቸዋል፡፡ በወጡም ጊዜ ልብሳቸው ሳይለበለብ፣ ሰውነታቸው ሳይሸበሸብ ቢያዩ ከአሕዛብ ብዙዎች አንገታቸውን ለስለት፣ ሥጋቸውን ለእሳት ሰጥተው በሰማዕትነት ዐርፈዋል፡፡

እንደማጠቃለያ

በአጠቃላይ ቅዱስ ቂርቆስና ቅድስት ኢየሉጣ የዚህን ዓለም ጣዕም በመናቅ “ሞት ቢኾን፣ ሕይወትም ቢኾን፣ መላእክትም ቢኾኑ፣ ግዛትም ቢኾን፣ ያለውም ቢኾን፣ የሚመጣውም ቢኾን፣ ኃይላትም ቢኾኑ፣ ከፍታም ቢኾን፣ ዝቅታም ቢኾን፣ ልዩ ፍጥረትም ቢኾን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል ተረድቼአለሁ” /ሮሜ. ፰፥፴፰-፴፱/ በማለት ቅዱስ ጳውሎስ የተናገረውን ቃል በተግባር በማሳየት ለክርስቶስ ፍቅር ሲሉ ራሳቸውን ለመከራና ለሞት አሳልፈው ሰጥተዋል፡፡ ቅዱሳኑ ተጋድሏቸውን እስኪፈጽሙ ድረስም ቅዱስ ገብርኤል አልተለያቸውም፡፡ በቅዱስ ገብርኤል ተራዳኢነት ቅድስት ኢየሉጣና ቅዱስ ቂርቆስ ብቻ ሳይኾኑ ብዙ ምእመናንም ተጠቅመዋል፡፡ ስሙ በሚጠራባቸው ገዳማትና አድባራት መልአኩ የሚያደርጋቸው ድንቅ ድንቅ ተአምራት ለዚህ ማስረጃዎች ናቸው፡፡ ይህም ቅዱሳን መላእክት በእግዚአብሔር ስም መከራ የሚቀበሉ ምእመናንን እንደሚጠብቁና ከልዩ ልዩ ደዌ እንደሚፈውሱ የሚያስረዳ ታሪክ ነው፡፡

ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስ “እናቴ ሆይ አትፍሪ” እያለ እናቱን በመከራ እንድትጸና እንዳረጋጋትና ለሰማዕትነት እንድትበቃ እንዳደረጋት ዅሉ፣ ዘለዓለማዊውን የእግዚአብሔርን መንግሥት በአንድነት ለመውረስ እንድንችል በዚህ ዓለም የሚገጥመንን መከራ ታግሠን፣እስከ ሞት ድረስ በሃይማኖታችን ጸንተን መኖር ይገባናል፡፡ የክርስትና ሕይወት በጋራ ዋጋ የሚያገኙበት የድኅነት በር ነውና፡፡ “የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙርያ ይሠፍራል፤ ያድናቸውማል” ተብሎ እንደ ተጻፈ /መዝ.፴፬፥፯፡፡ ቅዱስ ቂርቆስንና ቅድስት ኢየሉጣን የተራዳው የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ገብርኤል በአማላጅነቱ ይጠብቀን፡፡

የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት፣
የቅዱስ ገብርኤል ተራዳኢነት፣ የቅድስት ኢየሉጣ እና የቅዱስ ቂርቆስ
ጸሎታቸው፣ ምልጃቸው አይለየን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ምንጭ፡-
✍️ መጽሐፈ አክሲማሮስ
✍️ ድርሳነ ገብርኤል
✍️ ገድለ ቂርቆስ ወኢየሉጣ
✍️ ስንክሳር ወርኃ ሐምሌ
“ መሬት እንቁ የሆነበት ዘመን ስለሆነ ሁሉም አሰፍስፎ ዓይኑ ቤተ ክርስቲያን ላይ ሆኗል ” - ብፁዕ አቡነ ሄኖክ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሄኖክ በየካ ክፍለ ከተማ የኮተቤ ደብረ ልዑል ዳግማዊ ቁልቢ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያንን እድሳት መርቀዋል።

የቤተ ክርስቲያኗ ዋና አስተዳዳሪ መላከ ፀሐይ ቆሞስ አባ ገብረ ኢየሱስ፣ ለአስፋልት ንጣፉ ቁፋሮው ስራ በአንድ ወር እንደተጠናቀቀ ገልጸዋል።

በቅጥር ግቢ የአስፋልትና የቴራዞ ንጣፍ፣ የምዕመናን እድሳት ማረፊያ እድሳትና የመሳሰሉት ተግባራት መከናወናቸው አስረድተዋል።

ብፁዕ አቡነ ሄኖክ በበኩላቸው፣ " ከደብሩ በሚስማማ ምድራዊ ገነት በሚመስል መልኩ ቅጥር ግቢው እንደለማ በመግለጽ የእንኳን ደስ አላችሁ " ብለዋል። 

ኢትዮጵያዊያን የሚሰሯቸው ህንፃዎች ከ30 ዓመታት በላይ የሚያስቆጥሩ መሆናቸውን መስክረው፣ የሰው ልጅ ግን እየተዘነጋ መሆኑን አስምረውበታል።

“ ህንጻ መስራቱ ለትውልድ የሚተላለፍ ሆኖ ነገር ግን ህንፃ ሥላሴ ደግሞ (ካህናቱ፣ አገልጋዮቹ፣ ምዕመናኑ) የሚበላ፣ የሚላስ ነገር በማጣት እየተቸገሩ መሆኑን ዘንግተናል ብዬ አስባለሁ ” ነው ያሉት።

ብፁዕነታቸው አክለው፣ “ ትልቁን ህንፃ እንሰራለን ህንፃ ሥላሴ (የሰው ልጅ) ግን ወደ መዘንጋት የደረሰ ይመስለኛል ” ሲሉ ተናግረዋል።

“ 50፣ 50 ማድረግ ብንችል ! በጎን ልማቱን የማፋጠን ሥራ፣ ሥራ አጥ የሆኑ ልጆቻችን ሥራ የሚያገኙበትን ሥራ መስራት ትችላለች ቤተክርስቲያኗ ” ብለዋል።

“ ቤተ ክርስቲያኒቱ ብዙ አቅም አላት። ያንን አቅም የማስተዳደር፣ የማሰባሰብ፣ ባለሃብቶችን ጋብዛ ባላት መሬት ላይ ልማት እንዲያለሙ በማድረግ ገቢ የመፍጠር ሥራን ጎን በጎን ደግሞ ብትሰራ ጥሩ ነው ” ሲሉ አስገንዝበዋል።

“ እንደ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የመሬት አስተዳደር በኩል የወጣ አንድ ፕሮጀክት አለ ” ብለው፣ በዚያ መሠረት አባላት ወደ ልማት እንዲየመሩ ስልጠና በመስጠት የማንቃት ስራ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

መንግስት የልማት ሥራ እየሰራ መሆኑን የጠቀሱት ብፁዕነታቸው፣ “ ቤተ ክርስቲያንም ጎን በጎን ተሯሩጣ ልማትን ካላለማች ቆሞ ቀር ትሆናለች፣ ትወቀሳለች ” ብለዋል።

አክለው፣ “ ያላትም መሬት ደግሞ እንዳይወሰድ ስጋት አለን። ባላት መሬት ላይ ልማት ልታለማ ይገባል ” ነው ይሉት።

“ መሬት እንቁ የሆነበት ዘመን ስለሆነ ሁሉም አሰፍስፎ ዓይኑ ቤተ ክርስቲያን ላይ ሆኗል። እኛ ተኝተን ሌሎች መጥተው እንዳይወስዱብን ነቅተን በንቃት፣ በብልሃት እና በጥበብ ወደ ልማት መግባት ከእኛ ይጠበቃል ” ሲሉ አሳስበዋል።

#TikvahEthiopiaFamilyAA

@tikvahethiopia
2025/02/07 00:25:20
Back to Top
HTML Embed Code: